Monday, November 5, 2018

የጌታ ምጽአት መቼ እና እንዴት ክፍል ሁለት

የጌታ ምጽዓት መቼ እና እንዴት ነው?
በማቴዎስ 24 እንደተገለጸ

መግቢያ፦
የማቴዎስ 24ንም ሆነ በጥቅሉ የትንቢትን ፍጻሜ በራሱ በእግዚአብሔር ቃል ፈትቶ ለመረዳት አስተማማኝ የሆነ የመርህ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ለመነሻ እንዲሆነንም እነዚህን ነጥቦች እንመልከት፦
1. መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢትን በመተርጎም ሂደት ውስጥ ተጨባጭ የሆነ መረዳትን ለማግኘት ሁልጊዜ መመለስ የሚገባቸው ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ፣ እነርሱም፦
ሀ. የትንቢቱ ፍጻሜ ስለሚሆንበት አይነተኛ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?
ለ. የትንቢቱ ፍጻሜ ስለሚሆንበት አይነት/ተፈጥሮ/ ባህርይስ ምን ያስተምራል?
2. በቅድሚያ ትኩረት አድርጌና አድምቼ ላየው የምፈልገው የዳግመኛ ምጽአቱን (parousia) ጊዜው በተመለከተ ነው።
3. በክርስትናው አለም ሁለት አይነት ሰነዶች እንዳሉ ግልጽ ነው፣ እነርሱም፦ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተጻፉ 66ቱ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን  ቅዱሳት መጻህፍት እና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በጉባኤ የጸደቁና በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት ሳይሆን በሰው የተዘጋጁ የእምነትና የአቋም መግለጫ ታሪካዊ ሰነዶች ናቸው። ስለዚህ ጊዜውን በተመለከተ ስንነጋገር የምንመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ደግሞ ውጫዊ የታሪክ መዛግብትንም ጭምር እናያለን።
4. ያም ሆኖ ግን ኃላፋዊ እንደሆነ ፕሪቴሪስት ወንጌል አማኝ የክርስቶስን መመለሻ ጊዜውን በተመለከተ የምንንጠለጠለው መጽሐፍ ቅዱስ በጉዳዩ ላይ በተናገረው ነገር ላይ ብቻ ነው።
5. የጌታ ዳግም ምጽአት በ70 ዓ.ም ላይ እንደሆነ የምናምነው በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት ያልተጻፉ የታሪክ ድርሳናት ስለዘገቡት፣ ወይም የጌታ ዳግም ምጽአት በ70 ዓ.ም ላይ እንደሆነ የማናምነው እነዚሁ ታሪካዊ ድርሳናት ሳይዘግቡት ስለቀሩ አይደለም፤ ይልቁኑ ግን በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ የተነበየው ስለ ሆነ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ ሊሻር አይችልም።
6. ክርስቶስ በ70 ዓ.ም ላይ ልክ በቀኑ እመለሳለሁ ባለበት ሁኔታ እንደተነበየው ሆኖ እንደተመለሰ ለማመን የታሪክ መዛግብት ማረጋገጫ አያስፈልገንም። ይህንን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገን የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው።
7. ክርስቶስ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ውስጥ ይመለሳል ብሎ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ ያስተምራል። እንደዚያ በግልጽ የሚያስተምር ከሆነ ደግሞ፣ እንግዲያውስ፣ ያለ ምንም የታሪክ መዛግብት ማስረጃም ሆነ ሲያሻውም ከታሪካዊ ዘገባ በተቃራኒው ልክ እንደዚያው እንደተጻፈው የተፈጸመ መሆን አለበት። የትኛውም የታሪክ ድርሳናትና ዘገባ ለእግዚአብሔር ቃል ሊገዛ እና ራሱን በቅዱስ ቃሉ ሊያርም እንጂ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ለውድድር ሊቀርብና ሊፎካከር አይመጥንም። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል እስትንፋሰ መለኮት ሲሆን የተቀሩት ሰነዶች ግን ያ ተፈጥሮ የላቸውም።
8. መጻኢያን የእምነት መግለጫዎችንና በአለም ላይ አሉ የሚባሉትን የታሪክ መዛግብት ማስረጃዎችን በተቃውሞ ሊቆልሉ ይችሉ ይሆናል፣ ምንም ያህል በሰው የተደራጁ መግለጫዎችና የታሪክ ድርሳናት ቢቆለሉም በኃላፋውያን ዘንድ ግን አሁንም "ቅዱሳት መጻህፍት ብቻ" ጸንተው እንደቆሙ ናቸው። ይህም አቋም የቤተክርስቲያን አዳሾች እነ ማርቲን ሉተር ይዘውት የነበረ አቋም ነው። ይህንን ምሳሌ ከተሃድሶው ታሪክ ላካፍላችሁ፦
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መምህራን ማርቲን ሉተርንና የቤተክርስቲያን አዳሾችን አስተምህሮ ለመቃወምና ውድቅ ለማድረግ፣ የተጀመረውንም የወንጌላውያን የተሃድሶ እንቅስቃሴ ሃሰት ነው ብሎ ለመፈረጅና ሉተርን ለማውገዝ፣  ጥንታውያኑን የእምነት መግለጫዎችና አጠቃላዩን የቤተክርስቲያን ታሪክ ለክርክራቸው ይጠቀሙበት እንደነበር ከተሃድሶው ታሪክ እንረዳለን። ንጉሱ ቻርልስ አምስተኛም በሉተር የተሃድሶ አስተምህሮ ላይ አስተያየት ሲሰጥ "ከወንድሞች አንድ ግለሰብ ብቻውን መላውን የክርስቲያን ማህበረሰብ ተቃውሞ ቢቆም ስህተት መሆኑ የተረጋገጠ ነው፣ አለበለዚያ ላለፉት ሺህ አመታትና ከዚያ በላይ ክርስትና ተሳስቶ ነበር ማለት ነው" ሲል ሉተርን እየነቀፈ ተናግሮ ነበር።  ልክ እንደዚሁ ዮሐነን ኤይክ ሉተርን ተቃውሞ ባቀረበውና ዘለፋ በተሞላበት ክርክሩ "ቅዱሳት መጻህፍትን ጠቅሰህ እንድትደመጥ የምታቀርበው ልመና ሁልጊዜ በመናፍቃን ሲተገበር የነበረ ተግባር ነው። እጅግ የተከበሩና ታዋቂ የሆኑ ሰዎች እዚህ እያሉ እንዴት አንተ ከእነሱ የተሻለ እንደምታወቅ አድርገህ ስለ ራስህ ታስባለህ? ቅዱሳት መጻህፍትን የምትረዳ አንተ ብቻ እንደሆንክ ስለሚመስልህ ጥያቄ እንኳ ለማቅረብ ምንም መብት የለህም። እውነተኛ ሕግ ሰጪ የሆነው ክርስቶስ ባቋቋመው፣ በመላው አለም በሐዋርያት ሲታወጅ በነበረው፣ በሰማእታቱ ደም በታተመው፣ በቅዱሳን የአብያተ ከርስቲያናት የጉባኤ ውሳኔ በጸናው፣ ሁሉም አባቶቻችን እስከ ሞት ድረስ የታመኑለት ተብሎ በቤተክርስቲያን ሲገለጥ በኖረው በተቀደሰው ቀጥተኛና ትክክለኛ እምነት (Orthodoxy) ላይ የገዛ ራስህን ፍርድና ውሳኔ ልትጭን ትወዳለህን?" ነበር ያለው።
በነዚህ የማርቲን ለተር ተቃዋሚዎች ብይን ይሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ይመስለኛል፣ ለሺህና ከዚያ በላይ ለተቆጠረ አመታት የኖረ የቤተክርስቲያንን ታሪክና ጥንታውያኑን የእምነት መግለጫዎች የሚያፋልስ ማንኛውም አስተምህሮ የስህተት ትምህርት ነው ማለት ነው። የተሃድሶው እንቅስቃሴ አስተምህሮ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ለሺህ አመታትና ከዚያ በላይ ሲታመን የነበረውንና ጥንታዊውን የእምነት መግለጫ የሚያፋልስ ነበር ማለት ነው። ስለዚህም በዚህ አተያይ የተሃድሶው እንቅስቃሴ አስተምህሮ የስህተት ትምህርት ነበር ማለት ነው። ተቃዋሚዎቹ ሉተርንና አብረውት የቆሙትን በቅዱሳት መጻህፍት መሰረት ሊሞግቱአቸው ባለመቻላቸው የተሃድሶውን አስተምህሮ ውድቅ ለማድረግ ከቅዱሳት መጻህፍት ርቀው የተንጠለጠሉት በቤተክርስቲያን ታሪክና በጥንታውያኑ የእምነት መግለጫዎች ላይ ነበር። ያም ሆኖ ሉተር በተቃውሞ የተሰበሰበበትን ጉባኤና የጉባኤው ውሳኔ የተንጠላጠለባቸውን ጥንታውያን የእምነት መግለጫዎች ውድቅ አደረጋቸው። ይህንንም ያደረገው እነዚያን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በጉባኤ ውሳኔ የተዘጋጁ እንጂ በእግዚአብሔር እስትንፋስ ያልተሰጡ የእምነት መግለጫዎችን ስለማያከብራቸው ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ተክተው የሙግት መሰረት እንዲሆኑ ስላልፈለገ ነው
ሃሳቤን ግልጽ ለማድረግ ዛሬም ቢሆን  በነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ላይ የምንከተለውን ትርጉምና አቋም ውድቅ ለማድረግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ፣ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ እኩያ አድርጎ፣ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ እስበልጦ፣ ወይም በመጽሐፍ ቅደስ ላይ ጨምሮ፣ ጥንታውያኑን የእምነት መግለጫዎችና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የሙግት መስረት ማድረግ ትክክል ነው ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ፣ እንግዲያውስ ንጉሱ ቻርልስ አምስተኛና ዮሐነን ኤይክ በጥንታውያኑ የእምነት መግለጫዎችና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ ሙግታቸውን መስርተው የወንጌላውያኑን የተሃድሶ አስተምህሮ ኑፋቄ ነበር ብለው መበየናቸው ትክክል ነበር ማለት ነው። ስለዚህ በእምነት መግለጫዎችና በቤተክርስቲያን ታሪክ ተመርምሮ በጥንታዊት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መመዘኛ በጉባኤ የተወገዘ የወንጌላውያኑ ቤተ እምነት አባል የሆነ ሁሉ መናፍቅ ነው ማለት ነው።
ስለዚህ ይህንን ልብ እንበል፦ በታሪካዊ መዛግብትብና በእግዚአብሔር ቃል መካከል ተቃርኖ ያለ ቢመስል እንኳ፣ ድካሙ ወይም ውድቀቱ ያለው  በራሱ በታሪክና በመዛግብቱ በኩል ወይም ታሪክን ከምንመለከትበት አተያይ፣ ወይም የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረውን በአግባቡ ካለመረዳታችን የተነሳ  ነው እንጂ፣ ችግሩና ድካሙ ፈጽሞ በእግዚአብሔር ቃል በኩል አይደለም። "ሰው ሁሉ ውሸተኛ እግዚእብሔር ግን እውነተኛ ይሁን" እንደተባለ ምንግዜም ቢሆን የእግዚአብሔር ቃል ከየትኛውም የታሪክ መዛግብትና ድርሳናት፣ በጉባኤ ውሳኔም ከተመሰረቱ መግለጫዎች በላይ እና ያለእነርሱ ድጋፍ ብቻውን እውነት ሆኖ ይኖራል። ነገር ግን ታሪክን በትክክል ከተረዳነውና እንደ ማስረጃ እናጬኸው ካልን፣ ሁልጊዜም ቢሆን ጌታን ኢየሱስን እግዚአብሔር በወንድሞቹ መካከል ቀብቶ እንዳስነሳው እውነተኛ ነብይና እንደ እግዚአብሔር ልጅ በሚያከብረው መንገድ፣ ከእግዚአብሔርም ቃል ጋር ሊስማማ እንጂ ሊጣላ በማይችልበት መልኩ መሆን አለበት። ታሪክ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲደፈጥጥና የኢየሱስን ቃል እንዲያቃልል መረን ሊተው አይገባውም፣ በአግባቡና በደረጃው መያዝ አለበት። የለም ቤተክርስቲያን በሚበዛው ዘመንዋ ይህንን ስታደርግ ኖራለችና የአቋማችንን ሰንደቅ አላማ ታሪክ ላይ እናንጠለጠላለን ከተባለ ግን ያ የሰዉ ምርጫ ነው፤  የእግዚአብሔር ቃል ግን ሁልጊዜ አሸንፎ ይወጣል።
9.  ታሪክ ማናቸውንም ነገር ፍጹም በሚባል ደረጃ ማረጋገጥም ሆነ ውድቅ ማድረግ በእውነትም የማይችል እስከሆነ ድረስ ታዲያ እንደ ኃላፋዊ እዚህ ላይ ታሪካዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ ለምን አስፈለገን?
10. ታሪክ የእግዚአብሔርን ቃል ትክክለኛነት በማስረጃ ሊያረጋግጥም ሆነ ውድቅ ሊያደርግ አይችልም፣ ወይም የእግዚአብሔር ቃል ማናቸውንም ነገር ለመወሰን እንዳለው አይነት ፍጹም ስልጣን ከጀርባው ኖሮት ማናቸውንም ነገር መወሰን አይችልም። ሆኖም ግን ለአማኞችና ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ጠቀሜታ አለው። ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጣረስ ታሪክ ጠቃሚ ሰነድ እንጂ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጠ ሥልጣን አይደለም። ሥልጣን የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው።
11.  በአግባቡ ጥቅም ላይ የዋለ ታሪካዊ ማስረጃ፣ ቢያንስ ለሁለት ነገር ይጠቅማል፦
ሀ. እንደተከናወነ የምናውቀውን የትንቢት ፍጻሜ ዘግቦ በመያዙ ያበረታታናል - ረቂቁ እምነታችን በቆመበት መረዳት ላይ ኮንክሪት የሆነ እውቀትን እና በእርግጠኝነት ስለምናምነው የትንቢት ፍጻሜ ድፍረትን ይጨምርልናል። እነዚህ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ይሆናሉ ሲል በቀጠረላቸው የጊዜ ማእቀፍ ውስጥ ሳይዛነፉ በትክክል ለመሆናቸው ያለንን እምነት ይደግፋሉ፣ የእምነት ማጽኛችንንም ይሰጡናል።
ለ. እንዲሁም በታሪክ ውስጥ ፍጻሜውን ያገኘው ትንቢት የተፈጸመበትን አይነት/ባህርይ እና ተፈጥሮ በምንመለከትበት ጊዜ በዋናነት ምን እንደተተነበየ እጅግ ጥልቅ የሆነና የተትረፈረፈ እውቀትንና መረዳትን ያደርግልናል። ስለሆነም ታሪካዊውና ተጨባጭ የሆነው የትንቢት ፍጻሜ የፍጻሜውን ባህርይ ወይም ተፈጥሮ እንድንረዳ፣ እንዲሁም እምነታችንን በትንቢት ፍጻሜ ውስጥ እንድናየው  ያግዘናል።
እነዚህን የመርህ አቅጣጫ ነጥቦች ይዘን በማቴዎስ 24 ላይ የተሰጠውን የትንቢት ቃል ማጥናታችንን እንቀጥል፦
ወንጌላዊው ማቴዎስ በምዕራፍ 24፥ 1 ላይ ትራኬውን  ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቤተ መቅደሱን ትተው ሲወጡ በማሳየት ይጀምራል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በቤተ መቅደሱ እየተገረሙ ሳሉ፣ ለኢየሱስ ሕንጻው የተሰራበትን  ውበት  ሊያሳዩት እየጣሩ መደነቅ ጀመሩ፡፡ ኢየሱስ እንደ እነርሱው አብሮ ከመደነቅ ይልቅ ሌላ አስደንጋጭ ትንቢት ይናገር ጀመር፡፡
በምዕራፍ 23 በአይሁድ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን አስፈሪ ፍርድ ሲናገር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ለጥቆ በምዕራፍ 24 የዚያን እጅግ የሚያምር ቤተመቅደስ ውድመት አስመልክቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ “…. ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው” (ማቴ 24÷ 2)።
ይኼንን ንግግር በዚያን ዘመን ያለ አይሁዳዊ ሆናችሁ ብትሰሙት ክው አድርጎ የሚያስደነግጥ ንግግር ነው። በቤተ መቅደሱ ላይ የተነገረው ይህ የውድመት ትንቢት ቀሎ የሚሰማን እና መፈራረሱ በዘላለማዊው የያህዌ ፕሮግራም ውስጥ ያለውን ዋጋ አኮስምነን የምንመለከተው፣ እዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ያለና አይሁዳዊ ያልሆነ የትንቢቱ አንባቢ በመሆናችን ነው። አይሁድ የሚቀደሱበት፣ የማንነታቸው መገለጫ፣ አምላካቸው ከእነርሱ ጋር በመካከላቸው የማደሩ ምልክት፣ የአምልኮአቸውና የኃይማኖታቸው ማዕከል፣ የህልውናቸው መሰረት አድርገው የሚወስዱትን ያንን የሚያምር ቤተ መቅደስ "ይፈራርሳል" ማለት እንደ ሕዝብ ያበቃላችኋል፣ ከማለት በቀር ሌላ ትርጉም የለውም።  ስለዚህ የቤተ መቅደሱንና የከተማይቱን ውድመት ከመጨረሻው የጌታ ምጽአት እና ከዘመኑ ፍጻሜ ጋር አያይዘው መረዳታቸው የሚጠበቅ ነው።
ደቀ መዛሙርቱ ከቤተ መቅደስ ሲወጡና ወደ ደብረዘይት ተራራ ሲመጡ ከአስደንጋጩ የኢየሱስ ንግግር የተነሳ ምናልባት በድንጋጤና በዝምታ ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡  ይህ ለሐዋርያቱ የቀረበው ስብከት የደብረ ዘይት ተራራ ስብከት በመባል እንደሚታወቅ ባለፈው ክፍል ትምህርት ጠቁሜአለሁ፡፡ ማርቆስ 13 እና ሉቃስ 21 ይህንን ስብከት የዘገቡ ሲሆን እነርሱም በማቴዎስ ዘገባ ላይ ተጨማሪ የሆኑ ምልከታዎችን ይሰጡናል፡፡
እነዚያ ከኢየሱስ ንግግር የተነሳ የደነገጡና የፈሩ ደቀ መዛሙርት  በደብረዘይት ተራራ ላይ አረፍ ሲሉ፣ ስለዚያ አዕምሮአቸውን ስለያዘውና በሕዝቡ ላይ፣ በኢየሩሳሌምና በመቅደስዋ ላይ ስለተነገረው የፍርድ ትንቢት መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ስላመጣው የትንቢት መልዕክት እያሰላሰሉ እንደነበሩ መገመት እንችላለን፡፡
በመጀመሪያው የማቴዎስ መጽሐፍ ቅጅ በምዕራፍ የመከፋፈል ነገር እንዳልነበረ ልብ ይሏል፤ ስለዚህ በምዕራፍ 23 ላይ የተጀመረው የፍርዱ ትንቢት በማቴዎስ 24 ላይ የሚቀጥል ተያያዥ ነው፡፡ በማቴዎስ 24÷ 3 ላይ ያቀረቡአቸው ጥያቄዎችም እርስ በርሳቸው ተያያዥነት ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። እነርሱም "ይህ መቼ ይሆናል? ፣ የመምጣትህ እና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው?" የሚሉት ናቸው። ጊዜንና ምልክትን የተመለከተ ጥያቄ ነው።
በዚህ መለስተኛ ጥናት ውስጥ የያዝነው ምርመራ "የምትመጣው መቼና በምን አይነት ነው?" ሲሉ ደቀ መዛሙርት ያቀረቡትን ጥያቄ የሚመለከት ነው፣ የዚያን ጥያቄ መልስ በትክክል ለማግኘት በምዕራፉ ውስጥ የተገለጡትን  ምልክቶቸ ማስተዋል የግድ ይላል፡፡
ኢየሱስ በሕዝቡና በተወዳጁ ቤተ መቅደስ ላይ ከተናገረው የፍርድና የጥፋት ትንቢት የተነሳ ደቀ መዛሙርቱ በጭንቀት ተውጠውና ፈርተው፤ ስለ ጉዳዩ  የበለጠ ብዙ ለማወቅ እንደፈለጉ፣ በተለይም እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚሆኑት “መቼ” እንደ ሆነ ለማወቅ ጉጉት እንዳደረባቸው እናያለን፡፡ ይህ ፍርድ ሊቀርብ ሲሆን የሚያውቁበትን ከእግዚአብሔር የሆነ ”ምልክት” ይኖር እንደሆነ ለማወቅ መፈለጋቸውን እናያለን፡፡
ደቀ መዛሙርቱ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን በሕዝቦች ላይ ፍርድን ሲያመጣ፣ ስለ እነርሱ ፍትህን ሊያደርግ እንደደረሰ፣ ነብያቱም እርሱ እንደሚመጣ አዘውትረው ይናገሩ እንደነበር ያውቃሉ፡፡ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ  ስለመመለሱ የተናገረውን ነገር ሁሉ በጥንቃቄ ብንመረምር ያንን በሕዝቦች ላይ ሊመጣ ያለውን የጊዜውን የፍርድ ትንቢት ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ መምጣት ጋር አያይዘውታል።
ሐዋርያት ይጠብቁት የነበረው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ዳግመኛ ምጽዓት አንድ ብቻ ከሆነ፣ ያም ምጽዓት ይፈጸማል ተብሎ የሚታመነው አንዴ ብቻ ነው፡፡ የፍጻሜውም የጊዜ ማዕቀፍ እንደሚፈጸምላቸው ተስፋ ከተገባላቸው የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ወቅታዊ አውድ የሚዘል ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ጉዳዩን ከዚያ የሐዋርያቱ ዘመንና ትውልድ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ አውጥቶ መለጠጥና ወደ ሌላ ሩቅ ዘመን ማለትም እኛ ወዳለንበት ሁለት ሺህ እና ከዚህም በኋላ ገና ሦስትና አራት ሺህ ዘመን አሳልፎ ፍጻሜውን በዘመን ርቀት መጠባበቅ በእውነቱ የሌለ ነገር መጠበቅ ይሆንብናል። የሌለ ነገር እንደ መጠባበቅ ያለ አድካሚና አሰልቺ ነገር ደግሞ የለም።
መቼም አዲስ ኪዳን በመጻህፍቱ ሁሉ ውስጥ በግልጽ የሚያስተምረው ስለሆነ ሁሉም ክርስቲያኖች በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዐት ያምናሉ ብዬ አስባለሁ። የዳግመኛ ምጽዐቱን እውነታ መካድም በሁሉም ወንጌላውያን አማኞች ዘንድ እንደሚታመነው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነትና በመንፈስ ቅዱስ መሰጠቱን እንደመካድ ይቆጠራል። በዚህ መቼም እንደምንስማማ ይመስለኛል።
በዚያው ልክ ዳግመኛ ምጽዓቱ የሚፈጸምበትን ጊዜ እውነታም ቢሆን ልክ እንደ ዳግመኛ ምጽዓቱ ሁሉ ግልጽ መሆኑን አምናለሁ። ይህንን ለዳግመኛ ምጽዓቱ በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጠውን የጊዜ አገላለጽ መካድም ሆነ አስፈላጊነቱን ማሳነስ ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጡ መሆናቸውን መካድ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህስ ያስማማናል? ኢየሱስ ዳግመኛ ይመጣል የሚለውን የአዲስ ኪዳን ትምህርት ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ የሕይወት ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣ ከተሰጠው ተስፋ ነጥሎ መረዳት የተሳከረ ትምህርትን ይፈለፍላል።

ስለዚህም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን የሚጠይቁት የነበረው  ስለ መምጣቱ ምልክቶች ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ሕዝባቸው የሚደመሰስ፣ የሚጠፋ ከሆነ፣ ቤተ መቅደሳቸውም ፍርስራሽ ሆኖ የሚደመሰስ ከሆነ ያ ሁኔታ የጌታ በፍርድ መምጣት እና የእነርሱ ዓለም ፍጻሜ እንደሆነ ያውቁ ነበር፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ ይህ ቤተ መቅደስ መቼ ይፈርሳል? ማለት፣ መቼ ነው በፍርድ ተመልሰህ የምትመጣው? ወይም እንዴት ነው ልትፈርድ የምትመጣው? በፍርድ ከመምጣትህስ በፊት ምን ምን ምልክቶች ይሆናሉ? "ይህ አለምስ" መቼና እንዴት ያበቃል? የሚሉ ጥያቄዎችን የያዘ ነው።
በደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ውስጥ “ዓለም” የሚለው ቃል በተለያዩ የአማርኛም ሆነ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መግባቱ በኩረ ቃሉን ያላገናዘበ ትርጉም ነው፡፡ የግሪኩ የመጀመሪያ ቃል “አዮን” (aion) ነው፡፡ ሲተረጎምም “ዘመን” ተብሎ መተርጎም ነበረበት፤ አንዳንድ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን ትርጉም የተከተሉ እንደሆነ ይታወቃል [ለምሳሌ፡- RSV, NKJV, NIV፤ ቢያንስ አ.መ.ት. የተሰኘው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን እርማት ማድረግ ነበረበት። በግርጌ ማስታወሻውም ላይ እንኳ ለውጡን ለማሳየት የጣረው በደምሳሳው ነው]።
ስለዚህ የደቀመዛሙርቱን ጥያቄ ስንመለከት ማወቅ የፈለጉት ዘመናቸው መቼ እንደሚያበቃ ነው፡፡ የእነርሱ ዘመን፣ የሙሴ ዘመን፣ የአሮጌው ኪዳን ዘመን፣ የሙሴ ሕግ፣ እና የነቢያቱ ዘመን ማብቂያ ነው፡፡ ቤተ መቅደሳቸው ፈራርሶ የሚጠፋ ከሆነ፣ ሕዝባቸውና የኑሮ ዘይቤአቸው ፈጽሞ የሚደመሰስ ከሆነ፣ ያ የፍርድና የጥፋት ኹነት ዘመናቸውን የሚፈጽመውና ማብቂያ የሚሰጠው እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡
ዛሬ በአብዛኛው እንደሚመስለን ደቀ መዛሙርቱ የሚጠይቁት ስለተዳሳሹ ግዑዝ ፍጥረተ ዓለም መጨረሻ አልነበረም፡፡ በዚያ ጉዳይ ፍላጎት ሊያሳድርባቸው እንደሚችል የሚያስቡበት ምንም መነሻ ምክንያት አልነበራቸውም፡፡ ምክንያቱም በዚያ እነርሱም ተወልደው ባደጉበት፣ በኖረውና ረጅም ዘመን ባስቆጠረው የአይሁድ ሥነ መለኮታዊ እሳቤ ውስጥ ይህ ግዑዝ አለም ይጠፋል ብሎ የሚያምንና የሚያስተምር ምንም ነገር አልነበረም፤ ደቀ መዛሙርትን ከዚህ አውድና ሥነ መለኮታዊ እሳቤ ውጭ ልናስባቸው አንችልም። በኖረውና ረጅም ዘመን ባስቆጠረው የብሉይ ኪዳን አይሁዳዊ ሥነ መለኮትና ሥነ ፍጥረት ውስጥ እግዚአብሔር ይህንን ግዑዝ አለም ቡን አድርጎ ለማጥፋት ምንም እቅድ እንደሌለው መረዳት ይቻላል። ከዚህም በላይ በጊዜው ከነበረው የጂኦግራፊ እውቀት አንጻር ያኔ እነርሱ የሚያውቁት ዓለም  ከሜድትሬንያን ባህር ያልዘለለ ዓለም ብቻ እንደ ነበር በግልጽ ይታወቃል፡፡
♦♦♦♦♦♦♦♦♦

No comments:

Post a Comment