እርግጠኛው አይቀሬ
"μέλλω" (ሜሎው) የተሰኘው የግሪክ ቃል እና ነገረ ፍጻሜአዊ ጠቀሜታው ሲፈተሽ
አዲስ ኪዳን ከተጻፈበት የግሪክ ቋንቋ በቀጥታ ወደ እንግሊዝኛም ይሁን ወደ ልዩ ልዩ ጥንታዊና ዘመናዊ ቋንቋዎች የተደረጉ ትርጓሜዎች በየዘመኑ ላሉ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅስዱ በገጾቹ የያዘውን ቁምነገር ለመረዳት እንዲችሉ ሲያግዟቸው ኖረዋል። መጽሐፍ ቅዱስን በተለያየ ቋንቋ ተርጉመው ያቀረቡልን አብዛኞቹ ተርጓሚዎች በተለይ ለበኩረ ቋንቋው ለግሪኩ ታማኝ ለመሆን የተቻላቸውን ጥረት ሁሉ ያደረጉ መልካም ሰዎች ናቸው። በአማርኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ተሳትፎ ለነበራቸው አባቶችም ልዩ አክብሮት አለኝ። ዳሩ ግን የግሪኩን ቅጂ እያየን አማርኛችንንም ሆነ እንግሊዝኛውን እያጣቀስን እና እያመሳከርን ስናጠና ከቃላት አገባብንና ከሚሰጡት ትርጉም አንጻር ጉልህ ልዩነት የሚያደርጉ እንዳንድ ጉዳዮች ይኖራሉ፤ በተለይ መሰረታዊ አስተምህሮዎችን ሊቀርጹ ጉልበት ያላቸው ቃላትና ሃረጎች ሲሆኑ የበለጠ ያሳስባሉ።
በዚህ ረገድ ከነገረ ፍጻሜአዊ ይዘቷ አንጻር ከፍ ያለ ዋጋ ያላት፣ ነገር ግን ብዙዎች ልብ ያላልዋት μέλλω "MELLO" የተሰኘች አንዲት የግሪክ ቃል እናገኛለን፤ ግሱ በእንግሊዝኛው "ABOUT TO BE" በአማርኛው "ሊሆን ያለው" በሚል መተርጎም የነበረበት ይህ ሐረግ የያዘው ቁም ነገር ብዙም ትኩረት ሳይስጠው በብዙዎች በቀላሉ እንደታለፈም እንታዘባለን። ይህች μέλλω "MELLO" [በእንግሊዝኛው፣ ABOUT TO BE ጎግል ሲፈታው፦ Be (just) about to allows us to express an imminent action, or a very near future: ይልና፤ The train is just about to leave. The train will leave very soon. የሚል ምሳሌን ይሰጠናል] የተሰኘች አንዲት ቃል ግን በውስጧ ከጊዜ አንጻር በእጅጉ ቅርብ የሆነን ጉዳይ እርሱም የማይቀር እርምጃን ጓጉቶ የመጠባበቅን ጽንሰ አሳብ ይዛለች። ቃሉ ሊከሰት፣ ሊመለስ፣ ሊመጣ፣ ሊደርስ ወዘተ ያለ ነገርን 'ሰፍ ብሎ' መጠበቅን ሲያመለክት፣ የጉዳዩን ቅርበት የሚያሳይና 'እነሆ ሊሆን ነው' ብሎ በመጠባበቅ ስሜት፣ በተለይ ከጊዜ አንጻር በቅርብ ርቀት የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ የግድ መሆን ያለበትንና፣ እንዲሆን የተወሰነን አንዳች ነገርን የሚያመለክት፣ ስለሚሆነውም ነገር እርግጠኛነት የሚናገር የግሪክ ቃል ነው። [ለበለጠ ግንዛቤ Strong's word 3195፤ እንዲሁም ግሪክ ሌክሲከን /Greek Lexicon/ ላይ መሰረቱን አድርጎ የተዘጋጀው የጣየር እና የስሚዝ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ በተጨማሪም ሌሎች እንደ Theological Dictionary of the New Testament ያሉ ሰነዶችን ማመሳከር ይቻላል።]
ዘመናዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተዘጋጁበት ጊዜ፣ μέλλω "MELLO" (ABOUT TO BE) የተሰኘችው ቃል/ሀረግ በኢየሱስና በሐዋርያቱ ንግግር ውስጥ ያላት ጠቀሜታ ተርጓሚዎችን እንዳስቸገራቸው በብዙ ልንታዘብ እንችላለን። እነዚህ ተርጓሚዎች በአመዛኙ በነገረ ፍጻሜ እምነታቸውና አቋማቸው ገና ወደፊት ይመጣል ባይ "መጻኢያን" ስለሆኑ፣ ከዚህ የተነሳ ምንም እንኳ ይህች ቃል በያዘችው ትርጉም "ሊመጣ እንዳለው" μέλλω MELLO (ABOUT TO BE) ብላ እያስተማረች ቢሆንም እንኳ፣ እነርሱ ግን የሚመጣው ገና ወደፊት የሚመጣ እንደሆነ μέλλω "MELLO" (ABOUT TO BE) ሲተረጉሙ፣ የፍጻሜውንም ጊዜ ቅርበት አዲስ ኪዳንን በጻፉልን ሰዎች የህይወት ዘመን ውስጥ ማሰብ እና በዚህ ደርዝ ትርጉሙን ማስቀመጥ እንዳልተቻላቸው በግልጽ እናያለን። ስለዚህ የቃሉን ጠቀሜታ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፣ ወይም ሆን ብለው በነገረ ፍጻሜ አመለካከታቸውና አቋማቸው ተጽዕኖ ስር ወድቀው፣ ቃሉ ቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ጨርሶ እንዳልነበር ሁሉ፣ ይህንን MELLO የተሰኘ ቃል በአመዛኙ ትርጉማቸው ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው አድርገዋል። የዚህ ጽሁፍ አላማ የቃሉ ወዳጆችና ተማሪዎች የሆኑ የመሰማርያው በጎች በአንዲት ትንሽዬ ቃል የተነሳ ቅዱስ ቃሉ የሚለውን እንደማይል፣ የማይለውንም እንደሚል አድርገው የማሰብም ሆነ የመማር አደጋ ውስጥ እንዳይወድቁ፣ በእውነትም ግራ ከመጋባት የተጠበቁ ይሆኑ ዘንድና ከነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ አንጻር ጊዜ ጠቋሚ ለሆኑ ምንባባት ተገቢውን ትኩረት እንዳይነፍጉ ለመርዳት መሆኑን ልብ አድርጉ።
በዚህ መሰረት ምሳሌ የሚሆኑን ጥቅሶችን ከተወሰኑ ማብራርያዎች ጋር እየተመለከትን ይህ mello የተሰኘ አንድ ቃል በተለይ ከነገረ ፍጻሜ ጠቀሜታው አንጻር በየምንባባቱ ውስጥ ያለውን አገባብ አብረን እንድንፈትሽ በአክብሮት እጋብዛችኋለሁ።
ማቴዎስ 3፥ 7 (ሉቃስ 3፥ 7) "ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው [ሊመጣ ካለው/ mello] ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?" ["ሊመጣ ያለው ቁጣ" እንጂ "የሚመጣ ቁጣ" አይደለም]
መጥምቁ ዮሐንስ በዚህ አውድ ለአይሁድ ህዝብ እየሰበከ መሆኑን እናያለን፤ በስብከቱም በቅርቡ ስለሚደርስባቸው የእግዚአብሔር ቁጣ የአይሁድን የኃይማኖት መሪዎችን ያስጠነቅቃል። ቁጣው መቼ እንደሚመጣ የማይታወቅ ግን የሚመጣ ቁጣ ሳይሆን፣ የሚመጣበት ጊዜ የቀረበ ወይም በቅርብ የሚመጣ ቁጣ ነው። ኢየሱስም በሌላ ስፍራ በትምህርቱ “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች” ብሎ የጠራቸው እነዚሁኑ ቡድኖች ሲሆን፣ በዚህም ንግግሩ የእግዚአብሔርን ቁጣ “የገሃነም ፍርድ” በማለት ገልጾታል (ማቴዎስ 23፥ 33)። ኢየሱስ በዚያ ትውልድ ላይ ቤታቸው ባድማ ሆኖ የሚቀርበት ጊዜ እንደሚደርስ የተናገረው ፍርድ እና ይመጣል፣ "ከሰማይም ይገለጣል" የተባለው ቁጣ (ማቴዎስ 23፥ 38፤ ሮሜ 1፥ 18) ከ66-70 አ.ም ባለው ጊዜ (ለ3 አመት ተኩል) መጥቶ አልፏል። ያኔም የአሮጌው ኪዳን ቤተመቅደስ እና የኢየሩሳሌም ከተማ በሮማውያን ሰራዊት እጅ ወድቀው ተደምስሰው ወድመዋል። አስቀድሞ በእስራኤል ምድር ተቀስቅሶ ከነበረው አመጽ፣ የእርስ በርስ ውጊያና ጽኑ ረሃብ የተረፉ በሚልዮን የሚቆጠሩ የአይሁድ ሕዝብም በደረሰባቸው መቅሰፍተ ዕልቂት በገዛ ምድራቸው ተገድለው አልቀዋል፣ በምርኮ የተወሰዱትም በአለም ዙርያ ተበትነው ከእነርሱም የሚበዙት በአህዛብ ጣዖታት ክብረ በአላት ላይ ለጣዖታቱ እንደ መስዋእት ታርደው፣ ለነገስታቱና ለመኳንንቱ ክብር ጭዳ ሆነው፣ ገሚሱንም በጨዋታ ስፍራ ከአውሬ ጋር እያታገሉአቸውና እየተበሉ ዘራቸው ጥፍቷል፤ ይህም ሁሉ የተፈጸመው በ70 አ.ም ነው (ዳንኤል 12፥ 7-13 እና ሉቃስ 21፥ 5-36 ተመልከቱ)። ከ70ው አ.ም ፍጅት በኋላ በእናቱም በአባቱም ንጹህ የአብርሃም ልጅ የሆነ እስራኤላዊ በምድር ዙርያ ማግኘት የማይታሰብ ሆኖአል። "ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል" ያለው አስፈሪው የኢየሱስ የፍርድ ትንቢትም ተፈጽሟል።
ማቴዎስ 12፥ 32 "በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው [ሊመጣ ባለው/ mello] አይሰረይለትም።" [ ሊመጣ ባለው ዘመን እንጂ የሚመጣው ዘመን አይደለም]
እንደ ግሪኩ "ሜሎ" ሁሉ 'አለም' በሚል የትርጉም ስህተት የተሰራበት ሌላው የግሪክ ቃል 'ዘመን' (aion) የተሰኘው ነው። ኢየሱስ ግን "ይህ ዘመን" ሲል የሚጠራውንና ያኔ ይሰራ የነበረውን የብሉይ ኪዳንን አለም እና በ 70 ዓ.ም "ሊመጣ ያለውን" የአዲሱን ኪዳን ዘመን በተቃርኖ ያቀርባል እንጂ፣ የትርጉም ስህተቱ እንደፈጠረው እንግዳ ትምህርት "ይህ አለም" ማለት አሮጌው የሙሴ አለም መስተዳድር ካልሆነ በቀር፣ ይህ ግዑዝ አለም ማለት አይደለም፤ የሚመጣው ማለትም አሮጌውን የሙሴ አለም መስተዳድር ሽሮ የሚገለጥ አዲሱ ኪዳን የሚያበስረው የክርስቶስ ዘላለማዊ መንግስት ካልሆነ በቀር፣ ሌላ የሚመጣ አዲስ ግዑዝ አለም ማለት ፈጽሞ አይደለም። ለምንድነው ግን ኢየሱስ "በዚህ ዘመን ወይም ሊመጣ ባለው ዘመን" ይቅር አይባልም ሲል የተናገረው? በእርግጥ እርሱ እየተናገረ ያለው የአይሁድ ቤተ መቅደስ እንዲደመሰስ ከሆነበት ከ 70 አ.ም በፊት (ማለትም “ይህ ዘመን”) እና ከዚያ በኋላ (“በሚመጣው ዘመን”) ስለ ተፈጸሙ ኃጢአቶች ነው። ስለዚህ ይመጣል የተባለው ዘመን ቀኑና ጊዜው ቀርቦ የሚታወቅ እንጂ ሩቅ እና የጊዜውን ማእቀፍ ማወቅ የማይቻል አይደለም።
ማቴዎስ 16፥ 27-28 "የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና [mello]፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።" [ይመጣ ዘንድ አለው እንጂ ይመጣል አይደለም]
mello የተሰኘውን ቃል ጠቀሜታ እውቅና ሰጥተው አማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ለተረጎሙ ሰዎች እዚህ ላይ ዋጋ መስጠት ይገባል። ይህ ምንባብ በግልጽ እንደሚናገረው ኢየሱስ ሊመጣ ያለው የሰው ልጅ ነው፤ ከዚህም የተነሳ እዚያ ቆመው ይህንን ንግግሩን ያደምጡ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሳይሞቱ በህይወት ቆይተው 'ይሆናል' የተባለው ይህ ጉዳይ ሲፈጸም ማለትም መምጣቱን ያያሉ። ይህ ንግግር በግልጽ ጓጉቶ መጠባበቅን የግድ ይላል። እንዲህ ያለ ፊትለፊት እና በግልጽ ቋንቋ ከኢየሱስ አፍ የወጣ ንግግር ልክ እንደተጻፈው እውነት ካልሆነ ግን፣ ኢየሱስን ሀሰተኛ ነብይ ሊያሰኘው የሚችል ጣጠኛ የሆነ መዘዝ ይጎትታል። ኢየሱስ ጌታ ነው ብለን እያመንን በጌታችን ላይ እንዲህ ያለ ስድብ እና ነቀፋ የሚያስከትል "ትንቢት እስካሁን አልተፈጸመም፣ ጌታም ገና ወደፊት እንጂ እስካሁን አልመጣም" የሚል የመጻኢነትን ትምህርት አዝለን መኖራችንን አለማወቅ በእውነት እውርነት ነው። ኢየሱስ መንግስቱን ከእግዚአብሔር ጠላቶች ነጥቆ ሁሉ በሁሉ ሆኖ አሁንና ለዘላለም ሁሉን ለሚገዛው ለእግዚአብሔር ይመልሰው ዘንድ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ተመልሷል ብዬ የማምነውም ከዚህ የተነሳ ነው። ታዲያ እርሱ በግልጽ ፊት ለፊት "እዚህ የቆሙት" ሲል በተለይ በጠራቸው ሰዎች የህይወት ዘመን ተመልሷል ብዬ እንዳላምን፣ ይልቁንም 'አይ ሊል የፈለገው እንደዚህ ሳይሆን እንደዚያ ነው" በሚል ማመካኛና ሰዎች ለቃሉ በሚሰጡት ማስተካከያ እና እርማት መሰል ድፍረት ሊል ያልፈለገውን ሌላ ነገር እንድረዳና እንዳምን፣ የሰጠውንስ ተስፋ እንዳልፈጸመ እንድቆጥር ለምን ይፈርዱብኛል? እንደተናገረው እንደዚያው እንደ ተስፋ ቃሉ በፍርድና በክብር ተመልሷል ብዬ ላምነው የማልችለው 'ኢየሱስ' አዳኜስ ሊሆን እንዴት ይችላል?
ማቴዎስ 24፥ 6 "ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ [millo]፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።" [ትሰማላችሁ ሳይሆን ትሰሙ ዘንድ አላችሁ ነው]
ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የሚናገረው ለነዚያ ከእርሱ ጋር በዚያ ለነበሩ የመጀመሪያው ከፍለዘመን ደቀመዛሙርቱ ነው፤ እንጂ ዛሬ ይህንን የምናነብ ማናችንም ብንሆን የዚህ ቃል በኩረ ተደራስያን አይደለንም። የሚነግራቸውም በገዛ ራሳቸው ትውልድ ወቅት (ማቴዎስ 24፥ 34) በቅርቡ ሊሆንባቸው ስላለ ነገር ነው። ሊሆን ያለው የሚሆነው "እናንተ" ተብለው በተለይ ለተጠቀሱ ለመጀመሪያዎቹ አድማጮች እንጂ ለማናችንም አይደለም። በዚህ ምንባብ "ትሰሙ ዘንድ" በሚል 'እናንተ' ለተባሉት "መጨረሻው" ገና ወደፊት ነበር፣ ዳሩ ግን ሩቅ ሳይሆን እናንተ በተባሉት ሰዎች የሕይወት ዘመን የሚሆን ነው። ትንቢቱ 'እናንተ ትሰማላችሁ' በተባሉት ሰዎች የህይወት ዘመንና ትውልድ ውስጥ ያልሆነና ተፈጽሞ ያላለፈ ከሆነ፣ እንግዲያውስ እነዚህ ቃሎች ከተነገሩ ከ2000 አመታት በኋላ ለምናነባቸው ለእኛም ቢሆን መጨረሻው ገና ወደፊት ሊሆን ከቶ አይችልም።
ሉቃስ 21፥ 36 "እንግዲህ ሊመጣ ካለው [mello] ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።" [ሊመጣ ካለው ነው እንጂ ከሚመጣው አይደለም]
የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳን ትርጉም በዚህም ጥቅስ ላይ mello ለተሰኘው የግሪክ ቃል ታማኝነቱን አሳይቷል። እንደ ኢየሱስ ግልጽ ንግግር ከሆነ እርሱ "ይህ ሁሉ" ሲል የዘረዘረው "ሊመጣ ያለው" ነገር ሁሉ ፍጻሜው በዘመንና በትውልድ ርቀት የሚታሰብ ሳይሆን፣ ይልቁንም በግል በእያንዳንዳቸው በደቀመዛሙርቱ የህይወት ዘመን የሚሆኑ ነገሮች ናቸው። ኢየሱስ የሚናገረው ለገዛ ራሱ ደቀ መዛሙርት ነው እንጂ ለእኛ ወይም ለሌላ ሦስተኛ ወገን እንዳልሆነ ልብ አድርጉ።
ሐዋርያት 17፥ 31 "ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ [mello] ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።" [ይፈርዳል ሳይሆን ሊፈርድ ነው ማለት ነው]
አማርኛው ይህንንም ጥሩ አድርጎ አስቀምጦታል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ግልጽ ያደረገው አንድ ጉዳይ በራሱ ትውልድ እግዚአብሔር በአለሙ ሁሉ ላይ ሊፈርድ መሆኑን ነው። ኃላፋውያን በትምህርታቸው ቅዱሳት መጻህፍትን ሲተረጉሙ ጊዜ ጠቋሚ ለሆኑ እንዲህ ላሉ ንግሮች ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጣሉ፣ ነገረ ፍጻሜአዊ ምልከታችንን መልክና ቅርጽ የሚሰጠው አንዱ ይኸው ነውና። እግዚአብሔር በህያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ያለው፣ ቀን የቀጠረው በመጀመርያው ከፍለዘመን ትውልድ ወቅት ነበር። ይህንን በመለኮት የተመደበ ቀነ ቀጠሮ ከመጀመርያው ክፍለዘመን የጊዜ ማእቀፍ አውጥተን በየትኛውም ዘመናዊ ወይም መጻኢ ጊዜ ውስጥ ፍጻሜውን እንድንጠባበቅ የሚያስችለን ምንም አይነት አዲስ ኪዳናዊ ድጋፍ የለንም፣ አይኖረንምም።
ሐዋርያት 24፥ 14፣ 15 "ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው [mello] ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።" [ከሙታን ይነሳሉ ሳይሆን ከሙታን ይነሱ ዘንድ አላቸው ነው]
እዚህም ላይ የአማርኛው ትርጉም ጥሩ ነው። ጳውሎስ በዚህ ንግግሩ ግልጽ የሚያደርገው አንድ እውነት ምንድን ነው? "እኔ ከእነርሱ የምለየው በአምልኮዬ ነው፣ መንገዱንም ኑፋቄ ሲሉ ይጠሩታል፤ ሆኖም የማምነዉ እነርሱ እንደሚያምኑት በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ ነው፣ የሙታንን ትንሳኤ የምጠብቀውም እነርሱ እንደሚጠብቁት ነው፣ ተስፋ የማደርገውም እነርሱ ተስፋ አንደሚያደርጉት ነው"፤ እያለ ነው። የሙታን ትንሳኤን ጨምሮ በህጉ የተጻፈው ሁሉ በቅርቡ ፍጻሜውን የሚያገኝ መሆኑን ጳውሎስ ይጠባበቃል። ጳውሎስ ለአገረ ገዡ ለፊሊክስ እየነገረው ያለው፣ የጻድቃንና የኃጢአተኞች ትንሳኤ የሚከናወነው በእርሱ የህይወት ዘመን መሆኑን ነው። ጉዳዩ በእርግጠኝነት በቅርቡ የሚከናወን (NO DELAY) መሆኑን ያመለክታል። ስለዚህ ጳውሎስ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን አድማጮቹ ባቀረበው ሙግት፣ ትንሳኤ በቅርቡ ሊሆን እንደሆነ እየነገራቸው ነበር ማለት ነው። በመላው አዲስ ኪዳን፣ ወንጌል አስቀድሞ ለአይሁድ ከዚያም ለግሪክ እንደሚሆን የተገባው የእስራኤል ተስፋ መፈጸሙን በግልጽ እናያለን፤ ይህም በድህረ ጴንጤቆስጤ እየተካሄደ በነበረው ከአሮጌው ኪዳን ወደ አዲሱ ኪዳን የሚደረገው ሽግግርም በዚያው የመጀመርያው ክፍለዘመን ውስጥ የፍጻሜው ዘመን እየቀረበ የነበረ መሆኑን እና ያም ጠንካራ ምስክርነት እንደነበር ያሳያል።
ሐዋርያት 24፥ 25 "እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም [ሊመጣ ስላለው/ mello] ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ፦ አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት።" [ሊመጣ ስላለው ኩነኔ ነው እንጂ ስለሚመጣው አይደለም]
ፍርድ በገዛ ራሱ ትውልድ ውስጥ በቅርቡ ሊመጣ መሆኑን እየተናገረ ያለውን የጳውሎስን ግልጽ ንግግር ካልተረዳ በቀር ፊልክስ ለምን ይፈራል? ያኔ ጳውሎስ ለፊልክስ እየተናገረ ፊልክስም ጳውሎስን እየሰማው በነበረበት ዘመን ኩነኔ ሊመጣ በቅርብ ተዘጋጅቶ ነበር ማለት ነው።
ሮሜ 8፥ 13 "እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና [mello]፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።" [ትሞታላችሁ ሳይሆን ትሞቱ ዘንድ አላችሁ ነው]
ለአማርኛው ትርጉም ያለኝን አድናቆት አልሸሽግም። ጳውሎስ አይሁድ አማኞች የሆኑ “ወንድሞችን”፣ የሚናገራቸው ወደ ሥጋ ፈቃድ ተመልሰው “በሥጋ ትምክህት የሚሄዱ” ከሆነ “ሊሞቱ” እንደሆነ አያስጠነቀቃቸው ነው። ይህም ሥጋዊ በሆነው ሥርዓታቸው ላይ በመመካት በመንፈስና በሕይወት የሚገለጠውን ኑሮ እምቢ በሚሉት ላይ ፈጥኖ ሊሆንባቸው ያለውን ፍርድ ያሳያል።
ሮሜ 8፥ 18 "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው [mello] ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።" [ይገለጥ ዘንድ ያለው ነው እንጂ የሚገለጠው አይደለም]
በዚያን ጊዜ የነበሩ ምዕመናን እነዚህን ነገሮች በምን ያህል ናፍቆት ጓጉተው ይጠባበቁና ተስፋ ያደርጉ እንደነበር ለማየት የዚህን ጥቅስ አጠቃላይ አውድ (ቁጥር18-25) በጥንቃቄ አንብቡት። ለምን እነዚህን ነገሮች መጓጓትና በግል መጠባበቅ አስፈለጋቸው? ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ በግላቸው እነሱን ማሳተፍ የነበረባቸው ጉዳዮች በመሆናቸው ነው። ይገለጥ ዘንድ ያለው ክብር "ለእኛ" ነው፣ እኛ የተባሉትም ጳውሎስና የመጀመሪያው ክፍለዘመን ክርስቲያኖች ናቸው። "የአሁኑ ዘመን ሥቃይ" የተባለውም የእነርሱ ዘመን ሥቃይ ነው። በግል እያንዳንዳቸው ያልፉቡት የነበረው የመከራ ሕይወት የሚካሰውና የሚደመደመው ለእነርሱው ሊገለጥ ባለው ክብር ነው።
ሮሜ 8፥ 38፣39 "ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም [ሊመጣ ያለው mello] ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።" [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]
እዚህ ላይ ሁለቱን ኪዳናት እናያለን። "ያለውም" የተባለው እርሱም 'አሁን ያሉት ነገሮች (የሙሴ ዘመን)' እና "የሚመጣውም" የተባለው እርሱም ሊመጣ ያለው (መሲሐዊው ዘመን) ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም ተብሎ ከተዘረዘረው፣ ከሞት ፣ ከህይወት ፣ ከመላእክት ፣ ወዘተ ጋር ተቆራኝተው መነገራቸውን ልብ በሉ። "ያለውም" የተባለው በዚያ በአሮጌው ኪዳን እና በሙሴ ዘመን መስተዳድር ውስጥ ተካተው የነበሩ ያኔ እነርሱ ይኖሩበት የነበረው ስርአትና የሞት አገልግሎቱ ነው፤ "የሚመጣውም" (ሊመጣ ያለው) የተባለው ደግሞ አዲሱን ኪዳን ወይም የመሲሁን ዘመን የሚያካትት ነው። ይህም በእብራውያን 8 ላይ ስለ አሮጌው ዘመን፣ "አርጅቷል፣ አሮጌና ውራጅ ሆኖ ሊጠፋ ቀርቦአል!" (ቁጥር 13) እያለ ከሚናገረው ጋር የተቆራኘ ነው። አዲሱ በሙላት እስካልመጣ ድረስ አሮጌው ኪዳን አሮጌ ሊሆን እንደማይችል ይህንን አንድ ነገር አትርሱ። ያ በ70 አ.ም ላይ የተከሰተው የመቅደሱና የከተማይቱ ውድመት የዚያን አሮጌ ስርአት ፍጻሜው መሆኑን ያሳያል። አሮጌው ኪዳን በውስጡ የያዛቸው ሁሉም ዓይነት ነገሮች በኢየሱስ ተፈጽመዋል።
1ቆሮንቶስ 3፥21-23 "ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም [ሊመጣ ያለው mello] ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።" [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]
ከፍ ሲል ለሮሜ 8፥ 38 የተሰጠውን ማብራርያ ይመለከቷል። "የሚመጣውም [ሊመጣ ያለው mello] ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥" ሲል እዚህ ላይ "እናንተ" የተባሉት በመጀመርያው ከፍለዘመን ላይ የነበሩ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ናቸው። "የሚመጣውም" (ሊመጣ ያለው) የእነርሱ ከሆነ እንግዲያውስ የሚመጣው በእነርሱ የህይወት ዘመን ለእነርሱ ነው፣ እንጂ እነርሱ ካለፉ በኋላ ዘመናት ተቆጥረው ቢመጣ "የእናንተ ነው፥" መባሉ ምንም ትርጉም አይሰጥም።
ኤፌሶን 1፥ 20-21 "ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው [mello] ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤" " [በሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ባለው ነው]
ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው "ዓለም" የሚለውን ቃል እዚህ ያለቦታው የዶለው የተርጓሚዎች ስህተት ነው፤ ቃሉ "ዘመን" ተብሎ መተርጎም ነበረበት። ስለዚህ "ይህ ዘመን" (አሮጌው ኪዳን) እና "ሊመጣ ያለው ዘመን" (አዲሱ ኪዳን) በንጽይር የቀረቡልን ስለሆነ ትርጉማቸውን በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል፣ ምክንያቱም አይሁድ ነገረ ፍጻሜን የሚረዱትና የሚተረጉሙት በነዚህ ቃላትና ሃረጎች ላይ ቆመው ነው። "በዚህ ዘመን" የተባለው ትርጉሙ የአሮጌው ኪዳን ዘመን ሲሆን፣ "ሊመጣ ባለው ዘመን" የተባለው ደግሞ የአዲሱ ኪዳን ዘመን ነው። በእብራውያን 8 የተገለጸውን እንዲሁም የአሮጌውን ፍጻሜ እዚህ ላይ ልብ በሉ።
ቆላስይስ 2፥ 16-17 "እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ያሉት [mello] ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።" [የሚመጡ ነገሮች ሳይሆን ሊመጡ ያሉት ነገሮች ነው]
ይህ ምንባብ በክርስቶስ ፍጻሜውን ሊያገኝ ያለውን አሮጌውን ኪዳን (ማለትም የአይሁድን በአላት፣ ልዩ ልዩ ስርአቶቻቸውን ተስፋዎቻቸውን፣ ወዘተ) በአግባቡ ለመረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። እዚህ ላይ በአሮጌው ኪዳን ዘመን ስለተካተው የአመጋገብ ስርአት፣ በአላትን ስለማክበር እንዲሁም ወቅቶችን አስመልክቶ ስለሚሰጥ ትምህርትና ሰንበትን ስለመጠበቅ እናያለን። እነዚህም ጉዳዮች ያኔ ሊመጡ ቀርበው ላሉት ጥላው ነበሩ፣ እነዚህ ጥላ የነበሩት፣ ያረጁ ፣ ያፈጁ እና ሊጠፉ የተቃረቡ ጉዳዮችና (እብራውያን 8)፣ ከክርስቶስ ጋር ተያያዥነት ባላቸውና እርሱ በሚገዛቸው ቁምነገሮች ሊተኩ የተዘጋጁ ነበሩ!። አንዳንድ መጻኢያን የሆኑ ወገኖቻችን እነዚህ ነገሮች በመስቀል ላይ ተጠናቀዋል ብለው ያምናሉ ዳሩ ግን ተመልከቱ ጳውሎስ ይህንን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ ፍጻሜአቸው ገና እንደነበር እናያለን። ስለዚህ በግልጽ እንደምናየው እነዚህን ነገሮች በ 70 ዓ.ም. ተፈጽመው ያለቁ በመሆናቸው አሁን በዚህ ዘመን እንለማመዳቸው አንልም።
1ጢሞቴዎስ 4፥ 8 "ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው [ሊመጣ ያለው/ mello] ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል።"" [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]
በነ ጳውሎስ ዘመን ሕይወት የአሁንና የሚመጣው የተሰኘ ሁለት Dispensation ነበረው፤ ለእነርሱ የአሁኑ ሕይወት ማለት አጠቃላዩ አሮጌው የሙሴ ዘመን እና ከአሮጌው ወደ አዲሱ ኪዳን ለመሸጋገር እነርሱ ራሳቸው ይኖሩበት የነበረው በብዙ ትግል ስጋን የመግራት ዘመን የምንለው ወቅት ሲሆን፤ የሚመጣው ግን እነርሱ "በህይወት እያለን የሚመጣ" ነው ብለው ተስፋ ያደረጉትና ከዚያን ጊዜ የጀመረውና እኛም ያለንበት፣ ለዘላለምም የማይዘጋው የአዲሱ ኪዳን ዘመን ነውና ያም ሕይወት በክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት በሙላት ተገልጧል። ለጥንት ክርስቲያኖች ያ የሚመጣው ሕይወት የሚመጣበት ጊዜ የማይታወቅ ሳይሆን፣ ይልቁንም mello /ሊመጣ ያለው/ የሚለው የግሪክ ቃል ጊዜው ያንን ሕይወት ተስፋ ያደርጉ ለነበሩቱ ቅርብ አይቀሬ እንጂ ሩቅና ጊዜውን ማሰብ የሚቸግር አልነበረም። ስለዚህ ያንን ሕይወት ለመቀበል እነርሱ ጋር የነበረውን ከፍ ያለ መጠባበቅና ጓጉቶ መናፈቅ በዚህ mello በተሰኘ ቃል ውስጥ በጉልህ እናየዋለን።
2ጢሞቴዎስ 4፥ 1 "በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው [mello] በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤" [በሚፈርደው ሳይሆን ሊፈርድ ባለው ነው]
ይህ ጥቅስ የመጻኢያንን አመለካከት ለመደገፍ በሚደረግ ክርክር ላይ ያለውን ጉዳይ ሁሉ ይዘጋዋል። mello የተሰኘውን የግሪክ ቃል ፍትሃዊና አግባብነት ባለው መልኩ በትክክል እንተርጉመው ካልን ይህ በግልጽ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው? ቃሉ እነደሚያሳየው ኢየሱስ ያኔ ነው በህያዋን እና በሙታን ላይ ሊፈርድ ያለው። እርሱ በህያዋን እና በሙታን ላይ በሚያደርገው ፍርዱ እና በመገለጡ መካከል ግልጽ ግንኙነት ያለ በመሆኑ ላይ ምንም ጥርጥር የለም። ፍርዱ ሊመጣ ያለው ከነበረ እንግዲያውስ መገለጡ እና መንግስቱም ሊመጣ ያለው ነበር ማለት ነው። ክርስቶስ በተመለሰበት ጊዜ ክፉዎች ሁሉ ተፈርደው ያኔውኑ ወደ ዘለአለማዊው ሥቃይ ተጥለዋል፣ ያም ደግሞ ሌሎች ክፉዎች ሁሉ በሚሞቱበት ቅጽበት የሚሄዱበት ስፍራ ነው። የሰው ዘር ሁሉ ወኪል የሆነው አዳም በገነት ውስጥ ሳለ ያጣውን ያንን የትንሣኤ ሕይወት፣ ጻድቃን የሆኑ ሁሉ ግን ለመጀመርያ ጊዜ በእግዚአብሔር ሀልዎት ፊት መልሰው ወርሰውታል። የትንሳኤ ህይወት "ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ" (ራእይ 2፥ 7) እንደሚል፣ ገነትን ማስመለስ ነው። የህይወት ዛፍ የሆነው ኢየሱስ የዘላለምን ሕይወት ሰጥቶናል።
እብራውያን 1፥ 13-14 "ነገር ግን ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው [mello] ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?" [መዳንን ለሚወርሱ ሳይሆን ይወርሱ ዘንድ ላላቸው ነው]
ያኔ የክርስቶስ ጠላቶች እነማን ነበሩ? በማቴዎስ 23 "ግብዞች"፣ "የነብያት ገዳዮች ልጆች" ተብለው የተነቀፉ፤ በሉቃስ 19፥ 11-27 "ክፉ ባርያ" ደግሞም "ጠላቶቼ" ያላቸው፤ በሐዋርያት 7፥ 51-53 "አንገተ ደንዳኖች"፣ "ያልተገረዙ"፣ "ተቃዋሚዎች"፣ "አሳዳጆች"፣ "ነፍሰ ገዳዮች"፣ "ሕግን ያልጠበቁ" ተብለው የተወቀሱ፤ በሮሜ 11፥ 28 "የወንጌል ጠላቶች" በሚል መጠሪያ የተገለጡ፤ በፊልጵስዩስ 3፥ 2፣ 18፣ 19 "ውሾች"፣ "ክፉ ሰራተኞች"፣ ብሎም "የመስቀል ጠላቶች" ወዘተ እየተባሉ በግብራቸው የተጠቀሱት አይሁድ ናቸው። እነዚህ የክርስቶስ ጠላቶች የተባሉ ልባቸውን በምድራዊው ነገር ላይ ያደረጉ፣ በሰማያዊውም የተስፋ ቃል ላይ ያመጹ ናቸው። ክርስቶስ ግን የጠላቶቹን ራስ፣ ሞትንም ጭምር ቀጥቅጧል። ለዘላለምም ሁሉን ይገዛ ዘንድ በአባቱ ቀኝ ተቀምጧል፤ ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም። ከውድቀት ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ቅዱሳን ሁሉ በሰማይ ያለውን መዳናቸውን (ቤዛነታቸውን) ይወርሱ ዘንድ አላቸው። አማኞች ይወርሱት ዘንድ ያላቸው መዳን ምን ይሆን? አስቀድሞውኑስ ድነው አልነበርምን? በመላው አዲስ ኪዳን ሞልቶ በሚፈስ ምስክርነት አዎ ደግሞም አይደለም! ብለን ብንመልስ ግር የማይለው ይኖራልን? የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ ሄደው የሚከማቹበት እና ሙሉ የሆነውን ቤዛነታቸውን እየተጠባበቁ የሚቆዩበት ሀደስ የተባለው ስፍራ ያኔ ገና በስራ ላይ ነበር። ኢየሱስ ለመጀመርያው ከፍለዘመን ደቀመዛሙርቱ በሉቃስ 21፥28 ላይ "ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና (እናንተ) አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ" ሲል የተናገራቸውን አስታውሱ። ይህ እንግዲህ ቀደም ሲል ሊሆን ያለው በሚል ለማሳየት የተሞከረው ለአዲስ ሕይወት የመነሳት ትንሳኤ ነው። ይህም በቅበት አይን ሊለወጡ ያለበት፣ ሞትም ድል በመነሳት ሊዋጥ ያለበት፣ የሚሞተውም የማይሞተውን ሊለብስ ያለበት፣ ፍጥረታዊው ሆኖ የሚታየውም መንፈሳዊ ሆኖ ሊነሳ ያለበት የ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ፍጻሜ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሞት አያሸንፍም፣ መውጊያም ደግሞ የለውም፤ ብንሞትም ህያዋን ነን፣ ህያዋንም ከሆንን ፈጽሞ አንሞትም! ልንል እንችላለን። ያለ ትንሳኤ ይህንን ለራሳችን ማድረግ አንችልም፣ ስለዚህ ሁላችንም በምንሞትበት ጊዜ በቀጥታ ወደ ሰማይ ሳይሆን በተቃራኒው ገና የወደፊቱን የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት ልንጠባበቅ ወደሀደስ እንሄዳለን ማለት ነው፤ ይህ ግን በእግዚአብሔር ቃል ላይ መዋሸት ይሆናል። ትንሳኤ ገና ወደፊት እንጂ ከአሁን በፊት አልሆነም ብለው የሚያምኑ መጻኢያን አስተማሪዎች፣ ያኔ በመጀመርያው ክፍለዘመን እንደሚሆንና ሊሆን እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የተናገረለት ያ ትንሳኤ ገና ሳይሆንና ያም ፍርድ እስካሁን ሳይፈጸም በፊት፣ አማኞች አሁን በሚሞቱበት ጊዜ የትንሳኤን ቀን ሊጠባበቁ ሁሉም ወደ ሀደስ የሚሄዱ ስለሆነ፣ ወደሰማይ እንደሚሄዱ አድርገው የሚያስተምሩትንና ምዕመናንን የሚዋሹትን ነገር ፈጽሞ ማቆም አለባቸው።
እብራውያን 2፥ 5 " ስለ እርሱ የምንናገርበትን የሚመጣውን [ሊመጣ ያለውን mello] ዓለም ለመላእክት ያስገዛው አይደለምና።" [የሚመጣው ዓለም/ ዘመን ሳይሆን ሊመጣ ያለው ዓለም /ዘመን ነው]
እዚህ ላይ ጸሐፊው ለመላእክት ተገዝቶ የነበረውን ዓለም አንስቶ ይነጋገራል። ለመላእክት ተገዝቶ ከነበረው አለም (ይህም የሙሴ ዘመን ነው) ጋር ይህ እንዴት ይነጻጸራል? በሐዋርያት 7፥ 51-53 "አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ" የተባሉትን ተመልከቱ። ነብያትን እያሳደዱ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የነገሩአቸውን ይገድሉ እንደነበረው ሁሉ አይሁድም ልክ አባቶቻቸው ያደርጉ እንደነበረው አይነት አይሁድም መንፈስ ቅዱስን ይቃወሙ ነበር (ማቴዎስ 23 ተመልከት)። ሕጉን በመላእክት ትእዛዝ የተቀበሉ ቢሆኑም እንኳ ዳሩ ግን አልጠበቁትም፣ ይልቁንም በክፋታቸው ብሰው ነፍሰ ገዳዮችና አሳልፈው የሚሰጡ ከሃዲዎች ሆኑ። አሮጌው ኪዳን በመላእክት ትእዛዝ የመጣ ነበር፣ ይመጣ ዘንድ ያለው አዲሱ ግን ለኢየሱስ እንጂ "ለመላእክት የሚገዛ" አይደለም። የዚህ መልእክት ጸሐፊ ለመጀመርያው ከፍለዘመን ተደራስያኑ "ስለምንነጋገርበት" ብሎ መጻፉን ልብ አድርጉ። የ70ው አ.ም ፍርድ ገና የተከናወነ ባለመሆኑ፣ ይነጋገሩታል እንጂ ያኔ ሁሉም ነገር በኢየሱስ የተገዛ እንደነበር ገና አላዩም።
እብራውያን 6፥ 5 "መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን [mello] የዓለም ኃይል የቀመሱትን" [ሊመጣ ያለው እንጂ የሚመጣው አይደለም]
ከክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በፊት የነበረው የጥንት ቤተክርስቲያን ዘመን፣ እርሱም ከበአለ ሃምሳ እስከ 70 አ.ም ያለው የአርባ አመታት የሽግግር ወቅት፣ በሙላት ሊገለጥ ያለውንና "ሊመጣ ያለውን [mello] የዓለም ኃይል" የተለማመዱበት የቅምሻ ወቅት ነበር። በሽግግሩ ወቅት በቅምሻ ደረጃ የተለማመዱት ሊመጣ ያለው የዓለም ኃይል በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በሙላት ተገልጧል። የእግዚአብሔርን ቃል እንደተጻፈ ብናምን አሁን እኛ በዚያ የአዲሱ አለም ኃይል ውስጥ እርሱም በአዲሱ ኪዳን ውስጥ እንኖራለን።
እብራውያን 9፥ 11 "ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው [mello] መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥" [ለሚመጣው መልካም ነገር ሳይሆን ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ነው]
ይህ በዚያን ዘመን ከነበረው ቤተመቅደስና ከእርሱ ጋር ግንኙነት ካላቸው ነገሮች ጋር ግልጽ የሆነ ተቃርኖ ነው። እንዲህ ያለው ንጽጽርና ተቃርኖ የእብራውያን መልዕክት አንዱ ገጽታ መሆኑን ለማስተዋል እብራውያን 8፥ 6-13፤ 9፥ 8-12፣ 15 ይነበብ። ይህ መልዕክት በሚጻፍበት ጊዜ ምድራዊው ቤተመቅደስ ገና በስፍራው ቆሞ ሳለ ሊቀ ካህናቱ ክርስቶስ በሰማያት ካለችው እውነተኛይቱ ቅድስት ወጥቶ ገና አልታየም ነበር። በብሉይ ኪዳን ሊቀካህናቱ የእንስሳውን መስዋእት ካቀረበ በኋላ በዚያ የስርየት ቀን ደሙን ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል። ሊቀ ካህኑም ከቅድስተ ቅዱሳን ወጥቶ ወደ ህዝቡ ወደ አውደምህረቱ ሲመጣ ያኔ ዋናውና ትክክለኛው የስርየት አዋጅ ይገለጣል። እግዚአብሔር ስለኃጢአት ስርየት የቀረበውን መስዋእት ተቀብሎ የህዝቡን መተላለፍ ይቅር እንዳለ አይነተኛ ማረጋገጫው የሊቀ ካህኑ ከቅድስተ ቅዱሳን ወጥቶ መታየቱ ነው (ዘሌዋውያን 16፥ 16-18)። ነገር ግን የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ሊያስወግድ አይችልም (እብራውያን 10፥ 4)። ኢየሱስ ግን ሊያስተሰርይ ከገባበት ቅድስት በዳግመኛ ምጽአቱ ወጥቶ የመጣ በመሆኑ አሁን መዳናችን ፍጹም ሆኖአል፤ ስለዚህም እርሱ ምርጦቹን ሁሉ በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ክብር፣ ወደ ሀልዎቱ አምጥቷቸዋል። ጳውሎስ፣ በመጀመርያው ከፍለዘመን የ70 አ.ም ዳግመኛ ምጽአቱ ላይ፣ ያኔ አዲሱ ኪዳን በሙላት ተጠናቆ ሲገለጥ፣ "እስራኤል ሁሉ (በልባቸው የተገረዙ መንፈሳዊው እስራኤል) ይድናል" ሲል ሊተነበይ የተቻለውም ለዚህ ነው። ስለዚህ ነው እኛም በሮሜ 11፥ 5፣ 25-29 እንደተጻፈ ቤተመቅደሱ በወደመበት ጊዜ በሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ በስጋ እስራኤል የሆኑ ሁሉም የተመረጡቱ ድነዋል የምንለው፣ (እብራውያን 9፥ 15፣ 28 ተመልከት)። የሐዋርያው ጳውሎስ "እስራኤል ሁሉ ይድናል" እና የነብዩ ዳንኤል "በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።" የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጽሟል። አብርሃም ሲጠብቃት የነበረውን "እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማም" (እብራውያን 11፥ 10) ክርስቶስ በመምጣቱ አምጥቷታል። ክርስቶስ ስላመጣው ነገር የሚበልጠውና እና ፍጹም የነበረው ምን ነበር? አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለዘላለም ኃጢአትን ማስወገዱ ነው። ከዚያም ወዲያ ኩነኔ የለም (ሮሜ 8- ሞት)፣ ከእግዚአብሔር ሀልዎት መነጠልም (ሮሜ 8- ሀደስ) የለም! ታዲያ ብዙዎች እነርሱ ለገዛ ራሳቸው ፈጽሞ የማይመኙትን ጉዳይ ይኸውም ሞትና ኩነኔን፣ ከእግዚአብሔርም ሀልዎት ተነጥሎ በሀደስ መሆንን ለአብርሃምና ለሌሎች የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ለምን ይናፍቁላቸዋል? ምጽአቱ እስካሁን አልሆነም የሚለው የመጻኢያን ትምህርት አብርሃምንና በእቅፉ ያሉትን ልጆቹን ከእግዚአብሔር ሀልዎት አርቆ፣ ሲናፍቋት ከነበረው ከተማ አርቆ በሀደስ ውስጥ ገና አሁንም ለሺህዎች ዘመናት ይረሳቸዋል። እነርሱ ግን የተስፋውን ቃል በሩቅ እያዩ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች ሆነው ራሳቸውን በባዕድ አገር እንደሚኖሩ አድርገው ይቆጥሩና ይጠባበቁ ነበር። የሚሻል ሰማያዊ አገርም ይናፍቁ ነበር። ያ የሚናፍቁት ደርሶላቸዋል። ከዚያን ጊዝ ጀምሮ ሁሉም የእግዚአብሔር ምርጦች ሞት አይገዛቸውም፣ ኩነኔም የለባቸውም፤ ሀደስ አያስፈራቸውም፣ ከእግዚአብሔር ሕይወትና ሀልዎት የመነጠል ስጋት የለባቸውም። እኛ የዳንን በምንሞትበት ጊዜ ይህንን ሰውነታችንን አውልቀን ጥለን በምንቀበለውና በተዘጋጀልን አዲስና መንፈሳዊ በሆነው የማይሞት አካል በሰማያት ከእግዚአብሔር ጋር እንደምንሆን በጽኑ አምናለሁ።
እብራውያን 10፥ 1 "ሕጉ ሊመጣ ያለው [mello] የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም።" " [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]
የእብራውያን ጸሐፊ የአይሁድን ህዝብ ሊያስታውሳቸው የሚፈልገው በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጻሜውን ሊያገኝ ያለውን የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ነው። "ጥላ" የተባለውም በቅርቡ "ሊመጣ ባለው በጎ ነገር" ሊተካ ያለው ሕጉ ነው።
እብራውያን 10፥ 26፣ 27 "የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው [mello] የእሳት ብርታት አለ።" [የሚበላው ሳይሆን ሊበላ ያለው ነው]
ይህ ለነዚያ የለክርስቶስ ሆነው ለቀሩ ሁሉ በክርስቶስ ጠላቶች ላይ ሊደርስባቸው ስላለው የያኔው ፍርድ የተሰጠ ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ነው። ስለዚህ መልእክቱ በዘመኑ የነበሩትን አይሁድ ከያዙት የጥፋት ጎዳና ዘወር ብለው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመለሱ ማስጠንቀቅ ነው፣ አለበለዚያ እየመጣ ያለውና ሊገናኛቸው የተዘጋጀው የእግዚአብሔር ቁጣ ይበላቸዋል። እብራውያን 10፥ 25-39 ያለው ምንባብ በአውዱ ቢነበብ የተሻለ ነው።
እብራውያን 13፥ 14 "በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን [mello] እንፈልጋለን።" [ትመጣ ዘንድ ያላትን እንጂ የምትመጣዋን አይደለም]
እብራውያን 11 እና የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ይጠባበቁት የነበረውን ጉዳይ አነጻጽሩት፤ ይህ ጥቅስ በግልጽ የሚናገረው ስለ የአዲሲቷ ኢየሩሳሌም ነው እዚህም ላይ በአሮጌዋ ኢየሩሳሌም (ያረጀ፣ አሮጌ፣ ውራጅ፣ ያኔ ሊጠፋ የቀረበ፣ ሊመጣ ላለውም ነገር ጥላ የሆነው -እብራውያን 8) እና ትመጣ ዘንድ ባላት በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም (እብራውያን 11፥ 16፤ ራእይ 21፥ 1-7፣ 9-10) መካከል ያለውን ንጽጽርና ተቃርኖ እናያለን። አሮጌዋ ኢየሩሳሌም ፈጽሞ ተደምስሳ ከተወገደችና ውራጅ ሆና ከጠፋች በኋላ
አዲሲቱ ትገለጣለች።
1ጴጥሮስ 5፥ 1 "እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው [mello] ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤" [ሊገለጥ ካለው ክብር እንጂ ከሚገለጠው አይደለም]
ይህ ጉዳይ የሚሆነው በዚያን ዘመን፣ በእነዚያ ቀናት ለነበሩ ሰዎች ነው። ጴጥሮስ ሊገለጥ ያለ ክብር እየመጣ መሆኑን ተረድቷል። በእግዚአብሔር መንፈስ እየተነዳና በመጨረሻው ዘመን ላይ መሆኑን እያወቅ የሚጽፍ መሆኑን ልብ አድርጉ (1ጴጥሮስ 1፥ 4-13፣ 20፤ 2፥ 6-8፤ 4፥ 7 በጥንቃቄ ይነበብ)። በምዕራፍ 4፥ 13 ላይ ጴጥሮስ አስቀድሞ በመልዕክቱ እነዚያ የመጀመርያው ክፍለዘመን አንባቢዎቹን ሊመጣ ያለው ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ሐሴት አድርገው ደስ እንደሚላቸው ጽፎላቸው እንደነበር አስታውሱ።
ያዕቆብ 2፥ 12 "በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው [mello] ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ።" [ፍርድን እንደሚቀበሉ ሳይሆን ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ነው]
የያዕቆብ መልዕክት ተደራስያን "የተበተኑ አስራ ሁለቱ ወገኖች" ማለትም ዳያስፖራው የአይሁድ ክርስቲያን ወገን ነው። ጥቅሱም የሚያወራው ያኔ ለእነርሱ ቀርቦ ስለነበር ፍርድ ነው። ሕጉም ያላቸውና በሕጉ የሚፈረድላቸውና የሚፈረድባቸው እነርሱው ናቸው፣ እንጂ ሕጉ የሌላቸውን ያለ ሕግ የሚፈረድባቸውና የሚፈረድላቸው አህዛብ ክርስቲያኖች አይደሉም። አይሁድም ያንን ፍርድና ዳኝነት የሚቀበሉበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ንግግሩ ያሳያል። ይኸውም በ70 እ.ም የተፈጸመ ሲሆን ሕጉ ሳላቸው ለሕጉ ባለመታዘዝ ክርስቶስን ያላመኑትን ሁሉ እንደ ሕጉ ፈርዶ ሲያጠፋቸው፤ ሕጉ የመሰከረለትን በክርስቶስ የማመን ነጻነትን ተቀብለው የዳኑትን ትሩፋን ግን ፈርዶላቸዋል።
ራእይ 1፥ 19 "እንግዲህ ያየኸውን (ራእይ 1፥ 9-20) አሁንም ያለውን (ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተላከው ደብዳቤ ይዘት ራእይ 2፥ 1-3፥ 22) ከዚህም በኋላ (ራእይ 4፥ 1-22፥ 5) ይሆን ዘንድ ያለውን [mello] ጻፍ።" [የሚሆነውን ሳይሆን ይሆን ዘንድ ያለውን ነው]
የራእዩ መጽሐፍ የያዛቸው ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ይህ "ይሆን ዘንድ ያለው" በሚል የተገለጸው የመጨረሻ ክፍል በዮሐንስ ትውልድ ውስጥ ሊከናወን መሆኑን ልብ በሉ። ይህንን የሚናገረው ኢየሱስ ነው፣ ጻፍ ብሎ ትዕዛዝ የሚሰጠውም በመጀመርያው ከፍለዘመን ላይ ይኖር ለነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ነው። ይህ "ከዚህ በኋላ ይሆን ዘንድ ያለው" በሚል የተጠቀሱት ጉዳዮች ይፈጸማሉ ተብሎ በግልጽ ጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸውና የተነገሩት ለመቼ ነው? ከተባለ ቶሎ፣ በቅርቡ፣ በቶሎ (ራእይ 1፥ 1፣ 3፤ 22፥ 6፣ 7፣ 12፣ 20) ነው፤ ይህም ያኔ ዮሐንስ ይኖርበት ለነበረው ዘመን ቅርብ የሆነ ጊዜ ማለት ነው (ራእይ 1፥ 3፤ 22፥ 10)። እነዚህ ቃሎች በውስጣቸው የፍጥነትን እና የችኮላን ሃሳብ የያዙ ሲሆን፣ በጥቅሉ ይሆናሉ የተባሉት አይቀሬ ጉዳዮች ለፍጻሜአቸው የማይዘገዩና በዘመኑም ይህንን ለሰሙ በኩረ ተደራስያኑ "ጊዜ የለም" የሚል መልዕክት አላቸው። በግልጽ ቋንቋ የተነገሩትን እነዚህን አይቀሬ ንግግሮች እንዳለ እንደተጻፈው ከመቀበል ይልቅ፤ መካድ፣ ማሻሻል፣ ማስተባበልም ሆነ ለገዛ ራሳችን አስተምህሮ ትክክለኛነት ተጨንቀን "አይ እንዲህ ሊል ፈልጎ ነው" ብሎ ለቃሉ እርማት ለመስጠት የሚደረግ ሙከራና ማብራርያ ሁሉ፣ በማያምነው አለም ፊት ኢየሱስን ሐሰተኛ ነብይ፣ ሐዋርያቱንም ሐሰተኛ መምህራን፣ ክርስትናችንንም ሐሰተኛ ኃይማኖት ያደርጋቸዋል። ቅዱሳን ወንድሞቼ ሆይ፣ ቃሎቹ በያዙት አይቀሬነትና ጊዜ ጠቋሚነት ተስፋ ቆርጣችሁ፣ እነዚህ ንግግሮች ላይ 2ኛ ጴጥሮስ 2፥ 8 ላይ ያለውን ቃል ያለቦታው እየጠቀሳችሁ፣ ይግባኝ በማለት እንዲሰረዙላችሁ ወይም ቃሎቹ የሌሉ ያህል ወደ ጎን እንዲተውላችሁ አታስቡት፤ እግዚአብሔር ተናግሯቸዋልና የሚያድነን፣ የሚያቆመንና የሚያጸናን በተጻፈው እውነት አንጻር መጎንበስ ብቻ ነው እንጂ፤ አይቀሬነትን የያዙትን እነዚህን መግለጫዎች በራሳችን መንገድ ለማብራራት መሞከር ፈጽሞ የለብንም።
ራእይ 3፥ 10 "የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው [mello] ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።"" [ከሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ካለው ነው]
"ዓለም ሁሉ" የሚለው መላውን የሮምን ግዛት ያመለክታል (ሉቃስ 2፥ 1) ፈተናውን ግዛቱን የሚያናውጥ ፈተና ነው። እንዲሁም በምድሪቱ በእስራኤል ነዋሪዎች ላይ ስለሚከሰት ፈተና እርሱም "ታላቁ መከራ" የተነገረ ቃል ነው። በ 68 አ.ም ላይ የኔሮን ሞት ተከትሎ በ70 አ.ም ቨስፓስያን የሮም ንጉሰ ነገስት እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ በሚቀሰቀስ የሮም የእርስ በርስ ጦርነት በመላው የሮም አለም ላይ ነውጥ ይኖራል፣ ይህም በተለይ አይሁድን ጭንቅ ውስጥ ይከታቸዋል። ጌታ የሚናገርለት የተለየ አለምአቀፋዊ ፈተና ይህ ነውና ይህ የፈተና ጊዜ የፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን በነበረችበት ዘመን እና ስፍራም የሚኖር "ሊመጣ ያለው [mello]" ፈተና ነው። ጌታም ይህችን የፊላደልፍያ ቤተክርስቲያን ለመጠበቅ የሰጠው ተስፋ ሊፈጸም የሚችለውና የሚፈጸመው በዚያው በቤተክርስቲያኒቱ ዘመን ነው።
ራእይ 12፥ 5 "አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን [mello] ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።" [የሚገዛቸውን ሳይሆን ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ነው]
አማርኛው መጽሐፍ ቅዱሳችን "ይገዛቸው ዘንድ ያለውን" በማለት የግሪኩን mello በአግባቡ አስፍሮታል። "ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።" (ዮሐንስ 3፥ 13)፣ እንደተባለ ሁሉን ሊገዛ በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ዙፋን የተነጠቀው ልጁ ኢየሱስ ብቻ ነው። እርሱም እንደ ዮሐንስ ራእይ ገለጻ "አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለው" የተባለለት የእግዚአብሔር ወንድ ልጅ ነው። አገዛዙም የሚጀምረው ቀያፋ በነበረበት የሕይወት ዘመኑ፣ ኢየሱስ ሁሉን ሊገዛ "በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ" ይህንን ለማየት (ማቴዎስ 26፥ 64) የተነገረው ቃል ፍጻሜ ላይ ነው።
አንዲት አነስተኛ የምትመስል ቃል በአረፍተ ነገር ትርጉም ውስጥ ያላትን ቦታና ዋጋ አሳንሶ፣ በበኩረ ቋንቋው ውስጥ ያላትን ጠቀሜታ ሳይረዱ ለመተርጎም መሞከር፣ በእውነትም ከፍ ላለ የአስተምህሮ ህጸጽ ይዳርጋል። በዚህች አንዲት የግሪክ ቃል ላይ የተሰራ መቀባባትም ሆነ ማድበስበስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የዳግመኛ ምጽአቱን አይቀሬነት የሚያመለክቱ እና፣ ከፍተኛ ጠቀሜታና ትርጉም ያላቸውን፣ ለምሳሌ እንደ "ቅርብ ነው"፣ "በደጅ ቆሟል"፣ "ፈጥኖ"፣ "ቶሎ"፣ "ቶሎ የሚሆነውን"፣ "ይህ ትውልድ አያልፍም" ወዘተ የመሳሰሉትን ቃላትና ሀርጎች አሁንም ገና ካልታወቁ ሺህዎች አመታት በኋላ ወደፊት በማናቸውም ጊዜ ሊሆኑ እንደሚችሉ አድርጎ በመውሰድ የሚያስከትለው የትርጉም ስህተት ጉልህ ከመሆኑም በላይ፣ አድካሚና የሌለ ነገር መጠበቅም ይሆናል። እነዚህ ሊሆኑ ያሉ (Mello) ነገሮችን የሚያመለክቱ ሀረጎች እና አረፍተ ነገሮች እንድናምናቸውና እንድንታዘዛቸው በቀጥታ የተሰጡትና የተነገሩት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ በኢየሱስ፣ በሐዋርያቱና በአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ሆኖ ሳለ፣ የተያዝንበትን የኖረ አመለካከታችንንና የእምነት አቋማችንን ለማጽደቅ በሚሆን ግብዝነት ቃሉ ላይ አንዳች በመጨመር ወይም ከቃሉ አንዳች በማጉደል 'አይ የለም እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው' በሚል እግዚአብሔርን እና ቃሉን ለማረም የምናደርገው ጥምዘዛና ሙከራ ሁሉ በእውነትም በደል ነው (ዘዳግም 4፥ 2)። ቃሉ የማይለውን ወይም ሊል ያልፈለገውን እንዲል ልናስገድደው፣ ያለውንም ከማመን በቀር አላልክም ብለን ልንሸነግለው፣ ወይም ያለውን አይ እንዲህ ሊል ፈልጎ ነው ብለን ልንዋሸውና ልናታልለው ምንም መብት የለንም። ስለዚህ፣ በእውነት የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ያሉትን ነገር በእርግጥ የምራቸውን ብለውታልን? እነዚህስ ነገሮች በ70 አ.ም ላይ ተፈጽመዋልን? ለዚህ ጥያቄ ኃላፋውያን መልሳቸው ፍርጥም ያለ "አዎ"! ሲሆን፣ መጻኢያን ግን በመልሳቸው ሽምጥት አድርገው "አይደለም"! ይላሉ ።
አንድ ሰው በዚህ Mello በተሰኘ ቃል ጠቀሜታ ላይ ያፈጠጠውን እውነታ፣ እርሱም ለመጀመርያው ከፍለዘመን ቤተክርስቲያን መጨረሻው ሊደርስ እንደሆነ ትርጉም ይሰጣቸው የነበረውን የጉዳዩን እርግጠኝነት እና አይቀሬነት ለመቀበል ቢያቅማማ እንኳን፣ የጌታን መመለስ እርግጠኝነቱና አይቀሬነቱ ቃሉ በተነገረበት አውድና ትውልድ ወቅት በቅርቡ ተፈጻሚ እንደሚሆን የሚያሳዩ ሌሎች ከፍ ሲል የጠቀስናቸው እንደ "ቅርብ ነው"፣ "በደጅ ቆሟል"፣ "ፈጥኖ"፣ "ቶሎ" "ቶሎ የሚሆነውን"፣ "ይህ ትውልድ አያልፍም" ወዘተ የመሳሰሉ ቃላትና ሀረጎችን ምን አድርጎ ሊያስተባብላቸው ይችላል? ተመልከቱ፣ መጻኢያን እነዚህን ከዮሐንስ ራእይ የተወሰዱትን ቃላትና ሀረጎች ሲተረጉሙ፣ "ትንቢቱና ራእዩ እስካሁን ድረስ ገና አልተፈጸመም ዳሩ ግን አንዴ መፈጸም ከጀመረ ቶሎ ቶሎ ይሚፈጸም መሆኑን ያመለክታሉ" ይላሉ፤ ከማቴዎስ 24 የተወሰደውንም "ይህ ትውልድ አያልፍም" የሚለውን "የእስራኤል መንግስት እንደገና መቋቋሙን በአይኑ የሚያየው ትውልድ ጌታ እስኪመጣ ድረስ የሚቆየው ትውልድ ነው" ሲሉ ይተረጉማሉ። ይህ ግን ቃሉ የማይለውን እንዲል መጠምዘዝ ነው። በመጀመርያው ከፍለዘመን ላይ ተመልሶ እንደሚመጣ የተናገረው የኢየሱስ ቃል በትክክል ያኔውኑ እርሱ እንደተናገረው ሆኗል ብለን ለማመን ግን በብዙ ማስረጃ ምስክር የምንጠራው ራሱን የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ነው (ለምሳሌ፣ ማቴዎስ 24፥ 33-34፤ ማቴዎስ። 10፥ 23፤ ማቴዎስ 16፥ 27-28፤ ያዕቆብ 5፥ 8-9፤ ራእይ። 1፥ 1፤ ራእይ 22፥ 7)
በሦስተኛው መቶ ከፍለዘመን መገባደጃ ላይ የክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ኢውሳብዮስ የተናገረውን ልጥቀስ፤ የጌታ ወንድም ስለነበረው ስለ ያዕቆብ የጻፈው ይህ ነበር፣ ያእቆብ ተከሶ ከአይሁድ መሪዎች ጋር በተከራከረ ጊዜ "እርሱም (ያእቆብ) ድምጹን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፣ 'ኢየሱስን የሰው ልጅ ነው ብዬ እንዳከብረው ብቻ ለምን ትጠይቁኛላችሁ? እርሱ አሁን በታላቁ ኃይል ቀኝ በሰማያት ተቀምጧል፣ በሰማያት ደመናም ይመጣ ዘንድ አለው' ሲል ተናገራቸው" ይላል፤ (Eusebius Ecclesiastical History p. 77 ተመልከቱ)። የኃላፋውያን ምልከታ ከቅዱሳት መጻህፍት ጋር የሚስማማ ነው፤ የትርጉም ፍሰቱም ቀዋሚነትን ጠብቆ ከቃሉ ጋር አብሮ የሚፈስ ነው። አቋማችንም ከሁሉ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ይተርጎም የሚል ነው። የግሪክ ቃላትንና አንዳንድ ታሪክ አዋቂዎችን ስፈትሹና ስተመልከቱ ያኔ የኃላፋውያን አቋምና አቋቋም በየትኛውም የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ላይ ጠንካራና አስተማማኝ መከላከያ እንዳለው ታያላችሁ። ከፍ ሲል በዝርዝር ባቀረብኳቸው ምንባባት አንጻር መጻኢያን ራሳቸውንና ትምህርታቸውን እንዴት መመከትና መከላከል እንደሚቻላቸው አላውቅም። የቃሉ ተማሪዎች ነን ካልን ግን "የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነን፥ የተፈተነውን ራሳችንን ለእግዚአብሔር ልናቀርብ ልንተጋ።" (2ጢሞቴዎስ 2፥ 15) ይገባናል እንጂ በቅጡ ባላጠናነውና ባላሰብንበት ርዕሰ ጉዳይ ቀደዳ ልናበዛ አይገባንም።
በዚህች አንዲት የግሪክ ቃል ላይ ሲሰራ የኖረውን ስህተት ለማረም በሚሆን ሰበብ ግን ትዕቢተኛና ተጨቃጫቂ የመሆን ፍላጎት የለኝም፤ ነገር ግን ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻችን እና በአስተምህሯችን ውስጥ በአግባቡ እንዲቀመጥና ዋጋ እንዲሰጠው መስራት እንዳለብን አምናለሁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ በተለቀሙ ቃሎች፣ ሀረጎች እና ቋንቋዎች ላይ፣ ተገቢ ትርጓሜአቸውን እና ጠቀሜታቸውን ከማጣጣምና ከመማማር ባለፈ፣ እጅግ በበዛ የወግ አጥባቂነት አጽንዖት ተይዘው ክርክር የሚመቻቸው ሰዎችንም ሳይ መንገዴን ቀይሬ እሄዳለሁ እንጂ "ይዋጣልን" የምል አይደለሁም። ምክንያቱም ደጋግሜ ለማየት እንደታደልሁት እንዲህ ያሉ ጉንጭ አልፋ አድካሚ እሰጥ እገባዎች መጽናናት የሞላባቸውን ቅዱሳት መጻህፍት ያላቸውን ንጹህና ግልጽ ትምህርት አግኝቶ ከመታነጽና ከመተናነጽ ይልቅ ግልጽና ንጹህ የሆነውን ሌላውን የቅዱሳት መጻህፍት ትምህርት የሚደፈጥጡ ወይም ዋጋ የሚያሳጡ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ኪሳራ የሞላበት እንዲህ ያለው መታለል ድርሻዬና እድል ፈንታዬ እንዲሆንም አልፈቅድለትም። ለምሳሌ፣ በአሽከርካሪ የመንገድ ላይ ስርአትና ደንብ የተቀመጠው "ቁም" /STOP/ የተሰኘውን አስገዳጅ ምልክት ያየ አሽከርካሪ፣ "ቁም ማለት በእግርህ ቁም /STAND UP/ ማለት ነው" ብሎ በመተርጎም ከገገመና ከተሽከርካሪው ወጥቶ በእግሩ ሊቆም ከወደደ፣ "ስራህ ያውጣህ" ብዬ ከመተው በቀር ምን አድርጌ ላርመው እችላለሁ?። ልክ በዚሁ አይነት ብዙዎች የመጻኢነትን ነገረ ፍጻሜ የሚያቀነቅኑ መምህራን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ላሉ አንድንድ ወሳኝ ቃላት የሚሰጡት ትርጉም ቃሉ የማይለውን ሌላ ነገር እያስነበበን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ልንማማርና ልንደማመጥ ካልቻልን በቀር እንዲህ አይነቱ ጭቅጭቅ በሚፈጥረው ስሜት ወንድሞቼን ማጣት ግን ስለማልመኘው እየታዘብኩ ለማለፍ እገደዳለሁ።
በመጨረሻም፣ ወንጌል አማኝ ለሆኑቱ የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ተስፋም ጸሎትም ያለኝ መሆኑን አልሸሽግም። ከሁሉ አስቀድሞ፣ በተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉ መጻኢያን ወንድሞቼና እህቶቼ የትኛውንም የነገረ ፍጻሜአዊ ጎራ ተተግነውና ያላቸውን የነገረ ፍጻሜ አቋም ይዘው ከዘመን መዳብያን (Dispensationalism) አስተምህሮም ሆነ ከየትኛውም የለዘብተኛው ስነ መለኮት 'ክህደትና' የዘመነኛው ኒዎ ጰንጠቆስጤ 'እብደት' እምነታቸውን መከላከል እንደማይችሉ ይህን አንድ ነገር ሊያውቁ ይገባል። ምክንያቱም የሚከተሉት የነገረ ፍጻሜ ትምህሮታቸው ክህደትን የሚያሾልክ አንዳች ቀዳዳ ነገር አለበት። "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" ብለው መቆም የሚፈልጉ የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ኃላፋዊነትን ከመቀበልና ነገረ ፍጻሜአዊ አስተምህሮአቸውን ከመከለስና ከማረም ውጭ ቀዳዳቸውን የሚከድን ሌላ ምንም አማራጭ የላቸውም። ሙሉ ኃላፋዊነትን ከተቀበሉ ብቻ የተሃድሶው ቤተ እምነት ብቸኛ ጡንቻ የሆነው "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" የሚለው ታሪካዊው አቋማቸው ከማንኛውም የተሳሳተ ኃይማኖት እምነታቸውን መከላከል የሚችሉበት መሰረት ይሰጣቸዋል። ደርዝ ባለው አስተሳሰብ በቅንነት እምነታቸውን የሚጠይቁ፣ በትህትናም የቃሉ ተማሪ ለመሆን የሚወዱና ኃላፋዊነትን የሚቀበሉ የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ልዩነትን ማድረግ ይችላሉ። ዘመነኛው ክርስትና ለዛውን ከማጣት፣ ተረት ተረት ሆኖ እንደ ኃሰተኛ ኃይማኖት፣ ሴክትና ከልት መስሎ ከመቆጠር የሚታደገው ብቸኛ ተስፋው ወንጌላዊ መሰረት ያለውን ሙሉ ኃላፋዊነትን መቀበል ብቻ ነው።
ማንበብ ለምትወዱ ተዛማጅ የሆኑ የፕሪቴሪዝም ጽሁፎቼን ላጋራችሁ፦
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/blog-post.html?m=1
http://gizachewkr.blogspot.com/2020/01/blog-post.html?m=1
ቸር ያሰማን፣ ቸር ያሰንብተን!!
ግዛቸው ከበደ \ቄስ\