ጳውሎስ የሰበከው ሙሴና ነብያት ያስተማሩትን ነው፦
ሐዋ 26፥ 6-8 "አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ። ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከአይሁድ እከሰሳለሁ። እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደ ሆነ ስለ ምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቈጠራል?"
በእውነት እግዚአብሔር ብቻ ሙታንን ተከማችተው ካንቀላፉበት ከሲኦል ለማስነስትና በእርሱ የተቀደሰ ህልዎት ፊት የሚበልጠውን የሕይወት ትንሳኤ ሰጥቶ ለዘላለም ለማኖር ይችላል። ጳውሎስም ትንሳኤን የሰበከው የእስራኤል ተስፋ እንደሆነ እያመነና እየተረዳ፣ ተስፋውም ሊፈጸም መቅረቡን እየተጠባበቀ ነው።
ሐዋ 24፥ 14-15 "ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።"
የትንሳኤ ተስፋ ተሰጥቶ የነበረው ለአሮጌው ኪዳን እስራኤላውያን ነበር። ሰለዚህ የትንሳኤ ተስፋ የብሉይ ኪዳን ተስፋ ነበር፣ እንጂ ብሉይ ኪዳን የማያውቀውና በአዲስ ኪዳን የተሰጠ አንድ አዲስና እንግዳ ነገር አልነበረም። ትንሳኤ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ አዲስና እንግዳ ተስፋ አልነበረም።
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ የሙታን ትንሳኤ የሚፈጸመው በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው፤ ተስፋውም ለእስራኤል የተሰጠ እስከሆነ ድረስ፣ መፈጸም ያለበት በእስራኤል ዘመን መጨረሻ ላይ ነው እንጂ በሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ ላይ አይደለም። ምክንያቱም የታሪክ መጨረሻ ወይም የሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ እና የጊዜ ማብቂያ የተሰኘው ጽንሰ ሃሳብ የሰው ልብ ወለድ ትምህርት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ገጹ ላይ የማያውቀው ርእሰ ጉዳይ ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳዊው አስተምህሮተ ነገረ ፍጻሜ የ70 አ.ም ነገረ ፍጻሜ ሲሆን፣ እርሱም የእስራኤል ነገረ ፍጻሜ ነው እንጂ የዚህ ግዑዝ አለም፣ የሰማይና የምድር ፍጻሜ አይደለም። ለእስራኤል የተሰጠው የነገረ ፍጻሜ ተስፋ የሚፈጸመው ደግሞ በእስራኤል ዘመን መጨረሻ ከሆነ ይህም መጨረሻ ነብያቱ፣ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ እንዳስተማሩት ቤተመቅደሱ የወደመበት የ70ው አ.ም የእስራኤል ፍርድ የተፈጸመበት መጨረሻ ነው። ስለሆነም የሙታን ትንሳኤ የሆነው፣ መሆንን የሚገባው ያኔ ነው። በአስተምህሮተ ነገረ ፍጻሜ የዘመኑን ፍጻሜ፣ የጌታን ዳግም ምጽአት፣ ትንሳኤንና የፍርድን የምናየው በዚያው በእስራኤል ዘመን ማብቂያ ውስጥ ነው። ከእስራኤል ዘመን ፍጻሜ ተነጥሎ የሚሰጥ ማንኛውም የነገረ ፍጻሜ ትንታኔ በቅዱስ ቃሉ ሚዛን ሊረጋገጥ የማይችል ሽብርና ቅዠት ነው።
ጳውሎስ ስለ ሙታንም ትንሣኤ አስተምህሮቱ ምን እንደሚል ተመልከቱ፦
ሐዋ 26፥ 22-23 "ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።"
ጳውሎስ እዚህ ላይ እያለ ያለው፣ እርሱ የሚያስተምረው ነብያቱና ሙሴ ካስተማሩት በቀር ሌላ እንዳልሆነ ነው። ሰለዚህ የጳውሎስ ትምህርት ስለ ሥጋ ትንሣኤ ቢሆን ኖሮ የሥጋ ትንሣኤን ጽንሰ አሳብ በብሉይ ኪዳን ገጾች ውስጥ ማግኘት በሆነልን ነበር። ይልቁንም እኛ ደግሞ የሌለውን የሥጋ ትንሳኤ ትምህርት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ማግኘት የማይቻለን ከሆነ ጳውሎስም ደግሞ እንደ ሐዋርያነቱ እና የሕጉ ሊቅ እንደ መሆኑ የሥጋ ትንሣኤን ያስተምራል ብለን መጠበቅ አያስፈልገንም።
በኢሳይያስ ምእራፍ 24 እግዚአብሔር ስለ ሰማይና ምድር ወይም በሰማይና በምድር የተወከሉ ኃይላት የሚጠፉ ስለመሆናቸው አቡቀለምሲሳዊ በሆነ የቋንቋ ዘይቤ ከተናገረ በኋላ ቀጥሎ በምዕራፍ 25 ላይ ሞትን በተመለከተ ምን እንደሚል ስሙ:-
ኢሳ 25፥ 8 "ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።"
ቃሉ የሚለው እግዚአብሔር ሞትን ያጠፋዋል ነው። ሞት ምንድን ነው? አካላዊ ተዳሳሽ ነው ወይስ መንፈሳዊ? በምእራፍ 24 ላይ ሲናገር ሞት የመጣው እነርሱ ቃል ኪዳንን ስላፈረሱ ነው ይላል፣ ይኸውም የሞትን መሰረታዊ ተፈጥሮ ግልጽ ያደርጋል:-
ኢሳ 24፥ 5 "ምድርም ከሚቀመጡባት በታች ረክሳለች፥ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፥ የዘላለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና።"
እዚህ ላይ ይዋጣል የተባለው መንፈሳዊው ሞት እንጂ ባዮሎጂካሉ ሞት አይደለም። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን አንዳች አስገራሚ ነገር ደግሞ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ምእራፍ 15 ላይ ለሰጠው የአስተምህሮተ የሙታን ትንሣኤ ምንጭና መሰረት ኢሳይያስ 24 እና 25 መሆኑን ነው። ጳውሎስም የሚያስተምረው የሙታን ትንሣኤ "ሙሴና ነብያት ያስተማሩትን" የመንፈሳዊ ትንሣኤ ትምህርት እንጂ አካላዊ የሆነ የሥጋ ትንሣኤ አይደለም።
እንደገና ወደ ሌላ የመጀመርያው ኪዳን መጽሐፍ ልመልሳችሁና በትንቢተ ሕዝቅኤል ምእራፍ 37 ላይ ስለ ትንሳኤ የተጻፈውን እንመልከት። የዚህ አውደ ምንባብ ታሪካዊ ዳራ የእስራኤል ልጆች ወደ ባቢሎን ምርኮኛና ግዞተኛ ሆነው የመወሰዳቸው ጉዳይ ነው፤ ባቢሎናውያን በይሁዳ (ደቡብ) በሚኖሩት ላይ የፈጸሙት ምርኮ ደግሞ ቀደም ሲል አሶራውያን በእስራኤል (ሰሜን) ላይ የፈጸሙትን ምርኮ ተከትሎና ተክቶ የመጣ ነው። ባቢሎናውያንም ልእለ ኃያል ሆነው አሶራውያንን ፈጽሞ አጥፍተዋቸው ነበር። ስለዚህም አሁን በአሶር የነበሩ ምርኮኞች ሁሉ ተግዘው ወደ ባቢሎንተወስደው ነበር።
ሕዝ 37፥1-10 "የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ። በእነርሱም አንጻር በዙሪያቸው አሳለፈኝ፤ እነሆም፥ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፥ እነሆም፥ እጅግ ደርቀው ነበር። እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን? አለኝ። እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ። ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ስናገርም ድምፅ ሆነ፥ እነሆም፥ መናወጥ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ። እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም። እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል አለኝ። እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።"
የደረቁ አጥንቶች ሞትን የሚያሳዩ ናቸው - ነገር ግን እንዲነሱና በሕይወት እንዲኖሩ ተደርገዋል። ትንሣኤ እንግዲህ ይህ ነው።
ሕዝ 37፥ 10-12 "እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች የእስራኤል ቤት ሁሉ ናቸው፤ እነሆ፦ አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል ፈጽመንም ተቈርጠናል ብለዋል። ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ፥ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ።"
እግዚአብሔር የሚናገረው ለእስራኤል ዘሥጋ ነው፣ እነርሱም አጥንቶቻቸው እንደደረቁና ተስፋችውም ሁሉ ተሟጦ እንዳለቀ የናገራሉ። ልብ አድርጉ፣ በስጋ ሞተው እንደነበሩ እየተናገሩ አልነበረም። ከእግዚአብሔር ግን ተለይተው ነበሩ፤ ከምድሪቱም ወጭ ርቀው ተበትነው ነበሩ። እንደ አይሁድ መምህራን ጽሁፎች ከሆነ እስራኤል በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ከምድራቸው ወጭ ለመሆን ተገደው በባዕድ ምድር ከባእዳን በታች ካደሩ ያኔ ሞተዋል፣ አብቅቶላቸዋል ማለት ነው። ለአይሁድ ከምድሪቱ ተነጥሎ ሕይወት አይታሰብም። ሕይወት ያለው እግዚአብሔር በሚያድርበት በምድሪቱ ነው።
እዚህ ላይ ግን እግዚአብሔር እያላቸው ያለው መቃብራችሁን እከፍታለሁ ነው፣ ይህ ደግሞ የፈረሰ በድን የተኛበት ተዳሳሹ መቃብር አይደለም ምክንያቱም ያኔ ገና በሥጋ አልሞቱም ነበርና።
ሕዝ 37፥ 13-14 "ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡"
እግዚአብሔር መንፈሱን በእስራኤል ያገባባቸውና ህያዋን ያደረጋቸው መቼ ነው? መንፈሱን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ባፈሰሰበት በበአለ ሃምሳ ቀን ነው!
ሕዝ 37፥ 23 "ከዚያ ወዲያም በጣዖቶቻቸውና በርኵሰታቸው በመተላለፋቸውም ሁሉ አይረክሱም፥ ኃጢአትም ከሠሩባት ዓመፅ ሁሉ አድናቸዋለሁ አነጻቸውማለሁ፤ ሕዝብም ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።"
እግዚአብሔር ያጠራቸውና ሕዝቡ ያደርጋቸዋል። ይህም የአዲሱን ኪዳን ድምጸት ይዞአል። መንፈሳዊው ሕይወትም ደግሞ ይህ ነው።
ሕዝ 37፥ 26-27 "የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘላለምም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ እኔም እባርካቸዋለሁ አበዛቸውማለሁ መቅደሴንም ለዘላለም በመካከላቸው አኖራለሁ። ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።"
ራእይ 21 ላይ ያለውን ልብ በሉ፦
ራእይ 21፥3 "ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤"
እግዚአብሔር ለእስራኤል በቃል ኪዳኑ ውስጥ ያለውን ህልዎቱን ይኸውም የትንሣኤን ሕይወት ተስፋ ይሰጣታል።
ሰለዚህ በሐዋርያት ሥራ 24፥15 ላይ "ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው" ሲል ጳውሎስ የሚናገርለት ይህ "ሊሆን ያለው" (about to happen) የተሰኘው ትንሣኤ እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን ሕዝብ እንደገና በመንፈስ የሚሰበስብ መሆኑን የሚገልጥ ነው። በአሮጌው ኪዳን መጨረሻ በ70 አ.ም ላይ የሆነው የሙታን ትንሣኤ፣ በሰማያዊው መንግስቱ ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅና በአንድነት ለመሆን በሲኦል ሆነው ለዘመናት ሲጠባበቁ የነበሩ ነፍሳት መፈታትና መለቀቅ ነው እንጂ፣ በመቃብር ውስጥ የበሰበሱና የፈራረሱ በድን ሙታኖች ባዮሎጂካል የሆነ ተዳሳሽ አካላዊ ትንሣኤ አይደለም። እነርሱም። ከእንግዲህ በኋላ ከእግዚአብሔር የተለዩና የተነጠሉ (ሙታን) አይሆኑም፣ ይልቁንም አሁን በህልዎቱ ውስጥ (ህያዋን) ናቸው።
ከ70 አ.ም ጀምሮ ወደዚህ ባሉ ዘመናት ውስጥ ለምንኖር አማኞች ከሙታን የተነሣነው እምነታችንን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባደረግንበት በቅድስት ጥምቀታችን ቅጽበት ነው። ያኔ ኢየሱስ በመንፈስ ሙታን ሆነን ከነበርንበት ሁኔታ አውጥቶ መንፈሳዊ ሕይወትን ሰጥቶናል። አሁን የዘላለም ህይወት ተሰጥቶናል፣ ለዘላለምም በህልዎቱ ውስጥ በሕይወት እንኖራለን እንጂ ፈጽሞ በመንፈስ ልንሞት አይቻለንም። ሰለዚህ "የሚበልጠውን ትንሣኤ" ስለተቀበልን ሌላ ትንሣኤ አያስፈልገንም። በምንሞትበት ጊዜ ይህ ሥጋችን ወደ አፈር ይመለሳል፣ እኛም በቅጽበት ወደ ሰማይ እንሄዳለን። ከእንግዲህ ወዲያ ገና የሚጠበቅና ሳይፈጸም የቀረ ምንም ነገር ስለሌለ ከ70 አ.ም በፊት በአሮጌው ኪዳን ውስጥ እንደነበሩ ሟች ቅዱሳን ወደ ሲኦል ሄዶ መከማቸትም ሆነ ማንቀላፋት አያስፈልገንም። የኃጢአታችንን ዕዳ ሊከፍል የሞተልንና፣ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለኃጢአት ይታይላቸው ዘንድ የተገለጠው ኢየሱስ ትንሣኤያችን ነው። እንደ ወንጌል አማኝ ክርስቲያን ይህንን ማመን አለመቻል ሲያስገርመኝ ይኖራል።
ዮሐ 11፥ 25-26 "ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።"
እዚህ ላይ ኢየሱስ የሚናገረው:-
¶ "የሚያምንብኝ (በስጋው) ቢሞት እንኳ (በመንፈስ) ሕያው ይሆናል ፣
¶ "ሕያው የሆነም (ማለትም ገና በስጋው ያልሞተ) የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም (ማለትም በመንፈስ ሕያው ሆኖ ይኖራል)" እያለ ነው።
እዚህ ላይ በሁለት የተከፈሉ አማኞችን እናያለን፦ በአንድ በኩል፣ ከትንሳኤ በፊት አምነው የሞቱ ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ አምነው ከትንሳኤ በፊት ያልሞቱ ናቸው። ከአሮጌው ኪዳን በታች ሆነው ከትንሳኤ በፊት አምነው በስጋ ለሞቱ (በትንሣኤ ተስፋ ለሞቱ) እርሱ ትንሳኤያቸው ነበር፣ ነገር ግን በአዲሱ ኪዳን ውስጥ ከትንሳኤ በኋላ ላለን በጌታ ታምነን ለምንኖርና ገና ወደፊት በሥጋ ለምንሞት እርሱ ሕይወታችን ነው። እኛ ያመንን በሥጋ መሞትን የምንገናኘው በመዋቲነት ሳይሆን በሕያውነት ነው። ትንሳኤና ሕይወት አንድ ነው፣ እርሱም ኢየሱስ።
አዲሱ ኪዳን የሕይወት ኪዳን ነው እንጂ የሞት ቀጠና አይደለም። ሃሌሉያ! ክብር ሁሉ ለትንሣኤው ጌታ ይሁን። አሜን!! ከክርስቶስ የተነሳ ከጸጋው ኪዳን በታች ስንኖር በሕያው እግዚአብሔር ፊት ዘላለማዊ ሕያውነት እንጂ በዚያ ሞት የለም፣ መንፈሳዊ ሞት የለም፦
1ቆሮ 15፥ 54-57 "ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።"
ትንሳኤ ያስፈለገው ሞት የሚባል ጠላት ስለነበረ ነው፣ ይህም ሞት "ይሻራል" የተባለው የኋለኛው ጠላት ነው። ሞት የሚሻርበትን ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ "የኋለኛው ዘመን" ሲል ይጠራዋል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው "የኋለኛው ዘመን" ማለፉን ለመረዳት ሊቅ መሆን አይጠይቅም። ሞት ያበቃለት ያኔ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቀውን "የመጨረሻ ዘመን" የሚባል ትምህርት በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ አምጥተን ስንሰነቅር መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቀው እንግዳ የሆነ "የሥጋ ትንሣኤ" አስተምህሮ ይወለዳል። ስለዚህም በቃሉ ድጋፍ የማይገኝለትን "በሥጋ ትንሣኤ አምናለሁ" የሚል ያለ እውቀት የሆነ ምስክርነት ስንሰጥ ኖረናል።
አሁን ግን በዚህ የመንግስት ዘመን ሞት በሌለበት ሁኔታ ትንሳኤ አያስፈልግም። አሁን ሞት በሕይወት ተውጧል፣ የለም። ሞት ራሱ ሞቷል! እኛም በክርስቶስ የዘላለምን ሕይወት ስለተቀበልን በመንፈስ መሞት አይቻለንም። የሙታን ትንሣኤ ተስፋ ተፈጽሞ አልፎአል፣ አሁን ያለው ሕይወትና ሕያውነት ነው። ሕያው ከሆነው ከክርስቶስ የተነሳ በሕያው እግዚአብሔር ፊት በሕያው እምነት ለዘላለም ሕያዋን ሆነን እየኖርን ስለሆነ በአዲሱ የጸጋ ኪዳን ሞት የለም። ሰለዚህ ትንሳኤ አያስፈልገንም። ትንሣኤ አስፈላጊነቱ ሞት ይሰለጥንበት በነበረው በአሮጌው የሞት አገልግሎት በታች የቤዛነታቸውን ቀን እየናፈቁ በመቃተትና በምጥ ለነበሩ የቀደመው ኪዳን ቅዱሳን ነው። እኛ ይህንን ግን በሥጋ ስንሞት ክርስቶስን በማመን የጀመርነውን ይህንን የማያልፍ ሕይወት ኑሮ ለመቀጠል ከዚህ ቁርበት ተለይተን ወዲያውኑ ወደ ሰማይ እንሄዳለን።
የሙታን ትንሳኤ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ሲጠብቁት የኖሩትና በመጨረሻም ከጌታ ጋር ለመሆን ሞትን ድል በመንሳት ከሲኦል ነጻ የወጡበት የአንድ ጊዜ ሁኔታና ክስተት ነው። አሁን ግን እኛ የቅዱሳን ትንሣኤ ከተፈጸመ በኋላ በብዙ የዘመን ርቀት የምንኖርና በክርስቶስ ያመንን፣ የማይሞተውን ክርስቶስን ለብሰናል። በሥጋ ስንሞትና ይህ አሮጌ ቁርበት ሲወልቅ ክርስቶስን ለብሰናልና በእግዚአብሔር ፊት ራቁታችንን አንሆንም። ካመንበት ቅጽበት ጀምሮ ለዘላለም በእግዚአብሔር ሕልዎት ውስጥ በሕይወት እንኖራለን። የምድር ላይ ቆይታችንን ጨርሰን በማንኛውም ምክንያት በሥጋ ስንሞት ግን ያኔ ይህንን ሥጋ አውልቀን ጥለን የምንኖረው በአዲሱ መንፈሳዊ አካል በመንፈሳዊው አለም (realm) ብቻ ነው። ክርስቲያን በሥጋው የሚሞተው መጽናናት በሞላበት ደስታ ነው። መጽናናት በሞላበት እንዲህ ባለ የእግዚአብሔር ሕይወት ውስጥ የመኖር ሚስጥር ከቀለለብንና የክርስትናን ሕይወት ወደ ምድር ዝቅታ አውርደን ትንሳኤን ቃሉ በማይመሰክርለት ሰፈር ያለ አድራሻው የምንፈልገውና የምንጠባበቀው ከሆነ ግን ገና ከወንጌሉ ጋር አልተግባባንም ማለት ነው።
ስለዚህ ወደፊት ይሆናል ብለን ልንጠባበቀው የሚያስፈልገን የተዳሳሹ ሥጋ ባዮሎጂካል ትንሳኤ ሊኖረን የማይችል እስከሆነ ድረስ የሌለ ነገር ማመንም ሆነ ማስተማር አይገባንም። ለእኛ በእምነት ለጸደቅን ሰዎች ታዲያ በሥጋ ከሞትን በኋላ ምን ይቆየን ይሆን? በውኑ አንዳንዶች እንደሚሉት ፕሪቴሪዝም ተስፋ ገዳይ አስተምህሮ ነውን? ከቶ አይደለም። በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረውን የመጽናናት ቃል ስሙኝና ላብቃ፦
"ከሰማይም፦ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ፦ አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።" (ራእይ 14፥ 13)
እኔ ይህንን የተጻፈ ድምጽ ዛሬም እሰማዋለሁ። እናንተስ አይሰማችሁም? "ከእንግዲህ ወዲህ" ከተባለበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን፣ ደግሞም ለአለምና ለዘላለም በጌታ ሆኖ መሞት ብፅዕና፣ እረፍትና ብድራት ያለበት ከሚታየው ወደማይታየው የሚደረግ ሽግግር ነው።
ግዛቸው ነኝ
<><><>
No comments:
Post a Comment