ክርስቲያን መምህራን በጥቅሉ በሚከተሉት የሥነ ሰብ አስተምህሮ፣ ሰው ስጋና ነፍስ/መንፈስ የሚባሉና በየራሳቸው ያሉ የተለያዩ የማንነት ክፍሎች ያሉት ፍጡር የመሆኑን ጽንሰሃሳብ በብዛት ተቀብለው ያስተምራሉ። በርግጥም ስጋና ነፍስ/መንፈስ የሚባል ርዕሰ ጉዳይ በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑ ብዙም አያከራክርም፤ የሁንና በመካከላቸው ያለውን ጉለህ ልዩነት ወይም አንድነት፣ እንዲሁም የመጨረሻ እጣ ፈንታቸውን በተመለከተ አብዛኛው ሰው የሚረዳበት መንገድ ብዙዎችን ሲያጠያይቅ ኖሮአል። በዋናነትም ነፍስ በርግጥ ከስጋ ሞት በኋላ በቀጣይነት ኢ-መዋቲ (immortal) ሆና በራስ አወቅነት (Consciously) ትኖራለችን? ይህንን አይነቱን አስተሳሰብስ በመጽሓፍ ቅዱስ መደገፉን ለመጠራጠር የሚያስችሉ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ይኖሩ ይሆንን? የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ነው።
[ኢ-መዋቲነት (immortality) ሲተረጎም፣ ያው 'አለመሞት' ነው፤ ይህም በሥርወ-ቃሉም ሆነ በትርጓሜው "መሞት አለመቻል” ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። አለመሞትም የአንድን ሰው ሕልውና በሞትም ቢሆን እንኳ የማይገደብ አድርጎ ማስቀጠል ነው። በተለመደው አነጋገር፣ ኢ-መዋቲነት ማለት "ከሞት በኋላ" (after death) እንደማለትም ነው፣ ዳሩ ግን ፍልስፍናዊ በሆነ አነጋገር ሁለቱ ጉዳዮች አንድና ተመሳሳይ ነገሮች እንዳልሆኑ ደግሞ ማስተዋል ያስፈልጋል። ከሞት በኋላ ያለው ሕይወት ቀጣይነቱ ያልተወሰነ ይሁን ወይም አይሁን ብቻ የነፍስ ኢ-መዋቲነት ከስጋ ሞት በኋላ የመኖር ቀጣይነት ነው። ኢ-መዋቲነት ማለት ክርስትና የሚሰጠው ተስፋ እርሱም የዘላለም ሕይወት፣ ማለትም ከሞት ነፃ መሆን፣ እና የማያልቅ ኑሮ፣ የማያልፍ ሕልውና ነው። በአንጻሩም አንዳንድ ዘመናዊ የሆኑ ዝርያዎች በተፈጥሯቸው ባዮሎጂካዊ የሆነ ኢ-መዋቲነት ሊኖራቸው እንደሚችል ይታሰባል። ያም ሆኖ ኢ-መዋቲነት ማለት፣ አካላዊው ሰውነት ሞተም አልሞተም ማለቂያ የሌለውን ሕልውና ያመለክታል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ አንዳንድ የሕክምና ቴክኖሎጂዎች በሚያቀርቡት ሳይንሳዊ መላምት ወይም ልበ-ወለድ ከሞት በኋላ ያለ ቀጣይነትን ባይሆንም እንኳ የአካል አለመሞት ተስፋን ይሰጣሉ።]
ከክርስቶስ ልደት በፊት ቀደም ብሎ በነበረው የግሪኩ አለም ታዋቂ በሆኑ የፍልስፍና ምሁራን የነፍስን ምንነት ለማብራራት የተደረጉ በርካታ ጥረቶች አሉ። ለምሳሌ ሆሜር የተባለው ፈላስፋ፣ 'ሶማ' የሞተ አካል ነው ሲል፣ ህያው የሆነውን አካል ወይም የአካል ክፍል ለመጥቀስ ግን 'ሜሌአ' የሚለውን ቃል ይጠቀማል፤ 'ሲይኺ' ደግሞ በአካል ብልቶች ውስጥ የሚኖር ዋነኛና አስፈላጊ የሆነ አቅም ሲሆን በእስትንፋስ አማካኝነት የሚታወቅ ህልውና ነው ይላል። 'ስይኼ' ሰውየውን ትቶ ከምድር በታች የሚሄደው በሞት ጊዜ ነው ሲልም ያምናል።
ምናልባት የነፍስን ተፈጥሮ ጠጋ ብሎ ለመረዳት በአይሁድ ሥነ ጽሁፎች ውስጥ የሚገኙትን የበለጠና የተራቀቀ ትንተና ተጠግቶ ማየት ያስፈልግ ይሆናል፤ የሆነ ሆኖ በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ ለድርጅት ማንነት (corporate identity) ከሚሰጠው ከፍተኛ ዋጋ የተነሳ ግለሰባዊ ማንነት (individual person) በእስራኤል ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በጊዜ ሂደት እያደገና እየሰፋ በመጣው ግንዛቤ ውስጥ ግን፣ ነፍስ የማንነታችን መደበኛ ቅርጸ-ቁምፊ (font) ወይም ልኬቱ ሆኖ የሚያገለግል ውስጣዊ ኃይል ነው፤ ወይንም ደግሞ ሕይወትን አልያም እራሳችንን ጥልቅ በሆነ እሴት፣ ተዛምዶ፣ ልብ፣ እንዲሁም ግላዊ መገለጫችንን የምንለማመድበት ጥራት ወይም መስፈርት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ነፍስ የሚታይ፣ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ነገር ስላልሆነ በትርጓሜው ባለ ብዙ ገፅታ እና የማይጨበጥና የማይዳሰስ አይነት ነው። ነፍስ የእኛ ውስብስብ የማንነታችን አንድ ክፍል ተደርጋ ትታያለች። ብዙ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያው ቋንቋ ወደ እንግሊዝኛ ሲተረጉሙ “ነፍስ” ከሚለው ቃል ይልቅ “ልብ” የሚለውን ቃል ሲጠቀሙም ይስተዋላሉ። በአይሁድ ልማድ ውስጥ ነፍስን ለመረዳት የሚቀርቡ በርካታ መግለጫዎች አሉ። የተለመደው የመነሻ ነጥብም ነፍስ እግዚአብሔርን የመገናኛ መስመር ከመሆን ያነሰ አይደለም፣ የሚለው ነው።
ከዚህ በታች በአስረጅነት የቀረቡትን ጥቅሶች ካተዋልን በየምንባባቱ የነፍስን ተፈጥሮና ባህርይ ለመግለጥ የተጠቀመበተን ዘይቤ ማያት እንችላለን፦
ኢሳይያስ 1፥ 14 “መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ።”
በዚህ ጥቅስ ላይ ጌታ በሰውኛ ዘይቤ ስናገር ራሱ ነፍስ ያለው መሆኑን እና መታዘዝ በጎደለው የእስራኤል ኃይማኖታዊ ልማድ እንዴት እንደተጎዳ ሰሜቱን ያጋራል። ተመልከቱ ነፍስ የከፉ ምግባር "ጥላቻን" እየገለፀች ሲሆን፣ "እንደተጨነቀች" እና በህዝቡ ድርጊት "እንደደከመችም" ተመላክቷል።
ኢሳይያስ 38፥ 15 " ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፥ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ።"
እዚህም ባለው ጥቅስ ላይ ነፍስ እንዴት ባለ ኃዘን ስሜቱ የሚነካ እንደሆነ ተጠቁሟል። ነፍስ “ምሬት” እያጋጠማት እንደሆነም ተመላክቷል።
ማርቆስ 14፥ 34 "ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው።"
ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ ስለ ነፍሱ ኃዘን ምን እያለ እንደሆነ እዩ፣ ነፍሱ እጅግ በጣም በኃዘን መጎዳትዋን ይገልጣል።።
ሚክያስ 6፥ 7 "እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጎች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? ወይስ የበኵር ልጄን ስለ በደሌ፥ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት እሰጣለሁን?"
ነፍስ ኃጢአት መሥራት ትችላለች ማለት ነው። ጥቅሱም ‘’ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ’ (ሕዝቅኤል 13፥ 19) ተብሎ እንደተጻፈ ነፍስ ኃጢአትን ትሰራለች ሲል ያረጋግጣል። ተመልከቱ፤ ነፍስ ሆነ ብላ በእቅድ ኃጢአትን ልትሠራ የምትችል እስከሆነ ድረስ ማድረግ ስለምትፈለገው ከፉ ሰራ መረጃን የምታዘጋጅ እና የምታደራጅ እንዲሁም የምታደርገውን ከፉ ስራ እንዴትና መቼ እንደምታደርገው፣ ምን እንደምታደርግ እና እንደማታደርግ ባሉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማድረግ ትችላለች ብለን መደምደም እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱ ድምዳሜ ደግሞ ነፍስ አእምሮን እና ፈቃድን የያዘች እንደሆነ እንድናምን ያደርገናል። ሰው መልካምን ለማድረግ ፈቃድ ወይም ፍላጎት ሊኖረው ይችል ይሆናል፣ አቅም ግን የለውም፤ ክፉውን ለማድረግ ግን በነፍስያው ውስጥ ዕምቅ አቅም ሸሽጎ ይዟል። ራሱ ውድቀት ከሆነው ከዚህ እውነታ አንጻር ስለ ፍቃድ ጽኑ እስራትና ባርነት ካልሆነ በቀር ሰለ ፈቃድ ነጻነት እና የትብብር አቅም መነጋገር ምንም ትርጉም አይኖረውም። በአስረጅነት ካነሳናቸው ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች ተነስተን ነፍስ በአእምሮ፣ በፈቃድ እና በስሜቶች የተሠራች እንደሆነ እንረዳለን።
ነፍስ ለሚለው በብሉይ ኪዳን ጥቅም ላይ የዋለው የዕብራይስጥ ቃል "ነፌሽ" (נֶ֫פֶשׁ / nephesh) የተተኘው ነው። አዳምን ሲያበጀው ቶራህ እንደሚናገረው "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።" (ዘፍጥረት 2፥ 7) ይላል። የነፍስን ገጽታዎች ለመግለጥ በአይሁድ ኃይማኖታዊ ወግ ውስጥም ከሚያገለግሉ ቃላት መካከል ይህ "እስትንፋስ" የሚለው ቃል አንዱ ነው፤ እርሱም ምንጩ ፈጣሪ ሲሆን፣ ፈጣሪ እንደማይዳሰስ ሁሉ ነፍስም የማይዳሰስ መሆኑን ያሳያል፤ ሕይወትንም ተንቀሳቃሽ /activate/ የሚያደርገው እና የፍጥረት ሁሉ ምንጭ ከሆነው አምላክ ጋር በህያውነት የሚያገናኘው ይኸው የነፍስ መንፈሳዊ ተፈጥሮ ነው። የአይሁድ መምህራን ሲያስተምሩ፦ "እግዚአብሔር አጥናፍ አለሙን እንደሚሞላ ሁሉ እንደዚሁ ነፍስም አካልን ሁሉ ትሞላለች። እግዚአብሔር እንደሚያይ ነገር ግን እርሱ በማንም እንደማይታይ ሁሉ እንደዚሁ ነፍስም ታያለች፣ እርሷ ግን በማንም አትታይም። እግዚአብሔር መላውን አለም እንደሚመግብ ነፍስም እንዲሁ መላውን አካል ትመግባለች። እግዚአብሔር ንጹህ እንደሆነ ሁሉ ነፍስም ንጽህት ናት። እግዚአብሔር በአጥናፍ አለሙ ውስጥ በሁሉ ስፍራ እንደሚኖር ሁሉ ነፍስም በአካል ውስጥ ታድራለች" ይላሉ።
በእብራይስጥ "እስትንፋስ" የሚለውን ለመግለጥ ሦስት ቃላት ጥቅም ላይ ውለዋል፣ እነርሱም፦ "ነፌሽ"፣ "ሩኼ"፣ እና "ነሻምባ" ናቸው። ይህ "ነፌሽ" የተሰኘ ቃል ከብዙ ትርጉሞቹ መካከል ሥጋን እና ነፍስን እንደ አንድ የማይነጣጠሉ አካላት የሚያመለክት ሆኖ፣ በእብራይስጥ "ሰው" (human being) እንደ ማለት ነው። "ነፌሽ" ወይም ሰው ፣ ከሁሉ በፊት እስትንፋስ ያለው ሕያው ፍጡር ነው። የአንድ ሰው ሕይወት በደሙ ውስጥም ሆነ በአተነፋፈሱ ውስጥ እንደሚኖር ነዋሪ ሆኖ ይታያል (ዘዳግም 12፥ 23፣ 24)፤ ስለዚህም በህጉ እንደተገለጸው፣ ደምን ማፍሰስ ወይም መብላት ፈጽሞ የተከለከለ ነው።
በአዲስ ኪዳንም ነፍስ ለተሰኘው ቃል የግሪኩ አቻ ሲይኺ (ψυχή / psychí) ሲሆን አንዳንዴም ሱኼይ ወይም ሱኼ ይሰኛል። አንዳንድ ሰዎች ነፍስ ከስጋ የመለየቱ ጽንሰ ሃሳብ ከግሪካውያን አስተሳሰብ የተቀዳና ክርስቲያኖች ከግሪክ ፍልስፍና ተውሰው የራሳቸው ያደረጉት ስህተት ነው ሲሉ ይከራከራሉ። እርግጥ ነው ግሪኮች ሰው በሚሞትበት ጊዜ ሲይኺ ሥጋውን ትታ ከምድር በታች ትሄዳለች ሲሉ ያምናሉ። ክርስቲያኖችም ይህንንው አስተሳሰብ ያስተጋባሉ። በእርግጥ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በጉዳዩ ላይ ምን ያስተምራል? በሞት ጊዜ የሰውየው ሥጋ ሞቶ መበስበሱ፣ ነፍሱ ግን በሼዖል ማደርዋ፣ እርሱም የሞት ጥላ መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም በግሪክ አስተሳሰብ ውስጥ እንዳለው አይነት ኦርቶዶክሳዊ የእስራኤል ሃይማኖት ተብሎ በሚጠራው ውስጥ፣ ከሞት በኋላ ለነፍስ የተለየ ቀጣይ ሕልውና እንዳለው አድርጎ የሚያስተምር ምንም ሀሳብ አይገኝም። እንደ አይሁዳዊው እምነት ከሆነ በሲዖል ማደር ያው መሞት በቻ ነው እንጂ ኢ-መዋቲነትን አያመለክትም። በአይሁድ ዘንድ ሞት የተፈጥሮ ዑደት አንድ ክፍል ተደርጎ ይወሰዳል፣ ይሁንና የሚሞተው ሰው እሱነቱን እስከወዲያኛው የሚያጣበት ስለሆነ ማንም ሰው ቢሆን ሞቱ ፍጹም ደስታን አይሰጠውም። ዘማሪውም በምስጋና ጸሎቱ ውስጥ "ወደ ጥፋት ብወርድ በደሜ ምን ጥቅም አለ? አፈር ያመሰግንሃልን? እውነትህንም ይናገራልን?" (መዝሙር 30፥ 9) ሲል የገዛ ሞቱ ምንም እንደማይጠቅመው ወይም እንደማያስደሰተው ለጌታ ይናገራል። ስለዚህ በአይሁዳዊው አስተሳሰብ ሞት የሁሉም ስሜታዊ ሕይወት መጨረሻ እንደሆነ ይታሰባል። ሰውየው ራሱ ሞተ እንጂ በተናጠል ነፍሱ ሞተ፣ ሥጋው ሞተ የሚባል ነገርም በአይሁድ ዘንድ አይታሰብም።
በብሉይ ኪዳን ነፍስ (nephesh) የተሰኘው ቃል አጠቃቀም አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ከነፍስ ሞት ጋር የተያያዘ ነው፤ /በእርግጥም ይህ nephesh የተሰኘ ቃል በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከ750 ጊዜ በላይ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ200 ጊዜ በላይ የሚሆነው ከመሞት ጋር የተያያዘ ነው። ከብዙ በጥቂቱ ለምሳሌ ቀጥሎ የቀረቡትን እነዚህን ምንባባት ብናመሳክር ነፍስ ከሞት ጋር የተቆራኘች እንደሆነ እናያለን፦
"በዚያም ቀን ኢያሱ መቄዳን ያዛት፥ እርስዋንና ንጉሥዋንም በሰይፍ ስለት መታ፤ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ከእነርሱም አንዱን ስንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ እንዳደረገ በመቄዳ ንጉሥ አደረገ።" ኢያሱ 10፥ 28፤
"ዕለት ዕለትም በቃልዋ ነዘነዘችው አስቸገረችውም፥ ነፍሱም እስከ ሞት ድረስ ተጨነቀች።" መሳፍንት 16፥ 16፤
"ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅ መታነቅንና ሞትን መረጠች።" ኢዮብ 7፥ 15፤
"ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ።" መዝሙር 33፥ 19፤
"አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ታይልኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው ብችነቴንም ከአንበሶች አድናት።" መዝሙር 35፥ 17፤
"ለቍጣው መንገድን ጠረገ፤ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥ እንስሶቻቸውንም በሞት ውስጥ ዘጋ፤" መዝሙር 78፥ 50፤
"ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።" ኢሳይያስ 53፥ 12፤
"ውሸታችሁን ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት ትገድሉ ዘንድ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን ነፍሳት በሕይወት ታኖሩ ዘንድ ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቍራሽ እንጀራ በሕዝቤ ዘንድ አርክሳችሁኛል።" ሕዝቅኤል 13፥ 19፤
"እነሆ፥ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፤ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።" ሕዝቅኤል 18፥ 4፤
nephesh የተሰኘው የእብራይስጥ ቃል አንዳንድ ጊዜ ነፍስ ከሚለው የተለየ ትርጉም ይዞ የሚገኝበት ጊዜ አለ። በእነዚህ ከላይ በቀረቡ ምንባባት የአማርኛውም ሆነ የእንግሊዝኛው ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነፍስ የሚል ቃል በጉልህ ባይታያችሁ እንኳ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትና የእብራይስጥ ብሉይ ኪዳን የጥቅስ ማውጫ መርጃ መጻህፍትን ተከትለን ጥቅሶችን በጥንቃቄ ብናነባቸው፣ ይህ nephesh ወይም ነፍስ የሚለውን ቃል በምንባባቱ ውስጥ መኖራቸውን እናስተውላለን።
በርካታ ሰዎች ከፍጥረታት መካከል ነፍስ ያለው ሰው ብቻ እንደሆነ አድርገውም ያስባሉ፤ ነገር ግን በዘፍጥረት መጻሐፍ ላይ እንስሳትን እንኳ ነፍስ እንዳላቸው እናያለን። በበርካታ ስፍራዎች፣ ለምሳሌ ዘፍጥረት 1፥ 21፣ 24፣ 30 nephesh የሚለውን ቃል ከእንስሳትም ጋር ተገናኝቶና በቋሚነት ህያው ፍጥረት ወይም ህይወት ተብሎ መተርጎሙን እናየዋለን።
አንዳንድ ሰዎች ስነ ሰብን (anthropology) ሲተነትኑ ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ አለው ሲሉ ሰውን በሦስት መደብ ከፍለው ያዩታል፣ እነዚህ በአመለካከታቸው ትራይኮቶሚስት ይባላሉ። ጥያቄው ግን ይህ አይነቱ አመዳደብ ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው? የሚል ነው። በእርግጥ ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ የተባሉ ቃላት በአንድ ላይ ተጠቅሰው ጥቅም ላይ ሲውሉ የምናይበት ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በአዲስ ኪዳን ይገኛሉ፣ ለምሳሌ 1ኛተሰሎንቄ 5፥ 23 "የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።" ይላል። በእውነቱ ግን ይህ በራሱ እኛ በአፈጣጠራችን ሦስት መደብ ያለን መሆናችንን አያረጋግጥም። እነዚህ ሦስት ቃላት ጥቅም ላይ የዋሉት የሁለንተናን ፍጽምና አጽንዖት ለመስጠት ነው። መንፈስ እና ነፍስ የተሰኙት ቃላት የአንድን ሰው መንፈሳዊ ይዘት ለማመልከት በተመሳሳይ ጥቅም ላይ ሲውሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይስተዋላሉ። ቃላቱ እዚህና በእብራውያን 4፥ 12 ላይ በአንድነት ሲታዩ በያዙት ትርጉም ምንም አይነት የተለየ ትርጉም ልናገኝባቸው አስቸጋሪ ይሆናሉ። በተለዋጭ መጽሐፍ ቅዱስ በማርቆስ 12፥ 30 ላይ ሌሎች አራት የሚሆኑ መደቦችን ሲገልጥ "ልብ"፣ "ነፍስ"፣ "አሳብ"፣ እና "ኃይል" ሲል መጥቀሱንም አስተውሉ። ታዲያ መደበኛው የስነ ሰብ ምዳቤ የትኛው ነው?
በአዲስ ኪዳንም ነፍስ (Ψυχή / psyche) ማለት "ህይወት" መሆኑን እና ሊሞት፣ ሊገደል ወይም ሊጠፋ የሚችል መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ምንባባት ያሉ መሆናቸው ግልጽ ነው። ለምሳሌ ቀጥሎ ያሉትን ምንባባት ተመልከቱ ፦
“ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።” ማቴዎስ 10፥ 28፤
“ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው።” ማቴዎስ 26፥ 38፤
“ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ።” ሐዋርያት 3፥ 23፤
“ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።” ያዕቆብ 5፥ 20፤
“ሁለተኛውም ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፥ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ።” ራዕይ 16፥ 3
psyche የተሰኘው የግሪክ ቃል (ወይም የቃሉ አመጣጥ) በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከ100 ጊዜ በላይ ተደጋግሞ የሚገኝ ሲሆን ከመሞት ጋር በተገናኘ ደግሞ ከ30 ጊዜ በላይ እየተደጋገመ ጥቅም ላይ ውሏል። "ኢ መዋቲ" (immortal) የተሰኘው ቃልም ሆነ ጽንሰሃሳብ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ"ነፍስ" ጋር ተጋጥሞ የሚገኝበት አንድም ስፍራ የለም። ለእብራይስጡና ለግሪኩ ቃላት ብዙ ዓይነት አጠቃቀሞች ያሉ በመሆናቸው ምክንያት ይህ ትንታኔ እና ድምዳሜ ግራ አጋቢ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የማስረጃው ቀዳሚነት በእርግጥም ነፍስ ከስጋ ተለይታ የምትኖር አካል አለመሆንዋን ያመለክታል። ከዚያ ይልቅ ነፍስ ሕይወት ወይንም የሕይወት ትርጉም ናት ማለት ነው። ስለዚህ ነፍስ ማለት አንድ ሰው ‘አለኝ’፣ ወይም ‘የኔ’ ከሚለው ነገር በላይ በብዙ የሚያሳየው ራሱ ሰውየውን፣ የሆነውን ወይም ማንነቱን ነው፣ ማለትም እሱነቱ ነው።
ስለዚህ፣ ኢ መዋቲ የሆነ ነፍስ ከሥጋ ሰውነት ተለይቶ ወይም ራሱን ችሎ በራሱ የሚኖር አካል ነው የሚለው መደበኛ የሆነውና የተለመደው እይታ በራሱ ችግር ያለበት ነው። ይህ እይታ በአብዛኛው ራሱን ያቆመው ደካማ በሆኑ ግምቶችና መላምቶች ላይ፣ ወይም በወጉ ባልተብራራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ላይ በተደገፈ ልማድ ብቻ ላይ ሲሆን፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በሆነ እንግዳ የፍልስፍና አስተሳሰብ ተጽዕኖም አርፎበታል። እንግዲህ የነፍስ ኢ መዋቲነት ጽንሰ አሳብ በበርካታ ክርስቲያኖች ዘንድ የተቀዳው ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ከግሪክ አስተሳሰብ እንደሆነ እናያለን።
ይህ ከሆነ ታዲያ ክርስቲያን የሆነ ሰው በሥጋው አካላዊውን ሞት ሲሞት ምን ይሆናል? በዚህ ነጥብ ላይ በክርስቲያኖች ዘንድ ግራ የተጋቡ አመለካከቶች ይስተዋላሉ። የሚበዛው ክርስቲያን ማህበረሰብ አመለካከቱ አማኝ በሚሞትበት ጊዜ ነፍሳችን "ከጌታ ጋር ልትሆን" ትሄዳለች ሥጋችን ግን እስኪነሳ እና በሰማይ ካለችው ነፍሳችን ጋር እስኪገናኝ ድረስ የመጨረሻውን የትንሣኤ ቀን በመቃብር ሆኖ ይጠብቃል የሚል አመለካከት አላቸው። በዚህ አተያይ "ከጌታ ጋር" የመሆን ጉዳይ በትክክል ብዥታ ያጠላበት ነገር ነው። ከጌታ ጋር መሆን በሰማይ ወይም ሰማይ ባልሆነ ሌላ ስፍራ ሆኖ አንዳንድ ጊዜም የሆነ በጊዜያዊነት የሚቆዩበት ወይም መካከለኛ ስፍራ ወይም ግዛት እንደሆነም ተደርጎ ይታሰባል። አንዳንዶችም፣ ከሞት በኋላ እስከመጨረሻው ፍርድ ድረስ ሁሉም ሰው ያንቀላፋል፣ ከዚያ በኋላ ክርስቲያን የሆኑ እያንዳንዳቸው በትንሳኤ ወደ ሰማይ ወይም ያላመኑቱ በፍርድ ወደ ገሃነም ያላካሉ ብለው ያስባሉ። አማኞች ሞተው ሲቀበሩ በቀብር ስርአታቸው ላይ ሰባክያን የሚሉት ቀዋሚነት የማይታይበት የተለያየ ነገር ብዙዎችን ግራ ያጋባል። ሟቹ ሰው አማኝ ከሆነ ሰባኪው "ወንድማችን አሁን በሰማይ ነው" ወይም አሁን "ከጌታ ጋር ነው" ሲል ሊደመጥ ይችላል። ሟቹ በሰማይ ነው ቢል እንኳ፣ ጉዳዩን አለፍ ብሎ ሊያስረዳ ሲሞክር ሰውየው በእርግጥም ገና በሰማይ እንዳልሆነ ነገር ግን "በመጨረሻው ቀን እስኪነሳ" ወይም እስከመጨረሻው ቀን ድረስ በጊዜያዊ የማቆያ ስፍራ እንዳለ አድርጎ ሊያስብ ወይም ሊናገር ደግሞ ይችል ይሆናል። በዚህ ጉዳይ ቤተክርስቲያን በታሪክ ውስጥ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ስታስተናግድ ኖራለች። የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንም ፑርጋቶሪ የምትለው ነፍሳት ከአንዳንድ ኃጢአቶቻቸው እየነጹ የሚቆዩበት ስፍራ የሆነ አንዳች ጽንሰሀሳብ ፈልስፋ ታስተምራለች፤ እንዲህ ያለው አስተሳሰብና ትምህርት ግን በተሃድሶው ወቅት በወንጌላውያን የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የተወገዘ ትምህርት ሆኗል። ስለ ነፍስ የሚደረግ እንዲህ ያለ አጭር ውይይትም በምንደርስበት መደምደሚያ ላይ ጥላውን ያጠላል።
“አዳም ሲፈጠር የሰው ልጆች በሥጋ እንዳይሞቱ ወይም በአካላዊ ሁኔታ ለዘላለም እንዲኖሩ ሆነው የተፈጠሩ ነበሩ፣ መዋቲ የሆኑት በውድቀት ጊዜ ነው” ብሎ ማሰብም ፈጽሞ ስህተት ነው። መበስበስን እንዳያይ የተስፋ ቃል የነበረው እግዚአብሔር አዘጋጅቶት በድንግል ማርያም ማሕጸን ያደረው የኋለኛው አዳም የኢየሱስ ክቡር ሥጋ ብቻ ነው (ሐዋርያት 2፥ 27፣ 31፤ 13፥ 35)። እብራውያን 9፥ 27 ሰው ከመነሻው ሟች እንደሆነ ሲያመለክት አዳምን ጨምሮ ለሰዎች ሁሉ አንድ ጊዜ መሞት እንደተመደበ ይናገራል፤ ይህንን በኢዮብ 14፥ 5 እና በመዝሙር 139፥ 16 ካለው ጋር በማመሳከር ብናነበው ሰው ለምን በሥጋ እንደሚሞት ግልጽ ያለና አውዱን የጠበቀ ማብራርያ ይሰጠናል ስለዚህ ከቅዱሳት መጻህፍት ትምህርት ጋር የማይታረቀውን በልማድ ላይ የተመሰረተ የማናቸውንም የቤተክርስቲያን ምሁር ነኝ ባይ ትንታኔ ማስቆም ይገባል። ተዳሳሹ አካላችን እንደሆነ ወደ አፈር ሊመለስ ከአፈር ተሰርቷል፣ አለቀ! (ዘፍጥረት 2፥ 7፤ 3፥ 19፤ መዝሙር 90፥ 3)፤ እንሞታታለን እንጂ በአየር ላይ ተንሳፎ መሄድ የለም። ሥጋችንም ከዚያ ያለፈ ምንም የመጨረሻ ዕድል የለውም። በኃጢአት ወደቀም አልወደቀም፣ በበሽታ ተይዞ ወይም በሌላ በማናቸውም ሰበብ በአካላዊው ሞት ማለፍ የሰው ተፈጥሯዊ እጣ ፈንታውና፣ እግዚአብሔር ተገቢ እንደሆነ አስቦ በዘላለማዊ እውቀቱ ወስኖ ያዘጋጀው ነው፤ ተረት አትመኑ፣እውነታው ይሄው ነው።
ካስተዋልነው ከአዳም ኃጢአት አስቀድሞ አዳምና መላው ሕያው ፍጥረት ሁሉ በህይወት የሚኖሩ ብቻ ሳይሆን የሚሞቱም ደግሞ ነበሩ። ልማዳዊ በሆነው ነገረ መለኮትና ትምህርተ ሰብ ውስጥ ይህንን ማስተዋል ብዙዎች እንደሚቸግራቸው ግልጽ ነው፤ ዳሩ ግን የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመርያዎቹ ጥቂት ምዕራፎች ላይ የሚደረግ ጥልቅ የቃሉ ጥናት ይህንን በብዙ ማስረጃ ያረጋግጣል። እግዚአብሔርም ፍጥረታትን ሁሉ ከፈጠረ በኋላ የፈጠረውን አዳም በገነት አኖረውና ህይወቱን ማቆየት ይችል ዘንድ ከሕይወት ዛፍ ፍሬ እንዲበላ እድል ሰጠው። ይህ እውነታ ብቻውን አዳም ከውድቀቱ በፊትም እንኳ ሊሞት የሚችል እንጂ ኢ መዋቲ እንዳልሆነ ይነግረናል። እንደተቀሩት ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ አዳምም እንኳ መመገብ ያለበት መኖር እንዲችል ነው፣ ካልበላና ሥጋውን ካላበረታ ተርቦ ይሞታል። ካልሆነ ግን ሆድ ለምን አስፈለገው? ሆድና አጠቃላዩ የምግብ መፈጨት ሥርዓት ደግሞ ከአዳም ውድቀት አስቀድሞም እንኳ ነበር። ኃጢአትን ባደረገ ጊዜ ግን ወደ ሕይወት ዛፍ እንዳይደርስ ነው የተከለከለው፣ "አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤" (ዘፍጥረት 3፥ 22) ይላልና። ስለዚህ ሥጋዊው ሞት ለአዳምም እንኳ የተፈጥሮ ዑደት ነው እንጂ በአዳም ውድቀት ሰበብ የመጣ አይደለም።
እንደ ዘፍጥረት 3፥ 19 እና 2፥ 7 ከሆነ አዳም ስሪቱ አካላዊውን ሞት እንዲሞት ተደርጎ ነበር። ውድቀት ከመከሰቱ አስቀድሞ እንኳ ሰው ከምድር አፈር ለአፈር የተፈጠረ፣ ወይንም ወደአፈር ሊመለስ አስቀድሞ ተወስኖ ከምድር አፈር የተሰራ ነበር። ተመልከቱ አዳም ሲፈጠር የተሰራው ከምድር አፈር ነው፣ ሲወድቅም ያው አፈር ነው፤ ስለዚህ አፈርነት፣ ማለትም አፈር መሆን ከመጀመርያ የነበረ ነገር ነው እንጂ የውድቀት ውጤት አይደለም። ለአዳም መሬታዊነት ተፈጥሮው ነው እንጂ የደረሰበት የውድቀት ደረጃው አይደለም፤ የልቁንም በውድቀት ጊዜ አዳም የደረሰበት የሞት አይነትና ደረጃ ግን መንፈሳዊው ሞት ነው። በዘፍጥረት 3 ላይ አዳምና ሄዋን ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ በልተው አይኖቻቸው ሲከፈቱ፣ ከራቁትነታቸው የተነሳም ሲያፍሩና እርቃናቸውን ለመሸፈን ሲጥሩ የነበረውን ሁኔታ ስንመለከት፣ ከእግዚአብሔር መለየት የተባለውን ሞት የሞቱት ያኔ እነደሆነና፣ እነርሱም መሞታቸውን አውቀውት እነደነበር እናስተውላለን። ምላሻቸውም እግዚአብሔር ሲቀርባቸው እየሸሹ እና ከፊቱ ለመሰወር እየጣሩ የተገኙበት ነበር። አዳም የሞተው የኃጢአት ሞት ይህ ነበር። በሮሜ 6፥ 23 ጳውሎስ ሲያስተምር "የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው" ይላል። ይህ ሞት አካላዊው ሞት ቢሆን ኖሮና በክርስቶስ በማመን የቀረልንና ይቅር የተባልነው ሞት ቢሆን ኖሮ ታዲያ እስካሁን አካላዊውን ሞት ለምን እንሞታለን? ጉዳዩ ከሥጋዊው ሞት ጋር የተገናኘ ከሆነ እንግዲያውስ ከሥጋዊው ሞት ለማምለጥ ክርስቶስ ከከፈለው በላይ ምን የቀረ ሌላ ያልተከፈለ ዕዳ ይኖር ይሆን? እኛስ ገና ያልሞትን የሞታችንን ቀን እየጠበቅን ነው እንጂ ያው በወረፋችን መሞታችን አይቀርም፣ በከረስቶስ አምነው የሞቱ በርካታ የምናውቃቸው ዘመድ ወዳጆቻችን በወረፋቸው የሞቱትኮ መሞት የተፈጥሮ ዑደት ስለሆነና በከረስቶስ ማመናቸው የሥጋ ሞትን ስላላስቀረላቸው ነው። ጳውሎስ ግን የሚያወራው አዳም ስላለፈበት አይነት የኃጢአት ሞት፣ እርሱም የተከለከለውን ዛፍ ፍሬ በበላበት ቀን ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ሕብረት ስለተቋረጠበት የሞት አይነት እንጂ ስለ ሥጋዊው ሞት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ይሁንና ግን በስተመጨረሻ ያለን ዕድላችን በአዲሱ የከበረ አካል ሆነን ወደ ሰማይ የምንገባ መሆናችን ሲሆን፣ ይህም አማኞች ያላቸው የመጨረሻ ተስፋና ዕድል ፈንታ ነው። ይህንን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ለማወቅ ፍላጎቱ ያላችሁ በተለያየ አቀራረብ የጻፍኳቸውን ጽሁፎች በብሎገሬ http://gizachewkr.blogspot.com/ ገብታችሁ እንድትመለከቷቸው እጋብዛለሁ።