Monday, November 5, 2018

የጌታ ምጽአት መቼ እና እንዴት ክፍል ስድስት

የጌታ ምጽዓት መቼ እና እንዴት ነው?
በማቴዎስ 24 እንደተገለጸ

♦ ማቴዎስ 24÷ 29 ስለ ከዋከበት መውደቅ እና ስለ ጨለማ ሰማይ ይናገራል፡፡
ማቴ 24÷29 "ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥  ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥"
በብሉይ ኪዳን በስፋት ጥቅም ላይ ለዋለው አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ አጠቃቀም እንግዳ ከሆናችሁ፣ ክርስቶስ እዚህ ላይ የሚናገረውን ፈጽሞ መረዳት አትችሉም። ይህ አይነቱ የቋንቋ ዘይቤ መሰረቱን በብሉይ ኪዳን ያደረገና በነብያት ዘንድ በእጅጉ የተለመደ አነጋገር ነው።  ታላላቅ የሆኑ አስፈሪ ነገሮች በምድር ላይ እንደሚመጡ በሚያሳይ ትእይንታዊና ትዕምርታዊ በሆነ አቡቀለምሲሳዊ ቋንቋ የተነገሩት ከባባድ የነውጥ ክስተቶችንና ፍርድን ወይም መዓትን ሲያመለክቱ፣ የሚወክሉትም በሰማይ (hevenly realm) የሚሆነውን ክስተትና ለውጥ ነው። ስለዚህም ይህ ቋንቋ በቁሙ (literally) የሚወሰድና የሚተረጎም አይደለም።

ከሁሉ በፊት ኹነቱ የሚፈጸምበትን ጊዜ ልብ በሉ፣ ጥቅሱ "መቼ?" ለሚለው ጥያቄአችን የማያሻማ መልስን ይዞአል። ይህ አስፈሪ የኮስሞሎጂካል ቀውስ ክስተት ታላቁን መከራ ተከትሎ የሚፈጸም ኹነት ነው። ብዙዎች እንደሚመስላቸው ፊት ለፊት ባለው ትርጉም ቃል በቃል የሚፈጸም ኮስሞሎጂካል ቀውስ ቢሆን እንኳ ከጊዜ አንጻር ጉዳዩ መፈጸም ያለበት "ከዚያች ወራት መከራ በኋላ ወዲያው" ነው እንጂ ገና ቆይቶ ከሺህዎች አመታት በኋላ አይደለም። ያ መከራ ደግሞ ከቤተ መቅደሱ መፈራረስና ከኢየሩሳሌም ከተማ መቃጠል ጋር ተቆራኝቶ የተነገረው የእስራኤል መከራ እንደሆነ ቀደም ሲል አይተናል።
ይህ አይነቱ የኮስሞሎጂካል ቀውስ አገላለጽ በአይሁድ ማህበረ ሰብ ውስጥ በጣም የተለመደ እና ከብሉይ ኪዳን የተወሰደ አቡቀለምሲሳዊ ቃል  እና ንግግር ነው፡፡ ጠቀሜታውም በጥቅሉ የመንግስታትን አወዳደቅ እና የምድር ላይ ኃያላን ፖለቲካዊና ኃይማኖታዊ የበላይነት በሌላ ኃያል ሲፈራርስ ያለውን ሁኔታ ለመግለጥ፣ ፍጥረትን እና የተፈጠሩበትን ትንግርት ለመግለጥ፣ የሰው ልጆች በእግዚአብሔር እና በእርስ በርሳቸው ላይ የሚፈጽሙትን ኃጢአት እና የሚመጣባቸውን ፍርድ ለመግለጥ፣ ነው።
ጸሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰማይ ሰራዊት በመባል ይታወቃሉ (ለምሳሌ ዘዳ 4፥ 19፣ ኢሳ 34፥ 4፣ ኤር 33፥ 22)፤ በአቡቀለምሲሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሁፎችም ውስጥ ያላቸው ጠቀሜታና ትርጉም ስፊ ነው። ለአሁኑ ግን ከያዝነው ርእሰ ጉዳይ ጋር ባለው ተዛምዶ መጠነኛውን ነገር ልንመለከት እንችላለን። ለምሳሌ፦
በዮሴፍ ታሪክና በህልሙ ውስጥ ጸሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የእስራኤልን አባቶችና ጠቅላላውን የእስራኤል ህዝብ ለማመልከት አገልግለዋል። ዮሴፍ በህልሙ ጸሐይና ጨረቃ አስራ አንድ ከዋክብትም በፊቱ ሲሰግዱ ነበር ያየው፣ "... እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፤ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።" (ዘፍ 37፥ 9)። አባቱ ያእቆብ የህልሙ ፍቺ ገብቶት ነበር፣ "ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ አባቱም ገሠጸው፥ እንዲህም አለው፦ ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን? ወንድሞቹም ቀኑበት አባቱ ግን ነገሩን ይጠብቀው ነበር።" (ቁጥር 10ና 11)።
ይኸው ጉዳይ በራእይ መጽሐፍ 12፥ 1 ላይ ሴቲቱን በተመለከተ መሲሁ የመጣበትን የእስራኤልን ህዝብ በሚያመለክትበት ሁኔታ በቀረበው ራእይ ላይ እንደገና ይታያል፤ እርስዋም "...ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት..." የተባለችው እስራኤል ናት።
በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ውስጥ የጸሐይ፣ የጨረቃና የከዋክብት ትርምስ በየዘመኑ በአለም ገነው በተነሱ ኃያላንና መንግስታት ላይ ሊመጣ ያለን ታላቅ ነውጥ ሊያመለክት የሚችል አቡቀለምሲሳዊ ራእይን የሚያሳይ ነው። የእነዚህ የሦስቱ ብርሃናት መቋረጥ ስእላዊ ገለጻ የቀረበባቸው ከብዙ ጥቂቶቹ ምሳሌ የሚሆኑ የንባብ ክፍሎች እነሆ፦
♠ በባቢሎን ላይ የተነገረ
ኢሳ 13፥ 10 "የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።"
♠ በግብጽና በንጉስዋ ፈርዖን ላይ የተነገረ
ሕዝ 32፥7 " ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፤ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም።"
♠ በጽዮን ላይ የተነገረ
ኢዩ 2፥ 10 "ምድሪቱም ከፊታቸው ትናወጣለች፥ ሰማያትም ይንቀጠቀጣሉ፤ ፀሐይና ጨረቃም ይጨልማሉ፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ይሰውራሉ።"
♠ በኢየሩሳሌምና በመቅደስዋ ላይ የተነገረ፦
ማቴ 24፥ 29፥ "ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥  ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥"
♠ በእስራኤል ላይ ስለሚመጣ ታላቅ የመከራ ወቅት የተነገረ፦
ራእ 8፥ 12 "አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት።" አንዲሁም፣ 
♠ ከዘመኑ ፍጻሜ ጋር የተቀጠረውን ጭንቀት በተመለከተ፦
ሉቃ 21፥ 25 "በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤"    
እነዚህ ጸሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋከብት ተብለው የተጠሩት ሰማያዊ አካላት የሚወክሉት ኃይማኖታዊውንና ፖለቲካዊውን  የመንግስት አስተዳደርና  አገዛዝን  ነው፡፡ ጸሐይ ጨለመች ማለት የእስራኤልን ውርደት፣ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም ማለት ከእስራኤል ምንም አይጠበቅም ማለት፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ ማለት እስራኤል ኃይማኖቷንና ፖለቲካዋን እስከወዲያኛው እስክታጣ ድረስ በቃ ትወድቃለች ማለት ነው፡፡ እስራኤል እስራኤል መሆንዋ ለዘላለም ያበቃላታል ማለት ነው።
♦ ማቴዎስ 24÷ 30 የኢየሩሳሌም መፈራረስ ኢየሱስ እንደ ተመለሰና ከቅዱሳኑ ጋር  በመንግስቱ እንደሚገዛ ምልክት  መሆኑን   ይነግረናል፡፡
ማቴ 24÷ 30 "የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም  የምድር ወገኖች  ሁሉ  ዋይ  ዋይ  ይላሉ፥  የሰው ልጅንም  በኃይልና   በብዙ  ክብር  በሰማይ  ደመና  ሲመጣ ያዩታል፤"
የዳግመኛ ምጽአቱን ተፈጥሮ ወይም ባህርይ አስመልክቶ  በአብዛኛው የሚቀርበው የተለመደው አመለካከት፣  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በገሃድ ተዳሳሽ በሆነ ምድራዊና አካላዊ ሆኖ ሁሉም ሰው ሊያየው  በሚችልበት ደረጃ ተመልሶ እንደሚመጣ የሚታሰበው አመለካከት ነው። በዚህ ዘመን ያሉ የሚበዙ ክርስቲያኖች ይህንን እምነት እንደያዙ ምንም ጥርጥር የለውም፣ ጥያቄው ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው እንደዚህ አይነቱን አመጣጥ ነው ወይ? የሚል ነው። እድሜ ጠገብ ልማዳዊ አመለካከት ካልሆነ በቀር ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዊ በሆነ ተዳሳሽ አካል ወደ ምድር ተመልሶ  እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛው ገጹ ላይ አያስተምርም። በርካቶች ሐዋርያት ሥራ 1፥ 11 ላይ ያለውን ቃል እየጠቀሱ መጽሐፍ ቅዱስ በተዳሳሽ ስጋ ስለሚሆን አካላዊ የጌታ ዳግመኛ ምጽአት ያስተምራል ሲሉ ይሞግታሉ። (ጉዳዩን ከምር ለማሰብ ለሚሹ በዚህ ክፍል ላይ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ማስነበቤን ልብ ይሏል)፣ ለአሁኑ ግን ክፍሉን በመጠኑ ቀረብ ብለን እንየው።
ሐዋ 1፥ 9-11 "ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።"
እርገቱ አካላዊና የሚታይ ነበር፣ ታዲያ መመለሱም እንደዚያው መሆን አለበትን? "እንዲሁ ይመጣል" ይላል። እንዲሁ የሚለው ቃል በእንግሊዝኛው ትርጉም "like manner" ሲሆን በግሪኩ "hon tropon." የሚል ሃረግ ነው። ይህ ሃረግ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያለውን አገባብና እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ በመመርመር በእያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ልክ የሆነ ተመሳሳይነትን የሚያመለክት እንዳልሆነ በግልጽ እንረዳለን። ለምሳሌ ይህ ሃረግ በሌላ የንባብ ክፍል ያለውን አገባብ ተመልከቱ፤
ሉቃስ 13፥ 34 " ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ፥ እናንተም አልወደዳችሁም።"
ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን ሊሰበስባት የፈለገው ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ውስጥ ሸሽጋ እንደምታቅፋቸው አይነት ልክ በዚሁ አይነት (hon tropon) መንገድ ነውን? እንደዚያ ነው ብዬ ፈጽሞ አላስብም። ይልቁንም አገላለጹ ምሳሌአዊና ዘይቤአዊ ነው እንጂ፣ ኢየሱስ እንደ ዶሮ ክንፋም ነው ማለት አይደለም። በሐዋ 1፥ 11 ላይ ያለው አጽንኦትም ልክ በደመና ተሰውሮ እንደሄደ ክርስቶስ በደመና የሚመጣ መሆኑን ማሳየት ነው፣ ስለዚህ በደመና ይመጣል ማለት ነው፣ እንጂ በገሃድ በአካል እየታየ ይመጣል ማለት አይደለም።
በብሉይ ኪዳን "ደመና" የተሰኘውን ጽንሰ ሓሳብ ባልተረዳንበት ሁኔታ ይህንን ጥቅሰ ልንተረጉም ስንነሳ መሳሳታችን አይቀርም። ኢየሱስ በደመና ተሰውሮ የሄደበትም ነገር ፍጥረታዊ የሆነው ነጭ ጥጥ መሳይ የደመና ክምር ነው እንደማንል ተስፋ አደርጋለሁ። ሉቃስ "ደመና ከአይናቸው ሰውራ ተቀበለችው" ብሎ ሲጽፍ በዚያ የነበሩት አይሁድ የሆኑ የአይን ምስክሮች የሚያውቁትና የሚገባቸው አንድ ነገር ወደ እግዚአብሔር መወሰዱን ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱን ሲገልጥ መገለጡን አዘውትሮ በደመና ያደርገው እንደነበር፣ ይኸውም የእርሱ ሀልዎት እንደሆነ ከቅዱሳት መጻህፍቶቻቸው ያስተውላሉ (ዘጸ 16÷ 10፤ 19÷ 9፤ 34÷ 5፤ ዘሌ 16÷ 2፤ ዘሁ 11÷ 25)።
በሚቀጥለው ዝግጅቴ በደመና ስለመምጣት በዝርዝር እሄድበታለሁ።
ኢየሱስ አካላዊ እና ሥጋዊ በሆነ መንገድ ተመልሶ እንደሚመጣ የሚያስተምር ግን አንድም የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባብ የለም። የብሉይ ኪዳንን የቋንቋ ዘይቤ በወጉ መረዳት አመጣጡ ተዳሳሽ አካላዊ እንደማይሆን ግንዛቤ ያስጨብጠናል። ማንንም ለቅዱስ ቃሉ ሥልጣን ሊገዛ የሚፈቅደውን ሰው የማቴዎስ 24 ጥናት በነገረ ፍጻሜ ምልከታው ላይ ስር ነቀል ለውጥ እንዲያደርግ ያደርገዋል። ምክንያቱም በጌታችን ዳግመኛ ምጽአት ላይ ከሚናገሩ የቅዱሳት መጻህፍት ምእራፎች መካከል አንዱና ዋነኛው የንባብ ክፍል ይህ ምእራፍ እንደሆነ አምናለሁ። ይህንን ምእራፍ በወጉ መረዳት ከቻልን የዳግመኛ ምጽአቱን ተፈጥሮ ለመረዳት እይታችንን ያስተካክልልናል።
በማቴዎስ 24 ከቁጥር 23-26 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ትእዛዝና ማስጠንቀቂያ ካስተዋላችሁ የኢየሱስ መምጣት እዚህና እዚያ የማይባል አካላዊና ተዳሳሽ እንዳልሆነ ትረዳላችሁ።አንድ ሰው ተነስቶ እነሆ ክርስቶስ እዚህ ጋር ወይም እዚያ ጋር ነው ቢል ማመን እንደማይገባቸው አስጠንቅቆ ይነግራቸዋል። አንዱም ተነስቶ ክርስቶስ በበረሃ ነው ወይም የለም በእልፍኝ ውስጥ ነው ቢል ማንንም ማመን የለባቸውም። ለምን? ከተባለ የእርሱ አመጣጥ ፈጽሞ አካላዊና ተዳሳሽ ባለመሆኑ ነው፤ ነገር ግን የሚመጣው በግልጽ እየታየ ነው።
እርሱ ሲመጣ እነርሱ እንዴት ነው ሊያዩት የሚችሉት? እርሱ ሲመጣ የሚታየው በኢየሩሳሌም ላይ በሚወርደው ፍርድ ነው።
♥ ቁጥር 27 ላይ እንደተባለው አመጣጡ እንደመብረቅ ብርሃን ነው። የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል ከራሱ የቅዱሳት መጻህፍት ቃል ጋር በማነጻጸር የመብረቅ ብርሃን የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚያመለክት እንደሆነ ማየት እንችላለን። ኢየሱስ ዳግመኛ ምጽአቱን ከመብረቅ ብልጭታ ጋር አነጻጽሮ ሲያቀርበው ሊያመልክተን የፈለገው ዳግመኛ ምጽአቱ በፍርዱ ውስጥ የሚታይ መሆኑን ነው።
♥ በቁጥር 28 ላይ ደግሞ አመጣጡ በበድን ላይ እንደሚሰበሰብ አሞራ ነው። ይህም አይነቱ የንግግር ዘይቤ በብሉይ ኪዳን ያለ የፍርድ አገላለጽን የያዘ ቋንቋ ነው። 
♥ በቁጥር 29 የእርሱ አመጣጥ የምድር ፍንዳታ ክስተትን ወይም የተፈጥሮ ቀውስን ይመስላል "ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥" ሲል ማቴ 24፥ 29 ይናገራል።
ኢየሱስ በቁጥር 21 ላይ ስለሚናገረው ጉዳይ አንድ ነገር ልበልና የዛሬውን ላብቃ፤ " በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና"
"እንግዲህም ከቶ የማይሆን" የሚለው ሃረግ ከታላቁ መከራ በኋላም ቢሆን ጊዜ የማያበቃ ይልቁንም የሚቀጥል እንደሆነ ያመለክታል። ታላቁ መከራ የሚመጣው በአለም መጨረሻ ላይ ገና ወደፊት ሳይሆን ይልቁንም ያኔ በ70 አ.ም ላይ የአሮጌው ኪዳን ዘመን ሲያበቃ አብሮ ያለፈ ታሪክ ነው።
♥ ከቁጥር 23-26 ያለው የሚነግረን ዳግመኛ ምጽአቱ ምን እንደማይመስል ነው። መመለሱ በተዳሳሹ አካል የሚሆን አይደለም።
ይህ ቁጥር 30 እና 31 ላይ ያለው ሃሳብ ግን አብሮ የሚሄደው ከቁጥር 27-29 ካለው ክፍል ጋር ነው። 
♥ ከቁጥር 27- 31 ያለው ዳግመኛ ምጽአቱ ምን እንደሚመስል ይነግረናል። ክፍ ሲል ለመግለጥ እንደሞከርኩት ዳግመኛ ምጽአቱ በፍርድ የሚገለጥ እንደሆነ አይተናል።
♦♦♦♦♦♦♦♦♦

No comments:

Post a Comment