አዲሲቱ ኢየሩሳሌም
"አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።" ራእይ 21፥ 1-4
"ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም። ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር። አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፥ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤ በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፥ የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ። ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።" ራእይ 21፥ 22-27
ራእይ 21 ላይ ያለውን ይህንን ምንባብ በቁሙ የሚተረጉሙ (literalist) እና በመጻኢነት ነገረ ፍጻሜ ቅኝት የሚረዱት በርካታ ክርስቲያኖች ናቸው። ስለዚህም አዲሱ ሰማይና ምድር ሆነ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለእነርሱ ወደፊት በሺሁ አመት ማብቂያ ላይ ወይም በዳግመኛ ምጽአት ጊዜ የሚፈጠር አዲስ ፕላኔት እና ዩኒቨርስ፣ በአዲሱ ፕላኔት ላይም የምትሰራ አዲስ ከተማ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ጉዳዩ ግን እንደእርሱ አይደለም። መንፈሳዊውን ነገር በመንፈስ ማስተዋልና መረዳት ያስፈልጋል። ይህ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ግን ጳውሎስ "አዲስ ፍጥረት" (2ቆሮንቶስ 5፥17) ሲል የሚጠራውን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ኪዳን በማድረግ በክርስቶስ በኩል ወደ አዲስ ኪዳን ህብረት የገቡትን የሚወክል መጠርያ ነው። አሮጌው ሰማይና አሮጌው ምድር ደግሞ ያለፈውንና የተሻረውን አሮጌ ኪዳን ይወክላል። አዲሲቱ ኢየሩሳሌምም በቅድስተ ቅዱሳን መልክና ስዕል የቀረበች ራስዋን ቤተክርስቲያንን የበጉን ሙሽራ ናት፤ በዚያም፣ ማለትም በአሁኑ የምድራዊ ህይወት አኗኗር የእግዚአብሔር መቅደስ በሰዎች መካከል የመሆኑን እውነታ ያሳያል።
አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ሁሉም የእግዚአብሔር ሕዝቦች፣ አሁንና ከሞት ወዲያ ማዶ ለዘላለም የሚኖሩባት ሰማያዊት ወመንፈሳዊት መኖርያቸው ናት። በነጻነት የምትኖረው የነጻነት ከተማ ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም እናታችን ናት (ገላትያ 4፥ 26) ሲል ጳውሎስ ያስተዋውቀናል። ጳውሎስ በመዝሙር 87 ላይ ስለ እግዚአብሔር ከተማ የተዘመረውን መዝሙር የሚያመለክት ይመስላል። መዝሙሩም በአዲሱ መደበኛ ትርጉም፦
"መሠረቱን በተቀደሱ ተራሮች አቆመ፤ እግዚአብሔር ከያዕቆብ ማደሪያዎች ሁሉ ይልቅ፣ የጽዮንን ደጆች ይወዳል። የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፤ ስለ አንቺ ክቡር የሆነ ነገር እንዲህ ተብሎ ይነገራል፤ “ከሚያውቁኝ መካከል፣ ረዓብንና ባቢሎንን እጠቅሳለሁ፤ እነሆ፤ ፍልስጥኤምና ጢሮስ ከኢትዮጵያ ጋር፣ ‘ይህ ሰው በዚያ ነው የተወለደው’ ይላሉ።” በእርግጥም ስለ ጽዮን፣ “ይህም ያም ሰው በእርሷ ውስጥ ተወለዱ፤ ልዑልም ራሱ ያጸናታል” ይባላል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ሲመዘግብ፣ “ይህ ሰው የተወለደው በዚያ ነው” ብሎ ይጽፋል። የሚያዜሙም መሣሪያ የሚጫወቱም፣ “ምንጩ ሁሉ በአንቺ ውስጥ ይገኛል” ይላሉ።" የሚል ነው።
በእርስዋ ያልተወለዱና ልጆችዋ ለመሆን ያልታደሉ ፈጽሞ አያውቋትም፤ በወንጌሉ ጸጋ በቅዱስ ጥምቀት በእርስዋ የተወለዱ ብቻ ግን "እናታችን ጽዮን" (የድሮው ትርጉም) ሲሉ ይጠሯታል። እርስዋም በቅድስና ተራሮች ላይ ከፍ ብላ የተሰራች አይነ ግቡ ከተማ ናት። የጽዮን ደጆች ሲል እግዚአብሔር በህዝቡ መካከል የሚያድርበትን የመረጠውን ስፍራ መቅደሱን ያመለክታል። ለእኛ ለዳንን የዚያ አገር ዜግነታችን "እኔ ግን በእርስዋ ተወለድሁ" የሚሰኝ ባለ መብት የሚያደርግ ሙሉ የዜግነት ክብር የተሞላ ነው እንጂ፣ "እኔ ይህንን ዜግነት በብዙ ገንዘብ አገኘሁት" (ሐዋርያት 22፥ 27-28 ይመለከቷል) የሚያሰኝ አይደለም። በእርስዋ ተወለድሁ በሚለው ገለጻ የእግዚአብሔር ህዝቦች ለተወለዱበት ስፍራ ቤተሰብ መሆናቸውን ያመለክታል፤ እንደ ኢየሱስ ትምህርት ደግሞ ይህ መወለድ የቅዱስ ጥምቀት ተአምር የሚሰራው ዳግመኛ ልደት ነው (ዮሐንስ 3፥ 3-8)። የዚያ አገር ዜግነት የሚገኘው በልደት ብቻ ነው። እግዚአብሔር በቅድስት ከተማው ውስጥ በአዲስ ልደት በኩል ተወላጅ በመሆን የዜግነት መብት እንዲኖራቸው የሰጣቸውን ሰዎች በመዝገብ ጽፎ በሚያስቀምጥበት አኳኋን ተገልጧል።
በዚያ የተወለደም ሰው "በዚያ ነው የተወለደው" ተብሎ በሌሎች ይታወቃል። የዚያ አገር ሰዎች የከበሩ ታዋቂዎች ናቸው። እነዚህ ያውቁኛል ተብለው የተዘረዘሩት የአለም ሕዝቦች ከመላው አለም የጸጋው ተካፋይ እንዲሆኑ ተጋብዘው የመጡና ከቅዱሳኑ ጋር እንዲቀላቀሉ የታደሉ የአህዛብ ሙላት ስብስብና ወኪሎች ናቸው። በዚያች ከተማ ውስጥ እንደ ባለ ሙሉ መብት የዜግነት ክብር ስንኖር በእግዚአብሔርና በእርስ በርሳችን ፊት ያለን እውነተኛው ማንነታችን የመጣንበት ዘር፣ የምንናገረው ቋንቋ፣ የቤተሰብ ትስስራችን፣ የቆዳችን ቀለም፣ የሀብትና የእውቀት ደረጃችን፣ ወይም ማናቸውም ምድራዊ ትምክህትና ኩራት አይደለም። እግዚአብሔር የእርሱ የብቻው እንድትሆኑ እናንተን የገዛ ራሱ ብቻ ልጆች ለማድረግ የከፈለው ዋጋ ታላቅ ነው፤ በከበረው የእግዚአብሔር በግ ደም ተዋጅታችሁ፣ በቅድስት ጥምቀት ውሃ ተሻግራችሁ ዜግነት ወዳገኛችሁበት መንግስት ፈልሳችኋል።
የቅዱሳን ሃገር፣ እርሷም ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተሸልማና በውበትዋ አጊጣ ወርዳለች፣ በመንፈሳዊውም አለም በመካከላችን ናት። "ስለ አንቺ ክቡር የሆነ ነገር እንዲህ ተብሎ ይነገራል" እንደተባለ በእምነትና በመንፈስ የሚያዩ ብቻ ግርማዋንና ውበትዋን ያደንቃሉ። "ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።" (ዕብራውያን 12፥ 22-24) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ወደ እርሷ የደረሱ ብቻ ያውቋታል።
እግዚአብሔርም ራሱ ብርሃንዋ ሆኖ በዚያ ሁሉን ይገዛል። ወደ ቅድቲቱ ከተማ የዳኑ ብቻ ይገቡባታል እንጂ "ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።" ይልቁንም "በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ" (ራእይ 20፥ 15) ተብሎ እንደተጻፈ የእርኩሳን ሁሉ ዕድል ከከተማይቱ ውጭ ነው። "ስሞቻቸው በሕይወት መይሐፍ የተጻፉት" (ፊልጵስዩስ 4፥ 3)፣ ቅዱሳን የሆኑ አማኞች ሁሉ ግን እያንዳንዳቸው በግላቸው በክርስቶስ ሀልዎት ፊት ለመሆን እድሉ አላቸው። "ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ለተጻፉት" እና እግዚአብሔር ለመዘገባቸው፣ ዳግም ለተወለዱ ሁሉ፣ በክርስቶስ ለተቀደሱና ለጸደቁ ለተመረጡት ቅዱሳን ሕዝቡ ሁሉ ክርስቶስ ጌታቸውን በውበቱና በግርማው ፊቱን እያዩ ሊኖሩበት የተሰጣቸው የሚበልጥ ሰማያዊ አገር ይህ ነው። "የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።" (መዝሙር 46፥ 4)፣ እንደተባለ "ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ" (ሮሜ 14፥ 17) የሚፈልቅባትና የሚፈስባት ምርጥ አገር አለችን። ከእርሱ ጋር ለዘላለም በፊቱ እንዲኖሩ ከተማይቱን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን አዘጋጅቶላቸዋልና፣ በዚያም እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም። "አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።" (ዕብራውያን 11፥ 16)
ዳግመኛ የተወለዱ አማኞች ሁሉ በአዲሲቷ የኢየሩሳሌም ከተማ የተከፈቱ በሮች፣ በዘላለማዊው የወንጌል ስብከት፣ በእምነትና በንስሃ በማያቋርጠው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በቀጣይነት በቅዱሳት ምስጢራት በኩል በሚታደል ጸጋ ወደፊት እየተጓዙ፣ በመንፈሳዊ ሁኔታ መግባታቸውን አያቆሙም ይቀጥላሉ። ይህም ሊካድ የማይቻል አሁን በዚህ ምድር ላይ በህይወት እያሉ በክርስቶስ ካገኙት ስፍራቸው የተነሳ ወይም ከእርሱ ጋር ካላቸው አንድነትና ግንኙነት የተነሳ ያለው የሚለማመዱት እውነታ ነው፤ ዳሩ ግን ለእያንዳንዳቸው አማኝ ግለሰቦች እስከ ሞታቸው ድረስ፣ ማለትም የማይሞተውን አዲሱን አካል ለብሰው ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር ለመኖር ይህንን ስጋቸውን እስከሚለዩበት ቀን ድረስ ገና በፍጹምነት የታወቀላቸውና በሙላት ያገኙት አይደለም። የሞታችን ቀን የማያስፈራን ከዚህ ልምምዳችንና ከዘላለም ህይወት ተስፋ እውነት የተነሳ ነው። በዚያ መሆን የሚሻል እንደሆነ አምነን፣ ሞተን ከጌታ ጋር ለመሆን፣ ልንሄድ ከእርሱም ጋር ልንኖር የምንናፍቅ እኛ የዳንን ብቻ ነን።
እምብዛም የመጻኢነት አመለካከት እንዳልተጫነው አስቤ እየዘመርኩ የምጽናናበትን የወንድማችንን የዘማሪ ሸዋዬ ዳምጤ መዝሙር ልጋብዛችሁና ነገሬን ልጨርስ፤ እነሆ አዝማቹ እንዲህ ይላል፦
በውቢቱ ኢየሩሳሌም፣ በቅድስቲቱ ሃገር
ተስፋ አለን እኛም በጌታ፣ ለዘላለም ልንኖር
አልፈን የሞትን መንደር፣ ከዚያ ወዲያ
አልፈን የሞትን መንደር
ስጋ ከኛ ተገፎ
አሮጌው ሁሉ አልፎ
እንለወጣለን ጌታን እንለብሳለን
ልታነቡ ለምትወዱ "ከዚህ ህይወት በኋላ ለሚያምኑና ለማያምኑ" በሚል ርዕስ የለጠፍኩትን ጽሁፍ ጋበዝኳችሁ። እነሆ ሊንኩ፦
http://gizachewkr.blogspot.com/2019/02/blog-post_28.html
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/