የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ማርቆስ 13 ፥40
ሰይጣን የታሰረ ከሆነና በእሳት ባህር ውስጥ ከተጣለ ገና አሁንም ኃጢአትና ክፋት በዚህች ምድር ላይ የሚኖረው ለምንድን ነው? ሲሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ። ይህም ጥያቄአቸው ትንቢት ሁሉ ተፈጽሞአል ብለን አቋም ለያዝንና እንዲህ ለምናምን የማያፈናፍን አፋጣጭ ተግዳሮት እንደሚሆንብን ይመስላቸዋል። እውነታው ግን እርሱ አይደለም።
ለተዳሳሹና ለቁሳዊው በእጅጉ በተጋለጠውና "ሊተራሊስት" በሆነው በዘመናዊው ክርስትና ዘንድ በስፋት ታዋቂ የሆነው አስተሳሰብ ሰይጣን አንድ ጊዜ ከተፈረደበት፣ እንዱሁም ስለ ዓለም ፍፃሜ የሚናገሩ ትንቢቶች በሙሉ ፍጻሜአቸውን ካገኙ በኋላ፣ ታላቁና ቀንደኛው ፈታኝ የክፋት ኃይል ፈጽሞ የማይኖር በመሆኑ ምንም ዓይነት ክፋትና ኃጢአት በዓለም ላይ አይኖርም የሚል ነው። ይህ ነው የተለመደው አስተሳሰብና የብዙዎች እምነት።
ከባልንጀሮቼ አንዱ በአንድ ወቅት አብረን በተቀመጥንበት የካፌ በረንዳ ንፋስ ያስነሳው የመንገድ ላይ አቧራ ድንገት በላያችን ላይ ቢሞጀር የተበሳጨው ጓደኛዬ ወደ እኔ ዘወር ብሎ፣ "ትንቢት ሁሉ ተፈጽሞአል፣ ጌታም መጥቶአል፣ እኛ ክርስቲያኖችም አሁን ያለነው በአዲሱ ሰማይና ምድር ባዲሲቱ ኢየሩሳሌም ነው የምትለው ይሄ ትምህርትህ አሁን የምንጠጣውን ይህን አቧራ እንዴት ያየዋል?" ሲል እየቀለደ እንደጠየቀኝ አስታውሳለሁ። "የጌታ ምጽአት ንፋስ የሚያነሳውን የምድርን አቧራ እንደሚያስቀር ከቅዱስ ቃሉ ማንበቤን አላስታውስም፤ አልተጻፈማ"፤ ስል እኔም መልሼለታለሁ። በዚህ ተዳሳሽ አለም ክፋትና ክፉ ፍጻሜውን አግኝቶ ሁሉ መልካም ሆኖ ካላየን፣ እሳዳጅና ተሳዳጅ፣ ገዳይና ሟች፣ አጥፊና ጠፊ የሌለበት፣ የሰላም አለም ተቋቁሞ ካላየን አናምንም የሚሉኝ በማየት የሚያምኑ እጅግም ከማከብራቸው መካከል የዋሃን ሞልተዋል። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይቶ መንፈስ በሚናገረው ቃል ያንን መተርጎምና መረዳት የምንኖርበት መንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰጥ "መሰረተ ትምህርት" ነው። አለዚያ ዱባና ቅል ለየቅል ሆነን ሳንመረቅ እንቀራለን።
እንደ ፕሪንተሪስቶች ሁሉ የመጨረሻው ዘመን ትንቢቶች በሙሉ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ተፈፅመዋል ብዬ አምናለሁ፤ ነገር ግን አሁንም ድረስ ከአዲሱ ሰማይና ምድር በቀር፣ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ቅድስት ሆና ለባልዋ እንደተሸለመችም ሙሽራ ሆና ከወረደችው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በቀር፣ ከመንግስቱ በቀር ኃጢአት በዚህ ተዳሳሽ አለም በምድር ላይ አለ፤ ይኖራልም ብዬ ደግሞ አምናለሁ። "ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።" (ራእይ 22፥ 15)።
በውስጥ ያለው በውጭ ካለው ይለያል። በውስጥ ያለው፣ " የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት" (ሮሜ 14፥ 17) ተብሎ እንደተጻፈ፣ የውስጡ ተፈጥሮና ባህርይ ፈጽሞ ይለያል። ውስጡ እጅግ እንደሚያምርና እንደሚማርክ አጥርተን እንይ። በውስጥ ያለው ጉልበት ኃያል ነው፤ "የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና" (1ቆሮ 4፥ 20)። በእግዚአብሔር መንግስት ምስጢር እውቀት እያደግን፣ በውስጥ የተገለጠው የብርሃን ግርማ ካልማረከን በቀር ውጭውን የሸፈነው ድቅድቅ ጨለማ እያስፈራራን እንኖራለን። በብርሃን ተከቦ በቤት ውስጥ እየኖሩ ከቤት ውጭ ያለውን ጥላና ጨለማ እየፈሩ መጨነቅና መደንገጥ ብዙዎቻችን በህጻንነት እድሜአችን ያሳለፍነው ልምምድ ነው። ስናድግ ግን ያንን ትተናል። ስለዚህ እንደግ እንጂ ወደፊት ህጻናት መሆን አይገባንም።
"ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።" (1ቆሮ 6፥9-10) እንደተባለ የእግዚአብሔር መንግስት ፍጹም ንጹህ ነው። የእግዚአብሔር መንግስት የስጋና ደም መንግስት አይደለም፤ ጳውሎስ፣ "ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም" (1ቆሮ 15፥ 50) ብሎአልና፤ አሁን የምንኖርበትን የእግዚአብሔርን መንግስት በስጋና በደም አንገምተው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእንክርዳዱን ምሳሌ ተርጉሞ ባስተማረበት በማርቆስ 13 ያለውን ትምህርት ካጤነው፣ "የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥" (ማርቆስ 13 ፥40) ሲል፣ ክፋት የሚለቀመው "ከመንግስቱ" ነው እንጂ ከአለም ላይ አለመሆኑን እናስተውላለን። መንግስቱ ደግሞ ከዚህ አለም አይደለችም።
ክርስቶስ በዙፋኑ ሆኖ የነገሰባትና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ለዘላለም የሚገዛባት፣ ጽድቅና ቅድስና የሰፈነባት፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ኃሴትና ደስታ የሞላባት መንግስቱ፣ እዚህ ተዳሳሹ አለም ላይ ካለ ከየትኛውም ሥጋዊና ነባራዊ የሰው ስርአት ጋር እናስተያያት ዘንድ የሚመጥናትና የሚገልጣት ምንም አምሳያ የላትም። የምድር ላይ ኃያላን በመንግስታቸው የለበሱትን ካባ እና በራሳቸው ላይ የደፉትን ዘውድ፣ የተቀመጡበትን ዙፋንና የሚሰጡትን ፍርድና ዳኝነት ስንራቀቅ ውለን ብናድርበት ክርስቶስ በመንግስቱ ካለው ግርማና ክብር ጋር ሊጠጋጋ ቀርቶ ምሳሌ ለመሆን እንኳ አይበቃም።
"በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።" (ራእይ 12፥ 7-10)
"በሰማይ" በሆነው ሰልፍ ድል የተመታው ዘንዶ "በሰማይ" ስፍራ የለውም፤ በክርስቶስና በቅዱሳኑ ሰማይ ዕድል ፈንታ መብትና መታሰቢያ የለውም። ወደ ምድር ተጥሎአል እንጂ በክርስቶስ ሆነን በምንኖርበት በሰማያችን ላይ ቦታ የለውም። የክርስቶስና የክርስቲያኖች ሰማይ ንጹህ ነው፣ በዚህ ሰማይ ስትኖሩ ስለ ዘንዶው ውጊያና ስለ ከሳሽነቱ ስጋት አይግባችሁ። ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሰይጣንን ድል ነስቶታልና። ድላችሁን በእምነት ያዙ እንጂ በማየትና በስሜት አትፈልጉት። ሰይጣን ታስሮአል፣ ወደ ምድርም ተጥሎአል፤ ሰማይም ከክፉውና ከክፋት ነጻ ነው።ክፉውና ክፋት ፍጻሜውን ያገኘው በሰማይ ነው። "እንቅፋት ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉ" ሁሉ ከመንግስቱ ተለቅመው ተጠርገዋል። አስተውሉ፣ ዘንዶው ተሸንፎ የተጣለው ወደ ምድር ነው፣ ከመንግስቱ ውጭ።
ከተገለጠው ድል መንሳትና ከዘንዶው መጣል የተነሳ የተነገረውን የሰማይ ድምጽ ስሙ፣ ይህ ድምጽ ሰማይ ብቻ የሚሰማውና የሚረዳው ድምጽ ነው፦ " አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥" ይህ የሆነው ከጊዜ አንጻር እንጂ ከጆግራፊ አንጻር አይደለም፤ ከጊዜ አንጻር "አሁን" ነው፣ ከአድራሻ አንጻር ደግሞ "በሰማያዊው ስፍራ" ነው። "በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ" (ኤፌ 1፥3)። ይህም ስፍራ የእግዚአብሔር ቀኝ መንፈሳዊው የክርስቶስ ግዛት ነው፣ ትንሳኤን እንደተቀበለ አማኝም መቀመጫችን በሰማይ ነው፤ "በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን" (ኤፌ 2፥ 7)።
ስለዚህ፣ ሰይጣን በእሳት ባሕር ውስጥ እንደተጣለ እና በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደነበረው አጋንንቱ ትንሳኤ ያገኘነውን እኛን መውረስ እንደማይችሉ አምናለሁ፤ ነገር ግን ይህ በፍጥረታዊው አዕምሮአችንና በአስተሳሰባችን ውስጥ የመሳለብና የመወሰድ ፈተና የለብንም ማለት አይደለም። በዚህ ፍጥረታዊ አለም በስጋዊው ተፈጥሮአችን በምድር ላይ ሳለን በዚህ ትግል ውስጥ እናልፋለን። ለዚያም ነው እንደ ክርስቲያን የጥሞናን ሕይወት ጠብቀን በጸሎትና በእግዚአብሔር ቃል እየተጋን ከእግዚአብሔር ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረትና መጠበቅ ያለብን።
No comments:
Post a Comment