Monday, November 5, 2018

የጌታ ምጽአት መቼ እና እንዴት ክፍል አራት

የጌታ ምጽዓት መቼ እና እንዴት ነው?
በማቴዎስ 24 እንደተገለጸ

በማቴዎስ 24÷ 4 ላይ ኢየሱስ የሐዋርያቱን ጥያቄ መመለስ ይጀምራል፡፡ አብዛኛው የዚህ ምዕራፍ ክፍል የሚያወራው ለነዚያ እርሱ ሥራውን እንዲሸከሙ ለመረጣቸው ሰዎች የተሰጡ የምክር ቃላት ናቸው፡፡ እነዚህ የጠየቋቸው ነገሮች ሁሉ ተፈጽመው ከማየታቸው አስቀድሞ ብዙ ነገሮችን መታገስ እንዳለባቸው ይነግራቸዋል፡፡ ሊመለከቷቸው የሚገቡ ምልክቶችንና መጻዒ በሆኑ ሁነቶች አንጻር ምን ምላሽ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይመክራቸዋል፡፡ በማቴዎስ 24 ውስጥ ከተባሉት ነገሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት የሚከተሉት ናቸው፡-
ከዋነኞቹ ምልክቶች አንዱ፦
   ♦ብዙ ሐሰተኛ ነብያትና ሐሰተኛ ክርስቶሶች ተነስተው ብዙዎችን ያስታሉ፤ ( ማቴ 24፣ 4፣ 5፣ 11፣12 እና 23-26፡)፣ የተባለው ነው። የአስመሳይ አሳች ነብያትና ክርስቶሶች መነሳት የቀኑ መጨረሻ ለመድረሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠው አንዱ ምልክት ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ "ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።" (1ዮሐ 2፥ 18) ሲል፣ ይህ ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ወቅት እየተፈጸመ እንደነበር ተረድቶ ነበር። ዮሐንስ በዚህ ጥቅስ ለአንባቢዎቹ የሚነግራቸው ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች እየተነሱ ስለሆነ፣ ሰአቱ የመጨረሻው ሰአት (የመጽሐፍ ቅዱሳዊው ይሁዲነት የመጨረሻ ሰአት) መሆኑን ማወቅ የሚችሉ መሆኑን ነው።
በሌላ አነጋገር ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ብዙ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነብያት ይነሳሉ በማለቱ፣ ብዙ አሳቾችም ያኔውኑ ተነስተው ስለነበር፣ ዮሐንስና በዚያ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ የነበሩ ሌሎች ክርስቲያኖች ሁሉ  መጨረሻው ለእነርሱ ፈጽሞ የቀረበ መሆኑን ያውቁ ነበር ማለት ነው።
አሁን በእኛ ዘመን ውስጥ የምናያቸው ሐሰተኛ ነብያት ወሐዋርያትና ሐሰተኛ ክርስቶሶች በጥቅሉ የሐሰት መምህራን የመጨረሻው ዘመን ምልክት አይደሉም፤ ምክንያቱም የመጨረሻው ዘመን ካለፈ ብዙ ዘመን ሆኖታል። ይልቁንም እነዚህ የዘመናችን አሳቾች ያለመማርና ያአሮጌው ሰው እኔነት ውጤቶች ብቻ ናቸው። አርፈን የቃሉን ወተት ካልተመገብን እንደ ምዕመን የሐሰተኞች ሰለባ መሆናችን እንደ አገልጋይ ብዙዎችን ማሳታችን አይቀርም። የእግዚአብሔርን ቃል የመናቅ መዘዙ ከባድ ነው።
♦ጦርነቶች፣ ረሃብ፣ መቅሰፍቶች እና የመሬት መንቀጥቀጥ ይኖራሉ (ማቴ 24፣ 6- 7)። ጦርነትና የጦርነት ወሬ የዘመኑ መጨረሻ ምልክት እንደሆነ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸዋል። በዓለም ታሪክ ውስጥ ጦርነትንና የጦርነትን  ወሬ  ሰምተን የማናውቀው መቼ  ይሆን? ይህ የቁጥር 6 ጦርነት ታዲያ ምን ዓይነት ምልክት ነው? "የሮም ሰላም" /Pax Romana/ በተሰኘው ዘመን ላይ ለኖረ ሰው ይህ  አይነተኛ የዘመኑ መጨረሻ ምልክት ይሆነዋል።
በአለም ታሪክ ውስጥ ይህ እንደ አንድ ምልክት ሊሆን በሚችልበት ደረጃ ትርጉም የሚሰጠው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን "የሮም ሰላም" ወቅት ብቻ ነው። በእኔም ሆነ በብዙዎቻችን የህይወት ዘመን ላለፉት ሺህ አመታት አለም ከገዙአት ክፉና ጀብደኛ ሰዎች የተነሳ ከጦርነት ለአንድ አስርት አመት እንኳ አርፋ የሰላምን ጊዜ አጣጥማ አታውቅም። የኢየሱስ ንግግር ስሜት ሊሰጥ የሚችለው ከዚያ ትውልድ የመጨረሻዎቹ ቀናት በፊት ብቻ ነው። ሰዎች ግን በተለይ መጻኢያን ላለፉት ሁለት ሺህ አመታት በየዘመናቸውና በየትውልዳቸው የተቀሰቀሱትን ፍትሃዊና ኢ-ፍትሃዊ ጦርነቶች ዋቢ እያደረጉ "የመጨረሻው ዘመን ላይ ለመሆናችን ይኸው ምልክቱ" ሲሉን ይደመጣሉ። እውነታው ግን ሁልጊዜም ቢሆን ጦርነትና የጦርነት ወሬ በአለም ላይ ያለ መሆኑ ነው። ሁልጊዜም ቢሆን ረሃብ በአለም ላይ አለ፤ መቅሰፍቶች እና የመሬት መንቀጥቀጥም በአለም ላይ አለ፤ እርግጡን ማወቅ ከፈለጋችሁ ደግሞ እነዚህን ነገሮች እየጠየቃችሁ ጎግል አድርጉ፣ አለም በዘመንዋ ያስተናገደችውን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ጥፋቶች ዘርግፎ ያስነብባችኋል፤ ታዲያ የየትኛው ዘመን የተለየ ጥፋት የመጨረሻው ዘመን ምልክት ሊሆን ይችላል?
♦መከራ፣ ታልፎ መሰጠት፣ ጥላቻ፣ እና መገደል( 24፣ 9 - 10)።
ይህ መከራ ወደሚጠብቃቸው ክብር እና ብድራት ከመግባታቸው በፊት እነዚያ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን የሚያልፉበት ሥደትና መከራ ነው፤ ከአይሁድ ወንድሞቻቸውና ከሮም የአረማዊነት አምልኮ የደረሰባቸውን ሥደትና የተቀበሉትን መከራ አዲስ ኪዳን በተለይም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በዝርዝር ይነግረናል።
አማኞች በዚህ በምንኖርበት ዘመን በልዩ ልዩ ስፍራ የሚገጥመን መከራ የዘመኑ መጨረሻ ምልክት አይደለም፤ ዘመኑ ከተፈጸመ ብዙ ዘመን ሆኖታልና። ታዲያ የዚህ ዘመን የእኛ መከራ የዘመኑ መጨረሻ ምልክት ካልሆነ ምን ትርጉም አለው? አላማውስ ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ይነሳል። ተገቢ ጥያቄ ነው። ላረጋግጥላችሁ የምችለው ይህ የማቴዎስ 24 መከራ እኛን የሚመለከት ለእኛ የተነገረ አለመሆኑን ነው። ታዲያ እኛስ ስለሚደርስብን መከራ ምን የተነገር ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይኖር ይሆን?
መከራ የሰው ሕይወት አንዱ ክፍል መሆኑን ከሁሉ በፊት ማወቅ አለብን። ሰው ሁሉ በምድር ላይ ሕይወቱ በተወሰነ ደረጃ ስቃይንና መከራን ይለማመዳል፤ የአንዳንዶች ከሌሎች በተለየ መጠኑ ሊበዛ፣ አይነቱም ሊለያይ ይችላል።
"ችግር ከትቢያ አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይበቅልም፤  የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥ ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል።" (ኢዮብ 5፥ 6-7)
መከራና ችግር ዝም ብሎ ከአመድና ከትቢያ ላይ የሚበቅል፣ መገኛው የማይታወቅ፣ ወፍ ዘራሽ አረም፣ የሚፈላም እንጉዳይ፣ አይደለም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር አለምን በሚያስተዳድርበት ሉአላዊና መለኮታዊ ሥርዓት የተመሰረተ ነው። የአሞራ መብረር ተፈጥሮአዊ (ኖርማል) እንደሆነ ሁሉ የሰውም መከራ ተፈጥሮአዊ (ኖርማል) ነው።
መከራ አማኞችን ዲስፕሊንድ ያደርጋቸዋል፣ በመዝመር 119፥ 71  "ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ።" እንደሚል መከራ አማኞችን ወደ እግዚአብሔር አብዝቶ ያቀርባቸዋል፣ ያስጠጋቸዋልም፤ በእነርሱም ይሰራ ዘንድ እንዲታመኑት ያደርጋቸዋል። (2ቆሮንቶስ 1፥ 8-9 ተመልከቱ)
በእግዚአብሔር መታመናችንን እንድንቀጥል ይረዳን ዘንድ መከራ ያስፈልገናል ወይ? ከተባለ አዎን በሚገባ ያስፈልገናል! ነው መልሴ። ስለዚህ የብልጽግናና የጤንነት ወንጌል የሚባል የትምህርት ቅርሻት ፈጽሞ ያፈጠጠ የሲዖል ውሸት መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። መቼም ቢሆን ዲሲፕሊን የሚያደርገንና ወደ እግዚአብሔር ገፍቶ የሚያቀርበን መከራ እንጂ ብልጥግና አይደለም። ጳውሎስ ስለመከራው ምን እንደሚል ልብ ብላችሁ ስሙ፦
"ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።" (2ቆሮ 12፥ 10)
ይህ ማለት፣ ድካሙ በክርስቶስ ኃይል እንዲታመን ያደርገዋል ማለት ነው። እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ይቆጣጠራል፤ መከራችሁንም ቢሆን እንኳ እርሱ ይቆጣጠረዋል። በመከራችሁ ውስጥ በእርሱ ታመኑና በጌታ ዳግም ምጽዓት ፈጽሞ በተሰጣችሁ በድል ነሺው የአዲሱ ሕይወት ክብር ደስ ይበላችሁ እንጂ፣ የምታልፉበት የመከራ ኑሮ የመጨረሻው ዘመን ለመድረሱ ምልክት እንደሆነ በማሰብ አንድ ቀን ወደፊት ጌታ ሲመጣ ይህንን መከራ እገላገለዋለሁ ብላችሁ አትዘናጉ። የመጨረሻው ዘመንና መከራው ያኔ ድሮ አልፎአል።
♦ብዙዎች እምነትን ይተዋሉ( ማቴ 24፣ 12)።
♦ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል( ማቴ 24፣ 14 )። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ወንጌል በአለም ሁሉ ይሰበካል ሲል ኢየሱስ ተናግሮአል።
   ኢየሱስ አይሁዳዊ እንደነበር ለአይሁድም እንደሚናገር መዳንም ደግሞ የአይሁድ እንደነበር አስተውሉ፡፡ የመጀመሪያዋ የክርስቲያን ቤተክርስቲያን አይሁድ በሆኑ  ምዕመናን የተዋቀረች ነበረች፡፡ አሕዛብ የይሁዲነት ተከታይ ሳይሆኑ በቀጥታ ወደ ቤተክርስቲያን የገቡት ከበዓለ ሃምሳ ቀን በኋላ በግምት አስር ዓመት  ያህል ቆይቶ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ተልዕኮን "በዓለም ሁሉ" የማዳረስ እንቅስቃሴ የተጀመረው በአንጾኪያ በተደረገው ውሳኔ ነበር /ሐዋ 11÷ 19-30/፡፡ መጨረሻው ከመሆኑ በፊት ወንጌል ከአይሁዳዊነት በላይ አልፎ መሄድ ነበረበት፡፡ ይህም ማለት ከአለም ፍጻሜ በፊት የታላቁ ተልእኮ ትእዛዝ ተፈጽሞ ነበር ማለት ነው። ስለዚህም በዚያው ዘመን ወንጌል  ለዓለም ሁሉ  ተሰብኮ እንደ ነበር መጽሐፍ  ቅዱስ በማስረጃ ያሳየናል።
  የሮሜ መልእክትና የቆላስይስ መልእክት በተጻፉበት ጊዜ ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ወንጌሉ በአለም ሁሉ ተሰብኮ ነበር፦
  ሮሜ 1፥ 8 "እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማች አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ።"
  ሮሜ 10፥ 18 "ዳሩ ግን፦ ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት፦ ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።"
ቆላ 1፥ 23 ".... ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ።"
ወዲያውኑ በዚያ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ወንጌል በመላው አለም ከተሰበከ በኋላ፣ በ70 ዓ.ም ላይ የክርስቶስን ጠላቶች ከምድረ ገጽ በማጥፋትና በመደምሰስ፣ ያኔውኑ የዚያ የአሮጌው ኪዳን አለም የቃጠሎ ፍርድ ሲከናወን ፍጻሜው ይሆናል።
♦♦♦♦♦♦♦♦

No comments:

Post a Comment