ኢየሱስ እና የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ተሳስተው ነበር ወይ?
የፕሪቴሪዝም አመለካከት ሊብራሎችና ተጠራጣሪ ከሃድያን በኢየሱስ እና በአዲስ ኪዳን ታማኝነት ላይ የሚሰነዝሩትን ትችት እና ተቃውሞ በመመከት ዋና የሆነውን የሙግታቸውን ውቅር ፈጽሞ ውድቅ ያደርጋል። ለምሳሌ ታዋቂው ሊበራል የነገረ መለኮት ምሁር የሆነው አልበርት ሽዌይዘር ፣ The Quest For The Historical Jesus በተሰኘው መጽሐፉ ክርስቶስ በባልንጀሮቹና በእርሱ ዘመን በነበሩ አብሮ አደጎቹ የህይወት ዘመን ውስጥ (ማለትም፣ “በዚህ ትውልድ”፣ "በዚያ ከእርሱ ጋር ከቆሙት መካከል አንዳንዶቹ ሳይሞቱ" በፊት) ተመልሶ እንደሚመጣ የተነበየ መሆኑን ለማሳየት በርካታ ቃላቱንና ንግግሮቹን ይጠቅሳል። ሽዌይዘር በደረሰበት ድምዳሜ ኢየሱስ ቃል በገባው መሰረት እመለሳለሁ ባለበት ጊዜ መመለስ አልቻለም፣ ስለዚህ በትንቢቶቹ ተሳስቶ ነበር ብሎ ጉዳዩን ዘግቶታል። የዚህን ምሁር መስመር ተከትለው ቲኦሎጂ እናስተምራለን የሚሉ ሊብራሎች በመካከላችን እንዳሉ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? ቤተ ክርስቲያንስ ቲኦሎጂ እናስተምርልሻለን ከሚሉ እንዲህ ካሉ ሊብራሎቿ በጌታዋና በአዳኝዋ ታማኝነት ላይ የሚሰነዘረውን እንዲህ ያለ ትችትና ነቀፋ ለመመከት ምን ያህል በቃሉ ትምህርት ታጥቃ ተዘጋጅታለች?
በርትራንድ ራስል የተባለ ከሃዲ ደግሞ፣ Why I am not a Christian በሚለው መጽሐፉ፣ ያንን ክርስቶስ ዳግመኛ ለመመለስ የሰጠውን ተስፋ ባለመፈጸሙ ከታማኝነቱ የወደቀ መሆኑን ለማሳየት፣ የራሱን የክርስቶስን ቃል ተጠቅሞ ጌታችንን ለማጣጣልና ክርስትናን ለመቃወም ሲያውለው ይታያል። ብዙ እንደዚህ ያሉ ተቺዎችና ተቃዋሚዎች (ሊበራሎች፣ ተጠራጣሪዎች፣ አምላክ የለሾች፣ አይሁዶች እና እስላሞች) ወደነዚያው የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ዝርዝር እያመለከቱ ጌታችን ኢየሱስን ሐሰተኛ ነቢይ እንደሆነ እንዲሁም መላው የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን በጽሁፎቻቸው ተሳስተው እንደነበሩ እንጂ ምንም አይነት ትክክለኛነት እንዳልነበራቸው፣ በመንፈስም ተመርተው እንዳልተናገሩ አረጋግጠናል ብለዋል።
በበርካታ ክርስቲያኖች የሃያኛው ክፍለ ዘመን ዕቅበተ እምነት ምሁር ተደርጎ የሚቆጠረው ሲ.ኤስ.ሉዊስም እጅግ ተነባቢ ከሆኑ ሥራዎቹ በአንዱ፦The World's Last Night: And Other Essay,፣ በተሰኘው መጽሐፉ፦ "የፈለጋችሁትን ማለት ትችላላችሁ፣ ጥንታውያን የሆኑቱ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ግን ያምኑት የነበረው አቡቀለምሲሳዊ እምነት ሃሰት መሆኑ ተረጋግጧል። ምክንያቱም፣ ዳግመኛ ምጽአቱ እንዲፈጸም ይጠባበቁ የነበሩት በገዛ ራሳቸው የምድር ላይ የህይወት ዘመን መሆኑን ከጠቅላላው የአዲስ ኪዳን ገጾች በግልጽ ማየት ይቻለናልና። እጅግ የከፋው ደግሞ ለዚህ መጠባበቅ አሳፋሪ የሆነ ምክንያት የነበራቸው መሆኑ ነው፤ መምህራቸውና ጌታቸው ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ የነገራቸው እንደዚያ እንዲጠባበቁ ነበርና። ያንን ቅዠት ያካፈላቸውና የፈጠረባቸውም እርሱው ነበር። በብዙ ሌላ ቃልም "ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" ሲል ነገሯቸው ነበር፤ ዳሩ ግን ይህን ሲል ተሳስቶ ነበር። እንደውም እርሱ ከማንም በተሻለ ስለአለም መጨረሻ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው፤ ይህም ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ሁሉ እጅግ አሳፋሪው ጥቅስ ነው" ሲል ይጽፋል። (ገጽ 97-98.)
መጻኢያን በነገረ ፍጻሜ አስተምህሯቸው ይህንን ትችት ለመመከት የሚያቀርቡት፣ ኢየሱስ እስካሁን እንዳልመጣ ወይም ገና ወደፊት አልያም በቅርቡ እንደሚመጣ አዲስ ኪዳንን ጠቅሰው የሚሰነዝሩት መከላከያ መሰል ውዥንብር ሙከራ ለሊብራሎችና ለከሃዲያን ምሁራን በእጃቸው ዱላ እንደማቀበል ይቆጠራልንና የሚሉትን ካላወቁ ዝም ቢሉ ይመከራል። በታናሽዋ የንባብ ልምምዴ ከፍ ሲል የጠቀስኩትን ይህንን አሳፋሪ የሆነ የሊብራሎችና የከሃዲያን አስተያየትና ትችት በመመከት በጌታችን ፊት ላይ የተተፋውን "ምሁራዊ" ቅርሻት ለመጥረግ አቅም ያለው አስተምህሮ ግን ፕሪቴሪዝም ብቻ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ከዚህ በታች ያሉት የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባት ዝርዝር እነዚህ ተቺዎችና ነቃፊዎች የክርስቶስንና የአዲስ ኪዳንን ተአማኒነት ለማጥቃት ሲሉ ጠቅሰው የሚጠቀሙባቸው ናቸው። የጠላትህን ትጥቅ አይነቱንና ብዛቱን ሳታውቅ እንዲሁ በሜዳ "ኢየሱስ ይመጣል" የሚል መፈክር እያሰማህ ጦርነቱን አታሸንፍም። ተመልከቱ በነዚህ ምንባባት አብዛኛዎቹ የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን በዝርዝር ተወክለዋል። ቃሉን እናምናለን፣ ለህይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚጠቅመው ምክር ሁሉ አለበት፣ በቤተክርስቲያንም ውስጥ አስተምህሮንና ልምምድን ሁሉ የሚገዛ ብቸኛ ሥልጣን ነው ብለን የምንሰብክና የምናስተምር ሁሉ ይህንን የእነርሱን የትችት ክብደት በቀላሉ ለመረዳት እንዲቻለን እነዚህን ጥቅሶች ስናነብ ከተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሆነን በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ታሪካዊ አውድ ውስጥ እየተመለከትን እንድናጠናቸው አሳስባለሁ፡-
ሀ. የዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅርብ እንደነበር የሚያሳዩ የአዲስ ኪዳን ምንባባት
♦ ማቴዎስ 10፥ 23 (ከመመለሱ በፊት ሐዋርያት እስራኤልን ዞረው አይጨርሱም።)
♦ ማቴዎስ 16፥ 27-28 (ከእርሱ ጋር ከነበሩት መካከል አንዳንዶች አስቀድመው ሳይሞቱ በሕይወት ኖረው ሲመጣ ያዩታል)
♦ ማቴዎስ 24፥ 33-34 (ትንቢቱ ፍጻሜውን የሚያገኘው፣ ጌታም የሚመጣው ትውልዱ ከማለቁ በፊት)
♦ ማቴዎስ 26፥ 64 (ያኔ የአይሁድ ገዢዎች የነበሩቱ እርሱ በደመና ሲመጣ እንዲያዩት በሕይወት መቆየት አለባቸው)
♦ ሮሜ 13፥ 11-12 (የሮሜ መልዕክት እየተጻፈ "አሁን" በተባለበት በዚያን ጊዜ ሰአቱ ደርሶና ቀርቦ ነበር)
♦ ሮሜ 16፥ 20 (ያኔ የሮሜ ክርስቲያኖች ገና እያሉ ሰይጣን ከእግራቸው በታች ፈጥኖ እንደሚቀጠቀጥ ይጠበቅ ነበር)
♦ 1ቆሮንቶስ 7፥ 26-31 (ያኔ 1ኛ ቆሮንቶስ እየተጻፈ ሳለ ጊዜው እያጠረ፣ አለሙም እያለፈ ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር)
♦ 1ቆሮንቶስ 10፥ 11 ("እኛ" በተባሉት በጳውሎስና በቆሮንቶስ ምዕመናን ላይ የዘመናት መጨረሻ ደርሶ ነበር)
♦ 2ተሰሎንቄ 2፥ 7 (የአመጽ ሚስጥር "አሁን" በተባለው ጊዜ ያኔ በስራ ላይ ነበር)
♦ ዕብራውያን 1፥ 2 ("በዚህ" ሲል የጠቀሰው ያ ጊዜ የመጨረሻው ዘመን ነበር)
♦ ዕብራውያን 9፥ 26 ( እነርሱ የኖሩት ጌታ ኃጢአትን ሊሽር በተገለጠበት የአለም / የዘመን ፍጻሜ ላይ ነበሩ)
♦ ዕብራውያን 10፥ 25 (ለጸሐፊውና ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ያኔ ቀኑ እጅግ እየቀረበ ነበር)
♦ ዕብራውያን 10፥ 37 ("ሊመጣ ያለው" እርሱ ሳይዘገይ ሊመጣ የቀረው "ጥቂት ጊዜ" ነበር)
♦ ያዕቆብ 5፥ 7-9 (ያኔ ያዕቆብ እየጻፈ የጌታ መምጫው ቀርቦ ሊፈርድ በደጅ ነበር) ፊልጵስዩስ 4፥ 5ን አስተያይ
♦ 1ጴጥሮስ 1፥ 20 (ያኔ ጴጥሮስ መልዕክቱን እየጻፈ ሳለ ጊዜው የመጨረሻው ዘመን ነበር)
♦ 1ጴጥሮስ 4፥ 7 (ያኔ ጴጥሮስ መልዕክቱን እየጻፈ ሳለ የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦ ነበር)
♦ 1ጴጥሮስ 4፥ 17 (ፍርድ የሚጀምርበት ጊዜ ጴጥሮስ መልዕክቱን እየጻፈ ሳለ ያኔ ደርሶ ነበር) ራዕይ 3፥ 10ን አስተያይ
♦ 1ዮሐንስ 2፥ 8፣ 17፣ 18 (ሐዋርያው ዮሐንስ ያኔ "አሁን" እያለ በጠቀሰው ጊዜ ሰአቱ የመጨረሻ እንደሆነ ያውቅ ነበር)
♦ ይሁዳ 18፣19 (ይሁዳ መልዕክቱን እየጻፈ ሳለ ያኔ የመጨረሻው ዘመን ዘባቾች ነበሩ)
♦ ራዕይ 1፥1-3፤ 22፥ 6፣10 (ራእዩ እይተጻፈ ሳለ በራእዩ የተነገረው ነገር ሁሉ "ቶሎ" እና ፈጥኖ ሊሆን "በቅርብ" ነበር)
♦ ራዕይ 22፥ 7፣ 12፣ 20 (ዮሐንስና ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ክርስቶስ ቶሎ ይመጣል ሲሉ ተንብየዋል፣ ጠብቀዋልም) ራዕይ 2፥ 16 እና 3፥ 11ን አስተያይ
ለ. ስለ ዘመኑ መጨረሻና ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ በምሳሌ የቀረቡ ትምህርቶች፦
♦ ማቴዎስ 13፥ 24-43 የእንክርዳዱና የመከሩ ምሳሌ
♦ ማቴዎስ 13፥ 47-50 ወደ ባህር ተጥላ ከሁሉ አይነት የሰበሰበች መረብ ምሳሌ
♦ ማቴዎስ 21 33 ጀምሮ (ማርቆስ 12፥ 1 ጀምሮ፤ ሉቃስ 20፥ 9 ጀምሮ) የወይኑ አትክልት ምሳሌ
♦ማቴዎስ 22፥ 1ጀምሮ (ሉቃስ 14፥ 16 ጀምሮ) የሰርጉ ድግስ ምሳሌ
♦ ሉቃስ 19፥ 11-17 መንግስትን ይዞ ሊመለስ ወደሩቅ አገር የሄደ መኮንን ምሳሌ
♦ ማቴዎስ 25 የአስሩ ቆነጃጅትና የመክሊቱ ምሳሌ
♦ ሉቃስ 13፥ 6-9 የፍሬ ቢሷ በለስ ምሳሌ
ሐ. ሊመጣ ስላለ ጥፋትና ስለ ምጽአቱ የሚያመለክቱ ሌሎች ንግግሮች
♦ ማቴዎስ 3፥ 7-12 (ሉቃስ 3፥ 7-17፤ ሉቃስ 12፥ 49)
♦ ማቴዎስ 10፥ 17-34 (ሉቃስ 10፥ 3-21፤ ሉቃስ 12፥ 11-56)
♦ ማቴዎስ 23፥ 29-24፥ 44 (ሉቃስ 13፤ ሉቃስ 17፥ 20-37፤ ሉቃስ 21)
♦ ሉቃስ 11፥ 42-52፤ 12፥49፤ 13፥ 33-35፤ 19፥ 41-44፤ 23፥ 27-31
በመጨረሻም፣ ቤተክርስቲያንን የራሷን የእምነት መጽሐፍ ተጠቅመው በጥርጣሬና በክህደት በትር ለሚመቷት፣ ጌታዋንና መድሐኒቷን እያዋረዱ ለሚያጠለሹ፣ የምትመራበትንም የህይወት ቃል ተአማኒነት ውድቅ ለማድረግ በምሁራዊ ለዘብተኛነት ማብራርያ ለሚሰጡና የብዙዎችን እምነት ለሚገለብጡ ከሃዲያን፣ ሞልቶ ከፈሰሰው የመጻኢያን ጎራ ምሁራን ምን ምካቴ ይኖር ይሆን? ወዮ! አዝናለሁ፣ ምንም የለም። ይልቁኑ መጻኢነት የሚያቀርበው መከላከያ ራሱን መጻኢነትን ጎርፍ ሆኖ ጠርጎ የሚወስደውን ውሃ ይተፋል። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሆይ በዚህ የኪሳራ ነገረ ፍጻሜ ምንም ተስፋና ተገን የለሽም። እንዲህ ያለውን ተረትና ቡትቶ የሆነ ትምህርት እምቢ ማለትን እንዲሰጥሽ እጸልያለሁ።
Gkr ታናሽ ባሪያው ነኝ።
ፕሪቴሪዝም ይለመልማል!!