Saturday, May 28, 2022

ጴጥሮስን በጴጥሮስ (የመጻኢነት መከላከያ ሲደረመስ)

                                                                   ጴጥሮስን በጴጥሮስ

(የመጻኢነት መከላከያ ሲደረመስ)

 "እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ አመት ሺህ አመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ" (2ጴጥሮስ 3፥ 8)

ይህች ምንባብ ለበርካታ ጊዜያት የነገረ ፍጻሜ ርዕሰ ጉዳይ ተነስቶ ከአንዳንድ ወገኖች ጋር ስለጌታ ዳግም ምጽአት ውይይት (አንዳንድ ጊዜም ክርክር ይመስላል) ሲጀመር፣ ብዙዎቹ እንደመጨረሻ ጥይት የሚጠቀሙባት ጥቅሳቸው ናት። እነዚህም የመጻኢነት አቋም ያላቸው ወንድሞቼ፣ በአዲስ ኪዳን የሚገኙና የዳግመኛ ምጽዓቱ አመልካች የሆኑ የትንቢት ምንባባት ሁሉ በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ትውልድ ወቅት የሚፈጸሙ እንዳልሆኑ፣ ይልቁንም ገና ያልተፈጸሙ መሆናቸውን  ወይም ገና ወደ ፊት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ለማስረዳት፣  ብዙ ርቀት ሄደው የሚያቀርቡት መከላከያና መከራከርያ እንዳላቸው እየመሰላቸው የሚያነሱት ጥቅስ ነው።

ይህ ጥቅስ ለመጻኢነት አቋም ድጋፍ ነው ተብሎ የሚታስብ እንደሆነ በስፋት ይታወቃል። እኔም እግዚአብሔር ምሕረት ያድርግልኝና ይህንን ጥቅስ እስከ ቅርብ አመታት ድረስ መጻኢያን ወገኖቼ በሚጠቀሙበት መንገድ ጴጥሮስን አጉል እየጠቀስኩ ያለቦታው ስሰነቅረው ኖሬአለሁ። እንዲህ የሚተረጉሙት በርካታ ወዳጆችም አሁንም ድረስ አሉኝ።

 ጴጥሮስ በዚህ ጥቅስ ሊነግረን የሚፈልገው "ዳግምኛ ምጽዓቱ በሺህዎች  ለሚቆጠር አመታት ክፍለ ጊዜ ይዘገያል ማለቱ አይደለም" ብዬ ለያዝኩት አቋም መከላከያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለኝ ወይ? አዎን አለኝ ስል እውነትን እናገራለሁ፣ ራሱን ቅዱስ ጴጥሮስን ዋቢ አድርጌም እመሰክራለሁ። ስለመጨረሻው ቀን የጴጥሮስ ምስክርነትና የራሱ የጴጥሮስ እምነት ስለ ዘመኑ ግልጽ አድርጎ የሚናገረው እውነት በኖረውና እድሜ ጠገብ በሆነው ልማዳዊ አመለካከቴ ላይ እርማት የሰጠኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መገለጥ ነው።  

ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ አምሳ ቀን ባቀረበው ስብከቱ፣ "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ….ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ…." (ሐዋ 2፥ 17-18) ሲል ነብዩ ኢዩኤልን ጠቅሶ መንፈስ ቅዱስ የፈሰሰበትን ያንን ጊዜ የመጨረሻው ቀን ነው ሲል መስክሯል። መልዕክቱንም ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ምዕመናን አንባቢዎቹ ሲጽፍላቸው"ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ" (1ጴጥሮስ 4፥ 7)፣ ሲል መክሯል።

እነዚህ የጴጥሮስ ንግግሮች ግልጽ ያደረጉልኝ አንድ ነገር፣ ሐዋርያው ራሱም ሆነ፣ ወይም የመልዕክቱ አድማጮችና አንባቢዎች ራሳቸውም ቢሆኑ፣ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ላይ መሆናቸውንና የነገር ሁሉ መጨረሻም ቀርቦ እንደነበር ያምኑ የነበረ መሆናቸውን ነው። እነርሱ ከሚያምኑት የተለየውን ማመን ምንፍቅና ይሆናል። እነርሱ ያኔ ከሁለት ሺህ አመታት በፊት በመጨረሻው ቅኖች ውስጥ እንደነበሩ በእውነት ያምኑ ነበር፣ እኛም ዛሬ ከሁለት ሺህ አመታት በኋላ አሁንም በመጨረሻወቹ ቀኖች ውስጥ ነን ያለነው ብለን በስህተት ብናምን ሐዋርያቱ ያላመኑትን አምነን እንስታለን።

ቀጣይ የሆኑት የዚህ የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ምንባብ በርካታ ቁጥሮች በዚሁ ፍሰት ያንኑ ሃሳብ የሚያመለክቱ መሆናቸውንም አስተውያለሁ፦

"ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሳል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፣ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኲሳት ይቀልጣል፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀጥል ከሆነ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኮላችሁ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማያትም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይፈታል፣ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ ወዳጆች ሆይ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፣ የጌታችንም ትዕግስት መዳናችሁ እንደሆነ ቁጠሩ። እንዲሁም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ" (2ጴጥሮስ 3፥ 9-15) 

እንግዲህ ጴጥሮስ ዳግመኛ ምጽዓቱ ከሺህዎች አመታት በኋላ ይፈጸማል ብሎ  የሚያምንም የሚያስተምርም እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ከዚያ ይልቅ ግን ጥቅሱ እግዚአብሔር ጊዜን አስመልክቶ ሰው ከሚያይበት አተያይ በተለየ እንደሚያየው ሐዋርያው ጴጥሮስ ያስተማረበት ሃሳብ ነው። የሆነው ሆኖ ግን ለእግዚአብሔር እንደ ቅጽበት አይን ጊዜ የነበረ ቢሆንም እንኳ፣ ለጴጥሮስ ትውልድ ሰዎች ግን "ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም" የተባለለትን የዳግመኛ ምጽዓቱን ተስፋ ፍጻሜ፣ ረጅም ለሚመስል ጊዜ፣ ማለትም በ70 ዓ.ም ላይ እስከሆነው የኢየሩሳሌም ውድመት ድረስ  ወደ አርባ አመታት ለሚጠጋ ጊዜ መጠበቅ ነበረባቸው። በብሉይና በሐዲስ የተገለጠውን ሙሉውን እና ፍጹሙን የእግዚአብሔርን ምክር ይዘን እንጂ፣ አንዲት ጥቅስ አንጠልጥሎ ወይም በአንዲት ጥቅስ ተንጠልጥሎ ዶክትሪን አይሰራም።  (GKR)


No comments:

Post a Comment