Tuesday, November 6, 2018

የእግዚአብሔር ቁጣ

"ቁጣን የሚያመጣ እግዚአብሔር" (ሮሜ 3፥ 5)

የእግዚአብሔር ቁጣ በመጀመሪያው ኪዳን፦     
የእግዚአብሔርን ቁጣ አስመልክቶ የመጀመሪያው ኪዳን ሲናገር የመለኮታዊ ባህሩዪ መገለጫው እና፣ የእግዚአብሔር ክብር አካል ወይም ክፍል አድርጎ ይገልጠዋል፡፡ "ቁጣ" የሚለው ቃል በጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ወደ 365 ጊዜ መጠቀሱንና የሚበዛውም ማጣቀሻ እግዚአብሔር በጽድቁ ምክንያት በፍጡር ስንፍናና በደል ላይ የገለጠው ፍርዱ መሆኑን ስንቶቻችን እንረዳለን? ብዙዎቻችን "አትፍራ" የሚለውን ቃል በዚህን ያህል ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጻፈልን እናውቃለን፤ ቁጣም ቁጥሩ ያን ያህል እንደሆነ እናስተውልና ለኃጢአተኛው ሞልቶ በሚትረፈረፈው መለኮታዊው ረድዔትና በኃጢአተኛው ላይ ሞልቶ በሚፈሰው መለኮታዊው ፍርድ መካከል ሚዛናችንን እንጠብቅ። የዚህች አነስተኛ ጽሁፍ አላማ መዓት እያወሩ ማንንም በማስፈራራት ማሸበር ሳይሆን ቅዱሱን አምላክ በመፍራት ማጽናናት ነው።

ክብርን እኛ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው፣ እርሱም አንዳች እንደሚጎድለው ጓግቶ የሚጠባበቀው ሳይሆን፣ ይልቁንም እርሱ፣ በራሱ፣ በማንነቱ፣ ከዘላለም ክብር ያለው ሆኖ ይኖራል፡፡ ከፍጡራንም መካከል ለእርሱ ክብርን ሊያመጣም ሆነ ሊሰጠው የሚበቃ፣ ለዚህም የሚመጥን አንድም የለም። ፍጡር ከሆነ ከማንም የሚገኝ ጽድቅም ሆነ ክብር በቅዱሱ አምላክ ፊት አጸያፊ የመርገም ጨርቅ ብቻ ነው። እርሱ በማንነቱ የሆነውን በመሆኑ ክብር የተገባው ሆኖ ክቡር ሆኖ በራሱ ይኖራል፡፡ ክብርን ከፍጡር እስኪቀበል ድረስ ክብር አይጎድልበትም። እጦትም አይታይበትም። ልናመልከው ከታደልን በክብሩ ብዛት እንደመማለን እንጂ ክብር አናዋጣለትም።

ሰውም ሆነ መላዕክት ማናቸውም የተፈጠሩ ብቻ ሲሆኑ፣ እግዚአብሔር ግን የክብር አምላክ ሆኖ አለ ይኖራልም፡፡ እርሱ ብቻውን የራሱን ክብርና ምስጋና በሕጻናትና በሚጠቡት አፍና ሕይወት እያደረገ ራሱን ያከብራል። እግዚአብሔርን ለማክበር እድሉን አግኝተን ከሆነ፣ ያ ማለት ስለማንነታችን የሚናገረው አንድ ትልቅ እውነት አለው፣ ይኸውም እርሱ በጸጋው ያከበረን ህጻናትና የሚጠቡ መሆናችን ብቻ ነው። እግዚአብሔርን የምናከብረው እጅግ በጣም አስፈላጊዎቹ (Very Important Person) በመሆናችን ሳይሆን እርሱ በእኛ ሊከብር ስለወደደ ብቻ ነው። ሁላችንም በጸጋው የዳንን ኃጢአተኞች እንጂ፣ በመካከላችን VIP የሆነ ማንም የለም።  ይህም እግዚአብሔራዊ ክብር የመለኮታዊ ባህርዩ መገለጫ ነው፡፡ የእርሱን መለኮታዊ ባህርይ በምናይበት ጊዜ ክብርን እንድንሰጠው፣ እንድናመሰግነውና እንድንሰግድለት ግድ ይለናል፡፡

እግዚአብሔር ቁጣው ክብርን ያመጣለታል፡፡ ቁጣውም እርሱን የሚያሳፍረው ወይም የሚያሸማቅቀው ነገር አይደለም፡፡ እርሱ እንደሰው ማፈር የሚያስፈልገው፣ በግልፍተኝነትም የሚቆጣ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣ ከክብሩ ጋር የማይነጣጠል ሆኖ የተቆራኘ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቁጣውን በሚገልጥበት ጊዜ ለራሱ ክብርን ያመጣል፡፡ ሰዎች ቃሉን በመቃወም በክርስቶስ የተገለጠውን የጸጋ ወንጌል ሲገፉ እና በእርሱ ላይ ዓምጸው ሲንቀሳቀሱ የእግዚአብሔር ቁጣ ይነዳል፣ ይቃጠልማል፡፡

እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ ምድር ካወጣቸው በኋላ፣ ለእርሱ በመካከላቸው ለሚያድር አምላክ የተቀደሱ ሕዝብ ይሆኑለት ዘንድ ባህርያቸውንና አኗኗራቸውን እንዲመራ እና እንዲገዛ ሕጉን ሰጣቸው፡፡ በዘዳግም 28፥ 1-14 እርሱ ከእነርሱ ጋር በሲና ተራራ ላይ ባደረገው ቃል ኪዳን፣ ኪዳኑን በመታዘዝ የሚገኘውን በረከት ይዘረዝራል፡፡ ከቁጥር 15-68 ይህንን ቃል ኪዳን በመተላለፍ የሚመጣውን መዘዝ፣ እጅግ የበዛውንና ዝርዝር የሆነው እርግማናዊ የፍርዱን ገለጻ ያቀርባል፡፡ በዚህ የዘዳግም 28 አውድ እስራኤል እንደማትታዘዝ፣ ቃል ኪዳኑንም እንደምትተላለፉና እንደሚፈርዳባቸው ግልጽ ነው፡፡

እግዚአብሔር በሌሎች አህዛብ ዘንድ ያለውን ኃጢአት ከሚታገሰው በላይ በሕዝቡ መካከል ያለውን ኃጢአት አይታገስም፡፡ ምክንያቱም፤ "እኔ ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ" (አሞጽ 3፥ 2) ተብሎ እንደተጻፈ፣ እግዚአብሔር እንዳወቀውና ራሱንም እንደገለጠለት ህዝብ ለእርሱ ያለን ተጠያቂነት እግዚአብሔር በሰጠን ብርሃን ልክ የሚታይ ነው። እስራኤላውያን ግን በአመጻቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር የቁጣው ጽዋ እንዲጨልጡ የተወሰኑ ነበሩ፡፡

የእግዚአብሔር ቁጣ የተገለጠባቸውን ሁነቶች ከመጀመሪያው ኪዳን በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንድ ሰው የእብራውያንን ቅዱሳት መጻህፍት እያነበበ የእግዚአብሔርን ቁጣ በጉልህ የማያይ ሊሆን አይችልም፡፡ ለምሳሌ የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ብታነቡ ስለ እግዚአብሔር ቁጣ በኢየሩሳሌም ላይ የተነገረውን ተመልከቱ፦

" ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። "ሕዝ 22፥ 31

ከዚያም በምዕራፍ 23 ይህንን እንመለከታለን     

" የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንዲት እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ። በግብጽም አመነዘሩ፥ በኰረዳነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ምዋሸሹ በዚያም የድንግልናቸውን ጡቶች ዳበሱ።  ስማቸውም የታላቂቱ ኦሖላ የእኅትዋም ኦሖሊባ ነበረ፥ ለእኔም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት።  ኦሖላም ገለሞተችብኝ፥ ውሽሞችዋንም ጎረቤቶችዋን አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው። " ሕዝ 23፥ 1-5

እናቲቱ 12ን ነገድ የያዘችው እስራኤል ናት። ሁለቱ ሴቶች ልጆች ደግሞ የደቡቡ መንግስት ኦሆሊባ (ይሁዳ) እና የሰሜኑ መንግስት ኦሆላ (እስራኤል) ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት መንግስታት ከእስራኤል የወጡት ከያዕቆብ ሁለቱ ሚስቶች እና ከሁለት ጋብቻው ነው። የይሁዳ ዋና ከተማ ኢየሩሳሌም ስትሆን፣ የእስራኤል ዋና ከተማ ደግሞ ሰማርያ ነበሩ፡፡

እግዚአብሔር ይሁዳ ለሆነችው ለኦሆሊባ የሚላትን ሰሙ፦

" ስለዚህ፥ ኦሖሊባ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየች ውሽሞችሽን አስነሣብሻለሁ፥ በዙሪያሽም በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ። "ሕዝ 23፥ 22

ቀጥሎም እግዚአብሔር በእርስዋ ላይ አስነስቶ የሚያመጣቸውን የተለያዩ መንግስትን ይዘረዝርና "በመሣሪያና በሰረገላ በመንኮራኩርም  በአሕዛብም ጉባኤ ይመጡብሻል" ይላታል፡፡

" በወገባቸው ዝናር የታጠቁ ራሳቸውንም በቀለማዊ መጠምጠሚያ የጠመጠሙ ነበሩ፤ ሁሉም ከተወለዱባት አገር የሆኑትን የከለዳውያንን ልጆች መስለው መሳፍንትን ይመስሉ ነበር። "ሕዝ 23፥ 15

እግዚአብሔር ቀጥሎ እንዲህ ይላል፡-

" ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽ በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ "ሕዝ 23፥ 28

እስራኤልን ለመቅጣት በአሕዛብ እጅ አሳልፎ የሚሰጥና አሕዛብን እንደ በትር የሚጠቀም ያለው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ልብ በሉ፡፡

በመጀመሪያው ኪዳን እግዚአብሔር ቁጣውን የገለጸው በአመጸኛዋ እስራኤል ላይ ብቻ ሳይሆን በኃጢአተኛ የአሕዛብ ምድር ሕዝቦችም ላይ ቁጣውን ገልጦአል፡፡ በጥፋት ውሃ የምድር ሕዝቦችን ፈጽሞ አጥፍቶአል (ዘፍ 6-9)። ኃጢአተኞቹን የሰዶምና የገሞራ ከተሞች በፍርዱ አጥፍቶአል (ዘፍ 19) ከዘጸዓትም በኋላ ኃጢአተኞቹን የከነዓንን ምድር ሕዝቦች ልክ አስቀድሞ ለአብርሃም እንዳመለከተው ስለ ኃጢአታቸው በእስራኤል ተጠቅሞ ፈርዶባቸዋል ዘፍ (15፥ 12-16)።

" ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እጄን በኤዶምያስ ላይ እዘረጋለሁ ከእርስዋም ዘንድ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ ከቴማንም ጀምሮ ባድማ አደርጋታለሁ፥ እስከ ድዳንም ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምያስን እበቀላለሁ፤ እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴም መጠን በኤዶምያስ ያደርጋሉ፤ በቀሌንም ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። "ሕዝ 25፥ 13-14

እግዚአብሔር ለአሞን እንደህ ይለዋል፡-

" ቍጣዬንም አፈስስብሃለሁ፥ በመዓቴም እሳት አናፋብሃለሁ፥ ማጥፋትንም ለሚያውቁ ለጨካኞች ሰዎች እጅ አሳልፌ እሰጥሃለሁ። "ሕዝ 21፥ 31

እስራኤላውያን ኃጢአተኛ ሕዝቦችን በተመለከተ የእግዚአብሔር ቁጣ መሣሪያዎች ነበሩ፡፡

የእግዚአብሔር ቁጣ በአዲስ ኪዳን፦
እግዚአብሔር የቁጣ አምላክ እንደሆነ የሚያስቡ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔርን ከሁሉ በፊት የቁጣ አምላክ መሆኑ የመጀመሪያው ኪዳን ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ማየት ይፈልጉና፣ ዛሬ ለሚኖሩ ሰዎች ከእንግዲህ የሚያስፈራ እንዳልሆነ ይመስላቸዋል። የቁጣ ርዕስ ጉዳይ ከጌታችን ከኢየሱስ ወደዚህ ዓለም መምጣት ጋር ያለፈ የቆየ ታሪክ እንደሆነ ማሰብም ይፈልጋሉ፡፡ ጉዳዩ ግን እንደዚህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

"እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም። " ሚል 3፥ 6

መጥምቁ ዮሐንስ የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻው ነበይ እስከሆነ ድረስ ስለ መለኮታዊ ቁጣ ይናገራል ብለን ልንገምት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ዮሐንስ ስለሚመጣው ቁጣ ሲናገር፣ ከክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት ጋር ባለው ግንኙነት አውድ ውስጥ ይገለጠዋል፡፡ እንደ ዮሐንስ ትምህርት ከሆነ፣ መለኮታዊው ቁጣ ከመሲሁ መምጣት ጋር በሁለት መንገድ ይገናኛል። በመጀመሪያ፦ መሲሁ ራሱ የእግዚአብሔርን ቁጣ እንደሚቀበል ሲሆን፤ ሁለተኛው፦ መሲሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚፈጽም /የሚገልጥ/ እንደሆነ ዮሐንስ ይናገራል፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን ለመጀመሪያ ባየው ጊዜ፣ እንደመሲህ አውቆታል፣ስለ እርሱም የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚቀበል ኃጢአት ተሸካሚ የእግዚአብሔር በግ እንደሆነ ተናገረ፡፡ 

" በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።"  ዮሐንስ 1፥ 29

ዮሐንስ የጠቀሰው "የእግዚአብሔር በግ" የሚለው መግለጫ በመጀመሪያው ኪዳን አውዱ በርካታ ሃሳቦችን ይዞአል። እስራኤል ከግብጽ በወጣበት ጊዜ የታረደው "የፋሲካ በግ" (ዘፍ 12) ይኸውም የጌታችን ምሣሌ ነበር (1ቆሮ 5፡7 ተመልከቱ)፡፡ በኢሳያስ ምዕራፍ 53 የተገለጠው "የእግዚአብሔር በግ " በግልጽ መሲሁን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ይመለከታል። ይህ ትንቢት ኃጢአትን የሚሸከመውን፣ የዓለም ሁሉ ኃጢአት በእርሱ ላይ የሚሆነውን፣ ስለ ሁላችን ኃጢአት እንደ ተቀሰፈ የሚቆጠረውንና የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚቀበለውን የመሲሁን  መከራ  ይመለከታል፡፡

የጌታ ከባዱና ታላቁ መከራ በእርሱ ላይ የወረደው የቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቁጣ ሲሆን እርሱም እንደ ተቸገረ፣ እንደ ተቀሰፈም ተቆጥሮ በአባቱ መተዉ የመራራ ልቅሶው ምክንያት ነበረ፡፡ የጌታችን ታላቁ መከራ መሲሂዊ ትንቢት ተብሎ በሚጠራው በመዝሙር 22 በተጻፈው ቃል በግልጽ ታይቶአል፣ ያም ጌታችን በመሰቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ የተናገረው ነው፡-

" አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ።" (መዝ 22፥ 1)

እግዚአብሔር ውድ ልጁን ስለኃጢአታችን በመስቀል ላይ ቸንክሮ የተወበት የፍርድ ጭከናው እና ለኃጢአተኞች ሁሉ ማዳኑን የገለጠበት የፍቅሩ ርህራሄ የአንዱ አምላክ መለኮታዊ ባህርያት ናቸው። በወንጌሉም ያለው የምሥራች "የእግዚአብሔር በግ" በሆነው በጌታ በኢየሱስ ላይ እምነታቸውን ያኖሩ ሰዎች መለኮታዊው ቁጣ መቼም ቢሆን አያገኛቸውም የሚል ነው፡-

" እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ።" 1ተሰ 5፥ 9

መጥምቁ ዮሐንስ የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ነብይ ሆኖ የእስራኤልን መሲህ ለማስተዋወቅ የታደለ ነበር፡፡ ዮሐንስ ስለመሲሁ መምጣት በተናገረ ጊዜ መለኮታዊው ቁጣ እርሱ ላይ እንደሚሆን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን እርሱ ራሱ መለኮታዊ ፍርድን እንደሚያመጣ ተናገሮአል፡፡

" ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና። ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።"  ማቴ 3፥ 5-12

በቁጥር 11 መጨረሻ ላይ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ሲናገር ከበዓለ ሃምሳ አንስቶ እስከ እየሩሳሌም ጥፋት ያለውን ወቅት "ገለባውንም በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል" በማለት ተናግሮአል- ይኽውም ስለ ቁጣ የተነገረ ነው፡፡ ንስሃ የሚገቡትን በመንፈስ ቅዱስ፤ ጠላቶችን ደግሞ በፍርድ እሳት ያጠምቃል፡፡ በነገራችን ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ለሚታዘዙት ሲሆን የእሳት ጥምቀት ደግሞ ለአመጸኞች መሆኑን ልብ አድርጉ። እሳት እዚህ ላይ ፍርድን ያመለክታል፡፡

እግዚአብሔር ቁጣውን ይገልጠው ዘንድ መብት አለውን? ፍትሁንና ፍርዱንስ የሳይ ዘንድ መብት አለውን? በእርግጥ አለው! ቁጣና ፍትሃዊ ፍርድ እንደ ምህረት፣ ጸጋ እና ፍቅር ሁሉ የመለኮታዊ ባህርዩ አካል ነው፡፡ በርካታ ሰዎች እግዚአብሔር በቁጣው ምን አይነት ክብር እንዳለው ማሰብ ይቸግራቸዋል፤ እርሱ ለቁጣ የዘገየ ነው፣ ብዙ ይታገሳል፣ ቻይነቱ ወደር የለውም፣ ለንስሃም እድል ይሰጣል፤ ዳሩ ግን በቁጣው ክብር ያለው መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ እርሱ በቁጣው ይደሰታል ጽድቁንም ይገልጣል፡፡ ይህም ልክ ፍቅር የእርሱ ባህርይ መገለጫ የሆነውን ያህልና በፍቅሩ የሚከብር፣ የሚደሰትና የሚያድን የሆነውን ያህል ነው፡፡

" አምላክህ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነውና። " ዘዳ 4፥ 24

መለኮታዊ ቁጣ የብሉይ ኪዳን አስደናቂ ክስተት ብቻ ሳይሆን በእርግጠኝነት ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይፈልጉና በሚቃወሙት ሁሉ ላይ የሚሆን ነው፡፡ አይሁድ ኢየሱስን አልፈለጉም፣ ገደሉትም፤ ቤተክርስቲያንንም እስከ ጥግ ሄደው አሳደዱ፣ መከራንም ያበዙባቸው ዘንድ በደቀ መዛሙርት ላይ እጃቸውን ጫኑ። ለንስሃ ፍሬ እንዲያደርጉ ብዙ የታገሳቸውና እድል የሰጣቸው የርህራሄ አምላክ ግን ጽዋቸው ሲሞላ በዛፎች ስር የተቀመጠውን ምሳር አንቀሳቀሰው፤ ፈጽሞም ያጠፋቸው ዘንድ በፍርድ እሳት አጠመቃቸው። የእስራኤልን ሕዝብ መጨረሻ ከታሪክ መዛግብት እያነበበ እግዚአብሔርን በፍርዱ ጭከና አለመፍራት የሚቻለው በልቡ እልከኝነት የእስራኤልን ፍርድ የሚፈልግ ብቻ ነው።

ምዕመናን በጥንቃቄ አዳምጡ፣ እኛ ሁላችንም የእግዚአብሔር ቁጣ ይገባናል! ነገር ግን ከእግዚአብሔር ምህርት የተነሳ የሚገባንን ቁጣ አላገኘንም፣ ምክንያቱም በእኛ ላይ የነበረው የእግዚአብሔር ቁጣ ሁሉ እምነታችንን ባኖርንበት በእርሱ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፈስሶአልና

" ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። " ሮሜ 5፥ 9

የእግዚአብሔር ቁጣ የእግዚአብሔርን ቅድስናና እግዚአብሔር ለኃጢአት ያለውን የጥላቻውን ልክ የሚያስታወሰን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣ ለሚያቀጣጥሉአት ለኃጢአተኞች ልካቸው ናት፡፡ ወደ ኃጢአት የሆነው የእግዚአብሔር ቁጣ ግዝፈት እርሱ በኃጢአት ላይ ያለውን ቅዱስ ጥላቻ የሚያመለክት ነው፡፡ እኛም እንደዚሁ ልንጠላው ይገባናል፡፡

የእግዚአብሔ ቁጣ ከኃጢአት ጋር ምቾት እንዳይሰማን ያደርገናል። በተጨማሪም ኃጢአታችን እግዚአብሔር ቁጣውን ሁሉ ባፈሰሰበት በመድሃኒታችን ላይ መከራንና ሥቃይን ያመጣ እንደሆነ ከቶ መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለ ኃጢአት ለዘበተኛ ሆኖ አቅልሎ ማሰብ የክርስቶስን መከራ አቅልሎ እንደማሰብ ይሆናል፡፡

ስለ እግዚአብሔር ቁጣ ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ እኛም ምህረት ብቻ የተደረገልን ኃጢአተኞች በሌሎች ኃጢአተኞች ላይ እንዳንበሳጭና ተስፋ እንዳንቆርጥ ያስተምረናል፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣ ብቻ የሚገባቸውና ለዚያ ብቻ የምንመጥን፣ "ከኃጢአተኞች ዋና" እኔ ነኝ የምንል እኛ፣ እንግዲያውስ ለእኔ የደረሰ ምህረት ለሌሎች ኃጢአተኞችም አለኝታ ነው እያልን እንታገሳቸው። ሰዎች ግን የእግዚአብሔርን ትእግስት እየገፉ፣ የተሰጣቸውንም የንስሃ እድል እየደፉ፣ በክፋታቸውም እየባሱ በሄዱ ቁጥር በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር እየወደቁ መሄዳቸው አይቀርም፡፡

ይህንን የእግዚአብሔርን ቁጣ አስተምህሮ በጥንቃቄ መያዝ ይገባልና፡፡ ቸል ልንለውም ሆነ ልንሸሸው አይገባንም፡፡ የእግዚአብሔር መልካምነት እና ክብር አካል መሆኑን አክብረን እንመልከት። ይህ የእግዚአብሔር ቁጣ አስተመህሮ ወንጌልን ለማሰራጨት እና የጸጋውን ወንጌል ለማወጅ የሚገፋፋንና የሚያበረታታን ይሁን፡፡ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት የገዛ ራሱ ኃጢአተኛ ተፈጥሮ ያላሸማቀቀው፣ በእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ስር የወደቀ ኃጢአተኛ መሆኑ ያላሸበረው፣ በወንጌል ያለውን ታላቅ የምህረት መጽናናትና በክርስቶስ የተገለጠውን የጸጋ ብዛት ለማድነቅ ምንም እድል የለውም።
በተከታታይ በዚህ በወጉ ባልደረጀ ጽሁፍ ያስነበብኳችሁ አሳብ ለእግዚአብሔር ክብርን የሚያመጣ ለእኛም ለራሳችን በጎነት እንዲሆንና ቅዱስ በሆነ እኗኗር ለሚገለጥ ታላቅ ሕይወት መሠረት ይሁንልን፡፡ አሜን!

No comments:

Post a Comment