Wednesday, January 12, 2022

ስለ ሰይጣን አንዳንድ ጉዳዮች

ስለ ሰይጣን አንዳንድ ጉዳዮች


መግቢያ፦ አስተማሪው ተማሪዎቹን ስለ እግዚአብሔር እና ስለሰይጣን አምስት አምስት ገጽ ጽሁፍ ይዛችሁ እንድትቀርቡ ባለው መሰረት፣ ብዙዎቹ የታዘዙትን አቀረቡ። ከተማሪዎቹ አንዱ ግን ዘጠኙንም ገጽ ስለእግዚአብሔር ጽፎ መጨረስ ሲያቅተው በቀረችው አንድ ገጽ ላይ "ለሰይጣን ጊዜ የለኝም" ብሎ እንደመለሰው እናንተም አንባቢዎቼ ለሰይጣን ጊዜ የለኝም እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በመሰረቱ ወንጌልን የመስበክ እንጂ ሰይጣንን የማስተዋወቅ ጥሪ የለኝም፣ ክርስቶስን ለማወቅ በተጋንና እርሱን ለመምሰል በተጋደልን መጠን ግን ሰይጣንን እና አሰራሩን ገልበን እናውቀዋለን። እንግዲህ ሴጣን ሳይቆጠር ከጥራዞችና ከባህር ማዶ ኑሮ ጋር እየታገልሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተይዤ ያቀረብኩትን ጽሁፍ በእግዚአብሔር ብርሃን እየመረመራችሁ ብትማሩበትም ብትባረኩበትም ደስታዬ ወደር የለውም።


ሰይጣን ሲሰየጥን፣


ከሁሉ በፊት ሰይጣን ፍጡር ነው፣ ለዚያውም በአንድ ጊዜ አንድ ስፍራ ላይ ብቻ መገኘት የሚችል ውሱን ፍጡር ነው።  በሌላም በኩል ለምሳሌ ጻድቁን ኢዮብን ከመፈተኑ አስቀድሞ እንኳ የእግዚአብሔርን ፈቃደኝነት የግድ ማግኘት የነረበት መሆኑን በኢዮብ ምዕራፍ 1 ውስጥ እንማራለን። እግዚአብሔር እንደወደደ ወዲያና ወዲህ ፈቃዱን እየጠመዘዘ ያንቀሳቅሰዋል እንጂ በራሱ ምንም የማድረግ ሥልጣን የለውም። እንደገናም በአዲስ ኪዳን እንዲህ ያለውን ተመሳሳይ ውሱንነት ሐዋርያው ጴጥሮስን ለመፈተን እንዲፈቀድለት ሲለምን (ሉቃስ 22፥ 31) ባለው ሁኔታ እናያለን። 


የቀደመው እባብ


ዘፍጥረት 3፥ 1 ላይ "እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ።" የሚል ቃል እናነባለን። ከዚህም ገና ከመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ እባብ ፍጡር እንደሆነ እንመለከታለን። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍም ደግሞ ሌላ የእርሱን ስያሜዎች ይነግረናል። ራእይ 12፥ 9 ላይ "ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።" የሚል እናነባለን። እንግዲህ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመርያው መጽሐፍ አንስቶ እስከመጨረሻው መጽሐፍ ድረስ ሰይጣን ለእግዚአብሔር እና ለሰው ጠላት እንደሆነ ግልጽ ነው። እንደ ዮሐንስ 8፥ 44 ትምህርት ዲያብሎስ ኃሰተኛና ነፍሰ ገዳይ ነው። ደግሞም አታላይ፣ ፈታኝ እና ርኩስ ነው። ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ የሚመጣ ሌባው ተብሎም ተገልጧል (ዮሐንስ 10፥ 10))። ከሌሎች ሁሉ ይልቅ እርኩስና ክፉ መልአክ ነው። ዲያብሎስና አፖልዮን (አጥፊ) ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚታወቁ በርካታ ሌሎች ባህርዩን የሚገልጡ ስያሜዎች አሉት፣ እባብ ተብሎ እንደተጠራ ሁሉ የሚውጠውን ፈልጎ የሚያገሳ አንበሳ፣ ዘንዶው ተብሎም ተጠርቷል (ራእይ 12፥ 9፤ 20፥ 2፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፥ 8)። 


በእግረ መንገድ የአዳም አሟሟት፤ ዘፍጥረት 2፥ 16-17 "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።" ይላል እዚህ ላይ አዳም የተከለከለውን ዛፍ ፍሬ በላ፣ ነገር ግን እንደ ዘፍጥረት 5፥ 5 ከሆነ አዳም ፍሬዋን ከበላና ከእግዚአብሔር ገነት ከወጣ በኋላ በምድር ላይ የኖረው አጠቃላይ እድሜ 930 አመታትን ነው፣ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? 


ከቅዱሳት መጻህፍት እንደምናውቀው አዳም በዚያች ፍሬዋን በበላባት ቀን አካላዊውን ሞት አልሞተም። አዳም ያንን የተከለከለ ዛፍ ፍሬ ፈጽሞ ባይበላም እንኳ አካላዊውን የሥጋ ሞት ይሞት እንደ ነበር ታያላችሁ? አዎ መሞቱ አይቀርም ነበር፤ የተቀየረው ግን የአሟሟቱ ሁኔታ ነበር። አካላዊውን ሞት በሥጋው እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ በገነት ውስጥ በእግዚአብሔር ሀልዎት ፊት ከመሆን ይልቅ፣ አዳም አካላዊውን የሥጋ ምት እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ ከእግዚአብሔር ሀልዎት የተነጠለ ሆኖ ኖረ። ከእግዚአብሔር ጋር ሆኖ በሚሞትበት ጊዜ ወደ ሕይወት ከመድረስ ይልቅ ያለእግዚአብሔር በመሞት የከፋውን ጥፋት መንፈሳዊውን ሞት ሞተ። የአዳም ኃጢአት የመንፈሳዊው ሞት ሰበብ ነው። አዳም ሲፈጠር ያለኃጢአት ወይም ያለ ሞት ነበር ማለት በህይወት ከእግዚአብሔር ጋር በሞትም ከእግዚአብሔር ጋር ነበር ማለት ነው። ለአዳም ሕይወቱ እግዚአብሔር ነው እንጂ በምድር ላይ መኖሩ አይደለም፤ አዳም እግዚአብሔርን ባጣበት ቀን ሞተ። ከዚያ በኋላ በምድር ላይ የኖረው ኑሮ ሞቶ የኖረውና ሞቶ የሞተው ሞት ነው። ይህም ማለት አዳም ኃጢአትን ሲያደርግ ወይም ሲሞት በሕይወት ያለእግዚአብሔር በሞትም ያለእግዚአብሔር ሆነ ማለት ነው። ለአዳም በሕይወት መኖር ማለት ሳይሞቱ መኖር ማለት ሳይሆን በሕይወትም ሆነ በሞት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ማለት ነውና። አዳም እግዚአብሔርን በማጣት ከእግዚአብሔር ጋር መኖርንና መሞትን አጣ፣ ስለዚህም አዳም ከ930 አመታት እድሜ በኋላ ያለእግዚአብሔር ኖሮ ያለእግዚአብሔር ሊሞት በዚያች የቀን ጎደሎ በሆነች አሳዛኝ ቀን አሰቃቂውን መንፈሳዊ ሞት ሞተ። "ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ" (1ቆሮ 15፥ 22) እንደተባለ አዳም ያወረሰን ያለእግዚአብሔር ኖሮ ያለእግዚአብሔር መሞትን ነው። እንደ ኤፌሶን 2፥ 1 ከሆነ ሙታንነት የበደለኝነትና የኃጢአተኝነት ውጤት ነው፣ አለመታዘዝ ይኸውም የአዳም አለመታዘዝ የእኛም የልጆቹ አለመታዘዝ ሲሆን (ሮሜ 5፥ 19)፣ አኗኗራችንን እና አሟሟታችንን "በማይታዘዙ ልጆች ላይ ለሚሰራው መንፈስ አለቃ በአየር ላይም ሥልጣን ላለው አለቃ ፈቃድ" አድርጎታል።


የሰይጣን መቀጥቀጥ


በእባቡ ላይ የተነገረውን የመቀጥቀጥ ፍርድ በዘፍጥረት 3፥ 15 ላይ ሲናገር "በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።" የሚል ተስፋ እናነባለን። የሰይጣን መቀጥቀጥ፣ ይህ የሆነው መቼ ነበር? በአዲስ ኪዳን ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በሞቱና በትንሳኤው ሰይጣንን ድል ነስቶት የነበረው ኢየሱስም "የአዳም ልጅ፣ የእግዚአብሔር ልጅ" (ሉቃስ 3፥ 38) "ኋለኛውኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ" ተብሎ ተጠርቷል። ቅዱሱ መጽሐፍ ይህንን ይደግፋልን? አዎ! አሜን ነው! 


ጌታ ኢየሱስ ከመስቀል ሞቱ አስቀድሞ ሲናገር፣ "የዚህ ዓለም (ዘመን) ፍርድ ደርሷል፣ አሁን የዚህ ዓለም (ዘመን) ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፣ /ወይም  ይፈረድበታል/" ማለቱን አስታውሱ (ዮሐንስ 12፥ 31 ፤ 16፥ 11)፤ ይኸውም ተሸንፏል፣ አልቆለታል ማለት ነው።  እንደ አዲስ ኪዳን ትምህርት፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቱ እና ከሙታን ተለይቶ በመነሳቱ ይህንን ታላቅ የድል ተስፋ ለአማኞች ያጎናጸፈን መሆኑ እሙን ነው፤ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው ደግሞ ያንን ታላቅ ድል በመጨረሻው መደምደሚያና በፍጻሜው ከፍታ ላይ ሙላት ሰጥቶ እና ገልጦ አቀዳጅቶናል። ድሉም ያለ ዳግመኛ ምጽዓቱ ሙላትና ፍጻሜ እንደማይኖረው ግልጽ ነው። ከአሮጌው የብሉይ ኪዳን ዘመን ወደ አዲሱ የቃል ኪዳን ዘመን የተደረገው ያ የመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን የሽግግር ጊዜ፣ ልክ እንደ ጥንታዊቲቱ እስራኤል የ40 ዓመቱ የምድረ በዳው ጉዞ አይነት፣ ከመስቀል አንስቶ የዳግመኛ ምጽዓቱ ፓሮውዥያ እስከሆነበት 70 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የሽግግር ጊዜ ይሸፍናል (ዕብራውያን 8፥ 13 ፤ 9፥ 8)። የብሉይ ኪዳን እስራኤል በፋሲካው ደም ከግብጽ ባርነት አርነት ወጥቶ ከ40 አመታት የምድረ በዳ ጉዞ በኋላ የተስፋይቱን ምድር እንደወረሰ፤ እንዲሁ በመስቀል ላይ በታረደው በግ ደም ቤዛነቱን ያገኘው የአዲሱ ኪዳን ቅዱስ ህዝብ ከበአለ ሃምሳ ጀምሮ በሚቆጠር ከሌላ የ40 አመታት የስደትና የመከራ ጉዞ በኋላ በዳግመኛ ምጽአቱ የተስፋ ቃሉን ፍጻሜና ሙላት ለማግኘት እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ጌታን እየጠበቀ በመከራ መታገስ ነበረበት። 


ሐዋርያው ጳውሎስም በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፥ 4 "የዚህ አለም /ዘመን/ አምላክ" ስለሆነው "አይን አሳዋሪ" ይናገራል፣ እዚህም ላይ "ይህ አለም" የተባለው ዘመኑን ማለት እንጂ ተዳሳሹን ግዑዝ አለም ማለት እንዳልሆነ ልብ አድርጉ። በ“ዘመን” መጨረሻ፣ ይኸውም በማቴዎስ 24፥ 3 በተጠቀሰው በብሉይ ኪዳን ዘመን ማብቂያ፣ ሰይጣን ከገዥነቱ ስልጣን ወርዶ፣ ሉተር እንደሚያስተምረው፣ ያኔ ገና የተሸነፈ ጠላት ሆኗል፡፡  እንደ እግዚአብሔር ፕሮግራም ከላይ ሆኖ በአየሩ ላይ ይገዛ የነበረው አለቃ እርሱ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ከሚገዛበት ከሰማይ (ኤፌሶን 2፥ 2)፣ ከገዥነቱ ሥልጣንና ከከፍታው "እንደ መብረቅ" መውደቅ ነበረበት (ሉቃስ 10፥ 18) የአወዳደቁ ሁኔታ ግን  ያኔ በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ሂደቱ ገና ጅምር ነበር፣ በዳግመኛ ምጽአቱም ፈጽሞ ተሸንፎ ከኢየሱስ እግሮች በታች መቀጥቀጥ እና መገዛትም ይገባው ነበርና (ሮሜ 16፥ 20 - ዘፍጥረት 15፥ 15 ፤ ራእይ 2፥ 26፣ 27 ተመልከት)፣ እግሮች የተባሉትም የአካሉ ክፍል የሆኑት ሁሉ ናቸው፡፡ 


ዲያብሎስና ክፋት ተወግዷል


ጌታ ኢየሱስ ስለፓሮውዥያው ሲናገር "የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥" ማርቆስ 13 ፥40 ብሏል። ታዲያ ሰይጣን የታሰረ ከሆነና በእሳት ባህር ውስጥ ከተጣለ፣ ገና አሁንም እኩይ ሁሉ፣ ኃጢአትና ክፋት በዚህች ምድር ላይ የሚኖረው ለምንድን ነው? ሲሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ። ይህም ጥያቄአቸው በተለይ ትንቢት ሁሉ ተፈጽሞአል ብለን አቋም ለያዝንና በተፈጸመ ወንጌል ለምናምን ሰዎች የማያፈናፍን አፋጣጭ ተግዳሮት እንደሚሆንብን ይመስላቸዋል። እውነታው ግን እርሱ አይደለም። ለተዳሳሹና ለቁሳዊው በእጅጉ በተጋለጠውና "ሊተራሊስት" በሆነው በዘመናዊው ክርስትና ዘንድ በስፋት ታዋቂ የሆነው አስተሳሰብ ሰይጣን አንድ ጊዜ ከተፈረደበት፣ እንዱሁም ስለ ዓለም ፍፃሜ የሚናገሩ ትንቢቶች በሙሉ ፍጻሜአቸውን ካገኙ በኋላ፣ ታላቁና ቀንደኛው ፈታኝ የክፋት ኃይል ፈጽሞ የማይኖር በመሆኑ ምንም ዓይነት ክፋትና ኃጢአት በዓለም ላይ አይኖርም የሚል ነው። ይህ ነው የተለመደው አስተሳሰብና የብዙዎች እምነት።


ከባልንጀሮቼ አንዱ በአንድ ወቅት አብረን በተቀመጥንበት የካፌ በረንዳ ንፋስ ያስነሳው የመንገድ ላይ አቧራ ድንገት በላያችን ላይ ቢሞጀር፤ የተበሳጨው ጓደኛዬ ወደ እኔ ዘወር ብሎ፣ "ትንቢት ሁሉ ተፈጽሞአል፣ ጌታም መጥቶአል፣ ሰይጣንም ተፈርዶበታል፣ እኛ ክርስቲያኖችም አሁን ያለነው በአዲሱ ሰማይና ምድር ባዲሲቱ ኢየሩሳሌም ነው የምትለው ይሄ ትምህርትህ አሁን የምንጠጣውን ይህን አቧራ እንዴት ያየዋል?" ሲል እየቀለደ እንደጠየቀኝ አስታውሳለሁ። "የጌታ ምጽአት ንፋስ የሚያነሳውን የምድርን አቧራ እንደሚያስቀር ከቅዱስ ቃሉ ማንበቤን አላስታውስም፤ አልተጻፈማ"፤ ስል እኔም መልሼለታለሁ። 


በዚህ ተዳሳሽ አለም ክፋትና ክፉ ፍጻሜውን አግኝቶ ሁሉ መልካም ሆኖ ካላየን፣ እሳዳጅና ተሳዳጅ፣ ገዳይና ሟች፣ አጥፊና ጠፊ የሌለበት፣ እኩይ አልባ የሰላም አለም ተቋቁሞ ካላየን አናምንም የሚሉኝ፣ በማየት የሚያምኑ እጅግም ከማከብራቸው መካከል የዋሃን ሞልተዋል። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይቶ መንፈስ በሚናገረው ቃል ያንን መተርጎምና መረዳት ግን የምንኖርበት መንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰጥ "መሰረተ ትምህርት" ነው። አለዚያ ዱባና ቅል ለየቅል ሆነን ሳንመረቅ እንቀራለን። በግሌ እንደ ፕሪንተሪስቶች ሁሉ የመጨረሻው ዘመን ትንቢቶች በሙሉ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ተፈፅመዋል ብዬ አምናለሁ፤ ነገር ግን አሁንም ድረስ ከአዲሱ ሰማይና ምድር በቀር፣ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ቅድስት ሆና ለባልዋ እንደተሸለመችም ሙሽራ ሆና ከወረደችው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በቀር፣ ከመንግስቱ በቀር፣ ኃጢአት ከመንግስቱ ውጭ ተብሎ በተጠራው በዚህ ተዳሳሽ አለም በምድር ላይ አሁንም አለ፤ ይኖራልም ብዬ ደግሞ አምናለሁ። "ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።" (ራእይ 22፥ 15)።


ክርስቲያኖች ሆይ ልብ አድርጉ፣ በውስጥ ያለው በውጭ ካለው ይለያል። በውስጥ ያለው፣ "የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት" (ሮሜ 14፥ 17) ተብሎ እንደተጻፈ፣ የውስጡ ተፈጥሮና ባህርይ ፈጽሞ ይለያል። ውስጡ እጅግ እንደሚያምርና እንደሚማርክ ውበቱንና ግርማውን አጥርተን እንይ። በውስጥ ያለው ጉልበት ኃያል ነው፤ "የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና" (1ቆሮ 4፥ 20)። በእግዚአብሔር መንግስት ምስጢር እውቀት እያደግን፣ በውስጥ የተገለጠው የብርሃን ግርማ ካልማረከን በቀር ውጭውን የሸፈነው ድቅድቅ ጨለማ እያስፈራራን እንኖራለን። በወንጌል አምነናል ከሚሉት መካከል ብዙዎች ሰይጣንና ክፋቱን እየፈሩ በውጭው የጨለማ ግርማ ሲደነብሩ ይስተዋላሉ። በእግዚአብሔር ቤት እየኖሩ የውስጡን ብርሃን ማክበር ተስኗቸው በውጭው ጨለማ የተወሰዱ ፈሪዎችና ድንጉጦች "ፈሪ ልብ ላላቸው፦ እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው።" (ኢሳይያስ 35፥ 4) የሚል ቃል ሊሰበክላቸው ይገባል። ካልሆነ ግን ትእዛዙን ስሙ "ማንም ፈሪና ድንጉጥ ሰው ቢሆን እርሱ ፈርቶ የወንድሞቹን ልብ ደግሞ እንዳያስፈራ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ" (ዘዳግም 20፥ 8)። እንግዲህ በብርሃን ተከቦ በቤት ውስጥ እየኖሩ ከቤት ውጭ ያለውን ጥላና ጨለማ እየፈሩ መጨነቅና መደንገጥ ብዙዎቻችን በህጻንነት እድሜአችን ያሳለፍነው ልምምድ ነው። ስናድግ ግን ያንን ትተናል። ስለዚህ እንደግ እንጂ ወደፊት ህጻናት መሆን አይገባንም።


ይህንን ደግሞ ተመልከቱ፣ "ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።" (1ቆሮ 6፥9-10) እንደተባለ፣ የእግዚአብሔር መንግስት ፍጹም ንጹህ ነው። የእግዚአብሔር መንግስት የስጋና ደም መንግስት አይደለም፤ ጳውሎስ፣ "ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም" (1ቆሮ 15፥ 50) ብሎአልና፤ አሁን የምንኖርበትን የእግዚአብሔርን መንግስት በስጋና በደም አይገመትም።


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእንክርዳዱን ምሳሌ ተርጉሞ ባስተማረበት በማርቆስ 13 ያለውን ትምህርት ካጤነው፣ "የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥" (ማርቆስ 13 ፥40) ሲል፣ ክፋት የሚለቀመው "ከመንግሥቱ" ነው እንጂ ከአለም ላይ አለመሆኑን እናስተውላለን። መንግሥቱ ደግሞ ከዚህ አለም አይደለችም። በአለም ላይ ግን ክፋትም ደግነትም፣ ጥፋትም ልማትም አለ ይኖራልም። አስተውሉ አለም ከክፋት አይጸዳም። ክርስቶስ በዙፋኑ ሆኖ የነገሰባትና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ለዘላለም የሚገዛባት፣ ጽድቅና ቅድስና የሰፈነባት፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ኃሴትና ደስታ የሞላባት መንግስቱ፣ እዚህ ተዳሳሹ አለም ላይ ካለ ከየትኛውም ሥጋዊና ነባራዊ የሰው ስርአት ጋር እናስተያያት ዘንድ ግን የሚመጥናትና የሚገልጣት ምንም አምሳያ የላትም። የምድር ላይ ኃያላን በመንግስታቸው የለበሱትን ካባ እና በራሳቸው ላይ የደፉትን ዘውድ፣ የተቀመጡበትን ዙፋንና በፖለቲካ አስተዳደራቸው የሚሰጡትን ፍርድና ዳኝነት ስንራቀቅ ውለን ብናድርበት ክርስቶስ በመንግስቱ ካለው ግርማና ክብር ጋር ሊጠጋጋ ቀርቶ ምሳሌ ለመሆን እንኳ አይበቃም። ተመልከቱ፦


"በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።" (ራእይ 12፥ 7-10)


"በሰማይ" በሆነው ሰልፍ ድል የተመታው ዘንዶ "በሰማይ" ስፍራ የለውም፤ በክርስቶስና በቅዱሳኑ ሰማይ ዕድል ፈንታ መብትና መታሰቢያ የለውም። "ወደ ምድር" ወደማያምነው አለም ተጥሎአል እንጂ፣ በክርስቶስ ሆነን በምንኖርበት በሰማያችን ላይ ቦታ የለውም። የክርስቶስና የክርስቲያኖች ሰማይ ንጹህ ነው፣ በዚህ ሰማይ ስትኖሩ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሰይጣንን ድል ነስቶታልና፣ ስለ ዘንዶው ውጊያና ስለ ከሳሽነቱ ስጋት አይገባችሁም። ድላችሁንም በእምነት ትይዛላችሁ እንጂ በማየትና በስሜት አትፈልጉትም። ሰይጣን ታስሮአል፣ ወደ ምድርም ተጥሎአል፤ ሰማይም ከክፉውና ከክፋት ነጻ ነው። ክፉውና ክፋት ፍጻሜውን ያገኘው በሰማይ ነው። "እንቅፋት ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉ" ሁሉ ከመንግስቱ ተለቅመው ተጠርገዋል። አስተውሉ፣ ዘንዶው ተሸንፎ የተጣለው ወደ ምድር ነው፣ ከመንግስቱ ውጭ።


ከተገለጠው ድል መንሳትና ከዘንዶው መጣል የተነሳ የተነገረውን የሰማይ ድምጽ ስሙ፣ ይህ ድምጽ ሰማይ ብቻ የሚሰማውና የሚረዳው ድምጽ ነው፦ " አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥" ይህ የሆነው ከጊዜ አንጻር እንጂ ከጆግራፊ አንጻር አይደለም፤ ከጊዜ አንጻር "አሁን" ነው፣ ከአድራሻ አንጻር ደግሞ "በሰማያዊው ስፍራ" ነው። "በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ" (ኤፌ 1፥3)። ይህም ስፍራ የእግዚአብሔር ቀኝ መንፈሳዊው የክርስቶስ ግዛት ነው፣ መዳንን እንደተቀበለ አማኝም መቀመጫችን በሰማይ ነው፤ "በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን" (ኤፌ 2፥ 7)። የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ባለማመን ከዚህ ብርሃን እንዳትጎድሉ እጸልያለሁ።


ሰይጣን ገደብ ተጥሎበት እንዲሰራ የተፈረደበት ነው። 


አስቀድመን ሰይጣን በዘመኑ ላይ የነበረውን አገዛዝ እንመልከት፤ በሽግግሩ ወቅት ላይ አገዛዙ በሂደት እየተገለበጠና እየተለወጠ ነበር። በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎትና በጠቅላላው በዚያ የሽግግር ዘመን የወንጌል አገልግሎት አንዱና ዋናው ተጽዕኖም ይኸንንው ሂደት ማሳለጥ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 17፥ 6)። ያኔም በረጅሙ የብሉይ ኪዳን ዘመን ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ ብዙ ሰዎች በአጋንንት እስራት ተይዘው በጌታና እርሱ በላካቸው አገልጋዮቹ ነጻ ይወጡ ነበር። በራእይ 20፥ 7 ላይ ለጥቂት ጊዜ ከእስራቱ እንዲፈታ በተባለለት አኳኋን፣ ሰይጣን በቄሳር ኔሮ ዙፋን ላይ ሆኖ የመጨረሻውን የመልሶ ማጥቃት በቅዱሳን ላይ አድርሶ ነበር። ዲያብሎስ ራሱ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ያውቅ ስለነበር፣ ያኔ ይሰራ የነበረው፣ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ፣ በታላቅ ቁጣ ነበር (ራእይ 12፥ 12፤ 1 ጴጥሮስ 5፥ 8-9)፤ ከዚህም የተነሳ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያን መከራዋ ታላቅና አለም አቀፋዊ ነበር። በሕጉ ስርአት በኩል ጉልበታም ሆኖ የሚሰራው የኃጢአት ኃይል ዋና የማዘዣ ጣቢያው የሚገኘውም ደግሞ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደሱ ነበር፣ "የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው" (1 ቆሮንቶስ 15፥ 56) ተብሏልና። የዚያ የአሮጌው ዘመን ስርዓት የሰይጣንን ክስ እና የውንጀላውን ስድብ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደታች እያወረደ  የሞትን እና የኩነኔን አገልግሎት ያስፈጽም ነበር። ቤተክርስቲያንም ከብዷት ስትቃትት የኖረችው በዚህ ወቅት ነበር። ከዚያም በኋላ ግን በ70 ዓ.ም ላይ ሰይጣን በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት "ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።" (ራእይ 20፥ 10) በሚለው ቃል ዘላለማዊ ሽንፈቱንና  ፍርዱን አገኝቷል። 


በማቴዎስ 25፥ 41 ላይ ያለውንና የዘላለም እሳት ለሰይጣን እና ለመላእክቱ የተዘጋጀ መሆኑን የሚናገረውን ቃል ተመልከቱ። ሰይጣን አጋንንት የተባሉት የወደቁ መላእክት ሁሉ አለቃ ነው። የሳቱትን ሁሉ ያሳሳተ፣ የተሸነፈም የክርስቶስ ጠላት ነው። በ70 ዓ.ም ላይ በሆነው ፍርድም በዲን ወደሚቃጠል የእሳት ባህር ተጥሏል፣ በዚያም ከዘላለም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሰቃያል፣ ይህም የአሁኑ የመንግስት ዘመን እውነታ ነው። ድኝ ከሰልፈር ጋር ተመሳሳይ ነገር ነው። ድኝ የሚሰነፍጥና የሚተፈንግ የሚሸታቸውን ሁሉ በከፋ ሁኔታ የሚረብሽ ጠረን ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም የእሳቱን መቀጣጠል እንዳይጠፋ አድርጎ ጠብቆ የሚያቆይ ነው። እጅጉን እየተቃጠለ ብረቶችን ሁሉ የሚያቀልጥ እሳት ነው። አሁን ባለው ዲስፔንሴሽን ሰይጣን የተቀበለው የመጨረሻ ፍርዱ ይሄ ነው። ይሄ ግን ፈጽሞ እስከወዲያኛው አጥፍቶታል ወይም ወደ አለመኖር ቀይሮታል ማለት አይደለም። ሰይጣን የለም የሚል ትምህርትም የክርስትና ትምህርት አይደለም። ይልቁን ግን ሁልጊዜ እንደሆነውና እንደነበረው ያው የተፈረደበትና የተጣለ፣ እንደፈለገ የሚጠመዝዘው፣ በቁጥጥሩ ስር ያለ፣ ንስሃን እምቢ ብለው በአመጻቸው የሚገፉ አመጸኞችን በመረጡት የጥፋት መንገድ ላይ እንዲያስታቸው በእርሱ የሚላክ የጥፋት መልእክተኛና የእግዚአብሔር  ዲያብሎስ ሆኖ ይኖራል፡፡ ምን ማለት ነው? 


ሰይጣን፣ ተጥሎ በሚገኝበት የእሳት ባህር፣ ልክ እንደ መንጋ አለቃ አክት እያደረገ፣ ከእርኩሳን መላእክቱ ጋር ይሰራል፤ ያም ስፍራ ዘላለማዊ የማዘዣ ጣቢያው ነው። የእርሱ ውሸቶችና ማታለያዎች ሁሉ እድል የሚኖራቸው ለእርሱ ተጽእኖ ራሳቸውን ክፍት ባደረጉ፣ በወንጌል በማያምኑና ባልዳኑ ኃጢአተኞች ላይ ነው። እነዚህም ያልዳኑና ያላመኑ ኃጢአተኞች በ70 ዓ.ም በተፈጸመው ፍርድ ከዘላለም ከእርሱ ጋር ለእርሱ የተመደቡና ተላልፈው የተሰጡ ናቸው። እነርሱም የሚያደርጉት ማናቸውም ነገር፣ ሃይማኖትም ቢሆን እንኳ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ኃጢአት ነው። መንፈስ ቅዱስ የሌላቸው ስለሆኑ የትኛውም ጥረታቸው በእግዚአብሔር ፊት እንደ ጽድቅ አይታይም። በሚኖሩት ያለማመንና የአመጽ ኑሮ የሰይጣንን ሃሳብ ለማገልገል ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ለዚህም የተመደቡ ናቸው። ከዚያ ፍርድ ማምለጥ የሚቻለው በክርስቶስ ብቻ ነው። ሰይጣን በወንጌል አምነው ክርስቲያኖች በሆኑ በማናቸውም ላይ ቢሆን አንዳች ሥልጣንና ኃይል የለውም። የትኛውም ኃጢአታችን እና ውድቀታችን ከጌታችንና ከመድሐኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ስራ የተነሳ ፈጽሞ ለዘለአለም  ይቅር ተብሏል። በሰይጣን ተጽእኖ ውስጥ ባይሆኑም እንኳ ከሥጋ ድካም የተነሳ ሰዎች ገና ኃጢአትን ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን በወንጌሉ ባመንን በእኛ እና ባላመኑት መካከል ያለው ልዩነት ኃጢአታችን በክርስቶስ ይቅር የተባለ መሆኑ ነው። በዚህ ነባራዊ አለም ያሉ ሰዎች ሁሉ ምድባቸው ኃጢአታቸው የተሰረየላቸውና ኃጢአታቸው የተያዘባቸው በሚል ከሁሉት በአንዱ ነው። ለኛ ላመንን በክርስቶስ የተሰጠን የኃጢአት ይቅርታ ዘላለማዊው አለኝታችን ነው። 


ክርስቲያኖች በጠንካራ ምኞቶቻቸው ላይ አጥብቆ የመስራት ትግል አለባቸው። ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያላቸውን ዲቮሽን ለመጠበቅ ሳያቋርጡ መጸለይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት፣ እና በእግዚአብሔር እና በሰዎች ሁሉ ፊት በእምነት መኖር ያስፈልጋቸዋል። ይህም ፈቃዳቸውን በእግዚአብሔር ፈቃድ ስር እያደረጉ ጠንካራ ምኞቶቻቸውን ጌታን ደስ ለማሰኘት እንዲጠቁሙቡት ያስችላቸዋል። ነገር ግን ሰይጣን በእሳት ባሕር ውስጥ እንደተጣለ እና በአሮጌው ኪዳን ዘመን እንደነበረው አጋንንቱ መዳን ያገኘነውን እኛን መውረስ እንደማይችሉ እርግጠኞች ደግሞ እንሁን፤ ይህ ግን በፍጥረታዊው አዕምሮአችንና በአስተሳሰባችን ውስጥ ከሥጋ ድካም የተነሳ የመሳለብና የመወሰድ ፈተና ፈጽሞ የለብንም ማለት ደግሞ አይደለም። በዚህ ፍጥረታዊ አለም በሥጋዊው ተፈጥሮአችን በምድር ላይ ሳለን በዚህ ትግል ውስጥ እናልፋለን። ለዚያም ነው እንደ ክርስቲያን የጥሞናን ሕይወት ጠብቀን በጸሎትና በእግዚአብሔር ቃል እየተጋን ከእግዚአብሔር ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረትና መጠበቅ አለብን ስንል የምንመክረው።


ስለሰይጣን የተነዙ መሰረታዊ ውሸቶች


ዘፍጥረት 3፥ 15 ላይ "በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።" ለሚለው የተስፋ ቃል በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ፍጻሜ የሚሰጠው "የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል" ሲል ሮሜ 16፥ 20 ላይ የተጻፈው ቃል መሆኑን እናስተውል። ልክ እንዲሁ ሉቃስ 10፥ 17-18፤ ዮሐንስ 12፥ 31፤ ቆላስይስ 1፥ 13፤ 2፥ 13-15፤ ዕብራውያን 2፥ 14፤ እንዲሁም 1ኛ ዮሐንስ 3፥ 8 ተመሳሳዩን ያስተምራሉ። እነዚህ ሰባት የሚሆኑ የቅዱሳት መጻህፍት ማጣቀሻዎች ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ አጽንዖት ይሰጣሉ። እንግዲህ እግዚአብሔርን በቃሉ ልናምነውና ቃሉን እንደተናገረው እንደተጻፈም ሳንጨምርና ሳንቀንስ እንዲሁ ልንቀበለው እንጂ ሃሰትን ማመንና መመስከር አይገባንም፤ በመጀመርያ ከቃሉ ምክር ተምረን "ሰይጣን በአሁን ጊዜ ይህንን አለም እየገዛ ነው" የሚልን ይህን የኃሰት ትምህርትና አዋጅ ማቆም አለብን። አሁን እየገዛ ያለው ንጉሰ ነገስት ኢየሱስ ጌታችን ነው። በሰማይም በምድርም ሁሉ ሥልጣን የእርሱ ነው (ማቴዎስ 28፥ 18)። ከፍ ሲል የጠቀስኳቸው "የዚህ አለም ገዢ" እና "የዚህ አለም አምላክ" የተሰኙት የሰይጣን መጠርያዎች (ዮሐንስ 12፥ 31፤ 14፥ 30፤ 16፥ 11፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፥ 4) ሁሉም የሚያመለክቱት በ70 ዓ.ም በተፈጸመው የጌታ ዳግም ምጽአት ሳይፈረድበት አስቀድሞ የነበረውን ሚና ብቻ ነው እንጂ የአሁኑን የመንግስት ዘመን ሁኔታ አያሳዩም።


ሉሲፈርን አስመልክቶ ሲዋሽ የኖረውን ሁለተኛውንና ሌላውን ውሸት ደግሞ እንመልከት። ሉሲፈር ማለት "የአጥቢያ ኮከብ" ማለት ነው። አስቀድመን ኢሳይያስ 14፥ 12 ላይ "አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ!" የሚለውን ተመልከቱ። ከቁጥር 4 እንደምንረዳው ይህ ትንቢት የባቢሎን ንጉስ የነበረው ናቡከደነፆርን የሚመለከት ነው። በምሳሌና በትዕምርታዊ ገለጻ ለናቡከደነጾር አወዳደቅ የተነገረውን ቃል ወስዶ ሰይጣንን ለማለት ተፈልጎ ነው የሚል ድርቅና የቃሉን መንፈስና አውድ አለማወቅ ነው። ዳንኤል 5፥ 20-21 ያለውም "ልቡ ግን በታበየ በኵራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ፥ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፥ ክብሩም ተለየው። ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ የሚወድደውንም እንዲሾምበት እስኪያውቅ ድረስ ከሰው ልጆች ተይለቶ ተሰደደ፥ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፥ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።" ሲል ይህንኑ ያጸናልናል። ልብ አድርጉ፣ ሰይጣን ፈጽሞ ሉሲፈር ተብሎ ተጠርቶ አያውቅም። 'ሰይጣን ይህንን አለም እየገዛ ነው' ከሚለው ቀደዳ ቀጥሎ፣  'ሉሲፈር የሰይጣን ስም ነው' የሚለውን ይህን ቀደዳ፣ ውሸት ቁጥር ሁለት ልንለው እንችላለን።


ልክ እንደዚሁ በርካቶች ሕዝቅኤል 28፥ 13 ላይ ያለውንና "በእግዚአብሔር ገነት በዔድን ነበርህ፤ የከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅ፥ ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር።" በሚል የተነገረውን አንብበው፣ በተለይ ከዚህ አይነቱ ገለጻ የተነሳ ይህ ንግግር እባቡን ያመለክታል ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ግን የአመስጥሮ (allegorization) ስህተት ነው። ምንባቡን በሙሉ አውዱን ጠብቆ በጥንቃቄ የሚያነብ ሰው ግን ከቁጥር 2 እና 12 ላይ ተመስርቶ ትንቢቱ በጢሮስ ገዥ ላይ የተነገረ መሆኑን ያስተውላል። ከዚህም በላይ ከንግዱ ብዛት የተነሳ ባከማቸው ሀብት ልቡ እንደታበየ (ቁጥር 5 እና 16) ተነግሮናል። ለጢሮስ ገዢ የተነገረውን "አይ ሰይጣንን ማለቱ ነው" ብሎ መገገም ያልተጻፈ ማንበብ ነው። ይልቁንም ይህ ምንባብ ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ያደርገው በነበረው ጉዞው ላይ ያኔ ጴጥሮስን በገሰጸው ጊዜ "አንተ ሰይጣን" (ማርቆስ8፥ 33) ብሎ ከጠራበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። ተግሳጹ የተነገረው በቀጥታ ለደቀመዝሙሩ ሆኖ ሳለ፣ የለም ለሰይጣን ነው ብሎ መተርጎምም ሆነ በዚህ ክስተት ጴጥሮስን ማሰይጠን በትልቁ ስህተት ነው።


ዲያብሎስ ሉሲፈር ተብሎ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ አንድም ቦታ እንዳልተጠራ፣ ኢየሱስም ገና ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ድል እንደነሳው ይህንን እውነት አጥብቃችሁ ያዙ እንጂ ሀሰትን አትመኑ። ይልቁን ግን ትምህርት የማይወዱና በተሳሳተ ትርክት የተወሰዱ የሚበዙ የዘመናችን "አገልጋዮች" እና ምዕመናን አሁን እዚህ ላይ እዘረዝረው ዘንድ የሚያታክቱ ልበ ወለድ የሆኑ በርካታ ውሸቶችን በየመድረካቸው ሲያስተጋቡ፣ ጉባኤዎቻቸውም ሲያምኑ ይስተዋላል። የኛ ትውልድ ሕዝብ 'ማን መጥቶ ባሳሳተኝ' በሚል ረሃብ፣  ያለና የተጻፈውን ከማመን ይልቅ የሌለና ያልተጻፈ ለማመን ራሱን አሳልፎ የሰጠ ይመስለኛል።  ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ስመለስ፣ በርካቶች የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ 20፥ 1-4 እና 7-10 ያለውን ጠቅሰው እያነሱ ሰይጣን ወደፊት ይፈታ አይደለምን? ሲሉ ይጠይቃሉ። አዎ፣ ሰይጣን በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ተፈትቶ ተለቆ ነበር፣ ነገር ግን በዚህ የእኛ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ፈጽሞ ተፈትቶ አይለቀቅም። 


ልብ አድርጉ የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው በ65 አም ላይ ነው፣ የመጽሐፉም ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ70 አም ላይ ነው። ዳንኤል 8፥ 26 ላይ "የተነገረውም የማታውና የጥዋቱ ራእይ እውነተኛ ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ስለሚሆን ራእዩን ዝጋ።" የሚለውም ቃል በራእይ 22፥ 10 "ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።" በሚለው ቃል ፍጻሜውን አግኝቷል። የራእይ መጽሐፍ በአግባቡ አውዱን ጠብቆ እንዲተረጎም ከተፈለገ፣ የራእይ 1፥ 1 እና 3 ትክክለኛውን ጊዜ አመልካች የሆኑ ምንባባት፣ እንዲሁም ፈጥኖ፣ ቶሎ፣ የተሰኙት ቃላት በጥሬው ትርጉም መወሰድ አለባቸው። 


እኛ አሁን እየኖርን ያለነው ከሽግግሩ ዘመን ማዶ ባለው፣ አሮጌው ዘመን በተሻረበት እና በዳግመኛ ምጽአቱ በተጀመረው በዘላለማዊው ዘመን በአዲሱ ኪዳን ዘመን ውስጥ ነው፣ (ኢሳይያስ 9፥ 7 ፤ ዕብራውያን 13፥ 20)። ይህም ዘመን የመንግስት ዘመን ይባላል። ይኸውም አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ነው። በዚህ ክቡር ዘላለማዊ ኪዳን ስር አድረው ክርስቶስን የሚያከብሩት እነዚያ እርሱ የተቤዣቸው ሕዝቦቹ እና እያንዳንዳቸው ቅዱሳኑ ብቻ ናቸው (መዝሙር 2)፤ እነርሱም ብቻ ድል የነሱ እና የተባረኩ፣ ከፍ ከፍ ብለው በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር ያሉ እና ሥልጣንና ኃይል የተሰጣቸው ናቸው።  ከመጀመሪያው ምዕተ-ዓመት ጀምሮ ደግሞም ሁልጊዜ የማይበገሩ ኃያላን ሆነው በሰማያዊው ስፍራ ከክርስቶስ ጋር የነገሱ እና የሚገዙ ክርስቶስን የሚያከብሩ ሕዝቦች እነርሱ ብቻ ናቸው።  ክርስቶስንና የጽድቅ መንግስቱን የሚቃወሙ ማናቸውም የምድር ህዝቦች ተሰብረውና ተደምስሰው፣ እርሱ ከፍ ከፍ ባደረጋቸው፣ ክርስቶስንም ሊያከብሩ በተገባቸውና የእርሱን ጽድቅ በተሸከሙ ሕዝቦቹ እግር ስር ተጥለው ተረግጠዋል ፡፡ ክርስቶስ የዚህ የአዲሱ አለም /ዘመን ጌታና አምላክ ስለሆነ፣ ከኔሮ ዘመን በኋላ በቅዱሳኑ ላይ በዓለም ዙሪያ ግሎባል የሆነ ስደት ያልነበረው እና ደግሞም ከዚህ በኋላ በጭራሽ የማይኖረው ለዚህ ነው። ምክንያቱም የነገስታት ንጉስ እና የጌታዎች ጌታ የሆነው የቤተክርስቲያን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ረግጦ፣ ግዛትና መንግስትም ተሰጥቶት ለቅዱሳኑ ዘላለማዊ እረፍት በአባቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ የሚገዛ በመሆኑ ዘመኑ ተቀይሯል። በዚህ በተቀየረ ዘመን አሁንም በክፉ የተያዙትን የሚያስጥል የመዳን ቃል፣ እርሱም የተፈጸመው የክብር ወንጌል ይሰበካል። 


በመጨረሻም፣ ጉዳዩን ኮምጨጭ ብሎ ለመደምደም፣ በመጀመርያ ሰይጣን ፈጽሞ ሉሲፈር ተብሎ ተጠርቶ አያውቅም። በመጽሐፍ ቅዱስ ባልተጠራበትና ባልታወቀበት ስያሜ ሰይጣንን ማካበድም ሆነ ማሰይጠን ያልተማሩትንና የሚስቱትን ግራ ማጋባት ይሆናል። አስከትሎም፣ ሰይጣን በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከዘላለም እስከ ዘላለም 100 ፐርሰንት ፈጽሞ የተሸነፈ ነው። መንግስት በተሰጣቸው ዘንድ ዋጋ የለውም። ለአለምና ለዘላለም የነገስታት ሁሉ ንጉስ እና የጌቶች ሁሉ ጌታ ሆኖ ሁሉን ሊገዛ በእግዚአብሔር ዙፋን የተቀመጠው ገዢ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! ከእርሱ በቀር ሌላ የለም!! አሜንና አዎን እርሱ ነው።


ለተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማረጋገጫ፣ እንደ ማቴዎስ 24፥ 34 እና ሉቃስ 21፥ 22 ያሉ ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ በርካታ ምንባባት ላይ ተምስርቼ ያዘጋጀኋቸውን ተከታታይ ጽሁፎች በዚህ ማስፈንጠርያ    

http://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/24.html?m=1 ገብታችሁ በብሎገሬ ላይ ተመልከቱ። ስለ ታላቁ መከራ ሁለተኛ አጋማሽ እና ስለ መጨረሻው የአርማጌዶን ጦርነትም The War Of the Jews በተሰኘው የፍላቪየስ ጆሳፈስ መጽሐፍ የተተረከውን የታሪክ መዝገብ አገላብጡ። አይምሮ ያለው ሰው ከዚያ በኋላ እንደተለመደው ማሰብ ያቆማል።

(Gkr)


No comments:

Post a Comment