ክፍል ፪
የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ መቼ ተጻፈ?
የራዕይ መፅሐፍ ተርጓሚን የሚፋጠጠው እጅግ አስፈላጊ የሆነ አንድ ጉዳይ መፅሐፉ የተፃፈበትን ጊዜ በተመለከተ የሚነሳው ክርክር ነው፡፡ አቡቀለምሲሱ ለዮሐንስ የተገለጠበትንና እርሱም በመጽሐፍ የጻፈበትን ጊዜ ለመወሰን የሚደረግ ይህ ክርክር በምንከተለው አመለካከትና በጠቅላላ በመጽሐፉ ላይ በምናደርገው ሥነ አፈታታዊ የትርጉም ሥራ ላይ ያለው ተጽእኖ ቀላል ግመት የማይሰጠው ነው። በዚህ ረገድ በአንድ ወገን "ውጫዊ ማስረጃንና" በሌላ ወገን "ውስጣዊ ማስረጃን" ዋቢ አድርገው እርስ በርሳቸው የሚፎክከሩ ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች አሉ።
ውጫዊ ማስረጃን ዋቢ የሚያደርጉ ተርጓሚዎች፦ መጽሐፉ የተጻፈው ከኢየረሳሌም ውድመት በኋላ ነው የሚሉ ሲሆን፣ እነርሱም ከ95-96 ዓ.ም ባለው በኋለኛው ጊዜ ተጽፎአል የሚል አመለካከት የሚከተሉ ናቸው። ይህ አመለካከት የአብዛኞቹ የዚህ ዘመን ወንጌል አማኞች የተለመደ አመለካከት ነው። ይህን አመለካከት የሚከተሉ ተርጓሚዎች በዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ላይ በርካታ የትርጉም ዓይነቶችን እንዲከተሉ ይገደዳሉ፤ ይኸውም መፅሐፉ የእግዚአብሔርን መንግሥት መጨረሻ እና የቤተክርስቲያንን ታሪክ ማብቂያ የሚናገር እንደሆነ እንዲታሰብ የሚያደርግ ነው። ነገር ግን በአዲስ ኪዳናዊ የትንቢት መጽሐፍና በይዘቱ ላይ ብርቱ ሥራ በሰሩ ምሁራን እይታ የትርጉም ቀዋሚነት (consistency) የሚጎድለው አመለካከት ነው በሚል የሚሰነዘርበትን ትችት በበቂ መከላከል ይሳነዋል፡ ፡
ውስጣዊ ማስረጃን ዋቢ የሚያደርጉ ተርጓሚዎች፦ መጽሐፉ የተጻፈው ከኢየሩሳሌም ውድመት በፊት ነው ሲሉ እነርሱም ከ65-66 ዓ.ም ቀደም ባለው ጊዜ ተጽፎአል የሚል አመለካከት የሚከተሉ ናቸው። የዚህ አመለካከት ደጋፊዎች የራዕይ መፅሐፍ የእግዚአብሔርን መንግሥት ውልደት ምጥ፣ የምጡን መፋፋም እና የቤተክርስቲያንን ታሪክ መጀመሪያ የሚናገር ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አመለካከት የጠቅላላ የመጽሐፉ ይዘትና አውድ ከትርጉም ቀዋሚነት (consistency) ጋር የሚያቀርበው ሙግት ጠንካራና የብዙ የቃሉ ተማሪዎችን አእምሮ ሊማርክ የሚችል ነው።
አገላለጹ እንደሚያመለክተው ውጫዊው ማስረጃ የምንላቸው ከራሱ የዮሐንስ ራዕይ ከተሰኘው መጽሐፍ ውጭ ያሉ ሌሎች ጽሑፎችን እንደ ዋነኛ የሙግት ጭብጥ ሆነው የሚቀርቡበት ሲሆን ይኸውም፦ የጥንታዊ ጸሐፊያን ምስክርነት፣ ትምህርቶቻቸው፣ በቃልና በጽሁፍ የተላለፉና ሊቀርቡ የሚችሉ ጥቅሶቻቸው፣ ወይም ከሌሎች ጸሐፊያን የሚለዩበትን አመለካከቶቻቸው፣ አና የመሳሰሉትን የሚመለከት ነው፡፡ ያም ሆኖ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈበትን ጊዜ ያመለክታል በሚል በሊቃውንቱ ዘንድ ለመሞገቻነት የሚቀርበው ውጫዊ ማስረጃ በኅይለኛው ሲያከራክር ኖሮአል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ በርካታ ሊቃውንታዊ የሆኑ አመለካከቶች በዓመታት ውስጥ ወዲያና ወዲህ ሲያዋዥቁ ኖረዋል፡፡ በሁለቱም ወገን የሚቀርቡትን ማስረጃዎች ከቆይታ በኋላ እናያለን።
ኬኔት ኤል ጀንትሬይ ጄ አር የተባሉ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሥነ መለኮት ምሁር ይህንን ክርክር አስመልክቶ በዶክትሬት ጥናታዊ የምርምር ስራቸው ውስጥ በስፋት በዳሰሱበት በዘገባቸው እንዲህ ይጽፋሉ፡- "በእጅጉ ወግ አጥባቂ የነበሩ ወገኖችን እስከ ተመለከተ ድረስ በ1800 ዓ.ም አካባቢ ለአዲስ ኪዳን ቀኖና መጠናቀቅ ይሰጥ የነበረው የጊዜ ማእቀፍ በ50 ዓ.ም እና በ100 ዓ.ም መካከል ያለውን ጊዜ ይሸፍን ነበር፡፡ በ1850 ዓ.ም ከቱቢንገን የፍልስፍና ትምህርት እና ከኤፍ ሲ ባወር ተጽዕኖ የተነሳ ጊዜው ሰፋ ተደርጎ ከ50 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 160 ዓ.ም ድረስ ይሸፍናል የሚል ሃሳብ ተሰራጨ፡፡ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈበትን ጊዜ በተመለከተ በቱቢንገን በተደረገው የአመለካከት ለውጥ ላይ፣ "በቱቢንገን ፍልስፍና ውስጥ ሊታሰብ የማይችል፣ እርስ በርሱ የሚጋጭ ትምህርት፣ ጳውሎስን ከአራት መልዕክቶች ጋር ብቻ ያስቀረ፣ ወይም እጅግ ዘመናዊ በሆነ አስተሳሰብ በአዶልፍ ሂልገንፊልድ እንደተፃፈው፣ ጳውሎስን ከሰባት መልዕክቶች ጋር ብቻ በማስቀረት፣ በርካታ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎችን ደግሞ የተጻፉበትን ዘመን ወደ ኋላ ላይ እንዲመጡ ያደረገ የአቡቀምሲሱንም መጽሐፍ በተመለከተም የመጽሐፉን ሐዋርያዊ ሥልጣን በማረጋገጥ የተፃፈበትን ጊዜ በተለምዶ ይታመን ከነበረው ይልቅ የክፍለ ዘመኑን ቀዳሚ ሩብ ይጠቅስ ነበር" ይላሉ፡፡ (Gentry, Before jerusalem Fell, ገጽ፡.27 የተጠቀሰውም Arthur S. Peake, The Revelation of John, Hartley Lectures (London: Joseph Johnson, 1919 P 77 ለይ ነው)
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ያሉ በርካታ የስነ መለኮት ሊቃውንት ክፍሎች የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ከ 70 ዓ.ም በኋላ የተፃፈ ነው ብለው ቢያምኑም እንኳ፣ ጀንትሬይ ግን በርካታ የስነ መለኮት ሊቃውንት ከ70 ዓ.ም በፊት ተጽፎአል ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ደግሞ በዝርዝር ያስታውቃሉ፡፡ በዝርዝሩ ከተከታተት መካከል ግሬግ ኤል ባህንስን፣ አዳም ክላርክ፣ ኤፍ ደብልዩ ፌረር፣ ጆን ኤ.ቲ ሮቢንሰን፣ ሄንሪ ባርክሌይ ስዊት፣ ሚልተን ኤስ ቴሪ፣ ዊልሄልም ቦውሰት፣ ኤፍ ኤፍ ብሩስ፣ ሩዶልፍ ቡልትማን፣ ሳሙኤል ዴቪድሰን፣ አልፍሬድ ደድርሼይም፣ ጆሃን ኢክሆርን፣ ጆሴፍ ኤ. ፊትዘርሜየር፣ ጂ፡ቢ ላይትፉት፣ ሲ. ኤ.ኤፍ.ዲ ሞውል፣ እና አውግስጦስ ኤች ስትሮንግ የተባሉት ሊቃውንት ሰምቻቸው ከተጠቀሱት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጄንትሬይ በጠቅላላ 138 ሊቃውንትን ዋቢ አድርገው የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ከ70 ዓ.ም በፊት መጻፉን የሚያምኑና የሚቀበሉ ምሁራን ያሉ መሆናቸውን በጥናታቸው ይጠቅሳሉ፡፡
ከፍ ሲል በጃንትሬይ ስለቀረበው ስለዚህ ዝርዝር ግን ሁለት ነገሮችን ማለት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ፣ ዝርዝሩ ከየትኛውም የስነ መለኮት ጎራ የሚመደቡ ሊቃውንትን የሚመለከት መሆኑ ነው፤ (ራእይ ከ70 ዓ.ም በፊት ተጽፎ አል ብሎ አቋም ለመያዝ በኃላፍያን ጎራ መሰለፍም ሆነ የአንድ ቤተ እምነት ማእቀፍ ውስጥ መሆን የግድ አይደለም ማለት ነው)። ሁለተኛው ደግሞ፣ ዝርዝሩ ብቻውን በራሱ የራዕይ መፅሐፍ ቀደም ያለው ጊዜ ላይ እንደተፃፈ አያረጋግጥም፣ ምሁራንን በመቁጠር ላይ የተመሰረተ አመለካከት ብቻ መሆን ያለበትምና፡፡ ዝርዝሩ የሚያስታውቀው አንድ ነገር ግን አለ፣ ይኸውም የራዕይ መጽሐፍ ቀደም ባለው ጊዜ ነው የተፃፈው የሚለው አመለካከት ያለ ጥርጥር እንግዳ ወይም አዲስ አመለካከት አለመሆኑን ነው።
ጄይ ኢ. አዳምስ ስለዚህ የጃንትሬይ የዶክርሬት መመረቂያ ሥራ ስለሆነው መጽሐፍ ሲመሰክሩ:- "አንዳንዶቻችን ለዓመታት ስንጠብቀው የነበረ መጽሐፍ ይህ ነው! አሁን እዚህ አለ ልናጣጥመው እንችላለን፡፡ ሚስተር ጀንትሬይ ማንም ካደረገው በላይ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈው በ70 ዓ.ም ከሆነው የኢየሩሳሌም ውድመት በፊት ቀደም ብሎ እንደተፃፈ እውነታውን አሳማኝ በሆነ መልኩ ቁልጭ አድርጎ አቅርቦልናል፡፡ ብዙዎች ሊያነቡት የሚባ ደግሞም በርካታ እይታዎችን ሊሰጠን የሚችል መጽሐፍ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በነገረ ፍጻሜ አመለካከታቸው ኃላፋዊ ያልሆኑ ጆርጅ ደብልዩ ናይት የተባሉም ሰው "ይህ የጀንትሬይ መጽሐፍ የራዕይ መጽሐፍ ቀደም ሲል እንደተፃፈ ባለው ጉዳይ ላይ ጥልቅና የሚደነቅ አገላለጽ አለው፡፡መጽሐፉ ማስረጃዎቹን በመጽሐፉ ማለትም በራሱ በራእይ ውስጥ፣ እንዲሁም በጥንት ቤተክርስቲያን ምንጮች ውስጥ፣ እያደረገ፣ ደግሞም የዚህን ዘመን እና ቀደም ያሉ ዘመናት የአዲስ ኪዳን ሊቃውንት የሆኑ ሙግቶችን እያቀረበና እየተነተነ ጥያቄውን ለመፍታት አንድም ድንጋይ ሳያስቀር ሁሉን ተጠቅሞ መጽሐፉ የተጻፈበትን ትክክለኛ ጊዜ ያመለክታል፡፡" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የራዕይን መጽሐፍ የተጻፈበትን ጊዜ በተመለከተ የአልቦ ሺህ አመት አገዛዝ አስተምህሮን የሚከተሉና በቅርቡ በሞት የተለዩን አር. ሲ ሰፕሮል የተባሉ ሊቅ ስለ ጄንትሬይ መጽሐፍ አስተያታቸውን ሲሰጡ፡- "እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ስራ፣ ይሉና መጽሐፉ የተጻፈው ከ70 ዓ/ም በፊት ቀደም ባሉት ጊዜያት በቄሳር ኔሮ ዘመን ኢየሩሳሌም ሳትደመሰስ እና መቅደስዋ ገና ቆሞ እያለ ነው የሚለው የጄንትሬይ ሙግት ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ፣ እንግዲያውስ እንደ ሥነ መለኮት ሞያተኛ የመጽሐፉን ይዘት እና ትኩረት ለመረዳት ብሎም በአግባቡ ለመተርጎም ባለን ዝግጅትና ጥረት ላይ ሰፊ የሆነ የክለሳ ሥራ መስራት ይጠበቅብናል" ሲሉ ያክላሉ፡፡ የነዚህን ምሁራን አስተያየት ዋጋውን አሳንሶ በማየት በራዕይ መጽሐፍ ይዘትና በተጻፈበት ዘመን ላይ የምንደርስበት ድምዳሜም ሆነ ክርክራችን ውሃ የማይቋጥር ይሆናል።
ስለ መጽሐፉ መጠየቅ ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ:- የዮሐንስ ራዕይ መፅሐፍ በዚህ በአሁኑ ዘመን ወይም ገና ከዚህ በኋላ በሚመጣው የአለም ታሪክ፣ በመላው ዓለም ላይ ሊሆን ስላለ እጅግ አስፈሪ ስለ ሆነ ታላቅ መከራና የሰው ልጆች ፍዳ የሚናገር መፅሐፍ ነውን? ወይንስ ደግሞ የዚያን የመጀመሪያውን ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች የነበሩበትን ከባድ እና ፈታኝ ጊዜ እያመለከተ፣ ክርስትና በዘመኑ ሊውጠው የተነሳበትን የመከራና የስደት ማዕበልን እና ሞገድን እንዴት እንደ ተቋቋመ ደግሞም ድል ነስቶ እንደሚወጣ የሚዘግብ መጽሐፍ ነው? የሚለው ነው። በዚህ መሰረታዊ ጥያቄ ላይ የምንደርስበት ድምዳሜ መጽሐፉ ወደተጻፈበት አውድ የሚያስጠጋንና ለመጽሐፉ የሚመጥን ትርጉም የሚያስጨብጠን፣ አለዚያም ከአውዱ አርቆ በመውሰድ በልብ ወለድ ትረካ የመሰለንን ትርጉም እንድንፈጥር የሚገፋን በጣም አስፈላጊና ዋና የሆነ ነገር ነው፡፡
እዚህ ላይ ታዋቂው የሥነ አፈታት ሊቅ ሚልተን ቴሪ የተናገሩትን መጥቀስ ተገቢ ነው፡- “የዮሐንስ ራእይ የተጻፈበትን ትክክለኛ ወቅት መቼ እንደሆነ በሚሰነዘሩ የክርክር ሃሳቦች ላይ እና ታሪካዊ አቋሞች ላይ እርግጠኛ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነጥብ ነው፡፡ ይህ የትንቢት መጽሐፍ ከኢየሩሳሌም ውድቀት በፊት ቀደም ባለው ጊዜ የተጻፈ ከሆነ እንግዲያውስ በርካታ የሆኑ እነዚያ ከዚያች ከተማና ከውድቀትዋ ጋር ግንኙነት ያላቸው ነገሮች ሁሉ እያንዳንዳቸው ተጨባጭ በሆነ መልኩ ከትንቢቱ ፍጻሜ ጋር የተገናኙ መሆን አለባቸው፡፡ ነገር ግን በርካቶች እንደሚያምኑት በዶሚኑስ የዘመነ መንግስት ማብቂያ ላይ (ከ95-96 ዓ.ም አካባቢ) ተጽፎ ከሆነ፣ እነዚያን ታሪካዊ ሁነቶች ለመተርጎምና ለማብራራት ሌላ የትርጉም መንገድ መፈለግ የግድ ይሆናል፡፡”
በኋለኛው ጊዜ ተጽፎአል የሚለውን አመለካከት የሚከተሉ ተርጓሚዎች ማስረጃቸውን የሚያቀርቡት ውጪያዊ ማስጃ ተብሎ ከሚታወቅ መነሻ ነው ብለናል። ለዚህ ለዮሐንስ ራዕይ ዘግየት ብሎ በኋለኛው ዘመን ላይ ተፅፎአል ለሚለው አቋም ብቸኛ ማስረጃ ሆኖ የሚጠቀስ አንድ ሰው ደግሞ ኢረንዩስ የተባለ የጥንት ቤተ ክርስቲያን አባት ነው /የኖረው ከ120-202 ዓ.ም ነው/፣ ሌሎች ምንጮች ሁሉ። በዚሁ ሰው ምስክርነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ዮሐንስ በ70 ዓ.ም ላይ ከሆነው ከኢየሩሳሌምና ከቤተ መቅደሱ ውድመት እጅግ ቀደም ብሎ በቄሳር ኔሮ በተቀሰቀሰው ከባድ የስደትና የመከራ ወቅት ላይ የራዕዩን መጽሐፍ ያኔ ጽፎታል ብለው አቋም የያዙና አቋማቸውን በጠንካራ ማስረጃዎች የሚያስደግፉ በርካታ የጥንት ፀሐፊያንም ያሉ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
የመጀመሪያውንና ራእይ ዘግየት ብሎ በዶሚኑስ ዘመን ተጽፎአል፣ ለሚለው አቋም መከራከርያ ሆኖ የሚቀርቡትን ውጫዊ ማስረጃዎች እንመልከትና ኢራንዩስን ዋቢ የሚያደርገውን ዋነኛ የክርክሩን ጭብጥ አንስተን እንተቻለን:-
፩. ነገስታትን ማምለክ /ለነገስታት መስገድና ማጠን/ በምዕራፍ 13 ያለው አይነት ስግደት ማለት ነው፣ እስከ ደሚኑስ ዘመነ መንግስት ድረስ በግድ አልተጫነም የሚለው ነው፡፡
፪. በራዕይ 13 የተፈወሰውም ለሞት የሆነው ቁስል በኔሮ ዘመን ታውጆ የነበረው የክርስቲያኖች ስደት በደሚኑስ ዘመን በባሰ መንገድ በመቀጣጠሉ ምክንያት ዶሚኑስ ሁለተኛው ኔሮ እየተባለ በመጠራቱና ዮሐንስን እና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሁሉ ከቀድሞ በባሰ መንገድ ያሳደደ በመሆኑ ነው፡፡
፫. ሌላው መከራከሪያ የኔሮ ዘመን ስደት ከሮም ከተማ ያልዘለለ መሆኑ እና በደሚኑስ ዘመን የሆነው ሰደት ግን መላውን የሮምን ግዛቶች ያጥለቀለቀ መሆኑ ነው፡፡ ከሮም ከተማ ርቀው ይገኙ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ቱርክ ያሉት የኔሮን ሰደት ሳይሆን የሚያውቁትና የተለማመዱት የዶሚኑስን ሰደት ነው ብለው ያስባሉ፡፡
፬. በራዕይ 2 እና 3 የተጠቀሱት ሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት በአካባቢያቸው ከነበሩት ተቃዋሚዎች የሚደርስባቸው ስደት እንዳለ እንጂ ደብዳቤው በተጻፈላቸው ጊዜ ከገዢ ይቀበሉት የነበረ መከራ እንዳለ አልተገለጸም በማለት በኋላኛው ጊዜ ተጻፈ የሚለውን ይደግፋሉ፡፡ እነዚህ አራቱም የመከራከርያ ማስረጃዎች በባህርያቸው ውጫዊ ዝንባሌ ያላቸው ናቸው። ከመጽሐፉ የሚጠቅሱት ምንባብ ቢኖራቸው እንኳ ማስረጃቸውን ያስደገፉት በምንባባቱ ዝምታ ላይ ነው እንጂ ምንባባቱ በግልጽና በቀጥታ የሚያቀርቡትን ሙግት አይደግፉም።
፭. የኋለኛው ዘመን ላይ እንደተጻፈ የሚቀርብ ውጫዊ ማስረጃ ዋናው የመከራከሪያ ጭብጥ አሁንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያለ ምስክርነት ሆኖ የሚቀርበው እና በርካታ የቤተክርስቲያን አበው ዩሐንስ ራዕዩን በጻፈበት ጊዜ ዶሚኑስ ንጉሰ ነገስት ነበር የሚሉት በኢራኒዮስ ምስክርነት ላይ ተመስርተው ነው፡፡ ኢራኒዮስ “ኑፋቄን በመቃወም” በተሰኘው መጽሐፉ እንዲህ የሚል ቃል አስፍሯል፡-
“እንግዲህ ይህ እንደዚህ ከሆነ፣ ይህም ቁጥር (666) በሁሉም መልካም የጥንት ቅጂዎች ውስጥ የሚገኝ ከሆነ፣ ዮሐንስንም ፊት ለፊት ያዩት ሰዎች ከመሰከሩ፣ እንዲሁም የአውሬው ስም ቁጥርም በግሪኩ የፊደል ገበታ ቀደም ተከተል መሰረት እንደሆነ አመክንዮ ካስተማረን፣ እንግዲያውስ የክርስቶስ ተቃዋሚ የተሰኘውን ስም በአወንታዊ መልኩ የመጥቀስን ኃላፊነት አንወስድም፤ ስሙም በዚህ በአሁኑ ዘመን በከፍተኛ ደረጃ መገለጥ ያለበት መሆኑ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ፣ የአቡቀለምሲሱን ራዕይ ባስተላለፈልን በእርሱ በራሱ በተነገረን፡፡ የታየውም በእኛው ዘመን በደሚኖስ ዘመነ መንግስት ማብቂያ ላይ ነው እንጂ፣ ከታየ በጣም ረጅም ጊዜ አላስቆጠረምና ነው፡፡”
ይህ የኢራኒዩስ አባባል ግን በትርጉሙ ሲያከራክር ኖሯል፡፡ በዶሚኖስ ዘመነ መንግስት ማብቂያ ላይ ምን ነበር የታየው? ዮሐንስ ያስተላለፈው ራዕይ? ወይስ በነዚያ በመሰከሩ ሰዎች ፊት ለፊት ታይቶ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ራሱ? “የታየው” (ታይቶ የነበረው) የሚለው ቃል/ ሐረግ ምንአልባት የመጀመሪያውን ትርጉም ‹ታይቶ የነበረው እርሱ› የሚለውን አነባበብ የለወጠ ወይም የተካ አገባብ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ፣ እንግዲያውስ ሊያረጋግጥ የሚችለው ዮሐንስ አቡቀለምሲሱን ቀደም ብሎ ጽፎ፣ የኖረው ግን እስከ ዶሚኑስ ዘመነ መንግስት ድረስ ነው የሚለውን ያረጋግጣል፡፡
ኢራኒዮስ፣ ራዕዩ የተጻፈው በኋለኛው ዘመን ነው የሚል ከሆነ፣ እንግዲያውስ የእርሱ ምስክርነት ትኩረት የሚሰጠው እና ክብደት ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ ኢራኒዮስ ሐዋርያው ዮሐንስን በአካል የሚያውቀውን ፖሊካርፕን በአካል ያውቀዋልና በዚህ ምክንያት ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት የታሰረበትን ጊዜ ትክክለኛ መረጃ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በርካታ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ኢራኒዮስን ተከትለው ራዕዩ የተጻፈበትን ዘመን በተመለከተ ተመሳሳይ የሆነን ጊዜ ያመለክታሉ፡፡
ነገር ግን ከፍ ሲል ይህ የኢራንዩስ ምስክርነት አከራካሪነት አለው ስንል እንደጠቀስነው፣ ሊከተል የሚችለው ጥያቄ የኢራኒዮስ አባባል ትክክለኛ ትርጉም ይህ ነው ወይ? የሚል ነው፡፡
የኢራኒዮስን አባባል ለመተርጎም በዶሚኖስ ዘመነ መንግስት የታየው ዮሐንስ ራሱ እንጂ ራዕዩ አይደለም በማለት ከፍ ሲል ዋቢ ያደረግኋቸው የኃላፊያኑ አመለካከት ሊቂ ዶክተር ኬኔት ጄንትሬ አንዳንዱ ቋንቋዊ፣ አንዳንዱ አውዳዊ፣ አንዳንዱ ደግሞ አመክኒዮአዊ የሆኑ ሰባት ጠንካራ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡
ለምሳሌ፡- ከኢራኒዮስ በተወሰደው ጽሁፍ የመጀመሪያው መስመር ላይ የራዕይ መጽሐፍ “በሁሉም… የጥንት ቅጂዎች” ሲል ይጠቅሳል፡፡ ይህም የሚያሳየው ይህ አረፍተ ነገር ከመጻፉ በፊት አስቀድሞ መጽሐፉ ለረጅም ጊዜ በዚያው ዘመን አካባቢ ነበር እንደ ማለት ነው፡፡ “የጥንት ቅጂዎች” የነበሩ ከሆነ፣ የመጀመሪያው ታዲያ የበለጠ ጥንታዊ አይሆንምን? ሆኖም በኢራኒዮስ ግምት የዶሚኑስ ዘመነ መንግስት በጣም የጥንት ታሪክ ነው ተብሎ አይወሰድም፣ ምክንያቱም ኢራንዪስ ስለ ጊዜው ሲናገር “በእኛው ዘመን” ብሏልና፡፡ ኢራኒዮስ በእርሱ ዘመን እንደተጻፈ ስለሚናገርለት ስለ መጀመሪያው መጽሐፍ እንዴት ጥንታዊ ቅጂ ብሎ መናገር ይቻለዋል? የዶሚኑስን ዘመነ መንግስት በመጥቀሱ ኢራኒዮስ የተናገረለት ዘመን ዮሐንስ አቡቀለምሲሳዊውን ራዕይ ካየበት ጊዜ ይልቅ ዮሐንስ በወንድሞቹ የታየ የመጨረሻ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
ሌላው የኢራንዩስ ምስክርነት ችግር የጽሁፎቹ ተዓማኒነት ችግር እንደሆነ በሰፊው ይታወቃል፡፡ የራዕይ መጽሐፍ ስለተጻፈበት ትክክለኛ ጊዜ ኢራንዩስ በግልጽ ምንም ያለው ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢራንዩስ ከጽሁፎቹ በአንዱ ስለ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ቆይታ ሲነግረን እንኳ አገልግሎቱ የተጠናቀቀው በግምት በሃምሳ አመታት ውስጥ ነው በማለት ኢየሱስ የኖረው 50 ዓመት ያህል እንደሆነ ይናገራል፡፡ በዚህ ምክንያት ጀንተሬይ ሲያጠቃልሉ “የራዕይ መጽሐፍ የተጻፈው በኋለኛው ጊዜ ላይ ነው ብሎ ኢራንዩስን ዋቢ ማድረግም ሆነ፣ በወፍራም ድምጸት ጮክ ብሎ "ኢራንዩስ እንዲህ ብሏል" በማለት እንደ ዋና መከራከርያ የእርሱን ጽሁፎች መጥቀስ ተዓማኒነት ይጎድለዋል” ይላሉ፡፡
ውስጣዊ ማስረጃ የተባለውን ደግሞ እንመልከት፡፡ ይህም ማለት ራሱ የዮሐንስ ራዕይ መፅሐፍ የተፃፈበትን ወቅት የሚጠቁም ምስክርነት በውስጡ አለው ማለት ነው፡፡ በዚህች ጽሁፌ ዋና ዋና የሆኑትን ማስረጃዎች እያቀረብሁ ወደ አውራው ክርክር አልፋለሁ።
ኢየሩሳሌም ከመፈራረስዋና መቅደስዋም ተቃጥሎ ከመውደሙ በፊት ቀደም ብሎ በቄሳር ኔሮ ዘመነ መንግስት ጊዜ ተቀስቅሶ በነበረው የስደትና የመከራ ወቅት ራዕዩ ያኔ ተጽፏል ለሚለው ሙግት ከሚቀርቡ ውስጣዊ ማስረጃዎች መካከል ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
፩ኛ. በርካታ “ቶሎ” እና “ቀርቦአል” የሚሉት ጊዜን አመልካች የሆኑ ቃላት በምንባባቱ (1÷ 1፤ 2÷ 16፤ 3÷ 11፤ 22÷ 6-20 ይመለከቷል) ውስጥ ትርጉም ሊሰጡን የሚችሉት፣ ሁነቶቹ በራእይ መጽሐፍ ከተገለጹት ምልክቶችና ምስሎች ጋር ተጋጥመው ፍጻሜያቸው ወደ ፊት ሊሆን ላለው ፍርድና ብድራት በጣም ሩቅ ያልሆኑ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡
፪ኛ. ራዕዩ በተጻፈ ጊዜ ቤተ መቅደሱ በኢየሩሳሌም ታይቷል፣ ተለክቷልም (11÷ 1-2)፡፡ ያኔ ገና አልፈረሰም ነበር ማለት ነው። ይኸውም ከ70 ዓ.ም በፊት መሆኑ ነው፡፡ ራዕዩ ከመጻፉ በፊት ቀደም ብሎ ቤተ መቅደሱ ፈርሶ ቢሆን ኖሮ ግን ያንን የሚገልጥ አንድ ሃሳብ በመጽሐፉ አንድ ቦታ ላይ መኖር ነበረበት፡፡ ከዚህም በላይ የፈራረሰ፣ ያበቃለትንና የሌለ ቤተ መቅደስ በራእይ መለካት ፈጽሞ ትርጉም የሌለው ጉዳይ ነው።
ይህ አይነተኛው መከራከሪያ በመሆኑ ማስረጃውን ዘርዘር አድርጌ ማቅረብ ይኖርብኛል። ራእዩ ሲጻፍ ቤተ መቅደሱ ገና አልፈረሰም ነበር ማለት ምን ማለት ነው?
"በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፥ እንዲህም ተባለልኝ። ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።" (ራዕ11 ÷1-2)
ጥቅሱ የሚያመለክተው "የተቀደሰችው ከተማ" ተብላ በምትጠራ ሥፍራ ቆሞ ስላለ ቤተ መቅደስ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መፃህፍት ላይ ተመስርተው እንደ ዮሐንስ ያሉ ክርስቲያን አይሁዶች ምን ጊዜም ቢሆን በሃሳባቸው ታሪካዊቷን ኢየሩሳሌምን "ቅድስቲቱ ከተማ" ብለው እንደሚጠሩአት ከብሉይ ኪዳን ልናውቅ እንችላለን፡፡
"ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፥ ኃይልሽን ልበሺ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ አይገባብሽምና ጌጠኛ ልብስሽን ልበሺ።" (ኢሳ 52÷ 1)
"የሕዝቡም አለቆች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ ከቀሩትም ሕዝብ ከአሥሩ ክፍል አንዱ በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም፥ ዘጠኙም በሌሎች ከተሞች ይቀመጡ ዘንድ ዕጣ ተጣጣሉ።" (ነህ 11፥ 1)
ዮሐንስ በራእዩ "የተቀደሰችው ከተማ" ሲል የጠራት ኢየሩሳሌምን ሲሆን በመጽሐፉ ሌላ ክፍል ደግሞ እንዴት እንደሚገልጣት ተመልከቱ፦
"በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።" (ራዕ11፥ 8)
ከተማይቱ ጌታችን የተሰቀለባት ቦታ ናት፤ ይህችም ከተማ የኢየሩሳሌም ከተማ ብቻ ናት፡፡ ታዲያ በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ የትኛው ቤተ መቅደስ ነው? የተባለ እንደሆን፣ ንጉሱ ሄሮድስ ያሰራው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተብሎ የሚታወቀው ቤተ መቅደስ ብቻ ነው፡፡ ታላቁ ሄሮድስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ0037 ላይ ወደ ዙፋን ሲመጣ የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ከቀድሞ በተሻለ በማስፋት እና አሳምሮ በመሥራት በንጉሳዊ ተመራጭነቱ አየሁዳዊ የሆኑት የግዛቱን ነዋሪዎች ደስ ለማሰኘት በመፈለግ ሮማውያንንም ለማስገረም ተንቀሳቅሶ ነበር፡፡
ይህ ጥንታዊውን ቤተ መቅደስ የሚያመለክት ንግግር እንደሆነ ታሪካዊ ይዘቱን የሚጠቁሙ የሚከተሉትን ምክንያቶች ላቅርብ፡-
1. ከሁሉ በፊት ቤተ መቅደሱ ያለበት ቦታ ኢየሩሳሌም ነው።
2. እንደ ዮሐንስ ራዕይ 11፥ 2 ከሆነ ለ42 ወራት ከተማይቱ ልትረገጥ ወይም ጥቃት ሊደርስባት ተወስኗል። ይህ ማለት፣ ኔሮ በእስራኤል ላይ ጦርነት እንዲከፍት ያለ የሌለ ጦሩን አስከትቶ ሮማዊውን ጀነራል ፍላቪያስ ቨስፖሲያንን ያዘመተው ከክ.ል.በኋላ በ0067 የካቲት ወር ላይ ነበር። ወራሪው ኃይል በትክክል ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ኢየሩሳሌም የገባው እና ጦርነት የገጠመው በዚያ የጸደይ ወራት ወቅት ሲሆን ይህ የአይሁድ ሮም ጦርነት የተጠናቀቀው ደግሞ የአይሁድ ማህበረሰብ መታወቂያና መገለጫ የሆነው ቤተ መቅደሱ ፈጽሞ በተደመሰሰበት በነሐሴ ወር በ70 ዓ.ም ላይ ነው። ይህ ጊዜ በጠቅላላ ሲቆጠር በትክክል "አርባ ሁለት ወር" ይሸፍናል፡፡
ሉቃስ 21÷ 20 የቤተ መቅደሱን መፈራረስ አስመልክቶ ጌታ ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢታዊ ቃል ይዟል "ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደቀረበ እወቁ።"
በራዕይ 11 ላይ የተቀመጠውና ጊዜን አመልካች የሆነው ቃል ስለ አይሁድ ጦርነት ታሪክ ከሚነግረን እውነታ ጋር ይስማማል፡፡
3. የራዕይ 11÷ 1 እና 2 አወቃቀር ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ከተናገረው እና በሉቃስ 21÷ 20-24 ከተዘገበው ፍካሬው ጋር ትይዩ ሆኖ አብሮ የሚሄድ ነው፡፡
በሉቃስ 21÷ 5-7 ደቀ መዛሙርቱ ወደ እየሩሳሌም እያመለከቱ ስለ ከተማይቱና ቤተ መቅደሱ የወደፊት እጣ ፋንታ ጥያቄ ሲያቀርቡ ይታያል፡፡ ኢየሱስም ለጥያቄአቸው መልስ ሲሰጥ በቅርቡ "ድንጋይ በድጋይ ላይ" እንደሚፈርስ ይነግራቸዋል፡ ፡
በሉቃ 21÷ 24 ላይ ከፍ ብለን ያነበብነውና “የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች” የሚለው በራዕይ 11÷ 2 ላይ "በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል" ሲል የተስተጋባውን ሃሳብ የያዘ ነው፡፡ እነዚህም ሁለት ምንባባት የኢየሩሳሌምን መደምሰስ የሚናገረውን ያንንው አንዱን ሁነት በተመለከተ የተነገሩ ናቸው፡ ፡
ታዲያ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተጻፈው መቼ ነው? ዘግይቶ ኋላ ላይ ተጽፎአል የሚለው አመለካከት ወይንስ ቀደም ብሎ ተጽፎአል የሚለው አመለካከት የትኛው ትክክለኛና ሚዛን የሚደፋ አመለካከት ነው?
ከታሪካዊ እና ከምድር ቁፋሮ የቅርስ ምርምር ማስረጃዎች እንደምንረዳው ቤተ መቅደሱ የፈራረሰው እና የተደመሰሰው በ70 ዓ.ም ነው፡፡ ዮሐንስ ራዕዩን በጻፈ ጊዜ ቤተ መቅደስ ገና አሁንም ቆሞ ከነበር፣ ስለዚህ ይህ የዚህች ከተማ ውድመትና የቤተመቅደሱ መፈራረስ ትንቢታዊ ይሆን ዘንድ ራእዩ መጻፍ ያለበት ከ70 ዓ.ም በፊት መሆኑ አስተማማኝ ነው፡፡
፫ኛ. በእስያ 7 አብያተ ክርስቲያናት ብቻ የነበረበት ጊዜ በ60ዎቹ መጀመርያ ላይ ነበር፡፡ ራእዩ በ96 ዓ.ም ላይ ተጽፎ ቢሆን ኖሮ በዚያን ጊዜ በአካባቢው የነበሩት አብያተ ከርስቲያናት ከ7 በላይ ስለነበሩ የሁሉንም ዝርዝር በጠቀሰ ነበር።
፬ኛ. ራዕይ 2÷ 2 ሌሎች ሐዋርያት እንደነበሩ ያመለክታል፡፡ ሆኖም ከዮሐንስ በቀር ሁሉም ከ70 ዓ.ም በፊት እንደሞቱ ይታመናል፡፡
፭ኛ. ራዕዩ በተጻፈ ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ አይሁዳዊ ከሆነው ኃይማኖታዊ ተቃርኖ ጋር የነበረው ውጥረት ገና እንዳለ ነበር (ለምሳሌ 2÷ 9 ፤3÷ 9)፡፡ ኢየሱስ በራዕዩ ለቤተ ክርስቲያን የሚነግራት የማያምኑት አይሁድ በእውነት አይሁድ እንዳልሆኑ፣ እነርሱ ራሳቸውን አይሁድ ነን ይላሉ እንጂ አለመሆናቸውን ነበር። እነርሱ መድህን ሊሆንላቸው የመጣውን ኢየሱስን የግፍ አገዳደል የፈጸሙበት ነበሩ። በእውነትም የእርሱ አይሁድ ክርስቶስን በማመን መንፈሳዊ አይሁድ የነበሩት ናቸው እንጂ በሥጋ አይሁድ የሆኑት አይደሉም። "እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ፦ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።" (ራዕይ 3÷ 9) እንግዲህ ይህ ሁኔታ የተለወጠው ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም በሮማውያን ስትደመሰስ በመሆኑና ከ70 ዓ.ም በኋላ ይህ የማይታሰብ በመሆኑ ይሁዲነትና ሐይማኖታዊ መሰረቱ ከአቅመ ክርክር ውጭ ሆኖአል፡፡ ይሁዲነት ሕልውናው ቤተ መቅደሱ ቆሞ እስካለና የመስዋእት ስርአቱ እሰከተካሄደ ድረስ ብቻ ነበር። የአይሁዳዊነት ርዕሰ ጉዳይና ሌጋሲ ከ70 ዓ.ም በኋላ ምንም ትርጉም የለውም፣ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ የቀረ ምንም የአይሁድ ዘርም ሆነ ሐይማኖታዊ አገዛዝ የለም፡፡ የራእይ መጽሐፍ በ96 ዓ.ም ላይ ተጽፎአል የሚለው የሊቃውንቱ ድምድዳሜ ግን የመጽሐፉን ውበት ያጠፋዋል። ጥንታዊው የራዕይ መጽሐፍ ቅጅ ግን "ራዕዩ የተጻፈው ኔሮ ቄሳር በነበረበት ዘመን (ማለትም ከ68 ዓ.ም በፊት) ነው" ይላል፡፡
፮ኛ. ሌላው አስፈላጊ መከራከሪያ በራዕይ 17÷ 10 ላይ ራዕዩ በተጻፈበት ጊዜ ይገዛ ስለነበረው ንጉስ የሚናገረው ነው፡፡ “ሰባት ነገስታት…አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ የቀረውም ገና አልመጣም ሲመጣም ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል::" የዚህ ቃል ትክክለኛ ትርጉም ራዕዩ ከመጻፉ በፊት አምስት የሮም መንግስታት በተፈራራቂነት እንደነበሩ እና እንደወደቁ ፣ ስድስተኛው ድግሞ ራዕዩ በተጻፈ ጊዜ ይገዛ የነበረ ንጉስ መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ በሮም ግዛት ቄሳር ኔሮ ስድስተኛ ንጉስ ሆኖ የገዛ በመሆኑ ራእዩ የተጻፈው በዚያው በኔሮ ዘመነ መንግስት ውስጥ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ይህም ነጥብ ሌላኛው አይነተኛ መከራከሪያ በመሆኑ ማስረጃው ዘርዝር ተደርጎ መቅረብ ይኖርበታል። ራእዩ ሲጻፍ ቄሳር ኔሮ ገና በዙፋኑ ላይ ነበር ማለት ምን ማለት ነው?
ራዕይ 17 ራዕዩ ቀደም ባለው ጊዜ ተጽፏል ለሚለው አመለካከት የሚጠቀስ ብርቱ ውስጣዊ ማስረጃ ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ስለ ባለሰባት ራሱ አውሬ የተጻፈ ራዕይ ተዘግቧል፡፡ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ከቄሳር ኔሮ ሞት በፊት ቀደም ብሎ ለመጻፉ ይህ ሁኔታ ግልጽ ማስረጃን ያቀርብልናል፡፡ ኔሮ ራሱን ያጠፋው ሰኔ 9 ቀን 68 ዓ.ም ላይ እንደሆነ ይታወቃልና፡፡
"ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ ና በብዙም ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አ ውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ። ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጎናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤ በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም ታላቂቱ ባቢሎን፥ የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት ተብሎ ተጻፈ። ሴቲም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ።" (ራዕ 17÷ 1- 6)
"ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፥" ራዕ 17÷ 9
በዚህ የንባብ ክፍል ቁጥር 1፣ 3 እና 6 ላይ የራዕዩን ምንነት ሲያብራራ ቁጥር 9 ደግሞ የራዕዩን ትርጉም የሚያመለክት ሃሳብ ይፈነጥቅልናል፡፡
ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ማለት በሚቻልበት ደረጃ የራዕይ 17÷ 9 "ሰባት ተራራዎች" የሮምን ሰባት ተራራዎች ይወክላሉ ብለው ይሰማማሉ፡፡ "ጠቢብ የሆነ ይህንን ሚስጥር ይረዳዋል" ብሎ ዮሐንስ ይጠቁመናል፤ የዚህ መልዕክት በኩረ ተደራሲያን ይኖሩ የነበረው በመላው ዓለም በሰባት ተራራዎቹ ተለይቶ በሚታወቀው በሮም አገዛዝ ስር ነበር፡፡ በሮም ንጉሳዊ አገዛዝ ስር በትንሹ እስያ በነበሩ ሰባት ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ እነዚያ የዚህ መልዕክት ተደራሲያን ከዚህ የመልክዓ ምድር ገጽታን አመልካች ከሆነ ንግግር ተነስተው ከዚህ የተለየ ሌላ ነገር ሊያስቡ ከቶ አይችሉም።
"ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፥ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።" ራዕይ 17÷ 10
ይህ ጥቅስ እንደሚያሳየው ሰባቱ ራሶች የዚያን ወቅት ፖለቲካዊ ሁኔታን ያመለክታሉ። "ሰባቱ ነገስታት ደግሞ ናቸው" እነዚህ ሰባቱ ራሶች ከቄሳር ሥርወ መንግስት ጋር እንዴት እንደሚናገኙ ያሳያል፣ "አምስቱ ወድቀዋል" /የሃላፊ ጊዜ አመልካች ነው/ የመጀመሪያዎቹ አምስት ቄሳሮች ጁለየስ፣ አውግስጡስ ፣ ጢባርዮስ፣ ካሊጉላ እና ቀላውዴዎስ ነበሩ፡፡ እነዚህም ዮሐንስ ራእዩን ከመቀበሉ በፊት ቀደም ባሉት አመታት ውስጥ ተፈራርቀው የነገሱ ነገስታ ናቸው። "አንዱም አለ" /የአሁን ጊዜ አመልካች ነው/፣ ይህም ስድስተኛው ንጉስ ቄሳር ኔሮ ነበር፣ እርሱም ዮሐንስ ራዕዩን በፃፈበት ጊዜ ገና በዙፋኑ ላይ ነበር፡፡ ኔሮ ደግሞ የገዛው ከ54 ዓ.ም እስከ 68 ዓ.ም ድረስ ነበር፣ በ68 ዓ.ም ኔሮ ራሱን ሲያጠፋ ያኔ ግዛቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች፡፡ "የቀረውም ገና አልመጣም ሲመጣም ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል" /ይህም የወደፊት ጊዜን አመልካች ነው/። ይህም ሰባተኛው ቄሳር ጋልባ ነው፣ እርሱም ዮሐንስ ራእዩን ከተቀበለና ከጻፈ በኋላ ጥቂት ጊዜ ማትም ከ7 ወራት ያነሰ ጊዜ / ከሰኔ 68 ዓ.ም እስከ ጥር 69 ዓ.ም ብቻ/ ቆይቶ ገዝቷል፡፡
በራዕይ 17÷ 7 ላይ መልዓኩ "አትደነቅ.... ምን ማለት እንደሆነ እኔ አሳይሃለሁ" ይለዋል፣ በቁጥር 9 እና 10 ላይ ራዕዩ ሲብረራ እናያለን፡፡ ሰባቱ ራሶች የሚያመለክቱት አንድ ታሪካዊ ቦታን ማለትም ሮምን እና አንድ ፖለቲካዊ ሁኔታን ማለትም የኔሮን አገዛዝ ነው፡፡ እንግዲህ የዮሐንስ ራዕይ ኔሮ በ68 ዓ.ም ራሱን ከማጥፋቱ በፊት ቀደም ብሎ የተጻፈ መሆን አለበት። ውስጣዊ ማስረጃ የምንለው በግልጽ የሚያሳየው ራዕዩ "አንዱም አለ" የተባለው ስድስተኛው ንጉስ ይኸውም ቄሳር ኔሮ ገና በሮም ግዛት ሁሉ እየገዛ በነበረበት ጊዜ ቀደም ብሎ መጻፉን ነው፡፡ "አለ" የተባለው የአሁን ጊዜ አመልካች ቃል ዮሐንስ ራእዩን የሚጽፍበትን ጊዜ ያመለክታልና። እንግዲህ በየተራ የነገሱትን የሮም ቄሳሮችና የግዛታቸውን ዘመን ከታሪክ ማህደር ስንመረምር ነብዩ ዮሐንስ በራእዩ ሊያመለክተን የፈለገው አይነተኛ ዘመን የቱ እንደሆነና መጽሐፉም መቼ እንደተጻፈ በማያሻማ ማስረጃ እናረጋግጣለን።
፯ኛ. ሌላው ማረጋገጫ ኔሮ የተሰኘው ስያሜ 666 ከተሰኘውና በራእይ 13 ከተጠቀሰው የአውሬው ቁጥር ጋር ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በዚያን ዘመን የፊደል ገበታ (Alphabetical Symbols) ቁጥርን ወክለው ያገለግሉ እንደነበር የታወቃል። ጽኑ ሥደትና መከራ በነበረበት በዚያ ክፉ ዘመን ዮሐንስና ጠቅላላው ቤተ ክርስቲያን ያለ ጊዜው ራሳቸውንና ሌሎችን ለአደጋ ላለማጋለጥ በዋናነት ምልክቶችን ለመግባቢያነት የመጠቀም ልምምድ ነበራቸው። በዚህ መሰረት "ቄሳር ኔሮ" የሚለው ስያሜ በግሪኩ የፊደል ገበታ ቅደም ተከተል በሚሰጠው ቁጥር የሂሳብ ቀመር 666 የተሰኘውን ቁጥር በምልክትነት ያመጣል፣ ይኸውም፡-
N = 50 q = 100
R = 200 o = 60
W = 6 ደግሞም r = 200
N = 50
=306 =360
(ስለዚህ 306 + 360= 666 እንደ ማለት ነው)፡፡
፰ኛ. በተጨማሪም የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያንን ዝምታ ዋቢ የሚያደርጉ አጥኝዎች የሚሰጡት አስገራሚና አወዛጋቢ ምክንያት "ቅዱሳን ተነጥቀው ሰለነበር ያንን ሁነትና ታሪክ ዘግቦ ለማስቀረት የቻለ ማንም አልነበረም" የሚል ነው። (ይህ "የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አካላዊ ንጥቀት" ርዕሰ ጉዳይ ግን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በወጉ ጥናት ሊደርግበት ይገባል፤ ምናልባት እንድተባለው ክርስቲያኖች ያኔ በአካል ተነጥቀው ከምድር ላይ መወሰዳቸው እውነት ከሆነ የአመለካከት ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት አለኝ።)
በእኔ እምነት ከመጽሐፉ ርቆ ሙግቱን በውጫዊ የታሪክ ዘገባ ላይ ካስደገፈው ቀጣዩ መከራከርያ ይልቅ ከራሱ ከመጽሐፉ ውስጣዊ ማስረጃውን እያቀረበ መጽሐፉ ቀደም ባለው ጊዜ መጻፉን የሚያረጋግጠው እስካሁን ያየነው ይህ ሙግት ከሁሉ የተሻለና እጅግ አስተማማኝ የሆነ ለጥናታችንም የሚረዳን የራዕይ መጽሐፍ የተፃፈበትን ትክክኛ ጊዜ የሚጠቁመን ነው እላለሁ።
በመጨረሻም መጽሐፉ የተጻፈበትን ጊዜ በመወሰን ላይ ማጠቃለያ አድርጌ ላቀርብ የምወደው ታዋቂው የሥነ አፈታት ሊቅ ሚልተን ቴሪ የተናገሩትን በመጥቀስ ነው፡- “የዮሐንስ አቡቀለምሲስ የተጻፈበትን ትክክለኛ ወቅት መቼ እንደሆነ በሚሰነዘሩ የክርክር ሃሳቦች ላይ እና ታሪካዊ አቋሞች ላይ እርግጠኛ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነጥብ ነው፡፡ይህ የትንቢት መጽሐፍ ከኢየሩሳሌም ውድቀት በፊት ቀደም ባለው ጊዜ የተጻፈ ከሆነ እንግዲያውስ በርካታ የሆኑ እነዚያ ከዚያች ከተማና ከውድቀትዋ ጋር ግንኙነት ያላቸው ነገሮች ሁሉ እያንዳንዳቸው ተጨባጭ በሆነ መልኩ ከትንቢቱ ፍጻሜ ጋር የተገናኙ መሆን አለባቸው፡፡ ነገር ግን በርካቶቹ እንደሚያምኑት በዶሚኑስ ዘመን ማብቂያ ላይ (በ96 ዓ.ም አካባቢ) ተጽፎ ከሆነ፣ እነዚያን ታሪካዊ ሁነቶች ለመተርጎምና ለማብራራት ሌላ የትርጉም መንገድ መፈለግ የግድ ይሆናል፡፡”
እንግዲህ እነዚህ ማስረጃዎችና የክርክር ጭብጦች ሁሉም ተርጓምያን ራእይን ለመተርጎም ከመነሳታቸው በፊት በመጀመርያ ሊያውቁአቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። አለበለዚያ ግን በትምህርታቸው ቤተ ክርስቲያንን በዝባዝንኬ ተረት ተረት ሲሞሏት ይገኛሉ።
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/
No comments:
Post a Comment