የጥፋት ወንጌል
"ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።" 2 ቆሮ 12፥ 7-10
፩.
እንደ መነሻ የጠቀስኩትን ይህንን የንባብ ክፍል ኋላ ላይ እመለስበታለሁ። ልንሰማው በሚያስፈልገን የመዳን ወንጌል ጤናማ ቃልና እኛ ልንሰማው በምንፈልገው "ጥሩ ዜና" መካከል ልዩነት አለ። እንደሚታወቀው ሰዎች የሆንን ሁሉ ልንሰማው የሚያስፈልገን መልካሙ የምስራች አንድ ነው። ነገር ግን በዚህ አለም ብዙ አይነት ጥሩ ዜናዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እስቲ ሰው ሁሉ ሊሰማው የምፈልገውን ጥሩ ዜና ላሰማችሁ። ምናልባትም ይህ አንዳንዶቻችሁ ሰምታችሁት የማታውቁት፣ ብዙዎቻችሁ ግን አሁንም ድረስ እንደ እግዚአብሔር መልዕክት የምትቆጥሩት ስሜት ኮርኳሪ ምርጥ ዜና ሊሆንላችሁ ይችላል። ልትሰሙት ዝግጁ ናችሁ?
"እነሆ እግዚአብሔር ሁላችሁም ጤናማ እንድትሆኑ፣ በሽታም እንዳያገኛችሁ፣ ሀብታም እንድትሆኑ፣ ድህነትም እንዲርቃችሁ፣ ከሥቃይ ነፃ እንድትሆኑ እና በምትሠሩት ሁሉ እንድትበለጽጉና በብዙ እንድትከናወኑ ፈቃዱ ነው፤" የሚል ዜና ነው። ይህ ታዲያ ጥሩ ዜና ነው ወይስ መጥፎ? ይህ እኛ መስማት እጅጉን ደስ የሚለን ዜና ነው፣ አይደል? ይህ ታዲያ ምን ክፋት አለው? እንዲህ ያለው ዜና የያዘውን መልእክት መስማት አትወዱምን? በርግጥም ትወድዳላችሁ እንጂ ለምን አትወዱም? እግዚአብሔር ሁላችሁም ጤናማ እንድትሆኑ፣ ሀብታም እንድትሆኑ፣ ከሥቃይ ነፃ እንድትሆኑ እና በምትሠሩት ሁሉ እንድትበለጽጉ የሚፈልግ መሆኑ መልእክቱ አሪፍ ዜና ካልሆነ ታዲያ ምን ሊሆን ይችላል?
የዚህ መልእክት ብቸኛው ችግር ግን እውነት አለመሆኑ ነው። እውነት ደግሞ መስማት ደስ ከሚለንና ከምንፈልገው ነገር በላይ ዋና አስፈላጊ ነው። አዎን፣ በተለይም ይህ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቱን ስንናገር የሚሰራ ነው።
እስቲ ልጠይቃችሁ፣ ስለ ጤንነት/ብልጥግና ወንጌል ምን ይሰማችኋል? እንዲህ ላለው ጉዳይ ግድ የለሾች ናችሁን? እሱንስ ሳይጎረብጣችሁ ታግሶ ለመስማት አቅም አላችሁን? ሲሰሙት ለጆሮ የሚጥም ከመሰለ፣ ቃሉን እያጣመመ ከሚሰራ እንዲህ ካለ ትምህርት ጋር በጽኑ ካልተጣላችሁ፣ እንዲህ ያለው ትምህርት በንዴት ካላቃጠላችሁ፣ ከሁለት ነገሮች አንዱ በህይወታችሁ እውነት ነው ማለት ነው፦ 1ኛ. የብልጽግና ወንጌል የሚያስተምረው ግልሙትና ምን እንደሆነ አልገባችሁም ወይም ጨርሶ አታውቁትም ማለት ነው፤ አልያም 2ኛ. ወንጌል ራሱ ከመሰረቱ አልገባችሁም። ወንድሜ ሆይ፣ ወንጌልን በአግባቡ ተረድተኸው ከሆነ ያኔ ሕያው ሆነህ የጤንነት/ብልጥግና ወንጌል አስተማሪዎች የሚሰብኩትን አደጋ በንቃት ታውቃለህ፤ ራስህንም ሆነ በአጠግብህ ያለውን ክርስቲያን ከአደጋው ለመጠበቅም ትተጋለህ። ካልሆነ ግን ሞት በመሰለ ከባድ እንቅልፍ ተይዘሃል፣ ሳትቀበር በፊት ፈጥነህ መንቃት አለብህ። ዝም ብለን ተጎልተን አገሩን የሞላው የሀሰት ወንጌል ህዝባችንን እየጠራረገው ነው። "ሰይፍ ከዋጠው ሕዝብ ሁሉ ይልቅ ዱር ብዙ ዋጠ" (2ሳሙኤል 18፥ 8) እንደተባለ ኮምኒዝምና መከራው ካደረሰው ጥፋት በላይ የነጻነቱ ዘመን የትምህርት አሰስ ገሰስ ብዙዎችን ውጧል።
እኔ እንደማስበው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን የተናገረው ቃል ዛሬ እኛን የሚመለከት ይመስለኛል፡-
"ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።" (ፊልጵስዩስ 1፥ 27)
ጳውሎስ ለእነዚህ አማኞች "ጸንታችሁ ቁሙ" የሚል ምክር ይሰጣቸዋል። ይህም ስቴኮ (Steko) ከሚለው የግሪክ ቃል የተተረጎመ ነው። ይህ ቃል የሚልቴሪ ሳይንስ ሙያዊ ቃል ሲሆን፣ ትርጉሙም "በጦርነት ውስጥ ያለመናወጥ መቆም፣ መረጋጋት" ማለት ነው። የገጠመው ጦርነት የቱንም ያህል ቢከፋ ስፍራውን ለማይለቅና ከቦታው የማይነቃነቅ ወታደርን ለመግለጥ ጥቅም ላይ ይውላል።
ጳውሎስ በተሰጣቸው የወንጌል ባላደራነታቸው፣ ከስህተት ወይም ከኃጢአት ጋር ባላቸውም ተጋድሎ ጸንተው እንዲቆዩ፣ በትምህርታቸውም ሆነ በምግባራቸው ሳይነቃነቁ እንዲቆሙ እየነገራቸው ነው። ይህ ወታደራዊ የሆነ ያነጋገር ዘይቤ በከፍተኛ ጥቃት ውስጥ እያሉ ቢሆን እንኳ ገዢ ቦታን ሳይለቁ ገትሮ ከመያዝና ወጥሮ ከመዋጋት ጋር የተያያዘ ነው። “ጸንታችሁ ቁሙ” ሲልም በአእምሮው ውስጥ በአስተምህሮ እና በሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች ላይ የማመቻመች ፈተናን የመቃወም ነገር አለው።
ጳውሎስ “ለወንጌል እምነት አብራችሁ ተጋደሉ” በማለት ይነግራቸዋል። “በአንድነት መጋደል” የሚለው የግሪክ ቃል "ሱናትሊዮ" (sunathleo) ከሚለው ሁለት ቃል የተገኘ ሲሆን፣ እሱም sun “በጋራ” እና athleo "ውድድርን ወይም ፉክክርን መሳተፍ" ማለት ነው። አትሌቲክስ የተሰኘው ስፓርታዊ ውድድርም ስያሜውን ያገኘውን ከዚሁ የግሪክ ቃል ነው።
ይህ ተጋድሎ በጦር ግንባር እና በጨዋታ ሜዳ ላይ እንደሚደረግ የሕይወትና የሞት ሽረት ትግል እንዳለበት የግላዲያተር ፍልሚያ ከውድድርና ከፉክክር ጋር የተያያዘ ነው። ይህም አብሮ መጋደል በቡድን ተጣምሮ ለማሸነፍ ጥረትን ሁሉ የማሳየት ጥሪ ነው። በወንጌል የመጋደልን ጥሪ እና አደራ ያላወቀ አማኝ የወንጌልን እውነት እያመቻመቸ ለአለም የሚመች ማህበረረባዊ ወንጌል (social gospel) አቀንቃኝ ይሆናል። እኛ የወንጌል አማኞች ግን፣ “በአንድ መንፈስ ጸንተን በአንድ ልብ ለወንጌል እምነት አብረን የምንጋደል” መሆን አለብን። በዛሬው ዘመን ክርስትና ግን የወንጌል መልእክት ምንነት ግልጽ አይደለም፣ ማንኛውም ሰው ወንጌል ምን እንደሆነ የብልጭታን ያህል ፍንጭ ቢኖረው በጤንነት/ብልጥግና ወንጌል ላይ አሰላለፉን ባስተካከለ ነበር።
ወንጌል እግዚአብሔር በልጁ ሞት በኩል ለኃጢአተኛው ሰው ቤዛ ሆኖ እንዳቀረበ የሚታወጅ የምስራች ነው። ይህ ቤዛነት ለሚያምኑ ሁሉ በጸጋ ይታደላል። በክርስቶስ ላይ የሚያርፈው እምነት በአእምሮው፣ በአካሉና በመንፈሱ የተበላሸውን ኃጢአተኛ ወስዶ ከኃጢአቱ ሁሉ ያነጻዋል፣ በእግዚአብሔርም ፊት ጻድቅ ያደርገዋል፣ የዘላለምንም ሕይወት ይሰጠዋል። ያ ነው እንግዲህ መልካም ዜና ነው የምንለው።
፪.
ክርስቶስ የኃጢያት እዳዬን እንደከፈለልኝ አምናለሁ ከዚህ የተነሳ ኑሮዬና ደረጃዬ ፍጹም ተለውጦ ከችግር ሁሉ ተላቅቄ ሁሉ መልካም ይሆናል ብሎ ማሰብ ግን ፈጽሞ አይሰራም፤ እስቲ አሁን የምኞትና የቅዠት ጥግ ካልሆነ በቀር የኃጢአት ዕዳ ክፍያና የኑሮ ደረጃ ለውጥ ምን ያገናኛቸዋል? እንዲህ ያለው እብደት ፈጽሞ የክርስቶስ ወንጌል አይደለም። በክርስቶስ የሙስቀል ሞት የተገኘው የኃጢአት ዕዳ ክፍያ ከዘላለም ኩነኔ መዳኛ እንጂ ከችግር ነጻ ሆኖ የመኖር ዋስትና አይደለም። አሁንም የእለት ጉርስ ማጣት፣ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ ያለቀ ጫማና የተቀደደ እራፊ፣ የተኛ የመኪና ጎማ፣ የተሰበረ አጥንት፣ የታመመ አካል ሊኖረኝ፣ የትዳር ጭቅጭቅ፣ የገንዘብ እጥረት ትግል ሊኖርብኝ ይችላል፤ እውነታው ደግሞ ይኸው ነው። የአገር ቀበኞች የደኃውን ገንዘብ ከመመዝበር እጆቻቸውን ካልሰበሰቡና በላብ ሰርቶ በኢኮኖሚ ከመለወጥ ውጪ ህይወት እንደሁ ሁልጊዜ ትግል ናት!
ነገር ግን የጤንነት/ብልጥግና ወንጌል አቀንቃኞች ደረጃው እየጨመረ በሚያድግ እምነት እግዚአብሔር በከፍተኛ ጤና እና ሀብት አትረፍርፎ እንደሚከፍል ደፍረው ያስተምራሉ። ሲናገሩም እግዚአብሔር የዘላለም ሕይወትን ብቻ ሳይሆን ብራንድ ሀብታም እና ህመም የማያውቀው ፍጹም ጤናማ እንድትሆኑ፣ እንዲሁም ከየትኛውም ስቃይና መከራ ነፃ እንድትሆኑ፣ ከችግር ተላቃችሁም እንድትኖሩ ይፈልጋል ሲሉ በአዎንታዊ ማነቃቂያ እያባበሉ ያስተምራሉ።
እንዲህ ያለ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያፈነገጠ ነገር "ወንጌል አማኝ" ነን በሚሉት ዘንድ እንዴት ሊታሰብ ቻለ? እንዴትስ ስር ሰዶ በመሰራጨት "ወንጌላውያን አማኞችን" ከክርስቶስ ወንጌል ሊያርቃቸው ቻለ? በእውነቱ ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው። ይህንን ለማስተዋል እንዲቻለን በአገራችን እንደ ጉድ የፉሉትን አነስተኛና ጥቃቅን እባብ የብልጥግና ሰባኪዎች ላይ ጊዜ ከምናጠፋ ዘንዶ እና አናኮንዳ የሆኑ አባቶቻቸውን፣ ትምህርቶቻቸውንና ልምምዶቻቸውን ነቅሰን እያወጣን ስለ ብልጽግና ወንጌል ታሪካዊ ዳራ ጥቂት ነገር ለማለት እንሞክራለን። ከምዕራባውያን የቴሌቪዥን ሰባኪዎች በተቀዳ ትምህርትና በተኮረጀ ስታይል የሚያቅራሩብንን የአገራችንን የብልጥግናና የስኬት እርኩስ ወንጌል ሰባክያንን ተውት አድርገን ምንጫቸውን እንመርምር።
እንደ ቅደም ተከተላቸው የመጀመሪያዎቹ የአዎንታዊ አስተሳሰብ አራማጆች፣ ፊኒያስ ፒ. ኩዊቢ እና ሜሪ ቤከር ኤዲ፣ የመሰሉ የአዲስ አስተሳሰብ እንቅስቃሴን እና የክርስቲያን ሳይንስ መንፈሳዊ አስተሳሰብ መስራቾች ቀደምት ፈጣሪዎች ነበሩ። በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ የቤቴል መጽሐፍ ቅዱስ ተቋም መሥራች እና መጋቢ ኤሴክ ዊልያም ኬንዮን ስለ ክርስቶስ የተጠናቀቀ ሥራ በሚሰብክበት ጊዜም ተመሳሳይ የሆኑ የአዎንታዊ ሐሳቦችን አካትቶ ያስተምር ነበር። ኬንዮን ክርስቲያኖች ስሜታዊ እና አካላዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት “አዎንታዊ ኑዛዜ” (positive confession) ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጽፏል። ሲናገርም "እኔ የተናዘዝኩትን (ያልኩትን) ነኝ/አለኝም" ይል ነበር።
በ1930ዎቹ ኬኔት ሀገን የቃል-እምነት እንቅስቃሴን ሲጀምር የኬንዮንን ትምህርት እንዳለ በመቅዳት ከጴንጤቆስጤ እምነትና አስተምህሮ ጋር ቀይጦ ማስተማርን ጀመረ። የእግዚአብሄር ማኅበረ ቅዱሳን የተባለ ቤ/ክ መጋቢ የነበረው ይህ ኬኔት ሀገን ክርስቲያኖች በቂ እምነት በማሰባሰብ ሀብታም መሆን እንደሚችሉ ሲያስተምር ይደመጣል። "በእምነት በለው፣ አድርገው፣ ተቀበለው፣ አውራው" የሚሉ የቃል እምነት መርሆዎችን ፈብርኮ ክርስቲያኖችን በቅዠት አለም ያሰክራችው ነበር። በእምነት የሚነገሩ ቃላቶች መሟላት እንዳለባቸው የሚገልጽ “ጥራው" እና "በይገባኛል ውረሰው” የሚሉ መፈክሮችን ያስከተለውን “የሬማ አስተምህሮ” አስፋፍቷል። ይህን ተከትሎ በ1960ዎቹ የኦራል ሮበርትስ ወጣት ተባባሪ ኬኔት ኮፕላንድ እምነት “ኃይል” እንደሆነ ማስተማር ጀመረ፤ እሱም ጮክ ባለ ድምጸት በይሆናል አይነት ስሜት ሲናዘዝ (ሲመሰከር) የተጠበቀውን ቁሳዊ ውጤት ያመጣል፣ ይል ነበር። በሁለት አስርት አመታት ውስጥ፣ ይህ Word-Faith ልክ እንደ ካንሰር ሆኖ ወደ ትልቅ የካሪዝማቲክ እምነት ዘር አድጓል።
የእነዚህን ሰዎች አስተምህሮ እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል፡- እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው እንደ ሉዓላዊ ፍጡራን “የእግዚአብሔር ዓይነት እምነት”ን በመጠቀም ነገሮችን በመጥራት ወደ መኖር እንዲያመጣቸው፣ በብልጽግናና በስኬት የመኖር ችሎታ ያለው አድርጎ “በእግዚአብሔር ደረጃ” (ወይንም እንደ “ትናንሽ አማልክት”) እንዲሆን ነው። ነገር ግን በገነት ውስጥ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ እና የሰይጣንን ተፈጥሮ በመያዝ ይህንን እድል አጥተናል። ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነና፣ በመንፈስ ሞተ (በዚያም የሰይጣንን ባሕርይ ለብሶ/ ሰይጥኖ)፣ ወደ ሲኦል ወረደ፣ “በሲኦልም ዳግመኛ ተወለደ”፣ እንደገናም በእግዚአብሔር ባሕርይ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፣ ከዚያም መንፈስ ቅዱስን ላከ። በዚህም ትስጉዑቱን በአማኞች ውስጥ ሊያባዛ ይችላል፣ ከዚህም የተነሳ አማኞች እንደ እርሱ ትናንሽ አማልክት የመሆን ጥሪያቸውን ይፈጽማሉ። አሁን የተጠራነው እንደዚህ አይነት ህይወት እንድንለማመድ ስለሆነ በሁሉም የህይወታችን ዘርፍ ስኬታማ መሆን ይኖርብናል። እንግዲህ እነዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እንደሚያስተምሩት በዕዳ የመያዝ ሁኔታ ቢሆን፣ ወይም ጤና የማጣት ጉዳይ፣ ወይም ትዳርን የማጣትና የቤተሰብ መበተን ሁኔታ፣ እንዲሁም ማናቸውም እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮችን በተመለከተ የእግዚአብሔርን ተስፋዎች "በማወጅ" መፍትሄን አለማግኘት ያው የእምነት ማነስን ያሳያል፣ ይላሉ። ከላይ ያለው አስተምህሮ አንዳንድ ገጽታዎች ከአስተማሪ ወደ አስተማሪ ሊለያዩ ቢችሉም ቅሉ፣ አጠቃላይ ዝርዝሩ ግን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ያው አንድ አይነት ነው።
የዚህ ዓይነቱ ሥነ-መለኮት ከምዕራቡ አለም እየናኘ ድንኳኖቹን በማስፋት ካስማዎቹንም በማርዘም ወደሩቅ ደርሷል። መላውን የሩቅ ምስራቅ ክርስትናና የአፍሪካን ምድር እያጥለቀለቀ በተለይ ከኮምኒዝም ስደት በኋላ በምድራችን በኢትዮጵያ ያለቅጥ ተሰራጭቷል። ይህ ትምህርት በእርግጥ ሰዎችን በጤናና በስኬት እያባበለ ይማርካል፣ ትምህርቱና ልምምዱ ከእምነት በስተቀር ምንም ስለማይፈልግ እርሱም ደግሞ በቂ እምነት ከሆነ፣ ከዚህ የተነሳ ሰዎች ባለጠጋና ጤናማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተስፋ ይሰጣል። እንዲህ ያለው መልዕክት "በህልሙ ቅቤ እንደሚጠጣ ደሀ" ሰዎች ሊሰሙት የሚፈልጉት አይነት ስለሆነ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ መልእክት ሆኖላቸዋል።
የዚህ ጠማማ ወንጌል አንዳንድ አስተማሪዎች የሚሉትን ስሙ፦ "እኔ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ --እስከፍጻሜዬም እንደዚያም ነው ብዬ ማንም አማኝ በብሽታ እንዳይታመም በኢኮኖሚም እንዳይቸገር፣ እያንዳንዱም አማኝ በዚህ ምድር ላይ እድሜው ሳይቀጠፍ ሙሉ ህይወቱን ቆይቶ እንዲኖር፤ በታላቅ ፍቅሩ እና በታላቅ ምህረቱ የተገለጠ የአባታችን የእግዚአብሔር እቅድ ነው ብዬ በዚሁ እምነት እሞታለሁ፤ እያንዳንዱም አማኝ በመጨረሻ በኢየሱስ ሆኖ መተኛት አለበት" (ኬኔት ኢ ሃጊን፣ ስለ መለኮታዊ ፈውስ ማወቅ ያለብህ ሰባት ነገሮች፣ ገጽ 21)።
ኬኔት ኮፕላንድ "የብልጽግና ህጎች" በተሰኘው መጽሃፉ በገጽ 51 ላይ "እንዲያበለጽግህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ መገንዘብ አለብህ። ይህም ለአንተ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅህ ነው፣ እውነቱን ለመናገር እስካሁንም ከሱ አለመካፈልህ ትልቅ ሞኝነት ነው" ይላል።
የብልጽግና ወንጌል ዋና ስህተት አንዱ ማዕከላዊ መርህ ፦ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ክርስቲያን በገንዘብ ባለጸጋ እንዲሆን ፈቃዱ ነው፣ ስለዚህም አማኝ በድህነት መኖሩ እግዚአብሔር ካሰበለት ፈቃዱ ውጭ መኖር ነው የሚለው ነው። በተለምዶም ራሱን የሸሸገበት አንዳች ቦታ፦ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን ሁል ጊዜም ቢሆን የመጀመሪያውንና የታላቅነትን ደረጃ መያዝ አለብን፣ ራስ እንጂ ጅራት ስላልሆንን ከሁሉ ከፍ ያለውና መልካም የሆነው ሁሉ ሊኖረን ይገባል። ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመጣውም ይህ ብቻ ነው! የሚለው ማረጋገጫው ነው። ሰሞኑን እንደውም አንዱ ያገራችን ጉድ ድህነት አርነት መውጣት የሚጠይቅ ሰይጣናዊ እስራትና እርግማን ነው እያለ ጣቃውን ሲቀደድ በሶሻል ሚዲያ ሰማሁት። እንዲህ ያለው ሰባኪ ነኝ ባይ በጥልቅ ድህነት ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን የሜቄዶንያን ቅዱሳን ምን ሊላቸው ነው? ምነው ጳውሎስስ ቢሆን ከዚህ እስራት ሳይፈታቸው ቀረ?
እነዚህ የሐሰት ወንጌል አስተማሪዎች በአብዛኛው የእግዚአብሔርን ቃልና ተገቢነት ያለውን አተረጓጎም ችላ ቢሉም፣ ያንን እርኩስ ትምህርታቸውን ግን እዚህም እዚያም በተቆነጠረ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶች ለማስደገፍ ይሞክራሉ። መቼም የቃል እምነት መልእክትን የሚያስተላልፉ ማናቸውም የሕትመት ሥራ ሆነ ወይም አስተማሪ ነኝ ባይ ከ3ኛ ዮሐንስ መልዕክት ቁጥር 2 መጥቀስ ቋሚ ልማዱ ነው፤ ጥቅሱም "ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ።" ይላል።
የብልጽግና ወንጌል አስተማሪዎች ይህን ጥቅስ ልክ የአዲስ ኪዳን ዶክትሪን የሆነ ያህል፣ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ከነፍሳቸው የመከናወን ሁኔታ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መጠን እንደሚበለጽጉ በእርግጠኝነት ያሳያል ሲሉ ይተረጉሙታል። በሌላ አነጋገር፣ በአካሄድህ ከእግዚአብሔር ጋር የምትራመድ ከሆነ፣ ማለትም ነፍስህ ከተከናዋወነ፣ በውጤቱ ኑሮ የተከናወነለት ባለጠጋና የማይታመም ጤነኛ ሰው ትሆናለህ። በድህነት ውስጥ የምትኖር ከሆነ ግን ገና አሁንም በኃጢአትህ ውስጥ መሆን አለብህ፤ እንደ ማለት ነው፣ ይላሉ።
ይህ ጥቅስ ዮሐንስ ለወዳጁ ለጋይዮስ ያቀረበው ሰላምታና የጸሎት ዘገባ ብቻ ነው እንጂ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለክርስቶስ አካል ሁሉ የተሰጠ የእምነት መግለጫ ወይም አቋም አይደለም፤ ዶክትሪን ሆኖ እንደ ተስፋ ቃል ወይም እንደ እምነት እንቀጽ መቆጠርም የለበትም። ሰላምታንና የጸሎት ርዕስን ሁሉ እየሰበሰቡ ዶክትሪን ለማድረግ መሞከር በእውነቱ አለመማር ብቻ ሳይሆን፤ ሁሉም የተጻፈው ለእኔ ነው የሚል ብልጣብልጥነትና ራስ ተኮርነትም ጭምር ነው። የብልጥግና ወንጌል ክፋቱ ሰዎችን ራስ ወዳድና ስግብግብ ማድረጉ ነው
ተመልከቱ፣ ይህ መልእክት የተቀረጸው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በነበረው የተለመደ የደብዳቤ አጻጻፍ ቅርጽ ነው። ዊልያም ባርክሌይ ይህንን በ3ኛ ዮሐንስ 2 ላይ ያለውን የተለመደ የደብዳቤ አጻጻፍ ቅርጽ እውነታ የሚመለከተው አንድ የመርከብ ካፒቴን ሸኝዎቹን ሲሰናበት ከሚጠቀምበት የስንብት ቃልና አብረውት የሚጓዙትን ሲያበረታታ ከሚጠቀምበት ማበረታቻ አረማዊ የመልካም ምኞት መግለጫ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ሐረጎችንና ቃላትን በመጥቀስ ነው። ሃዋርድ ማርሻልም፣ በኒው ኢንተርናሽናል የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያው ውስጥ፣ ሽማግሌው (ዮሐንስ) ለወዳጁ ለጋይዮስ መልካም ምኞቶችን በመግለጽ በጊዜው የነበረውን ባህላዊ ወግ እና እሴት እንደሚከተል በመግለጽ የባርክሌይን አስተያየት ያረጋግጣል። ይህ ልክ በሃገራችን ልማድ "ጤና ይስጥልኝ" ብሎ በመልካም ምኞት መግለጫ ሰላምታ የማቅረብ ሁኔታ እንጂ "የመከናወንና የጤንነት" ዶክትሪን ፈጽሞ አይደለም። ለሁሉም አማኞች ፈቃዱን በተመለከተ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሁለንተናዊ መግለጫም አዋጅም አይደለም። እንደዚያ ነው ብሎ መገመት ግን ከሥነ-ጽሑፋዊው እና ታሪካዊው አውድ ውጭ መሆን ነው።
አስተውሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለእኛ ተጽፎልናል እንጂ በቀጥታ ለእኛ አልተጻፈም። ጳውሎስ እስክንድሮስን በአይነ ቁራኛ እንዲጠብቅ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ትዕዛዝ፣ እንዲሁም ከክረምት በፊት በርኖሱን ይዞለት እንዲያመጣ፣ ቲቶም በቀርጤስ እንዲኖር የተሰጠው መመሪያ፤ ወይም ጌታችን ኢየሱስ "ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ" ያለው፣ ወይም "በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ" ያለው፣ አልያም "በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ" ያለው እና ይህን የመሰለ ነገር ሁሉ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል አካል መሆኑ እሙን ነው፥ ዳሩ ግን እንዲህ ያለው ትዕዛዝ በቀጥታ ለእኛ የተጻፈ አይደለም። ብዙዎች ግን ይህንን መለየት ተስኗቸዋል። የብልጽግና ወንጌል መምህራንም ይህን በተመለከተ በያዙት ግንዛቤ ግለሰብን ጠቅሶ በአድራሻው በተጻፈለት ሰላምታን በያዘ የመልካም ምኞት መግለጫና ለሁሉ በሚሆን ሉል አቀፍ ዶክትሪናል የተስፋ ቃል መካከል ያለውን ልዩነት አደባልቀዋል።
፫.
አሁን እንግዲህ ታዲያ ይህ ምንአለበት፣ በእኛ ላይስ ምን ጉዳት ሊያደርስ ይችላል? ተብሎ ይጠየቅ ይሆናል። በእርግጠኝነት ለመናገር የእግዚአብሔርን ቃል እየተማርን የምናድግ ማናችንም ብንሆን በዚህ የውሸት ወንጌል ልናምን የምንችልበት ምንም መሰረት እንደሌለን ይህንን አንድ ነገር እገነዘባለሁ፤ ይሁንና ግን ልታስተውሉት የሚገባችሁ ነገር እንዲህ ያለ የተሳሳተ ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ላይ እየናኘ የብዙወችን ልብ እየወሰደ መሆኑን ነው። በኢንተርኔት በተደረገ ጥናት 61 በመቶ የሚሆኑት የአሜሪካ ጰንጤቆስጤ አማኞች እግዚአብሔር ሰዎች እንዲበለጽጉ እንደሚፈልግ ያሚያምኑ ናቸው። "የእርስዎ ምርጥ ህይወት አሁን"፣ በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትሞ ከ4 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች የሸጠው የጆኤል ኦስቲን ድርሰት ይህንን ያሳያል። በግሌ መጽሐፍ ተራ ጎራ ብዬ አይኔን ሳማትር በየመደርደሪያው ላይ እዚህም እዚያ በርከት ብሎ አይኔን የሚያደናቅፈኝ እንደ ዚህ ሰውዬ ድርሳን ሌላ መጽሐፍ ብዙ አልገጠመኝም።
ይህ እምነት የጰንጤቆስጤ መሰረቱን እያሰረገ ወደ ወንጌል አማኝ አብያተ ክርስትያናት ሁሉ ዘልቆ ግብቷል። በአገራችንም የወንጌል እምነት ታሪክ ውስጥም የቃል እምነት ህጸጹን አሹልኮ በማስገባት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ጰንጤቆስጤ ነው። እኔ በበኩሌ እንደ ጰንጤቆስጤ ከጤንነትና ከብልጽግና ወንጌል ጋር እርኩስ ጋብቻን የፈጸመ ሌላ እምነት አላየሁም፤ ይህም ግልሙትና እንደ ወረርሽኝ ወንጌላውያንና ካርዝማውያን ነን ሲሉ ራሳቸውን የሚጡሩትን እያዳረሰ በሁሉም ቤት እንደ ቀኖና የሚታመን እየሆነ ለመምጣት ጥቂት ስብከቶቻቸውንና መዝሙሮቻቸውን መታዘብ ብቻ ይበቃል።
እንደሰሜን አሜሪካ ባሉ አገሮች ውስጥ ትላልቆቹን ጉባኤያት ከሚመሩና ብዙሃኑ ካደነቃቸው ዝነኛ ሰባክያን ጋር በሥነ-መለኮታዊ ጉዳዮች አለመስማማት በተለይም በአሁኑ ጊዜ እንደ ሞኝነት እንደ እብደትም ሊመስል ይችላል። ተመልከቱ ሠላሳ ሺህ የሚሆኑ ጎልማሶች በየእሁዱ የጆኤል ኦስቲንን ስብከት ለመስማት በቤተክርስቲያኑ ይገኛሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ በየቤታቸው ሆነው የእሱን ብሔራዊ እና የዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ስርጭቶችን በቻናሎቹ ይከታተላሉ። በእርግጠኝነት ይህ ለቁጥር የሚያታክት ተከታይ ያለው ሰው በትክክለኛው መንገድ ላይ የመሆኑ ምልክት ነው ብሎ ማንም ሰው መገመት ይችላል። እውነታው ግን ይህ አይደለም! ቢከፍቱት ተልባ የሆነ ይህ ሰው ኃሰተኛ የምኞት ወንጌል እየሰበከ ያለ የስህተት አስተማሪ ነው።
ጆኤል ኦስቲን ያተረፈው እንዲህ ያለ እውር ተወዳጅነት በእውነት በአሜሪካ ውስጥ ላለው አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ አይነተኛ ማረጋገጫ ነው። ይህ ሰው በሚያቀርበው ዲስኩር የሚደመጠው አነቃቂ ንግግሩ በእውነት ስለ ኃጢአታቸው የማይወቀሱና ሊወቀሱ የማይወዱ ሰዎችን ጆሮ ይማርካል። እነዚህም ንስሃ መግባት እና ኃጢአታቸውን መጥላት የማይፈልጉ ናቸው። ስለዚህም ጆኤል ኦስቲን፣ ሆነ ብሎ የእግዚአብሔርን እውነት ርዕሰ ጉዳዮች በሙሉ በስብከቱ ሜኑ ውስጥ አያካትታቸውም። በዚህም ምክንያት ከእግዚአብሔር ክብር ወይም ክርስቶስ ለኃጢያታችን ከከፈለው የኃጢአት ዕዳ ክፍያ ጋር የማይገናኝ ሁለመናው ራስን ስለ ማሻሻል የሆነ፣ የተዛባና፣ ከረሜላ ከረሜላ የሚል "የምኞት ወንጌል" ያቀርባል። ይህ የምኞት ወንጌል ፈጽሞ ወንጌል አይደለም፤ እውነት እላችኋለሁ ግማሹንም ያህል እንኳ ወንጌል አይደለም። ለዚያም ነው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚፈልጉትን የምኞት ወንጌል ለመመገብ ወደ ስፍራው የሚጎርፉት፣ እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች በቲቪ የሚመለከቱት። አስተውሎ ለተከታተለው ሰው፣ የዚህ ሰው ወንጌል ቅዱስና የተፈራ አምላክ የለውም፣ አስፈሪውን መለኮታዊ ፍርድም አያቀርብም፣ የስርየት አስፈላጊነትንም አያሳይም። ምናልባት በእርሱ ስብከት የሚነቃቃ ይኖር ይሆናል እንጂ ንስሃ የሚገባና ከክፉ ስራው ተጸጽቶ የሚመለስ አንድ ሰው የለም። በስብከቱም ራስን ስለመውደድ እንጂ ለራስ ወዳድነት ስለመሞት ፈጽሞ አይናገራትም፣ በእኔነት ላይ ያተኮረ፣ እኔ፣ እኔ የሚለው ስብከቱ ሲደመጥ እውነተኛውን ወንጌል በሚያውቁ ሰዎች ዘንድ እንጨት እንጨት ይላል።
የሰው ሃይማኖተኛ ዝንባሌ ሁል ጊዜ ለገዛ ራሱ ጥቅም ሲል የገዛ ፍላጎቱን የሚያሟላለትን አማላክ ይፈበርካል። ወንጌል ካልገባህ የፈለግኸውን የሚሰጥህንና የአንተ አገልጋይ የሆነ አምላክ ለመፈልሰም አትቦዝንም። ይህ ሰዎችን በምኞት የሚያጠፋ የጤናና የብልጥግና ነገረ መለኮት ወንጌላዊውን ክርስትና ከደረጃው አውርዶ ዝቅተኛ ከሆነው የሰው ሀይማኖቶታዊ ዝንባሌ የማይለይ ተራ የከልት ስርዓት አድርጎታል። አምላክ በሰዎች ምርጫ እጁ የሚጠመዘዝ፣ ፈቃዱን ለመለወጥ የሚገደድ፣ በሰዎች አቀራረብ የሚታለል፣ በማባበያ የሚሸነገል፣ ሰዎች ሊቆጣጠሩትና ወደፍላጎታቸው ሊስቡት የሚችሉትና ክርስቲያኖች ለጥቅማቸው የሚበዘብዙት አይነት ከሆነ እንዲህ ያለው አምላክ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ አይደለም። እንዲህ ያለውን የተፈበረከ አምላክ የተቀበለ ክርስትና ደግሞ አፍሪካዊ ተፈጥሮ ያለውን የቩዱ ሃይማኖት ዓይነት ጣዖታዊ መልክ አለው።
ጆኤል ኦስቲን ምን አይነት ወንጌል እንደሚያስተምር መረዳት እንድንችል 30,000 ለሚሆኑ አባል ቤተ ክርስቲያኑ ከላከላቸው መልእክቶች አንዱን ወስደን እንመልከት፡-
"እርሱ ከከፈለው ዋጋ የተነሳ በድል አድራጊነት የመኖር መብት አለን። ጥሩ ቤተሰብ መመስረት፣ ጥሩ ጤንነት ማግኘት ወደቻልንበት ግማሽ ድል ውስጥ ገብተንም ሊሆን ይችላል፣ በገንዘብ አቅማችን ውስጥ ግን ያለማቋረጥ እየታገልን እንኖራለን፤ ይሄ ግን ፈጽሞ ሙሉ እና አጠቃላይ ድል አድራጊነት አይደለም። እግዚአብሔር በአንዱ ዘርፍ መልካም ካደረገላችሁ በሌላው ዘርፍም መልካም ሊያደርግላችሁ ይወዳል። እንዲህ ላለው ስኬት ግን ራዕይ ይኑራችሁ። በግሌ ብዙ ገንዘብ ያላቸውን ሰዎች አውቃለሁ፣ ጥሩ ጤንነትም አላቸው፣ በቤተሰባዊ ግንኙነቶቻቸው ውስጥ ግን እርስ በርስ መግባባት አይችሉም። በቤታቸው ውስጥ ሁል ጊዜ ጠብና ጭቅጭቅ አለ ፣ ይህ በእውነት ሙሉ በሙሉ ድል አይደለም። ምናልባት ደግሞ እግዚአብሔር ባርኮህ ጥሩ ቤተሰብ እና ጥሩ ስራ ይኖርህ ይሆናል፣ ነገር ግን በሰውነትህ ላይ ለዓመታት እና ለዘመናት የሚታገልህ ህመም ያለብህ ልትሆንና፣ እርሱንም እየተቃወምህ ስትጸልይ ምናልባትም ከህመምህ ነፃ እንደምትወጣ ታምን ነበር። አሁን ግን ይህ በህይወቴ ውስጥ ዕጣ ፈንታዬ ነው…ብለህ ተቀብለኸው መኖር ከወሰንክ በጣም ብዙ ጊዜ አልፎታል፣ አንድ ነገር ግን እወቅ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንድንሆን ኢየሱስ ዋጋ ከፍሏል። ይህ ማለት ከመጥፎ ልማዶች እና ከሱሶች ሁሉ፣ ከተስፋ መቁረጥ እና ከጭንቀት ሁሉ፣ ከድህነት እና ከእጦት ሁሉ፣ ነፃ እንድትሆን፣ ለራስህም ከፍ ያለ ዋጋ እንዳትሰጥ ከሚያደርግህ የዝቅተኛነት ስሜት ነፃ እንድትሆን ማለት ነው። እግዚአብሔር ፍጹም ነፃ እንድንሆን ይፈልጋል። ቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ የሞተለትንና የተነሣበትን ሁሉ እንድንቀበል ይነግሩናል። እግዚአብሔር ጤናማ እና ሙሉ አድርጎሃል፣ የእኛ ቀዳሚ ስፍራም ሙሉ ነፃነት ነው... አማካኝ ቦታ ላይ እንድትሆን አለመፈጠርህን አረጋግጥልሃለሁ። በጭንቅ ውስጥ እንድታልፍ እና ክፉንም ደጉንም ሁሉንም አይነት ነገሮች እንድትቀበል አልፈጠረህም። ትክክለኛውን የህይወት ራዕይ ማግኘት አለብህ። እግዚአብሔር የፈጠረህ ፍፁም ነፃ እንድትሆን፣ በአእምሮህ ሰላም እንዲኖርህ፣ በመለኮታዊ ጤንነት እንድትመላለስ፣ ጥሩ ቤተሰባዊ ግንኙነት እንዲኖርህ፣ የብድር ዕዳህን እንድትከፍልና ከብድር ህይወት ነጻ እንድትሆን፣ እንድትበዛና እንድትትረፈረፍ ነው። ይህ ሁሉ የሚገባህና ልዩ መብትህ ነው። ከነዚህ መብቶችህ ውስጥ አንዱ አጠቃላይ ድል ነው። ነፃ ሆኖ መኖር ያለ ጥርጥር ይገባናል፣ ይህም ማለት በአእምሯችን ነፃ ሆነን ከጭንቀት ሁሉ የጸዳን መሆን ማለት ነው። የባንክ ሂሳባችን ምንም አይነት ቢመስልም፣ ከድህነት እና ከእጦት የጸዳ መሆን ማለት ነው። አመለካከታችንም ተለውጦ እኔ እንደተባረኩ አውቃለሁ፣ የተረገምሁ ልሆንም ፈጽሞ አልችልም። እኔ የነካሁት ሁሉ ይበለጥጋል ይሳካለታልም እንድንል ነው"።
ይህ እንግዲህ የጆኤል ኦስቲን ንግግር ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በወጉ ላልተማሩ ሰዎች ይህ ንግግር ምንም ችግር የሌለበት ሆኖ ይሰማቸዋል። የክርስቶስን ወንጌል ተፈጥሮ ስታውቀው ግን ይህ ንግግር ወንጌልን የሚበርዝ በማር የተለወሰ መርዝ መሆኑን አስተውለህ ራስህንና የሚሰሙህን ከዚህ የጥፋት ወንጌል ለማዳን ትናጠቃለህ። ልብ አድርጉ፣ በዚህ ሰው ትርጓሜ መሰረት ከእግዚአብሔር ጋር በመንፈሳዊ ብስለት መሄድ ማለት ባለጠጋ መሆን ማለት ነው፣ ጤናማ፣ የማይታመም፣ ጥሩ ቤተሰባዊ ግንኙነት ያለህ፣ ሁልጊዜ ያለ ህመምና ያለ ጭንቀት በድል አድራጊነት እየኖርክ በሁሉ ቀዳሚና አንደኛ ሆነህ እንደ ባለ መብት መኖር አለብህ ማለት ነው። የዚህ አመለካከት ችግሩ ግን ኢየሱስ የኖረውን ህይወትና መላው የአዲስ ኪዳንን ቤተ ክርስቲያን ያለፉበትን የህይወት ትግል ያገለለ መሆኑ ነው።
የዚህን ሰባኪ ንግግር ካደመጣችሁ በኋላ፣ ኢየሱስና በወንጌሉ የምናውቀው ኑሮው ከዚህ ሰው አሳብ ጋር እንዴት ነው ሚስማሙት? ብላችሁ ጠይቁ። በውኑ ወንጌሉ የሚያስተዋውቀን ኢየሱስ ባለጠጋ ነበርን? ደልቶትስ ይኖር ነበርን? ፈጽሞ እንደዚያ አልነበረም! በሶስት ዓመት ተኩል አገልግሎቱ፣ የሚጠለልበት እንኳን ሳይኖረው በምድር ላይ እየተንከራተተ በድህነት ኖረ (ሉቃስ 9፥ 58)፤ የሚያርፍበት ቤት አልነበረውም፣ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ለማግኘት ሁልጊዜም ቢሆን የሌሎች ድጋፍ አስፈልጎት ነበር። ብዙዎች የብልጥግና ወንጌል አጋፋሪዎች ግን ይህንን የእግዚአብሔር ልጅ ኑሮ "ድህነት" ነው ብሎ ለመጥራት ይፈተናሉ።
ኢየሱስ በማበራዊ ግንኙነቱ ላይ ችግር ነበረበትን? ተመልከቱ ሁሉም የሃይማኖት መሪዎች ይጠሉት ነበር፣ የገዛ ቤተሰቦቹ ንቀውት ነበር፣ ጴጥሮስ ክዶታል፣ ይሁዳ አሳልፎ ሰጥቶታል፣ ሕዝቡም ሁሉ "ስቀለው ስቀለው" እያሉ ጮኸዋል። ጌታ ኢየሱስ በማህበራዊ ግንኙነቱ ውስጥ ጆኤል ኦስቲን በሚናገርለት አይነት በድል አድራጊነት እየኖረ እንዳልነበር አስባለሁ። ብዙዎች ተወዳጅነትና ከበሬታን ነፍገውታል። ከከበሩትም ሰዎች መካከል የሚበዙት በቀንና በአደባባይ ከእርሱ ጋር መታየትም ሆነ ሊተባበሩት አይፈልጉም ነበር። ኢየሱስ የህማም ሰው ነበር። ከባድ ሥቃይ ደርሶበታል። ተገርፏል፣ ጉሰማና ድብደባ ደርሶበታል። አዋርደው ተፍተውበታል፣ እርሱ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዲገደል በእግዚአብሔርም በሰውም የተተወ የህማም ሰው ነው። ስለዚህ ጆኤል ኦስቲን እየተናገረለት ያለው ይህ አይነቱ የድል ሕይወት በኢየሱስ አልተኖረም። መፅሃፍ ቅዱስም በግልጽ ሲያስተምረን እርሱን መስለን መኖር እንዳለብን ይናገራል።
1ዮሐንስ 2፥ 6 "በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።"
እንግዲህ ይህን ካደረግንና እንደ ኢየሱስ የምንኖር ከሆነ ኢየሱስ ያጋጠመውንና ያለፈበትን ዓይነት የህይወት ውጣ ውረድ እኛም ያጋጥመናል። ክርስቶስ እንደኖረ ከኖርን ጆኤል ኦስቲን የሚሰጠውን ሃሰተኛ የድል ሕይወት ተስፋ አናይም። የኢየሱስ ነኝ የምትሉ ሁሉ ስሙኝ፣ በጤንነት ብልጥግና ወንጌል ኃሰተኛ ተስፋ ተታላችሁ ኢየሱስ በስጋው ወራት ያልኖረውን የቅምጥል ህይወት ለመኖር አታስቡ።
የጌታችን ደቀመዛሙርትስ እንዴት ነበር የኖሩት? በአጠቃላይ የድል ኑሮ የሚኖሩ ህመም የማያውቃቸው ፍጹም ጤነኛ ነበሩን፣ ባለጠጎችስ የነበሩና በምድራዊ ፍላጎቶቻቸው ጉድለት ያላዩ ነበሩን? በጭራሽ ቅምጥሎችም አልነበሩም ያንንም ተስፋ አድርገው አልተመኙም! ተመልከቱ ከሐዋርያት መካከል አንዳቸውም ባለጠጋ አልነበሩም። ሁሉም ሊታመን የማይችል ፈተናና መከራ ነበረባቸው፣ ቢያንስ የጳውሎስን ጉዳይ እንኳ ብናነሳ መሰረታዊ የቁሳዊ ጉዳዮች እጦት እና ከባድ የጤና ችግሮች ለህይወቱም አስጊ የነበሩ ተስፋ አስቆራጭ ከፍተኛ ፈተናዎች ደርሰውበታል።
ሐዋርያው ጳውሎስን ከእግዚአብሔር ጋር በመልካም ኅብረት የተራመደ፣ ነፍሱ የተከናወነለት የእግዚአብሔር ሰው ነበርን? አዎ በሚገባ ነበር። እግዚአብሔር ራሱ በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት እያደረገ፣ ለድውዮችም ከአካሉ ላይ ጨርእቅ ወይም ልብስ ይወስዱ እንደነበር እናውቃለን። አብዛኛውን አዲስ ኪዳንን እንዲጽፍ እግዚአብሔር ጳውሎስን በብዙ ተጠቅሞበታል። ጳውሎስ ግን በማህበራዊ በግንኙነት ላይ ችግር አጋጥሞት ያውቃልን? አዎ። በእርግጥም እንዲህ ያለው ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው በሰዎች መተውና መረሳት ደርሶበት ያውልቃ፤ አመዛኙን ህይወቱን ያሳለፈውም ወህኒ ቤት ውስጥ እንደነበር እናውቃለን፦
2ጢሞቴዎስ 4፥ 16 "በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፥ ሁሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው፤"
አካላዊ ሕመምን በተመለከተስ? ፣ ጳውሎስ የአካላዊ ጤና ችግር ነበረበትን?
2ቆሮንቶስ 12፥ 7 "ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው።"
እዚህ ላይ ጳውሎስ አካላዊ የጤንነት ዕክል የነበረበት መሆኑን እናያለን። ይህን ችግር ያጋጠመው ለምን እንደሆነም የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። በጠቅላላ ህይወቱ በድል ስላልተራመደ ወይም መንፈሳዊ የሕይወት ድካም ስለነበረበት ሳይሆን ይልቁንም ትህትናውን ጠብቆ ለማቆየት እግዚአብሔር የተጠቀመበት መንገድ ነበር። "እግዚአብሔር ለትሑታን ጸጋን ይሰጣልና" ያ ደግሞ መልካም ነገር ነው።
2ቆሮንቶስ 12፥8 "ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ።"
ይህንን ችግር እግዚአብሔር እንዲወስድለት ጳውሎስ በጸሎት ጠየቆ ነበር። እግዚአብሔር ግን የሰጠውን መልስ ልብ በሉ፦
2ቆሮንቶስ 12፥ 9 "እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።"
ጳውሎስ በድህነቱና በሥቃዩ ላይ ስለተቀዳጀው አጠቃላይ ድል ይመካ ነበርን? ደስታውስ ይህ የጤናና የኢኮኖሚ ችግር ከእርሱ ስለተለየ ነበርን? ፈጽሞ ደስታውም ትምክህቱም በዚያ አልነበረም! ይልቁንም በነዚያ ድክመቶቹ ሲመካ ይታያል። ይህ ለምን እንደሆነ ልብ አድርጉ፦
2ቆሮንቶስ 12፥ 10 "ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።"
ልብ አድርጉ፣ ይህ የጤና/ብልጥግና ወንጌል የተባለ የትምህርት አረም ይህንን እውነት ሙሉ በሙሉ ስቶታል። ጳውሎስ፣ “ስደክም፣ ማለትም በዚህ አካላዊ ሕመሜ፣ በማልፍበት እጦትና ድህነት፣ በሚገጥመኝ የማህበራዊ ተቀባይነት እጦት፣ በመከዳቴ እና በሰዎች በመረሳቴ እመካለሁ፣ ደስ ይለኛል” ሲል ተናግሯል። አያችሁ፣ በሕይወታችን ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሙን ያኔ ነው እንደ ጳውሎስ ወደ ክርስቶስ የምንዞረው እና በኃይሉ የምንታመነው።
የጳውሎስን የግል የህይወት ምስክርነት ተመልከቱ እና ምን ያህል ከጆኤል ኦስቲንን አጠቃላይ የድል ኑሮ ሃሳብ እና አስተምህሮ ጋር መስማማት አለመስማማቱን መዝናችሁ እዩ፦
2ቆሮንቶስ 11፥ 23-27 "እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።"
ጆኤል ኦስቲን ይህን ምስክርነት አንብቦ ያውቃልን? እንጃ። ለክርስቶስ መኖር እና እግዚአብሔርን በመታዘዝ መመላለስ ለጳውሎስ ይህን ይመስል ነበር። ምን ያህሎቻችሁ ለእንደዚህ አይነት የህይወት ስርአት መፈረም ትሻላችሁ? ጆኤል ኦስቲን ይህንን ህይወት የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ብሎ ለአማኞች ሰብኮ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለ ትልቅ የሕንፃ ካቴድራል ባልኖረውም ነበር።
፬.
ያለህባት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ሀብት ሰጥቶ ባለጠጋ ሊያደርግህ እንደሚፈልግ የምታምን ከሆነ፣ ፓስተርህም ይህንንው እየደጋገመ ሲሰብክ፣ አንተ ግን "በእምነትህ ማነስ " ምክንያት ከዚህ እንደጎደልህ ማወጅና ማስተማር ሲጀምር፣ እንዲህ ያለው ይህ የትምህርት እብደት በተለይ በድህነት ውስጥ ለሚኖሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ሰዎች ምን ማለት ይሆን?
ተመልከቱ በገጠራማዋ የኢትዮጵያ መንደሮች በየእሁዱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማምለክ 3 በ 5 ስፋት ባላት አነስተኛ "የጸሎት ቤት" ውስጥ ወይም በዛፍ ጥላ ስር ይሰበሰባሉ። ያቺ ቤተመቅደስ በሰዎች አይን የምታምር አይደለችም፣ ነገር ግን በምድር ላይ ካሉት በጣም ድሆች ከሆኑ አማኞች ጥቂቶቹን በአባልነት ያቀፈች ቤተክርስቲያን ናት። ነገር ግን የእነዚህ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ ዝቅተኛነት ያለባቸውን መንፈሳዊ የበታችነት አያመለክትም። እርግጥ ነው እነዚህ ሰዎች እንደብዙዎቹ ምዕራባውያን የጤና እንክብካቤ ዋስትና የላቸውም፣ ነገር ግን በህመማቸው ጊዜ ጌታ እንዲፈውሳቸው በጸሎት ይጠይቃሉ። ምናልባትም ከብዙዎቻችን በተለየ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ላይ የመተማመን እጅግ የላቀ ደረጃ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ሰዎች "የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን" ብለው ሲጸልዩ - በእርግጥ ለማለት ያህል በልማድ ሳይሆን የምራቸውን መለመናቸው ነው። በጣም መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ሊሰጣቸው እንደሚችልም በእግዚአብሔር እየታመኑ ውሱን በሆኑ ግብአቶቻቸው በገዛ እጃቸው ለሥራ ይተጋሉ እንጂ አይለግሙም።
የሚቀጥለው ምግብ እንዴትና ከየት እንደሚመጣ የማያውቁ ነገር ግን መንፈሳዊ ኃያላን የሞሉባት እንዲህ ያሉ ታናናሽ መንጋ ያሏቸውን ታናናሽ የቅዱሳን ማህበራት ኢትዮጵያን ከመሰሉ የአፍሪካ ገጠራማ መንደሮች ማግኘት የተለመደ ነው። ሆኖም በድህነታቸውና በሥቃያቸው መካከል እግዚአብሔርን በደስታ ውዳሴ ሲያመልኩት ነፍስ አይቀርላቸውም። እኔ ከወንጌል እንደምረዳው ጆኤል ኦስቲን ከሚደሰኩረው ኃሰተኛ የድልና የስኬት ህይወት ይልቅ ፍጹም ድል ይህ ነው።
ምእመናን አጥብቀን ልንረዳው የሚገባን እውነት እዚህ አለ፤ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ውስጥ መኖር እንደሚገባው ያህል በጽድቅ ሕይወት በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ ወንጌልን በኃይል ለማስፋፋት እና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ እየተጋደሉ ለጽድቅ ሲቆሙ የዚህ ተፈጥሮዋዊ ውጤት መከራ መቀበል ይሆናል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ይህንን እንዲረዱ ይፈልጋል፣ መከራንም እንዲጠብቁ ያስተምራል። ጳውሎስም እንዲሁ ሲያመለክተን፡-
2ጢሞቴዎስ 3፥ 12 "በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።" ይላል።
ይህ ጥቅስ ክርስቲያኖች ሁሉ በጅምላ ስደትን መጠባበቅ ይችላሉ አይልም። ይልቁን ምን ይላል? "በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።" ነው የሚለው። መከራንና ስደትን ወዳለንበት ስቦ የሚያመጣው እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት ነው። ማለትም ከእግዚአብሔር ጋር ስትቆም፣ ኃጢአትን ስትቃወም፣ ውርጃን፣ ግብረ ሰዶማዊነትን፣ ተመሳሳይ ጾታዊ ጋብቻን ስትነቅፍ እና የስነምግባር ዝቅጠትን ተቃውመህ ስትናገር፣ ያኔ በዚህ ምክንያት ስደት ሊደርስብህና መከራን ልትቀበል እንደምትችል ጠብቅ!
ጳውሎስ በብዙ መልዕክቶቹ የንባብ ክፍሎች ላይ መከራና ስቃይ የሐዋርያዊ አገልግሎት አስፈላጊ አካል እንደሆ በማሰብ ጽፏል። በሌሎች ክፍሎች ግን ጳውሎስ መከራን እና ስቃይን በሐዋርያት አገልግሎት ላይ ብቻ አልወሰናቸውም። ይልቁንም አለፍ ብሎ የደቀመዝሙርነት ኑሮ አስፈላጊ አካል እንደሆነም ያመለክታል። ይህም ትምህርት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ወጥነትና ቀዋሚነት ያለው አጽንዖት ነው። ችግሮችና ፈተናዎች፣ ተግዳሮቶችና ግጭቶች ህመምም ከደቀመዝሙርነት ኑሮ ጋር የማይነጣጠሉ ሆነው የተቆራኙ ናቸው።
ምእመናን፣ ልንረዳው የሚገባን አንድ ጉዳይ ህመምና ስቃይ ድኅነትም የዚህ ሕይወት ሥርአትና አካል ናቸው፤ ክርስቲያን መሆናችንም ሆነ የድል ኑሮ መኖር ደግሞ ሁሉም ከህይወታችን እንዲወገዱ አያደርጋቸውም። ጥበበኛ፣ ቅዱስ እና አፍቃሪ የሆነው አምላካችን በህመማችን እና በመከራችን ውስጥ የማይመረመር አላማ አለው። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የሚነገራቸውን ልብ አድርጉ፦
2ቆሮንቶስ 1፥ 8 "በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤"
ይህ ጆኤል ኦስቲን የሚናገርለትን አጠቃላይ የድል ኑሮ ፈጽሞ አይመስልም። ጳውሎስ ግን እርሱና ባልደረቦቹ መከራ ለምን እንደደረሰባቸው በግልጽ ነግሮናል፣ ተመልከቱ፦
2ቆሮንቶስ 1፥ 9 "አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።"
ወገኖች ሆይ፣ መከራን መቀበል በራስ የመደገፍ ኃጢያትን ከላያችን ያራግፍልናል። ብዙ ወንዶች እና ሴቶች የእግዚአብሔር ልጆች እግዚአብሔር ይህን ትምህርት በህይወታቸው እንዳስተማራቸው፣ በእርሱም ላይ ጥገኛ እንዳደረጋቸው፣ በስህተት የተመኩባቸውን ነገሮቻቸውን ሁሉ ከውስጣቸው ነቅሶ በማውጣት የእርሱ ተደጋፊ እንዳደረጋቸው መስክረዋል። በአብዛኛው የሚያጋጥመን ሥቃይና መከራ አላማው በእግዚአብሔር ጸጋ እና ኃይል ላይ ብቻ የማይቋረጥ ጥገኛነትን ማምጣት ነው። መከራችን ፍጥረቱ የተነደፈውና የተሰራው በእኛ በራሳችን እንድንደገፍ ሳይሆን በእግዚአብሔር ችሎታ፣ ኃይል እና ዝግጅት እንድንመላለስ ነው። እርሱ ብቻ በገዛ ራሳችን አለን ከምንለው ሀብታችን እያላቀቀ ወደ ባለጠግነቱ ዘወር እንድንል ያደርገናል።
ምእመናን ይህን ስሙ፣ ሌሊቱ ሲነጋ፣ ፀሀይ ስትወጣላችሁ ሰማዩ ጥርት ያለ ሲሆን፣ የተነቃቃ ታላቅ ስሜት ሲሰማችሁ፣ ብዙ ገንዘብ ያላችሁና "ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም" ለማለት ስትፈተኑ፣ ሁሉም ሰው ሲወዳችሁና ሁሉንም ሰው ስትወዱ፣ ተቀባይነታችሁና ተፈላጊነታችሁ ሲጨምር፣ ያኔ በእርግጠኝነት እግዚአብሔርን ችላ የማለት ዝንባሌ መኖሩ አይቀርም። እንዲህ ባለው ስኬት በሚመስል ውድቀት ውስጥ በራሳችን የመታመን እና እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ የመርሳት ዝንባሌ በእርግጥ አለ። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ስለ ብልጽግና አስጠንቅቋቸው የነበረው ለዚህ ነው።
ዘዳግም 8፥ 11 "ዛሬ እኔ አንተን የማዝዘውን ትእዛዙንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፤"
እግዚአብሔር እዚህ ላይ እስራኤላውያንን የሚያስጠነቀቃቸው፣ ስለ ድህነት አደጋ ሳይሆን ስለ ሀብት አደጋ ነው እያስጠነቀቃቸው ያለው።
ዘዳግም 8፥ 12-16 "ከበላህና ከጠገብህ በኋላ፥ መልካምም ቤት ሠርተህ ከተቀመጥህበት በኋላ፥ የላምና የበግ መንጋ ከበዛልህ በኋላ፥ ብርህና ወርቅህም ያለህም ሁሉ ከበዛልህ በኋላ፥ ልብህ እንዳይጓደድ፤ ከግብፅም ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን፥ እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለባት፥ ውኃም በሌለባት፥ በታላቂቱና በምታስፈራው ምድረ በዳ የመራህን፥ ከጭንጫ ድንጋይም ውኃን ያወጣልህን፥ በመጨረሻም ዘመን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሊፈትንህ ሊያዋርድህም አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤"
ልባቸው እንዲጓደድ፣ በትዕቢት እንዲኮሩና ጌታን እንዲረሱ የሚያደረጋቸው ድህነታቸው ሳይሆን የሚያከማቹት ሀብት መሆኑን ልብ በሉ።
ይህንኑ ሃሳብ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ እናያለን።
ምሳሌ 30፥ 8-9 "ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፤ ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም፦ እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።"
ስንጠግብ፣ ሁሉም ነገር ሲስተካከል ጌታን የመካድ አደጋም አብሮት አለ።
ቅዱሳን ስሙኝ፣ በእውነቱ ለአንድ አማኝ የዚህ ምድር ህይወቱ በጣም ከባድ ሊሆንበት የሚችል መሆኑ ነው፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ስንታመን ጤናንና ሀብትን ሊሰጠን የገባው ቃል የለም። እግዚአብሔርን በመምሰል የምንኖር ከሆነ ግን ስደት እንደሚደርስብን ቃል ገብቷል። የወንጌል መልእክትም እነ ጆኤል ኦስቲንና መሰሎቻቸው አጣመው እንደሚያስተምሩት በድህነት እና በበሽታ ላይ፣ በማህበራዊ ግንኙነቶችም ተቀባይነት ማጣት ላይ በድል አድራጊነት ፈጽሞ ስለመኖር አይደለም። ወንጌል በብቸኝነት የሚናገረው እግዚአብሔር በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ የኃጢአትን ዕዳ ለመክፈል የሚወደውን አንድያ ልጁን መስዋዕት አድርጎ ስለማቅረቡ ነው። እግዚአብሔር የዘላለም ሕይወትን ሊሰጠን እንጂ የሀብትና የመጽናናት ሕይወት እንድንኖር ቃል አልገባልንም።
እግዚአብሔር በእርሱ እንድንታመንና፣ በእርሱ ላይ በመታመን ብቻ እንድንኖር ይፈልጋል፣ ያንንም ለማድረግ የሚረዱን የህይወት ፈተናዎቻችን ናቸው።
ስለዚህ ጆኤል ኦስቲን "አጠቃላይ የድል ህይወት" እያለ በሚሰብከው የቅዠት አለም ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጽሞ እንዳልኖረበት ወንጌሉ ነግሮናል፤ ሐዋርያትም ሆኑ የየዘመኑ ቅዱሳን ሁሉ ባለፉት ዘመናት እንዲህ ባለ ቅዠት አልኖሩም። ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ስትጠጉ ይህ የጤና/ብልጥግና ወንጌል ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዳልሆነ ታያላችሁ። ታዲያ ብዙዎች ይህንን የውሸት መልእክት በውድ ዋጋ እየገዙ ወደዚህ ትምህርት የሚሳቡት፣ የነዚህ ኃሰተኞችስ ግባኤ በብዙ ቁጥር እያደገ የመጣው ለምንድነው? በመጀመሪያ ስለ እድገታቸው መገረምና መደነቅ የለብንም ምክንያቱም ካንሰርም ያድጋል። እኔ እንደማስበው ግን የዚህ እድገት ዋናው ምክንያት የትምህርቱ ድምጸት በጣም ጥሩ ስለሚመስል ነው። መቼም ቢሆን ጤናማ ለመሆን፣ ሀብት ለማግኘት፣ ከችግርም ነጻ የሆነ ኑሮ መኖር የማይፈልግ ማን ሰው አለ? ስለዚህ የስብከቱ ድምጸት ጥሩ ስለሚመስል ብዙ ሰው ይከተለዋል። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በቅጡ ስለሚያውቁ፣ አብዛኛው ግን ቃሉን መማርና ማወቅ እምቢ ስላለ፣ ወይም ንጹሁን ወንጌል የሚያስተምረው ስላጣ ይህ የጤና/ብልጥግና ወንጌል እግዚአብሔር ለእነርሱ እንዲሰሙትና እንዲከተሉት የሚፈልገው ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው። አማኞች በዚህ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ አጉል ትምህርት ውስጥ ሲጠመዱ ስናይ በቅዱሳን መካከል ይህንን የሚመዝን መለኪያ ድምጽ በመሆን ኃሰትን ለመጋፈጥ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት አውቀን ልንቆም ይገባናል።
በአገራችንም እንደ አሸን የፈሉት የጥፋት ወንጌል ሰባኪዎች ቢከፍቱት ተልባ የሆነው ዲስኩራቸው ምንጩና መሰረቱ ይኸው ከላይ በስፋት የተቸነው መስቀል አልባ የትምህርት ቅዠት ነው። ስራ ጠል የሆኑ ቁጭ ይበሉዎች በኃሰተኛ ትንቢታቸው እያዋዙ ሕዝብ በሚያደነቁሩበት የትባረካላችሁ ስብከት መንጋው እየከሳ ዘርፈው የጠገቡ እነርሱው ብቻ ናቸው። "ማን መጥቶ ባሳሳተን" በሚል ክፉ ምኞት ተይዘው ላይ ላዩን የሚጋልቡና አጥብቀው የማጠይቁ ሰነፍ የቤተስኪያን ደንበኞችም ይጠፉ ዘንድ ለዚህ የተመደቡ ናቸው፤ ቃሉንም ከመማር ርቀው በዝነኞቻቸው የትምህርት ንፋስ ተጠርገዋል። ብዙ ዘመን በውሃ ውስጥ የኖረ ጥቁር ድንጋይ ውሃው ወደውስጡ እንደማይገባ ሁሉ እነዚህም ደጋግመን በወንጌል ያስጠነቀቅናቸው ሆነው ሳሉ ትምህርታችንና የምክር ቃላችን አልገባቸውም።
እንግዲህ በብዙ ዝርዝር ልናየው የሞከርነውና ይህ “የጥፋት ወንጌል” ስል የሰየምኩት የጤና/ብልጥግና ወንጌል አደገኛነቱ ሊሰማን ይገባል። የዚህ ወንጌል አራማጆች እንደሚደሰኩሩት እግዚአብሔር አማኞች ሁሉ ጤናማና ባለጸጋ እንዲሆኑ፣ ከየትኛውም አካላዊ ስቃይና መከራ ነጻ እንዲሆኑ፣ በሚያደርጉት በማናቸውም ነገር እንዲበለጽጉና እንዲከናወንላቸው ይፈልጋል ብለው ያስተምራሉ። በመግቢያዬ ላይ እንዳመለከትኩት ይህ ጥሩ ዜና ይመስላል። ብቸኛው ችግሩ ግን እውነት አለመሆኑ ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ወንጌል ሳይሆን ሰዎች ሊሰሙት የሚፈልጉት "ማጽናኛ" (ማዝናኛ ቢባል ይቀላል) እና ስሜትን የሚኮረኩር ማነቃቂያ ብቻ ነው።
የዚህ የጤና/ብልጥግና ወንጌል ሰባኪዎች የሚያደርጉት አንድ ክፉ ስራ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሀብት የሚናገረውን ዋና መልዕክት ገልብጠው ስሜታችን ሊሰማው የሚፈልገውን እየደሰኮሩ ባህላችን ስለ ሀብት/ብልጽግና በሚናገረው ለመተካት የሚያደርጉት እውር ጥረት ነው። እርግጥ ነው፣ “እግዚአብሔር ባለጠጋ ሊያደርግህ ይፈልጋል” የሚለውን መልእክት ስትሰብክ፣ ትርጉሙ አጠቃላዩ የወንጌል መልእክት ስለ እኛና ስለ ፍላጎቶቻችን ነው የሚል ብቻ ሳይሆን፣ ወንጌሉ እግዚአብሔር ፍላጎቶቻችንን እንዲያሟላልን የምናደርግበት መንገድ፣ በራሳችንም ላይ ብቻ እያተኮርን ራስ ተኮር በሆነ ህልማችን የምንወሰድበትም ጭምር ይሆናል። ያኔ የእኛ ትክክለኛ የህልውናችን ማእከልም የፍላጎቶቻችን መሟላት እንጂ ራሱ እግዚአብሔር አይሆንም። ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኘው ከእግዚአብሔር ልናገኘው በምንችለው ነገር ብቻ ነው ማለት ነው። ትክክለኛው የህልውና ማእከላችንም "እግዚአብሔር ስኬታማ የአኗኗር ደረጃዬን ይባርክልኝ" በሚል ምኞት የሚነዳ በራሳችን ላይ ያተኮረ የብልጽግና እና የስኬታማ የህይወት ዘይቤአችን መሆኑ ነው።
(gkr)