ክፍል ፬
ለዮሐንስ ራዕይ ተመራጩ የትርጉም አቅጣጫ
የዮሐንስን ራዕይ ለመረዳትና ወደ መጽሐፉ ዋና መልእክት ለመቅረብ ትክለኛውና ተገቢው የትርጉም አቅጣጫ የትኛው ነው?
በታሪካዊው የሥነ አፈታት ሥነ መለኮት የዮሐንስ ራዕይን መጽሐፍ ለመተርጎም ቢያንስ አራት መሰረታዊ የአመለካከት ጉራዎች እንዳሉ ይታወቃል፣ እነርሱም፡-
የታሪካዊያን አመለካከት/Historist view/
የሃሳባዊያን አመለካከት /Idealist view/
የመፃኢያን አመለካከት /futurist view/
የሃላፋዊያን አመለካከት/preterist view/ ናቸው።
እያንዳንዱ አመለካከት የራዕይን መጽሐፍ እንዳለ ለመተርጎም የተለያየ አተረጓጎም ይከተላሉ፡፡ ራዕይን በመተርጎም አንጻር ያሉትን አራቱን አመለካቶች በግርድፉ ለማየት ያህል፡ -
♦ የታሪካዊያን አመለካከት፡- የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በመጨረሻ ገና ወደ ፊት እስከሚሆነው የኢየሱስ መመለስ ድረስ እየተደጋገመ የሚመጣ የቤተክርስቲያን ዘመን ነው፡፡ የተለያዩየ የፍርድ ሂደቶች ለተለያዩ የታሪክ ሁነቶች የሚዛመዱ ናቸው፡፡ ይህ አይነቱ የምሁራን አመለካከት ሁልጊዜ ታሪክን እየከለሰ እንደሚደጋግመው አይነት ነው፡፡
♦ የሃሳባውያን አመለካከት፡- የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ማንኛውንም አንድን የተለየ ሁነት እንደሚያመለክት ተደርጎ ፈጽሞ የሚወሰድ መሆን የለበትም፤ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የሚሰራውን ለመግለጥ እንደ መሰረታዊ መርህ መግለጫ የሚወሰድ ነው፡፡ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ በብርሃን መንግስት እና በጨለማ መንግስት መካከል የሚደረገውን በዘመን የማይገደበውን ትግል የሚገልጥ ሥነ መለኮታዊ ሥነ ጽሁፍ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህ አይነቱ አመለካከት የዮሐንስ ራዕይ ሁነቶች ባለፈውም ዘመን ይሁን ገና ወደ ፊት የሚሆን ማንኛውም ዓይነት ታሪካዊ የትንቢት ፍጻሜ ያገኛሉ ብሎ አይቀበልም፡፡
♦ የመፃኢያን አመለካከት፡- ይህ አመለካከት በተለይ ከራዕይ ምዕራፍ 4 በኋላ ያለውን የመጽሐፉን ክፍል የራዕዩ ትንቢት አድርጎ በመውሰድ ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ ወደ ፊት ገና ይሆናል ብሎ የሚጠብቅ አመለካከት ነው፡፡ ይህ አመለካከት የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፉ የዓለምን እና ወይም የቤተክርስቲያንን የመጨረሻ ታሪክ በተመለከተ የሚናገር ነው ብሎ ይረዳል፡፡ ዘመን ቆጣሪነት /Dispensationalism/ ከተሰኘው እና በአስራ ዘጠነኛው ምዕተ ዓመት ላይ በስፋት እየታወቀ ከመጣው የነገረ ፈፃሜ አስተሳሰብ ተጽፅኖ የተነሳ በዘመናችን በእጅጉ ታዋቂ መሆኑ የሚነገርለት አመለካከት ነው፡፡ አመለካከቱ ተለይቶ ከሚታወቅባቸው ነጥቦች መካከል ጥቂቶቹን ልጥቀስ፦
1ኛ/ ሁለት መሰረታዊ የሆኑ የዘመን ቆጣርያን መለያ አስተምህሮዎች ያሉ መሆናቸውን አስተውሉ፡-
1. እግዚአብሔር እስራኤልና ቤተክርስቲያን የተባሉ ሁለት የተለያዩ ሕዝቦች አሉት፣ ሁለቱም የተለያየ ተስፋ፣ የተለያየ ዕጣ ፋንታ እና የተለያየ ዓላማ አላቸው ይላሉ።
2. የትርጉም ቀዋሚነት (consistency) በጎደለው አቀራረብ የተሳከረ የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ላይ የተመሰረተ ዳግመኛ ምጽአትን እየተጠባበቀ የዘመን ቆጣሪነትን /Dispensationalist/ ማቀንቀኑ ሌላው መለያው ነው፡፡ በትምህርታቸውም "በቅርቡ አንድ ቀን /ሁልጊዜ በቅርቡ እንደሚሉ ልብ ይሏል/ ክርስቶስ ወደ ምድር በማይታይ ሁኔታ በሚስጥር ይመለስና ሁሉንም ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ነጥቆ ይወስዳል" ሲሉ "ንጥቀትን" የሚሉት ነገር ይጠባበቃሉ፡፡ እንደ ትምህርታቸው ከሆነ፣ "እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን በመጨረሻው ቀን ድንገት ወደ ሰማይ ነጥቆ በመውሰድ ከዚህ አለም ዘወር ካደረጋት በኋላ፣ እንደገና ወደ እስራኤል ተመልሶ የእርስዋን መዳን በተመለከተ ደግሞ ይሰራል" ይላሉ፡፡ "ያኔም በርካታ አይሁድ የሚድኑበት 'ታላቁ መከራ' የተሰኘ የሰባት ዓመታት ክፍለ ጊዜ ይጀምራል፡፡ በመከራው መጨረሻ ላይ ክርስቶስ በይፋ ይመጣና የሺህ ዓመት መንግስትን ይመሰርታል፡፡ በሺህ ዓመት መጨረሻ ላይ ዓመጽ ይሆንና በክርስቶስ መምጣት ዘላለማዊ መንግስት ይመሰረታል" ይላሉ። እንግዲህ በዚህ እይታ መጻእያን የሚጠብቁአቸውን ሦስት የተለያዩ ምጽዓቶችን ያሳያችሁ፣ ይኸውም ክርስቲያኖችን ነጥቆ ሊወስድ፣ የሺህ አመት መንግስቱን ሊመሰርት፣ ዘላለማዊ መንግስቱን ሊመሰርት እንደሚመላለስ የሚያምኑትንና የሚያስተምሩትንም ምጽአቶች መቁጠር ይቻላል፡፡
የዘመን ቆጣሪነት ነገረ ፍጻሜ አጠቃላይ ነገሩን ሰናየው፣ ምንም ያህል በቅርብ ዓመታት ውስጥ ታዋቂ እየሆነ ቢመጣም እንኳ በታሪካዊው የክርስትና ትምህርትም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ታሪክ ውስጥ ምንም አይነት መሰረት የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህ አመለካከት "የመጨረሻውን ዘመን" በተመለከተ በሚሰነዘሩ የተለያዩ አመለካከቶችን በሚከተሉ የስህተት ትምህርቶች፣ በሞርሞኖች፣ በመጠበቂያ ግንብ አማኞች፣ እና ራሳቸውን አለም አቀፍ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ሲሉ በሚጠሩት የእምነት ክፍሎችና በመሳሰሉት ሁሉ ዘንድ የሚታመን ነው፡፡
2ኛ/ አመለካከቱ ስለ ሺህ ዓመት መንግስት ልዩ ልዩ ጎራዎችን አቅፏል፣ ከነዚህም መካከል በጉልህ የሚታወቁትን በአጭሩ እንመልከት፦
1. አንዳንዶች ገና ወደ ፊት ከሚመጣው የሺህ ዓመት መንግስት /ሚሊኒየም/ በፊት ክርስቶስ ይመጣል ይላሉ፤ ነገር ግን የሚመጣው ከመከራው በኋላ ነው ይላሉ ይኸውም ድህረ መከራው/Post-tribulation/ ቅድመ ሺህ አመት መንግስት /Pre-millennialism/ ይባላል።
2. ሌሎችም ገና ወደፊት ከሚመጣው የሺህ ዓመት መንግስት /ሚሊንየም/ በኋላ ክርስቶስ ይመጣል ይላሉ፤ ይኸውም ድህረ ሺህ ዓመት መንግስት /Post millennialism/ ይባላል፡፡
3. በሌላ መልኩ ደግሞ አልቦ ሺህ አመት መንግስት /Amillenialism/ የራዕይ 20 ሺህ አመታትን የሚረዱት ሊገለጥ የማይችልን ረጅም ዘመን ሲሆን፣ የሚሸፍነው ከክርስቶስ የመጀመሪያ በስጋ መምጣት ጀምሮ በታላቅ ክብር እስከ ሚሆነው ዳግም ምጽአቱ ድረስ ያለውን ጊዜ ነው የሚል ነው፡፡ የምዕራፍ 20 አብዛኛው ነገር እንደ አብዛኛው የራዕይ መጽሐፍ ተምሳሌታዊ ነው ይላሉ፡፡ የሰይጣን መታሰር በመስቀሉ ላይ ያኔ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሆኖአል፤ የቅዱሳን መንገስ በአሁኑ ዘመን ነው፤ የሰይጣን መፈታት በዘመኑ መጨረሻ በአለም ላይ የሚሆነው የመጨረሻ የማሳሳት ጊዜ ነው፤ ከሰማይ የወረደውና ኃጢአተኞችን የበላው እሳት የክርስቶስ ዳግም ምጸአት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ከኦግስቲን ጀምሮ እስከ ተሃድሶ ዘመን ድረስ ያሉ ሁሉም የስነ መለኮት ሊቃውንትና አባቶች ይህንን አመለካከት ይከተላሉ፡፡
4. ሌሎች ደግሞ ገና ወደፊት ከሚሆነው መከራና የሺህ ዓመት መንግስት በፊት ክርስቶስ ይመጣል፤ ደግም ምጽዓቱም በሁለት ክፍል ይከፊላል ይላሉ፤ ይኸውም ቅድመ መከራ ንጥቀት /pre-tribulation rapture/፣ ቅድመ ሺህ አመት መንግስት /pre-millennialism/፣ ወይም ዘመን ቆጣሪ ወቅድመ ሺህ አመት መንግስት /dispensational pre-millennialism/ ይባላል፡፡ በዚህ ሁለት በሚከፈለው ምፅዓት አንዴ ቤተክርስትያኑን ሊነጥቅ በሌላ ጊዜ ደግሞ ለሺህ ዓመት መንግስት ይመለሳል ይላሉ፡፡
5. ሌሎችም በቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ክርስቶስ መጥቶአል ይኸውም የሺህ ዓመት መንግስት ነው ብለው ይሉታል፡፡ አጠራራቸውም፡- ቅድመ ሺህ አመት መንግስት ምዳቤ ቀናት /pre- millennial date setting/ ይባላሉ፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ የወደፊት ጊዜ አመልካች futurist ናቸው፡ ፡
3ኛ/ የመጻኢነት አመለካት አራማጆች በምዳቤ ቀናት ስህተቶቻቸው የታወቃሉ። እዚህ ላይ ያልተፈጸሙ ትንበያዎችን በመስጠት የሚታወቁ የታሪክ ሰዎችን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህም በታሪክ ውስጥ ሓላፊ ሆነው የተፈጸሙና ያልታረሙ ስህተቶች ናቸው። እነዚህን በምሳሌነት በዚህ ጥናታዊ ሥራ ላይ ሳነሳ ዓላማዬ ችግሩን ማሳየት እንጂ የማንንም እምነትና ስብዕና ማጣጣል አይደለም። በዚህ ላይ ከምጠቅሳቸው አባቶች መካከል አንዳንዶቹን ከነገረ ፍጻሜ ትምህርታቸው ውጭ ብዙ የተማርኩባቸው ሰዎች እንደ ሆኑ እመሰክርላቸዋለሁ። በዚህ ውስጥ ማንም አንባቢ ሊጠይቃቸው የሚገቡም ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉ። ይኸውም እነዚህ ሰዎች ምን የሚያመሳሰላቸው የጋራ ነገር አላቸው? የሚለውና ከዚህስ ታሪክ ከሚያውቀው ተደጋጋሚ ስህተት እኛ ምን የምንማረው ነገር አለ? የሚለው ነው።
ለአብነት ያህል፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ170- 236 የኖረው የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አባት ሑፓሊቱስ የዓለም መጨረሻ በ500 ዓ.ም ላይ ይሆናል ብሎ ነበረ፤ ያም ባልሆነ ጊዜ በ999 ዓ.ም የራዕይ መጽሓፍ የሺህ ዓመት መንግሥቱ አብቅቶ በ1000 ዓ/ም ክርስቶስ ይመለሳል ተብሎ እየተጠበቀ ነበረ፤ ይህም ባልሆነ ጊዜ እንደገና ትንቢቱ ተሻሽሎ በ1033 ዓ.ም ምጽአት ይሆናል ተባለ። በ1100 ዓ.ም ላይ የዘመኑ የትንቢት መጽሓፍቶች የአተርጓጎም ሊቅ የነበረው ጣሊያናዊው መነኩሴ ዩዓቄም መጨረሻው በ1200 ዓ.ም እና በ1260 ዓ.ም መካከል ነው ሲል ጊዜውን ወስኖ አስቀመጠ። ክርስቶፎል ኮሎንባስ በ1501 ዓ.ም ከ155 ዓመት በኋላ ሁሉም ሰው ወደ ክርስትና ይመለሳል ከዚያም በኋላ የዓለም ፍፃሜ ይሆናል ብሎ ነበረ። የተሐድሶ አባት የሆነው ማርቲን ሊተርም ከተባረከው ሞቱ በፊት የፍርድ ቀን ወይም የዓለም መጨረሻ በጣም ሩቅ እንዳልሆነ፣ እንዲያውም ከ300 ዓመት በኋላ ሊሆን እንደሚችል በመገመት ሁሉም ምልክቶች ታይተዋል ብሏል። በ1835 ዓ.ም ላይ የሞርሞኖች የእምነት አባት ጆሴፍ ስሚዝ የጌታ ምጽዓት ከ56 ዓመታት በኋላ ይሆናል በማለት ተንብዮ ነበረ።
ባሳለፍነው ሃያኛው ምእተ አመት ይህ ሁነት መቼ እንደሚሆን በርካቶች ቀን ቆርጠው ትንበያቸውን ሲሰጡም ተስተውሎአል።
በ1926 ዓ.ም ታዋቂው ሚስዮናዊው ኦስዋልድ ጄ. ስሚዝ በዚህ ጉዳይ ንስሓ ከመግባቱና አመለካከቱን ከማስተካከሉ በፊት የሚስዮናዊነትን ተልዕኮ በሚገልጸውና በታወቀው “Is the Antichrist at Hand” በተሰኘው መጽሓፉ ታላቁ መከራ፣ የሮም መንግሥት ምሥረታ፣ የክርስቶስ ተቃዋሚ አገዛዝና የአርማጌድን ጦርነት ከ1933 ዓ.ም በፊት መሆን አለበት ሲል ጽፏል።
ሚኬል ዳሄል የተባለ ሰው ይህ የአሁኑ ዘመን በ1980 ላይ እንደሚያበቃ ተንብዮ ነበር። ኤድዋርድ ዱናንስም ሩስያ በአሜሪካን ላይ ወረራ ስትፈጽም ያኔ በ1979 የሺህ አመት መንግስት ይጀምራል ሲል ትንበያውን ሰጥቶ ነበር። የደቡብ ምእራብ ራድዮ ቤተክርስቲያኑ ኤሚል ጋቨርሉክም ንጥቀት በ1981 ላይ እንደሚሆን ግምቱን ተንብዮ ነበር።
በ1970 ዓ.ም ሃል ሊንዲንሲ “The Late Great Planet Earth” በተሰኘውና ሰፊ የገበያ ሽፋን ባገኘው መጽሓፉ ላይ በ1948 ዓ.ም የእስራኤልን መንግሥት ዳግም ውልደት እንደ ትንቢታዊ ምልክት ነው ሲል ይጠቅሳል። ከዚሁ ጋር አያይዞም ይህ ሰው የአሥራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ አሥርት ዓመታት ትውልድ የዘመናችን የመጨረሻ ትውልድ ነው ሲል ያምናል። አያይዞም በአንድ ትውልድ ውስጥ (አርባ ዓመት ሲሞላ በ1988 ዓ.ም) የአሁኑን የዓለም ፍፃሜና የክርስቶስን መመለስ በዐይናችን እናያለን ሲል ተናግሯል። የ1977 ዓ.ም እትም የሆነው የዚህ ሰው መጽሓፍ አንባቢዎቹን ከ1985 ዓ.ም የዘለለ እቅድ እንዳያቅዱ ያስጠነቅቃል።
ሀል ሊንደሲ እንዲህ ብሎ ነበር፦ "በግምት ከ2,000 አመታት ግዞት በኋላ የአይሁድ ህዝብ ከነበሩበት የስደት ሕይወት ተላቀው በሜይ 14 ቀን 1948 አ.ም እንደገና ሕዝብና አገር ሆነው ሲቋቋሙ፣ ይህ ማለት በለሲቱ ስትለመልምና ቅጠልዋ ሲያቆጠቁጥ ነው። ኢየሱስ እንደተናገረው፣ ይህ የሚያመለክተው ለመመለስ በደጅ መሆኑን ነው። ከዚያም እንዲህ አለ "እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" (ማቴ 24፥ 34)።" ሲል የጌታችንን ቃል ይጠቅሳል።
ሀል ሊንደሲ ይህንን ቃል አንስቶ "የትኛው ትውልድ?" ሲል ይጠይቅና ራሱ ሲመልስ፣ "በግልጽ አውዱ እንደሚነግረን ምልክቶቹን የሚያየው ትውልድ ነው። ከእነርሱም መካከል የእስራኤል እንደገና መመስረት ነው። አንድ ትውልድ በመጽሐፍ ቅዱስ የአርባ አመታት ጊዜ ነው። ይህ ትክክለኛ ቀመር ከሆነ፣ እንግዲያውስ በአርባ አመታት ውስጥ ወይም ከ1948 ጀምሮ እነዚህ ነገሮች መሆን ይጀምራሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ያጠኑ በርካታ ምሁራንም ይህ እንደዚህ እንደሆነ ያምናሉ" ይልል። (The Late Great Planet Earth, pp53-54)
በ1990 ዓ.ም የዳላስ ቲዎሎጂካል ሴሚናሪዮም ፕሬዘዳንት የሆኑት ጆን ኤፍ ዋልቩርድ የ1974 ዓ.ም እትም የሆነውንና በሰሎሞን ደጀኔ ወደ አማርኛ ቋንቋ የተመለሰውን “አርማጌዶን፣ የነዳጅ ዘይትና የመካከለኛው ምሥስራቅ ውዝግብ” የተሰኘውን መጽሓፋቸውን ለንባብ አበቁ። ይህ መጽሓፍ በሚልዮን ቅጅ የተሸጠ መጽሓፍ ነው። መጽሓፉም ሰሜን አሜሪካ ከኢራቅ ጋር በምታደርገው ጦርነት ወደ መጨረሻው የአርማጌዶን ጦርነት የሚያመራ እንደሆነ በማሳየት አቡቀለምሲሳዊ ፍርሃት ይቀሰቅሳል። የባህረ ሰላጤው ጦርነቱም በተጠናቀቀ ጊዜ አብሮ የመጽሓፉ ሽያጭም አበቃ። በ1991 ዓ.ም አሁንም የዳላስ ቲዎሎጂካል ሴሚናሪዮም ፕሮፌሰር የሆነው ቻርለስ ዳየር “The Rise of Babilon: Sign of The End Time” በተሰኘው መጽሓፉ የኢራቁ ሳዳም ሁሴን የጥንቷን ባቢሎንን የሚገነባ እንደሆነና ይህም በራዕይ መጽሓፍ ላይ የተነገረውን የመጨረሻ ጥፋት የሚያስተናግድ ነው ሲል ያትታል። በባህረ ሰላጤው ጦርነት ኢራቅ በአሜሪካን ስትሸነፍ የዚህም ፕሮፌሰር የትንተናና የምርምር ውጤት አብሮ ጊዜው ያለፈበት ሆኖ ቀረ ።
በ1948 እስራኤል እንደ ህዝብና አገር ስትቋቋም ብዙዎች ይህንን ጉዳይ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች መፈጸም እንደ አይነተኛ ምእራፍ ሲወስዱት ተስተውሏል። በዚያን ጊዜ በነበረው ትውልድ ውስጥም (በአርባ አመታት ውስጥ) ንጥቀት ይሆናል ብለው ሲጠባበቁም ነበር። ዛሬም ድረስ በክርስትናው አለም የዘመነኛይቱን እስራኤል አመሰራረት፣ ፓለቲካዊ፣ መልክአ ምድራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳይዋን ከትንቢት ፍጻሜ ምልክት ጋር ለማጣጣምና ለመተርጎም የሚጥሩ እጅግ ብዙዎች እንደሆኑ የተሰወረ አይደለም። በጥናታችን መግቢያ ላይ የጠቀስነው ኤድጋርድ ሲ ዌስናንት የተባለ ሰውም ንጥቀት በ1988 ላይ ለምን የግድ መሆን እንዳለበት ለማስረዳት 88 ምክንያቶችን የሚዘረዝር መጽሐፍ ጽፎ ፣ በ1988 ብቻ በወንጌል አማኞች ዘንድ የዚህ መጽሐፍ ስድስት ሚልዮን ቅጂ ተሰራጭቶ ነበር። ዌስናንት ሲያስረዳ ክርስቶስ በመስከረም 1988 ወደ ምድር ለምን መመለስ እንዳለበት ይሞግታል። አስቂኙ ነገር፣ በርካታ ክርስቲያኖች የዚህን ሰው መልእክት እውነት አድርገው በመውሰድ ስራዎቻቸውን ያቆሙና የክርስቶስን ድንገተኛ መምጣት ለመጠባበቅ እንዲመቻቸው ከሚተዳደሩበት የስራ ገበታቸው የአመት ፈቃድ ጠይቀው ጊዜ ወስደው እንደነበር በርካታ የዜና አውታሮች ዘግበውታል። የአመት ፈቃድ ወስዶ ምጽአቱንና ንጥቀትን መጠባበቅ ምን የሚሉት ነገር እንደሆነ በእውነት ግራ ይገባል።
ዌስናንት ለከት ባጣ ድፍረቱ ሲናገር "ልሳሳት የምችለው መጽሐፍ ቅዱስ ከተሳሳተ ብቻ ነው፣ በሁሉ ስፍራ ላሉ ሰባክያን በማያሻማ መንገድ ላረጋግጥላቸው የምችለውም በመጽሐፍ ቅዱስ ረገድ እኔ ልሳሳት የምችልበት ምንም መንገድ የሌለ መሆኑን ነው"፣ ብሎ በግልጽ ይናገር ነበር። በኋላም እንደ ዌስናንት ትንቢት ይጠበቅ የነበረው ንጥቀት ሳይሆን ቀርቶ መስከረም 1988 ካለፈ በኋላም ዌስናንት ለቀድሞው የሃሰት ትንበያው ንስሃ ሳይገባ እንደገና The Final Shout: Rapture Report 1989 የተሰኘ ሌላ መጽሐፍ አሳተመ። በዚህ መጽሐፉ ደግሞ "ስህተቴ የሂሳብ ቀመሬ ላይ በአንድ አመት ጉድለት ማሳየቴ ነው" ብሎ ተናገረ። እንደገናም ግን በትንበያው ስህተት ፈጽሞ ነበር።
አንድ የኮርያውያን ቡድን የሚያሳትመው ጋዜጣም በማስታወቂያ ገጹ ላይ የሰጠው ትንበያ ንጥቀት በኦክቶበር 28 ቀን 1992 ላይ እንደሚሆን ነበር። ያኔም ምንም ባልሆነ ጊዜ፣ ሃኪም ታጂን የተባለ ሰው ጉዳዩን ያለ እፍረት ሲያስተባብል "ከእግዚአብሔር ያገኘነው መልእክት ስህተት ነበር፤ ኢየሱስ ግን ከብዙ አመታት በኋላ ይመለሳል" ሲል ተናግሮአል። በውኑ "ስህተት" ግን ደግሞ "ከእግዚአብሔር የሆነ መልእክት" ምን የሚሉት ቅዠት ነው? ይህስ ስህተት የሚታረምው "ኢየሱስ ግን ከብዙ አመታት በኋላ ይመለሳል" በሚል ሌላ ስህተት መሆን ነበረበትን?
በ1992 የበጋ ወራት ቻርልስ አር ቴይለር የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ ዜናዎችን ጽፎ በሚያቀርብበት ስራው የኢየሱስ መመለሻ ጊዜ የሚሆነው ፎል እየተባለ በሚጠራው በዚያው አመት የክረምት ወራት መግቢያ ላይ እንደሚሆን ነበር፤ ሲጽፍም፦ "ምናልባት ማንበብ ያለባችሁን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የመጨረሻ ዜናዎቼን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን ሊነጥቅ በ1992 ከፎል ወራት በፊት እንደሚመለስ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ፍጻሜ የሚያበስረውን ጽሑፌን አሳትማለሁ" ብሎ ነበር።
ጄፍሪ የተባለ ሰውም Armageddon: Appointment with Destiny በተሰኘው መጽሐፉ "ምናልባት 2000 አ.ም 'የመጨረሻው ዘመን' ፍጻሜ ሊሆን ይችላል" ሲል ጽፎአል። ሊስተር ሱምራልም I Predict 2000 በተሰኘው መጽሐፉ ላይ፦ "በ2000 አ.ም የሰው ልጅ ጭቆና ከምድር ላይ ፈጽሞ ያበቃል" ሲል ይተነብያል።
ባለፉት ቅርብ አመታት ሜይ 21 ቀን 2011 ዓ.ም የዓለም መጨረሻ ፣ የጌታ ምጽዓትና የንጥቀት ጊዜ እንደሚሆን ይህም የእኛው ትውልድ ለጥፋት የተመደበውና የሚፈረድበት ትውልድ እንደሆነ፣ ቀኖቻችንም ወደ እርማጌዶን እየቀረቡ እንዳለ በአሜሪካኑ የቴሌቭዥን ሰባኪ በሃሮልድ ካምፒንግ የተነገረው ትንቢትም የስድብና የፌዝ ጉዳይ ሆኖ አለፈ። በእለቱ መላው የዓለማችን የዜና አውታሮች ሲቀባበሉበትና ሲያሽሟጥጡት ውለው አመሹበት። ለክርስትና እምነት ከዚህ የበለጠ ስድብ የለም። ቀደም ሲል ይህ ሰው በ1992 ዓ.ም ታትሞ በነበረውና “ 1994” በተሰኘው መጽሓፉ የክርስቶስ ተመልሶ መምጫና የዓለማችን መጨረሻ በመስከረም 1994 ዓ.ም እንደሚሆን ተንብዮ እንደነበረ አይዘነጋም። በ2011 ዓ.ም ትንቢቱን አሻሽሎ ያቀረበው የቀድሞው ትንቢቱ ባለመሳካቱ ነበር። የተሻሻለውም ትንበያ ስላልተሳካ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ሌላ ቀን ወስኖ እየተናገረ ይገኝ ነበር። የአለም መጨረሻና የፍርድ ቀን በ2020 ወይንም ከ2020 በኋላ እስከ 2030 ባለው ጊዜ ውስጥ ይሆናል ተብሎ በበርካታ የመጻዲያን ጎራ በሚያምኑም ይሁን በማያምኑም ዘንድ ገና እስካሁን ይሚወራ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል (www religiovsterance.org ተመልከት)፡፡
ወደ አገራችን ኢትዮጵያ መለስ ስንል ደግሞ በሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን የቀጠና ሁለት አጥቢያ መጋቢ የሆኑት ፓስተር በቀለ ወ/ኪዳን ቤተ ክርስቲያናቸው ባሳተመችው “ ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው?” በሚለው መጽሓፋቸው በገጽ 65 ላይ በሰፈረው ሓሳብ በ37 ዓመት ውስጥ የጌታ ምጽዓት እንደሚሆን በእርግጠኝነት ትንበያቸውን አስቀምጠዋል። ይህንንም በየምስባኩ ላይ ሲያስተምሩት ተሰምተዋል። ይህ በመጻኢነት አመለካከት የተቃኘ የዘመን ቆጣሪው (dispensationalist) የትርጉም ተጽዕኖ ያረፈበት መጽሐፍ ደራሲ መጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን ከኤክሰደስ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ "አርባ አመት" የሚለውንና ከፍ ሲል የተጠቀሰውን የሀል ሊንደንሲን ቀመር ወደ መቶ አመታት ለውጦ ከማቅረብ ውጭ ሙሉ በሙሉ ሃሳቡን ቃል በቃል እንደሚጋሩ አንጸባርቀዋል።
ምንም እንኳ በቃለ ምልልሳቸው፣ "እኔ ያልኩት እንደ እርሱ አይደለም" ብለው ቢያስተባብሉም፣ በግልጽ ግን ያስቀመጡትን የጊዜ ገደብ የሚደግፍላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በሉቃስ 21፥ 32 ያለውና "ይህ ትውልድ አያልፍም" የሚለው እንደሆነ፣ ይህም ማለት "የእስራኤልን መንግስት መመስረት ያየው ትውልድ የጌታንም ምጽአት ያያል ማለት ነው ብለው አንዳንዶች ይተረጉሙታል። እንደዚህ እነርሱ እንደሚተረጉሙት ከሆነ በሚቀጥሉት 37 አመታት ውስጥ ጌታ ይመጣል ማለት ነው ብዬ ያንን አስቀመጥሁ እንጂ ያልኩት እንደዚያ አይደለም" በማለት ለማስተባበል ሞክረዋል። በቃለ ምልልሳቸውም የበለሲቱን ማቆጥቆጥ ምሳሌ ከእስራኤል መንግስት መመስረት ጋር፣ "ይህ ትውልድ አያልፍም" የሚለውንም የእስራኤል መንግስት ሲመሰረት በአይኑ የሚያየውን ትውልድ ማለት ነው ሲሉ፣ አቋማቸውን የሚቀበሉ ሌሎችም "ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች" ያሉ እንደሆነ መስክረዋል። አክለውም ምጽአቱን የሚያየውም ሆነ ከሚመጣው የታላቁ መከራ በፊት ለንጥቀት የሚበቃው ይኸውም የእስራኤልን መንግስት እንደገና ማቆጥቆጥ በአይኑ የሚያየው ትውልድ ነው ብለው ተናግረዋል። በዚሁም ንግግራቸው ለጌታ ዳግም ምጽዓት የቀረው ጊዜ ቢበዛ ወይም ቢያንስ 37 አመታት ያህል ነው ሲሉ በመጽሐፋቸው የነገሩንንም አጽንተውልናል። ይህ ግን በጥንቃቄ ላስተዋለው ቀደም ሲል በመጽሐፋቸው ካስታወቁት እምነትና አቋማቸው እምብዛም ያልተለየ እንደሆነ ግልጽ ነው።
እንዲህ ያሉ ታሪካዊ ስህተቶች በቀደመው የቤተክርስቲያን ዘመን የመለመዳቸውን ያህል አሁንም ወደፊትም መኖራቸው አይቀሬ ነው። መጻኢነት የተሰኘው የዘመን ቆጣሪው የነገረ ፍጻሜአዊ ሥነ መለኮት የዚህ ሁሉ ታሪካዊ ቅዠትና መላምት ወላጅ አባቱ ነው። አሳዛኝ የሆነውና ከነዚህ ቁልል ስህተቶች የምንማረው አንድ ዋና ነጥብ ግን በአመለካከታችን እና በአስተምህሮአችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለመሆን ባልወደድንና ልማዳዊውን አስተሳሰብ ባልመረመርን መጠን፣ ምን ያህል ልንሳሳትና ሌሎችንም ልናሳስት እንደምንችል፣ ከዚህም በላይ ከስህተታችን ልንታረምም የማንችል ሆነን ልንዘልቅ እንደምንችል ነው።
እነዚህን ሁሉና መሰል ግራ መጋባቶች በተመለከተ ያለው አሳዛኝ ነገር የዮሐንስ ራዕይን እና የአዲስ ኪዳንን ትንቢቶች ግልጽ ዓላማ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፣ በራእይ መፅሐፍ ውስጥ ያለው ዓላማ ግን መደበቅና ግራ ማጋባት ሳይሆን መግለጥ ነው፡፡
♦ የኀላፊዊያን አመለካከት፡- ይህ አመለካከት ከፊል እና ሙሉ የኃላፋውያን ጎራ ተብሎ ለሁለት ይከፈላል፣
ከፊል ኃላፋውያን የተባሉት የዮሐንስ ራዕይ ሁሉም ትንቢቶች ሳይሆኑ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ቀደም ሲል ተፈጽመዋል ብለው የሚረዱ ናቸው፡፡ መላው የራዕይ መጽሐፍ እስከ ምዕራፍ20 ያለው ተፈጽሞአል ብለው ያምናሉ፡፡ አሁን ያለውን ጊዜ የምዕራፍ 20 የሺህ አመት መንግስት እንደሆነና በዚያ ዘመን ውስጥ እንዳለን ያዩናል፡ ፡ በአብዛኛው ታሪካውያን ከተሰኘው የአመለካከት ጎራ ጋር የሚመሳሰልበት ቅርጽ ያለው ሆኖ በሺህ ዓመት መንግስት ላይ የድህረ ሺህ ዓመት መንግስትን /Post millenialism/ እና የአልቦ ሺህ ዓመት መንግስትን /Amillenialism/ አቋም በተለዋዋጭ ሲያንጸባርቁ ይስተዋላል፡፡
ሙሉ ኃላፋዊያን ደግሞ ሁሉም የዮሐንስ ራዕይ ትንቢቶች ሙሉ ለሙሉ አንድም ሳይቀር ተፈጽሞአል ብለው የሚረዱ ናቸው፡፡ ሙሉ ኀላፋውያን አሁን በምዕራፍ 21 እና 22 በተገለጠው አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ውስጥ እንዳለን ያየናል፡፡ ይህንን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የምናየው እንደ መንፈሳዊ እውነታ /spiritual reality/ ነው እንጂ እንደ ተዳሳሽ አካላዊ ተምኔት /physical utopla/ አድርገን አይደለም፡፡ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የሚናገርለት ትንቢት ከራሱ ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ ያሉትን ጉዳዮችና ሁነቶች ሲሆን፤ በሙሉ ኃላፋውያን እይታ እነዚህ ጉዳዮች ቀደም ሲል በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ያኔውኑ የተፈጸሙ ናቸው ማለት ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ኃላፋዊ /Preterist/ የተሰኘው ቃል አልፎአል እንደማለት ነው፡፡
ከላይ ባየናቸው የተለያዩ የአመለካከት ጎራዎች ተመድበው የዮሐንስ ራዕይን መጽሐፍ ለመተርጎም የሰሩ በርካታ ምሁራን በወንጌል አማኞች ዘንድ እንዳሉ ይታወቃል፣ ነገር ግን በአብዛኛው የሚበዙት አብያተ ክርስቲያናት ወይ የመፃኢነትን አልያም በታሪካዊው ጎራ የሚመደቡትን የከፊል ኃላፋዊነትን አመለካከት የሚቀበሉ ናቸው፡፡ በዚህ ትምህርት እኔ በግሌ ቀዋሚ የሆነ ትርጉምን ይከተላል፣ ጌታ ኢየሱስንም እግዚአብሔር በወንድሞቹ መካከል ቀብቶ እንዳስነሳው እውነተኛና ታማኝ ነብይ ያከብረዋል፣ የእግዚአብሔርን ቃል ታማኝነትም ያረጋግጣል ብዬ በማምነውና አቋም በያዝሁበት በሙሉ ኃላፋውያን አመለካከት አንጻር የዮሐንስ ራዕይን መጽሐፍ ለመተርጎም እጥራለሁ፡፡ ምናልባት ብዙ ሰዎች የመፃኢነትን ጎራ የሚከተሉ በመሆናቸው እና ከነጭራሹም የኃላፋዊነትን አመለካከት ሰምተው ስለማያውቁ ጉዳዩን እንግዳ አድርገው ሊመለከቱት ይችሉ ይሆናል፡፡ ቢሆንም በልብ ስፋት ሆኖ ጉዳዩን ማጤን ምሁራዊ አካሄድ ይመስለኛል፡፡
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች /commentators/ የራዕይን መጽሐፍ ሲተረጉሙ መሰረታዊ የሆነውን የሥነ- አፈታት መርህ /basic hermeneutical principle/ ይተላለፋሉ፤ ይኸውም የተደራሲያኑን ወቅታዊና አውዳዊ ገጽታ የመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን እና አንባቢዎች መጽሐፉን እንዴት እንዳነበቡት እና እንደ ተረዱት ፈልጎ የማግኘት ጥበብ ነው፡፡ የወንጌል አማኝ ተርጓሚ ትኩረቱ መሆን ያለበት የመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን በነበሩበት ታሪካዊ ሁኔታ እና በአውዳቸው ብርሃን ውስጥ ሆኖ የምንባቡን ግስ መረዳት እና ማየት ነው፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፉ የተጻፈላቸው ሰዎች እነ ማን ነበሩ? የሚለው ሲሆን የተጻፈውም በመጀመርያው ከፍለ ዘመን ላይ በአንድ ወቅት በተመሳሳይ የመልክዓ ምድር አሰፋፈር በአንድ ተመሳሳይ አካባቢ እዚህም እዚያም በተንተን ብለው ይገኙ ለነበሩ ሰባት ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት ነበር፡፡
አውድን ለይቶ የሚያሳዩንን ቢያንስ ሦስት ጉዳዮችን ከዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ማውጣት ይቻላል፣ ይኸውም የመጀመሪያዎቹን ተደራሲያን እና የነበሩበትን ሁኔታ አጽንኦት የሚሰጡ ናቸው፤ እነዚህም ሶስት ጉዳዮች የኃላፋውያን አመለካከት ወደ ሆነው የትርጉም አቅጣጫ የሚወስዱን ናቸው፡ ፡
1. ራዕ 1÷ 4 “ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት”፤ በማለት ዮሐንስ በተለይ የሚጽፈው ተለይተው ለሚታወቁ እና በዘመኑ ለነበሩ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት ነው፣ በራዕይ 1÷ 11 "የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊልድልፍያም ወደ ሎዶቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ።" የነዚያን ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት ስም ዝርዝር ይገልጻል፡፡ ዮሐንስ የሚጽፈው በተደጋጋሚ በየዘመናቱ እየተለዋወጡ ለሚመጡ ተደርሲያን አይደለም፣ ይልቁንም የሚጽፈው በአንድ ወቅት በታሪክ ለሚታወቁ አብያተ ክርስቲያናት ነው፡ ፡ ምዕራፍ ሁለት እና ሦስት ለነዚሁ አብያተ ክርስቲያናት በግል በየአድራሻቸው የተፃፉላቸውን መልዕክቶች የሚመለከቱ እና የነበሩበትን አይነተኛ ታሪካዊ ሁኔታ በተመለከተ ለአውዳቸው የተነገሩትን ጉዳዮችን የያዙ ምዕራፎች ናቸው፡፡
2. ዮሐንስ ለነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የሚጽፈው እንዲያውቁ እና እንዲረዱ ነው፡፡ ዮሐንስ ሲጽፍ ሙሉ በሙሉ በጽሑፉ የነበረው እቅድ ለመግለጥ እና ራዕዩን ለማሳወቅ ነው፤ /በግሪኩ apakolopsis/ ማለትም የተሸነፈነውን አንስቶ መግለጥ እና ገልቦ ማሳየት ነው፡፡ ዮሐንስ የጻፈው እውነትን ለመሸፈን ሳይሆን ለመግለጥ ነው፡፡ በራዕይ1÷ 3 ላይ "ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው"፤ ሲል ተደራሲያኑ እነዚያን መርሆዎች ከራሳቸው ጋር ያዛምዱ ዘንድ ከመረዳት ጋር እንዲሰሙአቸው ይጠባበቃቸዋል፡፡ ለሁሉም ለሰባቱም አብያተክርስቲያናት "መንፈስ ለአብያተ ክርስቲናናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይሰማ" ይላል፡፡
3. በራዕይ 1÷ 9 ላይ "እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ"፣ በማለት ዮሐንስ ከተደራሲያኑ ጋር የመከራ ተከፋይ መሆኑን ይናገራል፡፡ ዮሐንስ እና ተደራሲያኑ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉም ራዕዩ በተጻፈበት ጊዜ አብረው በመከራ ውስጥ እያለፉ ነበር፡፡ ሌላው ራዕዩ በተጻፈበት ዘመን የነበረው የዚያን ጊዜውኑ ወቅታዊ መጠባበቅ አግባብነት ካለው ከተደራሲያኑ ወቅታዊና ትክክለኛ ሁኔታ ጋር አንድ ላይ ተጣምሮ ኃላፋውያን በራዕይ መጽሐፍ ላይ ላላቸው አመለካከት ጠንካራ ድጋፍ ይሆናል፡፡
በራዕይ 1÷ 1 ላይ "ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ" በማለት ዮሐንስ ይህ የራዕዩ መጽሐፍ ትንቢት በአጭር ጊዜ ውስጥ "ቶሎ" የሚፈጸም እንደሆነ በግልጽ ይነግረናል፡፡ ይህንም እውነት በተለያዩ የቋንቋ አጠቃቀምና አገላለጽ ሲያጸናው እናያለን፡፡ በጉዳዩም ላይ ምንም አይነት ግራ መጋባት እንዳይኖር በራሱ የአገላለጽ ዘይቤ በጥንቃቄ እውነታውን ይነግረናል፡፡
በራዕይ 1÷ 1 ላይ "ቶሎ" ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል ታኮስ /tachos/ ይባላል፡፡ በአርንደት እና በጊንግሪች የግሪክ መዝገበ ቃላት /lexicon/ መሰረት tachos የተሰኘው ቃል ሰባ ሊቃናት በተረጎሙት የግሪክ ብሉይ ኪዳን መፃህፍት /LXX/ ውስጥ እና በአንዳንድ የቅዱሳት መፃህፍት ክፍል ሆነው ባልተካተቱ /non-canoanical/ ጽሑፎች ውስጥ ጥቅም ለይ የዋለው ፍጥነትን፣ ችኮላን ፣ ፈጣን የሆነን ጉዳይ፣ ጥድፊን፣ ሳይዘገይ የሚፈጸምን ነገር ለማመልከት ነው፡፡ ይህንኑ ተመሳሳይ ቃል ዮሐንስ በራዕይ 2÷ 16፤ 3÷ 11፤ 22÷ 6፣ 7፣ 12፣ 20 ላይ ጥቅም ላይ አውሎታል፡፡
ሌላው ዮሐንስ የሚጠቀምበት የግሪክ ቃል "ቀርቦአልና" ተብሎ በራዕይ 1÷ 3 እና 22÷ 10 የተተረጎመው የግሪኩ ቃል ኤንጉስ /engus/ ነው፡፡ ይህ ቃል የሚያሳየው የጊዜውን ቅርበት ሲሆን ዮሐንስም ደግሞ የጠቅላላ መጽሐፉ ማዕቀፍ /ቅንፍ/ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡
ሶሰተኛው የግሪክ ቃል ሜሎው /mello/ ሲሆን ይኸውም በራዕይ 1÷ 19 እና 3÷ 10 ላይ "ይሆን ዘንድ ያለውን" እና "ሊመጣ ያለው" /በእግሊዘኛው"about to"/ ተብሎ የተተረጎመው ቃል ነው፡፡ በራዕይ 1÷ 19 "ይሆን ዘንድ ያለው" የተሰኘው ሃርግ ቀጥተኛ ትርጉም "ሊከሰቱ ያሉ ነገሮች" እንደማለት ሲሆን በ 3÷ 10 ላይም "በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው" የሚለው ቀጥተኛ ትርጉሙ በዓለም ላይ ሊደረስ ያለው ነገር ማለት ነው፡፡
እንግዲህ የተደራሲያኑን ወቅታዊ ሁኔታ በትርጉም መርሃችን ውስጥ መጠቀማችን ለትክክለኛና ተገቢ ለሆነ ሥነ አፈታት ቁልፍ ጉዳይ ከሆነ ታዲያ እነዚያ የመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን እነዚህን ከላይ ያየናቸውን ቃላት በዚያ ለእነርሱ በተጻፈላቸው የራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ሲመለከቱ ምን የሚያስቡ ይመስላችኋል?
ዮሐንስ እነዚህን ቃላት እና ሃረጎች በመግቢያው ላይ እና በመጽሐፉ ማጠቃልያ ላይ የተጠቀመው በዓላማ ነው፡፡ ዮሐንስ እነዚያን ሰባቱን አብያተ ክርስቲያናት የሚነግራቸው በራዕዩ የተካተቱትን እነዚህን ነገሮች እነርሱ ባለብት በማንኛውም ጊዜ ሊፈጸሙ የሚችሉ አድርገው እንዲጠባበቁአቸው ነው፡፡
አንዳንዶች ግን እነዚህን ቃላት የራሳቸውን ሥነ መለኮት ለመከላከል ሲሉ በራሳቸው መንገድ ሊተረጉሟቸው ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ አንድ ዘመን ቆጠሪ /Dispensationalist/ የሆነ ጸሐፊ በራዕይ 1÷ 1 ላይ ያለውን /tachos/ የተሰኘውን ቃል አጠቃቀም ሲያብራራ "ኃሳቡ የሚነግረን እነዚያ ሁነቶች ያኔውኑ ቶሎ የሚፈጸሙ ነገሮች መሆናቸውን ሳይሆን ዳሩ ግን በሚሆኑበት ጊዜ መሆን ሲጀምሩ የሚሆኑት ወዲያውኑ በፍጥነት ነው" ብሎ ተናግሮአል፡፡ ጥያቄው ግን ለነዚያ በጽኑ መከራና ሥደት ውስጥ ለነበሩ የመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን ይህ ትርጉም ምን ዓይነት መጽናናትን ሊያመጣላቸው ይችላል? የሚለው ነው፡፡ በእውነቱ እነዚህን ምንባባት ዋቢ አድርጎ፣ 'ከተወሰኑ ሁለት ወይም ሶስት ሺህ ዓመታት በኋላ ገና ወደ ፊት በፍጥነት ኢየሱስ ይመጣል' ብሎ መተርጎም በነዚያ በመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን ታሪካዊ ሁኔታ ላይ ማለትም በመከራቸውና በስደታቸው ላይ እንደ መቀለድ ይቆጠራል፡፡
ምክንያቱም፣ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የኢየሱስን ምጽዓት የሚያስተዋውቀን እንደ እረፍት አድርጎ ነው፤ 'ከተወሰነ ሺህ ዓመታት በኋላ እርሱ አንድ ጊዜ መምጣት ከጀመረ በፍጥነት ይመጣል' የሚለው የመጻእያን ትርጉም ግን ለመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን ምንም መጽናናት የማይሰጣቸው ሆኖ የሚደመጥ ይሆናል፡፡ ይህ ከላይ የጠቀስነው ዘመን ቆጠሪ ጽሐፊ 'tachos' የተሰኘውንና በፊልጲ 2÷19 "ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ" ተብሎ የተጻፈውን ቃል እንዴት ሊተረጉመው ይሆን? ታዲያ ይህ ማለት መቼም ጊዜ ቢሆን ጢሞቴዎስ ወደ እነርሱ ሲመጣ እየተጣደፈና እየሮጠ ይመጣል ማለት ይሆንን?
ኃላፋዊ በሆነው የነገረ ፍፃሜ ትምህርት አመለካከት ላይ የሚሰነዘረው ዋነኛ ተቃውሞ የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽዓት በተመለከተ ነው፡፡ በርካታ የዚህ የራዕይ መጽሐፍ ክፍሎች የክርስቶስን ምጽዓት በተመለከተ የያዙአቸው ጥቅሶች /ራዕ2÷ 16 ፤ 3÷ 11፣ 22÷7/ "እነሆ በቶሎ ብዬ እመጣለሁ" የሚሉ ናቸው፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን መጥቶ ነበርን? እኔ እንደመጣ አምናለሁ። ልክ እንደተናገረው መጥቶአል፡፡
ይህ ወደ ተከታዩ ጥያቄ ማለትም ወደ ጭብጥ መልዕክቱ የሚያንደረድረን ሃሳብ ነው፡፡ እርሱን ለቀጣዩ ጽሁፌ አሳድሬ ከዚያ በፊት ግን ከፊል ኃላፋውያን እነዚህን ጥቅሶች "በእስራኤል ላይ የሚሆነውን የእርሱን የፍርድ አመጣጥ ብቻ ያመለክታሉ እንጂ ዳግመኛ ምጽዓቱን አይደለም" ማለታቸውን አስተያየት ሰጥቼበት ልለፍ፡፡ በእውነትም የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ በእስራኤል ላይ እርሱ በፍርድ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ የራዕዩን ጭብጥ መልዕክት የሚነግረን ጥቅስ እንዲህ ይላል፦
ራዕይ 1÷ 7 "እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን ፥ አሜን"
ይህ ቃል አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ አገላለጽ ሆኖ እግዚአብሔር በፍርድ ሲመጣ ያለውን የብሉይ ኪዳንን የደመና አመጣጥ ያመለክታል። እነሆ የብሉይ ኪዳን ማስረጃ፡-
መዝ 104÷ 3 "እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሰረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ"
ኢሳ 19÷ 1 "ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።"
በመዝ 18÷ 7 እና ኢዩ 2÷ 1-2 ያለውም የደመና መምጣትን በተመለከተ የተነገሩ ናቸው፡፡ በራዕይ 1÷ 7 ላይ የተነገረው የክርስቶስ መምጣት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን እስራኤል ላይ የሚያተኩር የፍርድ መምጣት ነው፡፡ የሚመጣውም በእነርሱ በወጉት ላይ ነው፡፡ የመምጣቱ ውጤት ደግሞ ፍርድ ነው፣ "የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ" 'ምድር' የሚለው በግሪኩ ትርጉም 'ghay' ሲሆን ትርጉሙም አፈር፣ ሃገር፣ መሬት፣ ምድር፣ ዓለም ማለት ነው፡፡
"እንግዲህ ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ" ሐዋ2÷36
ኢየሱስ ለአይሁድ አለቆች ሲነግራቸው እነርሱ በግል የሚመጣው ፍርድ ምስክሮች እንደሆኑ ነግሯቸዋል፦
ማቴ 26÷ 63-64 "ሊቀ ካህናቱም አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው። ኢየሱስም፦ አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው።"
በ70 ዓ.ም የሆነው የኢየሩሳሌም መፈራረስ ኢየሱስ ለነዚያ ታሪካዊ ሰዎች በደመና እንደመጣ ማስረጃ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን በእስራኤል ላይ እንደሆነ የፍርድ መምጣት ብቻ ነው የምናየው። ቀዋሚ የሆነውን ትርጉም የሚከተሉ ሙሉ ኃላፊውያን ይህንንው በእስራኤል ላይ የሆነውን የ70ውን ዓ.ም የፍርዱን መምጣት እንደ ክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዓት ያዩታል፡፡ ምክንያቱም ከፍ ሲል በተጠቀሱት የብሉይ ኪዳን ምንባባት የተገለጸው በደመና የሆነ አምላካዊ አመጣጥ በፍርድ የሆነ መምጣት ከሆነ፣ አዲስ ኪዳንም ብሉይ ኪዳን የማያውቀውን ሌላ አይነት በደመና መምጣት አያስተዋውቀንም። መጻእያን የሚጠብቁት ያለው የጌታ በደመና መምጣት ባህርዩና ተፈጥሮው ለአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንግዳና ባእድ የሆነውን አይነት አመጣጥ ነው።
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዱ ገና በሕይወት እያሉ እንደሚመጣ ሲናገር በእስራኤል ላይ ለመፍረድ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን በአባቱ ክብር ከመላዕክቱ ጋር ሲመጣ ለሁሉም ሰው ዋጋውን እንደሚያስረክብ ደግሞ ይናገራል።
ማቴ 16÷ 27-28 "የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያንጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።"
ራዕ 22÷12 "እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።"
ክርስቶስ በመምጣቱ በክፉዎች ላይ ፍርድን ሲያደርግ ለጻድቃን ደግሞ ብድራት ይሰጣል፣ ይኸውም የሚሆነው በቶሎ ነው፡፡ በማቴዎስ 13 ላይ በተነገረው የእንክርዳዱ ምሳሌ እንደምናየው የክፉዎቹ ፍርድ እና የጻድቃን ብድራት በአንድ ጊዜ የሚሆን ነው፡፡
ማቴ 13÷30 "ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ።"
እዚህ ላይ እንደምናየው የኢየሩሳሌምን መፈራረስ የሚያመለክተው የእንክርዳዱን በፍርድ መቃጠል ብቻ ሳይሆን ፣ ነገር ግን ጻድቃንም በአብ ጎተራ ይሰበሰባሉ፡፡
ማቴ 13÷ 36-43 "በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።"
ከፊል ኃላፋውያን እንደ መጻእያን ሁሉ ይህ መሰባሰብ ገና ወደ ፊት በሚሆነው ዳግም ምጽዓት ጊዜ ማለትም 'ሶስተኛው ምጽዓት' በሚሉት ወቅት ይፈጸማል ይላሉ፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሚሆነው የኢየሩሳሌም ፍርድ በሚሆንበት ጊዜ እንደሆነ በግልጽ ያስተምራል፡፡ ይኸውም በአሮጌው ኪዳን በአሮጌው ዓለም ፍፃሜ ላይ ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ዳግመኛ ምጽዓት አንድ ጊዜ ብቻ የሚሆን የመጨረሻ ምጽዓት ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ጨምሮ ሲያስተምር ጻድቃንም ክፉዎችም ሁለቱም በዚያው ቀን ከሙታን ይነሳሉ፡፡ በተሰሎንቄ መልዕክት በክርስቶስ የሞቱ ሰዎች እርሱ በሚመለስበት በዚያው ቀን እንዲነሱ እናያለን፦
1ተሰ 4÷ 16። "ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤"
ይህ ትንሳኤ በዮሐንስ ወንጌል እንደ ተብራራው የሚሆነው በመጨረሻው ቀን ላይ ነው፣ ይኸውም የሚያመለክተው የአሮጌው ኪዳን እስራኤል የመጨረሻውን ቀን ነው።
ዮሐ 6÷ 40 "ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።"
እንደ ዮሐንስ ወንጌል ከሆነ ለክፉዎችም ደግሞ የትንሳኤ ቀን ተጠብቆላቸዋል፦
ዮሐ5÷ 28-29 "በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።"
ይህ ትንሳኤ የሚሆንበት ጊዜ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ እጅግ ርቆ ያለ ጊዜን የሚመለክት አይደለም፡፡ ጊዜው የሆነው እና የደረሰው በዚያው ትውልድ ወቅት ነው።
ዮሐ 5÷ 25 "እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።
የጻድቃን መሰብሰብና ትንሳኤ የኃጢአተኞችም ፍርድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገና ተመልሶ በሚመጣበት በዚያው አንዱ የመጨረሻ ቀን ላይ የሚሆን ነው ብለን መደምደም እንችላለን፡፡ ግልጽ በሆነው የቃሉ ትምህርት የሙታን ትንሳኤን ተፈጥሮ እና አይነቱን የሚወስነው ያው ለትንሳኤ የተቀጠረው ጊዜ ነው፣ ጊዜውን ስናውቅ ተፈጥሮው ላይ ግራ አይገባንም። ጊዜውም የመጨረሻው ቀን ነው። የመጨረሻውም ቀን አሮጌው ኪዳን የሚደመሰስበትና የሚወገድበት የእስራኤል የፍርድ ቀን ነው። ከዚህ የተለየ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ሌላ የመጨረሻ ቀን፣ ከመጨረሻውም ቀን ያለፈ ሌላ ትንሳኤ የለም።
በኢየሩሳሌም መፈራረስ የሆነው የጌታ ምጽዓት በፍርድ በደመና የሆነው ዳግመኛ ምጽዓቱ ነው፣ ይኸውም የሆነው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ነበር፡፡ በክፉዎች ላይ ሊፈርድ እንዲሁም ቅዱሳኑን ሊሰበሰብ መምጣቱ ለነዚያ ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ምዕመናን መጽናናታቸው ነበር፣ እነርሱም አግዚአብሔር በእርሱ መምጣት እረፍትን እንደሚሰጣቸው እየጠበቁ ነበር፡፡
2ተሰ1÷ 6-10 ደግሞ "እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤ ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው። ከእናንተ ወጥቶ የጌታ ቃል በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አልተሰማምና፥ ነገር ግን ምንም እንድንናገር እስከማያስፈልግ ድረስ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚሆን እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል። እነርሱ ራሳቸው ወደ እናንተ መግባታችን እንዴት እንደነበረ ስለ እኛ ይናገራሉና፤ ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ፥ ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥ ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።"
ይህ ዳግመኛ ምጽዓት ፍርድን የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን የቅዱሳኑ መሰብሰብም ደግሞ ነው ሲል ይነግራቸዋል፡፡
2ተሰ 2÷1 "ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን"
በማቴዎስ 24÷29-31 ኢየሱስ በእስራኤል ላይ ለመፍረድ በዚያ ዘመን ማለትም በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ በነበሩ ትውልድ፣ ያኔ የነበሩትን ቅዱሳኑን ሊሰበስብ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሯል፡፡ በ1ኛተሰ 4÷ 16-17 ጳውሎስም ጌታ ቅዱሳኑን ሊሰበስብ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡
እንግዲህ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ አለ፡- በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከመላዕክቱ ጋር በእሳት፣ በኃይል፣ በስልጣን እና በክብር የሆነ የጌታ ምጽዓት ስንት ጊዜ ነው? አንድ ጊዜ ብቻ ነው፣ እርሱም የሆነው በ70 ዓ.ም ላይ ነው፡፡
የሥነ ፍታቴ ቀዋሚነት የሌላቸው ከፊል ኃላፋዊያን በሁለት የክርስቶስ ምጽዓቶች የምናሉ፣ አንዱ በ70 ዓ.ም እስራኤል ላይ ለመፍረድ መምጣቱን ሲሆን ነገር ግን ዳግሞ ሌላ ገሃዳዊ የሆነ የመጨረሻ የክርስቶስ ምጽዓት ገና ወደ ፊት ይሆናል ብለው ይጠብቃሉ፡፡ ይህም ማለት ገና አሁንም ከሕግ በታች፣ ከአሮጌው ኪዳን በታች እንደሆንን ያምናሉ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ገና ስለ አሮጌው ኪዳን እስራኤል የተነገረው ሰማይና ምድር እስኪያልፉ ድረስ በሥራ ላይ ነው ማለት ነው፡፡
ማቴ 5÷17-18 "እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።"
1ተስ 4-5 እና ማቴ 24 በአንድነት የሚናገሩት ስለ አንዱ መምጣት ስለ አንዱ ፍርድ እና ትንሣኤ ነው፡፡ ለሶስተኛ ምጽዓት ምንም አይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ የለም፤ ኢየሱስ እመጣለሁ ብሎ የተናገረለት ብቸኛ መምጣት በዚያው ትውልድ የሚሆነው መምጣቱ ነው፡፡ ይኸውም ፈጥኖ፣ በቶሎ፣ በቅርቡ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሆናል የተባለው ነው፡፡
ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የራዕይን መጽሐፍ እንዴት እንደሚዘጋው ስሙ፦
ራዕ 22÷ 6-7 "እርሱም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ"
ራዕ 22÷ 10 "ለእኔም ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።"
ራዕ 22÷ 12 "እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።"
ራዕ 22÷ 20-21 "ይህን የሚመሰክር አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።"
ፈጥኖ በቅርቡ እንደሚመጣ ከዚህ በተሻለ ግልጽነት አጽንቶ ሊናገር ይችላልን? በ70 ዓ.ም የሆነው የኢየሩሳሌም ጥፋት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ውስጥ ያለ የአቃቤ እምነት ዓብይ ነጥብ ነው፣ ምክንያቱም የዚያ ትውልድ ያ ሕዝብ በዘመኑ መጨረሻ በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ በፍርድ ሲመጣ እንደሚያዩት ኢየሱስ በግልፅ ተናግሮአል፡፡ ዮሐንስም ደግሞ እነዚህ በራዕዩ ያያቸው ሁነቶች በሙሉ እርሱ ራዕዩን ከጻፈ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፈጥነው ወይም በቶሎ እንደሚፈጸሙ ይጠብቅ ነበር፡፡
እንግዲህ የሙሉ ኃላፋውያን አቀራረብ የራዕይ መጽሐፍ በመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን ብርሃን ቀዋሚነት ባላቸው ሥነ ፍታቴ መተርጎሙ እጅግ የተሻለው ምርጫ ነው፣ ብዬ የራሴን አቋም ይዣለሁ፡፡ የራዕይ መጽሐፍ የተጻፈው በትንሹ እስያ ለነበሩ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ሲሆን የሚነግራቸውም በእነርሱው ዘመን በቅርቡ ቶሎ ሊፈጸሙ እና ሊሆኑ ስላሉት ነገሮች ነው፤ "ቶሎ" ለእነርሱ ነው እንጂ፣ ይህ ቶሎ ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ ላለን ለአኛም ሆነ ከዚህ በኋላ ላሉትም አይደለም፡፡ መጽሐፉ ለእነርሱ በቅርቡ ወደ ፊት የሚፈጸም ትንቢት ነው፡፡ ለእኛ ደግሞ ከሁለት ሺህ አመታት በኋላ ላለን ሰዎች ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የሆኑትን ሁነቶች የሚነግረን ታሪክ ነው ማለት እንችላለን ።
በዚህ በያዝነው የራእይ መጽሐፍ የመግቢያ ጥናት እስካሁን የተነጋገርነውን ለመከለስ ዋና ዋና የሆኑትን ጉዳዮች አንስተን ይህንን የጥናታችንን ክፍል እናጠቃልል።
የዮሐንስ ራዕይን መጽሐፍ መግቢያ በተከታታይ ማየት ጀምረናል፡፡ አሁንም መጽሐፉ ላይ መንደርደርያ ጥናት ማቅረብ እንጂ በጥልቀትና በዝርዝር በሁሉም የመጽሐፉ ክፍሎች ላይ ልንሄድበት የሚያስችለን ዝግጅት ያስፈልገናል። ጌታ ቢፈቅድ ወደ ፊት በሌላ መድረክ እንመለስበት ይሆናል። እስካሁን ባየናቸው የጥናት ክፍሎች ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ስንነጋገር ነበር፣ እነርሱም የመጽሐፉ መክፈቻዎች የተባሉት፣ መቼ ተጻፈ? የሚለውና ተገቢ የሆነው የትርጉም ዘይቤ እና አመለካከት ምንድን ነው? የሚሉት ናቸው፡ ፡
ራዕዩ የተጻፈበትን ጊዜ በተመለከተ ያለውን ጥያቄ አብራርተን ለማየት ሞክረናል፡፡ የዮሐንስ ራዕይ ትርጉም የተንጠለጠለው በ70 ዓ.ም ላይ ከሆነው የኢየሩሳሌም ውድመት "በፊት" ወይም "በኋላ" ላይ የተፃፈ በመሆኑ ላይ ነው፡፡ ጠንካራ የሆኑ ውስጣዊ ማስረጃዎች ቀደም ያለውን ጊዜ የሚጠቁሙ ነጥቦች ናቸው፣ ከማስረጃዎቹም ጥቂቶቹን ለዚህ ጽሁፍ ፍጆታ ለማስነበብተሞክሯል፤ በመሰረታዊነት መጽሐፉ የተጻፈበት ጊዜ ላይ እርግጠኛ መሆን በምንከተለው ሥነ ፍታቴ እና በምንደርስበት የነገረ ፍጻሜ ድምዳሜአችን ላይ ያለው ተጽእኖ ቀላል አይደለም። "የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ከ65-66 ዓ.ም ባለው ጊዜ የተፃፈ ነበር" የሚለው አቋም "ከ95-96 ዓ.ም ባለው ጊዜ ተጽፎአል" ከሚለው አቋም ይልቅ በእጅጉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ ቀደም ያለው ጊዜ ላይ ተጽፎአል ብሎ እንደሚያምነው እንደዚህ የቃሉ ድጋፍ እንዳለው አመለካከት ከሆነ፣ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የሚናገረው ስለ እግዚአብሔር መንግስት የምጥ ጣር፣ የአሮጌው ኪዳን እስራኤል መጨረሻ እና የቤተክርስቲያን ታሪክ ጅማሬን በተመለከተ ነው፡፡
ጨምረንም ያየነው ተገቢ የሆነውን የዮሐንስ ራዕይ የአተረጓጎም ዘይቤ እና አመለካከት ነው፡፡ የዮሐንስን ራዕይ መጽሐፍ ለመተርጎም እስከ አሁን በስፋት የሚታወቁ አራት ዓይነት የአመለካከት ጉራዎች እንዳሉ ተነጋግረናል፡፡ ትኩረታችንንም በተለይ እጅግ ታዋቂ በሆኑት ማለትም በመጻዒያን እና በኃላፋውያን አመለካከቶች ላይ አድርገን ነበር፡ ፡ እንደሚታወቀው የዘመን ቆጣሪነት አመለካት ካሣደረው ተጽዕኖ የተነሣ የመፃዒነት ትርጉም በዘመናችን እጅግ ታዋቂነትን ያተረፈ አመለካከት እንደሆነ አይተናል፣ ተችተንማል፡፡ ይህ አይነቱ አመለካከት በርካታ ወዳጆቻችን የሚከተሉትና ሁሉንም የዮሐንስ ራዕይን ትንቢቶች ገና አሁንም ወደ ፊት የሚፈጸሙ ናቸው ብሎ የሚጠብቅ አመለካከት ነው፡፡
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍን ከሙሉ ኃላፋውያን እይታ አንፃር ደግሞ በመጠኑ ተመልክተናል፡- ይህ አመለካከት በራዕይ መጽሐፍ ወስጥ ያሉ ትንቢቶች በሙሉ እንደተፈጸሙ የሚረዳና የሚያምን ነው፡፡ ይህ አመለካከት ታላቁ መከራ፣ ንጥቀት፣ ትንሳኤ፣ ፍርድ፣ የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዓት፣ ሁሉንም ከእኛ ዘመን በፊት ቀደም ሲል በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ መፈጸማቸውን ያምናል፡፡ እንደ ኃላፋውያን ከሆነ ታላቁ መከራ በ70 ዓ.ም በሮማውያን የተፈጸመው የኢየሩሳሌም ጥፋት ነው፡፡ እስከ አለፈው መቶ አመት እና ከዚያ ወዲህ ካልሆነ በቀር በመላው የቤተ ክርስቲያን ዘመን ውስጥ ይህ የክርስቲያኖች ሁሉ እምነት ሆኖ ኖሮአል፡፡ እንግዲህ ይህንን አመለካከታችንን የመሰረትነው የተደራሲያኑን ማንነትና ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መርህ ላይ ሲሆን፣ ይኸውም ደግሞ የመጀመሪያዎቹ አንባቢዎች ምንባቡን ምን ብለው ተረዱት? ብሎ የሚጠይቅ መርህ ነው፡፡
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ለምትገኝ ወይም በሌላ ከተማ ላለች ማህበረ ምዕመናን በቀጥታ ከኢየሱስ የተላከ ደብዳቤ ቢሆን ኖሮና እናንተም የዚያች ቤተክርስቲያን አባል ብትሆኑ ኖሮ በምዕራፍ 1 ቁ 1 እና 3 ላይ "ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ ..... ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።" ሲል የተፃፈውን ቃል ስታነቡ በእውነት ምን ታስቡ ነበር? በመጽሐፉ የተጠቀሱትን እነዚያን ሁነቶች ቶሎ እንደሚሆኑ ትጠብቃላችሁን? በእርግጥም የኢየሱስን ቃል ካልተጠራጠራችሁ በቀር እንደዚያ እንደምትጠበቁ ይመስለኛል። ልክ እንደዚሁ በቀጥታ ደብዳቤው በአድራሻቸው የተጻፈላቸው እነዚያም የመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን በኖሩበት ዘመን ያለጥርጥር እንዲሁ ይጠብቁ ነበር፡፡
እንግዲህ ይህ መርህ ወደ ተከታዩ የዮሐንስ ራዕይ ቁልፍ ነጥብ የሚያንደረድረን ይሆናል፣ ይኸውም የራዕዩን ጭብጥ መልዕክት የሚያመለከት ነው፡፡ በቀደሙት ጽሁፎቼ ላይ በከፊል የዳሰስነው ኃሳብ ነው። ምናልባት የዚህን ጥናት ቀዳሚ ክፍሎች ካላነበባችኋቸው ቀጥሎ በሚነሱ ሃሳቦች ላንግባባ ስለምንችል ጊዜ ወስዳችሁ ጽሁፎቹን እንድትመለከቷቸው እመክራለሁ። ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እንደሚስማሙበት የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍን ጭብጥ መልዕክት የሚነግረን ቃል በራዕይ 1÷ 7 ላይ ይገኛል፡፡ በሚቀጥለው የጥናት ክፍል እመለስበታለሁ።
∆∆∆∆∆∆∆∆∆∆∆
No comments:
Post a Comment