ክፍል ፫
የዮሐንስ ራእይ እና የመጨረሻው ቀን
በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ላይ ለጀመርነው ጥናት ተጨማሪ ግብዓት እንዲሆነን መታሰብ ያለባቸውን ሌሎች አጋዥ ነጥቦች አክዬ በአጭሩ አነሳለሁ። መጽሐፉን ጊዜ ወስደው በግላቸው ለማጥናትና ለመመርመር በእውነት ፍላጎቱ ያላቸው የቃሉ ተማሪዎች ቀጥሎ በማነሳቸው ነጥቦችና ጥያቄዎች አንጻር ምን መመለስ እንዳለባቸው በአግባቡ ካሰቡ ከብዙ አደናጋሪ ትርጉም ራሳቸውንም እምነታቸውንም መከላከል ይችላሉ።
♦የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ በይዘቱ ገና አሁንም ወደ ፊት በአለም ላይ ይሆናል ወይም ይደርሳል ተብሎ በብዙዎች ሰለሚጠበቀውና "መጻኢ" ስለሆነው ስለ "መጨረሻው ቀን" ነው የሚናገረው ከተባለ፣ ታድያ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በብዙ ስፍራ ስለ መጨርሻው ቀኖች የተነገሩ ክፍሎች ለምን በግልጽ የመጀመሪያውን ክፍለ ዘመን ያመለክታሉ?
ለምሳሌ ቀጥሎ የቀረቡትን ጥቅሶች አመሳክሩ፦
ሐዋ 2፥ 14-20፤ "ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው። እግዚአብሔር ይላል፦ በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።"
ገላ 4፥ 4 "ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤"
1ጢሞ 4፥ 1፤ "መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤.... "
2ጢሞ 3፥ 1፤ "ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።"
እብ 1፥ 2፤ "ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤"
1ጴጥ 1፥ 5፣ 20፣ "፤ ...ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።.....ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።"
2ጴጥ 3፥ 3፤ "በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤"
1ዮሐ 2፥ 18፤ "ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን"
ይሁዳ 18 "እነርሱ፦ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና።"
መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው "የመጨረሻው ዘመን" አንድ ብቻ ሲሆን፣ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዋችም እነርሱ ራሳቸው "በመጨረሻው ዘመን" ወይም "በዘመኑ ፍጻሜ" ውስጥ እንደነበሩ ያውቁና ያስተውሉ ነበር። ከፍ ሲል ከተጠቀሱት ክፍሎች የምናስተውለው መንፈስ ቅዱስ ለሰው የተሰጠበት አይነተኛ ጊዜ "የመጨረሻው ዘመን" ነበር ማለት ነው፤ እግዚአብሔር ልጁን ከሴት እንዲወለድ ከህግም በታች እንዲወለድ የላከው "የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ" ነበር ማለት ነው። ይህም ዘመን ቃሉ "የሚያስጨንቅ" ብሎ የሚጠራውና ጳውሎስና ጢሞቴዎስ የነበሩበት "የኋለኞች ዘመናት"፣ "የመጨረሻው ቀን" የሚባለው ጊዜ ነው። እግዚአብሔር በልጁ ለሰው ልጆች የተናገረበት አይነተኛ ጊዜ "የዚህ ዘመን መጨረሻ" የተባለው ጊዜ ነው። ጴጥሮስና ይሁዳ የመልእቶቻቸው በኩረ ተደራስያንም በዚያው የመጨረሻ ዘመን ውስጥ እንደነበሩ ያውቁ ነበር። የመጨረሻው ዘመን ከሐዋርያት ሁሉ በኋላ ቆይቶ በህይወት ለኖረው ለዮሐንስማ "የመጨረሻው ሰአት" ሆኖ ነበር። ከዚህ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ እንደነበር እነዚህ የንባብ ክፍሎች ከሚያረጋግጡትና ቃሉ ከሚያውቀው የተለየ ሌላ የመጨረሻ ዘመን የለም። የራእይ መጽሐፍም የሚናገርለት የመጨረሻ ዘመን ከዚህ ስለተለየ ስለ ሌላ ዘመን አይደለም።
♦የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ የያዛቸው ኩነቶች መጽሐፉ ከተጻፈበት ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የጊዜ ማእቀፍ በዘለለ ከሺህዎች አመታት በኋላ በሚሆን የዘመን ርዝመት በአለም ላይ የሚደርሱና የሚፈጸሙ ጉዳዮች ከሆኑ፣ ዮሐንስ በራእዩ ስለ "ስድስተኛው ንጉስ" በተናገረ ጊዜ ለምን "አንዱም አለ" ሲል ይናገራል?
ራእ 17፥ 10 "ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፥ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።"
ራዕዩ በተለይ ስለ ሰባት ነገስታት ጠቅሶ የሚናገር መሆኑን በቀደመው የጥናታችን ክፍል ዘርዘር አድርገን አይተነዋል፡፡ "አምስቱ ወድቀዋል" የተባሉት፣ ይኸውም ራዕዩ ከመሰጠቱና ከመጻፉ በፊት ተፈራርቀው የነገሱት ነገስታት ናቸው፡፡ "አንዱም አለ"፣ ይህ በአሁን ጊዜ አመልካች ንግግር የተጠቀሰውና "አለ" የተባለው ራዕዩ ሲጻፍና ሲሰጥ ይገዛ የነበረው ንጉስ ነው፡፡ ሰባተኛው ገና አልመጣም ሲመጣም ብዙ አይቆይም የተባለው ነው፣ እርሱም ራእዩ በተሰጠበት ጊዜ ገና ወደ መንግስት ያልመጣ ከራዕዩ መሰጠትና መጻፍ በኋላ ገና የሚነግሰው ነው፡፡ ስለዚህ የራእዩ ኩነቶች ፍጻሜ የሚጠበቀው በነዚህ ነገስታት ዘመነ መንግስት ውስጥ እንጂ ሺህ አመታት የሚቆዩ ጉዳዮች አይደሉም።
♦ዮሐንስ በራእዩ ምዕራፍ 14፥ 7 ላይ "የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና" ብሎ ሲናገር፣ እርሱ ከነበረበት ጊዜ በሺሆች አመታት ርቀት ገና ወደ ፊት ስለሚመጣ ጊዜ ሊያመለክት እንዴት ይቻለዋል?
የፍርዱ ጊዜ ያኔ ራእዩ በተሰጠበት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን የጊዜ ማእቀፍ ውስጥ "ሰአቱ ደርሶአል" በተሰኘ የችኮላ ጊዜ አገላለጽ ቀን የተቆረጠለት ነበር እንጂ ለሺህ አመታት የሚጠበቅ አልነበረም።
♦144,000ዎቹ (ራእ 7፥ 14፤ 14፥ 4) ከሺህዎች አመታት በኋላ ስለሚታተሙ ሰዎች የተነገረ ቃል ከሆነ፣ ታድያ የንባብ ክፍሉ እነዚህ የታተሙትን በተመለከተ "በኩራት" ናቸው ሲል ለምን ይናገራል?
የአዲሱ ኪዳን የቤተክርስቲያን ምዕራፍ ሲከፈት የምናገኛቸው የመጀመሪያዎቹ ምእመናን ከእስራኤል ሕዝብ ዘንድ በወንጌል ያመኑትን የአይሁድ የወንጌል በኩራትንና ቅሬታዎችን (remnants) ነው። እነዚህም የታተሙት ወይም የዳኑት ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ወቅት ነው።
♦መከራውስ ቢሆን ዮሐንስ ከነበረበት ጊዜ አንጻር ገና ወደፊት ያለና የሚጠበቅ ነገር ከሆነ፣ ታድያ ራእዩን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ ያኔውኑ እርሱ ራሱም ቢሆን በመከራው ውስጥ እንደነበር ለምን ይናገራል (ራእ 1፥ 9)?
"ታላቁ መከራ" (ራእይ 7፥ 14) ያ በመጀመርያይቱ ክፍለ ዘመን የወንጌል በኩራት ላይ ይደረስ የነበረው ስደትና ጽኑ መከራ ዮሐንስ ራሱ ይካፈለውና ያልፍበት የነበረው መከራ ነው።
♦የራእዩ መጽሐፍ ሁነቶች የሚፈጸሙት ከተጻፉበት ጊዜ አንጻር ገና ወደ ፊት ብዙ ዘመን ቆይተው ከሆነ ታዲያ "ዘመኑ ቀርቦአልና የመጽሐፉን ቃል በማህተም አትዝጋው" የሚልን መመርያ ለምን ተቀበለ (ራእ 22፥ 10)?
ይህ አይነተኛ የአዲስ ኪዳን የትንቢት መጽሐፍ በነብዩ ዳንኤል የትንቢት መጽሐፍ ማጠቃለያ ላይ (ዳን 8፥ 26፤ 12፥ 4) መጽሐፉን በማህተም ዝጋ ከሚለው ጋር የሚገናዘብና የሚነጻጸር ነው። ለነብዩ ዳንኤልና ለነብዩ ዮሐንስ የትንቢት መጻህፍቶቻቸውን በተመለከተ በየዘመናቸው የተሰጡአቸው ሁለት የተለያዩ መመርያዎች ለአንዱ "በማህተም ዝጋው" ሲሆን ለሌላው ደግሞ "በማህተም አትዝጋው" የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው የፍጻሜ ዘመን ነብዩ ዳንኤል ትንቢቱንና ራእዩን ከተቀበለበትና በነብይነት ካገለገለበት ዘመን አንጻር ሲታይ ገና ብዙ ዘመን ይቀረው ስለነበር ዳንኤል ትንቢቱን በማህተም እንዲዘጋው መመርያን ተቀበለ፤ ይኸው አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀውና "ዘመኑ" እየተባለ የሚጠራው የመጨረሻው ዘመን ደግሞ ሐዋርያው ዮሐንስ ካገለገለበት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አንጻር ሲታይ እጅግ የቀረበ ስለነበር የመጽሐፉን ቃል "በማህተም አትዝጋው" የሚልን መመርያ ተቀበለ።
♦የራእይ መጽሐፍ ሁነቶች የተጻፉትና የሚፈጸሙት መጽሐፉ ከተጻፈበት ጊዜ አንጻር በብዙ ሺህ አመታት ርቀት ለሚኖሩ ሰዎች ከሆነ፣ ያኔ ገና በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ይኖሩ የነበሩ የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ሰዎች በመጽሐፉ የተገለጠው አውሬው ማን እንደሆነና ማንን እንደሚያመለክት ሊረዱ ይችላሉ ሲል መጽሐፉ ለምን አጽንኦት ይሰጠዋል?
በአውሬው ማንነት ላይ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ይኖሩ የነበሩ እነዚያ የመልእክቱ በኩረ ተደራስያን የሰባቱም አብያተ ክርስቲያናት ክርስቲያኖች ምንም ጥርጣሬ አልነበረባቸውም። "እከሌ ነው" ማለት ይችሉ ነበር እንጂ እንደ ዘመናችን ተርጓሚዎች መላ ምት በመስጠት ገራ ገብቶአቸው ግራ አያጋቡም።
♦ በእስያስ ቢሆን ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ብቻ የነበሩበት ትክክለኛው ጊዜ በ60ዎቹ አ.ም መሆኑ ትክክለኛ ታሪክ አይደለም ወይ?
♦የዮሐንስ ራእይ አብይ መልእክትና ርእሰ ጉዳይ "ታላቂቱ ከተማ" እና "ጋለሞታይቱ" ተብላ በተጠራችው በባቢሎን ላይ የሚደርሰውን ፍርድ በተመለከተ እንደሆነ በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ዘንድ አጠቃላይ የሆነ መግባባት አለ። እንግዲህ "ባቢሎን" በሚል ሥያሜ የተጠራችው ከተማ በብዙ አመታት ርቀት ወደ ፊት ገና የምትጠበቅ አይነት ከሆነች፣ ታዲያ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ራሱ ባቢሎንና ታላቂቱ ከተማ ሲል የሚጠራትን ከተማ፣ "ጌታ የተሰቀለባት" (ራእ 11፥ 8፤ 18፥ 10፣ 19፣ 20፣ 24፤ 19፥ 2) ብሎ በመጥራት ለምን የብሉይ ኪዳንዋን ኢየሩሳሌምን ይገልጣታል?
በብሉይ ኪዳንስ ቢሆን እስራኤል ያልታመነች ሆና በተገለጠችበት ስፍራ ሁሉ "ጋለሞታ" እና "አመንዝራ" በተሰኙ አሳፋሪ ባህርያት ስትጠራ አልነበረምን (ኤር 3፥ 6-9፤ ሕዝ 16፥ 26፣ 28)? የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ የሚያውቃት ባቢሎንም መሲህዋን የሰቀለችው የአሮጌው ኪዳን ኢየሩሳሌም ናት እንጂ ሌላ ከተማ አይደለም።
በራእይ መጽሐፍ ትርጉም ላይ እነዚህ ነጥቦች ያላቸውን ተጽእኖ ቸል ብለን በየዘመናቱ የበቀሉ አደናጋሪ ትምህርቶች ላይ የምንንጠለጠል ከሆነ ያው ግራ እንደገባን መላ ምት እያስተማርን መዝለቃችን ነው። ወገኖች ምን ይበጃል ትላላችሁ?
∆∆∆∆∆∆∆∆∆∆
Wednesday, November 21, 2018
፫፣ ራእይ እና የመጨረሻው ቀን
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment