የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውድመት
"እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።….እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።"(ማቴዎስ 24፥ 2፣ 34)
በእኔ አስተሳሰብ ይህን ከላይ የጠቀስኩት የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል ፍቺው እና ታሪካዊ ፍጻሜው በአማኙ መንፈሳዊ ሕይወትና መረዳት ውስጥ ቦታ ሊያገኝ የሚገባውን ያህል ትኩረት የተነፈገው ቃል ነው። ነገር ግን ዓይንን በብዙ ሊከፍቱ ከሚቻላቸው ትንቢቶች መካከል አንዱና ዋናው ደግሞ ነው። ይህንን ጥቅስ በአግባቡ መረዳት ከቻልን ግን ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ጠለቅ ያለ የመረዳትን መንገድ የሚከፍትልን ከመሆኑም በላይ፣ እግዚአብሔርን በማወቅ ከቃሉ ጋር ያለንን ግንኙነት ይወስናል። በታሪክ ውስጥ ፍጻሜው የተረጋገጠውን የዚህን ቤተመቅደስ ውድመት በአዲስ ኪዳን ትንቢቶች ትርጓሜ ውስጥ ያለውን ፋይዳ አለማወቅና ቸል ማለትን የመሰለ ድንቁርና /ignorance/ ያለ አይመስለኝም።
ኢየሱስ ከላይ የተጠቀሰውን ይህንን ቃል በተናገረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ በአድናቆት ይመለከቱትና ያሳዩት የነበረው ያ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆሞ የነበረው ቤተ መቅደስ በዚያን ዘመን በዓለም ላይ ከነበሩ ታላላቅና ድንቃ ድንቅ ቅርሶች አንዱና ዋናው ነበር። ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ “ትውልድ” ወቅት “ይወድቃሉ” ሲል የተናገራቸው ቤተመቅደሱ የታነጹባቸው ድንጋዮች በእጅጉ አስገራሚና እና በይዘታቸው ግዙፍ ነበሩ። የፍርስራሹ የአይን ምስክር የሆነው ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንደዘገበው፣ የአንዱ ድንጋይ ወርዱና ስፋቱ አርባ ስድስት ጫማ በአሥራ አምስት ጫማ በሃያ ሁለት ጫማ የሚለካ ሲሆን ክብደታቸውም እያንዳንዳቸው አራት መቶ አሥራ አምስት ቶን የሚመዝኑ ነበሩ። (ጆሴፈስ፣ 'የአይሁድ ጥንታዊ ነገሮች'፣ሲል በጻፈው መጽሐፍ 15፣ ምዕራፍ 11፣ አንቀጽ 3፣ መስመር ቁጥር 392 ላይ ይህንን ዘግቦታል) ይህ በእርግጥ በኢየሱስ የተነገረ ታላቅ የትንቢት ቃል ሲሆን፣ ደቀ መዛሙርቱም ሲሰሙት ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነባቸው ከባድ ቃል መሆኑን እናስተውላለን። ስለሆነም፣ “ይህ መቼ ይሆናል…” (ማቴዎስ 24፥ 3) ብለው ኢየሱስን ከመጠየቅ መከልከል አልቻሉም። ይህ ቤተ መቅደስ እንዴት እና መቼ ነው ወደ ፍርስራሽና ባድማነት የተቀየረው?
የናዝሬቱ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን በፈጸመበት ጊዜ (ማለትም 30ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ)፣ ያኔ ሮም የዓለም ልዕለ ኃያል መንግሥት ነበረች። ይሁዳ፣ በዚህ ጊዜ የምትመራው በሮማውያን ቅኝ ገዢዎች ነበር፤ ከገዢዎቿም የሚበዙት ስለ አይሁድ ሃይማኖት የነበራቸው እውቀት እምብዛም ሲሆን ወይም ከነጭራሹ ምንም አያውቁም ነበር፤ ይህም ሁኔታ በአይሁዶች ላይ የማያቋርጥ ብስጭት እና ቁጭት አስከትሏል። በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥም ቀነናውያን በመባል የሚታወቀው ቡድን የሮማውያንን አገዛዝ ለማብቃት በዚህ ጊዜ ንቁ ተሳትፎ ያደርግ ነበር። ቀነናውያንም የቤተ መቅደሱን ካህናት ለንጉሠ ነገሥቱ እና ለመንግሥቱ በየጊዜው የሚገባውን ግብር እና ቀረጥ እንዲያቆሙ አግባብተዋቸውና አሳምነዋቸው ነበር፤ ይህም በመሠረቱ በሮም አገዛዝ ላይ የተደረገ አመጽ ነበር።
ሮም በኢየሩሳሌም የተቀሰቀሰውን አመፅ በሰማች ጊዜ ዓመፁን ለማጥፋት በሴስቲየስ ጋሉስ ትእዛዝ የሚመራውን የሮማን ጦር በ66 ዓም ላከች። ኢየሩሳሌምን ዙሪያዋን ከከበቧት በኋላ የከተማይቱን በሮች መዝጋት ጀመሩ፣ ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ ከበባ በኋላ፣ ያለ ምንም አሳማኝ ምክንያት ጀነራል ሴስቲየስ ወታደሮቹን በኃይል ከያዙት ይዞታ አስወጥቶ አፈግፍጎ ሄደ። ያኔም አይሁዶች ሮማውያንን አሳደዱ፣ ብዙዎችንም ገድለው በየጦሩ ግንባርና በከተማይቱ ቅጥር ዙሪያ የተተዉ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ማረኩ። ይህ ሮማውያንን ያዋረደ ክስተት አይሁዶች ስለራሳቸው የማይሸነፉ የሆኑ ያህል የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጎ በአመጻቸው እንዲቀጥሉ የልብ ልብ እንዲሰጣቸው አድርጓል። በተጨማሪም ይህ ክስተት፣ ያኔ በቅርቡ ድንገት በእነርሱ ላይ ከሚመጣው የጌታ ቀን ጥፋት በፊት “… ሰላምና ደኅንነት…” አገኘን፣ የሚሉበትን ድባብ ለመፍጠር ረድቷል (በተጨማሪ 1 ተሰሎንቄ 5፥ 3ን ተመልከት።)
ሮም በአይሁዳውያን መሸነፏን የሚገልጸው ዜና ወደ ንጉሠ ነገሥቱ በደረሰ ጊዜ ሴስቲየስ ባደረገው ደካማ አፈጻጸም ኔሮ ተበሳጨ። በምላሹ የአይሁድን አመጽ ለመደምሰስ እና የሮምን ውርደት ለመበቀል እንዲሁም በአገዛዝ ክብሯ ላይ የደረሰውን የሞራል ጉዳት ለመበቀል እንደገና በ67 ዓ.ም ላይ ኔሮ አንጋፋውን ጄኔራል ቬስፓሲያንን ወደ ኢየሩሳሌም ላከው። ቬስፓሲያንም ወራሪውን ጦር እየመራ ይዞታውን በማስፋት ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ወደምትገኘው ወደ ገሊላ ገሰገሰ። የእስራኤልን ታላላቅ ከተሞቿንም በውጊያ አሸንፎ ምድሪቱን አንበረከከ። በሰሜን በኩል ካለው የገሊላ ዘመቻ በኋላ ወደ ደቡብ ዘምቶ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ሰፈረ፣ ነገር ግን በዘመቻው ላይ ሆኖ ለሌላ ማጥቃት እየተዘጋጀ ሳለ ስለ ኔሮ ሞት ወሬ በሰማ ጊዜ ጀነራል ቬስፓሲያን ኢየሩሳሌምን ለመያዝ የነበረውን እቅድ ትቶና ወታደሮቹን አስወጥቶ ወደ አገሩ ወደ ሮም በመመለስ ተተኪው ንጉሠ ነገሥት ሆነ። አሁንም አይሁድ በጦርነቱ ያሸነፉና ድል የቀናቸው መስሎ ታያቸው።
ከዚያም በኋላ ብዙም ሳይቆይ በሚያዝያ ወር 70 ዓ.ም. ከፋሲካ በአል በፊት የቬስፓሲያን ልጅ የሆነው ጀነራል ቲቶ በሰሜናዊ ዳርቻ ካሉት ጭፍሮቹ ጋር ጣምራ ጦር በመሆን የአይሁድን አመጽ ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም እና አመፁን ለመደምሰስ ገስግሶ ኢየሩሳሌም ደረሰ። ጦሩም በገሊላ በኩል አድርጎ ወደ ደቡብ በመዝመት ከተማዋን በቅርብ ርቀት ለማየትና ለመቆጣጠር በሚያስችሉት ሦስት የጦር ካምፖች ላይ ሰፈረ። መጀመሪያ ላይ አይሁዳውያን እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ለማሳመንና ከተማይቱን ከመፍረስ ጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ የማግባባት ጥረት ተደረገ፤ ይህ ግን አይሁድ አስቀድሞ በነበራቸው የተሳሳተ የአሸናፊነት ስሜት የተነሳ አሁንም እንደቀድሞው ድል የሚቀናቸው ስለ መሰላቸው በቀረበላቸው የሰላም ጥሪ ላይ እየተሳለቁ ጥረቱ ሳይሳካ ቀረ።
ቲቶ ግን አይሁዳውያን እርዳታ እንዳይቀርብላቸው አድርጎ የከተማዋን ደጆች ዘግቶ በማስጨነቅ የመጨረሻውን ከበባ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ማናቸውም ሰው ቢሆን ከከተማይቱ ሸሽቶ ለመውጣት ሙከራ እንዳያደረግ ተከልክሏል፣ የሞከሩትም በከተማው ውስጥ ባሉ የአይሁድ አንጃዎች ተገድለዋል። አልያም ከከተማ ሲወጡ በሮማውያን ተይዘው ሁሉም ለመቀጣጫ እንዲያያቸው በከተማይቱ ቅጥር ላይ ተሰቅለው ተሰቃይተው እንዲምቱ ተደርጓል። ኢየሱስ በሉቃስ 19፥ 43፣ 44 ላይ "ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።" ሲል እንደተናገረው የሮም ጦር ለከበባው እንዲመቸው በከተማይቱ ዙርያ የሚቆም ቅጥር ወይም ግንብ አደረጉ።
የቲቶ ወታደሮች በግንቦት 25 የኢየሩሳሌምን ሦስተኛውን (ውጨኛውን) ቅጥር ጥሰው በመግባት አዲሱን የከተማውን ክፍል ያዙ። በሰኔ ወር ከበባው ወደ ሁለተኛው ቅጥር አካባቢ ተስፋፍቶ አይሁድ ከተማዋን ከጠበቀው የመጨረሻው ግድግዳ ጀርባ አፈግፍገው ሸሹ። የአንቶኒያ ምሽግም ሐምሌ 22 ቀን በቲቶ ተወሰደ፤ ከዚያም ሮማውያን የቤተ መቅደሱን በሮች በእሳት አቃጠሉ። ከቲቶ ፍላጎት በተቃራኒው በጥቃቱ ወቅት አንድ ወታደር በመስኮቱ አሳልፎ ወደ አንዱ የቤተ መቅደሱ ክፍል ውስጥ የእሳት ፍንጣቂ ወርውሮ አስገባ፣ በመቀጠልም ሁለተኛው የእሳት ቃጠሎ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ተወረወረ፣ ይህም የመቅደሱን ውስጠኛ ክፍል በእሳት እንዲያያዝ አደረገ።
ፍላቪዬስ ጆሴፈስ ስለ አይሁድ ጦርነቶች በሚተርከው መጽሐፉ ይህን ጉዳይ ሲያብራራ፣ ሮማዊው ጀነራል ቲቶ ቤተ መቅደሱ ከጥፋት እንዲተርፍ ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር ይተርካል፡፡ ቲቶ ቤተ መቅደሱ እጅግ የሚያምር ሕንጻ ከመሆኑ የተነሳ እንዳይፈርስ ፍላጎት ነበረው፡፡ ለሮም መንግስት ክብር እንደ ሮማውያን የስኬት መገለጫ አድርጎ ሊጠብቀውም ተመኝቶት ነበር፡፡ ቤተ መቅደሱን በተመለከተ የእርሱ ትዕዛዝ አንዳች ጉዳት እንዳይደርስበትም ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ከቲቶ ወታደሮች አንዱ ከቤተ መቅደሱ መስኮቶች በአንዱ ወርውሮ ያስገባው የእሳት ድንጋይ የዚያን ቅዱስ ሥፍራ መሠረት በእሳት አያያዘው፡፡ ቲቶ ነገሩን በሰማ ጊዜ በታላቅ ድንጋጤ ተነስቶ … ወደ ቅዱሱ ቤት ሮጦ በመሄድ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም ሞክሮ ነበር፡፡ በከፍተኛ ድምጽ፣ እየጮኸ፣ ለወታደሮቹም በቀኝ እጁ ምልክት እየሰጠ እሳቱን እንዲያጠፉ ወታደራዊ የአለቃ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍም ነበር፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ እነዚያ የአለቃቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም በአግባቡ የሰለጠኑና ሥነ- ሥርዓት የተማሩ የሮማውያን ወታደሮች ልክ አውሬ የሆኑ ያህል እንደ እብድ ሰው ተለውጠው የቄሳርን ትዕዛዝ እንዳልሰሙ ያህል በመሆን አሁንም አሁንም እየጨመረ ከሚሄድ ታላቅ የበቀል መነሳሳት ጋር እሳቱን እየጨመሩ ያቀጣጥሉት ያዙ፡፡
ይሄ ታሪክ ባስብኩት ጊዜ ሁሉ ሲያስገርመኝ ይኖራል! ታላቁ ሮማዊ የጦር ጀኔራል እና በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራዊቱ ቤተ መቅደሱን ሊያድኑት ከቶ አልቻሉም፡፡ ለምን ይህ ሆነ ቢባል ምክንያቱም ከቲቶ የሚበልጠው፣ ከቄሳርም የሚበልጠው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ከመሆኑ ከዓርባ ዓመታት በፊት ቀደም ብሎ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” (ማቴ 24÷ 3) ሲል ተናግሮአልና ነው፡፡ እግዚአብሔር ተናግሮአል፣ ጀነራል ቲቶም ትዕዛዙን ይከተላል እንጂ ምንም ሊያደርግ ስለማይችል ያ ቤተ መቅደስ ተቃጥሏል፡፡ ይህ እንግዲህ ድል ለመንሳት የተመመው የሮም ሠራዊት ኃይልና ጀግንነት ሳይሆን፣ በሕዝቡ ላይ የሚፈርደው የእግዚአብሔር ኃይል ነበር፡፡ በጆሳቨስ የታሪክ ዘገባ የሚከተለውን እናነባለን፡- “ቲቶ ወደ ከተማይቱ በገባ ጊዜ (መስከረም 26 ቀን 70 ዓ.ም ማለት ነው) የከተማይቱን ጥንካሬ በተለይ ከፍ ብለው የተሰሩትን ቅጠሮቿን እየተመለከተ ይገረም ነበር፡፡ እነዚያ ግንቦች ምን ያህል ረጃጅሞችና ጠንካሮች መሆናቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ የእያንዳንዱንም ግንብ ውፍረት እያየ ´´በእርግጥ አይሁድን ከነዚህ ጠንካራ ምሽጎች አውጥቶ ያዋረዳቸው እግዚአብሔር በጦርነቱ ከእኛ ጋር ነበር እንጂ፣ ምን ዓይነት እጅ ወይስ ማሽን ይህንን ግንብ ሊያፈርሰው ይችል ነበር? “ እያለ ይደነቅ ነበር” ይለናል፡፡ በተጨማሪም ወደ 6,000 የሚጠጉ በዚያ ጠለላ ፈልገው የነበሩ ሰዎች ያኔ በቃጠሎው ነደው አልቀዋል። በመስከረም 26፣ 70 ዓ.ም በከተማው ውስጥ የተቀጣጠለው የአይሁድ ተቃውሞ ሁሉ በኃይል ተቋረጠ። እንደዚህ አይነት ዝርዝር ጉዳዮችን ማንበብ ለሚፈልጉ፣ "የጆሴፈስ ስራዎች፣ የአይሁድ ጦርነት የተሰኘው ጥራዝ፣ መጽሐፍ 6 አስገራሚ ትረካን ያቀርባል።
እንደ ጆሴፈስ ገለጻ ከሆነ በከተማይቱ ላይ በተፈፀመው ጥቃት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን አይሁድ ሲገደሉ 97,000 ሰዎች ተማርከው ለባርነት በግዞት ተወስደዋል። ከእነርሱም መካከል አያሌዎቹ በአረማውያን የጣዖት ክብረ በአል ላይ፣ እንዲሁ ለነገስታቱና ለጦር አዛዦች ክብር በአሰቃቂ አገዳደል መስዋዕት ሆነው ታርደዋል። አይሁድ በገዛ አገራቹውና ተበትነው በነበሩበት የአህዛብ ምድር፣ በደረሱበት ሁሉ ተጨፍጭፈዋል። የቀሩትንም ባሪያዎችና ግዞተኞች አድርገው ሸጠዋቸዋል፡፡ ቅድስት ከተማቸው፣ ቤታቸውና ምድራቸው፣ የተቀደሰው መቅደሳቸው፣ እንዲሁም እንደ አይሁድ የነበራቸው የአኗኗር ዘይቤአቸው ሁሉ ሙሉ በሙሉ ፈጽሞ ተደምስሶ ጠፍቶአል፡፡
ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የቤተ መቅደሱ ድንጋዮች ፈራርሰው መሬት ላይ ተከምረው ነበር፤ ልክ ጆሴፈስ በዘገባው እንደገለጸውም "እስከመሠረቱ ድረስ በቈፈሩት መሬት ላይ የድንጋይ ቁልል ተከማችቶ ነበር፤ ስለዚህም በዚያ በኩል የሚያልፉ ሰዎች ከዚያ ቀደም በቦታው ላይ ሰው ይኖር እንደነበር እንኳ ማሰብ እስከማይችሉ ድረስ በስፍራው ምንም ነገር አልነበረም።" ቄሳርም ዛሬ በአይናችን ማየት ከምንችለው በስተቀር ሁሉም ነገር ድምድምና ድልድል እንዲሆን ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። የሮማውያን ጀግኖች ያወደሟት ምን አይነት ከተማ እንደነበረች ለዓለም ሁሉ ለመቀጣጫ ለማሳየት፣ ለወታደሮቹና ለሌሎች የጦር ክፍሎችም ካምፕ ለማዘጋጀት በሚል ከቅጥሩ የተወሰነው ክፍል ብቻ ቆሞ እንዲቀር ተደርጓል።.(የአይሁድ ጦርነት፣ መጽሐፍ 7፣ ምዕራፍ 1ን ተመልከት፤) የህ ታሪካዊ ዘገባ በራእይ 18 ቁጥር 15-18 “እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ፦ በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፥ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ፦ ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ።” ሲል ከተነገረው ትንቢታዊ የፍርድ ቃል ጋር ይስማማል።
የዚህን ታሪካዊ ክስተት አንድምታ ሙሉ ለሙሉ ለመግለጽ ከዚህ አጭር ጽሁፍ ሃሳብ በእጅጉ የላቀ ጥናትና ምርምር ይጠይቃል። በክርስቲያኑ አእምሮ ውስጥ “ብዙ ለማሰብ አቅም የሚሰጥ ምግብ” መሆን የሚችሉ ጥቂት ነገሮችን ብቻ በግርድፉ መዘርዘር ግን አስፈላጊ መስሎ ይሰማኛል።
ጆሴፈስ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱ ማንም ሊያድናቸው እስከማይቻለው ድረስ ፈጽመው እንዲወድሙ የወሰነውና እንዲህ ላለ የከፋ ጥፋት አሳልፎ የሰጣቸው እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን በታሪካዊ ዘግባው ከትቦታል፡- "....ከተማይቱም ሆነ መላው ቤተ መቅደስ አሁን በአገሩ ሰዎች የሙታን በድን የተሞሉ አይደሉምን? ከተማዋንና ቤተ መቅደሱን በሮማውያን እጅ ያነጻ ዘንድ ይህን እሳት የሚያቀጣጥለው እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ በብክለታችሁ የሞላችኊትን ይህችን ከተማ ሊነቅላት ነው።" (የአይሁድ ጦርነቶች፣ መጽሐፍ 6፣ ምዕራፍ 2፣ መስመር 110።)
ከላይ ያለው ታሪካዊ ክስተት በማቴዎስ 24፥ 2 እና 34 በኢየሱስ የተሰጠው የትንቢቱ ፍጻሜ ነው። "አንድ ትውልድ" በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ቀመር ግምቱ አርባ ዓመታት ያህል ጊዜን የሚያጠቃልል እንደሆነ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ይታወቃል። ያም “ትውልድ” ከ30 ዓ.ም እስከ 70 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚሸፍን መሆኑ ግልጽ ነው። ይህም በትንቢቱ እና በፍጻሜው መካከል ያለ እንደ የተወሰነ የጊዜ ክፍተት ሆኖ የሚታይ ነው።
የ1ኛ ጴጥሮስ መልዕክት የተጻፈበትን ጊዜ በ 60 ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው ብለን መስማማት ከቻልን፣ እንግዲያውስ ያ የመጀመሪያው የሮማውያን የከበባ ሙከራ ከመድረሱ በፊት ጴጥሮስ "ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነስቶ ሊጀምር" መሆኑን በማስታወቁ ጉዳዩ ከአጋጣሚ በላይ መሆኑን ማየት እንችላለን (1ጴጥሮስ 4፥ 17)።
ሐዋርያው ዮሐንስ በ1ኛ መልዕክቱ ምዕራፍ 2፥ 18 ላይ ሲጽፍ ሁለት ጊዜ እየደጋገመ "መጨረሻው ሰዓት ነው" ይላል። በርካቶች የኖሩበትን ጊዜ "የመጨረሻው ዘመን" ሲሉ የገለጹትን ዮሐንስ ግን መልዕክቱን እየጻፈ የነበረበትን ጊዜ "የመጨረሻው ሰዓት" በማለቱ መጨረሻው ምን ያህል እያጠረ እንደመጣ ያስገነዝባል።
ያኔ ገና በ27 ዓ.ም ላይ መጥምቁ ዮሐንስም እንኳ በሉቃስ 3፥ 7 ላይ በገዛ ዘመኑ የኖሩትን የትውልዱን ሰዎች "ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?" ሲል ይጠይቃቸዋል።
በዳንኤል አሥራ አንድ እና በሕዝቅኤል ሠላሳ ስምንት እና ሠላሳ - ዘጠኝ የተነገረለት ንጉሥ ወይም ከሰሜን ይነሳል የተባለው ወራሪ ኃይል ብዙዎች እንደሚመስላቸው ከሰሜን የሚመጣ የዘመናችን የሩሲያ ኃይል ወይም የኢራቅ ጦር አይደለም። ይልቁን ግን በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ከሰሜን ተነስቶ በሶስቱም ግንባር ወደ ደቡብ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ለወረራ የተመመው የሮማውያን ሠራዊት ነበር።
እነዚህ የቅዱሳት መጻሕፍት የንባብ ክፍሎች በ70 ዓ.ም በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ላይ ከተፈጸሙት ነገሮች አንጻር ሲታዩ በጣም ግልጽ ስለሆኑ አጠቃላዩን የአዲስ ኪዳን ትንቢት በወጉ ተርጉሞ ከመረዳት አኳያ ቸል ሊባሉም ሆነ፣ ወደ ጎን ሊገፉ አይገባም፤ ትንቢቱንም ከዚህ ፍጻሜው ነጥሎ ለማብራራት መሞከር አያስፈልግም የሚለው እንደ ፕሪቴሪስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋማችን ነው! ሊሰሙን ለሚወዱ ሁሉ የምናስረዳውም የ70ውን ዓ.ም ታሪካዊ ፍጻሜ ጠቅሰን ነው።
(gkr)
No comments:
Post a Comment