የጌታ ምጽዓት መቼ እና እንዴት ነው?
በማቴዎስ 24 እንደተገለጸ
፰
ማቴዎስ 24÷ 31 ብዙዎች መነጠቅ ብለው የሚጠሩትን ርእሰ ጉዳይ ያመለክታል፤
♦ ማቴ 24÷ 31 "መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።"
ይህንን ጥቅስ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4÷ 15-17 ካለው ጋር ብታነጻጽሩት ያው አንዱን ኹነት እንደሚናገሩ ታያላችሁ፡፡ (ንጥቀትና ትምህርቱ በተሰኘው ጽሁፌ ላይ ይህንን ንጽጽር በስፋት ስለሄድኩበት ያንን ጽሁፍ እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ) ይህም የተመረጡት በእግዚአብሔር መንግስት ስለ መሰብሰባቸው የተነገረ ነው፡፡
♦ በማቴዎስ 24÷ 32-34 ኢየሱስ ሲናገር እነዚህ ነገሮች በሙሉ የሚፈጸሙት እርሱ ይህ ትውልድ ብሎ በሚጠራው እና እርሱ ሲናገር ቆመው ይሰሙ በነበሩ ሰዎች ዘመን እንደሆነ እናያለን፡፡
ማቴ 24÷ 32-34 "ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።"
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ይህንን ቃል "ይህ ትውልድ አያልፍም" ብሎ ከማንበብና ከመተርጎም ይልቅ "ይህ ዘር አያልፍም" እያሉ ለመተርጎም ሲሞክሩ ይታያሉ፣ በቋንቋ አገባቡ ያየነው እንደሆነ እንኳ ይሄ ትርጉም የሚሰጥ አይሆንም፡፡ ቤተ መቅደሱ የፈራረሰው ከደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ በኋላ በአርባ አመታት ውስጥ ነው። ይኸውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የአንድ ትውልድ ጊዜ ነው። "ይህ ሁሉ" የተባለውን ልብ በሉ፣ የሚፈጸመው በዚያ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ነው፡ -ንጥቀቱ 24÷ 31 ፤ የሰማይና የምድር እልፈት 24÷ 34፤ እንዲሁም የጌታ ዳግመኛ ምጽዓት 24÷ 44፤ ይህ ሁሉ ያኔ እንደሚፈጸም የተነገረ ነው፡፡
ማቴዎስ 24 ስለ ምን ጉዳይ እየተናገረ እንዳለ እናስተውል፡፡ ከአማኞች መካከል አብዛኛዎቻችን በማቴዎስ 24፣ በማርቆስ 13 እና በሉቃስ 21 የተነገሩ ሁነቶችን ገና ያልሆኑና ያልተፈጸሙ ጉዳዮች ናቸው እየተባልን ስንማርና ስናምን ኖረናል፡፡ ብዙዎቻችንም እንዲህ እናስተምር ነበር፡፡ እስካሁንም እንዲሁ በማስተማር የጸኑ ብዙዎች ናቸው። አሁን ግን በነገረ- ፍፃሜ ላይ ሌሎች ነገረ መለኮታዊ አመለካከቶችን ቀረብ ብለን ማየት እንዳለብን እገነዘባለሁ፡፡ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ቤተ እምነቶች ውስጥ፣ አንዳንድ ጊዜም በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ የሚንጸባረቁ፣ ለዘመናት የኖሩና ለቁጥር የሚያታክቱ የተለያዩ የነገረ ፍጻሜ አመለካከቶች ቢያንስ አንዱ ሌላውን መናፍቅ እያለ ሳያጠለሸው ተቻችለው ይኖራሉ። ፕሪቴሪዝምን ግን በወጉ ሳይሞግቱት ፈጥኖ ለማጠልሸትና ኑፋቄ ለማለት አይታገሱትም። ይሄ ትዝብቴ ነው።
እነዚህ ሁነቶች በ21ኛው ክፍለ ዘመንና ከዚያ በኋላ ባለው ዘመን እንደሚሆኑና እንደሚፈጸሙ ያለ እውቀት ሲጠበቅ ተኑሯል፡፡ አሁን ግን ባለን ሥነ ትርጓሜ መጽሓፍ ቅዱስን በቁሙ፣ በታሪካዊነቱና በሰዋሰዋዊ አወቃቀሩ ትርጓሜ የምንስማማ ከሆነ “ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ” ስለእነዚህ ነገሮች እንዲናገሩ እንፍቀድ። እንደ ወንጌል አማኝ ሁላችንንም የሚያግባባ አንድ አቋም አለን ብዬ የማምነው “ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ” (SOLA SCRIPTURA) የተሰኘው የተሓድሶ መሪዎች አቋም ነው፡፡
ይህም ማለት መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የመጨረሻ መሪያችንና አስተምህሮታችን የሚቀዳበት ብቸኛ ምንጭ፣ ትምህርታችንና የህይወት አቋማችን የሚዳኝበት ብቸኛ መስፈርት፣ እምነታችንና ልምምዶቻችን የቆሙበት ብቸኛ ሥልጣን፣ የምንኖርበት የሕይወት መለኪያና ሚዛን ነው፡፡ ዓለማችን በብዙ ዓይነት ተፎካካሪ ሓሳቦች እና እሴቶች የተሞላች መሆንዋ ይታወቃል፣ ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ብዙ ድምጾች በየቦታው ይሰማሉ፡፡
የአሁኑን ዘመን የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካና የመልክዓ ምድር ውዝግቦች በተለይም እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም እንደገና እንደተቋቋመች የሚነገርላትን የእስራኤል ዘ ሥጋን ወቅታዊ ሁኔታ ወስዶ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች መተርጎሚያ አድርጎ የማቅረብ አካሄድ አንዱ የዚህ መገለጫ ነው፡፡ የዜና ማሰራጫ ጋዜጦችንና የልዩ ልዩ የህትመት ሥራዎችን ትኩስ ዜና ተንተርሶ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ለመተርጎም መሞከር የዚህ አካሄድ አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ይህ ግን በራሱ ፍጹምነት የሌለው ሆኖ የብዙ ግራ መጋባት መፈልፈያ አስተሳሰብ ነው፡፡
እንደ ወንጌል አማኝ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስልሳ ስድስቱ የብሉይና የሓዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህ ውጪ ለቤተ ክርስቲያን ሌላ ያልተጻፈ ወይም የተጻፈ ቃል ወይም ልዩ ብርሃን የላትም፡፡ ልማዳዊ አመለካከቶች እና የሰው የሆኑ ልዩ ልዩ ትምህርታዊ መላምቶች የቃሉን ብቸኛ ብርሃንነት እንዲያደበዝዙብን አንፈቅድም፡፡
የዚህን ምዕራፍ እውነታ ለመረዳት በሥነ ትርጓሜ ጊዜ የሚነሱትን መሠረታዊ ጥያቄዎች እንጠይቅ፡፡ ኢየሱስ የሚናገረው ለእነ ማን ነበር? ሊመጡ ያሉትንስ ነገሮች በተመለከተ የሚያስጠነቅቀው እነ ማንን ነበር? በማቴዎስ 23 እና 24 የተሰጠው ትንቢት ስለ እነማን ነበር? ይህንን ለቅዱሳት መጻሕፍት በሚሆን ታማኝነት በቅንነት ካደረግን፣ ይህ ምዕራፍ በጠቅላላ ስለ ሐዋርያቱ እና ስለ እነርሱው ዘመን ብቻ እንጂ እኛ ስላለንበት ዘመን የሚለው ምንም ነገር እንደሌለው እናያለን፡፡
ይህንን ክፍል በታሪካዊነቱ ከተመለከትነው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር ለእነርሱ ነው እንጂ ለዛሬዎቹ እኛዎች አይደለም፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጥልን እነርሱን በግል የሚመለከታቸውን ነገር ለይቶ መናገሩ ነው፡፡ ከማቴዎስ 24 በተወሰዱ እና ከዚህ በታች በተዘረዘሩ ጥቅሶች ሁሉም ነገር ከሐዋርያቱ ጋር በግል የተቆራኘና የተዛመደ እንደሆነ፣ ከ2000 ዓመታት በኋላ ካለን ሰዎች ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር እንደሌለ ከኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር ተመልከቱ፡- [በጥቅሶቹ ውስጥ እናንተ በሚል በተለዋጭ የገቡት ቃላት አጽንዖተ እኔ መሆናቸውን ልብ ይሏል።]
“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም (እናንተን) እንዳያስታችሁ (እናንተ) ተጠንቀቁ። (ማቴ 24÷ 4)”
“ጦርንም የጦርንም ወሬ (እናንተ) ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና (እናንተ) ተጠበቁ፥ (እናንተ) አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው( ማቴ 24÷ 6)።”
“በዚያን ጊዜ (እናንተን) ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል (እናንተን) ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ (እናንተ) የተጠላችሁ ትሆናላችሁ( ማቴ 24÷ 9)።”
“እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ (እናንተ) ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል( ማቴ 24÷ 15)”
“በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ( ማቴ 24÷ 16)”።
“እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ (እናንተ) በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ።”(ማቴ 24÷ 33)
ከላይ ያሉትን ጥቅሶች በጥንቃቄ ስትመለከቱ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው በቀጥታ ከሐዋርያቱ ጋር በግል ግንኙነት ስላላቸው የእነርሱ ዘመን፣ የእነርሱ ኑሮና ሕይወት ጉዳይ እንደሆኑ እንመለከታለን፡፡ ቃሎቹ በጠቅላላ ይህንን የሚያመለክቱ ናቸው ።
በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአግባቡ ያልተተረጎሙ አንድ ተጨማሪ ነገር ማየት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ፡- በቁጥር 6 ኢየሱስ የግሪኩን “ሚሎ” /Mello/ የተሰኘውን ቃል ተጠቅሟል፣ ይህም በእንግሊዝኛው “about to” ወይም “about to be” ማለት ሲሆን በአማርኛችን “ሊሆን” ወይም “ሊከሰት” የተቃረበ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትሰሙታላችሁ የተባለው ጦርና የጦርነት ወሬ የሚሰማው፣ የሚከሰተውና የሚሆነው እነርሱ ባሉበት ዘመን ነው፡፡ በማቴዎስ 24 ስለ ሐዋርያቱ ዘመን እና ቀኖች እንጂ ስለ ሌላ ዘመን እንደማይናገር ይህ አንድ ዋና ማስረጃ ነው፡፡
የአሁን ዘመን ሰባኪያን ግን በቁጥር 6 ላይ ያለውን ቃል እየጠቀሱ “የጌታ ምጽዓት ምልክቶች ዐይናችን ሥር ይኸው እየተፈጸሙ ናቸው” ይላሉ፡፡ ይህ ግን ቃሉን አሳስቶ መተርጎም ነው፡፡ ልዩ ልዩ የአለም በጎም ሆኑ ክፉ ሁነቶች ከዚህ ቀደም በአለም የነበሩ አሁንም ያሉ እንደሆኑ ሁሉ ወደ ፊትም በአለም ይኖራሉ፣ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው የነገረ ፍጻሜ ትንቢት ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱሳዊው የነገረ ፍጻሜ ትንቢት ግን ትኩረቱ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን እስራኤልና በቤተክርስቲያን ላይ እንደሆነ የትንቢቱ አውድና ትንቢቱ እንዲፈጸም የተቀጠረለት የጊዜ ማዕቀፍ ያንን ያስተምራል።
እንግዲህ ይህ ሁሉ በግል ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርትና ከዘመናቸው ጋር የተገናኘ መሆኑን ማየት አስቸጋሪ አይደለም፡፡ በዚህ ምዕራፍ ለእኛም ሆነ ላለንበት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠቀስ ምንም ነገር አናገኝም፡፡ በጠቅላላው የሚናገረው ስለ እነርሱና ስለዘመናቸው ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እየነገራቸው ያለው እውነት ስለእነርሱ፣ ለእነርሱ ወይም በእነርሱ ዙርያ፣ አስቀድመው ጠይቀውት ስለ ነበሩት ዋና ነገሮች፣ ሊሆኑ ስላሉ ጉዳዮች ነው እንጂ፣ ስለሌላ ሩቅ ዘመን አይደለም፡፡
ከዚያም በማቴዎስ 24÷ 32-33 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ በለስ በማንሳት አጠር ያለና ግልጽ ምሳሌ ይነግራቸዋል፡፡ በቀደመው የእስራሌል ማህበረሰብ ውስጥ በለስ ስትለሰልስና ስታቆጠቁጥ ለበጋ ወራት መምጣት ምልክት ሆና ታገለግል ነበር፡፡ ኢየሱስ ይህንን ትንቢት ሲናገር በእኛ አገር ሆኖ ቢሆን ኖሮ የሚጠቀምበት ምሳሌ የአደይ አበባ በሆነ ነበር፡፡ “አበቦች በሜዳ ሲፈኩ፣ የእንግጫ ሳር ሲበቅል ያን ጊዜ መስከረም ሊጠባ እንደሆነ ታውቃላችሁ” ይለን ነበር፡፡ ልክ እንደዚሁ እነዚያ የተነገሩ ምልክቶች መሆን ሲጀምሩ፣ እንግዲያውስ ያን ጊዜ “በደጅ እንደቀረበ” ያውቃሉ ማለት ነው፡፡ የመጻኢነትን ዘመን ቆጣሪነት የሚከተሉ ተርጓሚዎች ግን በዚህ ጥቅስ ላይ የምታቆጠቁጠው በለስ እስራኤል ዘሥጋ እንደሆነች ይኸውም በ1948 ዓ.ም መንግሥቷን ስትመሠርት እንደ ተፈጸመ በማስተማር ስህተት ሲፈጽሙ ይደመጣሉ፡፡
ኢየሱስ ግን እየተናገረ ያለው ከዚህ የተለየውን እንደ ሆነ ከዐውደ ምንባቡ ማየት ይቻላል፡፡ ከዚህም በላይ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነው ጌታችንን ጥያቄ ያቀረቡለት የእነዚያ 12 ደቀ መዛሙርት ትኩረትም ሆነ የኢየሱስ ትንቢታዊ ምላሽ ያንንው የነበሩበትን ትውልድ የሚመለከት እንጂ፣ እነርሱም ሆኑ ትውልዳቸው የምድር ላይ እድሜያቸውን ከጨረሱ በኋላ በብዙ መቶና ሺህ ዓመታት ከእነርሱ ርቆ ስላለ ዘመን እያሰቡ አይደለም። ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ እያሰቡ ቢሆን ኖሮ ትንቢቱ ከዐውዳቸው ጋር የማይገጥም ይሆን ነበር፡፡ እዚህ ላይ ግን አንድ ጥያቄ እናንሳ። ይኸውም በደጅ የቀረበውና ሊሆን የቀረበው ምንድን ነው? የሚለው ነው። ለዚህ ጥያቄ መልሳችን ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን የጠየቁት ነገር ሁሉ ነው። በይሁዳ ላይ ፍርዱ የቀረበ ነው። የሕዝቡ ጥፋት ቅርብ ነው። የቤተ መቅደሱ ጥፋትና ውድመት ቅርብ ነው፡፡ የአሮጌው ኪዳን ዘመንና የጠየቁት የዓለም መጨረሻ ቅርብ ነው። እንዲሁም የኢየሱስ መመለሻ፣ ዳግመኛ ምፅዓቱ ቅርብ ነው ማለት ነው፡፡
እንደገና በጽሑፌ የሓሳብ አጽንዖት ልስጥ፡፡ በማቴዎስ 24 ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም “በጭፍራ መከበብ” (ሉቃ 21÷ 20) ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች እና የሚሆኑትን ነገሮች ዘርዝሮ ተናግሮአል፡፡ በተለይ እየደጋገመ “በዚያን ጊዜ” የሚለውን ሐረግ ሲጠቀም እነዚያ የተቀሩት ሌሎች ሁነቶች ሁሉ የሚሆኑት ከከተማይቱ መከበብ እና ውድመት ጋር በመጣመር ነው። ለአብነት ያህል የሚከተሉትን የወንጌሉን ክፍሎች እንመለከት፦
“በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ (ማቴ 24÷ 16)”።
“በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና( ማቴ 24÷ 21)።”
“በዚያን ጊዜ ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም። ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ (ማቴ፣ 24÷ 23-24)።
“በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል (ማቴ 24÷ 30)”።
ኢየሱስ መቼ እንደሚመለስ ትንቢቱም መቼ እንደሚፈጸም ሲያመለክታቸው የሰጣቸው ዐብይ ምልክት ኢየሩሳሌም በጭፍራ ተከባ የሚታይበትን ዓይነተኛ ጊዜ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ይህንን ጭፍራ (ሠራዊት) ኢየሩሳሌምን ከብቦ ካዩ፣ ያኔ ከላይ በተዘረዘሩ ጥቅሶች ተነግሯቸው የነበረውን ነገር ያውቃሉ፡፡ በዚያን ጊዜ (ያኔ) ወደተራራዎች ይሸሻሉ (ቁ 16)፤ ከመጀመሪያ ጀምሮ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ መከራ በዚያን ጊዜ (ያኔ) ይሆናል (ቁ 21)፤ የተመረጡትን እስኪያስቱ ድረስ እንኳ ምልክቶችን የሚያሳዩ ሐሰተኛ ነብያት በዚያን ጊዜ (ያኔ) ይነሳሉ (ቁ 24) እንዲሁም ኢየሱስም በዚያን ጊዜ (ያኔ) በታላቅ ኃይልና ክብር ተመልሶ ይመጣል (ቁ 30)።
አንድ ጊዜ የሮም ሠራዊት ከመጣ በዚያን ጊዜ (ያኔ) እነዚህ ሁሉ ተከታታይ ምልክቶች ሲሆኑ፣ የኢየሱስ ዳግመኛ ምጽዓት ያኔ ይሆናል፡፡ የዚህን ትንቢት ዋና ዋና ጉዳዮች ይፈጸማሉ ተብሎ ከሚጠበቁበትና “ይህ ትውልድ” ከተሰኘው የጊዜ ማዕቀፍ ጋር አጣምረን በዚያው ታሪካዊ ዐውድ ውስጥ ምርመራችንን ብናደርግ፣ ይህ ጭፍራ የመጣው በ60ዎቹ መሆኑን፣ የጀመሩትን ጦርነትና የከተማይቱን ውድመት የፈጸሙት በ70ው ዓ. ም መሆኑን፣ ስለዚህም ኢየሱስ እንደ ተስፋ ቃሉ የተመለሰው በእነዚህ ጊዜያት መሆኑን ለማመን እንገደዳለን፤ ስለዚህም ኢየሱስ እንደ ተስፋ ቃሉ የተመለሰው በእነዚህ ጊዜያት ነው፡፡ ኢየሱስም መቼ እንደሚመለስ ለሐዋርያቱ ጥያቄ የሰጠው ሌላው ሁለተኛ መልሱ በቁጥር 34 ላይ ይገኛል ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።”
ኢየሱስ መቼ እንደሚመለስ ሲናገር “ይህ ሁሉ ብሎ” የዘረዘረው ነገር ይፈጸማል ባለበት በዚህ ትውልድ ዘመን ነው፡፡ ይህ ሁሉ የተባለው በቁጥር 30 እና 31 የተጠቀሰውን የምጽዓቱንም ትንቢት፣ “የሰው ልጅንም በሰማያት ደመና ሲመጣ ያዩታል” የሚለውን ይጨምራል፡፡ በኢየሱስ ንግግር ውስጥ “ይህ ትውልድ” የተባለው፣ ኢየሱስ እነዚህን ትንቢቶች የሰጠው ትውልድ ነው እንጂ መጻዒያን እንደሚመስላቸው የአይሁድን ሕዝብ እንደ አንድ ዘር አድርጎ የሚያሳይ አይደለም። እርሱ መመለስ ያለበት ያኔ እነዚህን የፍርድ ትንቢቶች ይናገር በነበረበት ጊዜ የነበረው ትውልድ (ሕዝብ) ገና እያለ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ዳግመኛ እንደ ተመለሰ መረዳት ያለብን በ70 ዓ.ም በአይሁድ ሕዝብ ላይ ይደርሳል ብሎ በተናገረውና በተፈጸመው የፍርድ ጊዜ ላይ ሲሆን፣ እንዲሁም “ያኔ” እነዚህን የፍርድ ትንቢቶች እርሱ ሲናገር ቆሞ ይሰማው የነበረው ያ ትውልድ ገና በሕይወት እያለ ነው፡፡ ይኸውም በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡
ኢየሱስ ትንቢቱን ሲጀምር በማቴዎስ 23 ቁጥር 36 ላይ “ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል” ብሎ ነበር፣ ትንቢቱን ሲያጠቃልልም በማቴዎስ 24÷ 34 ላይ ተመሳሳይ ነገር በመናገር “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ይላል ። እነዚህ ሁለት ጥቅሶች የትንቢቶቹን መነሻና መድረሻ፣ የፍጻሜአቸውንም የተወሰነ የጊዜ ማዕቀፍ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ እንግዲህ ያ ትውልድ በኢየሱስ በሥጋው ወራት፣ በሐዋርያቱና በጥንት ቤተክርስቲያን ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሕዝብ ትውልድ ማለት ነው፡፡
ደቀመዛሙርቱ “ይህ መቼ ይሆናል” በሚል ጥያቄ ማወቅ የፈለጉት የሁነቶቹን መቼት ነው፡፡ ታዲያ ኢየሱስ በንግግሩ ምን ያህል ግልጽ መሆን ችሏል? ኢየሱስ ቀኖችን አልጠቆመም፤ ነገር ግን እርሱ የተነበያቸው እነዚያ ነገሮች ሁሉ ተፈጻሚ የሚሆኑበትን የአርባ ዓመታት ጊዜን ሰጣቸው፡፡ እነዚህም ምልክቶች መጨረሻው መቼ እንደሆነ፣ የሚመጣበት ጊዜ እንደቀረበ የሚያውቁበትና የሚረዱበት ምልክቶች ናቸው፡፡ በመላው አዲስ ኪዳን ሐዋርያቱ እነዚህን ዘገባዎች ሁሉ ሲጠቀሙባቸው እናገኛለን፡፡ የኢየሱስ መመለሻ ጊዜ እየቀረበ በመጣ ቁጥር እንዲሁም በይሁዳ ሕዝብ ላይ የሚከናወነው ፍርድ እርግጠኝነት እየጨመረ ሲመጣ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ እና ቤተክርስቲያንን ለማዘጋጀት ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡ለማቴዎስ ምዕራፍ 24 ማጠቃለያ ሰጥተን ከማለፋችን በፊት ይህ ትውልድ የተሰኘው ቃል ከተጠቀሰበት ቁጥር ቀጥሎ በቁጥር 35 ላይ የተጻፈውን ተመልክተን እንጨርስ፡- “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።”
ኢየሱስ በመጀመሪያው ክፍለዘመን ላይ እንደሚመለስ መተንበዩ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ታዋቂው የ20ኛው ክፍለ ዘመን ጸሐፊ ሲ.ኤስ. ሉዊስ ሲሞግት ኢየሱስ እንደተሳሳተ አድርጎ “እርሱ ከማንም ይልቅ የአለምን መጨረሻ አስመልክቶ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረውም” ሲል ይደመድማል፡፡ [C.S Lewis, The World Last Night and Other Easayes, P. 98] ሉዊስ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ እንደሚፈጸም ጊዜ የተቀጠረለት የመመለስ ትንቢት ተነግሮ እንደነበር የሚያረጋግጠውን ትክክለኛ ስነ አፈታትን የተቀበለ ቢሆንም፣ በጌታችን ላይ ይህንን የማይረባ አቋም የያዘበት ምክንያት ግን ትንቢቱ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ተፈጽሞ ያለፈ ለመሆኑ ማስረጃ ለማቅረብ ከቶ ባለመቻሉ ነው፡፡ በእርግጥም በብሉይ ኪዳን ዘመን ማንም በእግዚአብሔር ስም የሐሰት ትንቢት ቢናገር በሞት ይቀጣ እንደነበር “ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል። በልብህም። እግዚአብሔር ያልተናገውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥ ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው” (ዘዳ18÷ 20-22) ከሚለው ቃል እናነባለን።
ኢየሱስ ቢያንስ ሦስት ጊዜ አጽንኦት በሚሰጥ የንግግር ሃረግ አስረግጦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ” እያለ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣ ተንብዮአል (ማቴ 10÷ 23፤ 16÷ 28፤ 24÷ 34)፡፡ እንግዲህ እርሱ ተሳስቶ ከነበር፣ ሞት የሚገባው ሃሰተኛ ነብይ ነበር ማለት ነው፡፡ ሉዊስ ባለማወቅ ለክርስቶስ ተሰቅሎ መሞት ተገቢነት ማረጋገጫ እያቀረበ ይመስላል፡፡ ነብዩ ኤርምያስ አንድ ነብይ ነብይ መሆኑ የሚረጋገጥበትን መመዘኛ በምዕራፍ 28÷ 9 ላይ “ስለ ሰላም የተናገረ ነቢይ፥ የነቢዩ ቃል በሆነ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በእውነት የሰደደው ነቢይ እንደ ሆነ ይታወቃል” ብሎ ሲነግረን፣ በተለይ በሃሰተኛ ትንቢቱ ጊዜን ገድቦ የተናገረውን ሃሰተኛውን ነብይ ሃናንያን እግዚአብሄር እንደገደለው ቁጥር 1-17 ይነግረናል። ሕዝቅኤልም በምዕራፍ 13÷ 3 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምንምን ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉ ለሰነፎች ነቢያት ወዮላቸው” ሲል፣ ዘካርያስም በምዕራፍ 13÷ 3 “ማንም ደግሞ ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባቱና እናቱ። አንተ በእግዚአብሔር ስም ሐሰትን ተናግረሃልና በሕይወት አትኖርም ይሉታል ትንቢትንም ሲናገር የወለዱት አባቱና እናቱ ይወጉታል” በማለት ሃሰተኛ ነብያትን ይኮንኗቸዋል።
በ1ኛ ሳሙኤል 3÷ 19 እና 9÷ 6 እንዲሁም በኢሳያስ 44÷ 24-26 እግዚአብሔር በራሱ ነብያት የተነገሩ ትንቢቶች እንደማይወድቁ ወይም ሳይፈጸሙ እንደማይቀሩ ያረጋግጣል፡፡ በዚህ መመዘኛ መሰረት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ እንደሚፈጸም የተነገረው የክርስቶስ ትንቢት ሳይፈጸም ከቀረና ክርስቶስ ከተሳሳተ እንግዲያውስ በእርሱ ያመንን ሰዎች በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ነው ያለነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ የሚያስብ አዕምሮ ያለው ማንስ ሰው ቢሆን አሁንም ገና ወደፊት ትንቢቱ ይፈጸማል በማለትም ሆነ ለደህንነቱስ ቢሆን ስለምን ይታመነዋል? ተቀባይነት ያለው ድምዳሜ አንድ ብቻ ነው፣ እርሱም ኢየሱስ አልተሳሳተም! ትክክልም ነበር፡፡ አለበለዚያ ከ”ሃሰተኞች” እና ከ”ሰነፎች” ጋር ተቆጥሮ በሞት መቀጣት ያለበት ሃሰተኛ ነብይ ነበር ማለት ነው፡፡ እርሱ ተሳስቶ ከነበረ፣ እንግዲያውስ እኛ ክርስቲያኖች እነዚያን ያልታመኑ የእርሱን ትንበያዎች በተመለከተ “ስህተት የሌለባቸው” ወይም “ንጹህ የእግዚአብሔር ቃል” ናቸው ብለን በማመናችንም ሆነ በማጥናታችን ጊዜአችንን በከንቱ እያባከንን ነው ማለት ነው፡፡ እባካችሁ ወንጌላዊ ወደሆነው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ስልጣንና ወደ መጀመሪያው አውድ ተመልሰን የክርስትናን እውነት ከስድብ እንታደግ!!
ኢየሱስ ያለውን ማስተዋል ከቻልን የንባብ ክፍሉን ለመረዳት የበለጠ ይረዳናል፡፡ ኢየሱስ ሲተነብየው የነበረውን ርዕሰ ጉዳይ አልቀየረም፡፡ አሁንም እየተናገረ የለው ጥፋት ሊደርስበት ስላለው የአይሁድ ዓለም ነው፡፡ ይህ የአይሁድ ሕዝብ እርሱም የአይሁድ ዓለም፣ ማለትም የእነርሱ “ሰማይና ምድር ያልፋሉ” እያለ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ቃሉ፣ ትንቢቱ፣ ግን አያልፍም። ልክ እንደተናገረው ይሆናል፤ ይፈጸማልም፡፡ ቃሎቹ አይወድቁም! በአርባ አመታት ውስጥ ያ እጅግ ውብ የሆነው ቤተ መቅደስ፣ እንዲሁም ያቺ ኢየሩሳሌም ተቃጥለው ይጠፋሉ፡፡ በዚያ የሚኖሩ ሁሉ ይገደላሉ፣ ይሰደዳሉ፣ ወይም በባርነት ይሸጣሉ፡፡ እንግዲህ ኢየሱስ እመለሳለሁ ያለበት ጊዜ በማቴዎስ 23 እና 24 ካደረግነው ጥናት ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር ፍርድ በይሁዳ ሕዝብ ላይ በሚፈጸምበት ጊዜ ነው። ፍርዱም በሕዝቡ ላይ የፈሰሰው ሲሆን፣ ወቅቱም ያ ትውልድ የነበረበት ጊዜ ነው። እንግዲህ ኢየሱስ ከገዛ ራሱ ትውልድ ውጭ በሌላ ትውልድ እመለሳለሁ ያለበት አንድም ጥቅስ ከማቴዎስ 23 እና 24 መጥቀስ የማንችል ሲሆን፣ በሌሎችም የአዲስ ኪዳን ምንባባት ምጽዓቱን የሚጠቁሙ ክፍሎች ይኸንንው የሚደግፉ ናቸው።
በዚህ አጭር ጥናት ማቴዎስ 24 ላይ ያለውን ሁሉ ቁጥር በቁጥር ጥናት አድርጎ ሰፊ ሥራ መሥራት ራሱን የቻለ ትልቅ መጽሓፍ ይወጣዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ከጊዜና ከሁኔታዎች አንጻር አሁን አልተቻለም፤ ቢሆንም ግን ወደ ፊት መለስተኛ ዝርዝር ሥራ ለማዘጋጀት እመኛለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment