Wednesday, January 12, 2022

ሶላ ስክሪፕቱራ

ሶላ ስክሪፕቱራ" የተሰኘው ይህ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የእምነት አቋም በቀላሉ ሲተረጎም “በቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ” ማለት ነው።  ይህ አቋም የአማኞችን ኅሊና የመግዛትና የመፍረድ፣ የትኛውንም የቤተክርስትያን አስተምህሮና ልምምድ የማጽናትና የመሻር ሥልጣን ያለው 66ቱን የብሉይና የሐዲስ ቅዱሳት መጻህፍት የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው የሚለውን ሃሳብ በግልጽ የሚያውጅ ነው።  ፕሮቴስታንቶች በየቤተእምነታቸው በጋራ ስምምነት የተቀበሏቸውና እንደ ቤተ ክርስቲያን እውቅና የሚሰጡአቸው የተለያዩ አገልግሎቶች፣ የሲቪል ተቋማት፣ የቤተ ክርስቲያን የእምነት መግለጫዎችና ታሪካዊ  ምስክርነቶችን የመሳሰሉ ሌሎች ደቂቅ የሥልጣን ዓይነቶች ሊኖሩዋቸው ይችሉ ይሆናል።  ዳሩ ግን እነዚህን ሥልጣናት አስመልክቶ ከእግዚአብሔር ሥልጣን የተቀዱና ለራሱ የእግዚአብሔር ሥልጣን የተገዙ እንደሆኑ አድርገው ደግሞ ይቆጥሯቸው ነበር። በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ከእነዚህ ደቂቀ ሥልጣናት ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ በእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን የሚዳኙ እንጂ በራሳቸው ፍጹም ተደርገው አልተቆጠሩም፣ ምክንያቱም ሁሉም እያንዳንዳቸው ስህተት ሊሰሩ የሚችሉና ለእርማት የተጋለጡ ናቸው።  እግዚአብሔር ብቻ ግን የማይሳሳትና በማንም የማይታረም ፍጹም ነው፤ በእግዚአብሔር መንፈስ መነዳት የተሰጠው ቃሉም እንደ እርሱ ነው።  እነዚያ  በተፈጥሯቸው ለእርማት የተጋለጡ፣ ሊሳሳቱ የሚችሉና በማንኛውም ጊዜ ሊሻሻሉና ሊለወጡ የሚችሉ ደቂቀ ሥልጣናት ፍጹምነት የሌላቸው በመሆኑ የአማኞችን ሕሊና በፍጹም መግዛትም ሆነ መፍረድ አይችሉም፤  ሕሊናን የመግዛት መብት ለእግዚአብሔር እና ለቃሉ ብቻ የተጠበቀ ሆኖ ይኖራል። የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ካልሆነ በቀር ማናቸውም የተጻፈም ሆነ ያልተጻፈ፣ ጥንታዊም ሆነ ዘመናዊ፣ ታሪካዊም ሆነ ካሪዝማዊ የትኛውም ትምህርትና ልምምድ የአማኙን ሕሊና እንዲገዛ ፈጽሞ ሊፈቀድለት አይገባም። በማንም የማይሻረው፣ ሊለወጥም ሆነ ሊሻሻል የማይችለው ዘላለማዊው ሥልጣን፣ እርሱም ፈጣሪዋ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ቤተክርስቲያንን አስገኝቷታል እንጂ ቤተክርስቲያን ቃሉን አላስገኘችውም፤ ቤተክርስቲያንን ቃሉ ቤተክርስቲያን አድርጓታል እንጂ ቤተክርስትያን ቃሉን የእግዚአብሔር ቃል አላደረገችውም፤ ቤተክርስቲያን ለእግዚአብሔር ቃል ትገዛለች እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ለቤተክርስቲያን አይገዜም። ቤተክርስትያንም በፈንታዋ በማንኛውም ጊዜ ሊሻሩ፣ ሊለወጡና ሊሻሻሉ የሚችሉ እነዚህን ታሪካዊ ደቂቀ ሥልጣናት አስገኝታለች፣ እነርሱም ጠቃሚ ታሪካዊ ሰነዶች ብቻ ናቸው እንጂ ሕሊናን የሚፈርዱ ሥልጣናት አይደሉም። ማርቲን ሉተር ሕይወቱን ሊያስከፍለው በሚችልበት የፍርድ አደባባይ ትምህርቱን እንዲያስተባብል የመጨረሻ ዕድል በተሰጠው ጊዜ የተናገረውን ልጥቀስ፦ "በቅዱሳት መጻሕፍት ወይም ግልጽ በሆነ አመክንዮ ተረጋግጦ እንዳምን ካላደረገኝ በቀር፣ ከያዝኩት አቋም አንድ ጋት ያህል እንኳ አልመለስም። ሕሊናዬም በእግዚአብሔር ቃል ተይዞ ሳለ የሕሊናዬን ፍርድ በመደፍጠጥ እቃወመው ዘንድ ትክክልም ተገቢም አይደለም።" ፕሮቴስታንቶች ያቀጣጠሉትን የተሃድሶውን አስተምህሮ ውድቅ ለማድረግ በጊዜው የነበሩ ካቶሊካውያን ከሳሾቻቸው ሉተርንና አብረውት የቆሙትን ወንጌላውያን በቅዱሳት መጻህፍት መሰረት ላይ ብቻ ቆመው ሊሞግቱአቸው ባለመቻላቸው ከቅዱሳት መጻህፍት ርቀው የተንጠለጠሉት በቤተክርስቲያን ታሪክና በጥንታውያኑ የእምነት መግለጫዎች ላይ እንደነበር ከታሪካቸው እናውቃለን። ማርቲን ሉተር ግን በንጉሰ ነገስቱና በጳጳሳቱ ጋሻ ጃግሬነት በተቃውሞ የተሰበሰበበትን ጉባኤና የጉባኤው ውሳኔ የተንጠላጠለባቸውን ጥንታውያን የእምነት መግለጫዎች በጽኑ በመቃወም ውድቅ አደረጓቸዋል። ይህንንም ያደረገው እነዚያን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በጉባኤ ውሳኔ የተዘጋጁ እንጂ በእግዚአብሔር እስትንፋስ ያልተሰጡ የእምነት መግለጫዎችን ስለማያከብራቸው ወይም ደቂቀ ሥልጣናቸውን ስለማይቀበል አይደለም፤ ይልቁንም እነዚህ ታሪካዊ ሰነዶች የእግዚአብሔርን ቃል ተክተው የሙግቱ መሰረት እንዲሆኑ ስላልፈለገ ነው። በእውነትም ሶላ ስክሪፕቱራ ዋጋ የሚያስከፍል አቋም ነው፣ በእኛ ዘመን ደግሞ እንደ ኋላ ቀር አክራሪና ወግ አጥባቂ እያስቆጠረ በማንም እንዳትፈለግ ሊያደርግህ ይችላል። ለሰዎች ስሜት እንደ ምት መች ሆነህ ካላመቻመችህ፣ ካልቀየጥክና ካልደባለቅህ በቀር፣ ወይንም ካልዘባረቅህና ካላጨናበርክ በቀር፣ በሶላ ስክሪፕቱራ ብቻ አትሮንስ ላይ ብትሰየም ማንም ሊሰማህ አይፈልግህም። ያም ቢሆን እንኳ "ያለ መነሳትና ያለ መናወጥ"፣ ያለ ማመንታትም እዚሁ ላይ "Hear I stand" ብሎ ጸንቶ መቆሙና መሞቱ ይመረጣል። ገና በጠዋቱ በሉተራዊው ወንጌላዊ እምነት ውስጥ የተዋወቅሁትና የእይታዎቼ ሁሉ ብርሃን የሆነልኝ ይህ "ሶላ ስክሪፕቱራ" በፕሪቴሪዝም የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ውስጥ የበለጠ እንድወደውና እንድማረክበት አድርጎ አጽንቶኛል። ይህ ደግሞ የዘወትር መጽናናቴ ነው። (gkr)




No comments:

Post a Comment