Sunday, December 8, 2024

የሕዝቅኤል ዳሰሳ


የሕዝቅኤል መጽሐፍ እጥጥር

አነሳሴ በሕዝቅኤል እና በዮሓንስ ራእይ ስለ ጎግ ማንጉግ የተሰጠውን ትምህርት ማጥናት እና በዚህ በኛ ዘመን ርዕሰ ጉዳዩን አስመልክቶ በስፋት የተሰራጨውን የዞረበት የመጻኢነት ስሁት ትምህርት ውድቅ ማድረግ ነው። ይሁንና የተነሳሁበትን ዋና አላማ ጠብቄ በጠቅላላ በሕዝቅኤል መጽሓፍ ላይ መለስተኛ እጥጥር በዳሰሳ መልክ ማቅረብ እንዳለብኝ የሰማኛል። ዳሰሳውም በስድስት ንኡስ ርዕሶች ዘርዘር ብሎ እንደሚከተለው ይቀርባል፦ 

  • በዚህ ዳሰሳ ክፍል አንድ መግቢያውንና የመጽሃፉን አከፋፈል አስቀደሜ፣ ስለ ጎግ ማንጎግ በመጠኑ አነሳለሁ፤ 
  • አስከትዬ በክፍል ሁለት የመጽሃፉ አብይ ትምህርት የሆነውን “እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” የተሰኘውን ርእሰ ጉዳይ ከሕዝቅኤል ራእይና መልዕክት ጋር አጣምሬ አቀርባለሁ፤ 
  • በመቀጠልም በዳሰሳችን ከፍል ሦስት የሕዝቅኤል መጽሐፍ መንፈሳዊ ጠቀሜታ ምን እንደሆነና የመንፈሳዊ አገልግሎት ፍላጎትና አቅርቦትን አመለክታለሁ። 
  • በክፍል አራት ዳሰሳችን ደግሞ የሕዝቅኤል መጽሐፍ የእግዚአብሔርን ወሰን አልባነት፣ የክርስቶስንና የአካሉንም ሁሉን አቃፊነት የሚገልጥልን መሆኑን ጨምሬ እንድናይ አደርጋለሁ። 
  • በክፍል አምስት ጥናታችንም በመጽሓፍ ቅዱስ የአጋግን እና ስለ አጋጋዊው ሐማ የተነገረውን አንስቼ በክፍል አንድ ካነሳሁት የጎግ ማንጉግን ትርክት ጋር ያለውን ግንኙነት በማውሳት ጉዳዩን እቋጫለሁ። 
  • በመጨረሻም በክፍል ስድስት ላይ የሕዝቅኤልን መንፈሳዊ መልዕክት፣ ስለ ከተማይቱ ቅጥር፣ ስለ በሮቿ እና ስለ መሠዊያው እንዲሁም በማጠቃለያችን በሕዝቅኤል ውስጥ ያለውን ወንዝ እና በራዕይ ውስጥ ያለውን ወንዝ በንጽጽር ተመልክተን የዳሰሳውን እጥጥር እደመድማለሁ።

gkr


ክፍል አንድ

መንደርደሪያ

ሕዝቅኤል የስሙ ትርጉም "እግዚአብሔር ያበርታል" ማለት ነው። ሕዝቅኤል ገና በወጣትነቱ በኢየሩሳሌም ባለው ቤተመቅደስ ካህን የመሆን ዕድል እና መብት የነበረው ወጣት ነበር። ያ ከመሆኑ በፊት ግን በምርኮው ዘመን በግዞት ወደ ባቢሎን ተወሰደ። በዚያም የነብይነት አገልግሎትን ተቀበለ። ሕዝቅኤል በነብይነት ያገለገለው ነብያቱ ዳንኤልና ኤርምያስ ያገለግሉ በነበረበት ተመሳሳይ ጊዜ ነው።  

አንዳንድ መጻህፍት በባህርያቸው ለመነበብ የማያስቸግሩ አይነት ሆነው ቶሎ ግን የሚረሱ አይነት ናቸው። ሌሎች ደግሞ ለመነበብ አስቸጋሪ ይሆኑና በያዙት ቁም ነገራቸው ግን በአንባቢዎቻቸው ህይወት በቀላሉ ሊረሱ የማይችሉ አይነት ሆነው ይቀራሉ። የሕዝቅኤል መጽሐፍ በባህርዩ የሚመደበው እንደዚህ እንደ ሁለተኛው አይነት ካሉት መጻህፍት ተራ ነው።

ባለፉት ብዙ መቶ ዘመናት መጽሐፉን አንብቦ ለመረዳት በአንባቢዎች ዘንድ የታዩ በርካታ ተደጋጋሚ መሰናክሎች ታይተዋል። ይሁንና ግን አንባቢዎች መሰናክሎቹን ተቋቁመው መጽሐፉን በማንበብ መልእክቱን ለማስተዋል ተችሏቸው ከፍ ያለ ብድራትን አግኝተውበታል። የሕዝቅኤል መጽሐፍ በቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና ውስጥ መካተት አለበት ወይስ የለበትም በሚለው ጉዳይ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በነበሩ ምሁራን የአይሁድ ረቢዎች መካከል ክርክር ተካሂዶ እንደነበር ይታወቃል። ሃኒና ቤን ሕዝቅያስ የተባለ የአይሁድ ምሁር ረቢ የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ተቀባይነት ደግፎ ይሟገት ነበር የሕዝቅኤልን መጽሐፍ በባልደረቦቹና በተቃዋሚ ምሁራኑ ፊት ለመከላከል ሲል መጽሐፉን ቁጭ ብሎ እያደረ ሲያጠና ላበራው የመቅረዝ ብርሃን ሦስት መቶ ማድጋ ዘይት እንደፈጀ ይነገራል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመጽሐፉ ላይ ብዙ ተንታኞች መልእክቱን ለመረዳት የተቸገሩበትን ስሜት ይገልጹ ነበር። ኤ.ቢ. ዴቪድሰን የተባለ የብሉይ ኪዳን ሊቅ ሲጽፍ “የዚህ መጽሐፍ ተማሪ የሆነ ማንም ሰው ቢሆን ተገቢውን ጥናት ያደርግ ዘንድ በተወሰነ የተሸናፊነት ስሜት ውስጥ ሆኖ የሚሰራውን ማናቸውንም ነገር መተው አለበት” ብሏል።

እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ድረስ ባለው የሥነመለኮት ጥናት፣ የሕዝቅኤልን መጽሐፍና መልዕክቱን ሙሉ በሙሉ የመረዳት ችግር በብዙዎች ዘንድ እንደተስተዋለ በርካታ የቃሉ ተማሪዎች ተረድተዋል። ነገር ግን ሁልጊዜ ባይገለጽም እንኳ ከሕዝቅኤል መጽሐፍ ጋር ተፋጠው ለማንበብና ለማጥናት የሚጋዱሉ ሰዎች ከገጠሙት ትግል ብዙ ባለጠግነትን ማትረፋቸው እውነት ነው፣ አይካድም። ምክንያቱም ሕዝቅኤል በሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻህፍት ውስጥ የእግዚአብሔርን ባሕርይ በተመለሉተ በቀላሉ የማይገኘውን ማስተዋል ያቀርብልናል። የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ከማንበብ ጀምሮ ያለውን ተግዳሮት ማወቅ ብልህነት ነው፤ ነገር ግን በትግዳሮቱ ምክንያት መጽሐፉን ለማንበብ ፈቃደኛ አለመሆን ደግሞ ሞኝነት ነው። መልእክቱን ፍፁም በሚባል ደረጃ ጠንቅቀን ልንረዳው የስቸግረን ይሆናል፣ ነገር ግን ለማንበብብን ለማጥናት በምናደርገው ጥረት እጅግ በጣም እንባረክበታለን።

የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ለመረዳት ከሚያስቸግሩ ጉዳዮች መካከል ቢያንስ ቋንቋውን፣ ምልክቶቹን እና ትዕምርታዊ ምስል ከሳች አጠቃቀሙን የመተርጎም ነገር ነው። ኖርማን ፔሪን የተባለ ሰው በአንድ ወቅት የሳይንስ ሊቃውንት የራዕይ መጽሐፍን በመረዳት ረገድ ባሳዩት መላምት ያጋጠሟቸውን ችግሮች ሲናገር “ገጣሚዎች፣ አርቲስቶች እና የስነ ጥበብ ባለሙያዎች ግን መጽሐፉ እጅግ አድርጎ ከፍተኛ ስሜት ቀስቃሽና ኃይለኛ የሆኑ ምስል ከሳች ምልክቶችን ስለሚጠቀም ለስነ ጥበባቸው የማያልቅ የመነሳሳት ምንጭና ግብዓት ሆኖ አግኝተውታል”፣ ሲል ገልጾ ነበር። በሕዝቅኤል መጽሐፍም ያለው እውነታ በተወሰነ መልኩ ያው ተመሳሳይ ነው። በርካታ ሊቃውንትም ባዘጋጇቸው ጽሑፋዊ ትንተናዎቻቸው በሕዝቅኤል የተነገሩ ትንቢቶችን በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ በሚወጡ የጋዜጦች ላይ የፊት ለፊት ትኩስ የአለም ዜና ክንውኖች ጋር ለማዛመድና ቃሉን ለመተርጎም በሚያደርጉት ሙከራ ተቸክለው ራሳቸውን አቂለዋል። ከእነርሱ ይልቅ ግን “የሚዞሩ መንኮራኩሮች” እና “የደረቁ አጥንቶች” እያሉ ሲዘምሩ የኖሩ ቆየት ያሉ የተወሰኑ መንፈሳውያን ዘማሪዎች የሕዝቅኤልን መልእክት ሕያውነት ይበልጥ ተጠግተው እንደነበር ይታመናል ። የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ተምሳሌታዊነት እና ምሳሌያዊነት፣ የመልእክቱንም ምሥጢር እና ሕያውነቱን ገልጦ ለመረዳት፣ ጠንቃቃ በሆኑት የትንቢት አንባቢዎች መካከል ይህ የበለጠ የተገለጠ ነው። የትኛውንም ትንቢታዊ የሆነ መጽሐፍ በተለይም ሕዝቅኤልን ለማንበብና ለመረዳት ተገዳዳሪ ከሆኑ ፈተናዎች መካከል የተወሰኑ ቦታዎችን እና ምስሎችን የመለየት ጉዳይ ዋነኛው ነው። ጎግ እና ማጎግ (ምዕ. 38-39) ምንድን ናቸው? አዲሱ ቤተ መቅደስስ (ምዕ. 40-43) ምንን ያመለክታል? እነዚህ ትንቢቶች የሚፈጸሙትስ መቼ እና በማን ነው? የሚሉት በዚህ ረገድ የአንባቢዎችን ትኩረት የሚስቡ ሁለቱ ምሳሌዎች ሲሆኑ፣ በዚህ ዳሰሳም ትኩረት ያልተነፈጋቸው ናቸው።

የሕዝቅኤል ትንቢቶች፣ ባመዛኙ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ያልተለመደ እና በእንስሳት ተፈጥሮና ባህርይ የታጀበ ገጸ ባህሪያትን ይጠቀማል። በአብዛኛው ትንቢቶቹንና መልእክቶችን በንግግር ብቻ ከመግለጥ ይልቅ ራሱ ሆኖ ተውኔታዊ በሆነ አቀራረብ ይጫወታቸዋል። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ከማለት ይልቅ እግዚአብሔር ሊል የፈለገውን ሆኖ፣ ለመልእክቱም ሥጋና አካል ሰጥቶ መልዕክቱን ማስተላለፍ ከመናገር በላይ ስቃይና ህመሙ ላቅ ያለ ነው።  ይህ በተለይ የህዝቡ ጆሮ ደንቁሮ መስማትን እምቢ ሲል ትኩረታቸውን ለመሳብ በእጅጕ ያገለግላል። የሕዝቅኤል መልእክቶች በሕዝብ ዘንድ እምብዛም ተወዳጅነት ያልነበራቸውና ሊሰሟቸው የማይመርጧቸው አይነት ከመሆናቸውም በላይ መልእክቶቹን ወደ ህዝቡ ለማድረስ እንኳ ለራሱ ለነብዩም አስቸጋሪ አይነቶች ነበሩ። አንድ ሰው ስለ ሌላው ሰው ኃጢአት በሥጋው ሲሰቃይ መስማትና ማየት የሚፈልግ ማን ሰው አለ? የሕዝቅኤል የነብይነት ጥሪ ያንን ስቃይ መቀበልንም የሚጨምር ነበር። የነብይነት ጥሪው የሚጠይቀውን መታዘዝ ለመፈጸምና መልዕክቱን ለማስተላለፍ እስከ ምን ጥግ እንደሄደ ማሳያ የሚሆኑ ምሳሌዎችን እንመልከት፦

  • ቆሞ የእግዚአብሔርን መልእክት ተቀብሏል (2፡1) 
  •  በቤቱ ውስጥ ራሱን ዘጋ፣ ታሰረ፣ ድዳም ሆነ (3፡24-27)
  • የእግዚአብሔርን መልእክት ለአመጸኞቹ በታማኝነት ሰበከ (3፡27) 
  • የኢየሩሳሌም ከተማን በሸክላ ጽላት ላይ ስሎ መከበቧን ለማሳየት በሚያፈርስ ግንድ እና በብረት ምጣድ ቅጥር አደረገባት (4፡1 ጀምሮ)
  • በግራ ጎኑ ለ390 ቀናት ተኛ (4፡4፣ 5)
  • በቀኝ ጎኑ ለ40 ቀናት ተኛ (4፡6)
  • በተወሰነ መልኩ የእስራኤልን ተግሳጽ ለማሳየት እንግዳና ዘግናኝ የሆነ የምግብ አዘገጃጀትና የአመጋገብ መመሪያዎችን ተከትሏል (4፡9-17)
  • የሚመጣባቸውን መለኮታዊ ፍርድ ለማሳየት ራሱንና ጢሙን በተሳለ ጎራዴ ተላጨ (5፡1-4)
  • ምርኮውን ለማሳየት እንደስደተኛ እክትን ተሸክሞ ከቤት ወጥቶ ከስፍራ ወደ ስፍራ ተጓዘ (12፡3-7)
  • ሐሰተኛ ነቢያትን እያጋለጠ በእነርሱም ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ተናግሯል (13፡1 ጀምሮ)
  • በእስራኤል አለቆች ላይ ሙሾን እያወረደ እስራኤል የደረሰባትን ጥፋት አመለከተ (19፡1 ጀምሮ)
  • በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ላይ ትንቢት ተነግሯል (21፡2)
  • የባቢሎን ንጉሥ በሟርቱና በሰይፉ በኢየሩሳሌምና በአህዛብ ነገስታት ላይ ጦሩን ለማዝመት የሚመጣናቸውን ሁለት መንታ መንገዶች አዘጋጅቷል (21፡19-23)
  •  በሚስቱ ሞት እንዳያዝን እና እንዳያለቅስ መመሪያን ተቀብሎ ተገበረው (24:16, 17)

በእውነቱ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ እና ፈቃዱን ለማድረግ የተጠራ ሰው አንዳንድ ጊዜ እርሱም ሆነ ያለበት ማህበረሰብ በቀላሉ የማይረዱትንና የማይገባቸውን መንገድ እንዲሄዱ ይደረጋሉ፤ ሕዝቅኤል የሆነው እንደዚያ ነው። በጊዜው የተነሱ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት እየሩሳሌም አትፈርስም፣ የምርኮውም ጊዜ አጭር ነው ሲሉ በግልጽና ብድፍረት ይናገሩ ነበር፤ አድማጭ ተመልካቾችም ነበሯቸው። በተቃራኒው፣ ሕዝቅኤልና ኤርምያስ የተነበዩት ግን ፍጹም ከዚህ የተለየውን ነው።

በዘሌዋውያን 26 እና ዘዳግም 28 ላይ ያሉት በረከቶች እና እርግማኖች ፍጻሜአቸውን እያገኙ በሥራ ላይ መዋል ጀምረው ነበር። ሕዝቡም እግዚአብሔርን አይታዘዙም ነበር፣ በዚህም ምክንያት በናቡከደነፆር እና በባቢሎናውያን ሠራዊት በኩል የሚሰራው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ፍርድ በእነሱ ላይ መጣ። ህዝቡም ያንን አስቸጋሪ እውነት መጋፈጥ ነበረባቸው፤ በደረሰባቸውም ፍርድ እግዚአብሔር አምላክን በማያውቁ ህዝቦች መካከል በባቢሎን ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ በግዞት እንዲቀመጡ ሆኑ።  

በሚገርም ሁኔታ በአዲስ ኪዳናችን የሚገኘው የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የሕዝቅኤልን የትንቢት መጽሐፍ እንደገና የክርስቲያን መጽሐፍ አድርጎ ደግሞ የጻፈው ይመስላል። የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ በውስጡ ከሕዝቅኤል መጽሐፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተወሰዱ 130 የሚያህሉ ማጣቀሻዎችን ይዟል። በሥነጽሁፍ ዘውጋቸው አቡቀለምሲሳዊ የአጻጻፍ ዘይቤ ያላቸው እነዚህ መጻህፍት ሁለቱም በባህርያቸው የቃል ኪዳን ክሶች ናቸው። በአቡ ቀለምሲሳዊ ባህርያቸው በአመዛኙ ከትንቢታዊነት ለየት የሚያደርጋቸው ሁለቱም ለፍጻሜአቸው ከገዛ ራሳቸው ትውልድ የዘለለ የሩቅ ዘመን ፍጻሜን የማያመለክቱ የመሆናቸውን ያህል በቃል ኪዳናዊ ክስ ይዘታቸውም እስራኤል የሁለቱም ትኩረታቸው መሆንዋ ነው። በዚያውም ልክ ሁለቱም ተመሳሳይ የሆነ መሰረታዊ መዋቅር አላቸው። የእያንዳንዱ መጽሐፍ የመጀመሪያ አጋማሽ የእስራኤል ዘሥጋ ጥፋትን ያመለክታል፣ በሁለተኛው አጋማሽ ግን በእያንዳንዱ መጽሐፍ አዲሲቱና ቅድስቲቱ ኢየሩሳሌም በውበቷና በግርማዋ ደምቃ ትታያለች። የህንን የመጽሓፍቱን ውቅር እና ምስስል ቆየት ብለን እንመለስበታለን፤ ለአሁኑ ግን የሚከተለውን ዝርዝር ለራሳችሁ አጥንታችሁ በሁለቱ መጻህፍት መካከል ያለውን ዝምድና መወስን እንድትችሉ ዝርዝር ነጥቦችን ላንሳላችሁ፦

  1. የዙፋኑ ራዕይ፤ (ሕዝቅኤል 1 እና ራዕይ 4) 
  2. መጽሃፉ፤ (ሕዝቅኤል 2-3 እና ራዕይ 5) 
  3. አራቱ መቅሰፍቶች፤ (ሕዝቅኤል 5 እና ራዕይ 6፥ 1-8) 
  4. ከመሠዊያው በታች ስለነበሩ ሰማዕታት፤ (ሕዝቅኤል 6 እና ራዕይ 6፥ 9-11) 
  5. የእግዚአብሔር ቁጣ፤ (ሕዝቅኤል 7 እና ራዕይ 6፥ 12-17) 
  6. የቅዱሳን ግንባር መታተም፤ (ሕዝቅኤል 9 እና ራዕይ 7) 
  7. ከመሠዊያው የወጣው ፍም፤ (ሕዝቅኤል 10 እና ራዕይ 8) 
  8. ወደፊት አይዘገይም፤ (ሕዝቅኤል 12 እና ራዕ 10፥ 1-7) 
  9. መፅሐፉን መብላት፤ (ሕዝቅኤል 2 እና ራዕይ 10፥ 8-11) 
  10. የቤተመቅደሱ መለካት፤ (ሕዝቅኤል 40-43 እና ራዕይ 11፥ 1-2) 
  11. እየሩሳሌም እና ሰዶም፤ (ሕዝቅኤል 16 እና ራእ 11፥ 8) 
  12. የቁጣው ጽዋ፤ (ሕዝቅኤል 23 እና ራዕይ 14) 
  13. የምድሪቱ ወይን፤ (ሕዝቅኤል 15 እና ራዕይ 14፥ 18-20) 
  14. ታላቂቱ ጋለሞታ፤ (ሕዝቅኤል 16 ፣ 23 እና ራእይ 17-18)
  15. ስለ ከተማይቱ የቀረበው የልቅሶ ሙሾ፤ (ሕዝቅኤል 27 እና ራዕይ 18) 
  16. የእግዚአብሔር የሰደቃ ድግስ፤ (ሕዝቅኤል 39 እና ራዕይ 19) 
  17. የፊተኛው ትንሳኤ፤ (ሕዝቅኤል 37 እና ራዕይ 20፥ 4-6) 
  18. ከጎግ እና ማጎግ ጋር ጦርነት፤ (ሕዝቅኤል 38-39 እና ራዕይ 20፥ 7 -9) 
  19. አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፤ (ሕዝቅኤል 40-48 እና ራዕይ 21) 
  20. የሕይወት ውሃ ወንዝ፤ (ሕዝቅኤል 47 እና ራዕይ 22) 

የሕዝቅኤል መጽሐፍ የኋለኞቹ ምዕራፎች ከዕዝራ፣ ከነህምያ፣ ከዘሩባቤል እና ከአስቴር ዘመን ታሪክ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። በእስራኤል ታሪክ የምርኮው ዘመን የነብያቱ ትንቢትና ራእያቸው መተርጎም ያለበት የምርኮው ዘመን መጻህፍት በሆኑት የብሉይ ኪዳን ታሪክ አውድ ውስጥ መሆኑን ማወቅ ይገባል። ለምሳሌ፣ በመጽሐፈ አስቴር ሀማ በመባል የሚታወቀው ገጸ ባህርይ በሕዝቅኤል 38፥ 11-15 ባለው ክፍል ከተገለጠው ግለሰብ ባህርይ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ልብ በሉ። ልብ ብላችሁ ካስተዋላችሁት፣ አስቴር 9፥16 ላይ ያለው ከሕዝቅኤል ምዕራፍ 38-39 ካለው ጋር በጥሩ ሁኔታ ይዛመዳል። 

ጎግ፣ በሕዝቅኤል 38-39 የማጎግ ምድር ገዥ ተብሎ የተገለፀው ነው። ጎግ በትንሿ እስያ የሚገኙ የሁለት ነገዶች የሞሣሕ እና የቱባል ምድር “ዋና አለቃ” ነው (የማጎግ ልዩ ቦታ ግን በካርታ ላይ አይታወቅም)። ጎግ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የድንበር ቦታዎች የአሕዛብን ጥምረት እየመራ እስራኤልን ለማጥቃት እንደመጣ (ሕዝ. 38.5-6) ​​በእስራኤል አምላክ በያህዌ ተጠቅሷል። ያም ሆኖ ያህዌ እስራኤልን ወክሎ ጣልቃ በመግባት የጠላቶቿን ጥምረት በአስደናቂ የኮስሞቲክ ነውጥ ለማጥፋት ቃል ገብቷል (ሕዝ. 38.19-23)። በራዕይ መጽሐፍም ስለ “ጎግ እና ማጎግ የተነገረው አመልካችነቱ ከተቀጠረው የሺህ አመት መንግስት ዘመን በኋላ ሰይጣን ቅዱሳንን ሊዋጋ በቅዱሳን ሰፈርና በተወደደችው ከተማ ላይ ያስከተተውን ወረራ” (20.7-10) ነው። 

ላድ የተባለ የዮሐንስ ራእይ ላይ ማብራሪያ የጻፈ የመጻኢያን ጎራ ጸሐፊ ስለ ጎግ እና ማጎግ ውክልና ሲናገር፦ “ጎግ እና ማጎግ በእግዚአብሔር ላይ ለሚያምፁ እና ሕዝቡን ለሚቃወሙ አሕዛብ የተሰጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስያሜዎች ናቸው”፤ ይላል። በመቀጠልም፣ “በሕዝቅኤል. 38፡ 1፣ ጎግ የማጎግ ምድር አለቃ ሲሆን በኋለኛው ዘመን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ሊዋጋ ከሰሜን ይመጣል”፣ ሲል የመጻኢነቱን ምልከታ ያጠናክራል። “በራዕይ መጽሐፍ ውስጥም ሁለቱም ቃላቶች የእግዚአብሔርና የቅዱሳኑ ጠላት የሆኑትን አህዛብን ያመለክታሉ”፣ ይላል። ላድ ጨምሮ በማብራሪያው፣ “አዲስ ኪዳን ስለ ጊዜያዊ መሲሐዊ መንግሥት የሚናገረው ጥቂት ቢሆንም፣ የሕዝቅኤል ትንቢት ግን ራዕይ 20 ላይ ካለው ጋር አንድ ዓይነት መሠረታዊ መዋቅር አለው። ምዕራፍ 36-37 ያለው የእስራኤልን መዳንና፣ ወደ ምድራቸው ተመልሰው በመሲሐዊ ድነት መባረካቸውን ያሳያል (36፥ 24-29 ያለውን ይመለከቷል)። ‘ሕዝቤ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ’ (ሕዝ. 36፡28) የሚለው አምላካዊ ቃልም የትንቢታዊውን ቃል ፍጻሜ የመጠባበቅ አይነተኛ ግብ ሲሆን፣ እርሱም አሁን እውን ሆኗል። የእግዚአብሔር ባርያ ዳዊትም በሕዝቡ ላይ ይገዛል፣ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ያድራል (37፡25, 28)”። ሆኖም ይላል ላድ፣ “ይህ ግን የመሲሐዊው መንግሥት በረከት መጨረሻ አይደለም። ከማጎግ በተነሳና በጎግ በሚመራው የፍጻሜ ጦርነት የመሲሁ መንግሥት እንደገና ይታወካል (ምዕራፍ 38-39)። ከመለኮታዊ ድል በኋላ ብቻም ዘላለማዊ አዲስ ስርዓት እንደ ሚመሰረት የሚያሳይ ምስል እዚህ ላይ አለን፤ ይህም ዘላለማዊ አዲስ ስርዓት በሕዝቅኤል መጽሐፍ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ እንደገና ከተገነባው ቤተመቅደስ አንፃር ተብራርቷል (ምዕራፍ 40-48)” ይልና፣ “ይህ የጊዚያዊ መሲሃዊ መንግሥት መዋቅር እና ዘላለማዊ መንግሥት አዲሱን ዘመን በምንተዋወቅበት በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ከተገለጠው ጋር አንድ ነው”፤ ይላል። ይህ የላድ ማብራሪያ በአመዛኙ የበርካታ መጻኢያንን አቋም ሊያንጸባርቅ እንደሚችል አስባለሁ። ይህንን የራእይ ትንቢት እና ፍጻሜውን በተመለከተ ቆየት ብለን እንመለስበታለን፣ እንደ ሕዝቅኤል መጽሐፍ ሁሉ በራዕይ መጽሐፍ የተነገረው የጎግ ማንጉግ ወረራ የሚቀለበሰው በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ተነግሯል። በዚህ ጥናት የራእይን መጽሐፍ የትንቢት ፍጻሜ ገና ወደፊት ይሆናል ብሎ ጠባቂ ለሆነው የመጻኢነት ምልከታ መጽሓፍ ቅዷስዊ ግባተ መሬቱን እንሰጠዋለን። አሁን ግን ትኩረታችንን በሕዝቅኤል ላይ አድርገን ጥቂት እንግፋ።

ጎግ እስራኤልን የወረረበት አንዱ ምክንያት የዕብራውያንን ከብቶች፣ ብርና ወርቅ ለመዝረፍ ነበር። በንባብ ክፍሉ ውስጥ ስለ ነዳጅ ዘይት ምንም የተጠቀሰ ነገር የለም። መላው የጎግ ወታደሮች በፈረሰኞች ላይ ተቀምጠው ይመጡ ነበር እንጂ ከእነርሱ ማናቸውም በሚሊቴሪ የመጓጓዣ መኪና፣ በታንክ፣ በሄሊኮፕተር ወይም በአውሮፕላን የሚዘምቱ አልነበሩም። ይልቁንም የጎግ ወታደሮች በቀስት፣ በፍላጻ፣ በዱላ፣ በጎራዴ፣ በጦር ብቻ የሚዋጉና በእንጨት ጋሻ ብቻ የሚመክቱ ነበሩ። በራሪ ድሮንም ሆነ ተወንጫፊ ሚሳኤል፣ የእጅ ቦንብም ሆነ፣ የሞርተር መትረየስ ወይም አር.ፒ.ጂ፣ የነፍስ ወከፍ ጠብመንጃም ሆነ መድፍ ወይም ፈንጂ እና የኒውክለር አረር የተጠመደባቸው ተቀጣጣይ ፈንጂዎች ወዘተ አልነበራቸውም። ከዚህ ይልቅ ግን እግዚአብሔር በአስደናቂ የኮስሞቲክ ነውጥ ካጠፋቸው በኋላ እነዚያ ድል ነሺዎች ከእንጨት የተሰሩ የጎግን የጦር መሳሪያዎች ለሰባት አመታት በእሳት አቃጥለዋቸዋል። በዛን ጊዜ ኤሌክትሪክ፣ ጋስ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ሞተሮች ወይም በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ማሽኖች ነበሩአቸውን? ፈጽሞ አልነበራቸውም። እንዲህ ያሉ መላ ምቶችን በመጽሓፉ ውስጥ እየሰነቀረ በቀጥታ ለዘመነኛው ዘመናችን እንደሚናገር አድርጎ የሚዘባርቀው ልማዳዊው የመጻኢነት አስተምህሮ ነው። አንድ ሰው ግን በቀላሉ ከምዕራፍ 38 - 39 ያለውን ምንባብ በአጠቃላይ በዐውደ-ምንባቡ አጥር ውስጥ ሊያነበው ከወደደ፣ ግልጽና ቀጥተኛ የሆነው የንባብ ክፍሉ ትርጉሙ በማያሻማ ሁኔታ በራሱ በሕዝቅኤል እና በምርኮኞቹ ዘመን ውስጥ የሚፈጸም እንደሆነ ጥርት ብሎ የሚታየው ይሆናል። 

ሌላው የተሳሳተ ትምህርት በሕዝቅኤል 38፡ 2 ላይ “ሞሳህ” የተሰኘውን ቃል በተመለከተ የሚሰነዘረው አስተያየት ነው። ይህ ቃል በእንግሊዝኛ ትርጉሞች “ሮሽ” ተብሏል፤ የትንቢት መጽሓፍ አዋቂዎች ነን የሚሉ የዘመናችን ሃሰተኛ መምህራን ይህንን ሲተረጉሙ የዘመናችን ሩሲያ ማለት ነው ሲሉ ይዘባርቃሉ። ሮሽ የሚለው ቃል ግን በመሰረታዊነት የዕብራይስጥ ቃል ነው እንጂ በጥቅሉ የስላቪክ ቋንቋ [ሩሲያኛ፣ ዩክሬንኛ እና ቤሎሩሲኛ (ምስራቅ ስላቪክ)፣ ፖላንድኛ፣ ቼክ፣ ስሎቫክ እና ሰርቢያን (ምዕራብ ስላቪክ) ቡልጋሪያኛ፣ ሰርቢያኛ፣ ክሮኤሺያኛ፣ መቄዶኒያ እና ስሎቬንን የሚያጠቃልለውን በኢንዶ-አውሮፓ የቋንቋ ዘውግ (ደቡብ ስላቪክ) ውስጥ የሚታወቅ ቃል አይደለም]። ይህም የእብራይስጥ ቃል “ራስ” ወይም “የበላይ አለቃ” ማለት ሲሆን በመላው ብሉይ ኪዳን ውስጥ ከ600 ጊዜ በላይ ጥቅም ላይ ውሏል። አግባብነት ያለው የቃላትን ትርጉምና አጠቃቀም የተመለከተ ጥናት እንዲህ ያለውን ኢ- መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ መላምትን ጠርጎ ያስወግድልናል። ለምሳሌ “ሮሽ ሃሻናህ” የተባለውን የአይሁድን በዓል አስታውሱ? ሮሽ ሃሻናህ የሃሻና በዓል እርሱም የቀኖችና የአመቱ የመጀመሪያ ወይም ዋና ቀን ማለት ነው።  

በሕዝቅኤል 40 ላይ ከነቢዩ ንግግር የተወሰደው እጅግ የበለጸገ ምሳሌያዊ ገልጻ አዲሱን ቤተመቅደስ እና አዲሲቷን ኢየሩሳሌምን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። የአዲሱ ቤተመቅደስ እና የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ክብር ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ ክብር ይበልጣል። ነገር ግን ይህ በ21ኛውና በ22 ክፍለ ዘመን ስለሚሰራ ተዳሳሽ ቤተ መቅደስ እድሳት፣ በእርሱም ስለሚቀርብ የእንስሳት መሥዋዕት ፈጽሞ የሚናገር አይደለም። ምክንያቱም በምዕራፍ 43 ላይ እንስሶቹ የኃጢአት መሥዋዕት ናቸውና። እንደገና በሚሰራ መጻኢ አዲስ የአይሁድ ቤተመቅደስ የእንስሳት መስዋእት ይቀርባል ብሎ ማመንም ሆነ መጠባበቅ የክርስቶስን መስዋእታዊ ሞት ማክፋፋትና የተቀደሰ ደሙን መርገጥ ነው። እንዲህ ያለውን መንፈሳዊ ግልሙትና የሚያበረታታ መጻኢነትም ሆነ ዘመን ቆጣሪነት እንደወላጅ አባቱ የአሮጌው ኪዳን ሥርአት በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ወድቋል። 

ለሚያምኑ ሁሉ በጌታ እራት የታደለው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከእንስሶች መሥዋዕት ይልቅ እጅግ የከበረ ሆኖ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለዘላለም እንዲህ ያሉ መስዋዕቶችን ሁሉ ሸፍኗል (ዕብ. 8-10)። ሊቀ ካህናታችን ክርስቶስ በሰማይ ባለችው ቅድስት፣ በእግዚአብሔር ፊት ካቀረበው መስዋዕት ሌላ የኮርማዎችና የእንስሶች ደም ከእንግዲህ አያስፈልግም። ጊዜ መዳቢ የሆነው መጻኢነት ግን የሌለና ከእንግዲህም የማይሆን፣ አስፈላጊነትም የሌለውንና በክርስቶስ መስዋዕት የተሻረውን በተዳሳሽ ቤተመቅደስ የሚቀርብ የእንስሶችን መስዋእት በዞረበት ነገረ ፍጻሜው በምድራዊትዋ ኢየሩሳሌም እንደገና ይጠባበቃል። ጽዮናዊያን እንዳሰቡት ሆኖላቸው ህንጻቸውን ገንብተው መስዋዕታቸውን ማቅረብ ቢጀምሩ እንኳ እንዲህ ያለውን በክርስቶስ መስዋዕታዊ ሞት ላይ የሚደረገውን መዘባበት የሚዋጋው እግዚአብሔር ነው። አዲሲቱ ቤተመቅደስ እና አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ማለት ግን በክርስቶስ ያሉ የአማኞች ጉባኤ ማለት ናቸው። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16 “እናንተ ራሳችሁ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውስጣችሁ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?” ይላልና። 

ለሕዝቅኤል መጽሐፍ ሐተታ እንዲያመቻችሁ የመጽሃፉን አከፋፈል ልጠቁማችሁና ይህንን የጥናት ክፍል ላብቃ።

የሕዝቅኤል መጽሐፍ አከፋፈል

  •  የይሁዳ ውግዘት ምዕራፍ 1-24፡- 

¶ ከኢየሩሳሌም ከበባ በፊት 4 ዓመታት የተነገሩ ትንበያዎች - 592-588 ዓ.ዓ. . 

  •  የነቢዩ ጥሪና ተልእኮው (ምዕራፍ 1-3) 
  • የነብዩ ራዕይ-ምዕራፍ (ምዕራፍ 1፡1-28) 
  •  ድምጽ-ምዕራፍ (ምዕራፍ 2-3) 
  •  እየቀረበ ስለነበረው ፍርድ የተነገሩ ትንቢቶች (ምዕራፍ 4-7)  
  •  በምስል ከሳሽ አቀራረብ የተላለፈ (ምዕራፍ 4-5)  
  •  እንደሚፈጸም በግልጽ የተነገረ (ምዕራፍ 6-7) 
  •  ፍርድን ለመስጠት የሚያስፈልገው የሞራል አስፈላጊነት (ምዕራፍ 8-11) 
  •  የይሁዳ ጥፋተኝነት እና ቅጣቷ(ምዕራፍ 8-9)፣ 
  •  የኪሩቤል ራእይ (ምዕራፍ 10) 
  •  የመኳንንቱ ኃጢአት እና የንስሐ ተስፋ (ምዕራፍ 11) 
  •  የፍርድ ፍፁም እርግጠኝነት (ምዕራፍ 12-19) 
  • በትንቢት የተነገረው ምርኮ፣ እና በመሪዎቹ ላይ የተሰነዘረ ወቀሳ (ምዕራፍ 12-14) 
  •  የይሁዳ፣ ፍሬ አልባነት እና እምነት የለሽነት፣ ሲጋለጥ (ምዕራፍ 15-16) 
  • ውድቀቱ በግልጽ መብራራቱ፣ የሚገባ መሆኑና እና ልቅሶው (ምዕራፍ 17-19) 
  • የፍርዱ መንስኤ የይሁዳ ባሕርይ ነው (ምዕራፍ 20-24) 
  • የያህዌ ቸርነት እና የይሁዳ በደል (ምዕራፍ 20፡1-44) 
  • የያህዌ ሰይፍ ከሰገባው የተመዘዘ ነው (ምዕራፍ 20:45;- 21) 
  • የኢየሩሳሌም፣ የእስራኤል እና የይሁዳ ኃጢአት (ምዕራፍ 22-23) 
  •  የጽዮን ሴት ልጆች ውርደት (ምዕራፍ 23) 
  •  ምሳሌው እና ምልክቱ (ምዕራፍ 24) 

¶ የህዝቦች ጉብኝት በኢየሩሳሌም ከበባ ወቅት ሊፈጽም የተነገረ ነው 2 ዓመታት - 588-586  

  •  በአሞን ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 25፡1-7) 
  • በፍልስጥኤማውያን ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 25፡15-17) 
  •  በሞዓብ ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 25፡8-11) 
  •  በጢሮስ ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 26-28:19) "
  •  በኤዶም ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 25፡12-14) 
  •  በሲዶና ላይ የቱነገረ (ምዕራፍ 28፡20-26) 
  • በግብፅ ላይ የተነገሩ ሰባት ትንቢቶች (ምዕራፍ 29-32) 
  •  የእስራኤል ተሃድሶ ምዕራፎች (ምዕራፍ 33-48) 

¶ ከኢየሩሳሌም ከበባ በኋላ የተነገሩ ትንበያዎች -14 ዓመታት 

  • ስለ አዲሱ ሕይወት መሰጠት የተነገሩ ትንቢቶች ምዕራፎች (ምዕራፍ 33-39) 
  • ጉበኛውንና እረኞችን በተመለከተ የተነገሩ ትንቢቶች ምዕራፎች (ምዕራፍ 33-34) 
  • የእስራኤል፣ የሞራል ስነምግባር እና የአንድነቷ ተሃድሶ (ምዕራፍ 35-37)
  • በጎግና በማጎግ ላይ የተሰጠ ፍርድ (ምዕራፍ 38-39) 
  • የሚቋቋመው የአዲሱ ስርዓት መግለጫ ምዕራፎች (ምዕራፍ 40-48) 
  •  የቤተ መቅደሱ ራእይ (ምዕራፍ 40-43)
  •  ሕዝቡና ቤተ መቅደሱ (ምዕራፍ 43፡13፤-46) 
  •  ምድሪቱና ቤተ መቅደሱ (ምዕራፍ 47-48)

gkr

ክፍል ሁለት

እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ

መግቢያ

ለዚህ የሕዝቅኤል ትንቢት ርእስ ሊሆንለት የሚገባው፡- “እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ” የተሰኘው የመጽሐፉ ታዋቂና ተደጋጋሚ ሐረግ ነው። ይህ ሐረግ በመጽሐፉ ውስጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለ65 ጊዜ ያህል በመደጋገም ሲገኝ 26 ጊዜ ግን በቀጥታ ተገልጾአል። ሕዝቅኤል ነቢይ ለመሆን ልመጠራቱንና የጥሪውን ባህርይ አስቀድሞ ሳይረዱ ስለ ትንቢታዊ መጽሐፉ መረዳት አይቻልም። 

ሕዝቅኤል በከለዳውያን ምድር በኮቦር ወንዝ አጠገብ ከምርኮኞች መካከል የነበረ በምርኮው ጊዜ ተግዞ የመጣ ካህን ነበር።

ከምዕራፍ 1-3 ባለው የመጽሐፉ የመግብያ ክፍል ካህኑ ሕዝቅኤል ከክህነት መብቱና ስፍራው በጌታ የተሰናበተ ሆኗል ማለት እንችላለን፤ በዚህ ሁኔታ ሕዝቅኤል ሥራውን ያጣ፣ የክህነት መብቱን ያጣ፣ መቅደሱን ያጣ፣ ከተማውንና የተስፋይቱን ምድር ያጣ ሲሆን። ነገር ግን በጌታ እጅ ላይ እንደገና ነቢይ ይሆን ዘንድ ሹመትንና ተልእኮን ተቀብሏል። በዚህም ሹመቱና ተልእኮው አምላክ የለሽ በሆነ የጨለማ ምድር፣ በዚያ ወዳለ ደረቅ ምድረ በዳ ተወስዶ በምርኮ ያሉትን የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ኃጢአት እንዲሸከም ራሱን ሰጠ።

ሥራውን የማጣት ሁኔታ የገጠመው ይህ ካህን ቀድሞ የነበረውን ጥሪ ሊፈጽም እንዳይችል ሆኖ ተለያይቶ ነበር፣ ይሁንና ግን አዲስ የተቀባ ነቢይ እንደመሆኑ መጠን ስለ መጻኢው እጣ ፈንታቸው የተሳሳተ ተስፋ በነበራቸው ምርኮኞች ጉባኤ መካከል መገኘትና ማገልገል ነበረበት። የሚቆምበት ምስባኩ የኮቦር የወንዙ ዳርቻ ሲሆን የመኖርያ ቤቱ ደግሞ በዚያ የአሕዛብ ጨለማ ምድር ሽማግሌዎች ተሰብስበው ብርሃን ለማየት፣ የእግዚአብሔርን ምክር ለመጠየቅና ለመስማት የሚገናኙበት ስፍራ ነበር።

ነብዩ ሕዝቅኤል የትንቢታዊ አገልግሎቱ ምንጭና ውጤት ምን እንደሆነ የሚያብራሩ ቢያንስ አምስት የሚሆኑ ወሳኝ መግለጫዎች በመጽሐፉ ውስጥ አሉት። እነርሱም፦

¶ “ሰማያት ተከፈቱ”፤ 

¶ “የእግዚአብሔርን ራእዮች አየሁ”፤ 

¶ “የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሕዝቅኤል መጣ”፤ 

¶ "እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ" እንዲሁም

¶ “እግዚአብሔር በዚያ አለ” - (ያህዌ ሻማህ)፤ የሚሉት ናቸው።

በተከፈቱት ሰማያት እና እግዚአብሔር በዚያ በህያውነት ያለ አምላክ በመሆኑ መካከል በዚያ መለኮታዊ ሀልዎት ውስጥ የምናገኘው የሕዝቅኤል ራእይ፣ ነብዩ የእግዚአብሔርን ቃል የተቀበለበት ሁኔታ እና የነብዩ የሕዝቅኤልን የራሱን ታሪክ እንዲሁም በባቢሎን ግዞት ውስጥ ራሱ ከምርኮኞቹ አንዱ ሆኖ ምርኮኛ ለሆኑ ሰዎች ያደረሳቸውን መልእክቶች፣ መልዕክቱም በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌም እና በአንዳንድ የአህዛብ አገራትና ሰዎች ላይ የሚያሳድረውን አስከፊ ተጽእኖ፣ ከዚያም ለሰው ልጆች ሁሉ ሕያው ሆኖ የሚታደለውን፣ መንፈሳዊውንና ሰማያዊ የሆነውን መሲሐዊ በረከት ጭምር ነው። 

በሕዝቅኤል ሕይወት እና አኗኗር ላይ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ጥሪ አጽንኦት ሰጥተን ማየት ይኖርብናል፤ ምክንያቱም በከፊልም ቢሆን እሱ ራሱ ጌታ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የተናገረውን ለመረዳት እና እሱና ምርኮኞቹ ሁሉ ከርስታቸው ተነቅለው በባቢሎን የተገኙበትን ምክንያት ለማስረዳት አይሁድ በገሃድ ሊያዩትና ሊሰሙት የሚገባቸው መልእክት ነው። በሕዝቅኤል ህይወትና አገልግሎት ውስጥ ነብዩ ለምርኮኞቹ መልእክተኛ ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ በምርኮኞች መካከል ያለ ምርኮኛ መልእክተኛ ነው።

ሕዝቅኤል በትንሳኤ እግዚአብሔርን በክብር ለማየት እና ህያው የሆነ ድምፁን ለመስማት ወደ ሞት መውረድ ነበረበት። ነብዩ ሕዝቅኤል ራሱ በሕይወቱ የእግዚአብሔር መልእክት ነው የምንለውም በዚህ ምክንያት ነው። እርሱ ወደ ሞት እየወረደ መልእክቱን ለማሳየት እና ለማሰማት ኖሯል። ስለዚህም መሞት፣ መቀበር እና መነሳት እንደሆነ ሁሉ የሕዝቅኤል ታሪክና ህይወትም እንዲሁ ነው። ተመልከቱ፣ እስራኤል ፈርሳለች፣ ሞታለች፣ ከዚያም በባቢሎን መቃብር ተቀብራለች፤ ነገር ግን ደግሞ መቃብሮቿ ተከፍተው፣ ከሙታንም ወጥታ መቅደሱ፣ የልምላሜ ገነቱ ሆናለች፤ በውስጧም የሕይወት ውሃ ወንዝ የሚፈስባትና ያም ውሃ በሚፈስስበት ሥፍራም ሁሉ ህይወት እና ፈውስ ያለባት ሆናለች። ይህም የእስራኤል ፍጻሜዋ “ያህዌ በዚያ አለ”፣ የተሰኘው ነው፣ "እርሱም አለ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ናት!

ይህ ነቢይ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት ከቀደመው ርስቱ ከሥፍራው የተለየና በዚያ ሥፍራ ዋስትና እንዳላቸው ከሚመስላቸው ሁሉ ጋር ያልተደባለቀ ነቢይ ነው። ሕዝቅኤል ከተዳሳሹ፣ ምድራዊው ከሆነውና ከሚታየው ነገር መንፈሳዊ፣ ሰማያዊ እና እውነተኛ ወደሆነው የአገልግሎት ከፍታ መንቀሳቀስ ነበረበት። ከምርኮኞቹም ሕይወት ኃሰተኛ ተስፋዎችን ማስወገድና እውነተኛዎችን ተስፋዎች ማነቃቃት ነበረበት፤ ይህም የሕዝቅኤል አይነተኛ ሸክሙ ነበር። ከጌታ ዘንድ የሆኑ መሲሐዊ ተስፋዎችን ለማምጣት፣ የጌታ የክብር ዕቃ የመሆን ጥሪ ያላትን፣ አሁን ግን ምርኮኛ የሆነችውን ሀገር ወደ እውነተኛ መንፈሳዊ ተልእኮዋ ለመመለስ ተስፋ በማድረግ፣ የመንፈሳዊ ተሃድሶና የመልሶ ግንባታ ነቢይ ሆኖላታል።  

ዓለማዊና ኃሰተኛ ከሆኑ ምኞቶቻቸው ጋርም ምንም ትብብር ባለማድሩጉ፤ ምርኮኞቹ አይሁዶች ሕዝቅኤልን እንደ ሞኝ አድርገው ይመለከቱት ነበር፣፤ እንደ ዛሬው ባይሆንም፣ ነቢያቶቻቸው በቀደሙት ዘመናት ይናገሩ በነበረው ነገር ላይ ያን ያህል ተቃውሞ አልነበራቸውም ነበር። ለዛሬው ግን እንደ እንቅልፋም ውሾች ሆነዋል እንጂ ምንም የህይወት ራዕይም ሆነ ለብርሃን የሚሆን ሽራፊ መንፈሳዊ ፍላጎት አልነበራቸውም። የሕዝቅኤል አገልግሎት የደነቆሩ ጆሮዎችን መክፈት እና የእውሮችን አይን ማብራት ነው። ምርኮኞቹም በዚያ ሁኔታቸው ጌታ በነብዩ የሚናገረውን ወይም የሚያደርገውን ካልሰሙ ወይም ካላዩ መጨረሻቸው ወደ መጥፋት መውደቅ ነው። የነብዩን ቃል ካልሰሙ ብቻቸውን ይተዋሉ፣ በጨለማም ውስጥ ይርመሰመሳሉ፣ በጥፋት ውስጥ እንዲወድቁም ይገደዳሉ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ የሚያደርገውን የማያውቁ ሆነው ይቀራሉ።

ሕዝቅኤል የእስራኤል ትሩፋንን ከምርኮ ወደ መንፈሳዊ ድል ይመራ ዘንድ የተጠራ የተሃድሶ ነቢይ ነው። ይህም ጥሪ አዲሱን የክህነት ስርዓት ይጨምራል፣ አገልግሎቱ ግን በግዞት አገር ባለ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነበር እንጂ በኢየሩሳሌም አልነበረም። ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርን ርስት ባፈርሱት ምርኮኞች ርኵሰትና በኃጢአታቸው ላይ በግልጽ ይናገራል። እነዚያን የውሸት ተስፋዎቻቸውንና የማይፈጸሙ ናፍቆቶቻቸውን በመቃወምና በመገሰጽ ለእያንዳንዳቸውም በግል መታደስን ለማምጣት ይጋደላል። ሕዝቅኤል እነዚያን የውሸት ተስፋዎቻቸውንና በነዚህ ተስፋዎች በኩል የሚሰራውን ዕቅዳቸውን የሚያጋልጥ የቀንደ መለከት ድምጽ እና፣ ትምክህታቸውንና ትርክታቸውን ሁሉ ከአፈር ደባልቆ የሚፈጭ አውድማ ነው። ሕዝቅኤል በፍጥነት ከምርኮ የመመለሳቸውን የውሸት ተስፋ ለማስወገድ፣ ምርኮኞቹም የደረሰባቸውን ውድቀት ከባድነት ሳያውቁ፣ ገና በጨለማ ውስጥ እየተርመሰመሱ ሳሉ፣ ኢየሩሳሌም ከባቢሎን ጦርነት እንደምትተርፍ በከንቱ በመታመን፣ ብርሃንን ሳያዩ ስለ ብርሃን ሲናገሩ፣ እነዚያን ያልተሰበሩ አንገተ ደንዳና ምርኮኞችን በግልጽ ማነጋገር ነበረበት። ጉዳዩና አጀንዳውም መንፈሳዊ ጉዳይ እርሱም ሕይወትና ሞት፣ ጽድቅና ክፋት፣ በረከትና እርግማን፣ ምሕረት ወይም ፍርድ የሚል ነበር።

ትንቢታዊ ቃል ሲተላለፍ አይሁድ እንደ ሕዝብ በመጨረሻ የወደቁት በአንድ በኩል ተዳሳሽና ፊት ለፊት በሆነው፣ እንዲሁም በማይታየውና በሚታየው፥ በመንፈሳዊውና በአካላዊው መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ባለመቻልና ባለመረዳት ነበር፤ እንግዲህ የሕዝቅኤል ተግባር ይህንን በመግለጥ፣ እነዚያ በምርኮ የሚገኙ አይሁዶች በዚያ ባሉበት ሁኔታ ውስጥም ቢሆን እንኳ የመረዳትን ባለጠግነት አግኝተው የጌታን ድምፅ እንዲሰሙ ማድረግ ነበር። ሕዝቅኤል በአገልግሎቱ የእግዚአብሔርን ማንነትና እርሱም ለህዝቡ ለእስራኤል ያለውን የወደፊቱን ዓላማ በመግለጥ ታማኝ ነው። በዚህም እግዚአብሔር የሁሉ ጌታ እንደ ሆነ ህዝቡና መላው የእስራኤል ማህበር ያውቃሉ።

የሕዝቅኤል ትንቢቶች አምላክን በአንድ ልዩ ቅዱስ ስፍራ መገደብና መወሰን እንደማይቻል ያስተምሩናል። [እግዚአብሔርን በአንድ ሳጥን ውስጥ ማስገባትና መቆለፍ አይቻልም]። ሕዝቅኤል በጌታ ፊት ለመገኘት፣ ድምፁን ለመስማት እና ቃሉን ለመናገር እንደ አሮጌው ኪዳን ካህን በምድራዊ እና በቁሳዊ ቦታ ተወስኖ አልተከለከለም፤ የእግዚአብሔርን ራዕይ ለማየትም የግድ በኢየሩሳሌም በምድራዊው ቤተመቅደስ መሆን አላስፈለገውም። ሕዝቅኤል ጥሪው ከተስፋይቱ ምድር እና ከኢየሩሳሌም ርቀው ላሉ ምርኮኞች የእግዚአብሔርን ክቡር ዙፋን ይገልጥ ዘንድ ተጠርቷል። ስለዚህም አሁን ስፍራ በማይወሰነው የአጥናፍ ዓለሙ አምላክ በያህዌ እና በምድሪቱ መካከል ያለውን ትስስር እየፈታ ነበር። እግዚአብሔር ሕዝቡን፣ ከተማይቱንና ቤተ መቅደሱን ትቶ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጥቶአቸው ስለነበር፣ ራእዩም ወደ ሕዝቅኤል የመጣው ተነቅሎ ከተጋዘበት ከኢየሩሳሌም ሳይሆን ተማርኮ ከተወሰደበት ከሰሜን ነው። 

የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት በይሁዳ ውድቀት አይጎዳም፣ ምንም እንኳን ህዝቡ በባቢሎን አረማዊ ሕዝብ እንደ ባርያ ቢረገጥም የልዑል ዘላለማዊ ንግስናውና መንግስቱ ግን አይቀንስም፤ እርሱ በዙፋኑ ሰማያዊነት እና በንፅህናው ጸንቶ ይኖራል። ይህም ከሁሉ በላይ ከፍ ብሎ ያለው እውነተኛ መኖሪያውና መገኛው በምድር ሁሉ ላይ ላሉ ህዝቦች ቅርብ መሆኑን ለማመልከት ነው። የዙፋኑም ሠረገላ በክልልና በቦታ ሳይገደብ በአጥናፍ አለሙ ላይ እየሰፈፈ ወደ ወደደበት ይሄዳል።

ራእዩ እና መልእክቱ

እግዚአብሔር ለሕዝቅኤል የሰጠው ራእይና መልእክቱ ጌታ ከሰዎች ጋር ሊያደርገው የሚገባበትን የቃል ኪዳን ህብረት፣ በዓለምም ፊት ራሱን ለመቀደስ እና እርሱ በእውነት እንዳለ ለሁሉ ራሱን ለመግለጥ ያለውን ታላቁን ዓላማ ይገልጣል።

ይህ መጽሐፍ በአንድ በኩል የብሉይ ኪዳን ዘመን መዝጊያ፣ የነገሥታትና የመንግሥታቱ ፍጻሜ፣ [የአህዛብ ዘመን ፍጻሜ፣ የንጉሣዊው አገዛዝ የመጨረሻ ውድቀት፣ ለአይሁድም ዘመን እጅግ የከፋውን የመጨረሻ ምዕራፍ የሚያሳይ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አዲስ የትንቢት ድምጽ እና የሚመጣውን የተሻለ ዘመን መገለጥ የሚያበስር ነው። እንደ አሕዛብ ልማድ ንጉሥ እንዲኖራቸው የነበራቸው ምኞት ተሳካላቸውን? ሕዝቅኤል የዚህን ሁሉ ፍጻሜና የሚመጣውን አዲሱን መሲሐዊ ዘመን [የአዲሱን ኪዳን ዘመን]፣ እውነተኛ ንጉሥ ማንነትና መንግሥቱን ገልጦላቸዋል።

ሕዝቅኤል ለጉባኤው ያቀረበው መንፈሳዊ መግለጫ ከመልእክቱ ጋር እነሆ፦

በእግዚአብሔር መግቦት በምርኮ ወደ ግዞት የተወሰዱት ከእስራኤል ሕዝብ መካከል በጣም የተሻሉትና መልካሞቹ ነበሩ። የነቢያቱን የነኤርምያስን ትንቢት የናቁና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሆነው በኢየሩሳሌም የቀሩቱ በገዛ አገራቸው ለመቆየት ከባእዳን አለቆቻቸው ፈቃድ ያገኙ ዘንድ ማንኛውንም መሥዋዕት ለመክፈል ዝግጁ ነበሩ። እግዚአብሄርን የሚፈሩ ሰዎች ግን የከተማይቱ ጥፋት የማይቀር እንደሆነ በግልፅ አይተዋል። ነገር ግን የተሃድሶ አይቀሬነቱ አስፈላጊ ሁኔታ ነበር፤ ስለሆነም የመጀመሪያውን ጥሪ በፈቃደኝነት በመታዘዝ እና የህይወት ብቸኛ መግቢያ ለመሆን በደስታ ወደ ሞት ሄዱ።

ሕዝቅኤል ለምርኮኞቹ ባመጣው ኃይለኛ መልእክቱ ላይ ትልቅ ሸክም ያለው ሲሆን ይኸውም በኢየሩሳሌምና በባቢሎን ስላለው ሁኔታ ከሁሉ የተሻለው ማብራርያ በኤርምያስ ምዕራፍ 24፡1-10 ተገልጦ ይገኛል። ይህም ስለ መልካሙና እና ክፉው በለስ የተነገረው ነው። በተጨማሪም በምዕራፍ 29፡1-19፣ በምርኮ ምድር በግዞት ያሉ አይሁዶች ለሚቀጥሉት ሰባ የምርኮ ዓመታት ምን ማድረግና እንዴት መኖር እንዳለባቸው መመሪያን ይሰጣቸዋል። ልክ እንደ ኤርምያስ ሁሉ፣ ሕዝቅኤልም የተጠራው “እነሆ። ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ” ተብሎ ነው -

ሄንግስተንበርግ “እግዚአብሔር በጣም እንደረሳቸው የሚመሰክሩ የሚመስሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ፣ እነርሱም ፈጽመው (ከመቅደሱ) ተቆርጠው እና (በባዕድ አገር) እንዲቀመጡ ተደርገዋል፤ ቅድስቲቱን ምድር እና ቤተመቅደሱን ይዘው ከምርኮ የቀሩ ወንድሞቻቸውም በእነርሱ ላይ እጅግ የላቀ የንቀት ስሜት አሳይተዋል፣ ይዞታቸውንም እንደ አንዳች ትክክለኛ የመብት ማረጋገጫ ይመለከቱት ነበር። ይህ ሁሉ ግን በምርኮ የተጋዙትን ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸው ነበር፥ ሲል እንዳመለከተው ጌታ በባቢሎን የነበሩትን ምርኮኞች አይሁዶች አልረሳቸውም ነበር፡-

ጌታ ግን አሁን በኤርምያስ በኩል ለምርኮኞች የተናገረውን መልካም ቃል መፈጸም ጀመሯል (ምዕ. 24)፤ በመካከላቸውም እንደ መለከት ድምጽ፥ ድምጹን ከፍ አድርጎ ለእስራኤል ልጆች ኃጢአታቸውን የሚናገረውን፣ ቃሉም ባረፈባቸው ደስ በሚሉ ሕልሞቻቸውና ሥራዎቻቸው ሁሉ ላይ እንደ መዶሻ ወድቆ እየቀጠቀጠ፥ እንደ ዱቄትም የሚያደቃቸውን፣ በአቀራረቡም ሁሉ አሁንም እንኳ በዚህ የግዞት ሁኔታ ውስጥ ጌታ በሕዝቡ መካከል በህያውነት እንዳለ በሁለንተናው ጠንካራ ማስረጃ የሚያቀርበውን፣ እርሱ ራሱም የጌታ ቤተ መቅደስ የሆነውን፣ ያንን ቤተ መቅደስ ተብሎ የሚጠራውንና ለጥቂትም ጊዜ ቢሆን እንኳ ገና በኢየሩሳሌም ቆሞ የቀረውን ቤት በፊቱ በራሱ ምንም ማለት እንዳልሆነ በድፍረት የሚናገረውን፣ ይልቁንም ጠንካራ፣ ግዙፍ በሆነው ተፈጥሮ ብርቱዎችና አስፈሪ፣ ግዙፍና ጨካኞች የሆኑ የባቢሎንን የዘመናት መናፍስት ያረፈበትን የቤተ ጣዖቱን መቅደስ በኃይለኛ እጆቹ ይዞ ወደ ምድር እንደጣላቸው፥ ብቻውን እንደቀረ ነገር ግን ከነብያት ትምህርት ቤት የሚወጡ መቶ ተማሪዎች ያህል ግምት ያለውን ሰው፥ ያንን መንፈሳዊ ሳምሶን የሆነውን፣ ብርቱዎች፣ ግዙፍና አስፈሪ፣ የሚመስሉ የባቢሎንን የዘመናት መናፍስት በተሳካ ሁኔታ ብቻውን ቆሞ መታገል የቻለውን፣ ሕዝቅኤልን አስነሣላቸው። 

በግዞት ያሉቱ አይሁድ ምርኮኞች ያልተረሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ይልቁንም የዳዊት ልጅ የሆነው የመሲሐዊ መንግስት መምጣትን ተከትሎ እንደገና ማገገምና መታደስ፣ ከስደት ነፃ መውጣት፣ ይሆንላቸዋል (ሕዝ 34፥ 22-27)። ያኔም ከተበተኑበት ከአሕዛብም መካከል ይሰበሰባሉ (ሕዝ 36፥ 24-28)። የደረቁ አጥንቶቻቸውም ህያው ሆነው ይነሣሉ በህይወትም ይኖራሉ (ሕዝ ምዕራፍ 37)። ጠላቶቻቸውም ይጠፋሉ (ሕዝቅኤል 38-39)። ጌታም ማለቂያ የሌለው የሕይወት ውሃ ወንዝ ያለው አዲስን ቤተ መቅደስ ይሰጣቸዋል። እርሱም ለአሕዛብ ሁሉ በረከት ይሆናሉ (ሕዝቅኤል 40-48)።

የሕዝቅኤልን መልእክት ለመረዳት፡- ማቲው ሄንሪ ለሕዝቅኤል መጽሓፍ በሰጠው መግቢያ መጽሐፉን በእነዚህ ጥበብ የተሞላባቸው አስተያየቶች አስተዋውቋል። " ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር ለመረዳት ወደ ነቢያቱ መጻሕፍት ዘልቀን ስንገባ የምንሰማው ለቅዱስ ዮሐንስ እንደመጣለት ያለ ‘ወደዚህ ውጣ’ የሚል ተመሳሳይ ጥሪ መስሎ ሊታየን ይችላል (ራዕ. 4፡1) ። የዚህ መጽሐፍ ትንቢት ግን ወደ ፊት ወደ ላይ ውጡ የሚል ድምፅ ይመስላል (ሕዝቅኤል አስቀድሞ ኤርምያስ እንደተነበየው በግዞት ቤት ሳለ ተንብዮአልና፣) ስለዚህ ወደ ላይ ከፍ ብለን ወደ መለኮታዊ ክብር ግኝቶች እንሄዳለን። ስለዚህ ወደላይ ወደላይ ወደ ግኝቶች እንሄዳለን በዚያው መጠን የበለጠ ወደ መለኮታዊው ክብር እንሸጋገራለን። እነዚህ የመቅደሱም ውኃ ጥልቀቱ አሁንም እየጨመረ ያድጋል፣ እስከ አሁን ድረስም በአንዳንድ ሥፍራዎቹ በቀላሉ ሊገመት የማይችል ከመሆኑ የተነሳ ከጥልቀቱ በሚወጡ ፈሳሾች የአምላካችንን ከተማ የልዑሉን ማደሪያ ቅዱስ ስፍራ ደስ ያሰኛሉ።”

“ምንም እንኳን በዚህ ያሉት ራእዮች ዝሆን ሊያስዋኝ የሚያስችል ጥልቀት ያላቸው አይነት አስቸጋሪ ቢሆኑም ስብከቶቹ ግን በአብዛኛው የበግ ጠቦትም እንኳ ሊገባባቸው የሚችልባቸው አይነት ቀለል ያሉ ደግሞ ናቸው፤ አላማቸውም የእግዚአብሔር ህዝብ ምናልባት ይጸጸቱና ንስሃን ያደርጉ እንደሆነ ምርኮ ለምን እንደመጣባቸው ለማሳየት ያደረጉትን መተላለፋቸውን በግልጽ ማመልከት ነው።

የሕዝቅኤል መጽሐፍ የአይሁድ መንግሥት ውድቀት እና ጥፋት እንዲሁም የመፍረሱ ታሪክ ነው። ሕዝቅኤል የሚናገረው እና የሚጽፈው የአይሁድ ሃይማኖት ውጫዊና ቁሳዊ ተቋማት ሁሉ እንደሚፈርሱ ነው። እርሱም ከእነዚያ ውጫዊና ቁሳዊ ከሆኑ ነገሮችና ስፍራዎች የመለየት ህያው ምሳሌ ነበር። አሮጌው እስራኤል መሞት አለበት፣ ለራሳቸው እና ለአለም ሁሉ አዲስ የወንጌል መልእክት ይሆኑ ዘንድ ሞተው በሲኦል ሆድ ውስጥ ከተጣሉ በኋላ እንደገና ከሞት መነሳት አለባቸው። ይህም ተስፋ በተገባው መሲህ እና ለእስራኤል አዲስ ልብ እና አዲስ መንፈስ ወደሚሰጣቸው፣ የእግዚአብሔርን የቤዛነት ጸጋ ምን እንደሆነ ለማየት እጅግ የላቀ እይታን የሚሰጣቸውን አዲሱን ኪዳን ወደሚያመጣው አዲስ ቃል ኪዳን፣ ይመራቸዋል።

ሕዝቅኤል በኮቦር ወንዝ አጠገብ ትንቢት ሲናገር ኤርምያስ በኢየሩሳሌም፣ ዳንኤል ደግሞ በባቢሎን ትንቢት ይናገሩ ነበር። ከዘመናት በፊት ኢሳይያስም የወንጌላዊነትን ወርቃማ የቀንደ መለከት ድምጽ አሰምቶ ነበር። ኤርምያስ በይሁዳ ኃጢአት ላይ ሙሾን የሚያወርድ የሐዘን እንጉርጉሮ ዋሽንት ሲነፋ ነበር። ሕዝቅኤልም በዚያ ኃጢአት ምክንያት የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍትሐዊ ፍርድ የሚገልጥ የብረት በገና ይመታ ነበር”

ልዩነቱ በኤርምያስ ሕዝቅኤል መካከል ካለው ንጽጽር በላይ ያልፋል፣ አንደኛው ለሕዝቡ ባለው ርህራሄ በእንባው ተለይቶ የሚታወቀው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ለእግዚአብሔር ባለው ቅንዓት ተለይቶ ይታወቃል። ምንም እንኳን እነዚህ ባህሪያት እርስ በርስ የሚጣረሱ ባይሆኑም፣ አንዱ በስሜት እና በተግባር ተለይቶ የሚታወቀው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በአመክንዮው እና ያንን በሚረዳበት ነገሩ ይታወቃል። እያንዳንዳቸው ሁለቱም ነቢያት አንዱ ከሌላው ጋር ሳይገናኙና ሳይነጋገሩ አንዱ የሌላውን ሃዘን እንደ ማሚቶ የሚያስተጋባ ነው። ለአሦር ጥልቅ በረሃ ጥልቅ መልሶች፤ ከጽዮን ቅጥር ላይ ሆኖ ሲቃረብ ላየው ማዕበል ያሰማው ጥልቅ የሆነ የወዮታ ጥልቀት ልክ ነው፣ ያንን ባይበልጥ እንኳ፣ ከኖረበት ጠሊቅ ወዮታ አንጻር፣ እራሱን ሊገልጥ ከሰሜን እየመጣ ያለውን የአውሎ ነፋሱን ብርታት፣ ታላቁን የደመና ክምችት፣ የእሳቱን ወላፈን፣ ከመድረሱ አስቀድሞ መላውን የፓለስታይንን ድንበር አድማሱን ከቦ ተሰብስቦ ያለውን የማዕበሉን ጫፍ ዘርፉን ማየት የቻለ ነው (ስታንሊ)። በታሪኩ ውስጥ ሕዝቅኤል የነበረው መቼት እንዲህ ያለ ነበር።

ሕዝቅኤል በባቢሎን ምርኮ ለነበሩ ግዞተኞችና መንፈሳዊ ዐመፅ በሞላበት በኢየሩሳሌም አካባቢ ለነበሩት ምርኮኞች የእግዚአብሔር ዓላማ ምን እንደሆነ ማሳወቅ ነበረበት፣ በስደት ያሉትን የአይሁድን ክፋት በማጋለጥ ሁሉንም ከእይታቸው ውጭ አርቀው ለመቅበር ብዙ በሚደክሙ በማያምኑ ምርኮኞች መካከል እየኖረ እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሆኖ በጽናት ቆመ። ምርኮኞቹ ሕዝቅኤል የሚናገረውን ለመስማት ይፈለጉ፣ ምናልባትም የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለማወቅ ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን የሚሰሙትን ነገር አልወደዱትም። አብዛኛው ሕዝቅኤል የሚያመጣው መልእክት “ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ” (ዕብራውያን 12፥ 3) በሚል ለክርስቶስ እንደሆነው ሁሉ ለእርሱም ብዙ ፈተናና ሥቃይ አድርሶበታል።

ሕዝቅኤል ሃይማኖትን፣ ዘርን እና ቁሳዊ ነገርን ብቻ ማእከል ያላደረገውን የእስራኤልን መንፈሳዊ ሕይወት እና ተልዕኮ እውነተኛ ዓላማ እና ትክክለኛ ተፈጥሮ ለመመለስ እና እንደገና ለማደስ የሚፈልግ የተሃድሶ ነቢይ ነበር። እንደ ነብዩ ዕንባቆም ሁሉ፣ ሕዝቅኤልም ተስፋ ቢስ የሆነ ያህል ቢመስልም የግድ ግን ጠባቂ ደግሞ ነው። “በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ የሚናገረኝንም፥ ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ። እግዚአብሔርም መለሰልኝ እንዲህም አለ፦ አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ፥ በጽላትም ላይ ግለጠው። ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2፥ 1-3)

ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር መንግሥት ውጫዊ መሠረትና መዋቅራዊ መልኩ ሲፈርስ፣ በእግዚአብሔር እና በእምነት ላይ ያለው ማንኛውም ፍላጎት የወረደ መስሎ ሲታይ ያኔ የጌታን እውነት ደረጃውን ከፍ አድርጎ በማሳየት እየሞቱ ያሉትን ምርኮኞች የረሱትንና የማያውቁትን አምላካቸውን እንዲያውቁ እና እንዲታመኑት ማድረግ ይገባዋል። “ሕዝቅኤል እንዲይዘው የተጠራው ፍጹም የተለየ ሥፍራን ነበር። ጥሪውም የነቢይ ልዩ ሥራ እና ጥሪ ነበር። ከመወለዱም ጀምሮ በልዩ ልዩ አገልግሎት ለእግዚአብሔር ያደረ የክህነት መሰረት ያለው ነው፤ በተለይም መለኮታዊው መንግሥትን በተመለከተ ስላሉ ውስጣዊ ጉዳዮች የተለየ ትኩረትን ያደረግ ነበር። ከፍ ያለ ጥሪ እና የነቢይ ተአምራዊ ስጦታዎች የተሰጡትም መሰረታዊ ከሆነው ከዚህ መንፈሳዊ ጥሪው ጋር በተያያዘ ነው። እንግዲህ በግዞት ወደ ምርኮ ተወስዶ ለአገልግሎት ሲላክ የአገልግሎት ኃላፊነቱ ለጊዜው በኢየሩሳሌም ቆሞ ካለው ከሚታየው ተዳሳሽ ቤተ መቅደስ በከለዳውያን ምድር ወደሚጠብቀው ወደመንፈሳዊ ቤተ መቅደስ እንዲዛወር፣ መደበኛና የተለመደ አይነት ከሆነው አገልግሎት ወደተመረጠና ከፍ ወዳለ ዓይነት አገልግሎት እንዲወጣ ተደርጓል። ስለዚህ፣ የመንግሥትን ተግባራት መምራት፣ እና የመንግሥት ጉዳዮችን ማሳለጥ የዳንኤል እጣ ክፍል የሆነውን ያህል፣ እግዚአብሔርን ወክሎ በሰዎች ልብ እና ሕሊና ውስጥ የእግዚአብሔርን ምክር ለማሳለጥ እና የእውነትንና የጽድቅን ደረጃ ከፍ አድርጎ ለማሳየት የተጠራው ደግሞ ሕዝቅኤል ነበር። አንዱ ዓለም አለኝ በምትሉው ግርማ ሞገስና ከበሬታ በተላበሱ ቦታዎች ላይ ሆኖ የእግዚአብሔርን ሉአላዊነት ወክሎ ሲጋደል፣ ሌላው ደግሞ በምርኮኞቹ የአይሁድ ማኅበረሰብ እቅፍ ውስጥ ተሸርጠው ከተቀመጡት የክፋት ዓይነቶች ጋር መጋደልና እነዚያን የእግዚአብሔርን ርስት የሚያበላሹትን ርኩሰቶች መታገል ነበረበት” ሲል ፓትሪክ ፌይርበርን ይጽፋል። 

በመንፈስ እንመራለን በሚሉ ሐሰተኛ ነቢያት ሰበብ በኢየሩሳሌም የነበሩት አይሁዳውያን እግዚአብሔር የሰጣቸውን የመጀመሪያ የተስፋ ቃል እርሱም ያንን ምድራዊ ርስት ፈጽሞ ላለማጣትና በዚያም እስከ መጨረሻው ድረስ ለመታገል ቆርጠዋል። በዚህ ምክንያት ኤርምያስ እና ሕዝቅኤል በህዝባቸው መካከል እንደ አክራሪና እንደ ጽንፈኛ ቢያስቆጥራቸውም፣ ወደ ምድራቸው ከመመለስና ከመታደስ የተስፋ ቃል ኪዳን ጋር አይሁዳዊ በሆነው ኃጢአት ላይ እና እየመጣ ባለው ፍርድ አንጻር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መጮህ ነበረባቸው። እግዚአብሔር ከተቀደሰችው የእስራኤል ምድር በላይ ሊሰራ እንደሚወድና የሚገዛ መሆኑን እንደመቀበልና ከዚህ እውነት ጋር እንደመኖር ያለ እንደሚጠሉ ሌላ ነገር የላቸውም። አምላክ ከተቀደሰች አገራቸው ውጭ የሚናገር ስለመሆኑ ወይም ከምድሪቱ ውጭ በሚደረግ ነገር ስለመቀደሱ ወይም እንዲህ ያለ ማናቸውንም ዓይነት ሐሳብ ማሰብ ርኩስ ነገር እንደሆነና፣ የአምላክ እውነት ከቅድስት አገር በቀር በተለይም ከመቅደሱ በቀር በሌላ በየትም ቦታ ቢገለጥ ያንን በቁላሉ የማይታገሱት እንደሆነ አለን በሚሉት የተለየ እድል የሚመኩበት የኖረ ኩራት አላቸው። 

ነገር ግን ሕዝቅኤል በምርኮ አገር በግዞት መካከል ያቀረበላቸው ጥሪ እግዚአብሔር ከባቢሎን ጨለማ ምድር ነቢይን ጠርቶ ቃሉን ስለሰደደላቸው ይህ የእግዚአብሔር ቸርነት ማለቂያ የሌለው እንደሆነ ግልጽ ያደርግላቸው ነበር። እግዚአብሔር በሉአላዊነቱ የሚሰራ፣ ከጨለማም ብርሃንን የሚያወጣ የማይገመት አምላክ ነው። የሕዝቅኤል ትንቢቶች ተራ በተራ ሳይቋረጡ የፈሰሰሱት በተረገመው የአሕዛብ ምድር ላይ ሳሉ ነው። ከሰማያት የሆኑት ብርሃናት እውነት የተራቡትንና በእርሱም የታመኑትን ዓይኖች ሲከፍቱ፣ ያኔም ንስሐ የሚገቡ እና ራሳቸውን የሚያዋረዱቱ የነቢዩንም መልእክት የሚረዱቱ የእግዚአብሔርን ሰማያዊ ክብር ለማየት ወደዚያ ብርሃን ዘልቀው መግባት ይችላሉ። ጌታ ሰማያትን ሲከፍት ለአገልጋዮቹ አዲስ ራዕይን ይሰጣል፣ ይህም አሰራሩ በአዲስ ኪዳንም ውስጥ በጉልህ ይታያል።

ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ማቴ. 3፡16፣ እስጢፋኖስም በሰማእትነት በተሰዋ ጊዜ፣ የሐዋርያት ሥራ 7፡56፣ እና ጌታ ኢየሱስም በትንሳኤው ጊዜ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር በኤማሁስ መንገድ ላይ ሲነጋገር ልባቸው በተቃጠለ ጊዜ ይህ እንደሆነ አስቡ።

የእግዚአብሔር ራእይ፣ የተከፈተስ ሰማይ ከባቢሎን ይገኛልን? መልካም ነገርስ ከናዝሬት ሊወጣ ይችላልን?፣ የእግዚአብሔር ፀጋ እውነተኛ ምስክርነትስ ከጣዖት ምድር ከሚፈለቅ ከተበከለው የአህዛብ ወንዝ ከኮቦር ሊቀዳ ይችላልን?

የእግዚአብሔር ሕዝብ ያለበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ በየትም ስፍራ ቢሆኑ እንኳ የእግዚአብሔር ቃል ግን በኢየሩሳሌም ሳሉ በኤርምያስ በኩል፣ በባቢሎን ሳሉ በዳንኤል በኩል፣ በኮቦር ወንዝ ሳሉ በሕዝቅኤል በኩል ይመጣ ነበር። ከቅድስት አገር ተነቅለው፣ ከመቅደሱም ርቀው ባሉበት የግዞት ምድርም ቢሆን እንኳ ቃሉ አልተዋቸውም። እርግጥ ምርኮኞቹ በአረማውያን ገዥዎቻቸው ክትትል ስር ሆነው ራሳቸውን ግን እንዲያስተዳድሩ እና የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን እንዲመሩ የተወሰነ ነፃነት ተፈቅዶላቸው ነበር። ምንም እንኳን ምርኮኞቹ ለብዙ አመታት በተወሰነ ጥብቅ ተግሣጽ ሥር ቢቆዩም፣ አሁንም ያለፈውን ክፉ መንገዳቸውን ከመከተል አልተመለሱም። ይልቁንም በቅርቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመለሱ ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል፣ የግዞቱም ዘመን አጭር ነው በሚል አጉል ተስፋ ያደርጉ ነበር። ነገር ግን በመለኮታዊ ፍርድ ሥር መሆናቸውን ሳያዩ፣ የደረሰባቸውን ተግሳጽ ሳይገነዘቡ ቀርተው ነበር።

ስለዚህ ክህነቱን ያጣው ሰው፣ ያ በኢየሩሳሌም ቆሞ ባለው ተዳሳሽ ቅዱስ ቤተመቅደስ ውስጠኛ ክፍል የመግባት እድልና ጥሪውን ያጣ ሰው፣ አሁን ነቢይ ተብሎ ለመጠራትና በኪሩቤል ላይ ከተቀመጠው ከእግዚአብሔር ዙፋን ሰረገላ ላይ ቆሞ የእግዚአብሔርን ድምፅ እንዲሰማ ወደ መቅደሱ መግባትን አገኘ። የሕዝቅኤል ትንቢት መለኮታዊ ቅደም ተከተል በራእይ፣ በሸክም እና ትንቢትን በመናገር ላይ የተመሠረተ ነው። ስለዚህ፣ ሕዝቅኤል እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዳልተገደበ ወይም እንዳልተውሰነ ያውቅና ያይ ዘንድ፣ አሁንም በባቢሎን በግዞት ላሉት ለመልካሞቹ በለስ እና በኢየሩሳሌምም ለቀሩት ለክፉዎቹ በለስ፣ እንዲሁም ለአሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔር “እኔ እግዚአብሔር እንደሆንኩ ታውቃላችሁ” ሲል እንደተናገረው ያለ መልእክት ይኖረው ዘንድ፣ በእግዚአብሔርም ዘንድ ቅጣትን የሚያስከትልባቸውን የኃጢአት ብዛት ያውቁ ዘንድ የክብሩ መገለጥ ከሆነውና በሉአላዊነት ከሚሰራው የእግዚአብሔር ህልው ዙፋን፣ ከዚያም ከተንቀሳቃሹ የእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ሆኖ ራእዩን ያሳየዋል። ቅጣቱም በእግዚአብሔር የጽድቅ መርሆ ላይ የተመሰረተ የኃጢአት ቅጣት ነው። ተሀድሶውም የተማረኩት ግዞተኞች ንስሃን እንዲያደርጉ፣ እንዲለወጡ፣ ብሎም ወደ ጽድቅም እንዲደርሱ የቀረበ ትንቢታዊ ጥሪ ነው።

ጥሪውም አዲስ የሕይወት ተስፋን ይሰጣል፣ አዲሱንም እረኛ ያስነሳል፣ እርሱም አዲስ የሆነ የሰላም ቃል ኪዳን ከበረከት ዝናብ ጋር ይመግባቸዋል። ንጹሑን ውሃም በአዲሱ ልባቸውና በአዲሱ መንፈሳቸው ላይ ይረጫቸዋል። ለደረቁ አጥንቶቻቸውም ሕይወትን ይሰጣል፣ ጠላቶቻቸውንም ለማጥፋት እንደ ኃያል ሠራዊት ያስነሳቸዋል፤ በውጤቱም የታላቁ ቤተ መቅደስ አዲሱ ሥርዓት በሚሄድበት ስፍራ ሁሉ እውነተኛ የሆነ መንፈሳዊ ፈውስን የሚያፈስ የሕይወት ወንዝ እንደ ጅረት ያፈልቃል።

gkr


ክፍል ሦስት

የሕዝቅኤል መጽሐፍ መንፈሳዊ ጠቀሜታ

ሕዝቅኤል በእግዚአብሔር የክብር ዙፋን ሠረገላ ፊት እንዳለ ካህን ሆኖ አዲሱን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አይቶ ነበር።

እግዚአብሔር ነገሠ፥ አሕዛብ ይደንግጡ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ፥ ምድር ትናወጥ። (መዝሙር 99፥ 1)

ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ። (መዝሙር 80፥ 1)

ሕዝቅኤል ዐውሎ ነፋስና ደመና፣ እሳትና ብርሃን በክብር ሲያበራ፣ አይኖች የተሞሉት የሚሽከረከሩ መንኮራኩሮች፣ አራት ሕያዋን ፍጥረታትም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ በአንድነት ሲንቀሳቀሱ አየ። ከከፍታ ጠፈርን አየ፣ ከላይም ድምፅን ሰማ፣ የዙፋን አምሳያና የሰው ልጅም በዙሪያው በብሩህ ብርሃንና በቀስተ ደመና መልክ ተገለጦ ተመለከተ። የሚያየው ነገርም ማለቂያ የሌለውን የእግዚአብሔርን አደራርግ፣ የሕይወትን መንፈስ፣ በመንፈሳዊ የእውቀት አይኖች ብቻ የሚታየውን በብርሃንና በእሳት አምሳል የሚገለጠውን የጌታን ክብር የሚያመለክተውን ራእይ ነበር። ይህም ራእይ የክርስቶስን እና በእርሱ የሚመራውን ሰማያዊ ጉባኤ የሚያመለክት ምሳሌያዊ ነበር፣ ይህም አስፈሪ የሆነውን የእግዚአብሔርን ግርማ የሚያሳይበትና በደካማ እና በኃጢአተኛ ሕይወታችን ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ይገልጣል።

የእግዚአብሔርን ቤት፣ እና መቅደሱን፣ ክርስቶስንም በግርማ ዙፋኑ ላይ ከፍ ብሎ እዩት፣ ይህም የእግዚአብሔርን ፍፁም ሉዓላዊነት ያመለክታል። ጌታ በሁሉም ላይ እና በሁሉም ስፍራ ሆኖ ሲገዛ ከምድራዊው መቅደሱ የአምልኮ ስርዓት ጋር በተያያዙ ምልክቶች ላይ ሆኖ በክብር ይታያል። እርሱም በሰማይ እና በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሁሉን ቻይ ንጉስ ነው፤ እርሱም የሉዓላዊነቱን አላማ በማይከለከል ዘላለማዊ ኃያልነቱ ይፈጽማል፤ እንግዲህ እዚህ ግርማ ጋር ሲደረስ ሰው የሚቀረው በቸኛና ትልቁ እድሉ እንደሞተ ሰው በድንጋጤ በግንባሩ ወድቆ መስገድና ማምለክ ነው፣ ይህም የግርማውን ብርሃን ማየት ከታደለ ሰው ሁሉ የሚጠበቅ ነው። ያየውም ነገር ሁሉ ማለቂያ የሌለውን የእግዚአብሔርን አደራረግ፣ የሕይወትን መንፈስ፣ በዙሪያውም ሁሉን የሚመሩምሩና የሚያውቁ አይኖች የሞሉበትን፣ መንፈሳዊ አይኖችን ከፍቶ እውቀት የሚሰጠውን በብርሃንና በእሳት የተከበበውን የጌታን ክብር ነው።

ስለ ዙፋኑ ሠረገላ በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የሚታየው ነገር በታሪክ ውስጥ ባሉ መንፈሳዊ ኃይሎች እና ሁነቶች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያለውን ፍፁም ገዥነቱን የሚያመለክት ሲሆን ሁሉም ኃይላትና ሁነቶች ደግሞ በራሳቸው ሊቆጣጠሩትና ሊገዙት ከሚችሉት በላይ ከንቃተ ህሊናቸውና ከእውቀታቸው በሚያልፍ መገዛት የአላማው መሣሪያዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

አሁን የጌታ የተቀደሰ መቅደሱ በእርሱ የተቀደሰው ማኅበሩ ነው፣ እርሱም አካሉ፣ የመንግሥቱና የአገዛዙ መቀመጫ የመገኘቱም የመጨረሻ ማረፊያው ነው።

እስራኤል የገባችበት ውድቀት የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት ሊነካ እንደማይቻለው፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም እርሱ ግን አሁንም በሉዓላዊነቱ ጸንቶ እንደሚኖር እና በሁሉ ላይ ነግሶ እንደሚገዛ ሕዝቅኤል ያሳያል።.ዙፋኑ በሕዝቅኤል ዘመን በሰማያዊ ንጽህናው ጸንቶ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም እንዲሁ በገዛ ጉባኤው ላይ በነጽህናው አርፎ ይኖራል።

እግዚአብሔር ከአሕዛብ፣ ከእስራኤል ወይም ከቅዱሳን ማኅበሩ ጋር ያለው ግንኙነት ለክብሩና ታላቅ ስሙን ለማክበር ባለው አላማ ስር የተገዛ ነው።

“ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም።” (ሕዝቅኤል 36፥ 22)

እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር የሚያደርገው ህብረት በዓለም ሁሉ ፊት ራሱን ለመቀደስና እርሱ በእውነት እንዳለ እንደ ማንነቱ ራሱን ለመግለጥ ካለው እጅግ የላቀ አላማው በታች የተገዛ ነው።

ሕዝቅኤል ጊዜያዊ ሁኔታውን ለማየት ችሏል፣ ነገር ግን በግዞት ቤት በምርኮ ሆኖ ያሳለፈበትን ጊዜ ምን መንፈሳዊና ዘላቂ ትርጉም እንዳለው ለማየት ደግሞ ተችሎታል። በኤርምያስ አፍ ለአይሁድ የተናገረው ቃል ይኸውም ቤተ መቅደሱ ተመልሶ በኢየሩሳሌም ሊገኝ አለመቻሉን ሲያይ፣ በአንጻሩ ግን በበላይ የተከፈተ ሰማይን እና የአምላክን ራእይ ለማየት ተችሎታል። በዚያ የባቢሎን ምድረ በዳ ሊማርባቸው የተዘጋጁ የጥናትና የምርምር፣ የትምህርት ተቋማት አልነበሩም፣ ወይም ሊያስተምሩት የሚችሉ የሴሚናሪ ምሁራኖች ወይም ቤተመጻሕፍት፣ አልያም ስብከት የሚሰማባቸው ሜጋ የሆኑ ታላላቅ ጉባኤዎች ወይም ህብረት የሚያደርግባቸው መለስተኛ ጉባኤያት ወይም የቲ.ቪ ሰባክያንና ሌሎች ሐሰተኛ የዩቱብ ነቢያት አልነበሩትም። ሕዝቅኤል ያየው ያ የተለየና የከበረ፣ በየትኛውም ምድራዊ ኢንስቲትዩት ኮርሱ የማይሰጥ ሰማያዊው ራእይ ግን በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን በክርስቶስ ያለውን እግዚአብሔርን የመምሰል ታላቅ ምስጢር ይገልጣል። “ እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፦ በሥጋ የተገለጠ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ ለአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ፣ ነው” (1ጢሞቴዎስ 3፥ 16)።

በሕዝቅኤል ራእይ በኪሩቤል ላይ የታየው የእግዚአብሔር መገለጥ በአራቱ ወንጌላት ውስጥ በግልጽ የሚታይ ነው፣ የእግዚአብሔርን መልክ የሚወክሉ እነዚያ የሕዝቅኤል ራእይ አራቱ እንስሳት በወንጌላት ውስጥ በክርስቶስ ሕይወት የተገለጠውን መልክ ይዘዋል።  

  • በማቴዎስ ወንጌል እንደ ቀረበው ከሆነ ክርስቶስ እንደ አንበሳ ነው፣ ይህም አንበሳ የአራዊት ንጉሥ እንደሆነ ሁሉ ክርስቶስም ንጉሥ የይሁዳ አንበሳ መሆኑን የገለጠና እንደ ንጉሥ በሰዎች መንግሥት ላይ የሚሰለጥንና የሚገዛ መሆኑን ያሳየበት ነው።  
  • በማርቆስ ወንጌል እንደቀረበው ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ የሚያሳየው ደግሞ ክርስቶስ እንደ መሥዋዕቱ በሬ አገልጋይ መሆኑን ያሳየበት ነው። 
  • በሉቃስ ወንጌል መሠረት ደግሞ እግዚአብሔርን የሚመስል በጎ ምግባራትን እና መልካም ምግባሮችን የሚያሳይ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን የእግዚአብሔርን ፍጹሙን ሰው ያሳያል። በመጨረሻም፣ 
  • በዮሐንስ ወንጌል መሰረት የእግዚአብሔርን ልጅ በአምላክነቱ ሲገልጠው እነደ ንስር ያቀርበዋል።  

ሰው በሚለው ጀምረን ካየነው አጠቃላዩ የክርስቶስ ማንነት በእግዚአብሔር አሰራር ውስጥ ሂደቱ በአራቱም መልክ ተገልጧል። ፍጹም ሰው ሆኖ ከሴቲቱ ዘር ሲወለድ ከሕግ በታች፣ ከውኃና ከደም በመወለድ ሥጋና ደም ለብሶ እናየዋለን። አምላክ ሰው ሆነ፣ ሕፃን ሆነ አንበሳም ሆኖ አደገም። 30 ዓመት በሞላውም ጊዜ የሰይጣንን አገዛዝ ለማፈራረስና ለመሻር መንግስቱንም በጽድቅ ለማጽናት ደፋር የአራዊት ንጉሥ ሆኖ በአባቱ ተቀባ። ከዚያም ለአብ በመታዘዝ ራሱን አዋርዶ የመጨረሻው መስዋዕት እስኪሆን ድረስ ለመስዋዕት እንደቀረበ በሬ ለዓለም ኃጢአት የቀረበ የዕርገት መስዋዕት ይሆን ዘንድ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ሕማምን እና በሽታን ሁሉ እየፈወሰ አገለገለ። በሲኦል ቆይቶ ከሦስት ቀናት በኋላ ከሞት በመነሳት፣ የትንሳኤ ጌታ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በኃጢአትና በሞት ላይ የተቀዳጀውን ድል ለአባቱ ክብር ለፍጥረት ሁሉ እያበሰረ እንደ ንስር ወደ ሰማያት ከፍ ከፍ እያለ ወጣ።

በሕዝቅኤል ራእይና እና ኋላም በወንጌላት የተገለጠው የእግዚአብሔር ባህርይ [እውነተኛ ተፈጥሮው] በሰው ልጆች ላይ የተዘረጋ የጨለማውን መጋረጃ በክርስቶስ ለማንሳት የተጠቀመበት አሰራሩ ነው፤ ሰው በሆነውና በእግዚአብሔር የክብር ዙፋን ላይ በተቀመጠው በክርስቶስ ኢየሱስ ህይወት እና ማንነት የተገለጸውን ወሰን የለሽ አላማውንና አስደናቂ ብርሃኑን እንዲሁም በእርሱ የሚሰራውን የህይወት ኃይል ዘላለማዊ እውነታ ያሳያሉ። ሕዝቅኤል በእግዚአብሔር ዓላማ ውስጥ ይህ መገለጥ እና ራዕይ እራሱን በሥጋ የመግለጥ ምስጢር መቼ እና እንዴት እንደሚሰራ በትክክል አያውቅም፣ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ከመታወቅ የሚያልፉ እውነታዎች፣ ይኸውም እርሱ በአገልግሎትና በመስዋዕትነት ብቸኛ የበላይ እንደሆነ በዘመኑ አይቷል። ሕዝቅኤል ራሱም ሆነ ምርኮኞቹ አይሁድ ሁሉ ዛሬም ቢሆን መላው የእግዚአብሔር ጉባኤ "እግዚአብሔርን ያውቁት ዘንድ" አሁን እዚህ በመካከላችን ከእኛ ጋር እንዲሁም ለዘላለም በህያውነት በሁሉ ስፍራ ያለ አምላክ መሆኑን ማለትም "እግዚአብሔር በዚያ እንዳለ"፣ መማር አለባቸው። የሕዝቅኤል ወንጌል የእግዚአብሔርን እውነተኛ ተፈጥሮ፣ ባህርዩን ለማወቅ እና ማንነቱን ለመረዳት በፍርድ፣ በተሃድሶ እና በፅድቅ ወደ ጌታ ፊት ግቡ እያለ እየተጣራ ነው። ይህ ዛሬ ለእኛ እንደ ትንቢት የሚሠራ አይደለም፣ እግዚአብሔር ራቅ ባለ ቦታ በሚገኝ አንድ ሳጥን ውስጥ ተቆልፎ እንደተቀመጠና እንደተወሰነ እንደ አንድ የሆነ ነገር ሳይሆን፣ ይልቁንም በሁሉ ስፍራ ያለና የሚገኝ መሆኑን እንደ እግዚአብሔር ጉባኤ እንድንማርና እንድንረዳ እንደ መመሪያ ሆኖ የተሰጠን ነው። እርሱ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለዘላለም “አማኑኤል! እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ሆኖልናል። መቅደሱ፣ እርሱም ማኅበሩ ደግሞ የእግዚአብሔር በምድር ላይ መገኘት የሚገለጥበት የክብር ዕቃ ሊሆን ይገባዋል። እርሱም በተሃድሶ የተገለጠ የቲኦክራሲ አገዛዝ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ነው። ይህም የክብር ዕቃ የድኅነት፣ የመታደስ እና የእግዚአብሔር ጸጋ መልእክት ወደ ዓለም ሁሉ የሚፈስበት ምንጭ ነው።

የመንፈሳዊ አገልግሎት ፍላጎትና አቅርቦት

ጂ ካምቤል ሞርጋን ስለ ዳንኤል በሰጠው ትንታኔ እንደተናገረው፣ የዚያ ዘመን ታሪካዊ ሌሊት ትንቢታዊ የሆነ ብርሃን ያስፈልገው ነበር ብሏል፤ እንደዚህ ባለው አስቸጋሪ ተግባር ውስጥ እንደ ኢየሩሳሌም፣ እንደ ባቢሎን፣ እና በኮቦር ወንዝ ዳርቻ እንዳሉ የጨለማ ስፍራዎች ላይ ሰማያዊ ራዕይንና ብርሃንን የማምጣት ሥራ ውስጥ ማንን እናገኛለን? ነብያቱ ኤርምያስ፣ ዳንኤል እና ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እነርሱ ሲመጣና የእግዚአብሔርን ራእይ ሲያዩ፣ ያኔ እንደ ሞኞች ይቆጠሩ ነበር። ባለራዕይ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስም ራሱ እንደ ሞኞች ሆነው ዋጋ ከፍለዋል። ሕዝቅኤል ከምርኮኞቹ ጋር የገጠመው ፈተና ለእነዚያ መንፈሳዊ እውነታን መረዳት ለማይችሉና የእግዚአብሔርን ፍትህ፣ ጽድቁንና እና በጸጋ የተሞላውን የምህረት ቀስተ ደመና ማየት ለተሳናቸው ዓይነ ስውራን ለሆኑ አናሳ ምርኮኛ ነፍሳት የጌታን ቃል ማምጣት ነበረበት። ይህም ቃል በሚመጣው መሲሐዊ ዘመን ወይም በአዲሱ ኪዳን ዘመን የሚከፈትላቸው ነው። እነርሱ ግን በሚመጣላቸው የእግዚአብሔር የበረከት ቃል ውስጥ የሚደመጠውን የድምጹን ጥዑመ ዜማ ለመስማት የደነቆሩ ነበሩ። የሕዝቅኤልና የኤርምያስ ቃል ካልታያቸውና ካልተጠነቀቁ ድግሞ ምድሪቱን ወደ ጨለምተኝነት እና ወደ ምናምንቴነት እንድትወርድ ያደርጓታል።

ሕዝቅኤል ሰማያት በተሞሉት ነፃነት ውስጥ እየተመላለሰ፣ ከኢየሱስ ጋር በገበታው ተቀምጦ ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንና መንፈሳዊ ራእዮችን ሲከፍት ተችሎታል። ሕዝቅኤል ለእስራኤልና ለአሕዛብ የተናገረው ቃል፣ ፣ የሞራል ልዕልና፣ የኃጢአት ወቀሳ፣ እና ክፉ የሆኑ የሰው ልጆች ሊተነፍሱት የማይችሉት አዲስ የሞራል ድባብን የያዘ “የሕይወት ራእይ” ነበር። ሕዝቅኤል መለኮታዊ ምሥጢርን ለመግለፅ በመንፈስ የበቃ፣ አይኖቹ የተከፈቱለት ነብይ ነበር እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት የሚሞክር ምሁር አልነበረም።

ሕዝቅኤል እውነተኛው መንግሥት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ፣ መስቀሉን፣ ደሙን፣ እውነተኛውን የክህነት አገልግሎት እና የስርየትን ሚስጥር ለማወቅ ይማር ዝንድ በመዋረድና በስብራት ወስጥ እያለፈ ነበር። ለራዕዩና ለትንቢቱ ይዘጋጅም ዝንድ በምስጢሩ ስፍራ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በእግዚአብሔር ዙፋን ሠረገላ አጠገብ እግዚአብሔርና እርሱ ብቻ በሚገናኙበት በኮቦር ወንዝ አጠገብ ብቻውን ይገኝ ነበር። ሕዝቅኤል ሰባኪ ካህን ብቻ አልነበረም፣ ይልቁንም የሚሰማ ድምጽም ጭምር ነበር። እግዚአብሔር በሕዝቅኤል ሲናገርና ሕዝቅኤል ትንቢቱን ሲጽፍ እስራኤል ያኔ የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት አስፈልጎት ነበር፣ ያም ድምጽ ደግሞ ሕያው የእግዚአብሔር መልእክት ነው። ሕዝቅኤል በባቢሎን ላሉት አድማጮቹ ሊጠቅማቸው የሚችሉትን እነዚህን ቃላት ሐዋርያው ​​ጳውሎስም በጲስድያ በምትገኘው አንጾኪያ በነበረው ምኩራብ ውስጥ፦ “በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤” (ሓዋርያት ሥራ 13፡ 27) ሲል አስተጋብቶታል።

ተጭኗቸው ከነበረው ብሄራዊ ጭፉንነት የተነሳና በዚያ በሚገድል የፊደል ስርአት ባርነት ውስጥ በመሆናቸው የእግዚአብሄርን ድምጽ እንዳይሰሙ ተስቷቸው ነበሩ፣ ሕዝቅኤልም ከነበረባቸው ዓይነ ስውርነት፣ ከግራ መጋባታቸው እና ከአቅመ ቢስነታቸው ጋር መስማማት አልተቻለውም ነበር።

ሕዝቅኤል እየተናገረ ያለውና የሚጽፈው ቃል በኢየሩሳሌም ከሚገኙ አንዳንድ የጥናትና የምርምር ተቋማት ከእነርሱ የተማረውን የተጠኑ የጽሑፍ ግልባጮችን ይዞ የሚናገር አልነበረም። እንደ ነቢይ ለመናገር፣ ንግግሩን አደራጅቶ አልቀረበም፣ ኮሚቴም አላቋቋመም፣ ወደ ወግ ወይም ወደ ሥርዓት አልወረደም፤ አዲስ የእምነት መግለጫዎችንም አላዘጋጀም። የሕዝቅኤል መጽሐፍ በመድረክ አሙቁልኝ ጩኸት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕሎች፣ በሥርዓተ አምልኮ፣ በአልባሳት፣ በገጽታ ግንባታ ፣ በድራማ ትዕይንታዊ አቀራረብ፣ በድምጾች፣ ብልጭ ድርግም እያለ ውበትን በሚከስት ብርሃንማ ስሜታዊ አቀራረብ የነፍስን ስሜቶች እየማረከ አልቀረበም። ይህ የነቢያት ጉዳያቸውም፣ ጭንቀታቸውም አልነበረም፤ እንዲህም ያለ የእግዚአብሔር ነቢይም የለም!

የሕዝቅኤል መጽሃፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስም ራሱ ለመንፈሳዊ ሰዎች ብቻ ክፍት ነው እንጂ የተዘጋ መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር አምላክ በዚያን ጊዜም ሆነ ገና ወደፊት ምን እንደሚያደርግ ሕዝቅኤል ለእስራኤልና ለአሕዛብ ሁሉ እየነገራቸው ነበር። በዙፋኑ ሰረገላ ላይ ከፍ ብሎ ያለው ያ አምላክ-ሰው ፍርድን፣ መመለስንና፣ መንፈሳዊ መነቃቃትን ወይም ተሀድሶን በሚመለከት ሁሉንም ነገር በሃይሉና በስልጣኑ በሰማይ እና በምድር ይገዛል ያስተዳድራልም። እርሱም ሁሉ የሚሰፈርበትና የሚለካበት የሁሉ ሚዛን ነው፣ ሁሉም ነገር የሚለካውና የሚሰፈረው በዚህ ሰው መሰረት ነው፤ እርሱም ወሰን የሌለውን የእግዚአብሔር አላማ እውን ለማድረግ ብቃት ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ መገለጥ ነው። የዚህ መጽሐፍ የመጨረሻው ፍጻሜ እና ታላቁ ዓላማ፣ እንዴት እንደሚጠናቀቅ የሚያሳየን ቃል "እግዚአብሔር በዚያ አለ' በሚለው ሐረግ ውስጥ ተሰብስቦ ይገኛል። ምንም ያህል አሁንም የሰው ኃጢያተኛነት፣ ዓመፀኛነት እና ውድቀት ቢኖርም እግዚአብሔር ግን ለክብሩ ሲናገር ይኖራል፣ የድል አድራጊው የእግዚአብሔር ዙፋን አሁንም በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ በመንግስቱና በአህዛብ ሁሉ ላይ በጸጋው በሚገዛ በዚያ ሰው በኩል ንቁና የሚሰራ ነው።

gkr

ክፍል አራት

ሕዝቅኤል ፡- የእግዚአብሄር ወሰን አልባነት፣ የክርስቶስንና የአካሉንም ሁሉን አቃፊነት ይገልጥልናል

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ መመራት ያለበት በመንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው - የመለኪያውም በትር መንፈስ ቅዱስና ክርስቶስ ነው። እርሱ እንደ እግዚአብሔር አሳብ የሆነ የእግዚአብሔር ቤት መለኪያ ነው፤ ሕዝቅኤል በአገልግሎቱ የሚገልጠው ቅድስናንና፣ መለየትን፣ ተስፋፍቶ መዘርጋትን ሲሆን፤ በክርስቶስ ታላቅነት እንዱሁም የክብሩ ስፍራ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት፣ ግዛቱና ዙፋኑ እንዲሆኑ እርሱ ለጠራቸው ለማህበሩ በሚቀና ሞልቶ በሚፈስስ ሸክም ያገለግላል። በሕዝቅኤል ውስጥ የእውነተኛው መንፈሳዊ አገልግሎትና የሕይወት ሥርዓት፣ ሁሉም ነገር የሚለካው በክርስቶስ ነው። ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርን ዓላማ፣ የእግዚአብሔርን መንገድ እና "እግዚአብሔር በዚያ አለ" ያህዌ ሻማ! የተባለላትን የእግዚአብሔር ቤቱ የሆነችውን ከተማ በሚገባ ተረድቷል።

የሕዝቅኤልን መጽሐፍ እና የዮሐንስ ራእይን መጽሐፍ በንጽይር የሚያቁርቡ አንዳንድ ምንባባትን ከዚህ በታች በዝርዝር ቀርበዋል። ሐዋርያው ​​ዮሐንስ የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በተቀበለ ጊዜ የሕዝቅኤልን መጽሑፍ እንዴት ባለ መንገድ ጥቅም ላይ እንዳዋለው በዚህ ንጽይር ውስጥ ለማየት እንችላለን።

የሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 እና 39 መግቢያን እዚህ ላይ እንመለከታለን፤ እነዚህ ሁለት ምዕራፎች አይሁዳውያንን ለማጥፋት በሚጥሩና የእግዚአብሔርን መሲሐዊ መንግሥት የትኛውንም ተስፋ ለማብቃት በሚሰሩ በእስራኤል ጠላቶች ላይ እግዚአብሔር ስላደረገው የድል ታሪክ ይናገራሉ።

ያ ያልተማረና በውጭ ባለ የድንቁርና ጨለማ ውስጥ የሚኖረው አረማዊ ኃይል ስለ እስራኤልና ስል አማላኳ፣ እነርሱም ከአምላካቸው ጋር በነበራቸው የኖረ ታሪክ ስላገኙት መለኮታዊ መገለጥ እና ስላዩት የዘላለም ኃይሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለውም። አሁን በግዞት ምርኮኛ ሆነው ያሉት አምላካቸው ሊጠብቃቸውና ሊታደጋቸው አቅቶት ስለተሸነፈ ሳይሆን ይልቁንም ከቅድስናውና ከጽድቁ የተነሳ ስለ ኃጢአታቸው ሊቀጣቸው እንደሆነም አያስተውሉም።

ሕዝቅኤል የጎግንና የሰራዊቱን እጣ ፈንታ፣ እነዚህም በእግዚአብሄር በራሱ ወደ ተዘጋጀላቸው ወደ ጥፋታቸው እንደሚመሩ፣ በዚህም ቤተ መቅደሱንና ኢየሩሳሌምን ለመገንባት ከምርኮ የሚመለሱትን የኢየሩሳሌምን ቅሬታዎች እንደሚጠብቃቸው ያሳውቃል። “ነገር ግን ማጥፋት፥ ጥቂት ያይደሉትንም አሕዛብን መቍረጥ በልቡ አለ።” (ኢሳይያስ 10፥ 7) እንደተባለው፣ በዚህም አውድ ውስጥ ጥቂቶች ያይደሉ አህዛብን ማጥፋትና ቆርጦ ማስወገድ የእግዚአብሔር ቀጣይ የፍርድ ዓላማ ሆኖ ቀርቧል። አላማውንም እግዚአብሔር ስያስታውቅ፣ “ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” (ሕዝቅኤል 38፥ 23) ብሏል።

ጎግ በራሱ ላይ ሊፈፀም ላለው ፍርድ ግልጽ ዓላማ በአይሁድ ላይ ተነስቷል። ሕዝቅኤል ምዕራፍ 38-39 ላይ የተነገረው በእውነት አስገራሚ ትንቢት ነው፣ ላለፉት ብዙ መቶ ዓመታት ብዙዎች እንደተናገሩት፣ ማንስ ሰው ቢሆን በአውዱ እንደተረዳው ወይም እንደሚገባው ሆኖ ማንን ሊያስረዳ ይቻለዋል? ብዙዎች በመገረም እና በጉጉት እየተቃጠሉ፣ ያለ የሌለውን እየቧጠጡ፣ እዚህ ከተገለጠው ጎግ እና ማጎግ በላይ ያለ ሌላ የሌለ ጎግ ፈጥረዋል። የጎግንም ማንነት ለማግኘት ‘ትንቢታዊት ጽዮናዊት እስራኤልን’ በውስጣቸው ስለው፥ ገና ሊመጣ ባለው የወደፊት ጊዜና የአለም ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ያልማሰኑት፣ ያልያዙትና ያልጩበጡት ነገር የላቸውም። ለነዚህ ማሳኞች ግን ከሁሉ አስቀድሜ የምነግራቸው የመጀመሪያ ነገር፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትኛውም መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተነጥሎ መተርጎም ወይም መረዳት እንደማይቻል ልትገነዘቡ ይገባል የሚል ነው። ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ የትኛውም ምዕራፍ የንባብ ክፍሉ ከተወሰደበት የመጽሐፉ አውድ ተነጥሎ ሊብራራ ወይም ሊተረጎም አይችልም፣ ማንኛውንም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ወይም የመጽሐፉ ምዕራፍም ቢሆን አስቀድሞ በተያዘ ቅድመ ግንዛቤ ማለትም ዘመን ቆጣርያን (Dispensationalists) ወይም የቅድመ-ሺህ አመት አቀንቃኞች (premillennialists) ወይም ማናቸውም የትንቢት ሊቃውንት ነን የሚሉ ሰዎች በሚያደርጉት በኖረው ልማዳዊ የትርጓሜ ዘዴ በመጠቀም ሊፈታ አይችልም። እነዚያ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፉት ነገሮች ሁሉ ያኔውኑ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ከመሆናቸው ባለፈ ገና አሁንም የወደፊቱን የአለም ሁኔታ ይናገራሉ ብለን አንወስዳቸውም። እኛ ትክክለኛው ግንዛቤ አለን ብለው የሚያስቡ እነዚህ ሰዎች የሚያራምዱትን ተራ የሆነ አሳብ ወዲያ አሽቀንጥረን ጥለነዋል፣ እንደዚህ የሚጫወቱቱ ላለፉት ብዙ መቶ ዘመናት በየጊዜው እነርሱና ትንቢታዊ ግምታቸው እየተለዋወጠ ስናይ ግኝታቸውና አለን የሚሉት ትምህርታቸው የማይረባ ነገር ብቻ እንደሆነ ደርሰንበታል።

ስለዚህ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የምዕራፍ 38 እና 39ን አውድ እንመልከት። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሕዝቅኤል እንዲህ ሲል መጣ፡— “ፊትህን በጎግ (20 ጊዜ) ላይ እና በማጎግ ምድር ላይ … አቅናበት፣ እንዲህም በል፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል (15 ጊዜ) ይልና እንዲህም እንደዚያ፣ም "አደርጋለሁ" ይላል። እግዚአብሔር አደርጋለሁ የሚላቸውን ጉዳዮች ተመልከቱ፦

  • እመልስህማለሁ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ፥ አንተንም…ታላቁን ወገን አወጣለሁ፥ (ሕዝቅኤል 38፥ 4)
  • በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ። (ሕዝቅኤል 38፥ 16)
  • በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ (ሕዝቅኤል 38፥ 21)
  • …በእርሱ ላይ… አዘንባለሁ (ሕዝቅኤል 38፥ 22)
  • (እኔም) ታላቅ እሆናለሁ (ሕዝቅኤል 38፥ 23)
  • እመልስሃለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 2)
  • እነዳህማለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 2)
  • ከሰሜንም ዳርቻ እጐትትሃለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 2)
  • ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 2)
  • ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። (ሕዝቅኤል 39፥ 4)
  • በማጎግ ላይ… እሳትን እሰድዳለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 6)
  • ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቅ ዘንድ አደርጋለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 7)
  • ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላስረክስም፤ (ሕዝቅኤል 39፥ 7)
  • የመቃብርን ስፍራ ለጎግ እሰጣለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 11)
  • ክብሬንም በአሕዛብ መካከል አኖራለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 21)
  • የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 25)
  • ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 25)
  • ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 25)
  • በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አልተውም (ሕዝቅኤል 39፥ 28)
  • ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሸሽግም፤ (ሕዝቅኤል 39፥ 29)

ሰው ያስባል፣ እግዚአብሔር ግን ምክሩን ይፈጽማል ማለት ይህ ነው። በታሪክ ወስጥ ሰው ከማሰብ ያለፈ ምንም ሊያደርግ አይችለም፣ ጎግና ጭፍራው እስራኤልም ሁሉም አቅመ ቢስ ናቸው፣ ያስባሉ፣ አንዱ ለማጥፋት ሌላው ላለመጥፋት፣ የሚጸናው ግን የእግዚአብሔር ምክር ብቻ ነው፣ አንዱን ወደጥፋቱ ሌላውን ወደ ድነቱ ያደርሰው ዘንድ ሉአላዊሉ አንድ ብቻነው። በዚህም ጎግ ራሱና በእርሱ የሚመራው ጭፍራው ሁሉ፣ ከምርኮ የተመለሰውም እስራኤል “እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” የእስራኤል አምላክ ያህዌ በምድር ኃያላን ላይ የወደደውን የሚያደርግ ሉዓላዊ አምላክ እንጂ "ፈጽሞ ቀን የሰጠው የአንድ ዘመን አምባገነን" እንዳልሆነ አስተውሉ።

ሰው በፈረሱ ለጓምን አስገብቶ እንደወደደ እንደሚያሾረው እንዲሁ እርሱ የጎግን ጭፍራ አፍንጫውን በመንጠቆ ይዞ ወደ ኋላ ሊመልሳቸው፣ ጥፋትንና ሞትን ካገለገሉ በኋላ ራሳቸው ወደጥፋታቸውና ሞታቸው እንዲነዱ ያደርጋቸዋል። ይህም እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት፦ 

“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ በዚያች ዘመን ብዙ ዓመት ትንቢት በተናገሩ በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያቶች በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን? በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፦ በእርግጥ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤ ከፊቴም የተነሣ የባሕር ዓሣዎችና የሰማይ ወፎች የምድረ በዳም አራዊት በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ በምድርም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮችም ይገለባበጣሉ ገደላገደሎችም ይወድቃሉ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል። በተራሮቼም ሁሉ በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ሲል የተናጋረው ነው። 

ምዕራፍ 39 ቁ 1 “አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሞሳሕና የቶቤል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤ እመልስሃለሁ፥ እነዳህማለሁ፥ ከሰሜንም ዳርቻ እጐትትሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ። ከግራ እጅህም ቀስትህን አስጥልሃለሁ፥ ከቀኝ እጅህም ፍላጾችህን አስረግፍሃለሁ። አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። አንተ በምድር ፊት ላይ ትወድቃለህ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ በማጎግም ላይ ሳይፈሩም በደሴቶች በሚቀመጡ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቅ ዘንድ አደርጋለሁ፥ ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላስረክስም፤ አሕዛብም እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እነሆ፥ ይመጣል ይሆንማል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያልሁት ቀን ይህ ነው።” (ሕዝቅኤል. 38፥ 17- 39፥ 1-8) ሲል እንደተናገረው መሆኑ ነው።

ይህ እንግዲህ የጎግ ሠራዊት በያህዌ ብርቱ ቍጣ የሚጠፋ ስለመሆኑ የሚናገር መግለጫ ነው። ይህ ግን በዚህ ታላቅ ጥፋት ውስጥ ታላቁን ፍጻሜአቸውን የሚቀበሉትን ያኔ ገና ያልተፈጸሙ ትንቢቶችንም አካቶ የቀረበ ነበር። ልብ አድርጉ፦ ያህዌ ፍርዱን የሚገልጽበት ዘዴ በግነታዊ ቋንቋ የተሞላ ነው፣ ወይም እኛ ምስል ከሳች የአነጋገር ዘይቤ፣ የቋንቋ ውበትን የተሞላ፣ አልያም አጽንዖት መስጠት እንደምንለው አይነት ነገር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በራሷ በእስራኤል ላይም ሆነ ወይም በእስራኤል ጠላቶች ላይ ያህዌ ቁጣውን ሲገልጥ ለእያንዳንዱ የፍርድ ተግባር ግነታዊ አገላለጽ ጥቅም ላይ መዋሉ የተለመደ ነው። ጌታ ኢየሱስም ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋትና ስለ ብሉይ ኪዳን ሥርዓት መወገድ ሲናገር ተመሳሳይ ትንቢታዊ ቋንቋ እና ዘይቤ ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 24፥ 29፤ ማርቆስ 13፥ 24፤ ሉቃስ 21፥25)

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የእግዚአብሔርን ጠላቶች እጣ ፈንታ የሚተነብዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እዚህ ላይ እናንሳ፦

ኢሳይያስ 13፥ 10 “የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።”

ኢሳይያስ 13፥ 13 “ስለዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት በጽኑ ቍጣ ቀንም ሰማያትን አነቃንቃለሁ፥ ምድርም ከስፍራዋ ትናወጣለች።”

ጌታ ኢየሱስም ኢሳ.13፥ 10 ላይ “የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።” የሚለውን ጠቅሶ፣ በኢየሩሳሌም ከተማ እና በቤተ መቅደሱ ላይ ስለሚሆነው ጥፋት ሲናገር ሊመጣ ያለውን ይህንን ፍርድ ለማመልከት ተጠቅሞበታል። ኢሳይያስ 13:13 ላይም “ስለዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት በጽኑ ቍጣ ቀንም ሰማያትን አነቃንቃለሁ፥ ምድርም ከስፍራዋ ትናወጣለች።” የሚለውም እንደ ቁጥር 10 ሁሉ በሜዶናውያን እና በፋርሳውያን ስለሚደርስ ፍርድ፣ ባቢሎንም ስለ መውደቋ የተነገረ ትንቢት ነው። ጌታ ኢየሱስ ግን ከዚህ ትንቢት በተወሰደ የቋንቋ ዘይቤ ይህንን ፍርድ በኢየሩሳሌም ከተማ እና በቤተ መቅደሱ ጥፋት ላይ ተጠቀመበት።

ሕዝቂኤል 32፡ 2፣ 7-8 “የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በለው፦ የአሕዛብን አንበሳ መስለህ ነበር፥ ነገር ግን እንደ ባሕር ዘንዶ ሆነሃል፤ በወንዞችህም ወጥተሃል፥ ወኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል። ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፤ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም። የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በላይህ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔ” ያህዌ ግብፅን እና ፈርዖንን ሊያጠፋ በተቃረበበት ወቅት በተመሳሳይ ትንቢታዊ ቋንቋ የተናገረው እንዲሁ ነው። እንደገናም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ኢየሩሳሌም በመንፈሳዊ ምሳሌ በራዕይ 11፡8 ላይ ስትጠቀስ “... እርስዋም…. ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።” በሚል ግብፅ ሆና መገለጧ የአጋጣሚ ጉዳይ አልነበረም፣። ዳግመኛም በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢየሩሳሌም በመንፈስ ግብፅ ሆና መገለጧ በአጋጣሚ አይደለም በራዕይ 11፡8። ከእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች የምንረዳው ኢየሱስ ባቢሎንን ያገኛት ታሪካዊ ጥፋት በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ላይ እንዴት እንደሚፈጸም እንዲሁም ዮሐንስ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ላይ የደረሰው ጥፋት በኢየሩሳሌም ላይ የሚደርሰውን ፍርድ እንዴት እንደሚያመለክት እንደተጠቀመበት ያስረዳናል። ሐዋርያው ​​ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፉ ውስጥ እነዚያ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አይሁድ የእግዚአብሄር ጠላቶቹ በመሆናቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ታላቁን የእግዚአብሔር የቁጣ ቀን በሚያሳይ ቃል ገልጾታል። ይህም በሉቃስ 19፡ 27 ላይ “እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው”፤ እንደተባለው ነው። 

ከሕዝቅኤል ንግግር የምናስተውለው አንድ ነገር እርሱ ቆየት ብሎ የተነበየው ጉዳይ በአይነቱ በአስቴር ዘመን የሚፈጸመውን ነው። እነዚያ አይሁዶች ተማርከው በተጋዙባቸው ግዛት የነበሩ ሰዎች ያኔ ከነበረው መንግስት ጋር ሰላም በነበራቸው ጊዜ ለአይሁድ ግን ጠላቶቻቸው ሆኑ። የሕዝቅኤል መጽሃፍ ጎግ ማንጉግ ሕዝቅኤል በኖረበት የአስቴር ዘመን በአስቴር መጽሓፍ የአይሁድ ሕዝብ ጠላቶች (የእግዚአብሄር ሕዝብ ጠላቶች) ሆነው እንደተገለጡ ሁሉ፣ የዮሓንስ ራእይ መጽሃፍ ጎግ ማንጉግም ዮሓንስ በኖረበት የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሄር ሕዝብ የቅዱሳኑ ጠላቶችና አሳዳጆች የሆኑትን ተቃዋሚ አይሁድን የሚያመለክቱ ናቸው። ይህም ለእኛ ምሳሌ ነው። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የማያምኑ አይሁዶች የእግዞአብሄር ቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ሆነው በግዛታቸው ውስጥ አማኞችን ከበው ያስጨንቁ ስለነበሩ በእግዚአብሔር ሕዝብ በክፋት ተነስተው የነበሩት የሕዝቄል ዘመን ጎግና ጭፍሮቹ በእግዚአብሄር ፍርድ እንዲጠፉ እንደተደረጉ እነዚህም ደግሞ በእግዚአብሄር ፍርድ ጠፍተዋል። በራዕይ 6፡12-17 እና በራዕይ 8፡12 ላይ የዚህን ተመሳሳይነት በጉልህ እናያለን። 

ራእይ 6፡ 12-17 “ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፥ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጕር ጥቁር ሆነ፥ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፥ በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፥ ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፥ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ። የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥ ተራራዎችንና ዓለቶችንም፦ በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።” 

ራእይ 8፡ 12 “አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት።” 

የጎግን ሽንፈት የሚጠቁሙ ሌሎች የብሉይ ኪዳን ምዕራፎች በኢዩኤል 3፡1 እና ዘካ. 12 እና 14፤ እንዲሁም በሶፎንያስ ትንቢትም እናገኛለን። እነዚህን የሕዝቅኤል መጽሓፍ ምዕራፎች በሕዝቅኤል ዘመን ከተከናወነውና በመጽሓፈ አስቴር ውስጥ ካለው ትረካ ጋር ጋር በተዛመደ ትክክለኛ ግንኙነት ውስጥ እያገናዘብን ነው ማየት ያለብን። ሕዝቅኤል ከ597 ዓ.ዓ እስከ 571 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ትንቢት የተናገረ እስከሆነ ድረስ፣ ከዚያ ጊዜ አንጻር ጥቂት ዓመታትን ወደፊት ወይም ወደኋላ ብንወሰድና ብንሰጥ ሁለቱም መጻህፍት የአንድ ዘመን ታሪክ እንዳላቸው እናስተወላለን። ሐማ የተባለው የአስቴር መጽሓፍ ከፉ ሰው ለአይሁዳዊው መርዶኪዮስ ባዘጋጀው የመሰቀያ ግንድ ላይ ተሰቅሎ የሞተው በ585 ዓ.ዓ አካባቢ ነበር። ምንም ያህል በመጻኢያን የሚቀነቀነው አስተምህሮ ያንን ቢልም እንኳን የአስቴርን መጽሐፍ ግን አሁን ወደፊት ባለችው በዘመናዊቷ ጽዮናዊት እስራኤል ላይ ከሚደርሰው እልቂት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለውም። እነዚህ የሕዝቅኤል ምዕራፎችንም ግልጽ በሆነ መንገድ በአውደ ምንባቡ ጎግንና ርኩሳን ጭፍሮቹን ሁሉ ወደ ጥፋታቸው እየመራቸው ያለው ጌታ እግዚአብሔር ራሱ እንደሆነ ያሳየናል። የአስቴር መጽሓፍ ከግዞት ታሪክ እና የኢየሩሳሌምን ከተማ ቤተመቅደሱንና የከተማይቱን ቅጥሮች እንደገና ለመገንባት ከግዞት ወደ ኢየሩሳሌም ከመመለስ ጋር ካለው ግኑኝነት አንጻር ሲታይ የሕዝቄል ትንቢት ከዚህ አውድ ጋር የስማማል፤ መጽሓፈ አስቴር በዕዝራ 5 እና 6 ላይ ያለው ታሪክ የተፈጸመበት የጊዜ ገደብ ወስጥ ያለ ነው።

ከ70ው ዓመት ምርኮ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲገነቡ ቂሮስ ባዘዘው መሠረት ወደ አገራቸው መምጣት የቻሉት 50,000 የሚያህሉ አይሁዳውያን ብቻ ነበሩ። ኤርምያስ 25:11-13። ወደ ባቢሎን ተማርከው የተወሰዱ ወይም በግዞት ላይ ተወልደው የነበሩት ሌሎቹ በሙሉ በዚያው በነበሩበት እንዲቆዩ መርጠዋል። የመጽሐፈ አስቴር አጠቃላይ ሁኔታ የሚያጠነጥነው እነዚያ በባቢሎን ቀርተው በነበሩቱ ላይ ነው። የታሪኩም ትዕይንት የተፈጸመው የፋርስ ዋና ከተማ በነበረቸው በሱሳ ነው፣ ዘመኑም አውሳብዮስ [Ahasuerus] ተብሎ የሚጠራው የንጉሱ የዳርዮስ ልጅ አርጤክስስ የገዛበት ዘመን ነበር። 

እግዚአብሔር በመጽሓፈ አስቴር ትረካ ውስጥ የሌለ ያህል ስሙ እንኳ አንዴ ሳይጠቀስ ተሸሽጓል፣ ያም ቢሆን ግን በስራ ላይ ደግሞ ነበር፣ ለህዝቡ በሚያደርገው ጥበቃና ማዳን ውስጥ ንቁ ሰራተኛ ነበር። ይህም እውነት ሎውል ባስቀመጠው ቃል ውስጥ “ታላቁ ተበቃይ ግድ የለሽ የሆነ ቢመስልም የታሪክ ገጾች ግን እየመዘገቡት ነበር። የሞት ድምጽ ያረጀው ስርዓቱና አስፈሪ ቃሉ፣ የሚውጠውን ፍለጋ በዚያ ጨለማ ውስጥ በኃይል እያገሳ ነበር። እውነት እስከ ወዲያኛው ሊሰቀል በመሞቻ ማማው ላይ፤ ስህተትም ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ያለ ይመስላል። ነገር ግን ያ የመሞቻ ማማ የመሰለ መንጠልጠያ ሊመጣ ያለውን የወደፊቱን ክብር ያውለበልባል፤ ከዚያ ድቅድቅ ጨለማ በስተጀርባ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑትን በጥላው እየጠበቀ ከበላዩ ቆሞአል” በሚል ቃል በግልፅ ሰፍሯል። 

ጄምስ ቢ. ጆርዳን አይሁዶችን ለመዝረፍ የተደረገውን ሴራ የምናገኘው በመጽሐፈ አስቴር ውስጥ ነው ብሎ ያምናል፣ ይህ ደግሞ በምላሹ ያስከተለው ውጤት አይሁዳውያን በተራቸው ጠላቶቻቸውን በመዝረፍ የተደመደመ ነው። ይህም ክስተት ከዚያ በኋላ ከዓመታዊው የፑሪም ክብረ በዓል ጋር በታላቅ ስነ-ስርዓት ተከብሮ ያልፋል። ጆርዳን በመቀጠል የሕዝቅኤል 38 እና 39ን አውደ ምንባብ በማጽናት፡- “ሕዝቅኤል የማጎጉ ልዑል የሆነው፣ ጎግ እና አጋሮቹ የሚፈጽሙትን ጥቃት ገልጿል። ሕዝቅኤል በዓለም ዙሪያ ያሉ ድብልቅ ህዝቦች በምድሪቱ ላይ በሰላም የሚኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ብሎ የሳላቸውን እንደሚያጠቁ በግልጽ ተናግሯል። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ግን ጠላቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ያሸንፏቸዋል፣ የሚበዘብዙት ምርኮም እጅግ በጣም ብዙ ይሆናል። በውጤቱም “ከእንግዲህም ወዲያ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” (ሕዝቄል 39፡ 21-23)፤ … የታሪኩን ቅደም ተከተል ካስተዋልነው ይህ ሁሉ በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ ይጣጣማል። የአስቴር መጽሓፍ ታሪክ የተከናወነው በዳርዮስ የግዛት ዘመን ሲሆን፣ ይህም በታላቁ ሊቀ ካህናት በኢያሱ እና በዘሩባቤል ጊዜ ቤተ መቅደሱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደገና ከተገነባ በኋላ፣ እንዲሁም ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና ለመገንባት ከመቻሉ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ነው...። ሕዝቅኤል 38-39 ጎግ (ሃማን) እና አጋሮቹ በአይሁዶች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ይገልጻል። ስለዚህ፣ ይህንን ውድቅ የሚያደርግ አሳማኝ ሃሳብ እስካልቀረበ ድረስ እኔ በግሌ የምጠቁመው የትርጓሜ መላምት፡- ሕዝቅኤል 34-37፣ ምርኮኞቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘሩባቤል ተመርተው ምድራዊውን ቤተ መቅደስ እንደገና ለመገንባት መመለሳቸውን ይገልፃል። ሕዝቅኤል 38-39 ጎግ (ሃማን) እና አጋሮቹ በአይሁዶች ላይ ያሴሩትን ጥቃት ይገልጻል፤ የሚል ነው።

የአስቴር መጽሐፍና የሕዝቅኤል መጽሐፍ እነዚያ የአይሁድ ጠላቶች ከየት እንደመጡ በሃሳብ ይስማማሉ። ሕዝቅኤል 38፡5-6 የእስራኤል ጠላቶች ከፋርስ፣ ከኩሽ እና ... ከሰሜን ራቅ ካሉ አካባቢዎች እንደመጡ ይነግረናል፣ እነዚህም ሁሉም ስፍራዎች በአስቴር ዘመን በፋርስ ግዛት ወሰን ውስጥ ይገኙ የነበሩ ናቸው። ከአስቴር እንደምንረዳው የፋርስ መንግሥት በጠቅላላ “ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ በ127 አውራጃዎች” የተስፋፋ ነበር፤ (አስቴር 8፡9)፣ ኢትዮጵያ (ኩሽ) እና ፋርስ በአስቴር 1፡1፣ 3 እና ሕዝቅኤል 38፡5 ላይ ተዘርዝረዋል፡ “ፋርስ ኢትዮጵያና ፉጥ ከእነርሱ ጋር ሁሉም ጋሻና ራስ ቁር ይይዙ የነበሩ ናቸው። ሌሎቹም አገራት የተመሠረቱት "ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ" ድረስ ባለው ጂኦግራፊያዊ ድንበር ውስጥ ሲሆን ንጉሡ አውሳብዮስ የሚገዛባቸው "127 አውራጃዎች" ነበሩ (አስቴር 1: 1) "በሌላ አነጋገር አይሁዳውያን ከሁሉም የፋርስ አውራጃዎች በመጡ ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል የሚለው ግልጽ ሀሳብ በሁለቱም ምንባባት ውስጥ የተነገረ ነው፣ በሕዝቅኤል የተዘረዘሩ አገራት ሕዝቦችም ትንቢቱ ፍጻሜውን የሚያገኝበት የፋርስ ግዛት አካል ነበሩ። በሁለቱም የመጻህፍቱ ምንባባት ውስጥ የሚገኙት ነጽጽሮች ሊያሳስቱ የማይችሉ ናቸው። ግራንት ጄፍሪ ሊከራከር ሲሞክር “ቅጥር የሌላቸው መንደሮች” (ሕዝ. 38፡11) የሚለው የሕዝቅኤል አባባልም እንኳ የወደፊቱን ሩቅ ፍጻሜ አያመለክትም። ይህም ከአስቴር መጽሓፍ ትረካ ጋር ላለው ግንኙነት ተጨማሪ ማስረጃ ነው። እርሱም የሁለት ኢምፓየር ወግ እና ጎግ በአይሁዶች ላይ ያቀደው የሴራ እቅድ እና አላማ አካል ነው።

“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይገባል፥ ክፉ አሳብንም ታስባለህ፥ እንዲህም ትላለህ፦ ቅጥር ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ ተዘልለው ወደሚኖሩ፥ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡ እገባለሁ”፤ (ሕዝቅኤል 38: 10-11)፤ “አስቴርም እንደ ገና በንጉሡ ፊት ተናገረች በእግሩም ላይ ወድቃ እያለቀሰች የአጋጋዊውን የሐማን ክፋትና በአይሁድ ላይ የተተነኰለውን ተንኰል ይሽር ዘንድ ለመነችው።” (አስቴር 8፡ 3)፤ ሴራ፣ እቅድ፣ ንድፍ ወይም አላማ በሚል የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል “ቻሳብ” ወይም “ማቻሼቤት” የሚል ሲሆን እርሱም የክፉ አስተሳሰብ ዓላማ፣ ወይም የተንኮል እቅድ ነው፣ ክፉ ሐሳብ መጥፎ፣ ሴራ፣ ወይም ጥሩ ያልሆነ ምክር እንደ ማለት ነው። አስቴር 8:3፣ 5፤ 9፡25።

ስለዚህ ጎግ በአይሁድ ላይ ክፉ ዕቅድን፣ የተንኮል ሐሳብን፣ መጥፎ ሴራን፣ ጥሩ ያልሆነ ምክር ነድፎ ነበር፣ ማሰቡንስ እርሱ አሰበ፣ እግዚአብሔር ግን ሊመታው እጆቹን አዘጋጅቶ መለሰው፣ ጎግም በወጥመዱ ተሰናክሎ ወደቀ ተበላም፣ እግዚአብሔርም በማጎግ ላይ እሳትን ያወርዳል። ለዚህ ማጣቀሻ እንዲሆን በመዝሙር 21፡ 7-13 እንዲህ ይላል፦ “ንጉሥ በእግዚአብሔር ተማምኖአልና፥ በልዑልም ምሕረት አይናወጥም። እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታግኛቸው፥ ቀኝህም የሚጠሉህን ሁሉ ታግኛቸው። በተቈጣህም ጊዜ እንደ እሳት እቶን አድርጋቸው፤ እግዚአብሔር በቍጣው ያጠፋቸዋል፥ እሳትም ትበላቸዋለች። ፍሬአቸውን ከምድር ዘራቸውንም ከሰው ልጆች ታጠፋለህ። ክፋትን በአንተ ላይ ዘርግተዋልና፥ የማይቻላቸውንም ምክር አሰቡ። ወደ ኋላቸው ትመልሳቸዋለህ፤ ፍላጻን በፊታቸው ላይ ታዘጋጃለህ። አቤቱ፥ በኃይልህ ከፍ ከፍ በል፤ ጽናትህንም እናመሰግናለን እንዘምርማለን።”

በመጽሓፈ አስቴር የቀረበው ታሪካዊ ዘገባም እነዚያ የሃማ ተንኮሎች እንዴት እንደተገለበጡ እና የአይሁድ ጠላቶች ወደ ኋላቸው እንደተመለሱ እንደጠፉም የሚገልጽ ዘገባ ነው። አስቴር 9:2, 5-6,12 እና 15-16 ያለውን ትረካ ከሕዝቅኤል 38:18-23: 39:2-6, 17-20 ካለው ትንቢት ጋር ለሚያነጻጸር አንባቢ የጎግንና የጭፍሮቹን መጨረሻ ለማወቅ ይህ አይታጣውም።

የአይሁዶች ጠላቶች ፍላጎታቸው አይሁድ ከተማይቱን መልሰው እንዳይገነቡ “ዓመፀኛይቱንና እጅግም የከፋቺቱን ከተማ ይሠራሉ፥ ቅጥርዋንም ያድሳሉ፥ መሠረትዋንም ጠገኑ።” (ዕዝራ 4፡ 6፣ 12 ) ሲሉ ባቀረቡባቸው ክስ ሊከለክሏቸው ነበር።

“የታሪክ መዛግብት ተፈልገው “ይህች ከተማ ዓመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጐዳች፥ ከጥንቱም ሽፍትነት በእርስዋ እንደ ተጀመረ …” ምርመራ እንዲደረግ እነዚያ ተቃዋሚ ከሳሾቻቸው ይጠይቃሉ (ዕዝራ 4፡ 5) ይህም ወደፊት ከእስራኤል ዘንድ ወታደራዊ ስጋት እንዳለባቸው የሚያመለክት ነው። እንግዲህ እነዚህ ኹነቶች ሐማ የንጉሱ የአርጤክስስን ጆሮ ያገኘው ለምን እንደሆነ ሊገልጹ የሚችሉ ናቸው። በተጨማሪም ኢየሩሳሌም ቅጥር የሌላት ከተማ እንደነበረች ይህም በሕዝቅኤል 38:11 ላይ ያለውን የወቅቱን ትንቢታዊ መግለጫ እና በአስቴር 9:19 ላይ ካለው ታሪካዊ ፍጻሜ ጋር የሚስማማ ያደርገዋል። 

በቀጣዩ ክፍል በዚሁ ላይ ትኩረት አድርገን፣ በዮሓንስ ራእይ ስለ ጎግ ማንጉግ የተነገረውን ማጠቃለያ አድርገን ተጨማሪ ብርሃን በሚሰጡን ነጥቦች እንመለሳለን።

gkr

ክፍል አምስት

አጋግ የተባለው ሁሉ ስለ አጋጋዊው ሐማ ነው

በመጽሓፈ አስቴር ያለው ዋነኛ የአይሁድ ጠላት የአጋጋዊው የሐመዳታ ልጅ ሐማን ነው። አስቴር 3:1, 10; 8፡3፣ 5፡9፡24። አጋጋዊነት የአማሌቅ ዘር ነው፣ እርሱም ከእስራኤል ጽኑ ጠላቶች አንዱ ነበር። ይህንንም በዘኁልቁ 24፡20 ላይ እናነባለን። "አማሌቅ የአሕዛብ መጀመሪያ ነበረ ፍጻሜው ግን ጥፋት ሆነ" በዘፍጥረት 10፡2፣ “ከአባታቸው ከያፌት የተወለዱ የያፌት ልጆች ጋሜር፥ ማጎግ፥ ማዴ፥ ያዋን፥ ይልሳ፥ ቶቤል፥ ሞሳሕ፥ ቴራስ ናቸው። የሚል እናገኛለን። ጋሪ ዴማር፣ Why the End of the World Is Not in Your Future" በሚለው ኤሌክትሮኒክስ መጽሓፉ ውስጥ ይህንን ነጥብ ግሩም አድርጎ አስቀምጦታልክ። እርሱም እነዚህ አኃዞች በሕዝቅኤል መጽሓፍ ውስጥ መዕራፍ 38 እና 39 ላይ ጎልተው እንደሚታዩ ተናግሯል። ፣ ሃማ እና ልጆቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገኙት አማሌቃውያን መካከል የመጨረሻዎቹ ናቸው።

በዘኍልቍ 24፡7፣ ሴፕቱጀንት (LXX) አጋግ የሚሉውን ጎግ ተብሎ ተተርጉሟል። ለአስቴር 3:​1 እና 9:​24 ዘግየት ብሎ የተጻፈ አንድ ጥንታዊ የብራና ጽሑፍ ሐማን ሲጠቅስ ጎጋዊ መሆኑን ያመለክታል። አጋግ እና ጎግ በዕብራይስጥ ሆሄያቸው እና ትርጉማቸው በጣም ተመሳሳይ ናቸው። አጋጌት ማለት "ወደ እላይ እላለሁ" ማለት ሲሆን ጎግ ደግሞ "ተራራ" ማለት ነው። ሌዊስ ባይልስ ፓቶን ስለ አስቴር በሰጠው ቴክኒካል ሐተታ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- በብሉይ ኪዳን የተጠቀሰው አጋግ ብቸኛው የአማሌቅ ንጉሥ ነው (ዘኍልቍ 24፡7፤ 1 ሳሙ. 15:9]። አይሁድ ሁሉ እና በርካታ ክርስቲያን የመጽሓፍ ቅዱስ ተንታኞች ሃማን በተመለከተ የዚህ አጋግ ዘር እንደሆነ ያስባሉ። ይህ አመለካከት ትክክል ሊሆን ይችላል፣ ምክንያቱም የእርሱ ተቀናቃኝ የሆነው መርዶክዮስ ቀደም ሲል አጋግን ከዙፋኑ ያወረደው የቂስ ልጅ የሳኦል ዘር ነውና፣ 1ሳሙኤል 15፡ 8-16፤ በተለየ ሁኔታም በሕጉ የተረገመ ነው [ዘዳ. 25፡17]። ስለዚህም ምናልባት የታሪኩ ጸሐፊ ሐሳቡ ሐማን ከዚህ ሕዝብ የዘር ሐረግ የተገኘ እንደሆነ ውክልናውን ለማሳየት ሲሆን ይህም በእስራኤል ላይ ጥንታዊና እና ሊጠፋ በማይችል ጥላቻ መገለጡን ለማሳየት ነው፤ (አስቴር 3፡10 ተመልከቱ፣ ቃሉ ሓማን ሲያስተዋውስተዋው “የአይሁድ ጠላት” ነው፣ ይለዋል)።

ጥንታዊ ጽሑፍ ሐማን የጎግ ተወላጅ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። ፖል ሃውፕ ስለሃማ በተደረጉ ገለጻዎች ውስጥ ያለውን ግንኙነት ሲያብራራ እንደ አጋጋዊ እና የጎግ ተወላጅ አድርጎ ይመለከተዋል። “በዘኍልቍ 24፡7 ላይ ያለው የሰባ ሊቃናት ትርጉም አጋግ በሚለው ፈንታ “ጎግ” ያሚለውን የሚጠቀም ሲሆን በአሞጽ 7፡1 ደግሞ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ (ጎግ) አጨዳ በኋላ የበቀለ የገቦ ነበረ።” በሚለው ላይ ጎግ የሚለውን ስም ጨምሮ ይጠቀማል። በጽሁፍ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ተያያዥነቶች ልንተዋቸው አይገባንም። ለዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ትርጉም በሆነው የአስቴር መጽሐፍ ክፍል በአራማይክ ቋንቋ ትርጉምም የሚከተለው ይገኛል፡- "የፍርዱ መጠን በዓለሙ ሁሉ ጌታ ፊት በቀረበ ጊዜ፥ ያ ከፉ ሰው ሐማ የመቅደስህ ቤት እንዳይሠራ ማንም ሰው ከሱሳ ወደ ኢየሩሳሌም እግሩን አያነሳም ብሎ በእብሪት ተናግሮ አልነበረምን?" 

አንቶን ሾልዝ (1892) ሲጽፍ፣ “የአስቴር መጽሐፍ ሕዝቅኤል ስለ ጎግ ለተናገረው ትንቢት ተጨማሪ እድገትና ትንቢታዊ ድግግሞሽ ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። በፓይቶን የተጠቀሰውና የመጽሐፈ አስቴር ወሳኝና ገላጭ ሐተታ (Commentary) ገጽ 56 ላይ በእነዚህ ሁሉ የጎግ-አጋጋውያን ማጣቀሻዎች ውስጥ ያለው ነጥብ በሕዝቅኤል 38 እና 39 እንዲሁም በመጽሐፈ አስቴር መካከል ያለውን ጽሑፋዊ ተመሳሳይነት ማየት የቻሉ በርካታ ምሁራን እንዳሉ ለማመልከት ነው።

የሃሞና ከተማ እና የሃሞን ጎግ ሸለቆ። የጎግ ሰራዊት የተቀበረው እዚህ ነው። ሕዝቅኤል. 39:11, 15:- በሕዝቅኤል ውስጥ ሃሞን የሚለው ቃል በዕብራይስጡ አጠራር ሐማን ከሚለው ስም ጋር በትክክል ይመሳሰላል። የሚለያዩት አናባቢዎቹ ብቻ ናቸው።

ሐማ በንጉሥ በአርጤክስስ የመጀመሪያ ፈቃድ ከ127ቱ አውራጃዎች የሰበሰበው የብዙ አህዛብ የጦር “አለቃ” የሆነ እና ደካማ ፍጥረት የሆኑ ጠላቶቹን አይሁድን ለማጥፋት የተነሳ ነው። : ዘጸ. 17:8-16; ዘኁ. 24: 7፤ 1ሳሙ 15: 8, 1ዜና 4: 42-43፤ ዘዳ. 25: 17-19። እርሱም ከእርሱ ጋር በነበሩት አለቆች ሁሉ ላይ ሥልጣን የነበረው ነው” (አስቴር 3፡1፤ ደግሞ 1፡3 ተመልከት)። 

“ከእርሱ ጋር በነበሩት አለቆች ሁሉ ላይ ሥልጣን” ስላለው ይህ በራሱ “አለቃ” ያደርገዋል። ለምሳሌ በአስቴር 3፡12 ሐማ የመኳንንቱ፣ የገዥዎችና የመሳፍንቱ መሪ ሆኖ እንዴት እንደተገለጸ እናነባለን። በሕዝቅኤል 38፡2-3 እና 39፡1 ላይ፣ በምዕራፎቹ ቀጣይ ምንባባትም የዚህ ማዕረግ አስፈላጊነት ግልጽ ይሆናል።” በሕዝቅኤል 38፡2-3 እና 39፡1 ላይ ዋናው ልዑል ሃማ እንደነበረ እናያለን።

በሕዝቅኤል ትንቢትና በአስቴር መጽሐፍ ላይ የሚታየውን የገንዘብ ብዛት ተከተሉ ሕዝቅኤል የጻፈው አይሁዶችን ለመውረርና ለመዝረፍ፣ መታቀዱን ነው (ሕዝ. 38:12-13)፤ እነዚያ ከምርኮ የተመለሱት አይሁዶች ብዙ ብርና፣ ወርቅን ከብቶችንም ይዘው ነበር (ዕዝራ. 7፡15-16፣ 18፣22፣ እንዲሁም ነህምያ 7:71-72). “ንጉሡም ሐማን፦ ደስ የሚያሰኝህን ነገር ታደርግባቸው ዘንድ ብሩም ሕዝቡም ለአንተ ተሰጥቶሃል አለው” ይላል።

ትንቢተ ዘካርያስ ከመጽሐፈ አስቴር እና ከሕዝቅኤል ምዕራፍ 38-39 ጋር ያለው ግንኙነት።

አይሁድ ከምርኮ የተመለሱበት ወቅት ነበር። ሁለተኛውም ቡድን ደግሞ ከዕዝራ እና ነህምያ ጋር ተመልሰዋል። ያኔ አይሁድ ገና እንደገና እያገገሙና የኢየሩሳሌምን እና የቤተ መቅደሱን ግንቦች እንደገና እየገነቡ ያሉበት ሁኔታ ነበር። ዘካርያስ በምዕራፍ 12 የፍጻሜውን ጊዜ አስመልክቶ ከሕዝቅኤል 38-39 ካለው ትንቢት ጋር በተያያዘ ማስረጃን ይሰጣል።

  • ጦርነቱ የሚካሄደው በፈረስ ላይ ተቀምጠው በሚመጡ ሰዎች ነው። ዘካርያስ. 12፡4
  • በግዞት የነበሩት አይሁዶች በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል። ዘካርያስ 12፡7 እና ኤር. 30፡10፣ 18
  • የደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ዋናው የሕዝብ ማዕከል ነው። ዘክ. 12:4, 6-8
  • ህዝቡም በየአባቶቻቸው ቤት ተዘርዝረው ይታያሉ፣ ዘካ. 12:5, 10, 12-13
  • የዳዊት ቤት ክብር አሁንም ድረስ እንኳ ይታወቃል። ዘክ. 12:7-8; ነህ. 3፡15፡; 12:24, 36, 45
  • ንጉሥ ኢዮስያስ በፈርዖን ኒኮ መገደሉም 2ኛ ነገሥት 23:28-30; 2ኛ ዜና 35፡22-27 እንደ ሀገር አሳዛኝ ክስተት አሁንም ይታወሳል። ዘክ. 12፡11።

ዘካርያስ 12 በመጽሐፈ ዕዝራና በመጽሐፈ አስቴር መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ክንውኖች በታሪካዊው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያያቸዋል። የኩነቶቹ ቅደም ተከተልም ይህን ይመስላል። በ598 ዓ.ዓ አይሁዶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የቂሮስ አዋጅ ወጣ ዕዝራ 1፡1-4፤ የቤተ መቅደሱ መልሶ ግንባታም ጅማሬው በ536 ዓ. ዓ ሲሆን የዘካርያስ ትንቢት ደግሞ በ520 ዓ.ዓ. ነበር፤ ቤተ መቅደሱም እድሳቱ የተጠናቀቀው በ516 ዓ.ዓ. ነው። በአስቴር መጽሐፍ እና በዕዝራ ውስጥ የተገለጹት አብዛኛዎቹ ክንውኖች የተፈጸሙት በዘካርያስ 12 ላይ ካለው ትንቢት በኋላ ነው። ነብዩ ሐጌና ነቢዩ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩት አይሁዳውያን በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት ተናገሩ፤ እነርሱም ቤተ መቅደሱን እንደገና ለመሥራትና ለመጨረስ እንደ ተነበዩ እናውቃለን፤ ዕዝራ 5፡1-2።

ከፍ ሲል ለማለት እንደተሞከረው፣ የሕዝቅኤል መጽሃፍ ጎግ ማንጉግ ሕዝቅኤል በኖረበት የአስቴር ዘመን በአስቴር መጽሓፍ አውድ የአይሁድ ሕዝብ ጠላቶች (የእግዚአብሄር ሕዝብ ጠላቶች) ሆነው እንደተገለጡ ሁሉ፣ የዮሓንስ ራእይ መጽሃፍ ጎግ ማንጉግም ዮሓንስ በኖረበት የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሄር ሕዝብ አውድ የቅዱሳኑ ጠላቶችና አሳዳጆች የሆኑትን ተቃዋሚ አይሁድን የሚያመለክቱ ናቸው። በብሉይ ኪዳን በተለያየ የታሪክ ምእራፍ እግዚአብሔር የፈረደባቸው የአህዛብ መንግስታት ግብጽ፣ ባቢሎን፣ ሰዶም፣ አሶር፣ ወዘተ እየተባሉ በየስማቸው ተጠቅሰዋል፤ በአመዛኙ እነዚህ የአህዛብ ነገስታተና ሕዝቦች በራእይ መጽሃፍ ውስጥ እግዚአብሔር ሊፈርድባት ባለችው በአመጸኛይቱና በአመንዝራይቱ እስራኤል ተወክለዋል። እስራኤልን ግብጽ፣ ባቢሎን፣ ሰዶም ወዘተ እያለ እንደሚጠራት ሁሉ ጎግ ማንጉግ ብሎ ደግሞ ይጠራታል። የሕዝቅኤል ዘመን ጎግ ማንጉግ እዚያው በነብዩ ዘመን ያለፈ የትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ባለመረዳት ጎትቶ አምጥቶ ገና ያለቀቀን የዘመናችን ጣጣ አድርጎ መተርጎምና ማስተማር በእውነቱ ልክ አይደለም። በይዘቱ እጅግ አድርጎ ምሳሌአዊና ምስል ከሳች በሆነው የራእይ መጽሃፍም ጎግ ማንጎግ መጠቀሱ ያን ያህል ግራ ሊያጋባን አያስፈልግም፤ ምክንያቱም የራእይም መጽሓፍ ቢሆን መተርጎም ያለበት በጸሓፊውና በበኩረ ተደራስያኑ አውድ መሆን ስላለበት ነው። ይህንን የሚያሳይ ጥቂት ነገር ላንሳና አምስተኛውን ክፍል ጥናታችንን ላብቃ። 

በራእይ 20፥ 8 ላይ የተነገረው የጎግ እና ማጎግ ማጣቀሻ ወደ 70 ዓ.ም የትንቢት ፍጻሜ የሚጠቁም መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም ይህ ከ70 ዓም በፊት ቀደም ብሎ የተጻፈ አቡቀለምሲስ የትንቢቱ ፍጻሜ ከኢየሩሳሌም ውድመት ጋር የተያያዘ ነውና። በብሉይ ኪዳን ያለው የጎግ እና ማጎግ ማጣቀሻ ሁሉም አሕዛብ እግዚአብሔርን የሚያውቁበት አውድ መቼ እንደሆነ በሚያመለክትበት መልኩ መቅረቡን ከፍ ሲል ተመልከተናል (ሕዝቅኤል 38፡16፣ 23፤ 39፡21) -ይህም ጊዜ በእርግጥ የአዲስ ኪዳንን የመሲሁን ዘመን የሚያመለክት እንደሆነ ግልጽ ነው። በሕዝቅኤል 38:16 “ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፥ ጎግ ሆይ፥ በዓይናቸው ፊት በተቀደስሁብህ ጊዜ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።” የሚለው ጊዜን አመልካች የሆነው የሕዝቅኤል ትንቢት በመጨረሻው ዘመን (“በኋለኛው ዘመን”) ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ይናገራል። ሕዝቅኤል ሲናገር ብዙውን ጊዜ “በዚያ ቀን” የሚለውን ሃረግ ይጠቀማል (ሕዝቅኤል 38: 10, 18, 19፤ 39: 8, 11, 13, 22) እርሱም የጌታን ቀን የሚያመለክት ትንቢታዊ ማጣቀሻ ነው። ያም ቀን ለፍጻሜው በእስራኤል ላይ የሚመጣውን ፍርድ ምልክት ያደርጋል (ሕዝ 38፡18)።

ይህም ሁሉ ለ70 ዓ.ም. ፍጻሜ የተነገሩ ትንቢቶችን የሚጠቁሙ ናቸው። ሐዋርያው ​​ጴጥሮስ ሲናገር ከሳሙኤል ፊት የተነሡት ነቢያት ሁሉ ጴጥሮስ ይህ ዘመን ሲል የተናገረለትን ዘመን እንደሚጠቁሙ በግልጽ ተናግሯል (የሐዋርያት ሥራ 3፡24) ስለዚህ ሕዝቅኤልም ቢሆን እየተናገረ ያለው ወደዚያው ጴጥሮስ እየተናገረለት ላለው ዘመን መሆኑን መረዳት እንችላለን። ጌታ ኢየሱስም ያኔ ገና በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትንቢቶቹ በሙሉ በእርሱው ትውልድ እንደሚፈጸሙ በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ አድርጎ ተናግሯል (ሉቃስ 21:22, 32፤ ራእይ 1:1፤ 22:6)።

ጴጥሮስ እና ኢየሱስ ያለ ልዩነት ግልጽ ባደረጉት የጊዜ መግለጫዎች ላይ ተገቢውን ትኩረት ሳናደርግ በራእይ 20 ስለተነሳው ስለ ጎግና ማጎግ የመጀመሪያውን መቶ ክፍለ ዘመን ማንነትም ሆነ ውክልና ሳናስተውል ልባችን የወለደውን ማናቸውንም ነገር መቀላመድ አንችልም። የራእይ መጽሐፍ ጎግ እና ማጎግ የሚያመለክቱት ምንም ይሁን ምንም ግን ፣ አንዳንድ የመጻኢነት ጎራ ዘመን ቆጣርያን እርግጠኛ ሆነው በለየለት ፈጠራ እንደሚያስተምሩት ዘመናዊውን ሩሲያ (ወይም በእኛ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለ ማናቸውንም አይነት ክፉ ተብሎ የተፈረጀ መንግስት ማለት ጨርሶ አይደሉም።

gkr

ክፍል ስድስት

 የሕዝቅኤል መንፈሳዊ መልዕክት ጠቀሜታ

ሕዝቅኤልን ለመረዳት የዮሐንስን ራዕይ ሕዝቅኤል እያየው ካለው ጋር ማነጻጸር አለብን። 

“በተማረክን በሀያ አምስተኛው ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ከወሩ በአሥረኛው ቀን፥ ከተማይቱ ከተመታች በኋላ በአሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ። በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፥ በዚያም ላይ በደቡብ ወገን እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር ነበረ” (ሕዝቅኤል 40፥ 1-2)። 

ከሕዝቅኤል የመጀመሪያው ምዕራፍ አንስቶ እስከ አርባኛው ምዕራፍ ድረስ ሕዝቅኤል ከጌታ ጋር ያደረገው ሕብረት ወደ ሃያ ዓመት ግድም እንደሆነ እናውቃለን። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርን ክብር እና የአሮጌው ኪዳን ህዝቦችን መጥፋት፣ እንዲሁም ተስፋን እና ወደፊት የሚገለጠውን የትንሳኤ ክብር አይቷል። ከአሮጌው ጋር መውጣትን እና ከአዲሱ ጋር መግባትን ተመልክቷል። ሕዝቅኤል ነብይነቱን ሲጀምር የሠላሳ ዓመት ሰው ነበር አሁን ግን አምሳ ዓመት ሆኖታል። የኖረው ህይወቱ ራሱ እንኳ በዚህ ለውጥ ውስጥ የተጠበቀ ነው። ትንቢቱም የአንዳች አሮጌ ነገር ወጥቶ የመሄድ ትንቢት ነው። በሠላሳ አመት እድሜው ክህነቱ ተጀምሮ የሚያበቃው በሃምሳ አመቱ ነው። ይህ ሕዝቅኤል ከምዕራፍ 40 እስከ 48 ያለው ራዕዩ ስለ ዘሩባቤል ቤተ መቅደስም ይሁን ወይም ሄሮድስ በራሱ ጨምሮ ስለሚሰራው ፈጽሞ አይደለም። ዮሐንስም ይህን ቤተ መቅደስ አይቶ ነበር፣ እርስዋም በሙሽሪት ውበት የተሸለመች፣ በሰዎች መካከል ያለች የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነች፣ ከሰማይም የምትወርድ ከተማ ነበረች። እነዚህ ሁሉ ከጌታ ጋር ስላለን ግንኙነት መጠንና መልክ የሚገልጡ ምልክቶች ናቸው። ቤተ መቅደሱ እሱን የሚመለክበትና የምከበርበት ሥፍራ ነው። በራሱም የተቀደሰ ሥፍራ ነው! በባል እና በሙሽሪት ወይም በሚስቲቱ መካከል እንደሚታየው አይነት የፍቅር ሕብረት በከፍተኛ ደረጃ ያለ መቀራረብ ነው! እርሱ እንደሚያድርበት ያለ እንደ ማደሪያው ድንኳን ነው። እርሱ በእኛ ዘንድ በመካከላችን የማደሩና የመገኘቱ መገለጥ ነው! ሕዝቅኤል በረጅም ተራራ ላይ እንደነበረ ሁሉ ዮሐንስም ወደ ረጅም ተራራ ተወስዷል። ጽዮን የእግዚአብሔር ራዕይ እና የእግዚአብሔር ክብር የሚታይባት ከፍተኛ መንፈሳዊ ቦታ ነች። የሕዝቅኤልንና የዮሐንስን ንጽጽር ከዚህ በታች እንመለከታለን። 

“ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፦ ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤ ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፥ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፥ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር። በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ። ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር። የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው። ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፥ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት አሥራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው።” (ራእይ 21፥ 9-16)።

በርካታ ሰዎች በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚታዩትን ሁሉንም ልኬቶች እና እያንዳንዳቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በቀጥታ አነጋገር እንዳለ በጥሬው ለመረዳት ሲጥሩ በትርጉማቸው የመጽሓፉን መልክት በመሳት ጠፍተዋል። በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው በቁጥሮች የተገለጡ ሁሉም ንግግሮች እና መስዋዕቶች እያንዳንዳቸው መንፈሳዊውን እውነታዎች ያመለክታሉ። ለምሳሌ ሐዋርያው ​​ጴጥሮስ በመጀመሪያው መልእክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ቁጥር አምስት ላይ የሚናገረው፣ በአንድ ላይ እየተገነባ ስላለ መንፈሳዊ ቤት፣ ስለ ክህነት ቤተ መቅደስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን መንፈሳዊ መስዋዕቶች ስለ ማቅረብ ነው፣ በንጉሣዊ ክህነታችን ውስጥ አብረን ስለማምለካችን፣ ስለመስራታችንና ስለመሰራታችን በዝርዝር ያወሳል። እነዚህ በጴጥሮስ መልእክቶች ውስጥ ያሉ መንፈሳዊ መሥዋዕቶች ነብያት አስቀድመው ያዩአቸውና በክርስቶስ ፍጻሜአቸውን ያገኙ መሆናቸው መመርመር አለባቸው። ሐዋርያው ጳውሎስም በ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ምእራፍ 3 ላይ ቤተክርስቲያንን ሲገልጻት የእግዚአብሔር ሕንፃ፣ የእግዚአብሔር መስክ እርሻ ይላታል። በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ለማብራራት የጊዜና የቦታ ውስንነት ይገድበናል። ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በጻፉአቸው መልእክቶቻቸው ውስጥ በምልክቶች የተዋቀሩ፣ ዘይቤያዊነት የተላበሱ እና ምሳሌያዊነት የተንጸባረቀባቸው አጠቃቀሞችን እንመለከታለን። አንዳንዶች ቅዱሳት መጻሕፍትን አመናፈሳችኋቸው ብለው ይወቅሱ ይሆናል፣ ይህ ግን ማመናፈስ አይደለምን ይልቁንም ይህ በሐዋርያቱ አስተምህሮ የተለመደ ተግባር ነበር፣ በብሉይ ኪዳን ያሉትን አካላዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮች በአዲሱ ኪዳን ውስጥ ወደ መንፈሳዊ እውነታዎች ለውጦ የማምጣት ከፍተኛ ልምምድ ነበራቸው።

ቅጥሩ፣ በሮቹ እና መሠዊያው

የዚህ ራዕይ የሚታዩ ሌሎች ገጽታዎች ስለ ከተማይቱ ቅጥር፣ ስለ በሮቿ እና በዚያ ስላለው መሠዊያ የተነገረው ነው። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ያለው የከተማይቱ ቅጥር መሠረቶች አሉት እነርሱም አሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት መሆናቸው ተነግሯል። የቅጥሩ ግንብ አገልግሎቱ ለመከላከያ እና ልዩነትን ለማድረግ ነው። ሐዋርያቱ በአገልግሎታቸው ለከተማይቱ እንደ መከላከያ ቆመው ከተማይቱን ከሐሰት እና ከነጣቂ ተኩላዎች ጠብቀዋታል። ቅጥር በአገልግሎቱ ከከተማይቱ ውጭ ያለውን እና በከተማይቱ ውስጥ ያለውን ልዩነት ግልጽ በማድረግ የወሰን ድንበርን ይፈጥራል። “ቅጥር የሌላት ግን የፈረሰች ከተማ” (ምሳሌ 25፡ 28) ሆና ሁልጊዜ ለጥቃት ትጋለጣለች። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ያሉት እነዚህ የቅጥሩ ግንቦች በከበሩ ድንጋዮች ያጌጡ ናቸው። በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል አንዱንም አንመለከትም ምክንያቱም እነዚህ ድንጋዮች የሚናገሩት እየሩሳሌም በሞትና በትንሣኤ ስለምታልፍበት ለውጥ ነውና። ዮሐንስ በራእዩ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ናት ያለው በዚህ ምክንያት ነው። አሮጌዋ እየሩሳሌም ግን ተፈርዶባት ተገድላለች። እርሱ ሲሞት ሰዎች ሁሉ ይሞቱ ዘንድ እስራኤል በጽድቅ ተገድሏል። በክርስቶስ ያመኑት ከክርስቶስ ጋር ሞተዋልና፣ ነገር ግን ደግሞ በክርስቶስ የትንሳኤ ሕይወት ለአዲስ ሕይወት ደግሞ ተነሥተዋል። (2 ቆሮ. 5፡ 14)

ለዚህ ነው የከተማይቱ በሮች በሌሊትና በቀን በየአቅጣጫው ክፍት ሆነው የተተዉት። ለሰዎች ሁሉ ክፍት ሆነው ለዘላለም አይዘጉም፣ የተጠሩና የወደዱ ሁሉ እየመጡ እንዲገቡ፣ አምነውም የዚህች የከበረች ሙሽራ አካል ይሆኑ ዘንድ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅ እና በምዕራብ ተከፍተው ሳይዘጉ ይኖራሉ። በራእዩ ገለጻ እንደተብራራው እያንዳንዱ ደጅ የተሰራው ከዕንቁ ነው። ዕንቁ ደግሞ በባህር ውስጥ ያለ ውድ የከበረ ድንጋይ ነው። በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ልዩ ልዩ አብረቅራቂና አብለጭላጭ ዕንቁዎችን ለመሰብሰብ የዛጎል ትሎችን ይሰበስባሉ። ይህንንም የሚያደርጉት በመጋቢት ወይም በሚያዝያ ወር ማለትም በፋሲካ በዓል ወቅት ነው። እንቁዎች የሚፈጠሩት የዛጎል ትል ሲሰቃይ እና በዚያ ምክንያት ሲሞት ነው፣ ምክንያቱም አንድ ባዕድ ነገር ወደ ዛጎል ትል ውስጥ ገብቶ የዛጎሉ ትል ውስጥ ሰርጾ ሲገባ ትሉ ይሞትና በዚያ ባዕድ ነገር ምክንያት ዕንቁው ይፈጠራል። እንግዲህ ያ የዛጎል ዕንቁ በመከራና በሞት የተፈጠረ አዲስ ንጥረ ነገር ምልክት ነው። እንግዲህ የከተማይቱ ደጆች እያንዳንዳቸው በዕንቁ የታነጹ ነበሩ፣ እርሱ ራሱንና ህይወታችንን ዋጋ ያስከፈለ በመሆኑ ራሳችንን ስለ ክርስቶስ አሳልፈን ስንሰጥ ያኔ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በሙላት እንገባለን። ክርስቶስ አሁን በመንፈስ ይኖር ዘንድ በስጋው መከራን ተቀብሎ ሞተ። እርሱም አሁን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም በከተማይቱ ቤተመቅደስ አሥራ ሁለት ዕንቁዎች (የከበሩ ድንጋዮች) ነበሩ። በእያንዳንዱ ዕንቁ ላይ የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስም ተጽፎአል። ግንቡ እና ደጆቹ በሆነ መንገድ ስለ ክርስቶስ ይነግሩናል። ተመልከቱ በዮሐንስ ራእይ 4፡ 3 ላይ “በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የኢያስጲድ ድንጋይ ነበረ ይለናል”። የከተማይቱም ቅጥር የኢያስጲድ ድንጋይ ሲሆን ከተማይቱም እራሷ እንደ ክሪስታል ጥርት ያለ የኢያስጲድ ድንጋይ ብሩህ ነበረች።

ክርስቶስ ኢያስጲድ ነው፣ ከተማይቱም ኢያስጲድ ነው፣ ቅጥሩም ኢያስጲድ ነው፣ የዚህ ሕንፃ ተፈጥሮም የክርስቶስ ተፈጥሮ ነው። ይህም እርሱን የሚገልጽ እና ባህሪውን የሚያሳይ ነው። በሕዝቅኤል ውስጥ ያለው የመሠዊያው ባሕርይ መሥዋዕቱ ስለሚቀርብበት ስፍራ ነው። በብሉይ ኪዳን መሠዊያው ሲሆን በአዲስ ኪዳን ደግሞ መስቀሉ ነው። ከመስቀሉ በኋላ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው። ይኸውም ለእግዚአብሔር በመንፈስ የመቀደስ ህይወት ነው። ይህም ሕይወታችንን ለመሠዊያው አሳልፈን የምንሰጥበት ነው። 

መሠዊያውን በተመለከተ የአዲስ ኪዳን መግለጫ እነሆ። ራእይ 16: 7 እንዲህ ይላል “ከመሰዊያውም፦ አዎን፥ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”

መሰዊያው ህያው ነው፣ ይናገራል፤ መሠዊያው እየተናገረ ያለውም ህይወታችንን የምንሰጠው እርሱ ስለሆነ ነው። እርሱ ለእርሱ የምንሰጥበት መሠዊያችን ነው። አስቀድመን መስዋዕት ሆኖ ለመሞት በመሠዊያው ላይ ካልተጋደምን በቀር ወደ ቤተመቅደሱ ውስጥ መግባት አንችልም። ከእርሱ ጋር ወደ ቅድስት ስፍራ ከፍ ብለን መውጣት የምንጀምረው እንደ ዕርገት መስዋዕት ስንሆን ነው። በመጀመሪያዎቹ ሰባት ደረጃዎች፣ ከዚያም ስምንት ደረጃዎች ወደ እግዚአብሔር የዙፋን ክፍል ውስጥ ከፍ ብለው ይገባሉ። እነርሱም እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት እንደ ንጉሥና ካህን ሆኖ የእግዚአብሔርን ምሕረት በሚያገለግል በስርየቱ መክደኛ ላይ ካለው ከእርሱ ጋር በሰማያዊ ስፍራ ተቀምጠዋል።

በኤደን ገነት ውስጥ ያሉት ሁሉም ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ የሚውሉበት ይህን መግለጫ በተመለከተ ተጨማሪ ነገር አለ። የዘንባባ ዛፎች፣ ወርቁ እና ሁሉም ተዳሳሽ የሆኑ ቁሳቁሶች አሁን በእግዚአብሔር ስራ ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ። አዳም በገነት ውስጥ ኃጢአት በሠራ ጊዜ ያኔ ከገነት ተባሮ ተጣለ። የተላለፈበት መርገምም አንዱ ክፍል በምድር ላይ ስራው ሁሉ አድካሚና ከንቱ ይሆን ዘንድ ጥረት ብቻ ነበር። እሾህና አሜከላም ያፈራ ነበር። በእሾህና በአሜከላም ምንም ነገር መሥራትና ምርታማ መሆን አይቻለውም። በገነት በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ እያለ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ሁሉ የሚሠራበትና የሚጠቀምበት ማንኛወም አስፈላጊ ነገር ሁሉ ነበረው፣ ወድቀቱና እርግማኑ ያሳጣውም ያንንው ነው። አሁን ቤዛነታችንን አግኝተን ወደ ጌታ ስራ በሙላት ገብተናል። “ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” (1ቆሮንቶስ 15፥ 58)

1ዜና 26፥ 30-31 “ከኬብሮናውያን ሐሸብያና ወንድሞቹ፥ ጽኑዓን የነበሩት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ለእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ ለንጉሡም አገልግሎት በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ባለው በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር።” 

እኔ እንደማስበው ጳውሎስ እየተናገረ ያለው አንዳች ነገር በእኛ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን አላማ እና ስራ በተመለከተ ነበር። የጌታ ስራም ለክብሩ የሚሆን ስፍራን የማነጽ አላማ ነው። ክርስቶስም ሲናገር “ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” ብሏል። ተመልከቱ፣ አሁን ሕዝቅኤል ክብር ከምሥራቅ ሲመጣ ያያል። ምሥራቅ ደግሞ አዲስን ቀን የሚያመለክት የፀሐይ መውጣት ምልክት ነው። የሕዝቅኤል ራእይ ስለ አዲስ ቀን፣ ስለ አዲስ ጊዜ ነው። የጌታም ድምፅ በራእይ 1፡15 እና በራዕይ 14፡2 እና 19፡6 ላይ እንደ ብዙ ውሃ ድምፅ ነው። በኋለኞቹ ሁለት ጥቅሶች ድምጹ የመቶ አርባ አራት ሺህዎቹ እና እጅግ ብዙ ተብለው የተገለጹት ሰዎች ድምጽ ነው። ጌታ እና ህዝቡም አንድ ድምፅ አላቸው። እርሱ የሚናገረውን ያንን ተመሳሳይ ነገር ያዳናቸው ህዝቡም እየተናገሩት ነው። እንግዲህ አዲሱ ቃል ኪዳን ጌታን እና ህዝቡን አንድ ያደርጋቸዋል። ማደሪያውም ለእርሱ የዙፋኑ ከፍታ እና የእግሩ መረገጫ ያለበት ስፍራ ነው። ይህም የክርስቶስ መልክ በሕዝቡ ውስጥ የሚታየው እንደ አካሉ ነው። 

“እነሆም፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር ታበራ ነበር። ያየሁትም ራእይ ከተማይቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮበር ወንዝ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ።” (ሕዝቅኤል 43፥ 2-3)።

“እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘላለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ መረገጫ ይህ ነው። ዳግመኛም የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በግልሙትናቸውና በከፍታዎቻቸው ባለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም፤” (ሕዝቅኤል 43፥ 7)

“ወደ መቅደሱም መዝጊያ መለሰኝ፤ እነሆም፥ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ ከቀኝ ወገን በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር። ደግሞ አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ ….እነሆ፥ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ። በወንዙም አጠገብ በዳሩ ላይ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉም አይረግፍም ፍሬውም አይጐድልም፤ ውኃውም ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኵር ያገኛል፤ ፍሬውም ለመብል ቅጠሉም ለመድኃኒት ይሆናል።” (ሕዝቅኤል 47፥ 1፣5፣7፣12)።

በሕዝቅኤል ውስጥ ያለው ወንዝ እና በራዕይ ውስጥ ያለው ወንዝ

ወንዙ የሚቀጥለው የጥናታችን ማጠቃለያ የሚያጠነጥንበት የውይይታችን ርእሰ ጉዳይ ነው። በተለይም ወንዙ እና በወንዙ ዙሪያ ያሉ ዛፎች ላይ ትኩርት አድርገን እናብቃ። ወንዙ የሕይወት ውሃ ወንዝ ነው። ይህም በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ያለው ያው ራሱ ወንዙ ነው (ራዕይ 22፡1)። በሕዝቅኤል መጽሃፍ ውስጥ ወንዙ በሚሄድበት ስፍራ ሕይወት ደግሞ አብሮ አለ። ይህ የሕይወት ወንዝ ነው፣ የሚፈሰውም በሕዝቅኤል እንደተገለጠው ከመቅደስ-ከተማ ነው። በራዕይ 22፡1 ላይ ሲናገር ወንዙ የሚወጣው ከእግዚአብሔር ዙፋን ነው ይላል። ሕዝቅኤል 43፡7 ደግሞ ሲናገር ይህ ስፍራ ዙፋኔ ነው ይላል። በሕዝቅኤል 47፡12 ላይ በወንዙ በሁለቱም በኩል ዛፎች ይበቅላሉ ይላል። በራዕይ 22፡2 ላይም የሕይወት ዛፍ በወንዙ በሁለቱም በኩል ይበቅላል ይላል። በሕዝቅኤል ውስጥ እንደተገለጠው ዛፎቹ በሁለት ቡድን ተከፍለዋል። በአዲስ ኪዳን አይሁድና አሕዛብ አንድ ሆነው አንድን አዲስን ሰው በራሱ በሠራው በእርሱ በመሆን ሁለቱ አንድ ሆነዋል። በሕዝቅኤል እና በራእይ በሁለቱም መጽሃፍት እንደተገለጠው የዛፎቹ ቅጠሎች ለመፈወስ ናቸው። በራእይ ውስጥ ዮሐንስ ማን እንደሚፈወስ ግልጽ አድርጓል። ቅጠሎቹ ለአህዛብ መፈወሻ ናቸው ይላልና። አህዛብን የፈወሳቸው ደግሞ ወንገል ነው። ያ የህይወት ዛፍ ፍሬን የሚያፈራ ነው። በመጻህፈ ምሳሌ መዕራፍ 11፡ 30 ላይ “የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ነፍሶችንም የሚሰበስብ እርሱ ጠቢብ ነው” ይላል። ይህ በግልጽ የሚያመሳስለው በሕዝቅኤል መጽሃፍ ካለው ቤተ መቅደስ ከከተማይቱ፣ ከማደሪያው ጋር ሲሆን፣ ይህም በራእይ ውስጥ ካለችው ከሙሽራይቱ፣ ከበጉ ሚስት ጋር ያው አንድ ነው። የሕዝቅኤል መጽሐፍ በአሥራ ሁለቱ ነገዶችና በእድል ፈንታቸው አንድነት የሚዘጋ ሲሆን ሕዝቅኤልም ቤተ መቅደሱን እንደ ከተማይቱ አድርጎ ትንቢቱን ሲያጠናቅቅ “እግዚአብሔር በዚያ አለ” በሚለው የታወቀ ንግግሩ ይደመድማል። ዮሐንስም ራእዩን ሲደመድም በከተማይቱ መካከል እግዚአብሔርና በጉ በዚያ መገኘታቸውን ይገልጥና “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” (ራእይ 22፥ 17) በሚለው ቃል ያጠቃልላል።

gkr








 






  







From Blogger iPhone client

No comments:

Post a Comment