ንጥቀት" እና ትምህርቱ
፩
ብዙውን ጊዜ ይህ በመጻእያን አቅንቃኞቹ "የተባረከው ተስፋ" ተሰኝቶ የሚሞካሸው "ንጥቀት" የተባለ ጉዳይ በተለይ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው በሺህ አመት መንግስት አማኞችና በአልቦ ሺህ አመት መንግስት አማኞች ዘንድ እንደሆነ ይታወቃል። በክርስትና የስነ መለኮት አስተምህሮ ስነ ፍጻሜ ዘርፍም ይህ "ንጥቀት" (Rapture) የተሰኘ ቃል ጥቅም ላይ ሲውል አዘውትሮ የሚታወቀው በትንቢት ከተነገረው የመጨረሻ ዘመን ሁነቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ያህል ተደርጎ ነው። ይኸውም ህያዋንም ሆኑ ሙታን የሆኑ ክርስቲያን አማኞች "አንድ ቀን፣ ወደ ፊት፣ በአለም መጨረሻ ጌታ ተመልሶ ሲመጣ በአየር ላይ ክርስቶስን ለመገናኘትና ወደ ዘላለም ለመግባት ከያሉበት ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ፣ የማያምኑ ሰዎች ደግሞ ለታላቁ መከራ በምድር ላይ ይተዋሉ የሚል ትምህርት ነው። መጻእያን በአብዛኛው ይህንን እንደሚያምኑና እንደሚያስተምሩ፣ ተስፋ አድርገው እንደሚጠባበቁትም ይታወቃል። ይኸውም ከዘመን ቆጣርያን የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ የተነሳ በዘመነኛው ክርስትና በስፋት የሚታወቅና ስሩን ሰዶ ያለ ብዙዎች የሚጋሩት እምነት ነው። ታዋቂነትን ያተረፉ መጻህፍት እና የፊልም ስራዎች ይህንን ጽንሰ ሃሳብ በማራገብ የክርስቲያኖች ንጥቀት ተፈጻሚ ስለሚሆንበት ሁናቴ ሲያስተምሩ ክርስቶስ በሁለት ጊዜ ዳግም ምጽአቱ፣ አንዴ በሚስጥር አማኞችን በአየር ላይ ሊወስድ በኋላም በግልጽ ወደ ምድር ሊመለስ ይመጣል ሲሉ በስፋት ይደመጣሉ። እንደዚህ የሚያምኑና የሚያስተምሩ ሰዎችን በአገራችን ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል በብዛት ማግኘትም አስቸጋሪ አይደለም። ብዙዎቻችንም በዚህ እይታ በተቃኙ አብያተ ክርስቲያናትና ቤተ እምነቶች ውስጥ ተወልደን ያደግን ስለሆነ አመለካከቱን ተቀብለን የምንኖር ነን፣ ነበርንም።
ዘመነኛውን ክርስትና ስንመዝነው የሚበዙት የትውልዳችን ምእመናንና አገልጋይ መሪዎች የእምነት እውቀትን የሚቀዱት ከእውነተኛውና ቀጥተኛ ከሆነው የቅዱስ ቃሉ ምንጭ ሳይሆን፣ ይልቁንም በየመድረኩ ከሚቀርቡ የዝነኛ ተናጋሪ ስብከታዊ ዲስኩሮች፣ ትእይንታዊና ተውኔታዊ ከሆኑ የድራማ አቀራረቦችና ሲኒማዎች፣ ከተለያዩ በራሪ ወረቀቶች፣ በየማህበራዊ ድረ ገጹ ከሚለጠፉ ትንግርታዊ ዘገባዎች፣ ታየኝ ተገለጠልኝ ከሚሉ አስደማሚ ትረካዎች በመሆኑ፣ እንዲህ ያሉ አማኞች ቀጥተኛውንና ግልጹን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ሲሰሙ ቃሉ እንግዳ ይሆንባቸዋል። ስለዚህም የአንድን ነገር ትክክለኛነት መፈተሽ መመርመር የሚባል ጥበብንና ጥንቃቄን አያውቁትምና ሁሉን እንደወረደ ይቀበላሉ። ንጥቀትም በየአብያተ ክርስቲያናቱ የአስተምህሮ ሜኑ ውስጥ እንደወረደ ተሰድሮ ሳይመረመርና ሳይፈተሽ በብዙዎች ልብ የሚናፈቅ አጓጊ "ተስፋ" ሆኖ ይጠበቃል። መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በጥንቃቄ ለመመርመር ፈቃደኛ የሆኑ አንባቢዎች ግን "መነጠቅ" የተሰኘው ጽንሰ ሃሳብ በእግዚአብሔር ቃል ተደግፎ ሊቆም እንደማይችል ይገነዘባሉ።
ጳውሎስ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፥ 13- 18 የለውን ክፍል ሲጽፍ ይህንን "ንጥቀት" (Rapture) የተሰኘውን ቃል አይጠቀምም። "በደመና እንነጠቃለን" የተሰኘውን ሃረግ ግን ከተለመደው የመጻኢያን ትርጉም በተለየ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ሃሳቡ የተጠቀሰበትን የንባብ ክፍል ተጠግቶ ማየት ይጠቅማል፦
1ተሰሎንቄ 4፥ 13- 18 "ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።"
"አምላጭ" አስተሳሰብ የያዙ የዚህ ዘመን በርካታ ክርስቲያኖች ይህንን ክፍል ሲያብራሩ "ንጥቀትን ያስተምራል" በሚል ትርጉም በስጋ መሞትን ሳያዩ ከዚህ አለም ጭንቀት የማምለጫ መንገድ እንደሆነ ያስባሉ። "አንድ ቀን በቅርቡ (ይህ እንግዲህ ሁልጊዜ በቅርቡ መሆኑ ነው፣ ኢየሱስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በነገራቸውም ጊዜ ያው ቅርብ ነው፣ ዛሬም ድረስ ይኸው ቅርብ ነው) ኢየሱስ በአካል ሰማይ ላይ በገሃድ ይታይና ወዲያውም ሁሉም ሙታን ከየመቃብራቸው ተነስተው ከእርሱ ጋር ሲገናኙ፣ ህያዋን የሆኑ ክርስቲያኖች ደግሞ ከእነርሱ ጋር በደመና ተነጥቀው በአየር ላይ ተንሳፎ በመወሰድ ከክርስቶስ ጋር ይሆናሉ" ይላሉ። ክርስቲያኖች በአካል ከዚህ ምድር ተነጥቀው ይወሰዳሉ ብለው ያምናሉ። መቼም ሰው አሳፍረው የሚሽከረከሩ መኪኖች በድንገት አሽከርካሪ አልባ ሲሆኑ፣ ሲገለበጡና ሲጋጩ፣ አውሮፕላኖች በድንገት አብራሪ አልባ ሲሆኑና ሲፈጠፈጡ፣ የሞቱና የተቀበሩ ስጋዎች ሲነሱና ከመቃብር ሲወጡ፣ ሁሉም ወደ ሰማይ ሊሰበሰብ ሲሄድ የሚያሳይ ስእል ወይንም ፊልም ሳታዩ አትቀሩም። ሹፌሩስ ሆነ አብራሪው ምን አገኛቸው? የትስ ገቡ? ከተባለ በድንገት በቅጽበት አይን ወደ ሰማይ ስለ ተነጠቁ ነው ሲሉ ለማስረዳት ይሞክራሉ። ይህ ግን ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ይሆን? በእውነት ቃሉ እንዲህ ያለ ትምህርት አለውን?
ብዙዎች ይህ አስድናቂና አስደማሚ የሆነ የመነጠቅ ጽንሰ ሃሳብ በቤተክርስቲያን ታሪካዊ ስነመለኮት ውስጥ ፈጽሞ የማይታወቅ በጣም ዘመናዊ፣ አዲስና እንግዳ አስተሳሰብ እንደሆነ አያውቁም። እንደዚህ ዓይነቱን ክስተት የሚያመለክቱ የሚመስሉ አንድ ሁለት ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ማውጣት ይቻል ይሆናል፤ ሆኖም ግን እነዚህ ጥቅሶች በታሪካዊው ክርስትና በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን ብዙዎች አይገነዝቡትም።
የኖረውና ታሪካዊው የቤተክርስቲያን የክርስትና አስተምህሮ ፈጽሞ የማያውቀው ይህ "የቤተክርስቲያን ንጥቀት" የተባለው ጽንሰ ሃሳብ በይፋ የታወቀው በ1830ዎቹ ጆን ኔልሰን ደርባይ ይመራው በነበረና "የፖሊይሞዝ ወንድሞች" በተባለ ማህበረ ምእመናን በተጀመረ እንግዳና አዲስ ትምህርት ነው። የአስተሳሰቡ ጀማሪ እንደሆነች የሚነገርላት ግን ማርጋሬት ማክ ዶናልድ የምትባል አንዲት ሴት ስትሆን፣ እርስዋም በደረሰባት ድንገተኛ ራስን ስቶ የመውደቅ ሁናቴ ውስጥ ሆና ባየችው ወይም አየሁት ባለችው ራእይ ላይ ተመስርታ ያሰራጨችው ምስክርነቷ በዋናነት ይጠቀሳል። በተለይም የእርስዋን ምስክርነት የሰሙ ካቶሊካውያን መነኮሳትም ጉዳዩን ከበቁ ቅዱሳን የመጨረሻ እጣ ፈንታ ጋር እንደሚያያይዙት ይታመናል።
የንጥቀት ጽንሰ ሃሳብ አጀማመሩም ሆነ ሂደቱ እንዲህ ባሉ ቅዠታዊ መላ ምቶች ላይ ያረፈ ለመሆኑ ከዚህ በታች ለመዘርዘር የተሞከሩትን ታሪካዊ ስህተቶች አብነት ማድረግ ይቻላል። ትምህርቱ በተቀረው የክርስቲያን አለም ታዋቂነትን እንዲያገኝ ሆኖ የተራገበው ግን በእጅጉ በዘመን መዳብያን ስነ መለኮት (dispensationals theology) አተረጓጎም በተቃኘውና "ስኮፊልድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጣቀሻ" (Scofield Reference Bible) እየተባለ በሚጠራው ማብራርያ መጽሐፍና በክላረንስ ላርኪን ተዘጋጅቶ በታተመው "የመጨረሻው ዘመን ሁነቶች መግለጫ" በተሰኘው ሰነድ ነው። "የቤተክርስቲያን አካላዊ ንጥቀት" በመባል የሚታወቀው ይህ አስተምህሮተ ህጸጽ በሃያኛው ከፍለ ዘመን ላይ ታዋቂ የነገረ ፍጻሜ አመለካከት እየሆነ የመጣውም ከፍ ሲል በተጠቀሱት ታሪካዊ ኩነቶች ነው።
ዘመን ቆጣሪው የንጥቀት ቀጠሮ:-
ባሳለፍነው ሃያኛው ምእተ አመት ይህ ሁነት መቼ እንደሚሆን በርካቶች ቀን ቆርጠው ትንበያቸውን ሲሰጡም ተስተውሎአል። ሚኬል ዳሄል የተባለ ሰው ይህ የአሁኑ ዘመን በ1980 ላይ እንደሚያበቃ ተንብዮአል። ኤድዋርድ ዱናንስም ሩስያ በአሜሪካን ላይ ወረራ ስትፈጽም ያኔ በ1979 የሺህ አመት መንግስት ይጀምራል ሲል ትንበያውን ሰጥቶአል። የደቡብ ምእራብ ራድዮ ቤተክርስቲያኑ ኤሚል ጋቨርሉክም ንጥቀት በ1981 ላይ እንደሚሆን ተንብዮ ነበር።
በ1948 እስራኤል እንደ ህዝብና አገር ስትቋቋም ብዙዎች ይህንን ጉዳይ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች መፈጸም እንደ አይነተኛ ምእራፍ አይተውታል። በዚያን ጊዜ በነበረው ትውልድ ውስጥም (አርባ አመት) ንጥቀት ይሆናል ብለው ሲጠባበቁ ነበር። ዛሬም ድረስ በክርስትናው አለም የዘመነኛይቱን እስራኤል አመሰራረት፣ ፓለቲካዊ፣ መልክአ ምድራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳይዋን ከትንቢት ፍጻሜ ምልክት ጋር ለማጣጣምና ለመተርጎም የሚጥሩ እጅግ ብዙዎች እንደሆኑ የተሰወረ አይደለም። ኤድጋርድ ሲ ዌስናንት የተባለ ሰውም ንጥቀት በ1988 ላይ ለምን የግድ መሆን እንዳለበት ለማስረዳት 88 ምክንያቶችን የሚዘረዝር መጽሐፍ ጽፎ ፣ በ1988 ብቻ በወንጌል አማኞች ዘንድ የዚህ መጽሐፍ ስድስት ሚልዮን ቅጂ ተሰራጭቶ ነበር። ዌስናንት ሲያስረዳ ክርስቶስ በመስከረም 1988 ወደ ምድር ለምን መመለስ እንዳለበት ይሞግታል። አስቂኙ ነገር፣ በርካታ ክርስቲያኖች የዚህን ሰው መልእክት እውነት አድርገው በመውሰድ ስራዎቻቸውን ያቆሙና የክርስቶስን ድንገተኛ መምጣት ለመጠባበቅ እንዲመቻቸው ከሚተዳደሩበት የስራ ገበታቸው የአመት ፈቃድ ጠይቀው ጊዜ ወስደው እንደነበር በርካታ የዜና አውታሮች ዘግበውታል። የአመት ፈቃድ ወስዶ ምጽአቱንና ንጥቀትን መጠባበቅ ምን የሚሉት ነገር እንደሆነ በእውነት ግራ ይገባል።
ዌስናንት ሲናገር "ልሳሳት የምችለው መጽሐፍ ቅዱስ ከተሳሳተ ብቻ ነው፣ በሁሉ ሰፍራ ላሉ ሰባክያን በማያሻማ መንገድ ላረጋግጥላቸው የምችለው በመጽሐፍ ቅዱስ ረገድ እኔ ልሳሳት የምችልበት ምንም መንገድ የሌለ መሆኑን ነው"፣ ብሎ በድፍረት ይናገር ነበር። በኋላም እንደ ዌስናንት ትንቢት ይጠበቅ የነበረው ንጥቀት ሳይሆን ቀርቶ መስከረም 1988 ካለፈ በኋላም ዌስናንት ለቀድሞው የሃሰት ትንበያው ንስሃ ሳይገባ እንደገና The Final Shout: Rapture Report 1989 የተሰኘ ሌላ መጽሐፍ አሳተመ። በዚህ መጽሐፉ ደግሞ "ስህተቴ የሂሳብ ቀመሬ ላይ በአንድ አመት ጉድለት ማሳየቴ ነው" ብሎ ተናገረ። እንደገናም ግን በትንበያው ስህተት ፈጽሞ ነበር።
ሀል ሊንደሲ እንዲህ ብሎ ነበር፦
"በግምት ከ2,000 አመታት ግዞት በኋላ የአይሁድ ህዝብ ከነበሩበት የስደት ሕይወት ተላቀው በሜይ 14 ቀን 1948 አ.ም እንደገና ሕዝብና አገር ሆነው ሲቋቋሙ፣ ይህ ማለት በለሲቱ ስትለመልምና ቅጠልዋ ሲያቆጠቁጥ ነው። ኢየሱስ እንደተናገረው፣ ይህ የሚያመለክተው ለመመለስ በደጅ መሆኑን ነው። ከዚያም እንዲህ አለ "እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" (ማቴ 24፥ 34)።" ሲል የጌታችንን ቃል ይጠቅሳል።
ሀል ሊንደሲ ይህንን ቃል አንስቶ "የትኛው ትውልድ?" ሲል ይጠይቅና ራሱ ሲመልስ፣ "በግልጽ አውዱ እንደሚነግረን ምልክቶቹን የሚያየው ትውልድ ነው። ከእነርሱም መካከል የእስራኤል እንደገና መመስረት ነው። አንድ ትውልድ በመጽሐፍ ቅዱስ የአርባ አመታት ጊዜ ነው። ይህ ትክክለኛ ቀመር ከሆነ፣ እንግዲያውስ በአርባ አመታት ውስጥ ወይም ከ1948 ጀምሮ እነዚህ ነገሮች መሆን ይጀምራሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ያጠኑ በርካታ ምሁራንም ይህ እንደዚህ እንደሆነ ያምናሉ" ይልል። (The Late Great Planet Earth, pp53-54)
ከሌሊቱ ሰንት ሰዓት ነው" የተሰኘውና በመጻኢነት አመለካከት የዘመን ቆጣሪው (dispensationals) የትርጉም ተጽዕኖ ያረፈበት መጽሐፍ ደራሲ ኢትዮጵያዊው መጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳንም ከኤክሰደስ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ "አርባ አመት" የሚለውን የሀል ሊንደንሲን ቀመር ወደ መቶ አመታት ለውጦ ከማቅረብ ውጭ ሙሉ በሙሉ ይህንንው ሃሳብ ቃል በቃል እንደሚጋሩ አንጸባርቀዋል። በቃለ ምልልሳቸውም የበለሲቱን ማቆጥቆጥ ምሳሌ ከእስራኤል መንግስት መመስረት ጋር፣ "ይህ ትውልድ አያልፍም" የሚለውንም የእስራኤል መንግስት ሲመሰረት በአይኑ የሚያየውን ትውልድ ማለት ነው ሲሉ፣ አቋማቸውን የሚቀበሉ ሌሎችም "ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች" ያሉ እንደሆነ መስክረዋል። አክለውም ምጽአቱን የሚያየውም ሆነው ከሚመጣው የታላቁ መከራ በፊት ለንጥቀት የሚበቃው ይኸውም የእስራኤልን እንደገና ማቆጥቆጥ በአይኑ የሚያየው ትውልድ ነው ብለው ተናግረዋል። በዚሁም ንግግራቸው ለጌታ ዳግም ምጽዓት የቀረው ጊዜ ቢበዛ ወይም ቢያንስ 37 አመታት ያህል ነው ሲሉ በመጽሐፋቸው የነገሩንንም አጽንተውልናል።
አንድ የኮርያውያን ቡድን የሚያሳትመው ጋዜጣም በማስታወቂያ ገጹ ላይ የሰጠው ትንበያ ንጥቀት በኦክቶበር 28 ቀን 1992 ላይ እንደሚሆን ነበር። ያኔም ምንም ባልሆነ ጊዜ፣ ሃኪም ታጂን የተባለ ሰው ጉዳዩን ያለ እፍረት ሲያስተባብል "ከእግዚአብሔር ያገኘነው መልእክት ስህተት ነበር፤ ኢየሱስ ግን ከብዙ አመታት በኋላ ይመለሳል" ሲል ተናግሮአል። በውኑ "ስህተት" ግን ደግሞ "ከእግዚአብሔር የሆነ መልእክት" ምን የሚሉት ቅዠት ነው? ይህስ ስህተት የሚታረምው "ኢየሱስ ግን ከብዙ አመታት በኋላ ይመለሳል" በሚል ሌላ ስህተት መሆን ነበረብትን?
በ1992 የበጋ ወራት ቻርልስ አር ቴይለር የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ ዜናዎችን ጽፎ በሚያቀርብበት ስራው የኢየሱስ መመለሻ ጊዜ የሚሆነው ፎል እየተባለ በሚጠራው በዚያው አመት የክረምት ወራት መግቢያ ላይ እንደሚሆን ነበር፤ ሲጽፍም፦ "ምናልባት ማንበብ ያለባችሁን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የመጨረሻ ዜናዎቼን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን ሊነጥቅ በ1992 ከፎል ወራት በፊት እንደሚመለስ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ፍጻሜ የሚያበስረውን ጽሑፌን አሳትማለሁ" ብሎ ነበር።
ጄፍሪ የተባለ ሰውም Armageddon: Appointment with Destiny በተሰኘው መጽሐፉ "ምናልባት 2000 አ.ም 'የመጨረሻው ዘመን' ፍጻሜ ሊሆን ይችላል" ሲል ጽፎአል። ሊስተር ሱምራልም I Predict 2000 በተሰኘው መጽሐፉ ላይ፦ "በ2000 አ.ም የሰው ልጅ ጭቆና ከምድር ላይ ፈጽሞ ያበቃል" ሲል ይተነብያል።
እንዲህ ያሉ መጻኢነት እና ዘመን ቆጣሪነት በተሰኘ ትምህርተ ህጸጽ ላይ የታነጹ ሌሎች በርካታ ከንቱ የሃሰት ትንበያዎችን ከዚህ ቀደም ማስነበቤን አስታውሳለሀ። ፍላጎቱ ያለው አንባቢ ሊመለከታቸው ይችላል። ለዚህ ጽሁፍ ፍጆታ ይህን ይህል ካልኩኝ ለአንባቢዎቼ ያለኝ ቀጣዩ ጥያቄዬ፦ እናንተስ ምን ታስባላችሁ? ከዚህ በኋላ ንጥቀት በማናቸውም ጊዜ ሊሆን ይችላልን? ከዚህ ሁሉ የተሳሳቱ ግምቶችና መላምቶች በኋላ አሁንም እንኳ ሰው ከታሪካዊ ስህተቱ ተምሮ እርማት ሳይወስድ የኸንንው ትንበያና ንግርት ቀጥሎበታል። በነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ የመጻኢያኑን በተለይም የዘመን ቆጣሪነትን ትርጉምና አቋም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ብላችሁ እስከተቀባላችሁ ድረስ፣ ዳግም ምጽአትና ንጥቀት የሚሆንበትን፣ የአለም ፍጻሜም የሚሆንበትን ጊዜ መተንበይ ወይም መገመት በአንድም ሆነ በሌላ እጣ ክፍላችሁ እንዲሆን መርጣችኋል ማለት ነው። እንደዚያ ከሆነ ገና በእግዚአብሔር ቃል የምናርመው ደርዘን መላ ምት ይጠብቀናል ማለት ነው።
ለአሁኑ እዚህ ላይ ላብቃ፤ በሚቀጥለው ጽሁፌ እስከምንገናኝ ቸር ሰንብቱ
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/
♦♦♦♦♦♦♦♦
"ንጥቀት" እና ትምህርቱ
፪
የቤተክርስቲያንን አካላዊ ንጥቀት የሚያስተምረው ዘመናዊው አስተሳሰብ የተደገፈበትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንባብ አድምተን እንይ፦
1ተሰ 4፥ 13-18 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።
የሥነ ፍታቴ ሀሁ:-
በመጀመርያ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚጽፈው ለማን ነው? የሚለው ነው። "ታውቁ ዘንድ"/ "እናንተ" / የተባሉት እነማን ናቸው? ግልጽና የማያሻማው መልስ በመጀመርያው ከፍለ ዘመን በተሰሎንቄ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ናቸው። እነርሱም የዚህ መልእክት በኩረ ተደራስያኑ ናቸው።
ምንግዜም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብም ሆነ ስናጠና በሃሳባችን ውስጥ የበኩረ ተደራስያኑን ታሪካዊ አውድ ማስተዋል አለብን - የመጀመርያዎቹ ተደራስያን ይህንን ንግግር የተረዱት እንዴት ነበር? ብለን መጠየቅ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ስለ እኛም ነው እንጂ አስቀድሞ ወደ እኛ አይደለም። እንዲህ ያለ ነገር ስናገር የሚቆጡ አንዳንድ ክርስቲያኖች አይጠፉም። መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ወደ እኛ እንደተጻፈ ይመስላቸዋልና። ጳውሎስ 1ኛ ተሰሎንቄ መልእክቱን በሚጽፍበት ጊዜ የሚጽፈው በመጀመርያው ከፍለ ዘመን ላይ በተሰሎንቄ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች ነው። እርሱ የሚለውን ነገር በአግባቡ ለመረዳት ይህንን መረዳት አለብን።
ምንባበ እስኪገባን በያዘው ፍሬ ነገር አውድ ውስጥ እንየውና ጌታ በዚህ ቃል ምን እያስተማረ እንደሆነ ለመረዳት ብርሃን እንለምን።
1ተሰ 4፥13-14 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደ ሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና።
ይህ የጳውሎስ ትንቢት በጥንት ቤተ ክርስቲያን የጌታ ምጽዓት በእጅጉ ቅርብ እና ከመሆን የማይቀር እንደሆነ ከነበረው እምነት እና ትምህርት ተወልዶ ያደገ ነው። በርካቶችም ቅዱሳን መመለሱን ለማየት በሕይወት እንደሚኖሩ ያምኑም ይጠባበቁም ነበር፡፡ ሆኖም በተሰሎንቄ የነበሩ ቅዱሳን ጌታ ከመምጣቱ በፊት ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው አስቀድመው በስጋ ስለሞቱ ተስፋ እየቆረጡ መጥተዋል፡፡ ምናልባትም ብዙዎቹ የሞቱት በቤተክርስቲያን ተነስቶ ከነበረው ከባድ ስደት የተነሳ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ቤተ ክርስቲያን ያንን የመሰለ ከባድ ሓዘን ውስጥ የወደቀችው ምዕመናን የሚወዱአቸውን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በሞት ስላጡ ብቻ አልነበረም፣ ነገር ግን እነዚያ የሞቱ ቅዱሳን ጌታ በሚመለስበት ጊዜ በሕይወት ስለማይኖሩ ቤተ ክርስቲያን ስትጠባበቀው የነበረውን ተስፋ ለመቀበል አይችሉም ብለው ያስቡና ይሰጉ ስለነበር ጭምር ነው፡፡ "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ" (ሮሜ 8÷ 18) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ በጌታ ምጽዓት ጊዜ የሚገለጠውን ወይም ሊገለጥ ያለውን ክብር ሳይቀበሉ ይቀራሉ ብለው ለሞቱ ወዳጆች እና ቤተሰቦቻቸው ይጨነቁና ያዝኑ ስለነበር፤ በዚህ የንባብ ክፍል ይህንን የተሰሎንቄ ምዕመናን የጊዜውን ጥልቅ ሓዘን የተመለከተ እና ለቤተ ክርስቲያኑም መጽናናትን ለማምጣት የተጻፈላቸው የጳውሎስን ማጽናናት እናያለን፡፡
በመጀመርያ እነዚህ "በኢየሱስ ያንቀላፉ" የተባሉቱ እነማን ናቸው? እነማን እንደሆኑ ለማወቅ የተሰሎንቄ አማኞች የነበራቸው ያልዳኑ ሰዎች ግን ያልነበራቸው ይህ "ተስፋ" ምን እንደነበር ማወቅ አለብን።
/በትንቢተ ዳንኤል ምእራፍ 12 ጥናት ስለ እስራኤል "ተስፋ" ስለ ትንሳኤ የተነሳውን ሃሳብ ይመለከቷል/
"ያንቀላፉ" የተባሉቱ በአሮጌው ኪዳንና ዘመን እንዲሁም ወደ አዲሱ ኪዳንና ዘመን በነበረው የሽግግር ወቅት ውስጥ የሞቱና በሲኦል/ ሀደስ ውስጥ የነበሩ ቅዱሳን ናቸው። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች ሲጽፍላቸው "ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣ ያኔ በመቃብር ያሉትን የአሮጌው ኪዳን ቅዱሳንን በትንሳኤ ያድናቸዋል" ሲል ዋስትናን ይሰጣቸዋል።
በጌታ ቃል፦
ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ከንግግሩ የተሰሎንቄ ምእመናን በሞት ስለተለዩአቸው ወንድሞቻቸው ሃሳብ ሳይገባቸው እንዳልቀረ እንረዳለን። በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፥14-18 ባለው ክፍል ጳውሎስ በክርስቶስ ምጽአት ጊዜ እንደሚነሱ እየነገራቸው እንዳይጨነቁ እየደጋገመ ዋስትናን ይሰጣቸዋል፣ ከዚያም "እኛ ሕያዋን የሆንን በተራችን ደግሞ እንከተላለን" ይላል። ይህ "እኛ ሕያዋን የሆንን" የሚለው ሃረግ በዋናነት የሚያመለክተው የመጀመርያው ከፍለ ዘመን የተሰሎንቄ አማኞችን ነው።
እነዚያ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አማኞች ጌታ እስኪመጣ ሳይሞቱ ቆይተው መምጣቱን የሚያዩ እንደሆነና ጌታም ዘመናቸውና ትውልዳቸው ሳያልፍ የሚመለስ መሆኑን ያምኑና ይጠባበቁ ነበር። ይህም "በጌታ ቃል" የተሰጠ ተስፋ ነው። እንዲህም እንዲያምኑና እንዲጠብቁ የነገራቸው ጌታ ነው፣ (ማቴ 10፥ 23፤ 16፥ 28፤ 24፥ 34፤ 26፥ 64 ወዘተ.. ይመለከቷል)። ይህም እምነትና መጠባበቅ በጌታ ቃል ላይ የተመሰረተ፣ በመንፈስ ቅዱስ የተመራና ያልተሳሳተ እምነትና መጠባበቅ ነበር። ስለዚህ በዚህ ምንባብ የተነሳው ርእሰ ጉዳይ ኢየሱስ ራሱ ደግሞ ያስተማረው ነበር እንጂ አዲስና እንግዳ ትምህርት አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ አካላዊ ንጥቀትን ፈጽሞ አያስተምርም፣ ያስተምራል ቢባል እንኳ ይህ ንጥቀት በጌታ ዳግም ምጽአት ጊዜ የሚፈጸም እስከሆነ ድረስ፣ ዳግመኛ ምጽአቱም ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የኢየረሳሌምና የቤተ መቅደሱ ውድመት ጋር የተጋመደ በመሆኑ፣ እንግዲያውስ ከምጽአቱ ጋር የሚጠበቀው አካላዊ ንጥቀት መፈጸም ያለበት ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን በሆነ ነበር፤ ዳሩ ግን ከጌታ ምጽአት በኋላም በምድር ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ የመጀመሪያው ከፍለዘመን ቅዱሳን ይህንን ታላቅ ልምምድ በተመለከተ ምንም የነገሩን ነገር የለም። ምክንያቱም የሌለ ነገር እንዲነግሩን ጌታ አልላካቸውም።
1ኛ ተሰ 4፥15 በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤
ጳውሎስ ምን ብሎ እንደሚጽፍ ልብ በሉ፦ "ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሕያዋን ሆነን በጌታ ቃል የምንቀር እኛ" ። "ሕያዋን ሆነን የምንቀር" የተባሉት እነዚህ "እኛ" ተብለው የተገለጹ ሰዎች አንድን የጊዜ ማእቀፍ የሚያመለክት ንግግር ነው። "እኛ" የሚያመለክተው ጳውሎስንና የበኩረ ተደራስያኑን ስብስብ በአንድነት ነው። እነርሱ (ጳውሎስና የተሰሎንቄ ሰዎች) የጌታን መመለስ በራሳቸው ዘመን ይጠባበቁ ነበር። ይህም በመላው መጽሐፉ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ ነው። ማስርጃዎቹን ከብዙ በጥቂቱ በተስሎንቄ መልእክት ውስጥ ብቻ ያሉትን እንይ፦
1ተሰ 1፥ 10 ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ፥ ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥ ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።
1ተሰ 2፥19 ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን?
1ተሰ 3፥ 13 ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።
1 ተሰ 5፥ 23 የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።
በሁሉም ምንባባት በግልጽ የምናየው ጳውሎስና የተሰሎንቄ ምእመናን የክርስቶስን መመለስ በዘመናቸው ለማየት ይጠባበቁ የነበሩ መሆናቸውን ነው። በተጨማሪም ይህንን ተመልከቱ፦
2ተሰ 1፥6-10 ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።
በመጀመርያው ከፍለ ዘመን ላይ ለነበሩ የተሰሎንቄ ምእመናን ጳውሎስ ሲጽፍ እግዚአብሔር መከራ ለሚያሳዩአቸው መከራን ለእነርሱ መከራን ለሚያዩ የተሰሎንቄ ምእመናን ደግሞ እረፍትን ብድራት አድርጎ እንደሚሰጥ የናገራል። ይህንን የሚያደርገው መቼ ነው ይላል?
ጌታ በዳግም ምጽአቱ ሲመለስ ያኔ የተሰሎንቄ ምእመናን ከጠላቶቻቸው ያርፋሉ። ዳግም ምጽአቱ ደግሞ በእነርሱ የሕይወት ዘመን የማይሆን ከሆነ፣ እንግዲያውስ ጌታ የሰጣቸው ይህ የእረፍት ብድራት ተስፋ ሃሰተኛ የሆነና እንደውም እያታለላቸው ነበር ማለት ነው። ጌታ ግን ሃሰትን ይናገር ዘንድ እንደ ሰው አይደለም።
ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች የሚያረጋግጥላቸው ክርስቶስ እነርሱ በሕይወት ባሉበት ዘመን በትውልዳቸው ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ያኔ በሕይወት የሚገኙ የሞቱትን ቀድመው ወደ ሰማይ፣ ወደ እግዚአብሔር ሃልዎት የሚገቡ አይሆኑም። ቅድሚያ የሚያገኙት በጌታ ሆነው ያንቀላፉቱ፣ እነርሱም በሲኦል/ሀደስ ያሉ የቀድሞው ኪዳን ቅዱሳን ናቸው።
ጳውሎስ በዚህ ምንባብ ለተሰሎንቄ ምዕመናን የነገራቸውን ያንንው ተመሳሳይ ነገር ለቆሮንቶስ ምዕመናን በጻፈው በመጀመሪያው መልዕክቱም “እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን” (1ቆሮ 15 51-52) ሲል፣ በእርግጠኝነት መልሶ ይነግራቸዋል ፡፡ በሕይወት ለነበሩ ምዕመናን “ሁላችንም አናነቀላፋም” ወይም በሌላ አገላለጽ “አንሞትም” ብሎ ተስፋ ሲሰጥ፣ የሞቱትን በተመለከተ “ሙታንም ይነሳሉ” ይላል፡፡ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ምዕመናን የሚሰጣቸው ተስፋ ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ ጌታ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ በሕይወት እንደሚኖሩ ነው፣ ሙታንንም በተመለከተ “በክርስቶስ የሞቱ አስቀድመው ይነሳሉ” ይላል፡፡ ጳውሎስ አስቀድመው ሙታን ይነሳሉ ከዚያም ሁለተኛ ሕያዋን ይለወጣሉ በሚልበት በዚህ በ1ኛቆሮንቶስም ቢሆን ቅደም ተከተሉ ያው ተመሳሳይ ነው፡፡
1ተሰ 4፥16 ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤
የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ስለመተርጎም ግድ የሚሰጠን ከሆነ፣ የስነ ፍታቴን መርሆዎች ተከትለን በትጋት ልንፈጽመው ይገባናል። በስነፍታቴና ትርጓሜ ሂደት ውስጥ ደግሞ ፈጽሞ መረሳት የሌለበት መርህ "የእምነት ተመሳስሎ" /Analogy of Faith/ ተብሎ ይጠራል። ይህም ማለት መጽሐፍ ቅዱስ የሚተረጎመው በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው ማለት ነው። የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በግልጽ ከተሰጠው ትምህርት ጋር ሊጣረስ በሚችልበት መንገድ ሊተረጎም አይችልም አይገባምም። ከዚህ በመለስ ያለው የትኛውም መጽሓፍ ቅዱስን የመተርጎሚያ ዘዴ ለዚህ ታላቅ መርህ አሽከርና ሎሌ ሊሆን እንጂ በዚህ መርህ ላይ እንዲሰለጥን አንፈቅድም።
እንግዲህ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር ስናስተያይና ስናነጻጽር፣ እንዲህ ያለው አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ አጠቃቀም ስለ ፍርድ የሚናገር እንደሆነ እናያለን። ይህንን የንባብ ክፍል በማቴዎስ 24 ካለው ምንባብ ጋር ስናነጻጽረው ደግሞ ትርጉሙን የበለጠ ለመረዳት የሚያስችለንን እውቀት እናገኛለን።
ማቴ 24፥ 30-31 የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።
ይህ ይንባብ ክፍል በተሰሎንቄ ካለው ጋር የሚስተያይ ምንባብ ነው። ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የሚናገረው በኢየሩሳሌም ውድመት አውድ ውስጥ ሲሆን እነርሱ ይኖሩ የነበሩበት ትውልድም ይህ ሁሉ ሲሆንና ሲፈጸም እንደሚያይ ይናገራል (ማቴ 24፥ 34)። በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አቡቀለምሲሳዊ ቋንቋ "ደመና" እግዚአብሔር በህዝቡ ጠላቶች ላይ ለሚያመጣው ቁጣና ፍርድ ምልክት ነው። ዳዊት በመዝሙር 18፥ 3-15 እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሊያድነው በደመና እንደወረደ ይናገራል። ኢሳይያስም ጌታ በደመና ሆኖ ወደ ግብጽ እንደሚወርድና እንደሚቀጣቸው ይናገራል፦
ኢሳ 19፥1 ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።
እግዚአብሔር ቃል በቃል ደመና ላይ ተሳፍሮ ይመጣል ማለት ሳይሆን ግብጽ ግን በአሶር እጅ ፍርድዋን ትቀበላለች ማለት እንደሆነ ቀጥሎ ባለው ምእራፍ የተገለጠ ነው (ኢሳ 20፥ 1-6)። የኢየሱስን በደመና የመምጣት ሃሳብ በተዳሳሹ ደመና እንደሆነ አድርጎ መረዳት የብሉይ ኪዳን ነብያት ጉዳዩን ይረዱበት ከነበረው የትርጉም ባህርይ ጋር የሚጣረስ ያደርገዋል። (በጌታ ዳግም ምጽአት ላይ በተከታታይ በፌስ ቡክ በለጠፍኩት ጽሁፌ ስለ አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ አጠቃቀም የሰፈረውን ሃሳብ እንድትመለከቱ እጋብዛለሁ።)
በ1ኛ ተሰሎንቄ 4-5 እና በማቴዎስ 24 መካከል ያለው ንጽጽር አስገራሚ ነው። ኢየሱስ በማቴዎስ 24 ይጠቀምበት የነበረው የቋንቋ ዘይቤ አቡቀለምሲሳዊ ሆኖ ሳለ፣ በ1ኛ ተሰሎንቄ ምእራፍ 4-5 ያለው ተመሳሳይ የቋንቋ ዘይቤ የፊት ለፊት እንዲሆን ማሰብ ፈጽሞ ትክክል አይደለም። በማቴዎስ የተጠቀሰው መምጣት የኢየሩሳሌምን ውድመት ከበው ያሉትን ሁነቶች የሚያመለክቱ ናቸው ብለው የሚያምኑ ተርጓሚዎች ደመናውን፣ መላእክቱን ወይም የመለከቱን ድምጽ የፊት ለፊት ትርጉም ሰጥተን እንዳንተረጉም ያሳስባሉ። እነዚህ ጉዳዮች በማቴዎስ ውስጥ የፊት ለፊት ትርጉም የሌላቸው ከሆኑ በዚያው አይነት አገላለጽ በተሰሎንቄ ውስጥ የተነገሩት ጉዳዮች እንዴት የፊት ለፊት ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል? ማቴዎስ በተሰሎንቄ ውስጥ ጥቅም ላይ ለዋለው የቋንቋ ዘይቤ እንደ ምንጭ ነው።
1. ክርስቶስ ራሱ ይመለሳል።
ማቴ 24፥30
1ተሰ 4፥16
2. ከሰማይ
ማቴ 24፥ 30
1ተሰ 4፥16
3. ከታላቅ ድምጽ ጋር
ማቴ 24፥ 30
1ተሰ 4፥ 16
4. በ መላእክት ታጅቦ
ማቴ 24፥31
1ተሰ 4፥16
5. ከእግዚአብሔር መለከት ጋር
ማቴ 24፥31
1ተሰ4፥16
6. አማኞች ይሰበሰባሉ
ማቴ 24፥31
1ተሰ 4፥17
7. በደመና
ማቴ 24፥30
1ተሰ4፥17
8. ጊዜው አይታወቅም
ማቴ 24፥ 36
1ተሰ 5፥1-2
9. እንደ ሌባ ይመጣል
ማቴ 24፥43
1ተሰ 5፥2፣4
10. የሚሆነውን ፍርድ የማያምኑ ሰዎች ሊያውቁት አይችሉም
ማቴ 24፥ 37-39
1ተሰ 5፥3
11. ፍርዱ የሚመጣው ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት በድንገት ነው
ማቴ 24፥8
1ተሰ 5፥3
12. አማኞች ይመለከታሉ
ማቴ24፥ 42
1ተሰ 5፥ 4
13. ለመጠጥና ለስካር የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
ማቴ 24፥ 49
1ተሰ 5፥ 7
ኢየሱስ በማቴዎስ 24 መምጣቱ በዚያ ትውልድ ውስጥ ያሉትን ቅዱሳን ለመሰብሰብ እንደሆነ ይተነብያል። ጳውሎስም በ1ኛ ተሰሎንቄ 4-5 ስለዚያው አንድ አይነት የጌታ መምጣት ሲናገር ቅዱሳንን ለመሰብሰብ እንደሆነ ይናገራል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያለው ከመላእክቱ ጋር የሆነ፣ በእሳት፣ በኃይል፣ እና በክብር የሆነ፣ ቅዱሳንን ለመሰብሰብ የሚደረግ የጌታ ምጽአት ሰንት ነው? አንድ ብቻ ነው! መጠቅለያው ሃሳብ እንግዲህ ልናመልጠው የማንችለው ነው፦ 1ተሰሎንቄ 4-5 የሚናገርለት ምጽአት፣ ፍርድና፣ መሰብሰብ ያው ማቴዎስ 24 የሚናገርለትን ነው።
1ተሰ 4፥16 ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤
ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ምእመናን የሚነግራቸው ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ላይ በፍርድ ስለ መምጣቱ ነው፣ ይኸውም በ70 አ.ም ላይ የሆነው ጥፋትዋ ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ ያኔ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ከሲኦል/ ሀደስ ወጥተው ወይም ተነስተው ወደ እግዚአብሔር ኃልዎት ይመጣሉ። ብሉይ ኪዳን የሚያስተምረውም የሙታን ትንሳኤ ይኸው በኢየሩሳሌም ውድመት ጊዜ ሊፈጸም ቀን የተቀጠረለትን ትንሳኤ ነው (ዳንኤል 12ን ይመለከቷል)።
"አካላዊ የንጥቀት ትወራን ይደግፋል" ተብሎ የሚጠቀሰው ጥቅስ እንግዲህ ይህ ነው:-
1ተሰ 4፥ 17 ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።
ሕያዋን የሆኑት ጌታ ሲመጣና የሞቱት ሲነሱ በዚያው በተመሳሳይ ጊዜ የሚነጠቁና የሚለወጡት ከሆኑ፣ ታዲያ "በጌታ የሞቱ አስቀድመው ይነሳሉ" ማለት ምን ማለት ነው? ጳውሎስ እያለ ያለው ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ በክርስቶስ የሞቱቱ ይነሳሉ፣ ከዚያ በኋላ ሕያዋን የሆኑት ደግሞ በአካል ሲሞቱ ከእነርሱ ጋር በደመና ይነጠቃሉ።
"መነጠቅ" የተሰኘው ቃል "harpazo" ከተሰኘው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን፣ ትርጉሙም "ለቀም ማድረግ" ወይም "መውሰድ" ወይም "መቀማት" ነው፣ ሲሉ የስትሮንግና የጣየር መዝገበ ቃላት ይፈቱታል። ቫየንና ባወር ደግሞ "መነጠቅ" በተሰኘው በዚህ ቃል ውስጥ በዋናነት "ድንገተኛነትን" ያሳያሉ። ከዚህም የተነሳ በቅጽበት መነጠቅ የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 52 "ቅጽበተ አይን" የተባለው "በድንገት" መለወጥን የሚያካትት መሆኑ ግልጽ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ harpazo የተሰኘ የግሪክ ቃል በውስጡ "አንድነትን" ወይም "አንድ መሆንን" የሚያሳይ አሳብ ተሸክሞአል፤ ይኸውም አንድ ሰው ከራሱ ጋር አንድ እንዲሆኑ የሚፈልጋቸውንና የሚመርጣቸውን ነገሮች ወይም ሰዎች መውሰዱን፣ እነርሱም በዚህ ሂደት ውስጥ ከእርስ በርሳቸው ጋር አንድ እንደሚሆኑ ወይም ወደ አንድነት የሚመጡ መሆኑን ያሳያል። ስለዚህ harpazo "በአንድነት የመሰብሰብን" ወይም ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ነገሮችን ወደ አንድነት ማምጣትን የሚያሳይ ነው።
መነጠቅ ለሚለው ቃል የእንግሊዘኛው አገባብ "to snatch away" የሚል ሲሆን "መውጣት" እንደ ማለት ነው። "rapture" የተሰኘው ቃልና የንጥቀት ጽንሰ ሃሳብም የተገኘውም ይህንንው ሃረግ በመተርጎም ነው፤ ይህም አካላዊውና ተዳሳሹ ሰጋ ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከፍ ብሎ ወደ ሰማይ ንፍቀ ክበብ በአካል የወሰዳል የሚል አስተሳሰብን የሚያንጸባርቅ ነው። ነገር ግን ይህ መነጠቅ (cought up/ snatch away) ፈጽሞ የአካላዊ ስጋ ከምድር ላይ ወደ ሰማይ ንፍቀ ክበብ ከመወሰዱ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የሌለው መሆኑን harpazo ለተሰኘው ከፍ ሲል ለተብራራው የግሪክ ቃል የቀረበው ፍቺ ያሳያል። ይህ መነጠቅ (cought up) ከዳግም ምጽአቱ በኋላ የሚሆን አንድ ነገር እንደሆነ አትርሱ፤ ዳግመኛ ምጽአቱ ደግሞ በሁሉም የቅዱሳት መጻህፍት ክፍሎች ከኢየሩሳሌም የፍርድ ውድመት ጋር የተጋመደ ኹነት ነው። ተግባብተንም መነጋገር የምንችለው በዚሁ አግባብ ነው።
"Harpazo" ሰጋ ወደ ላይ ሲወሰድ (cought up ሲሆን) ያንን ለመግለጥ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበት አጋጣሚ ይኖር እንደሆን አላውቅም፤ ነገር ግን ደግሞ ክርስቲያን ያለ ሰጋ ወይም ከስጋው ተለይቶ ሲወሰድ (cought up ሲደረግ) ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን ሀኔታ በግልጥ እናያለን። በዚህ መንገድ ቃሉ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ተመልከቱ፦
2ቆ 12፥ 2-4 ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።
ጳውሎስ የዚህን ሰው መወሰድ በስጋው ይሁን ወይም አይሁን አያውቅም። እንግዲያውስ በHarpazo ሂደት ስጋ የግድ አስፈላጊ አይደለም ማለት ነው፣ ወይም ጳውሎስ ይህንን ሊያረጋግጠው ያልቻለውን ነገር ሊያብራራው አልተቻለውም ማለት ነው። ጳውሎስ ሲጽፍ በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ጊዜ በህይወት ያሉ ክርስቲያኖች ህያው በሆነ፣ በተዳሳሹ ስጋ በአካል ወደ ላይ ይወሰዳሉ ማለቱ እንዳልሆነ እናውቃለን፤ ትርገሙ እንደዚያ ነው ቢባል እንኳን ጌታ ሲመጣ ያኔ ይህ ፈጽሞ አልሆነም። ታሪክ እንደሚነግረን ደግሞ ከዳግም ምጽአት በኋላም እንኳ ቢሆን ክርስቲያኖች በምድር ዙርያ ነበሩ።
ኬኔት ኤል ጄንትሬይ ጄ. አር የተባሉ የስነ መለኮት ምሁር፣ የራእይ መጽሐፍ ከ70 አ.ም በፊት እንደተጻፈ ለማረጋገጥ ጥናታዊና ታሪካዊ ሙግት ባቀረቡበት "Before Jerusalem Fell: Dating the Book of Revelation" በተሰኘው መጽሐፋቸው በ90ዎቹ አመተ ምህረት ወቅት ፖሊካርፕ የተባለው የጥንት ቤተክርስቲያን አባት ሐዋርያው ዮሐንስን በአካል አይቶት እንደነበር ማስረጃቸውን ያቀርባሉ። ሰለዚህ በ70 አ.ም ከሆነው ዳግመኛ ምጽአት በኋላም ቢሆን እንኳ ለተወሰኑ ሃያ አመታት ያህል ዮሐንስ በምድር ላይ በሕይወት ይኖር ነበር ማለት ነው።
1ተሰ 4፥ 17 ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።
ጳውሎስ እያለ ያለው በኋላም በዳግም ምጽአት ጊዜ በሕይወት የሚገኙ ክርስቲያኖች አስቀድመው ከሚነሱት ሙታን ጋር ጌታን በአየር ለመቀበል ይነጠቃሉ ነው።
"ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር እንነጠቃለን" ሲል ታዲያ ምን ማለቱ ነው? ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ብዙዎች እንደሚያስቡት በተለወጠ ተዳሳሽ አካላችን እንዳለን ወደ ሰማይ ሽቅብ እንተኮሳለን ማለቱ ነውን? "አየር" የተሰኘው ቃል ምን ማለት ነው? በዙርያችን ያለው ከባቢ አየር ነው ወይስ የምንተነፍሰው አየር?
አየር ተብሎ ጥቅም ላይ የዋለው ቃል ከጥንታዊ የግሪክ አማልክት ስያሜ ጋር የተያያዘ ነው። ግሪኮች ለአየር ouranos እና aer የተሰኙ ሁለት የተለያዩ ቃላት አሉአቸው። እዚህ ላይ እና በሌሎች ስድስት ቦታዎች ላይ የተጠቀሰው ይህ አየር የተሰኘ ቃል በግሪኩ aer የተሰኘው ሲሆን፣ ouranos የተሰኘው ግን በመላው አዲስ ኪዳን 284 ጊዜ ያህል ጥቅም ላይ እንደዋለ የግሪክ አዲስ ኪዳን መዝገበ ቃላት ያመላክታሉ። ይህ ouranos የተሰኘ ቃል ከግሪክ አማልክት መካከል አንዱ እንደሆነ የሚታወቀውን ከምድር በላይ ከዋክብትን ሰብስቦ የያዘውን የጠፈሩን የአየር ክፍል፣ ይኸውም ሰማዩን ወይም ህዋውን የሚገዛው አምላክ ስያሜ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ በዋለበት ቦታ ሁሉ የሚያመለክተው በጠፈሩ ላይ የፈሰሱትን ሰማያዊ አካላትን ነው። በአንጻሩ ይህ aer የተሰኘው ቃል ግን የሚያመለክተው ከምድር ከፍ ብሎ ያለውን የመሬት ከባቢ የአየር ክፍል ሲሆን፣ ይኸውም የምንተነፍሰውን አየር የሚቆጣጠር የግሪክ አምላክ ስያሜ ነው። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ በጥንቃቄ የመረጠውና ጥቅም ላይ ያዋለው ቃል aer የሚለው ነው። የጣየር የግሪክ መዝገበ ቃላት "ታችኛው አየር" ሲል "ከላይኛው አየር" ወይም በከባቢ አየር ክልል ካለው የተቃርኖ ልዩነት ጋር ይተረጉመዋል።
እስቲ በኤፌሶን ምእራፍ 2 ላይ ያለው ቃል አየር ምን እንደሆነ አንዳች ሃሳብ ይሰጠን እንደሆነ እንመልከተው፦
ኤፌ 2፥ 2 በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።
አየር የተሰኘው ቃል ለሰማያዊው ወይም ለመንፈሳዊው አለም ግዛት / Spiritual realm/ ሌላው ቃል ነው። በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናየው፣ ሰይጣን ሁልጊዜ በወደቀው አለም ላይ የሚገዛ የዋጆአዊው እቅድ ተጻራሪና ጠላት ነው። በአየር ላይ ስልጣን ያለው አለቃ ነበር። እስቲ እነዚህን ደግሞ እዩአቸው፦
ራእይ 9፥ 1-2 "አምስተኛውም መልአክ ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፥ የጥልቁም ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። የጥልቁንም ጕድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ ፀሐይና አየርም በጕድጓዱ ጢስ ጨለሙ።"
ራእይ 16፥ 17 "ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ፦ ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ።"
በእጅጉ አቡቀለምሲሳዊ በሆነው የራእይ መጽሐፍ ውስጥ እነዚህ "ኮስሞሎጂካል" የሆኑ ፍጥረተ አካላትና በእነርሰም ላይ የሚፈጸሙ የፍርድ ተግባራት በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ስነ ፍታቴ ምንን እንደሚወክሉ በወጉ ካልተረዳን አየሩ ላይና ሰማዩ ላይ እንዳፈጠጥን ቃሉ የገባን መስሎን መሸወዳችን ነው።
በሮሜ 16፥ 20 ጳውሎስ ሲናገር ሰይጣን ከእግራቸው በታች "ፈጥኖ" ይቀጠቀጣል ይላል (የመጀመርያውን አውዳዊ ትርጉም አትርሱ፣ በሞትና በኩነኔ ኊይል በአሮጌው መስተዳድር /dispensation/ ላይ ይገዛና ይሰለጥን የነበረው ሕግ፣ ይሁዲነት ነው፣ እርሱም ሞትና ኃጢአት የነገሰበት የሙሴ ዘመን ነው)። አሁን ኢየሱስ በዳግመኛ ምጽአቱ ከኢየሩሳሌም ውድመት ጀምሮ ያንን ግዛት ነጥቆ በመውሰድ አየሩን ተቆጣጥሮታል። ግርማን በተሞልው ስልጣኑ ከቅዱሳኑም ጋር በአየሩ ላይ ይገዛል። ከሙታን የተነሳው ንጉሰ ነገስት ጌታችን ኢየሱስ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር የእርሱ ነው። የሞትና የሲኦልንም ኃይል ይዞአል። በስጋ ሁሉ ላይ ስልጣን ያለው እርሱ የሕይወት ጌታና ሰጪ ሆኖ በዙፋኑ ላይ አለ። አሁን በክርስቶስ የምንተነፍሰው አየር ጸጋና እውነት ነው። መንግስትና ግዛትም በዘመናት ወደ ሸመገለው ለቀረበው ለክርስቶስ ነው። ሃሌሉያ!! እንግዲህ ቅዱሳን የሚገናኙበት አየር ያው ራሱ የጌታችን አየር ነው። ይህ አየር በስጋዊ ሞት ምክንያት አይቋረጥም። ክርስቲያኖች አሁን የሚተነፍሱትን ጸጋና እውነት በስጋም ከሞቱም በኋላ ቀጥለው ይተነፍሱታል። ያ ከሆነ ደግሞ ንጥቀትን በተዳሳሹ አለም ህዋ ላይ እየተንሳፈፉ መብረር እንደሚሆን አድርገን ማሰብም ሆነ ማመን አያስፈልገንም።
ጌታ በዘመኑ እንደሚመለስ ጳውሎስ አስረግጦ ያምን ነበር። ስለ ዳግም ምጽአት፣ ስለ ትንሳኤ እና ስለ ፍርድም በጥብቅ ያስተም ነበር፤ በሕይወት ስላሉ ክርስቲያኖች አካላዊ ንጥቀት ግን ፈጽሞ አላስተማረም።
የሚነጠቀው ተዳሳሹ ሰጋ አይደለም። አማኝ በስጋው በሚሞትበት ጊዜ ከሞተ በኋላ ስጋውን ሲተው የሚነጠቀውና ወደ መንፈሳዊው አለም የሚሄደው ከርስቲያኑ ራሱ ነው። ጌታ በሚመለስበት ጊዜ አስቀድመው የሞቱ አማኞች ይነሳሉ፣ የተቀሩት ያልሞቱ ክርስቲያኖች ሁሉ ደግሞ በስጋቸው በሚሞቱበት ጊዜ ይነጠቃሉ። ይህ ነው የቃሉ ትምህርት።
2ቆሮ 5፥ 1 ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።
ንጥቀት የሚሆነው ምድራዊውን መኖርያችንን ስንተው እና ወደ መንፈሳዊው መኖርያችን ስንሄድ ያውም በሞታችን ጊዜ ነው። የዳነ ሰው ሞቱ ንጥቀቱ ነው።
ምጽአቱን ተከትሎ ሊሆኑ ስለሚገባቸው ጉዳዮች የሚናገሩ ሌሎች ተዛማጅ ምንባባትን ስንመለከት በማቴዎስ 24፥ 31 ላይ "ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ" የሚለውን፣ በ1ቆሮንቶስ 15፥23 "ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤" የሚለውን፣ በ1ተሰሎንቄ 4፥ 17 "ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን" የሚለውን፣ እንዲሁም በራእይ 14፥ 13 "ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው" የሚለውን እናገኛለን። እነዚህ ሁሉም እኩል ናቸው፣ ከእኛም ሕይወት ጋር ሊዛመዱ የሚችሉ ናቸው። ከሞትና ከሃደስ የመነጠቅ ወይም የመወሰድ እና በቀጥታ በሰማይ የመሰብሰብ ሂደት በ70 አ.ም ተጀምሮአል። "ንጥቀት" የሚጋመደው የሰማያዊውን ሰፍራ ኹነት ከሚናገሩ የንባብ ክፍሎች ጋር ነው። ሁሉም አማኞች በሚሞቱበት ጌዜ ሁላቸውም ይነጠቃሉ። "ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው" የሚለው የራእይ 14፥ 13 ቃል በአዲሱ ዘመን ማለትም በ70 አ.ም የተጀመረውን ቀጣይ ሁኔታ በግልጽ ያሳያል። እስከዚህ ዘመን ድረስ ዘልቆ የቀጠለውና ከቶሞ የማይቋረጠው ይህ መሰብሰብ የተጀመረው ጌታ ያኔ በዳግመኛ ምጽአቱ መንግስቱን በተቀዳጀ ጊዜና የሞቱ ቅዱሳን ከሃደስ የመውጣት ትንሳኤን ካገኙ በኋላ ነው።
ማጠቃለያ
የ"አካላዊ ንጥቀት" አሰተሳሰብ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ክፍል ሊገኝም ሆነ ትምህርቱም ሊሰጥ አይችልም። ይህንንም የሚደግፍ አንዳች የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅስ የለም። ይህ አስተሳሰብ "የአምላጮች ፍልስፍና" የሆነ ልብ ወለድ ብቻ ነው። በቅዱሳት መጻህፍት ትምህርት ውስጥ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ለበጎ እንደሚያደርገው እያወቅን (ሮሜ 8፥ 28-30) እንድንጋፈጠው እንጂ እውነታን እንድናመልጥና እንድንሸሽ አልተማርንም። በስጋ መሞትን ሁላችንም እንሞታለን፤ አይቀርልንምም። ይህንን እውነታ ተቀብለን በእምነት መቆም ብቻ ይበቃናል። "ስሞት ወደ ጌታ እሄዳለሁ" ነው መዝሙሩ!
የእብራውያን ጸሐፊ፦ "ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥እናውቃለን " ይላል፤ እብ 9፥ 27
አካላዊ ሞትን አናመልጥም፣ ሁላችንም አንድ ቀን ልናገኘው ቀጠሮ ይዘናል። በሥጋ በምንሞትበት ጊዜ ግን ወዲያውኑ ወደ ሰማያዊው መኖርያ እንነጠቃለን፣ በዚያም "ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን"።
1ተሰ 4፥ 18 ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።
ተስፋችን ከመሞታችን በፊት በሥጋችን ከምድር ላይ ሽቅብ እንደ ሮኬት መተኮስ አይደለም። ነገር ግን ተስፋችን በሥጋችን ስንሞት ወደ ሰማያዊው መኖርያችን እንነጠቅና በእግዚአብሔር ሃልዎት ፊት ለዘላለም ማደራችን ነው። "ሰለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ"፣ ይህ የሚጽናኑበት ቃል ጳውሎስ ያመለከታቸው እውነታ ነው። እርሱም አስቀድመው ለሞቱና በሲኦል ለነበሩ ቅዱሳን የተጠበቀው የሙታን ትንሳኤ ተስፋ እና በሕይወት ላሉ ምእመናን ሲኦልን ሳያዩ በሞታቸው ሰአት ሁልጊዜ ከጌታ ጋር ለመሆን በቅጽበት የሚወሰዱበት ተስፋ ነው።
እናንብብ፣ እንመርምር፣ እንጠይቅ፣ እንሞግት፤ በደቦ አንመን!!
ጸጋው ይብዛላችሁ!
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/
ጌታ ኢየሱስ ይባርክህ ውድ ወንድሜ በጣም ተጠቅሜአለሁ፡፡
ReplyDeleteጌታ ይባርክህ ወንድሜ
ReplyDeleteተባረክ
ReplyDelete