Friday, January 3, 2025

ቅድስት ሥላሴ

ቅድስት ሥላሴ


 


እንደ መነሻ በተወሰኑ ምንባባት ርዕሰ ጉዳያችንን መመልከት እንጀምር። 


ማርቆስ 1፥ 9-11 ”በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። ወዲያውም ከውኃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና፦ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ።“


በዚህ የአዲስ ኪዳን ጥቅስ ውስጥ ሥላሴን በሙላት በተግባራቸው ላይ የሚያሳየንን አንቀጽ እናገኛለን። ተመልከቱ እግዚአብሔር ወልድ ሲጠመቅ፣ እግዚአብሔር አብ ከሰማይ ይናገር ነበር፣ መንፈስ ቅዱስም በዕርግብ አምሳል ይወርድ ነበር። ሦስቱንም የሥላሴ አካላት በሌሎች ጽሑፎች ውስጥም በአንድነት እናያቸዋለን፡-


ማቴ 28፥ 19 “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤”


2 ቆሮንቶስ 13፥ 4 “በድካም ተሰቅሎአልና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንደክማለንና፥ ነገር ግን ስለ እናንተ በሆነ በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን።”


መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው ክርስቲያናዊ ግንዛቤ ከመሠረቱ ሥላሴአዊ ግንዛቤ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የተገኘ፣ ክርስቶስን ማእከል ያደረገ እና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ መጽሓፍ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ከሁሉ የተሻለው ፍቺም ‘መጽሐፍ ቅዱስ አብ ስለ ልጁ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሰጠው ምስክርነት ነው’ የሚል ሲሆን፣ ይህም ሥላሴአዊ ያደርገዋል።


ሥላሴ፣ የጥንት ቤተክርስቲያን ከነበረችባቸው ከመጀመሪያዎቹ ምዕተ-አመታት ጀምሮ እግዚአብሔርን በተመለከተ እንደ ክርስቲያናዊ ፅንሰ-ሀሳብ ዋና እና ልዩ ገጽታ፣ የክርስትና እምነትም ማዕከላዊ ምስጢር እንደሆነ ተደርጎ የሚወሰድ እጅግ ወሳኝ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ይህም ጥልቅ የሆነውን የክርስትናን እውነት በወጉ ለማስቀመጥ እና ለማደራጀት የሌሎቹም ሁሉ የክርስትና አስተምህሮ ዘርፎች ሥርና መሰረት ሆኖ የሚያገለግል፣ ነገር ግን ርዕሰ ጉዳዩን በበቂ ሁኔታ ለመግለጽና ለማስረዳት በእጅጉ አስቸጋሪ የሆነ መሆኑ እናገኛለን።


እንደ ማቴዎስ 28፥ 19 እና 2ኛ ቆሮንቶስ 13፥ 14 ባሉት ምንባባት ርዕሰ ጉዳዩን በጉልህ የሚጠቁሙ ንግግሮች ያሉ ቢሆንም፣ ነገር ግን በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ፅንሰ አሳቡን እናገኛለን እንጂ፣ ስላሴ የተሰኘ እንዲህ ያለ ቃል የትም ቦታ በግልፅ አልተቀመጠም። በቤተክርስቲያን ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን መገለጥ የክርስቶስ ማህበር የሆነች ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ላይ ያላትን እምነትዋን በተገቢው መንገድ ለማብራራትና ለመተርጎም ሲያስፈልጋት ያኔ ትምህርቱ በአባቶች ተቀርጿል። ቅድስት ስላሴ አንድ አምላክ ነው። አንዱም አምላክ በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ በሶስት አካል ተገልጦ ለዘላለም ይኖራል። በምዕራቡ ዓለምም ትምህርቱን ለማብራራት ደረጃውን የጠበቀ የቃላት አገባብ ሲያስፈልግ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ጽንሰ አሳቡን እና ስያሜውን እቆራኝቶ (“God is una substantia, [one being or nature], et tres personae, [three "personae]") በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረውን ተርቱሊያንን በቀዳሚነት እናገኛለን።


ትምህርቱን እንደ ቤተክርስቲያን ይፋዊ አስተምህሮ ለማቋቋምና ለማጽናት ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎች የተወሰዱት ግን ከአሪያኒዝም ጋር በነበረው የአስተምህሮና የእምነት ተፋልሶ ግጭት ምክንያት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጠቅላላ የቤተክርስቲያን ጉባኤዎች ወቅት ነው (እነርሱም በ325 ዓ.ም በተካሄደው የኒቂያ ጉባኤና ኋላም በ381 ዓ.ም በተካሄደው የቁስጥንጥንያ ጉባኤ ናቸው)። እነዚህ ሁለቱም ጉባኤዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር ሳይሆን እውነተኛ አምላክ፣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፣ መንፈስ ቅዱስም ከእግዚአብሔር አብ እና ከእግዚአብሔር ወልድ ጋር አምልኮን የሚቀበል ፍፁም አምላክ መሆኑን፣ ይህም የሚታመነውና የሚመሰከረው አንዱን አምላክ ሳይከፋፍሉ እንደሆነ አረጋግጠዋል። በዚህም የእምነትና የአስተምህሮ መሠረት ላይ የተገነቡት በምስራቅ እና በምዕራብ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ተጨማሪ ማብራሪያዎችን አደራጅተዋል። ምናልባት በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የጥንት ቤተክርስቲያን ምን ያህል እንደተጋችና አስተምህሮታዊ ድንበሯን ለማስከበር እንዴት እንደተጋደለች በሰፊው ማንበብ ለሚወዱ ዊልያም ጂ ሩስች ያዘጋጁትን The Trinitarian Controversy የተሰኘውን ግሩም መጽሃፍ እንዲያነቡ እመክራለሁ። በዚህች አጭር ዝግጅት ግን ስላሴን በተመለከተ ቤተክርስቲያን በታሪኳ ያስተናገደቻቸውን ልዩ ልዩ ክርክሮች መዳሰስ ዋና አላሜዬ አይደለም። ይሁንና ግን በዋናነት የትምህርቱን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት በማሳየት ከታሪካዊው የቤተክርስትያን ጉባኤዎችና ከውሳኔዎቻቸው ትሩፋት በመጠኑ እየጨለፍሁ ለእምነት ቤተሰብ የሚመጥነውን ብቻ በገባኝ ልክ ለማመልከት እወዳለሁ።


በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በብዝሃ ቁጥር እንደሆነ አስተውላችኋልን? ተመልከቱ፡-


ዘፍጥረት 1፥ 1 “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።”


እዚህ ላይ እግዚአብሔር ተብሎ የተተረጎመው ቃል በእብራይስጡ “ኤሎሂም” ነው። ይህ የዕብራይስጥ ቃል በዘፍጥረት 1፥ 1 ላይ የተጠቀሰ የእግዚአብሔር መጠሪያ ሲሆን፣ ቃሉ በተለምዶ “አምላክ” ተብሎ ይተረጎማል። የቃሉ ተራ ስሜት ግን በብዝሃ አገባብ "አማልክት" እንደማለት ነው። ከአመታት በፊት በትምህርተ ክርስቶስ ላይ ያነበብኩትና ጸሓፊውን በስም የማላስታውሰው ጽሁፍ አይሁድ በሃይማኖታቸው አንድ አምላክን የሚያመልኩ (Monotheistic) ቢሆኑም፣ ነገር ግን ከአህዛባዊ የብዝሃ አማልክት (Polytheistic) ጽንሰ አሳብ ርቀው ለዘመናት ለራሳቸው ብቻ ሸሽገው የያዙትን የአንዱን አምላክ የብዝሃነት መገለጥ በተወሰነ ብርሃን ያውቁ እንደነበር ያትታል። እንግዲህ ብሉይ ኪዳን በዚህ ላይ “ኤሎሂም” ከሚለው የአምላክ ስም ጀምሮ አልፎ አልፎ እግዚአብሔር ስለራሱ “እኛ” እያለ መናገሩንና እንደ አብርሃም ካሉ ቅዱሳኑ ጋር በብዝሃነቱ ያደረጋቸውን መስተጋብሮች ስንመለከት ይህ ስለ አይሁድ የተነገረውን ጉዳይ በቀላሉ የምናየው አይሆንም። 


ይህ “እግዚአብሔር” የሚለው መጠሪያ በዕብራይስጡ “ኤሎሂም” ግሱ የ”ኤል” ብዙ ቁጥር ነው፤ ቃሉም "ሀይል፣ ብርታት፣ ስልጣን" የሚል ትርጉምን ይይዛል። “ኤሎሂም” ብዝሃ ነው፣ ግን የቋንቋ ሰዋሰዋዊ ሊቃውንት ቃሉን ሞርፎሎጂያዊ ብዝሃ ብለው ይጠሩታል። [ሞርፎሎጂካል ብዝሃነት በቋንቋ ዘይቤዎች ውስጥ የቃላትን መልክ በመቀየር፣ በተለይም በሥርዓተ-ሞርፎሎጂ ሂደት ውስጥ የ"ከአንድ በላይ" ጽንሰ-ሐሳብን የሚገለጹበትን መንገድ ያመለክታል።] በ"im" የሚጨርሱ የዕብራይስጥ ስያሜዎች ብዝሃ ናቸው። በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ግን በታናካህ ውስጥ ትርጉማቸው ነጠላ ይሆናል። ጉዳዩ ግን በብሉይ ኪዳንና በአይሁድ እምነት ላይ ኮምጨጭ ያለ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በእኔ እምነት የኢየሱስን ወይም የሥላሴን አምላክነት የሚክድ ሰው ግን ክህደቱ የዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻህፍትን ካለመረዳት የሚመጣ ነው ብዬ እወስደዋለሁ።


ምንም እንኳን ይህ “ሥላሴ” የተሰኘው ቃል በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን የቅዱሳት መጻሕፍት ገጾች በአንዳቸውም ውስጥ ፈጽሞ ባይገኝም፣ ትምህርቱ ግን በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ፥ በታናክም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚሰጥ ግልጽ ትምህርት ነው። "ሥላሴ" በሦስት የተለያዩ አካላት በህላዌነት የሚኖረውን የእግዚአብሔርን አንድነት ለመግለጽ የሚያገለግል አይነተኛ ቃል ነው፤ ይኸውም የመለኮትን አንድነት የሚገልጽ ቃል ነው። ሥሉስ ብዝሃ የሆኑ፣ በዘላለማዊ አንድነት አብረው ያሉ፣ አብረው ዘላለማዊ የሆኑ፣ አንድ አይነት እኩል ማንነት ያላቸው፣ እያንዳንዳቸውም በየራሳቸው “እኔ” ማለት የሚችሉ፣ የየራሳቸው አካላዊ ማንነት ያላቸው ሆነው በአካል የተለያዩ፣ በመለኮታዊ ማንነታቸው ግን አንድ የሆኑ ናቸው። ይህንን ማንነት አመክንዮ በሚተነትነው መረዳት አውቆ መጨረስ አይቻልም። ሆኖም ግን ሥላሴ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ራሱን የገለጠውን የአንዱን እውነተኛ አምላክ ማንነት ሙሉ በሙሉ በግልፅ ለመተረክ ይመቻት ዘንድ ትምህርቷን ስትቀርጽ ቤተክርስቲያን የፈጠረችው አይነተኛ ቃል ነው። የቃሉም ትርጉም ሦስትነት እንደማለት ሲሆን ሦስትነትም አንድነት ነው።


እንደ ክርስቲያን፣ እግዚአብሔር ተብሎ የሚታወቅ አንድ ዘላለማዊ ማንነት ያለና የሚኖር እንደሆነ ከእግዚአብሔር ቃል እናረጋግጣለን። በእግዚአብሔርም ቃል መሰረት ይህ አንድ ዘላለማዊ ማንነት ቅዱስ ስሉስ በሆኑ ዘላለማዊ አካላት ማለትም በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦ ይኖራል፣ ይሰራልም (ማቴዎስ 28፥ 19 እና 2ቆሮንቶስ 13፣ 14)። በአመክንዮ፣ የሰው አእምሮ ሊያስብ በሚችልበት አቅምም ይህ አንድ ማንነት በሶስት አካላት እንዴት ሊኖር እንደሚችል ሙሉ በሙሉ መረዳት ከቶ አይቻለንም። ሆኖም፣ እንደ ክርስቲያን፣ ይህ እውነት የማይለወጥ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል እውነት መሆኑን በእምነት አረጋግጠናል፤ ጠንቅቀን አውቀነዋል ለማለት ባንደፍርም እንኳን ከዘላለም ሥሉስ ሆኖ ያለና የሚኖረውን አንዱን እውነተኛ አምላክ እናመልካለን!


በዚህ መለኮታዊ፣ ወሰንና ዳርቻ በማይገኝለት ህላዌ ውስጥ፣ አብ፣ ቃል ወይም ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ የተባሉ ሦስት አካላት በአንድ መለኮታዊ ማንነት፣ በአንድ ኃይል እና በዘላለማዊነት አብረው አሉ ይኖራሉም። እያንዳንዳቸውም ያልተከፋፈለ ሙሉ መለኮታዊ ይዘት ያላቸው ናቸው፤ አብ በማንም አልተሰራም፥ አልተወለደም ወይም ከማንም አልተገኘም፤ ወልድ ከዘላለም ከአብ የተወለደ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ከዘላለም ከአብና ከወልድ የሚሰርጽ ነው። ቅድስት ስላሴ የማይወሰኑ ናቸው፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፣ ደግሞም አንድ አምላክ፣ በባህርይና በማንነት ፈጸሞ የማይከፋፈል፣ ነገር ግን በበርካታ ልዩ አንጻራዊ ተግባራት እና ግላዊ ግንኙነቶች ተለይተው፣ አብ የራሱ አካል ኖሮት፣ ወልድም የራሱ አካል ኖሮት፣ መንፈስ ቅዱስም የራሱ አካል ኖሮት በመለኮታዊ አንድነት የሚታወቁ ናቸው። ይህ ስለ ሥላሴ ያለን መጽሃፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ኅብረት ቋሚ መሠረት እና በእርሱ ላይ ለሚያርፈው እምነታችን ጽኑ መታመን ነው። (1 ዮሐንስ 5፥ 7፤ ማቴዎስ 28፥ 19፤ 2 ቆሮንቶስ 13፥ 14፤ ዘጸአት 3፥ 14፤ ዮሐንስ 14፥ 11፤ 1 ቆሮንቶስ 8፥ 6፤ ዮሐንስ 1፥ 14፣ 18፤ ዮሐንስ 15፥ 26፤ ገላትያ 4፥6 ይመለከቷል)።  


በመጽሓፈ ስምምነት የሉተራውያን የእምነት መግለጫ ገጽ 417 እንደተብራራው፣ ይህ የቅድስት ሥላሴ ምሥጢር እጅግ የላቀው ምስጢር ሲሆን (1ጢሞቴዎስ 3፥ 16)፣ እርሱም ብቸኛ መጽናናታችን፣ ሕይወትና ድነታችን ያረፈበት ምስጢር ነው፣ ይለዋል። እንደሚታወቀው ሥላሴ በክርስትና ውስጥ በዋናነት ከተያዙ ትምህርቶች መካከል አንዱ እና ልዩ አስተምህሮ ነው። ይህ የከርስትና ትምህርት ግን ገና ከሦስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ መምህራን ነን በሚሉ በተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥቃት ሲደርስበት የቆየ ትምህርት ነው። በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ አስርት ዓመታት ውስጥ የእስክንድርያው ካህን የነበረው አርዮስ ኑፋቄውን ማስተማር ጀመረ፤ እንዲህ ሲል፦ “ወልድ እውነተኛ የእግዚአብሄር ልጅ ከሆነ፣ እንግዲያውስ አባቱ ከእርሱ በፊት ነበረ ማለት ነው፤ ስለዚህ መለኮት የሆነው አብ መለኮት ከሆነው ወልድ በፊት አስቀድሞ የነበረ ሲሆን፤ ወልድ ደግሞ ከእርሱ አስቀውድሞ በነበረው በግዚአብሔር አብ የተፈጠረ ፍጡር ነው፤ ወልድ ከእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ ታላቍ እና የመጀመሪያው እንደሆነ እርሱም አምላክ እንደሆነና ነገር ግን አሁንም የተፈጠረ መሆኑን በድፍረትና በግልጽ ተናገረ። ስለዚህ፣ ቀደም ሲል እንዳልነበሩ እንደ ፍጥረታት ሁሉ ወልድም ከዘላለም ያልነበረበት ጊዜ ነበር” ሲል አስተማረ።


አርዮስም፣ የእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ ዘላለማዊ ነው ብሎ ከሚያምነውና ቃሉ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ነው የሚለውን የአርዮስን ትምህርት ውድቅ ካደረገው የእስክንድርያው ጳጳስ እስክንድር ጋር ተጋጨ። በአርዮስ አነጋገር “እርሱ (ወልድ) በዘላለም ውስጥ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ” ማለት ነው። አርዮሳውያን ከዚህ በመነሳት ክርስቶስ ከዓለም ፍጥረት በፊት የነበረ ቢሆንም ዳሩ ግን እርሱ ራሱ የአብ ፍጥረት ነው ሲሉ ሸምጥጠዋል።


እስክንድሮስም ይህ አስተምሀሮ ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ መሆኑን ስለተረዳ የአርዮስን ትምህርት በአደባባይ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ጥሪ እንዲወገድ አደረገ። ይህም ሂደት በታሪክ የመጀመርያው የሆነውን የቤተክርስቲያን ጉባኤ፣ እርሱም የኒቂያ ጉባኤ እንዲጠራ ምክንያት ሆነ። በጉባኤውም ከተመከረ በኋላ የአርዮስ ትምህርት በይፋ ተወግዟል። ክርክሩ ግን በጉባኤው ከግንቦት 20፣ 325 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 19፣ 325 ድረስ ለአንድ ወር የዘለቀ ነበር፤ የኒቂያ የሃይማኖት መግለጫ የመነሻ አሳብም ያኔ ተዘጋጀ፣ እርሱም የአርዮሳዊነትን አስተምህሮ ያወገዘ እና የሥላሴን ትምህርት ያቋቋመ መግለጫ ነበር። በመግለጫው ስላሴ ተኮር የሆነውን አንቀጽ ተመልከቱ፦


ሁሉን በሚችል ሰማይንና ምድርን፣ የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ አምናለሁ። እርሱ ብቻ የአብ ልጅ በሚሆን፣ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ በተወለደ፣ ከአምላክ በተገኘ አምላክ፣ ከብርሃን በተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ በተገኘ እውነተኛ አምላክ፣ በህልውናው ከአብ ጋር አንድ የሆነ፣ በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ፣ ሁሉ በእርሱ በሆነ፣ ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለ ደህንነታችንም ከሰማይ በወረደ፣ በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም ሥጋ ነስቶ ሰው በሆነ፣ …. ለመንግሥቱም ፍጻሜ በሌለው በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ። ከአብና ከወልድ ጋር በሚሰገድለትና በሚከበር፣ ከአብ በሚሠርጽ፣ በነቢያት በተናገረ፣ የሕይወት ጌታና ሰጪ በሆነ፣ በመንፈስ ቅዱስም አምናለሁ። …።


ምንም እንኳ ቤተክርስቲያን በዚህ የእምነት መግለጫ ቆማ የመጣባትን የኑፋቄ ተግዳሮት መመከት ቢቻላትም የአርዮስ ትምህርት ግን ወዲያውኑ ፍጻሜና ማብቂያ አላገኘም ነበር፤ እንዲያውም በአብያተ ክርስቲያናቱና በየገዳማቱ ትልቅ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጥሎ ነበር። በእርግጥም በቤተክርስቲያን ጉባኤ የተወገዘው የአሪዮስ ትምህርተ ክርስቶስ እየገነነ በሁሉ ዘንድ ይደመጥ ነበር። ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እስክንድር ሲሞት በእርሱ አገልግሎት አትናቴዎስ በፈንታው ተተካ። ቅዱስ አትናቴዎስም ቤተክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ የወንጌል ተጋዳዮች አንዱ እንደነበር ይታወሳል።


አስቀድሞ የተዘጋጀው የኒቂያ ጉባኤ አስተምህሮ በአትናቴዎስ እና በሌሎች አባቶች የቃላት ጥበብ እና አገላለጽ ተከሽኖ በድጋሚ በቁስጥንጥንያው ጉባኤም አጽንዖት ተሰጥቶታል። ስለዚህ “ክርስቶስ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ” የሚለው የአርዮስ አስተምህሮ እንደገና ውድቅ ሆነ፣ የክርስቲያን ቤተክርስቲያንም ክርስቶስ ያልነበረበት ጊዜ እንደሌለ በጽኑ በመግለጽ፤ እርሱ ከመጀመሪያው ነበር፣ አብ ያለውን (‘ለ’ ሲጠብቅ) እና የሆነውን አይነት መሰረታዊ የመለኮት ባህርይ ነበረው፣ ከዘላለምም ከአብ ተወለደ እንጂ እርሱ የሆነውን በማንም አልሆነም፣ በማንምም አልተፈጠረም ስትል የጉባኤውን ውሳኔ ደግፋ ለመቆም በቅታለች። እነዚያ ሁለቱም ታሪካዊ ጉባኤዎች ሆሞኡስየስ [homoousia] (መሰረታዊ ማንነቱ ወይም መሰረታዊ ይዘቱ") የተሰኘውን እውነታ መስርተው አቁመውታል። በሌላ አነጋገር፣ ኢየሱስ በመሰረታዊ ማንነቱ፣ በባህርዩ እና “በተፈጥሮው” ይዘቱ ከአብ ጋር አንድ ነው፣ ከአብ ጋር “ተመሳሳይ መሰረታዊ ማንነት” አለው። እርሱ አብን አይደለም፣ ነገር ግን ከአብ ጋር አንድ ነው፤ አብም በማንነቱ የሆነውና ያለው ሆኖ ወልድ በማንነቱ የሌለውና ያልሆነው ነገር የለም ሲሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክነት አውጀዋል።


ከላይ ለማለት እንደሞከርኩት በዚህ ጽሁፍ ታሪካዊውን አስተምህሮታዊ ክርክር መዳሰስ አላማዬ ባይሆንም፣ በቅዱስ አትናቴዎስ የኃይማኖት መግለጫ አንቀጽ 3-26 ስለ ቅድስት ስላሴ የሰፈረውን ግልጽና ግሩም ማብራሪያ እዚህ ላይ መጥቀስ ግን ተገቢ ነው፣ አንባቢዎችም በእያንዳንዱ አንቀጽ ስለ ስላሴ የተቀመጠውን በስነ መለኮት ንጽህና የዳበረውንና አስደናቂ በሆነ የቋንቋ ውበት የሰፈረውን መግለጫ በአንክሮ ሊመለከቱት ይገባቸዋል፦ 


በሦስትነቱ አንድነቱን፥ በአንድነቱም ሦስትነቱን አምነን አንድ አምላክን እናመልካለን። ይህም እውነተኛ የክርስትና ሃይማኖት ነው።

ይህንንም የምናደርገው አካላቱን ሳንደባልቅ መለኮታዊ ህልውናውንም ሳንከፍል ነው።

ምክንያቱም የአብ አካል ለብቻው የወልድ ለብቻው፥ የመንፈስ ቅዱስም ለብቻው ስለሆነ ነው።

ሆኖም የአብ፥ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ መለኮት አንድ ነው፥ ክብሩ ሥልጣኑም እኩል ሆኖ ይኖራል።

ወልድ በህልውናው እንደ አብ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ ነው።

አብ አልተፈጠረም፥ ወልድ አልተፈጠረም፥ መንፈስ ቅዱስም አልተፈጠረም።

አብ ወሰን የለውም፥ ወልድ ወሰን የለውም፥ መንፈስ ቅዱም ወሰን የለውም።

አብ ዘላለማዊ ነው፥ ወልድ ዘላለማዊ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም ዘላለማዊ ነው።

ቢሆነም ዘላለማዊ የሚሆን አንድ እንጂ ሦስት አይደሉም።

ያልተፈጠረና ወሰን የሌለው ሦስት እንዳልሆነ እንደዚሁም ያልተፈጠረና ወሰን የሌለው አንድ ነው።

እንዲሁም አብ ሁሉን የሚችል ነው፥ ወልድ ሁሉን የሚችል ነው፥ መንፈስ ቅዱስም ሁሉን የሚችል ነው።

ቢሆንም፥ ሁሉን የሚችል አንድ አንጂ ሦስት አይደሉም።

ስለዚህ አብ አምላክ ነው፥ ወልድ አምላክ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው።

ሆኖም አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም።

ስለዚህ አብ ጌታ ነው፥ ወልድ ጌታ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም ጌታ ነው።

ሆኖም አንድ ጌታ እንጂ ሦስት ጌቶች አይደሉም።

ምክንያቱም የክርስትና እምነት እውነተኛነት እያንዳንዱ አካል አምላክና ጌታ መሆኑን እንድናምን እንደሚያስገድደን ሁሉ የክርስትና ሃይማኖት ሦስት አማልክት ወይም ሦስት ጌቶች እንዳንል ይከለክለናል።

አብ በማንም አልተሠራም፥ አልተፈጠረም፥ አልተወለደምም።

ወልድ ከአብ ተወለደ እንጂ አልተሠራም አልተፈጠረምም።

መንፈስ ቅዱስ አልተሠራም፥ አልተፈጠረም፥ አልተወለደምም፥ ነገር ግን ከአብ የሚሠርጽ ነው።

ስለዚህ አብ አንድ ስለሆነ ሦስት አብ አይደለም፥ ወልድም አንድ አንጂ ሦስት ወልድ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስም አንድ እንጂ ሦስት አይደለም።

ከሦቱ አካላት አንዱ ከሌላው ቀዳሚነት ወይም ደኃሪነት የለውም፤ አንዱም ከሌላው የሚበልጥ ወይም የሚያንስ አይደለም።

ስለሆነም፥ ሦስቱ አካላት በእኩልነትና በዘላለማዊነት አንድ ናቸው። ከዚህ የተነሣም ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው ሦስቱ አካላት በአንድ መለኮት አንድ አምላክም በሦስት አካላት ይመለካል።


ሥላሴ ክርስትናን ልዩ ከምያደርጉ አስተምህሮዎች አንዱና ዋነኛው ነው። ቤተክርስቲያን በታሪኳ ከላይ በተጡቀሱት ጉባኤዎች እና የጉባኤዎቿ ትሩፋት በሆኑ የእምነት ሙግለጫዎቿ ሥላሴን በተመለከተ ለትውልድ ሁሉ የሚሆን ችንካር የሆነ አስተምህሮዋን ቀርጻልናለች። ማናችንም ብንሆን የህንን ታሪካዊ ሥነመለኮት ተቀብለን በዚህ አስተምህሮ ካልጸናን በቀር ስለ እግዚአብሔር አለን የምንለው፣ አካላቱን የሚደባልቅ፣ መለኮታዊ ህልውናውን የሚከፍል ማናቸውም መረዳት እና እምነት፣ ኑፋቄ ይሆናል። 


ናታን ቡሴኒትዝ የተባሉ ጸሓፊ አሪየስ ያስከተለውን ተፅእኖ በዚህ መልኩ ጠቅለል አድርገው አቅርበውታል፡-


“በጥንት ጊዜ የአርዮስ አስተምህሮዎች ለክርስትና ኦርቶዶክሲ ዋነኛና ቀዳሚ ስጋት ሆኖ ነበር፤ - ለዚህም ነው እንደ አሌክሳንደር ማካይ ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች አርዮስን 'ጥንታዊ መናፍቅ' ብለው የሰየሙት። ይህም የክርስቶስን አምላክነት የሚክደውን ማናቸውንም ትምህርት ቤተክርስቲያን ምን ያህል አደገኛ ትምህርት እንደሆነ መመልከቷን አስመልክቶ የተወሰነ ሀሳብን ይሰጠናል።”.

በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ አሪያኒዝም ጨርሶ ጠፋ፣ ነገር ግን በ16ኛው እና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሶሲኒያውያን የተባሉ ክፍሎች በዮሐንስ 14፥ 28 ላይ “ከእኔ አብ ይበልጣልና” የሚለውን ጥቅስ እንደ ማረጋገጫ እየተጠቀሙበት የክርስቶስን አምላክነት ክደው ማስተማር ጀመሩ። እነዚህ ሶሲኒያውያን የሥላሴን አስተምህሮ እና ሌሎች መሰረታዊ የክርስትና አስተምህሮዎችን ውድቅ ያደረጉ ቡድኖች ናቸው።


“ጥንታዊቷ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የተነሳባትን የአርዮሳዊነትን ተግዳሮት ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም እስከ ዛሬ ድረስ ግን የዚያን ኑፋቄ ዘር ተከትለው መንፈቅ የቀጠሉ የእምነት ቅርንጫፎች በዙርያው አሉ። እነዚህም ኑፋቄዎቻቸውን አሹልከው እያስገቡ በወንጌል የማናውቀውን ሌላ ባዕድ አምላክ ያስተዋውቃሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ራሳቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ሲሉ የሚጠሩት ናቸው። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህም ከህደታቸው ያው አርዮሳውያን ናቸው። በትምህርተ ክርስቶስ የተገለጠውን የወልድን ዘላለማዊነት በጽኑ እንደሚክዱ ሁሉ በትምህርታቸው ሥላሴንም ይክዳሉ። የእግዚአብሔርን ልጅ አምላክነትም አይቀበሉም። ሞርሞኖችም የእግዚአብሔርን ልጅ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ቢያዩትም ዘላለማዊነቱን ባለመቀበል አምላክነቱን ይክዳሉ። የሥላሴን መሰረታዊ የክርስትና ትምህርትም አይቀበሉም።” ሲሉ ሪያን ተርነር የተባሉ ጸሓፊ አስረግጠው ተናግረዋል።


እኔ እንደማስበውና ለራሴም ጥሩ ልማድ አድርጌ እንደምወስደው ከታሪካውያኑ የቤተክርስቲያን የእምነት መግለጫዎች ድንበር ውጪ “በእግዚአብሔር ቃል ጥናት ብቻ” የሥላሴን ትምህርት ለመዋጥ በእጅጉ አስቸጋሪ ሆኖ የሚተናነቅ በመሆኑ ማንም እንደዚያ እንዲያጠና አልመክርም። ሥላሴ ለሰው አእምሮ በቀላሉ ለመረዳት አስቸጋሪ በመሆኑ ብቻ ግን አስተምህሮው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ ሊመስለንም አይገባም፣ እንደ እርሱም ማሰብም ሆነ ከሃዲያን መሆን አይኖርብንም።  


ማቴዎስ እግዚአብሔርን በፍጹም አሳባችን መውደድ እንዳለብን ሲነግረን፡-


ማቴዎስ 22፥ 37 “ ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” ይላል።


አስተውሉ፣ ክርስትና ፍጹም ልብ፣ ፍጹም ነፍስ እና ፍጹም አሳብን የሚጠይቅ፣ ዲቮሽናችንን እና ዓእምሯችንን የሚፈልግ ምሁራዊ ነው። ክርስትና የሚያስቡ ሰዎች እምነት፣ የጠያቂ አማኞችም መንገድ ነው። እንደ ዕርግብ የዋሃን በሆንበት በስብከት ሞኝነት ያመንን እኛ “ነገሩ እንዲህ ይሆንን?” እያልን በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርቶች ውስጥ የሚያስቡ፣ እምነታቸውን የሚጠይቁ ብልሆች ልንሆን ደግሞ ይጠበቅብናል። እንደ ቤርያ ሰዎች እንድንሆንም ያስፈልጋል። በርግጥ ደግሞ ሥላሴ የምሁራዊ ነገር ብቻ አይደለም፤ ከፍ ሲል በተጠቀሰው የአትናቴዎስ የእምነት መግለጫ አንቀጽ 26 ላይ ምን እንደሚል ተመልከቱ፦ 


“ለመዳን የሚፈልግ ሁሉ ስለ ሥላሴ እንደዚህ ማሰብ የገባዋል” 


ይህ ታላቅ ምሥጢር ከድነታችን ጋር ያለው ግንኙነት መሰረታዊ ነው። በመጽሓፈ ስምምነት የሉተራውያን የእምነት መግለጫ ገጽ 521 እንደተብራራው፣ “መላው ሥላሴ እግዚአብሔር አብ፣ ወልድ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የአብን የዘላለም ምርጫ ሊሹበት ወደሚገባቸው የሕይወት መጽሓፍ ወደሆነው ክርስቶስ ሰዎችን ሁሉ ይመራሉ። ምክንያቱም ክርስቶስ ራሱ “በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” [ዮሓንስ 14፥ 6] እንዳለው እግዚአብሔር ሊያድናቸው የፈለጋቸውን በክርስቶስ በኩል ሊያድናቸው እንደሚፈቅድ ከዘላለም ወስኗል።” ሲል የህንንው እውነት ያስረግጣል። ልጆቹ ፈጽመው የእርሱ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡና ሙሉ ዋስትና እንዲኖራቸው እግዚአብሔር ይፈልጋል፣ በጥርጣሬና እርግጠኝነት በሌለው ፍርሃት ውስጥ እንድንኖርም ከቶ አይፈልግም። ስለዚህ፣ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል በዚህ ጉዳይ ማረጋገጫን እየሰጠ ሊኖረን ለተገባው ዋስትና አስተዋጽኦን ያበረክታል። እግዚአብሔር አብ ስለ እግዚአብሔር ወልድ ሥራ የተናገረውን ቃል የሚያረጋግጠው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው ምስክርነት ነው።


ቅዱሳት መጻሕፍትን ስንመረምር፣ ሥላሴን በተመለከተ እውነት የሆኑ ቢያንስ 4 ነገሮችን እናያለን።

አንደኛው፡ የሥላሴን መለኮትነት የምናይበት ነው። ይህም ጉዳይ ሥላሴን በመቀበል እና በመረዳት ረገድ ብዙዎች ከሚቸገሩበ ጉዳይ ጀርባ ያለ ዋነኛ ጥያቄ ነው። በዋናነትም የክርስቶስን እና የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት የሚመለከተው ጥያቄ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ አንድ መለኮታዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ማስተማሩ ግልጽ ነው። ለምሳሌ፦

ዘዳግም 32፥ 39 “አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም።”

ኢሳይያስ 43፥ 10 “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም።”


እግዚአብሔር አንድ ብቻ ነው ብሎ የሚያስተምረው ያው አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ መልሶ በዚያው አጽንዖት አብ እግዚአብሔር እንደሆነ ይነግረናል። ወልድንም እግዚአብሔር ነው ይለናል። መንፈስ ቅዱስንም ደግሞ እግዚአብሔር ነው ብሎ ያስተምረናል። ስለዚህ እነዚህ አካላት ያለምንም መደባለቅና መከፋፈል አንዱን እውነተኛ አምላክ መሆን አለባቸው።


እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው። እርሱ አንድ... እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። ስለአንድነቱ ምንም ጥያቄና ጥርጥር ሊኖር አይችልም። ክርስቲያን የሆነ አማኝ ይህንን እውነት እንደ ማንኛውም አይሁዳዊ አጽንዖት የሚሰጠው እምነት ነው።  


ዘዳግም6፥ 4 "አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው”


ኢሳይያስ 45፥ 5 “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር አምላክ የለም ይላል" 


የመለኮት አንድነት ለወንጌል ስብከት መሠረታዊ ጉዳይ ነው፤ ያለና የሚኖረው አምላክ አንድ ነው፣ እርሱም የሚፈልገውና የሚገባው ሙሉ የሆነ የሰው ልጆች ሁሉ ታማኝነት ነው። ሁሉ ሊታመኑበት የሚገባ አንዱ እርሱ ብቻ ነውና። ነገር ግን ይህ አንድ አምላክ (አስቀድሞ እንደ እስራኤል አምላክ፣ ከዚያም ሥጋ በለበሰው ጌታ፣ ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ) ራሱን በሦስት አካላት ማለትም በእነዚህ በየግላቸው ዘላለማዊ ህላዌነት ባላቸው ሦስቱ ሥላሴዎች ውስጥ ለዘላለም የሚኖር እንደሆነ በሚያሳይበት መንገድ ገለጧል። ስለዚህም ከሙታን የተነሣው ጌታ ኢየሱስ አህዛብ ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲጠመቁ በታላቁ ተልዕኮ አዟል፤ (ማቴ. 28፡19)።


ከዚህ በተቃራኒው ግን “ኢየሱስ ብቻ” የተሰኘ እንቅስቃሴ [Jesus Only Movement]፣ በመባል የሚታወቀው አንድ ብቻ ጰንጤቆስጣዊ እምነት፣ ከዚህ ያፈነገጠ አመለካከት አለው። ይህ እንቅስቃሴ በመለኮት ውስጥ ያለው አካል አንድ ብቻ ሲሆን እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብሎ ያምናል። በቤተ ከርስቲያን ውስጥ የኖረውንና በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚፈጸመውን የጥምቀት የሥላሴአዊ ቀመር ከመጠቀም ይልቅም እውነተኛው ጥምቀት “በኢየሱስ ስም” መከናወን እንዳለበት ተከታዮቹን ያስተምራል። በዚህ ኢየሱስ ብቻ በተሰኘ አስተምህሮ የሚታወቁ ተከታዮች የአብን ወይም የመንፈስ ቅዱስን መኖር ባይክዱም፣ እነዚህን ሚናዎች በመለኮት ውስጥ ካሉ የተለያዩ አካላት ይልቅ ኢየሱስ እንደተገለጠባቸው መገለጫዎቹ አድርገው ይተረጉሟቸዋል። ይህ አይነቱ እምነት ብዙ ጊዜ “ሞናርኪያኒዝም” አልያም “ሞዳሊዝም” ተብሎ ከሚታወቀው ሥነ-መለኮታዊ አቋም ጋር ይያያዛል፣ ይህም እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ወይም ቅርጾች ራሱን እንደገለጠ ይጠቁማል ባዮች ናቸው።


ሞናርኪያኒዝም በክርስትና ታሪክ ውስጥ ገና ከጠዋቱ ያቆጠቆጠ ኑፋቄአዊ የነገረ መለኮት ትምህርት ሲሆን፥ በአስተምህሮቱም የእግዚአብሔርን ሥሉስ መሆን እያደበዘዘ አንድነቱን (አንድ ብቻ መሆኑን) የሚያጎላ ነው፤ የሞናርኪያኒዝም ትምህርት ሦስት የተለያዩ፣ ማለትም አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የተባሉ አካላትን ያቀፈ አምላክነትን ከሚያሳየው ከትምህርተ ሥላሴ ጽንሰ አሳብ ጋር በእጅጉ ይቃረናል።ይህም ትምህርት የእግዚአብሔርን ማንነት እንዲሁም በእግዚአብሔር እና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማብራራት የሚሞክር በ2ኛውና በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የተጀመረ እሳቤ ነው። ሞናርኪያኒዝም ከሚያነሳቸው ቁልፍ አሳቦቹ መካከል፦ አንደኛው፣ የእግዚአብሔር አንድነት (አንድ ብቻ መሆን) ነው፡- ሞናርክያኒዝም እግዚአብሔር አንድ የማይከፋፈል ማንነት መሆኑን አጽኖት ይሰጣል። ይህ አተያይ ብዙውን ጊዜ የአብ “ንጉሣዊ አገዛዝ” ተብሎ ይገለጻል፣ ይህም በአንድ ብቸኛ ታላቅ አምላክ ላይ ያለውን እምነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው። ሁለተኛው፣ ክሪስቶሎጂያዊ አቋሙ ነው፡- ሞናርክያውያን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኝ ቢመለከቱትም ነገር ግን የሎጎስ (የቃሉን) ራሱን የቻለ ማነነት፣ ወይም ግላዊ ህልውናውን ይክዳሉ። ይልቁንም ለሞናርኪያኒዝም ኢየሱስ የተባለው ፍፁም አምላክ ቢሆንም ነገር ግን በማንነቱ ከእግዚአብሔር አብ የተለየ አካል አይደለም፣ ኢየሱስ ራሱ አብ ነው ብለው ያስተምራሉ። ሦስተኛው፣ በሞዳሊዝም እና በተለዋዋጭ ሞናርኪያኒዝም መካከል ያለው ተቃርኖ ነው፦ ሞናርክያኒዝም በሁለት ዋና ዋና ቅርንጫፎች ሊከፈል ይችላል። አንዱ፣ ከፍ ሲል የተጠቀሰው ሞዳሊዝም (ወይም ሞዳሊስት ሞናርኪያኒዝም) ሲሆን፡- ይህ አመለካከት እግዚአብሔር የሚገለጠው በሦስት ዓይነት ራሳቸውን በቻሉ አካላት ሳይሆን ይልቁንም በሦስት ዓይነት መንገዶች ወይም ቅርጾች (አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ) እየሆነ ነው የሚለው ነው፤ ሌላኛው ደግሞ ተለዋዋጭ ሞናርኪያኒዝም ነው፣ ይህኛው አመለካከት ደግሞ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር የተቀበለው፣ ወይም መለኮታዊ ሃይልን የተጎናጸፈ ሰው ብቻ መሆኑን ያሳያል፣ ትምህርቱም የክርስቶስ ሰብኣዊነት ላይ ብቻ አጽንዖት ይሰጣል። ሞናርክያኒዝም በጥንታዊው የክርስትና ሥነ-መለኮት፣ በተለይም በትምህርተ ሥላሴ ጽንሰ አሳብ ዙሪያ ተፈጥረዋል ላላቸው ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት ያሰበ አስተምህሮ ነው። ይህ እንቅስቃሴ አንድን አምላክን ብቻ ለማምላክ የነበረውን የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እምነት ኋላ ላይ ስለ ሥላሴ በተሰጡ ትርጓሜዎች እንደተጣሰ ስለመሰለው የጥንት የሚለውን አንድን አምላክ ብቻ የማመንና የማምለክ ትውፊት ጠብቆ ለማቆየት ይጥራል።


ሞዳሊዝምም፣ በሚከተለው አስተምህሮተ ክርስቶስ አንድ ብቻ ክሪስቶሎጂ [Oneness Christology] በመባልም ይታወቃል፤ በመለኮት ውስጥ ምንም የተለያዩ አካላት የሉም የሚል ሥነ-መለኮታዊ አስተምህሮ ነው። ከዚህ ይልቅ ሞዳሊዝም እግዚአብሔር ራሱን እንዴት እንደገለጠ ሲያስተምር በሦስት የተለያዩ “ሞዶች” ወይም “ጭምብሎች” ወይም ገጸባህርያት እንደ አብ፣ እንደ ወልድ፣ ወይም እንደ መንፈስ ቅዱስ እየተወነ ተገለጠ የሚል አጉል ትምህርት ነው። በዚህ አተያይ መሰረት፣ እግዚአብሔር በባህሪው አንድ ነው ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት በተለያየ መልክ ይሰራል። ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር እንደ አብ ሆኖ ታይቷል በአዲስ ኪዳን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ እንደ ወልድ ተገለጧል አሁን ደግሞ እንደ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ይሰራል፣ እንጂ ከመጀመሪያ አንስቶ አንድ ብቻውን፣ ነጠላውን ነው ይላሉ። ይህ አተያይ እግዚአብሔር በመለኮታዊ ባሕርዩ አንድ እና በሦስት አካል የተገለጠ ነው ከሚለው ክርስቲያናዊ ከሆነው የሥላሴ አስተምህሮታዊ ኦርቶዶክሲ ጋር በእጅጉ ይቃረናል።


በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሞዳሊዝም የታየው በተለይም ሳቤሊየስ ከተባለ ጳጳስ አስተምህሮ ጋር በተያያዘ ነው። ጳጳሱም ሆነ አስተምህሮው ዋና በሆኑ የጥንት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንደ መናፍቅ እና እንደ ኑፋቄ ይቆጠራሉ። ምክንያቱም የአብ፣ የወልድን እና የመንፈስ ቅዱስን አንድነት፣ አካላዊ ልዩነቱንም የሚያጎላውን የሥላሴን ትውፊታዊ ግንዛቤ የሚክድ በመሆኑ ነው። በኖረው የቤተክርስቲያን የሥላሴ አስተምህሮ እና ከፍ ሲል በተጠቀሰው የሞዳሊዝም አተያይ የሳቤሊየስ የመንፈስ ልጆቹ በሆኑ “ኢየሱስ ብቻ” በተሰኘው ጰንጤ ቆስጣዊ እንቅስቃሴ መካከል ያለው ክርክር የእግዚአብሔርን መሰረታዊ ባህርይ እና የኢየሱስን ማንነት በተመለከተ በክርስትና ውስጥ የሚነሱ ጉልህ የሆኑ ሥነ-መለኮታዊ ልዩነቶችን የሚዳስስ ነው። ታሪካዊው የቤተክርስቲያን ትምህርተ ሥላሴ በሶስት አካላት መካከል ያለውን በሦስትነቱ አንድነቱ በአንድነትም ሦስትነት የሚብራራበትን ምጡቅ አንድነት ያለመከፋፈልና ያለመደባለቅ ሲያጎላ፣ “ኢየሱስ ብቻ” የተሰኘው የጰንጤ ቆስጤ እንቅስቃሴ ግን ይህንን ምጡቃዊ አስተምህሮ ገሸሽ አድርጎ ለራሱ የሚመቸውን ቀለል ያለ ምንገድ በመፈለግ ኢየሱስን የእግዚአብሔርና የመንፈስ ቅዱስ ብቸኛ መገለጫ አድርጎ በነጠላው ይወስደዋል፣ በዚህም ኑፋቄው መለኮትን አንድ ነጠላ አካል ብቻ ያደርገዋል። “ኢየሱስ ብቻ” ለሚሉ የሳቤሊየስ ልጆች አምላክ መልኩንና ባህርዩን እየቀያየረ ተውኔት እንደሚጫወት አይነት ነው፤ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር (አብ) ሆኖ የተወነው ራሱ በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ (ወልድ) ሆኖ ተውኗል፣ አሁን ደግሞ በአማኞች ውስጥ ያው ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን ሆኖ እየተወነ ነው የሚል ሦስትነቱንና አንድነቱን ወደ ነጠላነት የቀየረ አስተምህሮ ነው። እንግዲህ እነዚህን ልዩነቶችና የኑፋቄውን ታሪካዊ መሰረት መረዳት በክርስቲያናዊ አንኳር አስተምህሮ እና እምነት ዙርያ ውይይት ለማድረግና የሳቱትን ለመመለስ ወሳኝ ነው። ቀጥሎ ያቀረብኳቸውን ነጥቦች ተመልከቱ፦


፩ኛ/ በቅዱሳት መጻሕፍት አብ አምላክ እንደሆነ በግልጽ የተነገረ ትምህርት ነው፡-


ዮሓንስ6፥ 37 “አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤”


መጽሓፍ ቅዱስ አምላክ ስለሆነው እና አብ ተብሎ ስለሚጠራው ማንነት በግልጽ ይነግረናል። በአንዱ አምላክ ሥላሴአዊ ማንነት ውስጥ አብ ተብሎ የሚታወቅ ቀዳሚ አካል አለ። 


ማቴዎስ 6፥ 6 “አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።”


ኤፌሶን 4፥ 6 “ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።”


አብም የቅድስት ሥላሴ የመጀመሪያው ተጠሪ ሲሆን፣ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ነው።


ቆላስያስ 1፥ 2 “….ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ይሁን።”


1ጴጥሮስ 1፥ 2 “…እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት…”


2ጴጥሮስ 1፥ 17 “¹⁷ ከገናናው ክብር። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤”


ሁሉንም ማለት በሚቻልበት አኳዃን በተለይ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክቶች ከተመለከታችሁ ለሚጽፍላቸው ሰዎች ሰላምታ ሲያቀርብ “በእግዚአብሔር አብ ስም ሰላም” በማለት መልእክቱን እንደሚጀምር ሁሉ መልእክቱን ሲያጠቃልልም ተሚዘጋው በሥላሴዎች በረከት ነው፤


2 ቆሮንቶስ 13፥ 14 “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።”


ምክንያቱም መባረክ የሚችል በሕያውነት ያለ አንድ ነውና፦


ኤፌሶን 4፥ 4 “አንድ መንፈስ …አንድ ጌታ…አንድ አምላክ ..አባት” ነው። 


ስለዚህ አብ ራሱ እግዚአብሔር አምላክ እንደሆነ እናውቃለን። 


፪ኛ/ ወልድ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም እግዚአብሔር አምላክ እንደሆነ የሚያስተምሩ በርካታ ጥቅሶችም አሉ።


ለምሳሌ፣ ነብዩ ኢሳይያስ ስለሚመጣው መሲሕ በተናገረበት በትንቢቱ ጌታ ኢየሱስን “ኃያል አምላክ” ብሎ ጠርቶታል።


ኢሳያስ 9፥ 6 “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።”


ተመልከቱ ስለሚወለደው ሕጻን በይፋ የተነገሩ፣ ማንነቱን የሚገልጹና የሚጠራባቸው ስያሜዎቹ አለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ማንም ያልተጠራባቸው ናቸው። መጽሓፍ ቅዱስ አምላክ ስለሆነው እና የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ ተብሎ ስለሚጠራው ማንነት በግልጽ ይነግረናል። በአንዱ አምላክ ሥላሴአዊ ማንነት ውስጥ ወልድ ተብሎ የሚታወቅ ሌላ ሁለተኛ አካል አለ። 


ማርቆስ 1፥ 1 “የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።”


ዮሓንስ 20፥ 31 “ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።”


እርሱም ስለህዝቡ ኃጢአት የፍጻሜ ማስተሰረያውን ሊያቀርብ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ከድንግል ማሪያም ሥጋን ነስቶ የመጣው መሲሁ ሲሆን፣ የህዝቡንም መዳን ፍጹም ያደርግ ዘንድ በዚያው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በ70 ዓ.ም ይጠባበቁት ለነበሩ ለቅዱሳኑ በዳግመኛ ምጻቱ ፓሮዥያ በክብርና በፍርድ የተመለሰው ነው።


እብራውያን 9፥ 28 “እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።”


ወልድ ተብሎ የሚጠራው እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው። እርሱም የቅድስት ስላሴ ሁለተኛ ተጠሪ ነው። ነገር ግን ደግሞ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ነው። እርሱ ስለ እኛ ልናየው እንዲቻለን በሥጋ የተገለጠ አምላክ ነው። እርሱ ለእኛና ስለ እኛ እውነተኛውን አምላክ የሚገልጥልን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ መገለጥ ነው፣ እርሱን ስናይ እግዚአብሔርን እናያለን።


ዮሓንስ 1፥ 1 እና 14 “¹ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።….¹⁴ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።”


ቆላስያስ1፥ 15 “እርሱም (ኢየሱስ) የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው።…ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው።”


እግዚአብሔር ራሱ ካልሆነ በቀር እግዚአብሔርን ሊገልጥልን የተቻለው የለም። አሁን እዚህ ላይ ከአዲሱ መደበኛ የመጽሓፍ ቅዱስ ትርጉም አንድ አስገራሚ ጥቅስ ላሳያችሁ፦


ዮሃንስ 1፥ 18 “ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ለጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።”


አዎ እርሱ (ልጁ) እግዚአሔር አምላክ ነው። የቶማስን የተጠራጣሪነት ታሪክ ታስታውሳላችሁን? ከሞት የተነሳውን ክርስቶስን ለመጀመሪያ ጊዜ በአይኖቹ አይቶ የተወጋውን ጉኑን በጣቶቹ በነካ ጊዜ የተናገረውን ቃል አታስታውሱም? እንዲህ ነበር ያለው:-


ዮሐንስ 20፥ 28 “ቶማስም፣ ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።”


ኢየሱስም ቶማስን መልሶ። “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤” አለው፣ ይህም በትክክል መልሰሃል እኔም ማን እንደሆንሁ አሁን በደንብ ገብቶሃል! ማለት ነው። ኢየሱስ ቶማስን አላረመወም።


ዕብራውያን 1፥ 8 “ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው።”


ተመልከቱ እዚህ ላይ እንደውም “አምላክ ሆይ፥” ብሎ ስለ ልጁ የሚናገር ራሱ እግዚአብሔር ነው። ጆን ስቶት Authentic Christianity በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 36 ላይ የኢየሱስን አምላክነት አስመልክቶ ጥያቄ አንስተው ሲመልሱ “ኢየሱስ የሚገባው አምልኮ ነው ወይስ አድናቆት ብቻ? በእውነት እርሱ አምላክ ከሆነ እንግዲያውስ አምልኳችን፣ በእርሱ ላይ መታመናችን እና እርሱን መታዘዛችን ይገባዋል። እርሱ አምላክ ካልሆነ ግን እንዲህ ያለውን አምልኮ ለእርሱ መስጠት ጣዖትን ማምለክ ይሆናል” ይላሉ። እንግዲህ ኢየሱስን አምላክ ብሎ በመጥራት ጉዳይ ቶማስንም እግዚአብሔርንም ተሳስተው ነበር ልንል እኛ ማነን?


፫ኛ/ መጽሓፍ ቅዱስ አምላክ ስለሆነው እና መንፈስ ቅዱስ ተብሎ ስለሚጠራው ማንነት በግልጽ ይነግረናል። በአንዱ አምላክ ማንነት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ተብሎ የሚታወቅ ሌላ ሦስተኛ አካል አለ። እርሱም የቅድስት ሥላሴ ሦስተኛ ተጠሪ ነው፤ ነገር ግን ደግሞ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል ነው። ጳራቅሊጦስ የተባለው እርሱ አጽናኝችንና ረዳታችን ነው። እርሱም ከአብ ዘንድ የሆነ ስለ ክርስቶስ የሚመሰክረው ነው (ዮሓንስ 15፥ 26)። መንፈስ ቅዱስ ሁል ጊዜ ሲጠቀስ “እርሱ” ተብሎ በህላዌ ማንነቱ ይታወቃል እንጂ እንደ አንድ ነገር ወይም ቁስ “ይህ” አይባልም። (ዮሓንስ 14፥ 16-17፣ 26፤ ሓዋርያት 5፥ 32 ተመልከቱ)። 


መንፈስ ቅዱስ ተብሎ የሚጠራው ማንነት ራሱ አምላክ ነው። መንፈስ ቅዱስም አምላክ እንደሆነ የሚያስተምሩ ጥቅሶችም ደግሞ አሉ። በተለይ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 5 ላይ ሐናንያ እና ሰጲራ ከንብረታቸው ሽያጭ ከፊሉን ሸሽገው ለቤተክርስቲያን የሰጡት ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ በተጋለጡና መንፈስ ቅዱስን በዋሹ ጊዜ ጴጥሮስ ምን ብሎ እንደተናገራቸው ቃሉን ታስታውሳላችሁን? እንዲህ ነበር ያላቸው:-


ሐዋርያት ሥራ 5፥ 3-4 “ጴጥሮስም፦ ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለ ምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው።”


ስለዚህ መንፈስ ቅዱስን መዋሸት እግዚአብሔርን ከመዋሸት ጋር አንድ ነው፣ ምንም ልዩነት የለውም። ምክንያቱም እርሱ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ አምላክ ነውና! ስለ እግዚአብሔር የተነገረ ነገር ስለመንፈስ ቅዱስም የተነገረ መሆኑን ስናይ መንፈስ ቅዱስ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን እናስተውላለን።


ሓዋርያት 3፥ 21 “እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥…”


2ጴጥሮስ 1፥ 21 “²¹ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”


መጽሓፍ ቅዱስ የአማኞች ሰውነት “የሕያው እግዚአብሔር ቤተመቅደስ” መሆኑን በሚናገርበት በዚያው ድምጸት መልሶ የአማኞች ሰውነት የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ መሆኑን ይናገራል (1ቆሮንቶስ 6፥ 16 እና 19)። በአማኞች ዘንድ እንዲኖር የተሰጠው እርሱ ራሱ እግዚአብሔር የሆነው መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ ደግሞም የክርስቶስ መንፈስ ነው፤ 

ሮሜ 8፥ 9 “እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም”። 


ሁለተኛው፣ የሥላሴን አንድነት የምናይበት ነው። በተለይ በአለም አፈጣጠር ውስጥ ይህንን አንድነት በጉልህ እናያለን፡-


ዘፍጥረት 1፥ 26 “እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ”


ልብ በሉ፣ ሰውን እኔ ልፍጠረው አላለም። ይልቁንም "እኛ እንፍጠር!" ነው ያለው። ስላሴ የሆነው አምላክ በሰው ልጅ መፈጠር ውስጥ በአንድነት ተሳትፎ ያደርጋል። ይህ ስለ መላእክት አለመናገሩን እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ተመልከቱ በዘፍጥረት 1፥ 1 ላይ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ አምላክ እንዳለ ያሳያል። ያኔም በቁጥር 2 ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በውሃው ላይ ሰፍፎ ነበር ይለናል። በቆላስይስ መልዕክት ደግሞ ክርስቶስ ሰማይንና ምድርን እንደፈጠረ ተነግሮናል!


ቆላስይስ 1፥ 16 “የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤”


ሥላሴዎች በመለኮታዊ አንድነት ተባብረው አብረው መሥራታቸው በቤተክርስቲያን ውስጥ ነገሮች እንዴት መሆንና መከናወን እንዳለባቸው የሚያሳይ ውብ ሥዕል ነው።


ዮሐንስ 17፥ 11 “ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።”

ዮሐንስ 17፥ 20-21 “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።”


አንድነት እግዚአብሔር ለህዝቡ የሚፈልገው የከበረ ነገር ነው። ባፕቲስቶች ቢሆኑ፣ ሉተራውያን፣ ወንጌላውያን ቢሆኑ፣ ጴንጤቆስጤዎችና ተሐድሶዎች - ሁሉም ወንጌል አማኞች የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን የመስበክ ዓላማ ይዘው በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት እና በሥራው ዙሪያ አንድ ሆነዋል። እንግዲህ ክርስቲያናዊ አንድነት አስቀድሞ በሥላሴ ውስጥ ያለውና የሚኖረው አንድነት ነጸብራቅ መሆን አለበት።


ሦስተኛው፣ የሥላሴ ልዩ ልዩ አሰራር የምናይበት ነው። የሥላሴ አካላት የሚሰሩት አብረው ነው፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ሁሉም አንድ ዓይነት ነገር ላያደርጉ ይችላሉ። ለምሳሌ ድነትን ተመልከቱ። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በድነት ስራ ውስጥ ያላቸው ሚና ልዩ ልዩ ነው፤ ይህ ልዩነት አንዱ ከሌላው ጋር በአሰራር ያለውን ልዩነት ወይም ተቃርኖ ማለት ሳይሆን ይልቁንም ልዩ ልዩ አሰራርን የሚያመለክት ነው። አስቀድሞ ከዘላለም በክርስቶስ የመረጠው ህዝቡ መዳንን እንዲያገኝ በሉዓላዊ ጥበብ፣ በመለኮታዊ ሀይል እና በፍቅር አብረው የሚሰሩ ሶስት የመለኮት አካላትን ተመልከቱ፤ አብ ከዘላለም ይመርጣል፣ ወልድ በቤዛኑቱ የአብን ፈቃድ ይፈጽማል፣ መንፈስ ቅዱስም ተሃድሶን በመስጠት የአብንና የወልድን ዓላማ ያስፈጽማል። ድነትን እውን ያደረጉ ሦስት የተለያዩ ሚናዎች፣ ግን ሁሉም ለአንድ ዓላማ ይሰራሉ።


የክርስቶስ አካል በሆነችው፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ ብዙ ልዩ ልዩነቶች አሉ፣ ነገር ግን ደግሞ አንድነትም አለ። ጳውሎስ ይህንን ለማስረዳት የሰውን አካል እና የአካል ብልቶችን አንስቶ በምሳሌ ይጠቀማል። በፊታችንም እየሳለ የሰው አካል በይዘቱ ከክርስቶስ አካል አሠራር ጋር ባለው ትይዩነት ትምህርቱን ያስተላልፍበታል:-


1ቆሮንቶስ 12፥ 12 “ አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤”


የሰው አካል እጅግ አስደናቂ የሆነ አይነተኛ የእግዚአብሔር ፍጥረት ነው። የአካሉ ተፈጥሮና እርስ በርሱ የተጋጠመበት ጅማት በሚያስደንቅ ሁኔታ ውስብስብ ነው፣ ነገር ግን ደግሞ ብልቶች አንዱ ከሌላው ጋር የተዋሃደ፣ ወደር የማይገኝለት መግባባት ትስስር እና መስተጋብር ያለው ነው። የሰው አካል ብልቶች ተስማምተው ሊሰሩ የማይችሉት በበሽታ ምክንያት ነው። በበሽታ ምክንያት አዕምሮው ካለበት ከማዘዣው ጭንቅላት ተገቢውን ምላሽ መስጠት የተሳነውን አካል ወይም የአካል ክፍል ማየት እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ነው።


1ቆሮንቶስ 12፥ 14-16 “አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና። እግር፦ እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፥ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም፦ እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን?”


እያንዳንዳችን በማህብረሰቡ ውስጥ ልዩ የሆነ ነገር ማበርከት እንዲቻለን እግዚአብሔር ሆን ብሎ ልዩ ልዩ አድርጎ ሰርቶናል። ሥላሴን በተመለከተም ያለው አሰራር በዚሁ ተመሳሳይ መንገድ ነው። እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ሕይወታችንን በተመለከተ በአይነቱ የተለየ እና በአሰራሩ ልዩ የሆነ ነገርን ያበረክታል። ለምሳሌ ሮሜ 8፥ 28 ላይ እግዚአብሔር ነገርን ሁሉ ለበጎ ይሰራል ይላል። ቁጥር 34 ላይም ኢየሱስ ስለ እኛ ይማልዳል ብሎ ይናገራል። በቁጥር 26 ላይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ይማልድልናል፣ እንዴት እንደምንጸልይም ይረዳናል ይላል። ይህ እንግዲህ የሚያሳየው በሕይወታችን ውስጥ ያለውን የሥላሴን ልዩ ልዩ አሰራር ነው።


እስካሁን የሥላሴን መለኮትነት፣ የሥላሴን አንድነት፣ በሥላሴ ውስጥ ያለውን ልዩ ልዩ አሰራር አይተናል።


አራተኛው ደግም በሥላሴ ውስጥ ያለውን መቀራረብ የምናይበት ነው።


ዮሐንስ 3፥ 35 “አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል።”


ዮሐንስ 14፥ 31 “ነገር ግን አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፥ አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።”


ይህ የሚነግረን አምላካችን በግል የሚታወቅና የቅርብ መሆኑን ነው። እርሱ ከራሱ ጋር መገናኘት የሚችልና የሚወድ በህብረት ውስጥ ያለ አምላክ ነው። እግዚአብሔር በእርሱ ውስጥ እንዳለው አይነት ያማረ ቅርርብ ከእኛም ጋር ተመሳሳዩ ህብረት እንዲኖረው መፈለጉ ደግም እጅግ የከበረ ነገር ነው።


አንዱ አምላክ ቅድስት ሥላሴ ነው፣ ቅድስት ሥላልሴም አንዱን አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም አንድ አምላክ እንዳለ፣ እርሱም በሦስት አካላት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ለዘላለም ያለና የሚኖር እንደሆነ ማስተማሩ ግልጽ ነው። ሦስት አካላት እንጂ ሦስት አማልክት የሉም። ያለው ሥሉስ የሆነ አንድ አምላክ ነው። ታዲያ ይህንን ለሰዎች እንዴት እንዲገባቸው እንዴት ልናብራራው ይቻሉናል? ደካማ የሆነ የሰው ልጅ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለውን ሁሉ ጠንቅቆ ሊያውቅ የሚችልበት ምንም መንገድ የሌለ መሆኑን በሚገባ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። ከፈለጋችሁ በአለም ሁሉ ወዳለ ቤተመጻህፍት ሂዱና የደረሳችሁበትን ያህል መጽሕፍትን ማንበብ፣ ስለ እግዚአብሔርም የሆነውን የተባለውን ነገር መቧጨር ትችላላችሁ። ያ ሁሉ እግዚአብሔርን ወደማወቅ አያደርስም። ጳውሎስ የተናገረውን ስሙ:-


ሮሜ 11፥ 34 “የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር?”


ኢሳይያስም በዚህ መንገድ አስቀምጦታል:-


ኢሳይያስ 55፥ 8-9 “አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።”


ዋናው ነገር ሥላሴን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ለሰው ልጅ እጅግ በጣም ከባድ ጉዳይ መሆኑ ነው። እንኳንም ከባድ፣ አይምሮንም የሚያልፍ ሆነ። ከመታወቅ የሚያልፈውን፣ መርምረው የማይደርሱበትን፣ ጠንቅቀንም አውቀን የምንጨርሰው አምላክ አናመልክም። ሥላሴ በእውነት ለእኛ በጣም ትልቅና አይምሮን የሚያልፍ ምጡቅ ርእሰ ጉዳይ ነው። እርሱን የምናስተያይበትና የምናመሳስልበት ማናቸውም ጉዳዮች በእውነቱ ፈጽመው ይፈርሳሉ።


የሥላሴን ትምህርት የምቀበለው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተገለጠ ትምህርት መሆኑን ስላየሁ ነው እንጂ እኔ ፈጽሜና ጠንቅቄ ልረዳው የምችለው ስለሆነ አይደለም። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እኛን የማይገባን ነገር ያልገባን ስለሆነ ብቻ የእግዚአብሔር ቃል እውነትነቱ ያበቃል ማለት አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል ብንረዳውም ባንረዳውም፣ ቢገባንም ባይገባንም እውነት ሆኖ የሚኖር ነው። እኛ ስለ ገባን የእግዚአብሔር ቃል እንደማይሆን ሁሉ እኛን ስላልገባን የእግዚአብሔር ቃል ከመሆን አይጎድልም።


በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሚስጥር የሆኑና እንቆቅናሽ የሆኑ ነገሮች መኖራቸውን በተመለከተ ፈጽሞ አያሳስበኝም፣ የተገለጠው እንጂ ምስጢር ሆኖ የተሰወረው አያስጨንቀኝም፤ እስከምሞትበት ቀን ድረስ እንኳ በቅጡ ሳልረዳቸው የሚቀሩ ነገሮች በመኖራቸው ላይ ምንም ስጋት አይገባኝም። እኔ በዚህ ጉዳይ ተጨንቄ አላውቅም። ልረዳቸው የተገቡ ጉዳዮችን በተመለከተ ጌታ በፊቴ ባዘጋጀው ገበታዬ ላይ የሚበቃኝንና የተትረፈረፈ ማእድ አግኝቻለሁ! አሁን ግን እርሱ በዘላለማዊነቱ፣ በማይመረመረው፣ ሊታወቅ በማይችለውና ከመታወቅ በሚያልፈው ማንነቱ ከዘላለም በራሱ የሆነውን ሁሉ ለመመርመር ከሚሆን ደካማ መፍጨርጨር ይልቅ እግዚአብሔር እኔ እንድኖረውና እንድታዘዘው የተገባኝን፣ እርሱ በሰጠው መገለጥ ያዘዘውን ስለማድረግ የበለጠ ያሳስበኛል። እስቲ በማርቆስ ወንጌል ስለ ኢየሱስ ማንነት የተሰጡ አራት ምስክሮች አንስተን እያንዳንዳቸው ምን እንዱሚመሰክሩ፣ ከዚህም በላይ ሌላ ምንም ማስረጃ እንደማያስፈልገን እንመልከት:-


1. ማርቆስ ኢየሱስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተናግሯል (ማር. 1፥ 1)።


 2. ነቢያትም ኢየሱስ ጌታ ነው ብለው መስክረዋል (ማር 1፥ 2-3)። 


 3. መጥምቁ ዮሐንስም ከእኔ በኋላ የሚመጣው ኢየሱስ ከእኔ ይልቅ የሚበረታ ነው ብሏል (ማር 1፥ 7-8)።


 4. እግዚአብሔር አብም ከሰማይ በሆነ ድምጹ ኢየሱስ የተወደደው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተናግሯል (ማር 1፥ 10-11)።


በመጨረሻም ለእምነትና ለሕይወት የተሰጠንን በቂ መገለጥ ስሙ:-


ዮሐንስ 20፥ 30-31 “ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።”

gkr



From Blogger iPhone client