ክፍል ፭
ፍርድ፣ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ጭብጥ
ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እንደሚስማሙበት የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍን ጭብጥ መልዕክት የሚነግረን ቃል በራዕይ 1÷7 ላይ ይገኛል ብለን ነበር ያለፈውን ጥናት ቀጣይ ሃሳብ በይደር ያስቀመጥነው።
ራዕ 1÷ 7 "እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።"
ይህ ምንባብ ክርስቶስ በእስራኤል ላይ በፍርድ ዳግመኛ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ በብሉይ ኪዳን የደመና መምጣት በተደጋጋሚ የሚያመለክተው እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ በፍርድ እንደሚመጣ ያለውን ትንቢታዊ ገለጻ ነው፡፡ በራዕይ መጽሐፍ ላይም "ይመጣል" ተብሎ የተነገረው ፍርድ የሚፈጸመውም "የወጉት" ተብለው በተገለጹት ላይ ነው፡፡ ታዲያ እነርሱ እነማን ናቸው? አዲስ ኪዳን ክርስቶስን የወጉ ብሎ በተደጋጋሚ የሚጠቁመው የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አይሁድን ነው፡፡ እነዚያ ክርስቶስን የወጉት ደግሞ "የምድር ወገኖች" የተባሉት የሚያመለክተው፣ ማለትም ምድር የተባለው የተስፋይነቱን ምድር ወይም እስራኤልን ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ለአንባቢዎቹ የሚያስተዋውቀው የፍርድን ሥነ-መለኮት ሲሆን፣ ይኸውም በተለይ የእግዚአብሔር ፍርድ የእስራኤልን ሕዝብ በመቃወም የጸና እና የተወሰነ በመሆኑ ላይ ነው፡፡
የእስራኤል ሕዝብ ጌታን የሰቀሉ እና በግልጽ በአደባባይ የእግዚአብሔርን ፍርድ በራሳቸው ላይ የጋበዙና የጠሩ ሕዝቦች ናቸው፡- "ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ።" (ማቴ 27÷ 25)፡፡ በ70 ዓ.ም በእስራኤል ላይ የሆነው የእግዚአብሔር ፍርድ በውድ ልጁ በመሲሃቸው ላይ የፈጸሙትን ግፍና ወንጀል የሚመጥን ነበር፣ ወንጀላቸውም የክርስቶስ ስቅላት ነበር፡፡ ይህ ወንጀል በታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት እጅግ የከፋው ወንጀል ሲሆን ፣ ለዚህ ተወዳዳሪ ለማይገኝለት ወንጀል የሚገባውም ቅጣት በታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋው መሆን አለበት፤ እርሱም "ታላቁ መከራ" ተብሎ የሚጠራው ነው። ከዚህ የተለየውንና ያነሰውን ማንኛውንም የዚህ አለም መከራ "ታላቁ መከራ" ብሎ መጥራት ያዚያን ትውልድ ወንጀል አሳንሶ መመልከት ይሆናል።
በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ የተዘገበው የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ተብሎ የሚጠራው የጌታችን ትንቢት የቤተመቅደሱን መፈራረስ እና የዚህን መከራው ሁኔታ የሚያሳይ ትንቢትን ይዞአል፡፡ እጅግ የሚበዙ የመፅሐፍ ቅዱስ መምህራን ዮሐንስ በደብረ ዘይቱ ተራራ ላይ የተነገረውን የክርስቶስን ፍካሬ ያየበት እና የተረጎመበት አስፋፍቶም ያቀረበበት የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፉ እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ለአሁኑ ከደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ እና ከዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ላይ የተወሰኑ መመሳሰሎችን በመጠኑ አንስተን እንመልከት፡፡
* ከሁሉ በፊት፦
ራዕ 1÷ 1 እነዚያ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ሁነቶች የሚሆኑት "ቶሎ" እንደሆነ ይነግረናል፡፡ በደብረዘይቱ ተራራ ፍካሬም ክርስቶስ "እውነትት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፉም" /ማቴ 24÷34/ ይላል፡፡
* በሁለተኛ ደረጃ ሁለቱም ታላቁን መከራ ይጠቅሳሉ፣
ማቴ 24÷21 "በዚያ ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።"
ራዕ 7÷ 14 "እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።"
* በመጨረሻም ሁለቱም ተመሳሳይ በሆነ የቋንቋ አጠቃቀም ቤተ መቅደሱን እና እየቀረበ ያለውን ውድመቱን ይጠቀሳሉ፡-
ሉቃ 21÷ 24 "በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።
ራዕ 11÷ 2 "በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።"
ለዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ እንደ መሰረት ሆኖ በአዲስ ኪዳን የመጀመሪያዎቹ ሶስት ተመሳሳይ ወንጌላት የተዘገበው የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ በእስራኤል እጣ ፋንታ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ከአራቱም ወንጌላት ይህንን የደብረ ዘይቱን ፍካሬ ያላካተተ ብቸኛ መጽሐፍ የዮሐንስ ወንጌል ሲሆን ፣ ዮሐንስ ይህንን ጉዳይ በስፋት የሚዳስሰው አቡቀለምሲሳዊ በሆነው በዮሐንስ ራዕይ መጽሐፉ ላይ ነው፡፡ የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ሥነ መለኮታዊ አውድ የሚጀምረው ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በለሲቱን ከረገመበት ከማቴዎስ 21÷ 19 ላይ ነው። ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ በማቴዎስ 21÷ 33 ላይ ስለ ወይን አትክልቱ ባለቤት ምሳሌ ይናገራል፡፡ በዚህም ምሣሌ "የእግዚአብሔር መንግስት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች" (ማቴ 21÷ 43) ብሎ ትንቢት ይናገራል፡፡ ስለ እስራኤል እየተናገረ እንደ ሆነ አውቀዋል /ማቴ 21÷45/፡፡
በማቴዎስ 23 ላይ ኢየሱስ ጻፎችንና ፈሪሳዊያንን በተደጋጋሚ ከባድ ዘለፋ "ግብዞች" እያለ ይጠራቸዋል /ማቴ 23÷ 13-15/፤ በማቴዎስ 23÷ 31-36 እስራኤል በታሪኳ ነብያትን እንደ ገደለች አስታውሶ አሁን ደግሞ የእግዚአብሔርን ልጅ ልትገድለው እንዳላት ያመለክታል፡፡ በማቴዎስ 23÷ 36 "በዚህ ትውልድ" ላይ ሲል በቁጥር 37-38 እንደተገለጸው ትኩረቱ እስራኤል መሆንዋ አያከራክርም፡፡ እንግዲህ የደብረ ዘይቱ ተራራም ፍካሬ አጠቃላይ አውድ የተመለከተው እና የሚገነባው በዚህ ዳራ ላይ ነው፡ ፡
የደብረ ዘይቱን ተተራ ፍካሬ የሚከፍት ዋነኛ ጥያቄ ቤተ መቅደሱን በተመለከተ የቀረበው ንግግር ሲሆን፣ ይኸውም በማቴ 24÷ 1 እና 2 የተገለጸው ነው፡፡
"ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው"።
ለዚህ የኢየሱስ ንግግር የደቀ መዛሙርቱ ምላሽ "ይህ መቼ ይሆናል?" የሚል ጥያቄ ነበር፡፡ በቁጥር 3 ላይ "ዓለም" ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ /aion/ የተሰኘው ቃል የተሻለው ትርጉም "ዘመን" የሚለው ነው፡፡ በደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ውስጥ ማዕከላዊ ቦታን የያዘው የአይሁድ ቤተ መቅደስ ጉዳይና የህዝቡ እጣ ፈንታ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በማቴዎስ 24 ላይ የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች ሆነው ከቀረቡት መካከል የተወሰኑትን በወፍ በረር እንመልከታቸው፦
♦ ማቴ 24÷ 15 ሰለ ተቀደሰችው ሥፍራ ይናገራል፡፡
ማቴ 24 ÷ 6 ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።
በዓለም ታሪክ ውስጥ ጦርነትንና የጦርነትን ወሬ ሰምተን የማናውቀው መቼ ይሆን? ይህ የቁጥር 6 ጦርነት ታዲያ ምን ዓይነት ምልክት ነው? የሮም ሰላም /Pax Romana/ በተሰኘው ዘመን ላይ ኖራችሁ ቢሆን ኖሮ ይህ አይነተኛ ምልክት ይሆንላችሁ ነበር፡፡ በሮም ነገስታት ታሪክ ይህ የሰላም ዘመን በአንጻራዊነት ብዙም የጎላ ብጥብጥ ሳይታይበትና ሳይሰማበት እስከ ቄሳር ኔሮ ዘመን ድረስ ቀጥሎአል፡፡ በሮም ሰላም /Pax Romana/ ዘመን ውስጥ ጦርነቶች እና የጦርነት ወሬ ወዲያውኑ መከራውን ቀድመው ታይተዋል፡፡
♦ በማቴ 24÷14 እንደተገለጠው ወንጌል ለዓለም ሁሉ ይሰበካል
ማቴ 24 ÷14 "ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።
ኢየሱስ አይሁዳዊ እንደነበር ለአይሁድም እንደሚናገር መዳንም ደግሞ የአይሁድ እንደነበር አስተውሉ፡፡ የመጀመሪያዋ የክርስቲያን ቤተክርስቲያን አይሁድ በሆኑ ምዕመናን የተዋቀረች ነበረች፡፡ አሕዛብ የይሁዲነት ተከታይ ሳይሆኑ በቀጥታ ወደ ቤተክርስቲያን የገቡት ከበዓለ ሃምሳ ቀን በኋላ በግምት አስር ዓመት ያህል ቆይቶ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ተልዕኮን በ"ዓለም ሁሉ" የማዳረስ እንቅስቃሴ የተጀመረው በአንጾኪያ በተደረገው ውሳኔ ነበር (ሐዋ11÷ 19-30)፡፡ መጨረሻው ከመሆኑ በፊት ወንጌል ከአይሁዳዊነት በላይ አልፎ መሄድ ነበረበት፡፡ ይህም ማለት ከአለም ፍጻሜ በፊት የታላቁ ተልእኮ ትእዛዝ ተፈጽሞ ነበር ማለት ነው። ስለዚህም በዚያው ዘመን ወንጌል ለዓለም ሁሉ ተሰብኮ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ በማስረጃ ያሳየናል።
ቆላ 1÷ 5-6 "ስለዚህም ተስፋ በወንጌል እውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ። ይህም በዓለም ሁሉ ደግሞ እንዳለ ወደ እናንተ ደርሶአል፥ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከከሰማችሁበትናካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ ደግሞ እንዳለ እንዲህ በዓለም ፍሬ ያፈራል ያድግማል።"
ሮሜ 1÷8 "እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማች አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ።
♦ ማቴዎስ 24÷15 ስለ ጥፋት ርኩሰት ይናገራል፡፡
ማቴ 24÷ 15 "እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥"
ጆሳፈስ እንደ ጻፈው "ቤተመቅደሱ በተደመሰሰ ጊዜ የቲቶ ሰራዊት የሮማዊያን ግርማ ምልክት የሆነውን SPQR የተጻፈበትንና የሮምን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እና የሕዝብ ኃይልና ብዛት የሚወክል የንስር ምልክት ይዘው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ዘልቀው በመግባት በዚያ አስቀመጡት፤ በዚያም በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በግንባራቸው ወድቀው ቄሳርን አመለኩ" ሲል ይዘግባል /Wars, መጽሐፍ 6፣ ምዕራፍ 6 አንቀጽ 1/፡፡ ይህ እንግዲህ ጥፋትን ያደረገው ርኩሰት የመጨረሻ ተግባር ነው፣ ነገር ግን ይህ የጥፋት ርኩሰት የጀመረው በሉቃስ 21÷ 20 እንደተዘገበው ገና ኢየሩሳሌም በሮማውያን ጦር ተከባ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡
ሉቃ 21÷ 20 "ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።"
የጥፋት ርኩሰቱ ገና ሲጀምር በይሁዳ ያሉ ፈጥነው ከዚያ እንዲወጡ የሚያሰጠነቅቅ ቃል በማቴዎስ 24÷ 16 ላይ እናገኛለን፡፡
ማቴ 24÷ 16 "በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥"
በ68 ዓ.ም በጦርነቱ መሃል ኔሮ በቤተ መንግስቱ ውስጥ ራሱን ካጠፋ በኋላ፣ ኢየሩሳሌምን ለመሰባበር ዘምቶ የነበረው የሮማውያን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል ቨስፓሲያን ወደ ሮም በመመለስ አዲሱ ተተኪ ንጉሰ ነገስት ለመሆን ውጊያ አደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ክርስቲያኖች በማቴዎስ 24÷ 16 ያለውን ማስጠንቀቂያ ስላስተዋሉ ኢየሩሳሌምን ለቀው ወጡ፤ አይሁድ ግን በተቃራኒው የቨስፓሲያንን እና የጦሩን ወደ ሮም መመለስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነላቸው የድል መንሳት ምልክት አድርገው ስለ ወሰዱት በኢየሩሳሌም ከቀድሞው ይልቅ በብዙ ቁጥር በመሰባሰብ አመጹን ቀጠሉበት፡፡ ሮማውያንም ተመልሰው መጥተው ከተማይቱን ፈጽመው አወደሟት፡፡
♦ ማቴዎስ 24÷ 21 ስለ ታላቁ መከራ ይናገራል፡፡
ማቴ 24÷ 21 "በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።"
እንደ ቨስፓስያን ዘገባ፣ ሮማውያኑ ያንን ከአይሁድ ጋር የገጠሙትን ጦርነት ቀጥለው ባሉበት ጊዜ እጅግ ጨካኞች በመሆን የሚያደርጉትን ሁሉ በከፋ በቀል ያደረጉ ነበር፡፡ ብዙ ደም መፍሰስ በምድሪቱ ሁሉ ሲሆን ቤቶች በእሳት ይጋዩ ነበር፡፡ በይሁዳ አውራጃዎችና በቅድስት ከተማ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ሕዝቡም ሁሉ የሚበሉት ስላልነበራቸው ምግብ ለማግኘት ሲሉ እርስ በእርሳቸው በግልጽና በከፋ ጭካኔ ይተራረዱ ነበር፣ እናቶችም የገዛ ልጆቻቸውን ቀቅለው ይበሉ ነበር፡፡ ስለዚህ መከራ ምን ተብሎ እንደተነገረ ልብ በሉ፣ "ምንም የሚስተካከለው የለም" ነው የተባው፡፡ የኢየሩሳሌም ውድመት ማለት በመለኮታዊው ፕሮግራም ውስጥ የሚሰጠው ትርጉም ከአንዲት የአይሁድ ከተማ አወዳደቅ በላይ ከፍ ያለ ነው፣ ይህ ውድመት ማለት የአሮጌው ኪዳን እስራኤል ውድመትና ፍጻሜ ማለት ነው፡፡
♦ ማቴዎስ 24÷ 28 ስለ አሞሮች መሰበሰብ ይናገራል።
ማቴ 24÷ 28 "በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ።"
አሞራ የሮማውያን ምልክት ነው፡፡ በሌላ አባባል ሮማውያን መሰብሰብ በሚጀምሩበት ጊዜ ያኔ እስራኤል የሚዘነጣጠል በድን ሆኖአል ማለት ነው፡፡
♦ ማቴዎስ24÷ 29 ስለ ከዋከበት መውደቅ እና ስለ ጨለማ ሰማይ ይናገራል፡፡
ማቴ 24÷29 "ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥"
ይህ በጣም የተለመደ እና ከብሉይ ኪዳን የተወሰደ አቡቀለምሲሳዊ ቃል እና ንግግር ነው፡፡ ከዋከብት የሚወክሉት የመንግስት አስተዳደርና አገዛዝን ነው፡፡ እስራኤል በቃ ወደቀች ማለት ነ ው፡፡
♦ ማቴዎስ 24÷ 30 የኢየሩሳሌም መፈራረስ ኢየሱስ እንደ ተመለሰና ከቅዱሳኑ ጋር በመንግስቱ እንደሚገዛ ምልክት መሆኑን ይነግረናል፡፡
ማቴ 24÷ 30 "የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤"
♦ ማቴዎስ 24÷ 31 ብዙዎች መነጠቅ ብለው የሚጠሩትን ጉዳይ ያመለክታል፤
ማቴ 24÷ 31 "መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።"
ይህንን ጥቅስ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4÷ 15-17 ካለው ጋር ብታነጻጽሩት ያው አንዱን ኹነት እንደሚናገሩ ታያላችሁ፡፡ ይህም የተመረጡት በእግዚአብሔር መንግስት ስለ መሰብሰባቸው የተነገረ ነው፡፡
♦ በማቴዎስ 24÷ 32-34 ኢየሱስ ሲናገር እነዚህ ነገሮች በሙሉ የሚፈጸሙት እርሱ "ይህ ትውልድ" ብሎ በሚጠራው እና እርሱ ሲናገር ቆመው ይሰሙ በነበሩ ሰዎች ዘመን እንደሆነ እናያለን፡፡
ማቴ 24÷ 32-34 "ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።"
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ይህንን ቃል "ይህ ትውልድ አያልፍም" ብሎ ከማንበብና ከመተርጎም ይልቅ "ይህ ዘር አያልፍም" እያሉ ለመተርጎም ሲሞክሩ ይታያሉ፣ በቋንቋ አገባቡ ያየነው እንደሆነ እንኳ ይሄ ትርጉም የሚሰጥ አይሆንም፡፡ ቤተ መቅደሱ የፈራረሰው ከደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ በኋላ በአርባ አመታት ውስጥ ነው። ይኸውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የአንድ ትውልድ ጊዜ ነው። "ይህ ሁሉ" የተባለውን ልብ በሉ፣ የሚፈጸመው በዚያ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ነው፡ -ንጥቀቱ 24÷ 31 ፤ የሰማይና የምድር እልፈት 24÷ 34፤ እንዲሁም የጌታ ዳግመኛ ምጽዓት 24÷ 44፤ ይህ ሁሉ ያኔ እንደሚፈጸም የተነገረ ነው፡፡
የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ትኩረቱ በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዓት ወቅት የሚሆነው የኢየሩሳሌም ውድመት ነው፡፡ (በማቴዎስ 24 ላይ ሰፋ ላለ ግንዛቤ "የጌታ ዳግም ምጽአት፣ መቼ እና እንዴት" በሚል ያቀረብሁትን የቪድዮና የጽሁፍ መልዕክት በብሎገሬና በዩትዩብ ቻናሌ ላይ እንዲጎበኙ አበረታታለሁ)።
እንግዲህ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍም ቢሆን በቀላሉ በዚሁ የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ላይ ዘርዘር ባለ መልኩ ተስፋፍቶ የተነገረ ትንቢት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የዮሐንስ ራዕይ ትኩረት የእስራኤል ጥፋት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ያ የእርስዋ ጥፋትና ውድመት አንዳች ትኩረትን የሚስብ ነገር አለው፡፡ እርስዋ የተቀጣችው ስለ ግልሙትናዋ እና ስለ ዝሙትዋ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እስራኤል የያሕዌ አምላክ ሚስቱ እንደ ሆነች ትቆጠር ነበር፡፡
ኤር 31÷ 31 "እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር "ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥" ይልና (ይህ ጥቅስ በእንግሊዝኛው NKJV ትርጉም 'እኔም ለእነርሱ ባል ነበርሁ' ይላል እግዚአብሔር)" በሚል የተቀመጠ ነው፡፡
ነብያት አዘውትረው በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካል የነበረውን ቃል ኪዳናዊ ሕብረት ይጠቅሱ ነበር፡፡ እስራኤል ግን የባዕዳንን አማልክት ተከትላ ትነጉድ ነበር፣ በተደጋጋሚም ስለ መንፈሳዊ ግልሙትናዋ ትከሰስ ነበር፡፡ በመጨረሻም እስራኤል "ከቄሳር በቀር ንጉስ የለንም… ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን" ብላ እየጮኸች የእግዚአብሔርን ልጅ አዋርዳና ሰቅላ ገደለችው፡፡
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ እስራኤል ያልታመነች ሚስቱ በመሆንዋ ስለ መንፈሳዊ ግልሙትናዋ የሚገባትን ፍርድ፣ የእግዚአብሔርን የፍቺ ጽሑፍና ንጉሳዊ አዋጅ የሚወክል መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ የፍቺና የጦርነትን መልእክት የያዘ ነው። በሚቀጥለው ጥናት ይህንን ሃሳብ ዘርዘር አድርገን እንመለከታለን።
∆∆∆∆∆∆∆∆∆
No comments:
Post a Comment