ቅንጫቢ፦
በተስፋ እና በእምነት እየናፈቁ በታላቅ መቃተት ሲጠባበቁት ለነበሩ ለቅዱሳኑ ብድራታቸው "ሰማያዊ ወዘላለማዊ" የሆነችው ሁሉን የምትገዛ መንግስቱ ናት፤ እርስዋም በንስሐና በዳግም ልደት የሚገባባትና ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ለነበረው ትውልድ "ቀርባለች" ተብላ የተሰበከችው ናት። ለእነርሱም "አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ" ሲል በመንግስቱ የተስፋ ቃል ያበረታቸውም ያጽናናቸውም ነበር። ይህች በሐዋርያቱ የተሰበከችና በናፍቆት የተጠበቀች መንግስት ጠባይዋም መንፈሳዊት የሆነች፣ ምድር ላይ ባለና ገናም ወደፊት በሚኖር ማናቸውም አካላዊና ተዳሳሽ በሆነ ነገር የማትለካና የማትተረጎም "ክብርት ወንጽህት" ናት።
ቅዱሳን የእምነት ቤተሰቦች ይናፍቁትና ይጠባበቁት የነበረውን ብድራት ተፈጥሮውን እዚህ ምድር ላይ ካለ ከማነኛቸውም ነገር ጋር እናስተያየውና እናነጻጽረው ዘንድ የሚመጥነው ምንም ነገር የለም። "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁን ዘመን ስቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ" እንደተባለ እንደ አልማዝ የሚብለጨለጭ ክብር ያላትን መንግስት ይወርሱ ዘንድ ታላቅ መከራና ብዙ ተጋድሎ ይጠብቃቸው ነበር። ወደ መንግስቱ ሙላት የሚገቡበት በክርስቶስ የተገለጠው ይህ የክርስትና ሕይወት "ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን እንደሚታረዱም በጎች ተቆጠርን" እያሉ፣ መከራን የሚታገሱበት ህይወት ነበር ። እርሱም አሁንና እዚህ ነው፣ በሙላትም ተሰጥቶናል። እምነትን ቅርጥፍ አድርጎ ከሚበላና እርቃንን ከሚያስቀር ፍጥረታዊ ከሆነ ከየትኛውም ነገር ጋር ልናስተያየው አንድፈር፣ እርሱንም ገና እንዳልተገኘ ማሰብ አይገባንም።
የማያምኑት የክርስትና ጠላቶችና አሳዳጆች የነበሩ የዚያ ዘመን አይሁድ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ የፈጸሙትን ግፍና ወንጀል የሚመጥን ፍርድና በቀል እንደተቀበሉ ለመረዳት ይደርስባቸው ዘንድ የተነገረባቸውን (ለምሳሌ ዘዳ 28 እና ማቴ 24) የፍርድ ቃል ከታሪካዊው የ70 አ.ም እልቂታቸው ጋር አስተያይቶ ማንበብ የአስተዋዮች መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ከታሪካዊ መዛግብት በላይ እጅግ የጸናው የትንቢት ቃል፣ "ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል" ሲል ጌታ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ነው እንጂ፤ ታሪካዊ መዛግብት የጌታ ትንቢት መፈጸሙን ለማመን ቀዳሚ መሰረታችን አይሆኑም። ያመንነው ቃሉን ብቻ ነው። ተጠራጣሪ ሰዎች ቃሉን ብቻ በማመን ስለማይረኩ ታሪካዊ ማስረጃ ቢቀርብላቸውም መጠራጠራቸውን አያቆሙም። ለእምነት ቤተሰብ ግን የእምነት ቃል ብቻ ይበቃዋል።
ይሁንና ግን የዚያ የ70ው አ.ም የአይሁድ ሮማውያን ጦርነት በጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረባቸው መለኮታዊው ፍርድ እንደሆነ በውል አለመረዳት ደግሞ በታሪካዊው የስነ ትርጓሜ መረዳታችን ላይ ብዙ ውዥንብርን ሲያስከትል ኖሮአል። በጦርነቱ የቅድስቲቱ ከተማ ቅጥር መሰበር፣ የቤተመቅደሱ መቃጠልና በህዝቡ ላይ የመጣባቸው ዘግናኝ ጥፋት፣ ነብያቱን አሳድደው ሲገድሉና፣ ቅዱሱን ለአህዛብ ፍርድ በመስቀል እንዲሰቀል አሳልፈው ሲሰጡ ያኔ እነዚያ የእግዚአብሔር ፍርድ በራሳቸው ላይ እንደሚገባቸው የቆጠሩ አመጸኛ ሰዎችን በትውልዳቸው አግኝቶአቸዋል። ለአህዛብ ፍርድ አሳልፈው የሰጡት ንጹሁን ሰው ሲሰቅሉት "ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን" ሲሉ ለጥፋታቸው ፈርመው ነበርና።
ያንን ንጹህና የዋህ ሰው፣ መሲሃቸውን፣ ሊፈታው ቆርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት ካዱት፣ እርሱ ግን በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት መልካሙን መታመን መሰከረ። እነርሱ ግን በግፍ ገደሉት፤ በፍርድ አስወገዱት። የነብያት ሁሉ ደም በእጃቸው ላይ ሳለ በእርሱ አምነው ሊነጹና ሊቀደሱ ሲገባቸው እርሱን በመግደል የፍርድ ጽዋቸውን ሞሉ። ቅዱሳንንም እስከ ጥግ ድረስ አሳደዱ። "ወራሹ ይህ ነው፣ ኑ እንግደለውና ርስቱን ለእኛ እናድርግ"፣ ሲሉ ልጁን የገደሉበት አባት ለዘመናት የታገሳቸውን ያህል እንዳይመለሱ ልባቸውን እልከኛ አደረጉ። የተሰጣቸውንም የንስሃ እድል ጢቅ ብለው ተፉበት፣ "የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ..." እያሉ በከንቱ መታመናቸውንና "እኛ እስራኤላውያን ነን" የሚለውን ከንቱ ትምክህታቸውን ተከትለው ጸኑ። የ70ው ዓ.ም ኹነት እግዚአብሔር ያንን ባዶ ትምክህትና ብሔራዊ ኩራት ለዘላለም ከአፈር የቀላቀለበት አስፈሪ ጥፋት ነው። "ያልወለዱ ማህጸኖች፣ ያላጠቡ ጡቶች" ምንኛ የታደሉ ናቸው? እነዚያማ የወሉዱና ያጠቡቱ በወለዱአቸውና ባጠቡአቸው ላይ እስኪጎመዡና አብስለው እስኪበሉአቸ ድረስ አረማውያን እንኳ የሚጸየፉትን፣ እንስሳትም የማያደርጉትን ተግባር ከማድረግ አልተመለሱም።
እግዚአብሔርንና የልጁን ወንጌል አልፈለጉም፣ ስለዚህም የእሳትን ፍርድ አመጣባቸው። በጥንቱ ዘመን ለአህዛብ አሳልፎ እየሰጠ ነብያትን የገደሉት አባቶቻቸውን እንደቀጣና እንደማራቸው አይደለም፤ ይልቁንም ከምድረ ገጽ ፈጽሞ ያጠፋቸው ዘንድ "ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል" ሲል እንዳስጠነቀቃቸው፣ ቤታቸውን ላይሰራ አፈራርሶታል። ጀነራል ቲቶ እንኳ ለክብሩና ለዝናው ያንን የሚያምር ቤት ሊያድነው ፈልጎ ሕንጻውን እንዳይጎዱት ለወታደሮቹ የአለቃ ትእዛዝ ቢሰጥም የሰማውና የታዘዘው አልነበረም፤ እነዚያ አለቃቸውን ለመታዘዝ በሚገባ የሰለጠኑ የሮማ ወታደሮች ወደ አውሬነት የተለወጡ ያህል ያገኙትን ነገር ያወድሙ ዘንድ ፈጠኑ፣ ህዝቡንም የቻሉትን ያህል በሰይፍ ገደሉ፣ ቤተመቅደሱንም በእሳት አያይዘው ሲያቃጥሉት ፈጽሞ እንዲፈርስ እስከመሰረቱ ድረስ ይቆፍሩት፣ ግንቡንም ይነድሉ ነበር፤ ግን ለምን? ምክንያቱም የነገስታት ንጉስና የጌታዎች ሁሉ ጌታ የሆነው፣ የቲቶንና የቄሳሩን እስትንፋስ በእጁ የያዘው ጌታችን ኢየሱስ ያንን ቤት ይፈርስ ዘንድ ትእዛዝ አውጥቶ ነበር።
"ወራት ይመጣብሻልና፣... ልጆችሽንም ወደታች ይጥላሉ" ሲል ለኢየሩሳሌም ያለቀሰላት የናዝሬቱ ኢየሱስ የዋሁ የእግዚአብሔር በግ አሁን በነዚያ ክፉ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ላይ የተቆጣ አንበሳ ሆነባቸው። ይገድሉአቸው ዘንድ ለክፉዎች አሳልፎ ሰጣቸው፣ የእግዚአብሔርን ልጅ የሰቀሉ ለእነርሱ የሚሰቀሉበት እንጨት ከምድሩ እስከሚታጣ ድረስ ተሰቀሉ፣ ታረዱም፤ በድናቸው ቀባሪ እስኪያጣ ድረስ አብጦ እየፈነዳ በየጎዳናው ወድቆ ግማቱ ምድሪቱን ሞላ። ተማርከው ለባርነት የተሸጡትም በምርኮ በተጋዙበት አገር በአህዛብ የጣዖት ክብረ በአልና የነገስታት/ የመኳንንት የልደትና የንግስና በአል ላይ ለጣዖታቱና ለመኳንንቱ ክብር መስዋእት ሆነው ቀረቡ። በእግዚአብሔርና በቀባው ላይ ሆን ብለው በጠላትነት ጎራ የቆሙ አይሁድ በአህዛብ ምድር ምርኮኛና ግዞተኛ ሆነው የሮማውያን መኳንንት መወዳደርያና መፎካከርያ ሆኑ። "ምን ያህል አይሁዳዊ አርደህ ታከብረኛለህ?" የመኳንንቱና የሎሌዎቻቸው መገባበዣ ነበር። በእነርሱም ላይ ዕጣ እየተጣጣሉ የአረማውያን መቆመሪያ ሆኑ። እንደ ምንም ነገር ይቆጠሩ ዘንድ እግዚአብሔር ህዝቡን ምን ያህል እንደጣላቸው ለመናገር በእውነት ይዘገንናል። እስከመጨረሻው እግዚአብሔር ተዋጋቸው፣ ኦ! ፍርዱ ምንኛ አስፈሪ ነው። "የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ። የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሰክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል? በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም፦ ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል። በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው።" (ዕብራውያን 10፥ 26-31) ሲል ሐዋርያው የዕብራውያንን ክርስቲያኖች ያስጠነቀቀበት ቃል ከዚሁ ጋር ይስማማል።
ያንን የኪዳኑን ሕዝብ መጨረሻና በ70 ዓ.ም የሆነባቸውን እልቂት አቅልለን ባየንበት አተያይ ዘመናችንን ሁሉ እንደዳከርን እንቀራታለን እንጂ፣ የትንቢትን ቃል ትርጓሜም ሆነ ፍጻሜውን ሳናስተውል፣ በትንቢት ፍጻሜ ውስጥም እግዚአብሔር ለክርስትና የሸሸገውንና የጠበቀውን ምክሩን ሳንማር፣ የድል ነሺውን የይሁድ አንበሳ ግርማና ክብር ማየት እንደተሳነን ዘመናችን ያበቃል።
ቅዱሳን ሐዋርያቱማ ወንድሞቻቸው ይህ ጥፋትና ፍርድ እንዳያገኛቸው በብዙ እንባ እየለመኑ፣ እየተሳደዱና እየተገደሉ በወንጌል መክረዋል፤ "ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ሲሉ ስለ ክርስቶስ ለምነዋቸዋል" አልሰማ ብለው ልባቸውን ያደነደኑ እነዚያ የኃይማኖት አወሳሳቢዎች ግን ያንን ጽኑ ፍርድ በስጋቸውም በነፍሳቸውም ሲቀበሉ፤ ቅዱሳኑ ግን ምንም ጉዳት ሳያገኛቸው ጌታ አስቀድሞ እንደነገራቸው ያቺን ልትጠፋ የቀረበች ከተማና ምድር ለቀው እንደወጡ ታሪክ ያረጋግጣል። ጌታ ኢየሱስ ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር በፍርድ በመጣ ጊዜ ጠላቶቹን ሲደመስስ በእርሱ ያመኑትንና ያድናቸው ዘንድ ሲጠብቁት የነበሩትን አድኗቸዋል።
በአይሁድ ማህበረሰብ ውስጥ በሰፊው ስለሚታወቅና በስነጽሁፎቻቸው ውስጥ ጥቅም ላይ ስለዋለው ስለ አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ አጠቃቀም ምን ያህል እናውቅ ይሆን? ምን ማለት እንደሆነ ትርጉሙን ማወቅ የሚፈልግ ሰው አዲሱ መደበኛ ትትጉም መጽሐፍ ቅዱስ ከማጥኛ ጽሁፍ ጋር በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ መግቢያ ላይ ያስቀመጠውን መጠነኛ መግለጫ ማየቱ ብቻ ለጅማሮ ጥሩ ይመስለኛል።
ሰማይና ምድር በትንቢት ውስጥ የሚይዙት ትርጉም አቡቀለምሲሳዊ ነው እንጂ literally የሚወሰድ አይደለም። በብሉይ ኪዳን በዘመኑ የነበሩትን ኃያላን መንግስታት በሚወክሉበት መልኩ እንደቀረቡ ሁሉ እስራኤልም የነበራትን ፓለቲካዊና ኃይማኖታዊ የበላይነት በሚገልጥበት መልኩ ጥቅም ላይ ውሎአል።
አሁን ያለው ምድራዊ መንግስት እግዚአብሔር በሉአላዊው ፈቃዱ የምድርን ስርአት ለመጠበቅ ያቆመው ነው። የአለም ታሪክ በተቀደደለት ቦይ ሲፈስና ትውልድ ሲፈራረቅ እንደየሁኔታውና ህብረተሰቡ እንደደረሰበት የአስተሳሰብ ሥልጣኔ የሚለዋወጥም ነው። ከመንፈሳዊውና ዘላለማዊው መንግስት ጋር አይገናኝም። እርስዋ ለማንም የማትሰጥ የንጉሱ ጌታ ክርስቶስ መንግስት ናት። እነሆ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ መንግስት፣እነሆ የክርስትናችን አዲሱ ኪዳን አዲሱ ሰማይና ምድር። ለአለምና ለዘለአለም የማያልፍ ጽኑ መንግስት ውስጥ እንኖራለን። አሮጌው የአይሁድ ሰማይና ምድር አልፎአል፣ ለዘላለምም አይታሰብም።
አዲሱ ሰማይና ምድር እነሆ፣ ዘላለምም ላያልፍ ጀምሮአል። ከዚህ በኋላ የምንጠብቀው የለንም። ጌታም መጥቶአል፣ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የሌለ ነገር መጠበቅ የሆነውን ያህል አሁን የነገስታት ንጉስ እንዳልሆነ ሁሉ ገና ወደፊት ይነግሳል ብሎ መጠበቅ ነው። የነገሰ እና የሚገዛ ጌታ እንጂ ገና የሚመጣ እና የሚጠበቅ አይደለም። እኔ በበኩሌ ግን ጠባቂ መሆኔን አቁሜአለሁ። ጠባቂ የሆኑ ወንድሞቼን በክርስቶስ ቃል በመገዳደርና በመፋጠጥ "የተባረከውን ተስፋቸውን" በተፈጸመው ወንጌል ከመሞገት ያለፈ ምንም አላማ የለኝም። እንደ እውነተኛ የቃሉ ተማሪ በቤርያን ሰዎች ልብ በትንቢት ትርጉምና ፍጻሜው ላይ የቤት ስራቸውን እንዲሰሩ ግን አሳስባለሁ። እምነታቸውን ለመጠየቅ የሚደፍሩ አብረውኝ እንዲጠይቁ እንጂ በኃሰተኛ የንግድ ትርፍ ማንንም ግራ የማጋባትና የማሳሳት ፍላጎት ፈጽሞ የለኝም።
ይሄንን አንድ ነገር ግን ተረድቼአለሁ፦ አዲስ ኪዳንን ሳነብ በመንግስቱ ሁሉን የሚገዛውን ንጉሱን ኢየሱስን በውበቱና በግርማው አየዋለሁ። ከዚህ የተለየ መጽናናት የሞላበት ምድራዊና literal የሆነ ነገር አያስፈልገኝም። እርሱ ሞቶ በመከራው የፈጸመውን እና ቃሎቹን በማመን የተቀበልሁትን ታላቅ መዳን በፍጹምነት የሚያለማምደኝ የተፈጸመው ዳግመኛ ምጽዓቱ ነው።
No comments:
Post a Comment