የአሕዛብ ዘመን ተፈጽሟል!!
ኢየሱስ የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም ትረገጣለች በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ይህ ጉዳይ ምንድን ነው? ወይስ ምን ነበር? ከዚህ በኋላስ ይህ የአሕዛብ ዘመን መጨረሻው ወደፊት ቅርብ ነውን?
ሉቃስ 21፥ 23-24 “በዚያን ወራት ለእርጕዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይሆናልና፤ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።”
የአህዛብ ዘመን የጀመረው፣ የሚፈጸሙውስ መቼ ነው? የአህዛብ ዘመን የጀመረው ባቢሎን ኢየሩሳሌምንና ይሁዳን ስትቆጣጠር እንደሆነ ዘመን መዳቢዎች (Dispensationalists) ሊነግሩን ይሞክራሉ። ከእነርሱም መካከል አንዳንዶች ደግሞ የአሕዛብ ዘመን በ1967 ዓ.ም ላይ እንዳበቃ ይናገራሉ። ዘመነኞቹ ደግሞ ገና ወደፊት የሚያበቃ ነው ይሉናል። የቃሉ አማኝና ተማሪ ነኝ ባይ ማንም ሰው ቢሆን፣ የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል እና በጥቅሉ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ክፍል በተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከተገለጠው ትምህርት ነጥሎ ሊተረጉምም ሆነ ክፍሉ ከተነገረበት መጽሐፍ ተፈጥሮ በተለየ ሊረዳው እንደማይቻልና እንደማይገባ መገንዘብ ያስፈልገዋል። ምንም ቢሆን ከመፅሃፍ ቅዱስ የተወሰደ የትኛውም ምዕራፍ ምንባቡ ከተወሰደበት ክፍል ተነጥሎ ሊተረጎምም ሆነ ሊብራራ አይችልም። እንዲሁም የትኛውንም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ወይም ምዕራፍ አስቀድሞ በተደረሰበት ቅድመ ግንዛቤ፣ ወይም ሲነገረንና ሲመስለን በኖረው ቅድመ እሳቤ ፣ ወይም ብዙሃኑ በተቀበለውና በተለመደው የአተረጓጎም ዘዴ ተርጉሞ ማቅረብ አይቻልም። ቃሉ ራሱን በራሱ እንዲተረጉም የማይፈቅድ ተርጓሚ ነኝ ባይ ሁሉ ይስታል፣ ሌሎችንም ያሳስታል።
ለምሳሌ እንደ ራንዳል ፕራይስ ያሉ፣ Pretrib Premillennialists “የአህዛብ ዘመን ፍጻሜ” የሚለውን ቃል ሲተረጉሙ በሮሜ 11፥ 25 ላይ ካለው “የአሕዛብ ሙላት” ከሚለው ጋር ያገናኙትና ሁለቱም ጥቅሶች ገና ወደፊት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ይጠባበቃሉ፤ በዚህም ጊዜ “ሁሉም እስራኤል” ንስሐ ይገቡና፣ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ ለዘላለም እንዳይጠፉ አይሁድ ኢየሱስን እንደ መሲሕ ይቀበላሉ፤ ሲሉ ያስተምራሉ። በዚህም እይታቸው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ70 ዓ.ም ከሆነው ጥፋት ጀምሮ እነርሱ ገና ይመጣል ብለው እንደሚጠባበቁት እስከ መጪው እድሳት ድረስ ያለውን ጊዜ “የመረገጥ” ዘመን ወይም ባድማ የመሆን ጊዜ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። በርካታ ኮሜንታተሮችም፣ (ለምሳሌ፣ አልበርት ባርነስ፣ አዳም ክላርክ፣ ቤዛ፣ ባለአራት ወንጌል፣ JFB እና ሌሎችም) በዚሁ መስመር እያሰቡ ይህንኑ አመለካከት ይጋራሉ።
ጆኤል ቢ. ግሪንም በሉቃስ ወንጌል ማብራሪያው ላይ በገጽ 739 ላይ “የአህዛብ ዘመን” የሚለውን ሁለት መንታ ትርጓሜ አለው፣ አንዱ በኢየሩሳሌም ላይ የተነገረውን የእግዚአብሔርን ፍርድ በማስፈጸም ረገድ አሀዛብ የእግዚአብሔር ወኪል የመሆን ሚናቸውን ሲያመለክት፣ ከዚህ በላቀ ግን በአህዛብ መካከል የወንጌሉ የምስራች የሚታወጅበትን ጊዜ ያመለክታል ይላል:: ይህ በሉቃስ “የአህዛብ ዘመን” የተሰኘ ሃረግ በጳውሎስ የሮሜ መልዕክት ከተነገረው “የአህዛብ ሙላት” ከሚለው ጽንሰ አሳብ ጋር ለምን እንደሚሳከር አይገባኝም።
ዲ. ኤ. ካርሰን አርታኢው በሆነበት NIV Biblical Theology Study Bible የሉቃስ ወንጌል ማብራርያው ላይ ይህንን ጥቅስ ሲተረጉም በዚሁ ፍሰት [ከሰባ ሊቃናት የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም] በዘካርያስ 12፥ 3 “በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፤ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቈስላሉ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ።” የሚለውን ጠቅሶ እንዲህ ይላል፦ ምንም እንኳ ይህ ጊዜ በሮሜ 11፥ 25 የተጻፈውን የአሕዛብን መዳን ሊመሰክር ቢችልም፣ የአሕዛብ ዘመን እርሱም አሕዛብ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያሳድዱበት ጊዜ ማለት ነው። ይህም ተፈጽሟል፤ ይልና፣ አክሎም እግዚአብሔር ቁጣውን እንደሚገድበው ይህ ይጠቁማል (ማቴዎስ 24፥ 22፤ ማርቆስ 13፥ 20) ይላል። ኤፍ. ኤፍ ብሩስም አርታኢው በሆነበት የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ይህንንው ጥቅስ አንስቶ የአሕዛብ ጊዜ እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ ትረገጣለች የሚለውን የቁጥር 24 ቃል “ሲተረጉም ይህ ምናልባት የአሁኑን አለም ስርዓት መጨረሻ ያመለክታል”፤ ይልና ፍጻሜውን ከዚህ ዘመናዊ አለም መጻኢ ጊዜ ጋር ያገናኘዋል።
ለእንግሊዝኛ አንባብያን የተዘጋጀው የኤሊኮት ማብራርያም በጥቅሱ ላይ የሚያቀርበው ትንታኔ፣ የእስራኤል ቅጣትና የኢየሩሳሌም ጥፋት ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ሁለቱም የሚታደሱበት አንድ ቀን እንዳለ፣ ከጠቅላላው የቅዱስ ጳውሎስ ሐሳብ ጋር እንደሚስማማ የሚታወቅ ነው፤ ሲል በዚህ አንቀጽ ላይ የተገለጸውን ሐሳብ ያስተጋባል። በሮሜ 9-11፣ የተሰጠውን ትምህርትም በማምጣት በተለይ በሮሜ 11፥ 25፣ “የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ”፣ የሚለውን ጥቅስ ሉቃስ “የአሕዛብ ዘመን” ሲል ከሚጠራው ጊዜ ጋር በማገናኘት ያ ጊዜ የአህዛብ የተሻሉ፣ ወቅቶች ናቸው፣ እነርሱም እስኪፈጸሙ ድረስ” የሚሉትን ቃላት ያስተገባሉ” ሲል ይተረጉማል። የቤንሰን ኮመንታሪም ስለዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ ሲሰጥ “የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ - ማለት አሕዛብን ለመለወጥ በእግዚአብሔር ምክር የተወሰነውን ጊዜ የሚያካትት ነው፣ ይልና፣ ቀጥሎም ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ክፍል ግልጽ ማብራሪያ በሮሜ 11፥ 25 ላይ ሰጥቶናል ሲል ያክላል። ይህም የሉቃስ ወንጌል የትንቢቱ ክፍል በዳንኤል 9፥ 27 ላይ ኢየሩሳሌምን እስከ ፍጻሜ ድረስ ባድማ ያደርጋታል ለሚለው ትንቢታዊ ቃል መልስ ይሰጣል፤ በዚህ ሕዝብ ላይ ቁጣ ይፈስሳል፣ ምድሪቱንም ባድማ ያደርጋታል ይላል። እዚህ ላይ ያለው የሁለቱም ምንባቦች ትርጉም እንደሚያሳየው፣ በሉቃስ ላይ ከተነገረው ጥፋት በኋላ፣ ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና ትቀጥላለች፣ እግዚአብሔር የወሰነውን ቁጣ በእርሷ ላይ እስኪያፍሥባት ድረስ፥ አሕዛብም ወደ እግዚአብሔር ዘወር እስኪሉ ድረስ ይህ በምደሪቱ ላይ የተወሰነው ቁጣ አይጠናቀቅም ይላል።
የሆነው ሆኖ እንደ ሜየር እና ላይትፉት ያሉ ተርጓሚዎች ደግሞ ይህ የአህዛብ ዘመን ሙላት በ70 ዓ.ም ላይ ሙሉ በሙሉ እንደተፈጸመ አድርገው ለበኩረ ተደራስያኑ አውድ ተስማሚ በሆነ መንገድ ያዩታል። ለምሳሌ፣ ሜየር “የአህዛብ ዘመን” የሚለውን ቃል ትርጉም “. . . መለኮታዊ ፍርድ በፓሮዥያው እስከሚጠናቀቅ፥. . . እንዲህ አይነቱ የአሕዛብ ዘመን በራሳቸው በበኩረ ተደራስያኑ የሕይወት ዘመን (ቁጥር 28) ላይ የሚያበቃና፣ የሚያልቅ ነው (ሉቃ. 21፥ 25-27) …. ስለዚህም እነዚያ ካይሮስ (አይነተኛ ጊዜዎች) የሆኑ የጊዜ መደቦች እንደ ረጅም የጊዜ ቆይታ ሊቆጠሩ አይችሉም…” ሲሉ ይረዱታል።
በተመሳሳይም ላይትፉት የተባሉ ኮሜንታተርም ይህ “የአሕዛብ ዘመን” የተሰኘው የጊዜ ምዕራፍ ምልክቶቹን ባዩት የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ወቅት እንዳበቃ ይገነዘባሉ፣ እንዲህም ይላሉ:- “… ከዚህ ከቁጥር 32 ይልቅ የበለጠ ግልጽ ሊባል የሚችል ነገር የለም፣ “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም”። የሚገርመው ነገር ይህ ዘመን ወደ ፊት ድጋሚ እንዳይታይ ሆኖ መነገሩ ነው… ”፤ ማለትም፣ ከአሁን በኋላ መታየት ወይም መደገም የሌለበት አስገራሚ ነገር ነው…[ምክንያቱም] እነዚህ ቃላቶች በጠቅላላው በምዕራፉ ውስጥ ትርጉምን አመልካች [ጠቋሚ] ናቸው…”
ሜየርም ሆኑ ላይትፉት ሁለቱም (በተለይ ከቁጥር 25-28 እና 32 የተጠቀሰውን) የፍጻሜውን ጊዜ የሚያመለክቱ በርካታ ጥቅሶችን በዐውደ-ምንባቡ አገባብ ጠቅሰው አቅርበዋል። ከዚህ በታች የተዘረዘሩት በርካታ የዐውደ-ምንባቡ ፍንጮችም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የተከሰተው ይህ “መረገጥ” እና “የአሕዛብ ዘመን” የተሰኙ ጽንሰ አሳቦች ፍጻሜእቸውን የሚያገኙ እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ።
ጌታ ኢየሱስ በሉቃስ 21፥ 20 ላይ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ አይነተኛ ምልክት ሲሰጣቸው፥ ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው በዘመኑ ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ነው እንጂ፣ ወደ ፊት በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ለሚመጡ ትውልዶች አይደለም። ይህም አይነተኛ ምልክት ኢየሱስ ሲናገር በዙሪያው ሆነው ሲሰሙት የነበሩትን ደቀመዛሙርቱን ብቻ የሚመለከት ካልሆነ ሌላ በየትኛወም ዘመን እና ትውልድ ያለን ሰው አይመለከትም።
ሉቃስ 21፥ 22 “የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል ጊዜ ነውና።” ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ስለተተነበዩት አጠቃላይ ስለሆኑ በርካታ ክንውኖች እየተናገረ ነው፣ እነዚህም ሁሉ (ማለትም “መረገጥን” እና “የአሕዛብ ዘመን”ን ጨምሮ) ተፈጻሚ የሚሆኑት በእነዚያ “የበቀል ቀናት” ይኸውም በዘመኑ የነበሩ ደቀመዛሙርት በሕይወት እያሉ ነው።
ሉቃስ 21፥ 23-27 “በዚያን ወራት ለእርጕዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይሆናልና፤ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች። በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።”
ጌታ ኢየሱስ በአይሁዶች እና በሮማውያን መካከል ስለሚደረገው ጦርነት እና በመጨረሻም ምን እንደሚመጣባቸው በግልጽ እየነገራቸው ነው። በአጭሩ፦
ብዙዎቻቸው በሰይፍ ስለት ተገድለው ይወድቃሉ፤ እንደ ጆሴፈስ እና ሌሎች የታሪክ ምሁራን ዘገባ ከሆነ በእነዚያ አይሁድ በቀሰቀሱት አመጽ እና የሮማውያን ወታደሮች የከተማይቱን ቅጥር ሰብረው በህዝቡ ላይ በከፈቱት ዘግናኝ ጦርነት ከአሥራ አንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎች በሰይፍ እንደተገደሉ ይገመታል። ይህ በኢየሩሳሌም ላይ የተደረገው ከበባ ግልጽ ወታደራዊ ጭፍጨፋ ነበር።
የቀሩት ይማረካሉ፤ ይህ ቀደም ባለው ታሪካቸው ከለዳውያን በእነርሱ ላይ ድል ተቀዳጀው ወደ ምድራቸውና ወደ ሕዝባቸው በምርኮ አግዘው እንደወሰዷቸው አይነት አይደለም፤ አዎ ያኔ ከአሁኑ በተሻለ የተወሰዱት ወደ አንድ ህዝብና አገር ነው፤ አሁን ግን በዚህኛው ምርኮ እርስ በርሳቸው ለመገናኘትና ሃሳብ ለመለዋወጥ እስከማይችሉ ድረስ፥ እርስ በርሳቸውም እስከማይዋሃዱ ድረስ በምድር ላይ ተንሰራፍተው ወዳሉ ወደ አሕዛብ ሁሉ ይበተናሉ።
ኢየሩሳሌም ራሷ በአሕዛብ ተረግጣለች። ዓመፀኛና ክፉ ከተማ፣ ነገሥታትንና አውራጃዎችን የምትጎዳ፣ ስለዚህም የተጠላች ከተማ ተደርጋ ባድማ እስክትሆን ድረስ ሮማውያን ራሳቸውን ገዥ አድርገው ይሰለጥኑባታል። ምድሪቱ የተነገረባትን መለኮታዊ የበቀል ጊዜ ለመንገር ግን ያዳግታል። ይህ የትንቢት ቃል የተፈጸመበት መንገድ በእውነቱ አስገራሚ እንደሆነ ጥቂት የታሪክ ማሳያዎችን እናንሳ:-
አይሁዶች ከሮማውያን ጋር ባደረጉት ዘግናኝ ጦርነት ሞትን እና ግዞትን አስተናግደው ውድመት ከደረሰባቸው በኋላ፣ የሮማው ቄሳር ቬስፓሲያን የመንግስቱ ወኪሎች ለሆኑ ባለስልጣናት መላውን የይሁዳ ምድር እየሸነሸኑ እንዲሸጡ ትዕዛዝ አውርዶ ነበር፣ "በዚያን ጊዜ ቄሳር የአይሁድን ምድር በሙሉ እንዲሸጡ ለባሱስ እና ለሊቤርየስ ማክሲሞስ አቃቤ ህግ ትዕዛዝ ጻፈ፤ በዚያም ምንም አይነት ከተማን መልሶ አልሠራም፥ ነገር ግን አገራቸውን በሙሉ የራሱ ገንዘብ አድርጎ ያዘ፥ በዚያም ስምንት መቶ ወታደሮችን ብቻ ትቶ ከኢየሩሳሌም ሠላሳ ምዕራፍ የምትሆን ኤማሁስ የምትባል መኖሪያን ይሰፍሩባት ዘንድ ሰጣቸው። ለአይሁድም ሁሉ ተበትነው በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ላይ ግብር ጣለባቸው፥ እንደ ቀድሞው ዘመን ለኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ይከፍሉ እንደበረው ሁሉ፣ እያንዳንዳቸውም ሁለት ድርሃም ወደ ማዘዣው ጣቢያ ያመጡ ዘንድ አዘዛቸው፥ በዚያን ጊዜም አይሁድ የነበሩበት አስከፊ ሁኔታ ይህ ነበር። በተለይ ኢየሩሳሌም፣ ከመላ ግዛቷ ጋር፣ በአህዛብ እጅ የወደቀች፣ የቄሳሩ የቬስፓዢያን የግሉ ንብረት ሆናለች፣ በዚያም ሊኖሩ ምርጫቸው ላደረጉ አሕዛብም ተቸብችባ ተሸጠች። ኢየሩሳሌም በዚህ ሁኔታ ባድማና ውድማ ሆና እንደቀጠለች ዲዮ ሲናገር፣ ንጉሠ ነገሥት አድሪያን መልሶ እንዲያሠራት፣ እንዲቀመጥባትም ቅኝ ግዛት የሚያደርጋትን ወኪል ልኮ ኤልያ ብሎ ሰየማት። ነገር ግን ሁኔታውን ቀይሮ ጽዮንን እና ቤዛታን ትቶ ጌታችን ወደ ተሰቀለበት ቀራንዮ ድረስ ተስፋፍቶ ያዘ። ከዚህም በላይ አድሪያን አንድም አይሁዳዊ ወደ ኢየሩሳሌም አካባቢ እንዳይጠጋና እንዳይገባ አስገዳጅ ሕግ እንዳወጣ ዩሴቢየስ በታሪካዊ ዘገባው ነግሮናል። ስለዚህ አይሁዶች ከርስታቸው እየተሳደዱ ተነቅለው ሲወጡ ብዙ እንግዶች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ገቡ፣ ከተማዋም የሮማውያን ቅኝ ግዛት ሆነች። በኋለኛው ዘመን ግን ጁሊያን፣ ጌታችን ስለ አይሁድ ሕዝብ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙ በአሕዛብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረና የመለወጣቸውም ዋና ምክንያት እንደነበረ በማስተዋሉ፣ ሃይማኖቱን ክዶ ይህንን ድጋፍ ከክርስትና ለመንፈግ ወስኖ ነበር። ያኔም አይሁዶች የራሳቸውን መሬት እንዲይዙ በማምጣትና ሃይማኖታዊ ሥርአታቸውን እንዲፈጽሙ የሲቪል መንግስት አይነት ፈቀደላቸው። አይሁድ ጸሎትና መስዋዕት የሚያቀርቡት በዚያ ስፍራ ብቻ እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ለዚሁ ዓላማው ሲል ኢየሩሳሌምን እንደገና ለመገንባትና ቤተ መቅደሱን በጥንታዊ መሠረቱ ላይ ለማቆም ወስኖ ነበር። በዚህም እቅዱ መሰረት ለአይሁድ ማህበረሰብ ደብዳቤ ጽፎ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ጋብዟቸው ነበር፤ ደብዳቤውም ከሌሎች ሥራዎቹ መካከል አሁንም ድረስ አለ። ከሌሎች ብዙ ነገሮች ጋር ሲያበረታታቸውም፦ “ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ልትቀመጡባት ስትመኟት የነበረችውን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን እኔ ራሴ ባለኝ አቅም ሁሉ እሠራታለሁ አኖራታለሁም” ይላቸው ነበር። ንጉሠ ነገሥቱም ታላቅ ዝግጅት አድርጎ ቤተ መቅደሱን እንደገና በመገንባት እቅዱን መፈጸም ጀመረ፤ ነገር ግን እርሱ ለሥራው ያሰማራቸው ሠራተኞች ግልጽ በሆነ በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ወዲያውኑ ስራውን ለማቆምና ከስፍራው ለመሸሽ ተገደዱ። አሚያኑስ ማርሴሊኑስም ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር “በኢየሩሳሌም ትልቅ ዋጋ ያለው ቤተ መቅደስ ለመሥራት ወሰኖ ነበር” ሥራውንም ያፋጥነው ዘንድ ለአንጾኪያው አሊጲዮስ ሰጠው ነገር ግን አሊፒዮስ በታላቅ ትጋት ሥራውን ለመፈጸም እየጣረ ሳለ፣ ስለ ስራውም ለግዛቲቱ ገዥ በማስረዳት ላይ እያለ ከህንጻው መሠረት አጠገብ እጅግ አስፈሪ የሆኑ የእሳት ኳሶች መፈንዳት ጀመሩ፣ ፍንዳታውም ተደጋጋሚ እና ለብዙ ጊዜ የቀጠለ በመሆኑ በፍንጣሪውና በሚተፋው እሳት ሠራተኞችን በማቃጠል ገደላቸው፣ ሰውም የማይደረስበትን ቦታ ሁሉ አቃጠለው፤ እሳቱ ያለማቋረጥ ስላባረራቸው በዚህ ምክንያት ስራው ቆመ። ይህም ክስተት እና እውነታው የተረጋገጠው በአይሁዳዊው ዘሙት ዳዊት ሲሆን፣ ጁሊያንም ይህ ሙከራ በራሱ እግዚአብሔር እንደተደናቀፈ በሐቀኝነት መስክሯል። በተመሳሳይም በናዚያንዜን እና በክሪሶስቶም በግሪኮች፣ በአምብሮስ እና በሩፊን በላቲን መካከል ነገሩ ሲነገር ኖሯል፣ ክስተቱም በተከሰተበት ጊዜ በህይወት የኖሩት፣ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች ከተከሰቱ በኋላ ባሉት የሃምሳ አመታት ጊዜ ውስጥ ቆይተው ታሪኩን የፃፉና የአይን ምስክሮች ሆነው በህይወት ከነበሩ መካከል ቴዎዶሬት እና ሶዞሞን፣ ፊሊስተርዮስ፣ አርያን፣ ፎቲየስ እና የኖቫታውያን ደጋፊ የነበረው ሶቅራጥስ ይጠቀሳሉ። ስለዚህ፣ አይሁዶች እና አረማውያን፣ በሮም ንጉሠ ነገሥት እየተመሩ፣ ጌታችን በኢየሩሳሌም ከተማና በቤተመቅደስዋ ላይ “እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ሲል የተናገረውን ወድሞ የመቅረት ትንቢት ለማደናቀፍ ኃይላቸውን ሁሉ አንድ አድርገው ቢያስቡም፣ ያሰቡትንም ቢያደረጉ፣ መለኮታዊ እርግማን ያለባትን ከተማ መልሰው ሊያነሷት ግን አልቻሉም።
ጌታ ኢየሱስ ስለ እነዚያ “የበቀል ቀኖች” በድጋሚ ሲናገር ይህ አጠቃላይ ክንውን እንደማይቀር ነግሯቸዋል፣ እነርሱም ፦
ነፍሰ ጡር የሆኑ እርጉዞች እና ህጻናትን የሚያጠቡ ሴቶች በዚያን ጊዜ “ታላቅ ጭንቀት” ይደርስባቸዋል
የአይሁድ ሕዝብ ላይም “ቁጣ” ይደርስባቸዋል
“በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፣”
“ወደ አሕዛብ ሁሉ ተማርከው ይወሰዳሉ”
ከእግር በታችም “የተረገጡ” ይሆናሉ፤
“በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ያሉ ምልክቶች” ይደረጋሉ፣
“ድንጋጤ”፣ “ግራ መጋባት” እና “ፍርሃትም” ይሆንባቸዋል፣
“የሰማያት ኃይላትም ይናወጣሉ” እንዲሁም
“የሰው ልጅ ሲመጣ ያዩታል፤ የሚሉት ናቸው።
እነዚህም ክንውኖች “በእነዚያ ቀናት” ውስጥ የሚፈጸሙ እንደሆኑ በግልጽ ያመለክታል። ይህ በአይሁድ ላይ እንደሚደርስ ሉቃስ የሚነግረን የበቀልና የቁጣ ቀን የአይሁድ ህዝብ ታላቁ መከራ ነው እንጂ የቤተክርስቲያን ታላቁ መከራ አይደለም። እርግጥ ኢየሱስም ሆነ የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን የህንን ታላቁ መከራ የተሰኘውን ሃረግ በቤተ ከርስቲያንም ሆነ በአይሁድ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን መከራ ለማመላከት ተጠቅመውበታል። ሉቃስ 21፥ 24 ላይ ያለው ግን ሮማውያን በየሩሳሌምና በመላው የአይሁድ ሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት የሚያመለክት ነው። ታሪክ አዋቂው ጆሴፈስም እነዚህን ሁሉ ነገሮች በታሪካዊው ድርሳኑ ውስጥ ጠቅሶ ዘግቧቸዋል። የሚያጠቡ እናቶች ጡት ያልጣሉ ጨቅላ ልጆቻቸውን ቀቅለው የበሉበትን ታሪክ፤ በአይሁድ ላይ የደረሰባቸውን በቀል እና በከተማቸው መካከል በሰይፍ ስለት ተገድለው ስለመውደቃቸው፤ በሰማይ ኃይላት ላይ ሰለታዩ ምልክቶች በዝርዝር ያስነብበናል። አለማቀፍ የፕሪቴሪስት ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ስቲቨን ኤድዋርድም የነዚህን ክስተቶች ዝርዘር ታሪካዊ ፍጻሜ አደራጅተው ለንባብ ባበቁት ጥልቅ ጥናታዊ ሰነድ ሌሎችን በርካታ የታሪክ ምሁራን ጠቅሰው በማስረጃ ያቀርባሉ
ሉቃስ 21፥ 28 “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።”
ጊዜን አመልካች በሆኑ በእነዚህ ክንውኖች መካከል ለተፈጻሚነታቸው ምንም አይነት የጊዜ ልዩነት የለም። ኢየሱስ ከላይ የተጠቀሱትን እነዚህን ዘጠኙንም ክንውኖች (“እነዚህ ነገሮች” ሲል) እንደ አንድ አጠቃላይ የክስተቶች ስብስብ ጠቅሷቸዋል፣ እነዚህም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ደቀ መዛሙርቱ በህይወት እያሉ የሚያዩአቸው ጉዳዮች ነበሩ፣ እነርሱም “እነዚህ ነገሮች” የተባሉትን ክንውኖች ሲያዩ በዚህ መንገድ ቤዛቸው እንደቀረበ ያውቃሉ ማለት ነው።
ሉቃስ 21፥ 31-32 “እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።”
ኢየሱስ እዚህ ላይ “እናንተ” ሲል የሚጠቅሳቸውና በእርሱ ዘመን የነበሩ ደቀ መዛሙርቱ “እነዚህ ነገሮች” የተባሉ ክንውኖች ሲፈጸሙ እንደሚያዩ፣ ከሚያዩትም ነገር የተነሳም (ማለትም መረገጡን እና የአሕዛብን ዘመን ጨምሮ) በዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት ልትመጣ እንደ ቀረበች እንደሚያውቁ ይነግራቸዋል። ይህም ፍጻሜ ሌላ ባዕድ ፍጻሜ ሳይሆን በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን፣ በደቀ መዛሙርቱ የህይወት ዘመን የሚጠበቅ ብቸኛ ፍጻሜ መሆኑን ንግግሩ ይበልጥ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። በንግግሩ ሁለት ጊዜ (ቁ. 22፣ 24) “እነዚህ ነገሮች” የሚለው ቃል ጥቅም ላይ እንደዋለ አስተውሉ (ቁ.22፣ 32)። ምናልባት የቀሩ ጥርጣሬዎች ቢኖርባቸው እንኳ ኢየሱስ እርሱ ስለተናገራቸው ስለ እነዚህ ጉዳዮች፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሉም ነገር እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ሲል ጉዳዩን በመኃላ በማረጋገጥ ሁሉንም ጥርጣሬ ያስወግዳል። ይፈጸማሉ የተባሉት እነዚህ ጉዳዮች “ይህ ትውልድ” በተባለው የዚያን ዘመን ትውልድ ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮች መሆናቸውን እንዳንጠራጠር ኢየሱስ በመኃላ አስሮታል። መጻኢነት ግን የሚጠራጠረው ይህንን የእግዚአብሔር ልጅ መኃላ ነው። በዚህ አውድ ውስጥ የተጠቀሱት ሁሉም ክንውኖች የሚፈጸሙት የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ከማለፉ በፊት ነው። ትንቢቱ አልተፈጸመም በሚል ሌላ ብዙ ተረት የመሰለ ‘የሊቃውንትን’ ግራ-ገብ ማብራሪያ ተቀብሎ እርሱኑ እንደበቀቀን ከማስተጋባትና ሃሰትን ከማመን ይልቅ፣ ጌታ ኢየሱስ በእውነት መኃላ የተናገረውን ብቻ አምኖ ትንቢቱ በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ተፈጽሟል ብሎ መቆም ይመረጣል።
ላይትፉት ከላይ እንደተናገሩት፣ ኢየሱስ ከዚህ የበለጠ በንግግሩ ግልጽ ሊሆን አይችልም። ከቁጥር 20-32 የተጠቀሱት ሁሉም ክንውኖች በአንድ ላይ የተጠቃለሉት “ሁሉ” (ቁ. 22)፣ “ነገሮች” (ቁ. 26)፣ “እነዚህ ነገሮች” (ቁ. 28፣ ቁ. 31) በሚሉት ቃላት ነው (። ልብ አድርጉ “ሁሉም ነገር” (ቁ. 32) ማለትም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚፈጸሙበት ጊዜው ደግሞ (“እናንተ” እና “የእናንተ” የተባሉት ከቁጥር 20፣ 28 እና 31-32 ይመልከቱ) እነርሱ ራሳቸው በዘመኑ የነበሩት ደቀ መዛሙርት አሁንም ይህንንው ፍጻሜ “ለማየት” “በእነዚያ የበቀል ቀናት” (ቁ. 22-23) በሕይወት ይኖራሉ (ቁ. 20፣ 27፣ እና 31) ተብሏል። በዚህ ላይ የቀረ ጥርጣሬ ካለ፣ ኢየሱስ ሲናገር (ቁ. 32) እነዚህ ሁሉ ክንውኖች ማለትም “የመረገጡ” ጊዜ እና “የአሕዛብ ዘመን”ን ጨምሮ ይፈጸማሉ የተባሉት ነገሮች ሁሉ ተፈጻሚ የሚሆኑት “ይህ ትውልድ የተባለው የትውልድ ጊዜ ከማለፉ በፊት ነው ሲል የፍጻሜውን ጊዜ አንዴ አስረግጦ ነግር ጨርሷል። እዚህ ላይ ምንም ለመወዛገብ እድል የሚሰጥ ነገር የለም። ‘የመረገጡ’ እና “የአሕዛብ ዘመን” የሚባለው ምንም ይሁን ምን በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ውስጥ ሊፈጸሙ የተወሰኑ ክንውኖች አድርገን ልንገነዘባቸው ይገባል።
በተጨማሪም፣ በቁጥር 22 ላይ እዚህ የተጠቀሱት ሁሉም ክስተቶች በብሉይ ኪዳን እንደተተነበዩ ኢየሱስ ተናግሯል። ይህም “ብሉይ ኪዳን “የመረገጡን” እና “የአሕዛብን ጊዜ” የሚተነበየው በየትኛው ክፍል ነው? የሚል ጥያቄን ሊያስነሳ ይችላል፤ መልሱም በቀላሉ የሚገኘው ሉቃስ 21፥ 20ን በማቴዎስ 24፥ 15 ካለው ተመሳሳይነት ጋር ስናነጻጽርና ስናስተያየው ነው። ኢየሱስ ስለ “ጥፋት ርኩሰት” ሲናገር ምንጩን ከዳንኤል መጥቀሱን ልብ ይሏል። ስለዚህ በዳንኤል ላይ ስለ “መረገጥ” እና ስለ “አሕዛብ ዘመን” የሚናገሩ ሐሳቦችን ስናገኝ እምብዛም ሊያስገርመን አይገባም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መረገጥና ስለ አሕዛብ ዘመን ተጠቅሶ የምናገኘው በዳንኤል ብቻም አይደለም። አንዳንዶቹን አለፍ አለፍ ብለን እንመልከት፡-
ሰቆ.ኤር 1፥ 15 “ጌታ ኃያላኖቼን ሁሉ ከውስጤ አስወገዳቸው፤ ጕልማሶቼን ያደቅቅ ዘንድ ጉባኤን ጠራብኝ፤ ጌታ ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በመጥመቂያ (የወይን መጥመቂያ) እንደሚረገጥ አድርጎ ረገጣት።” በዚህ ጥቅስ የወይን መጥመቂያውን ረገጣ የሚያሳየውን ስዕል ልብ አድርጉ። በ70 ዓ.ም. የአይሁድን ፍርድ በተመለከተ በራእይ መጽሐፍ በተነገረው ቃል ውስጥም ይኸው ተመሳሳይ ንግግር ጥቅም ላይ ውሏል፦ “መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፥ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቍጣ መጥመቂያ ጣለ። የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፥ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ” (ራእይ 14፥ 19-20)። ይህ ቃል እንዴት እንደተፈጸመ በጥቂቱ አመልክቼ ወደኤርምያስ ሰቆቃ እመለሳለሁ።
ስዕሉን ተመልከቱ፣ መልአኩ ማጭዱን ወደ ምድር ጥሎ የምድርን ወይን ሰበሰበና ፍሬውን ታላቁ የእግዚአብሔር ቁጣ ወደሚጠመቅበት ወደ መጥመቂያው ጣለው (ይህንን ተመሳሳይ ስዕል በነዚህም ክፍሎችም ማየት ይቻላል፦ ኢሳ. 63፥ 1-6፤ ኤር 25፥ 29-33፤ ሰቆ. 1፥ 15፤ ሉቃ 19፥ 42-44)። የወይን መጭመቂያው ከትልቅ ድንጋይማ አለት ተፈልፍሎ የተሰራ ወይም በድንጋይ የተገነባ ጉድጓድ ሆኖ ወይኑ እየተቆረጠ የሚጣልበት እና ጭማቂው ተንጠፍጥፎ እስኪወጣ ድረስ በሰው እግር የሚረገጥበት ቦታ ነው። የወይኑ ደምም ከመጭመቂያው ጉድጓድ በታች ባለው ትንሽ ቀዳዳ ውስጥ ይንጠባጠባል፣ ከዚያም በየማድጋው ውስጥ ይደረጋል። የምድር ወይን በሆነችው በእስራኤል ላይ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ቁጣም ይህን ይመስላል። በእርግጥ ይህንን በዓይነ ሕሊና ለመሳል አያስቸግርም። በ70 ዓ.ም የጸደይ ወቅት፣ የእስራኤል ሕዝብ የፋሲካን በአል ለማክበር በኢየሩሳሌም በተሰበሰቡ ጊዜ፣ ሮማውያን በድንገት ከተማይቱን ከበቡ፣ በቅጥሮቿ ውስጥ ያለውን ሕዝብ እንዳይወጣና እንዳይገባ አጥምደው ዘግተው፣ ከተማይቱ እስክትፈርስ ድረስ አምስት ወራት የፈጀውን የኢየሩሳሌምን ከበባ ጀመሩ፤ ረገጣው የጀመረው ያኔ ነው።
ዮሐንስ በራእዩ ይህ የወይን መጥመቂያ ከከተማው ውጭ ሲረገጥ ተመልክቷል። በተለመደው መንገድ ጭማቂውን ከወይኑ ፍሬ አሟጦ በማውጣት ዘዴ፣ ጭማቂው ሙሉ በሙሉ ወጥቶ እስኪያልቅ ድረስ በወይን መጭመቂያው ውስጥ መረገጥ አለበት፤ ሳይጨመቅ ባክኖ የሚቀር ወይም የሚያመልጥ የወይን ፍሬ የለም። ይህ የወይን መጭመቂያ ግን ከከተማው ውጭ ተረገጠ። በውስጧ ያለው የደም ጠብታ ፈስሶ እስኪያልቅ ድረስ ሮማውያን ከከተማይቱ ውጭ ሆነው እሳትና ሞት የሚተፉ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ያለማቋረጥ በእየሩሳሌም ላይ እያወረዱና እያዘነቡ ኢየሩሳሌምን ይረግጧት ጀመር።
የወይኑ መጭመቂያ “እስከ ፈረስ ልጓም” ድረስ ተረገጠ፣ ማለት ደሙም ከመጥመቂያው እስከ ሽህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ድረስ እስከ ፈረሶች ልጓሞች ድረስ ወጣ ማለት ነው። እንደ ጆሴፈስ ዘገባ በኢየሩሳሌም ብቻ 1,337,490 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ተነግሯል። ይህ ምልክት በእስራኤል እና በኢየሩሳሌም ላይ የፈሰሰውን አስፈሪውን የእግዚአብሔርን ቁጣ አስከፊ ተፈጥሮ ያሳያል። ቁጣው የተገለጠበት ቋንቋ ምሳሌያዊ ነው፣ ነገር ግን ጆሴፈስ የከተማዋን ውድመት አስመልክቶ ከሰጠው ቀጥተኛ መግለጫ ጋር በእጅጉ ይስማማል። ሲናገርም፦ “ከተማይቱ በሞላ በደም ተጥለቀለቀች፤ በብዙ ቤቶች የነደደ እሳትም በተገደሉት ሰዎች ደም ጠፋ” ይላል፤ እልቂቱም እጅግ በጣም ብዙ ነበር። ለፈሰሰው ለእያንዳንዱ ሰው ደም ስድስት ሳንቲም ከፍታ ደም እንኳ ብንወስድ ጎርፍ ሆኖ ወደ ሄኖም ሸለቆ የገባው የደም መጠን ከሁለት ሚሊዮን ጋሎን ደም በላይ ይደርስ ነበር። ከሰሜን እስከ ደቡብ (1600 ምዕራፍ ወይም ከ182 እስከ 200 ማይል ርቀት) መላውን የፓለስታይን ምድር የሰዎች ደም ሞላው።
የከተማይቱም መከላከያ በረሃብና በጦርነት በተዳከመ ጊዜ በመጨረሻ ላይ የሮማውያን ጦር የቅጥሩን የተወሰነ ክፍል ደርምሰው ወደ ከተማይቱ ገባና የጭፍጨፋ ሥራውን አጠናቀቀ። በእየሩሳሌም ላይ ስለተፈጸመው ስለዚህ ነገር አስፋፍቶ መግለጫ መስጠትም ሆነ ጥቂት ቃላት ተጠቅሞ በተሻለ ሁኔታ ዕልቂቱን መገለጽ በእውነት አይቻልም።
ከፍ ሲል በተጠቀሰው በሰቆቃወ ኤርምያስ ያለው ንግግርም ከዚህ በታች በቀረበው የቃሉ አጠቃቀም፣ አገባብና ታርጉሙን ልብ በሉ፦
እግዚአብሔር ኃያላኖቼን ሁሉ በውስጤ አደቀቀ፤ የብላቴኖቼንም ብርታት ወደ ሚሰብርበት ጊዜ ውስጥ ስቦ እስገብቶኛል። አሕዛብም ከጌታ ዘንድ በሆነ የአዋጅ ድምጽ በሜምራ [ሎጎስ ወይም ቃል] ትእዛዝ ወደ ይሁዳ ቤት ገብተው ደናግሉን አረከሱ፣ የወይን ፍሬ በሰው ሲረግጥ ከወይን መጭመቂያው የወይን ጠጅ እንደሚፈስ እንዲሁ የድንግልናቸውን ደም አፈሰሱ። ይህ ትርጉም ኢየሩሳሌም በመለኮታዊ ፍርድ የደረሰባት መከራ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ያሳያል፣ ይህም መለኮታዊ ፍርድንና ጥፋትን እጅግ ግልጽና አሳዛኝ የሆነ ምስልን ያሳያል። በአዲሱ መደበኛ ትርጉም “በውስጤ ያሉትን ተዋጊዎች ሁሉ እግዚአብሔር ተቃወመ፣ ጎልማሶቼን ለማድቀቅ ሰራዊት በላዬ ጠራ፤ ድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ፣ እግዚአብሔር በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረገጣት።” በሚል ተገልጧል።
እዚህ በሰቆቃወ ኤርምያስ 1፥ 15 ላይ “ረገጣት” የሚለው ቃል የኃላፊ ጊዜ አመልካች ግስ መሆኑን ተመልከቱ። ይህ መረገጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ586 የሆነ እንጂ ከዚያ በኋላ መረገጡ (እንደ ቀጣይ ጥፋት ሆኖ) እስከአሁን የቀጠለ አልነበረም። ይህ “መረገጥ” በተወሰነለት ቀጠሮ በባቢሎናውያን የአህዛብ መንግስት (በ586 ዓክልበ.) ተፈጽሞ ያለፈ አንድ ነገር ነው። ያ መረገጥ በ586 ዓክልበ በኢየሩሳሌም ላይ የተወሰነው “የአሕዛብ ጊዜ” ነበር። ያም ጊዜ፣ ኤርምያስ ሰቆቃውን በጻፈበት ወቅት ያኔ ጨርሶ አልፎ ነበር። ከተማይቱም ሆነች በጠቅላላ ምድሪቱ ወድመው ነበሩ፣ ዳሩ ግን (እንደ ራንዳል ፕራይስ እና ሌሎች መጻኢያን ተርጓሚዎች እንደሚመስላቸው) ያ ቀጣይነት ያለው ጥፋት እንደ መረገጥ የሚወሰድ አልነበረም።
ኤርምያስ ይህን የኃዘን እንጉርጉሮ የጻፈው ናቡከደነፆር በ586 ዓክልበ. ስላደረሰው የኢየሩሳሌም ጥፋት ለማዘን ነው። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ለነበሩት አይሁዳውያን ኢየሩሳሌም ጠላት በሆኑ በአሕዛብ (እንደ ወይን መጭመቂያ) የመርገጧን አሳብን ኢየሱስ አንስቶ ሲናገር ለእነርሱ ጨርሶ የማያውቁት አዲስና እንግዳ ነገር አልነበረም። ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ የተከሰተ የታሪካቸው አካል ነው። ከሁሉ በላይ የሚታወሰው ግን በ586 ከክልበ. ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሰው ጥፋት ነው። የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ የተጻፈው የአሕዛብ መንግስት በሕዝቡ ላይ ያደረሰውን ታላቅ “መረገጥ” አስመልክቶ ሙሾ እና የሐዘን እንጉርጉሮ ለማውረድ ነው። ይህ በናቡከደነፆር የተደረገ ‘መረገጥ’ “የተቀጠረ” ጊዜ” እንደሆነ ኤርምያስ መናገሩን ልብ አድርጉ። በእርግጥ፣ በሉቃስ 21፥ 24 ውስጥ የተካተቱት አራቱም ነገሮች (ኢየሩሳሌም ለተወሰነ ጊዜ በአሕዛብ መረገጧን ጨምሮ፣) እዚህ በሰቆቃወ ኤር. 1፥ 15 ውስጥ ይገኛሉ። ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በአንድ ቀን አላሸነፋትም። በኋላ ላይ ሮማውያን እንዳደረጉት ሁሉ እርሱም ያኔ ከተማይቱን በተመሳሳይ ጊዜ ከበባ ማድረግ ነበረበት። ጦርነቱ በቬስፔዥያን (67 ዓ.ም.) ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቲቶ የከተማይቱን ቅጥር ንዶ በመዝለቅ ቤተ መቅደሱን እስካቃጠለበት ጊዜ ድረስ (70 ዓ.ም.) ሦስት ዓመት ተኩል ያህል ቆይቶ ነበር።
እዚህ በሰቆቃወ ኤርምያስ. 1፥ 15 የተነገረው "የተቆረጠ ጊዜ" [ማለትም፣ ጎልማሶቿን ለማድቀቅ የጠራው ጉባኤ ወይም የብላቴኖቿን ጉልበት የሚሰብርበት የተወሰነ ጊዜ] እንዲሁም "የመረገጡ" ሀሳቦች በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ካየናቸው “ከአሕዛብ ዘመን” እና “ከመረገጥ” ሃሳቦች ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ናቸው። “የተቀጠረው (የተወሰነው ጊዜ” ወይም “የአህዛብ ጊዜ” የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ወይም “አርባ ሁለት ወር” ሆኖ ከሚታይበት በቀር እነዚያን ሁለቱንም ሃሳቦች በራዕ 11፥ 2 ላይም በድጋሚ እናገኛቸዋለን።
በራዕ 11፥ 2 “በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።”
ስለዚህ እዚህ ላይ ሰቆቃወ ኤርምያስ 1፥ 15፣ በሉቃ.21፥ 24፣ እና በራእ.11፥ 2 መካከል ብዙ መመሳሰል አለ። ሦስቱም ምንባባት ተመሳሳይ የሆኑት እነዚህ አራቱም ጉዳዮች (ማለትም አሕዛብ፣ ለአህዛብ የተወሰነው የመርገጥ ጊዜ፣ ኢየሩሳሌም፣ የኢየሩሳሌም መረገጥ) አሏቸው። ሰቆቃወ ኤርምያስ እነዚያን አራት ጉዳዮች በ586 ዓክልበ. የኢየሩሳሌምን ጥፋት ለማመልከት ተጠቅሞባቸዋል።
ራእይ 11፥ 2 ባቢሎን ከተባለችው ከጋለሞታይቱ ከተማ መውደቅ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ የሆኑ አራት ነገሮችን ይጠቅሳል። መረገጡ ለሦስት ዓመታት ተኩል ብቻ የፈጀ ክስተት እንደነበር በሁሉም ምንባባት ላይ ትርጉሙ ግልጽ ነው፡- እነዚያ የአሕዛብ ጭፍሮች ማጥፋትን በጨረሱ ግዜ መረገጡ ያበቃል። አህዛብ ከተማይቱን የሚረግጡበት ዘመን ገና ወደፊት ከሺህ ዓመታት በኋላ ስለሚሆን ጥፋት ጨርሶ አያመለክትም።
ራእይ 11፥ 2 ከሉቃስ 21፥ 24 ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ነው፣ እዚህ ላይ በግልጽ የሚናገረው የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜም (42 ወራት) ነው። በሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተጠቀሱት አራቱም ተመሳሳይ ጉዳዮች (አሕዛብ፣ ለአህዛብ የተወሰነው የመርገጥ ጊዜ፣ ኢየሩሳሌም፣ የኢየሩሳሌም መረገጥ)፣ እዚህ በራዕይ 11፥ 2 ውስጥ ተጠቅሰዋል። ይህ በጣም ግልጽ የሆነ ጥቅስ ስለ ሉቃስ 21፥ 24 ትርጉም ምንም አይነት ጥርጣሬ አይፈጥርብንም።
በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ነገሮች በሙሉ ሊፈጸሙ ያሉ ነገሮች ናቸው። [ዮሐንስ ራእዩን የጻፈው በ62-63 ዓ.ም አካባቢ ማለትም የአይሁድ-ሮም ጦርነት ከመጀመሩ ሦስት ዓመታት በፊት ነው።] ራእይ 11፥ 2 የሚያመለክተው ይህ የኢየሩሳሌም ርኩስ በሆኑ አሕዛብ የመረገጧ ጊዜ ለሦስት ዓመት ተኩል የሚቆይ ሲሆን፣ ይህም የመጨረሻው የደም ጠብታ ከወይን መጥመቂያው እስኪረገጥ ድረስ ነው። እንግዲህ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በወይን መጭመቂያ ውስጥ ስትረግጥ ማለት ምን እንደሚመስል አስቡ! ከእግራችሁ በታች ከዋለው የወይኑ ፍሬ ብዛት ውስጥ ምንም አይነት ያለ መጨመቅ የቀረ አንዳች ፍሬ አይኖርም። ይህስ የነበረው ቁጣው በአጭሩ የቆመ አልነበረም። ይልቁንም አይሁድ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፉ ድረስ ያለማቋረጥ ቀጥሏል። ከዚያም ማምለጥ የሚባል ነገር አልነበረም። በተቀጠረለት ጊዜ ውስጥ የተያዘለትን ሙሉ የሆነ ኮርስ መጨረስ ነበረበት። ሁሉም ነገር ተፈጸሞ ባለቀ ጊዜ ብቻ ያኔ መረገጡ ቆመ፤ ያኔም ይረግጡ ዘንድ ለአሕዛብ የተወሰነው ጊዜ አብቅቷል።
“የአሕዛብ ዘመን” ቬስፓሲያን በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃቱን ከጀመረበት ጊዜ (67 ዓ.ም.) ጀምሮ በ70 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ረግጦና ደምስሶ እስኪያጠፋት ድረስ ረገጣው የሶስት ዓመት ተኩል ጊዜ ነበር። ዘመኑም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተፈጸሙበት “የበቀል ቀናት” ነበሩ። እዚህ ሉቃስ 21፥ 24 ላይ ዐውደ-ምንባብ ብቻ ንጉሥ ነው። በተለይም ከቁጥር 20-24 ያለውን አስተውሉ። ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየቀረበ ያለውን ሠራዊት እንዲመለከቱ ለደቀ መዛሙርቱ ይነገራቸዋል። ከኢየሩሳሌም እና ከይሁዳ ፈጥኖ ለመውጣት እና ወደ ተራራዎች ለመሸሽ ይህ አይነተኛ ምልክት ይሆናቸዋል። በብሉይ ኪዳን የተነገረው ትንቢት ሁሉ ፍጻሜውን የሚያገኝበት የበቀል ጊዜ የሚጀምረውም ያኔ ነው። ያ የተወሰነው የኢየሩሳሌም ውድመት በብሉይ ኪዳን የተነገሩ እነዚያን ትንቢቶች ሁሉ ፍጻሜ ይሰጣቸዋል። በሉቃ 21፥ 22 ላይ “እንዲፈጸም” የሚለውን ቃል ልብ አድርጉ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? ይህ የሚፈጸመው በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የበቀል እርምጃ በተወሰደበት ጊዜ፣ ሠራዊትም በላያቸው ሰፍሮ እነርሱንና ከተማቸውን ባድማ ባደረጋቸው በዚያ ዘመን ነው። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ላይ አህዛብ ይረግጧታል ሲል የተናገረውን ትንቢት በተጨባጭ ፍጻሜ የሰጠው፣ በአውደ ምንባቡም መሰረት በብቸኝነትም ፍጻሜ ሊሰጠው በቂ የሆነው ክስተት የ70ው ዓ.ም ውድመት ነው።
ስለዚህ፣ መጻኢያን እንደሚያስቡት ይህ የአሕዛብ ዘመን ለትርጉምም ሆነ ለክስተቱ ፍጻሜ ክፍት ሆኖ የተተው ነገር አልነበረም። ተጀምሮ የሚያበቃበት የተወሰነ የመጨረሻ ነጥብ አለው። NIGTC [The New International Greek Testament Commentary] ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ተመልከቱ፤
እንደ ማርቆስ ዘገባ ከሆነ ይህ የሽብር ጊዜ ስለማጠሩ ምንም የተገለጸ ሀሳብ የለም። ሉቃስ ግን ከዚህ ይልቅ በአይሁዶች ላይ የሚደርሰውን ነገር እንደ ኤርምያስ ንግግር አንዳንዶች በሰይፍ ስለት ይወድቃሉ (ኤር. 20፥ 4–6፤ 21፥ 7) ሲል፤ እንደ ጳውሎስም… ታልፈው ይሰጣሉ (ሮሜ. 7፥ 23፤ 2 ቆሮ 10፥ 5፤ 2ጢሞ 3፥ 6) ሲል እንዲሁም በሌሎች ብዙዎች እንደተነገረው ወደ አሕዛብም በምርኮ ይጋዛሉ፣ ይወሰዳሉ (ጦቢት 1፥ 10፤ ዘዳ 28፥ 64)… ኢየሩሳሌምም ራሷ ‘ትረገጣለች’ (ሉቃስ 10፥ 19) ሲል በግልጽ አስፍሯል። …ነገር ግን ይህ ሁሉ የጊዜ ገደብ የተደረገለት ወቅት ሲሆን፣ ይኸውም የተወሰነው ጊዜ፣ በዚህ በሉቃስ ዘገባ መሰረት የአሕዛብ ዘመን ተብሎ የሚጠራው ነው። አህዛብ በእስራኤል ላይ እንዲያደርጉት የተፈቀደላቸውን የእግዚአብሔርን ፍርድና በቀል ሁሉ ይፈጽሙና ኢየሩሳሌምን ይረግጡ ዘንድ መለኮት በወሰነውና በቀጠረው ጊዜ እንዲሆን የተመደበ ነበር። ይህ በአይሁድ ላይ የሚደርስባቸው ፍርድ፣ ልክ ቤተ ክርስቲያን በታላቁ መከራ ወቅት እንደሚሆንላት አይነት ጊዜው እንደሚያጥር የሚጠቁም ነገር ጨርሶ የለም። ስለዚህ አስጨናቂ የፍርድ ጊዜ የተነገረው ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ይህ የቁጣ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተሟጦ ማለቅ አለበት።
ኢየሱስ በተጨባጭ፣ እየተናገረ ያለው አሕዛብ አይሁዶችን እንደሚገድሉ፣ ወደ ሮም መንግሥት ሕዝቦች ሁሉ እንደሚማርኩ፣ እና ሙሴ ስለ ዘመኑ ፍጻሜ የተናገረው ነገር ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ አሕዛብ (ሮማውያን) በእነርሱ ላይ ሊያደርሱባቸው የተተነበዩ ጉዳዮች ሁሉ እስኪያደርጉባቸው ድረስ - እነርሱም የድል ጊዜያቸው እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ እንደሚያጠፏት ነበር። ሮማውያንም አይሁዶችን ፈጽመው እስኪያጠፏቸው ድረስ በምድሪቱ ውስጥ ቆዩ።
ይህንን የሶስት ዓመት ተኩል የጊዜ ወሰን የመረገጥን” ሃሳብ በቅርብ በአውደ ምንባቡ ውስጥ ያለ ሃሳብ ሆኖ በዳንኤል ምዕራፍ 7 ውስጥም ሶስት ጊዜ የተደጋገመ ሆኖ እንደገና እናገኘዋለን።
ዳንኤል 7፥ 7 “ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት።”
ዳንኤል 7፥ 19 “ከዚህም በኋላ ከቀሩት ሁሉ ተለይታ እጅግ ስለምታስፈራው፥ ጥርሶችዋም የብረት ጥፍሮችዋም የናስ ስለሆኑት፥ ስለምትበላውና ስለምታደቅቀው የቀረውንም በእግርዋ ስለምትረግጠው ስለ አራተኛይቱ አውሬ፥”
ዳንኤል 7፥ 23 “እንዲህም አለ፦ አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች፤ እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፥ ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፥ ይረግጣታል ያደቅቃትማል።”
ዳንኤል 7፥ 25 “በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፥ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፥ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኵሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።”
በራእይ 11፥ 2 እና በዳንኤል 7፥ 7-25 የተጠቀሱት ምንባባት ይህ “የመረገጥ” ክስተት በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚፈጸም ሁለቱም ያመለክታሉ። ስለዚህ ኢየሱስ በደብረ ዘይት ፍካሬው ላይ (ማቴዎስ 24 እና ምስስሎቹ) በእርግጥም የዳንኤልን ንግግር እያጣቀሰ ከሆነ፣ እንግዲያውስ እርሱ እንደሚለው፣ በሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተጠቀሰው ይህ “የኢየሩሳሌም መረገጥ” በእርግጠኝነት የሚያመለክተው የሦስት ዓመት ተኩሉን ጊዜ መሆኑን ያሳያል። ያኔም ሮማውያን መጥተው ኢየሩሳሌምን አወደሙ (67-70 ዓ.ም.) ያም የጊዜ ምዕራፍ እንደ ኢየሱስ ትምህርትና እንደነብያቱ ቃል ከሆነ አሕዛብ አይሁድን የሚረግጡበት ጊዜ ነበር። ያ የተወሰነው “በአሕዛብ የተረገጡበት ጊዜ” ከ70 በኋላ ስላለው የጥፋት ዘመን እና አሁን ወደ ሁለት ሺህ ዓመታት የዘመን ርዝመት ስለሚጠጋ የአይሁድ ዲያስፖራ ትውልድ አይናገርም። በራዕዩም ሆነ በዳንኤል የተነገረው የመረገጥ ዘመን አጭር የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ሲሆን እርሱም በ70 ዓ.ም የሚያበቃ መሆኑን በግልጽ ያመለክታሉ።
ይህንን ጥቅስ አስመልክቶ ከላይ መግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸውን ጨምሮ በርካታ በመጻኢያን የተዘጋጁ ኮሜንታሪዎችን ለማገላበጥ ሞክሬአለሁ። በተጨማሪም እንደ ጄ.ኤስ. ራሰል፣ ሚልተን ቴሪ፣ ጆን ኤል ብሬይ፣ ኤፍ.ደብሊው ፌራር፣ ሜየር፣ እና ላይትፉት ያሉ መምህራን ባዘጋጁአቸው ጽሁፎች ርዕሰ ጉዳዩን እንዴት በአውዱ መሰረት መልስ እንደሰጡበት ለማየት ዕድሉን አግኝቻለሁ። እዚህ ላይ ሁሉንም ጠቅሶ ለማሳየት የቦታና የጊዜ ውስንነት ይገድበናል። ከዚህም ባለፈ የሙት ባሕር ጥቅልሎች መጽሐፍ ቅዱስን፣ የኩምራን ዶክመንቶችን፣ ፊሎ፣ ጆሴፈስ፣ ዮሲፖን፣ ታልሙድ፣ ሚድራሽ፣ ዞሃር፣ ታርጉምስ፣ ፕሴውዴፒግራፋ፣ ሴፕቱጀንት እና አፖክሪፋ የተባሉትን የዕብራይስጥ፣ የግሪክ እና የእንግሊዝኛ ጽሑፎችን ማስረጃ ጠቅሰው ስለ መረገጥ እና ስለ አህዛብ ዘመን ምንነት እንዴት ተመሳሳይ ቋንቋ እንደሚጠቀሙ ያሳዩበትን የተለያዩ ፕሪቴሪስት ጸሐፍያንን ስራዎችንም መዳሰስ ያስፈልጋል። በኮምፒውተር በመታገዝም የተለያዩ ድረ ገጾች ላይ ፍለጋን አድርጎ ተጨማሪ ብርሃን የሚፈነጥቁ የምርምር ግብአቶችን ማሰስም ይገባል። ይህ ግን ለትጉሃን የቃሉ ተማሪዎች ብቻ ነው።
ቀጥሎ በሚቀርቡ ዝርዝር የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባት ላይ ያለው የመጀመሪያው “የአሕዛብ ዘመን” የሚለውን ተመሳሳይ ሐረግ እንደሚጠቀሙ ያሳያል።
ሕዝቅኤል 30፥ 3 “የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል።”
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን ሐረግ የሚገልጹት እንዴት እንደሆነ እነሆ ተመልከቱ፡- “የሕዝቦች ጊዜ” [WEB፣ ASV፣ Darby] እና “የአሕዛብ ዘመን” [ጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኪጄቪ]፤ “(ወራሪ) ብሔራት (በሌሎች ብሄራዊ አገሮች ላይ)፤ የሚያደርሱት የጥፋት ሰዓት” [ታናካህ] ወይም “አሕዛብ የሚያደርሱት የጥፋት ቀን/ ጊዜ” (አዲሱ መደበኛ ትርጉምና NASB)። በዚህ አይነተኛ አውድ ውስጥ፣ (የአህዛብ ጊዜ) የሚለው ሐረግ በግብፅ፣ በኢትዮጵያ፣ በፑት፣ በሉድ፣ በአረቢያ እና በሊቢያ ሕዝቦች ላይ በናቡከደነፆር እጅ የሚፈጸመውን የጥፋት ጊዜን የሚያመለክት ይመስላል። እነዚያ የአህዛብ አገሮች በእስራኤል ላይ የጥፋቷ “ጊዜ” በደረሰ ወቅት ተሳልቀውባት ነበር። አሁን ደግሞ እነርሱ ራሳቸው ህመሙ የሚሰማቸው ተራቸው ወይም "ጊዜያቸው" ነበር። ይህ አይነቱ ትርጉም በሕዝቅኤል ዘመን ከነበረውና አንዱ ከሆነው የነብዩ ኤርምያስ ቃል ጋር ሲነጻጸር የበለጠ ተመሳሳይነት ያለው ይመስላል።
ኤርምያስ 27፥ 7 “የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና [ለናቡከደነጾር] ለልጁ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና [ሜዶንና ፋርስ] ታላላቆች ነገሥታት [ቂሮስ፣ ዳርዮስ] እርሱን ያስገዙታል።” እዚህ ላይ ይመጣል የተባለው “ጊዜ” የሚያመለክተው የቀደመው ወራሪ ሊመጣ ባለው ወራሪ ጦር በወራቱ እንዲጠፋ የተደረገበትን ጊዜ የሚያመለክት መሆኑ በጣም ግልፅ ይመስላል፤ እንጂ ከዚያ በኋላ ላልተወሰነው የጥፋት ዘመን የሚያመለክት ፈጽሞ አይደለም።
ማርቆስ 13፥ 33 “[የተቀጠረው/ የተወሰነው] ጊዜ(ው) መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።” [ይህ ከሉቃስ 21፥ 24 ጋር ትይዩ የሆነ ምንባብ ነው። ይህ ፍርድ፣ እርሱም “የተወሰነው ጊዜ” ቀደም ሲል ካነሳነው ከሰቆቃወ ኤርምያስ 1፥ 15 ጋር፤ እንዲሁም ከዳንኤል፡ 8፥ 19፤ 11፥ 27፤ 11፥ 29፤ እና 11፥ 35 ጋር የሚመሳሰል ነው። ለሰው ልጆች ዘመናትን ወስኖ የሚሰጥ ሉዓላዊው አምላክ መሆኑን በሐዋርያት ሥራ 17፥ 26 ላይ ጳውሎስ በግልጽ ይናገራ።
[Qumran War Scroll] 1QM 15:1] ለእስራኤል የጭንቀት ጊዜ ነውና፥ ከአሕዛብም ሁሉ ጋር ለመዋጋት የተወሰነው ጊዜ ነው። የእግዚአብሔርም አላማ ዘላለማዊ ቤዛነትን ማምጣት ነው። [ይህ በብርሃን ልጆች እና በጨለማ ልጆች መካከል ያለውን የምጽአት ፍጻሜ ጦርነት የሚገልጽ ከጦርነት የመጽሐፍ ጥቅልል የተገኘ እጅግ አስደማሚ ምንባብ ነው። ይህ ጦርነት “አሕዛብ ሁሉ” ለጦርነት ወደ እርስዋ የሚመጡበትና በላይዋ ላይ የሚሰለፉበት “ለእስራኤል የጭንቀት ጊዜዋ” እንደሚሆን ልብ በሉ። ስለ ተወሰነው ጊዜ እና ስለ አሕዛብ ህዝቦች የሚናገረውን ተመልከቱ። እነዚህ ሁለቱም ጉዳዮች ማለትም የአህዛብ በእርሷ ላይ መምጣት እና የጭንቀቱ ጊዜ በሉቃስ 21፥ 24 ውስጥም የሚገኙ ናቸው። ይህ የጦርነት መጽሐፍ ጥቅልል በ70 ዓ.ም ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት አስቀድሞ የተጻፈ ነው። ይህም የሚያሳየው በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ያለው የቃላት አጠቃቀም አግባብነት ለክርስቲያናዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ተወስኖ የሚያገለግል እንዳልሆነ ያሳያል። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እና ከዚያ በፊት በኤሴናውያን እና በሌሎች የኩምራኒያውያን ቡድኖችም እንኳ ለብቻው ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር እናያለን።]
ሴፈር ዮሲፖን- የካርቴጅ ንጉሥ ሃኒባል እሱና መላ ሰራዊቱ ከነሙሉ ኃይሉ ሄዶ ምድራችንን [ጣሊያንን] ረግጦ፣ ምሽጎቻችንን አፍርሶ የሠራዊታችንን ብዛት በሰይፍ አላጠፋምን? እኛ እናንተ ላይ አድርገን እንደነበረው ለብዙ ቀናት በከበባ ውስጥ አቆየን; ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ያዝነው…[እንግዲህ እዚህም ላይ ያለው ይህ የመረገጥ ሃሳብ የሚጠቁመው ጥፋትን ለማመልከት ነው እንጂ እንደ ተራዘመ ጥፋት የሚታይ አይደለም]።
1ኛ መቃብ 4፥ 6 “በዚያን ጊዜ ደግሞ አሕዛብ መጥተው እንዳይረግጡት የጽዮንን ተራራ በረጃጅም ቅጥርና በጽኑ ግንብ ዙሪያ ሠሩ።” [እዚህም ላይ የመረገጥን ሃሳብ የሚጠቀመው ጥፋትን ለማመልከት ነው እንጂ እንደ ተራዘመ ጥፋት አይደለም።]
ሄኖክ 99፥ 2…“ወዮላቸው … የዘላለምን ሕግ ለሚተላለፉ… በምድር ላይ በእግራቸው ይረገጣሉ” [እዚህም ላይ የመረገጥን ሃሳብ የሚጠቀመው ጥፋትን ለማመልከት ነው እንጂ እንደ ተራዘመ ጥፋት አይደለም]
እነዚህ ቀኖናዊ ያልሆኑ ምንባባት እያንዳንዳቸው የመረገጥን ሐሳብ እንዴት እንደሚገልጹ ልብ በሉ። በሚያጠፋ የጠላት ጦር ተከቦ መደምሰስን የሚያመለክት የአጭር ጊዜ ቆይታን እንጂ ከዚያ ጥፋት በኋላ የሚቆይ የተራዘመ የጥፋት ጊዜን የሚያመለክት አይደለም። ሙሉ በሙሉ መጥፋትን የሚያመለክቱ ሌሎች ተመሳሳይ የ"መረገጥ" አጠቃቀሞችን የሚያንጸባርቁ ምንባባትን ከተለያዩ ቀኖናዊ ከሆኑና ካልሆኑ ምኝጮች ተመልከቱ፣ ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ግሪክ ቴስታመንት ኮሜንታሪ (NIGTC) በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ማብራሪያ ሲያቀርብ፣ “እነዚህ ማጣቀሻዎች የሚያሳዩት በትንቢት ውስጥ ያለውን ጭብጥ እንጂ” ቀድሞ ያልነበረ በኢየሱስ እና በአዲስ ኪዳን ጸሃፊዎች እንደ አዲስ የተፈጠረ ነገርን አይደለም፤ ይላል።
ከርዕሰ ጉዳዩ ጭብጥ በስተጀርባ ስላለው መሰረታዊ ትርጉም ተጨማሪ ግንዛቤን ለማግኘት እንዲረዳን ተመሳሳይ የጥፋት ጽንሰ ሐሳብ የሚስተናገድባቸውን ዘዳ 28፥ 45-68 እና ዳንኤል 12፥ 7 ሁለቱንም ክፍሎች ማስተያየት ይጠቅማል። በተሉይ በሉቃ 21፥ 24 ላይ “የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም” የሚለውን ሐረግ በዘዳ ምዕራፍ 28-33 በኋለኛው ዘመን ጠማማ እና ክፉ በሆነው የእስራኤል ትውልድ ላይ “ፈጽሞ እስኪጠፉ ድረስ” የሚተላለፈውን የፍርድ ውሳኔ (ዘዳ 31፥ 29፤ 32፥ 5፤ 32፥ 20፤ ሐዋ 2፥ 40 እና ፊልጵ 2፥ 15) አስተያዩ። ኢየሱስ “የአሕዛብ ዘመን” ሲል የሚናገረው ሙሴ በዘዳግም ምዕራፍ 31-32 ላይ እንደተነበየው አይሁዶች የሚሸነፉበት፣ የሚገደሉበት፣ የሚባረሩበት እና የሚበተኑበትን ከሮማውያን (ከአሕዛብ) ጋር ስለሚደረገው ጦርነት ነው። ኢየሱስ ይህን በአሕዛብ የሚረገጡበትን ጊዜ ሲተነብይ በዘዳግም 28-33 ላይ የተጻፈውን በግልፅ ያሳሰበ ይመስላል።
በዘዳ 28-33፣ ሙሴ በቃል ኪዳኑ ፍርድ የሚቀበለውን የመጨረሻውን የአይሁድ ትውልድ በትንቢት ሲናገር፣ “እስክትጠፋ ድረስ” ወይም “እስኪያጠፋህ ድረስ” ወይም “እስክትጠፉ ድረስ” የሚለው ሐረግ ያለማቋረጥ ይደጋግማል።” በተለይ የእነዚህን ሐረጎች አጠቃቀም በዘዳ 28፥ 49-52 እንዴት እንደተገለጠ ልብ አድርጉ። በዘዳግም 28-33 ስለ “መረገጥ” ወይም ስለ “ኢየሩሳሌም” ወይም ስለ “ዘመናት” የተነገረ ነገር እንደሌለ ልብ አድእጉ። ነገር ግን አሕዛብ (አረማውያን) በመጨረሻው ዘመን ወደ አገራቸው ዘልቀው ገብተው “እስኪጠፉ ድረስ” እንደሚያጠቁአቸው ይጠቅሳል።
ይህ ዳንኤል በአሕዛብ ስለመረገጥ፣ ስለ ፍጻሜው፣ ስለተቀጠረው ጊዜና “በጊዜው፣ በዘመናቱም፣ በዘመኑም እኩሌታ” ወቅት ስለሚደረገው መፈራረስ ከተናገረው ጋር ተመሳሳይ ነው።
የአሕዛብ ህዝቦች “እስኪያጠፏት ድረስ” ወይም ሙሉ በሙሉ እስኪሰበሩአቸው (ወይም አሕዛብ ያደርጉባቸው ዘንድ የተተነበየላቸውን ሁሉ እስኪፈጽሙ ድረስ፣ ወይም “የአሕዛብ [የማጥፋት] ጊዜ እስኪፈጸም ድረስ”) ኢየሩሳሌምን ይረግጧታል። ይህ የመረገጥ አሳብ አገሮች በሌላ ኃይል ወረራ በሚፈጸምባቸው ወቅት ጥቅም ላይ የሚውል የተለመደ ሀሳብ ነበር። “አትረገጡኝ” ማለት “ሰራዊቶቻችሁን ወደ ድንበሬ አታግቡ” ማለቱ እንደሆነ ይታወቃል። ሙሴ በዘዳ 28፥ 49-53 ሲናገር፣ በምድሪቱ ውስጥ ያሉት የአይሁድ ምሽጎች ሁሉ እስኪፈርሱ ድረስ (እነርሱ በመጀመሪያ ከነዓንን በወረሩበት ወቅት እንዳደረጉት ያለ) ይረግጡአችሁ ዘንድ “ቋንቋቸውን የማታውቁትን” የባዕድ ጭፍሮችን እግዚአብሔር ይጠቀማል፣ ይላቸዋል። የዚህም መጨረሻው ማሳዳ ላይ የሆነው ነበር፤ ይህም የሆነው ከ66-73 ዓ.ም ባለው ጊዜ ነው። ሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተነገረውም በእርግጠኝነት ፍጻሜውን ያገኘው በዚያ ጊዜ ነው።
ዳንኤል. 12፥ 7 ፍፁም የሆነ መሰበርን፣ የተቀጠረውን መጨረሻ ወይም የፍጻሜውን ጊዜ ያመለክታል። ጌታ ኢየሱስም በሉቃስ 21፥ 20 ላይ ሲናገር ትይዩ በሆኑት ምንባባት በማቴዎስ 24 እና በማርቆስ 13 ላይ ባለው የደብረ ዘይት ፍካሬው ዘገባዎቹ እንደተጠቀሰው፣ የዳንኤልን ትንቢት (የጥፋት ርኩሰት) ከዚህ ትንቢታዊ ጥፋት ጋር አያይዞ ይጠቅሳል። ስለዚህ ዳንኤል ይህንን ጥፋት አስመልክቶ የተናገረውን በጥንቃቄ ማየት አለብን። ዳንኤል እንደተናገረው፣ በምዕራፍ 2፥ 44-45 በአራተኛው መንግሥት ዘመን (ሮም) ያኔ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥቱን ያቋቁማል። በዳን 7፥ 19 እና 7፥ 23 ላይ የተነገረውን ይኸውም አራተኛው መንግሥት ወይም አውሬ (ሮም) የብረት ጥርስ እንዳለውና ምድሪቱን ሁሉ እንደሚያደቅቅ ልብ በሉ። ከዚያም በዳንኤል 7፥ 25 ላይ ይህ መረገጥ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል እንደተባለ (ለዘመን፣ ለዘመናት እና ለዘመናት እኩሌታ ጊዜ - ማለትም፣ ለሶስት ዓመት ተኩል) እንደሆነ ጊዜውን አስተውሉ። ይህም ጊዜ አራተኛው አውሬ ምድሪቱን የሚረግጥበት ጊዜ ነው። ከ67-70 ዓ.ም የሆነውም ይኸው ነው። ሮማውያን በቬስፔዥያን መሪነት ከ67 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሁም በቲቶ ፊት አውራሪነት እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ቀጥለው ባደረጉት ከበባ ከገሊላ እስከ ይሁዳ ያለውን መላውን ምድር ሁሉ ረግጠዋል፣ በዚህም ጌታ ኢየሱስ በሉቃስ ወንጌል የተናገረውን ትንቢት እና እዚህ በሉቃስ 21 ላይ የሚጠቅሰውን የዳንኤልን ትንቢት ሁሉ ፍጻሜ ይሰጠዋል።
ዳንኤል ስለ “ፍጻሜው” ሲናገር “የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል” (ዳን 12፥ 7) ይላል። ሙሴም እንዲህ ስላለው ፍጻሜ ሲናገር “ጠማማውና ክፉው የእስራኤል ትውልድ” ብሔራዊ ሕልውናቸው በሚያበቃበት በመጨረሻው ቀን ጠላቶቻቸው ሙሉ በሙሉ እስኪያጠፉአቸው ድረስ እንደሚያጠቁአቸው ተንብዮአል (ዘዳ. 28-33 ተመልከቱ)። ይህም የሙሴ ትንቢት፣ ከአዲስ ኪዳን የፍርድ ትንቢቶች ጋር ያለውን ግንኙነት እና ዘግናኝ ፍጻሜውን ያስነበብኩበትን ጽሁፍ ልትመለከቱ ትችላላችሁ።
“የአሕዛብ ዘመን” ( ሉቃስ 21፥ 24 ) የተሰኘው ጊዜ በዳንኤል 12፥ 7 ላይ ከተጠቀሰው “ፍጹም የመበተን” ሁኔታ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። ጂ.ቢ. ካየርድ በሉቃስ ወንጌል ማብራሪያው ስለዚህ የአህዛብ ዘመን ሲናገር “….እስራኤልን እንዲያስጨንቁ ‘ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኩሌታ’ እግዚአብሔር ለአህዛብ መንግስታት የሰጠውን ሥልጣን ያመለክታል። ይህም ጊዜ የበቀል ጊዜ በመባል ይታወቃል…፤” ይላል። ዳንኤል እንደ ተቀጠረ ጊዜ ገልጾታል። ሮማውያን መጥተው መላውን የእስራኤልን ምድር እና በተለይም ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ሲረግጡ የተፈጸመ ነበር። በ73 ዓ.ም የአይሁድን ምድር “መርገጣቸውን” ጨርሰው የቤተ መቅደሱ መዋቅር ፈርሶ የኢየሩሳሌም ምሽግ ሙሉ በሙሉ ተሰብሮ ፍጻሜውን ያገኘ ትንቢት ነበር።
ክፍሉን በገዛ ራሱ አውድ ስንመለከተው የሚሰጠን ሰዕል ግልጽ ነው፤ ምንም እንኳን ይህ ቆመው እያዩት ያለው ቤተ መቅደስ ታላቅ አካላዊ ውበትና ግርማ ቢኖረውም፣ የሚፈርስበት እና የሚተውበት ጊዜ ግን እየመጣ ነበር (ቁ.5-6)። ይህ መቼ እንደሆነ ማንም አያውቅም፣ ዳሩ ግን ይከሰታሉ የተባሉ በርካታ ምልክቶች ይቀድሙት ነበር። አስቀድሞ ጦርነቶች ይኖራሉ፣ ያኔም ኢየሩሳሌም ትጠፋለች "በአሕዛብም ትረገጣለች" ህዝቦቿም "ወደ አሕዛብ ሁሉ ይማረካሉ" (ቁ.24)። የመረገጡም ጊዜ ቆይታው የተወሰነው “የአህዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ” (ቁ.24) የሚረዝም ነው። ቀጥሎም በዳንኤል መጽሐፍ በትንቢት እንደተነገረው ከዚህ ሁሉ በኋላ የሰው ልጅ "በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና" ይመለሳል (ቁ.27)። እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች” (ቁ.31) ማለት ነው። “ይህም ሁሉ እስኪሆን” ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም (ቁ.32) የሚለውም የተፈጻሚነቱን እርግጠኝነትና የተያዘለትን ቀነ ቀጠሮ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ይህም ፍጻሜ ሮም እስራኤልን ድል በማድረጓም የተጠናቀቀ ነበር። ያኔም እስራኤል “ሙሉ በሙሉ ተሰበረች። ስለዚህ፣ ይህ የአሕዛብ መርገጥ እና ጊዜው እንደ ዳንኤል ያሉ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ይህን ፍፁም የመፍረስ፣ የመበተን እና የፍርድ ጊዜ በእስራኤል ላይ እንደሚመጣ የተነበዩትን የሚያመለክት ነው።
እጄ ላይ የሚገኙትን በርካታ ሶፍት ኮፒና ሀርድ ኮፒ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎች አገላብጬ በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ያለውን “የአሕዛብ ዘመን” የሚለውን ሃረግ እንዲተረጉሙልኝ ባማክራቸውና እንዴት እንደሚተረጉሙት ብፈትሽ ሁሉም በሚባል ደረጃ ሮሜ. 11፥ 25፤ ላይ ካለው “የአሕዛብ ሙላት” ከሚለው ሃረግ ጋር አጣምሮ የማየትና ተፈጻሚነታቸውንም ገና ወደፊት ባሉ ትውልዶችና ዘመናት የመጠበቅ ነገር አለባቸው። ይህ ግን ፈጽሞ ቃላቶቹ የተነገሩበትን መሰረታዊ አውድ ከማሳከር የመጣ ችግር ነው። ኤሊኮት፣ ቤንሰን፣ ቤንገል፣ ጄምሰን ፋውሴት ወዘተ ይህንኑ ያንጸባርቃሉ።
ዳሩ ግን ሉቃስ 21፥ 24 እና ሮሜ 11፥ 25፤ እነዚህ ሁለት ምንባባት የሚያወሩት (1) የአሕዛብ ዘመን (66-70 ዓ.ም.) እና (2) የአሕዛብ ሙላት (30-64 ዓ.ም.) የተሰኙ ሁለት የተለያዩ አሳቦችን ነው። ሉቃ 21፥ 24 እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በአሕዛብ እጅ የሚፈጽመውን የፍርድ አውድ ሲሆን ሮሜ. 11፥ 25 ግን እግዚአብሔር ለአህዛብ ያቀደውን የድነት አውድ ነው።
ጆን ኤል ብሬይም እነዚህ ሁለት ጥቅሶች የሚናገሩት ስለ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች እንደሆነ ይስማማሉ፡- “አንደኛው የሚናገረው አሕዛብ ኢየሩሳሌምን ስለሚቆጣጠሩበት ጊዜ ነው። ሌላኛው ደግሞ እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ሁኔታ ለአሕዛብ የሚያደርገውን መግቦት እና ፍጻሜውን ነው። እነዚህ በአጠቃላይ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው." ይብላሉ።
“የአሕዛብ ዘመን” የተባለው (ማለትም እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ላይ ለመፍረድ የአሕዛብን ሠራዊት አምጥቶ የተጠቀመበት ጊዜ ነው) እርሱም በ70 ዓ.ም. ፍጻሜውን አግኝቷል። “የአሕዛብ ሙላት” ወይም የአሕዛብ ቁጥር ሲሞላ የተባለው (ማለትም፣ የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀን ከመዘጋቱ በፊት ወደ ክርስትና ስለሚጨመሩ አህዛብ የተነገረ ነው) ይኸውም ፓሮውዥያው በ66 ዓ.ም ከመጀመሩ በፊት በእግዚአብሔር ምርጫ እና ታሪካዊ እውነታ ተፈጽሟል።
“የአሕዛብ ሙላት” (ሮሜ 11፥ 25) አሕዛብ ሙሉ በሙሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ (ከአይሁዶች ጋር እኩል እንደሆኑ ተደርገው ተቀባይነትን ስያገኙ) ማለት ነበር። አይሁድም አሕዛብም በክርስቶስ አንድ አካል እንዲሆኑ ጳውሎስ የአሕዛብን ውህደት ለመፈጸም በብዙ ደክሟል (በኤፌሶን 4 ያለውን ትምህርቱን ልብ ይሏል)። በቆላስይስ እና በሮሜ መልእክቶች ውስጥ አንስቶ በተናገረው ሐሳብ መሠረት ከአይሁድ ወገን ክርስቲያኖች የሆኑት ከአሕዛብ ወገን ክርስቲኖች የሆኑትን አማኞች ሊመጣ ያለው መንግሥት ተባባሪና ወራሾች አድርገው እንዲቀበሏቸው የማድረጉን ሥራ በእርግጥም ያከናወነ ይመስላል። አህዛብ ከሆኑ ባልንጀሮቹ ጋር መስዋዕትን ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገው ጉዞ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሕዛብን እንደ ወንድሞች እንዲቀበሏቸው መንገዱን እንዲያመቻች ረድቷቸዋል። ለአብያተ ክርስቲያናት የጻፋቸው መልእክቶቹም፣ አህዛብ በመንግሥቱ ውስጥ መካተታቸውን ደግፈው አጥብቀው የሚከራከሩ ነበሩ፣ በመጨረሻም ቅዱስ ጴጥሮስ ኔሮ ባቀጣጠለው ታላቅ ስደት ሰማእት ሆኖ ከመሞቱ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ (በ64 ዓ.ም. መጨረሻ) እነዚያ የቅዱስ ጳውሎስ መለዕክቶች በሐዋርያው ጴጥሮስ ቀኖና የተደረጉ ናቸው (2ጴጥ. 3፥ 15-16) የአሕዛብ ሙላትም ኢየሩሳሌም ፈጽማ ከመውደሟ በፊት ቀደም ብሎ ያኔ የመጣ ይመስላል።
ስለዚህ፣ በሮሜ. 11፥ 25 ላይ ስለ “የአሕዛብ ሙላት” የሚያወራው ከ30-70 ዓ.ም ባለው የሽግግር ወቅት ስለ አህዛብ ወደ ቤተክርስቲያን መቀላቀል ነው። ይህም የአሕዛብ ሙላት የተጠናቀቀው በ64 ዓ.ም (ከጦርነቱ በፊት) ነው። መንግሥቱ ከነዚህ አመጸኞችና የማያምኑ ከሆኑ አይሁድ ተወስዶ ያመኑ የአይሁድ ጻድቃን ቅሬታዎች ለተካተቱበት ስብስብ እና ለሚያምኑ አሕዛብ ተሰጠ።
ያ ሂደት በይፋ የጀመረውም ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ክርስትና በመመለሱ ነው፣ ቀስ በቀስም እየገፋና እያደገ ሄዶ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሁሉም ሐዋርያት ወንጌልን በአህዛብ ዘንድ እንዲሰብክ ቀኝ እጃቸውን በሰጡት ጊዜ የመገረዝን ስርዓትና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ሳያስገድዷቸው ወደ ቤተክርስቲያን እንዲቀላቀሉ ወስነዋል። ይህን የአይሁድና የአህዛብን አንድነት ያነሳሳውና ያቀጣጠለው ሐዋርያው ጳውሎስ ያደረጋቸው ተከታታይ ሚስዮናዊ ጉዞዎቹ ነበሩ። ያኔም መንግሥቱ ከማይታዘዙትና ከማያምኑ አይሁድ ከመወሰዱ በፊት በአህዛብ ሁሉ ዘንድ (በሮማውያን ግዛት) ተበትነው የነበሩ ሁሉም ዲያስፖራ አይሁድ አማኞች ወደ መንግሥቱ ሙላት መምጣት ነበረባቸው። ያኔም መንግሥቱ ከማይታዘዙትና ከማያምኑት አይሁድ ተወስዶ ፍሬ ለሚያፈራ አዲስ ሕዝብ ተሰጥቷል፤ ይህም አዲስ ሕዝብ ከሁለቱ ወገን ጻድቃን የአይሁድ ቅሬታዎችንና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ አማኞችን ያቀፈ ነበር።
ማጠቃለያ
አንድ ሰው በአህዛብ መርገጡ መቼ ተጀምሮ መቼ የሚያበቃ ነው ብሎ አግባብነት ያለውን ጥያቄ ሊጠይቅ ይችላል። በእርግጥም ረገጣው እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ያልጀመረ ከሆነ በእርግጥም መጻኢያን በሚያቀርቡት የክርክር ጭብጥ ጠንካራ መከራከሪያ ይኖራቸዋል። ነገር ግን እዚህ ላይ በዝርዝር የተመለከትናቸው የቃሉ ማስረጃዎች የሚያሳዩት ረገጣው የተፈፀመው ከ66-70 ዓ.ም መካከል ባለው በዚያ የበቀል እና የቁጣ ዘመን ላይ ነው።
ሚልተን ኤስ. ቴሪ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የስነ ፍታቴ መጽሐፋቸው ውስጥ ይህንው ጉዳይ በጥሩ ሁኔታ ጠቅለል አድርገው አቅርበውታል፦ በሉቃስ 21፥ 4 ላይ “የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች” የሚለው ንግግር በዚያ ትውልድ ውስጥ ያልተከሰቱ ክስተቶችን ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል። "የአህዛብ ጊዜ" (kairoi eqnwn) በወንጌል ስር ለአሕዛብ የተሰጣቸው የጸጋ ጊዜያት እና አጋጣሚዎች እንደሆኑ በብዙዎች ይታሰባል። ነገር ግን ቫን ኦስተርዚ እንደተመለከተው ቃላቱን በዚህ መልኩ መረዳት አንድን ሀሳብ ለዐውደ-ምንባቡ ባዕድ ከሆነ እሳቤ ጋር መቀየጥ ይሆናል። ቤንገልም ሲያስረዳ “የአሕዛብ ዘመን የተባለው ከተማይቱን ለጥፋት እንዲረግጡ የተመደበላቸውን ጊዜ ነው” ይላል። ነገር ግን በምንባቡ ወይም በዐውደ-ምንባቡ ውስጥ “አሕዛብ ወደ ክርስትና የሚለወጡበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን አግኝቶ በዚህ ዘመን ላይ ያበቃል” ወይም በሮማውያን፣ በፋርሳውያን፣ በሳራሴንሶች፣ በፍራንኮች እና በቱርኮች ለሺህዎች አመታት መረገጣቸውን የሚያስረዳ ምንም ነገር የለውም። ይህ ካይሮስ በግልጽ የሚያመለክተው በኢየሩሳሌም ላይ የሚሆነውን የፍርድ ጊዜ ነው እንጂ ለአሕዛብ የተሰጠውን የመዳን ጊዜ አይደለም። ከዚህ ምንባብ ጋር ግልጽ የሆነ ተመሳሳይነትና በእጅጉ ተፈጥሯዊ ስምምነት ያለው በራእይ 11፥ 2 ላይ የተጻፈው ሲሆን “በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቷል” የተባለበት፣ በእነሱም ቅድስቲቱ ከተማ ለአርባ ሁለት ወር መረገጧ ከዚህ ጊዜ ጋር የሚስተያይና የሚመጣጠን ነው። ይህም ለአርባ ሁለት ወር በዮሐንስ ራዕይ 12፥ 14 እና በዳንኤል 7፥ 25፤ 12፥ 7 “አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ” ከሚለው ጋር እኩያ ነው። ይህም የፍርድ ጊዜ ምልክት ነው፣ ነገር ግን ዘመናትን እና ትውልዶችን አያመለክትም። ይኸውም ሦስት አመት ተኩል ነው - እርሱም ለሁለት የተከፈለ አንድ አጭር ሰባት ሄኖ፣ ነገር ግን የወዮ ጊዜን አመልካች ኑው። ስለዚህ “የአሕዛብ ዘመን” ማለት የአሕዛብ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን የከበቡበትና አስጨንቀው የረገጡበት የሦስት አመት ተኩል ጊዜ ነው።
በሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተገለጹት እነዚህ “መረገጥ” እና “የአሕዛብ ዘመን” የተሰኙት ጉዳዮች የሚያመለክቱት ማለትም ለሦስት ወይም ለአራት ዓመታት ያህል የሚቆይ በጣም አጭር ጊዜን እንደሆነ ጠቅሰን ካየናቸው ከእነዚህ ሁሉ ቀኖናዊ ከሆኑና ቀኖናዊ ካልሆኑ ጽሑፎች በግልጽ መረዳት ይቻላል። የአህዛብ ጦር መላውን የፓለስታይን ምድር ይረግጣል፣ ምሽጎቿን ሁሉ ያወድማል፣ የአይሁድ ህዝብንም ሙሉ በሙሉ አፍርሶ ይበትናል። “የአህዛብ ዘመን” ቆይታው ለብዙ መቶ ዘመናት እንደሆነ ወይም ለሺህ ዓመታት አልያም ላልተወሰነ የጥፋት ጊዜ የሚዘልቅ እንደሆነ የሚገልጽ ምንም ዓይነት ምንባብ ከቅዱስ ቃሉ አናገኝም። “የአህዛብ ዘመን” ከ“መረገጥ” ዘመን ጋር ተመሳሳይ የሆነ የጊዜ ርዝመት ያለው ሲሆን “መረገጡ” ያለፈ ጊዜ (“መርገጥ”፣ “የተረገጠ” ወዘተ) ብቻ የሚያመለክት መሆኑን በተለያዩ ምንባባት ላይ አስተውለናል። ይኸውም በሽንፈት ወደተጠናቀቀው ጦርነት የሚያመለክት ነው እንጂ ከዚያ በኋላ ለመጣውና ዘመናት ላስቆጠረው የጥፋት ጊዜ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህም በኋላ እንዲህ ያለ ነገር የለም። በመካከለኛው ምሥራቅ የሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ፖለቲካዊትና ዘመናዊት እስራኤል ላይ እያፈጠጡ ግጭት ኮሽ ባለ ቁጥር የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል እየመዠረጡ በተሰማው ኮሽታና በሚታዩ ነገሮች ተመርቶ ለመተርጎም የሚደረግ ጥረት ሁሉ ለአዲስ ኪዳን ክርስትና ባዕድ እምነት ጎጂ ባህል ነው።
ከሉቃስ 21፥ 24 ጋር በተያያዘ እያነሳን ከመረመርናቸው ከእነዚህ ሁሉ ጥቅሶች አንጻር ያየነው እንደሆነ፣ መጻኢያን የሚያቀርቡት የተራዘመ የጊዜ ቆይታም ሆነ ያልተገደበ የአሕዛብ ረገጣ ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመ ነው የሚለው መከራከሪያ በምንም በማስረጃ የተደገፈ አይመስልም። የሉቃስ ወንጌል አንባቢዎችም እነዚህ ቃላት በብሉይ ኪዳን የሚገኙ እነዚህን ፅንሰ-ሀሳቦች እና ጭብጦች፣ የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን፣ በተለይም የነብዩ የዳንኤል መጽሐፍ፣ እርሱም መፈፀም ስላለበት ስለተቀጠረው የፍጻሜ ጊዜ እንደሚናገር በእርግጠኝነት በሚገባ ተረድተዋቸዋል። በሉቃስ 21 ዐውደ-ምንባብ ውስጥ የተጠቀሱት ሁሉም ምልክቶች ይህንን በአሕዛብ የመረገጥ ጊዜን ጨምሮ ይህንን በሰሙ በደቀ መዛሙርቱ የሕይወት ዘመን እና በትውልዳቸው ውስጥ የሚፈጸም ነገር መሆኑን ጄ. ኤስ ራስል በሚገባ አስተውሎ የሚከተለውን ብሏል፡-
እዚህ ላይ ትንቢቱ እና ምሳሌው የሚወክሉት አንድ አይነት ትዕይንትንና፣ ተመሳሳይ ጊዜን ነው፡- ይኸውም ስለ ግዑዝ ዓለም ፍጻሜ ወይም ስለ ቁሳዊው አጽናፈ ዓለም ውድመት የሚናገሩ ሳይሆኑ ይልቁንም ስለ አዮን ወይም ስለ ዘመን መቃረብ ይናገራሉ፤ በተመሳሳይ መልኩ ስለዚያ ታላቁ የፍርድ ዘመን ያመለክታሉ። ቅዱስ ሉቃስ የደብረ ዘይት ተራራን ፍካሬ በዘገብበት የትንቢት ቃል ላይ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።” (ሉቃስ 21፥ 28) ሲል ጉዳዩ እንዴት በደቀ መዛሙርቱ የሕይወት ዘመን ውስጥ የሚደርስ ታላቅ ጥፋት እንደሆነ በግልጽ እንዳመለከተ አስተውሉ። ይህ ቃል የተነገረው ንግግሩን ይሰሙ ለነበሩ ደቀ መዛሙርት አይደለምን? ይሆናሉ የተባሉትስ ጉዳዮች እነርሱን የሚመለከቱና ከእነርሱ ጋር የተዛመዱ ጉዳዮች አልነበሩምን? የኢየሱስን ቃል ጓግቶ እየጠጣ ላለ እዚያ ለቆመ አንድ ቡድን የተነገሩ ቃላት እንጂ፣ ከዚያ ቡድን ትውልድ በኋላ በሺዎች በሚቆጠሩ ሩቅ ዓመታት ለሚታሰብ ለሌላ ታዳሚ ወገን የተነገሩ ናቸው ብሎ ለመጠርጠር የሚያስችል አንዳች የንባብ ቦታ ይኖር ይሆንን? እንዲህ ዓይነቱ መሰረት አልባ መላምት ራሱን ውድቅ ለማድረግ በእርግጠኝነት የገዛ ራሱን ማስተባበያ ይሸከማል።
እዚህ ላይ የተጠቀሰው የአህዛብ ዘመን በሉቃስ 21፥ 24 ውስጥ የሚያመለክተው ለሦስት ዓመት ተኩል የቆየውን በአህዛብ የመረገጥን ሂደት ብቻ ነው። በተጨባጭ ሁኔታ አሕዛብ ምድሪቱን ለዘመን፣ ለዘመናት እና ለዘመን እኩሌታ (በዳንኤል የተናገረውን የዘመን ቀመር ይመለከቷል) ይረግጣሉ፣ በዚህም ጊዜ በነብዩ ዳንኤል የተተነበዩትን ጥፋቶች ሁሉ ይፈጽማሉ እያለን ነው። በዳንኤል የተጠቀሰው አሕዛብ ምድሪቱን የሚረግጡበት ጊዜም የሚፈጸመው በእነዚህ አምስት ቁጥሮች (ሉቃስ 21፥ 20-24) ውስጥ የተገለጹት ጉዳዮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ ሲፈጸሙ (በተለይም ኢየሩሳሌም ራሷ በመጨረሻ ስትጠፋ)፣ የሮም የአህዛብ ሰራዊት ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ሲያፈርሱ፣ ነው። ያኔም ዘመናቸው ይኸውም ምድሪቱን የረገጡበት (የሦስት ዓመት ተኩል) ጊዜአቸው ያበቃል። አሕዛብ እንዲያደርጉ የተነበየላቸውን ሁሉ እስኪፈጽሙ ድረስ ምድሪቱን ረግጠው ይቆያሉ፣ ይህም ለሦስት ዓመት ተኩል ብቻ ነው። በነዚህም አመታት በነቢያቱ የተነገሩትን መቅሰፍቶችና ጥፋቶች ሳያደርጉ አንድም ነገር አልተዉም። የተወሰነው የጥፋት ጊዜ ተሟጥጦ እስኪያበቃ ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈጽሟል። ስለ መጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የማቴዎስ 24 ንግግር ፍጻሜዎች እንዲሁም በማርቆስ 13፣ በሉቃስ 17 እና በሉቃስ 21 ላይ ስላለው ተመሳሳይነት የበለጠ ለማጥናት ፍላጎቱ ካላችሁ አበክሬ የምመክረው አንዳንድ ግብዓቶችን እንድትመለከት ነው፣ ሁሉም በIPA ድህረ ገጽ ላይ በስፋትና በዝርዝር ይገኛሉ።
ግዛቸው
No comments:
Post a Comment