በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የበኩረ ተደራሲያኑ ዋጋ እና አግባብነት
ጌታችንን በማይጠፋ ፍቅር የሚወዱ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስትና ሕይወት የሚናገረውን በማንበብ፣ በማጥናትና በማዳመጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የጥሞና ሰዓታት ያሳልፋሉ። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያለኝ ዓላማ፣ የሚማርና የተከፈተ ልብ ያላቸውና የመጽሓፍ ቅዱስ ተማሪ የሆኑ ክርስቲያን አማኞች እንዲህ ባለ ብርቱ ተግባር ላይ በሚሰማሩበት ጊዜ በተለይ “የበኩረ ተደራሲያኑ ዋጋ እና አግባብነት” የሚለውን ርዕሰ ጉዳይ ለመረዳት እንዲቻላቸው ትኩረት ሰጥተው እንዲያስቡበት መርዳት ነው።
“የበኩረ ተደራሲያኑ ዋጋ እና አግባብነት” ምን ማለት እንደሆነና ፍሬ ነገሩን ለማስረዳት እንዲመቸኝ ከማቴዎስ ወንጌል መጽሐፍ ሃያ አራተኛውን መዕራፍ በወፍ በረር ምልከታ ለመጠቀም መርጫለሁ። በዚህ አንድ ምዕራፍ ላይ በዝርዝር ጽፌ ያስተማርሁበትን ማንበብ ለምትሹ በብሎገሬ ግብታችሁ እንድትካፈሉ በዚህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ ሊንኩን አስቀምጫለሁ።
‘ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ ….አላቸው”፦ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ስለ “በኩረ ተደራሲያኑ ዋጋ እና አግባብነት” የመጀመሪያ ማሳያ ሊሆን የሚችል ግልጽ ነገር ስላለን እዚህ ቆም ማለት አለብን። ልንጠይቀው የሚገባን መሰረታዊ ጥያቄ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው “አላቸው” የተባሉት “እነሱ” እነማን ናቸው? “እነርሱ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው “ደቀ መዛሙርቱን” መሆኑን ከዚህ ምንባብ ክፍል በጣም ግልፅ ነው ብዬ አምናለሁ። በዚህም ኢየሱስ በቀጥታ ይናገር የነበረው የነግግሩ “ተደራሲያን” የነበሩትን - ደቀ መዛሙርቱን ነው።
ካቆምንበት ተነስተን ጥናታችንን ስንቀጥል፣ “ይህን ሁሉ [የቤተመቅደሱን ሕንፃ እያመለከተ] ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።” እዚህ ላይ “ታያላችሁን?” በሚል መጠይቅ የተጠቆሙትን "እናንተ" የተባሉትን እነማን እንደሆኑ መለየት አለብን. “እናንተ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በቁጥር 1 ላይ ግንቦቹን ለማሳየት ወደ ኢየሱስ የቀረቡትን“ደቀ መዛሙርቱን” መሆኑ ግልጽ ነው። በዚህ ምንባቡ ውስጥ ከኢየሱስ ጋር እየተነጋገረ ያለ ሌላ ሰው ወይም ሌላቡድን የለም፣ ስለዚህ እዚህ ላይ ቀደም ሲል እንደነበረው “እናንተ” በማለት የተጠቀሱት “ደቀ መዛሙርቱ” በቻ ናቸው ማለት ነው ብለን መደምደም አለብን።
በመቀጠልም፦ “እውነት እላችኋለሁ [እኔ ኢየሱስ]፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው [ደቀ መዛሙርቱን]።” አሁን ተመልከቱ፣ ያ አይነት ንግግር በእውነት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው አስገራሚና አስደንጋጭ ንግግር ነበር። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ታላቁን ቤተ መቅደስ ያነጹት እነዚያ የሚያማምሩ ዕፁብ ድንቅ ድንጋዮችን አስመልክቶ በዚያ የቆሙት አድማጮቹ ሁሉ ቃሎቹን ሲናገር እያዳመጡና እየተመለከቱት አንዱ በሌላው ላይ ተነባብሮ መፍረሱ እንደማይቀር ነገራቸው። ይህ በእርግጠኝነት የወደፊቱን ክስተት የሚያመለክተውንና “ትንቢት” ተብሎ የሚጠራውን መስፈርት ያሟላል እላለሁ!ይህን ትንቢት የተሰኘ ጉዳይ በአምሮአችሁ ይዛችሁ ተከተሉኝ ምክንያቱም በኋላ ላይ ኢየሱስ ይህ ትንቢት የሚፈጸምበትን ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ በግልጽ እንደነገራቸው እንመለከታለን!
እርሱም [ኢየሱስ] በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ [ኢየሱስ] ቀርበው፦ ንገረን፥ [ደቀ መዛሙርቱ] ይህ [የቤተ መቅደሱ ድንጋዮች መፈራረስ] መቼ ይሆናል? የመምጣትህና [እዚህ ላይ “መምጣት” የሚለው ቃል በመጀመሪያው የግሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ “ፓሮዥያ” (“parousia”) ማለት ሲሆን ትርጉሙም “መምጣት” ወይም “መገኘት” ማለት ነው።] የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን የጠየቁትሁለት ጥያቄዎችን ነበር፦ (1) ቤተ መቅደሱ መቼ ይፈርሳል? የሚል እና (2) “በዘመኑ” [እዚህ ላይ ልብ አደርጉ፣ የአማርኛ መጽሓፍ ቅዱስ ትርጉሞች እና አንዳንድ ታዋቂ የእንግሊዝኛ ትርጉም መጽሓፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንዳሰፈሩት ያለ ”አለም” የሚል ቃል ተገቢ አይደለም] መጨረሻ ላይ የሚፈጸመው የኢየሱስ ፓሮዥያ ምልክቱ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉ ናቸው። እዚህ ላይ ኢየሱስ (1) በኢየሩሳሌም ያለው ቤተ መቅደስ መቼ ይፈርሳል? ለሚለው እና (2) “የዘመኑ ፍጻሜ” ተብሎ በሚጠራው ጊዜ ላይ የሚገለጠው የኢየሱስ ፓሮዥያ ምልክቱ ምን ሊሆን ይችላል? በሚል ደቀ መዛሙርቱ ላቀረቡለት ሁለት ጥያቄዎች ሙሉ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ልብ ማለት አለብን። በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ ለኢየሱስ ባነሱለት ጥያቄ ላይ እየተናገሩ ያሉት ስለ የትኛው “ዘመን” እንደሆነ መመርመር ያስፈልገናል።
“ኢየሱስም መልሶ [ለደቀ መዛሙርቱ] እንዲህ አላቸው፦ ማንም [እናንተን] እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ [እናንተ] አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ [እናንተ]፥ አትደንግጡ [ማለትም፣ በእነዚህ ኢየሱስ በሚናገራቸው ነገሮች]፤ ዳሩ ግን መጨረሻው [ማለትም፣ ደቀ መዛሙርቱ ቀደም ሲል በጥያቄአቸው ጠቆም ያደረጉት“የዘመኑ ፍጻሜ”ወይም መጨረሻው ማለት ነው] ገና ነው” በእነዚህ የቅዱሳት መጻሕፍት ቃላት ውስጥ እያደገ የመጣውን ሃሳብ እየከለስን እና እያስታወስን ጥናታችንን እነቀጥል። ኢየሱስ እስካሁን ድረስ ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጣቸው:- (1) ማንም እንዳያስታቸው መጠንቀቅ እንደ አለባቸው፣ (2) ሌሎች ደግሞ እርሱ ክርስቶስ መሲሑ እኔ ነኝ እያሉ በጊዜው ውስጥ የሚገለጡ እንደሆነ እና እነርሱ ግን አታላዮች መሆናቸውንና ብዙዎችም እነዚህን አታላዮች እነደሚያምኑዋቸው፣ በተጨማሪም (3) ደቀ መዛሙርቱ ጦርነትንና የጦርነትን ወሬ እንደሚሰሙ፣ ሆኖም ግን ደቀ መዛሙርቱ የዘመኑ መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት ሊፈጸሙ በሚገባቸው በነዚህ ጉዳዮች ሊደናገጡ እንደማይገባ ይነግራቸዋል።
“ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።”.በዚህ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 የንባብ ክፍል ውስጥ፣ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ከመፍረሱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ የሚያዩአቸውን አንዳንድ “ምልክቶች” (1) ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ የሚነሣ እንደሆነ፤ እንዲሁም (2) ራብ፣ ቸነፈርና የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ እነሚሆን ጨምሮ ተናግሯል። እነዚህ ምልክቶች የሚከናወኑት ቤተ መቅደሱ ከመፍረሱ አስቀድሞ እና የእርሱ ፓሮዢያ ከመከሰቱ በፊት ነው ለማለት እችላለሁ፣ ምክንያቱም እነዚህን ክስተቶች ከ"ምጥ ጣር" ሁነታ ጋር በማመሳሰላቸው ነው፣ ይህም አንዲት ሴት አዲስ ልጅ ከመገላገሏ በፊት የሚያጋጠማትን ህመም በግልፅ የሚያመለክት በመሆኑ ነው። ሁለት ሺህ አመት የሚፈጅ ምጥ የለም።
በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል [እናንተን] (እዚህ ላይ “እነሱ” የተባሉት ገዳዮች ማንን እነደሚያመለክት አልተገለጸም፣ ነገር ግን በመላው አዲስ ኪዳን ይህንን አሳልፎ የመስጠትና የመግደል ተግባር በደቀ መዛሙርት ላይ ሲፈጽሙ የነበሩትን የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎችን እንደሚያመለክት አምናለሁ።)፥ ይገድሉአችሁማል [እናንተን] (ኢየሱስ እየተነገራቸው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት ሞት ተጠያቂ የሚሆኑት እነማን እንደሆኑ ከዚህ ቋንቋ መረዳት እንችላለን) ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ [እናንተ] ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም (ይህ ሁሉ በደቀ መዛሙርቱ ላይ በሚደርስበት ጊዜ) ብዙዎች ይሰናከላሉ (ይህም ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ሲያስተምር ከነበረው ነገር ሊሆን ይችላል።) እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና (ይህም ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት የተናገረውን በማመን የሚቀጥሉ ናቸው።) ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል (ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት የሰበከው እና ለደቀመዛሙርቱ ያስተላለፈው መልእክት ነው) በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል። በዚህ የንባብ ክፍል የምንመለከተውይህ የመጨረሻ ንግግሩ በእጅጉ ጊዜን አመልካች የሆነ ንግግር ነው።. ኢየሱስ አሁን ለደቀ መዛሙርቱ እየነገራቸው ያለው የንግግሩ ርዕሰ ጉዳይ የሆነው መጨረሻው የተባለው ይህ የዘመኑ ፍጻሜ ከቤተ መቅደሱ መፈራረስና ከክርስቶስ የፓሮዥያ ምጽአት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የመንግሥቱ ወንጌል ለህዝቦች ሁሉ “በዓለም ሁሉ” እስኪሰበክና እስኪዳረስ ድረስ ሳይፈጸም የሚጠብቅ እንደሆነ ተናግሯል።
“እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል ዳናኤል. 9፥ 27፤ 12፥ 11 ላይ፣ የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ [እናንተ]፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት (በዚህ አይነተኛ በሆነ ጉልህ ክስተት ወቅት) ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያችም ወራት (ማለትም የጥፋት ርኩሰት በሚፈጸምበት ወቅት) ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።” በእነዚህ ንግግሮች፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ጥብቅ የሆነ ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያን እየሰጣቸው መሆኑን እንመለከታለን፣ ይህም መልእክት በዚያን ጊዜ ለነበሩ አማኞችና ኢየሱስ ከሞተ እና ከተነሳ በኋላም ወደቤተክርስቲያን ለተጨመሩ ሌሎች አማኞች ሁሉ እንደተሰራጨ በቀላሉ መገመትም እንችላለን። “ነገር ግን ሽሽታችሁ (የእናንተ፣ እነዚህን ምልክቶች አይታችሁ ከተማይቱን ለቃችሁ የምትሄዱ) በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ (የጥፋት ርኩሰት በሚታይበት ጊዜ) ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ [እናንተን] አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ [ለእናንተ]። እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ [እናንተን] ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ (ሐሰተኞቹ ክርስቶሶችና ሐሰተኞቹ ነቢያት)፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ (ለመሲሁ ከርስቶስ የተሰጠ መጠሪያ) መምጣት (እዚህ ላይ እንደገና ጥቅም ላይ የዋለው የግሪክ ቃል እንደ ቀድሞው “ፓሮውዥያ” የተሰኘው ነው፣ ትርጉሙም “መገኘት” ማለት ነው።) እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ (መሲሁ ክርስቶስ) ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም (ክርስቶስን) በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል (የክርስቶስ ፓሮውዥያ የሚከሰተው በዚህ ከተጠቀሰው የመከራ ወራት በኋላ መሆኑን ልብ አድርጉ)፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።” ወይኔ! ይህ የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር ቦምብ የሆነ ንግግር አይደለም ትላላችሁ! እስቲ ጠጋ ብለን በዝርዝር እንመልከተው።
"እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።" (ማቴዎስ 24፥ 33-34)።
በርካታ ክርስቲያኖች ዛሬ ላይ ቆመው ይህንን የጌታን ንግግር ለመተርጎም ሲሞክሩ ከጠቅላላ ቃሉ ከተነገረበት አውድ ነጥለው፣ ልክ ጌታ ዛሬ ከበርካታ መቶ አመታት በኋላ የመምጣቱ ምልክት ምን እንደሆነና በእኛው ትውልድ ውስጥ ሊሆን ያለውን ለእኛው የነገረን እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይህ ግን ቃሉን አሳስቶ ከማንበብ የተወለደና ዘመን ያስቆጠረ ድልብ ስህተት ነው፤ እርማት ይፈልጋል። ስለሆነም ወቅታዊውን የአለምን ፓለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ፣ በተለይም እንደ እስራኤልና አረቦች ያሉ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችን ውጥረት፣ እንደ አሜሪካና አውሮፓውያን ሸሪኮቿ ያሉ የኃያላን መንግስታትን የውጭ ፓሊሲ፣ እንደ ሩስያና ቻይና ያሉ ከምዕራባውያን በተቃራኒው የቆሙ ኃይሎችንና፣ ትንንሽዬ የኒውክለር ጡንቻ እያበቀሉ ያሉ እንደ ኢራንና ሰሜን ኮርያ ያሉ መንግስታትን ሁኔታ የሚዘግብ ትኩስ የአለም ዜና እያነፈነፉ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት በአለም ወሬ እየመተሩ ለመተርጎም የሚደረግ "የስነመለኮት አዋቂ ነን" ባዮች ሙከራ ሁሉ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት አውደ ምንባብና የአውደ ተደራስያኑን ዋጋ ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን ከንቱና የማይረባ ሆኖ በክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለበርካታ የስህተት ትምህርትና የስህተት እምነት መፈልፈያ ሰበብ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ አውደምንባብ እና የበኩረ ተደራስያኑ ተዛማጅነት ዋጋ ባለው ሁኔታ በቁሙ የሚወሰድ ከሆነ ግን፣ ያኔ በትንቢት ቃል ምንባብ ላይ ግልጽ እና ቀጥተኛ የሆነ ትርጉም ሊኖረን ይጀምራል። ከተሳሳተ መረዳትና እምነትም እንጠበቃለን። ፍጻሜውንም በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ውስጥ በማስተዋል የመጽናናትን ብዛት፣ የእምነትን ጽናትና የክርስቶስ ታማኝ ምስክርነት የሚሰጠውን ድልና ድፍረት ያለማምደናል። ስለዚህ በዋቢነት ያነሳነው የክርስቶስ ፍካሬ የሆነው ማቴዎስ 24 ምጽአቱ ከመሆኑና ፍጻሜ ከመሆኑ አስቀድሞ በደቀመዛሙርቱ ዘመንና ትውልድ ውስጥ የሚከናወነውን ቀዳሚ ክስተት በዝርዝር ይናገራል
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ይህ ሁሉ” ሲል ያነሳቸው“እነዚህ ሁሉ ነገሮች” እስካልሆኑ ድረስ ትውልዳቸው እንደማያልፍ [ሞተው እንደማያልቁ] ነግሯቸዋል።
“ይህ ሁሉ” ወይም “እነዚህ ነገሮች” በሚል ይደርሳሉ የተባሉት ጉዳዮች ምን ምን ናቸው? አውዱ የግድ እንደሚለው የሚከተሉትን ነገሮች ማካተት አለበት፡-
(ሀ) የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ይፈርሳል።
(ለ) የ“ዘመኑ” መጨረሻ ይሆናል።
(ሐ) ደቀ መዛሙርቱ በዘመናቸው ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት መነሳታቸውን ወይም መገለጣቸውን ይመሰክራሉ።
(መ) በዚያን ጊዜ ጦርነቶች እና የጦርነት ወሬዎች ይኖራሉ
(ሠ) ረሃብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል።
(ረ).የመከራ ጊዜ ይኖራል።
(ሰ) ቢያንስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዳንዶቹ 'ይገደላሉ'።
(ሸ) የመንግሥቱ ወንጌል በመላው አለም ለሁሉም ህዝቦች ይሰበካል።
(ቀ) በዳንኤል ትንቢት የተናገረው “የጥፋት ርኩሰት” ይፈጸማል
(በ) ከይሁዳ ከተሞች ወጥተው “ወደ ተራሮች የሚሸሹ የአማኞች ዘጸአት ይኖራል።
(ተ) የክርስቶስ “ፓሮውዥያ” ወይም “መገኘት” /ማለትም “መገለጥ” (ይህም አንዳንድ ክርስቲያኖች “ዳግመኛ ምጽአት” ብለው የሚጠሩት የተባረከው ተስፋ ይፈጸማል።
እነዚሀ ሁሉ ሁኔታዎችና ክንውኖች ተፈጻሚ የሚሆኑት እርሱ ቆሞ ሲናገር በዚያን ጊዜ ይሰሙት የነበሩ ሰዎች ትውልዳቸው ሳያልፍ በገዛ ዘመናቸው እንደሆነ ኢየሱስ ይናገራል። ኢየሱስ ንግግሩን ሲቀጥል፣ በዚያው በጠያቂዎቹ ትውልድና ዘመን ውስጥ ከምጽአቱ አስቀድሞ ስለሚሆኑ ጉዳዮች፣ ምልክቶችና ኹነቶች ከላይ ከ ሀ እስከ ተ በዝርዝር ያየነውን ይነግራቸዋል። በግልጽም የነገራቸው አንድ ጉዳይ እነርሱ እነዚህ ነገሮች ሲሆኑ እንደሚያዩና፣ በዚህም ሲሆኑ በሚያዩዋቸው ምልክቶች አማካኝነት መምጣቱ የቀረበ መሆኑን የሚያውቁ እንደሆነ ነው። ይህንን የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል በጥንቃቄ የሚያጠኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቢያንስ ከሚከተሉት መደምደሚያዎች ወደ አንዱ የደርሳሉ፦
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረውን በመናገሩ ተሳስቷል።
ኢየሱስ እነዚህን መግለጫዎች በመስጠት ሆን ብሎ ደቀ መዛሙርቱን አሳስቷቸዋል።
በዚህ ክፍል ውስጥ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ሁሉ እውነት እና ትክክለኛ ነገር ነበር፣ ኢየሱስ በተናገረው መሰረትም ተፈጽሟል
ከላይ በተራ ቁጥር 1 ወይም 2 ላይ የተቀመጠው ትክክለኛው አቋም ነው ብሎ የሚደምደም አንባቢ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚናገሯቸውን ነገሮች በሙሉ የማይታመኑ አድርጎ በጥርጣሬ ውስጥ ማስቀመጥ ስለሚኖርበት የክርስትና እምነቱን ወደ ኋላ ጥሎ ለመተው የተመደበ ሊሆን ይችላል። ተራ ቁጥር1 ወይም 2 ላይ የሰፈረው ድምዳሜ እውነት ነው ብለህ ካመንክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተሰጠው ትመህርት የትኛው እውነት ነው፣ ስህተትም የለበትም ብለህ ልታምን ትችላለህ? በማቴዎስ 24 ኢየሱስ ስለመመለሱ የሰጠው ትንቢት ላይ ማስተባበያ እያቀረብክና ማመን እየተቸገርክ ራሱ ኢየሱስ በዮሓንስ 3 16 ላይ ስለ ድነት እና ስለ ዘላለም ሕይወት የሰጠውን ተስፋስ እንዴት ማመን ይቻልሃል?
ጌታን እየወደድን በክርስቶስ ፍቅር ውስጥ ለምንኖር ሰዎች በተራ ቁጥር 3 ላይ ያለው መደምደሚያ እውነትና ተክክል የሆነ ብቸኛው ምርጫን ነው። ነገር ግን፣ እምነታችንን እና መረዳታችንን ቅዱሳት መጻህፍት ከሚያስተምሩት ጋር ለማስታረቅና ለማስማማት በብዙ የአስተምህሮና የአመለካከት አቋሞቻችን ላይ ተገቢውን እርማት እያደረግን ልማዳዊ እምነቶቻችንን መቀየርና ማረቅ ይጠበቅብናል። ይህ ደግሞ ጌታ ለራራላቸው ለአንዳንድ ክርስቲያኖች ብቻ ቀላል ነው፣ ልማድ ላነቃቸው ለሚበዙት ግን በእውነት ከባድ ነው።
እስካሁን ሳወራው በነበረው መሰረት እያንዳንዱ የመጽሓፍ ቅዱስ አማኝና ተማሪ የሆነ ክርስቲያን ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ሲቀርብ “የበኩረ ተደራሲያኑን ዋጋ እና አግባብነት” መረዳት አለበት ብዬ በጥብቅ የማምንበትን ምክንያት የተረዳችሁ ይመስለኛል። አንዳንድ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች በቀጥታ ለተወሰኑ ሰዎች የተጻፉ ናቸው፤ በመሆኑም እውነትን በሚያከብር እምነትና፣ ተአማኒነቱን ለጥያቄና ለጥርጣሬ በማያጋልጥ ዝግጅት፣ ለሚጠይቁንም ሁሉ መልስ ለመስጠት በምንችልበት አቋም ተጠንቅቀን የቃሉን ትምህርት አክብረን ልንይዘው ይገባናል። አውደ ምንባቡን እና የበኩረ ተደራሲያኑን ዋጋና አግባብነት እየደፈጠጥን ያቆምነውን የመጻኢነት አስተምሀሮ በጊዜ አርመን አግባብነት ወዳለውና ወደ ትክከለኛው ትምህርት ካልተመለስን የምንከተለውና የምንጮህለት ነገረ ፍጻሜ መልሶ እኛው ላይ ይጮህብናል፣ መዘዙንም የሚችለው የለም። መጽሐፍ ቅዱስ በሰነድነቱ በየትኛውም ዘመን ላሉ ለሁሉም ሰዎች የሚሆን መልእክት፣ ትምህርት፣ ተግሳጽ፣ ምክር እና ማጽናናት ያለው የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ነው፣ ዳሩ ግን በየትኛውም ዘመን ላሉ ለሁሉም አይነት ሰዎች በቀጥታ የተጻፈና በአድራሻቸው የተላከ ግን አይደለም፤ የራሱ የሆኑ ታሪክ የሚያውቃቸው ቀጥተኛ ተደራስያን አሉት። እኛ እነርሱን አይደለንም፤ አጠቃላዩን መርህ ተከትለን እንዴት ባለ እምነትና መታዘዝ እንደኖሩ ምሳሌነታቸውን እንማርበታለን እንጂ እነርሱ በትውልዳቸው የኖሩበት አውድና የእኛ አውድ ፈጽሞ ልዩነት አለው። የቅዱሳት መጻህፍት ቃላት ለተወሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች የተነገሩ ናቸው፣ እኛ ግን ዛሬ አንድን የቅዱሳን መጻሕፍት የንባብ ክፍል ወስደን ከራሳችን ጋር በማዛመድ ትምህርቱን ለማግኘት ጥበብን መጠቀም አለብን። የትኛውንም የቅዱሳት መጻህፍት ምንባብ በአግባቡ ተርጉሞ ለመረዳት ዋናና አስፈላጊ የሆነ አንድ ጉዳይ ቢኖር የምንባባቱን አውድ ማወቅ ነው። ይህም በአይነቱ የጽሁፉ በኩረ ተደራስያን የነበሩበት አጠቃላይ አውድ ማለት ነው። በዋናነትም ምንባቡ አስቀድሞ የተጻፈው ለነማን ነው የሚለውን ማወቅን ያካትታል። ከዚህ በተለየ አብዛኛውን ጊዜ ቅዱሳት መጻህፍትን በትክክል ያለመረዳት ችግር የሚከሰተው አንባቢው ምንባባቱን ለግሉ ወይም ለግሏ እንደተጻፈ አድርገው ሲወስዱ ነው። በመሰረታዊነት አዲስ ኪዳን በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጸሐፍያን የተጻፈው ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ሲሆን የተጻፈውም የመጀመሪያውን ክፍለ ዘመን ኹነቶች ለመነጋገር ነው።
በማቴዎስ 24 ላይ ያቀረብሁትን ጽሁፍና የቪድዮ ትምህርት እንዲሁም “ትንቢትን ለመተርጎም የአውደ ተደራሲያን ፋይዳ ለፕሪቴሪዝም” የተሰኘውን ጽሁፍ እንድትመለከቷቸው ጋበዝኳችሁ፦
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/24.html
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_60.html
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_33.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_91.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_95.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_32.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_93.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_43.html
https://www.blogger.com/blog/post/edit/6922722142324655915/8904540573557567607
gkr
.
No comments:
Post a Comment