Sunday, August 14, 2022

ኢየሱስና የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ተሳስተው ነበር ወይ?

ኢየሱስ እና የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ተሳስተው ነበር ወይ?

የፕሪቴሪዝም  አመለካከት ሊብራሎችና ተጠራጣሪ ከሃድያን በኢየሱስ እና በአዲስ ኪዳን ታማኝነት ላይ የሚሰነዝሩትን ትችት እና ተቃውሞ በመመከት ዋና የሆነውን የሙግታቸውን ውቅር ፈጽሞ ውድቅ ያደርጋል። ለምሳሌ ታዋቂው ሊበራል የነገረ መለኮት ምሁር የሆነው አልበርት ሽዌይዘር ፣ The Quest For The Historical Jesus በተሰኘው መጽሐፉ ክርስቶስ በባልንጀሮቹና በእርሱ ዘመን በነበሩ አብሮ አደጎቹ የህይወት ዘመን ውስጥ (ማለትም፣ “በዚህ ትውልድ”፣ "በዚያ ከእርሱ ጋር ከቆሙት መካከል አንዳንዶቹ ሳይሞቱ" በፊት) ተመልሶ እንደሚመጣ የተነበየ መሆኑን ለማሳየት በርካታ ቃላቱንና ንግግሮቹን ይጠቅሳል። ሽዌይዘር በደረሰበት ድምዳሜ ኢየሱስ ቃል በገባው መሰረት እመለሳለሁ ባለበት  ጊዜ መመለስ አልቻለም፣ ስለዚህ በትንቢቶቹ ተሳስቶ ነበር ብሎ ጉዳዩን ዘግቶታል። የዚህን ምሁር መስመር ተከትለው ቲኦሎጂ እናስተምራለን የሚሉ ሊብራሎች በመካከላችን እንዳሉ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? ቤተ ክርስቲያንስ ቲኦሎጂ እናስተምርልሻለን ከሚሉ እንዲህ ካሉ ሊብራሎቿ በጌታዋና በአዳኝዋ ታማኝነት ላይ የሚሰነዘረውን እንዲህ ያለ ትችትና ነቀፋ ለመመከት ምን ያህል በቃሉ ትምህርት ታጥቃ ተዘጋጅታለች? 

በርትራንድ ራስል የተባለ ከሃዲ ደግሞ፣ Why I am not a Christian በሚለው መጽሐፉ፣ ያንን ክርስቶስ ዳግመኛ ለመመለስ የሰጠውን ተስፋ ባለመፈጸሙ ከታማኝነቱ የወደቀ መሆኑን ለማሳየት፣ የራሱን የክርስቶስን ቃል ተጠቅሞ ጌታችንን ለማጣጣልና ክርስትናን ለመቃወም ሲያውለው ይታያል። ብዙ እንደዚህ ያሉ ተቺዎችና ተቃዋሚዎች (ሊበራሎች፣ ተጠራጣሪዎች፣ አምላክ የለሾች፣ አይሁዶች እና እስላሞች) ወደነዚያው የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ዝርዝር እያመለከቱ ጌታችን ኢየሱስን ሐሰተኛ ነቢይ እንደሆነ እንዲሁም መላው የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን በጽሁፎቻቸው ተሳስተው እንደነበሩ እንጂ ምንም አይነት ትክክለኛነት እንዳልነበራቸው፣ በመንፈስም ተመርተው እንዳልተናገሩ አረጋግጠናል ብለዋል።

በበርካታ ክርስቲያኖች የሃያኛው ክፍለ ዘመን ዕቅበተ እምነት ምሁር ተደርጎ የሚቆጠረው ሲ.ኤስ.ሉዊስም እጅግ ተነባቢ ከሆኑ ሥራዎቹ በአንዱ፦The World's Last Night: And Other Essay,፣ በተሰኘው መጽሐፉ፦ "የፈለጋችሁትን ማለት ትችላላችሁ፣ ጥንታውያን የሆኑቱ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ግን ያምኑት የነበረው አቡቀለምሲሳዊ እምነት ሃሰት መሆኑ ተረጋግጧል። ምክንያቱም፣ ዳግመኛ ምጽአቱ እንዲፈጸም ይጠባበቁ የነበሩት በገዛ ራሳቸው የምድር ላይ የህይወት ዘመን መሆኑን ከጠቅላላው የአዲስ ኪዳን ገጾች በግልጽ ማየት ይቻለናልና። እጅግ የከፋው ደግሞ ለዚህ መጠባበቅ አሳፋሪ የሆነ ምክንያት የነበራቸው መሆኑ ነው፤ መምህራቸውና ጌታቸው ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ የነገራቸው እንደዚያ እንዲጠባበቁ ነበርና። ያንን ቅዠት ያካፈላቸውና የፈጠረባቸውም እርሱው ነበር።  በብዙ ሌላ ቃልም "ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" ሲል ነገሯቸው ነበር፤ ዳሩ ግን ይህን ሲል ተሳስቶ ነበር። እንደውም እርሱ ከማንም በተሻለ ስለአለም መጨረሻ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው፤ ይህም ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ሁሉ እጅግ አሳፋሪው ጥቅስ ነው" ሲል ይጽፋል። (ገጽ 97-98.)

መጻኢያን በነገረ ፍጻሜ አስተምህሯቸው ይህንን ትችት ለመመከት የሚያቀርቡት፣ ኢየሱስ እስካሁን እንዳልመጣ ወይም ገና ወደፊት አልያም በቅርቡ እንደሚመጣ አዲስ ኪዳንን ጠቅሰው የሚሰነዝሩት መከላከያ መሰል ውዥንብር ሙከራ ለሊብራሎችና ለከሃዲያን ምሁራን በእጃቸው ዱላ እንደማቀበል ይቆጠራልንና የሚሉትን ካላወቁ ዝም ቢሉ ይመከራል። በታናሽዋ የንባብ ልምምዴ ከፍ ሲል የጠቀስኩትን ይህንን አሳፋሪ የሆነ የሊብራሎችና የከሃዲያን አስተያየትና ትችት በመመከት በጌታችን ፊት ላይ የተተፋውን "ምሁራዊ" ቅርሻት ለመጥረግ አቅም ያለው አስተምህሮ ግን ፕሪቴሪዝም ብቻ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

ከዚህ በታች ያሉት የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባት ዝርዝር እነዚህ ተቺዎችና ነቃፊዎች የክርስቶስንና የአዲስ ኪዳንን ተአማኒነት ለማጥቃት ሲሉ ጠቅሰው የሚጠቀሙባቸው ናቸው። የጠላትህን ትጥቅ አይነቱንና ብዛቱን ሳታውቅ እንዲሁ በሜዳ "ኢየሱስ ይመጣል" የሚል መፈክር እያሰማህ ጦርነቱን አታሸንፍም። ተመልከቱ በነዚህ ምንባባት አብዛኛዎቹ የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን በዝርዝር ተወክለዋል። ቃሉን እናምናለን፣ ለህይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚጠቅመው ምክር ሁሉ አለበት፣ በቤተክርስቲያንም ውስጥ አስተምህሮንና ልምምድን ሁሉ የሚገዛ ብቸኛ ሥልጣን ነው ብለን የምንሰብክና የምናስተምር ሁሉ ይህንን የእነርሱን የትችት ክብደት በቀላሉ ለመረዳት እንዲቻለን እነዚህን ጥቅሶች ስናነብ ከተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሆነን በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ታሪካዊ አውድ ውስጥ እየተመለከትን እንድናጠናቸው አሳስባለሁ፡-

ሀ. የዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅርብ እንደነበር የሚያሳዩ የአዲስ ኪዳን ምንባባት

♦ ማቴዎስ 10፥ 23 (ከመመለሱ በፊት ሐዋርያት እስራኤልን ዞረው አይጨርሱም።)

♦ ማቴዎስ 16፥ 27-28 (ከእርሱ ጋር ከነበሩት መካከል አንዳንዶች አስቀድመው ሳይሞቱ በሕይወት ኖረው ሲመጣ ያዩታል)

♦ ማቴዎስ 24፥ 33-34 (ትንቢቱ ፍጻሜውን የሚያገኘው፣ ጌታም የሚመጣው ትውልዱ ከማለቁ በፊት)

♦ ማቴዎስ 26፥ 64 (ያኔ የአይሁድ ገዢዎች የነበሩቱ እርሱ በደመና ሲመጣ እንዲያዩት በሕይወት መቆየት አለባቸው)

♦ ሮሜ 13፥ 11-12 (የሮሜ መልዕክት እየተጻፈ "አሁን" በተባለበት በዚያን ጊዜ ሰአቱ ደርሶና ቀርቦ ነበር)

♦ ሮሜ 16፥ 20 (ያኔ የሮሜ ክርስቲያኖች ገና እያሉ ሰይጣን ከእግራቸው በታች ፈጥኖ እንደሚቀጠቀጥ ይጠበቅ ነበር)

♦ 1ቆሮንቶስ 7፥ 26-31 (ያኔ 1ኛ ቆሮንቶስ እየተጻፈ ሳለ ጊዜው እያጠረ፣ አለሙም እያለፈ ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር)

♦ 1ቆሮንቶስ 10፥ 11 ("እኛ" በተባሉት በጳውሎስና በቆሮንቶስ ምዕመናን ላይ የዘመናት መጨረሻ ደርሶ ነበር)

♦ 2ተሰሎንቄ 2፥ 7 (የአመጽ ሚስጥር "አሁን" በተባለው ጊዜ ያኔ በስራ ላይ ነበር)

♦ ዕብራውያን 1፥ 2 ("በዚህ" ሲል የጠቀሰው ያ ጊዜ የመጨረሻው ዘመን ነበር)

♦ ዕብራውያን 9፥ 26 ( እነርሱ የኖሩት ጌታ ኃጢአትን ሊሽር በተገለጠበት የአለም / የዘመን ፍጻሜ ላይ ነበሩ)

♦ ዕብራውያን 10፥ 25 (ለጸሐፊውና ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ያኔ ቀኑ እጅግ እየቀረበ ነበር)

♦ ዕብራውያን 10፥ 37 ("ሊመጣ ያለው" እርሱ ሳይዘገይ ሊመጣ የቀረው "ጥቂት ጊዜ" ነበር)

♦ ያዕቆብ 5፥ 7-9 (ያኔ ያዕቆብ እየጻፈ የጌታ መምጫው ቀርቦ ሊፈርድ በደጅ ነበር) ፊልጵስዩስ 4፥ 5ን አስተያይ

♦ 1ጴጥሮስ 1፥ 20 (ያኔ ጴጥሮስ መልዕክቱን እየጻፈ ሳለ ጊዜው የመጨረሻው ዘመን ነበር)

♦ 1ጴጥሮስ 4፥ 7 (ያኔ ጴጥሮስ መልዕክቱን እየጻፈ ሳለ የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦ ነበር)

♦ 1ጴጥሮስ 4፥ 17 (ፍርድ የሚጀምርበት ጊዜ ጴጥሮስ መልዕክቱን እየጻፈ ሳለ ያኔ ደርሶ ነበር) ራዕይ 3፥ 10ን አስተያይ

♦ 1ዮሐንስ 2፥ 8፣ 17፣ 18 (ሐዋርያው ዮሐንስ ያኔ "አሁን" እያለ በጠቀሰው ጊዜ  ሰአቱ የመጨረሻ እንደሆነ ያውቅ ነበር)

♦ ይሁዳ 18፣19 (ይሁዳ መልዕክቱን እየጻፈ ሳለ ያኔ የመጨረሻው ዘመን ዘባቾች ነበሩ)

♦ ራዕይ 1፥1-3፤ 22፥ 6፣10 (ራእዩ እይተጻፈ ሳለ በራእዩ የተነገረው ነገር ሁሉ "ቶሎ" እና ፈጥኖ ሊሆን "በቅርብ" ነበር)

♦ ራዕይ 22፥ 7፣ 12፣ 20 (ዮሐንስና ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ክርስቶስ ቶሎ ይመጣል ሲሉ ተንብየዋል፣ ጠብቀዋልም) ራዕይ 2፥ 16 እና 3፥ 11ን አስተያይ

ለ. ስለ ዘመኑ መጨረሻና ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ በምሳሌ የቀረቡ ትምህርቶች፦

♦ ማቴዎስ 13፥ 24-43 የእንክርዳዱና የመከሩ ምሳሌ

♦ ማቴዎስ 13፥ 47-50 ወደ ባህር ተጥላ ከሁሉ አይነት የሰበሰበች መረብ ምሳሌ

♦ ማቴዎስ 21 33 ጀምሮ (ማርቆስ 12፥ 1 ጀምሮ፤ ሉቃስ 20፥ 9 ጀምሮ) የወይኑ አትክልት ምሳሌ

♦ማቴዎስ 22፥ 1ጀምሮ (ሉቃስ 14፥ 16 ጀምሮ) የሰርጉ ድግስ ምሳሌ

♦ ሉቃስ 19፥ 11-17 መንግስትን ይዞ ሊመለስ ወደሩቅ አገር የሄደ መኮንን ምሳሌ

♦ ማቴዎስ 25 የአስሩ ቆነጃጅትና የመክሊቱ ምሳሌ

♦ ሉቃስ 13፥ 6-9 የፍሬ ቢሷ በለስ ምሳሌ

ሐ. ሊመጣ ስላለ ጥፋትና ስለ ምጽአቱ የሚያመለክቱ ሌሎች ንግግሮች

♦ ማቴዎስ 3፥ 7-12 (ሉቃስ 3፥ 7-17፤ ሉቃስ 12፥ 49)

♦ ማቴዎስ 10፥ 17-34 (ሉቃስ 10፥ 3-21፤ ሉቃስ 12፥ 11-56)

♦ ማቴዎስ 23፥ 29-24፥ 44 (ሉቃስ 13፤ ሉቃስ 17፥ 20-37፤ ሉቃስ 21)

♦ ሉቃስ 11፥ 42-52፤ 12፥49፤ 13፥ 33-35፤ 19፥ 41-44፤ 23፥ 27-31

በመጨረሻም፣ ቤተክርስቲያንን የራሷን የእምነት መጽሐፍ ተጠቅመው በጥርጣሬና በክህደት በትር ለሚመቷት፣ ጌታዋንና መድሐኒቷን እያዋረዱ ለሚያጠለሹ፣ የምትመራበትንም የህይወት ቃል ተአማኒነት ውድቅ ለማድረግ በምሁራዊ ለዘብተኛነት ማብራርያ ለሚሰጡና የብዙዎችን እምነት ለሚገለብጡ ከሃዲያን፣ ሞልቶ ከፈሰሰው የመጻኢያን ጎራ ምሁራን ምን ምካቴ ይኖር ይሆን? ወዮ! አዝናለሁ፣ ምንም የለም። ይልቁኑ መጻኢነት የሚያቀርበው መከላከያ ራሱን መጻኢነትን ጎርፍ ሆኖ ጠርጎ የሚወስደውን ውሃ ይተፋል። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሆይ በዚህ የኪሳራ ነገረ ፍጻሜ ምንም ተስፋና ተገን የለሽም። እንዲህ ያለውን ተረትና ቡትቶ የሆነ ትምህርት እምቢ ማለትን እንዲሰጥሽ እጸልያለሁ። 

Gkr ታናሽ ባሪያው ነኝ። 

ፕሪቴሪዝም ይለመልማል!!


 


 

 


Sunday, August 7, 2022

ታሪካዊው የኢየሩሳሌም ቤ/መ ውድመት

የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውድመት

"እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።….እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።"(ማቴዎስ 24፥ 2፣ 34)

በእኔ አስተሳሰብ ይህን ከላይ የጠቀስኩት የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል ፍቺው እና ታሪካዊ ፍጻሜው በአማኙ መንፈሳዊ ሕይወትና መረዳት ውስጥ ቦታ ሊያገኝ የሚገባውን ያህል ትኩረት የተነፈገው ቃል ነው። ነገር ግን ዓይንን በብዙ ሊከፍቱ ከሚቻላቸው ትንቢቶች መካከል አንዱና ዋናው ደግሞ ነው። ይህንን ጥቅስ በአግባቡ መረዳት ከቻልን ግን ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ጠለቅ ያለ የመረዳትን መንገድ የሚከፍትልን ከመሆኑም በላይ፣ እግዚአብሔርን በማወቅ ከቃሉ ጋር ያለንን ግንኙነት ይወስናል። በታሪክ ውስጥ ፍጻሜው የተረጋገጠውን የዚህን ቤተመቅደስ ውድመት በአዲስ ኪዳን ትንቢቶች ትርጓሜ ውስጥ ያለውን ፋይዳ አለማወቅና ቸል ማለትን የመሰለ ድንቁርና /ignorance/ ያለ አይመስለኝም። 

ኢየሱስ ከላይ የተጠቀሰውን ይህንን ቃል በተናገረበት ጊዜ  ደቀ መዛሙርቱ በአድናቆት ይመለከቱትና ያሳዩት የነበረው ያ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆሞ የነበረው ቤተ መቅደስ በዚያን ዘመን በዓለም ላይ ከነበሩ ታላላቅና ድንቃ ድንቅ ቅርሶች አንዱና ዋናው ነበር። ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ “ትውልድ” ወቅት “ይወድቃሉ” ሲል የተናገራቸው ቤተመቅደሱ የታነጹባቸው ድንጋዮች በእጅጉ አስገራሚና እና በይዘታቸው ግዙፍ ነበሩ። የፍርስራሹ የአይን ምስክር የሆነው ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንደዘገበው፣ የአንዱ ድንጋይ ወርዱና ስፋቱ አርባ ስድስት ጫማ በአሥራ አምስት ጫማ በሃያ ሁለት ጫማ የሚለካ ሲሆን ክብደታቸውም እያንዳንዳቸው አራት መቶ አሥራ አምስት ቶን የሚመዝኑ ነበሩ። (ጆሴፈስ፣ 'የአይሁድ ጥንታዊ ነገሮች'፣ሲል በጻፈው መጽሐፍ 15፣ ምዕራፍ 11፣ አንቀጽ 3፣ መስመር ቁጥር 392 ላይ ይህንን ዘግቦታል) ይህ በእርግጥ በኢየሱስ የተነገረ ታላቅ የትንቢት ቃል ሲሆን፣ ደቀ መዛሙርቱም ሲሰሙት ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነባቸው ከባድ ቃል መሆኑን እናስተውላለን። ስለሆነም፣ “ይህ መቼ ይሆናል…” (ማቴዎስ 24፥ 3) ብለው ኢየሱስን ከመጠየቅ መከልከል አልቻሉም። ይህ ቤተ መቅደስ እንዴት እና መቼ ነው ወደ ፍርስራሽና ባድማነት የተቀየረው?

የናዝሬቱ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን በፈጸመበት ጊዜ (ማለትም 30ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ)፣ ያኔ ሮም የዓለም ልዕለ ኃያል መንግሥት ነበረች። ይሁዳ፣ በዚህ ጊዜ የምትመራው በሮማውያን ቅኝ ገዢዎች ነበር፤ ከገዢዎቿም የሚበዙት ስለ አይሁድ ሃይማኖት የነበራቸው እውቀት እምብዛም ሲሆን ወይም ከነጭራሹ ምንም አያውቁም ነበር፤ ይህም ሁኔታ  በአይሁዶች ላይ የማያቋርጥ ብስጭት እና ቁጭት አስከትሏል። በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥም ቀነናውያን በመባል የሚታወቀው ቡድን የሮማውያንን አገዛዝ ለማብቃት በዚህ ጊዜ ንቁ ተሳትፎ ያደርግ ነበር። ቀነናውያንም የቤተ መቅደሱን ካህናት ለንጉሠ ነገሥቱ እና ለመንግሥቱ በየጊዜው የሚገባውን ግብር እና ቀረጥ እንዲያቆሙ አግባብተዋቸውና አሳምነዋቸው ነበር፤ ይህም በመሠረቱ በሮም አገዛዝ  ላይ የተደረገ አመጽ ነበር።

ሮም በኢየሩሳሌም የተቀሰቀሰውን አመፅ በሰማች ጊዜ ዓመፁን ለማጥፋት በሴስቲየስ ጋሉስ ትእዛዝ የሚመራውን የሮማን ጦር በ66 ዓም ላከች። ኢየሩሳሌምን ዙሪያዋን ከከበቧት በኋላ የከተማይቱን በሮች መዝጋት ጀመሩ፣ ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ ከበባ በኋላ፣ ያለ ምንም አሳማኝ ምክንያት ጀነራል ሴስቲየስ ወታደሮቹን በኃይል ከያዙት ይዞታ አስወጥቶ አፈግፍጎ ሄደ። ያኔም አይሁዶች ሮማውያንን አሳደዱ፣ ብዙዎችንም ገድለው በየጦሩ ግንባርና በከተማይቱ ቅጥር ዙሪያ የተተዉ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ማረኩ። ይህ ሮማውያንን ያዋረደ ክስተት አይሁዶች ስለራሳቸው የማይሸነፉ የሆኑ ያህል የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጎ በአመጻቸው እንዲቀጥሉ የልብ ልብ እንዲሰጣቸው አድርጓል። በተጨማሪም ይህ ክስተት፣ ያኔ በቅርቡ ድንገት በእነርሱ ላይ ከሚመጣው የጌታ ቀን ጥፋት በፊት “… ሰላምና ደኅንነት…” አገኘን፣ የሚሉበትን ድባብ ለመፍጠር ረድቷል (በተጨማሪ 1 ተሰሎንቄ 5፥ 3ን ተመልከት።)

ሮም በአይሁዳውያን መሸነፏን የሚገልጸው ዜና ወደ ንጉሠ ነገሥቱ በደረሰ ጊዜ ሴስቲየስ ባደረገው ደካማ አፈጻጸም ኔሮ ተበሳጨ። በምላሹ የአይሁድን አመጽ ለመደምሰስ እና የሮምን ውርደት ለመበቀል እንዲሁም በአገዛዝ ክብሯ ላይ የደረሰውን የሞራል ጉዳት ለመበቀል እንደገና በ67 ዓ.ም ላይ ኔሮ አንጋፋውን ጄኔራል ቬስፓሲያንን ወደ ኢየሩሳሌም ላከው። ቬስፓሲያንም ወራሪውን ጦር እየመራ ይዞታውን በማስፋት ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ወደምትገኘው ወደ ገሊላ ገሰገሰ። የእስራኤልን ታላላቅ ከተሞቿንም በውጊያ አሸንፎ ምድሪቱን አንበረከከ። በሰሜን በኩል ካለው የገሊላ ዘመቻ በኋላ ወደ ደቡብ ዘምቶ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ሰፈረ፣ ነገር ግን በዘመቻው ላይ ሆኖ ለሌላ ማጥቃት እየተዘጋጀ ሳለ ስለ ኔሮ ሞት ወሬ በሰማ ጊዜ ጀነራል ቬስፓሲያን ኢየሩሳሌምን ለመያዝ የነበረውን እቅድ ትቶና ወታደሮቹን አስወጥቶ ወደ አገሩ ወደ ሮም በመመለስ ተተኪው ንጉሠ ነገሥት ሆነ። አሁንም አይሁድ በጦርነቱ ያሸነፉና ድል የቀናቸው መስሎ ታያቸው።

ከዚያም በኋላ ብዙም ሳይቆይ በሚያዝያ ወር 70 ዓ.ም. ከፋሲካ በአል በፊት የቬስፓሲያን ልጅ የሆነው ጀነራል ቲቶ በሰሜናዊ ዳርቻ ካሉት ጭፍሮቹ ጋር ጣምራ ጦር በመሆን የአይሁድን አመጽ ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም እና አመፁን ለመደምሰስ ገስግሶ ኢየሩሳሌም ደረሰ። ጦሩም በገሊላ በኩል አድርጎ ወደ ደቡብ በመዝመት ከተማዋን በቅርብ ርቀት ለማየትና ለመቆጣጠር በሚያስችሉት ሦስት የጦር ካምፖች ላይ ሰፈረ። መጀመሪያ ላይ አይሁዳውያን እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ለማሳመንና ከተማይቱን ከመፍረስ ጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ የማግባባት ጥረት ተደረገ፤ ይህ ግን አይሁድ አስቀድሞ በነበራቸው የተሳሳተ የአሸናፊነት ስሜት የተነሳ አሁንም እንደቀድሞው ድል የሚቀናቸው ስለ መሰላቸው በቀረበላቸው የሰላም ጥሪ ላይ እየተሳለቁ ጥረቱ ሳይሳካ ቀረ።

ቲቶ ግን አይሁዳውያን እርዳታ እንዳይቀርብላቸው አድርጎ የከተማዋን ደጆች ዘግቶ በማስጨነቅ የመጨረሻውን ከበባ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ማናቸውም ሰው ቢሆን ከከተማይቱ ሸሽቶ ለመውጣት ሙከራ እንዳያደረግ ተከልክሏል፣ የሞከሩትም በከተማው ውስጥ ባሉ የአይሁድ አንጃዎች ተገድለዋል። አልያም ከከተማ ሲወጡ በሮማውያን ተይዘው ሁሉም ለመቀጣጫ እንዲያያቸው በከተማይቱ  ቅጥር ላይ  ተሰቅለው ተሰቃይተው እንዲምቱ ተደርጓል። ኢየሱስ በሉቃስ 19፥ 43፣ 44 ላይ "ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።" ሲል እንደተናገረው የሮም ጦር ለከበባው እንዲመቸው በከተማይቱ ዙርያ የሚቆም ቅጥር ወይም ግንብ አደረጉ።

የቲቶ ወታደሮች በግንቦት 25 የኢየሩሳሌምን ሦስተኛውን (ውጨኛውን) ቅጥር ጥሰው በመግባት አዲሱን የከተማውን ክፍል ያዙ። በሰኔ ወር ከበባው ወደ ሁለተኛው ቅጥር አካባቢ ተስፋፍቶ አይሁድ ከተማዋን ከጠበቀው የመጨረሻው ግድግዳ ጀርባ አፈግፍገው ሸሹ። የአንቶኒያ ምሽግም ሐምሌ 22 ቀን በቲቶ ተወሰደ፤ ከዚያም ሮማውያን የቤተ መቅደሱን በሮች በእሳት አቃጠሉ። ከቲቶ ፍላጎት በተቃራኒው በጥቃቱ ወቅት አንድ ወታደር በመስኮቱ አሳልፎ ወደ አንዱ የቤተ መቅደሱ ክፍል ውስጥ የእሳት ፍንጣቂ ወርውሮ አስገባ፣ በመቀጠልም ሁለተኛው የእሳት ቃጠሎ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ተወረወረ፣ ይህም የመቅደሱን ውስጠኛ ክፍል በእሳት እንዲያያዝ አደረገ።

ፍላቪዬስ ጆሴፈስ ስለ አይሁድ ጦርነቶች በሚተርከው መጽሐፉ ይህን ጉዳይ ሲያብራራ፣ ሮማዊው ጀነራል ቲቶ ቤተ መቅደሱ ከጥፋት እንዲተርፍ ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር ይተርካል፡፡ ቲቶ ቤተ መቅደሱ እጅግ የሚያምር ሕንጻ ከመሆኑ የተነሳ እንዳይፈርስ ፍላጎት ነበረው፡፡ ለሮም መንግስት ክብር እንደ ሮማውያን የስኬት መገለጫ አድርጎ ሊጠብቀውም ተመኝቶት ነበር፡፡ ቤተ መቅደሱን በተመለከተ የእርሱ ትዕዛዝ አንዳች ጉዳት እንዳይደርስበትም ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ከቲቶ ወታደሮች አንዱ ከቤተ መቅደሱ መስኮቶች በአንዱ ወርውሮ ያስገባው የእሳት ድንጋይ የዚያን ቅዱስ ሥፍራ መሠረት በእሳት አያያዘው፡፡ ቲቶ ነገሩን በሰማ ጊዜ በታላቅ ድንጋጤ ተነስቶ … ወደ ቅዱሱ ቤት ሮጦ በመሄድ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም ሞክሮ ነበር፡፡ በከፍተኛ ድምጽ፣ እየጮኸ፣ ለወታደሮቹም በቀኝ እጁ ምልክት እየሰጠ እሳቱን እንዲያጠፉ ወታደራዊ የአለቃ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍም ነበር፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ እነዚያ የአለቃቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም በአግባቡ የሰለጠኑና ሥነ- ሥርዓት የተማሩ የሮማውያን ወታደሮች ልክ አውሬ የሆኑ ያህል እንደ እብድ ሰው ተለውጠው የቄሳርን ትዕዛዝ እንዳልሰሙ ያህል በመሆን አሁንም አሁንም እየጨመረ ከሚሄድ ታላቅ የበቀል መነሳሳት ጋር እሳቱን እየጨመሩ ያቀጣጥሉት ያዙ፡፡ 

ይሄ ታሪክ ባስብኩት ጊዜ ሁሉ ሲያስገርመኝ ይኖራል! ታላቁ ሮማዊ የጦር ጀኔራል እና በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራዊቱ ቤተ መቅደሱን ሊያድኑት ከቶ አልቻሉም፡፡ ለምን ይህ ሆነ ቢባል ምክንያቱም ከቲቶ የሚበልጠው፣ ከቄሳርም የሚበልጠው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ከመሆኑ ከዓርባ ዓመታት በፊት ቀደም ብሎ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” (ማቴ 24÷ 3) ሲል ተናግሮአልና ነው፡፡ እግዚአብሔር ተናግሮአል፣ ጀነራል ቲቶም ትዕዛዙን ይከተላል እንጂ ምንም ሊያደርግ ስለማይችል ያ ቤተ መቅደስ ተቃጥሏል፡፡ ይህ እንግዲህ ድል ለመንሳት የተመመው የሮም ሠራዊት ኃይልና ጀግንነት ሳይሆን፣ በሕዝቡ ላይ የሚፈርደው የእግዚአብሔር ኃይል ነበር፡፡ በጆሳቨስ የታሪክ ዘገባ የሚከተለውን እናነባለን፡- “ቲቶ ወደ ከተማይቱ በገባ ጊዜ (መስከረም 26 ቀን 70 ዓ.ም ማለት ነው) የከተማይቱን ጥንካሬ በተለይ ከፍ ብለው የተሰሩትን ቅጠሮቿን እየተመለከተ ይገረም ነበር፡፡ እነዚያ ግንቦች ምን ያህል ረጃጅሞችና ጠንካሮች መሆናቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ የእያንዳንዱንም ግንብ ውፍረት እያየ ´´በእርግጥ አይሁድን ከነዚህ ጠንካራ ምሽጎች አውጥቶ ያዋረዳቸው እግዚአብሔር በጦርነቱ ከእኛ ጋር ነበር እንጂ፣ ምን ዓይነት እጅ ወይስ ማሽን ይህንን ግንብ ሊያፈርሰው ይችል ነበር? “ እያለ ይደነቅ ነበር” ይለናል፡፡ በተጨማሪም ወደ 6,000 የሚጠጉ በዚያ ጠለላ ፈልገው  የነበሩ ሰዎች ያኔ በቃጠሎው ነደው አልቀዋል። በመስከረም 26፣ 70 ዓ.ም በከተማው ውስጥ የተቀጣጠለው የአይሁድ ተቃውሞ ሁሉ በኃይል ተቋረጠ። እንደዚህ አይነት ዝርዝር ጉዳዮችን ማንበብ ለሚፈልጉ፣ "የጆሴፈስ ስራዎች፣ የአይሁድ ጦርነት የተሰኘው ጥራዝ፣ መጽሐፍ 6 አስገራሚ ትረካን ያቀርባል።

እንደ ጆሴፈስ ገለጻ ከሆነ በከተማይቱ ላይ በተፈፀመው ጥቃት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን አይሁድ ሲገደሉ 97,000 ሰዎች ተማርከው ለባርነት በግዞት ተወስደዋል። ከእነርሱም መካከል አያሌዎቹ በአረማውያን የጣዖት ክብረ በአል ላይ፣ እንዲሁ ለነገስታቱና ለጦር አዛዦች ክብር በአሰቃቂ አገዳደል መስዋዕት ሆነው ታርደዋል። አይሁድ በገዛ አገራቹውና ተበትነው በነበሩበት የአህዛብ ምድር፣ በደረሱበት ሁሉ ተጨፍጭፈዋል። የቀሩትንም ባሪያዎችና ግዞተኞች አድርገው ሸጠዋቸዋል፡፡ ቅድስት ከተማቸው፣ ቤታቸውና ምድራቸው፣ የተቀደሰው መቅደሳቸው፣ እንዲሁም እንደ አይሁድ የነበራቸው የአኗኗር ዘይቤአቸው ሁሉ ሙሉ በሙሉ ፈጽሞ ተደምስሶ ጠፍቶአል፡፡ 

ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የቤተ መቅደሱ ድንጋዮች ፈራርሰው መሬት ላይ ተከምረው ነበር፤ ልክ ጆሴፈስ በዘገባው እንደገለጸውም "እስከመሠረቱ ድረስ በቈፈሩት መሬት ላይ የድንጋይ ቁልል ተከማችቶ ነበር፤ ስለዚህም በዚያ በኩል የሚያልፉ ሰዎች ከዚያ ቀደም በቦታው ላይ ሰው ይኖር እንደነበር እንኳ ማሰብ እስከማይችሉ ድረስ በስፍራው ምንም ነገር አልነበረም።" ቄሳርም ዛሬ በአይናችን ማየት ከምንችለው በስተቀር ሁሉም ነገር ድምድምና ድልድል እንዲሆን ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። የሮማውያን ጀግኖች ያወደሟት ምን አይነት ከተማ እንደነበረች ለዓለም ሁሉ ለመቀጣጫ ለማሳየት፣ ለወታደሮቹና ለሌሎች የጦር ክፍሎችም ካምፕ ለማዘጋጀት በሚል ከቅጥሩ የተወሰነው ክፍል ብቻ ቆሞ እንዲቀር ተደርጓል።.(የአይሁድ ጦርነት፣ መጽሐፍ 7፣ ምዕራፍ 1ን ተመልከት፤) የህ ታሪካዊ ዘገባ በራእይ 18 ቁጥር 15-18 “እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ፦ በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፥ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ፦ ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ።” ሲል ከተነገረው ትንቢታዊ የፍርድ ቃል ጋር ይስማማል።

የዚህን ታሪካዊ ክስተት አንድምታ ሙሉ ለሙሉ ለመግለጽ ከዚህ አጭር ጽሁፍ ሃሳብ በእጅጉ የላቀ ጥናትና ምርምር ይጠይቃል። በክርስቲያኑ አእምሮ ውስጥ “ብዙ ለማሰብ አቅም የሚሰጥ ምግብ” መሆን የሚችሉ ጥቂት ነገሮችን ብቻ በግርድፉ መዘርዘር ግን አስፈላጊ መስሎ ይሰማኛል።

  1. ጆሴፈስ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱ ማንም ሊያድናቸው እስከማይቻለው ድረስ ፈጽመው እንዲወድሙ የወሰነውና እንዲህ ላለ የከፋ ጥፋት አሳልፎ የሰጣቸው እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን በታሪካዊ ዘግባው ከትቦታል፡- "....ከተማይቱም ሆነ መላው ቤተ መቅደስ አሁን በአገሩ ሰዎች የሙታን በድን የተሞሉ አይደሉምን? ከተማዋንና ቤተ መቅደሱን በሮማውያን እጅ ያነጻ ዘንድ ይህን እሳት የሚያቀጣጥለው እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ በብክለታችሁ የሞላችኊትን ይህችን ከተማ ሊነቅላት ነው።" (የአይሁድ ጦርነቶች፣ መጽሐፍ 6፣ ምዕራፍ 2፣ መስመር 110።)

  2. ከላይ ያለው ታሪካዊ ክስተት በማቴዎስ 24፥ 2 እና 34 በኢየሱስ የተሰጠው የትንቢቱ ፍጻሜ ነው። "አንድ ትውልድ" በመጽሐፍ ቅዱሳዊው  ቀመር ግምቱ አርባ ዓመታት ያህል ጊዜን የሚያጠቃልል እንደሆነ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ይታወቃል። ያም “ትውልድ” ከ30 ዓ.ም እስከ 70 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚሸፍን መሆኑ ግልጽ ነው። ይህም በትንቢቱ እና በፍጻሜው መካከል ያለ እንደ የተወሰነ የጊዜ ክፍተት ሆኖ የሚታይ ነው።

  3. የ1ኛ ጴጥሮስ መልዕክት የተጻፈበትን ጊዜ በ 60 ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው ብለን መስማማት ከቻልን፣ እንግዲያውስ ያ የመጀመሪያው የሮማውያን የከበባ ሙከራ ከመድረሱ በፊት ጴጥሮስ "ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነስቶ ሊጀምር" መሆኑን በማስታወቁ ጉዳዩ ከአጋጣሚ በላይ መሆኑን ማየት እንችላለን (1ጴጥሮስ 4፥ 17)።

  4. ሐዋርያው ዮሐንስ በ1ኛ መልዕክቱ ምዕራፍ 2፥ 18 ላይ ሲጽፍ ሁለት ጊዜ እየደጋገመ "መጨረሻው ሰዓት ነው" ይላል። በርካቶች የኖሩበትን ጊዜ "የመጨረሻው ዘመን" ሲሉ የገለጹትን ዮሐንስ ግን መልዕክቱን እየጻፈ የነበረበትን ጊዜ "የመጨረሻው ሰዓት" በማለቱ መጨረሻው ምን ያህል እያጠረ እንደመጣ ያስገነዝባል።

  5. ያኔ ገና በ27 ዓ.ም ላይ መጥምቁ ዮሐንስም እንኳ በሉቃስ 3፥ 7 ላይ በገዛ ዘመኑ የኖሩትን የትውልዱን ሰዎች "ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?" ሲል ይጠይቃቸዋል።

  6. በዳንኤል አሥራ አንድ እና በሕዝቅኤል ሠላሳ ስምንት እና ሠላሳ - ዘጠኝ የተነገረለት ንጉሥ ወይም ከሰሜን ይነሳል የተባለው ወራሪ ኃይል ብዙዎች እንደሚመስላቸው ከሰሜን የሚመጣ የዘመናችን የሩሲያ ኃይል ወይም የኢራቅ ጦር አይደለም። ይልቁን ግን  በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ከሰሜን ተነስቶ በሶስቱም ግንባር ወደ ደቡብ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ለወረራ የተመመው የሮማውያን ሠራዊት ነበር።

እነዚህ የቅዱሳት መጻሕፍት የንባብ ክፍሎች በ70 ዓ.ም በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ላይ ከተፈጸሙት ነገሮች አንጻር ሲታዩ በጣም ግልጽ ስለሆኑ አጠቃላዩን የአዲስ ኪዳን ትንቢት በወጉ ተርጉሞ ከመረዳት አኳያ ቸል ሊባሉም ሆነ፣ ወደ ጎን ሊገፉ አይገባም፤ ትንቢቱንም ከዚህ ፍጻሜው ነጥሎ ለማብራራት መሞከር አያስፈልግም የሚለው እንደ ፕሪቴሪስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋማችን ነው! ሊሰሙን ለሚወዱ ሁሉ የምናስረዳውም የ70ውን ዓ.ም ታሪካዊ ፍጻሜ ጠቅሰን ነው።

(gkr)

 


 

 

 

 

 



Tuesday, August 2, 2022

ፖሮውዥያው ተፈጽሟል

ፓሮውዥያው ተፈጽሟል!

"ቶሎ" ማለት ምንም መቀባባት አያሻውም፣ ያው "ቶሎ" ማለት ነው።

መግቢያ፦

MELLO የተሰኘውን የግሪክ ቃል "ሊሆኑ ያሉ ነገሮች" በሚል መተርጎሙንና ይኸውም "እርግጠኛው አይቀሬ" እንደሆነ፣ በነገረ ፍጻሜ መረዳታችን ውስጥም ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ የዳሰስኩበትን ሰፋ ያለ ጽሁፍ ከዚህ ቀደም ማስነበቤን አስታውሳለሁ፤ ጽሁፉም በመጠኑ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር አነጋግሮን ነበር። ምናልባት ጽሁፉን የማየት አጋጣሚ ያላገኛችሁ በብሎገሬ ላይ ይገኛል፣ እነሆ ሊንኩ፦ 

http://gizachewkr.blogspot.com/2021/09/blog-post_26.html

አሁን ደግሞ እንደቀድሞው ሰፊ ባይሆንም፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሳነሳውና ስጥለው የቆየሁትን 'en tachei' የተሰኘውን የግሪክ ቃል "ቶሎ" በሚል እንደተተረጎመና በነገረ ፍጻሜ ምልከታችን ላይ ያለውን ጠቀሜታ በአጭሩ እንድንመለከት እወዳለሁ

"ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥" ራእይ 1፥ 1

"እርሱም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ።" ራእይ 22፥ 6

የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተናገረው ለሰዎች ትርጉም ባለው ቃል እንደነበር ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ጊዜ ጠቋሚ ምንባባቱም ቢሆኑ ሆነ ተብሎ እኛን ለማታለል እና ለማደናገር አልተጻፉም። እግዚአብሔር አምላክ ወደፊት ስለሚፈጸሙት ክንውኖች ለአማኞች እንዲነግራቸው መልአኩን ልኮ እንደ ነበር የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ለዚህ ማሳያ ነው። የራዕይ መጽሐፍ ማለት እንቆቅልሽ ወይም ድብቅ ሚስጥር ወይም ድፍን ቅል አይደለም፣ ይልቁንም  ሰዎች ሊከሰቱ ስላሉ ሁከቶች እና ብጥብጦች ያውቁ እና ይረዱ ዘንድ እንዲቻላቸው የተሰወሩ ነገሮችን የሚገልጥ 'መገለጥ' ነው። መጽሐፉን አክብሩት፣ ታዘዙትና ተጽናኑበት እንጂ ስታነቡት አትሸበሩ፤ እርሱን እንተረጉማለን እያሉ በምዕመናን ላይ ሽብርን ከሚነዙ መጻኢያን መምህራንና ሀሰተኛ ነብያት ራቁ፣ በማህበራቸውም አትደመሩ። የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ማስፈራርያና ያልተገባ ትርፍ መሰብሰቢያ ከሆነላቸው የቀበሮ ባህታውያን ጋር ምን ትሰራላችሁ?

የመጽሐፉ አውዳዊ ቅኝት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ጥንታዊው የሮም ዓለም ነው። መጽሐፉ በመሰረታዊነት ደግሞ ደብዳቤ ነው፣ ደብዳቤውም የተላከላቸው በኩረ ተደራሲያን ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በትንሿ እስያ (በዛሬዋ ቱርክ) ውስጥ በ62 ዓ.ም አካባቢ ለነበሩ ሰባት እውነተኛ፣ ታሪካዊና በስም ተለይተው ለሚታወቁ አብያተ ክርስቲያናት ነው እንጂ  ከ2000 ዓመታት በኋላ ግልጽ ባልሆነ አሻሚ ጊዜ ውስጥ ለሚኖሩ ለማይታወቁና ሚስጥር ለሆኑ ሰዎች የተነገረ ትንቢት ወይም ንግርት አይደለም። ይሄ መጽሐፉን ልንተረጉም ስንነሳ የሚገዛን አውዳዊ መርህ ነው።

የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ “በቅርቡ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች በመግለጥ በእምነታቸው ለማጽናትና ለማበረታታት ለእነዚያ እውነተኛና ታሪካዊ አማኞች፣ ከኢየሱስ የተላከ መልእክት ነው። በግሪኩ: 'en tachei' ማለት በፍጥነት (quickly) ማለት ነው፤ ቃሉ ጥቅም ላይ በዋለበት የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ሁሉ ከጊዜ አንጻር ቶሎ ሊፈጸሙ ያሉ ነገሮችን እና ፈጥነው በጥድፊያ እንዲከናወኑ የተመደቡ አስቸኳይ ጉዳዮችን "ጊዜ የለም" በሚል ስሜት በችኮላ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች ያመለክታል [the things which must soon take place and come to pass in quickness ] (ራእይ 1፥ 1፤  22፥ 6) 

በመጽሐፉ የመግቢያ ምዕራፍ እና በመዝጊያው ምዕራፍ ላይ የሚገኙት እነዚህ ሁለቱ ጥቅሶች (ራዕ 1፡1፣ 22፡6)፣ ራእዩ ያካተታቸውና በትንቢቱ መጽሐፍ የተነገሩት ክንውኖች ሁሉ በዚያው አንድ ትውልድ ውስጥ ማለትም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በቅርቡ እንደሚፈጸሙ የሚናገረውን መልእክት በአንድነት አዋቅረው እንደያዙ እንደ ሁለቱ የመጽሐፉ ቅንፍ መሆናቸውን አስተውሉ።

ኢየሱስም በትንቢቱ የእነዚህ ሁሉ ትንቢታዊ ክንውኖች መቃረቡን ለማጉላት " ዘመኑ ቀርቦአል….." [በግሪኩ: 'ho gar kairos engys' ማለትም ጊዜው ቅርብ ነው ማለት ነው] (ራእይ 1፥ 3) ሲል ተናግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ "ፓሮውዥያውን" (ዳግመኛ ምጽአቱን እንደማለት ነው) የሚያዩ አንዳንድ የተወሰኑ ሰዎችን "እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።" (ራእይ 1፥ 7) ሲል ግልጽ አድርጓል።

“የወጉት” የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው የአሮጌው ኪዳን እስራኤልን ሲሆን፣ ያም የመጨረሻው ዘመን ክፉ ትውልድ ነው፣ እነርሱም መሲሐቸውን የገደሉት ሰዎች ናቸው። በኃይልና በክብር ተመልሶ ሲመጣ ያዩት ዘንድ ያኔ እነርሱ በሕይወት መኖር አለባቸው።

ከዚያም ኢየሱስ፣ በመጽሐፉ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ፣ እነዚህ ሁሉ በመጽሐፉ ተካተው ያሉ ክንውኖች በቅርቡ እንደሚሆኑ የሚናገረውን ማስጠንቀቂያ ሦስት (3) ጊዜ ደጋግሞ "እነሆ በቶሎ እመጣለሁ" [በግሪኩ: 'tachy' ማለትም: quickly] (ራእይ 22፥ 7፣ 12፣ 20) ሲል ተናግሯል።

ሲጠቃለል፦
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ የሚያወራው “በቅርቡ” ቶሎ/ፈጥኖ፣ ስለሚሆኑ ነገሮች ነው፣ ይኸውም ማለት መጽሐፉ በመጀመሪያ የተጻፈላቸው ደቀ መዛሙርት በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ስለ ሚመጣው የፓሮውዥያ ምጽዓት ትንቢት ተናግሯል ማለት ነው፤ እንዲሁም እነዚያ የመጀመሪያው ከፍለዘመን የመሲሁ ገዳዮች እንኳን እርሱ በፍርድ ሲመለስ በሕይወት ሆነው ቁጣውን እንደሚያዩና እንደሚቀበሉ ይጠቁማል። እስካሁን ከመጽሐፍ ቅዱሴ ጋር ባለኝ ትውውቅ ይህንን ያፈጠጠ እውነታ ከሚክዱ በቀር እውነታውን በበቂ ሊያስተባብል የተቻለው ስነመለኮታዊ ምሁርም ሆነ ጥሁፍ አላየሁም።

መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት የሌለበት እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብላችሁ የምታምኑ ወንድሞችን ልጠይቅ፣ እስቲ መልሱልኝ፤ ኢየሱስ አሁንም እንኳ እንደተናገረው ገና ያልተመለሰ ከሆነ “የወጉትም እንኳ” ከደመና ጋር ሲመጣ ያዩታል ሲል የሚናገረው  ታዲያ  ለምንድን ነው? መከራና ግፍ ለሚቀበሉ ለነዚያ ለድሆቹ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አማኞች እና የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ተጽፎላቸው ለነበሩ በኩረ ተደራስያንስ ቢሆን እንዲህ ያለ የውሸት ተስፋ መስጠት እና 'ቶሎ' ይመጣል የሚሉ ባዶ መግለጫዎችን ማስተጋባትስ ምን የሚሉት ግራ ማጋባት ነው? እውነታውን ሳይክድ ይህንን ጥያቄዬን ሊመልስልኝ የሚቻለው ካለ በልብ ስፋትና በትህትና ላዳምጠው ዝግጁ ነኝ። የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ቤት ሁልጊዜ የተማሪ ቤት እንጂ የበቁ ምሩቃን የሉበትምና።

የሚሆነው ከሁለት አንዱ ነው፣ ይኸውም ወይ እነዚያ ቃላት ለዋናዎቹ በኩረ ተደራስያን ግልጽ የሆኑና የማያሻማ ትርጉም ያላቸው ናቸው (ማለትም "ቶሎ" ማለት ያው "በቶሎ" እንዲሁም " በቅርቡ" ማለት ያው "በቅርቡ"፣ "በፍጥነት" ማለትም ያው "በፍጥነት" ማለት ነው እንጂ ምንም ሰምና ወርቅ የላቸውም)፤ አልያም እነዚህ ቃላት ባዶና ምንም ትክክለኛ ትርጉም የሌላቸው ናቸው ከተባለ፣ እንግዲያውስ የትኞቹም ሰዎች ቢሆኑ ምንም ትርጉም ከማይሰጡ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክቶች ምንም መማር አይችሉም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን እያረማችሁና፣ "አይ 'ቶሎ' ሲል እኛ የሰው ልጆች ጊዜን በምንረዳበት አኳኋን ቶሎ ማለቱ ሳይሆን ሌላ ነገር ማለቱ ነው" እያላችሁ የምትደናበሩና የምታደናብሩ መምህራን ልምከራችሁ፤ በመጀመርያ ቁጭ በሉና ቃሉን እንደተጻፈው ማመንና ማጥናት ጀምሩ፣ ከዚያ በኋላ ታስተምሩናላችሁ። 

ተመልከቱ፣ የእግዚአብሔር ቁጣ ልክ ኢየሱስ የሰው ልጅ ተመልሶ በፍርድ እንደሚመጣ እንደተነበየው ሁሉ በመጨረሻው ክፉ የአሮጌው ኪዳን የእስራኤል ትውልድ ላይ፣ ያኔ በ70 ዓ.ም ላይ እንደወረደባቸው ታሪክ ዘግቦታል።

ፍላቪየስ ጆሴፈስ የተባለው የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አይሁዳዊ የታሪክ ምሁር፣ በኢየሩሳሌም እና በሌሎች የይሁዳ ከተሞች ያሉ ሰዎች ያኔ በ70 ዓ.ም. ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በከበቧት ወቅት የመላእክትን ሠራዊት “በደመና ላይ ሆነው ሲመጡ” ያዩበትን አስደናቂ ራእይ እንዲህ ዘግቦታል፦

….ከዚያ ከበዓሉ ጥቂት ቀናት በኋላ፣’… በ21ኛው በአርጤምስየስ [ጂያር] ቀን… “አንድ አስደናቂ እና ሁሉንም ያስገረመ ክስተት ታየ። ይህ ክስተት ታሪኩን ባዩት በነዚያ ሰዎች ህይወትና የእለት ተለት ኑሮ ውስጥ ምንም ተጽዕኖ ባይኖረውና፣ ከዚያም በኋላ ተከትለው የተፈጸሙ ድርጊቶች እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች የሚገባቸው አይነት ትላልቅ ተፈጥሮ ያላቸው ክስተቶች ባይሆኑ ኖሮ፣ እኔ ራሴ ታሪኩ ተረት ይመስላል ብዬ ባሰብሁና በተውኩት ነበር፤ የታየውና የሆነው ግን ይሄ ነው፣ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ሠረገሎችና በላያቸው ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡ የታጠቁ የሰራዊት ጭፍሮች በደመና መካከል ወዲህና ወዲያ እየተሯሯጡ ከተማይቱን ሲከብቧት ታዩአቸው። ከዚህም በላይ በዓለሃምሳ ብለን በምንጠራው በዚያ የበዓል ቀን ካህናቱ በሌሊት እንደ ልማዳቸው ወደ ውስጠኛው የቤተ መቅደሱ ክፍል ገብተው የዘወትሩን አገልግሎታቸውን እይፈጸሙ ሳለ፣ በመጀመሪያ ለራሳቸው የሚታወቅ መሸበርና ፍርሃት ይሰማቸው እንደነበሩ ሲገልጡ፣ በታላቅ ድንጋጤም ውስጥ ሆነው እየተንቀጠቀጡ የሰሙት ታላቅ ድምፅ "ኑ ከዚህ በኋላ ለቅቀን ከዚህ እንሂድ” የሚል እንደ ብዙ ሕዝብ ያለ ድምፅ ሰምተዋል። (Wars, 6-5-3, አንቀጽ 297-299)

ሮማዊው የታሪክ ጸሐፊ ቆርኔሌዎስ ታሲተስም ጭምር፣ እነዚህን አስገራሚ ድርጊቶች በኢየሩሳሌም መከሰታቸውን መዝግቧል (Histories, መጽሐፍ 5, ቁጥር. 13)።

መልዕክቴ፦ 

ምንም ዝንፍ ሳይል፣ ልክ ኢየሱስ እንደተነበየው፣ እነዚያ መሲሓቸውን “የወጉት" እንኳ ሳይቀሩ፣ ያኔ በ70 ዓ.ም ላይ በኃይል እና በታላቅ ክብር ሲመጣ የተገለጠውን የእርሱን ፓሮውዥያዊ ትዕይንት በሕይወት ቆይተው ተመልክተዋል። ንስሃ ግቡ፣ ይህንን እውነታ ተቀበሉ። በስነመለኮታዊ መተጣጠፍ ይህንን እውነታ ለማስተባበል መሞከር ግን በእግዚአብሔር ቃል ታማኝነት ላይ የሚፈጸም የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ክህደትና ግልሙትና ይሆናል።

ለተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራርያ ፈላጊዎች በብሎገሬ፣ በፌስ ቡክ ገጼ እና በphilologus66 የፌስ ቡክ ገጽ ያጋራሁዋቸውን ጥሁፎቼን ጉብኙ።
gkr