Sunday, January 28, 2024

የፕላኔቷ ዕጣ ፈንታ

የፕላኔት ጥፋት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነውን?

በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ብርሃን

መግቢያ፦

በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎችና ማብራሪያዎች ላይ እንደሰፈረው፣ በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ላይ ስላለው አሳብ፣ ፕላኔቷ ራሷ፣ ማለትም “የሰማይ ፍጥረት” /the elements/ “ይቃጠላሉ” የሚል አንድምታ ያለው ትርጉም በብዙዎች ተሰጥቶት እናነባለን።  የዛሬ ዘመን የቃሉ አንባቢዎችም ይህንን ክፍል ሲረዱ በብዙዎች ዘንድ ያለው የተለመደ አመለካከት፣ በእርግጥ ምንባቡ ስለ ሰው ልጆች የታሪክ ፍጻሜ እና ስለ አጥናፈ አለሙ /universe/ ዕጣ ፈንታ እየተናገረ ነው የሚል ግንዛቤን ይዘዋል። ዳሩ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱሳችንን በወጉ የምናጠና ከሆነ ይህ ምንባብ ቃል በቃል /literally/ ስለ ግዑዙ ፍጥረተ አለም መቃጠል ወይም ስለ ኮስሞስ ጥፋት የሚናገር ቃል አለመሆኑን፤ ይልቁን ግን እግዚአብሔር በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ ፍርዱን ባደረገ ጊዜ ያኔ በ70 ዓ.ም ሊመጣ ስላለው ክስተት የተነገረ ቃል መሆኑን እናስተውላለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ በተነበየውና፣ በ70 ዓ.ም ላይ ሮማዊያን ሲመጡ በህዝቡና በከተማይቱ ላይ በሆነው የእልቂት ጥፋት፣ ያኔ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዶች እንደተጨፈጨፉ፣ ቤተ መቅደሱም እንደፈረሰ እና ከእርሱም ጋር የአሮጌው ኪዳን ሥርዓት ለመጨረሻ ጊዜ እስከወዲያኛው እንደተወገደ ከቅዱሳት መጻህፍት (ማቴ 23፥ 29-24፥ 2፣ ወዘተ) እና ከታሪካዊ መዛግብት በግልጽ እናነባለን።

እንግዲህ የዚህ አይነተኛ ምዕራፍ ወሳኙና አከራካሪው ጥቅስም ምዕራፍ 3፥ 10 ላይ ያለው ነው፣ ቃሉም በአማርኛችን፦ “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” የሚለው ነው። 

ከመነሻዬ የቃሉን ባለቤት የማመሰግነው ይህ ይሆናል የተባለው “ኮስሚክ ውድመት” ድንገት ከሚመጣው የጌታ ቀን ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው፤ ምክንያቱም መላው አዲስ ኪዳ ይመጣል ሲል የሚናገርለት አንዱ የጌታ ቀን ያ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ከማለፉ በፊት ሊፈጸም ቀን የተቀጠረለት እና ከመሆን የማይቀር ምጽአት በመሆኑ ነው። የዚህ ጥቅስ ትርጉም ውሃ ልኩም የሚያርፈው መጽሐፍ ቅዱስ የጌታ ዳግመኛ ምጽአት በመጀመሪያው ክፍለዘመን ላይ የሚፈጸም ተስፋ አድርጎ ባቀረበበት አጠቃላይ አውድ ላይ ነው። ስለዚህ ይህንን ጥቅስ ለመተርጎም ከዚህ በኋላ ለማነሳላችሁ ነጥቦች ሁሉ ይህ ኣሳብ ምን ያህል የጀርባ አጥንት እንደሆነልኝ በውነት አልሸሽግም።

የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ይህንን ጥቅስ እንዴት እንደሚያስቀምጡት አንዳንድ ማሳያዎችን ላቅርብ፣ 

አዲሱ ትርጉም፦ “የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያን ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፤ ፍጥረት ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ የጠፋል። ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል።”

አዲሱ መደበኛ ትርጉም “የጌታ ቀን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል” ይላል።

ህያው ቃል፦ “ሌባ በምን ሰዓት እንደሚመጣ እንደማይትወቅ ሁሉ የጌታም ዳግም ምፅአት እንደዚያው ሳይታሰብ በድንገት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሰማያት በታላቅ ድምፅ ተነዋውጠው ያልፋሉ። የሰማይ አካላት እንደ ሰም ይቀልጣሉ። ምድርና በላይዋ ያለ ነገር ሁሉ በእሳት የጋያል።”

በአንዳንድ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ደግሞ። 

But the day of the Lord will come as a thief in the night, in which the heavens will pass away with a great noise, and the elements [stoicheion] will melt with fervent heat; both the earth and the works that are in it will be burned up [katakaio].  (2 Peter 3:10, New King James Version)

But the day of the Lord will come like a thief, and then the heavens will pass away with a roar, and the heavenly bodies [stoicheion] will be burned up and dissolved, and the earth and the works that are done on it will be exposed [katakaio].  (2 Peter 3:10, English Standard Version)

But the day of the Lord will come as unexpectedly as a thief. Then the heavens will pass away with a terrible noise, and the very elements [stoicheion] themselves will disappear in fire, and the earth and everything on it will be found to deserve judgment [katakaio].  (2 Peter 3:10, New Living Translation)

ቀጥሎ በማነሳቸው ነጥቦች ቅዱሳት መጻሕፍትን በራሳቸው በቅዱሳት መጻሕፍት በመተርጎም ይህንን ጥቅስ እየመረመርን የነገሩን ውል በአውደ ምንባቡ ውስጥ እንፈልጋለን። ምናልባት የህንን የምታነቡ፥ ምድር ተቃጥላ ትጠፋለች፣ የሰው ልጆች ታሪክም በዕልቂት የዘጋል፣ ወዘተ… የሚል ትምህርት መጽናናት የሚሰጣችሁ ክርስቲያኖች ካላችሁ ከዚህ ቀጥሎ የማነሳቸው 12 ነጥቦች ሊያስቆጣችሁ ስለሚችል ጽሁፉን ታግሳችሁ እንደታነቡ እጠይቃለሁ።  

፩ኛ/ በምዕራፍ 3፥ 10 ላይ ይህ “ይቃጠላሉ” የተባለው “የሰማይም ፍጥረት” ለሚለው ሃረግ የግሪኩ አቻ ቃል “ስቶይቺዮን” ነው።  ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ በዋለበት በሁሉም ስፍራ የሚያመለክተው ስለ ብሉይ ኪዳን “አካላት” ወይም የአይሁድን አካላትት /Jewish elements/ ነው እንጂ ስለ ተዳሳሹ አጥናፍ አለም ጉዳዮች አይደለም። ይህ  ስቶይቺዮን የተሰኘ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዴትና በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳዩንን እነዚህን ምንባባት በጥንቃቄ ተመልከቱ፡ 

ገላትያ 4፥ 3፣ 9፤ “እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት (stoicheia tou Kosmou) በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤…  አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን?”

እዚህ ላይ ቃሉ የሚያመለክተው ክርስትና ካስገኘላቸው ነጻነት በፊት በባርነት ይገዙበት የነበረውን ኃሰተኛ ትምህርት እና በእርሱ የሚዘወረውን የባርነት ኑሮ ነው። የገላትያ ሰዎች ዳግመኛ እየተወሰዱበት የነበረው ኃሰተኛ ሐይማኖት ደግሞ ይሁዲነት ነበር።

ቆላስይስ 2፥ 8-9፣ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት (stoicheia tou Kosmou) ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤”

ቆላ 2፥ 20-22፤ “ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት (stoicheia tou Kosmou) ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና”

በዚህም አሮጌውን ኪዳን የመሰሉ የተለያዩ ኃሰተኛ ኃይማኖቶች ከባርነት በታች ገዝቶ ለማቆየት የሚያሳድሩትን ክፉ ተጽዕኖ ነው የሚያሳየው። 

ዕብራውያን 5፥ 12-13 “ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት (stoicheia) እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።  ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤”

እዚህም ያለው ትርጉም በዐውደ ምንባቡ ውስጥ አነስተኛ ዋጋ ስላላቸውና  “የሕፃንነትን ትምህርት” በመባል ስለሚታወቁት ወይም በቁጥር 11 ላይ ጆሮቻቸውን ያፈዘዘ የህጉ ትምህርት ግልጽ ወይም የመጀመሪያ መርሆዎች በተመለከተ የተነገረ ነው።

እንግዲህ ይህ የግሪኩ “ስቶይቺዮን” የሚለው ቃል በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አጠቃቀም የቀደመውን አሮጌ ወይም አለማዊ የትምህርትና የባርነት አኗኗር በሚያመለክትበት ዘይቤ ቀርቦ ሳለ፣ 2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3፥ 10 ያለውን ግን ከዚህ የቃሉ ጠቀሜታ ነጥሎ፣ የለም ግዑዙን ፍጥረተ ዓለም ነው የሚያመለክተው ብሎ ለመተርጎም መሞከር ወደ ፍጹም ስህተት ያመራል። 

፪ኛ/ በሌላ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ በትምህርቱ ቀዋሚነት፣ ያለተፋልሶ ምድር ወይም ይህ ግዑዝ ዓለም ፍጻሜ የሌለው እንደሆነ አድርጎ ያስተምራል (ለምሳሌ መክብብ 1፥ 4፤ መዝሙር 78፥ 69፤ 104፥ 5፤ 148፥ 3-6፤ ኤፌሶን 3፥ 21ተመልከቱ)፤ እእግዚአብሔር አምላክም ሕያዋን ፍጥረታትን ዳግመኛ እንደማያጠፋ ቃል ገብቷል፣ (ዘፍጥረት 8፥  21፤ 9፥ 11)።

ይህንን ሃሳብ በተመለከተ ቀደም ሲል በብሎገሬ ላይ “ይህ አለም ፍጻሜ አለውን?” በሚል ርእስ በዝርዝር ያካፈልኩትን ጽሁፍ እንድታዩት ሊንኩን ላጋራችሁ፦

https://gizachewkr.blogspot.com/2016/11/blog-post.html?m=1

፫ኛ/ በጴጥሮስ መልዕክቶች እና ንግግሮች አውድ ካየነው ጴጥሮስ እየደጋገመ የሚያነሳው የመጨረሻው ዘመን ፍጻሜ፣ ያኔ ለእርሱና ለተደራስያኑ እጅግ የቀረበ ነበር። በ1ኛ ጴጥሮስ 4፥ 7 እንደተነገረው “የነገር ሁሉ” ፍጻሜ ጴጥሮስ የመጀመሪያ መልዕክቱን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ ያኔ “ቀረቦ” ነበር።  በ1ኛ ጴጥሮስ 4፥ 17 ላይ እንደተነገረው ደግሞ “ፍርድ የሚጀምርበት ጊዜ” ያኔ ደርሶ ነበር።  በሐዋርያት ሥራ 2፥ 14-20 እና 1 ጴጥሮስ 1፥ 20 መሠረትም ጴጥሮስ ራሱ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ይኖር እንደነበር ያውቅና ያምን ነበር። 

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ መጨረሻው ቀን/ስለ ፍጻሜ ዘመን 19 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል፣ ሁሉም የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች ያለ ልዩነት ቃላቸው አንድ ሆኖ በአንድ ድምፅ ሲናገሩ - እነሱ ራሳቸው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ ይመሰክራሉ፣ ይህም እነርሱ የኖሩበት የመጨረሻ ዘመን ማለት የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀናት ማለት ነው እንጂ የዚህ ተዳሳሽ ዓለም (የኮስሞስ) መጨረሻ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስም ያለ ልዩነት የሚያውቀው አንዱን የመጨረሻ ዘመን ብቻ ነው።

፬ኛ/ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስፋት የተነገረው ይህ “የጌታ ቀን” (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 10) ርዕሰ ጉዳይ እግዚአብሔር አምላክ በተለያዩ ህዝቦች ላይ በተከታታይ ስለሚያመጣው ፍርድ የሚናገር ነው እንጂ፣ ፈጽሞ ስለ ግዑዝ ፕላኔትና ስለ ተዳሳሽ ዓለም ጥፋት የሚናገር አይደለም። 

ለምሳሌ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ምንባባት ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፦ 

¶ በኢሳይያስ 34 ላይ ኤዶምያስን በተመለከተ ስለተነገረው የፍርድ ቀን ሲናገር በቁጥር 4 ላይ “የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፥ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፥ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋል።” ሲል ስለ ቀኑ ይናገራል፤  

¶ በኤርምያስ 46፥ 10 ላይ በስም በተጠቀሱ የተለያዩ ህዝቦች ላይ ስለሚመጣ ፍርድ ሲናገር “ያ ቀን ጠላቶቹን የሚበቀልበት የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የበቀል ቀን ነው፤…” ሲል ይናገራል፤ 

¶ በሰቆቃወ ኤርምያስ 2፥ 22 በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚመጣው የፍርድ ቀን ሲናገር “እንደ በዓል ቀን የሚያስፈሩኝን ከዙሪያዬ ጠራህ፥ በእግዚአብሔር ቍጣ ቀንም ያመለጠ ወይም የቀረ አልተገኘም፤ ያቀማጠልኋቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ በላቸው” ያላል፤  

¶ በሕዝቅኤል 13፥ 5 ላይም የእስራኤልን ሐሰተኛ ነቢያት ሲከስሳቸው ”በእግዚአብሔርም ቀን በሰልፍ ትቆሙ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ቅጥር አልሠራችሁም” ሲል በእግዚአብሔር የፍርድ ቀን እስራኤልን እንዳላዳንዋት ይመሰክርባቸዋል። 

¶ በሕዝቅኤል 30፥ 2-4 ላይም በግብፅና በኢትዮጵያ ላይ ስለሚሆን የፍርድ ቀን ሲናገር “የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ! ቀኑ ቅርብ ነው፥ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል። ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፤ የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል” ሲል ይናገራል፤ 

¶ በትንቢተ አሞጽ 5፥ 18-20 ባለውም ክፍልም የእግዚአብሔር ቀን በእስራኤል ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ ሲናገር “የእግዚአብሔርን ቀን ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም። ከአንበሳ ፊት እንደ ሸሸ ድብም እንዳገኘው ሰው፥ ወይም ወደ ቤት ገብቶ እጁን በግድግዳ ላይ እንዳስደገፈና እባብ እንደ ነደፈው ሰው ነው። የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?” ሲል ይናገራል፤  

¶ በአብድዩ ቁጥር 15 ላይም የእግዚአብሔር ቀንን አስመልክቶ “የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል” ሲል ኤዶምያስን ያስጠነቅቃል፤  

¶ በሶፎንያስ 1፥ 2-18 ባለውም ክፍል በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚደርሰው የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ይናገራል።  

እንግዲህ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ እንደሚመጣ የተነገረው የእግዚአብሔር ቀን ፍርድ አንዳንዶቹ በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤል በጠላቶችዋ እጅ በወደቀችበት ወቅት የተፈጸሙ ሲህን፣ እንደ ሚልክያስ 3፥ 2-5፤  4፥ 1-5 ባሉ ክፍሎች “የሚነድ/ የሚቃጠል” የእግዚአብሔር ቀን ተብሎ የተገለጠው ደግሞ ከ70 ዓ.ም የኢየሩሳሌም ጥፋት ጋር የተያያዘው ፍርድ ነው፤ ይህም የቁጣ ቀን በማቴዎስ 3፥ 7-12፣ ባለው ክፍል ላይ በሰፈረው የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት፦ “ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፦ አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና፦ ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” በሚል የተረጋገጠው ነው።  

በተመሳሳይ ማቴዎስ 13፥ 49-50;  21፥ 33-45;  22፥ 7;  ወዘተ ያለውም ስለዚሁ ፍርድ የሚናገር ነው። መጥምቁ ዮሐንስ በሚልክያስ 3፥ 1፤ 4፥ 5 የተነገረውን  የኤልያስን ዳግመኛ መምጣት በመንፈስ እንደፈፀመ አስተውሉ፤ (ማቴዎስ 11፥ 14፣ 17፥ 11-13)።  አዲስ ኪዳን በግልጽ የሚናገርለት ታላቁ ፍርድም ግልጽ ትኩረት የሰጠው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በነበሩ አይሁድ ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት ነው (ማቴዎስ 23፥ 29-24፥ 2፣ ወዘተ.) እንጂ—በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ስለሚደርስ ‘የፕላኔት አለም ጥፋት’ አይደለም።

፭ኛ/ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ያኔ በዘመናቸው የጌታ ቀን አስቀድሞ መጥቷል ብለው ማሰባቸው በእውነት የሚደንቅና ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው፤ “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን” ይላልና (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥ 1-2)!  ስለዚህ፣ እነርሱ ስለ ጌታ ቀን ሲያስቡ አሁን በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች ካላቸው የተለየ ግንዛቤ እንደነበራቸ አስተውሉ። አያችሁ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የጌታ ቀን የፕላኔት ምድርና ሰማይ መቃጠልን ሳያካትት፣ ሳያውቁት ሊያልፋቸው እንደሚችል እንኳ ያስቡ ነበር ።

፮ኛ/ ስለተፈጥሮ ሥርዓት የኮስሚክ ነውጥን የሚያመለክት የንግግር ዘይቤ መደበኛ በሆነው የዕብራይስጥ አቡቀለምሲሳዊ ቋንቋ የተለመደ ነው፤ ቃል በቃል ባልሆኑ አገላለጾች ስለ ሥነ-መለኮታዊ ወይም ቃል ኪዳናዊ ክንውኖች፣ እንዲሁም በተለይ እግዚአብሔር በደለኛ በሆኑና ቁጣው በሚገባቸው ህዝቦች ላይ ስለሚያመጣው ትክክለኛ ፍርድ ለመግለጥ እንዲህ ያለ ትዕምርታዊና አምሳላዊ የቋንቋ ዘይቤ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል እናያለን።  ጊዜ ወስዶ ቀጥሎ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች በመመልከት ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል:- 

¶ 2ሳሙኤል 22፥ 8-16፣ እግዚአብሔር በዳዊት ጠላቶች ላይ ያመጣውን ፍርድ በተመለከተ፤  

¶ ኢሳይያስ 13፥ 10-13፣ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ 

¶ ኢሳይያስ 34፥ 4፣ እግዚአብሔር በኤዶምያስ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ በተመለከተ፤

¶ ኤርምያስ 4፥ 1-31፣ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ 

¶ ሕዝቅኤል 32፥ 7-8፣ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፅ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ 

¶ ሚክያስ 1፥ 2-16፣ እግዚአብሔር በእስራኤልና በይሁዳ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ 

¶ ናሆም 1፥ 2-8፣ እግዚአብሔር በነነዌ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ እንዲሁም 

¶ ሶፎንያስ 1፥ 2-18፣ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በይሁዳ ጠላቶች ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ 

ከፍ ሲል በተጠቀሱ ምንባባት በኮስሚክ ነውጥ የተወከለው ገለጻ፣ ንግግሩ የተፈጥሮ ሥርዓት ነውጥን ሳይሆን በኃጢአት ምክንያት በህዝቦችና በነገስታት ላይ የሚደርሰውን መለኮታዊ ቁጣ የሚያመለክቱ መሆናቸውን አስተውሉ።

፯ኛ/ የሐዋርያው ጴጥሮስ “ሰማይና ምድር” የሚል አነጋገሩን ልብ አድርጉ፦  “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 13) ሲል ያነሳውን ተስፋ በቀጥታ የወሰደው በብሉይ እና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካለው የቃሉ አጠቃቀም ነው።  ስለ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ከሚናገሩት መሠረታዊ የንባብ ክፍሎች መካከል ኢሳይያስ 65-66 እና ራዕይ 21 ላይ የሚገኙት ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ እግዚአብሔር በጠላቶቹ ላይ ስለሚያደርገው ፍርድ በግልጽ እናያለን፤ ነገር ግን በክፍሉ ውስጥ በግልጽ እንደሚታየው ፍርዱ ከተፈጸመም በኋላ የተለመደው የሰው ልጅ ታሪክ ይቀጥላል እንጂ አይቋረጥም ። ይህም ማለት ኃጢአትና ሞት በተቀረው ፍጥረታዊ ዓለም ውስጥ መኖሩ ይቀጥላል ማለት ነው (ኢሳይያስ 65፥   20፤ ራእይ 22፥ 15)፤ አንዳንድ ሰዎችም ስለ እግዚአብሔር ገና ያልሰሙ በመሆናቸው የወንጌል ስብከት አገልግሎት አስቀድሞ በተፈጸመው ፍርድ ከመታወጅ ሳይቋረጥ ኃጢአተኞችን ውደ ጽድቅ በእምነትና በንስሃ የመጋበዙ ሥራ ይቀጥላል ማለት ነው (ኢሳይያስ 66፥ 19-24)።  ስለዚህ በአጠቃላይ አውዱ መሰረት አዲስ ሰማይ እና አዲስ ምድር ማለት ጨርሶ ቀድሞ ያልነበረ ሌላ ተዳሳሽ ግዑዝ ዓለም ይፈጠራል ማለት አይደለም፤ የአሮጌው ሰማይና ምድር ተጠቅልሎ ማለፍም ፍጥረታዊው የሰው ልጆች ዓለም  ታሪክ መጨረሻው ይሆናል ማለት ፈጽሞ አይደለም። በተጨማሪም በማቴዎስ 5፥ 17-18 ላይ ኢየሱስ አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርን ከጸጋ ዘመን መጀመር እና ከአሮጌው ኪዳን የህግ ዘመን ማብቂያ ጋር በማገናኘት መናገሩን ልብ ይሏል፤ እርሱም ያለፈውን አሮጌ ዘመን ፍጻሜ የሚያመለክት ሲሆን- ይህም የሰማይና የምድር ህልፈት በዕብራውያን 8፥ 13 “አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል” በሚል የተነገረውንና በ70 ዓ.ም.  የሆነውን የአሮጌውን ኪዳን ፍጻሜ የሚያሳይ ነው። ጴጥሮስም በዚሁ የቃሉ መንፈስ ከፊቱ ያለውን 70 ዓ.ም እያየ “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል” (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 7) ሲል ይመሰክራል። 

ስለዚህ ተስፋ የተገባው አዲሱ ሰማይ እና አዲሱ ምድር በውበቱ የሚያብረቀርቅና የሚያንጸባርቅ፣ መጻኢያንም እንደሚመስላቸው ይህኛው አለም ከጠፋ በኋላ ገና የሚፈጠር አዲስ ፕላኔት ማለት ሳይሆን፣ ይልቁንም ኃጢአትና ሞት የነገሰበት የአሮጌው ኪዳን አገዛዝ፣ እርሱም ይሁዲነት በእሳት ፍርድ ተወግዶ፣ ጽድቅ የሚገዛበት የአዲሱ ቃል ኪዳን መንግስት፣ እርሱም ክርስትናችን በህይወት የሚነግስበት ነው።

፰ኛ/ “ይቃጠላል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል “ካታካዮ” የሚለው ነው፤ በተለያዩ ትርጉሞች ውስጥ “የተጋለጠ፣” “ፍርድ የተገባው ሆኖ ተገኝቷል” ወይም “የተራቆተ” ተብሎ ተተርጉሟል።  እንደሚታወቀው ‘እሳት’ የፍርድ ምልክት ነው፣ ይኸውም ከፍ ሲል ካለው የንባቡ ክፍል የተሳበ ነው።  ይህም በ70 ዓ.ም በአሮጌው ኪዳን ላይ ለሆነው ጥፋት ተስማሚ ቋንቋ ነው።

፱ኛ/ በመልእክቱ ውስጥ “ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤” (2ጴጥሮስ 3፥ 6) በሚል የተገለጠው በኖህ ዘመን የሆነው ጥፋት ከዚህ በሰማይና ምድር መቃጠል ከተወከለ አነጋገር ጋር በንጽጽር ቀርቧል። በህጉ እንደተጻፈው ያኔ በኖህ የጥፋት ውሃ ዘመን ኃጢአተኞች ብቻ በጥፋት ውሃ ጠፍተዋል። “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥” (2ጴጥሮስ 2፥ 5) እንደተባለ፣ ኖህ እና ቤተሰቡ ግን ከዚህ ጥፋት በውሃ የዳኑበት ሁኔታ ነው ያለው።  ይህም በ70 ዓ.ም ከተፈጸመው ጥፋት ጋር ተመሳሳይ ነው። እግዚአብሔር በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ ስለ ኃጢአታቸው እና ኢየሱስን መሲሕ አድርገው ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የበቀል እርምጃ እንደወሰደባቸው (ማቴ 23፥ 29-24፥ 2፣ ወዘተ) ግልጽ ነውና።  ይህም የበቀል እርምጃ በቅዱሳት መጻህፍት ሁሉ ለዳግመኛ ምጽአቱ ከተቀጠረውና ከተነገረው ጊዜ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሲሆን፤ ይህ ጥፋትና በቀል በተፈጸመበት ታሪካዊው የ70ው አ.ም የኢየሩሳሌም ውድመት ጊዜ ግን ይህ ግዑዙ ፕላኔት ዓለም ምንም የሆነው ነገር አልነበረም።  ይልቁንም እግዚአብሔር በኖኅ የጥፋት ውኃ ዘመን ባደረገው ኪዳን መሰረት ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፈጽሞ እንደማያጠፋ ቃል መግባቱን እናውቃለን (ዘፍጥረት 8፥ 21)። 

፲ኛ/ “አንድ ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት” የሚለው አነጋገር (2ጴጥሮስ 3፥ 8) ብዙ ጊዜ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጊዜ ጠቋሚ ሆነው የተነገሩ አገላለጾችን፣ ማለትም “ይህ ትውልድ”፣ “እዚህ ከቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ”፣ “ቶሎ”፣ “ቅርብ”፣ “ሊሆን ያለ” ወዘተ ያሉትንና የመሳሰሉትን በርካታ የሆኑ መግለጫዎች ውድቅ ለማድረግ መጻኢያን ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ነገር ግን "አንድ ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት" የሚለው፣ ቃል በቃል በጥሬው ሊወሰድና ሊተረጎም  ከቶ አይችልም፣ እንደዚያ የሚወሰድና የሚተረጎም ከሆነ ግን በአውደ ምንባብ ውስጥ ያለው አጠቃላይ የመጨረሻው ዘመን አሳብና ትምህርት ምንም እርባና ወይም ትርጉም የሌለው ይሆናል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር አጭር ጊዜ ማለት ረጅም ጊዜ ማለት አይደለም፤ ለምሳሌ፣ ጌታ ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ የቆየው ለ3,000 ዓመታት ነበርን? የሚል፣ ወይም እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ ሰርቶ የጨረሰው በ6000 ዓመታት ነውን? ከሥራው ያረፈውስ በ7ኛው ሺህ ዓመት ነውን? የሚል እርባና የሌለው ጥያቄ ያስነሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን “አንድ ሺህ” የተሰኘው ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ የምልዓት ምሳሌያዊ ቃል ሆኖ ማገልገሉን አትዘንጉ።

በዚህ ሃሳብ ላይ “ጴጥሮስን በጴጥሮስ” በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገጼ ላይ ያካፈልኩትን አጭር ጽሁፍ እንድታነቡት ጋበዝኳችሁ፦

https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid0gnU6ufdWSxfXTMAs6WmR9AnZ8MVm8q7KYcFZmApgwyZEAtGeKs4iNx7W8kdEvfH3l&id=100002668627386&mibextid=Nif5oz

፲፩ኛ/ ጴጥይሮስ በመልዕክቱ 3ኛ ምዕራፍ ከቁጥር 11-13 ባለው ንግግሩ ለአንባቢዎቹ የሚመጣውን የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እንዲጠብቁ እና እንዲያስቸኩሉ “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” ሲል ይመክራቸዋል። በዚህ ምክሩ ውስጥም ይፈጸማሉ የተባሉ ድርጊቶች የሚከናወኑበትን ጊዜ አስመልክቶ “አንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን” ያህል ስለመሆኑ የተነገረውን፣ የመልዕክቱን ሃሳብ ማግኘት ካለብን ምናልባት ጉዳዩ በርካታ ክርስቲያኖች በጥሬው ከሚያስቡት በተለየ ተቃራኒውን ነገር ማለት እንደሆነ ልናስብበት ይገባል። ጴጥሮስ በዚህ ንግግሩ ይፈጸማሉ ተብለው የሚጠበቁት ጉዳዮች - በተለይ ጊዜውን አስመልክቶ በሌሎች ምንባባት ውስጥ ከተሰጡትና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፈጸማሉ ከተባሉት መግለጫዎች አንጻር ለፍጻሜአቸው ወደ ፊት የቀራቸው አጭር ጊዜ ብቻ ነው እንጂ - ብዙም አይደለም ማለቱ ነበር (ሐዋርያት ሥራ 2፥ 14-20፤ 1 ጴጥሮስ 1፥ 20፤ 4፥ 7፤ 17)።

፲፪ኛ/ አንዴ እዚህ ጋር ቆም ብላችሁ እስቲ አስቡት!  እዚህ በ2ጴጥሮስ 3፥ 3 የተነገረው “የመምጣቱ ተስፋ!” በእርግጥ ስለ ኢየሱስ ዳግመኛ መምጣት ነውን?  ልብ አድርጉ አዲስ ኩዳን ያለ ልዩነት በየመጻህፍቱ ሁሉ በቀጥታም በተዘዋዋሪ የሚናገርለት ይህ የጌታ ዳግመኛ ምጽአት ርዕሰ ጉዳይ ምንም ቢሆን ጊዜው የተነገረና የተገለጠ ነው። ይህም ጊዜ የሐዋርያቱ ዘመን፣ ያ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን መሆኑ አያጠራጥርም። ያኔ ደግሞ ዛሬ መጻኢያን የሚያስቡት አይነት ጥፋት ግዑዝዋ ፕላኔት ምድር ላይ የደረሰ ነገር የለም። በርካታ መጻኢያን ግን ዛሬም ድረስ ግዑዙ አለም ቡን ብሎ ስላልጠፋ፣ ወይም ሲጠፋ ስላላዩ እርግጠኛ ሆነው፣ ጌታ በ70 ዓ.ም አልተመለሰም! ሲሉ ይደመጣሉ፤ እኛ ግን የለም “ጌታ እንደ ተስፋ ቃሉ በፍርድ ተመልሷል” በሚል እርግጠኝነት ቆመናል። ይህን ያህል እርግጠኛ ለመሆን የሚያስፈልገው የጌታን ቃል ማመን ብቻ እንጂ ይህ አለም ሲቃጠል ማየት አይደለም። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ለማብራራት የሚሄዱቡት የተለያዩ መንገዶች አሏቸው።  አንዳንዶቹ ይህ ጥቅስ ስለ “ዳግመኛ ምጽአት” አይደለም ሲሉ በድፍረት ይክዳሉ።  ሌሎች ደግሞ ይህንን ጥቅስ ከዐውደ-ምንባቡ ይነጥሉና የቀረውን የምዕራፉን ክፍል ብቻ ባለፈው ታሪክ ውስጥ እንደተፈጸመ በማሰብ የዚህን “የፍጥረተ አለም ፍጻሜ” ግን ገና ወደፊት ላለ መጻኢ ዘመን ሊለጥጡትና ሊያሻግሩት ይፈልጋሉ። ይህንንም ባደረጉ መጠን ቃሉ የተነገራቸውን በኩረ ተደራስያን አግልለው የሌለና ያልተባለ ነገር ለማመንና ለመጠባበቅ ይገደዳሉ።  ሌሎቻችን ደግሞ በዚህ ክፍል የተነገረው የኢየሱስ “መምጣት” በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካለው ተደጋጋሚ የእግዚአብሔር “መምጣት” ጋር የሚመሳሰል “ለፍርድ መምጣት” እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተን እንናገራለን። ያም ሆነ ይህ፣ ጴጥሮስ በቅርቡ ይሆናል ሲል በሚያነሳው ማሳሰቢያ “ለዘባቾች” ከሰጠው ማስጠንቀቂያ በግልጽ የሚታይ አንድ ነገር አለ። በዚያን ዘመን ከ70 አ.ም በፊት የነበሩ አንዳንድ ዘባቾች (2ጴጥሮስ 3፥ 3) ኢየሱስ በትውልዳቸው መጥቶ ቤተ መቅደሱን እንደሚያፈርስ በገባው ቃል መሰረት (ማቴዎስ 24፥ 1-3፤ 29-34)፣ ቃሉን አክብሮ አልመጣም ሲሉ ክርስቲያኖች በነበራቸው ተስፋ ላይ ያፌዙና ይሳለቁ ነበር። ጴጥሮስ ግን “ጌታ የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም” (2ጴጥሮስ 3፥ 9) በማለት ይመልሳል።  ጴጥሮስ እነዚያ በክርስቲያኖች ተስፋ ላይ ይሳለቁ የነበሩትን ሰዎች እያስጠነቀቀ፣ ጌታ ኢየሱስ አንዳንዶቹ በሕይወት እያሉ በእስራኤል ላይ ለመፈጸም የገባውን የፍርድ ቃል ቸል ብሏል ብለው በማመን ስህተት እንዳይሠሩ በጥብቅ እየነገራቸው ነበር (ማቴዎስ 10፥ 15-23፤ 16፥ 27-28፤ 26፥ 64፤ ራእይ 1፥ 1-3፤ ወዘተ.) ባለቤቱ ተኝቶ ሳለ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣበት” በነዚያ ፌዘኞች ላይ ሳያስቡትና ሳይዘጋጁ “የጌታ ቀን” እንደሚመጣባቸው በማሳየት በማያሻማ መንገድ ፌዘኞችን አስጠንቅቋል። ሌሎችም የአዲስ ኪዳን ማስጠንቀቂያዎች፣ ለምሳሌ ማቴዎስ 24፥ 34-43፣ 1ተሰሎንቄ 5፥ 2-4፤ ራእይ 16፥ 15፤ 22፥ 6-20 በዚሁ መንፈስ የቀረቡ ነበር።  በክፍሉ ውስጥ የተጠቆመው የመዘግየት ሃሳብ ወይም “ዝግታ” ግን በዚያ የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ለነበሩ ሰዎች “ሁሉ ወደ ንስሃ” ይመጡ እና ከጥፋት ይድኑ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን ትዕግስት ማሳያ ብቻ ነው።

ማጠቃለያ፦

የብሉይ ኪዳን ነቢያት በትውልዳቸው ውስጥ በነበሩ ህዝቦችና ነገስታት ላይ ሊሆን ያለውን መልኮታዊ  ፍርድ ሲገልጹ፣ የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያንም እነርሱ የነበሩበትን  የመጨረሻውን ዘመን የፍርድ እውነታዎች ሲያመለክቱ ሁሉም በአንድ አይነት የአነጋገር ዘይቤ የኮስሞቲክ ነውጥ አዘል ቋንቋዎችን ይጠቀማሉ። ጴጥሮስም ወደፊት የሚመጣውን ጥፋት (እርሱም የኢየሩሳሌምን ጥፋት) ሲያመለክት በንግግሩ የጠፈር መነዋወጥ ቋንቋን መጠቀሙ ሊሆን ያለውን ጥፋት ምንነት እና ትርጉሙን ያጎላዋል እንጂ አያደበዝዘውም።  በእርግጥም የጴጥሮስ አፖካሊፕቲክስ ንግግሩ በኢየሩሳሌም ላይ ቀርቦ ያለውንና ፈጥኖ የሚመጣውን የፍርድ ትንቢት ይጠቁማል። ያኔም እርሱ ይህንን እየጻፈ ሳለ በኢየሩሳሌምና በህዝቡ ላይ ያ የሚያስፈራው የጌታ ቀን፣ እርሱም የመጨረሻው የፍርድ ቀን ፈጥኖ ሊገለጥ ከአድማሱ ላይ ቀርቦ ነበር፤ ስለዚህም:- “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።”  (2ጴጥሮስ 3፥ 10-13) ይላል። የጴጥሮስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ70 ዓ.ም. በሆነው በኢየሩሳሌም ጥፋት ነው። ጴጥሮስም ያንን በ70 ዓ.ም የሆነውን መለኮታዊ ፍርድ ለመግለፅ የተጠቀመበት የኮስሚክ ነውጥን የሚያንጸባርቅ ቋንቋ፣ ኃጢአት እና ሰይጣን በእግዚአብሔር አገዛዝ ላይ ያላቸውን የጠላትነት አቋቋም ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ እና ጽድቅን ለማንገስ የፍርድ ቀን በቅርቡ እንደሚመጣ ያሳየበት ነው።

በመጨረሻም ይህንን ጽሁፍ ሳጠቃልል፣ ምድር ትነዳለች ብለው ለሚያስቡ መጻኢያን አንዳንድ ቀላል ጥያቄዎችን ላንሳ፡- የሰው ልጆች መኖርያ ስለሆነችው፣ አንድ ቀን  ቡን ብላ ስለምትቃጠል ፕላኔት ምድር ማሰብ እንደምን ተስፋና መጽናናት ሊሰጣችሁ ይችላል?  ጌታ ኢየሱስን ለማወቅና ለማመን ገና ጊዜ ስላልነበራቸው፣ ስለሚጠፉት ሰዎችስ አይገዳችሁምን? ገናስ ለአለምና ለዘላለም ይኖሩባት ዘንድ በሚፈጠሩ ኃጢአተኛ የሰው ልጆች ትውልድ ደህንነትስ ደስ አይላችሁምን? ለትውልድ ስለሚታደል ደህንነትስ  አይናችሁ ለምን ትሰስታለች? ይህስ የእናንተ አስተሳሰብ ምድርን ላለማጥፋት ቃል ከገባ (ዘፍጥረት 8፥ 21፤ 9፥ 11) የአምላክ ደስታና ታማኝነት ጋር እንዴት ይስማማል? እግዚአብሔር አምላክስ ቁጣውንና ፍትሑን ያረካ ዘንድ የውድ ልጁ የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት አልበቃውም ነበርን?

ግዛቸው

በግብዓትነት የተጠቀምኳቸው መጻህፍት፦

-አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የ1962 እትም፣ የ1997 ትርጉም(አዲሱ ትርጉም)፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም፣ ህያው ቃል፤

- የእንግሊዝኛ ትርጓሜዎች(NKJV; ESV;NLT)

-The NASB, Interlinear Greek-English New Testament

-TKB, The Kingdom Bible

-Theological Dictionary of the New Testament

- Hnegraaff, Hank; The Apocalypse Code

-Meek, Charles S; Christian Hope through Fulfilled Prophecy

Bruce. F. F; The International Bible Commentary






Thursday, January 4, 2024

የዘዳግም 28 እርግማን እና ታሪካዊ ፍጻሜው

ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ሁሉ ይደቅቃሉ

መግቢያ:-

ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ሁሉ የሚያገኛቸው አስፈሪውን የዘዳግም 28 እርግማን እና ታሪካዊ ፍጻሜውን እናጠናለን።

በዘዳግም 28: 15 ላይ እግዚአብሄር እስራኤልን ሲያስጠነቅቅ “ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል።” (ኦሪት ዘዳግም 28:15) ይላል::

በ70 ዓ.ም የሮማውያን ጦር ኢየሩሳሌምን ከበባት። ከዚያም በሮማውያን የጰኔሞስ ወር በአሥራ ሰባተኛው ቀን [ሐምሌ-ነሐሴ] በሙሴ ሕግ ከተወሰነው በተቃራኒው የዘወትሩ መሥዋዕት ተቋረጠ።  በጦርነቱም ወቅት በዘዳግም 28 ላይ ያሉት እርግማኖች በሙሉ ያለ ምንም ልዩነት በእስራኤል ላይ ደረሰባቸው። ያኔም ብዙ እስራኤላውያን በግዞት ወደ ግብፅ ተወስደዋል። በዘዳግም 28፥ 68 ላይ ባለውና “ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች ትሆኑአቸው ዘንድ ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ፤ የሚገዛችሁም አይገኝም።” ተብሎ በተነገረው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በማዕድን ማውጫዎች ጉድጓድ ውስጥ እንዲሠሩ ባሪያዎች ሆነው ተወሰዱ። 

የኢየሩሳሌም ከተማና በዙሪያዋ ያለው መላው የእስራኤል ምድር አይሁዳውያን ወደዚያ ምድር ከመምጣታቸው አስቀድሞ የተቀደሰ ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም ብዙ ሊቃውንት ቅዱስ ንጉሥና ካህን የነበረው መልከ ጼዴቅ ይገዛት የነበረችው ሳሌም፣ በኋላም ኢየሩሳሌም ተብላ በምትጠራው ምድር ከጥንት ነገሥታት አንዱ እንደነበረ ያምናሉ። ዘዳግም 9፥ 5-6 የእስራኤል ቀደምት አህዛብ ነዋሪዎች በክፋታቸው ምክንያት ከምድሪቱ እንደተወገዱ ይናገራል። እስራኤልም ያችን ምድር በጦርነት ወርሶ በምድሪቱ በኖረበት ዘመን ሁሉ የእግዚአብሔር የተመረጠ ሕዝብ የመሆን ክብር ብዙ ዋጋ አስከፍሎታል። አይሁዳውያን የአምላክን ሕግ ካልተከተሉ፣ በፈንታው ለእርሱ ታማኝ ለሚሆለት ሕዝብ ሥፍራውን ለመስጠት ልክ በከነዓናውያን ላይ እንዳደረገው እንዲሁ እግዚአብሔር የገዛ ህዝቡንም ከምድሪቱ ላይ እንደሚነቅላቸውና እንደሚያጠፋቸው አስጠንቅቋቸዋል።

በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የነበሩት አይሁድ መሲሑንና ተከታዮቹን ለመግደል በብዙ ያሴሩ ነበር። ጌታ ኢየሱስም እነዚህን የግድያ ሴራዎች ይገነዘብ ስለነበር በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች “ክፉና አመንዝራ ትውልድ” (ማቴዎስ 12:፥ 39) ሲል ጠርቷቸዋል። እነዚህ ቃላት በጆሴፈስ የአይሁድ ሮም ጦርነት ታሪክ ውስጥ:- “ኢየሩሳሌም እንደደረሰባት ያለ መከራ ሌላ ከተማ አልደረሰባትም ወይም እንደዚህ ትውልድ ያለ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ በየትኛውም ዘመን በክፋትና በሴራ የተሞላ ትውልድ አልተፈጠረም ነበር፤’’ በሚል ተስተጋብተዋል። እነዚያ ለኢየሱስ ሞት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ክርስቶስን ብቻ ገድለው አላቆሙም። ኢየሱስ ከተሰቀለም በኋላ እንኳ በሐዋርያት ሥራ 8፥ 1-3 መሠረት የኢየሩሳሌም ከተማ አይሁዶች ቅዱሳን ክርስቲያኖችን ማሳደዳቸውን ቀጥለዋል። ዩሴቢየስ ይህን ስደት ሲናገር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በመጀመሪያ እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው ገደሉት። በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጅና የዮሐንስ ወንድም የነበረውን ያዕቆብን አንገቱን በሴራ አስቆረጡ። እና በመጨረሻም ከአዳኛችን ዕርገት በኋላ በመጀመሪያ ለኤጲስቆጶስ መንበር በቅቶ እንደነበር ሲገለጽ የነበረው ያዕቆብም ሕይወቱን አጥቷል፣ የተቀሩቱ ሐዋርያትም በገዳዮች ሴራ የማያቋርጥ ስጋት ውስጥ ሆነው በስደት ከይሁዳ ተባረዋል።”

የእስራኤል ሕዝብ በአይሁድ ሮም ጦርነት ወቅት ሕጉን ተላልፈዋል፣ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያለው እርግማን ሁሉም በእነርሱ ላይ ተፈጽሟል።

በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ በማሴር የፈጸሙአቸው እነዚህ ወንጀሎች ሳይቀጡ አልቀሩም። በ70 ዓ.ም የሮማውያን ጭፍራ ኢየሩሳሌምን ከበባት። ከዚያም በጰኔሞስ (ሐምሌ-ነሐሴ) በአሥራ ሰባተኛው ቀን፣ የዘወትሩን መሥዋዕት “ሊያቀርበው የሚችል ሰው በመጥፋቱ ምክንያት” ቆመ። በዘጸአት 12 ላይ፣ እግዚአብሔር የፋሲካን በግ ሳያርድ የቀረውን የእያንዳንዱን (ግብጻዊ) ቤተሰብ የበኩር ልጅ ገደሏል። ከዘመናት በኋላም እስራኤላውያን የዘወትሩን መሥዋዕት ማቅረብ ካቆሙ በኋላ ተመሳሳዩ ዕጣ ደረሰባቸው።  በዘፀአት 12 ላይ እንደተገለጹት ግብፃውያን ሁሉ፣ ከሮም ጋር በተደረገው ጦርነት ወቅትም ብዙዎቹ የኢየሩሳሌም ሰዎች በፋሲካው በግ ምትክ ተገድለዋል። ክርስቶስ የፋሲካውን በግ ሆኖ እንደታረደላቸው መቀበልና ማመን ያልፈለጉ አይሁድ መሲሃቸውን ገድለው ደሙን ባፈሰሱበት የፋሲካ በአል እግዚአብሔር የእነርሱ ደም እንደ ጎርፍ ይፈስስ ዘንድ በጨካኞች እጅ ተዋቸው፤ ያኔ እርሱን ሊገድሉ ሲያሴሩ፣ ጲላጦስ እንኳ “እኔ ለሞት የሚያበቃ ምንም በደል አላገኘሁበትም ገርፌ ልልቀቀው” እያለ ሲለምናቸው፣ የለም፣  “ይህንን ስቀለው፣ ደሙም በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ሲሉ በእግዚአብሔር ፍርድ ደማቸው በምድር ላይ ይፈስስ ዘንድ ለዕልቂታቸው ፈርመው ነበር።

የኪዳኑ እርግማን:-

በዘዳግም 28፡15-68 ላይ እንደተገለጠው፣ እግዚአብሔር እስራኤልን በብዙ የእርግማን ማስጠንቀቂያ ተናግሯቸው ነበር። እነዚህ እርግማኖች ግን ባዶ ማስፈራሪያዎች አልነበሩም። አንድ ጊዜ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ በባቢሎን በተደረገ ግዞት፣ በኋላም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እስራኤል ከሮም ጋር ባደረጉት ጦርነት እግዚአብሔር በዚህ ቃል ኪዳን መሰረት የሚገባውን ፍርድ አድርጓል። በዘዳግም 28 ላይ የተዘረዘሩት እርግማኖች ሁሉ የግብፅ መቅሰፍት፣ ጨለማ፣ ድርቅ፣ ክሳት፣ ጭንቀት፣ ደዌ፣ እባጭ፣ ጥብሳት፣ የሚያቃጥል ሙቀት፣ እብደት፣ ግፍ፣ ተገድዶ መደፈር፣ ክህደት፣ ግራ መጋባት፣ በምርኮ መወሰድ፣ የሰውን  ሥጋ መብላት፣ ሕፃናትን መግደል፣ ጭንቀት፣ እረፍት ማጣት፣ የግብፅ ባርነት፣ ስደትና ሞት እስራኤላውያን ከሮም ጋር ባደረጉት ጦርነት የደረሰባቸው ነገር ሁሉ ነው። ይህም አልበቃ ብሎ በስደት በተሰደዱበት የአሕዛብ ምድር ለንቀትና ለመሳለቂያነት ብቻ ሳይሆን ለአህዛብ ጣኦታት እንደ መስዋእት እየታረዱ፣ ለነገስታቱና ለመኳንንቱ ክብረ በዓል ማድመቅያ ጭዳ ሆነው ይገደሉ ነበር።

በዘዳግም 28 እና በዘሌዋውያን 26 የተንነገሩ እርግማኖች በእጅጉ ተመሳሳይ ናቸው። በሁለቱም ምዕራፎች ውስጥ ያሉት እርግማኖች በሙሉ የተፈጸሙት በአይሁድ ጦርነት ወቅት ነው። ዘዳግም 28 እና ዘሌዋውያን 26 ምንም እንኳን አንዳንድ አስገራሚ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም፣ ተመሳሳይ የሆኑ እርግማኖችን ይዘረዝራሉ። ዘሌዋውያን 26፥ 18፣ 21፣ 23-24 እና 27-28 በ4 የተመደቡ ሰባት እጥፍ እርግማንን ይዘረዝራሉ። እነዚህ 4 ምድብ ሰባት እጥፍ ቅጣቶች በራእይ 6 ላይ ያሉትን ሰባቱን ማኅተሞች፣ በራእይ 8-10 የተገለጠውን ሰባቱን መለከቶች፣ በራእይ 16 የታየውን ሰባቱን ጽዋዎች እንዲሁም ምናልባትም በራእይ 10፥ 3-4 የተነገረውን ሰባቱን ነጎድጓዶች ይመስላሉ። [አንባቢዎች እነዚህን ክፍሎች በጥንቃቄ እንዲያዩ ይመከራል]። ከዚህም ባለፈ ዘሌዋውያን 26፥ 31 እግዚአብሔር “የእስራኤላውያንን መቅደሶች” እንደሚያፈርስ ይተነብያል። በእርግጥም ይህ የእርግማን ማስጠንቀቂያ በመጀመሪያውና በኋላም በሁለተኛው ቤተመቅደሶች ውድመት ወቅት ተፈጽሟል። በኢየሩሳሌም የነበረው የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ባቢሎናውያን ይሁዳን በወረሩበት ወቅት ፈራርሷል። ሁለተኛውም ቤተ መቅደስ ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ 24 ላይ ይፈርሳል ብሎ እንደተናገረው የፈረሰው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ሮማውያን እስራኤልን በወረሩበት ወቅት ነው። ዘሌዋውያን 26 ንግግሩን ሲያበቃ ለየት ይላል። በዘሌዋውያን 26፥ 42-45 እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ለማሰብ፣  እንደማይጥላቸው እና ወይም እንደማይጸየፋቸው።” ቃል ይገባል። እነዚህ ጥቅሶች በሮሜ 11፥ 25-31 በተነገረው የጳውሎስ ትንቢት መሰረት በእስራኤል ቅሬታ ተሃድሶ ፍጻሜውን አግኝቷል።

የእርግማኑ ተፈጥሮ:-

ዘዳግም 28፥ 15 ንግግሩን የሚጀምረው በማስጠንቀቂያ ነው፦

ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል።በከተማ ርጉም ትሆናለህ፥ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ።17  እንቅብህና ቡሃቃህ ርጉም ይሆናል። የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ርጉም ይሆናል። አንተ በመግባትህ ርጉም ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ርጉም ትሆናለህ። እኔን ስለ ተውኸኝ፥ ስለ ሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር መርገምን፥ ሽሽትን፥ ተግሣጽን ይሰድድብሃል። እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ከምትገባባት ምድር እስኪያጠፋህ ድረስ ቸነፈርን ያጣብቅብሃል። እግዚአብሔር በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኲሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ይመታሃል፤ እስክትጠፋም ድረስ ያሳድዱሃል። በራስህም ላይ ሰማይ ናስ ይሆንብሃል፥ ከእግርህም በታች ምድሪቱ ብረት ትሆንብሃለች። እግዚአብሔር የምድርህን ዝናብ ትቢያና አፈር ያደርጋል፤ እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል።”

አብዛኛዎቹ እነዚህ እርግማኖች የማይቀሩና የማይቀየሩ የጦርነት ከበባ ውጤቶች ናቸው።

የመጀመሪያዎቹን በርካታ እርግማኖች ካጤንናቸው በጦርነት ጊዜ ሰለሚከሰት ዘረፋ አይቀሬነት የሚጠቁሙ ናቸው። ከዚያም በቁ.22 ላይ፣ እስራኤል በበሽታ፣ በትኩሳት፣ በእባጭ ፣ በጥብሳት፥ በፈንገስ፣ በሻጋታ እና በማያባራ ቀጣይ የቸነፈር ሞት፣ በነፍስ ክሳት እንደሚቀጡ የናገራል። እንደነዚህ ያሉት ቀጣቶች በስፋት በጦርነት ከበባ ወቅት የሚከሰቱ ተደጋጋሚ ውጤቶች ናቸው። ከዚያም በቁጥር 52 ላይ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ባዕድ ሕዝብ እንደሚያመጣ መናገሩም ያን ያህል አያስገርምም። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ እስራኤል በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ስትወድቅ ለጥፋትዋ ያመጣባት ይህ ባዕድ ኃይል የሮምን ጭፍራ ነበር።

በአይሁድ ጦርነት ወቅት ሮማውያን በመላው የእስራኤል ግዛት ያሉ ከተሞችን በከበባው ወቅት ጥርቅም አድርገው ዘግተው ያዙ። በከበባው ወቅትም አንድ ጦር በቅጥሮች ተጠብቃ የተመልሸገች ከተማን ከቦ የጠላቱን ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እንዴት መቀነስ እንደሚቻለውና በአነስተኛ ድካምና ዋጋ ሊሰብረው የሚያስችለው አይነት  የጦርነት ስትራቴጂን  ፈጥሯል። አላማውም ረዘም ላለ ጊዜ በማስፈራራት እና ከተማይቱን በማሸበር እጃቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ነው። ልክ እንደ ማንኛውም የከበባ ኃይል፣ ሮማውያን ማንኛውንም ነገር ወይም ማንም ሰው ወደ ከተማይቱ እንዳይገባ ወይም ከከተማይቱ እንዳይወጣ በጥብቅ ከልክለው ነበር። ያኔም መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን በማጣት የተራቡ አረጋውያን ሽማግሌዎች እና አቅመ ደካሞች በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን እየተጠቁ፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በውሃ እጦት የሚሞቱ ቀዳሚዎች ይሆናሉ። ይባስ ብሎም በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ አይሁድ የሙታናቸውን በድን መቅበር የሚችሉበት ሰላምና ጸጥታ አልነበራቸውም።  ከዚህ የተነሳ በየጎዳናዎቹ ላይ የተከማቹ የበሰበሱ የሙታን በድኖች እነዚያኑ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በጭንቀት የተዳከሙ ሰዎችን ለከፋ በሽታ ያጋልጣሉ።

ቁ.22 ላይ የተጻፈውን እርግማን ፍጻሜ በሚሰጠው መልኩ በአይሁድ ሮም ጦርነት ወቅትም ድርቅ ነበር።

በቁጥር 22 ድርቅንም እንደሚያመጣ ያስጠነቅቃል። ኢየሩሳሌም በተከበበች ጊዜ ጆሴፈስ ከቅጥሩ ፊት ለፊት ቆሞ የአገሩን የእስራኤልን ሰዎች በሰላም እጅ እንዲሰጡ ተማጽኗቸው ነበር። ጆሴፈስ በዚህ የተማጽኖ ንግግሩ ላይ ቲቶና ሮማውያን ለከበባ ከመምጣታቸው በፊት በምድሪቱ ላይ ያጋጠመውን ከባድ ድርቅና ረሃብ ለወገኖቹ አስታውሷቸዋል። በመቀጠልም በብዛት የሚፈስሱት እነዚሁ የውኃ ምንጮችና የውሃ ጉድጓዶች በሮማውያን ይዞታ ስር በመሆናቸው እስራኤል በጥም እየተሰቃየ ጠላቶቻቸው ግን የአትክልት ቦታዎቻቸውን ለማጠጣት ሊጠቀሙባቸው ችለዋል። ተከታዩ ምንባብ የዚህን ከበባ ውጤት ያመለክታል።

እግዚአብሔር ከጠላቶችህ ፊት የተመታህ ያደርግሃል በአንድ መንገድ ትወጣባቸዋለህ፥ በሰባት መንገድ ከእነርሱ ትሸሻለህ ለምድርም መንግሥታት ሁሉ ድንጋጤ ትሆናለህ። ሬሳህ ለሰማይ ወፎች ሁሉ ለምድርም አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራቸውም የለም። እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በግብፅ ቍስል በእባጭም በቋቁቻም በችፌም ይመታሃል።” (ዘዳግም 28፥ 25-27)

ከበባ:-

ከተማ በከበባ ስር ወድቃ ሳለ የሙታንን በድን መቅበር አለመቻል የሚያስከትለው ተፈጥሯዊ ውጤት በአስፈሪ አራዊት መከበብና፣ በበሽታ አምጪ ተህዋስ መጠቃት ነው።

የቁጥር 26 እና 27 ንግግሮች በምክንያት እና በውጤት ሰንሰለት የተቆራኙ ናቸው። የሙሴ ሕግ ሙታን እንዲቀበሩ ያዛል። አይሁድ ግን ይህን ትእዛዝ ተላለፉ።  ይህን ማድረግ አለመቻል የሚያስከትለው መዘዝ ቸነፈር መሆኑ በቁ.27 ላይ ተቀምጧል።  የቲቶ ሠራዊት ገና ከመድረሱ አስቀድሞ ኢየሩሳሌም በሦስት መንገድ የከተማ ውስጥ አመጽና ሽብር በሚያደርጉ ዘራፊዎች የእርስ በርስ ጦርነት ተወጥራ ነበር። በዚህ ግጭት ወቅት የአይሁድ ዓመፀኞች ሙታናቸውን አልቀበሩም ነበር። ስለዚህም ሬሳ በየመንገዱ ተጥለቀለቀ። በመጨረሻም፣ የኢየሩሳሌም ከተማ ሰዎች ብዙዎቹን አስከሬኖች በከተማይቱ ቅጥር ላይ አውጥተው ሰቀሉት፣ ሬሳውም እንዲበሰብስ ወይም በአእዋፍና በአውሬ እንዲበላ በመተው በቁ.26 ላይ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ፍጻሜውን አገኘ።

ዕብደት:-

እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በድንጋጤም ይመታሃል። በቀትርም ጊዜ ዕውር በጨለማ እንደሚርመሰመስ ትርመሰመሳለህ፥ መንገድህም የቀና አይሆንም፤ በዘመንህም ሁሉ የተጨነቅህ የተዘረፍህም ትሆናለህ፥ የሚያድንህም የለም።” (ዘዳግም 28፥ 28-29)

ቁጥር 29 ላይ እንዲህ ይላል፡- “በቀትርም ጊዜ ዕውር በጨለማ እንደሚርመሰመስ ትርመሰመሳለህ፥”። ይህ ትንቢት ቃል በቃል ፍጻሜውን አግኝቷል። የኢየሱስን ስቅለት በገለጸበት ምንባቡ  ሉቃስ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- “ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥” (ሉቃስ 23፥ 44-45)። ስድስተኛው ሰዓት ማለት እኩለ ቀን ላይ ነው፣ በግምት ከሰአት ቀትር ላይ ነው። ይህ የቁ.29 ተአምራዊ ፍጻሜ የኤርምያስ 33፥ 20-21 ከፊል ፍጻሜንም ይወክላል። 

እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በድንጋጤም ይመታሃል” (ዘዳግም 28፥ 28-29)

በዚህ ተአምራዊ ጨለማ የተፈጠረው ዓይነ ስውርነትም ምሳሌያዊ ነው። ቁጥር 28 እና 29 የአይሁድን አመጽና ጦርነቱን ቀስቅሶ ያንን ሁሉ ጥፋትና ዕልቂት እንዲመራ እና እንዲያቀጣጥል ያደረገውን ድንቁርና ይገልፃል። ጆሴፈስ እንደገለጸው እነዚያ የአይሁድን ዓመፅ ይመሩ የነበሩ መሪዎች እንደ እነርሱም ሁሉ ደናቁርት ለሆኑ ለብዙ ሰዎች ጉቦ እየሰጡ ወይም በሆነ መንገድ ነቢያት መስለው እንዲታዩ ያባብሉና ያስገድዷቸው ነበር። ከሮም ጋር በተደረገው ጦርነት ወቅትም፣ ሕዝቡን ለማታለልና እንዲከተሉአቸው ለማድረግ አምላክ እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው ነፃ እንደሚያወጣቸው፣ እነርሱም ለዚህ እንደተቀቡና እንደተመረጡ እንዲተነብዩላቸው መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። እነዚህ ትንቢቶች ግን ውሸት መሆናቸው ተረጋግጧል። ከትንቢቶቹ በተቃራኒው የሮማውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን በመጨረሻ ድል አደረጉ፤ ጆሴፈስ ሲጽፍ “በከተማዋም ውስጥ አስከሬን ያልነበረበት ቦታ አልነበረም፤ ነገር ግን [ከተማዋ] በረሃብም ሆነ በዓመፅ በተገደሉት ሰዎች ተሸፍናለች።” ይለናል። ከዚያም ጆሴፈስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:

“ስለዚህ እነዚህ የተጨነቁ ምስኪን ሰዎች በእነዚህ አታላዮች እና እራሱንም እግዚአብሔርን በካዱ ኃሰተኛ ነብያት እየተነዱ ነበር፤ እነርሱም በግልጽ ይታዩ የነበሩትን የጥፋት ምልክቶች ሳይከታተሉ ወይም ከፊት ለፊታቸው የሚጠብቃቸውን ጥፋት በተገቢው መንገድ ዋጋ ሳይሰጡ፣  በግልጽ ይተነብዩ ነበሩ። ነገር ግን ዓይን እንዳላቸው ሰዎች ሳይሆን፣ ዓይን እያላቸው ሳያዩ ወይም ሊያዩበትና ሊያስተውሉ የሚችሉበት አእምሮ ሳይኖራቸው፣ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ያወረደባቸውን የእርግማን መዓት ልብ አላሉም”  [አጽንዖተ እኔ]

ከፍ ሲል ከጆሴፈስ ከተጠቀሰው ሃሳብ በኋላ “በግልጽ የታዩት ምልክቶችም ወደፊት ሊመጣ ስላለው ጥፋት በግልጽ የሚናገሩ ምልክቶች” ነበሩ።  ከእነዚ ምልክቶች መካከል አንዱን ሮማዊው የታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ እንዲህ ሲል ዘግቦታል:- “በሰማይም ላይ ውጊያ የሚያደርጉ ጭፍሮችና የሚያብረቀርቅ የጦር ዕቃ ራእይ ታየ።” ይህ ትዕይንት አይሁዶች በመቃቢያን 5፥ 1-4 ላይ ያለውን ተመሳሳይ ክስተት ያኔም በማቃቢያን ጦርነቶች ድል ከማድረጋቸው በፊት የነበረውን ሁኔታ አስታውሷቸዋል። ቀነናውያን በዚህ ትዕይንት መሲሑ በቅርቡ እንደሚገለጥ የሚጠቁሙ ምልክቶችና በሮማውያን ጨቋኞቻቸው ላይ ድል እንደሚቀዳጁ ገምተው ሊሆን ይችላል።  ይህ ምልክት ግን እንቅፋት ነበር።  ምልክቱን ተከትሎ የወረደባቸው መዓት እንጂ የተጠባበቁት እንዲህ ያለ ድል አልመጣላቸውም።  በሰማይ ላይ በታየው በዚህ ምልክት የተሳሳተ ትርጉም የተነሳ በተፈጠረ ግራ መጋባት፣ እነዚያ የአይሁድ ቀነናውያን በሁሉም የተቀደሰ ታሪካቸው ውስጥ አይተውት ወደማያውቁት  እጅግ አሳዛኝ ወደሆነው ዘግናኝ የዕልቂት ጦርነት “በእብድ ወኔ” ተንቀሳቅሰዋል።

እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በድንጋጤም ይመታሃል። … በዘመንህም ሁሉ የተጨነቅህ የተዘረፍህም ትሆናለህ፥ የሚያድንህም የለም” (ዘዳግም 28፥ 29)

በቁ 28 ላይ የተነገረውን የእርግማን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ በሚሰጠው መልኩ የቀነናውያንን እብደት አስመልክቶ ጆሴፈስ ሲገልጽ፣ የሚከተለውን ይላል፦ “የዓመፀኞቹ እብደት ከረሃባቸው ጋር ተጨምሮ፣ ሁለቱም ሰቆቃቸውን በየቀኑ ይጨምሩት ጀመር”። ይህ እብደት እና  የምግብ እጦት ወደ ቀጣዩ ቸነፈርና ዘረፋ አመራ። 

ጆሳፈስ በታሪክ ዘገባው የነዚያ የአይሁድ ሕዝብ  ውንብድንና ዝርፊያ በውስጣቸው ከሞላባቸው ንጥቂያ የተነሳ የአጋንንትን ባህሪይ እንዳንጸባረቁ ጽፏል፤ በዚህ አይነቱ የከተማ ቀውስ ውስጥ በቀጥታና ፊት ለፊት በሆነ የሰዎች ክፋት አጋንት እንደተወከሉ እናያለን። ስለዚህም፣  ‘’ይህ አሁን ያለው የህዝብ ዓመጽ ከሌላ ስውር ኃይል የተወለደ አመጽ ስለሆነ ልክ ሃይለኛና ክፉ ሆኖ እየጨከነ እንደሚመጣ፣ ካገኘበትም ሁሉ የሚበላውን ምግብ እንደሚፈልግ ቁጡ አውሬ፣ አሁን የገዛ ሥጋውን ወደ መብላት እየወደቀ ነው፡፡‘’ ይላል።

ተመልከቱ ጆሴፈስ ምን እንደሚል፦ 

‘’ከተማይቱ በሁሉም አቅጣጫ በጦርነት ተጠምዳ ሳለ፣ ከነዚህ ክፉ ሰዎች የህዝብ አታላይነት የተነሳ፣ በመካከላቸውም ያሉ የከተማይቱ ሕዝብ፣ ፣ በትንሹ እንደተቆራረጠ አካል አይነት ነበሩ፡፡ በእድሜ የገፉ አረጋውያን ወንዶችና ሴቶች ከውስጥ በተነሳ ሽብር ምክንያት እንዲህ ባለ ጭንቀት ውስጥ ነበሩ፣ ከዚህም የተነሳ በአገሩ ውስጥ ካለው መራር ሁኔታ እንዲያድኑአቸው የሮማውያንን መምጣት እየተመኙ ከውጪ የሚመጣውን ጦርነት በጽኑ ተስፋ ያደረጉት ነበር፡፡ ዜጎች ራሳቸው እጅግ አስጨናቂ በሆነ ሽብርና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነበሩ‘’ ይላል። በመቀጠልም “የነዚያ እርስ በርሳቸው የሚዋጉ ሰዎች ሁከት፣ በቀንም ሆነ በማታ የማያቋርጥ ነበር፤ ነገር ግን የነዚያ የሚያለቅሱ ሰዎች ሰቆቃ የሌላውን ሰው የሚበልጥ ነበር፤ ሰቆቃቸውንና ሃዘናቸውን ለማስወገድና ለመተው ምንም አይነት አጋጣሚ ፈፅሞ አልነበረም፣ ምክንያቱም አደጋዎቻቸው ያለመቋረጥ አንዱ በሌላው ላይ እየተፈራረቁ ይመጡ ነበርና፡፡ እንዲሁም ደግሞ ጥልቅ የሆነ የጭንቀት ጩኸት እያሰሙ ውጫዊ ጩኸታቸው የተቃወሰ ነበር፤ ነገር ግን ውስጣዊ ጭከናችውን ለመደበቅ በፍርሃታቸው ተጨንቀው፣ በለቅሶ አፋቸውን ለመክፈት ሳይደፍሩ በውስጣቸው ይሰቃዩ (በግሪክ ebasanizonto፣ ማለትም ልክ በራዕይ 9÷ 5 ላይ እንዳለው አይነት ስቃይ) ነበር፡፡ ሁሉም ሰው በራሱ ተስፋ ቆርጦ፤ በህዝቡ አመጽ ተሳታፊ ያልነበሩት ሰዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚደመሰሱ እርግጠኛ ሆኖ ከመጠበቅ ውጪ፤ ሌላ ምንም ከፍ ያለ ፍላጎት ስለምንም ነገር አልነበራቸውም፤ ነገር ግን ራሳቸው አመጸኞቹ ደግሞ እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ፣ በተገደሉት ሬሳዎች ላይ እርስ በርሳቸው አንዱ በሌላው ላይ ተደርቦ በሚወድቅበት ጊዜ፣ ከነዚያ ከእግራቸው በታች ከረገጡአቸው የሙታን በድን፣ እንደገና የባሰ አስፈሪ አውሬ ሆነው በባሰ ጭከና ይታያሉ፡፡ በነሱ ላይ በጠላትነት እንደቆመ የሚያስቡትን ማንኛውንም ሰው፣ በዚህም ጉዳይ ምንም አይነት ማስረጃ ካገኙ ያለምህረት ይገድሉታል፣ የትኛውንም የማሰቀያ ዘዴ ወይም ጭቃኔ ሁሉ ይፈፅማሉ‘’ይላል፡፡ 

ጆሴፈስ ትረካውን በመቀጠል ስለ አንዱ የአመጹ መሪ እንዲህ ይላል፦ “የግስችላው ዮሐንስ በመባል የሚታወቀው አንዱና ዋነኛው የዓመጹ መሪ ‘መላው ሃገሩን በአስር ሺህ በሚቆጠር ዓመጽ የሞላው ሲሆን፣ እንዲህ ያለ በተፈጥሮው ከበቂ በላይ የደነደነና  በእግዚአብሔር ላይ ያመፀ ክፉና ተንኮለኛ ሰው መቼም አልነበረም።‘’ ስለመሪዎቹም “እነዚህ የህዝቡ መሪዎች እኛ ነን ያሉ ሰዎች ከሚከሰሱበት ከክፋታቸው ንሰሃ መግባት የማይችሉ ናቸው፣ (ከራዕይ 16÷ 9 ፣ 11 ጋር አነፃፀሩት) እነዚህም ነፍሳቸውን ከስጋቸው የነጠሉ ጨካኞች፣  ምስኪኑ ህዝብ የሌላ መንጋ እንጂ የራሳቸው ያልሆነ ያህል የቆጠሩአቸው ጨካኝ እረኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፉ ሰዎች ነፍሳቸውን የሚነካ ምንም ስሜት፣ ሥጋቸውንም የሚጎዳ ምንም ሕመም የለባቸውም፤ ውሾች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሙታንን በድን የሚገነጣጥሉ ናቸቅ፤ ወህኒ ቤቶችንም ታመው በተሰቃዩ ሰዎች የሚሞሉ እስከሆኑ ድርስ እነዚህ ምን ሰብአዊ ስሜት አላቸው?” ሲል ይጠይቃል።

ዘረፋ:-

ቁጥር 29 ላይ የተጻፈው “ከቀን ወደ ቀን ትጨቆናላችሁ ትዘረፋላችሁም” ማለት ነው።  ይህንን ጥቅስ ፍጻሜ በሚሰጠው ልክ ጆሴፈስ በዘገባው እንዲህ ሲል ጽፏል፦

[ዘራፊዎቹ ቀነናውያን] በከተማ መካከል በሩ የተዘጋ ቤት በሚያዩበት ጊዜ በነዚያ ቤቶች ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚበሉት አንዳች ምግብ እንዳላቸው  የሚያውቁበት ምልክታቸው ነበር። በሮቹንም ሰብረው በመግባት ወደ ውስጥ ተንደርድረው እዩገቡ፥ የቤተኞቹን ምግብ ከጉሮሮአቸው ላይ አንድም ሳያስቀሩ ይነጥቋቸውና በኃይል ይወስዱባቸው ነበር። ምግባቸውን ሸሽገው የሚይዙ አዛውንቶችም ይደበደቡ፣ ሴቶቹም በእጃቸው ያለውን ነገር ቢደብቁ ይህንን በማድረጋቸው ፀጉራቸውን ይነጩባቸው ነበር። ለአረጋውያንም ሆነ ለአራስ ሕፃናት ቢሆን ምንም ዓይነት ርኅራኄ አያሳዩም፤ ነገር ግን በሕጻናቱ አፍ ላይ ያገኙትን ማንኛውንም ቁራሽ ለመንጠቅ ሕፃኑን ከመሬት ላይ ጥለው ወለሉ ላይ ይፈጠፍጡት ነበር። ወደ ውስጥ እንዳይገቡ በሮቻቸውን ዘግተው የታገሉና ዘረፋውን የተከለከሉ፣ መብታቸውን በግፍ የተነጠቁ መስሎ የታያቸውን ተቆርቋሪዎች አይራሩላቸውም ነበር፣ የያዙትንም ማናቸውንም ምግብ በጭካኔ ይነጥቋቸው ነበር።  እንዲሁም ምግብ የት እንደሚገኝና ማን እንደሸሸገ ለማወቅ አሰቃቂ የስቃይ ዘዴዎችን ፈጠሩ። እና እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦ የነዚያን የተጨነቁ ሰዎች የመራቢያ አካላቸውን በሹል እንጨት በመውጋት፣ ስለት ያላቸው እንጨቶችና ብረቶችን ወደ ውስጣቸው እንዲገባ በማድረግ ስቃያቸውን ያበዙባቸው ነበር። 

እንዲህ ያለ አሰቃቂ ሥቃይ የታየበት ከተማ ወይስ ዘመን፣ እንዲህስ ያለ በእርኩሰትና በአመጽ የተሞላ ትውልድስ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ይኖር ይሆንን? ጆሳፈስ ይቀጥላል፡- የአመጸኞቹ እብደት ከረሃባቸው ጋር አብሮ ያድግ ነበር፣ ሁለቱም አይነት አስጨናቂ ነገር በየቀኑ እየጨመረ ይቀጣጠል ነበር፤ በግልፅ የሚገኝ የእህል አይነት የትም ቦታ አልነበረም፣ ነገር ግን ዘራፊ ወንበዴወቹ ከአንዱ ወደ አንዱ እየተሯሯጡና እየተጣደፉ በየሰው ቤት እየገቡ ይፈተሻሉ፣ ከዚያም አንዳች ነገር ካገኙ ያገኙባቸው ሰዎች ሌላ የደበቁት እህል እንዳለ ስለሚያስቡ ያሰቃዩአቸዋል፣ ከካዱአቸውም ያሰቃዩአቸዋል፣ ፈልገው ካጡባቸውም የባሰ ያሰቃዩአቸዋል (በግሪክ basanizo በራዕይ 9÷ 5 እንዳለው)፣ ምክንያቱም ሌላም የተሸሸገ እህል እንዳለ ስለሚመስላቸው ነው፡፡ የተለያዩ አሰቃቂ የማሰቃያ መንገዶችን ይፈለስፋሉ /basanismos፣ የ basanizo noun form ነው / ሌላ ምንም አይነት ምግብ ለማግኘት ሲሉ የማሰቃያ መንገዶችን የሚጠቀሙት እነርሱ ራሳቸው በራባቸው ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ይህንን የሚያደርጉት ዝርፊያ አስፈላጊ መስሎ ስለታያቸው፣ ደግሞም እብደታቸውን ጠብቀው ለማቆየት ስለፈለጉ ነው፡፡

ይህ በሃይለኛው የክፉ አጋንንት ሞገድ አመልካች ይመስላል፡፡ ይህም በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ክርስቶስ ሲናገር፦ “ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም። በዚያን ጊዜም፦ ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።” (ማቴዎስ 12÷ 43_45) እንዳለው ነው። “ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል” (ማቴ 12÷ 43_45) ሲል የተናገረውን ምሳሌ በእርግጠኝነት ይህ ታሪክ ፍጻሜን ይሰጠዋል፡፡ ‘ትውልድ‘ የተባለው እርሱን የካደው ትውልድ ነው፣ በእርግጠኝነት እንደምናውቀው ኢየሱስ እና ሐዋርያቱ በየምኩራቡ፣ በከተማዎችና በመንደሮች በአገልግሎታቸው ከአይሁድ ላይ የሚበዙ አጋንንትን አስወጥተው ነበር፣ አሁን ግን የሆነው ከበፊቱ የከፋ ነው፣ በትውልድ ላይ ሰባት እጥፍ ጋኔን ገባ ማለት እንዴት ከባድ ነገር ነው! በርካቶቹ አይሁድ መሞት ይመኙ ነበር ነገር ግን በብዙ ይሰቃዩ ነበር (ራዕ 9÷ 6)፣ ‘’በነበረው ረሃብ እጅግ ይሰቃዩ የነበሩት ሰዎች ለመሞት ይመኙ ነበር፤ እነዚያ ቀደም ብለው የሞቱ ሰዎች ደግሞ እድለኛ እንደሆኑ ይቆጠራሉ፣ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን አሰቃቂ ነገር ለመስማትም ሆነ ለማየት በህይወት መኖር ስላልቻሉ ነው፡፡‘’

ጭቆና:-

የፍሎረስ ጭቆና አይሁዶችን ከሮም ጋር ወደ ጦርነት እንዲገቡ የገፋፋቸው መንስኤ ነበር። (ዘዳግም 28፥ 29)

እንደ ጆሴፈስ ከሆነ የቁ.29 ጭቆና፣ የአይሁድ አመጽና የጦርነቱ ዋነኛ መንስኤ ነው።  ዓመፁ ከመቀስቀሱ በፊት የይሁዳ ገዥ የነበረው ሮማዊው ጌሲየስ ፍሎረስ በአይሁድ ሕዝብ ላይ ባደረገው ግፍ ዝነኛ ነበር።  ይህን እውነታ በመጠቀም አንድ ሄለናዊ የአምልኮውን ስፍራ በእርኩሰት ለማሳደፍ በአይሁድ ምኩራብ ደጃፍ ላይ ወፎችን አምጥቶ ሠዋ።  በፈጸመው በዚህ የሚያስቆጣ ድርጊቱ የተበሳጩት አይሁዶች ጉዳዩን ይዘው ለዐቃቤ ሕጉ አቤቱታ አቀረቡ።  ፍሎረስም ክሱን ለመስማት ስምንት መክሊቶችን በክፍያ መልክ ከተቀበለ በኋላ ቅሬታውን ለመፍታት ፈቃደኛ አልሆነም፣ ይልቁንም ጥያቄ ያነሱትን ሰዎች ወደ ወህኒ አገባቸው።  የኢየሩሳሌምም ሰዎች በዚህ ተናድደው ነበር።  ፍሎረስ ግን ወታደሮቹን ልኮ የላይኛውን ገበያ እንዲዘርፉ እና በየመንገዱ የሚያገኙትን ሁሉ በሰይፍ እንዲገድሉ በማድረግ ለአይሁድ ቁጣ ምላሽ ሰጠ።  በየመንገዱ ተይዘው የታሰሩትም ተገርፈው እንዲሰቀሉ ተደርጓል። ከዚያም የአይሁድ ጦርነት ተጀመረ።

ሚስት ታጫለህ፥ ሌላም ሰው ከእርስዋ ጋር ይተኛል፤ ቤት ትሠራለህ፥ አትቀመጥበትም፤ ወይን ትተክላለህ፥ ከእርሱም አትበላም። በሬህ በፊትህ ይታረዳል፥ ከእርሱም አትበላም፤ አህያህ ከእጅህ በግድ ይወሰዳል፥ ወደ አንተም አይመለስም፤ በግህ ለጠላቶችህ ትሰጣለች፥ የሚያድንህም አታገኝም።  ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፥ ዓይኖችህም ያያሉ፥ ሁልጊዜም ስለ እነርሱ ሲባክኑ ያልቃሉ፤ በእጅህም ኃይል ምንም አይገኝም።  የምድርህን ፍሬ ድካምህንም ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ አንተም ሁልጊዜ የተጨነቅህ የተገፋህም ትሆናለህ። ዓይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ። እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በክፉ ቍስል ጕልበትህንና ጭንህን ከእግርህ ጫማ እስከ አናትህ ድረስ ይመታሃል። እግዚአብሔርም አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤ በዚያም ሌሎችን የእንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካለህ። እግዚአብሔርም በሚያገባህ በአሕዛብ መካከል ሁሉ ድንጋጤ ምሳሌም ተረትም ትሆናለህ።” (ዘዳግም 28፥ 30-37)

ይህ ሁሉ ውርጅብኝ ወረራን መቀልበስ ያለመቻልና በጦርነት የመሸነፍ ተፈጥሯዊ መዘዝ ነው። ከቁጥር 30 እስከ 35 ወረራው ያስከተለውን በጦርነቱ ሽንፈትን መከናነብ  ያስከተለውን አስከፊ መዘዝ ይኸውም በግዞት መወሰድን ይገልጻል።  በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት፣ ውድ የሆነው ንብረት ሁሉ - ሚስት ብትሆን፣ ልጆችም ቢሆኑ - ተዘርፈው በግዞት ይወሰዳሉ። እነዚያ ከአይሁድ ሮም የጦርኑት ዕልቂት የተረፉ የእስራኤል ሰዎች ምርኮኛ ሆነው ወደ ባዕድ ምድር ተበተኑ።  ከምርኮኞቹም መካከል የአይሁድን ተቃውሞ የመሩት ሁለቱ ዮሐንስ እና ስምዖን በቁጥር 36 ላይ “እግዚአብሔርም አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤” በሚል የተገለጠው የእርግማን ትንቢት ፍጻሜውን  በእነርሱ ላይ አግኝቷል።

በቁጥር 37 ላይ እንደተተነበየው እነዚህ ምርኮኞች ተግዘው በተወሰዱበት ሃገር ሁሉ ለአሕዛብ መሳለቂያና መሳቂያ ሆኑ።  የኢየሩሳሌም ከተማ ቅጥሮች ተሰብረው በመጨረሻ በጦርነቱ ከተደመሰሰች በኋላ 97,000 የሚሆኑ አይሁዳውያን በመላው ሮም በግዞት ነበሩ።  በዚያም በሰይፍ የወደቁ፣ በአውሬ የተበሉ፣ ወይም በግላዲያተር የትግል ሜዳ ሊፋለሙ በባርነት የተሸጡ፣ ወይም እንዲሁ ለነገስታቱና ለመኳንንቱ ክብረ በዓል ለደስታቸው የተገደሉ ሆኑ።  የሮም ጎዳናዎችም የአይሁድን ሽንፈት በሚያሳዩ ታላላቅ ትርኢቶች ተሞሉ፣ ይህም ትርኢት ሲካሄድ ብርቱዎችና ጠንካራ ሆነው የታዩ ምርኮኞችን ለማዋረድ በሰንሰለት ታስረው በሮም ጎዳና ላይ እንዲጓዙ ይገደዱ ነበር።  ይህ ክብረ በዓል ሲያበቃም በመላው የሮም ግዛት ውስጥ ያሉ የአይሁድ ምርኮኞችን ሽንፈት የሚያሳዩ የመገበያያ ሳንቲሞች እንዲቀረጹ ተደርጓል፣ ስለዚህ የአይሁድ ምርኮኞች በሮማውያን መሸነፋቸውን የሚያሳይ ምልክት ያለበትን የተቀረጸውን የቄሳርን ምስል ሳይይዙ መግዛትም ሆነ መሸጥ እንዳይችሉ የሚደነግግ ሕግ በንጉሣዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጓል።

አንዳች ማጣት:-

እጅግ ዘር ወደ እርሻ ታወጣለህ፤ አንበጣም ይበላዋልና ጥቂት ትሰበስባለህ። ወይን ትተክላለህ ታበጀውማለህ፤ ትልም ይበላዋልና ከእርሱ ምንም አትሰበስብም፥ የወይን ጠጁንም አትጠጣም። የወይራ ዛፍ በአገርህ ሁሉ ይሆንልሃል፤ ወይራህም ይረግፋልና ዘይቱን አትቀባም። ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይወለዱልሃል፤ በምርኮም ይሄዳሉና ለአንተ አይሆኑልህም። ዛፍህን ሁሉ የምድርህንም ፍሬ ኩብኩባ ይወርሰዋል።” (ዘዳግም 28፥ 38-42)

የአንበጣ፣ የትልና የኩብኩባ ሰራዊት ይመጣብሃል፣ ሁሉንም ያሳጣሃል። አንበጣዎች ወራሪውን ሠራዊት የሚያመለክቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተምሳሌት ናቸው።  ይህ ተምሳሌታዊነት በኢዩኤል ምዕራፍ 1 ውስጥ በጣም ግልፅ ሆኖ ቀርቧል፣ በራእይ 9፥ 19 ውስጥም ቢሆን ይህንን ተምሳሌታዊ ምልክት እናያለን።  ከርቀት ሆኖ በሰፊ ሜዳ ላይ ሰፍሮ የሚታይ ሠራዊት የአንበጣ መንጋን ይመስላል፤ እነርሱም እንደ አንበጣ በመንገዳቸው ላይ ያለውን ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ እምሽክ አድርገው ይበላሉ፣ አንዳችም አያስቀሩም። ይህ ደግሞ የምግብና የውሃ አቅርቦቶችን አሟጦ መጨረስ ብቻ ሳይሆን፣ በአብዛኛው በዛፎች የተሞላውን የአገሪቱን  የመሬት ገጽታ በመጨፍጨፍ ለከበባቸው የሚያገለግላቸውን እሳት እና የእሳት ድንጋይ ማስወንጨፊያ መሳርያዎቻቸውን  በብዛት ይገነቡበታል።  ይህም በአይሁዶች ጦርነት ውስጥ በግልፅ ታይቷል፡- “[የሮማው ጄኔራል ቲቶም] .  .  .  ሰፈሩን በሞላ በእሳት እንዲያቃጥሉ ለወታደሮቹ ፈቃድ ሰጥቷቸው፣ እንጨቶችን እንዲሰበስቡና በከተማይቱ ላይ የሚንጠላጠሉበትን መሸጋገሪያ እንዲሰበሰቡ አዘዞ ነበር ።  .  .  .  ስለዚህም ዛፎቹ ወዲያው ተቆረጡ፣ የከተማይቱም ዳርቻዎችም ራቁታቸውን ቀሩ።” ከቁጥር 38-42 ባለው የእርግማኑ ምንባብ ላይ፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን በአንበጣ መንጋ እንደሚቀጣቸው አስጠንቅቆ ነበር።  የራዕይ መጽሐፍም የዚህን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ በራዕይ 9፥ 21 ላይ ሲያመለክት የሮም ጭፍራን እንደ አንበጣ መንጋ በመግለጽ መዝግቦታል።

በባዕዳን መበለጥ:-

በአንተ መካከል ያለ መጻተኛ በአንተ ላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አንተም ዝቅ ዝቅ ትላለህ። እርሱ ያበድርሃል፥ አንተ ግን አታበድረውም፤ እርሱ ራስ ይሆናል፥ አንተም ጅራት ትሆናለህ።” (ዘዳግም 28፥ 43-44)

ፍሎረስ የተከተለው ፀረ-አይሁድ የሆነው አድሏዊ ፖሊሲው እና ሮም ከአይሁዶች ጋር በነበራት ጦርነት ወቅት በመላው አይሁድ ላይ ያደረሰችው ዝርፊያ ከቁጥር 43-44 የተጻፈውን ቃል ፍጻሜ ይሰጠዋል።

ከፍ ሲል እንደተብራራው፣ በ66 ዓ.ም ተቀስቅሶ ከነበረው ሕዝባዊ አመጽ አስቀድሞ የይሁዳ አቃቤ ሕግ የነበረው ሮማዊው ጌሲየስ ፍሎሩስ ያራመደው ግሪኮችን የመደገፍና አይሁዶችን የመቃወም ፖሊሲዎች ለአይሁድ ጦርነት በዋነኛነት መንስኤ ነበሩ።  ፍሎረስ በግዛቱ ለነበሩት አይሁዶች ግልጽ ጥላቻን እያሳየ በእስራኤል የነበሩትን ግሪኮች በድብቅ ደግፏል።  እዚህ ላይ በቁጥር 43-44 ያለው የእርግማኑ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ፍጻሜውን እንዳገኘ ማየት ይቻላል።  ይህ ዜጎችን እየናቁና እያዋረዱ ባዕዳንን ከፍ ከፍ የማድረግ ዝንባሌ ከጦርነቱ በኋላም ተባብሶ ቀጥሏል።  ሮማውያን የይሁዳን ግዛት ካወደሙ እና ብዙ አይሁዳውያንን ወደ ሮም ግዛት በግዞተኝነት ካፈለሱ በኋላ፣ በዚያ ለመኖር የተፈቀደላቸው ብዙዎቹ ለባርነት ተሸጡ።  ከዚህም በላይ ከግዛቱ የተውጣጡ የውጭ አገር ወታደሮችን ያቀፈው የሮማውያን ሠራዊትና ረዳቶቻቸው በጦርነቱ ወቅት በዘረፋ የያዙት ብዙ ምርኮ ስለነበራቸው “በሶርያ አንድ ፓውንድ ወርቅ ቀድሞ ከነበረው ዋጋ በግማሽ ይሸጥ ነበር።” ከተማይቱ ከወደመች በኋላ አሥረኛው ሌጌዎን በመባል የሚታወቀው የጦሩ ክፍልም በኢየሩሳሌም እንዲሰፍር ተደርጎ ነበረ። ስለዚህ ፍሎረስ የተከተለው የፀረ-አይሁዳውያን ፖሊሲዎቹና፣ በአይሁድ ጦርነት ወቅት የነበረው አይሁዳውያን በውጭ አገር ጠላቶቻቸው የተፈጸመባቸው ዘረፋ በቁጥር 43 እና 44 ላይ ያለውን ቃል ፍጻሜ ይሰጠዋል: “ያበድሩሃል አንተ ግን አታበድረውም

ጽኑ ራብ:-

የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማህ፥ ያዘዘህንም ትእዛዙንና ሥርዓቱን ስላልጠበቅህ፥ እስክትጠፋ ድረስ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይወርዱብሃል፥ ያሳድዱህማል፥ ያገኙሁማል። በአንተም በልጅ ልጅህም ላይ ለዘላለም ለምልክትና ለድንቅ ይሆናሉ። ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሐና በሐሤት አላመለክህምና፣ በራብና በጥማት በዕራቁትነትም ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህ ለጠላቶችህ ትገዛለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭናል።” (ዘዳግም 28፥ 45-48)

በኢየሩሳሌም ከበባ ወቅት በከተማይቱ የነበረው ረሃብ፣ ጥማት እና ድህነት የዘዳግም 28፥ 48 የእእግማን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜው ነው። ጆሴፈስ ከበባው ስላስከተለው ረሃብ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:-

ከዚያም ረሃቡ እድገቱን አስፍቶ ህዝቡን በየቤተሰባቸውና በየቤተሰቡ ይበላው ጀመር።  በየደርቡ ያለው ክፍልም በራብ የሚሞቱ ሴቶችና ሕጻናት ሞልተውት ነበር፤ የከተማይቱም መንገዶች በሽማግሌዎች ሬሳ ተሞልቶ ነበር።  ሕፃናቱና ወጣቶቹም እንደ ጥላ በገበያ ስፍራ እየዞሩ የሚላስ የሚቀመስ ፍለጋ ተንከራተቱ፥ ከመከራቸውም ብዛት የተነሳ በስፍራ ሁሉ ወድቀው ከራብ የተነሳ ስለሞቱ እሬሳቸው አብጦ አብጦ በየስፍራው ወደቆ ተጥሎ ነበር።  ታመው ለሞታቸው የሚያጣጥሩ ሌሎች ሰዎችም በዙሪያቸው ሞተው የወደቁ ሰዎች ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ እነርሱን መቅበር አልቻሉም። ደህነኞቹም ቢሆኑ ከሬሳዎች ብዛት የተነሳ፣ ሌሎችን ሲቀብሩ ብዙዎች መሞታቸውን አይተዋልና፣ ራሳቸውም እንዴትና መቼ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚሞቱ እርግጠኛ ባልሆኑበት ሁኔታ ይህንን ከማድረግ ተከለከሉ፣ ይልቁንም ቀባሪ ባያገኙም ለመሞት በሚሆን ቅድመ ዝግጅት ብዙዎቹ በከፈኖቻቸው ገብተው የሚሆነውን ይጠባበቁ ነበር።

ወረራ:-

እግዚአብሔር ቋንቋቸውን የማታውቀውን፥ ፊታቸው የደነደነውን፥ ሽማግሌውንም የማያፍሩትን፥ ሕፃኑንም የማይምሩትን ሕዝብ ንስር እንደሚበርር ከሩቅ አገር ከምድር ዳር ያመጣብሃል። እስክትጠፋ ድረስ የከብትህን ፍሬ የምድርህንም ፍሬ ይበላሉ፤ እስኪያጠፉህም ድረስ እህልን የወይንም ጠጅ ዘይትንም የላምህንና የበግህን ርቢ አይተዉልህም። በአገርህ ሁሉ ያሉ፥ ትታመንባቸው የነበሩ፥ የረዘሙ የጸኑም ቅጥሮች እስኪፈርሱ ድረስ፥ በከተሞችህ ደጆች ሁሉ ከብበው ያስጭንቁሃል፤ አምላክህም እግዚአብሔር በሰጠህ ምድር ሁሉ በደጆች ሁሉ ከብበው ያስጨንቁሃል።” (ዘዳግም 28፥ 49-52)

በቁ.52 ላይ ያለው ቃል ፍጻሜውን በሚያገኝበት መንገድ ሮማውያን የእስራኤልን ከተሞች በከበባ ውስጥ አአድርገው ነበር። ምንም እንኳን በቁጥር 51 ላይ በተጻፈው ቃል በአጭሩ ማተኮር ተገቢ ቢሆንም፣ በቁጥር 49-52 ያሉት የእርግማን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜዎች ግን አብዛኞቹ ቀደም ብለው ተብራርተዋል።  በዚህ ቁጥር የተገለጠው አንድ ግዙፍ ወራሪ ኃይል የምድሪቱን ፍሬ ከሚበላው የአንበጣ መንጋ ጋር እንዴት እንደሚመሳሰል በድጋሚ የሚያስታውስ ነው።  በሚቀጥለው ቁጥር፣ ይህ የባዕድ ጦር የተመሸገችውን የተስፋይቱን ምድር ከተማ በሙሉ ይከብባል ተብሏል።  በአይሁዶች ጦርነት ወቅት፣ የሮማውያን ጦር የእስራኤልን ግዛት በሙሉ የጎርፍ ውሃ ምድርን እንደሚከድን  ከተማይቱን ከበበ።  በተጨማሪም በቁጥር 49 ላይ የተጠቀሰውን ንስር ስናይ የሮም ኦፊሴላዊ ምልክት የንስር መልክ መሆኑን ልናስተውለው የሚገባን ነው። 

ሰው በላነት:- 

ጠላቶችህም ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር የሚሰጥህን የሆድህን ፍሬ የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። በአንተ ዘንድ የተለሳለሰና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ይኖር የነበረ ሰው በወንድሙ፥ አቅፋውም በምትተኛ በሚስቱ፥ በቀሩትም ልጆች ይቀናል፤ በደጆችህ ሁሉ ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሌላ ነገር የቀረው የለምና ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ለአንዱ አይሰጥም። በአንተ ዘንድ ያለችው የተለሳለሰችና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ትኖር የነበረችው፥ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ የእግር ጫማዋን በምድር ላይ ያላደረገችው ሴት፥ አቅፋ በተኛችው ባልዋ፥ በወንድና በሴት ልጅዋም፥ በእግርዋ መካከል በሚወጣው በእንግዴ ልጅ፥ በምትወልዳቸውም ልጆች ትቀናለች፤ በደጆችህም ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሁሉን ስላጣች በስውር ትበላቸዋለች።” (ዘዳግም 28፥ 53-57)

ከተማይቱ ተከብባ በነበረበት ወቅት፣ ረሃቡ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ አንዲት ሴት የራሷን ልጅ እስከ መብላት መድረሷን ጠቅሶ በመተረክ ጆሴፈስ በከተማይቱ ነግሶ የነበረውን አስፈሪ የመበላላት ተግባር ያመለክታል። ይህም በዘዳግም 28፥ 53-57 የተዘረዘረውን የእርግማን ትንቢት ፍጻሜ ይሰጠዋል።

ጆሴፈስ በምግብ እጦት ምክንያት በከከማይቱ ተፈጥሮ የነበረውን ተስፋ አስቆራጭ ግጭት በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- በከተማይቱም በራብ ከሞቱት ሰዎች ቁጥራቸው እጅግ የበዛና የደረሰባቸውም ሰቆቃ በቃላት ሊገለጽ የሚችል አልነበረም።  የትኛውም ዓይነት የሚቀመስ የሚላስ ነገር ምልክቱ በየትም ቦታ ቢታይ፥ ወዲያውኑ ፍጅቱ ይጀመራል፣ የሚዋደዱ ባልንጀሮችም እርስ በርሳቸው መጣላት ይጀምራሉ፣ እጅግም በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ሰው ሕይወቱን ለማቆየት በሚሆን ስጋት የሸሸጋትን ቁራሽ እርስ በርስ ይነጣጠቁ ነበር”። 

ሱልፒቲየስ ሴቬሩስ ሲናገር በከበበው መሃል የነበሩ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሬሳዎቻቸውን ይበሉ ነበር ይላል።

ከዚህም በላይ በ70 ዓ.ም. በነበረው የኢየሩሳሌም ከበባ ወቅት በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ሆነው መውጣትም መግባትም የተከለኩሉ አይሁድ እጅግ አስጸያፊ የሆነውን ነገር ሁሉ ለመብላት ይጎመጁና ደፋ ቀና እያሉ ነበር፣ የበሰበሰውን የሰውንም አካል እንኳ ቢሆን እንደ ምግብ ለመጠቀም አልተዉም ነበር።

በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ 6÷ 5-6 የተነገሩው የሦስተኛው ማህተም መፈታትና፣ በጉራቻው (በጥቁር) ፈረስ ላይ ያለው ጋላቢ መምጣት ይህን የመሰለ አስከፊ ረሃብ እንደሚመጣ በእርግማኑ ዝርዝር ውስጥ የተጠቀሰውን ትንቢታው ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ ይሰጠዋል።

ጥቁሩ ፈረስ ላይ የተቀመጠው የሚወክለው በአይሁድ ሕዝብ ጦርነት የተነሳ የሚቀሰቀሰውን ረሃብ ወይም ከፍተኛ የምግብ እጥረት እና ሞት ነው፡፡  የቀለሙ ጥቁረት የረሃብ ወይም የችጋር መገለጫ ነው፣ “ከሚያቃጥል ከራብ ትኩሳት የተነሣ ቁርበታችን እንደ ምድጃ ጠቈረ” (ሰቆቃው ኤርምያስ 5÷ 10) ይላልና።  ይህ በጥቁሩ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ጋላቢ በእጁ የያዘው ሚዛን አለው፡፡ ይህም በምድሪቱ የሚገኘውን የምግብ እህል የሚለካበት እንደሆነ ከክፍሉ እንረዳለን፡፡ ይህም ሰዎች በእጃቸው ያለውን የገዛ ራሳቸውን እንጀራ የሚበሉት እየቆጠቡና በሚዛን እየሰፈሩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ እግዚአብሄርም በእርሱ ላይ በማመጽ የሚበድሉ ከሆነ እንዲህ እንደሚሆንባቸው አስቀድሞ “የእህላችሁንም ድጋፍ በሰበርሁ ጊዜ፥ አሥር ሴቶች እንጀራቸውን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም።” ሲል ነግሮአቸዋል (ዘሌ 26÷ 26)፡፡ 

አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥”  (ራዕይ 6፥ 6)፤ ተመልከቱ፣ ዲናር የበርካታ የቀን ሰራተኞች አማካይ የቀን ገቢያቸው ነው፡፡ እንግዲህ የቀን ገቢውን ይዞ ከስራው ሲመለስ በዚያች ሊሸምት የሚችለው በእርቦ የተሰፈረች ስንዴን ወይም ገብስን ብቻ ነው፣ ይህም የአንድ ሰው የቀን ሬሽኑ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ቀኑን ሙሉ ሰርቶ የሚያገኛት ገቢ የራሱን ሆድ ብቻ እንኳ ለመሙላት የማትበቃ ናት፡፡ ቤተሰብን መመገብ የማይታሰብ ሲሆን፣ በያዛት አንዲት ዲናር እህል መሸመት ከፈለገ ማድረግ ያለበት ረከስ የሚለውን አሰርና ብጣሪ ብቻ መግዛት ነበር፡፡ 

ሮማውያን ከተማይቱን ከበዋት በነበረበት ጊዜ አይሁድ እጅግ አስከፊ በሆነ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነበር፡፡ ይህም በእህል መጋዘናቸው በቂ ምግብ ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፣ እንደውም የተወሰነ ጊዜ ሊያቆያቸው የሚችል ክምችት ነበራቸው፡፡ ሆኖም በከተማይቱ በተለያየ አቅጣጫ መሽገው እርስ በርሳቸው ይዋጉ የነበሩ ቡድኖችና የአመጹ መሪዎች አንዱ ሌላውን ለመጉዳት በሚወስዱት የእብደት እርምጃ የተቃዋሚያቸውን ጎተራ እና የእህል ክምችት በእሳት ያቃጥሉት ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ ምግብ እጅግ ብርቅና ሊገኝ የማይችል እስኪሆን ድረስ ሁኔታው እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ ነበር፡፡ ጆሳፈስ የሁኔታውን ዘግናኝነት ሲዘግብ ዋቢ አድርጎ ካቀረባቸው ገጠመኞች መካከል የገዛ ራሷን ሕጻን ልጅ በቶፋ ቀቅላ ስለበላች ሴትናና የምግብ ሽታ ጥርቷቸው ምግብ ፍለጋ ድንገት ወደ ቤቷ ለገቡ እና ምግብ እንድታቀርብላቸው ለጠየቋት የሮም ወታደሮች “እኔ ለዛሬ የሚበቃኝን ያህል ተስተናግጃለሁ፣ ከዚህ ለከፋ ቀን ያስቀመጥኩትን ወስዳችሁ ብሉ” ስትላቸው ቶፋውን ሲከፍቱት የተበላ የህጻኑን ግማሽ አካል አዩ ሲል  የገጠማቸውን ሁኔታ ይተርካል።  ይህም በዘዳግም 28 ÷ 53 ላይ የተጻፈውን ፍጻሜ የሚሰጠው ሲሆን፣ ከ2 ነገስት 6÷ 28 ጀምሮ ካለው ጋርም የሚነጻጸር ነው። እነዚያ አረማውያን ወታደሮች ግን በሴትየዋ ቤት ያዩት አስፈሪ ተግብር ከፈጠረባቸው ድንጋጤ የተነሳ ፈርተው በፍጥነት ቤቷን ለቀው በሩጫ ወጥተው መሄዳቸውን ጆሴፈስ ይተርካል፡፡  ጌታችን ኢየሱስ ይህን አስከፊ ጊዜ እያመለከተ ሲናገር:- “ነገር ግን  ያን ጊዜ ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው” ብሏል (ሉቃስ 21÷ 20-23፤ 23÷ 28-29 ተመልከት)፡፡ የራዕይ መጽሐፍ ይህ ሦስተኛ የጥቁር ፈረስ ጋላቢ ንግግርና በጆሳፈስ የታሪክ ዘገባ መካከል ያለውን ትይዩነት ልብ በሉ፡- ለአንዲት ሩብ ያህል ብቻ ለምትሆን ለዚያውም ለስንዴ ሲሉ ያላቸውን ነገር ሁሉ ፈጽመው ሸጠው የጨረሱ፣ ዋጋ ሊያወጣ የሚችል ጥሪት የነበራቸው ሰዎች የሆኑ እንደሆነ ብቻ ነው፣ ምንም የሌላቸው ድሆች የሆኑ እንደሆነ ግን ባዶ ሆነው የሚመጣባቸውን ይጠብቃሉ፡፡ 

የግብጽ ደዌ:-

በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ታደርግ ዘንድ ባትጠብቅ፥ ይህንንም «አምላክህ እግዚአብሔር» የተባለውን የተመሰገነውንና የተፈራውን ስም ባትፈራ፥ እግዚአብሔር መቅሠፍትህን፥ የዘርህንም መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመንም የሚኖረውን ታላቅ መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመን የሚኖረውንም ክፉ ደዌ ያደርግብሃል። የፈራኸውንም የግብፅ ደዌ ሁሉ እንደ ገና ያመጣብሃል፥ ይጣበቅብህማል።” (ዘዳግም 28፥ 58-60)

እነዚያ በግብጽ ላይ ዘንበው የነበሩ አሥሩ የዘጸአት መቅሰፍቶች በአይሁድ ጦርነት ወቅት በእስራኤል ላይ ወርደው ነበር። 

በራእይ መጽሐፍ ላይ በተብራራውና አጽንዖት በተሰጠው መሰረት፣ በዘፀአት ጊዜ በግብፃውያን ላይ የደረሱት አሥሩ መቅሰፍቶች የቃል ኪዳኑ እርግማን ሆነው በአንዳንድ መንገድ ፍጻሜያቸውን ያገኙት በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው።  የራዕይ 16 ሰባቱ ጽዋዎች እያንዳንዳቸው የተለየ የዘፀአት መቅሰፍትን ያመለክታሉ።  የመጀመሪያው ጽዋ የእባጭ ቸነፈርን የተሞላ ነው።  ሁለተኛውና ሦስተኛው ጽዋዎች የደም መቅሰፍትን ያመለክታሉ። የአራተኛው ጽዋ ቸነፈር የዝንቦች ወይም የዱር አራዊቶች መቅሰፍት ስለመሆን አለመሆኑ በተርጓሚዎች ዘንድ አንዳንድ ክርክሮች አሉ።  አምስተኛው ጽዋ የጨለማ መቅሰፍት ነው።  ስድስተኛው ጽዋ የእንቁራሪቶችን መቅሠፍት ያስታውሳል፣ ሰባተኛው ደግሞ የበረዶ መቅሠፍት ነው።  የአንበጣ መቅሰፍት በራእይ 9፥ 27 በአምስተኛውና በስድስተኛው መለከቶች ውስጥ ተጠቅሷል። ስለ ዘጸአት አሥረኛው መቅሠፍት ጨለማ ማስታወሻ በራዕይ 13፥ 16-17 ላይ ከምድር የወጣው አውሬ እያንዳንዱ ሰው በእጁና በግንባሩ ላይ ምልክቱን እንዲቀበል ያስገድዳል። በዚህ መቅሠፍት ወቅት ዕብራውያን ባሪያዎች እና ዘሮቻቸው ከፋሲካ በግ መሥዋዕት በኋላ በእጃቸውና በግንባራቸው ላይ በመንፈስ ምልክት ተደርጎባቸዋል (ዘጸአት 13፥ 15-16)።  የቅማል እና የትንኝ መቅሰፍት እና የዝንቦች ወይም የአውሬዎች መቅሰፍት የኢየሩሳሌም አይሁዶች ከተማቸው በተከበበች ጊዜ የሙታኖቻቸውን በድን መቅበር ያለመቻላቸው ተፈጥሮአዊ ውጤት ነው።  አስከሬኖች በየጎዳናዎች ላይ ሲወድቁና ቀባሪ ሲያጡ ዝንቦችንና ትንኞች ይሰበስባል፣ እነርሱም ያንን ብስባሽ የሰው አካል ተመግበው እንቁላሎቻቸውን በእነዚሁ አስከሬኖች ውስጥ ይጥላሉ።  እነዚህ ትንኞችና ዝንቦች ይህን ያህል የተትረፈረፈ የምግብ ምንጭ ስለሚኖራቸው እጅግ በዝተው ከተማይቱንና ቤቶችን ሁሉ ይወርራሉ።  በቁ.26 ላይ እንደተተነበየው፣ የእነዚህ ሙታን አስከሬኖች ሬሳ ወፎችንና ሌሎች የዱር አራዊትንም ወደ ከተማው ይስባሉ።  በእንስሳት ላይ የሚደርስ ቸነፈር ደግሞ የጥንት ሮማውያን የሚያካሂዱት የጦርነት ውጤት ነው።  በቁጥር 18፣ 31-33 እና 49-51 የተገለጸውን የእርግማን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ በሚሰጠው መልኩ አይሁድ ከሮም ጋር ባደረጉት በዚያ ጦርነት ሮማውያን ሠራዊቶቻቸውን ለመመገብና ጠላቶቻቸው የሆኑትን እስራኤላውያንን ለማስራብ ከብቶቻቸውን ዘርፈው ይወሰዱባቸው ነበር።

ከርስት መነቀል:-

ደግሞም ይህ ሕግ ባለበት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፈውን ደዌ ሁሉ መቅሠፍትም ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር ያመጣብሃል። የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁምና ከብዛታችሁ የተነሣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የነበረው ቍጥራችሁ ጥቂት ሆኖ ይቀራል። እግዚአብሔርም በጎ ያደርግላችሁ ዘንድ ያበዛችሁም ዘንድ ደስ ይለው እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ሲያጠፋችሁ ሲያፈርሳችሁም ደስ ይለዋል፤ ትወርሱአትም ዘንድ ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ። እግዚአብሔርም ከምድር ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ወዳሉ አሕዛብ ሁሉ ይበትንሃል፤ በዚያም አንተና አባቶችህ ያላወቃችኋቸውን ሌሎችን አማልክት፥ እንጨትንና ድንጋይን፥ ታመልካለህ።” (ዘዳግም 28፥ 61-64)

የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁምና ከብዛታችሁ የተነሣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የነበረው ቍጥራችሁ ጥቂት ሆኖ ይቀራል።” (ዘዳግም 28፥ 62)

ጆሴፈስ እንዳለው፣ 1,100,000 ሰዎች በጦርነቱ ተገድለዋል፣ 97,000 የሚሆኑት ደግሞ በምርኮ ተወስደዋል። ሊቀ ጳጳስ ኡሸር የጆሴፈስን ጽሑፎች እንደ ማጣቀሻ ተጠቅመው በ70 ዓ.ም በተጠናቀቀው ጦርነት ኢየሩሳሌም ፈጽማ እስከ ወደቀችበት ጊዜ ድረስ 1,337,490 የተገደሉትን ሙታን ዘርዝረዋል።

“..... ትወርሱአትም ዘንድ ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።” (ዘዳግም 28፥ 63)

በቁጥር 63 ላይ “ለመውረስ ከገባችሁባት ምድር እነቅላችኋል” ይላል።  ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በተካሄደው የአይሁድ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዶች የተገደሉና የተሰደዱ ቢሆንም፣ የዚህ ጥቅስ ማስጠንቀቂያ ግን  በመጨረሻ ፍጻሜውን ያገኘው ከሁለተኛው የአይሁድ አመፅ በኋላ ይመስላል።  በዚህ ጊዜ ሃድሪያን  ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የቀሩትን አይሁዶች ከይሁዳ ለቅቀው እንዲሰደዱ በጥብቅ አዘዘ። ማንኛውም አይሁዳዊ የሆነ ጎሳ ይህንን ከአገሩ ተባርሮ የመውጣት ትዕዛዝ ተላልፎ ቢገኝና ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ቢደፈር ያለምንም ርህራሄ ይገደላል። እግዚአብሔር አይሁድ የተባለውን  ዘር ራሱን የፈለገው አይመስልም ስለዚህ ምድሪቱን እንዳይረግጡ አድርጎ አሳደዳቸው። ክርስትናን የተቀበሉ አይሁዶችም እንኳ ቢሆኑ በተመሳሳይ መልኩ ከኢየሩሳሌም እንዲባረሩ ተደርገዋል። ቤታር የተባለው የባር ኮክባ የመጨረሻው ምሽግ ከወደቀ በኋላም እንኳ በይሁዳ ምድር ውስጥ ከታወቁትና ከነበሩት ሰባ አምስት የአይሁድ ሰፈሮች መካከል የአይሁድ ሰዎች በአንደኛው ውስጥ እንኳን መኖር እንደቀጠሉ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።  አንዳንድ የአይሁድ መንደሮች ግን በዮርዳኖስ ሸለቆ፣ በበረሃው ጠርዝ በደቡብ እና በምዕራባዊው የባህር ዳርቻ ሜዳ ላይ ከሚገኙት የይሁዳ ኮረብቶች ዳርቻዎች ጋር ብቻ እዚያም እዚህ ተበታትነው ቀሩ።  ከዚያም የይሁዳ ሰዎች ከአገራቸው ተነቅለው ከሶርያውያንና ከአረቦች ጋር ተቀላቅለው ሰፈሩ። “ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ያለው የኢየሱስ ትንቢትም ፍጻሜው በዚህ ደረጃ መራር ነበር። አይሁዶች ከተባረሩ በኋላ ያሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት መቶ ዓመታት ግን በኢየሩሳሌም ታሪክ ውስጥ፣ ከተማይቱ ያለ አይሁድ በሽታዋ ለቅቆአት የሄደ ያህል ከሁሉም የበለጠ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰላማዊ ዓመታት ነበሩ።  በነዚህ ጊዜያት ውስጥ፣ የአሕዛብ ክርስቲያኖች ቁጥር በብዙ ጨምሯል “በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ እንኳ፣ አይሁዶች አሁንም ወደዚያች ከተማ በዓመት አንድ ቀን ካልሆነ በስተቀር እንዳይገቡ ታግደው ነበር። ኢየሩሳሌምም ከታሪካዊ እሴት አንጻር በአገሪቱ ውስጥ ብቸኛ የክርስቲያን ከተማ ሆነች፣ ብቸኛዋ።

የስጋት ኑሮ:-

በእነዚያም አሕዛብ መካከል ዕረፍት አታገኝም፥ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ አይሆንም፤ በዚያም እግዚአብሔር ተንቀጥቃጭ ልብ፥ ፈዛዛ ዓይን፥ ደካማም ነፍስ ያመጣብሃል። ነፍስህም ታመነታለች፤ ሌሊትና ቀንም ትፈራለህ፥ በሕይወትህም አትታመንም፤ አንተ ስለ ፈራህበት ስለ ልብህ ፍርሃት፥ በዓይንህም ስለምታየው አስተያየት፥ ማለዳ፦ መቼ ይመሻል? ትላለህ፤ ማታም፦ መቼ ይነጋል? ትላለህ።” (ዘዳግም 28፥ 65-67)

ይህ የአይሁድ ምርኮኞችን ጭንቀት ያሳያል። ከላይ እንደተገለጸው፣ ሮማዊው ጄኔራል ቲቶ ኢየሩሳሌም ከወደቀች በኋላ 97,000 አይሁዳውያንን በግዞት ምርኮ ወሰዷል፤ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ በሮማውያን አምፊቲያትሮች “በሰይፍና በአውሬ ተገድለዋል”። ለአህዛብ አማልክት መስዋእት እንዲሆኑ፣ ለነገስታቱና ለመኳንንቱ ክብርም በሰይፍ እንዲታረዱም ተደርገዋል። ታዲያ አይሁድ ምርኮኛና ባርያ በመሆናቸው እንዲሁ ጭዳ የተደረጉ የወንድሞቻቸው እጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው ወይም  በሮማውያን አምፊቲያትሮች ውስጥ እንዳይገደሉ የነበረባቸው የየእለቱ ፍራቻና ሰቆቃ ከቁጥር 65-67 የተተነበየው የእርግማኑ ማስጠንቀቂያ ምናልባት የጭንቀታቸው መንስኤ ሊሆን ይችላል።

ወደ ግብጽ መመለስ:-

ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች ትሆኑአቸው ዘንድ ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ፤ የሚገዛችሁም አይገኝም።” (ዘዳግም 28፥ 68)

የዚህ ምእራፍ የመጨረሻ ጥቅስ ምናልባት በጣም የሚገርም ነው። በዚህ ትንቢት መሰረት እስራኤላውያን በባርነት ወደ ግብፅ ተልከዋል።  ጆሴፈስ የቁ.68ን ፍጻሜ በግልፅ ሲጠቅስ፡- “ከአሥራ ሰባት ዓመት በላይ የሆናቸውን የቀሩትንም ሕዝብ አስሮ ወደ ግብፅ ማዕድን ማውጫ ላካቸው።” ይላል።    ሮማውያን ብዙ ምርኮኞችን በመርከብ መውሰዳቸውንም ሚድራሽ ውስጥ ተረጋግጧል። ከዚያም የተቀረው የቁጥር 68 ቃል ሲፈጸም፣ ሮማውያን ብዙ አይሁዶችን በባርነት ይዘው እንደነበርና በዚያው መጠንም የገዢዎች እጥረት እንደነበር ይናገራል፦

“ሕዝቡ እንደርካሽ  ሸቀጥ ሆኑ፣ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እያንዳንዳቸው በዝቅተኛ ዋጋ ይሸጡ ነበርና፤ ለሽያጭ የቀረቡትም እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ዋጋ ሰጥተው የሚገዙአቸው ጥቂቶች ነበሩ።”

ከላይ ባሉት ጥቅሶች ላይ እንደሚታየው እነዚያ ለእግዚአብሔር ያልታመኑ እስራኤላውያን ከዘጸአት በፊት ወደነበራቸው የጥንት የባርነት ታሪካቸው እንደገና ተመልሰው በግብፅ ባርያዎች ሆኑ። ባሪያዎችም ከመትረፍረፋቸው የተነሳ  ገዢዎች ጥቂት ብቻ ነበሩ። ይህ ጥቅስ በዘዳግም 28 ላይ በዝርዝር የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች ሁሉ በዘመኑ ፍጻሜ ላይ ምን ያህል ሙሉ በሙሉ እና ትክክለኛ በሆነ መንገድ  ፍጻሜአቸውን እንዳገኙ የሚያሳይ ፍጹም ምሳሌ ነው። 

ስለ ቀሪው የፍጻሜ ዘመን ትንቢቶችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በቃል በሆነ መልኩ ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል።  ይህንን የምትጠራጠሩ ሰዎች ልትኖሩ ትችላላችሁ፣ የተፈጸመውን ወንጌል እንደሚያምንና እንደ ሚያስተምር ፕሪቴሪስት የቅዱስ ቃሉን ትንቢት አይቀሬ ፍጻሜ ከቃሉ ተነስተን፣ ታሪካዊ ፍጻሜውን መርምረን የምናቀርበውን ማስረጃ ግን ማስተባበል የሚቻልበት ስነ መለኮት የለም። እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንበያዎች እንዴት ፍጹም በሆነ እና በሚያስገርም ሁኔታ እንደተፈጸሙ ልትመለከቱ ብትወዱ ብሎገሬን ይጎብኙ።

ግዛቸው ከበደ

ለዚህ ጥናት እንደ ግብዓት ያገለገሉ የጽሁፍ ስራዎች ከሞላ ጎደል፦

  • መጽሐፍ ቅዱስ

  • Bruce, F. F, The International Bible Commentary with the NIV

  • Coggins R. J & Houlden J.L. A dictionary of Biblical Interpretation

  • Eusebius, The History of The Church

  • Gentry,Jr. Kenneth L Before Jerusalem Fell, Dating the Book of Revelation

  • Whiston, William The New Compete Work of Josephus, 

  • Josephus, Flavius The Wars of the Jews

  • Duncan W. McKenzie, Ph.D., The Antichrist and the Second Coming: A Preterist Examination Volume 2: The Book of Revelation (USA: Xulon Press, 2012),

  • Tacitus The Histories 

  • M. Avi-Yonah, The Jews of Palestine: A Political History from the Bar Kokhba War to the Arab Conquest, (New York: Schocken Books, 1976)

  • Stevens, E. Edward. Final Decade Before the End.

  • Teddy Kollek and Moshe Pearlman, Jerusalem: A History of Forty Centuries, (New York: Random House, 1968)

  • Midrash Rabbah Lamentations

  • Mills, Jessie E, Jr Revelation survey and Research, 2004

  • Mason, Steve: Josephus and the New Testament 1992 Hendrickson Publisher

 






    













Thursday, July 20, 2023

ፕሪቴሪዝም፣ የተፈጸመው ሥነ-መለኮት: በታሪካዊ መዛግብት ከተረጋገጡ አንዳንድ ምልክቶችና ምስክሮች ጋር

ፕሪቴሪዝም፣ የተፈጸመው ሥነ-መለኮት
በታሪካዊ መዛግብት ከተረጋገጡ አንዳንድ ምልክቶች እና ምስክሮች ጋር

መግቢያ፦ ትንቢት ተፈጽሟል ብለን ለያዝነው አቋም ቀዳሚና ብቸኛው መሰረታችን የቅዱስ ቃሉ ትምህርት መሆኑ የልብ ስፋትና የአእምሮ ዝግጅት ባላቸው፣ በቅጡ ማሰብ በሚችሉም ሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው። ለእምነት ቤተሰብ ቃሉ ብቻ ይበቃዋል ብለን እንጂ እንደ ደመና ከበውን ያሉ እርግጠኛ የታሪክ ምንጮችን ጠቅሰን ማስረዳትም ሆነ ለሚጠይቁን መልስ መስጠት አያስቸግረንም። በመሆኑም ሊመረመሩ ይገባቸዋል ብዬ የማስባቸውን አንዳንድ ታሪካዊ የመረጃ ምንጮችን ልጠቁማችሁ እወዳለሁ። እነዚህ የመረጃ ምንጮች ለብዙዎቻችሁ ምን ማለት እንደሆኑ አላውቅም፤ ዳሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ  “ይህ ትውልድ አያልፍም”፣ “ጌታ በደጅ ነው”፣ “ዘሙኑ አጭር ሆኖአል”፣ “ፈጥኖ”፣ "ቶሎ" ፣ “ሊሆን ያለ” ወዘተ." ሲል ለሚገልጣቸው ጊዜ ጠቋሚ ለሆኑ ንግግሮቹ ተገቢውን ዋጋ ሰጥተን ልናያቸው ይገባናል።
 
አስተውሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት ሊመጣ ያለው ፍርድ ከጌታ ዳግመኛ ምጽአቱ (ፓሮውዥያው) ጋር የተቆራኘና፣ በከሃዲዋ እስራኤል ላይ ሊደርስ የቀረበ ፍርድ ነበር (ማቴ. 19፡28፤ ሉቃ. 21፡22-23፣ 32፤ ሉቃ. 22፡30)፤ ይኸውም ከ66-70 ዓ.ም ባለው ጊዜ በተካሄደው የአይሁድ-ሮም ጦርነት ወቅት፣ ለ42 ወራት (3 ዓመት ተኩል) የሚቆይ ማለት ነው። ይህንን በግልጽ የሚናገሩና ትንቢት ሁሉ ተፈጽሟል ብለን ለያዝነው አቋም በቀዳሚነት ዋቢ የምናደርጋቸውን የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባት ከብዙ በጥቂቱ በሁሉት ምድብ በዚህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ በዝርዝር አስቀምጫለሁ። በዚህ ጽሁፍ ግን ዋናው ትኩረቴ በተለይ የፍላቪየስ ጆሳፈስን "Wars"  እና የኢውሳብየስን "Ecclesiastical History" መጻህፍት ሳገላብጥ፣ ድረ ገጾችንም አስሼ ያገኘሁአቸውን ሰነዶች ተመልክቼ፣ ምን ያህል ከቃሉ ትምህርት ጋር የሚስማሙ እንደሆነ ግንዛቤ ከያዝሁና፣ ሰነዶችን በመጠቀም ረገድ ልምዱ ያላቸውን የተመሰገኑ ምሁራን የጽሁፍ ስራዎች አማክሬ፣ ሰነዶቹ የያዙአቸውን ታሪካዊ ማስረጃ የሚሆኑ ክስተቶችን በመጠኑ ጠቆም  ጠቆም ማድረግ ነው። እኔን ግን በእጅጉ የሚገረመኝ ነገር ቢኖር ብዙ ክርስቲያኖች፣ ባስ ሲልም ምሁራኖቻችን ስለ እነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች ምንም ሲሉ አለመሰማታቸው ነው። እስካሁን ባለኝ ምልከታ የተለያዩ የአገራችን "ሥነመለኮት አዋቂዎች" በትምህርታቸውም ሆነ በጽሁፎቻቸው እውቅና ሰጥተው ዋቢ ሲያደርጓቸውም ሆነ ሲተቹአቸው አልሰማሁም፣ አላየሁምም። ምናልባትም እነዚህ ሰነዶች ይኖሩ እንደሆነ ስለማወቃቸውም እጠራጠራለሁ።

የአዲስ ኪዳንን ታሪክና ስነመለኮት ለመመርመር ራሱን የሰጠ ማንም አማኝ ከነዚህ ታሪካዊ መዛግብትና ሰነዶች ጋር የሚፋጠጥበት ዕድል ከሌለው ስለ አዲስ ኪዳን የሚያውቀው በግርድፉ ነው ማለት ነው። ጌታ ቢፈቅድ በአዲስ ኪዳን ጥናት ውስጥ የሰነዶቹን ዋጋ የሚያስነብብ ጽሁፍ ሌላ ጊዜ አቀርባለሁ። እነዚህ ሰነዶች በጊዜው የተፈጸሙትን ክስተቶች የአይን ምስክር ሆነው በታሪክ ድርሳናቸው ከትበው ያስቀሩልንና የእነርሱን ምስክርነት ከቃሉ ትምህርት ጋር እያመሳከሩ የጻፉ የጥንት አባቶችና ምሁራን ስራ ስለሆኑ፣ ስለ ትንቢት ፍጻሜ ከቃሉ ምስክርነት ያለፈ ውጫዊ ማስረጃ ለሚፈልጉ አይነተኛ ግብዓት በመሆናቸው፣ በቀጥታ ወደ ማስረጃዎቹ ዝርዝር አልፋለሁ፦

1ኛ/ ጆሴፈስ (በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የኖረ፣ ስለ አይሁዶች ታሪክ እና ስለ ሮማ ግዛት በሰፊው የጻፈ አይሁዳዊ የታሪክ ምሁር ነው። የጆሴፈስ ጽሑፎች በተለይ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለተመዘገቡና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ለተከሰቱት ክስተቶች እና አንዳንድ ሰዎች ጠቃሚ ምስክርነት ስለሚሰጡ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ ስብዕናዎች እና ቡድኖች በጆሴፈስ ውስጥም አሉ። የጆሴፈስ ጽሑፎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለተገለጹ ክስተቶች ውጫዊ የሆነ ታሪካዊ አውድን በማቅርብ ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው።  ስራዎቹ በጊዜው ስለነበሩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ እውነታዎች ብርሃንን ይፈነጥቃሉ።  ስለዚህ፣ የጆሴፈስ ጽሑፎች አዲስ ኪዳንን ለሚማሩ የቃሉ ተማሪዎች ጠቃሚ የመረጃ ምንጭ ናቸው።) ከተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጆሴፈስ የአይሁድ ጦርነት በተሰኘው የታሪክ ድርሳኑ መጽሐፍ 6 ምዕራፍ 5 ክፍል 2 እና 3 ላይ ያሰፈረውን ዘገባ እንመልከት፦

War 6:286 (6.5.2.286) እንግዲህ፣ በዚያን ጊዜ የተነሱ እጅግ በጣም ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ነበሩ፤ እኑርሱም በሕዝቡ ላይ ቀንበርን እንዲጭኑ በወቅቱ ተነስተው በነበሩ አምባገነን ገዥዎች የሚታገዙ ነበሩ። ህዝቡንም መዳንን ከእግዚአብሔር ይጠባበቁ ዘንድ በውግዘትና በእርግማን ያስፈራሩአቹው ነበር (ልክ ቃል እንዳላወጣብህ እንደሚሉት እንደ ዘመናችን ሟርተኞች ማለት ነው )፤ እነዚህ ሟርተኛ ነብያት ይህንን  ያደርጉ የነበሩት ህዝቡ በከተማይቱና በሚኖሩባት ላይ ሊመጣ ካለው ጥፋት ሸሽተው እንዳያመልጡ  ለመከላከል ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህም በላይ፣ ከእነዚያ እየመጡባቸው ካሉ፣ ከሚፈሩአቸው እና ከሚያስጨንቋቸው ጠላቶቻቸው  እንደሚታደጉአቸው እንዲህ ያሉ አሳሳች ተስፋዎችንም ይሰጡአቸው ነበር።

War 6:288 (6.5.3.288) ስለዚህ እነዚህ የተታለሉ ምስኪን ሰዎች፣ እነዚያ በግልጽ የሚታዩትን እና የወደፊቱን መጻኢ ጥፋት በግልጽ የሚተነብዩና የሚያመለክቱ ምልክቶችን አስተውለው ሳይከታተሉ ወይም ተገቢውን ዋጋ ሳይሰጡአቸው፣ ይልቁንም፣ በዓይኖቻቸው እንዳያዩ ታውረው፣ ወይም አእምሮ እንደሌላቸው ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ እያወረደባቸው ያለውን ያንን ሁሉ መዓት ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ፣ የእነዚህ አታላዮች እና እራሱን እግዚአብሔርን የካዱ ነብያቶቻቸው ሰለባ ሆኑ።

War 6:289 (6.5.3.289) ስለዚህም በከተማይቱ ሰማይ ላይ ከፍ ብሎ የቆመና የተመዘዘ ሰይፍ የመሰለ ኮከብ እና አመቱን ሙሉ የቀጠለ የኮሜት አስፈሪ ትዕይንት ነበረ።
War 6:290 (6.5.3.290) እንዲሁም ደግሞ፣ ያ የአይሁድ ዓመፃ ከመቀስቀሱ በፊትና፣ ከጦርነቱ አስቀድሞ ከነበረው የህዝብ ቁጣና ግርግር በፊት፣ በዛንቲከስ [ኒሳን] ወር በስምንተኛው ቀን እና በዘጠነኛው ሰዓት ሕዝቡ እጅግ ብዙ ሆነው ወደ ቂጣ በዓል ወጥተው ነበር፣ ገና ሌሊትም ሳለ በቀን ጊዜ እንደሚያበራ ብሩህ እስኪመስል ድረስ ታላቅ ብርሃን በመሠዊያውና በቅዱሱ ቤት ዙሪያ አበራ፤  ይህም ብርሃን ለግማሽ ሰዓት ያህል በዚያ ቆይቶ ነበር።

War 6:291 (6.5.3.291) ይህ ብርሃን ለነዚያ በዚያ ተከማችተው ለነበሩ ላልተማሩ ሰዎች እንደ አንድ ጥሩ ምልክት ተደርጎ ይታይ ነበር፣  ቅዱሳት መጻህፍትን በሚመረምሩ በጸሐፍቱ ዘንድ ግን ወዲያውኑ በእነርሱ ላይ የተከሰቱትን የጥፋት ክስተቶች ለማስረዳት አስቀድሞ እንደተሰጠ የክፉ ነገር ምልክት ተደርጎ ተተርጉሞ ነበር።
War 6:296 (6.5.3.296) ከዚህም በተጨማሪ ከበዓሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ አርጤምስዮስ (ጂያር) በተባለው ወር ከወሩም በሃያ አንደኛው ቀን  ይህ ምልክት በእነርሱ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት እንደሚያሳይ በይፋ ተናገሩ።
  
War 6:297 (6.5.3.297)  “አንድ አስደናቂ እና ሁሉንም ያስገረመ ክስተትም ታየ፤ ያንን ክስተት በአይኖቻቸው ያዩ ምስክሮች ባይናገሩት ኖሮ ታሪኩ ተረት ይመስላል ብዬ እኔ ራሴም ባልዘገብኩት ነበር።

War 6:298 (6.5.3.298) የታየውና ያንንም ተከትለው የተፈጸሙ ድርጊቶች እንደዚህ አይነት ምልክቶች የሚገባቸው አይነት ተፈጥሮ ያላቸው ክስተቶች ነበሩ። ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ሠረገሎችና በላያቸው ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡ የታጠቁ የሰራዊት ጭፍሮችም በደመናው መካከል ወዲህና ወዲያ እየተሯሯጡ ከተማይቱን ሲከብቧት ታዩአቸው። 

War 6:299 (6.5.3.299) ከዚህም በላይ በዓለ ኀምሳ በተባለው በዚያ በዓል፣ ካህናት እንደ ልማዳቸው፣ ቅዱስ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም በሌሊት ወደ ውስጠኛው [ወደ ቤተ መቅደሱ] ገብተው ሳለ፣ በመጀመርያ ለራሳቸው ብቻ የሚታወቅ መሸበርና ፍርሃት ይሰማቸው እንደነበሩ ሲገልጡ አስከትለውም  ታላቅ ድምፅን ሰሙ።

War 6:300 (6.5.3.300) ከዚህም በኋላ በታላቅ ድንጋጤም ውስጥ ሆነው እየተንቀጠቀጡ የሰሙት ታላቅ ድምፅ "ኑ ከዚህ በኋላ ለቅቀን ከዚህ እንሂድ” የሚል እንደ ብዙ ሕዝብ ያለ ድምፅ ነበር።

2ኛ/ ኢውሳብየስ (በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ ክርስቲያን የታሪክ ጽሐፊ እና የቂሳርያ ቢሾፕ ነበር።) "የቤተክርስቲያን ታሪክ" በተሰኘ ባለ አስር ጥርዝ ስራው፣ መጽሐፍ 3፣ ምዕራፍ 8፣ ክፍል 1-6 እንደተዘገበው የጆሴፈስን ትረካ ምንጭ አድርጎ በስድስተኛው የታሪክ መፅሃፉ ላይ ያሰፈረውን ዘገባ እንመልከት፣ ቃሉም እንደሚከተለው ነው፦

94 “በዚህም ጊዜ ምስኪኑ ሕዝብ በአስመሳዮችና በሐሰተኛ ነቢያት ተሸነፈ፤ 95 ነገር ግን ሊመጣ ስላለው ጥፋት ያለውን ራእይና ምልክት አልሰሙም፤ አላከበሩምም።  በተቃራኒው ግን፣ ልክ በመብረቅ እንደተመታ ሰው፣ ዓይንና ማስተዋል እንደሌላቸው ሆነው፣ የእግዚአብሔርን አዋጅ ናቁ።

በአንድ ወቅት የተመዘዘ ሰይፍ የሚመስል ኮከብ፣ በከተማይቱ ሰማይ ላይ ቆሞ ታየ፤ ዳግመኛም ከዐመፁ በፊትና ወደ ጦርነቱ ያመራውን ግርግር ከመጀመሩ በፊት አንድ ዓመት ሙሉ የፈጀ የኮሜት ትዕይንትም ታይቶ ነበር። ሕዝቡም ለቂጣ በዓል በተሰበሰበ ጊዜ፣ በ ዛንቲከስ ወር በስምንተኛው ቀን፣ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ፣ ታላቅ ብርሃን በራ።  በመሠዊያው በቤተ መቅደሱ ሁሉ ብሩህ ቀን የሆነ ይመስል ነበር፤  ይህም ለግማሽ ሰዓት ያህል ቀጠለ። አላዋቂዎች የሆኑ ይህንን እንደ ጥሩ ምልክት አድርገው ወስደውት ነበር፣ ነገር ግን በጊዜው የነበሩ የቅዱሳት ጸሐፍት ተርጓሚዎች ጉዳዩን የተረዱት ከዚያ ወቅት ብዙም ሳይቆይ የተከናወኑትን እነዚያን ከባባድ ክፉ ክስተቶች እንደሚያመለክቱ አድርገው ነው።

በዚያም በዓል አንዲት ላም ለመሥዋዕት ልትቀርብ በሊቀ ካህናቱ ተመርታ በቤተ መቅደሱ መካከል ሳለች ድንገት ጥጃዋን ወለደች።

ከናስም የተሰራው፣ በብረትም በተሠሩ ምሰሶዎች ላይ ያረፈው፣ በመሬት ውስጥም የተተከሉ መወርወሪያዎች የነበሩት፣ በመሸም ጊዜ በሃያ ሰዎች ጉልበት በጭንቅ ይዘጋ የነበረው የውስጠኛው ቤተ መቅደስ ምስራቃዊ በር፣ ገና ከሌሊቱ ስድስተኛ ሰአት ሲሆን ድንገት በራሱ ተበርግዶ ሲከፈት ታየ።

ከበዓሉም ብዙ ሳይቆይ በአርጤምስ ወር ከወሩም በሃያ አንደኛው ቀን ለማመን የሚያስቸግር አንድ አስደናቂ ራእይ ታየ።  ይህም ራእይ ራእዩን ካዩት ሰዎች ህይወት ጋር ካልተዛመደ እና  በኋላም ራእዩን ተከትለው የተከሰቱት ጥፋቶች በእንደዚህ አይነት ተጨባጭ ምልክቶች የታዩ ባይሆን ኖሮ ጉዳዩ ተረት ሊመስል ይችል ነበር።  ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ሰረገሎችና የታጠቁ ጭፍራዎች በአየሩ ላይ ሆነው በየአገሩ ሁሉ በደመና ሲሽከረከሩ ከተሞችንም ሲከብቡ ታይተዋልና።

በዓለ ኀምሳ ተብሎ በሚጠራው በዓልም ካህናቱ እንደ ልማዳቸው በሌሊት ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው ሥርዓተ አምልኮውን እየፈጽሙ ሳሉ፣ በመጀመሪያ ላይ የሆነ እንቅስቃሴ የመሰለ መታወክና ታላቅ የጩኸት ድምጽ ሆነ፤ ከዚያም በኋላ "ኑ ከዚህ ለቀን እንሂድ" የሚል እንደ ብዙ ሕዝብ ያለ ድምፅ ተሰማ።

3ኛ/ ታሲተስ (ጆሴፈስ በኖረበት በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የኖረ ሮማዊ  የታሪክ ምሁር እና ፖለቲከኛ ነበር።) Histories, Book 5:

ይህ ሕዝብ አጉል ለሆነ እምነት የተጋለጠ ነበር፣ ነገር ግን ደግሞ ሁሉንም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚጠላ፣ ሕጋዊ እንደሆነ በማይቆጠር መባና የመሥዋዕት ማስተስረያን የሚለማመድ ነበር።  ያኔም በሰማይ ላይ ለጦርነት የሚንቀሳቀሱና እርስ በርሱ የሚቀላቀል የሰራዊት ጭፍራ፣ የእሳታማ ክንድ ብልጭታም ታይቷል፤ ቤተ መቅደሱም ከደመና ወጥቶ በመጣ ድንገተኛ ብርሃን ወጋገን ያበራ ነበር።  የመቅደሱ የውስጠኛው በሮችም በድንገት ተበርግደው ተከፈቱ፤ ከሟች ሲቃ ቃና በላይ የሆነ ድምፅ "አማልክት ለቅቀው እየሄዱ" ነው የሚል ታላቅ ጩኸት ተሰማ።  በዚያው ቅጽበትም  ተለይቶ እንደሚሄድ አይነት የብዙ ህዝብ ግርግር ሆነ።  ጥቂቶች በእነዚህ ክንውኖች ላይ አስፈሪ ትርጉም ሰጥተዋል፣ ዳሩ ግን በጥንታዊ የካህናቶቻቸው ትንቢታዊ መዛግብት ውስጥ ከምሥራቅ የሆነው ኃይል በዚህ ጊዜ እንዴት ኃያላን ሆነው እንደሚነሱ እና ገዥዎችም ከይሁዳ እንደሚመጡ፣ መላውን አለምም የሚገዛ ኢምፓየርም እንደሚነሳ ትንቢት ተጽፎ ነበር የሚል ጠንካራ እምነት ነበራቸው። 
 
4ኛ/ ሴፈር ዮሲፖን (በመካከለኛው ዘመን የተጻፈ የጥንቷ እስራኤል ታሪክ፣ ስራዎቹም የአይሁድ እምነትን እና የጥንቷን እስራኤልን ታሪክ ለሚመረምሩ ምሁራን ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች አሉት) ከዕብራይስጥ ቋንቋ በስቲቨን ቢ ቦውማን የተተረጎመ ሆኖ፤  ከምዕራፍ 87 “የመቅደሱ መቃጠል” ከሚለው ዘገባ ላይ የተወሰደ።

ቬስፓሲያን ከመምጣቱ አንድ ዓመት በፊት፣ ልክ እንደሚያበራ አንድ ታላቅ ኮከብ ከሰገባው የተመዘዘ ሰይፍ የሆነ ትዕይንት በቤተ መቅደሱ ላይ ታየ።  ምልክቱ በታየበት ጊዜ በነዚያ ቀናት የፋሲካ በዓል ነበር፤ በዚያም ሌሊት እንደ ቀኑ ብርሃን ሆኖ ሙሉ ቤተ መቅደሱ እንዳለ አበራ፣ቀኖቹም ሁሉም የፋሲካው በአል ሰባት ቀናት ነበሩ።  የኢየሩሳሌም ሊቃውንት ሁሉ ይህ ክፉ ምልክት እንደሆነ ያውቁ ነበር፣ ነገር ግን የቀሩት አላዋቂዎች ይህ መልካም ምልክት ነው አሉ።

. . . ከዚህም በኋላ ሌሊቱን ሙሉ የአንድ ሰው የፊቱ ገጽታ በቅድስተ ቅዱሳን ላይ ከላይ ሆኖ ታየ፤ በውበቱም የሚመስለውም በምድር ሁሉ ላይ እንደ እርሱ ያለ ከቶ አልታየም፣ መልኩም እጅግ የሚያስፈራ ነበረ።

ከዚህም በላይ በዚያን ጊዜ የእሳት ሰረገሎችና ፈረሰኞች፥ ታላቅ ሠራዊትም ሆነው ወደ ሰማይ እየበረሩ እንደገናም ወደ ምድር ሲመጡ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ምድር ሁሉ ሲከብቡ፥ ሁሉም የእሳት ፈረሶችና የእሳት ፈረሰኞች ሆነው ሲመጡ ታዩ።  በዚያም ወራት፣ የሻቩት በዓል በደረሰ ጊዜ ካህናቱ በሌሊት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያስተጋባ የሰዎችን ድምፅ የሚመስል ነገር ሰሙ፤ ሕዝቡም ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገቡ የብዙ ሰዎችን ድምፅ የሚመስል ነገር ሰሙ፤ የሚያስፈራና ታላቅ ድምፅም እየተናገረ፡ “ኑ፣ እንሂድና ከዚህ ቤት እንውጣ" ሲል ተሰማ።

5ኛ/ Pseudo-Hegesippus፣ (በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ ማንነቱ ያልታወቀ አይሁዳዊ ክርስቲያን ጸሐፊ ሲሆን፣ ስራውም በጆሴፈስ የተጻፈውን የአይሁድ ጦርነት የተሰኘ ስራ ከልሶ በ70 አ.ም ላይ ሮማውያን በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሱትን ጥፋት ይዘረዝራል) ምዕራፍ 44። (ይህ በዋድ ብሎከር ከላቲን የተተረጎመ ሲሆን በቪንሴንቴ ኡሳኒ ከላቲኑ ትርጉም ተቀንጭቦ የተጠቀሰ ነው)፡-

የአይሁድ መጻሕፍት እንደ ገለጹት ከሆነ ከብዙ ቀን በኋላ ብዙዎች ያዩት እጅግ ታላቅ ​​የሆነ ምስል እና ምልክት ታየ፤ ፀሐይም ገና ሳትጠልቅ ሠረገላዎችና የጦር ሠራዊቶች በደመና ውስጥ ይታዩ ነበር፤ በዚያም የይሁዳ ሁሉ ከተሞችና ግዛቶቿ ሁሉ ተወርረው ነበር።  በዓለ ሃምሳ የተባለው በዓል በሚከበርበት ወቅት ካህናቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል በሌሊት ሲገቡና የተለመደውን የዘወትሩን መስዋዕት ሲያቀርቡ መጀመሪያ ላይ የተወሰነ እንቅስቃሴ እና ድምፅ እንደተሰማቸው ራሳቸው አረጋግጠው መስክረዋል።  ድምጹም በድንገት "ከዚህ ተሻግረን እንሄዳለን" ብሎ ይጮኽ ነበር።

ሌላ ተጨማሪ ላካፍላችሁ፦

6ኛ/ “ቤት ኮል” እና የቤተ መቅደሱ ጥፋት በ70 ዓ.ም።
[ቤት ኮል፣ ቃሉ  የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም "የድምፅ ሴት ልጅ" ወይም "የመለኮት ድምፅ አስተጋባች" እንደ ማለት ነው። እሱም የሚያመለክተው በአይሁድ ምሥጢራዊ ልምምድ እና በትውፊታቸው ውስጥ የሚንጸባረቀውን የመንፈሳዊ ግንኙነት ዓይነት ነው። ይህም ከሰማይ የመጣ ድምጽ በግለሰቦች የሚሰማበት ልምምድ ነው።  ዳሩ ግን በተፈጥሮው ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ከሚገናኙበት የጸሎትና የአገልግሎት ልምምድ የተለየ ነው። ነገር ግን እንደ መለኮታዊ ተመስጦ ሊቆጠር የሚችል መንፈሳዊ ልምምድ ነው።  ቤት ኮል በነቢያት የተሰማውን እና በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበውን ሰማያዊ ድምጽ ሊያመለክትም ይችላል። በአይሁድ ሮም ጦርነት ወቅት ከደብረ ዘይት ተራራ ላይ በቀጥታ ለኢየሩሳሌም ከተማ ነዋሪዎች ይሰማ የነበረ ድምጽ ነው።]

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የይሁዳ ክህደት በነበረበት ወቅት፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል የክብር ደመናው ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ወደ ምሥራቅ ወደ ደብረ ዘይት ሲሄድ አይቶ ነበር (ሕዝ. 10÷ 18-19፤ 11፥ 22-23)።  በኋላም፣ ስለ አዲሲቱ እየሩሳሌም ባየው በራዕዩ፣ የክብር-ደመናው ወደ አዲሱ ቤተ መቅደስ፣ ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሶ ሲመጣ ደግሞ አይቷል (ሕዝ. 43፥ 1-5)።  ይህም ራእይ የተፈጸመው ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክብር ከደብረ ዘይት ወደ አባቱ በደመና ሲያርግ (ሉቃስ 24፥ 50-51) እና  በ30 ዓ.ም አካባቢ በበዓለ አምሳ ቀን- ቤተክርስቲያኑን እንዲሞላ መንፈሱን በላከ ጊዜ ነው።

በኋላም የዚህ የእግዚአብሔር ክብር ሽግግር አምሳል በአይሁድ ታሪካዊ ጽሑፎች ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። በ66 ዓ.ም በበዓለ አምሳ ዕለት፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያሉ ካህናት ገና ተግባራቸውን እየተወጡ ሳሉ፣ “ከዚህ እንሄዳለን!” እያለ የሚጮኽ ትላቅ ድምፅና “የሃይለኛ ግርግርና ሁካታ” ተሰማ።

ይህ በ66 ዓ.ም. በበዓለ አምሳ ዕለት መለኮት ከቤተ መቅደሱ የመውጣቱ ሁኔታ፣ ልክ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለት ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው በመጀመሪያው የክርስቲያን ጴንጤቆስጤ ላይ መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሐዋርያት እና ለሌሎች በኃይል በይፋ ከተሰጠ ከ36 ዓመታት በኋላ፣ አሁንም እንደገና ልክ በጰንጠቆስጤ ቀን፣ እግዚአብሔር ራሱ የኢየሩሳሌምን ቤተመቅደስ ትቶ እንደሄደ የተሰጠ ምስክርነት ነው። ይህ ማለት እግዚአብሔር ከተለየው በኋላ ቤተ መቅደሱ አሁን የተቀደሰ መቅደስ አይደለም፣ ሕንጻውም ከማንኛውም ዓለማዊ ሕንጻ የበለጠ የተቀደሰና የተለየ አይደለም ማለት ነው። መለኮት በይፋ አድሮበት የነበረውን ቤት በይፋ ተወው።

በሚያስደንቅ ሁኔታ በዚህ ጊዜ [በ66 ዓ.ም.] የእግዚአብሔር ሼክናህ ክብር ቤተ መቅደሱን ለቆ ወጥቶ በደብረ ዘይት ላይ ለ3 ዓመታ ከመንፈቅ እንደቆየ አይሁዶች ያንን እንደተገነዘቡት የአይሁድ ጽሑፎች ይገልጻሉ። በዚህ ወቅት አይሁድ ከሥራቸው ንስሐ እንዲገቡ የሚለምናቸው ድምፅ ከደብረ ዘይት አካባቢ ተሰምቷል (ሚድራሽ - ሰቆ. 2፡11)። ይህም በክርስትና ታሪክ ላይ አስገራሚ ተጽእኖ አለው፣ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ እንደተሰቀለ እና እንደተነሳ ስለምናውቅ ነው፣ -  የአይሁድ መዛግብት እንደሚናገሩት ከሆነ የእግዚአብሔር ሼክናህ ክብር በ66 አ.ም ላይ በጰንጠቆስጤ ዕለት ከቤተ መቅደሱ ከወጣ በኋላ፣ ለ3 ዓመት ከመንፈቅ እንደቆየ ትክክለኛውን የጊዜ ክልል ያመለክታሉ። አይሁድም ያላቸው የማመሳከሪያ ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ ሮማውያን በ70 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ላይ ከፈጸሙት የመጨረሻ ወረራ አስቀድሞ ከሼክናህ ክብር የተሰጠውን ይህን ማስጠንቀቂያ ("ቤት ኮል" ብለው የሰየሙትን የእግዚአብሔር ድምፅ) እርሱም ምድርን ትቶ ወደ ሰማይ እንደተመለሰ  አይሁድ አልሰሙም ይላል።
 
ከክርስቲያኖች መካከል ማንም ቢሆን፣ በ66 ዓ.ም ከሆነው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ ከቤተ መቅደሱ ጋር የተያያዙትን እነዚህን ግልጽ ተአምራዊ ምልክቶች አክብሮ የሚመለከት ሰው፣ ህንጻው በያዘው ውቅር ከአሁን በኋላ የእግዚአብሔር ቅዱስ መቅደስ እንደማይሆን ማመን ይችላል። ጆሴፈስም ራሱ እንኳ "መለኮት ከቅዱሳት ስፍራ ሸሽቶ" (Wars, 5.412) ከመውጣቱ የተነሳ፣ እግዚአብሔር “ከመቅደሱ ርቋል” ብለው የሚያምኑትን የብዙ ሰዎች እምነት ጠቅለል አድርጎ አቅርቦታል (Wars 2.539)።

7ኛ/ ከሌላ ተጨማሪ ምንጮች፦
እነዚህ ክንውኖች ያኔ በአይሁድ አእምሮ ውስጥ ከፍተኛውን ስፍራ ይዘው በነበሩበት ወቅት፣ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ሲጽፍ፣ "ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፦ ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤" (ራእይ 21፥ 9-11) በማለት፣ ያ የእግዚአብሔር ክብር የሆነው ሼክናህ፣ በእውነተኛይቱ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ማለትም የክርስቶስ ሙሽራ በሆነችው የፍጻሜው ገነት በከተማይቱ ላይ ያረፈ መሆኑን ገልጿል።
 
የያህዌህ “ሼክናህ” በመሲሑ የሕይወት ዘመንና በሞቱም ጊዜ ሁሉ እና ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ በደብረ ዘይት ላይ ሲወርድ እስከታየበት ጊዜ፣ ማለትም እስከ 66 ዓ.ም. ድረስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቆይቷል።

በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ይኖሩ የነበሩ የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ደብረ ዘይቱ ተራራ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳደረባቸው ሌላም ምክንያት አለ። ይኸውም በቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ይኖራል ተብሎ ይታመን የነበረው ሼክናህ የሆነው የእግዚአብሔር ክብር ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዶ በዚያ ስፍራ ላይ ሰፍፎ ሲያንዣብብ የነበረው በ70 ዓ.ም በተጠናቀቀው የሮም/አይሁድ ጦርነት ወቅት ነው። ሼክናህ የሆነው የእግዚአብሔር ክብር ያንን አሮጌውን ቤተመቅደስ ትቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ከፍታ ላይ መውጣቱ [የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊና ምሁር ለነበረው፣ ከ260-340 ዓ.ም ለኖረው] ለኤውሳቢየስ በጣም አስፈላጊና ትልቅ ክስተት ነበር። (ኧርነስት ኤል. ማርቲን "የጎልጎታ ሚስጥሮች"፣ ሲል  በአልሃምብራ፡ ካሊፎርኒያ በ1988፡ ያሳተመውን መጽሐፍ   ገጽ 83 ላይ ይመልከቱ)

8ኛ/ ኤውሳቢየስ "Proof of the Gospel" በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ ይህንን ምንባብ እናገኛለን
በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ከዓለም ዳርቻ ይሰበሰባሉ፣ ይኸውም እንደ ቀድሞው ዘመን ስለ ኢየሩሳሌም ክብር ወይም በኢየሩሳሌም ከተማ በታነጸው በጥንቱ ቤተ መቅደስ ሊሰግዱ ሳይሆን ይልቁንም... የእግዚአብሔር ክብር [የያህዌ የሼኪናህ ክብር] ከቀደመችው ከተማ ወጥቶ ወደፈለሰበት ከከተማይቱ አንጻር በምትገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ይሰግዱ ዘንድ ነው። (Book VI, Chapter 18 (288))

እንደ ኤውሳቢየስ አባባል “ሼክናህ” የሆነው ክብር ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሰፍፎ ያንዣበበው “ኢየሩሳሌም ስትከበብ” (ከ66 እስከ 70 ዓ.ም.) ነው።  ሆኖም፣ “ሼክናህ” የሆነው ክብር መቅደሱ በጦርነቱ ማብቂያ ከመፍረሱ በፊት ቤተ መቅደሱን ለቆ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሰፍፎ እንዳንዣበበ የጠቀሰው ኤውሳቢየስ ብቻ አልነበረም።  የኢየሩሳሌም ጥፋት የዓይን ምስክር የነበረው ዮናታን የሚባል አይሁዳዊ መምህርም (ራባይ)  -- "ሼክናህ" ክብር ለሦስት ዓመታት ተኩል ቤተ መቅደሱን ለቅቆ ነበር ብሏል።

እስራኤል ንስሐ እንዲገቡ ተስፋ በማድረግ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ አደረ፣ እነርሱ ግን እምቢ አሉ፤
"እናንተ ከዳተኞች ልጆች ተመለሱ" [ኤር.  3፥ 14]፤  "ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ" (ሚል.  3፥ 7) እያለ፣ ቤት ኮል ሲሉ የሚጠሩት ያ ልዕለ ተፈጥሯዊ የሆነ ድምፅ] ከሰማይ መጣ፤ ያኔም "ንስሐም ባልገቡ ጊዜ፡— ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ" (ሆሴዕ 5፥ 15)፣ አለ። (Midrash Rabbah, Commentary on Lamentations 2:11). -- Secrets of Golgotha, by Ernest L. Martin. 84.

ከሮማውያን ጋር ጦርነቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደሱ በመውጣት ተለይቶ የሄደውን “ሼክናህ” የተሰኘው የያህዌን ሃልዎት እውነታ የጻፈ ሌላም ጸሐፊ ነበር።  ጆሴፈስ በ66 ዓ.ም የጸደይ ወቅት በቤተመቅደስ ውስጥ አንዳንድ አስገራሚ ክስተቶች እንደተከሰቱ በዘገባው ጠቅሷል። ሲጽፍም ከያህዌህ “ሼክናህ” እና ከቤተ መቅደሱ ጋር የተያያዙ ሦስት ተአምራትን ዘግቧል -- በእያንዳንዱም  ዘገባው "ሼክናህ" ከቅድስተ ቅዱሳኑ ወጥቶ እየተለየ እንደነበር በግልፅ አሳይቷል።

War 6. 290 እንደሰፈረው፣ በ66 ዓ.ም. ከፋሲካ በዓል በፊት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ “ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ለሰላሳ ደቂቃ ያህል የቆየ ታላቅ ብርሃን በመሠዊያው ላይ አበራ፣ አስከትሎም ከዚያ ወጥቶ ሄደ። ሲናገርም፣ "የአይሁድ ቅዱሳን ጸሐፍት ይህንን ምልክት አስመልክቶ ሲናገሩ ለቤተ መቅደሱ መጻኢ እድል መጥፎ ምልክት አድርገው ተርጉመውታል" ብሏል። ልክ በምድረ በዳ ሳሉ የማደርያውን ድንኳኑን ነቅለው ወደ ሌላ ቦታ ሲያጓጉዙ እንደነበረው  ሼክናህ የሆነው ክብርም ከማደሪያው ርቆ ሲሄድ ነበር ።

ጆሴፈስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል “ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ (በፋሲካ በአል ወቅት) ሃያ ሰዎች ሆነው በጉልበ የሚከፍቱትና የሚዘጉት ግዙፍ የኒካኖር የናስ በሮች ገና መንፈቀ ሌሊት ሳለ በራሳቸው ፈቃድ ተበርግደው ተከፈቱ። (War 6. 293-295)። ይህም ክስተት ደግሞ በቤተ መቅደሱ ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንደሚያሳይ ተተርጉሟል። ከዚያም፣ ከሃምሳ ቀናት በኋላ ቆየት ብሎ፣ በበዓሉ አምሳ  ዕለት፣ ሌሎቹ ምልክቶች እንደሚያሳዩት የሼክናህ ክብር ቤተ መቅደሱን እየለቀቀ መሆኑን የሚያሳይ የመጨረሻው ምልክት ተሰጠ።

ከዚህም በላይ በዓለ ሃምሳ እየተባለ በሚጠራው በዓል ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም እንደ ልማዳቸው ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛው አደባባይ ሲገቡ፣ ያኔ በመሸ ጊዜ፣ ግርግርና ጩኸት መኖሩን በመጀመሪያ እንዳወቁና ከዚያም በኋላ  "ኑ፣ ከዚህ እንሄዳለን" ሲል የብዙ ሕዝብ ድምፅ የሚመስል እንደሰሙ ዘግቧል (War 6. 299)።

የጆሴፈስን መረጃ ሌላው የዓይን ምስክር የነበረው ራባይ ዮናታን ነው፤ የዚህ ሰው ምስክርነት በጥንቷ እስራኤል ስለተፈጸሙ ክንውኖች የበለጠና የተሟላ ግንዛቤን ይሰጣል። የጆሴፈስን መረጃ ከዚህ ሰው ምስክርነት ጋር አጣምረን ስንመለከተው ከፀደይ ወራት 66 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 69 ዓ.ም አካባቢ፣ ቤተ መቅደሱ በሮማውያን ከመፍረሱ ከስምንት ወራት በፊት ለሦስት አመት ተኩል "ሼክናህ" የሆነው ክብር በቀጥታ ወደ ደብረ ዘይት ሄዶ ከተራራው ጫፍ ላይ  - እንደቆየ፣ ከዚያም ወደ ሰማይ ተመልሶ እንደሄደና ይህ የራባይ ዮናታን ምክርነት እስከ ተጻፈበት ጊዜ ድረስም ወደ ምድር እንዳልተመለሰ እናያለን። 

¶ የዳግመኛ ምጽአቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክሮች፦ 
የሰው ልጅ (ኢየሱስ) አስቀድሞ እርሱና ሐዋርያቱ እንደተነበዩት የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆ ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ያኔ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ በክብር መጥቷል፡- ማቴ  13፥ 41-43፤ 16፥ 27-28፤  24፥ 29-31፤  25፥ 31፤ ማርቆስ 8፥ 38፤ 9፥ 1፤ 13፥ 26-27፤ ሉቃስ 9፥ 26-27፤  1 ተሰ 4፥ 13-18፤ 2 ተሰ 1፥ 4-10፤ ይሁዳ 14-15

¶ እነዚህ ሁሉ ነገሮችም የሚጠበቁትና የሚፈጸሙት ደግሞ ራሱ ኢየሱስ በነበረበትና በሐዋርያቱ ትውልድ ውስጥ እንደነበር አዲስ ኪዳን በግልጽ ያስተምራል፦ ማቴ  11፥ 16፤ 12፥ 38፣ 41-45፤ 16፥ 4፤ 23፥ 36፤  24፥ 34፤  ማርቆስ 8፥ 38፤  9፥ 1፤ 13፥ 30፤ ሉቃስ 7፥ 31፤ 11፥ 29-32፣ 50-51፤ 17፥ 25፤ 21፥ 32፤ የሐዋርያት ሥራ 2፥ 40፤  ፊል  2፥ 15፤  ዕብ 3፥ 9-11።

ጥቂት መጻሕፍት ልጠቁማችሁ፦

- The New Complete Works Of Josephus, Translated by William Whiston.
_ Eusaebius, The History of the Church 
 - Mason, Steve. Josephus and the New Testament
- Stevens, Edward E. Final Decade Before the End. Jewish and Christian History Just Before the Jewish Revolt.
- Barrett, C.K. The New Testament Background: Selected Documents.
- Bruce, F.F. Israel and the Nation.
- Bruce, F.F. New Testament History.
- Gentry, Kenneth L., Jr. Before Jerusalem. Fell.



 

Friday, June 30, 2023

የብልጥግናና የጤንነት "ወንጌል"

የጥፋት ወንጌል

"ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ።  እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።" 2 ቆሮ 12፥ 7-10

፩.

እንደ መነሻ የጠቀስኩትን ይህንን የንባብ ክፍል ኋላ ላይ እመለስበታለሁ። ልንሰማው በሚያስፈልገን የመዳን ወንጌል ጤናማ ቃልና እኛ ልንሰማው በምንፈልገው "ጥሩ ዜና" መካከል ልዩነት አለ። እንደሚታወቀው ሰዎች የሆንን ሁሉ ልንሰማው የሚያስፈልገን መልካሙ የምስራች አንድ ነው። ነገር ግን በዚህ አለም ብዙ አይነት ጥሩ ዜናዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እስቲ ሰው ሁሉ ሊሰማው የምፈልገውን ጥሩ ዜና ላሰማችሁ።  ምናልባትም ይህ አንዳንዶቻችሁ ሰምታችሁት የማታውቁት፣ ብዙዎቻችሁ ግን አሁንም ድረስ እንደ እግዚአብሔር መልዕክት የምትቆጥሩት ስሜት ኮርኳሪ ምርጥ ዜና ሊሆንላችሁ ይችላል።  ልትሰሙት ዝግጁ ናችሁ?

 "እነሆ እግዚአብሔር ሁላችሁም ጤናማ እንድትሆኑ፣ በሽታም እንዳያገኛችሁ፣ ሀብታም እንድትሆኑ፣ ድህነትም እንዲርቃችሁ፣ ከሥቃይ ነፃ እንድትሆኑ እና በምትሠሩት ሁሉ እንድትበለጽጉና በብዙ እንድትከናወኑ ፈቃዱ ነው፤" የሚል ዜና ነው። ይህ ታዲያ ጥሩ ዜና ነው ወይስ መጥፎ? ይህ እኛ መስማት እጅጉን ደስ የሚለን ዜና ነው፣ አይደል? ይህ ታዲያ ምን ክፋት አለው?  እንዲህ ያለው ዜና የያዘውን መልእክት መስማት አትወዱምን? በርግጥም ትወድዳላችሁ እንጂ ለምን አትወዱም?  እግዚአብሔር ሁላችሁም ጤናማ እንድትሆኑ፣ ሀብታም እንድትሆኑ፣ ከሥቃይ ነፃ እንድትሆኑ እና በምትሠሩት ሁሉ እንድትበለጽጉ የሚፈልግ መሆኑ መልእክቱ አሪፍ ዜና ካልሆነ ታዲያ ምን ሊሆን ይችላል?

የዚህ መልእክት ብቸኛው ችግር ግን እውነት አለመሆኑ ነው። እውነት ደግሞ መስማት ደስ ከሚለንና ከምንፈልገው ነገር በላይ ዋና አስፈላጊ ነው። አዎን፣ በተለይም ይህ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቱን ስንናገር የሚሰራ ነው።

እስቲ ልጠይቃችሁ፣ ስለ ጤንነት/ብልጥግና ወንጌል ምን ይሰማችኋል?  እንዲህ ላለው ጉዳይ ግድ የለሾች ናችሁን?  እሱንስ ሳይጎረብጣችሁ ታግሶ ለመስማት አቅም አላችሁን? ሲሰሙት ለጆሮ የሚጥም ከመሰለ፣ ቃሉን እያጣመመ ከሚሰራ እንዲህ ካለ ትምህርት ጋር በጽኑ ካልተጣላችሁ፣ እንዲህ ያለው ትምህርት በንዴት ካላቃጠላችሁ፣ ከሁለት ነገሮች አንዱ በህይወታችሁ እውነት ነው ማለት ነው፦ 1ኛ. የብልጽግና ወንጌል የሚያስተምረው ግልሙትና ምን እንደሆነ አልገባችሁም ወይም ጨርሶ አታውቁትም ማለት ነው፤ አልያም 2ኛ. ወንጌል ራሱ ከመሰረቱ አልገባችሁም። ወንድሜ ሆይ፣ ወንጌልን በአግባቡ ተረድተኸው ከሆነ ያኔ ሕያው ሆነህ የጤንነት/ብልጥግና ወንጌል አስተማሪዎች የሚሰብኩትን አደጋ በንቃት ታውቃለህ፤ ራስህንም ሆነ በአጠግብህ ያለውን ክርስቲያን ከአደጋው ለመጠበቅም ትተጋለህ። ካልሆነ ግን ሞት በመሰለ ከባድ እንቅልፍ ተይዘሃል፣ ሳትቀበር በፊት ፈጥነህ መንቃት አለብህ። ዝም ብለን ተጎልተን አገሩን የሞላው የሀሰት ወንጌል ህዝባችንን እየጠራረገው ነው። "ሰይፍ ከዋጠው ሕዝብ ሁሉ ይልቅ ዱር ብዙ ዋጠ" (2ሳሙኤል 18፥ 8) እንደተባለ ኮምኒዝምና መከራው ካደረሰው ጥፋት በላይ የነጻነቱ ዘመን የትምህርት አሰስ ገሰስ ብዙዎችን ውጧል።

እኔ እንደማስበው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን የተናገረው ቃል ዛሬ እኛን የሚመለከት ይመስለኛል፡-

"ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።" (ፊልጵስዩስ 1፥ 27)

ጳውሎስ ለእነዚህ አማኞች "ጸንታችሁ ቁሙ" የሚል ምክር ይሰጣቸዋል። ይህም ስቴኮ (Steko) ከሚለው የግሪክ ቃል የተተረጎመ ነው።  ይህ ቃል የሚልቴሪ ሳይንስ ሙያዊ ቃል ሲሆን፣ ትርጉሙም "በጦርነት ውስጥ ያለመናወጥ መቆም፣ መረጋጋት" ማለት ነው። የገጠመው ጦርነት የቱንም ያህል ቢከፋ ስፍራውን ለማይለቅና ከቦታው የማይነቃነቅ ወታደርን ለመግለጥ ጥቅም ላይ ይውላል።

ጳውሎስ በተሰጣቸው የወንጌል ባላደራነታቸው፣ ከስህተት ወይም ከኃጢአት ጋር ባላቸውም ተጋድሎ ጸንተው እንዲቆዩ፣ በትምህርታቸውም ሆነ በምግባራቸው ሳይነቃነቁ እንዲቆሙ እየነገራቸው ነው። ይህ ወታደራዊ የሆነ ያነጋገር ዘይቤ በከፍተኛ ጥቃት ውስጥ እያሉ ቢሆን እንኳ ገዢ ቦታን ሳይለቁ ገትሮ ከመያዝና ወጥሮ ከመዋጋት ጋር የተያያዘ ነው። “ጸንታችሁ ቁሙ” ሲልም በአእምሮው ውስጥ በአስተምህሮ እና በሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች ላይ  የማመቻመች ፈተናን የመቃወም ነገር አለው። 

ጳውሎስ “ለወንጌል እምነት አብራችሁ ተጋደሉ” በማለት ይነግራቸዋል። “በአንድነት መጋደል” የሚለው የግሪክ ቃል "ሱናትሊዮ" (sunathleo) ከሚለው ሁለት ቃል የተገኘ ሲሆን፣ እሱም sun “በጋራ” እና athleo "ውድድርን ወይም ፉክክርን መሳተፍ" ማለት ነው። አትሌቲክስ የተሰኘው ስፓርታዊ ውድድርም ስያሜውን ያገኘውን ከዚሁ የግሪክ ቃል ነው።

ይህ ተጋድሎ በጦር ግንባር እና በጨዋታ ሜዳ ላይ እንደሚደረግ የሕይወትና የሞት ሽረት ትግል እንዳለበት የግላዲያተር ፍልሚያ ከውድድርና ከፉክክር ጋር የተያያዘ ነው።  ይህም አብሮ መጋደል በቡድን ተጣምሮ ለማሸነፍ ጥረትን ሁሉ የማሳየት  ጥሪ ነው። በወንጌል የመጋደልን ጥሪ እና አደራ ያላወቀ አማኝ የወንጌልን እውነት እያመቻመቸ ለአለም የሚመች ማህበረረባዊ ወንጌል (social gospel) አቀንቃኝ ይሆናል። እኛ የወንጌል አማኞች ግን፣ “በአንድ መንፈስ ጸንተን በአንድ ልብ ለወንጌል እምነት አብረን የምንጋደል” መሆን አለብን። በዛሬው ዘመን ክርስትና ግን የወንጌል መልእክት ምንነት ግልጽ አይደለም፣ ማንኛውም ሰው ወንጌል ምን እንደሆነ የብልጭታን ያህል ፍንጭ ቢኖረው በጤንነት/ብልጥግና ወንጌል ላይ አሰላለፉን ባስተካከለ ነበር።

ወንጌል እግዚአብሔር በልጁ ሞት በኩል ለኃጢአተኛው ሰው ቤዛ ሆኖ እንዳቀረበ የሚታወጅ የምስራች ነው።  ይህ ቤዛነት ለሚያምኑ ሁሉ በጸጋ ይታደላል።  በክርስቶስ ላይ የሚያርፈው እምነት በአእምሮው፣ በአካሉና በመንፈሱ የተበላሸውን ኃጢአተኛ ወስዶ ከኃጢአቱ ሁሉ ያነጻዋል፣ በእግዚአብሔርም ፊት ጻድቅ ያደርገዋል፣ የዘላለምንም ሕይወት ይሰጠዋል።  ያ ነው እንግዲህ መልካም ዜና ነው የምንለው።

፪.

ክርስቶስ የኃጢያት እዳዬን እንደከፈለልኝ አምናለሁ ከዚህ የተነሳ ኑሮዬና ደረጃዬ ፍጹም ተለውጦ ከችግር ሁሉ ተላቅቄ ሁሉ መልካም ይሆናል ብሎ ማሰብ ግን ፈጽሞ አይሰራም፤ እስቲ አሁን የምኞትና የቅዠት ጥግ ካልሆነ በቀር የኃጢአት ዕዳ ክፍያና የኑሮ ደረጃ ለውጥ ምን ያገናኛቸዋል? እንዲህ ያለው እብደት ፈጽሞ የክርስቶስ ወንጌል አይደለም። በክርስቶስ የሙስቀል ሞት የተገኘው የኃጢአት ዕዳ ክፍያ ከዘላለም ኩነኔ መዳኛ እንጂ ከችግር ነጻ ሆኖ የመኖር ዋስትና አይደለም። አሁንም የእለት ጉርስ ማጣት፣ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ ያለቀ ጫማና የተቀደደ እራፊ፣ የተኛ የመኪና ጎማ፣ የተሰበረ አጥንት፣ የታመመ አካል ሊኖረኝ፣ የትዳር ጭቅጭቅ፣ የገንዘብ እጥረት ትግል ሊኖርብኝ ይችላል፤  እውነታው ደግሞ ይኸው ነው። የአገር ቀበኞች የደኃውን ገንዘብ ከመመዝበር እጆቻቸውን ካልሰበሰቡና በላብ  ሰርቶ በኢኮኖሚ ከመለወጥ ውጪ ህይወት እንደሁ ሁልጊዜ ትግል ናት! 

ነገር ግን የጤንነት/ብልጥግና ወንጌል አቀንቃኞች ደረጃው እየጨመረ በሚያድግ እምነት እግዚአብሔር በከፍተኛ ጤና እና ሀብት አትረፍርፎ እንደሚከፍል ደፍረው ያስተምራሉ።  ሲናገሩም እግዚአብሔር የዘላለም ሕይወትን ብቻ ሳይሆን ብራንድ ሀብታም እና ህመም የማያውቀው ፍጹም ጤናማ እንድትሆኑ፣ እንዲሁም ከየትኛውም ስቃይና መከራ ነፃ እንድትሆኑ፣ ከችግር ተላቃችሁም እንድትኖሩ ይፈልጋል ሲሉ በአዎንታዊ ማነቃቂያ እያባበሉ ያስተምራሉ። 

እንዲህ ያለ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያፈነገጠ ነገር "ወንጌል አማኝ" ነን በሚሉት ዘንድ እንዴት ሊታሰብ ቻለ?  እንዴትስ ስር ሰዶ በመሰራጨት "ወንጌላውያን አማኞችን" ከክርስቶስ ወንጌል ሊያርቃቸው ቻለ? በእውነቱ ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው። ይህንን ለማስተዋል እንዲቻለን በአገራችን እንደ ጉድ የፉሉትን አነስተኛና ጥቃቅን እባብ የብልጥግና ሰባኪዎች ላይ ጊዜ ከምናጠፋ ዘንዶ እና አናኮንዳ የሆኑ አባቶቻቸውን፣ ትምህርቶቻቸውንና ልምምዶቻቸውን ነቅሰን እያወጣን ስለ ብልጽግና ወንጌል ታሪካዊ ዳራ ጥቂት ነገር ለማለት እንሞክራለን። ከምዕራባውያን የቴሌቪዥን ሰባኪዎች በተቀዳ ትምህርትና በተኮረጀ ስታይል የሚያቅራሩብንን የአገራችንን የብልጥግናና የስኬት እርኩስ ወንጌል ሰባክያንን ተውት አድርገን ምንጫቸውን እንመርምር።

እንደ ቅደም ተከተላቸው የመጀመሪያዎቹ የአዎንታዊ አስተሳሰብ አራማጆች፣ ፊኒያስ ፒ. ኩዊቢ እና ሜሪ ቤከር ኤዲ፣ የመሰሉ የአዲስ አስተሳሰብ እንቅስቃሴን እና የክርስቲያን ሳይንስ መንፈሳዊ አስተሳሰብ መስራቾች ቀደምት ፈጣሪዎች ነበሩ።  በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ የቤቴል መጽሐፍ ቅዱስ ተቋም መሥራች እና መጋቢ ኤሴክ ዊልያም ኬንዮን ስለ ክርስቶስ የተጠናቀቀ ሥራ በሚሰብክበት ጊዜም ተመሳሳይ የሆኑ የአዎንታዊ ሐሳቦችን አካትቶ ያስተምር ነበር።  ኬንዮን ክርስቲያኖች ስሜታዊ እና አካላዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት “አዎንታዊ ኑዛዜ” (positive confession) ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጽፏል። ሲናገርም "እኔ የተናዘዝኩትን (ያልኩትን) ነኝ/አለኝም" ይል ነበር።

በ1930ዎቹ ኬኔት ሀገን የቃል-እምነት እንቅስቃሴን ሲጀምር የኬንዮንን ትምህርት እንዳለ በመቅዳት ከጴንጤቆስጤ እምነትና አስተምህሮ ጋር ቀይጦ ማስተማርን ጀመረ።  የእግዚአብሄር ማኅበረ ቅዱሳን የተባለ ቤ/ክ መጋቢ የነበረው ይህ ኬኔት ሀገን ክርስቲያኖች በቂ እምነት በማሰባሰብ ሀብታም መሆን እንደሚችሉ ሲያስተምር ይደመጣል።  "በእምነት በለው፣ አድርገው፣ ተቀበለው፣ አውራው" የሚሉ የቃል እምነት መርሆዎችን ፈብርኮ ክርስቲያኖችን በቅዠት አለም ያሰክራችው ነበር።  በእምነት የሚነገሩ ቃላቶች መሟላት እንዳለባቸው የሚገልጽ “ጥራው" እና "በይገባኛል ውረሰው” የሚሉ መፈክሮችን ያስከተለውን “የሬማ አስተምህሮ” አስፋፍቷል።  ይህን ተከትሎ በ1960ዎቹ የኦራል ሮበርትስ ወጣት ተባባሪ ኬኔት ኮፕላንድ እምነት “ኃይል” እንደሆነ ማስተማር ጀመረ፤ እሱም ጮክ ባለ ድምጸት በይሆናል አይነት ስሜት ሲናዘዝ (ሲመሰከር) የተጠበቀውን ቁሳዊ ውጤት ያመጣል፣ ይል ነበር። በሁለት አስርት አመታት ውስጥ፣ ይህ Word-Faith ልክ እንደ ካንሰር ሆኖ ወደ ትልቅ የካሪዝማቲክ እምነት ዘር አድጓል።

የእነዚህን ሰዎች አስተምህሮ እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል፡- እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው እንደ ሉዓላዊ ፍጡራን “የእግዚአብሔር ዓይነት እምነት”ን በመጠቀም ነገሮችን በመጥራት ወደ መኖር እንዲያመጣቸው፣ በብልጽግናና በስኬት የመኖር ችሎታ ያለው አድርጎ “በእግዚአብሔር ደረጃ” (ወይንም እንደ “ትናንሽ አማልክት”) እንዲሆን ነው። ነገር ግን በገነት ውስጥ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ እና የሰይጣንን ተፈጥሮ በመያዝ ይህንን እድል አጥተናል። ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነና፣ በመንፈስ ሞተ (በዚያም የሰይጣንን ባሕርይ ለብሶ/ ሰይጥኖ)፣ ወደ ሲኦል ወረደ፣ “በሲኦልም ዳግመኛ ተወለደ”፣ እንደገናም በእግዚአብሔር ባሕርይ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፣ ከዚያም መንፈስ ቅዱስን ላከ።  በዚህም ትስጉዑቱን በአማኞች ውስጥ ሊያባዛ ይችላል፣ ከዚህም የተነሳ አማኞች እንደ እርሱ ትናንሽ አማልክት የመሆን ጥሪያቸውን ይፈጽማሉ። አሁን የተጠራነው እንደዚህ አይነት ህይወት እንድንለማመድ ስለሆነ በሁሉም የህይወታችን ዘርፍ ስኬታማ መሆን ይኖርብናል። እንግዲህ እነዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እንደሚያስተምሩት በዕዳ የመያዝ ሁኔታ ቢሆን፣ ወይም ጤና የማጣት ጉዳይ፣ ወይም ትዳርን የማጣትና የቤተሰብ መበተን ሁኔታ፣ እንዲሁም ማናቸውም እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮችን በተመለከተ የእግዚአብሔርን ተስፋዎች "በማወጅ" መፍትሄን አለማግኘት ያው የእምነት ማነስን ያሳያል፣ ይላሉ። ከላይ ያለው አስተምህሮ አንዳንድ ገጽታዎች ከአስተማሪ ወደ አስተማሪ ሊለያዩ ቢችሉም ቅሉ፣ አጠቃላይ ዝርዝሩ ግን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ያው አንድ አይነት ነው።

የዚህ ዓይነቱ ሥነ-መለኮት ከምዕራቡ አለም እየናኘ ድንኳኖቹን በማስፋት ካስማዎቹንም በማርዘም ወደሩቅ ደርሷል። መላውን የሩቅ ምስራቅ ክርስትናና የአፍሪካን ምድር እያጥለቀለቀ በተለይ ከኮምኒዝም ስደት በኋላ በምድራችን በኢትዮጵያ ያለቅጥ ተሰራጭቷል። ይህ ትምህርት በእርግጥ ሰዎችን በጤናና በስኬት እያባበለ ይማርካል፣ ትምህርቱና ልምምዱ ከእምነት በስተቀር ምንም ስለማይፈልግ እርሱም ደግሞ በቂ እምነት ከሆነ፣ ከዚህ የተነሳ ሰዎች ባለጠጋና ጤናማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተስፋ ይሰጣል። እንዲህ ያለው መልዕክት "በህልሙ ቅቤ እንደሚጠጣ ደሀ"  ሰዎች ሊሰሙት የሚፈልጉት አይነት ስለሆነ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ መልእክት ሆኖላቸዋል።

የዚህ ጠማማ ወንጌል አንዳንድ አስተማሪዎች የሚሉትን ስሙ፦ "እኔ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ --እስከፍጻሜዬም እንደዚያም ነው ብዬ ማንም አማኝ በብሽታ እንዳይታመም በኢኮኖሚም እንዳይቸገር፣ እያንዳንዱም አማኝ በዚህ ምድር ላይ እድሜው ሳይቀጠፍ ሙሉ ህይወቱን ቆይቶ እንዲኖር፤ በታላቅ ፍቅሩ እና በታላቅ ምህረቱ የተገለጠ የአባታችን የእግዚአብሔር እቅድ ነው ብዬ በዚሁ እምነት እሞታለሁ፤ እያንዳንዱም አማኝ በመጨረሻ በኢየሱስ ሆኖ መተኛት አለበት" (ኬኔት ኢ ሃጊን፣ ስለ መለኮታዊ ፈውስ ማወቅ ያለብህ ሰባት ነገሮች፣ ገጽ 21)።

ኬኔት ኮፕላንድ "የብልጽግና ህጎች" በተሰኘው መጽሃፉ በገጽ 51 ላይ "እንዲያበለጽግህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ መገንዘብ አለብህ። ይህም ለአንተ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅህ ነው፣ እውነቱን ለመናገር እስካሁንም ከሱ አለመካፈልህ ትልቅ ሞኝነት ነው" ይላል።

የብልጽግና ወንጌል ዋና ስህተት አንዱ ማዕከላዊ መርህ ፦ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ክርስቲያን በገንዘብ ባለጸጋ እንዲሆን ፈቃዱ ነው፣ ስለዚህም አማኝ በድህነት መኖሩ እግዚአብሔር ካሰበለት ፈቃዱ ውጭ መኖር ነው የሚለው ነው። በተለምዶም ራሱን የሸሸገበት አንዳች ቦታ፦ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን ሁል ጊዜም ቢሆን የመጀመሪያውንና የታላቅነትን ደረጃ መያዝ አለብን፣ ራስ እንጂ ጅራት ስላልሆንን ከሁሉ ከፍ ያለውና መልካም የሆነው ሁሉ ሊኖረን ይገባል። ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመጣውም ይህ ብቻ ነው! የሚለው ማረጋገጫው ነው። ሰሞኑን እንደውም አንዱ ያገራችን ጉድ ድህነት አርነት መውጣት የሚጠይቅ ሰይጣናዊ እስራትና እርግማን ነው እያለ ጣቃውን ሲቀደድ በሶሻል ሚዲያ ሰማሁት። እንዲህ ያለው ሰባኪ ነኝ ባይ በጥልቅ ድህነት ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን የሜቄዶንያን ቅዱሳን ምን ሊላቸው ነው? ምነው ጳውሎስስ ቢሆን ከዚህ እስራት ሳይፈታቸው ቀረ?

እነዚህ የሐሰት ወንጌል አስተማሪዎች በአብዛኛው የእግዚአብሔርን ቃልና ተገቢነት ያለውን አተረጓጎም ችላ ቢሉም፣ ያንን እርኩስ ትምህርታቸውን ግን እዚህም እዚያም በተቆነጠረ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶች ለማስደገፍ ይሞክራሉ። መቼም የቃል እምነት መልእክትን የሚያስተላልፉ ማናቸውም የሕትመት ሥራ ሆነ ወይም አስተማሪ ነኝ ባይ ከ3ኛ ዮሐንስ መልዕክት ቁጥር 2 መጥቀስ ቋሚ ልማዱ ነው፤ ጥቅሱም "ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ።" ይላል።

የብልጽግና ወንጌል አስተማሪዎች ይህን ጥቅስ ልክ የአዲስ ኪዳን ዶክትሪን የሆነ ያህል፣ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ከነፍሳቸው የመከናወን ሁኔታ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መጠን እንደሚበለጽጉ በእርግጠኝነት ያሳያል ሲሉ ይተረጉሙታል። በሌላ አነጋገር፣ በአካሄድህ ከእግዚአብሔር ጋር የምትራመድ ከሆነ፣ ማለትም ነፍስህ ከተከናዋወነ፣ በውጤቱ ኑሮ የተከናወነለት ባለጠጋና የማይታመም ጤነኛ ሰው ትሆናለህ።  በድህነት ውስጥ የምትኖር ከሆነ ግን ገና አሁንም በኃጢአትህ ውስጥ መሆን አለብህ፤ እንደ ማለት ነው፣ ይላሉ።

ይህ ጥቅስ ዮሐንስ ለወዳጁ ለጋይዮስ ያቀረበው ሰላምታና የጸሎት ዘገባ ብቻ ነው እንጂ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለክርስቶስ አካል ሁሉ የተሰጠ የእምነት መግለጫ ወይም አቋም አይደለም፤ ዶክትሪን ሆኖ እንደ ተስፋ ቃል ወይም እንደ እምነት እንቀጽ መቆጠርም የለበትም። ሰላምታንና የጸሎት ርዕስን ሁሉ እየሰበሰቡ ዶክትሪን ለማድረግ መሞከር በእውነቱ አለመማር ብቻ ሳይሆን፤ ሁሉም የተጻፈው ለእኔ ነው የሚል ብልጣብልጥነትና ራስ ተኮርነትም ጭምር ነው። የብልጥግና ወንጌል ክፋቱ ሰዎችን ራስ ወዳድና ስግብግብ ማድረጉ ነው

ተመልከቱ፣ ይህ መልእክት የተቀረጸው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በነበረው የተለመደ የደብዳቤ አጻጻፍ ቅርጽ ነው። ዊልያም ባርክሌይ ይህንን በ3ኛ ዮሐንስ 2 ላይ ያለውን የተለመደ የደብዳቤ አጻጻፍ ቅርጽ እውነታ የሚመለከተው አንድ የመርከብ ካፒቴን ሸኝዎቹን ሲሰናበት ከሚጠቀምበት የስንብት ቃልና አብረውት የሚጓዙትን ሲያበረታታ ከሚጠቀምበት ማበረታቻ አረማዊ የመልካም ምኞት መግለጫ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ሐረጎችንና ቃላትን በመጥቀስ ነው። ሃዋርድ ማርሻልም፣ በኒው ኢንተርናሽናል የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያው ውስጥ፣ ሽማግሌው (ዮሐንስ) ለወዳጁ ለጋይዮስ መልካም ምኞቶችን በመግለጽ በጊዜው የነበረውን ባህላዊ ወግ እና እሴት እንደሚከተል በመግለጽ የባርክሌይን አስተያየት ያረጋግጣል። ይህ ልክ በሃገራችን ልማድ "ጤና ይስጥልኝ" ብሎ በመልካም ምኞት መግለጫ ሰላምታ የማቅረብ ሁኔታ እንጂ "የመከናወንና የጤንነት" ዶክትሪን ፈጽሞ አይደለም። ለሁሉም አማኞች ፈቃዱን በተመለከተ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሁለንተናዊ መግለጫም አዋጅም አይደለም። እንደዚያ ነው ብሎ መገመት ግን ከሥነ-ጽሑፋዊው እና ታሪካዊው አውድ ውጭ መሆን ነው። 

አስተውሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለእኛ ተጽፎልናል እንጂ በቀጥታ ለእኛ አልተጻፈም። ጳውሎስ እስክንድሮስን በአይነ ቁራኛ እንዲጠብቅ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ትዕዛዝ፣ እንዲሁም ከክረምት በፊት በርኖሱን ይዞለት እንዲያመጣ፣ ቲቶም በቀርጤስ እንዲኖር የተሰጠው መመሪያ፤ ወይም ጌታችን ኢየሱስ "ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ" ያለው፣ ወይም "በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ" ያለው፣ አልያም "በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ" ያለው እና ይህን የመሰለ ነገር ሁሉ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል አካል መሆኑ እሙን ነው፥ ዳሩ ግን እንዲህ ያለው ትዕዛዝ በቀጥታ ለእኛ የተጻፈ አይደለም። ብዙዎች ግን  ይህንን መለየት ተስኗቸዋል። የብልጽግና ወንጌል መምህራንም ይህን በተመለከተ በያዙት ግንዛቤ ግለሰብን ጠቅሶ በአድራሻው በተጻፈለት ሰላምታን በያዘ የመልካም ምኞት መግለጫና ለሁሉ በሚሆን ሉል አቀፍ ዶክትሪናል የተስፋ ቃል መካከል ያለውን ልዩነት አደባልቀዋል።

፫.

አሁን እንግዲህ ታዲያ ይህ ምንአለበት፣ በእኛ ላይስ ምን ጉዳት ሊያደርስ ይችላል? ተብሎ ይጠየቅ ይሆናል። በእርግጠኝነት ለመናገር የእግዚአብሔርን ቃል እየተማርን የምናድግ ማናችንም ብንሆን በዚህ የውሸት ወንጌል ልናምን የምንችልበት ምንም መሰረት እንደሌለን ይህንን አንድ ነገር እገነዘባለሁ፤ ይሁንና ግን ልታስተውሉት የሚገባችሁ ነገር እንዲህ ያለ የተሳሳተ ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ላይ እየናኘ የብዙወችን ልብ እየወሰደ መሆኑን ነው። በኢንተርኔት በተደረገ ጥናት 61 በመቶ የሚሆኑት የአሜሪካ ጰንጤቆስጤ አማኞች እግዚአብሔር ሰዎች እንዲበለጽጉ እንደሚፈልግ ያሚያምኑ ናቸው። "የእርስዎ ምርጥ ህይወት አሁን"፣ በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትሞ ከ4 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች የሸጠው የጆኤል ኦስቲን ድርሰት ይህንን ያሳያል። በግሌ መጽሐፍ ተራ ጎራ ብዬ አይኔን ሳማትር በየመደርደሪያው ላይ እዚህም እዚያ በርከት ብሎ አይኔን የሚያደናቅፈኝ እንደ ዚህ ሰውዬ ድርሳን ሌላ መጽሐፍ ብዙ አልገጠመኝም። 

ይህ እምነት የጰንጤቆስጤ መሰረቱን እያሰረገ ወደ ወንጌል አማኝ አብያተ ክርስትያናት ሁሉ ዘልቆ ግብቷል። በአገራችንም የወንጌል እምነት ታሪክ ውስጥም የቃል እምነት ህጸጹን አሹልኮ በማስገባት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ጰንጤቆስጤ ነው። እኔ በበኩሌ እንደ ጰንጤቆስጤ ከጤንነትና ከብልጽግና ወንጌል ጋር እርኩስ ጋብቻን የፈጸመ ሌላ እምነት አላየሁም፤ ይህም ግልሙትና እንደ ወረርሽኝ ወንጌላውያንና ካርዝማውያን ነን ሲሉ ራሳቸውን የሚጡሩትን እያዳረሰ በሁሉም ቤት እንደ ቀኖና የሚታመን እየሆነ ለመምጣት ጥቂት ስብከቶቻቸውንና መዝሙሮቻቸውን መታዘብ ብቻ ይበቃል።

እንደሰሜን አሜሪካ ባሉ አገሮች ውስጥ ትላልቆቹን ጉባኤያት ከሚመሩና ብዙሃኑ ካደነቃቸው ዝነኛ ሰባክያን ጋር በሥነ-መለኮታዊ ጉዳዮች አለመስማማት በተለይም በአሁኑ ጊዜ እንደ ሞኝነት እንደ እብደትም  ሊመስል ይችላል። ተመልከቱ ሠላሳ ሺህ የሚሆኑ ጎልማሶች በየእሁዱ የጆኤል ኦስቲንን ስብከት ለመስማት በቤተክርስቲያኑ ይገኛሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ በየቤታቸው ሆነው የእሱን ብሔራዊ እና የዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ስርጭቶችን በቻናሎቹ ይከታተላሉ። በእርግጠኝነት ይህ ለቁጥር የሚያታክት ተከታይ ያለው ሰው በትክክለኛው መንገድ ላይ የመሆኑ ምልክት ነው ብሎ ማንም ሰው መገመት ይችላል። እውነታው ግን ይህ አይደለም! ቢከፍቱት ተልባ የሆነ ይህ ሰው ኃሰተኛ የምኞት ወንጌል እየሰበከ ያለ የስህተት አስተማሪ ነው።

ጆኤል ኦስቲን ያተረፈው እንዲህ ያለ እውር ተወዳጅነት በእውነት በአሜሪካ ውስጥ ላለው አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ አይነተኛ ማረጋገጫ ነው። ይህ ሰው በሚያቀርበው ዲስኩር የሚደመጠው አነቃቂ ንግግሩ በእውነት ስለ ኃጢአታቸው የማይወቀሱና ሊወቀሱ የማይወዱ ሰዎችን ጆሮ ይማርካል። እነዚህም ንስሃ መግባት እና ኃጢአታቸውን መጥላት የማይፈልጉ ናቸው። ስለዚህም ጆኤል ኦስቲን፣ ሆነ ብሎ የእግዚአብሔርን እውነት ርዕሰ ጉዳዮች በሙሉ በስብከቱ ሜኑ ውስጥ አያካትታቸውም። በዚህም ምክንያት ከእግዚአብሔር  ክብር ወይም ክርስቶስ ለኃጢያታችን ከከፈለው የኃጢአት ዕዳ ክፍያ ጋር የማይገናኝ ሁለመናው ራስን ስለ ማሻሻል የሆነ፣ የተዛባና፣ ከረሜላ ከረሜላ የሚል "የምኞት ወንጌል" ያቀርባል። ይህ የምኞት ወንጌል ፈጽሞ ወንጌል አይደለም፤ እውነት እላችኋለሁ ግማሹንም ያህል እንኳ ወንጌል አይደለም። ለዚያም ነው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚፈልጉትን የምኞት ወንጌል ለመመገብ ወደ ስፍራው የሚጎርፉት፣ እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች በቲቪ የሚመለከቱት። አስተውሎ ለተከታተለው ሰው፣ የዚህ ሰው ወንጌል ቅዱስና የተፈራ አምላክ የለውም፣ አስፈሪውን መለኮታዊ ፍርድም አያቀርብም፣ የስርየት አስፈላጊነትንም አያሳይም። ምናልባት በእርሱ ስብከት የሚነቃቃ ይኖር ይሆናል እንጂ ንስሃ የሚገባና ከክፉ ስራው ተጸጽቶ የሚመለስ አንድ ሰው የለም። በስብከቱም ራስን ስለመውደድ እንጂ ለራስ ወዳድነት ስለመሞት ፈጽሞ አይናገራትም፣ በእኔነት ላይ ያተኮረ፣ እኔ፣ እኔ የሚለው ስብከቱ ሲደመጥ እውነተኛውን ወንጌል በሚያውቁ ሰዎች ዘንድ እንጨት እንጨት ይላል።

የሰው ሃይማኖተኛ ዝንባሌ ሁል ጊዜ ለገዛ ራሱ ጥቅም ሲል የገዛ ፍላጎቱን የሚያሟላለትን  አማላክ ይፈበርካል። ወንጌል ካልገባህ የፈለግኸውን የሚሰጥህንና የአንተ አገልጋይ የሆነ አምላክ ለመፈልሰም አትቦዝንም። ይህ ሰዎችን በምኞት የሚያጠፋ የጤናና የብልጥግና ነገረ መለኮት ወንጌላዊውን ክርስትና ከደረጃው አውርዶ ዝቅተኛ ከሆነው የሰው ሀይማኖቶታዊ ዝንባሌ የማይለይ ተራ የከልት ስርዓት አድርጎታል። አምላክ በሰዎች ምርጫ እጁ የሚጠመዘዝ፣ ፈቃዱን ለመለወጥ የሚገደድ፣ በሰዎች አቀራረብ የሚታለል፣ በማባበያ የሚሸነገል፣ ሰዎች ሊቆጣጠሩትና ወደፍላጎታቸው ሊስቡት የሚችሉትና ክርስቲያኖች ለጥቅማቸው የሚበዘብዙት አይነት ከሆነ እንዲህ ያለው አምላክ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ አይደለም። እንዲህ ያለውን የተፈበረከ አምላክ የተቀበለ ክርስትና ደግሞ አፍሪካዊ ተፈጥሮ ያለውን የቩዱ ሃይማኖት ዓይነት ጣዖታዊ መልክ አለው።

ጆኤል ኦስቲን ምን አይነት ወንጌል እንደሚያስተምር መረዳት እንድንችል 30,000 ለሚሆኑ አባል ቤተ ክርስቲያኑ ከላከላቸው መልእክቶች አንዱን ወስደን እንመልከት፡-

"እርሱ ከከፈለው ዋጋ የተነሳ በድል አድራጊነት የመኖር መብት አለን።  ጥሩ ቤተሰብ መመስረት፣ ጥሩ ጤንነት ማግኘት ወደቻልንበት ግማሽ ድል ውስጥ ገብተንም ሊሆን ይችላል፣ በገንዘብ አቅማችን ውስጥ ግን ያለማቋረጥ እየታገልን እንኖራለን፤ ይሄ ግን ፈጽሞ ሙሉ እና አጠቃላይ ድል አድራጊነት አይደለም።  እግዚአብሔር በአንዱ ዘርፍ መልካም ካደረገላችሁ በሌላው ዘርፍም መልካም ሊያደርግላችሁ ይወዳል።  እንዲህ ላለው ስኬት ግን ራዕይ ይኑራችሁ። በግሌ  ብዙ ገንዘብ ያላቸውን ሰዎች አውቃለሁ፣ ጥሩ ጤንነትም አላቸው፣ በቤተሰባዊ ግንኙነቶቻቸው ውስጥ ግን እርስ በርስ መግባባት አይችሉም።  በቤታቸው ውስጥ ሁል ጊዜ ጠብና ጭቅጭቅ አለ ፣ ይህ በእውነት ሙሉ በሙሉ ድል አይደለም።  ምናልባት ደግሞ እግዚአብሔር ባርኮህ ጥሩ ቤተሰብ እና ጥሩ ስራ ይኖርህ ይሆናል፣ ነገር ግን በሰውነትህ ላይ ለዓመታት እና ለዘመናት የሚታገልህ ህመም ያለብህ ልትሆንና፣  እርሱንም እየተቃወምህ ስትጸልይ ምናልባትም ከህመምህ ነፃ እንደምትወጣ ታምን ነበር።  አሁን ግን ይህ በህይወቴ ውስጥ ዕጣ ፈንታዬ ነው…ብለህ ተቀብለኸው መኖር ከወሰንክ በጣም ብዙ ጊዜ አልፎታል፣ አንድ ነገር ግን እወቅ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንድንሆን ኢየሱስ ዋጋ ከፍሏል።  ይህ ማለት ከመጥፎ ልማዶች እና ከሱሶች ሁሉ፣ ከተስፋ መቁረጥ እና ከጭንቀት ሁሉ፣ ከድህነት እና ከእጦት ሁሉ፣ ነፃ እንድትሆን፣ ለራስህም ከፍ ያለ ዋጋ እንዳትሰጥ ከሚያደርግህ የዝቅተኛነት ስሜት ነፃ እንድትሆን ማለት ነው። እግዚአብሔር ፍጹም ነፃ እንድንሆን ይፈልጋል።  ቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ የሞተለትንና የተነሣበትን ሁሉ እንድንቀበል ይነግሩናል። እግዚአብሔር ጤናማ እና ሙሉ አድርጎሃል፣ የእኛ ቀዳሚ ስፍራም ሙሉ ነፃነት ነው... አማካኝ ቦታ ላይ እንድትሆን አለመፈጠርህን አረጋግጥልሃለሁ።  በጭንቅ ውስጥ እንድታልፍ እና ክፉንም ደጉንም ሁሉንም አይነት ነገሮች እንድትቀበል አልፈጠረህም።  ትክክለኛውን የህይወት ራዕይ ማግኘት አለብህ።  እግዚአብሔር የፈጠረህ ፍፁም ነፃ እንድትሆን፣ በአእምሮህ ሰላም እንዲኖርህ፣ በመለኮታዊ ጤንነት እንድትመላለስ፣ ጥሩ ቤተሰባዊ ግንኙነት እንዲኖርህ፣ የብድር ዕዳህን እንድትከፍልና ከብድር ህይወት ነጻ እንድትሆን፣ እንድትበዛና እንድትትረፈረፍ ነው። ይህ ሁሉ የሚገባህና ልዩ መብትህ ነው።  ከነዚህ መብቶችህ ውስጥ አንዱ አጠቃላይ ድል ነው።  ነፃ ሆኖ መኖር ያለ ጥርጥር ይገባናል፣ ይህም ማለት በአእምሯችን ነፃ ሆነን ከጭንቀት ሁሉ የጸዳን መሆን ማለት ነው። የባንክ ሂሳባችን ምንም አይነት ቢመስልም፣ ከድህነት እና ከእጦት የጸዳ መሆን ማለት ነው። አመለካከታችንም ተለውጦ እኔ እንደተባረኩ አውቃለሁ፣ የተረገምሁ ልሆንም ፈጽሞ አልችልም።  እኔ የነካሁት ሁሉ ይበለጥጋል ይሳካለታልም እንድንል ነው"።

ይህ እንግዲህ የጆኤል ኦስቲን ንግግር ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በወጉ ላልተማሩ ሰዎች ይህ ንግግር ምንም ችግር የሌለበት ሆኖ ይሰማቸዋል። የክርስቶስን ወንጌል ተፈጥሮ ስታውቀው ግን ይህ ንግግር ወንጌልን የሚበርዝ በማር የተለወሰ መርዝ መሆኑን አስተውለህ ራስህንና የሚሰሙህን ከዚህ የጥፋት ወንጌል ለማዳን ትናጠቃለህ። ልብ አድርጉ፣ በዚህ ሰው ትርጓሜ መሰረት ከእግዚአብሔር ጋር በመንፈሳዊ ብስለት መሄድ ማለት ባለጠጋ መሆን ማለት ነው፣ ጤናማ፣ የማይታመም፣ ጥሩ ቤተሰባዊ ግንኙነት ያለህ፣ ሁልጊዜ ያለ ህመምና ያለ ጭንቀት በድል አድራጊነት እየኖርክ በሁሉ ቀዳሚና አንደኛ ሆነህ እንደ ባለ መብት መኖር አለብህ ማለት ነው።  የዚህ አመለካከት ችግሩ ግን ኢየሱስ የኖረውን ህይወትና መላው የአዲስ ኪዳንን ቤተ ክርስቲያን ያለፉበትን የህይወት ትግል ያገለለ መሆኑ ነው።

የዚህን ሰባኪ ንግግር ካደመጣችሁ በኋላ፣ ኢየሱስና በወንጌሉ የምናውቀው ኑሮው ከዚህ ሰው አሳብ ጋር  እንዴት ነው ሚስማሙት? ብላችሁ ጠይቁ። በውኑ ወንጌሉ የሚያስተዋውቀን ኢየሱስ ባለጠጋ ነበርን? ደልቶትስ ይኖር ነበርን?  ፈጽሞ እንደዚያ አልነበረም!  በሶስት ዓመት ተኩል አገልግሎቱ፣ የሚጠለልበት እንኳን ሳይኖረው በምድር ላይ እየተንከራተተ በድህነት ኖረ (ሉቃስ 9፥ 58)፤ የሚያርፍበት ቤት አልነበረውም፣ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ለማግኘት ሁልጊዜም ቢሆን የሌሎች ድጋፍ አስፈልጎት ነበር።  ብዙዎች የብልጥግና ወንጌል አጋፋሪዎች ግን ይህንን የእግዚአብሔር ልጅ ኑሮ "ድህነት" ነው ብሎ ለመጥራት ይፈተናሉ።

ኢየሱስ በማበራዊ ግንኙነቱ ላይ ችግር ነበረበትን? ተመልከቱ ሁሉም የሃይማኖት መሪዎች ይጠሉት ነበር፣ የገዛ ቤተሰቦቹ ንቀውት ነበር፣ ጴጥሮስ ክዶታል፣ ይሁዳ አሳልፎ ሰጥቶታል፣ ሕዝቡም ሁሉ "ስቀለው ስቀለው" እያሉ ጮኸዋል።  ጌታ ኢየሱስ በማህበራዊ ግንኙነቱ ውስጥ ጆኤል ኦስቲን በሚናገርለት አይነት በድል አድራጊነት እየኖረ እንዳልነበር  አስባለሁ። ብዙዎች ተወዳጅነትና ከበሬታን ነፍገውታል። ከከበሩትም ሰዎች መካከል የሚበዙት በቀንና በአደባባይ ከእርሱ ጋር መታየትም ሆነ ሊተባበሩት አይፈልጉም ነበር። ኢየሱስ  የህማም ሰው ነበር። ከባድ ሥቃይ ደርሶበታል።  ተገርፏል፣ ጉሰማና ድብደባ ደርሶበታል። አዋርደው ተፍተውበታል፣ እርሱ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዲገደል በእግዚአብሔርም በሰውም የተተወ የህማም ሰው ነው።  ስለዚህ ጆኤል ኦስቲን እየተናገረለት ያለው ይህ አይነቱ የድል ሕይወት በኢየሱስ አልተኖረም። መፅሃፍ ቅዱስም በግልጽ ሲያስተምረን እርሱን መስለን መኖር እንዳለብን ይናገራል። 

1ዮሐንስ 2፥ 6 "በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።"

እንግዲህ ይህን ካደረግንና እንደ ኢየሱስ የምንኖር ከሆነ ኢየሱስ ያጋጠመውንና ያለፈበትን ዓይነት የህይወት ውጣ ውረድ እኛም ያጋጥመናል።  ክርስቶስ እንደኖረ ከኖርን ጆኤል ኦስቲን የሚሰጠውን ሃሰተኛ የድል ሕይወት ተስፋ አናይም። የኢየሱስ ነኝ የምትሉ ሁሉ ስሙኝ፣ በጤንነት ብልጥግና ወንጌል ኃሰተኛ ተስፋ ተታላችሁ ኢየሱስ በስጋው ወራት ያልኖረውን የቅምጥል ህይወት ለመኖር አታስቡ።

የጌታችን ደቀመዛሙርትስ እንዴት ነበር የኖሩት?  በአጠቃላይ የድል ኑሮ የሚኖሩ ህመም የማያውቃቸው ፍጹም ጤነኛ ነበሩን፣ ባለጠጎችስ የነበሩና በምድራዊ ፍላጎቶቻቸው ጉድለት ያላዩ ነበሩን?  በጭራሽ ቅምጥሎችም አልነበሩም ያንንም ተስፋ አድርገው አልተመኙም! ተመልከቱ  ከሐዋርያት መካከል አንዳቸውም ባለጠጋ አልነበሩም።  ሁሉም ሊታመን የማይችል ፈተናና መከራ ነበረባቸው፣ ቢያንስ የጳውሎስን ጉዳይ እንኳ ብናነሳ መሰረታዊ የቁሳዊ ጉዳዮች እጦት እና ከባድ የጤና ችግሮች ለህይወቱም አስጊ የነበሩ ተስፋ አስቆራጭ ከፍተኛ ፈተናዎች ደርሰውበታል።

ሐዋርያው ​​ጳውሎስን ከእግዚአብሔር ጋር በመልካም ኅብረት የተራመደ፣ ነፍሱ የተከናወነለት የእግዚአብሔር ሰው ነበርን?  አዎ በሚገባ ነበር። እግዚአብሔር ራሱ በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት እያደረገ፣ ለድውዮችም ከአካሉ ላይ ጨርእቅ ወይም ልብስ ይወስዱ እንደነበር እናውቃለን። አብዛኛውን አዲስ ኪዳንን እንዲጽፍ እግዚአብሔር ጳውሎስን በብዙ ተጠቅሞበታል።  ጳውሎስ ግን በማህበራዊ በግንኙነት ላይ ችግር አጋጥሞት ያውቃልን? አዎ። በእርግጥም እንዲህ ያለው ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው በሰዎች መተውና መረሳት ደርሶበት ያውልቃ፤ አመዛኙን ህይወቱን ያሳለፈውም  ወህኒ ቤት ውስጥ እንደነበር እናውቃለን፦

2ጢሞቴዎስ 4፥ 16 "በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፥ ሁሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው፤"

አካላዊ ሕመምን በተመለከተስ? ፣ ጳውሎስ የአካላዊ ጤና ችግር ነበረበትን?

2ቆሮንቶስ 12፥ 7 "ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው።"

እዚህ ላይ ጳውሎስ አካላዊ የጤንነት ዕክል የነበረበት መሆኑን እናያለን።  ይህን ችግር ያጋጠመው ለምን እንደሆነም የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል።  በጠቅላላ ህይወቱ በድል ስላልተራመደ ወይም መንፈሳዊ የሕይወት ድካም ስለነበረበት ሳይሆን ይልቁንም ትህትናውን ጠብቆ ለማቆየት እግዚአብሔር የተጠቀመበት መንገድ ነበር።  "እግዚአብሔር ለትሑታን ጸጋን ይሰጣልና" ያ ደግሞ መልካም ነገር ነው።

2ቆሮንቶስ 12፥8 "ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ።"

ይህንን ችግር እግዚአብሔር እንዲወስድለት ጳውሎስ በጸሎት ጠየቆ ነበር።  እግዚአብሔር ግን የሰጠውን መልስ ልብ በሉ፦

2ቆሮንቶስ 12፥ 9 "እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።"

ጳውሎስ በድህነቱና በሥቃዩ ላይ ስለተቀዳጀው አጠቃላይ ድል ይመካ ነበርን? ደስታውስ ይህ የጤናና የኢኮኖሚ ችግር ከእርሱ ስለተለየ ነበርን?  ፈጽሞ ደስታውም ትምክህቱም በዚያ አልነበረም! ይልቁንም በነዚያ  ድክመቶቹ ሲመካ ይታያል።  ይህ ለምን እንደሆነ ልብ አድርጉ፦

2ቆሮንቶስ 12፥ 10 "ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።"

ልብ አድርጉ፣ ይህ የጤና/ብልጥግና ወንጌል የተባለ የትምህርት አረም ይህንን እውነት ሙሉ በሙሉ ስቶታል።  ጳውሎስ፣ “ስደክም፣ ማለትም በዚህ አካላዊ ሕመሜ፣ በማልፍበት እጦትና ድህነት፣ በሚገጥመኝ የማህበራዊ ተቀባይነት እጦት፣ በመከዳቴ እና በሰዎች በመረሳቴ እመካለሁ፣ ደስ ይለኛል” ሲል ተናግሯል።  አያችሁ፣ በሕይወታችን ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሙን ያኔ ነው እንደ ጳውሎስ ወደ ክርስቶስ የምንዞረው እና በኃይሉ የምንታመነው።

የጳውሎስን የግል የህይወት ምስክርነት ተመልከቱ እና ምን ያህል ከጆኤል ኦስቲንን አጠቃላይ የድል ኑሮ ሃሳብ እና አስተምህሮ ጋር መስማማት አለመስማማቱን መዝናችሁ እዩ፦

2ቆሮንቶስ 11፥ 23-27 "እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።"

ጆኤል ኦስቲን ይህን ምስክርነት አንብቦ ያውቃልን? እንጃ። ለክርስቶስ መኖር እና እግዚአብሔርን በመታዘዝ መመላለስ ለጳውሎስ ይህን ይመስል ነበር።  ምን ያህሎቻችሁ ለእንደዚህ አይነት የህይወት ስርአት መፈረም ትሻላችሁ?  ጆኤል ኦስቲን ይህንን ህይወት የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ብሎ ለአማኞች ሰብኮ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለ ትልቅ የሕንፃ ካቴድራል ባልኖረውም ነበር።

፬.

ያለህባት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ሀብት ሰጥቶ ባለጠጋ ሊያደርግህ እንደሚፈልግ የምታምን ከሆነ፣ ፓስተርህም ይህንንው እየደጋገመ ሲሰብክ፣ አንተ ግን "በእምነትህ ማነስ " ምክንያት ከዚህ እንደጎደልህ ማወጅና ማስተማር ሲጀምር፣ እንዲህ ያለው ይህ የትምህርት እብደት በተለይ በድህነት ውስጥ ለሚኖሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ሰዎች ምን ማለት ይሆን?

ተመልከቱ በገጠራማዋ የኢትዮጵያ መንደሮች በየእሁዱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማምለክ  3 በ 5 ስፋት ባላት አነስተኛ "የጸሎት ቤት" ውስጥ ወይም በዛፍ ጥላ ስር ይሰበሰባሉ። ያቺ ቤተመቅደስ በሰዎች አይን የምታምር አይደለችም፣ ነገር ግን በምድር ላይ ካሉት በጣም ድሆች ከሆኑ አማኞች ጥቂቶቹን በአባልነት ያቀፈች ቤተክርስቲያን ናት።  ነገር ግን የእነዚህ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ ዝቅተኛነት ያለባቸውን መንፈሳዊ የበታችነት አያመለክትም። እርግጥ ነው እነዚህ ሰዎች እንደብዙዎቹ ምዕራባውያን የጤና እንክብካቤ ዋስትና የላቸውም፣ ነገር ግን በህመማቸው ጊዜ ጌታ እንዲፈውሳቸው በጸሎት ይጠይቃሉ። ምናልባትም ከብዙዎቻችን በተለየ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ላይ የመተማመን እጅግ የላቀ ደረጃ ያላቸው ናቸው።  እነዚህ ሰዎች "የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን" ብለው ሲጸልዩ - በእርግጥ ለማለት ያህል በልማድ ሳይሆን የምራቸውን መለመናቸው ነው።  በጣም መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ሊሰጣቸው እንደሚችልም በእግዚአብሔር እየታመኑ ውሱን በሆኑ ግብአቶቻቸው በገዛ እጃቸው ለሥራ ይተጋሉ እንጂ አይለግሙም።

የሚቀጥለው ምግብ እንዴትና ከየት እንደሚመጣ የማያውቁ ነገር ግን መንፈሳዊ ኃያላን የሞሉባት እንዲህ ያሉ ታናናሽ መንጋ ያሏቸውን ታናናሽ የቅዱሳን ማህበራት ኢትዮጵያን ከመሰሉ የአፍሪካ ገጠራማ መንደሮች ማግኘት የተለመደ ነው።  ሆኖም በድህነታቸውና በሥቃያቸው መካከል እግዚአብሔርን በደስታ ውዳሴ ሲያመልኩት ነፍስ አይቀርላቸውም። እኔ ከወንጌል እንደምረዳው ጆኤል ኦስቲን ከሚደሰኩረው ኃሰተኛ የድልና የስኬት ህይወት ይልቅ ፍጹም ድል ይህ ነው።

ምእመናን አጥብቀን ልንረዳው የሚገባን እውነት እዚህ አለ፤ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ውስጥ መኖር እንደሚገባው ያህል በጽድቅ ሕይወት በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ ወንጌልን በኃይል ለማስፋፋት እና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ እየተጋደሉ ለጽድቅ ሲቆሙ የዚህ ተፈጥሮዋዊ ውጤት መከራ መቀበል ይሆናል።  ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ይህንን እንዲረዱ ይፈልጋል፣ መከራንም እንዲጠብቁ ያስተምራል። ጳውሎስም እንዲሁ ሲያመለክተን፡-

2ጢሞቴዎስ 3፥ 12 "በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።" ይላል።

ይህ ጥቅስ ክርስቲያኖች ሁሉ በጅምላ ስደትን መጠባበቅ ይችላሉ አይልም። ይልቁን ምን ይላል?  "በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።" ነው የሚለው። መከራንና ስደትን ወዳለንበት ስቦ የሚያመጣው እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት ነው።  ማለትም ከእግዚአብሔር ጋር ስትቆም፣ ኃጢአትን ስትቃወም፣ ውርጃን፣ ግብረ ሰዶማዊነትን፣ ተመሳሳይ ጾታዊ ጋብቻን ስትነቅፍ እና የስነምግባር ዝቅጠትን ተቃውመህ ስትናገር፣ ያኔ በዚህ ምክንያት ስደት ሊደርስብህና መከራን ልትቀበል እንደምትችል ጠብቅ!

ጳውሎስ በብዙ መልዕክቶቹ የንባብ ክፍሎች ላይ መከራና ስቃይ የሐዋርያዊ አገልግሎት አስፈላጊ አካል እንደሆ በማሰብ ጽፏል።  በሌሎች ክፍሎች ግን ጳውሎስ መከራን እና ስቃይን በሐዋርያት አገልግሎት ላይ ብቻ አልወሰናቸውም።  ይልቁንም አለፍ ብሎ የደቀመዝሙርነት ኑሮ አስፈላጊ አካል እንደሆነም ያመለክታል።  ይህም ትምህርት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ወጥነትና ቀዋሚነት ያለው አጽንዖት ነው። ችግሮችና ፈተናዎች፣ ተግዳሮቶችና ግጭቶች ህመምም ከደቀመዝሙርነት ኑሮ ጋር የማይነጣጠሉ ሆነው የተቆራኙ ናቸው።

ምእመናን፣ ልንረዳው የሚገባን አንድ ጉዳይ ህመምና ስቃይ ድኅነትም የዚህ ሕይወት ሥርአትና አካል ናቸው፤ ክርስቲያን መሆናችንም ሆነ የድል ኑሮ መኖር ደግሞ ሁሉም ከህይወታችን እንዲወገዱ አያደርጋቸውም።  ጥበበኛ፣ ቅዱስ እና አፍቃሪ የሆነው አምላካችን በህመማችን እና በመከራችን ውስጥ የማይመረመር አላማ አለው።  ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የሚነገራቸውን ልብ አድርጉ፦

2ቆሮንቶስ 1፥ 8 "በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤"

ይህ ጆኤል ኦስቲን የሚናገርለትን አጠቃላይ የድል ኑሮ ፈጽሞ አይመስልም።  ጳውሎስ ግን እርሱና ባልደረቦቹ መከራ ለምን እንደደረሰባቸው በግልጽ ነግሮናል፣ ተመልከቱ፦

2ቆሮንቶስ 1፥ 9  "አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።"

ወገኖች ሆይ፣ መከራን መቀበል በራስ የመደገፍ ኃጢያትን ከላያችን ያራግፍልናል።  ብዙ ወንዶች እና ሴቶች የእግዚአብሔር ልጆች እግዚአብሔር ይህን ትምህርት በህይወታቸው እንዳስተማራቸው፣ በእርሱም ላይ ጥገኛ እንዳደረጋቸው፣ በስህተት የተመኩባቸውን ነገሮቻቸውን ሁሉ ከውስጣቸው ነቅሶ በማውጣት የእርሱ ተደጋፊ እንዳደረጋቸው መስክረዋል።  በአብዛኛው የሚያጋጥመን ሥቃይና መከራ አላማው በእግዚአብሔር ጸጋ እና ኃይል ላይ ብቻ የማይቋረጥ ጥገኛነትን ማምጣት ነው።  መከራችን ፍጥረቱ የተነደፈውና የተሰራው በእኛ በራሳችን እንድንደገፍ ሳይሆን በእግዚአብሔር ችሎታ፣ ኃይል እና ዝግጅት እንድንመላለስ ነው። እርሱ ብቻ በገዛ ራሳችን አለን ከምንለው ሀብታችን እያላቀቀ ወደ ባለጠግነቱ ዘወር እንድንል ያደርገናል።

ምእመናን ይህን ስሙ፣ ሌሊቱ ሲነጋ፣ ፀሀይ ስትወጣላችሁ ሰማዩ ጥርት ያለ ሲሆን፣ የተነቃቃ ታላቅ ስሜት ሲሰማችሁ፣ ብዙ ገንዘብ ያላችሁና "ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም" ለማለት ስትፈተኑ፣ ሁሉም ሰው ሲወዳችሁና ሁሉንም ሰው ስትወዱ፣ ተቀባይነታችሁና ተፈላጊነታችሁ ሲጨምር፣ ያኔ በእርግጠኝነት እግዚአብሔርን ችላ የማለት ዝንባሌ መኖሩ አይቀርም። እንዲህ ባለው ስኬት በሚመስል ውድቀት ውስጥ  በራሳችን የመታመን እና እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ የመርሳት ዝንባሌ በእርግጥ አለ።  እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ስለ ብልጽግና አስጠንቅቋቸው የነበረው ለዚህ ነው።

ዘዳግም 8፥ 11 "ዛሬ እኔ አንተን የማዝዘውን ትእዛዙንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፤"

እግዚአብሔር እዚህ ላይ እስራኤላውያንን የሚያስጠነቀቃቸው፣ ስለ ድህነት አደጋ ሳይሆን ስለ ሀብት አደጋ ነው እያስጠነቀቃቸው ያለው።

ዘዳግም 8፥ 12-16 "ከበላህና ከጠገብህ በኋላ፥ መልካምም ቤት ሠርተህ ከተቀመጥህበት በኋላ፥ የላምና የበግ መንጋ ከበዛልህ በኋላ፥ ብርህና ወርቅህም ያለህም ሁሉ ከበዛልህ በኋላ፥ ልብህ እንዳይጓደድ፤ ከግብፅም ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን፥ እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለባት፥ ውኃም በሌለባት፥ በታላቂቱና በምታስፈራው ምድረ በዳ የመራህን፥ ከጭንጫ ድንጋይም ውኃን ያወጣልህን፥ በመጨረሻም ዘመን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሊፈትንህ ሊያዋርድህም አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤"

ልባቸው እንዲጓደድ፣ በትዕቢት እንዲኮሩና ጌታን እንዲረሱ የሚያደረጋቸው ድህነታቸው ሳይሆን የሚያከማቹት ሀብት መሆኑን ልብ በሉ።

ይህንኑ ሃሳብ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ እናያለን።

ምሳሌ 30፥ 8-9 "ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፤ ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም፦ እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።"

ስንጠግብ፣ ሁሉም ነገር ሲስተካከል ጌታን የመካድ አደጋም አብሮት አለ።

ቅዱሳን ስሙኝ፣ በእውነቱ ለአንድ አማኝ የዚህ ምድር ህይወቱ በጣም ከባድ ሊሆንበት የሚችል መሆኑ ነው፤  እግዚአብሔርም በእርሱ ስንታመን ጤናንና  ሀብትን ሊሰጠን የገባው ቃል የለም። እግዚአብሔርን በመምሰል የምንኖር ከሆነ ግን ስደት እንደሚደርስብን ቃል ገብቷል።  የወንጌል መልእክትም እነ ጆኤል ኦስቲንና መሰሎቻቸው አጣመው እንደሚያስተምሩት በድህነት እና በበሽታ ላይ፣ በማህበራዊ ግንኙነቶችም ተቀባይነት ማጣት ላይ በድል አድራጊነት ፈጽሞ ስለመኖር አይደለም። ወንጌል በብቸኝነት የሚናገረው እግዚአብሔር በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ የኃጢአትን ዕዳ ለመክፈል የሚወደውን አንድያ ልጁን መስዋዕት አድርጎ ስለማቅረቡ ነው።  እግዚአብሔር የዘላለም ሕይወትን ሊሰጠን እንጂ የሀብትና የመጽናናት ሕይወት እንድንኖር ቃል አልገባልንም።

እግዚአብሔር በእርሱ እንድንታመንና፣ በእርሱ ላይ በመታመን ብቻ እንድንኖር ይፈልጋል፣ ያንንም ለማድረግ የሚረዱን የህይወት ፈተናዎቻችን ናቸው።

ስለዚህ ጆኤል ኦስቲን "አጠቃላይ የድል ህይወት" እያለ በሚሰብከው የቅዠት አለም ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጽሞ እንዳልኖረበት ወንጌሉ ነግሮናል፤ ሐዋርያትም ሆኑ የየዘመኑ ቅዱሳን ሁሉ ባለፉት ዘመናት እንዲህ ባለ ቅዠት አልኖሩም።  ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ስትጠጉ ይህ የጤና/ብልጥግና ወንጌል ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዳልሆነ ታያላችሁ።  ታዲያ ብዙዎች ይህንን የውሸት መልእክት በውድ ዋጋ እየገዙ ወደዚህ ትምህርት የሚሳቡት፣ የነዚህ ኃሰተኞችስ ግባኤ በብዙ ቁጥር እያደገ የመጣው ለምንድነው? በመጀመሪያ ስለ እድገታቸው መገረምና መደነቅ የለብንም ምክንያቱም ካንሰርም ያድጋል። እኔ እንደማስበው ግን የዚህ እድገት ዋናው ምክንያት የትምህርቱ ድምጸት በጣም ጥሩ ስለሚመስል ነው።  መቼም ቢሆን ጤናማ ለመሆን፣ ሀብት ለማግኘት፣ ከችግርም ነጻ የሆነ ኑሮ መኖር የማይፈልግ ማን ሰው አለ?  ስለዚህ የስብከቱ ድምጸት ጥሩ ስለሚመስል ብዙ ሰው ይከተለዋል። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በቅጡ ስለሚያውቁ፣ አብዛኛው ግን ቃሉን መማርና ማወቅ እምቢ ስላለ፣ ወይም ንጹሁን ወንጌል የሚያስተምረው ስላጣ ይህ የጤና/ብልጥግና ወንጌል እግዚአብሔር ለእነርሱ እንዲሰሙትና እንዲከተሉት የሚፈልገው ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው።  አማኞች በዚህ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ አጉል ትምህርት ውስጥ ሲጠመዱ ስናይ በቅዱሳን መካከል ይህንን የሚመዝን መለኪያ ድምጽ በመሆን ኃሰትን ለመጋፈጥ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት አውቀን ልንቆም ይገባናል።

በአገራችንም እንደ አሸን የፈሉት የጥፋት ወንጌል ሰባኪዎች ቢከፍቱት ተልባ የሆነው ዲስኩራቸው ምንጩና መሰረቱ ይኸው ከላይ በስፋት የተቸነው መስቀል አልባ የትምህርት ቅዠት ነው። ስራ ጠል የሆኑ ቁጭ ይበሉዎች በኃሰተኛ ትንቢታቸው እያዋዙ ሕዝብ በሚያደነቁሩበት የትባረካላችሁ ስብከት መንጋው እየከሳ ዘርፈው የጠገቡ እነርሱው ብቻ ናቸው። "ማን መጥቶ ባሳሳተን" በሚል ክፉ ምኞት ተይዘው ላይ ላዩን የሚጋልቡና አጥብቀው የማጠይቁ ሰነፍ የቤተስኪያን ደንበኞችም ይጠፉ ዘንድ ለዚህ የተመደቡ ናቸው፤ ቃሉንም ከመማር ርቀው በዝነኞቻቸው የትምህርት ንፋስ ተጠርገዋል። ብዙ ዘመን በውሃ ውስጥ የኖረ ጥቁር ድንጋይ ውሃው ወደውስጡ እንደማይገባ ሁሉ እነዚህም ደጋግመን በወንጌል ያስጠነቀቅናቸው ሆነው ሳሉ ትምህርታችንና የምክር ቃላችን አልገባቸውም።

እንግዲህ በብዙ ዝርዝር ልናየው የሞከርነውና ይህ “የጥፋት ወንጌል” ስል የሰየምኩት የጤና/ብልጥግና ወንጌል አደገኛነቱ ሊሰማን ይገባል።  የዚህ ወንጌል አራማጆች እንደሚደሰኩሩት እግዚአብሔር አማኞች ሁሉ ጤናማና ባለጸጋ እንዲሆኑ፣ ከየትኛውም አካላዊ ስቃይና መከራ ነጻ እንዲሆኑ፣ በሚያደርጉት በማናቸውም ነገር እንዲበለጽጉና እንዲከናወንላቸው ይፈልጋል ብለው ያስተምራሉ።  በመግቢያዬ ላይ እንዳመለከትኩት ይህ ጥሩ ዜና ይመስላል።  ብቸኛው ችግሩ ግን እውነት አለመሆኑ ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ወንጌል ሳይሆን ሰዎች ሊሰሙት የሚፈልጉት "ማጽናኛ" (ማዝናኛ ቢባል ይቀላል) እና ስሜትን የሚኮረኩር ማነቃቂያ ብቻ ነው።

የዚህ የጤና/ብልጥግና ወንጌል ሰባኪዎች የሚያደርጉት አንድ ክፉ ስራ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሀብት የሚናገረውን ዋና መልዕክት ገልብጠው ስሜታችን ሊሰማው የሚፈልገውን እየደሰኮሩ ባህላችን ስለ ሀብት/ብልጽግና በሚናገረው ለመተካት የሚያደርጉት እውር ጥረት ነው።  እርግጥ ነው፣ “እግዚአብሔር ባለጠጋ ሊያደርግህ ይፈልጋል” የሚለውን መልእክት ስትሰብክ፣ ትርጉሙ አጠቃላዩ የወንጌል መልእክት ስለ እኛና ስለ ፍላጎቶቻችን ነው የሚል ብቻ ሳይሆን፣ ወንጌሉ እግዚአብሔር ፍላጎቶቻችንን እንዲያሟላልን የምናደርግበት መንገድ፣ በራሳችንም ላይ ብቻ እያተኮርን ራስ ተኮር በሆነ ህልማችን የምንወሰድበትም ጭምር ይሆናል። ያኔ የእኛ ትክክለኛ የህልውናችን ማእከልም የፍላጎቶቻችን መሟላት እንጂ ራሱ እግዚአብሔር አይሆንም።  ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኘው ከእግዚአብሔር ልናገኘው በምንችለው ነገር ብቻ ነው ማለት ነው። ትክክለኛው የህልውና ማእከላችንም "እግዚአብሔር ስኬታማ የአኗኗር ደረጃዬን ይባርክልኝ" በሚል ምኞት የሚነዳ በራሳችን ላይ ያተኮረ የብልጽግና እና የስኬታማ የህይወት ዘይቤአችን መሆኑ ነው። 

(gkr)