ጳውሎስ "የአመጽ ሰው" ሲል የሚጠራው ማንን ነው?
ጌታ ተመልሶ ሲመጣስ በመገለጡ የሚሽረው አመጸኛው ሰው ማን ነው?
2ኛ ተሰሎንቄ 2÷ 8 ምጽዓቱን በተመለከተ ከተዘገቡልን የንባብ ክፍሎች መካከል በዋናነት የሚመደብ ነው፡፡ ክፍሉም፡- “በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ ይገለጣል” ሲል ይነበባል፡፡ ከጥቅሱ እንደምንረዳው በጌታ መገለጥ ይኸውም በመምጣቱ የአመፀኛው ማንነት ይገለጥና ያኔ ይሻራል።
ይህንን ክፍል በአግባቡ ተረድተን ለማለፍ መላውን የርዕሰ ጉዳዩን ዐውደ ምንባብ ከቁጥር 1-8 ማየት ይገባል። ምንባቡ የጌታን ዳግመኛ ምጽዓት አስመልክቶ ላለው የክርስቲያን አስተምህሮ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ክፍል ነው፡፡ መልስ የሚሻው መሠረታዊ ጥያቄም ሐዋረያው ጳውሎስ ጌታ ተመልሶ ስለሚመጣበት ጊዜ መቼ እንደሆነ፣ በዚያን ጊዜ ስለሚከናወነውስ ጉዳይ ምን ያምን እንደነበርና ምን ብሎ እንዳስተማረ የሚመለከተው ነው፡፡ ይህንን ክፍል በአዲሱ መደበኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው እናነበዋለን፦
“ወንድሞች ሆይ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱም ስለ መሰብሰባችን ይህን እንለምናችኋለን፣ በመንፈስ መገለጥ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደተላከ መልእክት የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ ፈጥናችሁ ከአእምሮአችሁ አትናወጡ፣ አትደንግጡም። ማንም ሰው በምንም መንገድ አያታላችሁ፤ አስቀድሞ አመጽ ሳይነሳ፣ ለጥፋት የተመደበውም የጥፋት ሰው ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና። እርሱም አምላክ ከተባለና ከሚመለከው ነገር ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቀምጦ “እኔ አምላክ ነኝ” እያለ ዐዋጅ ያስነግራል። ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችሁ እንደነበር ትዝ አይላችሁምን? በራሱ ጊዜ ይገለጥ ዘንድ አሁን ምን እንደሚከለክለው ታውቃላችሁ። የዐመጽ ምስጢር አሁንም እንኳ እየሰራ ነውና፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው የሚከለክለው ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ ብቻ ነው። ከዚያም በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ እስትንፋስ የሚያስወግደውና በምጽአቱም ክብር ፈጽሞ የሚያጠፋው ዐመፀኛ ይገለጣል።”
የመጀመሪያዎቹ አምስት ቁጥሮች በዋናነት የጌታ ኢየሱስ ክርሰቶስን መምጣት እና ቅዱሳን አማኞች ወደ እረሱ ስለ መሰብሰባቸው በተመለከተ የሚናገሩ ናቸው፡፡ በቁጥር 2 ላይ የጌታን ምጽዓት አስመልክቶ በተሰሎንቄ ምዕመናን ዘንድ ስለ ነበረው የተሳሳተ መረዳት ሲናገር፣ እነርሱም ጌታ ቀደም ባሉት ጊዜያት መጥቶአል ብለው እስከ ማሰብ ደርሰው እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ ጳውሎስ ግን እንዲህ ያለውን በደብዳቤም ሆነ በቃል የተሰራጨ ስህተት የሆነ አስተሳሰብ በኃይለኛው እያረመ በዚያን ዘመን ኢየሱስ ገና እንዳልመጣ እያረጋገጠላቸው፣ ኢየሱስ ከመምጣቱ አስቀድሞ መሆን ስላለባቸው ጉዳዮች በዝርዝር ማስተማሩን ይቀጥላል፡፡
ኢየሱስ ከመምጣቱ አስቀድሞ መሆን ስላለባቸው ሁለት ነገሮች ጳውሎስ በቁጥር 3 ላይ ይናገራል፣ እነርሱም፡- 1/ አስቀድሞ ክህደቱ (ዐመጽ) ይነሳል፣ 2/ የኃጢአት ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ይገለጣል፣ የሚሉት ናቸው፡፡ ቀጥሎም በቁጥር 4 ላይ የዚህን የዐመጽ ሰው ተፈጥሮና ባህርይ፣ የሚቀመጥበትንም ቦታ፣ ራሱን እግዚአብሄር አድርጎ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚቀመጥ ይነግራቸዋል፡፡ ከዚያም በቁጥር 8 ላይ ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ሲመጣ ይህ የዐመጽ ሰው እንደሚጠፋ ጳውሎስ ይናገራል፡፡
እንግዲህ የንባብ ክፍሉ የሚናገረው ጌታ ኢየሱስ ሲመጣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቀምጦ እኔ እግዚአብሔር ነኝ በሚል የኃጢአት ሰው ላይ ስለሚሆነው ጥፋት ነው፡፡ ይህ የክርስቶስ መምጣት ቤተ መቅደሱ ገና ቆሞ እያለ ሳይፈርስ በፊት የሚፈጸም ነገር መሆን አለበት፡፡ ታሪካውያን ጳጳሱን በ ‹ናኦስ› ማለትም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተቀመጠ የኃጢአት ሰው ነው ይሉታል፡፡ መጻኢያን የሆኑ ተርጓሚዎች ደግሞ በዚህ ክፍል ላይ ተንተርሰው የክርስቶስ ተቃዋሚው ይቀመጥበት ዘንድ እንደገና በምድራዊቲቱ ኢየሩሳሌም ስለሚገነባ ቤተ መቅደስ ይነግሩናል። ነገር ግን በዚህ ትንቢትም ሆነ በሌላ የአዲስ ኪዳን ትንቢት እንደገና ስለሚገነባ ቤተ መቅደስ የተነገረ ምንም ነገር የለም፡፡ ክርስቶስ በደሙ ካቆመው ኪዳን የተነሳም ይህ ምድራዊ ቤተ መቅደስ መገንባቱ አስፈላጊ አይደለም። በዚህ ዘመን በየአብያተ ክርስቲያናቱ አስተምህሮና አስተሳሰብ ውስጥ ስለዚህ የኃጢአት ሰው ማንነት በሰዎች የተፈበረኩ መላምቶች አበዛዛቸውን ላስተዋለ ምን ያህል ግራ መጋባት እንደ ተሰራጨ መገመት አያስቸግረውም፡፡ አንዳንዶች ይህ ሰው በአውሮፓ አንድ ቦታ ላይ ተወልዶ እያደገ ነው በቅርቡም ዓለምን የሚገዛ ሆኖ ይገለጣል፣ ጌታ ኢየሱስም ሲመጣ ያጠፋዋል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
እንዲሁም በዚህ ትንቢት ውስጥ የተመለከተው የኃጢአት ሰው የሚታይበት ወይም የሚቀመጥበት ያለው ተዳሳሽ ቤተ መቅደስ እንጂ፣ በዚህ የንባብ ክፍል ስለ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ የተነገረም ሆነ የተባለ ምንም ነገር የለም፡፡ አዲስ ኪዳንን በወጉ ለተማረ ሰው ምድራዊውን ቤተ መቅደስ አስወግዶ በሚበልጥ ሰማያዊ ክብር የተገለጠው መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ እንዲህ ላለ ከንቱነትና ርኩሰት ታልፎ የማይሰጥ መሆኑን ማወቅ አይቸገርም። ክፍሉ የሚናገረው ግን ስለ አንድ ሊገለጥ ስላለና በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሊቀመጥ ስላለ ግለሰብ፣ ነገር ግን በክርስቶስ መምጣት ብርሃን ስለሚጠፋው ሰው ነው፡፡ ቤተ መቅደሱ ደግሞ የወደመው ያኔ በ70 ዓ.ም ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ትንቢት መፈጸም ያለበት ቤተ መቅደሱ ሳይፈርስ በፊት መሆኑ ጥርጥር የለውም። በፈረሰና በሌለ ቤተ መቅደስ የሚቀመጥ ማንም የለምና።
የዓመጽ ሰው የተባለው ግለሰብ የጳውሎስና የተሰሎንቄ ሰዎች ዘመን ሰው መሆኑን ማየትና መለየት አስቸጋሪም ከባድም አይደለም፡፡ ይህንንም ጳውሎስ በመልዕክቱ በግልጽ ከሚናገረው ነገር መረዳት ይቻላል፡፡ የሚከተሉትን ማስረጃዎች ልብ በሉ፡-
ይህ ሰው ማን እንደሆነ ጳውሎስ ያውቃል (ቁ 5-6)
የአመጽ ሰው የተባለውን ግለሰብ ከመገለጥ የሚከለክለው ከልካይም ማን እንደሆነ ጳውሎሰ ያውቃል፤ ስለሆነም ይህ የአመጽ ሰው ማን እንደሆነ ያውቃል ማለት ነው (ቁ 6)
እነዚህ ሁለት ሰዎች፣ የአመጽ ሰው እና ከልካዩ እነማን እንደሆኑ ጳውሎሰ የሚያውቃቸው እስከሆነ ድረስ ደግሞ በስም ጠቅሶ እከሌ እና እንቶኔ ብሎ ሊያመለክታቸው ይችል ነበር፡፡ ያንን ግን አላደረገም፣ ምክንያቱም ያንን ማድረግ የተሰሎንቄ ምዕመናንን ለከፋ አደጋ እና መከራ እንደ ማጋፈጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ደብዳቤው በአጋጣሚ በማን እጅ ሊገባ አንደሚችል ስለማይታወቅ፣ ይህ በአሉታዊ መልክ የሚጽፍበትም ሰው ያልተገደበ ስልጣን እና ኃይል ለራሱ የሚያደርግ ሰው ስለሚሆን ይህንን መግለጥ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡
ጳውሎስ ብቻ ደግሞ ሳይሆን የተሰሎንቄ ሰዎችም ይህ ሰው ማን እንደሆነ ያውቃሉ (ቁ 6)
የተሰሎንቄ ሰዎች በዚህ የአመጽ ሰው መንገድ ላይ የቆመው ከልካይ ማን እንደሆነ ስለሚያውቁ ይህ ሰው ማን እንደሆነ ያውቃሉ (ቁ 6)
ይህ ሰው በዘመኑ የነበረ አንድ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ሆኖ፣ የተሰሎንቄ ሰዎችን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ሰውየው በዚያን ጊዜ በነበረው አለም አለምአቀፋዊ ትኩረት ያገኘ ሰው ነበር። ጳውሎስም በተሰሎንቄ በነበረበት ጊዜ ስለዚሁ ሰው ቀደም ሲል ነግሮአቸዋል (ቁ 5)
እየተካሄደ ያለው ምንም አይነት የአመጽ ሥራ ይሁን፣ ይህንንም የኃጢአት ሰው ወደ ስልጣን ለማምጣት ምንም አይነት ጥረት ይደረግ፣ ገና ያኔ ጳውሎስ ሁለተኛውን መልዕክቱን ለተሰሎንቄ ቤተክርስቲያን በጻፈበት ጊዜ (ከ52-53 ዓ.ም ባለው ጊዜ) ውስጥ ይህ ሰው በስራ ላይ ነበር (ቁ 7)
ይህ ሰው በቤተመቅደስ ሄዶ የሚቀመጥና የሚያረክሰው ከሆነ፣ ይህንን ሊያደርግ የሚቻለው ገና ቤተመቅደሱ ሳይፈርስ በፊት መሆን አለበት፡፡ ሰውየውም ቤተመቅደሱ ከፈረሰበት ከ70 ዓ.ም በፊት ባለው ጊዜ የኖረ ሰው መሆን አለበት (ቁ 4)
ይህም የዚህን ሰው የሥራ ጊዜ ጳውሎስ ይህንን መልዕክት ከጻፈበት ከ52 ዓ.ም አካባቢ ቤተ መቅደሱ እስከ ፈረሰበት እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ያደርገዋል፡፡
ይህ ሁሉ እውነታ በቀላሉ የሚያስጨብጠን ድምዳሜ ይህ የኃጢአት ሰው ጳውሎስና የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በነበሩበት ዘመን የኖረ፣ በእነርሱም የሚታወቅ ሰው መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን የተሰሎንቄ ሰዎች ሊያውቁት እድሉ ስለማይኖራቸው ወይም ስለማይችሉት፣ ከዘመናቸውና ከአውዳቸው ስለራቀ የ21ኛው ክፍለ ዘመን እና ወይም ገና ከዚያም በላይ ላለ ዘመን ስለሚጠበቅ አንድ አለም አቀፋዊ አምባ ገነን ወይም ስለሌላ አንድ ሰው ጳውሎስ እየጻፈላቸው እንደሆነ ማሰብ በእውነቱ አስቂኝም አሳዛኝም ነው።
ይህ ታዲያ እንዴት ነው የተፈጸመው የሚል ጥያቄ ቢነሳ፦ የታሪክ ጸሐፊውን የጆሳፈስን የታሪክ ዘገባ ተከትለን ከገሊላ የሆነውን የሌዊን ልጅ የግስችላውን ዮሐንስ ሁኔታ ማየቱ የጠቅማል። ይህ ግለሰብ አስቀድሞ ከቀነናውያን ወገን የሆነና የቤተ መቅደሱን ዙርያ የተቆጣጠረ፣ በወቅቱ ተነስተው ለነበሩ ፖለቲካዊና ኃይማኖታዊ አላማ ላነገቡ ነጻ አውጭዎች የንቅናቄአቸው መሪ ነበር። በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ከተማና በዙርያዋ በየፊናቸው ተሰለፈው እርስ በርሳቸውና ደግሞም ከሮም ጋር በጠላትነት የሚፋለሙ ሦስት የቀነናውያን አንጃዎች እንደነበሩ ይታወቃል። ሰይጣንም "መሲሁ ነኝ" በሚሉ በኃሰተኞች ነብያትና በኃሰተኛ ክርስቶሶች አማካኝነት ያኔውኑ በህዝቡ መካከል በስፋት የማታለልና የማስመሰል ስራውን መስራት ጀምሮ ነበር። ይህም ዮሐንስ ከሌሎቹ የአንጃ መሪዎች በተለየ በቀጥታ ወደ ቤተ መቅደሱ በአካል ገብቶ ነበር። ለቀነናውያኑም "በእግዚአብሔር የተላክሁ አምባሳደር ነኝ" እያለ ራሱን በማስተዋወቅ እንዲከተሉት ጥሪ አቅርቦላቸው ነበር፤ የሮምንም ሕግ እንዲተላለፉ እያበረታታ "ነጻ አወጣችኋለሁ" በሚል የኃሰት ተስፋ ለጦርነት ያነሳሳቸውና ይቀሰቅሳቸው ነበር። ከተጽዕኖውም ስፋት የተነሳ ጥሪውን ወደ ኤዶማውያን በማስተላለፍ አይሁዳዊ ደጋፊዎቹን ለሮም ተላልፈው ከመሰጠት እንዲጠብቁአቸው አድርጎአል። ሊቀካህኑም አናን እንዲገደል ትእዛዝ ያስተላለፈና ከክህነቱም የሻረው እርሱ ነው። ይህንን አረመኔአዊ ተግባር ከፈጸና፣ የቤተ መቅደሱን ህጋዊ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ካህናቱን ከመንገዱ ላይ ዘወር እንዲልለት ካደረገው በኋላ በይፋ የቀነናውያኑ ቡድን መሪ በመሆን የቤተ መቅደሱን ዙርያ ተቆጣጠረና የግስችላው ዮሐንስ የገዛ ራሱ ቤተመቅደስ አደረገው። ይህ ደግሞ ኃይማኖቱንም ሆነ ፓለቲካውን እንደፈለገ ሊዘውር የሚያስችለውን ስልጣን ያቀዳጀዋል፤ ከዚያም የቄሳርን በአመጽ፣ የእግዚአብሔርንም በክህድት፣ በጠቅላላውም የሰውን ሕግጋት በመሻርና በማፍረስ መቅደሱን በህገወጥነት ካረከሰው በኋላ ከሮማውያን ሊታደጋቸው የሚችል እርሱ ብቻ እንደሆነ በመለፈፍ ሃሰተኛ ተስፋ ገባላቸው። ህዝቡም ተታልሎ በሙሉ ኃይሉ ተከተለው፣ ወዲያውም ከቀነናውያኑ ጋር ያለውን ቃል ኪዳን አፍርሶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በመቀመጥ አንባ ገነናዊ የሞናርኪያዊ የመንግስት ስልጣን ለመምስረት ይንቀሳቀስ ጀመር። ለዚህም እንዲያመቸውና የተታለሉና የተከተሉትን ሕዝቡን ሁሉ እያስፈራራ ለመግዛት እህል የሞላበትንም ግምጃ ቤት እንዲሁም በከበባ ጊዜ ለብዙ ዘመን እንዲያገለግል ተከማችቶ የነበረውን ምግብ ሁሉ በእሳት አቃጠለው። ለዚያ የተዋበ ቤተመቅደስ የተለየ ፍቅር ያላቸውን አይሁድን እየሸነገለ፣ የሮማውያን ሰራዊት ቤተመቅደሱንና በዙርያው ያሉትን ነገሮች ሁሉ ይወስዱባችኋል በማለት፣ የሚያድናቸውም የእርሱ ኃይል ብቻ እንደሆነ እየሰበከ አታለላቸው። ማንኛውንም ወደ ሮማውያን ይኮበልላል ብሎ የተጠራጠረውን፣ ይከዳኛል ብሎም የጠረጠረውን ሰው ሁሉ ጉሮሮውን እያነቀ እዚያው በቤተመቅደሱ በሰይፍ ስለት ይቀላቸው ጀመር። በርካታ ክፉ ነገሮችንም እያደረገ የቤተመቅደሱን ንዋያተ ቅዱሳን አረከሳቸው፣ ቤተመቅደሱንም የገዛ ራሱ ማደርያ አድርጎ አረከሰው።
ባጭሩ ጳውሎስ ይህንን የ2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቱን በሚጽፍበት ወቅት በዚያው በኢየሩሳሌም ዙርያ የነበረ ይህ ዮሐንስ የተባለ ሰው፣ ራሱን ከሮምና ከእግዚአብሔር በላይ ከፍ አድርጎ የእግዚአብሔርን ቦታ በመውሰድ "እግዚአብሔር ነኝ" ብሎ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራሱን ሰየመ። ይህ ሁሉ የሆነው በትክክል ጳውሎስ "የኃጢአት ሰው" ሲል የሚጠራው ይህ ግለሰብ ይህንን አመጽ ያደርጋል ባለበት ጊዜና ቦታ ላይ ያኔ እና እዚያው የሆነ ነበር። በትክክል ካየነው ጳውሎስ በመልእክቱ ከጌታ ዳግም ምጽአት አስቀድሞ "ይገለጣል" ያለውንና ጌታ ኢየሱስ "ሲመጣ በአፉ እስትንፋስ ያጠፋዋል" ሲል የተናገረለትን የዚህን "የአመጽ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ" በግልጽ የሚወክልና የዚህን ሰው መመዘኛ የሚያሟላ ሰው ይኸው የተረገመ የግስችላው ዮሐንስ መሆኑን እንረዳለን።
በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ውድመት ፍርዱን ባደረገበት በ70 አ.ም ላይ በሆነው የጌታ ምጽአት የግስችላው ዮሐንስ በጀነራል ቲቶ ተማርኮ ታስሮ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ ለእድሜ ልክ ጽኑ እስራትና ለብርቱ ቅጣት ወደ ሮም እንደ ተወሰደ፣ በሰንሰለትም ታስሮ ለጀነራል ቲቶ ጀግንነትና ክብር ማሳያ እንዲሆን በሮም አደባባይ በየጎዳናው እንዲዞር እንደ ተደረገ ታሪክ ይመሰክራል። በመጨረሻም በዚያው ውርደት በወህኒ እንዳለ መሞቱ ይገመታል። በዚህም ይህ "እኔ ነኝ" ያለ ሰው በጌታ ኢየሱስ የአፉ እስትንፋስና በምጽአቱ ክብር እንደሚጠፋ በጳውሎስ ትንቢትና ምሳሌአዊ ቋንቋ የተነገረው ፍጻሜውን አግኝቶአል (ኢሳ 11፥ 4፤ 30፥ 27-33፤ ሆሴ 6 ፥5፤ በተጨማሪም ዳን 7፥ 8፣ 19-28 ተመልከቱ)።
ቁጥር 11-12 "ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።"
ጆሳፈስ በታሪካዊ ዘገባው እንደሚናገረው የሮማው ጀነራል ቲቶ ቤተመቅደሱን ለማፍረስ ምንም ፍላጎት አልነበረውም ነበር። ሮማውያን የአሸናፊነታቸውና የክብራቸው መገለጫ ሆኖ እንዲጠበቅ ይፈልጉ ነበር። ራሱ ጆሳፈስም ቢሆን ገና ጦርነቱ ሳይጀመር አስቀድሞ፣ የግስችላው ዮሐንስ እጁን በሰላም እንዲሰጥ በግሉ ጥረት በማድረግ ተማጽኖት ነበር። ነገር ግን የሮምን ወራሪ ኃይል እንመክታለን የሚል እንዲህ ያለ እብደት በራሱና በተከተሉት አይሁድ ላይ ስለወጣባቸው ለመስማት አልፈለገም። በመንገዳቸውም ላይ ቆሞ የነበረው የክህነቱ ስልጣን ተወግዶ ሰለነበር በአመጻቸው ብዛት ራሳቸው ለራሳቸው ህግ ሆነው የእግዚአብሔርንም ሆነ የሰውን ስርአት በማፍረስ አመጽን ብቻ እንዲከተሉ ሰይጣን ገብቶባቸው ነበር።
የማያምኑት አይሁድ ኢየሱስን እንደ መሲህ እንደ ንጉስና አዳኝ ከመቀበል ይልቅ በሰይጣን ኃይልና በአይሁድ ሕዝብ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተላከ ስህተት ተስፋቸውን በዚህ የኃጢአትና የጥፋት ሰው ዮሐንስ በተባለ ኃሰተኛ መሲህ ላይ በማድረግ ስለጸኑ ሮማውያን እርምጃ እንዲወስዱባቸው አስገደዱአቸው። ወደ ድልና ነጻነት እንዲመራቸው ይህንን የኃጢአት ሰው ይመለከቱና ይጠባበቁ ነበር፣ "ከዚህም የተነሳ በሮማውያን የጭካኔ ሰይፍ ስር ወድቀው በገፍ እየታረዱ ሲገደሉ በሮማውያን ሰራዊት ተወርሮ እየፈረሰና እየተቃጠለ ከነበረው ቤተመቅደስ አንዳች መለኮታዊ ወይም ምትሃታዊ ኃይል ወጥቶ የሚያድናቸው እንደሆነ ያህል በመጠባበቅ አሟሟታቸው እንኳ አይኖቻቸውን በሕንጻው ላይ እንደተተከለ ነበር" ሲል ጆሳፈስ ዘግቦአል። በነሐሴ ወይም መስከረም 70 አ.ም ላይ የ2ኛ ተሰሎንቄ 2፥ 1-12 "የኃጢአት ሰው" የተባለውን ግለሰብ በተመለከተ የተነገረው መላው የጳውሎስ ትንቢትም ተፈጸመ። ከተማይቱ ኢየሩሳሌምና ያ የተመኩበት ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ በፍርስራሽ ሆነው ፈጽመው ተቃጥለው ወደሙ። የቃል ኪዳኑ ሕዝብ እስራኤል እና መላው መጽሐፍ ቅዱሳዊው የይሁዲነት ትምክህታቸው ሁሉ እስከ ወድያኛው ለዘላለም በእግዚአቢሔር ጽኑ ፍርድ ተደምስሶ ጠፋ።
እንግዲህ ከላይ በተዘረዘሩት ማስረጃዎች መሠረት የኃጢአት ሰው ጉዳይ ታሪክ ሆኖ አልፎአል፣ የትላንት ዜና ሆኖ ቀርቶአል ማለት ይቻላል፡፡ ስለ ክርስቶስ መምጣትም በምንናገርበት ጊዜ እየተናገርን ያለነው ሌላ ሳይሆን፣ ያ የክርስቶስ መምጣት በ70 ዓ.ም በእስራኤል ላይ ለፍርድ ስለሚሆነው መምጣቱ ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ነገረ ፍጻሜም እስከ 70 ዓ.ም ድረስ የነበረውን ያንን ቤተ መቅደስ ከበው ያሉ ኹነቶችን የሚመለከት ነገር ነው፣ እንጂ ከዚያ በኋላ ባለ በማንኛውም ጊዜ ሊፈጸም የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ እስካሁንም ባለው የአለም ታሪክ ጳውሎስ "የጥፋት ልጅ" ሲል በ2ኛ ተሰሎንቄ ምዕራፍ 2 ላይ ያመለከተውን ገጸ ባህርይ ሊወክል የሚችል ግለ ሰብ የግስችላው ዮሐንስን ያህል እከሌ የሚባል ሌላ ሰው የለም። ልብ ወለድ ከሆነ ነገረ ፍጻሜአዊ መላ ምት መውጣት ካልተፈለገ ግን በአቦ ሰጥ ያንንም ይህንንም "የአመጽ ሰው" እያሉ ለመጥቀስ ምርጫው የራሳችሁ ነው።
ግዛቸው ነኝ፣ ቸር ስንብት!
No comments:
Post a Comment