የጌታ ምጽዓት መቼ እና እንዴት ነው?
በማቴዎስ 24 እንደተገለጸ
፫
"በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።" ማቴ 10፥ 23
"እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ" ማቴ 16፥ 28
"እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።" ማቴ 24፥ 34
"ኢየሱስም፦ አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው።" ማቴ 26፥ 64
እንጸልይ.. ..
እነዚህን "ጊዜ ጠቋሚ" የሆኑ ጥቅሶች የዛሬው ትምህርቴ መግቢያ እንዲሆኑኝ ከማቴዎስ ወንጌል ብቻ በከፊል የለቀምኳቸው ኢየሱስ ራሱ ስለሚመለስበት አይነተኛ ጊዜ በግልጽ የተናገራቸው ንግግሮቹ በመሆናቸው ነው። አንድ ሰው እነዚህን ጥቅሶች በግልጽ አማርኛ አንብቦ ሲያበቃ "ኢየሱስ ተመልሶ የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ አላመለከተም፣ ... ስለዚህ ምጽአቱን እየጠበቅን ገና ወደፊትም እንቀጥላለን፣ .... ኃላፋውያንም አስተምህሮአቸውን ያንጠለጠሉት አንድ ጥቅስ ላይ ብቻ ነው፣ ..." ብሎ የሚያስተምርም ሆነ የሚከራከር ሰው ሆን ብሎ እንዳያይ አይኑን የጨፈነ ብቻ ነው።
በእስካሁኑ ምልከታችንና ጨምረንም እንደምናነሳው በአዲስ ኪዳን ትንቢት ውስጥ በግልጽ የተነገረውንና ክርስቶስ የሚመለስበትን አይነተኛ ጊዜ ማወቅ በነገረ ፍጻሜ ጥናት ውስጥ በእጅጉ አስፈላጊና ወሳኝ ነጥብ ነው። ይኸውም በአዲስ ኪዳን ትምህርት መሰረት ኢየሱስ መቼ ነው የተመለሰው ወይም የሚመለሰው? የሚለው ጥያቄ ነው። ጊዜውን ማወቅ ወሳኝ የሆነውን ያህል ደግሞ የምጽአቱን ፍጻሜ ተፈጥሮውን ወይም ባህርዩን ወይም አይነቱን ወይም ምጽአቱ የሚፈጸምበትን መንገድ ጨምሮ ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይኸውም ደግሞ በአዲስ ኪዳን ትምህርት መሰረት ኢየሱስ እንዴት ነው የተመለሰው ወይም የሚመለሰው? የሚለው ጥያቄ ነው። የሚበዙት መጻእያን የሆኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችንም ከኃላፋውያን ጋር በሚያደርጉት ክርክር የኃላፍያንን ኃሳብ ለመቃወም አይነተኛ መምቻ አድርገው የሚያነሱት ጉዳይ ቢኖር ይህንንው ሁለተኛውን ጉዳይ የተመለከተ የሚያነሱት የታሪካዊ ሰነድ ጥያቄ ነው። ኃላፋውያኑም ቢሆኑ በእጅጉ የሚፋጠጡበት ተግዳሮት ውስጥ የሚዶላቸው ጉዳይ ቢኖር ይኸው የትንቢቱን ፍጻሜ ተፈጥሮ በተመለከተ በሚጠየቁት የማስረጃ አቅርቦት አንጻር ነው።
መጻኢያን ለሆኑ ወንድሞቻችን ትንቢቱ የሚፈጸምበትን ጊዜ አመልካች የሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ መረዳቱን ማግኘት ያን ያህል ላያስቸግራቸው ይችል ይሆናል። ለምሳሌ፣ መጋቢ ስሜ ታደሰ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ "ታቃስ" ሲል የሰየመውን የአጠናንና የአተረጓጎም መርህ ተከትሎ ባስነበበን የነገረ ፍጻሜ አስተንትኖ ውስጥ ይህንን እውነታ በጥቂቱም ቢሆን ማስተዋል ይቻላል። ከአመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ እያለሁ በማገለግልበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግል የነበረና ስነ መለኮት የተማረ ወንድም እኔ በፕሪቴሪዝም ላይ የነበረኝን ዝንባሌ ያውቅና እንወያይም ስለነበር፣ የሥነ ፍታቴን ህግና መርህ የሚያውቅ ሰው በነዚህ ጊዜ ጠቋሚ በሆኑት ምንባባት ላይ ቃሎቹ ከሚያመለክቱት ትውልድና ጊዜ የተለየውን ሊያስብ አይችልም ሲልና የተከተልኩትን ትርጉም ትክክለኛነት ሲያረጋግጥ አስታውሳለሁ። ያም ሆኖ የያዘውን የመጻኢነት አቋም ጠብቆ ዛሬ በሌላ ጽንፍ የፕሪቴሪዝም ተቃዋሚ ለመሆን የተማረውን የሥነ ፍታቴ ህግና መርህ ሆን ብሎ ሲተላለፍ ታዝቤዋለሁ።
ወንድማችን መጋቢ ስሜ ግን ባስነበበን ጽሁፍ ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ ምንባባትን በከፊልም ቢሆን የመጀመርያውን ክፍለ ዘመን አመላካች እንደሆኑ የተገነዘበ ይመስላል። በጊዜው እኔም ራሴ አቀራረቡ ትኩረቴን ስቦት ምስራቅና ምዕራብ የሚመስሉ አመለካከቶች ቢያንስ ሳይነቃቀፉ ሊነጋገሩ የሚችሉበት የጋራ እሳቤ ሊኖራቸው እንደሚችል ተስፋ አድርጌ ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ወንድማችን ዘላለም መንግስቱ ፕሪቴሪዝምን ለመተቸት ባቀረበው ጽሁፍና ጽሁፉን ተከትሎ በተከፈተው ክርክርና ውይይት እንዳንጸባረቀው አቋሙ በተከተለው አፈታት ውስጥ ከመጋቢ ስሜ በተለየ "ይህ ትውልድ" የሚለውን ያየበት መንገድ ሌላ ጽንፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይኸውም ያንን የመጀመርያውን ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ትውልድ ማለት እንዳልሆነ ይልቁንም በየዘመኑ ያሉትን ገናም ወደፊት ጌታ እስኪመጣ ድረስ የሚኖረውን ትውልድ ማለት እንደሆነ ሊያስረዳን ሲሞክርም አስተውያለሁ።
ጥያቄው ግን እነዚህ ነገሮች በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ እንዴት ፍጻሜአቸውን አገኙ? የሚለው ነው፤ ፍጻሜውንም የሚያስረዳ አንዳች ሰነድ ይኖር እንደሆን ብዙዎች አጥብቀው ይጠይቃሉ። ይህ ጥያቄ ግን መጻኢያን ወንድሞቻችን ብቻ የሚጠይቁት ጥያቄ አይደለም። ተመልሶ የሚመጣበትን ጊዜ በተመለከተ ቀደም ብዬ በመግቢያዬ ላይ ከማቴዎስ ወንጌል ብቻ የጠቀስኳቸውንና፣ ኢየሱስ ራሱ የተናገራቸውን ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ ንግግሮቹን በማንሳት፣ መጻኢያን የሆኑ ክርስቲያን ተርጓሚዎች ለነዚህ የንባብ ክፍሎች የሚሰጡትን ፍቺና ትንታኔ ተመርኩዘው አምላክ የለሽ ከሃዲያን፣ ይሁዲነትን የሚከተሉ፣ ሙስሊሞችም አጥብቀው እየጠየቁ ጌታ እየሱስንና ለደቀ መዛሙርቱ እመለሳለሁ ያለበትን ጊዜ እና የሚመለስበትን መንገድ የገለጠበትን ቃሉን ሃሰት ነው ብሎ ለማስካድ ጽኑ መከራከሪያቸው አድርገውታል።
የደቀ መዛሙርቱን ጥያቄ ከልሶ ለመጀመር ያህል፣ ሁሉም እነዚህ ጥያቄዎች፣ ደቀ መዛሙርቱ ያ ከኢየሱስ የሰሙት አስፈሪ የፍርድ ሂደት የሚጀምረው "መቼ" እንደሆነ ለማወቅ ካላቸው ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ፣ የኢየሱስን ትንቢት አስመልክቶ ያቀረቡት ጥያቄ እነዚህ ነገሮች የሚሆኑት “መቼ” ነው? የሚል ነው፤ እነርሱ ማወቅ የፈለጉት፣ “በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችኋል” (ማቴ 23÷ 35) የተባለው ፍርድ በሕዝባቸው ላይ “መቼ” እንደሚመጣ፤ ኢየሩሳሌምን በተመለከተ፣ “ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” (ማቴ 23÷ 37-38) የተባለው “መቼ” እንደሚፈጸም፤ የቤተ መቅደሱንም መፍረስ በተመለከተ፣ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” (ማቴ 24÷ 2) የተባለው “መቼ” እንደሚሆን፤ እንዲሁም ኢየሱስ ተመልሶ የሚመጣውስ “መቼ” እንደ ሆነ እና የእነርሱ ዓለም (ዘመን) የሚያበቃበት ጊዜ “መቼ” እንደሚሆን ነው።
ለእነዚህ የሐዋርያቱ ጥያቄዎች የተሰጠው የኢየሱስ ሙሉ ምላሽ ሳይከፋፈል በማቴዎስ 24 ውስጥ የሚገኘው ሁሉ ነው፡፡ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ውስጥ እየኖሩ ስለመጀመርያው ክፍለ ዘመን የአይሁድ ሕዝብ የፍርድ ጥፋትና ስለ ቤተመቅደሳቸው ውድመት የኢየሱስን ትንቢት ሰምተው የደነገጡ እነዚያ ሰዎች እንዴት ከሺህዎች አመታት በኋላ "ሊሆን ስለሚችል" ስለ ግሎባል ጥፋትና ውድመት ሊያስቡ ይችላሉ? ይሄ ፈጽሞ ሊሆንም ሆነ ሊታሰብ የማይችል ነገር ነው። ይህን መሠረታዊ እውነታ ማየት ከቻልን ይህንን ምዕራፍ በሚገባ መረዳት እንችላለን፡፡
ማቴዎስ 24 እንዳለ ኢየሱስ በሕዝቡ ላይ የተናገረው የፍርድ ትንቢት ነው፡፡ በ70 ዓ.ም የሮማውያን ጦር ሠራዊት ይሁዳን በማጥቃት፣ ኢየሩሳሌምንና መቅደስዋን ወሮ ፈጽሞ እንዳጠፋቸው ከታሪክ እንረዳለን፡፡ እንደ አጠቃላዩ ትንቢትና በማቴዎስ 24 የደብረዘይቱ ፍካሬ በመለኮት እንደ ተደነገገው የመጨረሻው ዘመን መርሃ ግብር ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው መጨረሻ የተገደበውና የተቀነበበው በቤተመቅደሱ መፈራረስና በኢየሩሳሌም ከተማ ውድመት ነው። ከዚህ የተለየ ሌላ "መጨረሻ" አለ ከተባለ ልብ ወለድ ብቻ ነው። ማቴዎስ 24 በሙሉ፣ ኢየሱስ ይህንን ትንቢት ካስተላለፈበት ጊዜ፣ ማለትም ከ30 ዓ.ም ጀምሮ መጨረሻው እስከ ሚሆንበት 70 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ የሚሆኑ ነገሮችን የያዘ ምዕራፍ ነው፡፡ ይህም ማለት፣ ማቴዎስ 24 የሚመለከተው ከስቅለቱ እስከ ኢየሩሳሌም ውድመት ያለውን የ40 አመታት ክፍለ ጊዜ ወቅት ብቻ ነው። ይህም በማቴዎስ 24፣ በማርቆስ 13፣ እና በሉቃስ 21 ላይ የተዘገበልን የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ እውነታ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኘው በ70 ዓ.ም ላይ ነው።
እነዚያ የመጀሙርያዎቹ ደቀ መዛሙርት "ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዘመን መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው?" ብለው ሲጠይቁት፣ በእዕምሮአቸው ውስጥ የነበረውና የሚያስቡት አንድ ጉዳይ ኢየሱስ ይፈራርሳል ሲል የነገራቸው የቤተ መቅደሱ መፈራረስ ጉዳይ ነገር ነበር። ጌታ ኢየሱስ ይህ ቤተ መቅደስ ፈጽሞ ይፈራርስና ይወድማል ብሎ ሲነግራቸው በደቀ መዛሙርቱ አእምሮ ውስጥ ወዲያውኑ ቦታ የያዘው ጉዳይ የመምጣቱና እና የዘመኑ መጨረሻ ምልክት ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ነው። ይህ ጥናታችንን የበለጠ ግልጽ እያደረገው ይመጣል፡፡
እዚህ ላይ የቤተ መቅደሱን መፍረስ አስመልክቶ እምነታችንን የሚያጠናክሩልንና ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ ታሪካዊ ዘገባዎችን እንመለከት፡፡ እነዚህ ታሪካዊ እውነታዎች ግን እምነታችንን ያጠናክሩልን ይሆናል እንጂ ፈጽሞ የእምነታችን መሰረት አይደሉም፤ የእምነታችን መሰረት " እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።" እንደተባለ፣ ትንቢቱ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ውስጥ እንደሚፈጸም የነገረን የኢየሱስ ቃል ብቻ ነው። የቤተ መቅደሱን መፍረስ አስመልክቶ ኢየሱስ ትንቢት የተናገረው በ30 ዓ.ም ላይ ነበር፡፡ ይህም የሚሆነው የዚያ የእርሱ ዘመን ሰዎች የነበሩበት ትውልድ ከማለፉ በፊት እንደሆነ ቀደም ሲል ተመልክተናል፡፡ አንድ ትውልድ በመጽሐፍ ቅዱስ አርባ ዓመታት ያህል ናቸውም ብለናል፤ ስለዚህ የኢየሱስ ትንቢት እንዲፈጸም የቀረው ጊዜ ቢበዛ አርባ ዓመት ብቻ ነበር ማለት ነው፡፡ ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው ትንቢት ከአርባ አመታት በኋላ በ70 ዓ.ም ላይ የሮማውያን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ዘምተው ቤተ መቅደሱን ፈጽመው ደምስሰውታል! “ድንጋይ በሌላ ድንጋይ ላይ ተነባብሮ አይቀርም ይፈራርሳል” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ያኔ ፍጻሜውን አግኝቶአል፡፡
ይህ ትንቢት በብሉይ ኪዳን የተነገረውንና “በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፣ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል።” (ሚክ 3÷ 12) የሚለውን የነቢዩ ሚክያስን ትንቢት ጭምር ሙሉ በሙሉ የሚፈጽም ትንቢት ነበር፡፡
ጆርጅ ፒተር ሃልፎርድ “የቲቶ ሰራዊት ሺ አለቃ የነበረው ቴሬንቲሩስ ሩፉስ፣ የቤተ መቅደሱን ውስጠኛ መሰረት ከቆፋሪዎች ጋር በመረዳዳትና ፈጽሞ በመቆፋፈር የድንጋይ ቁልል አደረገው ተብሎ በታልሙድ እና በማይሞኒዴስ ተዘግቦልናል” [George Peter Holford, The Distruction of Jerusalem (1805) ገጽ 43] ሲሉ ይጽፋሉ፤ ይህ አያስደንቅምን?
ይህ ብቻ ደግሞ አይደለም ፍላቪዬስ ጆሳቨስ ስለ አይሁድ ጦርነቶች በሚተርከው መጽሐፉ "ሮማዊው ጀነራል ቲቶ ቤተ መቅደሱ ከጥፋት እንዲተርፍ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር" ይለናል፡፡ ቲቶ ቤተ መቅደሱ እጅግ የሚያምር ሕንጻ ከመሆኑ የተነሳ እንዳይፈርስ ፍላጎት ነበረው፡፡ ለሮም መንግስት ክብር እንደ ሮማውያን የስኬት መገለጫ አድርጎ በታሪካዊ ቅርስነት ሊጠብቀው ተመኝቶ ነበር፡፡ ቤተ መቅደሱን በተመለከተ የቲቶ ትዕዛዝ ማንኛውም ጉዳት እንዳይደርስበት የተላለፈ የቄሳር ትዕዛዝ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ከቲቶ ወታደሮች አንዱ ከቤተ መቅደሱ መስኮቶች በአንዱ ወርውሮ ያስገባው የእሳት ድንጋይ የዚያን ቅዱስ ሥፍራ መሠረት በእሳት አያያዘው፡፡ ቲቶ ነገሩን በሰማ ጊዜ በታላቅ ድንጋጤ ከነበረበት ስፍራ ተነስቶ … ወደ ቅዱሱ ቤት ሮጦ በመሄድ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም ሞክሮ ነበር፡፡ በከፍተኛ ድምጽ፣ እየጮኸ፣ ለወታደሮቹም በቀኝ እጁ ምልክት እየሰጠ እሳቱን እንዲያጠፉ ወታደራዊ የኢታማጆር ሹም ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ነበር፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ እነዚያ የአለቃቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም በአግባቡ የሰለጠኑና ሥነ- ስርዓት የተማሩ ቆፍጣና የሮማውያን ሠራዊት ልክ አውሬ የሆኑ ያህል እንደ እብድ ሰው ተለውጠው የቄሳርን ትዕዛዝ እንዳልሰሙ ያህል በመሆን አሁንም አሁንም እየጨመረ ከሚሄድ ታላቅ የበቀል መነሳሳት ጋር እሳቱን እየጨመሩ ያበዙት ቀጠሉ [Josephus, Complete Work, Kregel Publication, ገጽ 581]፡፡
ይህ እንዴት ያለ አስገራሚ ታሪክ ነው! ታላቁ ሮማዊ የጦር ጀነራል እና በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራዊቱ ቤተ መቅደሱን ሊያድኑት ከቶ አልቻሉም፡፡ ለምን ይህ ሆነ ቢባል ምክንያቱም ከቲቶ የሚበልጠው፣ ከቄሳርም የሚበልጠው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ቃጠሎ ከመሆኑ ከዓርባ ዓመታት በፊት ቀደም ብሎ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” (ማቴ 24÷ 3) ሲል ተናግሮአል፡፡ እግዚአብሔር ተናግሮአል፣ ጀነራል ቲቶም ትዕዛዙን ይከተላል እንጂ ምንም ሊያደርግ ስለማይችል ያ ቤተ መቅደስ ተቃጥሏል፡፡
ይህ እንግዲህ ድል ለመንሳት የፈለገው የሮም ሠራዊት ኃይል ሳይሆን፣ በሕዝቡ ላይ የሚፈርደው የእግዚአብሔር ኃይል ነበር፡፡ በጆሳቨስ የታሪክ ዘገባ የሚከተለውን እናነባለን፡- “ቲቶ ወደ ከተማይቱ በገባ ጊዜ (መስከረም 26 ቀን 70 ዓ.ም ማለት ነው) የከተማይቱን ጥንካሬ በተለይ ከፍ ብለው የተሰሩትን ቅጠሮቿንና የታነጹበትን ድንጋይ እየተመለከተ ይገረም ነበር፡፡ እነዚያ ግንቦች ምን ያህል ረጃጅሞችና ጠንካሮች መሆናቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ የእያንዳንዱንም ግንብ ውፍረት እያየ ´´በእርግጥ አይሁድን ከነዚህ ጠንካራ ምሽጎች አውጥቶ ያዋረዳቸው እግዚአብሔር በጦርነቱ ከእኛ ጋር ነበር እንጂ፣ ምን ዓይነት እጅ ወይስ ማሽን ይህንን ግንብ ሊያፈርሰው ይችል ነበር?´´ እያለ ይደነቅ ነበር” ይለናል፡፡ [Josephus, Complete Work, Kregel Publication, ገጽ 581]
እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ እንድንል እፈልጋለሁ። ይኸውም የአገራችን የክርስትና እምነት አብዛኛው ፈተናው ከለዘብተኛነት ይልቅ ልማዳዊ አመለካከት ቢሆንም፣ በእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስተምረን ማንም ለዘብተኛ የሆነ ሁሉ እምነታችሁን እንድትጠራጠሩ ምክንያት እንዲሆንባችሁ አትፍቀዱለት፡፡ ቲቶ ሊያድነው ቢወድም የወደመው ቤተ መቅደሱ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ቤተ መቅደስ የወደመው ኢየሱስ በትንቢቱ ይፈራርስ ዘንድ በወሰነለት ክፍለ ጊዜ ውስጥ ነበር ፡፡ ከተባለለት ጊዜና ዘመን አላለፈም። ጄኔራል ቲቶ ይህን ውብ ቤተ መቅደስ ሊያድነው ቢወድም እንኳ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ከተናገረው ትንቢት አንፃር ቲቶ በዚያ ጥፋት ፊት የጉንዳን ያህል ተስፋ አልነበረውም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀድሞውኑ ያንን ጥፋት አትሞታል። እንደ ሚክያስም ትንቢት ያቺ ቅድስት ከተማ እንደ እርሻ መሬት ፍንቅልቅል ብላ ታረሰች፡፡ ይህ ውድመት እና እርሱን በተመለከተ የተነገረው የትንቢት ቃል የጌታችንን ታማኝነት፣ በእውነትም እርሱ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ የታመነም ነብይ እንደሆነ ያጸናልናል። ልክ እንደተጻፈው ባይፈጸም ግን ብርቱ የእምነታችን ስድብ ሆኖ ይኖራል።
እግዚአብሔር እውነተኛ ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስም እውነተኛ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። እኛም በእርሱ ልናምንና የተናገረውን ልንታመን ይገባናል። ሆኖም የማያምኑ ሰዎችና የሚበዙት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ሊያደርግ የተናገረውን አስተካክለው እያነበቡለት፣ ገና በቃሉ አደርጋለሁ ያለውን እንዳላደረገ፣ ትንቢቱም ገና እንዳልተፈጸመ፣ ከአውዱና ከተቀጠረለት የጊዜ ማዕቀፍም ነጥለው ቃሉን በመተርጎም፣ ሥነ መለኮታዊና ፍልስፍናዊ መተጣጠፍ እየሰሩ የትንቢቱ ቃል ገና ወደፊት እንደሚፈጸም ሊነግሩን ይሞክራሉ፡፡ ይህንንም ባደረጉ መጠን በኢየሱስ ትንቢት ላይ የሚከተሉት አተረጓጎማቸው የኢየሱስን ቃሎች እንድንጠራጠር እንጂ እንድንታመን አያደርጉንም።
ከዚህ የተነሳ አጥርተን ለማየት እነዚያን የሥነ-ፍታቴ ጥያቄዎች አበክረን መጠየቅ እንዳለብን የኃላፋውያን አመለካከት ተከታዩች እንስማማለን፡፡ የዚህም ጥናት ዓላማ ይህንኑ ማሳየት ነውወ፡፡ እንደ ወንጌል አማኝ ኃላፋውያን በምንከተለው ስነ ፍታቴ ተጠራጣሪ በሆኑ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስንና የመጽሐፍ ቅዱስን ታማኝነት ዋጋ እና ሥልጣን እንደገና ተመልሶ ማየት እንፈልጋለን፣ እንጂ ማንንም የማሳሳት አላማ የለንም፡፡ ይህ ግን አስቀድሞ በሓሳባችን ውስጥ የገባውንና ለዘመናት ቦታ የያዘውን፣ ብዙዎችም በቀላሉ ሊያደርጉት ያልቻሉትን፣ አሮጌውን ልማዳዊ አስተሳሰባችንን እንደ ልብስ አውልቀን ካልጣልነው በቀር ከቶ የማይቻል ነው፡፡ የቆየውን ሰው ሠራሽ ልማዳዊ አስተሳሰብ በመጣበቅ የለዘብተኛውን ነገረ- መለኮት ተጠራጣሪ አቋም መመከት አይቻልም፡፡
ከሁለቱም አደጋዎች የሚታደገን መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ስለራሱ እንዲናገር ስንፈቅድና የተናገረበትን ዐውድ ማየት ስንችል ብቻ ነው፡፡ በዘመናዊው የለዘብተኛ ነገረ መለኮት የክህደት ትምህርት አንጻር ሊቆም የሚችል ጉልበት ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የሚወጣና የሚቀዳ ኃይል ብቻ ነው እንጂ ማናቸውም ታሪካዊም ሆነ ዘመናዊ ሰው ሰራሹ ልማዳዊ አስተሳሰብ ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡ የቤተ መቅደሱን መፈራረስና ያ መፈራረስ እርሱ በተናገረለት ትክክለኛ ጊዜ ላይ መፈጸሙ ያ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት አንድም ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ማግኘቱ ቃሎቹ እውነተኛዎች መሆናቸውን፣ እንዲሁም እርሱ ፈጽሞ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያሳይ ፍጹም ምሳሌ ነው፣ ብዬ በድጋሚ እናገራለሁ፡፡ "መቼ?" የሚለውን በዚህን ያህል ደረጃ አንስቼ ካሳየሁ በሚቀጥለው ዝግጅቴ "እንዴት?" ለሚለው እተጋለሁ። እስከዚያው ሰላማችሁ ይብዛ።
♦♦♦♦♦♦♦
No comments:
Post a Comment