Wednesday, January 12, 2022

ሶላ ስክሪፕቱራ

ሶላ ስክሪፕቱራ" የተሰኘው ይህ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የእምነት አቋም በቀላሉ ሲተረጎም “በቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ” ማለት ነው።  ይህ አቋም የአማኞችን ኅሊና የመግዛትና የመፍረድ፣ የትኛውንም የቤተክርስትያን አስተምህሮና ልምምድ የማጽናትና የመሻር ሥልጣን ያለው 66ቱን የብሉይና የሐዲስ ቅዱሳት መጻህፍት የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው የሚለውን ሃሳብ በግልጽ የሚያውጅ ነው።  ፕሮቴስታንቶች በየቤተእምነታቸው በጋራ ስምምነት የተቀበሏቸውና እንደ ቤተ ክርስቲያን እውቅና የሚሰጡአቸው የተለያዩ አገልግሎቶች፣ የሲቪል ተቋማት፣ የቤተ ክርስቲያን የእምነት መግለጫዎችና ታሪካዊ  ምስክርነቶችን የመሳሰሉ ሌሎች ደቂቅ የሥልጣን ዓይነቶች ሊኖሩዋቸው ይችሉ ይሆናል።  ዳሩ ግን እነዚህን ሥልጣናት አስመልክቶ ከእግዚአብሔር ሥልጣን የተቀዱና ለራሱ የእግዚአብሔር ሥልጣን የተገዙ እንደሆኑ አድርገው ደግሞ ይቆጥሯቸው ነበር። በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ከእነዚህ ደቂቀ ሥልጣናት ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ በእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን የሚዳኙ እንጂ በራሳቸው ፍጹም ተደርገው አልተቆጠሩም፣ ምክንያቱም ሁሉም እያንዳንዳቸው ስህተት ሊሰሩ የሚችሉና ለእርማት የተጋለጡ ናቸው።  እግዚአብሔር ብቻ ግን የማይሳሳትና በማንም የማይታረም ፍጹም ነው፤ በእግዚአብሔር መንፈስ መነዳት የተሰጠው ቃሉም እንደ እርሱ ነው።  እነዚያ  በተፈጥሯቸው ለእርማት የተጋለጡ፣ ሊሳሳቱ የሚችሉና በማንኛውም ጊዜ ሊሻሻሉና ሊለወጡ የሚችሉ ደቂቀ ሥልጣናት ፍጹምነት የሌላቸው በመሆኑ የአማኞችን ሕሊና በፍጹም መግዛትም ሆነ መፍረድ አይችሉም፤  ሕሊናን የመግዛት መብት ለእግዚአብሔር እና ለቃሉ ብቻ የተጠበቀ ሆኖ ይኖራል። የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ካልሆነ በቀር ማናቸውም የተጻፈም ሆነ ያልተጻፈ፣ ጥንታዊም ሆነ ዘመናዊ፣ ታሪካዊም ሆነ ካሪዝማዊ የትኛውም ትምህርትና ልምምድ የአማኙን ሕሊና እንዲገዛ ፈጽሞ ሊፈቀድለት አይገባም። በማንም የማይሻረው፣ ሊለወጥም ሆነ ሊሻሻል የማይችለው ዘላለማዊው ሥልጣን፣ እርሱም ፈጣሪዋ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ቤተክርስቲያንን አስገኝቷታል እንጂ ቤተክርስቲያን ቃሉን አላስገኘችውም፤ ቤተክርስቲያንን ቃሉ ቤተክርስቲያን አድርጓታል እንጂ ቤተክርስትያን ቃሉን የእግዚአብሔር ቃል አላደረገችውም፤ ቤተክርስቲያን ለእግዚአብሔር ቃል ትገዛለች እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ለቤተክርስቲያን አይገዜም። ቤተክርስትያንም በፈንታዋ በማንኛውም ጊዜ ሊሻሩ፣ ሊለወጡና ሊሻሻሉ የሚችሉ እነዚህን ታሪካዊ ደቂቀ ሥልጣናት አስገኝታለች፣ እነርሱም ጠቃሚ ታሪካዊ ሰነዶች ብቻ ናቸው እንጂ ሕሊናን የሚፈርዱ ሥልጣናት አይደሉም። ማርቲን ሉተር ሕይወቱን ሊያስከፍለው በሚችልበት የፍርድ አደባባይ ትምህርቱን እንዲያስተባብል የመጨረሻ ዕድል በተሰጠው ጊዜ የተናገረውን ልጥቀስ፦ "በቅዱሳት መጻሕፍት ወይም ግልጽ በሆነ አመክንዮ ተረጋግጦ እንዳምን ካላደረገኝ በቀር፣ ከያዝኩት አቋም አንድ ጋት ያህል እንኳ አልመለስም። ሕሊናዬም በእግዚአብሔር ቃል ተይዞ ሳለ የሕሊናዬን ፍርድ በመደፍጠጥ እቃወመው ዘንድ ትክክልም ተገቢም አይደለም።" ፕሮቴስታንቶች ያቀጣጠሉትን የተሃድሶውን አስተምህሮ ውድቅ ለማድረግ በጊዜው የነበሩ ካቶሊካውያን ከሳሾቻቸው ሉተርንና አብረውት የቆሙትን ወንጌላውያን በቅዱሳት መጻህፍት መሰረት ላይ ብቻ ቆመው ሊሞግቱአቸው ባለመቻላቸው ከቅዱሳት መጻህፍት ርቀው የተንጠለጠሉት በቤተክርስቲያን ታሪክና በጥንታውያኑ የእምነት መግለጫዎች ላይ እንደነበር ከታሪካቸው እናውቃለን። ማርቲን ሉተር ግን በንጉሰ ነገስቱና በጳጳሳቱ ጋሻ ጃግሬነት በተቃውሞ የተሰበሰበበትን ጉባኤና የጉባኤው ውሳኔ የተንጠላጠለባቸውን ጥንታውያን የእምነት መግለጫዎች በጽኑ በመቃወም ውድቅ አደረጓቸዋል። ይህንንም ያደረገው እነዚያን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በጉባኤ ውሳኔ የተዘጋጁ እንጂ በእግዚአብሔር እስትንፋስ ያልተሰጡ የእምነት መግለጫዎችን ስለማያከብራቸው ወይም ደቂቀ ሥልጣናቸውን ስለማይቀበል አይደለም፤ ይልቁንም እነዚህ ታሪካዊ ሰነዶች የእግዚአብሔርን ቃል ተክተው የሙግቱ መሰረት እንዲሆኑ ስላልፈለገ ነው። በእውነትም ሶላ ስክሪፕቱራ ዋጋ የሚያስከፍል አቋም ነው፣ በእኛ ዘመን ደግሞ እንደ ኋላ ቀር አክራሪና ወግ አጥባቂ እያስቆጠረ በማንም እንዳትፈለግ ሊያደርግህ ይችላል። ለሰዎች ስሜት እንደ ምት መች ሆነህ ካላመቻመችህ፣ ካልቀየጥክና ካልደባለቅህ በቀር፣ ወይንም ካልዘባረቅህና ካላጨናበርክ በቀር፣ በሶላ ስክሪፕቱራ ብቻ አትሮንስ ላይ ብትሰየም ማንም ሊሰማህ አይፈልግህም። ያም ቢሆን እንኳ "ያለ መነሳትና ያለ መናወጥ"፣ ያለ ማመንታትም እዚሁ ላይ "Hear I stand" ብሎ ጸንቶ መቆሙና መሞቱ ይመረጣል። ገና በጠዋቱ በሉተራዊው ወንጌላዊ እምነት ውስጥ የተዋወቅሁትና የእይታዎቼ ሁሉ ብርሃን የሆነልኝ ይህ "ሶላ ስክሪፕቱራ" በፕሪቴሪዝም የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ውስጥ የበለጠ እንድወደውና እንድማረክበት አድርጎ አጽንቶኛል። ይህ ደግሞ የዘወትር መጽናናቴ ነው። (gkr)




ስለ ሰይጣን አንዳንድ ጉዳዮች

ስለ ሰይጣን አንዳንድ ጉዳዮች


መግቢያ፦ አስተማሪው ተማሪዎቹን ስለ እግዚአብሔር እና ስለሰይጣን አምስት አምስት ገጽ ጽሁፍ ይዛችሁ እንድትቀርቡ ባለው መሰረት፣ ብዙዎቹ የታዘዙትን አቀረቡ። ከተማሪዎቹ አንዱ ግን ዘጠኙንም ገጽ ስለእግዚአብሔር ጽፎ መጨረስ ሲያቅተው በቀረችው አንድ ገጽ ላይ "ለሰይጣን ጊዜ የለኝም" ብሎ እንደመለሰው እናንተም አንባቢዎቼ ለሰይጣን ጊዜ የለኝም እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በመሰረቱ ወንጌልን የመስበክ እንጂ ሰይጣንን የማስተዋወቅ ጥሪ የለኝም፣ ክርስቶስን ለማወቅ በተጋንና እርሱን ለመምሰል በተጋደልን መጠን ግን ሰይጣንን እና አሰራሩን ገልበን እናውቀዋለን። እንግዲህ ሴጣን ሳይቆጠር ከጥራዞችና ከባህር ማዶ ኑሮ ጋር እየታገልሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተይዤ ያቀረብኩትን ጽሁፍ በእግዚአብሔር ብርሃን እየመረመራችሁ ብትማሩበትም ብትባረኩበትም ደስታዬ ወደር የለውም።


ሰይጣን ሲሰየጥን፣


ከሁሉ በፊት ሰይጣን ፍጡር ነው፣ ለዚያውም በአንድ ጊዜ አንድ ስፍራ ላይ ብቻ መገኘት የሚችል ውሱን ፍጡር ነው።  በሌላም በኩል ለምሳሌ ጻድቁን ኢዮብን ከመፈተኑ አስቀድሞ እንኳ የእግዚአብሔርን ፈቃደኝነት የግድ ማግኘት የነረበት መሆኑን በኢዮብ ምዕራፍ 1 ውስጥ እንማራለን። እግዚአብሔር እንደወደደ ወዲያና ወዲህ ፈቃዱን እየጠመዘዘ ያንቀሳቅሰዋል እንጂ በራሱ ምንም የማድረግ ሥልጣን የለውም። እንደገናም በአዲስ ኪዳን እንዲህ ያለውን ተመሳሳይ ውሱንነት ሐዋርያው ጴጥሮስን ለመፈተን እንዲፈቀድለት ሲለምን (ሉቃስ 22፥ 31) ባለው ሁኔታ እናያለን። 


የቀደመው እባብ


ዘፍጥረት 3፥ 1 ላይ "እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ።" የሚል ቃል እናነባለን። ከዚህም ገና ከመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ እባብ ፍጡር እንደሆነ እንመለከታለን። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍም ደግሞ ሌላ የእርሱን ስያሜዎች ይነግረናል። ራእይ 12፥ 9 ላይ "ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።" የሚል እናነባለን። እንግዲህ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመርያው መጽሐፍ አንስቶ እስከመጨረሻው መጽሐፍ ድረስ ሰይጣን ለእግዚአብሔር እና ለሰው ጠላት እንደሆነ ግልጽ ነው። እንደ ዮሐንስ 8፥ 44 ትምህርት ዲያብሎስ ኃሰተኛና ነፍሰ ገዳይ ነው። ደግሞም አታላይ፣ ፈታኝ እና ርኩስ ነው። ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ የሚመጣ ሌባው ተብሎም ተገልጧል (ዮሐንስ 10፥ 10))። ከሌሎች ሁሉ ይልቅ እርኩስና ክፉ መልአክ ነው። ዲያብሎስና አፖልዮን (አጥፊ) ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚታወቁ በርካታ ሌሎች ባህርዩን የሚገልጡ ስያሜዎች አሉት፣ እባብ ተብሎ እንደተጠራ ሁሉ የሚውጠውን ፈልጎ የሚያገሳ አንበሳ፣ ዘንዶው ተብሎም ተጠርቷል (ራእይ 12፥ 9፤ 20፥ 2፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፥ 8)። 


በእግረ መንገድ የአዳም አሟሟት፤ ዘፍጥረት 2፥ 16-17 "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።" ይላል እዚህ ላይ አዳም የተከለከለውን ዛፍ ፍሬ በላ፣ ነገር ግን እንደ ዘፍጥረት 5፥ 5 ከሆነ አዳም ፍሬዋን ከበላና ከእግዚአብሔር ገነት ከወጣ በኋላ በምድር ላይ የኖረው አጠቃላይ እድሜ 930 አመታትን ነው፣ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? 


ከቅዱሳት መጻህፍት እንደምናውቀው አዳም በዚያች ፍሬዋን በበላባት ቀን አካላዊውን ሞት አልሞተም። አዳም ያንን የተከለከለ ዛፍ ፍሬ ፈጽሞ ባይበላም እንኳ አካላዊውን የሥጋ ሞት ይሞት እንደ ነበር ታያላችሁ? አዎ መሞቱ አይቀርም ነበር፤ የተቀየረው ግን የአሟሟቱ ሁኔታ ነበር። አካላዊውን ሞት በሥጋው እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ በገነት ውስጥ በእግዚአብሔር ሀልዎት ፊት ከመሆን ይልቅ፣ አዳም አካላዊውን የሥጋ ምት እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ ከእግዚአብሔር ሀልዎት የተነጠለ ሆኖ ኖረ። ከእግዚአብሔር ጋር ሆኖ በሚሞትበት ጊዜ ወደ ሕይወት ከመድረስ ይልቅ ያለእግዚአብሔር በመሞት የከፋውን ጥፋት መንፈሳዊውን ሞት ሞተ። የአዳም ኃጢአት የመንፈሳዊው ሞት ሰበብ ነው። አዳም ሲፈጠር ያለኃጢአት ወይም ያለ ሞት ነበር ማለት በህይወት ከእግዚአብሔር ጋር በሞትም ከእግዚአብሔር ጋር ነበር ማለት ነው። ለአዳም ሕይወቱ እግዚአብሔር ነው እንጂ በምድር ላይ መኖሩ አይደለም፤ አዳም እግዚአብሔርን ባጣበት ቀን ሞተ። ከዚያ በኋላ በምድር ላይ የኖረው ኑሮ ሞቶ የኖረውና ሞቶ የሞተው ሞት ነው። ይህም ማለት አዳም ኃጢአትን ሲያደርግ ወይም ሲሞት በሕይወት ያለእግዚአብሔር በሞትም ያለእግዚአብሔር ሆነ ማለት ነው። ለአዳም በሕይወት መኖር ማለት ሳይሞቱ መኖር ማለት ሳይሆን በሕይወትም ሆነ በሞት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ማለት ነውና። አዳም እግዚአብሔርን በማጣት ከእግዚአብሔር ጋር መኖርንና መሞትን አጣ፣ ስለዚህም አዳም ከ930 አመታት እድሜ በኋላ ያለእግዚአብሔር ኖሮ ያለእግዚአብሔር ሊሞት በዚያች የቀን ጎደሎ በሆነች አሳዛኝ ቀን አሰቃቂውን መንፈሳዊ ሞት ሞተ። "ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ" (1ቆሮ 15፥ 22) እንደተባለ አዳም ያወረሰን ያለእግዚአብሔር ኖሮ ያለእግዚአብሔር መሞትን ነው። እንደ ኤፌሶን 2፥ 1 ከሆነ ሙታንነት የበደለኝነትና የኃጢአተኝነት ውጤት ነው፣ አለመታዘዝ ይኸውም የአዳም አለመታዘዝ የእኛም የልጆቹ አለመታዘዝ ሲሆን (ሮሜ 5፥ 19)፣ አኗኗራችንን እና አሟሟታችንን "በማይታዘዙ ልጆች ላይ ለሚሰራው መንፈስ አለቃ በአየር ላይም ሥልጣን ላለው አለቃ ፈቃድ" አድርጎታል።


የሰይጣን መቀጥቀጥ


በእባቡ ላይ የተነገረውን የመቀጥቀጥ ፍርድ በዘፍጥረት 3፥ 15 ላይ ሲናገር "በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።" የሚል ተስፋ እናነባለን። የሰይጣን መቀጥቀጥ፣ ይህ የሆነው መቼ ነበር? በአዲስ ኪዳን ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በሞቱና በትንሳኤው ሰይጣንን ድል ነስቶት የነበረው ኢየሱስም "የአዳም ልጅ፣ የእግዚአብሔር ልጅ" (ሉቃስ 3፥ 38) "ኋለኛውኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ" ተብሎ ተጠርቷል። ቅዱሱ መጽሐፍ ይህንን ይደግፋልን? አዎ! አሜን ነው! 


ጌታ ኢየሱስ ከመስቀል ሞቱ አስቀድሞ ሲናገር፣ "የዚህ ዓለም (ዘመን) ፍርድ ደርሷል፣ አሁን የዚህ ዓለም (ዘመን) ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፣ /ወይም  ይፈረድበታል/" ማለቱን አስታውሱ (ዮሐንስ 12፥ 31 ፤ 16፥ 11)፤ ይኸውም ተሸንፏል፣ አልቆለታል ማለት ነው።  እንደ አዲስ ኪዳን ትምህርት፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቱ እና ከሙታን ተለይቶ በመነሳቱ ይህንን ታላቅ የድል ተስፋ ለአማኞች ያጎናጸፈን መሆኑ እሙን ነው፤ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው ደግሞ ያንን ታላቅ ድል በመጨረሻው መደምደሚያና በፍጻሜው ከፍታ ላይ ሙላት ሰጥቶ እና ገልጦ አቀዳጅቶናል። ድሉም ያለ ዳግመኛ ምጽዓቱ ሙላትና ፍጻሜ እንደማይኖረው ግልጽ ነው። ከአሮጌው የብሉይ ኪዳን ዘመን ወደ አዲሱ የቃል ኪዳን ዘመን የተደረገው ያ የመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን የሽግግር ጊዜ፣ ልክ እንደ ጥንታዊቲቱ እስራኤል የ40 ዓመቱ የምድረ በዳው ጉዞ አይነት፣ ከመስቀል አንስቶ የዳግመኛ ምጽዓቱ ፓሮውዥያ እስከሆነበት 70 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የሽግግር ጊዜ ይሸፍናል (ዕብራውያን 8፥ 13 ፤ 9፥ 8)። የብሉይ ኪዳን እስራኤል በፋሲካው ደም ከግብጽ ባርነት አርነት ወጥቶ ከ40 አመታት የምድረ በዳ ጉዞ በኋላ የተስፋይቱን ምድር እንደወረሰ፤ እንዲሁ በመስቀል ላይ በታረደው በግ ደም ቤዛነቱን ያገኘው የአዲሱ ኪዳን ቅዱስ ህዝብ ከበአለ ሃምሳ ጀምሮ በሚቆጠር ከሌላ የ40 አመታት የስደትና የመከራ ጉዞ በኋላ በዳግመኛ ምጽአቱ የተስፋ ቃሉን ፍጻሜና ሙላት ለማግኘት እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ጌታን እየጠበቀ በመከራ መታገስ ነበረበት። 


ሐዋርያው ጳውሎስም በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፥ 4 "የዚህ አለም /ዘመን/ አምላክ" ስለሆነው "አይን አሳዋሪ" ይናገራል፣ እዚህም ላይ "ይህ አለም" የተባለው ዘመኑን ማለት እንጂ ተዳሳሹን ግዑዝ አለም ማለት እንዳልሆነ ልብ አድርጉ። በ“ዘመን” መጨረሻ፣ ይኸውም በማቴዎስ 24፥ 3 በተጠቀሰው በብሉይ ኪዳን ዘመን ማብቂያ፣ ሰይጣን ከገዥነቱ ስልጣን ወርዶ፣ ሉተር እንደሚያስተምረው፣ ያኔ ገና የተሸነፈ ጠላት ሆኗል፡፡  እንደ እግዚአብሔር ፕሮግራም ከላይ ሆኖ በአየሩ ላይ ይገዛ የነበረው አለቃ እርሱ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ከሚገዛበት ከሰማይ (ኤፌሶን 2፥ 2)፣ ከገዥነቱ ሥልጣንና ከከፍታው "እንደ መብረቅ" መውደቅ ነበረበት (ሉቃስ 10፥ 18) የአወዳደቁ ሁኔታ ግን  ያኔ በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ሂደቱ ገና ጅምር ነበር፣ በዳግመኛ ምጽአቱም ፈጽሞ ተሸንፎ ከኢየሱስ እግሮች በታች መቀጥቀጥ እና መገዛትም ይገባው ነበርና (ሮሜ 16፥ 20 - ዘፍጥረት 15፥ 15 ፤ ራእይ 2፥ 26፣ 27 ተመልከት)፣ እግሮች የተባሉትም የአካሉ ክፍል የሆኑት ሁሉ ናቸው፡፡ 


ዲያብሎስና ክፋት ተወግዷል


ጌታ ኢየሱስ ስለፓሮውዥያው ሲናገር "የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥" ማርቆስ 13 ፥40 ብሏል። ታዲያ ሰይጣን የታሰረ ከሆነና በእሳት ባህር ውስጥ ከተጣለ፣ ገና አሁንም እኩይ ሁሉ፣ ኃጢአትና ክፋት በዚህች ምድር ላይ የሚኖረው ለምንድን ነው? ሲሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ። ይህም ጥያቄአቸው በተለይ ትንቢት ሁሉ ተፈጽሞአል ብለን አቋም ለያዝንና በተፈጸመ ወንጌል ለምናምን ሰዎች የማያፈናፍን አፋጣጭ ተግዳሮት እንደሚሆንብን ይመስላቸዋል። እውነታው ግን እርሱ አይደለም። ለተዳሳሹና ለቁሳዊው በእጅጉ በተጋለጠውና "ሊተራሊስት" በሆነው በዘመናዊው ክርስትና ዘንድ በስፋት ታዋቂ የሆነው አስተሳሰብ ሰይጣን አንድ ጊዜ ከተፈረደበት፣ እንዱሁም ስለ ዓለም ፍፃሜ የሚናገሩ ትንቢቶች በሙሉ ፍጻሜአቸውን ካገኙ በኋላ፣ ታላቁና ቀንደኛው ፈታኝ የክፋት ኃይል ፈጽሞ የማይኖር በመሆኑ ምንም ዓይነት ክፋትና ኃጢአት በዓለም ላይ አይኖርም የሚል ነው። ይህ ነው የተለመደው አስተሳሰብና የብዙዎች እምነት።


ከባልንጀሮቼ አንዱ በአንድ ወቅት አብረን በተቀመጥንበት የካፌ በረንዳ ንፋስ ያስነሳው የመንገድ ላይ አቧራ ድንገት በላያችን ላይ ቢሞጀር፤ የተበሳጨው ጓደኛዬ ወደ እኔ ዘወር ብሎ፣ "ትንቢት ሁሉ ተፈጽሞአል፣ ጌታም መጥቶአል፣ ሰይጣንም ተፈርዶበታል፣ እኛ ክርስቲያኖችም አሁን ያለነው በአዲሱ ሰማይና ምድር ባዲሲቱ ኢየሩሳሌም ነው የምትለው ይሄ ትምህርትህ አሁን የምንጠጣውን ይህን አቧራ እንዴት ያየዋል?" ሲል እየቀለደ እንደጠየቀኝ አስታውሳለሁ። "የጌታ ምጽአት ንፋስ የሚያነሳውን የምድርን አቧራ እንደሚያስቀር ከቅዱስ ቃሉ ማንበቤን አላስታውስም፤ አልተጻፈማ"፤ ስል እኔም መልሼለታለሁ። 


በዚህ ተዳሳሽ አለም ክፋትና ክፉ ፍጻሜውን አግኝቶ ሁሉ መልካም ሆኖ ካላየን፣ እሳዳጅና ተሳዳጅ፣ ገዳይና ሟች፣ አጥፊና ጠፊ የሌለበት፣ እኩይ አልባ የሰላም አለም ተቋቁሞ ካላየን አናምንም የሚሉኝ፣ በማየት የሚያምኑ እጅግም ከማከብራቸው መካከል የዋሃን ሞልተዋል። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይቶ መንፈስ በሚናገረው ቃል ያንን መተርጎምና መረዳት ግን የምንኖርበት መንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰጥ "መሰረተ ትምህርት" ነው። አለዚያ ዱባና ቅል ለየቅል ሆነን ሳንመረቅ እንቀራለን። በግሌ እንደ ፕሪንተሪስቶች ሁሉ የመጨረሻው ዘመን ትንቢቶች በሙሉ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ተፈፅመዋል ብዬ አምናለሁ፤ ነገር ግን አሁንም ድረስ ከአዲሱ ሰማይና ምድር በቀር፣ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ቅድስት ሆና ለባልዋ እንደተሸለመችም ሙሽራ ሆና ከወረደችው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በቀር፣ ከመንግስቱ በቀር፣ ኃጢአት ከመንግስቱ ውጭ ተብሎ በተጠራው በዚህ ተዳሳሽ አለም በምድር ላይ አሁንም አለ፤ ይኖራልም ብዬ ደግሞ አምናለሁ። "ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።" (ራእይ 22፥ 15)።


ክርስቲያኖች ሆይ ልብ አድርጉ፣ በውስጥ ያለው በውጭ ካለው ይለያል። በውስጥ ያለው፣ "የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት" (ሮሜ 14፥ 17) ተብሎ እንደተጻፈ፣ የውስጡ ተፈጥሮና ባህርይ ፈጽሞ ይለያል። ውስጡ እጅግ እንደሚያምርና እንደሚማርክ ውበቱንና ግርማውን አጥርተን እንይ። በውስጥ ያለው ጉልበት ኃያል ነው፤ "የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና" (1ቆሮ 4፥ 20)። በእግዚአብሔር መንግስት ምስጢር እውቀት እያደግን፣ በውስጥ የተገለጠው የብርሃን ግርማ ካልማረከን በቀር ውጭውን የሸፈነው ድቅድቅ ጨለማ እያስፈራራን እንኖራለን። በወንጌል አምነናል ከሚሉት መካከል ብዙዎች ሰይጣንና ክፋቱን እየፈሩ በውጭው የጨለማ ግርማ ሲደነብሩ ይስተዋላሉ። በእግዚአብሔር ቤት እየኖሩ የውስጡን ብርሃን ማክበር ተስኗቸው በውጭው ጨለማ የተወሰዱ ፈሪዎችና ድንጉጦች "ፈሪ ልብ ላላቸው፦ እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው።" (ኢሳይያስ 35፥ 4) የሚል ቃል ሊሰበክላቸው ይገባል። ካልሆነ ግን ትእዛዙን ስሙ "ማንም ፈሪና ድንጉጥ ሰው ቢሆን እርሱ ፈርቶ የወንድሞቹን ልብ ደግሞ እንዳያስፈራ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ" (ዘዳግም 20፥ 8)። እንግዲህ በብርሃን ተከቦ በቤት ውስጥ እየኖሩ ከቤት ውጭ ያለውን ጥላና ጨለማ እየፈሩ መጨነቅና መደንገጥ ብዙዎቻችን በህጻንነት እድሜአችን ያሳለፍነው ልምምድ ነው። ስናድግ ግን ያንን ትተናል። ስለዚህ እንደግ እንጂ ወደፊት ህጻናት መሆን አይገባንም።


ይህንን ደግሞ ተመልከቱ፣ "ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።" (1ቆሮ 6፥9-10) እንደተባለ፣ የእግዚአብሔር መንግስት ፍጹም ንጹህ ነው። የእግዚአብሔር መንግስት የስጋና ደም መንግስት አይደለም፤ ጳውሎስ፣ "ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም" (1ቆሮ 15፥ 50) ብሎአልና፤ አሁን የምንኖርበትን የእግዚአብሔርን መንግስት በስጋና በደም አይገመትም።


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእንክርዳዱን ምሳሌ ተርጉሞ ባስተማረበት በማርቆስ 13 ያለውን ትምህርት ካጤነው፣ "የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥" (ማርቆስ 13 ፥40) ሲል፣ ክፋት የሚለቀመው "ከመንግሥቱ" ነው እንጂ ከአለም ላይ አለመሆኑን እናስተውላለን። መንግሥቱ ደግሞ ከዚህ አለም አይደለችም። በአለም ላይ ግን ክፋትም ደግነትም፣ ጥፋትም ልማትም አለ ይኖራልም። አስተውሉ አለም ከክፋት አይጸዳም። ክርስቶስ በዙፋኑ ሆኖ የነገሰባትና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ለዘላለም የሚገዛባት፣ ጽድቅና ቅድስና የሰፈነባት፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ኃሴትና ደስታ የሞላባት መንግስቱ፣ እዚህ ተዳሳሹ አለም ላይ ካለ ከየትኛውም ሥጋዊና ነባራዊ የሰው ስርአት ጋር እናስተያያት ዘንድ ግን የሚመጥናትና የሚገልጣት ምንም አምሳያ የላትም። የምድር ላይ ኃያላን በመንግስታቸው የለበሱትን ካባ እና በራሳቸው ላይ የደፉትን ዘውድ፣ የተቀመጡበትን ዙፋንና በፖለቲካ አስተዳደራቸው የሚሰጡትን ፍርድና ዳኝነት ስንራቀቅ ውለን ብናድርበት ክርስቶስ በመንግስቱ ካለው ግርማና ክብር ጋር ሊጠጋጋ ቀርቶ ምሳሌ ለመሆን እንኳ አይበቃም። ተመልከቱ፦


"በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።" (ራእይ 12፥ 7-10)


"በሰማይ" በሆነው ሰልፍ ድል የተመታው ዘንዶ "በሰማይ" ስፍራ የለውም፤ በክርስቶስና በቅዱሳኑ ሰማይ ዕድል ፈንታ መብትና መታሰቢያ የለውም። "ወደ ምድር" ወደማያምነው አለም ተጥሎአል እንጂ፣ በክርስቶስ ሆነን በምንኖርበት በሰማያችን ላይ ቦታ የለውም። የክርስቶስና የክርስቲያኖች ሰማይ ንጹህ ነው፣ በዚህ ሰማይ ስትኖሩ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሰይጣንን ድል ነስቶታልና፣ ስለ ዘንዶው ውጊያና ስለ ከሳሽነቱ ስጋት አይገባችሁም። ድላችሁንም በእምነት ትይዛላችሁ እንጂ በማየትና በስሜት አትፈልጉትም። ሰይጣን ታስሮአል፣ ወደ ምድርም ተጥሎአል፤ ሰማይም ከክፉውና ከክፋት ነጻ ነው። ክፉውና ክፋት ፍጻሜውን ያገኘው በሰማይ ነው። "እንቅፋት ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉ" ሁሉ ከመንግስቱ ተለቅመው ተጠርገዋል። አስተውሉ፣ ዘንዶው ተሸንፎ የተጣለው ወደ ምድር ነው፣ ከመንግስቱ ውጭ።


ከተገለጠው ድል መንሳትና ከዘንዶው መጣል የተነሳ የተነገረውን የሰማይ ድምጽ ስሙ፣ ይህ ድምጽ ሰማይ ብቻ የሚሰማውና የሚረዳው ድምጽ ነው፦ " አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥" ይህ የሆነው ከጊዜ አንጻር እንጂ ከጆግራፊ አንጻር አይደለም፤ ከጊዜ አንጻር "አሁን" ነው፣ ከአድራሻ አንጻር ደግሞ "በሰማያዊው ስፍራ" ነው። "በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ" (ኤፌ 1፥3)። ይህም ስፍራ የእግዚአብሔር ቀኝ መንፈሳዊው የክርስቶስ ግዛት ነው፣ መዳንን እንደተቀበለ አማኝም መቀመጫችን በሰማይ ነው፤ "በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን" (ኤፌ 2፥ 7)። የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ባለማመን ከዚህ ብርሃን እንዳትጎድሉ እጸልያለሁ።


ሰይጣን ገደብ ተጥሎበት እንዲሰራ የተፈረደበት ነው። 


አስቀድመን ሰይጣን በዘመኑ ላይ የነበረውን አገዛዝ እንመልከት፤ በሽግግሩ ወቅት ላይ አገዛዙ በሂደት እየተገለበጠና እየተለወጠ ነበር። በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎትና በጠቅላላው በዚያ የሽግግር ዘመን የወንጌል አገልግሎት አንዱና ዋናው ተጽዕኖም ይኸንንው ሂደት ማሳለጥ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 17፥ 6)። ያኔም በረጅሙ የብሉይ ኪዳን ዘመን ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ ብዙ ሰዎች በአጋንንት እስራት ተይዘው በጌታና እርሱ በላካቸው አገልጋዮቹ ነጻ ይወጡ ነበር። በራእይ 20፥ 7 ላይ ለጥቂት ጊዜ ከእስራቱ እንዲፈታ በተባለለት አኳኋን፣ ሰይጣን በቄሳር ኔሮ ዙፋን ላይ ሆኖ የመጨረሻውን የመልሶ ማጥቃት በቅዱሳን ላይ አድርሶ ነበር። ዲያብሎስ ራሱ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ያውቅ ስለነበር፣ ያኔ ይሰራ የነበረው፣ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ፣ በታላቅ ቁጣ ነበር (ራእይ 12፥ 12፤ 1 ጴጥሮስ 5፥ 8-9)፤ ከዚህም የተነሳ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያን መከራዋ ታላቅና አለም አቀፋዊ ነበር። በሕጉ ስርአት በኩል ጉልበታም ሆኖ የሚሰራው የኃጢአት ኃይል ዋና የማዘዣ ጣቢያው የሚገኘውም ደግሞ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደሱ ነበር፣ "የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው" (1 ቆሮንቶስ 15፥ 56) ተብሏልና። የዚያ የአሮጌው ዘመን ስርዓት የሰይጣንን ክስ እና የውንጀላውን ስድብ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደታች እያወረደ  የሞትን እና የኩነኔን አገልግሎት ያስፈጽም ነበር። ቤተክርስቲያንም ከብዷት ስትቃትት የኖረችው በዚህ ወቅት ነበር። ከዚያም በኋላ ግን በ70 ዓ.ም ላይ ሰይጣን በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት "ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።" (ራእይ 20፥ 10) በሚለው ቃል ዘላለማዊ ሽንፈቱንና  ፍርዱን አገኝቷል። 


በማቴዎስ 25፥ 41 ላይ ያለውንና የዘላለም እሳት ለሰይጣን እና ለመላእክቱ የተዘጋጀ መሆኑን የሚናገረውን ቃል ተመልከቱ። ሰይጣን አጋንንት የተባሉት የወደቁ መላእክት ሁሉ አለቃ ነው። የሳቱትን ሁሉ ያሳሳተ፣ የተሸነፈም የክርስቶስ ጠላት ነው። በ70 ዓ.ም ላይ በሆነው ፍርድም በዲን ወደሚቃጠል የእሳት ባህር ተጥሏል፣ በዚያም ከዘላለም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሰቃያል፣ ይህም የአሁኑ የመንግስት ዘመን እውነታ ነው። ድኝ ከሰልፈር ጋር ተመሳሳይ ነገር ነው። ድኝ የሚሰነፍጥና የሚተፈንግ የሚሸታቸውን ሁሉ በከፋ ሁኔታ የሚረብሽ ጠረን ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም የእሳቱን መቀጣጠል እንዳይጠፋ አድርጎ ጠብቆ የሚያቆይ ነው። እጅጉን እየተቃጠለ ብረቶችን ሁሉ የሚያቀልጥ እሳት ነው። አሁን ባለው ዲስፔንሴሽን ሰይጣን የተቀበለው የመጨረሻ ፍርዱ ይሄ ነው። ይሄ ግን ፈጽሞ እስከወዲያኛው አጥፍቶታል ወይም ወደ አለመኖር ቀይሮታል ማለት አይደለም። ሰይጣን የለም የሚል ትምህርትም የክርስትና ትምህርት አይደለም። ይልቁን ግን ሁልጊዜ እንደሆነውና እንደነበረው ያው የተፈረደበትና የተጣለ፣ እንደፈለገ የሚጠመዝዘው፣ በቁጥጥሩ ስር ያለ፣ ንስሃን እምቢ ብለው በአመጻቸው የሚገፉ አመጸኞችን በመረጡት የጥፋት መንገድ ላይ እንዲያስታቸው በእርሱ የሚላክ የጥፋት መልእክተኛና የእግዚአብሔር  ዲያብሎስ ሆኖ ይኖራል፡፡ ምን ማለት ነው? 


ሰይጣን፣ ተጥሎ በሚገኝበት የእሳት ባህር፣ ልክ እንደ መንጋ አለቃ አክት እያደረገ፣ ከእርኩሳን መላእክቱ ጋር ይሰራል፤ ያም ስፍራ ዘላለማዊ የማዘዣ ጣቢያው ነው። የእርሱ ውሸቶችና ማታለያዎች ሁሉ እድል የሚኖራቸው ለእርሱ ተጽእኖ ራሳቸውን ክፍት ባደረጉ፣ በወንጌል በማያምኑና ባልዳኑ ኃጢአተኞች ላይ ነው። እነዚህም ያልዳኑና ያላመኑ ኃጢአተኞች በ70 ዓ.ም በተፈጸመው ፍርድ ከዘላለም ከእርሱ ጋር ለእርሱ የተመደቡና ተላልፈው የተሰጡ ናቸው። እነርሱም የሚያደርጉት ማናቸውም ነገር፣ ሃይማኖትም ቢሆን እንኳ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ኃጢአት ነው። መንፈስ ቅዱስ የሌላቸው ስለሆኑ የትኛውም ጥረታቸው በእግዚአብሔር ፊት እንደ ጽድቅ አይታይም። በሚኖሩት ያለማመንና የአመጽ ኑሮ የሰይጣንን ሃሳብ ለማገልገል ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ለዚህም የተመደቡ ናቸው። ከዚያ ፍርድ ማምለጥ የሚቻለው በክርስቶስ ብቻ ነው። ሰይጣን በወንጌል አምነው ክርስቲያኖች በሆኑ በማናቸውም ላይ ቢሆን አንዳች ሥልጣንና ኃይል የለውም። የትኛውም ኃጢአታችን እና ውድቀታችን ከጌታችንና ከመድሐኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ስራ የተነሳ ፈጽሞ ለዘለአለም  ይቅር ተብሏል። በሰይጣን ተጽእኖ ውስጥ ባይሆኑም እንኳ ከሥጋ ድካም የተነሳ ሰዎች ገና ኃጢአትን ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን በወንጌሉ ባመንን በእኛ እና ባላመኑት መካከል ያለው ልዩነት ኃጢአታችን በክርስቶስ ይቅር የተባለ መሆኑ ነው። በዚህ ነባራዊ አለም ያሉ ሰዎች ሁሉ ምድባቸው ኃጢአታቸው የተሰረየላቸውና ኃጢአታቸው የተያዘባቸው በሚል ከሁሉት በአንዱ ነው። ለኛ ላመንን በክርስቶስ የተሰጠን የኃጢአት ይቅርታ ዘላለማዊው አለኝታችን ነው። 


ክርስቲያኖች በጠንካራ ምኞቶቻቸው ላይ አጥብቆ የመስራት ትግል አለባቸው። ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያላቸውን ዲቮሽን ለመጠበቅ ሳያቋርጡ መጸለይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት፣ እና በእግዚአብሔር እና በሰዎች ሁሉ ፊት በእምነት መኖር ያስፈልጋቸዋል። ይህም ፈቃዳቸውን በእግዚአብሔር ፈቃድ ስር እያደረጉ ጠንካራ ምኞቶቻቸውን ጌታን ደስ ለማሰኘት እንዲጠቁሙቡት ያስችላቸዋል። ነገር ግን ሰይጣን በእሳት ባሕር ውስጥ እንደተጣለ እና በአሮጌው ኪዳን ዘመን እንደነበረው አጋንንቱ መዳን ያገኘነውን እኛን መውረስ እንደማይችሉ እርግጠኞች ደግሞ እንሁን፤ ይህ ግን በፍጥረታዊው አዕምሮአችንና በአስተሳሰባችን ውስጥ ከሥጋ ድካም የተነሳ የመሳለብና የመወሰድ ፈተና ፈጽሞ የለብንም ማለት ደግሞ አይደለም። በዚህ ፍጥረታዊ አለም በሥጋዊው ተፈጥሮአችን በምድር ላይ ሳለን በዚህ ትግል ውስጥ እናልፋለን። ለዚያም ነው እንደ ክርስቲያን የጥሞናን ሕይወት ጠብቀን በጸሎትና በእግዚአብሔር ቃል እየተጋን ከእግዚአብሔር ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረትና መጠበቅ አለብን ስንል የምንመክረው።


ስለሰይጣን የተነዙ መሰረታዊ ውሸቶች


ዘፍጥረት 3፥ 15 ላይ "በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።" ለሚለው የተስፋ ቃል በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ፍጻሜ የሚሰጠው "የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል" ሲል ሮሜ 16፥ 20 ላይ የተጻፈው ቃል መሆኑን እናስተውል። ልክ እንዲሁ ሉቃስ 10፥ 17-18፤ ዮሐንስ 12፥ 31፤ ቆላስይስ 1፥ 13፤ 2፥ 13-15፤ ዕብራውያን 2፥ 14፤ እንዲሁም 1ኛ ዮሐንስ 3፥ 8 ተመሳሳዩን ያስተምራሉ። እነዚህ ሰባት የሚሆኑ የቅዱሳት መጻህፍት ማጣቀሻዎች ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ አጽንዖት ይሰጣሉ። እንግዲህ እግዚአብሔርን በቃሉ ልናምነውና ቃሉን እንደተናገረው እንደተጻፈም ሳንጨምርና ሳንቀንስ እንዲሁ ልንቀበለው እንጂ ሃሰትን ማመንና መመስከር አይገባንም፤ በመጀመርያ ከቃሉ ምክር ተምረን "ሰይጣን በአሁን ጊዜ ይህንን አለም እየገዛ ነው" የሚልን ይህን የኃሰት ትምህርትና አዋጅ ማቆም አለብን። አሁን እየገዛ ያለው ንጉሰ ነገስት ኢየሱስ ጌታችን ነው። በሰማይም በምድርም ሁሉ ሥልጣን የእርሱ ነው (ማቴዎስ 28፥ 18)። ከፍ ሲል የጠቀስኳቸው "የዚህ አለም ገዢ" እና "የዚህ አለም አምላክ" የተሰኙት የሰይጣን መጠርያዎች (ዮሐንስ 12፥ 31፤ 14፥ 30፤ 16፥ 11፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፥ 4) ሁሉም የሚያመለክቱት በ70 ዓ.ም በተፈጸመው የጌታ ዳግም ምጽአት ሳይፈረድበት አስቀድሞ የነበረውን ሚና ብቻ ነው እንጂ የአሁኑን የመንግስት ዘመን ሁኔታ አያሳዩም።


ሉሲፈርን አስመልክቶ ሲዋሽ የኖረውን ሁለተኛውንና ሌላውን ውሸት ደግሞ እንመልከት። ሉሲፈር ማለት "የአጥቢያ ኮከብ" ማለት ነው። አስቀድመን ኢሳይያስ 14፥ 12 ላይ "አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ!" የሚለውን ተመልከቱ። ከቁጥር 4 እንደምንረዳው ይህ ትንቢት የባቢሎን ንጉስ የነበረው ናቡከደነፆርን የሚመለከት ነው። በምሳሌና በትዕምርታዊ ገለጻ ለናቡከደነጾር አወዳደቅ የተነገረውን ቃል ወስዶ ሰይጣንን ለማለት ተፈልጎ ነው የሚል ድርቅና የቃሉን መንፈስና አውድ አለማወቅ ነው። ዳንኤል 5፥ 20-21 ያለውም "ልቡ ግን በታበየ በኵራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ፥ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፥ ክብሩም ተለየው። ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ የሚወድደውንም እንዲሾምበት እስኪያውቅ ድረስ ከሰው ልጆች ተይለቶ ተሰደደ፥ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፥ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።" ሲል ይህንኑ ያጸናልናል። ልብ አድርጉ፣ ሰይጣን ፈጽሞ ሉሲፈር ተብሎ ተጠርቶ አያውቅም። 'ሰይጣን ይህንን አለም እየገዛ ነው' ከሚለው ቀደዳ ቀጥሎ፣  'ሉሲፈር የሰይጣን ስም ነው' የሚለውን ይህን ቀደዳ፣ ውሸት ቁጥር ሁለት ልንለው እንችላለን።


ልክ እንደዚሁ በርካቶች ሕዝቅኤል 28፥ 13 ላይ ያለውንና "በእግዚአብሔር ገነት በዔድን ነበርህ፤ የከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅ፥ ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር።" በሚል የተነገረውን አንብበው፣ በተለይ ከዚህ አይነቱ ገለጻ የተነሳ ይህ ንግግር እባቡን ያመለክታል ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ግን የአመስጥሮ (allegorization) ስህተት ነው። ምንባቡን በሙሉ አውዱን ጠብቆ በጥንቃቄ የሚያነብ ሰው ግን ከቁጥር 2 እና 12 ላይ ተመስርቶ ትንቢቱ በጢሮስ ገዥ ላይ የተነገረ መሆኑን ያስተውላል። ከዚህም በላይ ከንግዱ ብዛት የተነሳ ባከማቸው ሀብት ልቡ እንደታበየ (ቁጥር 5 እና 16) ተነግሮናል። ለጢሮስ ገዢ የተነገረውን "አይ ሰይጣንን ማለቱ ነው" ብሎ መገገም ያልተጻፈ ማንበብ ነው። ይልቁንም ይህ ምንባብ ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ያደርገው በነበረው ጉዞው ላይ ያኔ ጴጥሮስን በገሰጸው ጊዜ "አንተ ሰይጣን" (ማርቆስ8፥ 33) ብሎ ከጠራበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። ተግሳጹ የተነገረው በቀጥታ ለደቀመዝሙሩ ሆኖ ሳለ፣ የለም ለሰይጣን ነው ብሎ መተርጎምም ሆነ በዚህ ክስተት ጴጥሮስን ማሰይጠን በትልቁ ስህተት ነው።


ዲያብሎስ ሉሲፈር ተብሎ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ አንድም ቦታ እንዳልተጠራ፣ ኢየሱስም ገና ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ድል እንደነሳው ይህንን እውነት አጥብቃችሁ ያዙ እንጂ ሀሰትን አትመኑ። ይልቁን ግን ትምህርት የማይወዱና በተሳሳተ ትርክት የተወሰዱ የሚበዙ የዘመናችን "አገልጋዮች" እና ምዕመናን አሁን እዚህ ላይ እዘረዝረው ዘንድ የሚያታክቱ ልበ ወለድ የሆኑ በርካታ ውሸቶችን በየመድረካቸው ሲያስተጋቡ፣ ጉባኤዎቻቸውም ሲያምኑ ይስተዋላል። የኛ ትውልድ ሕዝብ 'ማን መጥቶ ባሳሳተኝ' በሚል ረሃብ፣  ያለና የተጻፈውን ከማመን ይልቅ የሌለና ያልተጻፈ ለማመን ራሱን አሳልፎ የሰጠ ይመስለኛል።  ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ስመለስ፣ በርካቶች የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ 20፥ 1-4 እና 7-10 ያለውን ጠቅሰው እያነሱ ሰይጣን ወደፊት ይፈታ አይደለምን? ሲሉ ይጠይቃሉ። አዎ፣ ሰይጣን በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ተፈትቶ ተለቆ ነበር፣ ነገር ግን በዚህ የእኛ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ፈጽሞ ተፈትቶ አይለቀቅም። 


ልብ አድርጉ የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው በ65 አም ላይ ነው፣ የመጽሐፉም ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ70 አም ላይ ነው። ዳንኤል 8፥ 26 ላይ "የተነገረውም የማታውና የጥዋቱ ራእይ እውነተኛ ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ስለሚሆን ራእዩን ዝጋ።" የሚለውም ቃል በራእይ 22፥ 10 "ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።" በሚለው ቃል ፍጻሜውን አግኝቷል። የራእይ መጽሐፍ በአግባቡ አውዱን ጠብቆ እንዲተረጎም ከተፈለገ፣ የራእይ 1፥ 1 እና 3 ትክክለኛውን ጊዜ አመልካች የሆኑ ምንባባት፣ እንዲሁም ፈጥኖ፣ ቶሎ፣ የተሰኙት ቃላት በጥሬው ትርጉም መወሰድ አለባቸው። 


እኛ አሁን እየኖርን ያለነው ከሽግግሩ ዘመን ማዶ ባለው፣ አሮጌው ዘመን በተሻረበት እና በዳግመኛ ምጽአቱ በተጀመረው በዘላለማዊው ዘመን በአዲሱ ኪዳን ዘመን ውስጥ ነው፣ (ኢሳይያስ 9፥ 7 ፤ ዕብራውያን 13፥ 20)። ይህም ዘመን የመንግስት ዘመን ይባላል። ይኸውም አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ነው። በዚህ ክቡር ዘላለማዊ ኪዳን ስር አድረው ክርስቶስን የሚያከብሩት እነዚያ እርሱ የተቤዣቸው ሕዝቦቹ እና እያንዳንዳቸው ቅዱሳኑ ብቻ ናቸው (መዝሙር 2)፤ እነርሱም ብቻ ድል የነሱ እና የተባረኩ፣ ከፍ ከፍ ብለው በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር ያሉ እና ሥልጣንና ኃይል የተሰጣቸው ናቸው።  ከመጀመሪያው ምዕተ-ዓመት ጀምሮ ደግሞም ሁልጊዜ የማይበገሩ ኃያላን ሆነው በሰማያዊው ስፍራ ከክርስቶስ ጋር የነገሱ እና የሚገዙ ክርስቶስን የሚያከብሩ ሕዝቦች እነርሱ ብቻ ናቸው።  ክርስቶስንና የጽድቅ መንግስቱን የሚቃወሙ ማናቸውም የምድር ህዝቦች ተሰብረውና ተደምስሰው፣ እርሱ ከፍ ከፍ ባደረጋቸው፣ ክርስቶስንም ሊያከብሩ በተገባቸውና የእርሱን ጽድቅ በተሸከሙ ሕዝቦቹ እግር ስር ተጥለው ተረግጠዋል ፡፡ ክርስቶስ የዚህ የአዲሱ አለም /ዘመን ጌታና አምላክ ስለሆነ፣ ከኔሮ ዘመን በኋላ በቅዱሳኑ ላይ በዓለም ዙሪያ ግሎባል የሆነ ስደት ያልነበረው እና ደግሞም ከዚህ በኋላ በጭራሽ የማይኖረው ለዚህ ነው። ምክንያቱም የነገስታት ንጉስ እና የጌታዎች ጌታ የሆነው የቤተክርስቲያን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ረግጦ፣ ግዛትና መንግስትም ተሰጥቶት ለቅዱሳኑ ዘላለማዊ እረፍት በአባቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ የሚገዛ በመሆኑ ዘመኑ ተቀይሯል። በዚህ በተቀየረ ዘመን አሁንም በክፉ የተያዙትን የሚያስጥል የመዳን ቃል፣ እርሱም የተፈጸመው የክብር ወንጌል ይሰበካል። 


በመጨረሻም፣ ጉዳዩን ኮምጨጭ ብሎ ለመደምደም፣ በመጀመርያ ሰይጣን ፈጽሞ ሉሲፈር ተብሎ ተጠርቶ አያውቅም። በመጽሐፍ ቅዱስ ባልተጠራበትና ባልታወቀበት ስያሜ ሰይጣንን ማካበድም ሆነ ማሰይጠን ያልተማሩትንና የሚስቱትን ግራ ማጋባት ይሆናል። አስከትሎም፣ ሰይጣን በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከዘላለም እስከ ዘላለም 100 ፐርሰንት ፈጽሞ የተሸነፈ ነው። መንግስት በተሰጣቸው ዘንድ ዋጋ የለውም። ለአለምና ለዘላለም የነገስታት ሁሉ ንጉስ እና የጌቶች ሁሉ ጌታ ሆኖ ሁሉን ሊገዛ በእግዚአብሔር ዙፋን የተቀመጠው ገዢ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! ከእርሱ በቀር ሌላ የለም!! አሜንና አዎን እርሱ ነው።


ለተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማረጋገጫ፣ እንደ ማቴዎስ 24፥ 34 እና ሉቃስ 21፥ 22 ያሉ ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ በርካታ ምንባባት ላይ ተምስርቼ ያዘጋጀኋቸውን ተከታታይ ጽሁፎች በዚህ ማስፈንጠርያ    

http://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/24.html?m=1 ገብታችሁ በብሎገሬ ላይ ተመልከቱ። ስለ ታላቁ መከራ ሁለተኛ አጋማሽ እና ስለ መጨረሻው የአርማጌዶን ጦርነትም The War Of the Jews በተሰኘው የፍላቪየስ ጆሳፈስ መጽሐፍ የተተረከውን የታሪክ መዝገብ አገላብጡ። አይምሮ ያለው ሰው ከዚያ በኋላ እንደተለመደው ማሰብ ያቆማል።

(Gkr)


Monday, October 11, 2021

ሞት ድል በመነሳት ተውጧል

ሞት ድል በመነሣት ተውጧል 

በዚህች ጥፈት፣ ከዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው በፊት እና ከዚያ በኋላ ባለው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ፣ የሙታንንና የሕያዋንን መዳረሻ አስመልክቶ ግልጽ መሆን ያለባቸውን ጉዳዮች ላካፍላችሁ መልካም ሆኖ ታይቶኛል። በቃሉ መንገድ የምታስቡ ጥቂቶች ያይደላችሁ እና እምነታችሁን የምትጠይቁ በርካቶች እንደምትጠቀሙበት፣ እንደምትጽናኑበትና፣ እንደምትሞገቱበት አስባለሁ። መልካም ንባብ።  

"ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።…. ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል።" (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 50፣ 53-54)

፩. ሟች አባቶች ከፓሮውዥያው አስቀድሞ
1)ገና የእስራኤል ታሪክ ሳይጀመር በፊት፣ በነበረው ርዥም የአባቶች የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አማኞች ሁሉ፣ በበርካታ ጊዜያት ከተገለጡ ጥንታዊ ኪዳናት አንጓዎች ስር ተካፋይ የነበሩ ናቸው። ለምሳሌ፦ አዳማዊ ቃል ኪዳን፤ የኖህ ቃል ኪዳን፤ አብርሃማዊ ቃል ኪዳን፤ የሙሴ ቃል ኪዳን ወዘተ እያልን ልንጠቅሳቸው እንችላለን። ከአዳም እስከ አብርሃም ዘመን ያሉት ሁሉም የተመረጡ አማኞች ልዩ ልዩ የምድር ህዝቦች  ነበሩ፣ እስራኤል ዘሥጋ ያኔ ገና አልነበረም። ሟቾች የዚያን ዘመን አባቶች ሁሉ በተስፋ ሞተው በሚቀበሩበት ጊዜ ከሥጋቸው ተለይተው ያለ ተዳሳሹ አካልና፣ ደም፣ ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት ይሄዱ ወይም ይወሰዱና ይከማቹ የነበረው ሼዖል ወደተባለ ስፍራ (ወደሀደስ) ነበር። ተስፋቸውም በፍጻሜ ዘመን ላይ በሙታን ትንሳኤ ከዚያ ከተከማቹበት ሼዖል ወጥተው ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት ይገቡ ዘንድ ነበር። 

2)ከክርስቶስ የመስቀል ሞቱ አስቀድሞ፣ ማለትም ከአብርሃም እስከ ክርስቶስ ያሉ አባቶች አብዛኞቹ የተመረጡ አማኞች፣ ደግሞ በአመዛኙ ከአይሁድ ወገን የነበሩ ናቸው። ቃል ኪዳኑም ከአብርሃም ጋር ነበር፣ የቃል ኪዳኑ ህዝብ ዘሩም እስራኤል ነበር። ለእስራኤል ዘሥጋ የተሰጣቸው ኪዳንም ብሉይ ኪዳን ነው። እነርሱም በተስፋ በሚሞቱበት ጊዜ ከሥጋቸው ተለይተው ያለ ተዳሳሹ አካልና፣ ደም፣ ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት የሀደስ የእረፍትና የመጽናኛ ዞን ብለን ወደምንጠራው አብርሃምና አባቶች ሁሉ ወዳሉበት "ሀደስ ገነት" ወይም "የአብርሃም ዕቅፍ" ወደሚባለው ስፍራ ሄደው ከአባቶቻቸው ጋር ይከማቻሉ። በዚያም ክርስቶስ በእርገቱ ማርኮ፣ በዳግመኛ ምጽአቱ የሚቀበሉትን ትንሣኤ ሊጠባበቁ ወደሰማያዊው መቅደስ የደጁ አደባባይ ወዳለው ሥፍራ እስኪወስዳቸው ድረስ፣ ከዚያ የሼዖል እስራት ነጻ የሚያወጣቸውን  መሲሁ ኢየሱስን እየተጠባበቁ ይቆያሉ (ዮሐንስ 20፥ 17) 

3) ከመስቀል እና ከትንሣኤው አንስቶ  በ70 አ.ም ላይ እስከተፈጸመው ዳግመኛ ምጽአቱ ድረስ ባለው መካከኛ ጊዜ በነበረው የሽግግር ወቅት፣ እነዚያ ተፈጥሯዊውን ሞት በተስፋና በእምነት የሞቱ የሽግግሩ ዘመን አማኝ ደቀመዛሙርት፣ ክርስቶስ በእርገቱ፣ ሀደስ ከሆነው ገነት ጋር በምርኮ የወሰዳቸውና በአብርሃም ዕቅፍ የነበሩ የአሮጌው ኪዳን አማኞች ተሰብስበው ወደነበሩበት የጻድቃን መንፈሶች ማህበር  ሊቀላቀሉ ይወሰዱ ነበር። በዚያም በዳግመኛ ምጽአቱ የሚቀበሉትን ትንሣኤ እየተጠባበቁ ይቆያሉ። ይህንን ገነት የተባለ ስፍራ ከክርስቶስ እርገት በኋላ የምናገኘው፣ ሀደስ /ሲዖል በተባለ የቀድሞ መገኛው ሳይሆን ይልቁንም በሦስተኛው ሰማይ እንደሆነ አስተውሉ (2ቆሮንቶስ 12፥ 2-4)። ሲዖልንና መቃብርን ድል ነስቶ ከሃያላን ጋር ምርኮን የተካፈለው ክርስቶስ  በእርገቱ ይህንኛውን የሀደስ ዞን/ ገነትን ማርኮ በመውሰድ ወደ ሰማያዊው ስፍራ የደጁ አደባባይ አምጥቶታልና። በዚያም በዳግመኛ ምጽአቱ የሚገለጠውን የቤዛነታቸውን ቀን ይጠባበቁ ዘንድ አስቀድሞ በእርገቱ የሰበሰባቸውና ከዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው አስቀድሞ በተለያየ ምክንያት ተፈጥሯዊውን ሞት የሞቱ የጻድቃን መንፈሶች ሁሉ ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት ሆነው  ትንሣኤን እየተጠባበቁ ተከማችተዋል።

4) በተጨማሪም ለየት ባለ ሁኔታ የሽግግሩ ዘመን ሰማዕታትን ጨምሮ፣ በአይነታቸው ለየት ያሉ ጥቂት የማይባሉ የብሉይ ኪዳን ሰማዕታትም ሁሉ፣ ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት በሰማያዊው መቅደስ በቅድስተ ቅዱሳን የውጭው አደባባይ ደማቸውን በምድር ላይ ባፈሰሱ ገዳዮቻቸው ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድና በቀል እየጠየቁ በመሰዊያው ዙርያ ሆነው፣ ትንሣኤን ለማግኘት የክርስቶስን ፓሮዥያ እየተጠባበቁ ነበሩ። እነርሱም ከዳግመኛ ምጽአቱ አስቀድሞ የፍርዱንና የበቀሉን ቀን ለጥቂት ዘመን ታግሰው እንዲጠብቁ ነጩን መጎናጸፊያ የተቀበሉት ናቸው፤ ይኸውም "ጥቂት ዘመን" ጌታ እስኪመጣ ድረስ የነበረው የሽግግሩ ወቅት ሲሆን፣ በዚያ የሽሽግር ወቅት ዮሐንስ ራእዩን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ ገና አዳዲስ የሰማዕታት ድል ነሺዎች እየተገደሉ በቁጥራቸው ላይ ሊጨመሩ ያለማቋረጥ ወደዚያ ስፍራ እየገቡ ነበር፤ ስለዚህ  ብዛታቸው ሊቆጠር የማይችል ነበር (ራእይ 4፥ 4፤ 7፥ 9፤ 7፥ 13-14)። 

¶ እንግዲህ ከላይ በተለያየ መልኩ ያየናቸው ሁሉም አይነት አማኝ ሟቾች፣ ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት ሆነው በዳግመኛ ምጽአቱ ትንሳኤን የሚቀበሉበትን የቤዛነታቸውን ቀን እስከ 70 አ.ም ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። 

# የማያምኑ ሟቾች እድላቸው፦
ከ70 አ.ም በፊት በነበረው የዘመን ምድብ የሞቱ የማያምኑ ሁሉ ግን ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት በሲኦል የስቃይ ስፍራ ሆነው በ70 አ.ም የሚገለጠውን የመጨረሻውን የክርስቶስን ፍርድ ይጠብቁ ነበር። እነዚህም ሁላቸውም ከአይሁድና ከአህዛብ ወገን የሆኑ ያልዳኑ፣ ያልተዋጁ፣ ያላመኑና ያልተመረጡ ናቸው። እነርሱም በ70 አ.ም በነጩ ዙፋን ፍርድ ይጠፉ ዘንድ ለዘላለም በእሳት ባህር ሊነዱ ፍርዳቸውን ተቀብለዋል። ይህም ማለት በብሉይ ኪዳን ዘመን ላይ እየኖሩ የማያምኑ የነበሩ ሟቾች ሁሉ በሞታቸው ጊዜ ከአጸደ ሥጋ ተለይተው በአጸደ ነፍስ ሳሉ በሀደስ የስቃይ ዞን ሆነው በ70 አ.ም የሚገለጠውን የመጨረሻ ፍርድ ይጠባበቁ ነበር ማለት ነው።

፪. ሟች ቅዱሳን በፓሮውዥያው ወቅት
5) በ70 አ.ም በተፈጸመው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ወቅት፣ ክርስቶስ ከዚህ በላይ የጠቀስናቸውን እነዚህን ሟች ቅዱሳን ሁሉ በሰማያት ከያሉበት ሰብስቦ በአየር ላይ ወይም በሰማያት መካከል ወዳለ ሊታይ ወደማይቻል ሰማያዊ ስፍራና ግዛት ከራሱ ጋር አምጥቷቸዋል። እነርሱም እስከፍጻሜው ድረስ የታመኑ ሆነው በመገኘታቸው የተፈረደላቸው፣ ለአለምና ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር ሊነግሱ እና ሊገዙ መንፈሳዊና ሰማያዊ ሆኖ በከበረ የትንሣኤ አካል ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የገቡ ናቸው።

6) በ70 አ.ም ላይ በክርስቶስ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ወቅት ገና ሳይሞቱ በሕይወት የነበሩ እነዚያ ጥቂት የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ደግሞ፣ ጌታ ሲገለጥ በቅጽበተ አይን ተለውጠው ተነጥቀዋል። [መነጠቅ በግሪኩ "harpazo" የተሰኘው ቃል ስትሮንግስ በተሰኘው የግሪክ የቃላት መፍቻ #726  ከሩቅ ፣ ወደ ላይ ይዞ ማንሳት፣ ነቅሎ ወይም ጎትቶ (በኃይል መውሰድ፣ መንጠቅ፣ መንቀል፣ ወደላይ ማንሳት፣ ወይም ይዞ በኃይል ወደላይ መሳብ የሚል ትርጉም ተሰጥቶትታል።] ይኸውም። ተለውጦ መነጠቅ ሥጋዊውን ሞትን መለማመድ ሳያስፈልጋቸው ጌታን በአየር ላይ ወይም በመካከለኛው ሰማይ ላይ መገናኘት የሚያስችላቸው ነው። እነርሱም እስከፍጻሜው ድረስ የታመኑ ሆነው በመገኘታቸው የተፈረደላቸው፣  ለአለምና ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር ሊንነግሱ እና ሊገዙ መንፈሳዊና ሰማያዊ ሆኖ በከበረ የተለወጠ አካል ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የገቡ ናቸው።

"አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።" (ራእይ 21፥ 1-4)

"ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም። ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር። አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፥ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤ በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፥ የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ። ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።" (ራእይ 21፥ 22-27)

በ70 አ.ም ከእርሱ ጋር ያመጣቸው እነዚህ ቅዱሳን ሁሉ በሰማያዊቷ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከክርስቶስ ጋር የዘላለም ሕይወት አላቸው። በዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ወቅት እነዚህ ሁሉ የተለያዩ ቡድኖች የተዋጁ ፣ የተመረጡ የብሉይ ኪዳን እና የሽግግር ወቅት አማኞች አዲሱን፣ የማይበሰብሰውን ፣ የማይሞተውን ፣ የከበረውን ፣ መንፈሳዊውን ፣ ሊታይም የማይችለውን፣ ሰማያዊ አካል በትንሣኤ እና በመለወጥ ተቀብለዋል። "ትንሣኤና ሕይወት" ከሆነው ከኢየሱስ "የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤" (ዮሐንስ 11፥ 25) የሚል ጽኑ ተስፋ ይዘው፣ በሥጋ ቢሞቱም እርሱ በመጨረሻው ቀን እንደሚያስነሳቸው አምነው ሞተዋል፤ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሳይሞቱ ቢቆዩ ደግሞ በቅጽበት አይን ተለውጠው እንደሚነጠቁ ተስፋ አድርገው ኖረዋል። በመጨረሻውም ቀን ሙታንን አስነስቶ ከእርሱ ጋር አምጥቷቸዋል፣ ሕያዋንንም ለውጦ በንጥቀት ወስዷቸዋል።

፫. ሟች ክርስቲያኖች ከፓሮውዥያው በኋላ
7) በ70 አ.ም ከተፈጸመው የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ፓሮውዥያ በኋላ፣ የአዲሱ ኪዳን የወንጌል መንግስት እርሱም አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር በሙላት ተመስርቶ ተገልጧል። የአሮጌው ኪዳን አይሁዳዊ የኃይማኖት መስተዳድር እርሱም አሮጌው ሰማይ አልፏል። በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ እግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ የሚታወቀው የእስራኤል ሕዝብ፤ የኢየሩሳሌም ከተማ እና መቅደሱ እርሱም አሮጌው ምድር፣ ሁሉም ተደምስሶ አልፏል። ከእንግዲህም በኋላ በእግዚአብሔር ዋጆአዊ እቅድ ውስጥ ፈጽሞ ምንም ቦታ የሌላቸው ሆነዋል። 

ከ70 አ.ም በኋላ ያለን እኛን በክርስቶስ ያመንነውንና፣ ከዚህም በኋላ ለአለምና ለዘላለም በእርሱ እያመኑ ወደአካሉ ህብረት የሚገቡትን ሁሉ ጨምሮ፣ ገና በዚህ ህይወት እያለን እግዚአብሔር የዋጀን ምርጦች ሁላችንም (የተመረጡ አይሁድ እና የተመረጡ አህዛብ ሁሉ) በክርስቶስ የተፈረደልንና የተጠናቀቀ ድነታችንን ፍጻሜና ሙላት የተቀበልን ነን። ዘላለማችንንም በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከክርስቶስ ጋር ልናሳልፍ በእምነት ወደሀልዎቱ ገብተናል። ክርስቲያኖች ተብለን በክርስቶስ እንደተባበረ አንድ ሕዝብ እና አንድ አካል ነን እንጂ ወደፊት መቼም ቢሆን አይሁድ ወይም አህዛብ ተብለን አንጠራም (ገላትያ 3፥ 16፣ 28-29)። ሁላችንም በየግላችን በእንድ ወይም በሌላ ምክንያት በሥጋ እንሞታለን፣ ያኔም ወዲያውኑ በማይሞተው፣ በማይበሰብሰው፣ በከበረው፣ መንፈሳዊ በሆነው፣ ሊታይ በማይችለው ሰማያዊ አካል፣ ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ሀልዎቱ ፊት በክብር ለመሆን ወደ ሰማይ እንሄዳለን። *ትንሣኤና ሕይወት" ከሆነው ከኢየሱስ ዘንድ "ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም" (ዮሐንስ 11፥ 26) የሚል እንዲህ ያለ ጽኑ ቃል ያለን እኛ ይህንን እንዲሁ በጸጋ ያገኘነውን አዲሱን ዘላለማዊ ሕይወት ይዘን እንሞታለን፣ እርሱ ሕያው ስለሆነም ሕያዋን ነንና ለዘላለም አንሞትም።

# የማያምኑ ሟቾች ፍጻሜአቸው፦
ከ70 አ.ም በኋላ ባለው በዚህ ህይወት ሳሉ ባለማመን ጸንተው የሚሞቱ ሁሉ፣ ከላይ እንዳነሳነው እነርሱም አስቀድሞ በዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያው  በተፈጸመው በታላቁ የነጩ ዙፋን ፍርድ ውሳኔ ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው። እነዚህም ሁላቸው ከ70 አ.ም በኋላ የኖሩና የሞቱ በጠቅላላው የክርስቶስን ወንጌል የገፉ፣ ያልዳኑ፣ ያልተዋጁ፣ ያላመኑና ያልተመረጡ የጠፉ የምድር ህዝቦች ናቸው። ማናቸውም ቢሆኑ በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፉ ናቸው። "በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል" (ዮሐንስ 3፥ 18) እንደተባለ፣ ዘላለማዊው ፍርዳቸው እና ኩነኔያቸውም አስቀድሞ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተመደበ እና በይፋ የታወጀ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በህይወታቸው ጌታቸውና መድሃኒታቸው እስካልሆነ ድረስ ማናቸውም ቢሆኑ በማናቸውም ምክንያት በሚሞቱበት ጊዜ በ70 አ.ም ላይ በይፋ የተገለጠውን ዘላለማዊ ቅጣታቸውን በየራሳቸው ይቀበሉ ዘንድ ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት ይጠፉ ዘንድ በቀጥታ ወደ እሳት ባህር ይሄዳሉ (ራእይ 21፥ 8)። ስለዚህ ወደ ጸጋው መግባትን ያገኘች ቤተክርስቲያን ሌሎች በውጭ ያሉ በሥጋ ከመሞታቸው በፊት ፈጥነው እንዲገቡ ሰውን ሁሉ በፍቅር እየለመነች ለንስሃ እና ለእምነት በወንጌል ትጣራለች።

በመጨረሻም፣ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የበለጠ ለማሰብ ፍላጎት ካደረባችሁ በፊልጵስዩስ 3፥ 21 ላይ ተመስርቼ፣ "የተዋረደው 'ሥጋችን' ልውጠት" በሚል ርዕስ በጸሎትና በንባብ ያቀረብኩትን ሰፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜ ወስዳችሁ እንድትመለከቱት በአክብሮት እጋብዛለሁ። በውስጡም የሚያጽናና እና የሚሞግት የወንጌል ጸጋ ቀርቦበታልና ትካፈሉት ዘንድ እነሆ ሊንኩ፦  
https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/3265218500373240/ 

ግዛቸው ከበደ /ቄስ/

Sunday, September 26, 2021

ሜሎው፣ እርግጠኛው አይቀሬ


እርግጠኛው አይቀሬ


"μέλλω" (ሜሎው) የተሰኘው የግሪክ ቃል እና ነገረ ፍጻሜአዊ ጠቀሜታው ሲፈተሽ


 

አዲስ ኪዳን ከተጻፈበት የግሪክ ቋንቋ በቀጥታ ወደ እንግሊዝኛም ይሁን ወደ ልዩ ልዩ ጥንታዊና ዘመናዊ ቋንቋዎች የተደረጉ ትርጓሜዎች በየዘመኑ ላሉ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅስዱ በገጾቹ የያዘውን ቁምነገር ለመረዳት እንዲችሉ ሲያግዟቸው ኖረዋል። መጽሐፍ ቅዱስን በተለያየ ቋንቋ ተርጉመው ያቀረቡልን አብዛኞቹ ተርጓሚዎች በተለይ ለበኩረ ቋንቋው ለግሪኩ ታማኝ ለመሆን የተቻላቸውን ጥረት ሁሉ ያደረጉ መልካም ሰዎች ናቸው። በአማርኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ተሳትፎ ለነበራቸው አባቶችም ልዩ አክብሮት አለኝ። ዳሩ ግን የግሪኩን ቅጂ እያየን አማርኛችንንም ሆነ እንግሊዝኛውን እያጣቀስን እና እያመሳከርን ስናጠና ከቃላት አገባብንና ከሚሰጡት ትርጉም አንጻር ጉልህ ልዩነት የሚያደርጉ እንዳንድ ጉዳዮች ይኖራሉ፤ በተለይ መሰረታዊ አስተምህሮዎችን ሊቀርጹ ጉልበት ያላቸው ቃላትና ሃረጎች ሲሆኑ የበለጠ ያሳስባሉ። 


በዚህ ረገድ ከነገረ ፍጻሜአዊ ይዘቷ አንጻር ከፍ ያለ ዋጋ ያላት፣ ነገር ግን ብዙዎች ልብ ያላልዋት μέλλω "MELLO" የተሰኘች አንዲት የግሪክ ቃል እናገኛለን፤ ግሱ በእንግሊዝኛው "ABOUT TO BE" በአማርኛው "ሊሆን ያለው" በሚል መተርጎም የነበረበት ይህ ሐረግ የያዘው ቁም ነገር ብዙም ትኩረት ሳይስጠው በብዙዎች በቀላሉ እንደታለፈም እንታዘባለን።  ይህች μέλλω "MELLO" [በእንግሊዝኛው፣ ABOUT TO BE ጎግል ሲፈታው፦ Be (just) about to allows us to express an imminent action, or a very near future: ይልና፤ The train is just about to leave. The train will leave very soon. የሚል ምሳሌን ይሰጠናል] የተሰኘች አንዲት ቃል ግን በውስጧ ከጊዜ አንጻር በእጅጉ ቅርብ የሆነን ጉዳይ እርሱም የማይቀር እርምጃን ጓጉቶ የመጠባበቅን ጽንሰ አሳብ ይዛለች። ቃሉ ሊከሰት፣ ሊመለስ፣ ሊመጣ፣ ሊደርስ ወዘተ ያለ ነገርን 'ሰፍ ብሎ' መጠበቅን ሲያመለክት፣ የጉዳዩን ቅርበት የሚያሳይና 'እነሆ ሊሆን ነው' ብሎ በመጠባበቅ ስሜት፣ በተለይ ከጊዜ አንጻር በቅርብ ርቀት የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ የግድ መሆን ያለበትንና፣ እንዲሆን የተወሰነን አንዳች ነገርን  የሚያመለክት፣ ስለሚሆነውም ነገር እርግጠኛነት የሚናገር የግሪክ ቃል ነው። [ለበለጠ ግንዛቤ Strong's word 3195፤ እንዲሁም ግሪክ ሌክሲከን /Greek Lexicon/ ላይ መሰረቱን አድርጎ የተዘጋጀው የጣየር እና የስሚዝ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ በተጨማሪም ሌሎች እንደ Theological Dictionary of the New Testament ያሉ ሰነዶችን ማመሳከር ይቻላል።]


ዘመናዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተዘጋጁበት ጊዜ፣ μέλλω "MELLO" (ABOUT TO BE) የተሰኘችው ቃል/ሀረግ በኢየሱስና በሐዋርያቱ ንግግር ውስጥ ያላት ጠቀሜታ ተርጓሚዎችን እንዳስቸገራቸው በብዙ ልንታዘብ እንችላለን። እነዚህ ተርጓሚዎች በአመዛኙ በነገረ ፍጻሜ እምነታቸውና አቋማቸው ገና ወደፊት ይመጣል ባይ "መጻኢያን" ስለሆኑ፣ ከዚህ የተነሳ ምንም እንኳ ይህች ቃል በያዘችው ትርጉም "ሊመጣ እንዳለው" μέλλω MELLO (ABOUT TO BE) ብላ እያስተማረች ቢሆንም እንኳ፣ እነርሱ ግን የሚመጣው ገና ወደፊት የሚመጣ እንደሆነ μέλλω "MELLO" (ABOUT TO BE) ሲተረጉሙ፣ የፍጻሜውንም ጊዜ ቅርበት አዲስ ኪዳንን በጻፉልን ሰዎች የህይወት ዘመን ውስጥ ማሰብ እና በዚህ ደርዝ ትርጉሙን ማስቀመጥ እንዳልተቻላቸው በግልጽ እናያለን። ስለዚህ የቃሉን ጠቀሜታ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፣ ወይም ሆን ብለው በነገረ ፍጻሜ አመለካከታቸውና አቋማቸው ተጽዕኖ ስር ወድቀው፣ ቃሉ ቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ጨርሶ እንዳልነበር ሁሉ፣ ይህንን MELLO የተሰኘ ቃል በአመዛኙ ትርጉማቸው ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው አድርገዋል። የዚህ ጽሁፍ አላማ የቃሉ ወዳጆችና ተማሪዎች የሆኑ የመሰማርያው በጎች በአንዲት ትንሽዬ ቃል የተነሳ ቅዱስ ቃሉ የሚለውን እንደማይል፣ የማይለውንም እንደሚል አድርገው የማሰብም ሆነ የመማር አደጋ ውስጥ እንዳይወድቁ፣ በእውነትም ግራ ከመጋባት የተጠበቁ ይሆኑ ዘንድና ከነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ አንጻር ጊዜ ጠቋሚ ለሆኑ ምንባባት ተገቢውን ትኩረት እንዳይነፍጉ ለመርዳት መሆኑን ልብ አድርጉ።


በዚህ መሰረት ምሳሌ የሚሆኑን ጥቅሶችን ከተወሰኑ ማብራርያዎች ጋር እየተመለከትን ይህ mello የተሰኘ አንድ ቃል በተለይ ከነገረ ፍጻሜ ጠቀሜታው አንጻር በየምንባባቱ ውስጥ ያለውን አገባብ አብረን እንድንፈትሽ በአክብሮት እጋብዛችኋለሁ።


  1. ማቴዎስ 3፥ 7 (ሉቃስ 3፥ 7) "ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው [ሊመጣ ካለው/ mello] ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?" ["ሊመጣ ያለው ቁጣ" እንጂ "የሚመጣ ቁጣ" አይደለም]


  • መጥምቁ ዮሐንስ በዚህ አውድ ለአይሁድ ህዝብ እየሰበከ መሆኑን እናያለን፤ በስብከቱም በቅርቡ ስለሚደርስባቸው የእግዚአብሔር ቁጣ የአይሁድን የኃይማኖት መሪዎችን ያስጠነቅቃል። ቁጣው መቼ እንደሚመጣ የማይታወቅ ግን የሚመጣ ቁጣ ሳይሆን፣ የሚመጣበት ጊዜ የቀረበ ወይም በቅርብ የሚመጣ ቁጣ ነው። ኢየሱስም በሌላ ስፍራ በትምህርቱ “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች” ብሎ የጠራቸው እነዚሁኑ ቡድኖች ሲሆን፣ በዚህም ንግግሩ የእግዚአብሔርን ቁጣ “የገሃነም ፍርድ” በማለት ገልጾታል (ማቴዎስ 23፥ 33)። ኢየሱስ በዚያ ትውልድ ላይ ቤታቸው ባድማ ሆኖ የሚቀርበት ጊዜ እንደሚደርስ የተናገረው ፍርድ እና ይመጣል፣ "ከሰማይም ይገለጣል" የተባለው ቁጣ (ማቴዎስ 23፥ 38፤ ሮሜ 1፥ 18) ከ66-70 አ.ም ባለው ጊዜ (ለ3 አመት ተኩል) መጥቶ አልፏል። ያኔም የአሮጌው ኪዳን ቤተመቅደስ እና የኢየሩሳሌም ከተማ በሮማውያን ሰራዊት እጅ ወድቀው ተደምስሰው ወድመዋል። አስቀድሞ በእስራኤል ምድር ተቀስቅሶ ከነበረው አመጽ፣ የእርስ በርስ ውጊያና ጽኑ ረሃብ የተረፉ በሚልዮን የሚቆጠሩ የአይሁድ ሕዝብም በደረሰባቸው መቅሰፍተ ዕልቂት በገዛ ምድራቸው ተገድለው አልቀዋል፣ በምርኮ የተወሰዱትም በአለም ዙርያ ተበትነው ከእነርሱም የሚበዙት በአህዛብ ጣዖታት ክብረ በአላት ላይ ለጣዖታቱ እንደ መስዋእት ታርደው፣ ለነገስታቱና ለመኳንንቱ ክብር ጭዳ ሆነው፣ ገሚሱንም በጨዋታ ስፍራ ከአውሬ ጋር እያታገሉአቸውና እየተበሉ ዘራቸው ጥፍቷል፤ ይህም ሁሉ የተፈጸመው በ70 አ.ም ነው (ዳንኤል 12፥ 7-13 እና ሉቃስ 21፥ 5-36 ተመልከቱ)። ከ70ው አ.ም ፍጅት በኋላ በእናቱም በአባቱም ንጹህ የአብርሃም ልጅ የሆነ እስራኤላዊ በምድር ዙርያ ማግኘት የማይታሰብ ሆኖአል። "ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል" ያለው አስፈሪው የኢየሱስ የፍርድ ትንቢትም ተፈጽሟል።


  1. ማቴዎስ 12፥ 32 "በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው [ሊመጣ ባለው/ mello] አይሰረይለትም።" [ ሊመጣ ባለው ዘመን እንጂ የሚመጣው ዘመን አይደለም]


  • እንደ ግሪኩ "ሜሎ" ሁሉ 'አለም' በሚል የትርጉም ስህተት የተሰራበት ሌላው የግሪክ ቃል 'ዘመን' (aion) የተሰኘው ነው። ኢየሱስ ግን "ይህ ዘመን" ሲል የሚጠራውንና ያኔ ይሰራ የነበረውን የብሉይ ኪዳንን አለም እና በ 70 ዓ.ም "ሊመጣ ያለውን" የአዲሱን ኪዳን ዘመን በተቃርኖ ያቀርባል እንጂ፣ የትርጉም ስህተቱ እንደፈጠረው እንግዳ ትምህርት "ይህ አለም" ማለት አሮጌው የሙሴ አለም መስተዳድር ካልሆነ በቀር፣  ይህ ግዑዝ አለም ማለት አይደለም፤ የሚመጣው ማለትም አሮጌውን የሙሴ አለም መስተዳድር ሽሮ የሚገለጥ አዲሱ ኪዳን የሚያበስረው የክርስቶስ ዘላለማዊ መንግስት ካልሆነ በቀር፣ ሌላ የሚመጣ አዲስ ግዑዝ አለም ማለት ፈጽሞ አይደለም። ለምንድነው ግን ኢየሱስ "በዚህ ዘመን ወይም ሊመጣ ባለው ዘመን" ይቅር አይባልም ሲል የተናገረው? በእርግጥ እርሱ እየተናገረ ያለው የአይሁድ ቤተ መቅደስ እንዲደመሰስ ከሆነበት ከ 70 አ.ም በፊት (ማለትም “ይህ ዘመን”) እና ከዚያ በኋላ (“በሚመጣው ዘመን”) ስለ ተፈጸሙ ኃጢአቶች ነው። ስለዚህ ይመጣል የተባለው ዘመን ቀኑና ጊዜው ቀርቦ የሚታወቅ እንጂ ሩቅ እና የጊዜውን ማእቀፍ ማወቅ የማይቻል አይደለም።


  1. ማቴዎስ 16፥ 27-28 "የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና [mello]፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።" [ይመጣ ዘንድ አለው እንጂ ይመጣል አይደለም]


  • mello የተሰኘውን ቃል ጠቀሜታ እውቅና ሰጥተው አማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ለተረጎሙ ሰዎች እዚህ ላይ ዋጋ መስጠት ይገባል። ይህ ምንባብ በግልጽ እንደሚናገረው ኢየሱስ ሊመጣ ያለው የሰው ልጅ ነው፤ ከዚህም የተነሳ እዚያ ቆመው ይህንን ንግግሩን ያደምጡ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሳይሞቱ በህይወት ቆይተው 'ይሆናል' የተባለው ይህ ጉዳይ ሲፈጸም ማለትም መምጣቱን ያያሉ። ይህ ንግግር በግልጽ ጓጉቶ መጠባበቅን የግድ ይላል። እንዲህ ያለ ፊትለፊት እና በግልጽ ቋንቋ ከኢየሱስ አፍ የወጣ ንግግር ልክ እንደተጻፈው እውነት ካልሆነ ግን፣ ኢየሱስን ሀሰተኛ ነብይ ሊያሰኘው የሚችል ጣጠኛ የሆነ መዘዝ ይጎትታል። ኢየሱስ ጌታ ነው ብለን እያመንን በጌታችን ላይ እንዲህ ያለ ስድብ እና ነቀፋ የሚያስከትል "ትንቢት እስካሁን አልተፈጸመም፣ ጌታም ገና ወደፊት እንጂ እስካሁን አልመጣም" የሚል የመጻኢነትን ትምህርት አዝለን መኖራችንን አለማወቅ በእውነት እውርነት ነው። ኢየሱስ መንግስቱን ከእግዚአብሔር ጠላቶች ነጥቆ ሁሉ በሁሉ ሆኖ አሁንና ለዘላለም ሁሉን ለሚገዛው ለእግዚአብሔር ይመልሰው ዘንድ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ተመልሷል ብዬ የማምነውም ከዚህ የተነሳ ነው። ታዲያ እርሱ በግልጽ ፊት ለፊት "እዚህ የቆሙት" ሲል በተለይ በጠራቸው ሰዎች የህይወት ዘመን ተመልሷል ብዬ እንዳላምን፣ ይልቁንም 'አይ ሊል የፈለገው እንደዚህ ሳይሆን እንደዚያ ነው" በሚል ማመካኛና ሰዎች ለቃሉ በሚሰጡት ማስተካከያ እና እርማት መሰል ድፍረት ሊል ያልፈለገውን ሌላ ነገር እንድረዳና እንዳምን፣ የሰጠውንስ ተስፋ እንዳልፈጸመ እንድቆጥር ለምን ይፈርዱብኛል? እንደተናገረው  እንደዚያው እንደ ተስፋ ቃሉ በፍርድና በክብር ተመልሷል ብዬ ላምነው የማልችለው 'ኢየሱስ' አዳኜስ ሊሆን እንዴት ይችላል?


  1. ማቴዎስ 24፥ 6 "ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ [millo]፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።" [ትሰማላችሁ ሳይሆን ትሰሙ ዘንድ አላችሁ ነው]


  • ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የሚናገረው ለነዚያ ከእርሱ ጋር በዚያ ለነበሩ የመጀመሪያው ከፍለዘመን ደቀመዛሙርቱ ነው፤ እንጂ ዛሬ ይህንን የምናነብ ማናችንም ብንሆን የዚህ ቃል በኩረ ተደራስያን አይደለንም። የሚነግራቸውም በገዛ ራሳቸው ትውልድ ወቅት (ማቴዎስ 24፥ 34) በቅርቡ ሊሆንባቸው ስላለ ነገር ነው። ሊሆን ያለው የሚሆነው "እናንተ" ተብለው በተለይ ለተጠቀሱ ለመጀመሪያዎቹ አድማጮች እንጂ ለማናችንም አይደለም። በዚህ ምንባብ "ትሰሙ ዘንድ" በሚል 'እናንተ' ለተባሉት "መጨረሻው" ገና ወደፊት ነበር፣ ዳሩ ግን ሩቅ ሳይሆን እናንተ በተባሉት ሰዎች የሕይወት ዘመን የሚሆን ነው። ትንቢቱ 'እናንተ ትሰማላችሁ' በተባሉት ሰዎች የህይወት ዘመንና ትውልድ ውስጥ  ያልሆነና ተፈጽሞ ያላለፈ ከሆነ፣ እንግዲያውስ እነዚህ ቃሎች ከተነገሩ ከ2000 አመታት በኋላ ለምናነባቸው ለእኛም ቢሆን መጨረሻው ገና ወደፊት ሊሆን ከቶ አይችልም።


  1. ሉቃስ 21፥ 36 "እንግዲህ ሊመጣ ካለው [mello] ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።" [ሊመጣ ካለው ነው እንጂ ከሚመጣው አይደለም]


  • የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳን ትርጉም በዚህም ጥቅስ ላይ mello ለተሰኘው የግሪክ ቃል ታማኝነቱን አሳይቷል። እንደ ኢየሱስ ግልጽ ንግግር ከሆነ እርሱ "ይህ ሁሉ" ሲል የዘረዘረው "ሊመጣ ያለው" ነገር ሁሉ ፍጻሜው በዘመንና በትውልድ ርቀት የሚታሰብ ሳይሆን፣ ይልቁንም በግል በእያንዳንዳቸው በደቀመዛሙርቱ የህይወት ዘመን የሚሆኑ ነገሮች ናቸው። ኢየሱስ የሚናገረው ለገዛ ራሱ ደቀ መዛሙርት ነው እንጂ ለእኛ ወይም ለሌላ ሦስተኛ ወገን እንዳልሆነ ልብ አድርጉ።


  1. ሐዋርያት 17፥ 31 "ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ [mello] ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።" [ይፈርዳል ሳይሆን ሊፈርድ ነው ማለት ነው]


  • አማርኛው ይህንንም ጥሩ አድርጎ አስቀምጦታል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ግልጽ ያደረገው አንድ ጉዳይ በራሱ ትውልድ እግዚአብሔር በአለሙ ሁሉ ላይ ሊፈርድ መሆኑን ነው። ኃላፋውያን በትምህርታቸው ቅዱሳት መጻህፍትን ሲተረጉሙ ጊዜ ጠቋሚ ለሆኑ እንዲህ ላሉ ንግሮች ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጣሉ፣ ነገረ ፍጻሜአዊ ምልከታችንን መልክና ቅርጽ የሚሰጠው አንዱ ይኸው ነውና።  እግዚአብሔር በህያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ያለው፣ ቀን የቀጠረው በመጀመርያው ከፍለዘመን ትውልድ ወቅት ነበር። ይህንን በመለኮት የተመደበ ቀነ ቀጠሮ ከመጀመርያው ክፍለዘመን የጊዜ ማእቀፍ አውጥተን በየትኛውም ዘመናዊ ወይም መጻኢ ጊዜ ውስጥ ፍጻሜውን እንድንጠባበቅ የሚያስችለን ምንም አይነት አዲስ ኪዳናዊ ድጋፍ የለንም፣ አይኖረንምም።


  1. ሐዋርያት 24፥ 14፣ 15 "ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው [mello] ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።" [ከሙታን ይነሳሉ ሳይሆን ከሙታን ይነሱ ዘንድ አላቸው ነው]


  • እዚህም ላይ የአማርኛው ትርጉም ጥሩ ነው። ጳውሎስ በዚህ ንግግሩ ግልጽ የሚያደርገው አንድ እውነት ምንድን ነው? "እኔ ከእነርሱ የምለየው በአምልኮዬ ነው፣ መንገዱንም ኑፋቄ ሲሉ ይጠሩታል፤ ሆኖም የማምነዉ እነርሱ እንደሚያምኑት በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ ነው፣ የሙታንን ትንሳኤ  የምጠብቀውም እነርሱ እንደሚጠብቁት ነው፣ ተስፋ የማደርገውም እነርሱ ተስፋ አንደሚያደርጉት ነው"፤ እያለ ነው። የሙታን ትንሳኤን ጨምሮ በህጉ የተጻፈው ሁሉ በቅርቡ ፍጻሜውን የሚያገኝ መሆኑን ጳውሎስ ይጠባበቃል። ጳውሎስ ለአገረ ገዡ ለፊሊክስ እየነገረው ያለው፣ የጻድቃንና የኃጢአተኞች ትንሳኤ የሚከናወነው በእርሱ የህይወት ዘመን መሆኑን ነው። ጉዳዩ በእርግጠኝነት በቅርቡ የሚከናወን (NO DELAY) መሆኑን ያመለክታል። ስለዚህ ጳውሎስ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን አድማጮቹ ባቀረበው ሙግት፣ ትንሳኤ በቅርቡ ሊሆን እንደሆነ እየነገራቸው ነበር ማለት ነው። በመላው አዲስ ኪዳን፣ ወንጌል አስቀድሞ ለአይሁድ ከዚያም ለግሪክ እንደሚሆን የተገባው የእስራኤል ተስፋ መፈጸሙን በግልጽ እናያለን፤ ይህም በድህረ ጴንጤቆስጤ እየተካሄደ በነበረው ከአሮጌው ኪዳን ወደ አዲሱ ኪዳን የሚደረገው ሽግግርም በዚያው የመጀመርያው ክፍለዘመን ውስጥ የፍጻሜው ዘመን እየቀረበ የነበረ መሆኑን እና ያም ጠንካራ ምስክርነት እንደነበር ያሳያል። 


  1. ሐዋርያት 24፥ 25 "እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም [ሊመጣ ስላለው/ mello] ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ፦ አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት።" [ሊመጣ ስላለው ኩነኔ ነው እንጂ ስለሚመጣው አይደለም]


  • ፍርድ በገዛ ራሱ ትውልድ ውስጥ በቅርቡ ሊመጣ መሆኑን እየተናገረ ያለውን የጳውሎስን ግልጽ ንግግር ካልተረዳ በቀር ፊልክስ ለምን ይፈራል? ያኔ ጳውሎስ ለፊልክስ እየተናገረ ፊልክስም ጳውሎስን እየሰማው በነበረበት ዘመን ኩነኔ ሊመጣ በቅርብ ተዘጋጅቶ ነበር ማለት ነው።


  1. ሮሜ 8፥ 13 "እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና [mello]፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።" [ትሞታላችሁ ሳይሆን ትሞቱ ዘንድ አላችሁ ነው]


  • ለአማርኛው ትርጉም ያለኝን አድናቆት አልሸሽግም። ጳውሎስ አይሁድ አማኞች የሆኑ “ወንድሞችን”፣ የሚናገራቸው ወደ ሥጋ ፈቃድ ተመልሰው “በሥጋ ትምክህት የሚሄዱ” ከሆነ “ሊሞቱ” እንደሆነ አያስጠነቀቃቸው ነው። ይህም ሥጋዊ በሆነው ሥርዓታቸው ላይ በመመካት በመንፈስና በሕይወት የሚገለጠውን ኑሮ እምቢ በሚሉት ላይ ፈጥኖ ሊሆንባቸው ያለውን ፍርድ ያሳያል።


  1. ሮሜ 8፥ 18 "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው [mello] ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።" [ይገለጥ ዘንድ ያለው ነው እንጂ የሚገለጠው አይደለም]


  • በዚያን ጊዜ የነበሩ ምዕመናን እነዚህን ነገሮች በምን ያህል ናፍቆት ጓጉተው ይጠባበቁና ተስፋ ያደርጉ እንደነበር ለማየት የዚህን ጥቅስ አጠቃላይ አውድ (ቁጥር18-25) በጥንቃቄ አንብቡት። ለምን እነዚህን ነገሮች መጓጓትና በግል መጠባበቅ አስፈለጋቸው? ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ በግላቸው እነሱን ማሳተፍ የነበረባቸው ጉዳዮች በመሆናቸው ነው። ይገለጥ ዘንድ ያለው ክብር "ለእኛ" ነው፣ እኛ የተባሉትም ጳውሎስና የመጀመሪያው ክፍለዘመን ክርስቲያኖች ናቸው። "የአሁኑ ዘመን ሥቃይ" የተባለውም የእነርሱ ዘመን ሥቃይ ነው። በግል እያንዳንዳቸው ያልፉቡት የነበረው የመከራ ሕይወት የሚካሰውና የሚደመደመው ለእነርሱው ሊገለጥ ባለው ክብር ነው።


  1. ሮሜ 8፥ 38፣39 "ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም [ሊመጣ ያለው mello] ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።" [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]


  • እዚህ ላይ ሁለቱን ኪዳናት እናያለን። "ያለውም" የተባለው እርሱም 'አሁን ያሉት ነገሮች (የሙሴ ዘመን)' እና "የሚመጣውም"  የተባለው እርሱም ሊመጣ ያለው (መሲሐዊው ዘመን) ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም ተብሎ ከተዘረዘረው፣ ከሞት ፣ ከህይወት ፣ ከመላእክት ፣ ወዘተ ጋር ተቆራኝተው መነገራቸውን ልብ በሉ። "ያለውም"  የተባለው በዚያ በአሮጌው ኪዳን እና በሙሴ ዘመን መስተዳድር ውስጥ ተካተው የነበሩ ያኔ እነርሱ ይኖሩበት የነበረው ስርአትና የሞት አገልግሎቱ ነው፤ "የሚመጣውም"  (ሊመጣ ያለው)  የተባለው ደግሞ አዲሱን ኪዳን ወይም የመሲሁን ዘመን የሚያካትት ነው። ይህም በእብራውያን 8 ላይ ስለ አሮጌው ዘመን፣ "አርጅቷል፣ አሮጌና ውራጅ ሆኖ ሊጠፋ ቀርቦአል!" (ቁጥር 13) እያለ ከሚናገረው ጋር የተቆራኘ ነው። አዲሱ በሙላት እስካልመጣ ድረስ አሮጌው ኪዳን አሮጌ ሊሆን እንደማይችል ይህንን አንድ ነገር አትርሱ። ያ በ70 አ.ም ላይ የተከሰተው የመቅደሱና የከተማይቱ ውድመት የዚያን አሮጌ ስርአት ፍጻሜው መሆኑን ያሳያል። አሮጌው ኪዳን በውስጡ የያዛቸው ሁሉም ዓይነት ነገሮች በኢየሱስ ተፈጽመዋል።


  1. 1ቆሮንቶስ 3፥21-23 "ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም [ሊመጣ ያለው mello] ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።"  [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]


  • ከፍ ሲል ለሮሜ 8፥ 38 የተሰጠውን ማብራርያ ይመለከቷል። "የሚመጣውም [ሊመጣ ያለው mello] ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥"  ሲል እዚህ ላይ "እናንተ" የተባሉት በመጀመርያው ከፍለዘመን ላይ የነበሩ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ናቸው። "የሚመጣውም" (ሊመጣ ያለው) የእነርሱ ከሆነ እንግዲያውስ የሚመጣው በእነርሱ የህይወት ዘመን ለእነርሱ ነው፣ እንጂ እነርሱ ካለፉ በኋላ ዘመናት ተቆጥረው ቢመጣ "የእናንተ ነው፥"  መባሉ ምንም ትርጉም አይሰጥም።


  1. ኤፌሶን 1፥ 20-21 "ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው [mello] ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤" " [በሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ባለው ነው]


  • ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው "ዓለም" የሚለውን ቃል እዚህ ያለቦታው የዶለው የተርጓሚዎች ስህተት ነው፤ ቃሉ "ዘመን" ተብሎ መተርጎም ነበረበት። ስለዚህ "ይህ ዘመን" (አሮጌው ኪዳን) እና "ሊመጣ ያለው ዘመን" (አዲሱ ኪዳን) በንጽይር የቀረቡልን ስለሆነ ትርጉማቸውን በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል፣ ምክንያቱም አይሁድ ነገረ ፍጻሜን የሚረዱትና የሚተረጉሙት በነዚህ ቃላትና ሃረጎች ላይ ቆመው ነው። "በዚህ ዘመን" የተባለው ትርጉሙ የአሮጌው ኪዳን ዘመን ሲሆን፣ "ሊመጣ ባለው ዘመን" የተባለው ደግሞ የአዲሱ ኪዳን ዘመን ነው። በእብራውያን 8 የተገለጸውን እንዲሁም የአሮጌውን ፍጻሜ እዚህ ላይ ልብ በሉ።


  1. ቆላስይስ 2፥ 16-17 "እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ያሉት [mello] ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።" [የሚመጡ ነገሮች ሳይሆን ሊመጡ ያሉት ነገሮች ነው]


  • ይህ ምንባብ በክርስቶስ ፍጻሜውን ሊያገኝ ያለውን አሮጌውን ኪዳን (ማለትም የአይሁድን በአላት፣ ልዩ ልዩ ስርአቶቻቸውን ተስፋዎቻቸውን፣ ወዘተ) በአግባቡ ለመረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። እዚህ ላይ በአሮጌው ኪዳን ዘመን ስለተካተው የአመጋገብ ስርአት፣ በአላትን ስለማክበር እንዲሁም ወቅቶችን አስመልክቶ ስለሚሰጥ ትምህርትና ሰንበትን ስለመጠበቅ እናያለን። እነዚህም ጉዳዮች ያኔ ሊመጡ ቀርበው ላሉት ጥላው ነበሩ፣ እነዚህ ጥላ የነበሩት፣  ያረጁ ፣ ያፈጁ እና ሊጠፉ የተቃረቡ ጉዳዮችና (እብራውያን 8)፣ ከክርስቶስ ጋር ተያያዥነት ባላቸውና እርሱ በሚገዛቸው ቁምነገሮች ሊተኩ የተዘጋጁ ነበሩ!። አንዳንድ መጻኢያን የሆኑ ወገኖቻችን እነዚህ ነገሮች በመስቀል ላይ ተጠናቀዋል ብለው ያምናሉ ዳሩ ግን ተመልከቱ ጳውሎስ ይህንን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ ፍጻሜአቸው ገና እንደነበር እናያለን። ስለዚህ በግልጽ እንደምናየው እነዚህን ነገሮች በ 70 ዓ.ም. ተፈጽመው ያለቁ በመሆናቸው አሁን በዚህ ዘመን እንለማመዳቸው አንልም።


  1. 1ጢሞቴዎስ 4፥ 8 "ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው [ሊመጣ ያለው/ mello] ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል።"" [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]


  • በነ ጳውሎስ ዘመን ሕይወት የአሁንና የሚመጣው የተሰኘ ሁለት Dispensation ነበረው፤ ለእነርሱ የአሁኑ ሕይወት ማለት አጠቃላዩ አሮጌው የሙሴ ዘመን እና ከአሮጌው ወደ አዲሱ ኪዳን  ለመሸጋገር እነርሱ ራሳቸው ይኖሩበት የነበረው በብዙ ትግል ስጋን የመግራት ዘመን የምንለው ወቅት ሲሆን፤ የሚመጣው ግን እነርሱ "በህይወት እያለን የሚመጣ" ነው ብለው ተስፋ ያደረጉትና ከዚያን ጊዜ የጀመረውና እኛም ያለንበት፣ ለዘላለምም የማይዘጋው የአዲሱ ኪዳን ዘመን ነውና ያም ሕይወት በክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት በሙላት ተገልጧል። ለጥንት ክርስቲያኖች ያ የሚመጣው ሕይወት የሚመጣበት ጊዜ የማይታወቅ ሳይሆን፣ ይልቁንም mello /ሊመጣ ያለው/ የሚለው የግሪክ ቃል ጊዜው ያንን ሕይወት ተስፋ ያደርጉ ለነበሩቱ ቅርብ አይቀሬ እንጂ ሩቅና ጊዜውን ማሰብ የሚቸግር አልነበረም። ስለዚህ ያንን ሕይወት ለመቀበል እነርሱ ጋር የነበረውን ከፍ ያለ መጠባበቅና ጓጉቶ መናፈቅ በዚህ  mello በተሰኘ ቃል ውስጥ በጉልህ እናየዋለን።


  1. 2ጢሞቴዎስ 4፥ 1 "በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው [mello] በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤" [በሚፈርደው ሳይሆን ሊፈርድ ባለው ነው]


  • ይህ ጥቅስ የመጻኢያንን አመለካከት ለመደገፍ በሚደረግ ክርክር ላይ ያለውን ጉዳይ ሁሉ ይዘጋዋል። mello የተሰኘውን የግሪክ ቃል ፍትሃዊና አግባብነት ባለው መልኩ በትክክል እንተርጉመው ካልን ይህ በግልጽ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው? ቃሉ እነደሚያሳየው ኢየሱስ ያኔ ነው በህያዋን እና በሙታን ላይ ሊፈርድ ያለው። እርሱ በህያዋን እና በሙታን ላይ በሚያደርገው ፍርዱ እና በመገለጡ መካከል ግልጽ ግንኙነት ያለ በመሆኑ ላይ ምንም ጥርጥር የለም። ፍርዱ ሊመጣ ያለው ከነበረ እንግዲያውስ መገለጡ እና መንግስቱም ሊመጣ ያለው ነበር ማለት ነው። ክርስቶስ በተመለሰበት ጊዜ ክፉዎች ሁሉ ተፈርደው ያኔውኑ ወደ ዘለአለማዊው ሥቃይ ተጥለዋል፣ ያም ደግሞ ሌሎች ክፉዎች ሁሉ በሚሞቱበት ቅጽበት የሚሄዱበት ስፍራ ነው። የሰው ዘር ሁሉ ወኪል የሆነው አዳም በገነት ውስጥ ሳለ ያጣውን ያንን የትንሣኤ ሕይወት፣ ጻድቃን የሆኑ ሁሉ ግን ለመጀመርያ ጊዜ በእግዚአብሔር ሀልዎት ፊት መልሰው ወርሰውታል። የትንሳኤ ህይወት "ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ" (ራእይ 2፥ 7) እንደሚል፣ ገነትን ማስመለስ ነው። የህይወት ዛፍ የሆነው ኢየሱስ የዘላለምን ሕይወት ሰጥቶናል።


  1. እብራውያን 1፥ 13-14 "ነገር ግን ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው [mello] ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?"  [መዳንን ለሚወርሱ ሳይሆን ይወርሱ ዘንድ ላላቸው ነው]


  • ያኔ የክርስቶስ ጠላቶች እነማን ነበሩ? በማቴዎስ 23 "ግብዞች"፣ "የነብያት ገዳዮች ልጆች" ተብለው የተነቀፉ፤ በሉቃስ 19፥ 11-27 "ክፉ ባርያ" ደግሞም "ጠላቶቼ" ያላቸው፤ በሐዋርያት 7፥ 51-53 "አንገተ ደንዳኖች"፣ "ያልተገረዙ"፣ "ተቃዋሚዎች"፣ "አሳዳጆች"፣ "ነፍሰ ገዳዮች"፣ "ሕግን ያልጠበቁ" ተብለው የተወቀሱ፤ በሮሜ 11፥ 28 "የወንጌል ጠላቶች" በሚል መጠሪያ የተገለጡ፤ በፊልጵስዩስ 3፥ 2፣ 18፣ 19 "ውሾች"፣ "ክፉ ሰራተኞች"፣ ብሎም "የመስቀል ጠላቶች" ወዘተ እየተባሉ በግብራቸው የተጠቀሱት አይሁድ ናቸው። እነዚህ የክርስቶስ ጠላቶች የተባሉ ልባቸውን በምድራዊው ነገር ላይ ያደረጉ፣ በሰማያዊውም የተስፋ ቃል ላይ ያመጹ ናቸው። ክርስቶስ ግን የጠላቶቹን ራስ፣ ሞትንም ጭምር ቀጥቅጧል። ለዘላለምም ሁሉን ይገዛ ዘንድ በአባቱ ቀኝ ተቀምጧል፤ ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም። ከውድቀት ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ቅዱሳን ሁሉ በሰማይ ያለውን መዳናቸውን (ቤዛነታቸውን) ይወርሱ ዘንድ አላቸው። አማኞች ይወርሱት ዘንድ ያላቸው መዳን ምን ይሆን? አስቀድሞውኑስ ድነው አልነበርምን? በመላው አዲስ ኪዳን ሞልቶ በሚፈስ ምስክርነት አዎ ደግሞም አይደለም! ብለን ብንመልስ ግር የማይለው ይኖራልን? የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ ሄደው የሚከማቹበት እና ሙሉ የሆነውን ቤዛነታቸውን እየተጠባበቁ የሚቆዩበት ሀደስ የተባለው ስፍራ ያኔ ገና በስራ ላይ ነበር። ኢየሱስ ለመጀመርያው ከፍለዘመን ደቀመዛሙርቱ በሉቃስ 21፥28 ላይ "ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና (እናንተ) አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ" ሲል የተናገራቸውን አስታውሱ። ይህ እንግዲህ ቀደም ሲል ሊሆን ያለው በሚል ለማሳየት የተሞከረው ለአዲስ ሕይወት የመነሳት ትንሳኤ ነው። ይህም በቅበት አይን ሊለወጡ ያለበት፣ ሞትም ድል በመነሳት ሊዋጥ ያለበት፣ የሚሞተውም የማይሞተውን ሊለብስ ያለበት፣ ፍጥረታዊው ሆኖ የሚታየውም መንፈሳዊ ሆኖ ሊነሳ ያለበት የ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ፍጻሜ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሞት አያሸንፍም፣ መውጊያም ደግሞ የለውም፤ ብንሞትም ህያዋን ነን፣ ህያዋንም ከሆንን ፈጽሞ አንሞትም! ልንል እንችላለን። ያለ ትንሳኤ ይህንን ለራሳችን ማድረግ አንችልም፣ ስለዚህ ሁላችንም በምንሞትበት ጊዜ በቀጥታ ወደ ሰማይ ሳይሆን በተቃራኒው ገና የወደፊቱን የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት ልንጠባበቅ ወደሀደስ እንሄዳለን ማለት ነው፤ ይህ ግን በእግዚአብሔር ቃል ላይ መዋሸት ይሆናል። ትንሳኤ ገና ወደፊት እንጂ ከአሁን በፊት አልሆነም ብለው የሚያምኑ መጻኢያን አስተማሪዎች፣ ያኔ በመጀመርያው ክፍለዘመን እንደሚሆንና ሊሆን እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የተናገረለት ያ ትንሳኤ ገና ሳይሆንና ያም ፍርድ እስካሁን ሳይፈጸም በፊት፣ አማኞች አሁን በሚሞቱበት ጊዜ የትንሳኤን ቀን ሊጠባበቁ ሁሉም ወደ ሀደስ የሚሄዱ ስለሆነ፣ ወደሰማይ እንደሚሄዱ አድርገው የሚያስተምሩትንና ምዕመናንን የሚዋሹትን ነገር ፈጽሞ ማቆም አለባቸው።


  1. እብራውያን 2፥ 5 " ስለ እርሱ የምንናገርበትን የሚመጣውን [ሊመጣ ያለውን mello] ዓለም ለመላእክት ያስገዛው አይደለምና።" [የሚመጣው ዓለም/ ዘመን ሳይሆን ሊመጣ ያለው ዓለም /ዘመን ነው]


  • እዚህ ላይ ጸሐፊው ለመላእክት ተገዝቶ የነበረውን ዓለም አንስቶ ይነጋገራል።  ለመላእክት ተገዝቶ ከነበረው አለም (ይህም የሙሴ ዘመን ነው) ጋር ይህ እንዴት ይነጻጸራል? በሐዋርያት 7፥ 51-53 "አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ" የተባሉትን ተመልከቱ። ነብያትን እያሳደዱ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የነገሩአቸውን ይገድሉ እንደነበረው ሁሉ አይሁድም ልክ አባቶቻቸው ያደርጉ እንደነበረው አይነት አይሁድም መንፈስ ቅዱስን ይቃወሙ ነበር (ማቴዎስ 23 ተመልከት)። ሕጉን በመላእክት ትእዛዝ የተቀበሉ ቢሆኑም እንኳ ዳሩ ግን አልጠበቁትም፣ ይልቁንም በክፋታቸው ብሰው ነፍሰ ገዳዮችና አሳልፈው የሚሰጡ ከሃዲዎች ሆኑ። አሮጌው ኪዳን በመላእክት ትእዛዝ የመጣ ነበር፣ ይመጣ ዘንድ ያለው አዲሱ ግን ለኢየሱስ እንጂ "ለመላእክት የሚገዛ" አይደለም። የዚህ መልእክት ጸሐፊ ለመጀመርያው ከፍለዘመን ተደራስያኑ "ስለምንነጋገርበት" ብሎ መጻፉን ልብ አድርጉ። የ70ው አ.ም ፍርድ ገና የተከናወነ ባለመሆኑ፣ ይነጋገሩታል እንጂ ያኔ ሁሉም ነገር በኢየሱስ የተገዛ እንደነበር ገና አላዩም።


  1. እብራውያን 6፥ 5 "መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን [mello] የዓለም ኃይል የቀመሱትን" [ሊመጣ ያለው እንጂ የሚመጣው አይደለም]


  • ከክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በፊት የነበረው የጥንት ቤተክርስቲያን ዘመን፣ እርሱም ከበአለ ሃምሳ እስከ 70 አ.ም ያለው የአርባ አመታት የሽግግር ወቅት፣ በሙላት ሊገለጥ ያለውንና "ሊመጣ ያለውን [mello] የዓለም ኃይል" የተለማመዱበት የቅምሻ ወቅት ነበር። በሽግግሩ ወቅት በቅምሻ ደረጃ የተለማመዱት ሊመጣ ያለው የዓለም ኃይል በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በሙላት ተገልጧል። የእግዚአብሔርን ቃል እንደተጻፈ ብናምን አሁን እኛ በዚያ የአዲሱ አለም ኃይል ውስጥ እርሱም በአዲሱ ኪዳን ውስጥ እንኖራለን።


  1. እብራውያን 9፥ 11 "ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው [mello] መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥" [ለሚመጣው መልካም ነገር ሳይሆን ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ነው]


  • ይህ በዚያን ዘመን ከነበረው ቤተመቅደስና ከእርሱ ጋር ግንኙነት ካላቸው ነገሮች ጋር ግልጽ የሆነ ተቃርኖ ነው። እንዲህ ያለው ንጽጽርና ተቃርኖ የእብራውያን መልዕክት አንዱ ገጽታ መሆኑን ለማስተዋል እብራውያን 8፥ 6-13፤ 9፥ 8-12፣ 15 ይነበብ። ይህ መልዕክት በሚጻፍበት ጊዜ ምድራዊው ቤተመቅደስ ገና በስፍራው ቆሞ ሳለ ሊቀ ካህናቱ ክርስቶስ በሰማያት ካለችው እውነተኛይቱ ቅድስት ወጥቶ ገና አልታየም ነበር። በብሉይ ኪዳን ሊቀካህናቱ የእንስሳውን መስዋእት ካቀረበ በኋላ በዚያ የስርየት ቀን ደሙን ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል። ሊቀ ካህኑም ከቅድስተ ቅዱሳን ወጥቶ ወደ ህዝቡ ወደ አውደምህረቱ ሲመጣ ያኔ ዋናውና ትክክለኛው የስርየት አዋጅ ይገለጣል። እግዚአብሔር ስለኃጢአት ስርየት የቀረበውን መስዋእት ተቀብሎ የህዝቡን መተላለፍ ይቅር እንዳለ አይነተኛ ማረጋገጫው የሊቀ ካህኑ ከቅድስተ ቅዱሳን ወጥቶ መታየቱ ነው (ዘሌዋውያን 16፥ 16-18)። ነገር ግን የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ሊያስወግድ አይችልም (እብራውያን 10፥ 4)። ኢየሱስ ግን ሊያስተሰርይ ከገባበት ቅድስት በዳግመኛ ምጽአቱ ወጥቶ የመጣ በመሆኑ አሁን መዳናችን ፍጹም ሆኖአል፤ ስለዚህም እርሱ ምርጦቹን ሁሉ በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ክብር፣ ወደ ሀልዎቱ አምጥቷቸዋል።  ጳውሎስ፣ በመጀመርያው ከፍለዘመን የ70 አ.ም ዳግመኛ ምጽአቱ ላይ፣ ያኔ አዲሱ ኪዳን በሙላት ተጠናቆ ሲገለጥ፣ "እስራኤል ሁሉ (በልባቸው የተገረዙ መንፈሳዊው እስራኤል) ይድናል" ሲል ሊተነበይ የተቻለውም ለዚህ ነው። ስለዚህ ነው እኛም በሮሜ 11፥ 5፣ 25-29 እንደተጻፈ ቤተመቅደሱ በወደመበት ጊዜ በሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ በስጋ እስራኤል የሆኑ ሁሉም የተመረጡቱ ድነዋል የምንለው፣ (እብራውያን 9፥ 15፣ 28 ተመልከት)። የሐዋርያው ጳውሎስ "እስራኤል ሁሉ ይድናል" እና የነብዩ ዳንኤል "በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።" የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጽሟል። አብርሃም ሲጠብቃት የነበረውን "እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማም" (እብራውያን 11፥ 10) ክርስቶስ በመምጣቱ አምጥቷታል። ክርስቶስ ስላመጣው ነገር የሚበልጠውና እና ፍጹም የነበረው ምን ነበር? አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለዘላለም ኃጢአትን ማስወገዱ ነው። ከዚያም ወዲያ ኩነኔ የለም (ሮሜ 8- ሞት)፣ ከእግዚአብሔር ሀልዎት መነጠልም (ሮሜ 8- ሀደስ) የለም! ታዲያ ብዙዎች እነርሱ ለገዛ ራሳቸው ፈጽሞ የማይመኙትን ጉዳይ ይኸውም ሞትና ኩነኔን፣ ከእግዚአብሔርም ሀልዎት ተነጥሎ በሀደስ መሆንን ለአብርሃምና ለሌሎች የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ለምን ይናፍቁላቸዋል? ምጽአቱ እስካሁን አልሆነም የሚለው የመጻኢያን ትምህርት አብርሃምንና በእቅፉ ያሉትን ልጆቹን ከእግዚአብሔር ሀልዎት አርቆ፣ ሲናፍቋት ከነበረው ከተማ አርቆ በሀደስ ውስጥ ገና አሁንም ለሺህዎች ዘመናት ይረሳቸዋል። እነርሱ ግን የተስፋውን ቃል በሩቅ እያዩ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች ሆነው ራሳቸውን በባዕድ አገር እንደሚኖሩ አድርገው ይቆጥሩና ይጠባበቁ ነበር። የሚሻል ሰማያዊ አገርም ይናፍቁ ነበር። ያ የሚናፍቁት ደርሶላቸዋል። ከዚያን ጊዝ ጀምሮ ሁሉም የእግዚአብሔር ምርጦች ሞት አይገዛቸውም፣ ኩነኔም የለባቸውም፤ ሀደስ አያስፈራቸውም፣ ከእግዚአብሔር ሕይወትና ሀልዎት የመነጠል ስጋት የለባቸውም። እኛ የዳንን በምንሞትበት ጊዜ ይህንን ሰውነታችንን አውልቀን ጥለን በምንቀበለውና በተዘጋጀልን አዲስና መንፈሳዊ በሆነው የማይሞት አካል በሰማያት ከእግዚአብሔር ጋር እንደምንሆን በጽኑ አምናለሁ።


  1. እብራውያን 10፥ 1 "ሕጉ ሊመጣ ያለው [mello] የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም።" " [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]


  • የእብራውያን ጸሐፊ የአይሁድን ህዝብ ሊያስታውሳቸው የሚፈልገው በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጻሜውን ሊያገኝ ያለውን የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ነው። "ጥላ" የተባለውም በቅርቡ "ሊመጣ ባለው በጎ ነገር" ሊተካ ያለው ሕጉ ነው።


  1. እብራውያን 10፥ 26፣ 27 "የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው [mello] የእሳት ብርታት አለ።" [የሚበላው ሳይሆን ሊበላ ያለው ነው]


  • ይህ ለነዚያ የለክርስቶስ ሆነው ለቀሩ ሁሉ በክርስቶስ ጠላቶች ላይ ሊደርስባቸው ስላለው የያኔው ፍርድ  የተሰጠ ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ነው። ስለዚህ መልእክቱ በዘመኑ የነበሩትን አይሁድ ከያዙት የጥፋት ጎዳና ዘወር ብለው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመለሱ ማስጠንቀቅ ነው፣ አለበለዚያ እየመጣ ያለውና ሊገናኛቸው የተዘጋጀው የእግዚአብሔር ቁጣ ይበላቸዋል። እብራውያን 10፥ 25-39 ያለው ምንባብ በአውዱ ቢነበብ የተሻለ ነው።


  1. እብራውያን 13፥ 14 "በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን [mello] እንፈልጋለን።" [ትመጣ ዘንድ ያላትን እንጂ የምትመጣዋን አይደለም]


  • እብራውያን 11 እና የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ይጠባበቁት የነበረውን ጉዳይ አነጻጽሩት፤ ይህ ጥቅስ በግልጽ የሚናገረው ስለ የአዲሲቷ ኢየሩሳሌም ነው እዚህም ላይ በአሮጌዋ ኢየሩሳሌም (ያረጀ፣ አሮጌ፣ ውራጅ፣ ያኔ ሊጠፋ የቀረበ፣ ሊመጣ ላለውም ነገር ጥላ የሆነው -እብራውያን 8) እና ትመጣ ዘንድ ባላት በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም (እብራውያን 11፥ 16፤ ራእይ 21፥ 1-7፣ 9-10) መካከል ያለውን ንጽጽርና ተቃርኖ እናያለን። አሮጌዋ ኢየሩሳሌም ፈጽሞ ተደምስሳ ከተወገደችና ውራጅ ሆና ከጠፋች በኋላ 

  • አዲሲቱ ትገለጣለች።


  1. 1ጴጥሮስ 5፥ 1 "እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው [mello] ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤" [ሊገለጥ ካለው ክብር እንጂ ከሚገለጠው አይደለም]


  • ይህ ጉዳይ የሚሆነው በዚያን ዘመን፣ በእነዚያ ቀናት ለነበሩ ሰዎች ነው። ጴጥሮስ ሊገለጥ ያለ ክብር እየመጣ መሆኑን ተረድቷል። በእግዚአብሔር መንፈስ እየተነዳና በመጨረሻው ዘመን ላይ መሆኑን እያወቅ  የሚጽፍ መሆኑን ልብ አድርጉ (1ጴጥሮስ 1፥ 4-13፣ 20፤ 2፥ 6-8፤ 4፥ 7 በጥንቃቄ ይነበብ)። በምዕራፍ 4፥ 13 ላይ ጴጥሮስ አስቀድሞ በመልዕክቱ እነዚያ የመጀመርያው ክፍለዘመን አንባቢዎቹን ሊመጣ ያለው ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ሐሴት አድርገው ደስ እንደሚላቸው ጽፎላቸው እንደነበር አስታውሱ።


  1. ያዕቆብ 2፥ 12 "በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው [mello] ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ።" [ፍርድን እንደሚቀበሉ ሳይሆን ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ነው]


  • የያዕቆብ መልዕክት ተደራስያን "የተበተኑ አስራ ሁለቱ ወገኖች" ማለትም ዳያስፖራው የአይሁድ ክርስቲያን ወገን ነው። ጥቅሱም የሚያወራው ያኔ ለእነርሱ ቀርቦ ስለነበር ፍርድ ነው። ሕጉም ያላቸውና በሕጉ የሚፈረድላቸውና የሚፈረድባቸው እነርሱው ናቸው፣ እንጂ ሕጉ የሌላቸውን ያለ ሕግ የሚፈረድባቸውና የሚፈረድላቸው አህዛብ ክርስቲያኖች አይደሉም። አይሁድም ያንን ፍርድና ዳኝነት የሚቀበሉበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ንግግሩ ያሳያል። ይኸውም በ70 እ.ም የተፈጸመ ሲሆን ሕጉ ሳላቸው ለሕጉ ባለመታዘዝ ክርስቶስን ያላመኑትን ሁሉ እንደ ሕጉ ፈርዶ ሲያጠፋቸው፤ ሕጉ የመሰከረለትን በክርስቶስ የማመን ነጻነትን ተቀብለው የዳኑትን ትሩፋን ግን ፈርዶላቸዋል።


  1. ራእይ 1፥ 19 "እንግዲህ ያየኸውን (ራእይ 1፥ 9-20) አሁንም ያለውን (ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተላከው ደብዳቤ ይዘት ራእይ 2፥ 1-3፥ 22) ከዚህም በኋላ (ራእይ 4፥ 1-22፥ 5) ይሆን ዘንድ ያለውን [mello] ጻፍ።" [የሚሆነውን ሳይሆን ይሆን ዘንድ ያለውን ነው]


  • የራእዩ መጽሐፍ የያዛቸው ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ይህ "ይሆን ዘንድ ያለው" በሚል የተገለጸው የመጨረሻ ክፍል በዮሐንስ ትውልድ ውስጥ ሊከናወን መሆኑን ልብ በሉ። ይህንን የሚናገረው ኢየሱስ ነው፣ ጻፍ ብሎ ትዕዛዝ የሚሰጠውም በመጀመርያው ከፍለዘመን ላይ ይኖር ለነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ነው። ይህ "ከዚህ በኋላ ይሆን ዘንድ ያለው" በሚል የተጠቀሱት  ጉዳዮች ይፈጸማሉ ተብሎ በግልጽ ጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸውና የተነገሩት ለመቼ ነው? ከተባለ ቶሎ፣ በቅርቡ፣ በቶሎ (ራእይ 1፥ 1፣ 3፤ 22፥ 6፣ 7፣ 12፣ 20) ነው፤ ይህም ያኔ ዮሐንስ ይኖርበት ለነበረው ዘመን ቅርብ የሆነ ጊዜ ማለት ነው (ራእይ 1፥ 3፤ 22፥ 10)። እነዚህ ቃሎች በውስጣቸው የፍጥነትን እና የችኮላን ሃሳብ የያዙ ሲሆን፣ በጥቅሉ ይሆናሉ የተባሉት አይቀሬ ጉዳዮች ለፍጻሜአቸው የማይዘገዩና በዘመኑም ይህንን ለሰሙ በኩረ ተደራስያኑ "ጊዜ የለም" የሚል መልዕክት አላቸው። በግልጽ ቋንቋ የተነገሩትን እነዚህን አይቀሬ ንግግሮች እንዳለ እንደተጻፈው ከመቀበል ይልቅ፤ መካድ፣ ማሻሻል፣ ማስተባበልም ሆነ ለገዛ ራሳችን አስተምህሮ ትክክለኛነት ተጨንቀን "አይ እንዲህ ሊል ፈልጎ ነው" ብሎ ለቃሉ እርማት ለመስጠት የሚደረግ ሙከራና ማብራርያ ሁሉ፣ በማያምነው አለም ፊት ኢየሱስን ሐሰተኛ ነብይ፣ ሐዋርያቱንም ሐሰተኛ መምህራን፣ ክርስትናችንንም ሐሰተኛ ኃይማኖት ያደርጋቸዋል። ቅዱሳን ወንድሞቼ ሆይ፣ ቃሎቹ በያዙት አይቀሬነትና ጊዜ ጠቋሚነት ተስፋ ቆርጣችሁ፣ እነዚህ ንግግሮች ላይ 2ኛ ጴጥሮስ 2፥ 8 ላይ ያለውን ቃል ያለቦታው እየጠቀሳችሁ፣ ይግባኝ በማለት እንዲሰረዙላችሁ ወይም ቃሎቹ የሌሉ ያህል ወደ ጎን እንዲተውላችሁ አታስቡት፤ እግዚአብሔር ተናግሯቸዋልና የሚያድነን፣ የሚያቆመንና የሚያጸናን በተጻፈው እውነት አንጻር መጎንበስ ብቻ ነው እንጂ፤ አይቀሬነትን የያዙትን እነዚህን መግለጫዎች በራሳችን መንገድ ለማብራራት መሞከር ፈጽሞ የለብንም።


  1. ራእይ 3፥ 10 "የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው [mello] ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።"" [ከሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ካለው ነው]


  • "ዓለም ሁሉ" የሚለው መላውን የሮምን ግዛት ያመለክታል (ሉቃስ 2፥ 1) ፈተናውን ግዛቱን የሚያናውጥ ፈተና ነው። እንዲሁም በምድሪቱ በእስራኤል ነዋሪዎች ላይ ስለሚከሰት ፈተና እርሱም "ታላቁ መከራ"  የተነገረ ቃል ነው። በ 68 አ.ም ላይ የኔሮን ሞት ተከትሎ በ70 አ.ም ቨስፓስያን የሮም ንጉሰ ነገስት እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ በሚቀሰቀስ የሮም የእርስ በርስ ጦርነት በመላው የሮም አለም ላይ ነውጥ ይኖራል፣ ይህም በተለይ አይሁድን ጭንቅ ውስጥ ይከታቸዋል። ጌታ የሚናገርለት የተለየ አለምአቀፋዊ ፈተና ይህ ነውና ይህ የፈተና ጊዜ የፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን በነበረችበት ዘመን እና ስፍራም የሚኖር "ሊመጣ ያለው [mello]" ፈተና ነው። ጌታም ይህችን የፊላደልፍያ ቤተክርስቲያን ለመጠበቅ የሰጠው ተስፋ ሊፈጸም የሚችለውና የሚፈጸመው በዚያው በቤተክርስቲያኒቱ ዘመን ነው።


  1. ራእይ 12፥ 5 "አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን [mello] ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።" [የሚገዛቸውን ሳይሆን ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ነው]


  • አማርኛው መጽሐፍ ቅዱሳችን "ይገዛቸው ዘንድ ያለውን" በማለት የግሪኩን mello በአግባቡ  አስፍሮታል። "ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።" (ዮሐንስ 3፥ 13)፣ እንደተባለ ሁሉን ሊገዛ በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ዙፋን የተነጠቀው ልጁ  ኢየሱስ ብቻ ነው። እርሱም እንደ ዮሐንስ ራእይ ገለጻ "አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለው" የተባለለት የእግዚአብሔር ወንድ ልጅ ነው። አገዛዙም የሚጀምረው ቀያፋ በነበረበት የሕይወት ዘመኑ፣ ኢየሱስ ሁሉን ሊገዛ "በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ" ይህንን ለማየት (ማቴዎስ 26፥ 64) የተነገረው ቃል ፍጻሜ ላይ ነው።



አንዲት አነስተኛ የምትመስል ቃል በአረፍተ ነገር ትርጉም ውስጥ ያላትን ቦታና ዋጋ አሳንሶ፣ በበኩረ ቋንቋው ውስጥ ያላትን ጠቀሜታ ሳይረዱ ለመተርጎም መሞከር፣ በእውነትም ከፍ ላለ የአስተምህሮ ህጸጽ ይዳርጋል። በዚህች አንዲት የግሪክ ቃል ላይ የተሰራ መቀባባትም ሆነ ማድበስበስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የዳግመኛ ምጽአቱን አይቀሬነት የሚያመለክቱ እና፣ ከፍተኛ ጠቀሜታና ትርጉም ያላቸውን፣ ለምሳሌ እንደ "ቅርብ ነው"፣ "በደጅ ቆሟል"፣ "ፈጥኖ"፣ "ቶሎ"፣ "ቶሎ የሚሆነውን"፣ "ይህ ትውልድ አያልፍም" ወዘተ የመሳሰሉትን ቃላትና ሀርጎች አሁንም ገና ካልታወቁ ሺህዎች አመታት በኋላ ወደፊት በማናቸውም ጊዜ ሊሆኑ እንደሚችሉ አድርጎ በመውሰድ የሚያስከትለው የትርጉም ስህተት ጉልህ ከመሆኑም በላይ፣ አድካሚና የሌለ ነገር መጠበቅም ይሆናል። እነዚህ ሊሆኑ ያሉ (Mello) ነገሮችን የሚያመለክቱ ሀረጎች እና አረፍተ ነገሮች እንድናምናቸውና እንድንታዘዛቸው በቀጥታ የተሰጡትና የተነገሩት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ በኢየሱስ፣ በሐዋርያቱና በአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ሆኖ ሳለ፣ የተያዝንበትን የኖረ አመለካከታችንንና የእምነት አቋማችንን ለማጽደቅ በሚሆን ግብዝነት ቃሉ ላይ አንዳች በመጨመር ወይም ከቃሉ አንዳች በማጉደል 'አይ የለም እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው' በሚል እግዚአብሔርን እና ቃሉን ለማረም የምናደርገው ጥምዘዛና ሙከራ ሁሉ በእውነትም በደል ነው (ዘዳግም 4፥ 2)። ቃሉ የማይለውን ወይም ሊል ያልፈለገውን እንዲል ልናስገድደው፣ ያለውንም ከማመን በቀር አላልክም ብለን ልንሸነግለው፣ ወይም ያለውን አይ እንዲህ ሊል ፈልጎ ነው ብለን ልንዋሸውና ልናታልለው ምንም መብት የለንም። ስለዚህ፣ በእውነት የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ያሉትን ነገር በእርግጥ የምራቸውን ብለውታልን? እነዚህስ ነገሮች በ70 አ.ም ላይ ተፈጽመዋልን? ለዚህ ጥያቄ ኃላፋውያን መልሳቸው ፍርጥም ያለ "አዎ"! ሲሆን፣ መጻኢያን ግን በመልሳቸው ሽምጥት አድርገው "አይደለም"! ይላሉ ።


አንድ ሰው በዚህ Mello በተሰኘ ቃል ጠቀሜታ ላይ ያፈጠጠውን እውነታ፣ እርሱም ለመጀመርያው ከፍለዘመን ቤተክርስቲያን መጨረሻው ሊደርስ እንደሆነ ትርጉም ይሰጣቸው የነበረውን የጉዳዩን እርግጠኝነት እና አይቀሬነት  ለመቀበል ቢያቅማማ እንኳን፣ የጌታን መመለስ እርግጠኝነቱና አይቀሬነቱ ቃሉ በተነገረበት አውድና ትውልድ ወቅት በቅርቡ ተፈጻሚ እንደሚሆን የሚያሳዩ ሌሎች ከፍ ሲል የጠቀስናቸው እንደ "ቅርብ ነው"፣ "በደጅ ቆሟል"፣ "ፈጥኖ"፣ "ቶሎ" "ቶሎ የሚሆነውን"፣ "ይህ ትውልድ አያልፍም" ወዘተ የመሳሰሉ ቃላትና ሀረጎችን ምን አድርጎ ሊያስተባብላቸው ይችላል? ተመልከቱ፣ መጻኢያን እነዚህን ከዮሐንስ ራእይ የተወሰዱትን ቃላትና ሀረጎች ሲተረጉሙ፣ "ትንቢቱና ራእዩ እስካሁን ድረስ ገና አልተፈጸመም ዳሩ ግን አንዴ መፈጸም ከጀመረ ቶሎ ቶሎ ይሚፈጸም መሆኑን ያመለክታሉ" ይላሉ፤ ከማቴዎስ 24 የተወሰደውንም "ይህ ትውልድ አያልፍም" የሚለውን "የእስራኤል መንግስት እንደገና መቋቋሙን በአይኑ የሚያየው ትውልድ ጌታ እስኪመጣ ድረስ የሚቆየው ትውልድ ነው" ሲሉ ይተረጉማሉ። ይህ ግን ቃሉ የማይለውን እንዲል መጠምዘዝ ነው። በመጀመርያው ከፍለዘመን ላይ ተመልሶ እንደሚመጣ የተናገረው የኢየሱስ ቃል በትክክል ያኔውኑ እርሱ እንደተናገረው ሆኗል ብለን ለማመን ግን በብዙ ማስረጃ ምስክር የምንጠራው ራሱን የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ነው (ለምሳሌ፣ ማቴዎስ 24፥ 33-34፤ ማቴዎስ። 10፥ 23፤ ማቴዎስ 16፥ 27-28፤ ያዕቆብ 5፥ 8-9፤ ራእይ። 1፥ 1፤ ራእይ 22፥ 7) 


በሦስተኛው መቶ ከፍለዘመን መገባደጃ ላይ የክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ኢውሳብዮስ የተናገረውን ልጥቀስ፤ የጌታ ወንድም ስለነበረው ስለ ያዕቆብ የጻፈው ይህ ነበር፣ ያእቆብ ተከሶ ከአይሁድ መሪዎች ጋር በተከራከረ ጊዜ "እርሱም (ያእቆብ) ድምጹን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፣ 'ኢየሱስን የሰው ልጅ ነው ብዬ እንዳከብረው ብቻ ለምን ትጠይቁኛላችሁ? እርሱ አሁን በታላቁ ኃይል ቀኝ በሰማያት ተቀምጧል፣ በሰማያት ደመናም ይመጣ ዘንድ አለው' ሲል ተናገራቸው" ይላል፤ (Eusebius Ecclesiastical History p. 77 ተመልከቱ)። የኃላፋውያን ምልከታ ከቅዱሳት መጻህፍት ጋር የሚስማማ ነው፤ የትርጉም ፍሰቱም ቀዋሚነትን ጠብቆ ከቃሉ ጋር አብሮ የሚፈስ ነው። አቋማችንም ከሁሉ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ይተርጎም የሚል ነው።  የግሪክ ቃላትንና አንዳንድ ታሪክ አዋቂዎችን ስፈትሹና ስተመልከቱ ያኔ የኃላፋውያን አቋምና አቋቋም በየትኛውም የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ላይ ጠንካራና አስተማማኝ መከላከያ እንዳለው ታያላችሁ። ከፍ ሲል በዝርዝር ባቀረብኳቸው ምንባባት አንጻር መጻኢያን ራሳቸውንና ትምህርታቸውን እንዴት መመከትና መከላከል እንደሚቻላቸው አላውቅም። የቃሉ ተማሪዎች ነን ካልን ግን "የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነን፥ የተፈተነውን ራሳችንን ለእግዚአብሔር ልናቀርብ ልንተጋ።" (2ጢሞቴዎስ 2፥ 15) ይገባናል እንጂ በቅጡ ባላጠናነውና ባላሰብንበት ርዕሰ ጉዳይ ቀደዳ ልናበዛ አይገባንም።


በዚህች አንዲት የግሪክ ቃል ላይ ሲሰራ የኖረውን ስህተት ለማረም በሚሆን ሰበብ ግን ትዕቢተኛና ተጨቃጫቂ የመሆን ፍላጎት የለኝም፤ ነገር ግን ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻችን እና በአስተምህሯችን ውስጥ በአግባቡ እንዲቀመጥና ዋጋ እንዲሰጠው መስራት እንዳለብን አምናለሁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ በተለቀሙ ቃሎች፣ ሀረጎች እና ቋንቋዎች ላይ፣ ተገቢ ትርጓሜአቸውን እና ጠቀሜታቸውን ከማጣጣምና ከመማማር ባለፈ፣ እጅግ በበዛ የወግ አጥባቂነት አጽንዖት ተይዘው ክርክር የሚመቻቸው ሰዎችንም ሳይ መንገዴን ቀይሬ እሄዳለሁ እንጂ "ይዋጣልን" የምል አይደለሁም። ምክንያቱም ደጋግሜ ለማየት እንደታደልሁት እንዲህ ያሉ ጉንጭ አልፋ አድካሚ እሰጥ እገባዎች መጽናናት የሞላባቸውን ቅዱሳት መጻህፍት ያላቸውን ንጹህና ግልጽ ትምህርት አግኝቶ ከመታነጽና ከመተናነጽ ይልቅ ግልጽና ንጹህ የሆነውን ሌላውን የቅዱሳት መጻህፍት ትምህርት የሚደፈጥጡ ወይም ዋጋ የሚያሳጡ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ኪሳራ የሞላበት እንዲህ ያለው መታለል ድርሻዬና እድል ፈንታዬ እንዲሆንም አልፈቅድለትም። ለምሳሌ፣ በአሽከርካሪ የመንገድ ላይ ስርአትና ደንብ የተቀመጠው "ቁም" /STOP/ የተሰኘውን አስገዳጅ ምልክት ያየ አሽከርካሪ፣ "ቁም ማለት በእግርህ ቁም /STAND UP/ ማለት ነው" ብሎ በመተርጎም ከገገመና ከተሽከርካሪው ወጥቶ በእግሩ ሊቆም ከወደደ፣ "ስራህ ያውጣህ" ብዬ ከመተው በቀር ምን አድርጌ ላርመው እችላለሁ?። ልክ በዚሁ አይነት ብዙዎች የመጻኢነትን ነገረ ፍጻሜ የሚያቀነቅኑ መምህራን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ላሉ አንድንድ ወሳኝ ቃላት የሚሰጡት ትርጉም ቃሉ የማይለውን ሌላ ነገር እያስነበበን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ልንማማርና ልንደማመጥ ካልቻልን በቀር እንዲህ አይነቱ ጭቅጭቅ በሚፈጥረው ስሜት ወንድሞቼን ማጣት ግን ስለማልመኘው እየታዘብኩ ለማለፍ እገደዳለሁ።


በመጨረሻም፣ ወንጌል አማኝ ለሆኑቱ የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ተስፋም ጸሎትም ያለኝ መሆኑን አልሸሽግም። ከሁሉ አስቀድሞ፣ በተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉ መጻኢያን ወንድሞቼና እህቶቼ የትኛውንም የነገረ ፍጻሜአዊ ጎራ ተተግነውና ያላቸውን የነገረ ፍጻሜ አቋም ይዘው ከዘመን መዳብያን (Dispensationalism) አስተምህሮም ሆነ ከየትኛውም የለዘብተኛው ስነ መለኮት 'ክህደትና' የዘመነኛው ኒዎ ጰንጠቆስጤ 'እብደት' እምነታቸውን መከላከል እንደማይችሉ ይህን አንድ ነገር ሊያውቁ ይገባል። ምክንያቱም የሚከተሉት የነገረ ፍጻሜ ትምህሮታቸው ክህደትን የሚያሾልክ አንዳች ቀዳዳ ነገር አለበት። "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" ብለው መቆም የሚፈልጉ የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ኃላፋዊነትን ከመቀበልና ነገረ ፍጻሜአዊ አስተምህሮአቸውን ከመከለስና ከማረም ውጭ ቀዳዳቸውን የሚከድን ሌላ ምንም አማራጭ የላቸውም። ሙሉ ኃላፋዊነትን ከተቀበሉ ብቻ የተሃድሶው ቤተ እምነት ብቸኛ ጡንቻ የሆነው "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" የሚለው ታሪካዊው አቋማቸው ከማንኛውም የተሳሳተ ኃይማኖት እምነታቸውን መከላከል የሚችሉበት መሰረት ይሰጣቸዋል። ደርዝ ባለው አስተሳሰብ በቅንነት እምነታቸውን የሚጠይቁ፣ በትህትናም የቃሉ ተማሪ ለመሆን የሚወዱና ኃላፋዊነትን የሚቀበሉ የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ልዩነትን ማድረግ ይችላሉ። ዘመነኛው ክርስትና ለዛውን ከማጣት፣ ተረት ተረት ሆኖ እንደ ኃሰተኛ ኃይማኖት፣ ሴክትና ከልት መስሎ ከመቆጠር የሚታደገው ብቸኛ ተስፋው ወንጌላዊ መሰረት ያለውን ሙሉ ኃላፋዊነትን መቀበል ብቻ ነው።


ማንበብ ለምትወዱ ተዛማጅ የሆኑ የፕሪቴሪዝም ጽሁፎቼን ላጋራችሁ፦

http://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/blog-post.html?m=1

http://gizachewkr.blogspot.com/2020/01/blog-post.html?m=1


ቸር ያሰማን፣ ቸር ያሰንብተን!!

ግዛቸው ከበደ \ቄስ\