Tuesday, November 6, 2018

የኃጢአት ይቅርታ ወንጌል

የኃጢአት ይቅርታ ወንጌል
የሰው ልጆች የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፍ የሚጠየቁ ናቸው፤ የእግዚአብሔርን ሕግ አልታዘዙም። በኃጢአት የተበከለው ሰብአዊ ባህርያቸው፣ አሳባቸው፣ ቃላቸው፣ እና ተግባራቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ በመዋጋትና በመቃወም የተሰለፈ፣ በሁለንተናቸው ለእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነው የቆሙ ናቸው።
ከዚህ የተነሳ ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ቁጣ በታች የወደቁና፣ ሞት የሚገባቸው፣ ሁሉም አይነት ጊዜአዊና ዘላቂ የሥጋና የነፍስ ስቃይ የሚገባቸው፣ በገሃነምም እሳት ፍርድ ሊቀጡ የሚገባቸው ሆነዋል። ራሳቸውንም ከዚህ ፍርድ ማዳን የማይችሉ፣ ማንምም ሊረዳቸው የማይችል ምስኪኖች ናቸው።
ከዚህ በተቃራኒው ያለው ግን በወንጌል የቀረበው የነጻ ጸጋ ምስራች፣ ለነዚህ ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች እግዚአብሔር ብቻ የሚሰጠውና በቀላል እምነት ከእግዚአብሔር ብቻ የሚቀበሉት የኃጢአት ሥርየት ነው። ይኸውም ጌታችን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወድና አንድ ልጅ የሕጉን እርግማን በራሱ ላይ በማድረግና ኃጢአታችንንና መዘዙን ሁሉ በመሸከም ስላስተሰረየልንና የኃጢአታችንን እዳ በመክፈል ጽድቅን ሁሉ የፈጸመልን በመሆኑ ነው።
በእርሱ በኩል ብቻ ወደ እግዚእብሔር በንስሃና በይቅርታ መመለስ የሚቻል ሆኖአል። በእርሱ በኩል ብቻ በእምነት የኃጢአትን ይቅርታ መቀበልና፣ ከሞትና ከሁሉም አይነት የኃጢአት ቅጣት ተጠብቆ ለዘላለም መዳን የሚቻል ሆኖአል።
ይህ ነው የምስራች፣ ወንጌሉም ይህ ነው፤ መጽናናት የሞላበት ደስ የሚል የደስታ ዜና ይህ ነው። አሁን ታርቀናል፣ ሰላምም ወርዶአል፣ አሁን የእግዚአብሔር ጠላቶች አይደለንም። አሁን እግዚአብሔር ተቀብሎናል፣ ሰለ ውድ ልጁ ሲል ምህረትን አድርጎልናል፣ ፈጽሞም አይቀስፈንም።

No comments:

Post a Comment