ፓሮውዥያው ተፈጽሟል!
"ቶሎ" ማለት ምንም መቀባባት አያሻውም፣ ያው "ቶሎ" ማለት ነው።
መግቢያ፦
MELLO የተሰኘውን የግሪክ ቃል "ሊሆኑ ያሉ ነገሮች" በሚል መተርጎሙንና ይኸውም "እርግጠኛው አይቀሬ" እንደሆነ፣ በነገረ ፍጻሜ መረዳታችን ውስጥም ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ የዳሰስኩበትን ሰፋ ያለ ጽሁፍ ከዚህ ቀደም ማስነበቤን አስታውሳለሁ፤ ጽሁፉም በመጠኑ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር አነጋግሮን ነበር። ምናልባት ጽሁፉን የማየት አጋጣሚ ያላገኛችሁ በብሎገሬ ላይ ይገኛል፣ እነሆ ሊንኩ፦
http://gizachewkr.blogspot.com/2021/09/blog-post_26.html
አሁን ደግሞ እንደቀድሞው ሰፊ ባይሆንም፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሳነሳውና ስጥለው የቆየሁትን 'en tachei' የተሰኘውን የግሪክ ቃል "ቶሎ" በሚል እንደተተረጎመና በነገረ ፍጻሜ ምልከታችን ላይ ያለውን ጠቀሜታ በአጭሩ እንድንመለከት እወዳለሁ
"ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥" ራእይ 1፥ 1
"እርሱም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ።" ራእይ 22፥ 6
የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተናገረው ለሰዎች ትርጉም ባለው ቃል እንደነበር ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ጊዜ ጠቋሚ ምንባባቱም ቢሆኑ ሆነ ተብሎ እኛን ለማታለል እና ለማደናገር አልተጻፉም። እግዚአብሔር አምላክ ወደፊት ስለሚፈጸሙት ክንውኖች ለአማኞች እንዲነግራቸው መልአኩን ልኮ እንደ ነበር የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ለዚህ ማሳያ ነው። የራዕይ መጽሐፍ ማለት እንቆቅልሽ ወይም ድብቅ ሚስጥር ወይም ድፍን ቅል አይደለም፣ ይልቁንም ሰዎች ሊከሰቱ ስላሉ ሁከቶች እና ብጥብጦች ያውቁ እና ይረዱ ዘንድ እንዲቻላቸው የተሰወሩ ነገሮችን የሚገልጥ 'መገለጥ' ነው። መጽሐፉን አክብሩት፣ ታዘዙትና ተጽናኑበት እንጂ ስታነቡት አትሸበሩ፤ እርሱን እንተረጉማለን እያሉ በምዕመናን ላይ ሽብርን ከሚነዙ መጻኢያን መምህራንና ሀሰተኛ ነብያት ራቁ፣ በማህበራቸውም አትደመሩ። የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ማስፈራርያና ያልተገባ ትርፍ መሰብሰቢያ ከሆነላቸው የቀበሮ ባህታውያን ጋር ምን ትሰራላችሁ?
የመጽሐፉ አውዳዊ ቅኝት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ጥንታዊው የሮም ዓለም ነው። መጽሐፉ በመሰረታዊነት ደግሞ ደብዳቤ ነው፣ ደብዳቤውም የተላከላቸው በኩረ ተደራሲያን ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በትንሿ እስያ (በዛሬዋ ቱርክ) ውስጥ በ62 ዓ.ም አካባቢ ለነበሩ ሰባት እውነተኛ፣ ታሪካዊና በስም ተለይተው ለሚታወቁ አብያተ ክርስቲያናት ነው እንጂ ከ2000 ዓመታት በኋላ ግልጽ ባልሆነ አሻሚ ጊዜ ውስጥ ለሚኖሩ ለማይታወቁና ሚስጥር ለሆኑ ሰዎች የተነገረ ትንቢት ወይም ንግርት አይደለም። ይሄ መጽሐፉን ልንተረጉም ስንነሳ የሚገዛን አውዳዊ መርህ ነው።
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ “በቅርቡ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች በመግለጥ በእምነታቸው ለማጽናትና ለማበረታታት ለእነዚያ እውነተኛና ታሪካዊ አማኞች፣ ከኢየሱስ የተላከ መልእክት ነው። በግሪኩ: 'en tachei' ማለት በፍጥነት (quickly) ማለት ነው፤ ቃሉ ጥቅም ላይ በዋለበት የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ሁሉ ከጊዜ አንጻር ቶሎ ሊፈጸሙ ያሉ ነገሮችን እና ፈጥነው በጥድፊያ እንዲከናወኑ የተመደቡ አስቸኳይ ጉዳዮችን "ጊዜ የለም" በሚል ስሜት በችኮላ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች ያመለክታል [the things which must soon take place and come to pass in quickness ] (ራእይ 1፥ 1፤ 22፥ 6)
በመጽሐፉ የመግቢያ ምዕራፍ እና በመዝጊያው ምዕራፍ ላይ የሚገኙት እነዚህ ሁለቱ ጥቅሶች (ራዕ 1፡1፣ 22፡6)፣ ራእዩ ያካተታቸውና በትንቢቱ መጽሐፍ የተነገሩት ክንውኖች ሁሉ በዚያው አንድ ትውልድ ውስጥ ማለትም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በቅርቡ እንደሚፈጸሙ የሚናገረውን መልእክት በአንድነት አዋቅረው እንደያዙ እንደ ሁለቱ የመጽሐፉ ቅንፍ መሆናቸውን አስተውሉ።
ኢየሱስም በትንቢቱ የእነዚህ ሁሉ ትንቢታዊ ክንውኖች መቃረቡን ለማጉላት " ዘመኑ ቀርቦአል….." [በግሪኩ: 'ho gar kairos engys' ማለትም ጊዜው ቅርብ ነው ማለት ነው] (ራእይ 1፥ 3) ሲል ተናግሯል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ "ፓሮውዥያውን" (ዳግመኛ ምጽአቱን እንደማለት ነው) የሚያዩ አንዳንድ የተወሰኑ ሰዎችን "እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።" (ራእይ 1፥ 7) ሲል ግልጽ አድርጓል።
“የወጉት” የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው የአሮጌው ኪዳን እስራኤልን ሲሆን፣ ያም የመጨረሻው ዘመን ክፉ ትውልድ ነው፣ እነርሱም መሲሐቸውን የገደሉት ሰዎች ናቸው። በኃይልና በክብር ተመልሶ ሲመጣ ያዩት ዘንድ ያኔ እነርሱ በሕይወት መኖር አለባቸው።
ከዚያም ኢየሱስ፣ በመጽሐፉ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ፣ እነዚህ ሁሉ በመጽሐፉ ተካተው ያሉ ክንውኖች በቅርቡ እንደሚሆኑ የሚናገረውን ማስጠንቀቂያ ሦስት (3) ጊዜ ደጋግሞ "እነሆ በቶሎ እመጣለሁ" [በግሪኩ: 'tachy' ማለትም: quickly] (ራእይ 22፥ 7፣ 12፣ 20) ሲል ተናግሯል።
ሲጠቃለል፦
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ የሚያወራው “በቅርቡ” ቶሎ/ፈጥኖ፣ ስለሚሆኑ ነገሮች ነው፣ ይኸውም ማለት መጽሐፉ በመጀመሪያ የተጻፈላቸው ደቀ መዛሙርት በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ስለ ሚመጣው የፓሮውዥያ ምጽዓት ትንቢት ተናግሯል ማለት ነው፤ እንዲሁም እነዚያ የመጀመሪያው ከፍለዘመን የመሲሁ ገዳዮች እንኳን እርሱ በፍርድ ሲመለስ በሕይወት ሆነው ቁጣውን እንደሚያዩና እንደሚቀበሉ ይጠቁማል። እስካሁን ከመጽሐፍ ቅዱሴ ጋር ባለኝ ትውውቅ ይህንን ያፈጠጠ እውነታ ከሚክዱ በቀር እውነታውን በበቂ ሊያስተባብል የተቻለው ስነመለኮታዊ ምሁርም ሆነ ጥሁፍ አላየሁም።
መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት የሌለበት እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብላችሁ የምታምኑ ወንድሞችን ልጠይቅ፣ እስቲ መልሱልኝ፤ ኢየሱስ አሁንም እንኳ እንደተናገረው ገና ያልተመለሰ ከሆነ “የወጉትም እንኳ” ከደመና ጋር ሲመጣ ያዩታል ሲል የሚናገረው ታዲያ ለምንድን ነው? መከራና ግፍ ለሚቀበሉ ለነዚያ ለድሆቹ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አማኞች እና የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ተጽፎላቸው ለነበሩ በኩረ ተደራስያንስ ቢሆን እንዲህ ያለ የውሸት ተስፋ መስጠት እና 'ቶሎ' ይመጣል የሚሉ ባዶ መግለጫዎችን ማስተጋባትስ ምን የሚሉት ግራ ማጋባት ነው? እውነታውን ሳይክድ ይህንን ጥያቄዬን ሊመልስልኝ የሚቻለው ካለ በልብ ስፋትና በትህትና ላዳምጠው ዝግጁ ነኝ። የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ቤት ሁልጊዜ የተማሪ ቤት እንጂ የበቁ ምሩቃን የሉበትምና።
የሚሆነው ከሁለት አንዱ ነው፣ ይኸውም ወይ እነዚያ ቃላት ለዋናዎቹ በኩረ ተደራስያን ግልጽ የሆኑና የማያሻማ ትርጉም ያላቸው ናቸው (ማለትም "ቶሎ" ማለት ያው "በቶሎ" እንዲሁም " በቅርቡ" ማለት ያው "በቅርቡ"፣ "በፍጥነት" ማለትም ያው "በፍጥነት" ማለት ነው እንጂ ምንም ሰምና ወርቅ የላቸውም)፤ አልያም እነዚህ ቃላት ባዶና ምንም ትክክለኛ ትርጉም የሌላቸው ናቸው ከተባለ፣ እንግዲያውስ የትኞቹም ሰዎች ቢሆኑ ምንም ትርጉም ከማይሰጡ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክቶች ምንም መማር አይችሉም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን እያረማችሁና፣ "አይ 'ቶሎ' ሲል እኛ የሰው ልጆች ጊዜን በምንረዳበት አኳኋን ቶሎ ማለቱ ሳይሆን ሌላ ነገር ማለቱ ነው" እያላችሁ የምትደናበሩና የምታደናብሩ መምህራን ልምከራችሁ፤ በመጀመርያ ቁጭ በሉና ቃሉን እንደተጻፈው ማመንና ማጥናት ጀምሩ፣ ከዚያ በኋላ ታስተምሩናላችሁ።
ተመልከቱ፣ የእግዚአብሔር ቁጣ ልክ ኢየሱስ የሰው ልጅ ተመልሶ በፍርድ እንደሚመጣ እንደተነበየው ሁሉ በመጨረሻው ክፉ የአሮጌው ኪዳን የእስራኤል ትውልድ ላይ፣ ያኔ በ70 ዓ.ም ላይ እንደወረደባቸው ታሪክ ዘግቦታል።
ፍላቪየስ ጆሴፈስ የተባለው የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አይሁዳዊ የታሪክ ምሁር፣ በኢየሩሳሌም እና በሌሎች የይሁዳ ከተሞች ያሉ ሰዎች ያኔ በ70 ዓ.ም. ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በከበቧት ወቅት የመላእክትን ሠራዊት “በደመና ላይ ሆነው ሲመጡ” ያዩበትን አስደናቂ ራእይ እንዲህ ዘግቦታል፦
….ከዚያ ከበዓሉ ጥቂት ቀናት በኋላ፣’… በ21ኛው በአርጤምስየስ [ጂያር] ቀን… “አንድ አስደናቂ እና ሁሉንም ያስገረመ ክስተት ታየ። ይህ ክስተት ታሪኩን ባዩት በነዚያ ሰዎች ህይወትና የእለት ተለት ኑሮ ውስጥ ምንም ተጽዕኖ ባይኖረውና፣ ከዚያም በኋላ ተከትለው የተፈጸሙ ድርጊቶች እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች የሚገባቸው አይነት ትላልቅ ተፈጥሮ ያላቸው ክስተቶች ባይሆኑ ኖሮ፣ እኔ ራሴ ታሪኩ ተረት ይመስላል ብዬ ባሰብሁና በተውኩት ነበር፤ የታየውና የሆነው ግን ይሄ ነው፣ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ሠረገሎችና በላያቸው ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡ የታጠቁ የሰራዊት ጭፍሮች በደመና መካከል ወዲህና ወዲያ እየተሯሯጡ ከተማይቱን ሲከብቧት ታዩአቸው። ከዚህም በላይ በዓለሃምሳ ብለን በምንጠራው በዚያ የበዓል ቀን ካህናቱ በሌሊት እንደ ልማዳቸው ወደ ውስጠኛው የቤተ መቅደሱ ክፍል ገብተው የዘወትሩን አገልግሎታቸውን እይፈጸሙ ሳለ፣ በመጀመሪያ ለራሳቸው የሚታወቅ መሸበርና ፍርሃት ይሰማቸው እንደነበሩ ሲገልጡ፣ በታላቅ ድንጋጤም ውስጥ ሆነው እየተንቀጠቀጡ የሰሙት ታላቅ ድምፅ "ኑ ከዚህ በኋላ ለቅቀን ከዚህ እንሂድ” የሚል እንደ ብዙ ሕዝብ ያለ ድምፅ ሰምተዋል። (Wars, 6-5-3, አንቀጽ 297-299)
ሮማዊው የታሪክ ጸሐፊ ቆርኔሌዎስ ታሲተስም ጭምር፣ እነዚህን አስገራሚ ድርጊቶች በኢየሩሳሌም መከሰታቸውን መዝግቧል (Histories, መጽሐፍ 5, ቁጥር. 13)።
መልዕክቴ፦
ምንም ዝንፍ ሳይል፣ ልክ ኢየሱስ እንደተነበየው፣ እነዚያ መሲሓቸውን “የወጉት" እንኳ ሳይቀሩ፣ ያኔ በ70 ዓ.ም ላይ በኃይል እና በታላቅ ክብር ሲመጣ የተገለጠውን የእርሱን ፓሮውዥያዊ ትዕይንት በሕይወት ቆይተው ተመልክተዋል። ንስሃ ግቡ፣ ይህንን እውነታ ተቀበሉ። በስነመለኮታዊ መተጣጠፍ ይህንን እውነታ ለማስተባበል መሞከር ግን በእግዚአብሔር ቃል ታማኝነት ላይ የሚፈጸም የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ክህደትና ግልሙትና ይሆናል።
ለተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራርያ ፈላጊዎች በብሎገሬ፣ በፌስ ቡክ ገጼ እና በphilologus66 የፌስ ቡክ ገጽ ያጋራሁዋቸውን ጥሁፎቼን ጉብኙ።
gkr
No comments:
Post a Comment