የምጽአቱ ተስፋ እና አቋሜ
የምጽአቱ ተስፋ (parousia) ያኔ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ላይ፣ "ሁለተኛ እመጣለሁ" ሲል ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ ሲሰጥና፤ ኋላም በቅዱሳን ሐዋርያቱ ይኸው ተስፋ እየተደጋገመ ሲነገርና ሲዘገብ፤ ያኔውኑ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ውስጥ፣ ደግሞም በጣም በቅርቡ፣ ማለትም በዚያው አንድ ትውልድ የእድሜ ዘመን፣ ይኸውም በ70 አ.ም ላይ በተጠናቀቀው ዘግናኙ የእስራኤል ሮም ጦርነት ወቅት፣ "ከመሆን የማይቀር"፣ ቀንም የተቆረጠለት፣ ሳይዘገይ የሚፈጸም ጉዳይ ነበር። በ70 አ.ም ላይ ከሆነው ከዚህ ታሪካዊ ክስተት ተነጥሎ፣ 2000 አመታትና ከዚያም በላይ ተራዝሞ አሁን እኛ ባለንበት ዘመንም ይሁን ወይም ገና ወደ ፊት በሚመጣ ሌላ የሩቅ ዘመን የሚጠበቅ የጌታ ምጽአትም ሆነ የዘገየ ተስፋ የሚባል ነገር ፈጽሞ የለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እውቅና የሚሰጠው ዳግመኛ ምጽአት የተፈጸመ ተስፋ ሆኖ አልፏል። ይህን ስለሰማችሁ በፎቶው ላይ እንዳለው ህጻን አታለቃቅሱ። ደግሜ እላለሁ፣ ጌታ ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ወደፊት በየትኛውም ጊዜ ተመልሶ አይመጣም። ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው፤ ጥያቄው ከዚህ እውነታ ጋር ለመኖር ተዘጋጅታችኋል ወይ? የሚል ነው።
ሲጠጡት ከኖሩት " ይመጣል" ከሚለው የሰው ትምህርት የተነሳ ይሄ "ትንቢት ተፈጽሟል"፣ "ምንም የሚጠበቅ ነገር የለም" የሚለው እንቅጩን የሚናገረው እምነታችን ክህደት የሚመስላቸው ህልቆ መሳፍርት ክርስቲያኖች መኖራቸው እሙን ነው። ዳሩ እውነት የጥቂቶች መሆንዋን ሳያውቁ በደቦ የሚያስቡና ምንም የማይጠይቁ ብዙዎች አያስተውሉም። በወጉ ባልተተረጎሙ አንዳንድ ጥቅሶች ላይ ራሱን ካንጠለጠለው "ይመጣል" ከሚለው ያብዙዎች እምነት ይልቅ፣ መሰረቱን በቅዱሳት መጻህፍት ላይ አድርጎ፣ ጊዜ ጠቋሚ የሆኑትን የንባብ ክፍሎች በወጉ እየተረጎመ "እንደ ተስፋ ቃሉ ተመልሶ መጥቷል" የሚለው የጥቂቶች እምነት በማዕበሉና በወጀቡ አንጻር ያለመናወጥ ቀጥ ብላ እንደምትቀዝፍ መርከብ ያለፍርሃት ለመንሳፈፍ የትንቢቱ ቃል ያስተማምናል። የበኩረ ተደራስያኑን አውድ አክብራችሁና ጠብቃችሁ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን በወጉ አጥኑ እንጂ፣ ከስር በስዕሉ ላይ እንዳለው ሰው ወደመቃብር እስክትገቡ ድረስ የሌለ ነገር እያመናችሁ ዝም ብላችሁ በአቦ ሰጥ አትኑሩ።
ጌታ ገና ወደፊት ተመልሶ እንደሚመጣ የሚያምነውና የሚያስተምረው ሁሉም የመጻኢነት (futurism) ነገረ ፍጻሜ (eschatology) አስተምህሮ ፈተናውን የወደቀው፣ ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ቤተ ክርስቲያንና ከእስራኤል ህዝብ እጣ ፈንታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘውን አጠቃላይ የሆነ የዳግመኛ ምጽአቱን ትንቢት ባህርዩንና፣ እነዚያን ጊዜ ተኮር የሆኑ ደርዘን ሙሉ የአዲስ ኪዳን ምንባባት የተነገሩበትን የቋንቋ አጠቃቀም እውነታ ባለማወቅና ባለማስተዋል ነጥብ ላይ ነው። ያስተውላሉ የሚባሉትም እንኳ ከሚበዙት የመጻኢያን ጎራ ሊደርስባቸው የሚችለውን ነቀፋ በመፍራት ስለ ክብራቸው ሲሉ ጥቅሶቹ የሚያወሩለትን ጊዜ ላለማየት ሆን ብለው አይናቸውን ጨፍነዋል። ዳሩ ግን የመጻኢነት (futurism) አመለካከት በሚያቀነቅነው "እስካሁን ባልተፈጸመና በዘገየ ተስፋ" አስተምህሮ፣ ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ የተናገሩትን የትንቢት ቃል እውነተኛነቱን ማረጋገጥም ሆነ ክርስትናችንን ከጥቃትና ከስድብ መከላከል ግን ፈጽሞ አይቻለንም።
ኃላፋውያን (Preterists) ግን በትንቢት መጻህፍት ላይ የሚያቀርቡት የትርጉም ቀዋሚነትን የሚከተለው ትንታኔና፣ ተስፋውም በተቀጠረለት ጊዜ እንደ ተፈጸመ ለማስረገጥ ራሱን የቅዱሱን መጽሐፍ ቃል የታመነ ምስክር ማድረጋቸው፣ እንዲሁም እንደ ደመና ከበውን ያሉ ታሪካዊ መዛግብትን ተጨማሪ ማስረጃ አድርገው ማቅረባቸው፣ በስነ ፍታቴ (hermeneutics) መርህ ሊረጋገጥ የሚችል ንጹህ ትምህርት ከመሆኑም በላይ፣ የተሳዳቢዎችንና የነቃፊዎችን ጥቃት የሚመልስ፣ የከሃዲዎችንም አፍ የሚያዘጋ አስተምህሮ ነው።
እኛ ኃላፋውያን በቅዱሳት መጻህፍት ንባባችን ላይ የበኩረ ተደራስያኑን ዋጋና አስፈላጊነት እውቅና እንሰጣለን እንጂ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ላይ አንዳች አንጨምርም። ለቅድመ ተደራስያኑ ዋጋ ሰጥተን ቅዱሳት መጻህፍትንም ወደ በኩረ ተደራስያኑ አውድ መልሰን እናነባለን፣ ከዚያም እንተረጉማለን እንጂ፣ ከቅዱሳት መጻህፍት አንዳች አናጎድልም። ይህ ነው የስነ ፍታቴው መርህ። ኢየሱስ ክርስቶስንም ሊያከብረው የሚችል ትርጉም ይህ ብቻ ነው ብለን አቋም ይዘናል።
ይህ አቋማችን በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ከሚገኝ ያፈጠጠ እውነት፣ እርሱም የትንቢት ሙሉ ፍጻሜ ጋር ያገናኘናል። እኔ በግሌ እንደ አንድ ተራ ሉተራዊ ቄስ ከታናሽነቴ አንስቶ እውነትን ስፈልግ ካልተሸፈነው እውነት፣ ከተፈጸመው ወንጌል ጋር ተገናኝቻለሁ። ስለዚህም አቋቋሜንና አሰላለፌን አርሜ ኃላፋዊነትን ተቀብያለሁ፣ ያውም ሙሉ ኃላፋዊነት። በዘመኔ ሁሉ ያለእውቀት ስከተለው የኖርኩት፣ ዛሬም የሚበዙት ወዳጆቼ ያለጥያቄ ያንጠለጠሉት "መጻኢነት" እና ትምህርቱ ግን እውነትን የሚጋርድ፣ የትርጉም ቀዋሚነት የሌለው፣ ለቅዱሳት መጻህፍት በኩረ ተደራስያን አውድ ዋጋ ከመስጠት ይልቅ ለኖረው ልማዳዊ አመለካከቱ ትክክለኛ መሆን የሚጨነቅ፤ ከዚህም በላይ የጌታችንና የመድሃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ሆኖ ስላገኘሁት ወዲያ አሽቀንጥሬ ጥየዋለሁ። በዚህ ቅር የሚሰኝ ካለ ምንም ማድረግ አልችልም፣ ኃላፋዊነት የብርሃን ጉዳይ ነውና። "ቅዱሳት መጻህፍት ብቻ" በሚለው አስተማማኝ ምሰሶ ላይ የተደገፈው ወንጌላዊው ሉተራዊ እምነቴና ኃላፋዊው ነገረ ፍጻሜ በአመለካከቴ ውስጥ ታርቀው ሳያቸው ደስታዬ ወደር ይለውም። ስለዚህ አስተውሉ፣ ትክክል መስሎ የሚታያችሁና የሚሰማችሁ ነገር የእግዚአብሔር ቃል ከሚናገረው ጉዳይ ጋር የማይስማማ ከሆነ፣ ያ ስሜታችሁ ምንም ያህል የብዙሃኑ ስሜት ቢሆንም እንኳ በራሱ ትክክልና ልክ ሊሆን ከቶ አይችልም።
ሰው ሁሉ እንደኔ ይሁን የሚል ድርቅና የለብኝም፤ ሊማሩ ለሚወዱና ለሚጠይቁኝ ግን ጉዳዩን እስኪረዱትና መሬት እስኪይዙ ድረስ፣ ይህንን ለብዙዎች "ደብረ በጥብጥ" የሆነባቸውን እውነት ቅዱሳት መጻህፍትን ብቻ እየገለጥሁ መልስ ለመስጠት እተጋለሁ። ለዘመናት በማንም ሳይጠየቅ ወንበሩ ላይ ተንሰራፍቶ የተቀመጠ ልማዳዊው ዶግማ እምነቱን የሚያፋጥጥ የተፈጸመው ተስፋ እውነቱ መገለጥ ሲጀምር በድንቁርና ያቆመው መንግስቱ መበጥበጥ ጀምሯል። ምክንያቱም ኃላፋዊነት ወጥሮ ይጠይቃል ይጠየቅማል፣ ስለዚህ ልማዳዊው አመለካከት በፊቱ ሊቆም አይችልም። በመሆኑም "ለፍተሻው ተባበሩን" እንላለን፣ ምክንያቱም ሲታመን የኖረው ነገር ሁሉ በጥብቅ መፈተሽ አለበት፤ ሊፈተሽም የማይወድ ሁሉ አንዳች የሸሸገው ነገር ቢኖረው ነው። በቃሉ ብርሃን ፈትሼና ፈትኜ እውነት ሆኖ ያገኘሁትንና የገባኝን የትንቢት ፍጻሜ ያለፍርሃት አካፍላለሁ። ገለባውን የሰው ትምህርት ደግሞ ቃሉን ለሚወዱ ሁሉ አጋልጣለሁ። በዚህም ደስ ይለኛል። ቃሉን ከሚወዱ ሁሉ ጋር ብዙ ደስታ አለኝና። በሶሻል ሚድያ ጽሁፎቼንና ትምህርቶቼን ለሚከታተሉ ሁሉ አክብሮት አለኝ። ከቃሉ ተምረው ፕሪቴሪዝምን የተቀበሉ ወንድሞች እህቶች በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተ እምነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ስለሆነም ጌታን ስለእነርሱ አመሰግናለሁ። በዚህም አቋማቸው ምክንያት መገፋትን እንዲታገሱ፣ ልባቸውንም እያነጹ ያለፍርሃትና ያለመናወጥ እንዲኖሩ በዳንንበት ጸጋ እመክራለሁ። መጻእያንም ቢሆኑ እንኳ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ቅዱሳን ናቸውና፣ ልጅነቴን በኖርኩበትና ባገለገልኩበት በቤተ እምነቴ በየትኛውም በሚካፈሉት የወንድሞች ጉባኤ በልብ ስፋት፣ በናፍቆትና በትህትና ተገኝቼ የሚያካፍሉትን የጸጋ አገልግሎት በፍቅር እየተካፈልሁ፣ ደግሞም የምሰማውንና የማየውን በቃሉ ወንፊት እያጠለልሁ እጠጣለሁ እንጂ ነፍሴን አከሳት ዘንድ ከህብረቱ እንጀራና ከጌታ ማዕድ አላጎድላትም።
(ግዛቸው ከበደ)
No comments:
Post a Comment