ሰባው ሱባዔ
፩. ዝጋው፤ አትዝጋው።
(እንደ መግቢያ)
“እስከ ፍጻሜው ጊዜ ድረስ ቃሉን ዝጋው”፤ ለነብዩ ዳንኤል ትንቢታዊው ቃሉ “እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነው” ተብሎ ተነግሮታል። (ዳንኤል 12፥ 9) ይህም የሆነበት ምክንያት ትንቢቱ ለመፈጸም ብዙ ዘመን ተጠብቆ ስለሚቆይ፣ ፍጻሜውንም በፍጻሜው ጊዜ ስለሚጠብቅ ነው። ይህም የፍጻሜ ጊዜ “የጊዜ መጨረሻ” ወይም “የዓለም ፍጻሜ” ሳይሆን የአሮጌው ኪዳን የአይሁድ ዘመን ፍጻሜ ነው። ጉልህ በሆነ ልዩነት፣ እግዚአብሔር ለሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ባመለከተው በራዕዩ መጽሐፍ፣ የትንቢቱን ቃል በማህተም እንዳይዘጋው ነግሮታል! ምዕራፍ 22፥ 10 "እንዲህም አለኝ፡— ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። "
እዚህ ላይ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ልዩነት አስተውሉ። መጨረሻውና የትንቢቱ ፍጻሜ ለነብዩ ለዳንኤል ዘመኑ ገና ሩቅ ነበር፣ የመጨረሻው ዘመን የመጣው ግን ያኔ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ዮሐንስ የራእዩን መጽሐፍ በተቀበለበትና በሚጽፍበት ጊዜ ነው። ትንቢቱ ያኔ ድሮ በነብዩ ዳንኤል ዘመን ለፍጻሜው ከተያዘለት “የሩቅ ዘመን ቀጠሮ” አንጻር የታተመና የተዘጋ ሲሆን፥ የተፈታውና የተከፈተው ደግሞ ለፍጻሜው ከተያዘለት “የቅርብ ዘመን ቀጠሮ” አንጻር በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ነው። ጉዳዩ ለዳንኤል በብዙ ዘመን የወደፊት ነበር፣ ለዮሐንስ ግን በራሱ ዘመን ወቅታዊ ነበር። ይህም የሚያመለክተው የብሉይ ኪዳን የአይሁድ ዘመን መጨረሻ በመጀመሪያው መቶ ክፍለዘመን ላይ መድረሱን ነው። ዮሐንስ ራእዩን በሚቀበልበት በመጀመሪያው መቶ ክፍለዘመን ላይ ያኔ አሮጌው ኪዳን በአዲሱ ኪዳን የክርስትና ዘመን ሊተካ ዘመኑ ቀርቦ ነበር ማለት ነው።
በ538 ከክልበ አካባቢ፣ ይኸውም ከ2500 ዓመታት በፊት ማለት ነው፣ የእስራኤል ሕዝብ በባቢሎን ግዞት ውስጥ በምርኮ ላይ ነበሩ። ዳንኤልም እግዚአብሔር የ70 ዓመት የምርኮ ጊዜን በህዝቡ ላይ እንደወሰነ አስቀድሞ ያውቅ ነበር (ዳንኤል 9፥ 1-2፤ ኤርምያስ 25፥ 1 1-12፤ 29፥ 10)። ዳንኤልና የመጀመሪያዎቹ ምርኮኞች ወደ ባቢሎን የተወሰዱትም በ605 ከክልበ አካባቢ በመሆኑ፣ ያኔ የነብዩ የኤርምያስ ትንቢት ወደ ፍጻሜው እየቀረበ ወይም የ70ው አመት ግዞት እያበቃ እንደነበረ ያውቅ ነበር (605+-70=535+ ከክልበ.)።
ቂሮስ ባቢሎንን በ539 ከክልበ ተቆጣጠረ። የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው ያኔ ብዙም ሳይቆይ ነው። የንጉሱ የቂሮስ አዋጅም በ538 ከክልበ አይሁዳውያን ግዞተኞች ወደ ይሁዳ ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲገነቡ ፈቃድ ሰጠ። ይህም የተመላሾች ጉዞ በሰሳብሳር የተመራ ሲሆን እርሱም "የመጀመሪያው መመለስ" በመባል ይታወቃል (ዕዝራ 1፥ 8-11)።
ይሁን እንጂ ለዳንኤል ትንቢት (ዳንኤል 9፥ 24-27) የፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ ባዘዘው መሠረት ይህንን በዕዝራ መሪነት በ457 ከክልበ የተካሄደውን የተመላሾች ጉዞ በተለምዶ "ሁለተኛው መመለስ" የተሰኘውን ማመልከቱ የበለጠ ምክንያታዊ ነው።
፪. በቀነ ቀጠሮው
ዳንኤል 9፥ 24 “ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል” ይላል። ይህ የተቀጠረው የእስራኤል ህዝብ መጻኢ ታሪክ ሮድ ማፕ ነው።
ሀ) እግዚአብሔር ለአይሁዶች የወሰነውን ነገር መረዳት እንዲችል መልአኩ ገብርኤል ለዳንኤል ማስተዋልን ሰጠው። ያ ራዕይም በያዘው ቁምነገር ስለወደፊቱ “የሰባ ሱባኤ” የተነገረ ትንቢት ነበር። ይህም እያንዳንዳቸው 70 ሰባቶችን” ወይም የሰባት ዓመታትን ሰባ ሱባኤ (ሳምንታትን) የሚያካትት ነው (ዳንኤል 9፥ 24-27)፤ ይህም የ490 ዓመት የጊዜ ቀጠሮ (70 x 7) ሲሆን፣ የተወሰነው ወይም የተቀጠረው ደግሞ ለአይሁዶችና ለኢየሩሳሌም ከተማ ነው። ሰባ ሱባኤ የአሮጌው ኪዳን እስራኤል ሱባኤ እንጂ የአህዛብ ሱባኤ አይደለም።
ለ) ይህ የተቀጠረ “ጊዜ” ቀዳሚ ዋና ዓላማው መሲሑ ወደ እስራኤል ሲመጣ የሚገለጠውን አዲሱን ሥርዓት ማስታወቅ ነበር! ሌሎቹ ስድስቱ ዓላማዎችም በዚሁ አንድ አላማ ውስጥ ተካተው የቤዛነቱ ስራ አካል ተደርገው የተወሰዱ ናቸው፤ እነርሱም እንደሚከተለው ተወስነዋል ተገልጸዋልም፡-
(1) አመጻን መጨረስ፣
ይህ የመጀመሪያው ነገር ነው፣ መልአኩ እንዳለው እግዚአብሔር በሉአላዊነቱ በቀጠረው በዚህ የ490 ዓመታቱ ጊዜ መተላለፍ ያበቃለታል። የዕብራይስጡ አማራጭ ትርጉም “መገደብ” ይለዋል፤ ይህም “ኃጢአትን መከልከል” እና “ከመስፋፋት ማገድ” ማለት ነው። ይህም ቀጥሎ ካለው የቤዛነቱ ስራ አላማ ጋር ተወራራሽ ይመስላል። “ማሸግ” እንደማለት፣ እሱም ደግሞ ክፋቱ ከእንግዲህ ሊጨምር እንደማይችል የሚያመለክት ነው። እንግዲህ በመለኮት ከተያዘው ቀጠሮ አንጻር “አመጻን ይጨርስ ዘንድ” የሚለው ሃረግ ትርጉሙ በ490ኛው ዓመት መጨረሻ ላይ ወንጌል በእስራኤል ይሰበካል፣ ኃጢአትና በደልም ይዘጋሉ ማለት ነው። ይህም ለሚያምኑ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካኝነት የኃጢአት ይቅርታ መገኘቱን የሚያሳይ ምሳሌያዊ መግለጫ ነው። .
(2) ለኃጢአት ፍጻሜውን መስጠት፣
በ490 ዓመቱ መጨረሻ ላይ ክርስቶስ በመታዘዙ ኃጢአት ሊወገድ የሚችልበትን የደሙን ማስትሰርያ መስዋዕት ያቀርባል ማለት ነው። ይህም ለእስራኤል ቤት የተከፈተ ምንጭ (ዘካ. 13፥ 1)፣ ለአህዛብም የመጠጊያ የመሰብሰቢያ ስፍራ።” (ኢሳ. 2፥ 2-3 ) ይሆናል
(3) በደልን ማስተሰረይ፣
በመለኮት ቀን የተቀጠረላቸው ሁለቱ ቀደምት የቤዛነቱ ስራ አላማዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት በሰባው ሱባኤ ውስጥ ኃጢአት ፈጽሞ እንደሚቀርና እንደሚወገድ ያሳያሉ። ነቢዩ አሁን የጉዳዩን ሌላ ገጽታ ሲያመለክት፣ በቤዛነቱ ስራ አላማዎች ውስጥ የኃጢአት ይቅርታን ለመቀበል ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ የተትረፈረፈ ስርየት ይኖራል ይላል። ይህም ማለት በ490 ዓመታቱ መጨረሻ ላይ የሰው ልጅ በገነት ኃጢአትን ከሠራበት ጊዜ አንስቶ በሰው ልጆች ላይ ለደረሰው የኃጢአትና የበደለኛነት እርግማን ሁሉ ሙሉ መፍትሄ ሆኖ ሰውን ወደ እግዚአብሔር የሚመልሰው ፍጹምና የመጨረሻ የሆነውን የሥርየት መንገድ ያዘጋጃል ማለት ነው። እግዚአብሔር ለአይሁድ የሚሻልን ኪዳን ሊሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበርና (ኤር. 31፥ 31-33)። ይህም አዲሱ ኪዳን እንደ ኢሳያስ፣ ትንቢት ከሆነ በእግዚአብሔር የተዘጋጀላቸው አዲሱ ሰማይና ምድር ነበር (ኢሳ. 65፥ 12-19)። ሁሉም የብሉይ ኪዳን ነቢያት የመሲሑን መምጣት በጉጉት ይጠባበቁ እንደነበር ግልጽ ነው። ዳንኤል 9፥ 24-27 ያለው የንባብ ክፍላችን ሕዝቡን ለመሲሑ መምጣትና እርሱ ሲመጣ ለሚያመጣው የኃጢአት መንጻት ያዘጋጃቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ውሳኔ የ490 ዓመታት ጊዜና ዕድል እንደሚኖራቸው ይናገራቸዋል። ጌታ ኢየሱስም “ያመነ የተጠመቀም ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል” ብሏቸዋል። (ማር. 16፥ 16)
(4) የዘላለምን ጽድቅ ማግባት (ማምጣት)፣
ይህ በሌላ ስፍራ የማይገኝ ሐረግ ነው። ነቢዩ በሌሎች የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባት የመሲሐዊ ትንቢት ባህሪያት በመሆን የሚታወቁትን “ጽድቅ” እና “ዘላለማዊ” የሚሉትን ሃሳቦችም ያጣመራቸው እንደሆነ እናያለን ( ለምሳሌ፦ ኢሳይያስ 46፥ 13፤ 51፥ 5-8፤ መዝሙር 89፥ 36፤ ዳንኤል 2፥ 44፤ 7፥ 18፤ 7፥ 27 ተመልከቱ)። “ማግባት”፣ ወይም ማምጣት፣ ማለትም በመጨረሻ ላይ እውነተኛው ዘላለማዊ ጽድቅ ለዓለም እንዲገለጥ ማድረግ ነው። ይህም በእግዚአብሔር ፊት በእውነት ጻድቅ እንዲሆኑ ነው። የመሲሑን መምጣት ለማሳወቅ፥ ለዓለምም እውነተኛ ጽድቅን ለማስተማር ነው። ስለዚህ፣ “መምጣት የሚያመለክተው ጽድቅ የሚያመጣበትን እና ወደ ዓለም የሚያስገባበትን ቀጥተኛውን ወኪል ነው፣ በእርሱም ላይ የሞራልን ርዕሰ ጉዳይ ሁሉ በተሻለ መሠረት ያቆማል።
“የዘላለም ጽድቅ” ከሚለው ሐረግ ጋር የተያያዙ አንዳንድ በጣም አስፈላጊ ክንውኖች እንዳሉ እስተውሉ። በመጀመሪያ ጥቅሱ በአውደ ምንባቡ ከ“መጨረሻው ቀን” ጋር የተገናኘ መሆኑን ልብ አድርጉ። አይሁድ ዘመናትን “ይህ የሙሴ ዘመን” እና “የሚመጣው የመሲሁ ዘመን” ብለው ለሁለት ከፍለው በሚረዱበት አገባብ የመጨረሻ ቀኖች ማለት መሲሑ የሚመጣበትንና መንግሥቱን የሚመሠርትበት ቀን ማለት ነው። ይህም መንግሥት ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር፣ የማይለወጥና የማይተካ መንግስት ነው። ከእርሱም በቀር ሌላ መንግስት አይኖርም፤ ይህ መንግሥት ክርስቶስ ለዘላለም በጽድቅ የሚነግስበትና የሚገዛበት እርሱም ለዘላለም የሚቀዳጀው አንድ ብቻ የሆነ መንግስት ነው።
አግባብነት ያለው ትርጉሙም፣ አሁን ያለችው የክርስቶስ መንግሥት በ490 ዓመታትቱ ማብቂያ ላይ ወደ እግዚአብሔር የሚቀረብበት ብቸኛዋ መንገድ የመሆንዋ እውነታ ነው። የአይሁድ አምልኮ ብሔራዊ ሃይማኖት ነበረ፣ በኋላም የመሲሁ መንግሥት በሚያቀርበው ሁለንተናዊ የእምነት ሕይወት፣ እርሱም ጽድቅን በማንገስ እስከወዲያኛው የሚሻርና የሚለውጥ ሆኗል። ማለትም ክርስቶስ ምድራዊ መንግሥትን ለመመሥረት ተመልሶ የማይመጣ የመሆኑ እውነታ፣ ይህም ብቻውን በራሱ፣ በአምልኳቸው የሚመኩትን አይሁድንም ሆነ ሌሎችን "ጽዮናውያን ክርስቲያኖችን" ሁሉ ተስፋ ሊያስቆርጥ የሚገባው ነው። ብሔራዊት እስራኤል ብትሆንም መዳን የምትችለው በክርስቶስ መንግሥት ብቻ ነው፣ እንጂ ለመዳን ሌላ ምንም አይነት አማራጭ አይኖራትም፣ (ኢሳ. 51፥ 4፣ 8፤ 45፥ 17)።
(5) ራእዩንና ትንቢቱን ማተም (አትሞ መዝጋት)፣
በማህተም ማተም ማለት "ማሸግ" ማለት ነው፣ መዝጋት፣ ማብቃት ነው። የታሸገ ነገር ሁሉ ሌላ እንዳይጨመርበት ሞልቷል፣ ቆሟል ማለት ነው፥ ወደ ፊትም አይደረግም። የተጻፉ ራእዮች እና ትንቢቶች ሁሉ በሰባው ሱባኤ ወቅት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ በተርጓሚዎች ዘንድ የጋራ ግንዛቤ አለ። አልፍ ሲልም፣ የለም ነቢዩ እየተናገረ ያለው በጠቅላላ ስለ ትንቢቶች ሁሉ ፍፁም መቋረጡ [cessation] ነው ብሎ ለመገመት ያስችላል ሲሉ 1ኛ ቆሮንቶስ 13፥ 8 ላይ ያለውን ቃል እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡም አሉ። ጽድቅን የሚያመጣው የክርስቶስ መንግሥት ነው። እርሱም የእግዚአብሔር የመሆን ስልጣን ነው። በመንግሥቱ ሀልዎት የሚረጋገጠው የራዕይ እና የትንቢት መታተምም በቤተ መቅደሱ መጥፋት ፈጽሞ እስካልተረጋገጠ ድረስ ሊሆን የማይችል እንደሆነ ልንረዳ ይገባናል። በክርስቶስ ሞት ራእይና ትንቢት እንዳላቆሙ እናውቃለን። ስለዚህም ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ ሲፈርሱ ያኔ የብሉይ ኪዳን ትንቢት ሁሉ ፍጻሜውን አግኝቷል። ሉቃስም “የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይህ የበቀል ወራት ነውና” (ሉቃ.21፥ 22) ይላል።
ሐዋርያው ጳውሎስ የአዲስ ኪዳንን ራእዮች እና ትንቢቶችን አስመልክቶ ስለሚታተሙበት ጊዜና ሁኔታ የተናገራቸው ጉዳዮች አሉት። “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል።” (1ቆሮ 13፥ 8-10)። እዚህ ላይ “ፍጹም” የሚለው ቃል ክርስቶስ ማለት አይደለም፣ ቃሉ ወንዴ አጠራር ወይም ሴቴ አጠራር የለውም። ይልቁን ግን ጾታ አልባ ገለልተኛ ቃል ነው፣ ትርጉሙም (የሆነ) “ነገር” ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ሲያበቃ ያኔ የታተሙ ራእዮች ትንቢቶች ሊኖረን ጀምሯል። ሐዋርያት ሁሉም ቃላቸውን ጽፈው ያበቁት በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌም ፈጽማ ከመጥፋቷ በፊት ነው። ምናልባትም ሐዋርያው ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ ራእዩን እንደጻፈ አንዳንድ ሊቃውንት ይበሉ እንጂ፣ (እርግጥ ይህንን የሊቃውንቱን ድምዳሜ የራእዩ መጽሐፍ በያዘው ምስክርነት ውድቅ ያደርገዋል) ጳውሎስ ግን እንደ ተናገረው የራዕይ መጽሐፍ በተጻፈበት ጊዜ ያኔ ራእዮችና ትንቢቶች አቁመዋል።
(6) ቅዱሰ ቅዱሳኑን መቀባት።
የዚህ ዓረፍተ ነገር ትርጉሙ “እጅግ የተቀደሰ” [Most Holy] ወይም “ቅድስተ ቅዱሳን” [Holy of Holies] በሚሉት ቃላት ትርጓሜ ላይ የተመሠረተ ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ይህ መጠሪያ ያላቸው በርካቶች ናቸው፣ የተወሰኑትን ልዘርዝር፦
(1) መሠዊያው (ዘጸአት 29: 37) ጥቅም ላይ ይውላሉ;
(2) ማስተስረያ (ዘጸአት 30:10)፤
(3) የመገናኛው ድንኳንና ንዋየ ቅዱሳቱ (ዘጸአት 30:29)፤
(4) ከንጹህ እጣን የተቀመመው ጣፋጩ ሽቱ (ዘጸአት 30:36)፤
(5) ከእህሉ ቍርባን የተረፈው (ዘሌዋውያን 2:3፤ ዘሌዋውያን 2:10)፤
(6) የአሮን ወንዶች ልጆች የሚበሉት የእሳት ቁርባንና እነርሱን የሚነኩ ሁሉ (ዘሌዋውያን 6:18)፤
(7) በቅዱሱ ስፍራ መበላት ያለበት የኃጢአት መስዋዕት (ዘሌዋውያን 10:17)፤
(8) የበደል መስዋዕት (ዘሌዋውያን 14:13)፤
(9) በእሳት የተደረገው የእግዚአብሔር ቁርባን (ዘሌዋውያን 24:9)፤
(10) ለእግዚአብሔር እርም የሆነ ነገር ሁሉ (ዘሌዋውያን 27:28)፤
(11) ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቁርባን ሁሉ (ዘኍልቍ 18:9)፤
(12) የቤተ መቅደሱ አገልግሎትና የማጠኑና የማገልጉሉ ስራ፣ ወይም አሮን ራሱ (1 ዜና መዋዕል 23:13)፤
(13) የአዲሱ ቤተ መቅደስ ወሰንና ዳርቻው ሁሉ (ሕዝቅኤል 43:12);
(14) የአዲሱ ቤተ መቅደስ መቅደሱ (ሕዝቅኤል 45:3)፤
(15) ላልሳቱት ለሳዶቅ ልጆች የተለየው ክልል (ሕዝ 48፡12)።
እንግዲህ በዚህ መጠሪያ ከተዘረዘሩት ከእነዚህ ምልክቶች መካከል የትኛው በንባብ ክፍላችን ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል የሚለው የሚወሰነው በዐውደ-ምንባቡ ውስጥ ባለው አገባብ ብቻ ነው። “እንግዲህ እወቅ” በሚሉት ቃላት ከተያያዙት ንግግሮች አንጻር ይህ “ቅድስተ ቅዱሳን” የሚለው ቃል “መሲሕ”፣ “ልዑል” (ዳንኤል 9፡25) ከሚለው ጋር ትይዩ ሆኖ የሚታይ ነው። የሚያመለክተውም አንድ የሚቀባ ሰውን ነው፣ (ለምሳሌ፣ ከፍ ሲል በቀረበው ዝርዝር ውስጥ ዘሌዋውያን 6:18፤ 1 ዜና መዋዕል 23:13ን ተመልከቱ)። አውዱ መሲሁን ብቻ እንጂ ሌላ ማንንም ወይም ምንም ነገር የሚቀባ ቅዱሰ ቅዱሳን ብለን እንዳንወስድ ይከለክለናል። ስለዚህ ይህ ሐረግ የሚያመለክተው የማዕዘን ድንጋይ የሆነውን መቀደሱን ክርስቶስን ነው። በአንድ ወቅት እግዚአብሔር በቤተ መቅደሱ ውስጥ አደሮ ነበር፣ ከዚህም የተነሳ ያ ስፍራ ቅዱስ ቤተመቅደስ ነበር። እግዚአብሔር ግን አዲስን ቃል ኪዳን ሊገባ ተስፋ ሰጠ፣ (ኤር. 31፥ 31-33)፣ የዚያ ተስፋ ወራሽም መሲሁ ራሱ ነው፣ (ኢሳ. 7፥ 14)። እርሱም አለቅነትና መንግሥት በጫንቃው ላይ ይሆናል (ኢሳ. 9፥ 6-7)፣ የተባለለት የማዕዘኑ ድንጋይ በሆነ በዚያ አለት ላይ ለመሰረታት ለቤተክርስቲያኑ (ማቴ 16፥ 18) ራስ የሚሆነውም እርሱ ነው፥ (ቆላ. 1፥ 18)። ስለዚህም አንድ ሰው አዲስ ኪዳንን ተቀብሎ ወደዚያ ለአምልኮ ሲመጣ ክርስቶስ በዚያ በማደሩ ስፍራው ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል፣ (ማቴ 18፥ 20)። ስለዚህም ክርስቶስ የመንግስቱ ንጉስ ሆኖ መቀባቱ እና በአማኞች መንግስት ላይ ገዥ ንጉስ እንደሆነ ይታወቃል።
እርግጥ ነው ይህ እንዴት እንደሚደረግ ዳንኤል በግልጽ ማየት አልተቻለውም (ኤፌ 3፥ 5-6)። ዳሩ ግን በወንጌሉ የበራልን እኛ፣ እግዚአብሔር ኃጢአትን ፈጽሞ ያስወገደበትን መንገድ አሁን ሙሉ በሙሉ ስለተገለጠልን ይህ በክርስቶስ መስዋዕታዊ ደም እንዴት እንደተፈጸመ በግልጽ መረዳት ተችሎናል። በክርስቶስ ባገኘነው የአዲሱ ልደት ጥምቀታችን በክርስቶስ መስዋዕታዊ ደም እያጠበን ኃጢአታችንን ከድኖታል፥ ስርየትንም ተቀብለናል። "ያመነ የተጠመቀም ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል" (ማር 16፥ 16)
“ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።” (ዕብራውያን 12፥ 22-24)
“አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤” (ራእይ 21፥ 1-3)
፫. ኢየሩሳሌምን መጠገንና መስራት፦
ዳንኤል 9፥ 25 “ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።”
እዚህ ላይ አሁን አንድ የኢየሩሳሌምን ከተማ መልሶ ስለመገንባት የሚያወሳ የተለየ አዋጅ የተወሰነበትን ጊዜ በተመለከተ ምልክት ይሰጠዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ገብርኤል የዳንኤልን የማወቅ ፍላጎት ለመቀስቀስ ፈልጎ ነበር፣ በትኩረት የሚከታተልም ከሆነ ስለዚህ ጉዳይ ገብርኤል ሊሰጠው የነበረውን ሚስጥር ይገነዘባል። የሰባቱ ሱባኤ የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ እርሱን ተከትሎ ከሚመጣው በተለየ ነገር ተለይቶ የሚታወቅ ነው ወይም ያ የሱባኤው ክፍል አንድ ዋና አስፈላጊ ነጥብ ላይ ያደርሳል። ከዚያም ተከታታዮቹ ስድሳ ሁለት ሱባኤዎች ይከተላሉ፣ ከዚያም በኋላ የእስራኤልን ህዝብ ወደ ፍጻሜው ጊዜ የሚያመጣበት የቀረው ሱባኤ ይሆናል። ይህ እንግዲህ አጠቃላይ ሰባ ሱባኤያትን ያጠናቅቃል።
ሀ) ስለዚህ ከፍ ሲል ባየነው መሰረት መልአኩ ገብርኤል ሰባው ሱባዔ ወይም 490 ዓመታቱ በሦስት ክፍለ ጊዜ የተከፋፈለ እንደሚሆን ለዳንኤል ይነግረዋል፣ ይኸውም፡-
(1ኛ) ቀዳሚው የ"ሰባት ሱባዔ" ክፍለ ጊዜ (7x7=49 ዓመታት)፣
(2ኛ) የ"ስልሳ ሁለት ሱባኤ” ዘመን። (62x7=434 ዓመታት)፣ እንዲሁም
(3ኛ) የመጨረሻው የአንድ ሱባኤ ጊዜ" (7 ዓመታት) ናቸው።
እነዚህን ሦስቱን የሰባውን ሱባኤ ክፍሎች የዘመን አቆጣጠር ልብ አድርጉ። እዚህ ላይ የሰባ ሱባዔውን ቅደም ተከተል አንድ ብሎ መቁጠር የጀመረው ንጉሥ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ትእዛዝ ካወጣበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል። የፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ በ457 ከክልበ አዋጅ አውጥቶ የአዋጁን ግልባጭ ለዕዝራ ሰጠው (ዕዝራ 7፥ 11-26)። በዳንኤል መጽሐፍም “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ... " (ዳንኤል 9፥ 25) በሚል የተጠቀሰው የመጀመሪያ ቀንም ይኸው ነው።
ለ) የመጀመሪያዎቹ አርባ ዘጠኝ ዓመታት (ይኸውም አዋጁ ከወጣበት ከ 457 እስከ 408 ከክልበ) ያለው ጊዜ የኢየሩሳሌምን ቅጥር መልሶ ለማቋቋም እና ከተማይቱን እንደገና ለመገንባት የሰሩበትን ጊዜ ይሸፍናል። ይህም በዕዝራ እና በነህምያ ጊዜ የተከናወነ ነበር (ነህምያ ምዕራፍ 2-6)። አይሁድ ከምርኮ ተመልሰው በብዙ ችግር የቅጥሩን ሥራ ሠርተዋል፣ ሲሠሩም ከተቃዋሚዎቻቸውና ከጠላቶቻቸው የተነሳ የጦር መሣሪያን ከግንባታ ዕቃዎች ጋር አንግበው ይሰሩ እንደነበር፣ በዚያም የጭንቅ ሁኔታ ውስጥ የከተማይቱን ግንቦች መልሰው እንዳደሱ፣ መንገዶቿንም አሻሽለው፣ ቤቶችንም አስተካክለው፣ የሚተዳደሩበትንም የፍትሐ ብሔር ሕግ አውጥተው እንደገና ከግዞት መልስ በኢየሩሳሌም መኖር የጀመሩበት ጊዜ ነው። (ነህምያ 11፥ 1)
ሐ) ሁለተኛው የስድሳ ሁለት ሱባኤ ወይም የ434 ዓመታት ጊዜ ይኸውም ከክልበ ከ408 ዓ.ዓ. እስከ 26-27 ዓ.ም ድረስ ያለው ነው። በቀዳሚው 7ቱ ሱባኤ እና በተከታዩ 62ቱ ሱባኤ መካከል ምንም አይነት የጊዜ ክፍተት አልነበረም። ኢየሱስ ከድንግል ማርያም ሥጋን ነስቶ የተወለደው ከክልበ በ4 ዓ.ዓ ነበር እንጂ በ0 ዓ.ም ላይ አልነበረም፣ ይህም የጊዜ ልዩነት በዋነኛነት በክርስቲያን የቀን አቆጣጠር እና በአይሁድ የቀን አቆጣጠር መካከል ባለው ልዩነት ላይ የተመሰረተ ነው። የዳንኤል ሰባ ሱባኤ ማጠቃለያ የሆነው 70ኛው ሱባኤም የጀመረው በ26-27 ዓ.ም ላይ ነው። የ69ኛው ሱባኤ መጨረሻ (7+62=69) እና 70ኛውና የመጨረሻው ሱባኤ የጀመረበትን ልዩ ክስተትም ቀጥሎ እንመለከታለን።
፬. ከስልሳ ዘጠነኛው ሱባኤ በኋላ፡-
ዳንኤል 9፥ 26-27 “ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል። እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፤ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቈረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።”
ሀ) በ26-27 ዓ.ም፣ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ተስፋ የተደረገው መሲህ ሆኖ አገልግሎቱን በይፋ ጀመረ። ከክብሩ ራሱን ባዶ አድርጎ የባርያን መልክ በመውሰድ እንደሌሎች ሰዎች ሁሉ ፍጹም ሰው ሆነ (ፊልጵስዩስ 2፥ 7-8፤ ዕብራውያን 2፥ 17)። በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅም እርሱ እውነተኛው መሲሁ መሆኑ በይፋ ታወቀ። ያኔም በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ ነበር። በዚያን ጊዜም ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር (ሉቃስ 3፥ 22-23)።
ለ) ኢየሱስም ወደ ምኩራብ ገብቶ በኢሳይያስ 61:፥ 1 ላይ የሚገኘውን መሲሐዊ ትንቢት በሁሉ ፊት አነበበ፤ እንዲህ ሲል፦
"የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምስራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛልና"።
ይህም ገለጻ “የተቀባውን” መሲሕ መምጣት ያረጋግጣል። ቀጥሎም ኢየሱስ በሁሉ ፊት በግልጽ እንዲህ አለ፡- “ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ዛሬ ተፈጸመ።” ( ሉቃስ 4፥ 21 ) ኢየሱስ በንግግሩ በኢሳይያስ 61፥ 2 ላይ ያለውን የቀረውን የትንቢቱን ክፍል ይኸውም፦
“የተወደደችውን የጌታን ዓመት የአምላካችንንም የበቀል ቀን እናገር ዘንድ፣ የሚያዝኑትንም ለማጽናናት፣” የሚለውን አልጠቀሰም። ምክንያቱም በእስራኤል ላይ የሚፈፀመው ሙሉ ቅጣት ተፈጻሚ የሚሆንበት ጊዜ ያኔ በመጀመሪያው መምጣቱ ወቅት ገና አልደረሰም ነበና። በቀጣዮቹ 3 ዓመታት ከመንፈቅ ባሉት ጊዜያት ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ፣ እያስተማረና እየሰበከ የአዲሱን ኪዳን የእግዚአብሔርን መንፈሳዊ መንግስት ማስተዋወቅ ጀመረ።
ሐ) ትንቢቱ ከ69ኛው ሳምንት በኋላ (62 +7=69) ጥቂት ነገሮች ይከሰታሉ ይላል። በትክክል መቼ እንደሆነ ባይገለጽም "በኋላ" ብሏል። ምንም እንኳን አንዳንዶች በ 70ኛው ሱባኤ ውስጥ እነዚህ ክስተቶች የግድ ይከሰታሉ አይልም ቢሉም ቃሉ ግን “በኋላ” ብሏል። እንግዲህ "ከ62ቱ ሱባኤ በኋላ" የሚለው ሐረግ የመጀመሪያዎቹ ሰባት ሱባኤዎች ካለፉ በኋላ 62ቱ ሱባኤዎች ይጀምራሉ፤ 62ቱ ሱባኤዎች ካለፉ በኋላ ደግሞ መሲሑ ይገደላል ማለት ነው። ቀደም ሲል እንደተገለፀው የዚህ የስድሳ ሁለቱ ሱባኤ ክፍለ ጊዜ ማብቂያ በ 26-27 ዓ.ም ነው። አሁን ትኩረት የሚያሻው በ 69 ኛው ሱባኤ የኋለኛ ክፍል እና በመጨረሻው እና በማጠቃለያው ሱባኤ መጀመሪያ ላይ ሊከሰቱ ስለሚገባቸው ክስተቶች ነው።
በምዕራፍ 9፥ 26 ላይ ያሉት እነዚህ የተተነበዩ ነገሮች፦
(1) መሲሑ ይገደላል፣ የሚገደለውም ስለሌሎች ነው እንጂ በራሱ ጥፋት አይደለም፤
(2) የሚመጣ አለቃ አለ፣ የአለቃው ሰዎችም ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፣
(3) ፍጻሜው እንደ ጎርፍ ጥፋት ሆኖ ያበቃል፣ እንዲሁም
(4) ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስ ጥፋት ተወስኗል ወይም አስቀድሞ ተወስኗል፤
በምዕራፍ 9፡27 ላይ ያሉት ሌሎች የተተነበዩት ነገሮችም አሉ፦
(5) ከብዙዎች ጋር ለአንድ ሱባኤ ቃል ኪዳንን ያደርጋል
(6) መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል
(7) አስቀድሞ የተወሰነው ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስም የጥፋት ርኩሰት ይሆናል።
በመጨረሻው ሱባዔ ይከሰታሉ በሚል የተተነበዩ እነዚህ ሰባት ክስተቶችን ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ቀሪ ነጥቦቼ ላይ መጠነኛ ማብራርያ አቀርባለሁ።
፭. የ70ኛው ሱባኤ እኩሌታ፦
ሀ) የሰባት ዓመታት የመጨረሻው (70ኛው) ሱባኤ ከ26-27 ዓ.ም. እስከ 33-34 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው። በመጨረሻው ሱባኤ አጋማሽ ላይ ያለው ዋነኛ ክስተት የመሲሑ ስቅለት ነው። ይህም የሆነው በ30 ዓ.ም ነው። እርሱም በተጻፈው መሰረት “ተገድሏል፣ በመስዋዕታዊ ሞቱም መስዋዕትንና መባን አስቀርቷል። በዚህ ሱባኤ አጋማሽ ላይ ክርስቶስ ከአይሁድ መከራን ይቀበላል፣ ይጣላል፣ በመስቀል ላይ እንዲሞትም ይፈረድበታል። መስዋዕታዊ ሞቱ ብቻ መስዋዕትን ያስቆማል። መሲሑ ኢየሱስ ለኃጢአታችን የቀረበ የመጨረሻው መሥዋዕትና መባ ነው። ምንም እንኳን የእንስሳት መሥዋዕቶችና መባዎች ለሌላ ተጨማሪ አርባ ዓመታት የቀጠለ ስርአት ቢሆንም፣ ያ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ግን ያንን አሮጌ የመስዋእት ስርአት ጊዜው ያለፈበትና ለኃጢአት ይቅርታ ምንም የማይጠቅም አድርጎታል (ዕብራውያን 9፥ 26፤ 10፥ 10፤ 1 ጴጥሮስ 3፥ 18)።
ይህ ማለት ግን በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ መስዋዕት አይቀርብም ነበር ማለት አይደለም፣ ምክንያቱም በ70 ዓ.ም በእግዚአብሔር ቁጣ ቤተ መቅደሱ እስኪፈርስ ድረስ የመስዋዕቱ ስራ በዚያ ቀጥሎ ነበር፤ ጳውሎስም እንኳ በዚያ መስዋዕትን አቅርቦ እንደነበር፥ በሐዋርያት ሥራ ምዕ. 21ላይ እናነባለን። በእውነቱ በወገኖቹ መካከል ለወንጌል እንቅፋትን እንዳያኖር ተጠንቅቆ ነው እንጂ መስዋዕትን ማቅረብ አስፈላጊው ሆኖ አልነበረም። ምክንያቱም እግዚአብሔር የተቀበለው እውነተኛውና የመጨረሻው መስዋዕት አስቀድሞ ስለተከፈለ ነው። አዲስ ኪዳንም በመስዋእቱ ደም ተመርቆ ተሰጥቶ ነበር።
የመስዋእት ስርአት ለቀጣዮቹ አርባ አመታት መቀጠሉ የእግዚአብሔርን ትዕግስት ያሳያል፣ ወልድ ከሞተ ከአርባ ዓመታት በኋላ ቤተመቅደሱን ከማጥፋቱ በፊት እስራኤልን ወደ ወደ ክርስትና ለመመለስ የሰጣቸው የጸጋ እድል ነበር። ትክክለኛው ትርጉሙም ይኸው ነው፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መስዋዕት መሆን በሚያስፈልግበት ቦታ አሮጌውን የሙሴን ሥርዓት በህጋዊ መንገድ ማብቂያና ፍጻሜ ሰጥቶታል። ስለዚህ ኢየሱስ በምዕራፍ 9፥ 24 ላይ የተዘረዘሩትን የዳንኤልን 70 ሱባኤ የቤዛነት ዓላማዎች በሙሉ በመስዋዕታዊ ሞቱ ፍጻሜ ሰጥቷቸዋል።
ለ) አሮጌው ሥርዓት በ"ፍጻሜው ዘመን" ፈጽሞ እስኪወገድ ድረስ አዲሱ የቃል ኪዳን ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሊመጣ አልተቻለውም፣ ወይም እነዚያ በዳንኤል 9፥ 24 ላይ የተዘረዘሩት ስድስቱም መሲሐዊ ተስፋዎች እና የቤዛነት ዓላማዎች ሙሉ በሙሉ ሊመጡ እና ሙሉ በሙሉ እውን ሊሆኑ አልቻሉም። ያ ገና የዘመኑ ፍጻሜ አልነበረምና፣ ነገር ግን ያ የአይሁድ የብሉይ ኪዳን ዘመን የሚያበቃበት ጊዜ ነበር
ሐ) ከስቅለቱ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ (ሉቃስ 24፥ 49)። ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ከኢየሩሳሌም ወጥተው በመሄድ ኢየሱስ “አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ሲል እንዳዘዘው አሕዛብን ሁሉ አስተማሩ (ማቴዎስ 28፥ 19) ይህም የሆነበት ምክንያት በመጀመሪያ አዲስ ኪዳን የሚጸናው ለአንድ ሱባኤ ወይም ለ7 ዓመታት ስለሆነ ነው። ይህም የተቀጠረው ሙሉ በሙሉ ለአይሁዶች ነበር (ዳንኤል 9፥ 24፤ ሮሜ 1፥ 16፤ ዮሐንስ 4፥ 22)።
፮. ጽኑ ቃል ኪዳን ለአይሁድ
ሀ) የመጨረሻው ሱባኤ ለአይሁድ አዲሱን ቃል ኪዳን የሚያጸናበት ነበር። ተስፋ የተደረገው መሲሕ ኢየሱስ መሆኑን፣ መዳንም በእርሱ በኩል ብቻ እንደሆነ የሚገልጽ የቃል ኪዳን መልእክትን ለዚያ የአይሁድ ትውልድ ለመስጠት ነበር። ይህም በነቢዩ በኤርምያስ በኩል ተስፋ የተሰጠም ነበር (ኤርምያስ 31፥ 31-33)። በሱባኤው የመጀመሪያ አጋማሽ ወይም በ3 ዓመታት ተኩል ውስጥ፣ ጌታ ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ በነብዩ ዳንኤል በኩል ለአይሁድ የተናገረውን ትንቢት በከፊል ፍጻሜን ሰጥቶታል። ይህም በ26-30 ዓ.ም መካከል ነበር። በዳንኤል ትንቢት መሰረት ለአይሁዶች ብቻ የሚያገለግል ሌላ 3 አመት ተኩል ጊዜ ነበር። ዳንኤል 9፥ 27 "ከዚያም ከብዙ ሰዎች ጋር ለአንድ ሱባኤ (7 አመት) ቃል ኪዳን ያደርጋል"።
ከፍ ሲል በቁጥር 26 ላይ እንደተገለጸው፣ ይህ የመጨረሻው ሱባኤ የጀመረው ክርስቶስን በዮሐንስ ጥምቀት በመግለጥ፣ መንፈስ ቅዱስንም በእርግብ አምሳል በእርሱ ላይ በማውረድ፣ ከሰማይም በተሰማ የአብ ድምጽ ማረጋገጫን በመስጠት ሲሆን፤ ይኸውም የመገለጡ ጊዜ ለሦስት ዓመታት ተኩል የቀጠለ ነበር። በዚህም ጊዜ ውስጥ አዲስ ኪዳንን እርሱም የመንግሥቱን ወንጌል አስተማረ። ሦስት ዓመት ተኩሉ ሲያልቅ፣ ራሱን ለሰው ኃጢአትና በደለኛነት ቤዛ ሰጥቶ ሙሉ ክፍያን በማቅረብ አሮጌውን የመስዋዕት ሥርአት አቆመው። ራሱን ለቤዛነት ሊያቀርብ የሚችለው ኃጢአት የሌለበት የሆነ አንድ ብቻ ነው። ማንም ተራ ሰው ያንን አይነት የቤዛነት መስዋዕት ሊያቀርብ አይቻለውም። ይህም የቤዛነት ሥራ የክርስቶስን አምላክነት፣ ብሎም የክርስትና እምነትን ብቸኛና እውነተኛ የመዳን ምንጭ የመሆኑን ሚስጥር ይመሰክራል። ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ (ለምሳሌ ራቁትነትን የሚሸፍኑበት የቅጠል ግልድም ይሁን የእንስሳ ቆዳ)፣ ወይም በብሉይ ኪዳን የቀረቡ መስዋዕቶች ሁሉ ቢሆኑ፣ ማስተሰረያ ሊያቀርብ የሚችል ሌላ እውነተኛ ስም የለም። እነዚያ ሁሉ የመስዋዕት አይነቶች በክርስቶስ ቤዛነት፣ በመስዋዕታዊ ሞቱ ሊሻሩ የተመደቡ ነበሩ፤ ሰውንም ከኩነኔ የሚቤዠውና፥ ከእግዚአብሔር ጋር ውዳለ ኅብረት የሚመልሰው፣ ኃጢአቱን የሚከድንለት የእውነተኛው መስዋዕት የመምጣቱ ምሳሌ ብቻ ነበሩ።
ለ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የወንጌልን መልእክት ይዘው ወደ አሕዛብ እንዳይሄዱ አዘዟቸው እንደነበር አስታውሱ፡-
ማቴዎስ 10፥ 5-6 “እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ፦ በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ”
ማቴዎስ 15፥ 24 “እርሱም መልሶ፦ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ።”
ይህ ማለት እርሱ ያቀረበው የኃጢያት ዕዳ ክፍያ የትኛውንም የአህዛብ ክፍል አይመለከትም ነበር ማለት አይደለም፣ ነገር ግን የአዲስ ኪዳን መልእክቱ “አስቀድሞ ለአይሁዳዊ” (ሮሜ 1፥ 16፤ 2፥ 10) የተሰኘውን መጽሓፍ ቅዱሳዊ መርህ መጠበቅ የነበረበት በመሆኑ ነው። ልብ አድርጉ፣ “አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው” ይላል እንጂ “ኋላም ለግሪክ ሰው” አይልም። ይህ ወንጌል “አስቀድሞ ለአይሁዳዊ” የተሰበከው ነብዩ ዳንኤል ለህዝብ ተቀጥሯል ባለው በሰባው ሱባኤ መዝጊያ በሰባት አመታት ውስጥ ነው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ወንጌሉንም ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ጀምረው እስከሰማርያና እስከምደር ዳርቻ ድረስ መሰከሩ። ስለዚህ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እና ተከታዮቹ “አስቀድሞ ለአይሁዳዊ” ከሚለው የመለኮት ድንጋጌ በቀር፥ ወንጌሉን ከኢየሩሳሌም እና ከአይሁድ ክልል አውጥተው ለመውሰድ አይከለከሉም ነበር። የተወሰነውና የተቀጠረው ጊዜ እስኪጠናቀቅም ድረስ ቅድሚያ ሰጥተው ለአይሁድ ሰበኩ። በእስጢፋኖስ ላይ ከደረሰው መከራ የተነሳ “የተበተኑት … ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድ ስንኳ አይናገሩም ነበር” (ሐዋርያት 11፥ 19)።
ሐ) የዳንኤል ሰባኛው ሱባኤ መደምደሚያ አካባቢ ወንጌላዊው ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ሄዶ የክርስቶስን ወንጌል በሰበከበት ወቅት ነበር (የሐዋርያት ሥራ 8፥ 5)። ከአይሁድ ውጭ ላሉ ህዝቦች ወንጌልን በይፋ የመስበክ ስራ የተጀመረውም ያኔ ነው። በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትም ፊልጶስ በጀመረው ነገር ላይ ቀጥለው እንዲገነቡ ተከታይ ቡድን ሆነው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ሰማርያ ላኳቸው። (የሐዋርያት ሥራ 8፥ 14) ይህም በ33-34 ዓ.ም አካባቢ ነበር፤ ያኔም አዲሱ ቃል ኪዳን ለአይሁድ ብቻ የሚሰበክበት የጊዜ ገደብ እያበቃ ነበር። ወንጌሉ በመጀመሪያ ለአይሁዶች፣ ከዚያም ለሳምራውያን (ግማሽ ዝርያዎች) እና በመጨረሻም ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ጨምሮ በመላው ዓለም ላሉ አሕዛብ ተዳረሰ። (የሐዋርያት ሥራ 10፤ 11፥ 18-20) ያኔ የእስራኤል ጊዜ እያበቃ ስለነበር ጳውሎስና በርናባስ እንኳ ”ገልጠው፦ የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን” (ሓዋርያት ሥራ 13፥ 46) ይሏቸው ነበር።
መ) አይሁድን እና አህዛብን በአንድ መንፈሳዊ አካል በክርስቶስ አካል የሚያስተሳሰር የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክት ተዘጋጅቶም ወደ ዓለም ታሪክ ተዳረሰ። (ዮሃንስ 4፥ 22፤ ኤፌ. 3፥ 3-6፣ 9፤ ቈላስይስ 1፥ 26-27፤ 2፥ 2፤ 4፥ 3፤ ሮሜ 3:፥ 19-23፤ 15፥ 26-27 ) ትንቢቱ በሙሉ የጊዜ ክፍተት የሌለበት ሆኖ ለፍጻሜው በጠቅላላ የ490 ዓመታትን ጊዜ ያካትታል። በዚህም ወቅት ሁሉም ትንቢታዊ ክንውኖች በሉዓላዊነት ተወስነው አንድም ሳይቀር ሁሉም በትክክል ተፈጽሟል። ተወስኗል ማለትም ክስተቶቹ በእግዚአብሔር የተደራጁ፣ የተሰየሙ እና በትክክል የተቀመጡ ናቸው ማለት ነው። እነርሱም በመለኮት በተቀጠረውና በቅዱሳት ነብያት በተነገረው መሰረት በዚያ ትውልድ ውስጥ መከናወን የነበረባቸው ነበሩ። ይህ የትንቢት ቀጠሮ በመለኮት የተቀጠረ ነበር፣ እግዚአብሔር ደግሞ ቀጠሮ አክባሪ ነው። በነብያት አፍ ይፈጸማል ሲል የሰጠውን ተስፋ እርሱ በቀጠረው ዘመን ፈጽሞታል።
አሁን እንግዲህ የተቀጠረውን ጥፋት ራሱን ጥቂት ተመልክተን እናብቃ።
የዚህም ትንቢት ፍጹም ፍጻሜ የሆነውም ነብዩ ዳንኤል “መቅደሱ ይጠፋል”፤ “ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል”፣ “እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል”፣ ሲል እንደተነበየው፤ ጌታ ኢየሱስም “በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ…ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል”፤ “እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል”፣ “ይህ ሁሉ ይፈርሳል፣ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ይወድቃል” ሲል እንደተናገረው፤ ይህንን ሊያከናውን በአሮጌው ኪዳን ሥርዓት፣ በኢየሩሳሌም ከተማ እና በቤተ መቅደሱ ላይ መዓትን ሊያደርግ፣ ባላመኑት አመጸኛ የእስራኤል ህዝብ ላይም ቁጣውን ሊያፈስስ በ70 ዓ.ም ሮማውያንን ባመጣበት ፍርድ ዳግመኛ በመጣ ጊዜ ነው።
ሮማውያንን የጥፋት ኃይል አድርጎ በእስራኤል ላይ ያመጣቸው አህዛብን ሁሉ በሉአላዊነቱ የሚገዛው የሰማይ አምላክ፣ የምድር ሁሉ ንጉስ የሆነው እግዚአብሔር ነው። “በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል” እንደተባለ የተጻፈው እንዲፈጸም የጥፋት ርኩሰትንም እንኳ ያመጣው የሚመጣው ጌታ ነው እንጂ ያለእርሱ ፈቃድና ውሳኔ አልመጣም። በማቴዎስ 24 15 ላይ ገታ ኢየሱስ ይህንን የዳንኤልን ትንቢት ጠቅሶ የህ “የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ” ሲያዩ ምን ማስተዋል እንዳለባቸው ምልክት ሰጥቷቸዋል። ቅዱሱ እግዚአብሔር በማይመረመር ሉአላዊ አሰራሩ ጥፋትንም፣ ክፋትንም፣ የጥፋትን ርኩሰትንም እንኳ ለገዛ ራሱ ሉአላዊ ፈቃድ እየጠመዘዘ በወደደው መንገድ እንዲያገለግለው ማድረግ የሚችል ነው፤ ለምን ይህንን በዚህ መንገድ አደረግህ ተብሎ በማንም የማይጠየቅ፣ ክፋትንም ርኩሰትንም በፈቃዱ ስር አስገዝቶ የአላማው መፈጸሚያ ሲያደርጋቸው ቅድስናው የማይረክስበት የማይመረመር ምጡቅ አምላክ ነው። ስለዚህ እስራኤልን ያጠፋት አጥፊው ሌላ ግዑዝ፣ ሥጋዊና ምድራዊ ኃይል እንዳይመስላችሁ፤ ያጠፋት የፈጠራት ያህዌ ራሱ ነው። እርሱ የሚያስፈራ የፍርድ አምላክም ነውና።
ያ ቤተ መቅደስ እንዴት እንደ ጠፋ በታሪክ የተዘገበውን ልብ አድርጉ። ጆርጅ ፒተር ሃልፎርድ “የቲቶ ሰራዊት ሺ አለቃ የነበረው ቴሬንቲሩስ ሩፉስ፣ የቤተ መቅደሱን ውስጠኛ መሰረት ከቆፋሪዎች ጋር በመረዳዳትና ፈጽሞ በመቆፋፈር የድንጋይ ቁልል አደረገው ተብሎ በታልሙድ እና በማይሞኒዴስ ተዘግቦልናል” ሲሉ ይጽፋሉ፤ [George Peter Holford, The Destruction of Jerusalem (1805) ገጽ 43] ይህ አያስደንቅምን?
ይህ ብቻ ደግሞ አይደለም፤ ፍላቪዬስ ጆሳቨስ ስለ አይሁድ ጦርነቶች በሚተርከው መጽሐፉ "ሮማዊው ጀነራል ቲቶ ቤተ መቅደሱ ከጥፋት እንዲተርፍ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር" ይለናል፡፡ ቲቶ ቤተ መቅደሱ እጅግ የሚያምር ሕንጻ ከመሆኑ የተነሳ እንዳይፈርስ ፍላጎት ነበረው፡፡ ለሮም መንግስት ክብር እንደ ሮማውያን የስኬት መገለጫ አድርጎ በታሪካዊ ቅርስነት ሊጠብቀውም ተመኝቶ ነበር፡፡ ቤተ መቅደሱን በተመለከተ የቲቶ ቀጭን ትዕዛዝ ማንኛውም ጉዳት እንዳይደርስበት የተላለፈ የቄሳር ትዕዛዝ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ከቲቶ ወታደሮች አንዱ ከቤተ መቅደሱ መስኮቶች በአንዱ ወርውሮ ያስገባው የእሳት ድንጋይ የዚያን ቅዱስ ሥፍራ መሠረት በእሳት አያያዘው፡፡ ቲቶም ነገሩን በሰማ ጊዜ በታላቅ ድንጋጤ ከነበረበት ስፍራ ተነስቶ … ወደ ቅዱሱ ቤት ሮጦ በመሄድ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም ብዙ ሞክሮ ነበር፡፡ በከፍተኛ ድምጽ፣ እየጮኸ፣ ለወታደሮቹም በቀኝ እጁ ምልክት እየሰጠ እሳቱን እንዲያጠፉ ወታደራዊ የኢታማጆር ሹም ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ነበር፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ እነዚያ የአለቃቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም በአግባቡ የሰለጠኑና ሥነ- ስርዓት የተማሩ ቆፍጣና የሮማውያን ወታደሮች ልክ አውሬ የሆኑ ያህል እንደ እብድ ሰው ተለውጠው የቄሳርን ትዕዛዝ እንዳልሰሙ ያህል በመሆን፣ ቲቶም ምንም ማድረግ እስከማይችል ድረስ፥ አሁንም አሁንም እየጨመረ ከሚሄድ ታላቅ የበቀል መነሳሳት ጋር እሳቱን እየጨመሩ ያበዙት ቀጠሉ [Josephus, Complete Work, Kregel Publication, ገጽ 581]፡፡
ይህ እንዴት ያለ አስገራሚ ታሪክ ነው! ታላቁ ሮማዊ የጦር ጀነራል እና በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራዊቱ ቤተ መቅደሱን ሊያድኑት ከቶ አልቻሉም፡፡ ለምን ይህ ሆነ ቢባል ምክንያቱም ከቲቶ የሚበልጠው፣ ከቄሳርም የሚበልጠው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ቃጠሎ ከመሆኑ ከዓርባ ዓመታት በፊት ቀደም ብሎ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” (ማቴ 24÷ 3) ሲል ተናግሮ ነበርና ነው፡፡ ቤተ መቅደሱ እንዳይፈርስና ቅርስ ሆኖ እንዲቀመጥ ታላቅ ፍላጎት ከነበረው፣ የገዛ ወታደሮቹንም ማፍረስና ማቃጠል እንዲያቆሙ በከፍተኛ የአዛዥ ድምጽ ይናገር ከነበረው የጀነራል ቲቶ ቃል ይልቅ “ይህ ቤተ መቅደስ ይፈርሳል” ሲል የተናገረው የጌታችን ቃል ይበልጣል። እግዚአብሔር ተናግሮአል፣ ጀነራል ቲቶም ትዕዛዙን ይከተላል እንጂ ምንም ሊያደርግ ስለማይችል ያ ቤተ መቅደስ ተቃጥሏል፡፡
ይህ እንግዲህ ድል ለመንሳት የፈለገው የሮም ሠራዊት ኃይል ሳይሆን፣ በሕዝቡ ላይ የሚፈርደው የእግዚአብሔር ኃይል ነበር፡፡ በጆሳቨስ የታሪክ ዘገባ የሚከተለውን እናነባለን፡- “ቲቶ ወደ ከተማይቱ በገባ ጊዜ (መስከረም 26 ቀን 70 ዓ.ም ማለት ነው) የከተማይቱን ጥንካሬ በተለይም ከፍ ብለው የተሰሩትን ቅጠሮቿንና የታነጹበትን ድንጋይ እየተመለከተ በእጅጉ ይገረም ነበር፡፡ እነዚያ ግንቦች ምን ያህል ረጃጅሞችና ጠንካሮች መሆናቸውንም በተመለከተ ጊዜ፣ የእያንዳንዱንም ግንብ ውፍረት እያየ “በእርግጥ አይሁድን ከነዚህ ጠንካራ ምሽጎች አውጥቶ ያዋረዳቸው እግዚአብሔር በጦርነቱ ከእኛ ጋር ነበር እንጂ፣ ምን ዓይነት እጅ ወይስ ማሽን ይህንን ግንብ ሊያፈርሰው ይችል ነበር?” እያለ ይደነቅ ነበር” ይለናል፡፡ [Josephus, Complete Work, Kregel Publication, ገጽ 581]
ጌታ ኢየሱስ ሲናገር “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን [ጥፋት] እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም” ብሏል። እርግጥ ነው በቀዳሚ ምጽአቱ በከብቶች በረት “ሕጻን ተወልዶልናል፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል” የሚለው የምስራች ለምድር ሰላምን ያወጀ፣ “ስሙም የሰላም አለቃ” የተባለ፣ ተሰቅሎ በመሞት ህዝቡን ያዳነ ክርስቶስ የአለሙ ሁሉ መድሐኒት ነበር፤ እርሱ ራሱ መልሶ ግን፣ መጻኢውን የእስራኤልን ውድመት እያየ፣ “በምድር ላይ ጥፋትን ላመጣ መጥቻለሁ” ማለቱ የእስራኤል አዳኝ የሆነው እርሱ የእስራኤል አጥፊ መሆኑን ያመለክታል። ይህ የሚያስፈራ እውነት ነው፣ እስራኤልን ያጠፋው የፈጠረው ራሱ ነው። እግዚአብሔር በባህርዩ የሚምርም የሚራራም አፍቃሪ አባት የሆነውን ያህል፣ የሚቆጣ፣ የሚፈርድ፣ የሚገድል እና የሚያጠፋም የፍርድ አምላክ ነው። እስራኤልን ያጠፋት እና ለሚያጠፏት አሳልፎ የሰጣትም ያህዌ ነው። ቲቶና ግሪሳ ሰራዊቱን በእስራኤል ላይ ያዘመተና ለጦርነት ያስከተታቸው ፈቃዱን የማይቃወሙት የኃያሉ የእስራኤል አምላክ ክንድ ነው እንጂ ቄሳርም ሆነ የትኛውም የምድር ኃይል አይደለም።
ስለዚህ እግዚአብሔር በጸጋው ለእስራኤል በሰጠው የንስሃ እና የመመለስ እድል በሰባኛው ሱባኤ እኩሌታ ባሳያቸው የበዛ ትዕግስቱ፣ የወንጌሉን ምስክርነት በብዙ ማስረጃ ከተአምራት ጋር አቀረበላቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም በአሥራ ሁለቱና በመቶ ሃያው ላይ ሲያወርድ፣ የክርስቶስንም ትምህርት በግልጽ ሲያወጣው፣ እንግዲህ እስራኤል የምትመዘንበት፣ ተመዝናም ቀላ ወይም ከብዳ የምትገኝበት የመጨረሻው ሱባኤ ሚዛን ሲጀመር እናያለን።
መልአኩ ገብርኤል ፍጹም ጥፋት እንደሚሆን ለነብዩ ዳንኤል ነግሮታል፣ (ዳን. 9፥ 27)፤ ነብዩ ዘካርያስም ክርስቶስ በዚያ አስፈሪ ጥፋት ተመልሶ ሲመጣ አሕዛብን ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ ለጦርነት እንደሚሰበስብ ይናገራል (ዘካ 14፥ 1-4)። ነብዩ ሚልክያስም እግዚአብሔር ገለባውን በማይጠፋ እሳት አቃጥሎ ጻድቃንን የሚያድንበትን ቀን ሲያዘጋጅ፣ የዳኑቱ በጋጣው ውስጥ እንደ ሰባ እንቦሳ የሚቦርቁበት ቀን ያመጣል፣ (ሚል 4፥ 2) ሲል ይናገራል። ነብዩ ኢዩኤልም የቤተ ክርስቲያንን ዘመን ከክርስቶስ መመለስ ጋር ባለው ትስስር ሲናገር ይህንንው ክስተት ተናገሯል፣ (ኢዩ 2፥ 31)። ጌታ ኢየሱስም ለክፉዎች በበቀል ብድራትን ሊመልስ እንደሚመለስ በግልጽ ተናግሯል፣ (ማቴ. 16፥ 27-28፤ ጨምሮም በማቴ 23፥ 34-39፤ 24፥ 29-30; 26፥ 64; 21፤ 20-32 ያለውን ተመልከቱ)። እንደ ማቴ 10፥ 23 ከሆነም የሚመለስበትን ቀንና ይህን ታላቅና አስፈሪ የሆነ የእስራኤልን ጥፋት ጊዜውን ወስኖ እስከ መናገር ደርሷል። “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።” (ማቴ 23፥ 36) የሚለውም የመከራውን ወቅት ይጠቁማል። ይህ የመከራ ጊዜ እስራኤል እንደ ሕዝብ የምትሰበርበት፣ መጽሐፍ ቅዱስም ታላቁ መከራ እያለ የሚጠራው የፍጻሜ መከራ ነው።
እንግዲህ ቅዱሳት መጻሕፍትም ሆኑ የታሪክ መዛግብት ከ66 ዓ.ም ጀምሮ በአይሁድ ሕዝብ ላይ የመጣባቸውን ከባድ መከራ በግልጽ ያረጋግጣሉ። በዚህም የመከራ ክንፎች ላይ የእስራኤልን ሕዝብ እስከ መጨረሻ የሚያጠፋ አጥፊ ሰው እንደ ጎርፍ ሆኖ በወረራ ከሰሜን መጣባቸው። ስለዚህም የዳንኤል ራእይ ፍጻሜውን ያገኘው ይህ አጥፊ በመጣበት ወቅት ነው፣ (ዳን 12፥ 1፤ ማቴ. 24፥ 21)።
በመጨረሻም፣ ይህ የነብዩ ዳንኤል ሰባ ሱባኤ የመጨረሻውን ዘመን ትምህርት እናስተምራለን በሚሉ በርካታ ስሁታን [T(E)rrorist] ተርጓሚዎች ከአውደ ምንባቡ ተነጥሎ እየተተረጎመ ምዕመናን ለብዙ ግራ መጋባት (Confusion) ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓል። ለእስራኤል የተቀጠረው ሰባው ሱባኤ አልፏል፤ ወደፊትም የለም። አሁን ያለነው በመንግስት ዘመን ውስጥ ነው እንጂ በቀጠሮ ውስጥ አይደለም። ሰባው ሱባኤ ተፈጽሟል፣ የዘላለም መንግስት ዘመንም ተጀምሯል። ሰባው ሱባኤ ሊፈጸም ነው፣ በሰባኛው ሱባኤ መጨረሻ ላይ ነን፣ አስራ አንደኛው ሰአት ላይ ነን፣ የጌታ ምጽአት ቀርቧል፣ ልንነጠቅ ነው፣ አርማጌዶን እየመጣ ነው፣ ወዘተ፣ ይህ ሁሉ የሽብርና የስህተት እምነት የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ መሰረት አድርጎ የተፈጸመውን ወንጌል በሚያስተምር ሙሉ ኃላፍያንነት ፊት አይቆምም። እንግዲህ በሚመች ጊዜ ታሪካዊ ድርሳናትንም ዋቢ አድርጌ የዚህን ታሪካዊ ፍጻሜ በጽሁፍ ለማደራጀት እጥራለሁ። እስከዚያው ግን ከላይ በስድስት ነጥብና በንዑሳን አሳቦች ለማስነበብ የሞከርኩት ምናልባትም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ለማሰብ ፍላጎቱ ላላችሁ ይህ ምልከታ ለተሻለ ጥናት መንደርደሪያ እንደሚሆናችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።
ጸጋው ይደግፋችሁ!!
ግዛቸው።
ለዚህ ጽሁፍ ግብዓት የሆኑ ሥራዎች:-
Tommy Shaw, The Destruction of Jerusalem: It's Important Place in the Divine Plan, 1979
George Peter Holford, The Destruction of Jerusalem (1805)
Josephus, Complete Work,
Jessie E. Mills, Jr; Daniel: Fulfilled Prophecy (2003)
D.S. Russell, The Daily Study Bible Series: Daniel (1981)
Holman Bible Dictionary (1991)
Theological Wordbook of The Old Testament, Vol 1&2 (1980)
No comments:
Post a Comment