Saturday, February 20, 2021

የምጽአቱ ተስፋ እና አቋሜ


የምጽአቱ ተስፋ እና አቋሜ


የምጽአቱ ተስፋ (parousia) ያኔ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ላይ፣ "ሁለተኛ እመጣለሁ" ሲል ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ ሲሰጥና፤ ኋላም በቅዱሳን ሐዋርያቱ ይኸው ተስፋ እየተደጋገመ ሲነገርና ሲዘገብ፤ ያኔውኑ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ውስጥ፣ ደግሞም በጣም በቅርቡ፣ ማለትም በዚያው አንድ ትውልድ የእድሜ ዘመን፣ ይኸውም በ70 አ.ም ላይ በተጠናቀቀው ዘግናኙ የእስራኤል ሮም ጦርነት ወቅት፣ "ከመሆን የማይቀር"፣ ቀንም የተቆረጠለት፣ ሳይዘገይ የሚፈጸም ጉዳይ ነበር። በ70 አ.ም ላይ ከሆነው ከዚህ ታሪካዊ ክስተት ተነጥሎ፣ 2000 አመታትና ከዚያም በላይ ተራዝሞ አሁን እኛ ባለንበት ዘመንም ይሁን ወይም ገና ወደ ፊት በሚመጣ ሌላ የሩቅ ዘመን የሚጠበቅ የጌታ ምጽአትም ሆነ የዘገየ ተስፋ የሚባል ነገር ፈጽሞ የለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እውቅና የሚሰጠው ዳግመኛ ምጽአት የተፈጸመ ተስፋ ሆኖ አልፏል። ይህን ስለሰማችሁ በፎቶው ላይ እንዳለው ህጻን አታለቃቅሱ። ደግሜ እላለሁ፣ ጌታ ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ወደፊት በየትኛውም ጊዜ ተመልሶ አይመጣም። ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው፤ ጥያቄው ከዚህ እውነታ ጋር ለመኖር ተዘጋጅታችኋል ወይ? የሚል ነው።


ሲጠጡት ከኖሩት " ይመጣል" ከሚለው የሰው ትምህርት የተነሳ ይሄ "ትንቢት ተፈጽሟል"፣ "ምንም የሚጠበቅ ነገር የለም" የሚለው እንቅጩን የሚናገረው እምነታችን ክህደት የሚመስላቸው ህልቆ መሳፍርት ክርስቲያኖች መኖራቸው እሙን ነው። ዳሩ እውነት የጥቂቶች መሆንዋን ሳያውቁ በደቦ የሚያስቡና ምንም የማይጠይቁ ብዙዎች አያስተውሉም። በወጉ ባልተተረጎሙ አንዳንድ ጥቅሶች ላይ ራሱን ካንጠለጠለው "ይመጣል" ከሚለው ያብዙዎች እምነት ይልቅ፣ መሰረቱን በቅዱሳት መጻህፍት ላይ አድርጎ፣ ጊዜ ጠቋሚ የሆኑትን የንባብ ክፍሎች በወጉ እየተረጎመ "እንደ ተስፋ ቃሉ ተመልሶ መጥቷል" የሚለው የጥቂቶች እምነት በማዕበሉና በወጀቡ አንጻር ያለመናወጥ ቀጥ ብላ እንደምትቀዝፍ መርከብ ያለፍርሃት ለመንሳፈፍ የትንቢቱ ቃል ያስተማምናል። የበኩረ ተደራስያኑን አውድ አክብራችሁና ጠብቃችሁ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን በወጉ አጥኑ እንጂ፣ ከስር በስዕሉ ላይ እንዳለው ሰው ወደመቃብር እስክትገቡ ድረስ የሌለ ነገር እያመናችሁ ዝም ብላችሁ በአቦ ሰጥ አትኑሩ።


ጌታ ገና ወደፊት ተመልሶ እንደሚመጣ የሚያምነውና የሚያስተምረው ሁሉም የመጻኢነት (futurism) ነገረ ፍጻሜ (eschatology) አስተምህሮ ፈተናውን የወደቀው፣ ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ቤተ ክርስቲያንና ከእስራኤል ህዝብ እጣ ፈንታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘውን አጠቃላይ የሆነ የዳግመኛ ምጽአቱን ትንቢት ባህርዩንና፣ እነዚያን ጊዜ ተኮር የሆኑ ደርዘን ሙሉ የአዲስ ኪዳን ምንባባት የተነገሩበትን የቋንቋ አጠቃቀም እውነታ ባለማወቅና ባለማስተዋል ነጥብ ላይ ነው። ያስተውላሉ የሚባሉትም እንኳ ከሚበዙት የመጻኢያን ጎራ ሊደርስባቸው የሚችለውን ነቀፋ  በመፍራት ስለ ክብራቸው ሲሉ ጥቅሶቹ የሚያወሩለትን ጊዜ ላለማየት ሆን ብለው አይናቸውን ጨፍነዋል። ዳሩ ግን የመጻኢነት (futurism) አመለካከት በሚያቀነቅነው "እስካሁን ባልተፈጸመና በዘገየ ተስፋ" አስተምህሮ፣ ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ የተናገሩትን የትንቢት ቃል እውነተኛነቱን ማረጋገጥም ሆነ ክርስትናችንን ከጥቃትና ከስድብ መከላከል ግን ፈጽሞ አይቻለንም።


ኃላፋውያን (Preterists) ግን በትንቢት መጻህፍት ላይ የሚያቀርቡት የትርጉም ቀዋሚነትን የሚከተለው ትንታኔና፣ ተስፋውም በተቀጠረለት ጊዜ እንደ ተፈጸመ ለማስረገጥ ራሱን የቅዱሱን መጽሐፍ ቃል የታመነ ምስክር ማድረጋቸው፣ እንዲሁም እንደ ደመና ከበውን ያሉ ታሪካዊ መዛግብትን ተጨማሪ ማስረጃ አድርገው ማቅረባቸው፣ በስነ ፍታቴ (hermeneutics) መርህ ሊረጋገጥ የሚችል ንጹህ ትምህርት ከመሆኑም በላይ፣ የተሳዳቢዎችንና የነቃፊዎችን ጥቃት የሚመልስ፣ የከሃዲዎችንም አፍ የሚያዘጋ አስተምህሮ ነው።


እኛ ኃላፋውያን በቅዱሳት መጻህፍት ንባባችን ላይ የበኩረ ተደራስያኑን ዋጋና አስፈላጊነት እውቅና እንሰጣለን እንጂ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ላይ አንዳች አንጨምርም። ለቅድመ ተደራስያኑ ዋጋ ሰጥተን ቅዱሳት መጻህፍትንም ወደ በኩረ ተደራስያኑ አውድ መልሰን እናነባለን፣ ከዚያም እንተረጉማለን እንጂ፣ ከቅዱሳት መጻህፍት አንዳች አናጎድልም። ይህ ነው የስነ ፍታቴው መርህ። ኢየሱስ ክርስቶስንም ሊያከብረው የሚችል ትርጉም ይህ ብቻ ነው ብለን አቋም ይዘናል።


ይህ አቋማችን በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ከሚገኝ ያፈጠጠ እውነት፣ እርሱም የትንቢት ሙሉ ፍጻሜ ጋር ያገናኘናል። እኔ በግሌ እንደ አንድ ተራ ሉተራዊ ቄስ ከታናሽነቴ አንስቶ እውነትን ስፈልግ ካልተሸፈነው እውነት፣ ከተፈጸመው ወንጌል ጋር ተገናኝቻለሁ። ስለዚህም አቋቋሜንና አሰላለፌን አርሜ ኃላፋዊነትን ተቀብያለሁ፣ ያውም ሙሉ ኃላፋዊነት። በዘመኔ ሁሉ ያለእውቀት ስከተለው የኖርኩት፣ ዛሬም የሚበዙት ወዳጆቼ ያለጥያቄ ያንጠለጠሉት "መጻኢነት" እና ትምህርቱ ግን እውነትን የሚጋርድ፣ የትርጉም ቀዋሚነት የሌለው፣ ለቅዱሳት መጻህፍት በኩረ ተደራስያን አውድ ዋጋ ከመስጠት ይልቅ ለኖረው ልማዳዊ አመለካከቱ ትክክለኛ መሆን የሚጨነቅ፤ ከዚህም በላይ የጌታችንና የመድሃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ሆኖ ስላገኘሁት ወዲያ አሽቀንጥሬ ጥየዋለሁ። በዚህ ቅር የሚሰኝ ካለ ምንም ማድረግ አልችልም፣ ኃላፋዊነት የብርሃን ጉዳይ ነውና። "ቅዱሳት መጻህፍት ብቻ" በሚለው አስተማማኝ ምሰሶ ላይ የተደገፈው  ወንጌላዊው ሉተራዊ እምነቴና ኃላፋዊው ነገረ ፍጻሜ በአመለካከቴ ውስጥ ታርቀው ሳያቸው ደስታዬ ወደር ይለውም። ስለዚህ አስተውሉ፣ ትክክል መስሎ የሚታያችሁና የሚሰማችሁ ነገር የእግዚአብሔር ቃል ከሚናገረው ጉዳይ ጋር የማይስማማ ከሆነ፣ ያ ስሜታችሁ ምንም ያህል የብዙሃኑ ስሜት ቢሆንም እንኳ በራሱ ትክክልና ልክ ሊሆን ከቶ አይችልም። 


ሰው ሁሉ እንደኔ ይሁን የሚል ድርቅና የለብኝም፤ ሊማሩ ለሚወዱና ለሚጠይቁኝ ግን ጉዳዩን እስኪረዱትና መሬት እስኪይዙ ድረስ፣ ይህንን ለብዙዎች "ደብረ በጥብጥ" የሆነባቸውን እውነት ቅዱሳት መጻህፍትን ብቻ እየገለጥሁ መልስ ለመስጠት እተጋለሁ። ለዘመናት በማንም ሳይጠየቅ ወንበሩ ላይ ተንሰራፍቶ የተቀመጠ ልማዳዊው ዶግማ እምነቱን የሚያፋጥጥ የተፈጸመው ተስፋ እውነቱ መገለጥ ሲጀምር በድንቁርና ያቆመው መንግስቱ መበጥበጥ ጀምሯል። ምክንያቱም ኃላፋዊነት ወጥሮ ይጠይቃል ይጠየቅማል፣ ስለዚህ ልማዳዊው አመለካከት በፊቱ ሊቆም አይችልም። በመሆኑም "ለፍተሻው ተባበሩን" እንላለን፣ ምክንያቱም ሲታመን የኖረው ነገር ሁሉ በጥብቅ መፈተሽ አለበት፤ ሊፈተሽም የማይወድ ሁሉ አንዳች የሸሸገው ነገር ቢኖረው ነው። በቃሉ ብርሃን ፈትሼና ፈትኜ እውነት ሆኖ ያገኘሁትንና የገባኝን የትንቢት ፍጻሜ ያለፍርሃት አካፍላለሁ። ገለባውን የሰው ትምህርት ደግሞ ቃሉን ለሚወዱ ሁሉ አጋልጣለሁ። በዚህም ደስ ይለኛል። ቃሉን ከሚወዱ ሁሉ ጋር ብዙ ደስታ አለኝና። በሶሻል ሚድያ ጽሁፎቼንና ትምህርቶቼን ለሚከታተሉ ሁሉ አክብሮት አለኝ። ከቃሉ ተምረው ፕሪቴሪዝምን የተቀበሉ ወንድሞች እህቶች በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተ እምነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ስለሆነም ጌታን ስለእነርሱ አመሰግናለሁ። በዚህም አቋማቸው ምክንያት መገፋትን እንዲታገሱ፣ ልባቸውንም እያነጹ ያለፍርሃትና ያለመናወጥ እንዲኖሩ በዳንንበት ጸጋ እመክራለሁ። መጻእያንም ቢሆኑ እንኳ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ቅዱሳን ናቸውና፣ ልጅነቴን በኖርኩበትና ባገለገልኩበት በቤተ እምነቴ በየትኛውም በሚካፈሉት የወንድሞች ጉባኤ በልብ ስፋት፣ በናፍቆትና በትህትና ተገኝቼ የሚያካፍሉትን የጸጋ አገልግሎት በፍቅር እየተካፈልሁ፣ ደግሞም የምሰማውንና የማየውን በቃሉ ወንፊት እያጠለልሁ እጠጣለሁ እንጂ ነፍሴን አከሳት ዘንድ ከህብረቱ እንጀራና ከጌታ ማዕድ አላጎድላትም።


(ግዛቸው ከበደ)

Sunday, February 14, 2021

እስራኤል ሁሉ ይድናልን?

እስራኤል ሁሉ ይድናልን?


ሮሜ 11፥ 26 "እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል።


ይህ መግለጫ ማስረጃውን ከቅዱሳት መጻህፍት ያደረገና ሊፈጸም የተገባው የተስፋ ቃል ነው፤ እንዴትና መቼ ነው የሚፈጸመው? የሚለው ግን መሰረታዊ ጥያቄ ነው። መልሱም የሚወሰነው ልንከተለው በመረጥነው የነገረ ፍጻሜ ምልከታችን አንጻር ነው።


ከተለያዩ ሥነ መለኮታዊ እይታዎችና አቋሞች ጋር የሚንጸባረቁ በርካታ ትርጓሜዎች ለዚህ ምንባብ እንደሚሰጡ ይታወቃል። በዋናነት የሚጠቀሱ አንዳንዶቹን ትርጉሞች ለማመላከት ያህል፦


  1. "እስራኤል ሁሉ ይድናል" ማለት የሁሉም የእስራኤል ዘስጋ ሕዝብ/ ዘር/ ብሔረሰቦች ጥቅል መዳን ነው፣ የሚሉ አሉ። ይህ ግን ትክክለኛ ያልሆነ ትርጉም ነው። ምክንያቱም በስጋ እስራኤል የሆኑ ሁሉም እንዳሉ (ባዮሎጂካሊ) የሚድኑ ከሆነ ታዲያ ለአይሁድ ወንጌልን መስበክ ለምን ያስፈልጋል? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ኃጢአተኛም በዘሩ እየተመረጠ ይድናል ብሎ ማሰብና ማስተማርም ያፈጠጠ ኑፋቄ ብቻ ሳይሆን፣ በክርስቶስ መስቀል ላይ ማላገጥም ጭምር ነው። ስለዚህ ይህ አይነቱ የአፍቅሮተ እስራኤል እሳቤ ከመሰረቱ የፎረሸ ነው።


  1. የአማኞች መዳን ነው፣ የሚሉም አሉ። ይህ ትርጉም በሁሉም የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ያሉትን በሥጋ አይሁድ የሆኑትንና መንፈሳዊ አይሁድ የሆኑትን አማኞች ይመለከታል። በዚህ እሳቤ ላይ ሊነሱ የሚችሉ መከራከርያ ነጥቦች አሉ፤ ከእነርሱም:-


# ይህ አቋም የእስራኤልን ምንነትና ትርጉም ይቀይራል የሚለው በዋናነት ይጠቀሳል። ይህም ማለት፣  "እንግዲህ፦ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? እላለሁ። አይደለም እኔ ደግሞ እስራኤላዊና ከአብርሃም ዘር ከብንያምም ወገን ነኝና።" (ሮሜ።11፥ 1) በሚለው መሰረት እስራኤልን በቁሙ (literal) ከማሰብ ይልቅ፣ "እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል።" (ሮሜ 11፥ 26) በሚለው መሰረት እስራኤልን በመንፈሳዊ ሁኔታ ወደመረዳት ያመጣናል፣ ማለት ነው። ይህም አይነቱ እስራኤልን በመንፈሳዊ ሁኔታ መረዳት ለጠቅላላው የአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ህዝብ ምንነትና ማንነት ተገቢና ተመራጭ ትርጉም ነው፤ ሆኖም "እስራኤል ሁሉ ይድናል" ማለት ግን በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በአለም ሁሉ ያሉ አማኞች ይድናሉ ማለት ነው ብሎ በዚህ መንገድ መረዳት የንባብ ክፍሉን አውድ ያስለቅቃል። ምክንያቱም በንባብ ክፍሉ የቀረበው ሙግት፣ የክርስቶስን ወንጌል በመግፋት ልባቸውን እልከኛ ስላደረጉ ስለ ጳውሎስ የስጋ ዘመዶች እጣ ፈንታ የተነገረ በመሆኑ ነው።


  1. በሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ ላይ ስለሚሆን የአይሁድ ህዝብ ቅሬታ ደህንነት ነው፣ የሚሉም ደግሞ አሉ። ይህ አይነቱ የመጻኢነት እሳቤ ላይ የተንጠለጠለ አቋም በአብዛኛው የተቀዳው ከዌስት ሚንስቴር የእምነት መግለጫ አቋም ይመስላል። ያም ሆኖ ግን፣


# የሮሜ መልዕክት ከተጻፈ እነሆ ሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ያለፈው ሲሆን፤ ጳውሎስም በመልዕክቱ የሚያነሳቸው አይሁድ የገዛ ዘመኑን እስራኤል በመሆኑ እንዲህ ያለው ድምዳሜ ለጠቅላላው የሮሜ መልዕክት ፍሰት ባዕድ ትምህርት ይሆናል።

# አይሁድም ይቀኑ ዘንድ (ሮሜ 11፥ 1) በርካታ ዘመን /ጊዜ ነበራቸው። በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አይሁድ ቀናተኞች ነበሩ። አይሁድ ቤተክርስቲያንን እስከ ጥግ ሄደው ያሳደዱትም ከዚህ የተነሳ ነው።


  1. በታላቁ መከራ ጊዜ ከመከራው የሚድኑ አይሁድ ናቸው፣ የሚሉም አሉ።  ይህም እሳቤ፣ ታላቁ መከራ መቼ ነበር/ መቼስ ይሆናል? በሚል ስነ ፍጻሜአዊ ነጥብ ላይ በሚነሳ ክርክርና ክርክሩ በሚደርስበት ድምዳሜ ላይ የሚያርፍ ነው። 


# የአይሁድ ሕዝብ ቅሬታ በ70 ዓ.ም ከሆነው ከኢየሩሳሌም ጥፋት በፊት ድነው ከነበረ፣ እንግዲያዉስ ታላቁ መከራ በዚያን ጊዜ ያለፈ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ኹነት ነበር ማለት ነው። ስለ ታላቁ መከራ ምንነትና መቼ ይሆናል ሲል መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ጥናት ዘርዘር አድርጌ ያቀረብሁበትን ጽሁፍ ለመመልከት ይህንን ሊንክ ይጠቀሙ:-

http://gizachewkr.blogspot.com/2018/01/12.html?m=1


  1. በቃል ኪዳኑ የሽግግር ዘመን ወቅት ኢየሩሳሌም እስከሚፈረድባትና መቅደስዋ ወድሞ እስኪፈራርስ ድረስ ይኖሩ የነበሩ የአይሁድ ሕዝብ ቅሬታዎች ናቸው፣ የሚልም ትርጉምና አቋም አለ።


# ይህ አይነቱ ትርጉምና መረዳት በንባብ ክፍላችን ላይ ያለውን ጊዜ የሚጠቁምና የሚያመለክት ነገር ስላለው፣ ከዚህ የተነሳ በወጉ ለሚያስቡና እንደ ቤሪያን ሰዎች ለሚጠይቁ የቃሉ ተማሪዎች የበለጠ ሥሜት ሊሰጥ የሚችል ትርጉም ነው፣ ለማለት ይቻላል። ማስረጃዎችን በቅደም ተተከተል እንይ፦ 


ሀ/ ጳውሎስ በእርሱ ዘመን ያሉትን አይሁድ ሲገልጣቸው:-


 "እንደዚሁም በአሁን ዘመን ደግሞ በጸጋ የተመረጡ ቅሬታዎች አሉ።" (ሮሜ 11፥ 5) ይላል፤ ይህም ኤልያስ በገዛ ራሱ ዘመን ያሉትን ቅሬታዎች "ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።" (1ነገስት 19፥ 10) ሲል በገለጠበት መንገድ የሚታይ ነው። ነብዩ ኤልያስም ሆነ ቅዱስ ጳውሎስ በየራሳቸው ዘመን ስለነበሩ ስለትውልዳቸው ሰዎች ይናገራሉ እንጂ ስለሌላ ትውልድ ሰዎች እየተናገሩ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ጳውሎስ የሚለውን ቀጥላችሁ ተመልከቱ:-

 

"እንግዲህ፦ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? እላለሁ። አይደለም እኔ ደግሞ እስራኤላዊና ከአብርሃም ዘር ከብንያምም ወገን ነኝና።" (ሮሜ 11፥ 1) የገዛ ዘመኑን ትውልድ የተመለከተ ንግግር እንደሆነ ግልጽ ነው።


# ቅሬታው "በአሁን ዘመን" (ሮሜ11፥ 5) ላይ ተብሎ በተገለጠው የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ይኖር የነበረው ሕዝብ ነው -ያም የአሁን ዘመን የተባለው የጳውሎስና የሮሜ መልዕክት በኩረ ተደራስያን ዘመን ነው፣ እንጂ ሌላ የትኛውም ዘመን አይደለም።


# ጳውሎስ በወንጌል ስብከቱ በኩል ይድናሉ ብሎ ተስፋ ያደረገው ቅሬታም ያው የእርሱ ትውልድ አይሁድ ነበሩ፤ በርካቶቹ ደግሞ ያኔ በክርስቶስ አምነው የዳኑ ነበሩ (ሐዋ 2፥ 5-12፣ 37-41)


ለ/ በሮሜ 9-11 ባለው ክፍል የተጠቀሰ ከሺህዎች አመታት በኋላ የሚደርስ የወደፊት ጊዜ መከራም ሆነ ወይም "ከንጥቀት በኋላ" የተሰኘ ጊዜ ፈጽሞ የለም። ክፍሉ የማያወራውን ርዕሰ ጉዳይ ከሌለበት አምጥቶ መሰንቀር ስህተት ከመሆኑም በላይ ቃሉን "አስገድዶ" ማናገር ይሆናል። እንዲህ ያለውም ድፍረት ኑፋቄን ያዋልዳል።


ሐ/ ጳውሎስ ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹን ለማዳን በሚሆን ፍላጎትና ትጋት ለወንጌል እየሰራ ነበር 

"ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ።" (ሮሜ 11፥ 13ና 14) ይላል፤ ሥለዚህም፦


♦ የሚናገረው በሺህ አመታት ስለሚቆጠር የወደፊት ጊዜ ሳይሆን እርሱ ስለነበረበትና ስላገለገለበት የአሁን ጊዜ ነው።


♦ ይህ የእስራኤል ሁሉ መዳን ተስፋ ገና ወደፊት ከ2000 ዓመታት በኋላ ቆይቶ የሚፈጸም ከሆነ ታዲያ የጳውሎስ አገልግሎት ምን ሊረዳ ይችላል?


# የአሁን ጊዜ አመልካች የሆኑ እነዚህ ንግግሮቹን ልብ ብለን ካየን ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ስለራሱ ዘመን የአይሁድ ሕዝብ ነው። ለምሳሌ "እንዲሁ በተማራችሁበት ምሕረት እነርሱ ደግሞ ምሕረትን ያገኙ ዘንድ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም።" (ሮሜ 11፥ 31) የሚለው ግልጽ የሆነ የአሁን ጊዜ ንግግር ነው።


መ/ በመጨረሻም፣ ከምንድን ነው የሚያድናቸው?


# የሚያድናቸው በ70 ዓ.ም ላይ ከሚፈጸምና በዚያን ወቅት በኢየሩሳሌም ላይ ሊመጣ ካለው ጥፋትና ፍርድ ነው። ሊመጣ ያለው ቁጣም፣ በከተማይቱ ኢየሩሳሌም ውድመት፣ በቤተመደሱ መደምሰስ፣ በአሮጌው ስርዓት እስከወዲያኛው መወገድ፣ ብሎም በጦርነቱና በወረራው የእስራኤል ህዝብ ላይ በሰይፍ ስለት የሚፈጸም ዕልቂትና ፍጅት እንዲሁም ለከፋ ባርነት በምርኮ መወሰድን ያካተተ ዘግናኝ ፍጻሜ ነው። ከዚህ ጥፋት የሚያመልጡት እግዚአብሔር ለደህንነት የመረጣቸውና በውድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የነበሩ ከጦርነቱ መቀስቀስ አስቀድሞ በከተማይቱ ላይ የሚመጣባትን አደጋ ከጌታ ትምህርት ተረድተው ፈጥነው ከተማይቱን ጥለው የወጡት ቅዱሳን ብቻ ናቸው። እነዚያማ የእግዚአብሔርን ልጅ ሰቅለው ቤተክርስቲያንን እስከ ጥግ በማሳደድ በተሰበከላቸው የምህረት ወንጌል ላይ ያላገጡና ንስሃ ያልገቡ ሁሉ አለቁ፣ በእናቱ ሆድ ካለው ጽንስ ጀምሮ እስከሽበታሙ ድረስ አንድም የተረፈና ያመለጠ አልነበረም።


እንደ ማጠቃለያ፦


♦ አንዳንዶች "እስራኤል ሁሉ" የሚለውን መግለጫ በቋንቋ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተለዋዋጭ የሚሆን ክስተትን  እንደሚያመለክት የንግግር ዘይቤ (diachronic sense) ይረዱታል፤ ቋንቋው በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ ለውጦችን ጥናት የሚመለከት ነው። ማለትም በያዝነው ርዕሰ ጉዳይ፦


# "እስራኤል ሁሉ" የሚለው ሀረግ የሚያመለክተው በታሪክ ሁሉ ውስጥ ለሚኖሩና፣ ከትንሳኤ በኋላ ሊመጣ ባለው ዓለምም ተካፋይ ለሚሆኑና ለሚኖሩ የእስራኤል ሕዝብ አመልካች ነው ሲሉ፣ ከመንፈሳዊው እስራኤል ይልቅ በፍጥረታዊት እስራኤል ላይ ትኩረት አድርገው ይተረጉሙታል። ይህ እይታ ግን የተፈበረከውና originate የተደረገው በአይሁድ የሰዱቃውያን ሴክት school of thought ሲሆን፤ እግዚአብሔር እስራኤል እና ቤተክርስትያን የተሰኙ ሁለት ህዝቦች አሉት ብሎ፣ ለሁለቱም አንዱን በእምነት ሌላውን ያለ እምነት በዘሩ ምክንያት ያድነዋል ሲሉ እርስ በርሱ የተሉያየ የድነት መንገድ አለ ብሎ ከሚያምነውና ከሚያስተምረው ኑፋቄ ወለድ ከሆነው ከዲስፔንሴሽናሊዝም የአስተምህሮ ህጸጽ ተጽዕኖ የተነሳ በክርስቲያኑ አለም እንዲሰርጽ የተደረገ የክርስቲያን ጽዮናዊነት አስተሳሰብ ነው።


♦ ሌሎችም "እስራኤል ሁሉ" የሚለውን በ synchronic sense ማለትም በታሪክ ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ፣ በተለይም በነገረ ፍጻሜ (eschtological) መርሃ ግብር መሰረት በዘመን መጨረሻ ላይ ለሚኖረው ሕዝብ የተነገረ አድርገው ይወስዱታል።


# ይህ ሁለተኛው አማራጭ የነገረ ፍጻሜ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ተገድቦ፣ ቅዱሳት መጻህፍት በሚያውቁት የዘመኑ መጨረሻ ምንነትና ትርጉም ላይ እስካረፈና እስከታየ ድረስ ብቻ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረቱንና የሥነ ፍታቴ ቀዋሚነቱን የጠበቀ ተመራጭ ድምዳሜ ይሆናል። 


ዳግላስ ሙ የተባሉ ጸሐፊ ይህንን በግልጽ ሲያስረዱ፣ "እስራኤል ሁሉ" የሚለው ሃረግ diachronic በሆነ መንገድ የምንረዳው አይደለም፤ ይህም ማለት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በድግግሞሽ እየተራዘመ የሚለዋወጥ ትርጉም የለውም፤ ከዚህም በላይ ይህ የሮሜ መልዕክት ምንባብ የክፍሉ አውድ የሚያወራው "እስራኤል መሲሁን እምቢ ብላ ስለመቃወምዋ እና የአህዛብ ሙላት እስኪሆን ድረስ ልቧን እልከኛ አድርጋ በድንዛዜ ውስጥ ስለመቆየትዋ ነው" ሲሉ ያብራራሉ። ስለዚህ በአንድ በተወሰነ የታሪክ ወቅት ገና ወደፊት እስራኤል ሁሉ ደህንነትን ይቀበላል ብሎ ማለት ከጠቅላላ አውደ ምንባቡ ጋር የማይሄድ ትርጉም ነው። የ1948ቷን ዘመናይት እስራኤል እያሰቡ "እስራኤል ሁሉ ይድናል" የሚለውን ትንቢታዊ የተስፋ ቃል ከጠቅላላ አውደ ምንባቡ ነጥሎ መረዳትም ቃሉ የማይለውን እንዲል "አስገድዶ" መተርጎም ይሆናል።


ግዛቸው ከበደ /ቄስ/


Friday, February 12, 2021

የአህዛብ ሙላት

የአህዛብ ሙላት


"ወንድሞች ሆይ፥ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ምሥጢር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ ድንዛዜ በእስራኤል በአንዳንድ በኩል ሆነባቸው፤" ሮሜ 11፥ 25


"የአህዛብ ሙላት" የሚሆነው፣ አህዛብ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ኪዳን ተካፋይ ለመሆን በወንጌል ካመኑት አይሁድ ጋር በክርስቶስ በኩል በታደለ ጸጋ እኩል በሆነ ስፍራና አቋቋም በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ሲያገኙ ነው። ይኸውም የሆነው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ በነበረው በዚያ የሽግግር ወቅት በአዲሱ ኪዳን ቤተክርስቲያን፣ እርሱም እግዚአብሔር በተከለውና ባጸደቀው በመልካሙ የወይራው ዛፍ ውስጥ በእምነት እንዲገቡ ሲደረግ ያኔ ነው። የመንግስት ወንጌል ደግሞ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎት መጀመር ጋር አስቀድሞ ለአይሁድ የተሰጣቸው ልዩ ዕድል እንደነበር ግልጽ ነው፤ "ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥"፣ ደግሞም "የእርሱ ወደሆነው መጣ" ተብሏልና።


ክርስቶስ መሲሁ የመጣው ለአይሁድ ነበር፣ ከእነርሱም መካከል ቅሬታዎች የነበሩት አመኑበት። እነርሱም ከአይሁድ ህዝብ መካከል በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ወቅት በተከናወነው በክርስቶስ የመጀመርያ በሥጋ መምጣት እና በኋላም በዳግመኛ የክብር ምጽአቱ መካከል በነበረው በሽግግሩ ወቅት መጀመሪያ ላይ የተመረጡ ሐዋርያት እና  ደቀመዛሙርት ናቸው። ከዚያም ወንጌል ወደሰማርያውያን (ቅይጥ ዘሮች ወደሆኑት) ተስፋፍቶ በመጨረሻም ለአህዛብ ሁሉ ተዳረሰ።


"በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል" (ማቴዎስ 13፥ 15) እንደተባለ፣ የማያምኑት አይሁድ በመሲሁ እና በመልዕክተኞቹ ላይ ካሳዩት ግትርነት እና ከተሞሉት እምቢተኝነት የተነሳ፣ እነርሱ ሊቀበሉት ያልወደዱት ይህ የአዲሱ ኪዳን ወንጌል ለአህዛብ ደረሰላቸው። "ሂድ፥ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁ" (ሐዋ 22፥ 21) ተብሏልና። የዚህም ምስጢር እግዚአብሔር የአይሁድን ውድቀት ለአህዛብ ብልጥግናን የሚያመጣበት መንገድ አድርጎ መጠቀሙ ነው። አህዛብም የነበራቸው እምነት አይሁድን በቅናት ለማነሳሳት የቻለ ሲሆን ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ (ቅሬታዎች) መዳን ሆኖላቸዋል።


"ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ። የእነርሱ መጣል ለዓለም መታረቅ ከሆነ ከሙታን ከሚመጣ ሕይወት በቀር መመለሳቸው ምን ይሆን?" (ሮሜ 11፥ 13-15)


በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በተከናወነው የክርስቶስ የመጀመርያ መምጣትና በ70 አ.ም ላይ በተፈጸመው ዳግመኛ ምጽአቱ መካከል በነበሩት 40 ያህል የሽግግር አመታት ወቅት፣ ማለትም ለአንድ ትውልድ ዘመን፣  አማኞች ክርስቶስ ባደረገው የቤዛነት ስራ የተዋጁ ሆነው ነበር፤ ዳሩ ግን መዳናቸው በ70 አ.ም እስከሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፖሮዥያው ድረስ ገና ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀና ያበቃለት ደግሞ አልነበረም። ድነት ፍጻሜውን አግኝቶ በክብር የሚሞላው ጌታ ተመልሶ ሲመጣ ብቻ እንደሆነ ቃሉ ያስተምራል፤ ጌታ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ የማንም ሰው ድነት ፍጹም አይሆንምና። ስለዚህም እነዚያ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አማኞች እውነተኛ አማኞች መሆናቸውን እና እግዚአብሔር ተክሎ ባጸደቀው የወይራ ዛፍ ውስጥ የመቆየት መብት እንዳላቸው ለማረጋገጥ፣ በሚያልፉበት የስደትና የመከራ ልምምድ ውስጥ እንኳ ሆነው እየቃተቱ እስከ ዳግመኛ ምጽአቱ ድረስ በታማኝነት ጸንተው መቆም ነበረባቸው።


"እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ። እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና። አንተ በፍጥረቱ የበረሀ ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም?" (ሮሜ 11፥ 22-24)


ስለዚህ እግዚአብሔር ያመኑትን አህዛብ ከነበሩበት የበረሀ ወይራ አምጥቶ ወደመልካሙ ወይራ ወደ መንግስቱ አፈለሳቸው። እንዲሁም ደግሞ፣ ምንም እንኳ ከመነሻው ባለማመናቸው ምክንያት ተቆርጠው የቀሩ ቢሆኑም እንኳ፣ በዚያን ዘመን የመረጣቸውን የአይሁድ ቅሬታዎች ኋላ ላይ ንስሃ የገቡና በክርስቶስ ያመኑ ስለሆኑ እነርሱንም ወደ መንግስቱ አፈለሳቸው። ይህ ሁሉ የተከናወነው ያኔ የአዲሱ ኪዳን የመንግስት ወንጌል እየታወጀ ቤተክርስቲያኑ ትታነጽ በነበረበት ወቅት ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን አይሁድና አህዛብ ነው።


ክርስቶስ ለሆነው ለእግዚአብሔር እስራኤል የተሰጠውን የአብርሃምን የተስፋ ቃል ይወርሱ ዘንድ፣ የመንግስቱንም ቃል ኪዳናዊ በረከት ይቀበሉ ዘንድ፣ እግዚአብሔር በተከለውና ባጸደቀው መልካሙ የወይራ ዛፍ ውስጥ ገብተው የተጣበቁት መንፈሳዊ እስራኤል የሆኑ አማኞች ብቻ ናቸው። እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ይፋ አድርጎ የመረቀውና የከፈተው ለሚያምኑ አይሁድና፣ ደግሞም ለዘላለም ሕይወት ለተዘጋጁ ለሚያምኑ አህዛብ ሁሉና ብቻ ነው። የአህዛብ ሙላት ይህ ነው፣ እርሱም በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ የተፈጸመና የተሟላ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አግኝቷል (ሮሜ 11፥ 25)።


ለእስራኤል የተገባው የተስፋ ቃል ከዘላለም በእግዚአብሔር የተጠበቀ ነበር፣ ነገር ግን ተስፋው የተጠበቀው ታማኞች ለሆኑ የአይሁድ አማኝ ቅሬታዎች እና ከአህዛብ ወገን አማኝ ለሆኑ ጭምር ማለትም "መንፈሳዊ እስራኤል" ለሆኑት ብቻ ነው። የአዲሱ ኪዳን የክርስቶስ መንግስት እግዚአብሔር በተከለውና ባጸደቀው መልካሙ የወይራ ዛፍ ውስጥ እንደገና እንዲገቡ በተደረጉ አማኝ አይሁድና እግዚአብሔር ከበረሃ አምጥቶ ባስገባቸው ከአህዛብ ወገን በሆኑ አማኞች የተዋቀረ ነበር። እነዚህም ደግሞ በክርስቶስ አንድ የሆኑ "ክርስቲያኖች" ተብለው የሚጠሩ ሁሉ ናቸው። ይህም የአዲሱ ኪዳን መንፈሳዊው የወንጌል መንግስት በሙላት ተመስርቶ የተገለጠው በ70 አ.ም በዳግመኛ ምጽአቱ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ በመላው የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ቀጥሎ ሳይቋረጥ እየተሰበከ፣ ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ ላይዘጋ በተከፈተው በር በክርስቶስ በኩል ወደ ተገለጠው መንግስቱ በእምነትና በንስሃ ይገቡ ዘንድ በዘላለማዊ ድምቀት ወደፊት በክብር ሲያበራ ይኖራል።


"በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።" (ሮሜ 10፥ 12-13)


ቸር ያሰንብታችሁ።

(gkr)




Wednesday, February 3, 2021

የሽግግሩ ወቅት

የሽግግሩ ወቅት


[ይህ ጥፈት ከዚህ ቀደም "የዘመኑ ፍጻሜ" በሚል ርዕስ ላቀረብኩት አጭር ሀተታ ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲሆን ታስቦ የቀረበ ክትባት ነው፤ ይነበብ ዘንድ ጋበዝኋችሁ። የቀደመውን ጽሁፍ ለማየት ፍላጎቱ ላላቸው እነሆ ሊንኩ፦

https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/3099516486943443/ ]


እጅግ የሚበዙ አማኞች የጥንት ቤተክርስቲያን ከኖረችበት አይነተኛ የጊዜ ምዕራፍ በተለየ ዘመን ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸውን አይረዱም፡፡ ከዚህም የተነሳ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን አማኞች የተነገረውን የትንቢት ቃል ሁሉ ለእነርሱም ደግሞ የተነገረ እንደሆነ በማሰብ በአብዛኛው በሚከተሉት ትርጉም ይሳሳታሉ። እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች ግን የኖሩት መጽሐፍ ቅዱስ “የመጨረሻ ቀናት” ብሎ በሚጠራው የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ ነበር - እነዚያም ቀናት የብሉይ ኪዳን የመጨረሻ ቀናት ነበሩ።  እነዚያ “የመጨረሻ ቀናት” የተጀመሩት ደግሞ ምናልባትም በጴንጤቆስጤ ዕለት ሲሆን ቀኖቹም በይፋ የተፈጸሙት ከአርባ አመታት በኋላ የአይሁድ ቤተ መቅደስ በተደመሰሰበት በ 70ው ዓ.ም የእስራኤል- ሮም ጦርነት ወቅት ነው። ይህ የአርባ ዓመት ጊዜ ፣ ይኸውም ​​በጴንጤቆስጤ ቀን ማለትም ቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን ከተቀበለችበት ዕለት አንስቶ፣ እልቂተ መቅሰፍቱ እስከተከናወነበት እስከ ጭፍጨፋው ቀን ድረስ፣ ይኸውም የአይሁድ ህዝብ በእሳት ጥምቀት ፍርድን እስከተቀበሉበት ቀን ድረስ ያለውን፣ ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን ሽግግር የሚደረግበት ወቅት ነበር ፡፡  በዚህ የሽግግር ወቅት አዲሱ ኪዳን በክርስቶስ መስዋዕታዊ ሞት ተመረቆ፣ በሐዋርያቱ እየተሰበከ ነበር፤ ዳሩ ግን ገና ተጠናቆ በፍጹምነት እና በሙላት ሊገለጥ የጌታን ዳግመኛ መመለስ ይጠባበቅ ደግሞ ነበር። ስለዚህም የሽግግሩ ጊዜ “ቀድሞውኑ ሆኗል ግን እስካሁን ድረስ ገና አላለቀም” በሚል ስሜት የሚታወቀው "The already but not yet" የተሰኘው ጊዜ ነበር። አሁን እኛ ግን የምንኖረው ከሽግግሩ ወቅት በብዙ ዘመን ርቀን መጽሐፍ ቅዱስ “የሚመጣው ዘመን” እያለ በሚጠራው፣ የአዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ነው።  


ይህ የሽግግር ወቅት ብለን የምንጠራው ክፍለ ጊዜ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በክርስቶስ የመጀመርያ መምጣት እና በዳግመኛ ምጽአቱ መካከል በነበረው ጊዜ አርባ አመታት ያህል የሚሸፍን ነው። ይህ ጊዜ እንደሚጀመር ወይም የሽግግሩ ወቅት ሊጀመር እንደሆነ አስቀድሞ አይነተኛ ወቅቱን በበለጠ ያመላከተው መጥምቁ ዮሐንስ "መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ" (ማቴዎስ 3፥ 2) እያለና እያጠመቀ ወደይሁዳ የመጣበት የአገልግሎቱ ወራት ነው።   ያም ወቅት ጌታ አገልግሎቱን በይፋ የጀመረበት በ30 አ.ም አካባቢ የሆነው መገለጡ ነው። መጥምቁ ዮሐንስ የሽግግሩ ወቅት በይፋ የሚጀመርበትን ዕለተ በአለ ሃምሳን እርሱም የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ወደፊት እያየ የተናገረለት አይነተኛ የጊዜ ምዕራፍ በይፋ የሚጠናቀቀው በ70 አ.ም ላይ በሚሆነው የጌታችን በፍርድ ዳግመኛ ምጽአት በፓሮዥያው፣ እርሱም የእሳት ጥምቀት ነው። 


የሽግግሩ ወቅት የተጠናቀቀው ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን ሊያስነሳና ሊወስድ ዳግመኛ ተመልሶ በመጣበት በ70 አ.ም ላይ ነው (1ኛ ተሰሎንቄ 4፥ 16-17)። የጌታ ሐዋርያትም ይህንን በማያሻማ ቃል ሲያስታውቁ "የጌታ መምጣት ቀርቧል" (ያዕቆብ 5፥ 8)፤ "ጌታ ቅርብ ነው" (ፊልጵስዩስ 4፥ 5)፤ "የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቧል" (1ጴጥሮስ 3፥ 22)፤ እንዲሁም "ዘመኑ ቀርቧል" (ራእይ 22፥ 10)፤ ወዘተ ይሉ ነበር።


ከሽግግሩ ወቅት አስቀድሞ በነበረው አሮጌ ዘመን ያ ሊሻር የቀረበው የብሉይ ኪዳኑ አይሁዳዊ የሙሴ ስርአት ገና ሙሉ በሙሉ በስራ ላይ ነበር። በ70 አ.ም ላይ ግን የኢየሩሳሌምን ከተማ እና ቤተመቅደሱን ፈጽሞ ባወደመበት በሽግግሩ ወቅት መጨረሻ ላይ መንፈሳዊ የሆነው የአዲሱ ኪዳን የወንጌል መንግስት ሙሉ በሙሉ ተገልጦ በመላው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ወደፊት ቀጥሎ በፍጹምነት ይሰራና ይሰለጥን ዘንድ መሰረተው።


በዚህ የሽግግር ወቅት የሁለቱ ኪዳናት ስርአቶች መሳ ለመሳ ሆነው አዲሱ አሮጌውን ሽሮ በሙላት እስኪተካው ድረስ ሁለቱም በስራ ላይ ነበሩ። አሮጌው በ70 አ.ም ላይ በእሳት ፍርድ ሊያልፍና ሊጠፋ ተቃርቦ ነበር። አዲሱም በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ተመርቆና ተጀምሮ በ70 አ.ም ላይ በፍጽምና እና በሙላት እስኪገለጥ ድረስ እየታነጸና እየተሰራ ነበር። ክርስቲያን የነበሩት የክርስቶስ ሐዋርያት ሁሉም ራሳቸው አይሁድ የነበሩ እና በአይሁድ መካከል በነበሩበት ዘመን ሁሉ የብሉይ ኪዳኑን ስርአተ ህግን ይጠብቁና ይለማመዱም ነበር።


ሐዋርያት ህግጋትን ይጠብቁና ይፈጽሙ የነበረው በጊዜው የምድሪቱ የእስራኤል ህግ ስለ ነበረ ነው እንጂ፣ ለደህንነታቸውና ለጽድቃቸው አስፈልጓቸው፣ ወይም የጽድቅና የኩነኔ ቅድመ-መስፈርት ሆኖላቸው እንዳልነበር ግልጽ ነው። ሆኖም ይህንንም ሲያደርጉ፣ በዚያ በአሮጌው ኪዳን ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ አይሁድ ምስክርነታቸው ተቀባይነቱ እንዲጨምር ከፈሪሳውያን በተሻለ ታማኝነት ያደርጉት ነበር። ምስክርነታቸው በአይሁድ ዘንድ ተደማጭ ይሆን ዘንድ ጽድቃቸው ከፈሪሳውያን ጽድቅ የበለጠ እንደሆነ ማረጋገጥና ማሳየት ነበረባቸው (ማቴዎስ 5፥ 19-20)።


የወንጌሉ ግልጽ መልእክት፣ ጽድቅ በመሲሁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ የሚታደል መሆኑ ነው። የሽግግሩ ወቅት መልእክትም አይሁድ ወይም አህዛብ የሆኑ አማኞች ሁሉ ይድናሉ የሚል ነው። ያለ ልዩነት ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ ያለው እምነት አንድ ነው (ኤፌሶን 4፥ 4-5)

(gkr)