Wednesday, July 31, 2019

በክርስቶስ ማመን ብቻ

በክርስቶ ማመን ብቻ!
እግዚአብሔር በውድ ልጁ ምትካዊ ሕይወትና ሞት በኩል አለሙን ሁሉ ከራሱ ጋር ያስታረቀ መሆኑ በወንጌሉ የሚሰበከው የምሥራች ነው። ኃጢአተኞችም ሁሉ  አምነው ይድኑበት ዘንድ ይህ በክርስቶስ የተገለጠው የማስታረቅ ስራ  ለሰዎች ሁሉ ያለ ገደብ እንዲታወጅ   በወንጌሉ ያዘዘ መሆኑም የታመነ ነው። እነሆ እግዚአብሔር በክርስቶስ በገለጠው የእርቅ ወንጌል በደል አይቆጠርም። መታዘዝም ጽድቅ ሆኖ የሚቆጠር የእምነት መታዘዝ ብቻ ነው።
"ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።" (2 ቆሮ 5÷ 18፣ 19)
"በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤" (ሮሜ 1፥ 5)
"ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።......ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው"  (ሮሜ 4፥ 5፣ 24-25)
ስለዚህም ከእግዚአብሔር ጋር በግል እርቅን ለማድረግ፣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታን ለማግኘት በክርስቶስ ማመን ለኃጢአተኛ ሰው ብቸኛው መንገድ መሆኑን የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ሁሉም ቅዱሳት መጻህፍት በግልጽ ይመሰክራሉ፣
" በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።"(ሐዋ 10፥ 43)
"በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።...በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።"(ዮሐ 3፥ 16-18፣ 36)
ለመዳን ሌላ ተለዋጭና አማራጭ መንገድ የለም፣ ይህም በወንጌሉ የተገለጠው የድነት መንገድ የመለኮት ድንጋጌ ነው፤ ሳናፍርበት ለታላቁም ለታናሹም የምንሰብከው የክብር ወንጌል ነው እንጂ እኛ ይምናካብደው ወይም የምናከረው ኃይማኖታዊ ጉዳይ አይደለም። ሰዎች የኃጢአት ይቅርታን በሚያገኙበት በክርስቶስ በሆነው በዚህ እምነት ብቻ ይድናሉ ማለት የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትሎ የአምላክን ሕግ ለመፈጸም በሚደረግ ማናቸውም የሰው ጥረትና ኃይማኖታዊ ሙከራ ይድናሉ ማለት አይደለም። ሰዎችን ከኃጢአታቸው እንዲድኑ የምንመክረውን ያህል ለመጽደቅ ከሚያደርጉትም ኃይማኖታዊ ሙከራ እንዲድኑ በወንጌሉ ቃል አጥብቀን እንመክራለን። በወንጌሉ ማመን ይለያል፣ ይኸውም ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ  በተሰጠንና በወንጌሉ በቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ወይም ጽድቅ ማመን ብቻ ነው፣ አለቀ! በክርስቶስ ማመን እግዚአብሔር በታሪካችን ውስጥ ሊገኝ እርሱ ወደ እኛ የመጣበት ራሱ ያዘጋጀውና የመረቀልን ለድነታችን የሚሆን የእምነት መንገድ ነው እንጂ እኛ ወደ እርሱ ለመድረስ የምንኳትንበት አስቸጋሪ መንገድ አይደለም። ይህም እምነት የሚያጸድቀው ጸጋው ባቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ላይ ብቻ ሙሉ በሙሉ ባረፈ መጠን ነው እንጂ እምነት በራሱ የሰው ሥራና ሙከራ በሆነ መጠን አይደለም። ሐዋርያው ሲጽፍ "ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤" (ሮሜ 4፥ 16) ይላል። ጥረት ሆይ ምንኛ መላላጥ ሆንሽብኝ? በይ ኃይማኖተኝነት ደህና ሰንብች። (ቄስ ግዛቸው ከበደ)

Saturday, July 20, 2019

የሥርየቱ መንገድ

የሥርየቱ መንገድ
ከአሮጌው ኪዳን በታች ተገዝቶ ይሰራ በነበረው የአይሁድ የኃይማኖት ሥርዓት፣ እግዚአብሔር ካህናቱን ያለማቋረጥ ስለ ህዝቡ ኃጢአት በቤተመቅደሱ የመጀመርያ ክፍል የማስተሰርያውን መስዋእት እንዲያቀርቡ ይጠይቃቸው ነበር። ይህም የእንስሶችን መስዋዕት እና የእንስሶችን ደም በእግዚአብሔር መሰዊያ ላይ በመርጨት የሚከናወን አምልኮተ ሥርዓትን የሚጨምር ነበር። (ለምሳሌ፦ ዘሌ 9፥ 7፣ 12፣ 18፣ 23-24)። እንደገናም በአመት አንድ ጊዜ በሥርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ ብቻ ለራሱና ለህዝቡ ኃጢያት የሚያቀርበውን የመስዋዕቱን ደም ይዞ ቅድስተ ቅድሳን ወደ ሚባለው ሁለተኛው ክፍል ወይም ወደ መቅደሱ ውስጥኛ ክፍል ይገባል።

"ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤" (ዕብራውያን 9፥ 6-7)

ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የመጨረሻውን መስዋዕት ያቀረበ እውነተኛው ሊቀ ካህናት ነው። በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፣ ተቀበረም፣ ከመቃብርም ተነሳ። ከአርባ ቀናትም በኋላ ወደ ሰማይ አርጎ በሰማያት በምትገኘው ቅድስተ ቅዱሳን የማስተሰርያውን ሥራ አጠናቀቀ።

"ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው።" (ዕብራውያን 9፥ 14-15)

የክርስቶስ ደም እግዚአብሔር ለመረጣቸውና ለጠራቸው አማኞች የዘላለምን ሕይወት ተስፋ መቀበል ይችሉ ዘንድ ከኃጢአታቸው ሊነጹበት ለእግዚአብሔር የቀረበ ዘላለማዊው መስዋዕት ነው። የእርሱ ደም የመጨረሻ ማስተሰረያ ሆኖ ይቀርብ ዘንድ መፍሰሱ የግድ አስፈላጊ ነበር። አለበለዚያ ምንም አይነት ዘላልማዊ የኃጢአት ይቅርታና ሥርየት የሚባል ነገር አይኖርም።

"እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም።" (ዕብራውያን 9፥ 22)

ክርስቶስ የፈጸመው የማስተስረያ ስራ ተጠናቆ የተፈጸመው፣ ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ በሚጠራው በሰማያዊው መቅደስ በመጋረጃው ውስጥ ነው። (ዕብራውያን 9፥ 3) የአይሁድ ሊቀ ካህናት በምድራዊው ቤተመቅደስ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በየአመቱ የእንስሶችን ደም ይዞ በመግባት እንደሚያደርገው አይነት ራሱን ብዙ ጊዜ ምስዋእት ማድረግ አላስፈለገውም።

" እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነጻ እንጂ በሰማያት ያሉቱ ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።" (ዕብራውያን 9፥ 23-26)

ጌታ ኢየሱስ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ይኸውም በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ለኃጢአት ማስተሰረያ የሚሆነውን ስራ አከናውኖአል። ሆኖም ግን የህዝቡ ሁሉ ድነት እና በእግዚአብሔር ሀልዎት ፊት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ ለመቅረብ ያላቸው ዘላለማዊ ድፍረት ሁለት ነገሮች በይፋ እስኪከናወኑ ድረስ ገና ወደፊት ይጠብቅ ነበር።

የመጀመርያው፣ እርሱ የፈጸመው የማስተሰርያ ስራ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን እንዳገኘ ያሳይ ዘንድ ለነዚያ ያድናቸው ዘንድ ይጠባበቁት ለነበሩ ምዕመናን ሁለተኛ ጊዜ ተመልሶ መምጣት ነበረበት። የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት በአመት አንድ ጊዜ የመስዋእቱን ደም ይዞ ሊያስተሰርይላቸው፣ እግዚአብሔር እገኝበታለሁ ወዳለው ሥፍራ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ግብቶ ያቀረበው መስዋዕት ተቀባይነት እንዳገኘ ለመግለጥ በአውደ ምህረቱ ላይ ሊታይ ተመልሶ እንደሚወጣ ሁሉ፣ እንዲሁ ኢየሱስ  ይህንን ያከናወነው በ70 ዓም በዳግመኛ ምጽአቱ ነው። "እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (ዕብራውያን 9፥ 28)፤ እነዚህ ይጠባበቁት የነበሩ በትውልዳቸው ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣ የተነገራቸው የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ምዕመና ናቸው። ኢየሱስ እንደተስፋ ቃሉ ያኔውኑ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ተመልሶ ካልመጣ ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመቅረብና ለመግባት ገና የማይቻል ነው፣ ገናም በአሮጌው የሙሴ ሥርዓት ስር ተገዝተን አለን፣ እግዚአብሔር የክርስቶስን መስዋዕት እንደተቀበለውም ሆነ በአጠቃላይ ስለ መዳናችን እርግጠኞች መሆን አንችልም ማለት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ፣ ያ የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ፈራርሶ መጥፋት ነበረበት። ይህንንም እንደ ትንቢቱ ቃል ያከናወነው ያንን በኢየሩሳሌም የነበረውን ምድራዊ ቤተ መቅደስ በ70 አም ያጠፉት ዘንድ በአህዛብ እጅ አሳልፎ በመስጠት ነው። "ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።" (ዕብራውያን 9፥ 8)። ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ይገለጥ ዘንድ ያቺ ድንኳን መውደቋ ቅድመ ሁኔታ ነበር ማለት ነው።

"ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፥ እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ፤ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም።" (ዕብራውያን 9፥ 9-10)
(gkr)

በክርስቶስ ማመን ብቻ

በክርስቶስ ማመን ብቻ!

እግዚአብሔር በውድ ልጁ ምትካዊ ሕይወትና ሞት በኩል አለሙን ሁሉ ከራሱ ጋር ያስታረቀ መሆኑ በወንጌሉ የሚሰበከው የምሥራች ነው። ኃጢአተኞችም ሁሉ  አምነው ይድኑበት ዘንድ ይህ በክርስቶስ የተገለጠው የማስታረቅ ስራ  ለሰዎች ሁሉ ያለ ገደብ እንዲታወጅ   በወንጌሉ ያዘዘ መሆኑም የታመነ ነው። እነሆ እግዚአብሔር በክርስቶስ በገለጠው የእርቅ ወንጌል ለሚያምኑ በደል አይቆጠርም። መታዘዝም ጽድቅ ሆኖ የሚቆጠር የእምነት መታዘዝ ብቻ ነው።

"ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።" (2 ቆሮ 5÷ 18፣ 19)

"በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤" (ሮሜ 1፥ 5)

"ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።......ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው"  (ሮሜ 4፥ 5፣ 24-25)

ስለዚህም ከእግዚአብሔር ጋር በግል እርቅን ለማድረግ፣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታን ለማግኘት በክርስቶስ ማመን ለኃጢአተኛ ሰው ብቸኛው መንገድ መሆኑን የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ሁሉም ቅዱሳት መጻህፍት በግልጽ ይመሰክራሉ፣

" በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።"(ሐዋ 10፥ 43)

"በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።...በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።"(ዮሐ 3፥ 16-18፣ 36)

ለመዳን ሌላ ተለዋጭና አማራጭ መንገድ የለም፣ ይህም በወንጌሉ የተገለጠው የድነት መንገድ የመለኮት ድንጋጌ ነው፤ ሳናፍርበት ለታላቁም ለታናሹም የምንሰብከው የክብር ወንጌል ነው እንጂ እኛ ይምናካብደው ወይም የምናከረው ኃይማኖታዊ ጉዳይ አይደለም። ሰዎች የኃጢአት ይቅርታን በሚያገኙበት በክርስቶስ በሆነው በዚህ እምነት ብቻ ይድናሉ ማለት የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትሎ የአምላክን ሕግ ለመፈጸም በሚደረግ ማናቸውም የሰው ጥረትና ኃይማኖታዊ ሙከራ ይድናሉ ማለት አይደለም። ሰዎችን ከኃጢአታቸው እንዲድኑ የምንመክረውን ያህል ለመጽደቅ ከሚያደርጉትም ኃይማኖታዊ ሙከራ እንዲድኑ በወንጌሉ ቃል አጥብቀን እንመክራለን። በወንጌሉ ማመን ይለያል፣ ይኸውም ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ  በተሰጠንና በወንጌሉ በቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ወይም ጽድቅ ማመን ብቻ ነው፣ አለቀ! በክርስቶስ ማመን እግዚአብሔር በታሪካችን ውስጥ ሊገኝ እርሱ ወደ እኛ የመጣበት ራሱ ያዘጋጀውና የጀመረ ቀልብ ለድነታችን የሚሆን የእምነት መንገድ ነው እንጂ እኛ ወደ እርሱ ለመድረስ የምንኳትንበት አስቸጋሪ መንገድ አይደለም። ይህም እምነት የሚያጸድቀው ጸጋው ባቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ላይ ብቻ ሙሉ በሙሉ ባረፈ መጠን ነው እንጂ እምነት በራሱ የሰው ሥራና ሙከራ በሆነ መጠን አይደለም። ሐዋርያው ሲጽፍ "ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤" (ሮሜ 4፥ 16) ይላል። ጥረት ሆይ ምንኛ መላላጥ ሆንሽብኝ? በይ ኃይማኖተኝነት ደህና ሰንብች።
(ቄስ ግዛቸው ከበደ)

Tuesday, July 9, 2019

የእግዚአብሔር መንግስት

የእግዚአብሔር መንግስት
የአዲሱ ኪዳን የእግዚአብሔር መንግስት በይፋ ለአለም የተዋወቀው በክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት በስጋው ወራት በምድር ላይ በነበረው የአገልግሎት ቆይታ ነው። ይህ የእግዚአብሔር መንግስት አንዳንዴም መንግስተ ሰማያት ደግሞም የክርስቶስ መንግስት እና የፍቅሩ ልጅ መንግስት እየተባለ በተለዋጭ ሲጠራ ይስተዋላል። ይህ መንግስት የመሲሁን፣ የእግዚአብሔርን ልጅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ አለም በስጋ መምጣት ጨምሮ የተነገረለት መንግሥት ነው። ይህ መንግስት በመጀመርያ የተነገረው መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ ባቀረበው ስብከቱ ነው፤ እርሱም "መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ።" (ማቴዎስ 3፥ 1- 2) ይላል። ዮሐንስ "ቀርባለች" ሲል ያስተዋወቃት የሰማይ መንግስት በንስሃ የሚቀበሏትና የሚገቡባት መንግስት ናት። የዮሐንስን ታልፎ መሰጠት ተከትሎ "ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር" (ማቴዎስ 4፥ 17)፣ ሲሉ ወንጌላውያኑም ይነግሩናል።

ይህ የአዲሱ ኪዳን የእግዚአብሔር መንግስት ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከመሞቱ አስቀድሞ ለአይሁድ ያስተምራቸው በነበረበት ጊዜ ያኔ ገና ለማደግ በጅማሬው ላይ ነበር። የዚህ መንግስት ፍጹማዊ ሙላትና አገዛዙ የሚሰፍነው በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ላይ እንደሆነ ቃሉ በግልጽ ያስተምራል፣ ይህም የአብዛኛው ክርስቲያኖች እምነት ነው፤ በአመዛኙ ልዩነቱ ያለው ለዳግመኛ ምጽአቱ ተፈጻሚ መሆን የተቀጠረውንና የተወሰነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የጊዜ ማእቀፍ በመረዳትና በመተርጎሙ ላይ ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት መጻህፍት ገለጻ፣ ጌታ ኢየሱስ "እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ" (ማቴዎስ 16፥ 28) ብሎ ሲያስታውቅና፣ ደግሞም "እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" (ማቴዎስ 24፥ 34) ሲል እንዳስተማረውና፣ ሐዋርያቱም በተደጋጋሚ እንዳስተማሩት ከሆነ፣ የዳግመኛ ምጽአቱ ኹነት ፍጻሜ ከኢየሩሳሌም ከተማ መፈራረስና ከቤተ መቅደሱ መደምሰስ ጋር የተያያዘ ነው፤ እነርሱም ጌታ በነገራቸው የተስፋ ቃል ላይ ቆመው፣ በትውልዳቸውና በዘመናቸው እንደሚሆን ሲናፍቁትና ሲጠባበቁት የነበረው ዋና ጉዳይ ይኸው የጌታ የዳግሙኛ ምጽአቱ ፓሮዥያውን ነበር። ይህንንም ከእስራኤል ቤዛነትና ከአሮጌው የሙሴ ስርአት መወገድ ጋር አያይዘው ይረዱት ነበር።  ይህ ደግሞ የሆነው የዚያ አሮጌ ስርዓት ማእከልና መገለጫ የሆነው ቤተመቅደስ ፈጽሞ ሲደመሰስና ሲጠፋ፣ ከተማይቱም በእሳት ስትቃጠልና ሕዝቡም በሰይፍ ሲወድቁና ለባርነት ሲማረኩ በ70 ዓም ላይ በሆነባቸው ፍርድ ነው። የክርስቶስ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው በ70 አም ላይ እስኪሆን ድረስ ታዲያ መንግስቱ ገና በሙላት አልተመሰረተም ነበር።

ይህ የእግዚአብሔር መንግስት መንፈሳዊ መንግስት እንጂ፣ ተዳሳሽ መንግስት አለመሆኑን "መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም" (ዮሐንስ 18፥ 36) ሲል ኢየሱስ በግልጽ ተናግሯል። "ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው።" (ሉቃስ 17፥ 20- 21) ተብሎ እንደተጻፈ፤ በእምነት በኩል በክርስቶስ በሆኑቱ ሁሉና ዳግመኛ ተወልደው የእርሱ ምርጦች በሆኑት ምዕመናንን ውስጥ የሚኖር መንፈሳዊ መንግስት፣ የእግዚአብሔር አገዛዝ ነው እንጂ፣ እዚህ አለም ላይ በሚታወቅ በየትኛውም ፖለቲካዊ አገዛዝ የሚለካና የሚተረጎም መንግስት አይደለም። በመንግሥቱ በሚኖር በእያንዳንዱ ዳግም በተወለደ አማኝ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አድሮበታል።
ስለዚህም "ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን" (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 13) እንደተባለ፤ በመንግሥቱ ውስጥ የሚገኘው ጽድቅ ብቻ ነው፣ እንጂ አመጽ የለበትም። ምክንያቱም፣ "የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥" (ማቴዎስ 13 ፥40) ሲል፣ እንደ ተስፋ ቃሉ ይጠበቅ የነበረው ጽድቅ የሚኖርበት  አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይኸውም መንግሥቱ በዳግመኛ ምጽአቱና በፍርዱ ከክፉዎችና ከአመጻ የሚጸዳ መሆኑን ያሳያል። ክፋት የሚለቀመው "ከመንግስቱ" ነው እንጂ ከግዑዙ አለም ላይ አለመሆኑን እናስተውላለን። መንግስቱ ደግሞ ከዚህ አለም አይደለችም። ክርስቶስ በዳግመኛ ምጽዓቱ በዙፋኑ ሆኖ የነገሰባትና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ለዘላለም የሚገዛባት፣ ጽድቅና ቅድስና የሰፈነባት፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ኃሴትና ደስታ የሞላባት መንግስቱ፣ እደግመዋለሁ፣ እዚህ ተዳሳሹ አለም ላይ ካለ ከየትኛውም ሥጋዊና ነባራዊ የሰው ስርአት ጋር እናስተያያት ዘንድ የሚመጥናትና የሚገልጣት ምንም አምሳያ የላትም። እርስዋ የሰማይ መንግስት ናት። የምድር ላይ ኃያላን በምድራዊው መንግስታቸው የለበሱትን ካባ እና በራሳቸው ላይ የደፉትን ዘውድ፣ የተቀመጡበትን ዙፋንና የሚሰጡትን ፍርድና ዳኝነት ስንራቀቅ ውለን ብናድርበት፣ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ጋር ሆኖ በሚገዛበት በሰማያዊው መንግስቱ ካለው ግርማና ክብር ጋር ሊጠጋጋ ቀርቶ ምሳሌ ለመሆን እንኳ አይበቃም።

መንግስቱን ልንረዳውና ልናስተውለው የምንችለው የክርስቶስ አካል ተብላ በምትጠራዋና በማትታየዋ ሉል አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ባህርይና ተፈጥሮ ውስጥ ነው እንጂ፣ በሚታይና በሚዳሰስ የትኛውም ምድራዊና አለማዊ አደረጃጀት ውስጥ አይደለም። እርስዋም የብሉይ ኪዳንዋን እስራኤል ዘስጋን የተካቻት እውነተኛዋ የእግዚአብሔር እስራኤል፣ የእግዚአብሔር መንግስት ናት። እግዚአብሔርም በአብርሃም በኩል ለእስራኤል የሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ "አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚማላ የእርሱ ሙላቱ" በሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያኑ ውስጥ በክርስቶስ ፍጻሜውን አግኝቷል። መቼም ቢሆን ከነገድና ከቋንቋ ከህዝብም ተዋጅተው፣ በጽድቅና በጸጋ ተጠርተው የገቡባትን፣ መንግስቱና ግዛቱ ሊሆኑ የተመረጡቱ ቅዱሳን የሚኖሩባትን፣ እውነተኛዋን እስራኤልን ሊገልጣት የሚችለው ኪዳን ነው እንጂ ዘር አይደለም።

ይህ መንግስት ተፈጥሮው መንፈሳዊ ሲሆን፣ የወንጌል እና የክርስቲያን መንግስትም ነው፣ እንጂ ተዳሳሽ የሆነ፣ የሙሴ ሕግና የአይሁድ መንግስት አይደለም። ይህ በአሮጌው ሰማይ የተወከለው የአሮጌው ኪዳን ህጎች ሁሉ፣ መስዋአቶቹ፣ ኃይማኖታዊ ስርዓቶቹ፣ ልዩ ልዩ በአላቱ እና የበአላቱ ቀኖች ሁሉ፣ ከዚህ በአሮጌው ምድር ከተወከለውና በ70 አም ላይ ፍጻሜውን ካገኘው የእስራኤል ሕዝብ ውድመት፣ የኢየሩሳሌም ከተማ ጥፋት እና የመቅደሱ መደምሰስ ጋር ዳግም ላይታሰቡ በክርስቶስ ፍርድ እንዲያልፉ ተደርገዋል። በትንቢታዊ ገለጻቸው "ሰማይ እና ምድር" የሚወክሉት ኪዳንን ነው እንጂ በቁሙ አይተረጎሙም።

ያኔም በ70 አም ላይ አሮጌውን ሰማይና አሮጌውን ምድር በማስወገድ፣ በፍጥረቱ መንፈሳዊ የሆነው የአዲሱ ኪዳን ወንጌል ዘላለማዊው መንግስት፣ በሙላት ተመስርቷል፣ ይህም የእግዚአብሔር ፍጹማዊ አገዛዝ፣ በምድር ላይ በሚኖረው የሰው ልጆች ታሪክ ሁሉ ውስጥ፣ በተፈጠረው አዲሱ ሰማይ እና አዲሱ ምድር ሳይቋረጥ መግዛቱን ይቀጥላል። ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ መንግስት ንጉስና ገዢ፣ የምድርም ነገስታት ሁሉ ገዢ መሆኑ ለአለምና ለዘላለም እየታወጀ፣ በውጭ ያሉ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ በእምነትና በንስሃ ወደማይዘጋው ወደ ፍቅሩ ልጅ የጸጋ መንግስ እንዲገቡ ለትውልድ ሁሉ ጥሪና ግብዣ እየተደረገ አለም ይቀጥላል። መንግስቱ በምድርም በሰማይም የሚቀጥል መንግስት ነው። የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለከልካይ በሰማይ እንደሆነች በምድርም ደግሞ ናት፣ (ማቴዎስ 6፥ 10፤ ሉቃስ 11፥ 2)።

ማስታወሻ፦ ይህ ጽሁፍ ዘርዘር ብሎና በበርካታ የቅድሳት መጻህፍት ማገናዘቢያ ጥቅሶች ላይ ተመስርቶ ካዘጋጀሁት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ተጨልፎ የተወሰደ እጥጥር ሲሆን፣ ጌታ ፈቅዶ ጊዜ ከሰጠኝ ትምህርቱን አደራጅቼ በአንድ ወይም በሁለት ክፍል በስፋት እመለስበታለሁ። እስከዚያው ግን እንደ ፕሪቴሪስት ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምን እንደምናምን እና እንደምናስተምር በዚህች አጭር ክትባት በመጠኑ መረዳት ይቻላል። ተጨማሪ የነገረ ፍጻሜ ትምህርት የሚቀርብበትን philologus66 የተሰኘውን የፌስ ቡክ ገጽ እና http://gizachewkr.blogspot.com/ የተሰኘውን ብሎገር እንድትጎበኙ ግብዣዬ ነው።
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/

Saturday, June 15, 2019

የአዲስ ኪዳን ቀኖና

የአዲስ ኪዳን ቀኖና
"የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።" (ማቴዎስ 16፥ 19)

ይህ በቀጥታ እና በግል ለራሱ ለጴጥሮስ በጌታችን አፍ የተነገረ የስልጣን ንግግር ነው። ጌታ ለማንም እንደዚህ አልተናገረም። በክርስቶስ አካል ውስጥ ከጴጥሮስ በቀር የእነዚህን መክፈቻዎች የተስፋ ቃል የተቀበለ ማንም ሰው ወይም ተቋም የለም፤ ለማሰርም ለመፍታትም፣ ለማጽናትም ለመሻርም፣ ለመክፈትም ለመዝጋትም ክርስቶስ ባለስልጣን አድርጎ መክፈቻዎችን የሰጠው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ነው። እርግጥ በጥቅሉ ከእርቅና ይቅርታ አገልግሎት ጋር በተገናኘ ይህ የማሰርና የመፍታት ስልጣን ለቤተክርስቲያንም የተሰጣት እንደሆነ "እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።" (ማቴዎስ 18፥ 18) ከሚለው እንረዳለን። "የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች" የተባለው ግንን ለቤተክርስቲያን ከተሰጣት ስልጣን ይለያል።

መክፈቻዎች በመጽሐፍ ቅዱስ፦

መክፈቻዎች ተዳሳሽ ነገሮች ሆነው እምብዛም ባይሆን አልፎ አልፎ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ የሚታዩ፣ ሆኖም ግን በምሳሌነታቸውና በያዙት ለየት ባለ ትርጉም ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳንን በማገናኘቱ ረገድ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ሚናን የሚጫወቱ ናቸው።  መክፈቻዎች ከጥንት ዘመን ጀምሮ የተለየ የኃይልና የስልጣን ምልክት ሆነው ሲታወቁ ኖረዋል፤ ያም ሆኖ ይህ የመክፈቻዎች አምሳል በርካታ ምስጢርን በውስጡ ይዞአል። መክፈቻዎች በታማኝነት ሊፈርዱና ሊያስተዳድሩ ለተገባቸው ሰዎች የተሰጡ በመሆናቸው በያዙት ጠቀሜታ አንድን የተሰጠን ወይም የተላለፈን ኃይል ይወክላሉ። በጥንት ዘመንም ቢሆን እንኳ ቁልፍ ከትናንሽ ቁሶች ጋር የሚነጻጸር በመሆኑ በያዘው ጽንሰ አሳብ ከመክፈት ተግባር ጋር የተገናኘ ነው፤ የተዘጋን ከፍቶ ለሁሉ የተዘጋጀና የተፈቀደ እንዲሆን፣ የተከፈተንም ዘግቶ እንዲከለክል የሚያደርግ መሳርያ ሲሆን፣ ይኸውም ደግሞ ቁልፍ አንድን የሆነ ኃይል መጠቀምን ምስጢርን መግለጥና ልዩነት ማድረግን ያመለክታል።

መክፈቻዎች በብሉይ ኪዳን፣ አንድ ትልቅ ቤተሰብ ያለው  ጌታ ቤተሰቡን እንዲጠብቅለትና እንዲንከባከብለት በቤተሰዎቹ ጉዳይ ላይ መርጦ ለሾመውና ታማኝ ለሆነው አገልጋይ፣  ለቤቱ መጋቢ ወይም ለባላደራው የሚሰጠው ነው። ጌታችን ኢየሱስ በዳግመኛ ምጽአቱ ስለሚገለጠው ስለ ታላቁ የቁጥጥር ቀን በምሳሌ ሲያስተምር ምሳሌውን ያቀረበው ከዚሁ የብሉይ ኪዳን የባለአደራነት ጽንሰ አሳብ በመነሳት እንደሆነ እናስተውላለን።

"እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ክፉ ባሪያ ግን፦ ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፥ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።" (ማቴዎስ 24፥ 45-51)

በትንቢተ ኢሳይያስ መጽሐፍ ነብዩ ሲናገር ኃሰተኛው መጋቢ ከመጋቢነቱ የሚሻርበትን እና በምትኩ ኢየሩሳሌምን የሚንከባከባት እውነተኛው ታማኙ መጋቢ የሚሾምበትን ሁኔታ ያመለክታል። እግዚአብሔር የሚናገረው ሳምናስ ስለተባለ ያልታመነ አሳፋሪ መጋቢ በፍርድ ከመጋቢነት ስልጣኑ የሚሻር ስለመሆኑ እና በእርሱ ምትክ የቤቱ መጋቢ ሆኖ ስለሚሾመው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ወደ ስልጣን ስለመምጣቱ ነው

"የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በቤቱ ውስጥ ወደ ተሾመው ወደዚህ አዛዥ ወደ ሳምናስ ሂድ እንዲህም በለው፦ መቃብር በዚህ ያስወቀርህ፥ ከፍ ባለው ስፍራ መቃብር ያሠራህ፥ በድንጋይም ውስጥ ለራስህ መኖርያ ያሳነጽህ በዚህ ምን አለህ? በዚህስ በአንተ ዘንድ ማን አለ? እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይል ወርውሮ ይጥልሃል፥ አጠንክሮም ይጨብጥሃል። ጠቅልሎም ያንከባልልሃል ወደ ሰፊይቱም ምድር እንደ ኳስ ይጥልሃል፤ አንተ የጌታህ ቤት እፍረት! በዚያ ትሞታለህ በዚያም የክብርህ ሰረገላዎች ይሆናሉ። ከአዛዥነት ሥራህ አሳድድሃለሁ፥ ከሹመትህም ትሻራለህ። በዚያም ቀን ባሪያዬን የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን እጠራለሁ፥ መጐናጸፊያህንም አለብሰዋለሁ፥ በመታጠቂያህም አስታጥቀዋለሁ፥ ሹመትህንም በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለይሁዳም ቤት አባት ይሆናል። የዳዊትንም ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ይከፍታል የሚዘጋም የለም፤ እርሱም ይዘጋል የሚከፍትም የለም። በታመነም ስፍራ እንደ ችንካር እተክለዋለሁ፥ ለአባቱም ቤት የክብር ዙፋን ይሆናል። የአባቱንም ቤት ክብር ሁሉ ልጆቹንም የልጅ ልጆቹንም፥ ከጽዋ ዕቃ ጀምሮ እስከ ማድጋ ዕቃ ድረስ፥ ታናናሹን ዕቃ ሁሉ ይሰቅሉበታል። በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ በታመነው ስፍራ የተከለው ችንካር ይወልቃል፤ ተሰብሮም ይወድቃል፥ በእርሱም ላይ የተሰቀለው ሸክም ይጠፋል እግዚአብሔር ተናግሮአልና።" (ኢሳይያስ 22፥ 15-25)።

በተጨማሪም ለአዲሱ መጋቢ ስልጣን የሚተላለፍለትና የሚሰጠው መሆኑን፣ መክፈቻዎቹም የመታመንና የኃላፊነት ምልክት መሆናቸውን ጭምር በምንባቡ ውስጥ ተንጸባርቋል። ኢሳይያስ ስለመክፈቻው የተጠቀመበት ገለጻ ከፍ ያለ እንደሆነ እዩ፦ "የዳዊትንም ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ይከፍታል የሚዘጋም የለም፤ እርሱም ይዘጋል የሚከፍትም የለም" (ኢሳይያስ 22፥ 22) ይላል። "የዳዊት ቤት መክፈቻ" ያለው የዳዊትን ቤት የሚጠብቅና ዙፋኑን የሚያጸናው ነው። ያ ቤትና ዙፋን የሚገባው የሚከፍትና የሚዘጋ ባለስልጣን ደግሞ ከጌታችን በቀር ሌላ ማንም የለም። በነዚያ ዘመናት የነበሩ መክፈቻዎች ረዘም ያሉና ከባባድ ሆነው በትከሻ ላይ የሚሸከሟቸውና የሚያንጠለጥሉአቸው አይነት ነበሩ። መክፈቻዎችን የሚቀበሉ ሰዎች የታማኝነት ምልክት ሲሆኑ መጋቢ ሊኖረው በሚገባ ተፈጥሮና ባህርይ የሚታወቁና የሚያምኑ ደግሞ ናቸው። እነዚህን መክፈቻዎች የሚቀበሉ ሰዎች፣ በራሳቸው የኃላፊነትና የተጠያቂነት ምሳሌ ናቸው።

በወንጌል እንደተዘገበው የመክፈቻዎች ምሳሌ የብሉይ ኪዳኑን ጽንሰ አሳብ ጠብቆ በሁለት ስፍራ ላይ ተጠቅሶ ጥቅም ላይ ውሏል። በሉቃስ 11፥ 52 የህግ አዋቂዎች የሆኑ ሰዎች ታማኝነትና ኃላፊነት የሚጠይቀውን የስራ ድርሻቸውን ቸል በማለታቸው፣ "እናንተ ሕግ አዋቂዎች፥ የእውቀትን መክፈቻ ስለ ወሰዳችሁ፥ ወዮላችሁ ራሳችሁ አልገባችሁም የሚገቡትንም ከለከላችሁ።" ተብለው ሲከሰሱ እናያለን። እነዚህ ሕግ አዋቂዎች ወደ እውቀት ለመግባት ራሳቸውን ብቻ የከለከሉ አይደሉም፣ ነገር ግን ሌሎችም እንዳይገቡ ደግሞ የሚከለክሉ ናቸው። ቁልፍ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘይቤው ወደ እውነት መድረስንና አለመድረስን ይወስናል፣ መግባትንና አለመግባትን ይቆጣጠራል፣ ማለፍንና አለማለፍን ይጠብቃል፣ መፍቀድንና መከልከልን ይወክላል። እነዚህ ሕግ አዋቂዎች የስራ ድርሻቸውንና የተጠሩለትን የአገልግሎት ዘርፍ ለራሳቸው እውቀትን ያገኙበት ዘንድ ሊጠቀሙበትና፣ ደግሞ እውነትን የሚመግቡ ሆነው ለሌሎችም የእውቀትን በር ሊከፍቱበት ይገባቸው ነበር። ነገር ግን ተግባራቸውን በአግባቡና በታማኝነት ያልፈጸሙ በመሆናቸው መክፈቻዎቻቸው ከእነርሱ ይወሰዳሉ።

እጅግ ታዋቂ የሆነውና በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው የዚህ የመክፈቻ ምሳሌ በመነሻችን ላይ የጠቀስነው ጌታ ኢየሱስ ጴጥሮስን በመንግስተ ሰማያት መክፈቻዎች ባለስልጣን ያደረገበት በማቴዎስ 16፥ 13-20 የሚገኘው ንግግሩ ነው። ይህም ምንባብ ከላይ ያየናቸውን ሁለት መንታ ርዕሰ ጉዳዮች በመያዝ መታመንንና ስልጣንን ያሳያል። በክርስቶስ ማንነት ላይ ጴጥሮስ የሰጠው ምስክርነት ኢየሱስ እነዚህን መክፈቻዎች እንዲሰጠው ፊት ለፊት ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ነው። ኢየሱስ ማን እንደሆነ ጴጥሮስ ስላወቀ፣ "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ" ከሚለው በሰማያዊ መገለጥ ከተሰጠው ምስክርነት የተነሳ እነዚህን መክፈቻዎች ለመቀበል የሚታመን ሆኗል። ልክ እንደ እውቀት መክፈቻዎች ሁሉ ጴጥሮስም መክፈቻዎቹን ለማሰርና ለመፍታት ይጠቀምበታል። ስለዚህም በዚህ ምንባብ ያሉት መክፈቻዎች በአሰራራቸው በአንድ ጊዜ ከምድራዊውና ከሰማያዊው ጋር የተገናኙ እስከሆኑ ድረስ በመክፈቻዎቹ ያለው የጴጥሮስ ኃላፊነት ለመንግስቱ ምድራዊ ተግባር ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ነገር ግን ለሰማዩም ጭምር ደግሞ የተሰጠ ነው።

በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍም ላይ ይኸው የመክፈቻዎች አምሳል እንደገና ይታያል። እዚህም ላይ አጽንኦቱ ቀደም ሲል ያየነው ኃይልና ስልጣን ነው፣ ነገር ግን ይህም በመታመንና በኃላፊነት የተነገረ ነው። እውነተኛ መጋቢን አስመልክቶ ቀደም ሲል ያየነው የነብዩ ኢሳይያስ ቃል በዮሐንስ ራእይ ጥቅም ላይ ሲውል "በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፣ የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል"፣ በሚውለው የክርስቶስ መገለጥ ውስጥ ተጠቅሷል። ይህ ከኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ መጻኢውን በሚያመለክት አቀራረቡ የተወሰደ ገለጻ እዚህ በራእይ ላይ ሲቀርብ ግን የአሁን ጊዜን እውነታ የሚያመለክት ሆኖ ተንጸባርቋል፤ ክርስቶስ "ቅዱስና እውነተኛ" በመሆኑ ሊታመን የሚችል መጋቢ ሆኗል። ሆኖም የየዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ጸሐፊ ክርስቶስን በተመለከተ ስላሉት መክፈቻዎች ጥንቃቄን በተመላ መልኩ ገልጦ ይናገራል። እነዚህ መክፈቻዎች ለጴጥሮስ ከተሰጡት መክፈቻዎች  በአይነታቸውና በዘይቤአዊ አቀራረባቸው የሚለዩ ናቸው። የጴጥሮስ መክፈቻዎች "የመንግስተ ሰማያት መክፈቻዎች" ተብለው ሲለዩ፣ የከበረው ክርስቶስ ደግሞ "ቅዱስና እውነተኛ" ስለሆነ የያዘው መክፈቻ በአይነቱ "የሞትና የሲኦልም መክፈቻ" (ራዕይ 1፥ 18) ነው። በኋላም በራዕይ መጽሐፍ እንደሰፈረው፣ መክፈቻዎቹ የእግዚአብሔርን ፍርድ ለመልቀቅ የጥልቁን ጉድጓድ የሚከፈትበት ሆኖ ጥቅም ላይ ሲውል ደግሞ ይታያል፣ (ራእይ 9፥ 1፤ 20፥ 1)።

የመክፈቻዎቹና የቀኖናው ግንኙነት፦

ከፍ ሲል ለማሳየት እንደተሞከረው የመክፈቻዎች ትርክት በሁለቱም ኪዳናት አንድን አምሳል እያመላከተ የሚነበብ ነው። በመክፈቻዎቹ ለሁሉ ክፍት በተደረገና ደግሞም በማይዘጋ መንግስት ልንኖር በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን በንስሃና በቅዱስ ጥምቀት የገባን እኛ ሌሎች ሁሉ ሳይከለከሉ እንዲገቡ ማገዝ አለብን። በጥቅሉ ይህ መንግስተ ሰማያትን ለሰዎች ክፍት አድርጋ ልትጠብቅ አደራ ለተቀበለች ቤተክርስቲያን ያለባትን ተልእኮና በወንጌል የተሰጣትን ቀኖናዊ ኃላፊነት ግልጽ ያደርጋል። ሰዎችም በወንጌሉ እውቀት ፍጹም ነጻ ሆነው በመንግስቱ ውስጥ ይመላለሱ ዘንድ ለዚህ አገልግሎት ታማኝ ሆነው የተቆጠሩ ሰዎች በመክፈቻዎቹ በቆመው ቀኖና እንደ ካህናት የሚያገለግሉት ሁሉ ናቸው።

ቀኖና የተሰኘው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም፤ ትርጉሙ ግን ሕግ፣ ሥርዓት፣ ፍርድ፣ ቅጣት፣ መጠን፣ ልክ ማለት መሆኑን በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ "መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ" በተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 799 ላይ ተገልጾአል። በግሪኩ 'ካኖን' በእብራይስጡ 'ቃኒህ' የተባለ ይህ ቃል፣ የአንድን ነገር ትክክለኛነትና እውነተኛነት ለመለካት፣ ለመመዘን፣ ትክክል መሆን አለመሆኑን መዝኖና አመዛዝኖ ለመለየት፣ መጠኑን ለማወቅ የሚያገለግል መለኪያ ሚዛን ወይም መስፈርት ነው። የክርስቲያናዊ እምነትና ልምምድ ሁሉ የቆመበት መሰረቱ፣ ሚዛኑና መለኪያው የአዲስ ኪዳን ቀኖና ብቻ ነው። በታሪካዊው የቤተክርስቲያን ስነመለኮታዊ አስተምህሮ በልዩ ልዩ ክፍለ ዘመናት እየታወቁና ተቀባይነትን እያገኙ የመጡ ጥንታውያን የእምነት መግለጫዎችም ይሁኑ፣ ጠቃሚ የሰነድ መዛግብት በአዲስ ኪዳን ቀኖና ስር ተገዝተው ሊመዘኑና ሊፈረዱ ይገባቸዋል፤ ከተቀደሰው ቀኖና ባለፈ ልማድን መሰረት አድርገውም በተከተሉት አስተምህሮ አንጻር የአዲሱ ኪዳን እርማት ያስፈልጋቸዋል፤ እንጂ በራሳቸው ቀኖና ሆነው ሕይወታችንን፣ እምነታችንን እና ልምምዳችንን የመወሰን ሥልጣን የላቸውም። የአዲስ ኪዳን ቀኖና ስንል የቅዱሳት መጻህፍት ቀኖና ማለታችን ነው። ይኸውም፣ የመጽሐፍቱን እውነተኛነት፣ ተአማኒነት፣ ቅዱስነት፣ አምልካዊነት፣ አይነኬነት፣ አይተኬነትና አይለወጤነት የተመለከተ ነው። የቆዩና የኖሩትን ታሪካዊ የእምነት መግለጫዎችና ሰነዶች ግን በክርስትና ትምህርት ውስጥ ትክክለኛ ደረጃቸውን አስይዘን ካልጠበቅናቸው በእምነታችንና በልምምዳችን ላይ ፈራጅና ዳኛ ለመሆን ዞሮ ዞሮ ቅዱሳት መጻህፍትን ልተካ ማለታቸው አይቀርም።

ይህ የአዲስ ኪዳን ቀኖና መቼና በማን ስልጣን እንዴት እንደተሰጠና በምን ሁኔታ እኛ ጋር እንደደረሰ ያለን አስተሳሰብ ለእምነታችን ተአማኒነት ወሳኝ ነው። ቅዱሳት መጽህፍት እውነተኛነታቸውና ተአማኒነታቸው የሚያርፈው በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩና እየተነዱ መጻህፍቱን ጽፈው፣ ብዛታቸውን ቆጥረውና ልካቸውን ሰፍረው የሰጡን እነማን ናቸው፣ ጊዜውስ መቼ ነበር በሚለው ድምዳሜ ላይ ነው። ያን ያደረጉት በየትኛውም የቤተክርስቲያን ዘመንና ታሪክ ውስጥ የምናውቃቸው የጥንት ቤተክርስቲያን ሊቃውንትና አባቶች፣ ወይም የካቶሊካውያንና የኦርቶዶክሳውያን መምህራን አልያም የሉተራውያን አዳሾች አይደሉም። ቤተክርስቲያንም በታሪኳ የቅዱሳት መጻህፍት ፍጥረት ሆና ቅዱሳት መጻህፍቱን ተቀባይ ናት እንጂ፣ የቅዱሳት መጻህፍት ደራሲና ፈጣሪ አይደለችም።

"የመንግስተ ሰማያት መክፈቻዎች" የተሰኘውና ለጴጥሮስ የተሰጠው የአዲስ ኪዳን ቀኖና የተጻፈው፣ ከያለበትም የተሰበሰበው እና በሐዋርያትም ማረጋገጫ ተሰጥቶት ቅቡልነትን ያገኘው ሁሉም በምድር ላይ በሕይወት እያሉ ወይም ወደጌታ ከመሄዳቸው አስቀድሞ ከ66 አም በፊት ነው። ቀኖናው የተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ነው። ከክርስቶስ ጋር አብረው የነበሩና በቀጥታ እርሱን የማየትና የመስማት እድሉ ኖሯቸው የአይን ምስክሮች የነበሩ ሐዋርያቱ ብቻ ናቸው። እነርሱም በ70 አም አሮጌው የአይሁድ ኪዳን ከመጠናቀቁና ከመዘጋቱ አስቀድሞ የወንጌሉን መልእክት እና ኢየሱስ ያዘዛቸውን ሁሉ በትጋት ፈጽመዋል። ከእነርሱም መካከል ከአዕማዳቱ አንዱ ቀኖናውን እንዲለይ መክፈቻዎቹን ከክርስቶስ የተቀበለ ባለስልጣን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ነበር። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ጌታ "እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።" (ማቴዎስ 16፥ 18-19) ሲል፣ ለቅዱስ ጴጥሮስ ካልሆነ በቀር ለማንም እንደዚህ አልተናገረም።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ እግዚአብሔር ቃሉን እንዲናገር የሚልከውን ነብይ (ክርስቶስን)  እንደሚያስነሳ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ የተናገረውን ጠቅሶ፣ "ሙሴም ለአባቶች፦ ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን (ክርስቶስን) ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት።" (ሐዋርያት 3፥ 22) ሲል ይናገራል። ሞታችንም ሕይወታችንም የሚወሰንበትን እግዚአብሔር ያስነሳውን ክርስቶስን የማይሰማ ደግሞ ይጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍርድ ነው። እግዚአብሔርም እርሱን ክርስቶስን እንዲሰሙት "የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት" (ሉቃስ 9፥ 35) ብሎ ባዘዛቸው ጊዜ ይህንን ለሐዋርያቱ አጽንቶላቸዋል። ክርስቶስ ቃሉን ተናገረ፣ ሐዋርያቱም እርሱ የነገራቸውን በመንፈስ ቅዱስ እየተነዱ ጻፉ፣ ተረኩትም። እግዚአብሔር ስሙት ያለው ምርጥ ልጁ ደግሞ ስለ ምርጥ ሐዋርያቱ ሲናገር "የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል" (ሉቃስ 10፥ 16) ሲል ቃላቸውን ሞትና ሕይወት የሚወሰንበት የስልጣን ቃል አድርጎታል። እነርሱም ለዚህ አደራ የታመኑ ሆነው እንደተቆጠሩ መጠን፣ ሰው ሁሉ እንደዚያ እንዲያስባቸው " እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን" (1ኛ ቆሮንቶስ 4፤1)፣ እያሉ መክረዋል፤ ስለተጠያቂነቱም፣ "በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል" (1ኛቆሮንቶስ 4፥ 2) ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ክርስቶስም ለአይሁድ ሲናገር "ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?" (ዮሐንስ 5፥ 46-47) ባላቸው ጊዜ የብሉይንና የሐዲስን ኪዳን ቅዱሳት መጻህፍት አንድ ላይ አገናኝቷቸዋል። የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻህፍት በሙላት ተጠናቀው ያልተካተቱበት መጽሐፍም የክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ሊሆን አይችልም።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው የኢየሩሳሌም ከተማና መቅደሱ በእነርሱ የትውልድ ዘመን ውስጥ እንደሚደመሰሱ አስታውቋቸዋል። ሲነግራቸውም ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የሚቀር የለም ብሏቸዋል። ቃሉ የማያልፍ እንደሆነ ነገር ግን የአሮጌው ኪዳን አይሁዳዊ የኃይማኖት ስርዓት ይኸውም አሮጌው ሰማይና አሮጌው ምድር የሚያልፈው በእነርሱ የትውልድ ዘመን ውስጥ እንደሆነ "እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።" (ማቴዎስ 24፥ 34-35) ሲል ነግሯቸዋል።

እነርሱም ስለ እግዚአብሔር መንግስት ሚስጥር ሁሉን ያውቁ ዘንድ፣ "ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤" (ሉቃስ 8፥10) ሲል፣ አብ የነገረውንና ከአብ የሰማውን ሁሉ ለወዳጆቹ "ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና" (ዮሐንስ15፥ 15) በማለት ነግሯቸዋል። ሐዋርያት ያላወቁት የእግዚአብሔር መንግሥት ምሥጢርና እነርሱ ያልደረሱበት መንፈሳዊ ልምምድ በአንጻሩ ዛሬ ማንም ተነስቶ ከአዲስ ኪዳን ቀኖና ጋር በሚጣላ አስተምህሮ አወቅሁት፣ ተገለጠልኝ፣ ደረስኩበት የሚለው ነገር ሁሉ የተሳሳተና የተጭበተበረ ነው።

ሐዋርያትም በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍትንና መልዕክቶቻቸውን ሲጽፉና ማረጋገጫ ሰጥተው ሲያጸድቁ መንፈስ ቅዱስ ይመራቸው ነበር። "አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል" (ዮሐንስ 14፥ 26)፣ ባለው መሰረት ክርስቶስ ለእነርሱ የነገራቸውን ሁሉ እንዲያስታውሱ እና እንዲያስተውሉ ያደርጋቸውም ነበር።

ሐዋርያቱ በቀጥታ ከጌታ የሚቀበሉት መገለጥም ነበራቸው። ጳውሎስ ይህንን ሲመሰክር፣ "ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም" (ገላትያ 1፥ 11-12)፣ ይላል። ስለዚህ በሐዋርያቱ ተጽፈው በቅዱስ ጴጥሮስ መክፈቻዎች ማረጋገጫን አግኝተው በአዲስ ኪዳን የተካተቱ ጽሁፎች ሁሉ መገለጥ ናቸው። የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችም ለዚህ የጴጥሮስ መክፈቻዎች የመፍታትና የማሰር ስልጣን እውቅና ይሰጡ እንደነበር ሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል፤ "እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው" (ገላትያ 2፥ 2)። ከእነዚህ ዋኖች ሆነው ከሚታዩ የእናት ቤተክርስቲያን ኢየሩሳሌም መሪዎች መካከል አንዱና ዋናው ጴጥሮስ መሆኑ ግልጥ ነው። የተቀበሉትን መገለጥ እና የሚሰብኩትን ወንጌል ይዘው ከመሮጣቸው በፊት አምጥተው ለጴጥሮስ የማስታወቅ ልምምዱ ነበራቸው።

ሐዋርያት በራሱ በእግዚአብሔር የተመረጡ ሲሆኑ ቃሉንም እንዲናገሩ ሥልጣን ሰጥቶ የላካቸው እግዚአብሔር ራሱ ነው። "ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና። እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ" (ዮሐንስ 15፥ 15-16)። ቃሉን ለማገልገል የተሰጣቸው ጸጋ እና የሐዋርያነት ስልጣን በክርስቲያናዊ እምነትና ልምምድ ላይ የመጨረሻው ወሳኝ ስልጣን ነው። ጳውሎስም ስለዚህ ሲጽፍ "በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤" (ሮሜ 1፥ 5) ይላል።

ሐዋርያት ቀድሞ ኢየሱስ የነገራቸው እና የረሱት፣ ያላስተዋሉት፣ ዳሩ ግን በጊዜ ቆይታ አስታውሰውና አስተውለው የተናገሩትና የጻፉት የኢየሱስ ቃል አላቸው። "ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከእናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም" (ዮሐንስ 16፥ 4)። የመንፈስ ቅዱስ መምጣት የጌታን ቃል እያሰቡና እያስተዋሉ በድፍረት እና በስልጣን እንዲሰብኩ ደግሞም እንዲጽፉ በመንፈስ መነዳትን ሰጣቸው።

ኢየሱስ የአዲስ ኪዳን መጻህፍትን የመለየቱንና የመወሰኑን  ስልጣን በተለይ በመክፈቻዎቹ የሰጠው ለሐዋርያው ጴጥሮስ ነው። ኢየሱስ ለጴጥሮስ ሲናገር የመንግስተ ሰማያትን "መክፈቻዎች" ይኸውም የአዲሱን ኪዳን እውነቶች እሰጥሃለሁ ይለዋል። ከፍ ሲል ለማሳየት እንደተሞከረው "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ" በሚለው የመገለጥ ምስክርነት ይኸውም በኢየሱስ ማንነት ላይ ትኩረት የሚያደርገው መክፈቻ የቀኖናው መሰረት ነው። ይህ እንግዲህ ሁሉንም የተቀደሱ ቀኖናዊ ጽሁፎች ከ70 አም በፊት የመለየትን፣ አንድ ላይ የማሰርንና የመጠረዝን፣ ቀኖናዊነት የሌላቸዉንም ወደ ጥራዙ እንዳይካተቱ የማገድና የመቃወምንም ስልጣን የሚጨምር ነው። በአዲስ ኪዳን ቀኖና ውስጥ መካተት ያለባቸውን መጻህፍትና የጽሁፍ መልዕክቶች የለያቸውና የወሰናቸው በተለይ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ነው።

"እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።" (ማቴዎስ 16፥ 18-19)

ሁሉም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፈው የተጠናቀቁትና የተዘጋጁት ጴጥሮስ በ65 አም ላይ በሰማዕትነት ከመሞቱ አስቀድሞ ነው። ይኸውም የጴጥሮስ ሞት ሁለተኛውን የጴጥሮስ መልእክቱን በ64 አም ላይ ከጻፈ በኋላ ወዲያው ብዙም ሳይቆይ የሆነ ነው። ይህንንም ሞቱን በሁለተኛይቱ መልዕክቱ ሲያስታውቅ "ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና" (2ኛጴጥሮስ 1፥ 14) ብሏል።

ጳውሎስ ሲጽፍ ወንጌል አስቀድሞ በዚያው ትውልድ ለአህዛብ ሁሉ የተሰበከ መሆኑን፣ "ይህም በዓለም ሁሉ ደግሞ እንዳለ ወደ እናንተ ደርሶአል፥ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ ደግሞ እንዳለ እንዲህ በዓለም ፍሬ ያፈራል ያድግማል" (ቆላስይስ 1፥ 6፣ 23)፤ "እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማች አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ" (ሮሜ 1፥ 8)፣ ሲል ይናገራል። የበዓለ አምሳውም ኹነት ይህንው ያረጋግጣል፣ (ሐዋርያት 2፥ 5-12)።

ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለተጻፉት ለዮሐንስ፣ ለጳውሎስ፣ ለጴጥሮስ፣ ለሁለቱ የጌታ ወንድሞች ለያዕቆብ እና ለይሁዳ  ጽሁፎች እውቅናን ስጥቷቸዋል። ለአራቱ ወንጌላትና ለሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም ማረጋግጫን ሰጥቷል። በጴጥሮስ ይሁንታንና ተቀባይነትን ያላገኘ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ የለም። እኔ የዕብራውያን መልዕክትም ቢሆን በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተጽፏል ብዬ አምናልሁ። በተለይ አሥራ አራቱንም የጳውሎስን መልዕክቶች አንድ ላይ አስሮ የሰበሰባቸው ጴጥሮስ ነው። ጴጥሮስ ሲናገር አንዳንዶቹ ሳይሆኑ ነገር ግን ሁሉም የጳውሎስ መልዕክቶች ከተቀረው የቅዱሳት መጻህፍት ጽሁፎች ጋር ስሙም መሆናቸውን ያመለክታል።

"የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።" (2ኛ ጴጥሮስ 3፥15-16)።

በጠቅላላው ሃያ ሰባቱም የአዲስ ኪዳን መጻህፍት አስቀድሞ ቀኖና ሆነው የተመረጡት፣ የተለዩትና እውቅና የተሰጣቸው በጴጥሮስ ነው። ሐዋርያትም በስልጣናቸው የእነዚህን መጻህፍት ቅጂ ፈቅደው በአብያተክርስቲያናቱ ሁሉ እንዲሰራጩ አድርገዋል። እንግዲህ በመክፈቻዎቹ የተሰጠ ሐዋርያዊ ቀኖና ተብሎ የሚጠራው ይኸው ነው፣ ሌላ ቀኖና የለም። በዚያ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የእነዚህ ሃያ ሰባት የአዲስ ኪዳን መጻህፍት ሁሉም ቅጂ ያልነበራቸው አብያተክርስቲያናት እምብዛም አልነበሩም። በጊዜው የነበሩት የኢየሩሳሌም፣ የሮሜ፣ የአንጾኪያ፣ የእስክንድርያ፣ እና ምናልባትም ሌሎች ጥቂት ትላልቅ አብያተክርስቲያናት ያለጥርጥር የሁሉም መጻህፍት ቅጂዎች ነበሩአቸው።

የነዚህ አይነተኛ መጻህፍት ብቸኛ ማረጋገጫ እና ማስተማመኛ የሚወሰነው የአዲስ ኪዳንን ቀኖና ለማሰርና ለመፍታት በመክፈቻዎቹ የተቀመጠውን ሐዋርያዊ ስልጣን በመጠቀም ነው፤ እንጂ ከዚህ ሐዋርያዊ ስልጣን ውጪ ቀኖናን ሊወስን የሚችል ምንም አይነት ታሪካዊ የቤተክርስቲያን ጉባኤም ሆነ የእምነት መግለጫ የለም። ሞታችንን እና ሕይወታችንን የሚወስኑት በመንፈስ ቅዱስ ተሰጥተው መክፈቻዎቹን በተቀበለው ሐዋርያዊ ስልጣን ቀኖና የሆኑ የአዲስ ኪዳን መጻህፍት ናቸው፣ እንጂ በታሪካዊ የቤተክርስቲያን ጉባአኤዎች በስምምነትና በድምጽ ብልጫ ቅቡልነት ያገኙ ድርሳናትና መዛግብት አይደሉም። "ቅዱሳት መጻህፍት ብቻ" የተሰኘው የወንጌላውያን አማኞች የእምነት አቋም ቀኖናን ለመወሰን ክርስቶስ ካቆመው ሐዋርያዊ ስልጣን የሚመነጭ ካልሆነ ዝም ብሎ የቃላት ጨዋታ ብቻ ሆኖ የማንንም እምነት ሳያጸና ይቀራል። ጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ መጻህፍቱን ቀኖና አድርጎ ማረጋገጫ ሰጣቸው፣ እንዳይናወጡ እና እንዳይለወጡም በሰማያት አሰራቸው። ሐዋርያቱም "ከተጻፈው አትለፍ" (1ቆሮንቶስ 4፥ 6) የሚለውን በእኛ ተማሩ አሉን እንጂ ያልተጻፈ ሌላ መገለጥ አላቆዩልንም። ጴጥሮስም ሰማእት ሆኖ ከመሞቱ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ የወንጌሉን እና የክርስቶስን ትምህርት እንዲያሳስባቸውና እንዲያስታውሳቸው የአዲስ ኪዳንን ቀኖና እንደሚተውላቸው ዋስትና ሰጥቶ ሲያረጋግጥላቸው፣ "ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ" (2ኛ ጴጥሮስ 1፥ 15) ይላል። እያላቸው ያለው፣ "እኔ ጴጥሮስ ከዚህ ስጋዬ በሞት ከመለየቴ በፊት በተሰጠኝ ስልጣን እነዚህን የተማራችኋቸውን ጉዳዮች ዘወትር የሚያሳስቧችሁንና የሚያስታውሷችሁን ማለትም የአዲስ ኪዳንን ቀኖና በጥንቃቄ ልተውላችሁ አረጋግጥላችኋለሁ" ነው።

ኤድዋርድ ኢ. ስቲቨንስ የአዲስ ኪዳን ቀኖና መጻህፍቱ የተጻፉበትን ጊዜ በሚከተለው ዝርዝር አቅርቦታል፦

ማቴዎስ ከ49 ዓ.ም አስቀድሞ
ገላትያ 51-52 ዓ.ም
1ኛ ተሰሎንቄ 51-52 ዓ.ም
2ኛ ተሰሎንቄ 51-52 ዓ.ም
ማርቆስ 55 ዓ.ም
1ኛ ቆሮንቶስ57 ዓ.ም
2ኛ ቆሮንቶስ 57 ዓ.ም
ሮሜ 58 ዓ.ም
ሉቃስ 61 ዓ.ም
ሐዋርያት ሥራ 61-62 ዓ.ም
ዮሐንስ 60-62 ዓ.ም
ያዕቆብ 61-62ዓ.ም
1ኛ 2ኛ እና 3ኛ ዮሐንስ 61-62 ዓ.ም
ራዕይ 62-63 ዓ.ም
ኤፌሶን 62-63 ዓ.ም
ቆላስይስ 62-63 ዓ.ም
ፍሊሞና 62-63 ዓ.ም
ፍልጵስዮስ 62-63 ዓ.ም
ዕብራውያን 62-63 ዓ.ም
ቲቶ በ63 ዓ.ም አጋማሽ
1ኛ ጢሞቴዎስ በ63 ዓ.ም አጋማሽ
1ኛ ጴጥሮስ በ63 ዓ.ም አጋማሽ
2ኛ ጢሞቴዎስ በ63 ዓ.ም አጋማሽ
ይሁዳ 64 ዓ.ም
2ኛ ጴጥሮስ 64 ዓ.ም
gkr