Monday, November 5, 2018

የጌታ ምጽአት መቼ እና እንዴት ክፍል ሰባት

የጌታ ምጽዓት መቼ እና እንዴት ነው?
በማቴዎስ 24 እንደተገለጸ

♦ በማቴዎስ 24 ኢየሱስ መቼ እንደሚመለስ አስመልክቶ ለደቀ መዛሙርቱ ሁለት ዋና ዋና የሆኑ መልሶችን ይሰጣቸዋል፡፡ ሁለቱም መልሶች ተስማሚ ናቸው፣ ኢየሱስ የሚመለስበትን ጊዜ በምን ወቅት እንደሆነ የጊዜውን ማዕቀፍ እንዲለዩ ሁለት የተለያዩ መንገዶችን ይሰጣቸዋል፡፡ ቁጥር 30 የኢየሱስን የመጀመሪያ መልስ ይነግረናል፤ ቆየት ብለን በሌላ ክፍለ ጊዜ የምናየው ቁጥር 34 ደግሞ ሁለተኝውን መልስ ይሰጠናል። አሁን ግን ቁጥር 30 ላይ የተገለጸውን ቀዳሚውን እንይ፦

ቁ.30፦ “የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል”
[በደመና ስለመምጣት በተለይ በሐዋርያት ሥራ 1 9-11 ላለው ቃል የተሰጠውን ማብራሪያ ተመልከቱ።]
ከዚህ ቀደም ሲል ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ስለምን ነበር? ያልን እንደሆነ፣ የኢየሩሳሌምን ውድመት ስለሚቀድሙ ምልክቶች፣ ከተማይቱንና ቤተ መቅደሱን ስለሚያጠፋው ጦር ሠራዊት እንዲሁም በእነዚህ ጊዜያት ስለሚሆነው የሕዝቡ ጭንቀትና መከራ በተጨማሪም ስለ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነብያት መነሳት ነበር፡፡

ኢየሱስ ስለ እነዚህ ነገሮች እየተናገረ ሳለ፣ ቀጥሎ “በዚያን ጊዜም”  የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል፣ የዚህ ሐረግ ትርጉሙም እነዚህ ሁሉ ሁነቶች በሚፈጸሙበት ጊዜ ማለት ነው፣ ያኔ ይህ ሁሉ ሲሆን ይመጣል (ቁጥር 30)፡፡ በጊዜው ቅዱሳን እንዲጠብቁት የተነገራቸውን ጊዜ ስተን ዘመኑን ከኹነቱ እንዳንነጥል መጠንቀቅ ይኖርብናል።

ለእምነታችን ሌላ ምንም ተጨማሪ ማረጃና ድጋፍ ሳያሻን ትንቢቱ የሚፈጸምበትን ጊዜ ወስኖ የነገራቸው ጊዜን አመልካች የሆነው የራሱ የኢየሱስ ግልጽ ንግግር ከበቂው በላይ አለን። በምዕራፍ 23፥ 36 "ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል" ሲል ጊዜውን አስረግጦ ትንቢቱን መናገር የጀመረው ኢየሱስ አሁንም በትንቢቱ ማጠቃለያ ይኸንንው ጊዜን አመልካች የሆነ ንግግር በመጠቀም ትንቢቱ የሚፈጸምበትን ወቅት "እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።" ሲል በምዕራፍ 24፥ 34 ላይ ይናገራል። በዚሁ መሰረት ልክ ከ40 አመታት በኋላ ኢየሩሳሌም በሮማውያን ፈጽማ ተደመሰሰች። ከአውደ ምንባብ አገባብ አንጻር። "ይህ ትውልድ" የሚለው የምዕራፍ 24፥ 34 ንግግር ከማቴዎስ 23፥ 34 ንግግር ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚሁ በምዕራፍ 24 ውስጥ እየደጋገመ ለዘጠኝ ጊዜ ያህል “በዚያን ጊዜ” ተብሎ የተገለጡውን ሐረግ የምንረዳውም በዚሁ እግባብ ነው።
ቁ. 9  በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
ቁ. 10  በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤
ቁ. 14  ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።
ቁ. 16  በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥
ቁ. 21  በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።
ቁ. 23  በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤
ቁ. 30  የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤
ቁ. 40  በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤

ኢየሱስ እመጣለሁ ያለበት ጊዜ በይሁዳ ሕዝብ ላይ ይደርሳል ብሎ የተነበየው የእግዚአብሔር ፍርድ በሚፈጸምበት ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ “በዚያን ጊዜ” የሚለው ሐረግ “ያኔ” እንደ ማለት ሲሆን፣  በማቴዎስ 24 የተተነበየው ምጽዓቱን ቤተ መቅደሱን የሚያፈርስ ሠራዊት ሲመጣ የሚሆን ያደርገዋል፡፡ ይህ "በዚያን ጊዜ" የተባለው ወቅቱ መቼ ነው? ቢባል የሚያመልክተው በቁጥር 29 ላይ የተጠቀሰውን “ ከዚያች ወራት መከራ በኋላ” የተሰኘውን ነው ። የዳግመኛ ምጽአቱን ወቅት ቤተ መቅደሱ ከፈረሰበት ጊዜና ታሪክ ነጥሎ መጠባበቅ ለእግዚአብሔር ቃል ባእድና እንግዳ የሆነ ሌላ የልብ ወለድ ምጽአት ያደርገዋል።
በ70ው ዓ.ም ከሆነው የኢየሩሳሌም ውድመትና ታላቁ መከራ ጋር ይህ ምልክት ይታያል።  ሐሳቡ ላይ አጽንዖት እሰጣለሁ፣ ቤተ መቅደሱ የፈረሰው ሮማውያን በ70 ዓ.ም ሲመጡ እንደ ሆነ ከታሪክ እንረዳለን፡፡ “የዚያች ወራት ታላቁ መከራም” የሆነው ያኔ ነበር። ይህ ማለት ደግሞ ኢየሱስ እንደ ተስፋ ቃሉ ተመልሶ የሚመጣው በ70 ዓ.ም ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወቅቱን አስመልክቶ ከላይ ላነሳነው ጥያቄ ይህ የመጀመሪያው መልስ ነው፡፡ የመላው አዲስ ኪዳን ትምህርትም ከዚህ መልስ ጋር ይስማማል፡፡
እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ (ክሪሶሶም)፣ ቅዱስ ኦግስቲን፣ ጄሮም እና ኤራስመስ ያሉ አንዳንድ የጥንት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ምልክቱ በሰማይ የታየው መስቀል ነው ብለው ያምናሉ፡፡ አንዳዶችም ልደቱን ያመለከተው ኮከብ ተመልሶ መታየት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ አንዳንድ ዘመን ቆጣርያን ምልክቱ የሚያካትተው ከሰማይ የምትወርደውንና ከምድራዊቲቱ ኢየሩሳሌም በላይ ከፍ ብላ ተዘጋጅታ ያለችው ሰማያዊቱን የጠፈር ላይ ከተማ አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ሃል ሊንዴንሲ ደግሞ በበኩሉ “ምናልባት የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ሁሉ ሰው እንዲያየው የሚያንጸባርቅ እጅግ አስገራሚ የሆነው ሰማያዊ ምስል ይሆናል፡፡ ይኸውም ሁሉም ሰው በድንገት በመስቀሉም ላይ የተወጋውን የቁስሉን ጠባሳ በማየት እርሱ ማን እንደሆነ ያውቃሉ”  ይላል፡፡    
እዚህ ላይ ልብ ማለት እንደሚቻለው የንግግሩን አውዳዊ ጠቀሜታ ሳያስተውሉ እና ያንን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ የሚወሰድ ማንኛውም መላ ምት ምልክት ተደርጎ ሊቆጠር ይችል ይሆናል፤ ይህ ግን ግራ ተጋብቶ ሌላውንም ግራ ማጋባት እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ለመሆኑ ምልክት ጠያቂዎቹ እነማን ነበሩ? ደቀ መዛሙርቱ አልነበሩምን? (ቁ. 3) ኢየሱስስ ምልክቱን የሰጠው ለእነማን ነበር? ለደቀ መዛሙርቱ አይደለምን? ምልክቱ ምንም ይሁን ምንም ምልክትነቱ ከሁሉ በፊት ለምልክት ጠያቂዎቹ ነው። ምልክቱ የሚታይበት ጊዜ ደግሞ "በዚያን ጊዜ" በተባለውና የኢየሩሳሌም መፈራረስ ከሚሆንበት ከዚያች ወራት መከራ በኋላ ወዲያውኑ ነው፡፡ ይኸውም የ70ው ዓ.ም ወቅት ነው፡፡ ለዚያው ትውልድ የተሰጠ ምልክት ነበር እንጂ፣ ምልክት ጠያቂዎቹ እኛ ስላልሆንን ከ2000 ዓመታት በኋላ ስላለው ትውልድ (ስለ እኛ) የተሰጠ ምልክት አይደለም፡፡
    ይህ ምልክት ምን እንደሆነ ለመረዳት በመጀመሪያ ትክክለኛው ትርጓሜ ያስፈልገናል፡፡ አንዳንድ ትርጉሞች ምልክቱ የሚታይበትን ሥፍራ ሰማይ/ጠፈር (Sky) በማለታቸው እዚህ ላይ ለሚፈጠረው የመረዳት ስህተት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ የግሪኩን ትርጉም የቃል በቃል አነባበብ ካየነው ግን፣ ልብ መባል ያለበት ምልክቱ የሚታይበት ሥፍራ መንፈሳዊው ዓለም የሆነው ሰማይ (heaven) ነው እንጂ በእንግዚዝኛው ቃል ስካይ /sky/ ተብሎ የተቀመጠውና በአማርኛው ቃል ሰማይ ተብሎ የተተረጎመው ጠፈር አይደለም።
    ምልክቱም በሰማያት ያለው የሰው ልጅ ምልክት ነው፤ እንጂ በተፈጥሮው ዓለም  ሰማይ ወይም በጠፈር ላይ የሚሆን ምልክት አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይም ይኸውም የኢየሩሳሌምና የአይሁድ ቤተ መቅደስ መፈራረሰ የሰው ልጅ በሰማይ የመሆኑ ምልክት ነበር፡፡ ምልክቱ በሰማዩ ላይ የሚታይ ሌላ የትኛውም ምልክት ሳይሆን፣ ነገር ግን የኢየሩሳሌም መፈራረሰ የሰው ልጅ በሰማይ ላይ የመግዛቱ አመልካች ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ በዳንኤል 7÷ 13 ላይ  ወደ ተገለጸውና የሰው ልጅ ወደተባለው የሚወስደን ይሆናል፡፡ ኢየሱስ ስለ ምጽዓቱ ሲናገር እርሱን በተመለከተ ይህንን መጠሪያ አዘውትሮ ይጠቀማል፣ ለምሳሌ “መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤” (ማቴ 24÷ 27)፡፡
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ መጀመርያው ክፍለ ዘመን የፍርድ ምጽዓቱ  የነገራቸው  ፈጽሞ በአካላዊ ሁኔታ የሚገለጥ ስለመሆኑ አይደለም(ቁ 23-26 ተመልከቱ)። ይልቁኑ በፍርድ ተመልሶ የሚመጣው ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ ሊያጠፋት እንደሚችል መብረቅ ብልጭታ አይነት ሆኖ ነው (ቁ 27)። ይህ ምጽዓት በሚታይ አካል የሚሆን ተአምራዊ የፍርድ ምጽዓት ሳይሆን የልቁኑ በክርስቶስ የተመራና የተዘጋጀላቸው የፍርድ ምጽዓት ነበር።
በዚህ በማቴዎስ 24፥ 27 ላይ የተነገረው እንደ መብረቅ ብርቅታ የሆነው ምጽዓት በስፍራ ሁሉ ላሉ በይፋ ለሕዝብ ሁሉ በአንድ ጊዜ የሚታይ ተዳሳሽ መምጣት ጨርሶ አይደለም። ይልቁኑ "ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን" ሲሉ በራሳቸው ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ በጋበዙትና ፍርዱም እንደሚገባቸው በጠየቁ ሰዎች ላይ የሚመጣ ቁጣ ነው። ቃሉም፦ "እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤" (ሮሜ 1፥ 18) ይላል።
ጌታ እዚህ ላይ የሚናገረው "መብረቅ ከምስራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ" የተባለው ምሳሌአዊ ገለጻ በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚሆነው የፍርድ ምጽዓቱ ነው (ማቴ 23፥ 37- 24፥2)። ይህንን ምዕራፍ መተርጎም ስጀምር በልዩ ልዩ አጽንዖት ግልጽ ለማድረግ እንደጣርኩት ወቅታዊውና አካባብያዊ አውዱ የግድ "ይህ ትውልድ" (ቁ. 34) የሚለውን የጊዜ ማእቀፍ ይጠይቃል፣ ማለቴን አትርሱ፤ የሚያመለክተውም ቤተ መቅደሱ የሚፈራርስበትን ወቅት ነው።
በዚህ በማቴዎስ 24፥ 27 ላይ የተገለጠው የክርስቶስ የፍርድ ምጽዓት በትክክል የሚያሳየው ከኢየሩሳሌም በስተ ምስራቅ በኩል ዘምቶ የወረራትንና ከበባ የፈጸመባትን የሮምን ሰራዊት ነው። ጆሳፈስ የሮምን ወረራና የከበባውን ዘመቻ ሲተርክ በምስራቅ በኩል ተሰልፎ የመጣ መሆኑን ይዘግባል።

       በኢየሩሳሌም ላይ የሆነው ፍርድ የሰው ልጅ በዳንኤል 7÷ 13-14 ያለውን ትንቢት ለመፈጸም በሰማይ የመሆኑ ምልክት ነው፣ ትንቢቱም፡- “በሌሊት ራእይ አየሁ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” (ዳን 7÷ 13-14) የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ የሰው ልጅ የሆነውን ኢየሱስን በዘመናት ወደ ሸመገለው ሲመጣና ዘላለማዊ መንግሥቱን ሲቀበል እናየዋለን፡፡
ይህ ትንቢት የተፈጸመው ደግሞ በእርገቱ ወቅት እንደ ነበር፣ ጴጥሮስ ይመሰክራል፣ እንዲህ ሲል፦ “ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” (ሐዋ 2÷ 30-36)፡፡
በዘመናት ከሸመገለው የተቀበለው መንግስት ከተራራ ላይ ተቆርጦ በወጣ ድንጋይ ከተወከለው መንግሥት የተለየ አይደለም፣ “እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ። የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፥ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ ነፋስም ወሰደው፥ ቦታውም አልታወቀም ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ” (ዳን 2÷ 34-35) ይላልና፡፡      
         ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግስትን የተቀበለው በእርገቱ ጊዜ ሲሆን ይህ ደግሞ ለእስራኤል  የተገለጠው ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች አድርጎ በቀጠቀጠበት በ70 ዓ.ም በተፈጸመው የኢየሩሳሌምና የቤተ መቅደሱ ውደመት ጊዜ ነው፡፡ "የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ፈጥኖ ከእግራችሁ በታች ይቀጠቅጠዋል" የሚለው የሮሜ 16፥ 20 ንግግርም በዚሁ አውድ የሚተረጎም ነው። የብሉይ ኪዳንዋ ምድራዊቲቱ ኢየሩሳሌም ውድመቷ ኢየሱሰ ክርስቶሰ በሰማይ የእግዚአብሔር መሲህ የመሆኑ ምልክት ነው፣ “ሊቀ ካህናቱም አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው። ኢየሱስም፦ አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው” (ማቴ 26÷ 63-64)፣ ይላል። እዚህ ላይ ሊቀካህናቱ ቀያፋ ኢየሱስን የእግዚአብሔር መሲህ ስለመሆኑ ጥያቄ ባቀረበለት ጊዜ ኢየሱስ ለቀያፋ በሰጠው መልስ  እና በንባብ ክፍላችን በማቴዎስ 24÷ 30 መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ልብ በሉ፡፡ ኢየሱስ ለቀያፋ “የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ ታያላችሁ” ይለዋል፣ ለደቀ መዛሙርቱም የሰው ልጅ በሰማይ የመሆኑን ምልክት እንደሚያዩ ነግሮአቸዋል፡፡ በሁለቱም ምንባባት ያለው አንድ ተመሳሳይ ሁነት ነው፡፡ ለኢየሱስ ንግግር የቀያፋን ምላሽ ብታዩ ደግሞ ጉዳዩ የበለጠ ግልጽ ይሆናል፡- “በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ። ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል? አለ” (ማቴ 26÷ 65)፡፡

ስድብ የተባለው ምኑ ነው? ከተባለ ጽንሰ ሓሳቡን መረዳት ያስፈልገናል፡፡ በሰማይ ደመና የእግዚአብሔር መምጣት የእርሱ ሀልዎት / መገኘት ፍርድና ማዳን ምልክት አገላለጽ ነው፡፡ በመላው ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር በደመና መምጣት ሕዝቡን ለማዳን እና በጠላቶቹ ላይ ለመፍረድ መምጣቱን ያሳያል፣ ለምሳሌ ስለ ሀልዎቱ ዘጸ 16÷ 10፤ 19÷ 9፤ 34÷ 5፤ ዘሌ 16÷ 2፤ ዘኁ 11÷ 25፤ መዝ 18÷ 9-12 መመልከት ሲቻል፣ ስለ ፍርዱ ደግሞ ኢሳ 19÷ 1፤ ናሆም 1÷ 3፣ 5-6 መመልከት ይቻላል፡፡
ብሉይ ኪዳንን በወጉ ያልተረዳ ሰው አዲስ ኪዳንን መረዳት አይችልም የሚል እምነት አለኝ። ሁሉም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች አንባቢዎቻቸው ብሉይ ኪዳንን የሚያውቁ እንደሆኑ ታሳቢ አድርገው ጽፈውላቸዋል ብዬም አስባለሁ። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱሳችንን የመጀመሪያውን ሶስት አራተኛ ክፍል ካልተረዳን የመጨረሻውን አንድ አራተኛ መረዳት ከቶ አንችልም።
በርካታ የብሉይ ኪዳን የንባብ ክፍሎች እግዚአብሔርን በደመና የሚዋጋ እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። ለምሳሌ፣ ኢሳይያስ መጻኢውን እያየ እግዚአብሔር በግብጽ ላይ በፍርድ እንደሚነሳ ያመለክታል እንግዲህ የእግዚአብሔርን በደመና መምጣት በተመለከተ በብሉይ ኪዳን ያለውን አገባብ ብንመረምር በፍርድ የሚሆን መለታኮዊ ሕልዎት ምልክት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ኢሳይያስ በትንቢቱ ይህንን በደመና የሆነ የእግዚአብሔርን መምጣት አስመልክቶ ሲናገር “ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል” (ኢሳ 19÷ 1) ይላል፡፡  ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው የዕብራውያንን ቅዱሳት መጻህፍት በሚገባ ካላወቅን በአዲስ ኪዳን ግራ ልንጋባ እንችላለን። አዲስ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዐት በሚናገርበት ጊዜ በብሉይ ኪዳን ባለው የእግዚአብሔር ተደጋጋሚ አመጣጥ ዓይነት ያስቀምጠዋል። በብሉይ ኪዳን የቅኔና የትንቢት መጻህፍት አቀራረብ ደመና የእግዚአብሔር የጦርነት ሰረገላ እንደሆነ አይነት ያለው አቀራረብ የተለመደ ነው (መዝ 18፥ 9፤ 68፥ 4፤ 104፥ 4፤ ዳን 7፥ 13፤ ናሆ 1፥ 3)። ለጦርነት  በሰረገላ የሚሄድ የተዋጊ አምላክ ምስያ ጥንታዊና የተለመደ አስተሳሰብ ነው።
እግዚአብሔር በግብጽ ላይ ለመፍረድ በደመና እየመጣ ነበር፣ ነገር ግን የደመናው ተፈጥሮ ምንድን ነው? እግዚአብሔር ተዳሳሽ በሆነና በሚታይ አካል ወይም በነባራዊው ቁሳዊ ደመና ላይ ተፈናጦ ደመናን እየጋለበና እየበረረ እየመጣ አልነበረም፡፡ ይህ የእግዚአብሔር አመጣጥ በግልጽ መንፈሳዊና ትዕምርታዊ ሆኖ ነገር ግን ትክክለኛ የጌታ ምጽዓት ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ነው። እግዚአብሔር በግብጽ ላይ በፍርድ የመጣበትን ሁኔታ ስንመረምር ከትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 20 እንደምንረዳው ግብጽን ለመቅጣት የቁጣው መሳሪያ አድርጎ የተጠቀመው አሶርን ነበር። ስለዚህ ˝እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ይመጣል………. ግብጽም…….. በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል” ይላል። ወደ ግብጽ የመጣው በፍርድ ነበር። ህልዎቱም በፍርዱ ይታወቃል። በግልጽ በአካል ያኔ የመጣው ግን አሶር ነበር።
ይህ አይነቱ የእግዚአብሔር የፍርድ አመጣጥ ብዙ ጊዜ በብሉይ ኪዳን አቡቀለምሲሳዊ በሆነ የንግግር ዘይቤ ሲገለጥ ቃሉ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ለመመልከት ደመና የነበረውን አገባብ በሚከተሉት ክፍሎች ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ [መዝ 18÷ 8 ጀምሮ፤ 97÷ 2፤ 104÷ 3፤ ኢዩ 2÷ 1፣ 2፤ ናሆም 1÷ 2 ጀምሮ፤ ሶፎ 1÷ 14፣ 15 ተመልከት]፡፡ በመላው ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር በደመና መምጣት መለኮታዊ ሕልዎቱን እንዲሁም ሕዝቡን ለማዳን እና በጠላቶቹ ላይ ለመፍረድ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
የሆነ ሆኖ አዲስ ኪዳን ደመና የተሰኘውን ርእሰ ጉዳይ ጥቅም ላይ ሲያውለው ወደ ብሉይ ኪዳናዊው ቲኦፋኒክ (አምላካዊ መታየት) ወይም እጅግ በተለየ ሁኔታ በአዲስ ኪዳን ወደ ቀረበው ክሪስቶፋኒክ (የክርስቶስ መታየት) ተግባር መልሶ ያቀርበዋል፤ በደማስቆ መንገድ ላይ ለአሳዳጁ ሳውል የተገለጠበትን ሁኔታ እንደ አንድ የክርስቶፋኒክ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። በዚያ የክብር መለወጥ ተራራ ላይ እግዚአብሔር አብ ከደመና ውስጥ ሲናገር "የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው"(ሉቃ 9፥ 35) ብሎ ኢየሱስን ብቻውን እንደገለጠው እናያለን። ጌታ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ራሱን በሚገልጥበት መንገድ በደመና እንደሄደ ቀደም ሲል በሐዋርያት ስራ 1፥ 9 ላይ ያለውን ጠቅሰን ተመልክተናል። ስለ ጌታ መመለስ በስፋት ከሚታወቁት መግለጫዎች መካከል አንዱ በደመናው ላይ ሆኖ ጠላቶቹን ሊዋጋ ወደ ጦርነት እንደሚዘምት አይነት ሆኖ የቀረበበት አገላለጽ ዋናው ነው (ማቴ 24፥ 30፤ ማር 13፥ 26፤ 14፥ 62፤ ሉቃ 21፥ 27፤ ራእ 1፥7፤ እነዚህን ከዳን 7፥ 13 ጋር አነጻጽሩ)።
ስለዚህ ቀደም ሲል በጠቀስኩት የሊቀ ካህናቱ ጥያቄና የኢየሱስ መልስ አንጻር፣ በተለይም  በነዚህ አስቀድሞ ባነሳናቸው የብሉይ ኪዳን ንግግሮች ብርሃን ቀያፋ በአይሁድ ልማድ ውስጥ እንዳለ የህጉ ሊቅ የገባውና፣ ኢየሱስን 'ተሳድቦአል' ብሎ እየከሰሰ ልብሱን እስከ መቅደድ ያደረሰው ጉዳይ ኢየሱሰ በንግግሩ እርሱ ራሱ መሲሁ መሆኑን እየመሰከረ እንደሆነ ቀያፋ በደንብ ስለገባው ነው፡፡ ኢየሱስ የተናገረውን በሚገባ ለመረዳት በደመና መምጣት ከተሰኘው ጉዳይ ጀርባ ያለውን ብሉይ ኪዳናዊ ሃሳብ ማስተዋል የግድ ነው። እንደ ወንጀለኛ ታስሮ ከፊቱ የቆመው ያ ተከሳሽ ምስኪን ሰው ራሱ እግዚአብሔርን እንደሆነ ሁሉ "በሰማይ ደመና" ስመጣ ታያላችሁ በማለቱ ነው። ለአይሁድ በሰማይ ደመና የሚመጣ ያህዌ ብቻ ነው። በምጽአትም ጉዳይ ወልድ እንደ አባቱ ነው! እንጂ፣ ለብሉይ ኪዳን እንግዳና ባዕድ የሆነ ሌላ አይነት አመጣጥ የለውም።
♦♦♦♦♦♦♦♦♦

No comments:

Post a Comment