እስራኤል ሁሉ ይድናልን?
ሮሜ 11፥ 26 "እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል።"
ይህ መግለጫ ማስረጃውን ከቅዱሳት መጻህፍት ያደረገና ሊፈጸም የተገባው የተስፋ ቃል ነው፤ እንዴትና መቼ ነው የሚፈጸመው? የሚለው ግን መሰረታዊ ጥያቄ ነው። መልሱም የሚወሰነው ልንከተለው በመረጥነው የነገረ ፍጻሜ ምልከታችን አንጻር ነው።
ከተለያዩ ሥነ መለኮታዊ እይታዎችና አቋሞች ጋር የሚንጸባረቁ በርካታ ትርጓሜዎች ለዚህ ምንባብ እንደሚሰጡ ይታወቃል። በዋናነት የሚጠቀሱ አንዳንዶቹን ትርጉሞች ለማመላከት ያህል፦
"እስራኤል ሁሉ ይድናል" ማለት የሁሉም የእስራኤል ዘስጋ ሕዝብ/ ዘር/ ብሔረሰቦች ጥቅል መዳን ነው፣ የሚሉ አሉ። ይህ ግን ትክክለኛ ያልሆነ ትርጉም ነው። ምክንያቱም በስጋ እስራኤል የሆኑ ሁሉም እንዳሉ (ባዮሎጂካሊ) የሚድኑ ከሆነ ታዲያ ለአይሁድ ወንጌልን መስበክ ለምን ያስፈልጋል? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ኃጢአተኛም በዘሩ እየተመረጠ ይድናል ብሎ ማሰብና ማስተማርም ያፈጠጠ ኑፋቄ ብቻ ሳይሆን፣ በክርስቶስ መስቀል ላይ ማላገጥም ጭምር ነው። ስለዚህ ይህ አይነቱ የአፍቅሮተ እስራኤል እሳቤ ከመሰረቱ የፎረሸ ነው።
የአማኞች መዳን ነው፣ የሚሉም አሉ። ይህ ትርጉም በሁሉም የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ያሉትን በሥጋ አይሁድ የሆኑትንና መንፈሳዊ አይሁድ የሆኑትን አማኞች ይመለከታል። በዚህ እሳቤ ላይ ሊነሱ የሚችሉ መከራከርያ ነጥቦች አሉ፤ ከእነርሱም:-
# ይህ አቋም የእስራኤልን ምንነትና ትርጉም ይቀይራል የሚለው በዋናነት ይጠቀሳል። ይህም ማለት፣ "እንግዲህ፦ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? እላለሁ። አይደለም እኔ ደግሞ እስራኤላዊና ከአብርሃም ዘር ከብንያምም ወገን ነኝና።" (ሮሜ።11፥ 1) በሚለው መሰረት እስራኤልን በቁሙ (literal) ከማሰብ ይልቅ፣ "እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል።" (ሮሜ 11፥ 26) በሚለው መሰረት እስራኤልን በመንፈሳዊ ሁኔታ ወደመረዳት ያመጣናል፣ ማለት ነው። ይህም አይነቱ እስራኤልን በመንፈሳዊ ሁኔታ መረዳት ለጠቅላላው የአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ህዝብ ምንነትና ማንነት ተገቢና ተመራጭ ትርጉም ነው፤ ሆኖም "እስራኤል ሁሉ ይድናል" ማለት ግን በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በአለም ሁሉ ያሉ አማኞች ይድናሉ ማለት ነው ብሎ በዚህ መንገድ መረዳት የንባብ ክፍሉን አውድ ያስለቅቃል። ምክንያቱም በንባብ ክፍሉ የቀረበው ሙግት፣ የክርስቶስን ወንጌል በመግፋት ልባቸውን እልከኛ ስላደረጉ ስለ ጳውሎስ የስጋ ዘመዶች እጣ ፈንታ የተነገረ በመሆኑ ነው።
በሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ ላይ ስለሚሆን የአይሁድ ህዝብ ቅሬታ ደህንነት ነው፣ የሚሉም ደግሞ አሉ። ይህ አይነቱ የመጻኢነት እሳቤ ላይ የተንጠለጠለ አቋም በአብዛኛው የተቀዳው ከዌስት ሚንስቴር የእምነት መግለጫ አቋም ይመስላል። ያም ሆኖ ግን፣
# የሮሜ መልዕክት ከተጻፈ እነሆ ሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ያለፈው ሲሆን፤ ጳውሎስም በመልዕክቱ የሚያነሳቸው አይሁድ የገዛ ዘመኑን እስራኤል በመሆኑ እንዲህ ያለው ድምዳሜ ለጠቅላላው የሮሜ መልዕክት ፍሰት ባዕድ ትምህርት ይሆናል።
# አይሁድም ይቀኑ ዘንድ (ሮሜ 11፥ 1) በርካታ ዘመን /ጊዜ ነበራቸው። በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አይሁድ ቀናተኞች ነበሩ። አይሁድ ቤተክርስቲያንን እስከ ጥግ ሄደው ያሳደዱትም ከዚህ የተነሳ ነው።
በታላቁ መከራ ጊዜ ከመከራው የሚድኑ አይሁድ ናቸው፣ የሚሉም አሉ። ይህም እሳቤ፣ ታላቁ መከራ መቼ ነበር/ መቼስ ይሆናል? በሚል ስነ ፍጻሜአዊ ነጥብ ላይ በሚነሳ ክርክርና ክርክሩ በሚደርስበት ድምዳሜ ላይ የሚያርፍ ነው።
# የአይሁድ ሕዝብ ቅሬታ በ70 ዓ.ም ከሆነው ከኢየሩሳሌም ጥፋት በፊት ድነው ከነበረ፣ እንግዲያዉስ ታላቁ መከራ በዚያን ጊዜ ያለፈ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ኹነት ነበር ማለት ነው። ስለ ታላቁ መከራ ምንነትና መቼ ይሆናል ሲል መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ጥናት ዘርዘር አድርጌ ያቀረብሁበትን ጽሁፍ ለመመልከት ይህንን ሊንክ ይጠቀሙ:-
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/01/12.html?m=1
በቃል ኪዳኑ የሽግግር ዘመን ወቅት ኢየሩሳሌም እስከሚፈረድባትና መቅደስዋ ወድሞ እስኪፈራርስ ድረስ ይኖሩ የነበሩ የአይሁድ ሕዝብ ቅሬታዎች ናቸው፣ የሚልም ትርጉምና አቋም አለ።
# ይህ አይነቱ ትርጉምና መረዳት በንባብ ክፍላችን ላይ ያለውን ጊዜ የሚጠቁምና የሚያመለክት ነገር ስላለው፣ ከዚህ የተነሳ በወጉ ለሚያስቡና እንደ ቤሪያን ሰዎች ለሚጠይቁ የቃሉ ተማሪዎች የበለጠ ሥሜት ሊሰጥ የሚችል ትርጉም ነው፣ ለማለት ይቻላል። ማስረጃዎችን በቅደም ተተከተል እንይ፦
ሀ/ ጳውሎስ በእርሱ ዘመን ያሉትን አይሁድ ሲገልጣቸው:-
"እንደዚሁም በአሁን ዘመን ደግሞ በጸጋ የተመረጡ ቅሬታዎች አሉ።" (ሮሜ 11፥ 5) ይላል፤ ይህም ኤልያስ በገዛ ራሱ ዘመን ያሉትን ቅሬታዎች "ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።" (1ነገስት 19፥ 10) ሲል በገለጠበት መንገድ የሚታይ ነው። ነብዩ ኤልያስም ሆነ ቅዱስ ጳውሎስ በየራሳቸው ዘመን ስለነበሩ ስለትውልዳቸው ሰዎች ይናገራሉ እንጂ ስለሌላ ትውልድ ሰዎች እየተናገሩ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ጳውሎስ የሚለውን ቀጥላችሁ ተመልከቱ:-
"እንግዲህ፦ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? እላለሁ። አይደለም እኔ ደግሞ እስራኤላዊና ከአብርሃም ዘር ከብንያምም ወገን ነኝና።" (ሮሜ 11፥ 1) የገዛ ዘመኑን ትውልድ የተመለከተ ንግግር እንደሆነ ግልጽ ነው።
# ቅሬታው "በአሁን ዘመን" (ሮሜ11፥ 5) ላይ ተብሎ በተገለጠው የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ይኖር የነበረው ሕዝብ ነው -ያም የአሁን ዘመን የተባለው የጳውሎስና የሮሜ መልዕክት በኩረ ተደራስያን ዘመን ነው፣ እንጂ ሌላ የትኛውም ዘመን አይደለም።
# ጳውሎስ በወንጌል ስብከቱ በኩል ይድናሉ ብሎ ተስፋ ያደረገው ቅሬታም ያው የእርሱ ትውልድ አይሁድ ነበሩ፤ በርካቶቹ ደግሞ ያኔ በክርስቶስ አምነው የዳኑ ነበሩ (ሐዋ 2፥ 5-12፣ 37-41)
ለ/ በሮሜ 9-11 ባለው ክፍል የተጠቀሰ ከሺህዎች አመታት በኋላ የሚደርስ የወደፊት ጊዜ መከራም ሆነ ወይም "ከንጥቀት በኋላ" የተሰኘ ጊዜ ፈጽሞ የለም። ክፍሉ የማያወራውን ርዕሰ ጉዳይ ከሌለበት አምጥቶ መሰንቀር ስህተት ከመሆኑም በላይ ቃሉን "አስገድዶ" ማናገር ይሆናል። እንዲህ ያለውም ድፍረት ኑፋቄን ያዋልዳል።
ሐ/ ጳውሎስ ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹን ለማዳን በሚሆን ፍላጎትና ትጋት ለወንጌል እየሰራ ነበር
"ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ።" (ሮሜ 11፥ 13ና 14) ይላል፤ ሥለዚህም፦
♦ የሚናገረው በሺህ አመታት ስለሚቆጠር የወደፊት ጊዜ ሳይሆን እርሱ ስለነበረበትና ስላገለገለበት የአሁን ጊዜ ነው።
♦ ይህ የእስራኤል ሁሉ መዳን ተስፋ ገና ወደፊት ከ2000 ዓመታት በኋላ ቆይቶ የሚፈጸም ከሆነ ታዲያ የጳውሎስ አገልግሎት ምን ሊረዳ ይችላል?
# የአሁን ጊዜ አመልካች የሆኑ እነዚህ ንግግሮቹን ልብ ብለን ካየን ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ስለራሱ ዘመን የአይሁድ ሕዝብ ነው። ለምሳሌ "እንዲሁ በተማራችሁበት ምሕረት እነርሱ ደግሞ ምሕረትን ያገኙ ዘንድ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም።" (ሮሜ 11፥ 31) የሚለው ግልጽ የሆነ የአሁን ጊዜ ንግግር ነው።
መ/ በመጨረሻም፣ ከምንድን ነው የሚያድናቸው?
# የሚያድናቸው በ70 ዓ.ም ላይ ከሚፈጸምና በዚያን ወቅት በኢየሩሳሌም ላይ ሊመጣ ካለው ጥፋትና ፍርድ ነው። ሊመጣ ያለው ቁጣም፣ በከተማይቱ ኢየሩሳሌም ውድመት፣ በቤተመደሱ መደምሰስ፣ በአሮጌው ስርዓት እስከወዲያኛው መወገድ፣ ብሎም በጦርነቱና በወረራው የእስራኤል ህዝብ ላይ በሰይፍ ስለት የሚፈጸም ዕልቂትና ፍጅት እንዲሁም ለከፋ ባርነት በምርኮ መወሰድን ያካተተ ዘግናኝ ፍጻሜ ነው። ከዚህ ጥፋት የሚያመልጡት እግዚአብሔር ለደህንነት የመረጣቸውና በውድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የነበሩ ከጦርነቱ መቀስቀስ አስቀድሞ በከተማይቱ ላይ የሚመጣባትን አደጋ ከጌታ ትምህርት ተረድተው ፈጥነው ከተማይቱን ጥለው የወጡት ቅዱሳን ብቻ ናቸው። እነዚያማ የእግዚአብሔርን ልጅ ሰቅለው ቤተክርስቲያንን እስከ ጥግ በማሳደድ በተሰበከላቸው የምህረት ወንጌል ላይ ያላገጡና ንስሃ ያልገቡ ሁሉ አለቁ፣ በእናቱ ሆድ ካለው ጽንስ ጀምሮ እስከሽበታሙ ድረስ አንድም የተረፈና ያመለጠ አልነበረም።
እንደ ማጠቃለያ፦
♦ አንዳንዶች "እስራኤል ሁሉ" የሚለውን መግለጫ በቋንቋ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተለዋዋጭ የሚሆን ክስተትን እንደሚያመለክት የንግግር ዘይቤ (diachronic sense) ይረዱታል፤ ቋንቋው በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ ለውጦችን ጥናት የሚመለከት ነው። ማለትም በያዝነው ርዕሰ ጉዳይ፦
# "እስራኤል ሁሉ" የሚለው ሀረግ የሚያመለክተው በታሪክ ሁሉ ውስጥ ለሚኖሩና፣ ከትንሳኤ በኋላ ሊመጣ ባለው ዓለምም ተካፋይ ለሚሆኑና ለሚኖሩ የእስራኤል ሕዝብ አመልካች ነው ሲሉ፣ ከመንፈሳዊው እስራኤል ይልቅ በፍጥረታዊት እስራኤል ላይ ትኩረት አድርገው ይተረጉሙታል። ይህ እይታ ግን የተፈበረከውና originate የተደረገው በአይሁድ የሰዱቃውያን ሴክት school of thought ሲሆን፤ እግዚአብሔር እስራኤል እና ቤተክርስትያን የተሰኙ ሁለት ህዝቦች አሉት ብሎ፣ ለሁለቱም አንዱን በእምነት ሌላውን ያለ እምነት በዘሩ ምክንያት ያድነዋል ሲሉ እርስ በርሱ የተሉያየ የድነት መንገድ አለ ብሎ ከሚያምነውና ከሚያስተምረው ኑፋቄ ወለድ ከሆነው ከዲስፔንሴሽናሊዝም የአስተምህሮ ህጸጽ ተጽዕኖ የተነሳ በክርስቲያኑ አለም እንዲሰርጽ የተደረገ የክርስቲያን ጽዮናዊነት አስተሳሰብ ነው።
♦ ሌሎችም "እስራኤል ሁሉ" የሚለውን በ synchronic sense ማለትም በታሪክ ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ፣ በተለይም በነገረ ፍጻሜ (eschtological) መርሃ ግብር መሰረት በዘመን መጨረሻ ላይ ለሚኖረው ሕዝብ የተነገረ አድርገው ይወስዱታል።
# ይህ ሁለተኛው አማራጭ የነገረ ፍጻሜ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ተገድቦ፣ ቅዱሳት መጻህፍት በሚያውቁት የዘመኑ መጨረሻ ምንነትና ትርጉም ላይ እስካረፈና እስከታየ ድረስ ብቻ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረቱንና የሥነ ፍታቴ ቀዋሚነቱን የጠበቀ ተመራጭ ድምዳሜ ይሆናል።
ዳግላስ ሙ የተባሉ ጸሐፊ ይህንን በግልጽ ሲያስረዱ፣ "እስራኤል ሁሉ" የሚለው ሃረግ diachronic በሆነ መንገድ የምንረዳው አይደለም፤ ይህም ማለት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በድግግሞሽ እየተራዘመ የሚለዋወጥ ትርጉም የለውም፤ ከዚህም በላይ ይህ የሮሜ መልዕክት ምንባብ የክፍሉ አውድ የሚያወራው "እስራኤል መሲሁን እምቢ ብላ ስለመቃወምዋ እና የአህዛብ ሙላት እስኪሆን ድረስ ልቧን እልከኛ አድርጋ በድንዛዜ ውስጥ ስለመቆየትዋ ነው" ሲሉ ያብራራሉ። ስለዚህ በአንድ በተወሰነ የታሪክ ወቅት ገና ወደፊት እስራኤል ሁሉ ደህንነትን ይቀበላል ብሎ ማለት ከጠቅላላ አውደ ምንባቡ ጋር የማይሄድ ትርጉም ነው። የ1948ቷን ዘመናይት እስራኤል እያሰቡ "እስራኤል ሁሉ ይድናል" የሚለውን ትንቢታዊ የተስፋ ቃል ከጠቅላላ አውደ ምንባቡ ነጥሎ መረዳትም ቃሉ የማይለውን እንዲል "አስገድዶ" መተርጎም ይሆናል።
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/
No comments:
Post a Comment