Wednesday, November 21, 2018

፩፣ የራእይ ትምህርት አብይ መግቢያና ዳሰሳ

የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ጥናት አብይ እጥጥር
መግቢያ:-
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ "አቡቀለምሲስ" (Apocalypse) ነው፣ ይኸውም ወደፊት በቅርብ ርቀት የጊዜ ወሰን ውስጥ ሊፈጸም የተዘጋጀው የኢየሱስ ክርስቶስን ራዕይ ወይም መገለጥ በተመለከተ የተጻፈ መጽሐፍ ነው።
በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ በግልጽ የሚታየው ምስል ከሳች የሆነው አቀራረብ እና ትዕይንታዊ መልዕክቱ የአብዛኛውን ክርስቲያን ትኩረት የያዘ ቢሆንም፣ በአመዛኙ የሰው ፍላጎት የተመሠረተው ግን ዓይነተኛ የሆነውን የመጽሐፉን ባህርይ እና  ዓላማ ባለመረዳት  ጽንፍ  ላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካቶች በትርጉማቸው ሁሉንም ነገር እንዳለ ቃል በቃል የሚወስዱ(Literallist) ሆነዋል።
የዚህ ጽንፍ ሰለባ የሆነ ፈልፕ   ስካፍ  የተባለ የቤተክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊ ከመቶ ዓመታት በፊት እንዳሰፈረው "አቡቀለምሲሳዊውን ሥነ-ጽሑፍ መረዳት በጣም ከባድ ነው፣  አቀራረቡ በአብዛኛው ከገላጭነቱ ይልቅ አስቸጋሪነቱ  ያመዝና፣ ጽሑፉ ዋጋ ቢስ ወይም ደግሞ የሚያጭበረብር ከመሆኑ  የተነሳ የሚያሳስት እና የሚያታልል የሥነ ፅሑፍ ሥራ ነው" ሲል  ያለአግባብ ይተቻል፡፡
ኤድጋር ሲ.ዊሴናንት ባሳተመው መፅሐፉ ላይ የዚህን አቡቀለምሲሳዊ  መጽሐፍ በሚገባ  ካለመረዳት የተነሳ የሚፈጠር  ስህተት ምሳሌ ሊሆነን የሚችል አንድ ነገር ደግሞ እናገኛለን፡፡ የዚህ ሰው መፅሐፍ ስድስት ሚሊዮን ቅጅ በ1988 ዓ.ም ብቻ  በወንጌል ዓማኞች ዘንድ  በስፋት ተሰርጭቷል፡፡ ሚስተር ዊሴናንት በመጽሐፉ ክርስቶስ በመስከረም  1988 ወደ  ምድር  ለምን  እንደሚመለሰ  ለማስረዳት  ብዙ   ሲደክም   ይታያል፡ ፡   በርካታ የተታለሉ ክርስቲያኖች  የዚህን  ሰው  መልዕክት  መሠረት አድርገው  የክርስቶስን  መመለስ   ተዘጋጅቶ   ለመጠበቅ ሥራዎቻቸውን አቁመው እንደነበር በወቅቱ የዜና ማሰራጫዎች ዘግበውታል፡፡ ጌታ ከመመለሱ በፊት ሠራተኞች ከዓመት ፈቃዳቸው ላይ በሚታሰብ ወይንም  ከነጭራሹ ሥራ በማቆም ከሚወዱአቸው ቤተሰቦቻቸው  ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ከሥራ ገበታቸው እንደተለዩ በስፋት  ይነገራል፡ ፡  እጅግ  የሚያሳዝነው ነገር  ጌታ በተባለው ቀን  ብቅ  እንኳ  ብሎ  ስላልታየ   ብዙዎች  እጅግ  አዝነው ወደ  ሥራቸው እንደተመለሱ  ይታወቃል፡፡
በራዕይ መፅሐፍ ውስጥ አቡቀለምሲሳዊ የሆነውን ትንቢታዊ ዓላማ እና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ውስጥ  የሚፈፀምበትን  የጊዜ  ማዕቀፍ  አሳስቶ  ከመረደት  የተነሳ   የተፈጠሩ   አጅግ ብዙ የሆኑ ዘመናዊ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ግምታዊ  የሆኑና  አርግጠኝነት  የማይታይባቸውን መላምቶችን በዚህ ጥናት አራተኛው ክፍል ላይ እናያቸዋለን።
የዮሐንስ  ራዕይ  መፅሐፍ  የመፅሐፍ   ቅዱስ   አንዱ  ዋና አስፈላጊ መጽሐፍ ነው፡፡ ዮሐንስም በራዕዩ ከብይ ኪዳን በብዙዎች የሚቆጠሩ ምንባባትን ይጠቅሳል፣ የዕብራውያንን ኃይማኖታዊ ሥርዓቶችንም ብዙ ግዜ በራእዩ ውስጥ  ያንፀባርቃ፡፡ እንግዲህ ራዕይን ለመረዳት የመጽፍ ቅዱስን ታሪካዊ መሠረት በሚገባ አውቀን በርትተን  ለመስራት  እና  ለማሰብ ፈቃደኛ  ልንሆን ይገባል፡ ፡
1ተሰ 5÷20-22 "ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ።"  ሲል  ያስተምረናል፡፡
"ፈትኑ" የሚለው የግሪኩ ቃል dokimazo ሲሆን፣ ልክ አንድን ገንዘብ ሕጋዊ ወይም ሕገ ወጥ /የተጭበረበረ/ መሆኑን ፈትኖ ለመለየትና ለመወሰን ጥቅም ላይ የዋለ የመፈተኛ ሙያዊ ቃል ነው፡፡ ሁሉንም ነገር መፈተን ይገባናል፤ በዘመናችን ያሉ በርካታ ምዕመናን ግን ምንም ነገር ካለመፈተናቸው የተነሳ የሚኖሩት በአዕምሮአቸው ሳይሆን በስሜታቸው ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ ይህንን የራዕይን መጽሐፍ መግቢያ አብረን ስናጠና ከሁሉ በፊት በጥንቃቄ  ለማሰብ  ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል፤ ከለመድነው አስተሳሰብ ጋር የሚጣላ አሳብ ቢገጥማችሁም እንኳ ስሜታችሁን አደብ ማስገዛት እና የነበራችሁን ልማዳዊ  አመለካከታችሁን ወዲያ   መጣል ያስፈልጋችኋል፤ በርዕሰ ጉዳዩም ላይ "ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ" እንዲናገሩ  በመፍቀድ፣  የእግዚአብሔርን  ቃል በብዙ ጥንቃቄ እና ወደ ተጻፈበትም አውድ እጅግ  ተጠግቶ ማጥናት  ይጠይቃችኋል፡፡  የዮሐንስ ራዕይ መፅሐፍ ማለት በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት በአግዚአብሔር ከተሰጠ መጽሐፍ ያነሰ እና  ትኩረታችን የማይገባው ማለት  አይደለምና፡፡
የዮሐንስ ራዕይን መጽሐፍ ለመረዳትና ለመተርጎም እስከ ዛሬ ድረስ በየዘመናቱ የተደረጉ የተለያዩ የሊቃውንት ጥረቶች ለየት ያሉ ውዝግቦችን ሲያስተናግዱ የኖሩ ናቸው፡፡ ይህም ውዝግብ የሚያስቡ አእምሮ ዎች እስካሉ ድረስ የማይቆም ነው።
ከተቀሩት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በተለየ፣ ይህ ሐዋርያው ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ግዞተኛ በነበረበት ጊዜ በእስያ ለሚገኙ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት የጻፈው የራዕይ መጽሐፍ (ራዕይ 1÷ 1; 9-11) በአይነቱ ለየት ያለ ምስላዊ (generic)፣ አገላለጽ፣ የራሱ የሆነ  ዓላማ እና መልዕክቱን የሚያደርስበት መንገድ አለው፡፡ በባህርዩ አቡቀለምሲሳዊ የሆነውን ይህን ታላቅ መጽሐፍ በአግባቡ ለመረዳት ቢያንስ እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎችን መመለስ የግድ ይላል፡፡ እነርሱም፡- መጽሐፉ የተጻፈበት ጊዜ መቼ ነው? ጊዜን አስመልክቶ በመጽሐፉ የተባሉ ነገሮችን እንዴት እንረዳቸዋለን? ትንቢቱ የተፈጸመ  ወይስ ገና ወደ ፊት የሚፈጸም ነው? ትንቢቱ ዛሬ ለእኛ ያለው ጠቀሜታስ ምንድን ነው? የሚሉት በቀጣይ የጥናቱ ክፍል ዘርዘር አድርገን መልስ የምንፈልግላቸው ጉዳዮች ናቹው።
ጥናቱም በሚከተሉት ስድስት ክፍሎች ተከፋፍሎ ይቀርባል:-
በክፍል ፩ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ አጭር ዳሰሳ
በክፍል ፪ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ መቼ ተጻፈ?
በክፍል ፫ የዮሐንስ ራእይ እና የመጨረሻው ቀን
በክፍል ፬ ለዮሐንስ ራዕይ ተመራጩ የትርጉም አቅጣጫ
በክፍል ፭ ፍርድ፣ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ጭብጥ
በክፍል ፮ ራእይ፣ የፍቺው ጽህፈት እና የጦርነት አዋጅ
ስለዚህ የራዕይን መጽሐፍ በዝርዝርና በጥልቀት ማጥናት ከመጀመራችን በፊት አትኩሮታችንን የሚሹ ሶስት ቁም ነገሮችን ላሳስባችሁና ወደ ክፍል አንድ ጥናታችን እንለፍ።
1ኛ/ አውደ ምንባብ፣ 2ኛ/ አውደ ምንባብ፣ 3ኛ/ አውደ ምንባብ።
∆∆∆∆∆∆∆∆∆
ክፍል ፩
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ አጭር ዳሰሳ
በመጽሐፉ ትርጉም ላይ መደረግ ስላለበት የአስተሳሰብ ለውጥ ጠቋሚ የሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን በዚህና በቀጣዩ ጽሁፍ በዳሰሳ መልክ ለማንሳት እወዳለሁ።
በቅድሚያ የራእይን መጽሐፍ ስናጠና ከዘመን አኳያ በአግባቡ መመለስ ያለበትን መሰረታዊ ጥያቄ ልብ በሉ፦
መጽሐፉ የሚያወራው ያለ በቂ ጥናት በተለምዶ ሲታሰብና ሲታመን እንደነበረው፣ እኛ ካለንበት ከዚህ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን አንጻር ሲታይ ስለ መጻኢው ማለትም ስለ ወደፊቱ ነው? ወይንስ በተቃራኒው ስለ ኃላፊው? ማለትም በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ተፈጽሞ ስለ አለፈ ጉዳይ፣ ስለ የትኛው ዘመን ነው?
የዚህን መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ለመወሰን መመለስ ያለባቸውን ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ጥያቄዎች ከራሱ ከመጽሐፉ እያነሳን በራሱ በመጽሐፉ መመለስ ይኖርብናል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ሳይጣረስና ሳይጣላ መፈታትና መተርጎም ያለበት በራሱ "በእግዚአብሔር ቃል ብቻ" ነው እንጂ፣ በርካቶች በስብከታቸውና በትምህርታቸው ብሎም በመዝሙራቸው እንደሚያንጸባርቁት በዚህ በአሁኑ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አለም፣ በየእለቱ በመገናኛ ብዙሃን በምንሰማውና በጋዜጦች በምናነበው ትኩስ ዜና፣ በመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ውዝግብም ሆነ በየትኛውም ልዕለ ኃያል ሃገርና መንግስት የፖለቲካ ትኩሳት መተርጎም አግባብ አይደለም።
ሌላ ተያያዥ ጥያቄ፣ የራዕይ መጽሐፍ የሚናገረው መጽሐፉ ከተጻፈበት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አንጻር ከረጅም ዘመን በኋላ ምናልባትም ገና ከዚህ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ስለሚሆኑ ሁነቶች ነው ከተባለ፣ ታዲያ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ በርካታ የንባብ ክፍሎች የሚያነሱአቸው ጉዳዮች ለምን በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ከነበረችው እስራኤል ጋር የሚገናኙ ሁነቶች  ሆኑ?
እነዚህም በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ከነበረችው እስራኤል ጋር የሚገናኙ ሁነቶችን የሚያመለክቱ ከዚህ በታች የተጠቀሱ የንባብ ክፍሎች የተሰጡባቸውን አውድ ለቃሉ ብቻ ታማኝ ሆነን በጥንቃቄ ብንመለከት፣ ትንቢቱ ሲነገርና መጽሐፉ ሲጻፍ የሚፈጸምበትንም የጊዜ ማእቀፍ እያመለከተ የተሰጠ ቃል መሆኑን ጨምረን እናስተውላለን።
እነዚህን ምንባባት ስንመለከት፣ በመጽሐፉም ውስጥ በተለይ ልናስተውላቸው የሚገቡንን አራት ነጥቦች ላንሳላችሁ ( እነዚህም ለዚህ አጭር የመግቢያ ጥናት ብቻ በወፍ በረር ላነሳቸው የምፈልጋቸው ነጥቦች ናቸው)፦
(ሀ) በመጽሐፉ ውስጥ በግልጽ የተቀመጡ ጊዜን አመልካች የሆኑ ምንባባት ያሉ መሆናቸውን ልብ በሉና ተመልከቱ፣
(ለ) በግልጽ ተወስኖ ከተሰጠና ጊዜን አመልካች ከሆኑ ከሌሎች የአዲስ ኪዳን ምንባባት ጋር ዝምድና ያላቸው ምንባባት የሚገኙበት መሆኑንም አስተውሉ
(ሐ) በተለይ ጥንታዊዋንና የቀድሞውን ኪዳን ኢየሩሳሌምን ወይም የእስራኤልን ሕዝብ በማመልከት አንጻር የተነገሩ ምንባባት ያሉበት መሆናቸውንም ተመልከቱ፤ እንዲሁም
(መ) የመጀመሪያይቱ ክፍለ ዘመን ኢየሩሳሌም በወቅቱ ከነበረችበት አይነተኛ የአይሁድ ማህበረሰብ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር በራእዩ መጽሐፍ የተገለጡ አይነተኛ ቦታዎችና ዘመኑ የተገናዘቡ መሆናቸውንም ተረዱ።
የሚከተሉትን የንባብ ክፍሎች ከፍ ሲል ከተጠቀሱት 4 ነጥቦች አንጻር መጽሐፍ ቅዱሳችሁን እያመሳከራችሁ በጥንቃቄ ትመለከቱአቸው ዘንድ እጋብዛለሁ፦
ራእይ ምዕራፍ 1 ቁ. 1 "ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ "
ቁ.3 "ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው። "
ቁ.7 "እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን። "
ቁ.9 "እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ"
ቁ.10 "በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ትላቅ ድምፅ ሰማሁ፥" 
ቁ.19 "እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ"
ራእይ ምዕራፍ 2 ቁ. 10 "ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። " 
ቁ.16 "እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፥ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።"
ቁ.25 "ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ።"
ራእይ ምዕራፍ 3 ቁ. 10 "የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።"
ቁ .11 "እነሆ፥ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ።"
ራእይ ምዕራፍ 4 ቁ. 1 "ከዚያ በኋላም አየሁ፥ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ፦ ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ።"
ራእይ ምዕራፍ 6 ቁ.16-17 "ተራራዎችንና ዓለቶችንም፦ በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው። "
  ራእይ ምዕራፍ 8 ቁ.13 "አየሁም፥ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ፦ ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ።"
ራእይ ምዕራፍ 10 ቁ.6-7 "ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፥ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፥ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፥ ከዘላለምም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ።  ወደ ፊት አይዘገይም፥ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን፥ ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል አለ። "
ራእይ ምዕራፍ 11 ቁ. 1-2  "በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፥ እንዲህም ተባለልኝ፦ ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።"
ቁ. 8 "በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።"
ቁ.15-19 "ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም፦ የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ። በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ፦ ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤  አሕዛብም ተቈጡ፥ ቍጣህም መጣ፥ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፥ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ።  በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።"
ራእይ ምዕራፍ 12 ቁ. 5 "አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።"
ራእይ ምዕራፍ 14 ቁ.7 "በታላቅ ድምፅም፦ የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ። "
ቁ.14-20 "አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው። ሌላ መልአክም ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው፦ የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፥ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው ምድርም ታጨደች። ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፥ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጭድ ነበረው። በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን፦ ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቍረጥ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ። መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፥ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቍጣ መጥመቂያ ጣለ።  የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፥ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ። "
ራእይ ምዕራፍ 15 ቁ 5-8 "ከዚህም በኋላ አየሁ፥ የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ፥ ሰባቱንም መቅሠፍት የያዙ ሰባቱ መላእክት ከመቅደሱ ወጡ፤ ከተልባ እግርም የተሠራ ጥሩ የጌጥ ልብስ ለበሱ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጠቁ። ከአራቱም እንስሶች አንዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ የሚኖር የእግዚአብሔር ቍጣ የሞላባቸውን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው።  ከእግዚአብሔርም ክብርና ከኃይሉ ጢስ በመቅደሱ ሞላበት፥ የሰባቱ መላእክት ሰባቱ መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ አንድ እንኳ ወደ መቅደሱ ይገባ ዘንድ አልቻለም።"
ራእይ ምዕራፍ 16 ቁ.6 "የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፥ የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።"
ቁ. 19 "ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፥ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች።"
ራእይ ምዕራፍ 17 ቁ.8 "ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ። "
ራእይ ምዕራፍ 18 ቁ.24 "በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።"
ራእይ ምዕራፍ 20 ቁ. 7-10፣ "ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፥ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን፥ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው። ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው። ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ። "
ቁ. 11-15  "ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።  ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።  በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ። "
ራእይ ምዕራፍ 22 ቁ.6-7 "እርሱም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ። እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ። "
ቁ. 10 "ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።"
ቁ.12፣ "እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።"   ቁ. 20 "ይህን የሚመሰክር፦ አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና።"
የዳሰሳው ማጠቃለያ:-
ከነዚህ ምንባባት መካከል አንዳንዶቹ ጊዜን በማመልከት አንጻር በግልጽ የተቀመጡና ሊሆኑ ያሉትን ሁነቶች የሚያመለክቱ ሲሆኑ እነርሱም "ቶሎ" ወይም ቅርብ ወይም ሳይዘገዩ የሚፈጸሙ ጉዳዮች መሆናቸውን ያሳያሉ። በተጨማሪም ከነዚህ ምንባባት መካከል አንዳንዶቹ በግሪኩ 'mello' የተሰኘውን ቃል ይዘዋል (1፥ 19፤ 3፥ 10፤ 8፥ 13፤ 10፥ 7፤ 22፥ 10፣ 12፣ 20 ተመልከቱ) ይኸውም "ይሆን ዘንድ ያለው"  ("abaut to be") ተብሎ ተተርጉሞአል። ቃሉም አንዳች የሚጠባበቁት ጉዳይ ሳይዘገይና ምንም ጊዜ ሳይወስድ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ሊፈጸም ቀነ ቀጠሮ የተቆረጠለት መሆኑን ያመለክታል።
ይህ ጊዜን አመልካች የሆነው ንግግር በመላው የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ፣ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ፣ በመሐል እና በመጽሐፉ ማጠቃለያ ላይ ተደጋግሞ መጠቀሱ ትንቢቱ አንድ ወጥ ሆኖ ሳይነጣጠልና ሳይከፋፈል በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ይኸውም "ቶሎ"፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈጻሚ የሚሆንበትን አይነተኛ ጊዜ የሚያመለክት ነው። ይህም "ቶሎ" የትንቢቱ ተቀባዮች በኩረ ተደራስያኑ ገና በህይወት ሳሉ በትዉልዳቸዉ ውስጥ የሚደርስ ቶሎ ነው እንጂ የዚህ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የእኛ ቶሎ አይደለም። ይኸውም ደግሞ ጌታችን በስጋው ወራት እየደጋገመ ለተከታዮቹ ያስተማራቸውን ፍካሬውን የሚያስተጋባ ንግግር ነው። "እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል"፣ "ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም"፣ "የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ"፣ "እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም"፣ "የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ" ...ወዘተ።
ስለዚህ ማንም ቢሆን በዚህ የትንቢት መጽሐፍ ላይ አውድ ዘለል የሆነ ትርጉምን ተከትሎ ስህተትን ሳይፈጽም የነዚህን ሁነቶች ፍጻሜ ሊከፋፍልም ሆነ የትንቢቱን ፍጻሜ ከተጻፈበት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አንጻር በብዙ የዘመን ርቀት አራዝሞ አሁንም ሆነ ወደፊት ሊጠባበቅ አይችልም።
በቀጣዩ ጽሑፌ የራእይ መጽሐፍ ስለተጻፈበት ጊዜ አነሳና ጊዜውን አስመልክቶ ያለው ሙግት በምንከተለው አመለካከት ላይ የሚያሳርፈውን ተጽእኖ ለመዳሰስ እወዳለሁ።

No comments:

Post a Comment