ከዚህ ሕይወት በኋላ
(ለሚያምኑ እና ለማያምኑ)
“ከሕይወት በኋላ” የተሰኘውን ሃረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጨርሶ ማግኘት አይቻልም፤ ሆኖም ሰዎች በምድር ላይ ያላቸውን የሕይወት ዘመን ቆይታቸውን ጨርሰው ከሞቱ በኋላ ምን አይነት ሕይወት እንደሚኖራቸውና፣ ዘላለማዊ እድላቸውን በተመለከተ ያለውን ሁኔታ ሊያሳይ እንዲችል ሆኖ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል መሆኑ በሁሉ ዘንድ ይታወቃል ። አማኞች ለሆኑ ከልዩ ልዩ ዘርና ወገን ለተመረጡትና ለተዋጁት ኃጢአተኞች፣ ከዚህ ሕይወት በኋላ ያለው ሕይወት ማለት ሊታይ በማይችለው ሰማያዊ መንግስትና ግዛት፣ በማይታየው የክርስቶስ ሀልዎት ፊት ሊኖሩ የሚቀበሉት ዘላለማዊ በረከት ነው።
የመጨረሻው ፍርድ ከተሰጠና ከተጠናቀቀ ከ70 ዓም በኋላ ወዲህ ያለን እግዚአብሔር ለሕይወት የመረጠን ቅዱስን ሁሉ በምንሞትበት ቅጽበት፣ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር በክብር በሚገዛበት መንፈሳዊ ግዛት (spiritual realm)፣ ይኸውም በአዲሲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም ከ70 ዓም በፊት አስቀድመው ከሞቱ ቅዱሳን ጋር በሕይወት እንገናኛለን። ክርስቶስ በክብር በደመና ተመልሶ ከመጣበት ከ70 ዓም በኋላ ያሉ አማኞች ሁሉ እያንዳንዳቸው፣ የአዲሱ ኪዳን ወንጌል የሚያውጀው መንግስት አካል ሲሆኑ፣ “እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።” (ዕብራውያን 9፥ 28) ተብሎ እንደተጻፈ፣ በዳግመኛ ምጽአቱ በክርስቶስ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀውን ድነት አግኝተዋል።
አማኞች ሲሞቱ ወዲያውኑ በሰማያት የተዘጋጀላቸውንና የሚጠብቃቸውን፣ የማይሞተውን፣ የማይበሰብሰውን፣ የከበረውን፣ መንፈሳዊውን፣ የማይታየውን ሰማያዊውን አካል ይለብሳሉ። “ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል” (1ቆሮንቶስ 15፥ 53-54)። ስለዚህ ያ ከስጋና ከደም የተሰራው አሮጌው አካላቸው ተመልሶ እንደገና ላይታሰብና ላይታይ ወደ ምድር አፈር ገብቶ ብስባሽ ይሆናል። በሚሞቱበት ጊዜ የተሻለውንና የሚበልጠውን ሰማያዊ አካል ይለብሳሉ እንጂ ራቁታቸውን ሆነው አይገኙም። ሟች የሆነው የአሮጌው ሥጋዊ አካል ሞት በአዲሱ የማይሞት መንፈሳዊ አካል ሕይወት ይዋጣል፣ እንጂ የሥጋ ትንሳኤ የሚባል ተረት አይኖርም።
“ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን።” (2ቆሮንቶስ 5፥ 1-4)።
እግዚአብሔር በጸጋው ለመረጠን ለእኛ ለአማኞች ከዚህ ሕይወት በኋላ ያለው ዘላለማችን በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም በክርስቶስ ሀልዎት ፊት በደስታ የምንቆምበት ነው።
“ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” (ራእይ 21፥ 2-4)
የማያምኑ ግን ከዚህ ሕይወት በኋላ የሚጠብቃቸው እድል የማይታየው አለም አካል በሆነውና “ሲኦል” ወይም “የእሳት ባህር” ተብሎ በሚታወቅ ስፍራ ለዘላለም መሆን ነው። ቤዛነቱን የገፉ፣ እምነትን እምቢ ያሉ፣ መዳንንም ያልተቀበሉ የማያምኑ ኃጢአተኞች ሁሉ ከየትኛውም ዘር ቢሆኑ ዘላለማዊ ኩነኔ ይቀበላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የኃጢአተኞችን ዘላለማዊ እድል አስመልክቶ ሲናገር፦ “ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ” ተመድቦባቸዋል፥ (እብራውያን 9፥ 27)፣ ሲል ይደነግጋል። ይህም ማለት በዘላለማቸው ውስጥ ትክክለኛውንና ጽድቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቁጣ በነፍሳቸው ለዘላለም ይቀበላሉ፣ ማለት ነው። (ሮሜ 2፥ 5፤ 9፥ 22፤ ኤፌሶን 5፥ 6፤ ቆላስይስ 3፥ 6፤ተሰሎንአግኝተዋል።እይእይእይ 14፥ 10-11)። ይህም ለሰዎችን ሁሉ የምናስጠነቅቅበት የእግዚአብሔር እውነት፣ በኢየሱስ ክርስቶስም አለማመን የተሰኘውን ዋና ኃጢአት የሚመጥን ጽኑ ፍርድ ነው እንጂ፣ ማንንም የምናስፈራራበት የፈጠራ ሽብር አይደለም።
“በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐንስ 3፥ 36)
የዘላለምን ሕይወት ያገኙ በመሆንና ሕይወትን የማያዩ ሆኖ በእግዚአብሔር ቁጣ ስር የወደቁ በመሆን መካከል ያለው ወሳኝ መስመር በልጁ ማመን ወይም አለማመን ብቻ ነው። የማያምኑ ሰዎችም ሕይወትን ሳያዩ በእርግጠኝነት ዘላለማቸውን የሚያሳልፉት ስጋንና ደምን ባላካተተ አካላዊነት መሆኑ እሙን ነው። ከተዳሳሹ አካላቸው ተነጥለው ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በሙላት ያልገለጠልን አንዳች አይነት የተለየ “አካል” ኖሯቸው፣ “እያወቁ”፣ “እየተሰማቸው”፣ “እያለቀሱ”፣ “እየጮኹ”፣ በነፍሳቸው ጸጸት እየተንገበገቡና ጥርሳቸውን እያፋጩ የእግዚአብሔርን ቁጣ ይቀበላሉ። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር ያልዳኑ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ወደ ሲኦል ይሄዳሉ ብሏቸዋል። ወደ ሲኦል የሚሄዱ ሰዎችን በተመለከተ እንዴት እንደሆነ ባይገባንም፣ ቢያንስ ግን መጽሐፍ ቅዱስ “እጆች”፣ “እግሮች” እና “አይኖች” እንደሚኖራቸው፣ “ትላቸውም እንደማይሞት” “እሳቱም እንደማይጠፋ” ይጠቅሳል
“እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመሄድ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻላል። እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመጣል አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጣት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነመ እሳት ከመጣል አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል። (ማርቆስ 9፥ 43-48)፤ በተጨማሪም ኢሳይያስ 66፥ 24 ላይ “ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ” ይላል።
ክርስቶስ በትምህርቱ፣ በሲኦል በስቃይ ያለ አንድ ባለጠጋ ሰው “አይኖች” እና “ምላስ” እንደነበሩት፣ መናገርና ማሰብ እንደተቻለው፣ ስሜትም እንደነበረው ጠቁሞናል። ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ከዚያ ያለፈ ምንም ገለጻ አልተሰጠም (ሉቃስ 16፥ 22-24)፣ እኛም ከተጻፈው አልፈን ምንም ለማለት አንደፍርም። ክርስቶስ እንዳይነግስባቸው ለእምነት በማይታዘዙት ላይ የሚኖረው ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ቁጣ ግን እርግጥ ነው፣ ምንም ጥርጥር የለውም። ያልዳኑ ሰዎች፣ አዳኛቸው እንዳይሆን ክርስቶስን እምቢ ያሉ እስከሆነ ድረስ፣ ወዮ ለእነርሱ!! ከዚህ ሕይወት በኋላ ፈጽሞ ሕይወትን አያዩም፣ የእግዚአብሔርንም ጸጋ አያውቁም አይለማመዱትምም። ስማቸውም በሕይወት መጽሐፍ የለም፣ አልተጻፈምም፤ ዘላለማዊ እድላቸውም ለእያንዳንዳቸው በእሳት ባህር ውስጥ መጣል ብቻ ነው
“በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።” (ራእይ 20፥ 15)።