Wednesday, November 21, 2018

፮፣ ፍቺና ጦርነት በራእይ

ክፍል ፮
ራእይ፣ የፍቺው ጽህፈት እና የጦርነት አዋጅ

በራዕይ 4 ውስጥ እግዚአብሔርን በዳኝነት ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ እናያዋለን፡፡
የእግዚአብሔር ዙፋን በራዕይ  መጽሐፍ  ውስጥ ከሃያ ሁለቱ ምዕራፎች በአስራ ስምንቱ ውስጥ ተጠቅሶ ይታያል፡፡ በእርግጥ "ዙፋን" የሚለው ቃል በጠቅላላው በአዲስ ኪዳን 62 ጊዜ ሲጠቀስ 47 ያህሉ የሚገኘው በራዕይ መጽሐፍ ነው፡፡ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ጠንካራ የሆነ የዙፋን ችሎት አገላለጽ አለው፡፡
በራዕይ 5 እግዚአብሔር በእጁ የያዘውን እስራኤልን የሚቃወም የፍቺውን ጽህፈት የሚወክል  በሰባት ማህተም  የተዘጋ መጽሐፍን እንመለከታለን፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ በዘዳግም 24 ላይም በፍቺ ጉዳይ የሚጠይቀውን "የፍቺውን ጽህፈት" የግድ  እንዲቀርብ ሲጠይቅ እናያለን፡፡ እዚህ ራእይ መጽሐፍም ላይ እግዚአብሔር የፍቺውን ጽህፈት ለእስራኤል ያቀርባል፡፡ በፊትና በኋላ የተጻፈበት የመጽሐፍ ጥቅልል በሕቅዝቅኤል 2 ላይ በፊትና በኋላ የተፃፈበትንና በሕዝቅኤል እጅ የነበረውን የመጽሐፍ ጥቅልል የሚያመለክት ነው፡፡ በሕዝቅኤል 2 ላይ የተገለጸው ይህ መጽሐፍ በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚሆንው ኃዘን፣ ልቅሶ፣ እና ዋይታ በተመለከተ የተነገረ ነው፡፡ በሕዝቅኤልና በዮሐንስ ራዕይ ያሉ እነዚህ ሁለት የመጽሐፍ ጥቅልሎች ተመሳሳይ  ይመስላሉ፡፡  መጽሐፉ በሰባት ማህተም መዘጋቱ በዘሌዋውያን 26÷ 24 ላይ "እኔ ደግሞ በእንቢተኝነት እሄድባችኋለሁ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ" ሲል እግዚአብሔር እስራኤልን ያስጠነቀቀውን ሰባት እጥፍ ፍርድ ያመለክታል፡፡ በዘሌዋውያን ያለው ሰባት እጥፍ ፍርድ በዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ጠቅላላ  የፍርድ ቋንቋ  ሆኖ  ጠንካራ  ተጽዕኖን  የሚያሳድር አገላለጽ ነው፡፡
እግዚአብሔር በሕጉ ስለ ግልሙትና ገልጾ ያስቀመጠው ቅጣት በድንጋይ ተወግሮ መሞትን ነው፡፡ /ዘሌ 20/ በዮሐንስ ራዕይ 16÷ 21 "በሚዛንም አንድ ታላንት የሚያህል ታላቅ  በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ እግዚአብሔርን ተሳደቡ፥ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና " የሚል እናነባለን፡፡ እንግዲህ እስራኤል የግልሙትና ኃጢአትን እንደፈጸመች ጋለሞታ ሚስት  በድንጋይ ተወግራ ትሞታለች ማለት ነው፡፡
እስራኤል በብሉይ ኪዳን የያሕዌ ሚስቱ እንደሆነች ብቻ ሳይሆን እንደ ካህንም ደግሞ ታገለግለው ዘንድ ዕድሉ ነበራት፡፡ ስለሆነም በዮሐንስ ራዕይ እስራኤል የካህናት ልብስ እንደሆነ  ሁሉ  የግልሙትና አለባበስ ለብሳ ትታያለች፡፡ እንግዲህ ካህን እስከሆነች ድረስ ሌላው የብሉይ  ኪዳን  ሕግ  ደግሞ ተፈጻሚ ይሆንባታል ማለት  ነው፡ ፡ ሕጉም፦
"የካህንም ልጅ ራስዋን በግልሙትና ብታረክስ አባትዋን ታረክሰዋለች በእሳት ትቃጠል" /ዘሌ21÷ 9/ የሚለው ነው፡፡ 
እስራኤል በእሳት ስትቃጠል የሚያሳይ ራዕይ በዮሐንስ ራዕይ  17÷ 16 እናያለን፡፡
ራዕይ 17÷ 16 "ያየኃቸውም አስር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፥ ሥጋዋንም ይበላሉ፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል።"
እግዚአብሔር እስራኤልን ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲህ በድንጋይ ተወግራና በእሳት ተቃጥላ ካስወገዳት  በኋላ በዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ እግዚአብሔር አዲስ ሙሽራ የምትሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቤተክርስቲያን በውበትዋና በክብርዋ ይገልጣታል፡፡ በዮሐንስ ራዕይ 21 ከእስራኤል ሞት በኋላ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ድንግል ሙሽራ ከሰማይ የምትወርደውን ከተማ እናያለን፡፡ ከዚያም የበጉን የሰርግ ራት የሚተርክልንን  ክፍል እናነባለን፡፡ በዕብራውያን 12÷ 22 መሰረት   አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ናት።
እንግዲህ የዮሐንስ ራዕይ  መጽሐፍ ጭብጥ የሆነው ዋና ርዕስ  ከሌሎች አማልክት ጋር በነበራት የግልሙትና እና የሴሰኝነት  ግንኙነት  ምክንያት  እግዚአብሔር  በእስራኤል  ላይ  ያቀረበውን  የፍቺና  የፍርድ  ጽህፈት መግለጥ ነው፡፡ እርስዋ ስለ ጥፋትዋ እንድትገደል ካደረገ በኋላ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን የተባለችውን መንፈሳዊትዋን የእግዚዘብሔር እስራኤል አዲስቱ  ሙሽራ አድርጉ ይወሰዳታል፡፡
በቀደመው የጥናታችን ክፍል ለዮሐንስ ራዕይ  መጽሐፍ  ተገቢና ትክክለኛ ለሆነ ትርጉምና መረዳት ሦስት ቁልፍ የሆኑ  ጥያቄዎችን እና መጠነኛ ዝርዝር ሃሳቦችን  አንስተን  መጽሐፋን  ለመረዳት  መሠረት ጥለን እንደነበር ይታወሳል፡- የተፃፈው ከኢየሩሳሌም  ውድመት በፊት  ቀደም ብሎ  ሲሆን አብዛኛው የመጽሐፉ ትንቢት  ይህንንው ሁነት  የሚያመለክት ነው ብለናል፡፡ መጽሐፉ ማዕከል ያደረገው እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ጠላት ሁሉ  በፍርድ ሲያጠፋት ያለው ዕውነታ ላይ ነው፡፡
ሁለቱ የበጉ ጠላቶች፦
በዮሐንስ  ራዕይ  የተገለጡት ሁለቱ ዋና ዋና የሆኑ የበጉ ጠላቶች፣  ይኸውም:- "አውሬው"  እና "ጋለሞታይቱ"፣ ማንነታቸዉ የቀረበበት መንገድ፣  የዮሐንስ ራዕይ መፅሐፍ እንዴት እንደሚተረጎም ሌላ ተጨማሪ ፍንጭ ይሰጡናል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚያስፍሩ ምስሎች አንዱ አውሬው ነው፡፡ ሁሉም ሰው ስለ ቁጥሩ ማለትም ስለ 666 የሚያውቀውና የሚመስለው ነገር አለው ፡፡ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች በዮሐንስ ራዕይ ያለው የአውሬው አምሳል ተለዋዋጭ  እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ በአንዳንድ አውድ አውሬው ጠቅለል ባለ መልኩ መንግስትን እና ግዛትን የሚመለከት  ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ደግሞ በተለየ ሁኔታ በዚህ መንግስትና ግዛት ውስጥ ያለ አንድን ግለሰብ ያመለክታል፡፡ በዮሐንስ ራዕይ 13÷ 8 አውሬው  ሰው እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን በምዕራፍ 17÷ 11 ላይ  ለዮሐንስ ይተረጉምለት የነበረው መልአክ አውሬው ሰባት ነገስታት ብቻ ሳይሆኑ ስምንተኛው ንጉስ እንደሆነ ይነግረዋል፡፡ አጠቃላይ የአውሬው ማንነት የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የሮም መንግስት ነው፡፡ ኢየሱስ የተሰቀለው በሮም መንግስት ስልጣን ስር ሲሆን የራዕይ መጽሐፍም የተጻፈላቸው ሰባቱ አብያተ  ክርስቲያናትም በስደትና በጽኑ መከራ ይኖሩ  የነበሩት በሮም መንግስት  ግዛት  ውስጥ ነበር፡፡
የአውሬው የተለየ ማንነትስ ምን  ነበር? 666 የተባለውስ የራዕይ 13÷ 18 ግለሰብስ ማን ነው?
ራዕይ13÷18 "አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ  ስድሳ ስድስት ነው።"
የራዕይ መጽሐፍ አውሬ ኔሮ ቀላውዴዎስ ቄሳር ተብሎ በተሻለ ከሚታወቀው ከሉሴዩስ ዶሚሱስ  አሂናባርቡስ ከተባለው ሰው በቀር  ሌላ ማንም  አይደለም፡፡  ትክክለኛና ቀጥተኛ የሆነውን የአውሬውን መገለጫ የሚመጥን ብቸኛ  ሰው እርሱ ነው፡፡ ይህንን እንዴት እንደሚያሟላ መመዘኛዎቹን እንመልት፦
አውሬው 666 በተሰኘው ቁጥር ይወከላል፡፡ በጥንት ዘመን የፊደል ገበታ ሁለት ዓይነት አገልግሎት ነበረው፡፡ ቀዳሚውና የመጀመሪያ የሆነው አላማቸው በእግርጥም እንደ  ፊደል ማገልገላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ፊደሎች የቁጥር ሆሄያትን በመወከል ያገለግሉ ነበር፡፡ ስለዚህም እንደ ቁጥር ሆነው በመነበብ ያገለግሉ ነበር፡፡ በጣም ታዋቂ የሆነው የዚህ ምሳሌ  የሮማውያን የቁጥር አጻጻፍ ዘይቤ ሲሆን እነዚያም ቁጥሮች በፊደል የሚወከሉ መሆናቸው ነው፡፡ የግሪክና የእብራይስጥ ቋንቋዎችም በተመሣሣይ መንገድ ይሰራሉ፡፡ ኔሮ  ቄሳር  /Nero Caesar/ በዕብራውያን የፊደል ገበታ መልክ የተፃፈ ከሆነ /ዮሐንስ እና በርካቶቹ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ከእብራውያንነት የተወጣጡ ነበሩ/ በትክክል የ666 ቀመር የሆነውን የሂሳብ ውጤት ይሰጠናል፡፡ እነዚያ ሰባቱ አብያተ ክርስትያናት ይኖሩ በነበሩበት ዘመንና ዮሐንስ ራዕዩን በፃፈበት ዘመን የኖረ ንጉስ ይህንን ድምር ውጤት የያዘ ስም ያለው መሆኑ የሚያስገርም አይደለምን? ይህ ጉዳይ የአጋጣሚ ጉዳይ ወይስ ታሪካዊ ክስተት ነው?  አውድ ተኮር የሆነውን ጠቀሜታና የትርጉም አካሄድ ልብ በሉ፡፡ ዮሐንስ ለመጀመሪያዎቹ አንባቢዎቹ አስረግጦ የአውሬውን ማንነት ግልጽ በማድረግ አንፃር እርሱን እንዲረዱለት  ይፈልጋል፣  ነገር ግን ጉዳዩ ከዚህም ያለፈ ነው፡፡
የአውሬው ባህሪይ በዚህ ሚናው ምክንያት ለኔሮ የሚመጥን ነው፡፡ እርሱ የአውሬን ተፈጥሮ የተሞላ ሰው ነበር፡፡ ኔሮ ከዚህ የጨካኝ አውሬ ተፈጥሮው የአጥቂነትን ባህርይ ያሳይ ነበር፡፡ እንደ ታሪክ ጸሐፊው ሱቴንዩስ ዘገባ ከሆነ ኔሮ  አንድን ስፓሩስ የተባለ ልጅ ወንድነቱን ከሰለበውና ካኮላሸው በኋላ እንደ  ሚስት አድርጎ ለራሱ ያገባው ሰዶማዊ እንደ ነበር ዘግቦአል፡፡ ወንዶችን በመድፈር የግብረ ሰዶማዊነትን ተግባር እየፈፀመባቸው ጥቃት በማድረስና በማሰቃየት ይደሰትባቸውና ይዝናናባቸው ነበር፡፡  የገዛ ቤተሰቦቹን፣ ወንድሙን፣ ሚስቱን፣ አጎቱን እና በርካታ ለእርሱ ቅርብ የነበሩትን ሌሎችን ሁሉ  እያሰቃየ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎአቸዋል፡፡ ጠቅላላ ሰውነቱን  ካረከሰ በኋላ የገዛ ራሱን ክብረ ንፅህና ያጎደፈ እጅግ አፀያፊ የሆነ ሥራን የሚሠራ በሰዎች ላይ እየቀለደ የሚጫወት ባለጌና ጨምላቃ ሰው ነበር፡፡ ግብረ ሰዶማዊው ቄሳር ኔሮ ራሱን "የሴቶች ሁሉ ባል የወንዶች ሁሉ ሚስት" ሲል የሰየመ ሴሰኛ ሰው ነበር።  የሆነ የአውሬ ቆዳ ለብሶ ከሆነ ዋሻ ውስጥ ድንገት በመውጣት በእንጨት ላይ ታስረው ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ የወንዶችንና የሴቶችን ክብር በሚነካ ሁኔታ ጥቃት ያደርስባቸው ነበር፡፡
ራዕይ13÷ 7 አውሬው ከቅዱሳን ጋር ሊዋጋ  ሥልጣን እንደ ተሰጠው ይናገራል፡፡
ኔሮ ክርስትናን በይፋ ለማሳደድ እርምጃ የወሰደ የመጀመሪያው የመንግስት ሥልጣን ነው፡፡ የክርስቲያኖች ስደት በአዋጅ በተጀመረ ጊዜ  በሮም  የነበረውን ሁኔታ ታኪቱስ ሲዘግብ አሟሟታቸው ከብዙ መዘባበት በኋላ የሚፈፀም አሰቃቂ ነበር፣ በክፉ አናብስትና በአውሬዎች ይገነጣጠሉ ነበር፣ በውሾች ተቆራርጠውና ተዘነጣጥለው እንዲበሉ ይደረጉ ነበር፣ በእንጨት ላይ ታስረው እንዲንጠለጠሉ ከተደረገ በኋላ በእሳት ያቃጥሉአቸው ነበር፣ በተለይ ምሽት ላይ እንደ ጧፍ እያበሩ በእሳት ተለኩሰው ለጨለማው መብራት እንዲሆኑ ይደረጉ ነበር፡፡ በኔሮ የተጀመረው ሥደት በጠቅላላ የተከናወነው ከ64 ዓ.ም አንስቶ ራሱ ኔሮ እስከ ሞተበት ሰኔ 68 ዓ.ም ድረስ ማለትም ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ወይም  ከ42 ወራት በኋላ የተጠናቀቀ  ነው፡፡ እንግዲህ  ኔሮ የአውሬውን ባህርይ የሚመጥን ማንነት  ያለው ነው፡፡
እንደ ራዕይ 13 እና 14 ከሆነ አውሬው የሚሞተው በሰይፍ ነው፡፡ ኔሮ እንዴት እንደ ሞተ ታውቃለችሁ? ሱቴንዮስ ሲናገር በራሱ እጅ ጩቤ ወደ ጉሮሮው አስጠግቶ ሳለ በገዛ ራሱ የግል ጸሐፊ በኤጵአፍሮዲጡስ እየታገዘ ራሱን  አጠፋ  ይለናል፡፡  ኔሮ በሰይፍ ይገድል እንደነበር  ሁሉ  በሰይፍ ተገደለ፡፡
ራዕይ17÷ 3 አውሬው ቀይ እንደሆነ  ይነግረናል፡፡ ቀይ ቀለም ምናልባት በአውሬው እንዲፈስ የተደረገውን የደም ጎርፍ የሚያመለክተው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሱቴንዩስ የኔሮን  ቤተሰቦች  ቅድመ  አያቶች  በተመለከተ  ሲጽፍ  ስለ እርሱ ያልተለመደ እንግዳ ነገር  እንደነበረው ይጽፋል፡፡
የአውሬው ቁጥር 666 ነው፤ የኔሮ ስም ሲደመር 666 የተሰኘውን ቁጥር ያመለክታል፡፡ አውሬው የነበረው ባህርይ ጨካኝ ነበር፤ ኔሮም የአውሬ ዓይነት  ጠባይ  ነበረው፡፡  አውሬው ቅዱሳንን ለ42 ወራት ይዋጋቸው ነበር፤ ኔሮም ክርስቲያኖችን ለሦስት ዓመት ተኩል ሲያሳድዳቸው ነበር፡፡ አውሬው  በሰይፍ ተወግቶ ይገደላል፤ ኔሮም ራሱን በጩቤ ወግቶ ገድሎአል፡፡ አውሬው ቀይ ነበር፤ ኔሮም በነዚያ ዘመናት ያልተለመደ እንግዳ በሆነ ሁኔታ  ቀይ  ጢም ነበረው፡፡ ከነዚህ ማስረጃዎች የተነሳ የዮሐንስ ራዕይ አውሬ ቄሳር ኔሮ ነው፡፡ ዮሐንስ እነዚያን በትንሹ እስያ ይኖሩ የነበሩትን የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ሲናገራቸው እነዚህ ነገሮች ቶሎ የሚሆኑ   ነገሮች ናቸው ብሎ  እንደነገራቸው አስተውሉ፡፡ እኛ የሃያኛው  ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ታላቅ  መከራን   የሚያስነሳ ክፉ አውሬ ይመጣል ብለን መጠበቅ የለብንም፣ ይህ ያኔ በኔሮ እና በመጀመሪያው ክፍለ  ዘመን ክርስቲያኖች ጊዜ  የሆነና  የተፈጸመ ነው፡፡
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የሚገልጣት ሁለተኛዋ ጠላት ጋለሞታይቱ ፣ ናት
ራዕይ 17÷ 3-6 "በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ። ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት  የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤ በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም ታላቂቱ ባቢሎን፥ የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት ተብሎ ተጻፈ።  ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ  ታላቅ  ድንቅ አደነቅሁ።"
ሰባት ራስ ባለው አውሬ ላይ የተቀመጠች ሴት  ባቢሎን ተብላ ተጠርታለች፣ አንዳንዶች የሮምን ከተማ የምትወክል ናት ይላሉ፡፡ ነገር ግን አውሬው ራሱ  ሮም  በመሆኑ ይህ የተለየ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፤ ባቢሎን የእግዚአብሔር ጠላት የሆነውን ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በተለይ በዚሀ ጉዳይ የሚያመለክተው ኢየሩሳሌምን ነው፡፡
ጋለሞታይቱን ሴት ኢየሩሳሌም ናት ብሎ ለመተርጎም በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ጋለሞታይቱ  ባቢሎን ተብላ ተጠርታለች፡፡ በራዕይ 14÷ 8 ላይ ባቢሎን ታላቂቱ ከተማ ተብላ ተጠርታለች፤ ራዕይ 11÷ 8 ታላቂቱ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ  የተጠቀሰችበት ቦታ ሲሆን ጌታችን የተሰቀለባትን ቦታ ኢየሩሳሌምን ያመለክታል፡፡ በብሉይ ኪዳን ካላት የቃል ኪዳናዊ ማዕረግ የተነሳ ታላቅ  ነበረች፡፡ ኢየሩሳሌም ቀደም ሲል ከባቢሎን ጋር በሚነፃፀር የአሕዛባዊ ስያሜ ስትጠራ ነበር፣ በራዕይ 11÷ 8 እንደተባለው "በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ" የተባለችው ናት፡፡ በኢሳያስ 1÷ 9-10  እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከኃጢአተኝነትዋ የተነሳ "ሰዶም እና ገሞራ"  ብሎ ይጠራታል፡፡
ጋለሞታይቱ በራዕይ 17÷ 6 ፤ 16÷ 6 እና 18÷ 21 እና 24 እንደተገለጠው በቅዱሳን ደም ሰክራ ትታያለች፡፡ በመላው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ  ኢየሩሳሌም ክርስቲያኖችን በማሳደድ  ሥራ ዋና ፋና ወጊ  ሆና ትታያለች።
ሐዋ7÷ 51-53 "እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ። ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤  በመላእክት ሥርዓት ሕግን  ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን  እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት  ገደላችሁትም።"
በደብረ ዘይት ተራራ ፍካሬ አውድ ውስጥ በማቴዎስ 23÷ 34-36 ጌታ ኢየሱሰ እንዲህ ይላል፡-
"ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ  እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ  የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ፣  እውነት እላችኋለሁ፥  ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።".
እንደ ራዕይ 17÷ 4 አገላለጽ ጋለሞታይቱ በአይሁድ የክህነት አለባበስ ሕብረ ቀለማት ተጎናጽፋ  ትታያለች፡፡ በዘጸዓት 28 እነዚህን ሕብረ ቀለማት ለሊቀ ካህናት አለባበስ መድቦ ይናገራል፡፡ ሊቀ ካህኑ በግንባሩ ላይ የሚያደርገውና "ቅድስና ለእግዚአብሔር" የሚል ጽህፈት ያለበትን መጠምጠሚያ ያደርግ ነበር (ዘዳ  28÷ 36-38)። ይህቺ ጋለሞታ በግንባርዋ ላይ ያደረገችው የስድብ  ስም ነበረባት፣ ራዕይ 17÷ 5፡፡ ለጌታ ቅዱስ ልትሆን ይገባት ነበር፣  ነገር ግን  የጋለሞታዎችና የእርኩሰት  ሁሉ  እናት ሆነችበት፡፡
በጋለሞታይቱ እና ከሰማይ በምትወርደው ሙሽራ መካከል ግልጽ የሆነ ተቃርኖ ሲነፃፀር ይታያል፡፡ ራዕይ 21 እና 17 ብናነፃፅር ሁለት ሴቶችን እናያለን፡- አንዲቱ ጋለሞታ ስትሆን ሌላይቱ   ድንግሊቱ ሙሽራ ናት፤ አንዲቱ ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ስትሆን ሌላይቱ ደግሞ ከታች የሆነችው ኢየሩሳሌም ናት፡፡
ጳውሎስ በገላትያ 4÷ 25-26 ስለ እነዚህ ስለ ሁለቱ ኢየሩሳሌሞች  ይናገራል፡-
"ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረሲና ናት፤  አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት።"
ዮሐንስ ስለ ጋለሞታይቱ ምን ብሎ እንደሚያስተዋውቀን ልብ በሉ፣ እንደገናም ስለ ሙሽራይቱ ምን ብሎ እንደሚያስተዋውቀን ልብ በሉ፡፡ በጣም ተቃራኒ የሆነ መልክና ገጽታ ነው ያላቸው፡-
ራዕይ 17÷ 1 "ሰባቱንም ጽዋዎች  ከያዙ  ከሰባቱ  መላእክት አንዱ መጥቶ። ና በብዙም  ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤"
ራዕይ 21÷ 9 "ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ። ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት  ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ።"
ጋለሞታይቱ ሮምን በሚወክለው ባለ ሰባት ራሱ አውሬ ላይ ተቀምጣ ትታያለች፡፡ ይህ ከሮም ጋር መመሳሰልን ወይም አንድ መሆንን የሚያመለክት ሳይሆን ነገር ግን  ከሮም ጋር  የነበረን  አንድ የሆነ የስምምነትና የሕብረት ሁኔታ ያሳያል፡፡  የክርስቶስን ተሰቅሎ መሞት አጥብቀው  የጠየቁ አይሁድ ነበሩ፡፡  ጲላጦስ በእርሱ ላይ ምንም ጥፋትን ስላላገኘበት ኢየሱስን ፈትቶ  ሊለቅቀው ቢፈልግም አይሁድ ግን  እንዲህ  ይሉ ነበር፡-
ዮሐ19÷15 "እነርሱ ግን አስወግደው፥ አስወግደው፥ ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። ንጉሣችሁን ልስቀለውን? አላቸው። የካህናት አለቆችም። ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም ብለው መለሱለት።"
አይሁድ ኢየሱስን በመቃወም ከቄሳር ወገን ሆነው ነበር፡፡ አይሁድ በክርስቲያኖች ላይ ስደትን ባማነሳሳታቸው በዚህ ተግባር ተባባሪ እንዲሆኑዋቸው ሮማውያንን ያለማቋረጥ ያግባቡአቸው ነበር፡፡ በሐዋርያት ሥራ 17÷ 7 ክርስቲያኖች በአይሁድ ሲከሰሉ እና ከቄሳር አዋጅ በተቃራኒው ክርስቲያኖች ሌላ  ንጉስ አለ ብለው ይሰብካሉ በለው ያሳጡአቸው ነበር፡፡ በአውሬው ላይ የተቀመጠችው ጋለሞታይቱ ኢየሩሳሌም ክርስቲያኖችን ለማሳደድ በሮም ላይ ስለተደገፈች  ነው፡፡ የራዕይ መጽሐፍ በትክክል የተፃፈው በ68 ዓ.ም ከሆነው የኔሮ ሞት  ቀደም ብሎ  ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ትንቢቶች ተፈጽመዋል፡፡ ከተፃፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ቶሎና በቅርቡ የሚፈጸሙ ነገሮችን በተመለከተ የተፃፈ ነበር፡፡ ይህ መጽሐፍ ትኩረቱ በአይሁድና በሮም አማካኝነት በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሰውን ስደት  የተመለከተ ሲሆን፣ በእነዚህ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ይተነብያል፡፡ ስለሆነም የመጽሐፉ ዓላማ በመከራ ጊዜ አማኞችን ለማጠንከርና  ለማበረታታት ነው፡፡
የጥናቱ ማጠቃለያ፦
ይህንን መጽሐፍ በሚገባ መረዳት የሚቻለው በኃላፊውያን እይታ እንጂ በመፃአያ እይታ አይደለም፡፡ ይህንንም በማድረግ ሁሉንም  ነገር በየዕለቱ በሚነገር የጋዜጣ ዜና በኩል የዘመኑ ምልክት እንደተገኘ አድርጎ ያልሆነ እንግዳ ትርጉም መስጠትን እንድናቆም ያደርገናል፡፡ የዓለማችንም ሆነ የሃገራችን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበትና እየከፋ የሚሄደው ክርስቲያኖች ብርሃንና ጨው የመሆን ጥሪያቸውን ቸል በማለታቸው እንጂ በመሰረቱ የመጨረሻው ዘመን ስለሆነ  አይደለም፡፡ ፡፡ እኛ ጨውና ብርሃን መሆን አለብን፡፡ ዓለማችንን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምን በወንጌል ልንጠረው ይገባናል፡፡ የመፃኢነት   አስተሳሰብ ስለ መጪው ዘመን እና እድል በሁሉ ረገድ የጨለምተኝነትን ዝንባሌ ይከተላል ብዬ አስባለሁ፣ ለአዲሱ  ቃል  ኪዳን  ተዓምራትም  የእምነትን  ዓይን  ያሳውራል፡፡ ወደ ፊት እንደሚሆን ሁሉ የማይሆንን ዳግመኛ ምጽዓት ቶሎ ይሆናል በማለት የሚጠባበቁ አማኞች ራሳቸውን ለተስፋ መቁረጥ  እና  ለሕይወት ድካም የሚያጋለጡ ናቸው፡፡ ምሳሌ 13÷ 12 "የምትዘገይ ተስፋ ልብን  ታሳዝናለች የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት  ዛፍ ናት" ይላልና።
በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዓት ውስጥ ባለን በእኛ ተስፋ እና መሻት  ውስጥ፣  የእግዚአብሔር  ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፡፡ እርሱ ከእኛ ጋር አድሯል፡፡ የምንኖረው በከበረው የአዲሱ ቃል  ኪዳን ዘመን ውስጥ ነው፡፡ እርሱም ይህ በክርስቶስ ያገኘነው የጸጋና  የዘላለም ጽድቅ አዲስ ሕይወት፣ ክርስትናችን ነው።  በእውነት እንደ እግዚአብሔር ቃል ብናስብ በእምነት የምንኖርበት አዲሱ  ሰማይና  አዲሱ ምድር፣ ዘላለማችን ነው፡፡   ሃሌሉያ!!
2ኛ ቆሮ 5፥ 17 "ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል"
ማሳሰቢያ፦ ይህ አጠር ተደርጎ የተዘጋጀ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የመግቢያ ጥናት በመጽሐፉ ውስጥ የተባሉትን ሁሉ ነገሮች ለመዳሰስ  ያለመ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ምልከታ እንዲኖረን ለምንሻ የእግዚአብሔር እውነት ፈላጊዎች ብርቱ ጥናት ልናደርግ ያስፈልገናል። ይህ ጽሁፍ ግን አገርኛውን የሥነ ፍጻሜ ጥናት ደርዝ ለማስያዝ መለስተኛ መነሻ እንዲሆን ጸሎቴ ነው። በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የበለጠ ንባብ ሊያደርጉ ለሚወዱ የቃሉ ተማሪዎች የምጠቁመውና ከጉግል ቋት በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ፣ ለዚህም ጥናት እንደ ግብዓት ያገለገሉ መጻህፍት ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፦
Gentry, Kenneth L., "Before Jerusalem Fell, Dating the Book of Reveltion," 1989. 
"The beest of Revelation," 1989.
Terrry Milton S., "Biblical Apocalyptics, A Study of the most notable Revelation of God and of Christ," Baker Book House, 1988.
Chilton, David., "The Days Of Vengeance, An Exposition of the Boook Of Revelation," Dominion Press Ft.Worth, Texas, 1987.
Arthur S. Peake, "The Revelation of John", Hartley Lectures (London: Joseph Johnson, 1919
አዘጋጅ ቄስ  ግዛቸው ከበደ
Email: gizachewkebederoba@gmail.com

፭፣ ፍርድ የራዕዩ ጭብጥ

ክፍል ፭
ፍርድ፣ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ጭብጥ

ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እንደሚስማሙበት የዮሐንስ  ራዕይ  መጽሐፍን ጭብጥ መልዕክት የሚነግረን ቃል  በራዕይ  1÷7 ላይ ይገኛል ብለን ነበር ያለፈውን ጥናት ቀጣይ ሃሳብ በይደር ያስቀመጥነው።
ራዕ 1÷ 7 "እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ  እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ።  አዎን፥  አሜን።"
ይህ ምንባብ ክርስቶስ በእስራኤል ላይ በፍርድ ዳግመኛ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ በብሉይ  ኪዳን የደመና መምጣት በተደጋጋሚ የሚያመለክተው እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ በፍርድ እንደሚመጣ ያለውን ትንቢታዊ ገለጻ ነው፡፡ በራዕይ መጽሐፍ ላይም "ይመጣል" ተብሎ የተነገረው ፍርድ የሚፈጸመውም "የወጉት" ተብለው በተገለጹት ላይ ነው፡፡ ታዲያ እነርሱ እነማን ናቸው?  አዲስ ኪዳን ክርስቶስን የወጉ ብሎ በተደጋጋሚ የሚጠቁመው የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አይሁድን ነው፡፡ እነዚያ ክርስቶስን የወጉት ደግሞ "የምድር ወገኖች" የተባሉት  የሚያመለክተው፣ ማለትም ምድር የተባለው የተስፋይነቱን ምድር ወይም እስራኤልን ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ለአንባቢዎቹ የሚያስተዋውቀው የፍርድን ሥነ-መለኮት ሲሆን፣ ይኸውም በተለይ የእግዚአብሔር ፍርድ የእስራኤልን  ሕዝብ  በመቃወም  የጸና  እና  የተወሰነ በመሆኑ ላይ ነው፡፡
የእስራኤል ሕዝብ ጌታን የሰቀሉ እና በግልጽ በአደባባይ የእግዚአብሔርን ፍርድ  በራሳቸው ላይ  የጋበዙና የጠሩ ሕዝቦች ናቸው፡- "ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ።" (ማቴ 27÷ 25)፡፡ በ70 ዓ.ም በእስራኤል ላይ የሆነው የእግዚአብሔር ፍርድ በውድ ልጁ በመሲሃቸው ላይ የፈጸሙትን ግፍና ወንጀል  የሚመጥን ነበር፣  ወንጀላቸውም የክርስቶስ ስቅላት ነበር፡፡ ይህ ወንጀል በታሪክ  ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት እጅግ የከፋው ወንጀል ሲሆን ፣  ለዚህ ተወዳዳሪ ለማይገኝለት  ወንጀል  የሚገባውም ቅጣት  በታሪክ  ውስጥ እጅግ የከፋው መሆን አለበት፤ እርሱም "ታላቁ መከራ" ተብሎ የሚጠራው ነው። ከዚህ የተለየውንና  ያነሰውን ማንኛውንም የዚህ አለም መከራ "ታላቁ መከራ" ብሎ መጥራት ያዚያን ትውልድ ወንጀል አሳንሶ መመልከት ይሆናል።
በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ የተዘገበው የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ተብሎ የሚጠራው የጌታችን ትንቢት የቤተመቅደሱን መፈራረስ እና የዚህን መከራው ሁኔታ  የሚያሳይ ትንቢትን ይዞአል፡፡ እጅግ የሚበዙ የመፅሐፍ ቅዱስ መምህራን ዮሐንስ በደብረ ዘይቱ ተራራ ላይ የተነገረውን የክርስቶስን ፍካሬ ያየበት እና የተረጎመበት አስፋፍቶም ያቀረበበት የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፉ እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ለአሁኑ ከደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ እና ከዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ላይ የተወሰኑ  መመሳሰሎችን በመጠኑ አንስተን እንመልከት፡፡
* ከሁሉ በፊት፦
ራዕ 1÷ 1 እነዚያ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ሁነቶች የሚሆኑት "ቶሎ" እንደሆነ ይነግረናል፡፡ በደብረዘይቱ ተራራ ፍካሬም ክርስቶስ "እውነትት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ  እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፉም" /ማቴ   24÷34/ ይላል፡፡ 
* በሁለተኛ ደረጃ ሁለቱም  ታላቁን መከራ ይጠቅሳሉ፣
ማቴ  24÷21 "በዚያ ጊዜ  ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ   እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ  መከራ ይሆናልና።"
ራዕ 7÷ 14 "እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ  መከራ የመጡ ናቸው፥   ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።"
* በመጨረሻም ሁለቱም ተመሳሳይ በሆነ የቋንቋ አጠቃቀም ቤተ መቅደሱን እና እየቀረበ ያለውን ውድመቱን ይጠቀሳሉ፡-
ሉቃ 21÷ 24 "በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።
ራዕ 11÷ 2 "በመቅደሱም ውጭ  ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።"
ለዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ እንደ መሰረት ሆኖ በአዲስ ኪዳን የመጀመሪያዎቹ ሶስት ተመሳሳይ ወንጌላት የተዘገበው የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ በእስራኤል እጣ ፋንታ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡  ከአራቱም ወንጌላት ይህንን የደብረ ዘይቱን ፍካሬ ያላካተተ ብቸኛ መጽሐፍ  የዮሐንስ  ወንጌል  ሲሆን ፣  ዮሐንስ ይህንን ጉዳይ በስፋት የሚዳስሰው አቡቀለምሲሳዊ በሆነው በዮሐንስ ራዕይ መጽሐፉ ላይ ነው፡፡ የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ሥነ መለኮታዊ አውድ የሚጀምረው ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በለሲቱን ከረገመበት ከማቴዎስ 21÷ 19 ላይ ነው። ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ በማቴዎስ 21÷ 33 ላይ ስለ ወይን አትክልቱ ባለቤት ምሳሌ ይናገራል፡፡ በዚህም ምሣሌ "የእግዚአብሔር መንግስት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም  ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች" (ማቴ 21÷ 43) ብሎ ትንቢት ይናገራል፡፡ ስለ እስራኤል እየተናገረ እንደ ሆነ አውቀዋል /ማቴ  21÷45/፡፡
በማቴዎስ 23 ላይ  ኢየሱስ ጻፎችንና ፈሪሳዊያንን በተደጋጋሚ ከባድ ዘለፋ  "ግብዞች" እያለ ይጠራቸዋል /ማቴ 23÷ 13-15/፤ በማቴዎስ 23÷ 31-36 እስራኤል  በታሪኳ ነብያትን እንደ ገደለች አስታውሶ አሁን ደግሞ የእግዚአብሔርን  ልጅ  ልትገድለው እንዳላት ያመለክታል፡፡  በማቴዎስ 23÷ 36 "በዚህ ትውልድ" ላይ ሲል በቁጥር 37-38 እንደተገለጸው ትኩረቱ እስራኤል መሆንዋ አያከራክርም፡፡ እንግዲህ የደብረ ዘይቱ ተራራም ፍካሬ አጠቃላይ አውድ የተመለከተው እና  የሚገነባው በዚህ  ዳራ ላይ ነው፡ ፡
የደብረ ዘይቱን ተተራ ፍካሬ የሚከፍት ዋነኛ ጥያቄ ቤተ መቅደሱን በተመለከተ የቀረበው ንግግር ሲሆን፣ ይኸውም በማቴ  24÷ 1 እና 2 የተገለጸው ነው፡፡
"ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው"።
ለዚህ የኢየሱስ ንግግር የደቀ መዛሙርቱ ምላሽ  "ይህ መቼ ይሆናል?" የሚል ጥያቄ ነበር፡፡ በቁጥር 3 ላይ "ዓለም" ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ /aion/ የተሰኘው ቃል የተሻለው ትርጉም "ዘመን" የሚለው ነው፡፡ በደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ውስጥ ማዕከላዊ ቦታን የያዘው የአይሁድ ቤተ መቅደስ ጉዳይና የህዝቡ እጣ ፈንታ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡  በማቴዎስ 24 ላይ የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች ሆነው ከቀረቡት መካከል የተወሰኑትን በወፍ በረር እንመልከታቸው፦
♦ ማቴ  24÷ 15 ሰለ ተቀደሰችው ሥፍራ ይናገራል፡፡
ማቴ 24 ÷ 6 ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።
በዓለም ታሪክ ውስጥ ጦርነትንና የጦርነትን  ወሬ  ሰምተን የማናውቀው መቼ  ይሆን? ይህ የቁጥር 6 ጦርነት ታዲያ ምን ዓይነት ምልክት ነው? የሮም ሰላም /Pax Romana/ በተሰኘው ዘመን ላይ ኖራችሁ ቢሆን ኖሮ  ይህ  አይነተኛ ምልክት ይሆንላችሁ ነበር፡፡ በሮም ነገስታት ታሪክ ይህ የሰላም ዘመን በአንጻራዊነት ብዙም የጎላ ብጥብጥ ሳይታይበትና ሳይሰማበት እስከ  ቄሳር ኔሮ  ዘመን ድረስ ቀጥሎአል፡፡ በሮም ሰላም /Pax Romana/ ዘመን ውስጥ ጦርነቶች እና የጦርነት ወሬ ወዲያውኑ መከራውን ቀድመው ታይተዋል፡፡
♦ በማቴ  24÷14 እንደተገለጠው ወንጌል ለዓለም ሁሉ ይሰበካል
ማቴ 24 ÷14 "ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን  ጊዜም መጨረሻው  ይመጣል።
ኢየሱስ አይሁዳዊ እንደነበር ለአይሁድም እንደሚናገር መዳንም ደግሞ የአይሁድ እንደነበር አስተውሉ፡፡ የመጀመሪያዋ የክርስቲያን ቤተክርስቲያን አይሁድ በሆኑ  ምዕመናን የተዋቀረች ነበረች፡፡ አሕዛብ የይሁዲነት ተከታይ ሳይሆኑ በቀጥታ ወደ ቤተክርስቲያን የገቡት ከበዓለ ሃምሳ ቀን በኋላ በግምት አስር ዓመት  ያህል ቆይቶ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ተልዕኮን በ"ዓለም ሁሉ" የማዳረስ እንቅስቃሴ የተጀመረው በአንጾኪያ በተደረገው ውሳኔ ነበር (ሐዋ11÷ 19-30)፡፡ መጨረሻው ከመሆኑ በፊት ወንጌል ከአይሁዳዊነት በላይ አልፎ መሄድ ነበረበት፡፡ ይህም ማለት ከአለም ፍጻሜ በፊት የታላቁ ተልእኮ ትእዛዝ ተፈጽሞ ነበር ማለት ነው። ስለዚህም በዚያው ዘመን ወንጌል  ለዓለም ሁሉ  ተሰብኮ እንደ ነበር መጽሐፍ  ቅዱስ በማስረጃ ያሳየናል።
ቆላ 1÷ 5-6 "ስለዚህም ተስፋ በወንጌል እውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ። ይህም በዓለም ሁሉ ደግሞ እንዳለ ወደ እናንተ ደርሶአል፥ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከከሰማችሁበትናካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥  በእናንተ ደግሞ እንዳለ  እንዲህ  በዓለም ፍሬ  ያፈራል ያድግማል።"
ሮሜ 1÷8 "እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማች አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ  አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ።
♦ ማቴዎስ  24÷15 ስለ ጥፋት ርኩሰት ይናገራል፡፡
ማቴ 24÷ 15 "እንግዲህ  በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን  የጥፋትን ርኩሰት  በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ  ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥"
ጆሳፈስ  እንደ ጻፈው "ቤተመቅደሱ በተደመሰሰ ጊዜ  የቲቶ ሰራዊት  የሮማዊያን ግርማ ምልክት የሆነውን SPQR የተጻፈበትንና የሮምን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እና የሕዝብ ኃይልና ብዛት የሚወክል የንስር ምልክት  ይዘው  ወደ ቅድስተ ቅዱሳን  ውስጥ  ዘልቀው በመግባት   በዚያ አስቀመጡት፤ በዚያም በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በግንባራቸው ወድቀው ቄሳርን አመለኩ" ሲል ይዘግባል /Wars, መጽሐፍ 6፣ ምዕራፍ 6 አንቀጽ 1/፡፡ ይህ እንግዲህ ጥፋትን ያደረገው ርኩሰት የመጨረሻ ተግባር ነው፣ ነገር ግን ይህ የጥፋት ርኩሰት  የጀመረው በሉቃስ 21÷ 20 እንደተዘገበው ገና ኢየሩሳሌም በሮማውያን  ጦር ተከባ  በነበረበት ጊዜ  ነው፡፡
ሉቃ  21÷ 20 "ኢየሩሳሌም ግን  በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።"
የጥፋት ርኩሰቱ ገና ሲጀምር በይሁዳ ያሉ ፈጥነው ከዚያ  እንዲወጡ የሚያሰጠነቅቅ ቃል በማቴዎስ 24÷ 16 ላይ እናገኛለን፡፡
ማቴ  24÷ 16 "በዚያን  ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ  ተራራዎች ይሽሹ፥"
በ68 ዓ.ም  በጦርነቱ  መሃል  ኔሮ በቤተ መንግስቱ ውስጥ  ራሱን ካጠፋ በኋላ፣ ኢየሩሳሌምን ለመሰባበር ዘምቶ የነበረው የሮማውያን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል ቨስፓሲያን ወደ ሮም በመመለስ አዲሱ ተተኪ ንጉሰ ነገስት ለመሆን ውጊያ አደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ክርስቲያኖች በማቴዎስ 24÷ 16 ያለውን ማስጠንቀቂያ ስላስተዋሉ ኢየሩሳሌምን ለቀው ወጡ፤ አይሁድ ግን በተቃራኒው የቨስፓሲያንን እና የጦሩን ወደ ሮም መመለስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነላቸው የድል መንሳት ምልክት አድርገው ስለ ወሰዱት በኢየሩሳሌም ከቀድሞው ይልቅ በብዙ ቁጥር በመሰባሰብ አመጹን ቀጠሉበት፡፡ ሮማውያንም ተመልሰው መጥተው ከተማይቱን ፈጽመው አወደሟት፡፡
♦ ማቴዎስ  24÷ 21 ስለ ታላቁ መከራ ይናገራል፡፡
ማቴ  24÷ 21 "በዚያን ጊዜ  ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ   እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን  ታላቅ  መከራ ይሆናልና።"
እንደ ቨስፓስያን ዘገባ፣ ሮማውያኑ ያንን ከአይሁድ ጋር የገጠሙትን ጦርነት   ቀጥለው ባሉበት ጊዜ እጅግ ጨካኞች በመሆን የሚያደርጉትን ሁሉ በከፋ በቀል ያደረጉ ነበር፡፡ ብዙ ደም መፍሰስ በምድሪቱ ሁሉ ሲሆን ቤቶች በእሳት ይጋዩ ነበር፡፡ በይሁዳ አውራጃዎችና በቅድስት ከተማ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ሕዝቡም ሁሉ የሚበሉት ስላልነበራቸው ምግብ ለማግኘት ሲሉ እርስ በእርሳቸው በግልጽና በከፋ ጭካኔ  ይተራረዱ ነበር፣ እናቶችም የገዛ ልጆቻቸውን ቀቅለው ይበሉ ነበር፡፡ ስለዚህ መከራ ምን ተብሎ እንደተነገረ ልብ በሉ፣ "ምንም የሚስተካከለው የለም" ነው የተባው፡፡ የኢየሩሳሌም ውድመት ማለት በመለኮታዊው ፕሮግራም ውስጥ የሚሰጠው ትርጉም ከአንዲት የአይሁድ ከተማ  አወዳደቅ በላይ  ከፍ  ያለ  ነው፣   ይህ ውድመት ማለት የአሮጌው ኪዳን እስራኤል ውድመትና ፍጻሜ ማለት ነው፡፡
♦ ማቴዎስ 24÷ 28 ስለ አሞሮች  መሰበሰብ ይናገራል።
ማቴ  24÷ 28 "በድን  ወዳለበት በዚያ  አሞራዎች ይሰበሰባሉ።"
አሞራ የሮማውያን ምልክት ነው፡፡ በሌላ አባባል ሮማውያን መሰብሰብ በሚጀምሩበት ጊዜ ያኔ እስራኤል የሚዘነጣጠል በድን ሆኖአል ማለት ነው፡፡
♦ ማቴዎስ24÷ 29 ስለ ከዋከበት መውደቅ እና ስለ ጨለማ ሰማይ ይናገራል፡፡
ማቴ 24÷29 "ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥  ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥"
ይህ በጣም የተለመደ እና ከብሉይ ኪዳን የተወሰደ አቡቀለምሲሳዊ ቃል  እና ንግግር ነው፡፡ ከዋከብት የሚወክሉት  የመንግስት አስተዳደርና  አገዛዝን  ነው፡፡ እስራኤል በቃ ወደቀች ማለት ነ ው፡፡
♦ ማቴዎስ 24÷ 30 የኢየሩሳሌም መፈራረስ ኢየሱስ እንደ ተመለሰና ከቅዱሳኑ ጋር  በመንግስቱ እንደሚገዛ ምልክት  መሆኑን   ይነግረናል፡፡
ማቴ 24÷ 30 "የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም  የምድር ወገኖች  ሁሉ  ዋይ  ዋይ  ይላሉ፥  የሰው ልጅንም  በኃይልና   በብዙ  ክብር  በሰማይ  ደመና  ሲመጣ ያዩታል፤"
♦ ማቴዎስ 24÷ 31 ብዙዎች  መነጠቅ ብለው የሚጠሩትን ጉዳይ  ያመለክታል፤
ማቴ 24÷ 31 "መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ  ነፋሳት  ለእርሱ  የተመረጡትን ይሰበስባሉ።"
ይህንን ጥቅስ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4÷ 15-17 ካለው ጋር ብታነጻጽሩት ያው አንዱን ኹነት እንደሚናገሩ ታያላችሁ፡፡ ይህም የተመረጡት በእግዚአብሔር መንግስት ስለ መሰብሰባቸው የተነገረ ነው፡፡
♦ በማቴዎስ 24÷ 32-34 ኢየሱስ ሲናገር እነዚህ ነገሮች በሙሉ የሚፈጸሙት እርሱ "ይህ ትውልድ" ብሎ በሚጠራው እና እርሱ ሲናገር ቆመው ይሰሙ በነበሩ ሰዎች ዘመን እንደሆነ እናያለን፡፡
ማቴ 24÷ 32-34 "ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥   ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ  ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥  ይህ  ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።"
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ይህንን ቃል "ይህ ትውልድ አያልፍም" ብሎ  ከማንበብና   ከመተርጎም ይልቅ "ይህ ዘር አያልፍም" እያሉ ለመተርጎም ሲሞክሩ ይታያሉ፣ በቋንቋ አገባቡ ያየነው  እንደሆነ እንኳ ይሄ ትርጉም የሚሰጥ አይሆንም፡፡ ቤተ መቅደሱ የፈራረሰው ከደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ በኋላ በአርባ አመታት ውስጥ ነው። ይኸውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ  የሆነ የአንድ  ትውልድ ጊዜ ነው። "ይህ ሁሉ" የተባለውን ልብ በሉ፣ የሚፈጸመው  በዚያ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ነው፡ -ንጥቀቱ   24÷ 31 ፤  የሰማይና የምድር እልፈት 24÷ 34፤   እንዲሁም የጌታ ዳግመኛ ምጽዓት 24÷ 44፤ ይህ ሁሉ ያኔ እንደሚፈጸም የተነገረ ነው፡፡
የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ትኩረቱ በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዓት ወቅት የሚሆነው የኢየሩሳሌም  ውድመት ነው፡፡ (በማቴዎስ 24 ላይ ሰፋ ላለ ግንዛቤ "የጌታ ዳግም ምጽአት፣ መቼ እና እንዴት" በሚል ያቀረብሁትን የቪድዮና የጽሁፍ መልዕክት በብሎገሬና በዩትዩብ ቻናሌ ላይ እንዲጎበኙ አበረታታለሁ)።
እንግዲህ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍም ቢሆን በቀላሉ በዚሁ የደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬ ላይ ዘርዘር ባለ መልኩ ተስፋፍቶ የተነገረ ትንቢት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የዮሐንስ ራዕይ ትኩረት የእስራኤል ጥፋት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ያ የእርስዋ ጥፋትና ውድመት አንዳች ትኩረትን የሚስብ ነገር አለው፡፡ እርስዋ የተቀጣችው ስለ ግልሙትናዋ እና ስለ ዝሙትዋ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እስራኤል የያሕዌ አምላክ ሚስቱ እንደ ሆነች  ትቆጠር ነበር፡፡
ኤር 31÷ 31 "እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር  "ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥" ይልና (ይህ ጥቅስ በእንግሊዝኛው NKJV ትርጉም 'እኔም ለእነርሱ ባል ነበርሁ' ይላል እግዚአብሔር)" በሚል የተቀመጠ ነው፡፡
ነብያት አዘውትረው በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካል የነበረውን ቃል ኪዳናዊ ሕብረት ይጠቅሱ ነበር፡፡ እስራኤል ግን የባዕዳንን አማልክት ተከትላ ትነጉድ ነበር፣ በተደጋጋሚም ስለ መንፈሳዊ ግልሙትናዋ ትከሰስ ነበር፡፡ በመጨረሻም እስራኤል "ከቄሳር በቀር ንጉስ የለንም… ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን" ብላ እየጮኸች የእግዚአብሔርን ልጅ አዋርዳና ሰቅላ ገደለችው፡፡ 
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ እስራኤል ያልታመነች ሚስቱ በመሆንዋ ስለ መንፈሳዊ ግልሙትናዋ የሚገባትን ፍርድ፣ የእግዚአብሔርን የፍቺ ጽሑፍና ንጉሳዊ አዋጅ የሚወክል መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ የፍቺና የጦርነትን መልእክት የያዘ ነው። በሚቀጥለው ጥናት ይህንን ሃሳብ ዘርዘር አድርገን እንመለከታለን።
∆∆∆∆∆∆∆∆∆