የአህዛብ ሙላት
"ወንድሞች ሆይ፥ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ምሥጢር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ ድንዛዜ በእስራኤል በአንዳንድ በኩል ሆነባቸው፤" ሮሜ 11፥ 25
"የአህዛብ ሙላት" የሚሆነው፣ አህዛብ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ኪዳን ተካፋይ ለመሆን በወንጌል ካመኑት አይሁድ ጋር በክርስቶስ በኩል በታደለ ጸጋ እኩል በሆነ ስፍራና አቋቋም በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ሲያገኙ ነው። ይኸውም የሆነው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ በነበረው በዚያ የሽግግር ወቅት በአዲሱ ኪዳን ቤተክርስቲያን፣ እርሱም እግዚአብሔር በተከለውና ባጸደቀው በመልካሙ የወይራው ዛፍ ውስጥ በእምነት እንዲገቡ ሲደረግ ያኔ ነው። የመንግስት ወንጌል ደግሞ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎት መጀመር ጋር አስቀድሞ ለአይሁድ የተሰጣቸው ልዩ ዕድል እንደነበር ግልጽ ነው፤ "ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥"፣ ደግሞም "የእርሱ ወደሆነው መጣ" ተብሏልና።
ክርስቶስ መሲሁ የመጣው ለአይሁድ ነበር፣ ከእነርሱም መካከል ቅሬታዎች የነበሩት አመኑበት። እነርሱም ከአይሁድ ህዝብ መካከል በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ወቅት በተከናወነው በክርስቶስ የመጀመርያ በሥጋ መምጣት እና በኋላም በዳግመኛ የክብር ምጽአቱ መካከል በነበረው በሽግግሩ ወቅት መጀመሪያ ላይ የተመረጡ ሐዋርያት እና ደቀመዛሙርት ናቸው። ከዚያም ወንጌል ወደሰማርያውያን (ቅይጥ ዘሮች ወደሆኑት) ተስፋፍቶ በመጨረሻም ለአህዛብ ሁሉ ተዳረሰ።
"በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል" (ማቴዎስ 13፥ 15) እንደተባለ፣ የማያምኑት አይሁድ በመሲሁ እና በመልዕክተኞቹ ላይ ካሳዩት ግትርነት እና ከተሞሉት እምቢተኝነት የተነሳ፣ እነርሱ ሊቀበሉት ያልወደዱት ይህ የአዲሱ ኪዳን ወንጌል ለአህዛብ ደረሰላቸው። "ሂድ፥ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁ" (ሐዋ 22፥ 21) ተብሏልና። የዚህም ምስጢር እግዚአብሔር የአይሁድን ውድቀት ለአህዛብ ብልጥግናን የሚያመጣበት መንገድ አድርጎ መጠቀሙ ነው። አህዛብም የነበራቸው እምነት አይሁድን በቅናት ለማነሳሳት የቻለ ሲሆን ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ (ቅሬታዎች) መዳን ሆኖላቸዋል።
"ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ። የእነርሱ መጣል ለዓለም መታረቅ ከሆነ ከሙታን ከሚመጣ ሕይወት በቀር መመለሳቸው ምን ይሆን?" (ሮሜ 11፥ 13-15)
በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በተከናወነው የክርስቶስ የመጀመርያ መምጣትና በ70 አ.ም ላይ በተፈጸመው ዳግመኛ ምጽአቱ መካከል በነበሩት 40 ያህል የሽግግር አመታት ወቅት፣ ማለትም ለአንድ ትውልድ ዘመን፣ አማኞች ክርስቶስ ባደረገው የቤዛነት ስራ የተዋጁ ሆነው ነበር፤ ዳሩ ግን መዳናቸው በ70 አ.ም እስከሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፖሮዥያው ድረስ ገና ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀና ያበቃለት ደግሞ አልነበረም። ድነት ፍጻሜውን አግኝቶ በክብር የሚሞላው ጌታ ተመልሶ ሲመጣ ብቻ እንደሆነ ቃሉ ያስተምራል፤ ጌታ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ የማንም ሰው ድነት ፍጹም አይሆንምና። ስለዚህም እነዚያ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አማኞች እውነተኛ አማኞች መሆናቸውን እና እግዚአብሔር ተክሎ ባጸደቀው የወይራ ዛፍ ውስጥ የመቆየት መብት እንዳላቸው ለማረጋገጥ፣ በሚያልፉበት የስደትና የመከራ ልምምድ ውስጥ እንኳ ሆነው እየቃተቱ እስከ ዳግመኛ ምጽአቱ ድረስ በታማኝነት ጸንተው መቆም ነበረባቸው።
"እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ። እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና። አንተ በፍጥረቱ የበረሀ ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም?" (ሮሜ 11፥ 22-24)
ስለዚህ እግዚአብሔር ያመኑትን አህዛብ ከነበሩበት የበረሀ ወይራ አምጥቶ ወደመልካሙ ወይራ ወደ መንግስቱ አፈለሳቸው። እንዲሁም ደግሞ፣ ምንም እንኳ ከመነሻው ባለማመናቸው ምክንያት ተቆርጠው የቀሩ ቢሆኑም እንኳ፣ በዚያን ዘመን የመረጣቸውን የአይሁድ ቅሬታዎች ኋላ ላይ ንስሃ የገቡና በክርስቶስ ያመኑ ስለሆኑ እነርሱንም ወደ መንግስቱ አፈለሳቸው። ይህ ሁሉ የተከናወነው ያኔ የአዲሱ ኪዳን የመንግስት ወንጌል እየታወጀ ቤተክርስቲያኑ ትታነጽ በነበረበት ወቅት ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን አይሁድና አህዛብ ነው።
ክርስቶስ ለሆነው ለእግዚአብሔር እስራኤል የተሰጠውን የአብርሃምን የተስፋ ቃል ይወርሱ ዘንድ፣ የመንግስቱንም ቃል ኪዳናዊ በረከት ይቀበሉ ዘንድ፣ እግዚአብሔር በተከለውና ባጸደቀው መልካሙ የወይራ ዛፍ ውስጥ ገብተው የተጣበቁት መንፈሳዊ እስራኤል የሆኑ አማኞች ብቻ ናቸው። እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ይፋ አድርጎ የመረቀውና የከፈተው ለሚያምኑ አይሁድና፣ ደግሞም ለዘላለም ሕይወት ለተዘጋጁ ለሚያምኑ አህዛብ ሁሉና ብቻ ነው። የአህዛብ ሙላት ይህ ነው፣ እርሱም በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ የተፈጸመና የተሟላ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አግኝቷል (ሮሜ 11፥ 25)።
ለእስራኤል የተገባው የተስፋ ቃል ከዘላለም በእግዚአብሔር የተጠበቀ ነበር፣ ነገር ግን ተስፋው የተጠበቀው ታማኞች ለሆኑ የአይሁድ አማኝ ቅሬታዎች እና ከአህዛብ ወገን አማኝ ለሆኑ ጭምር ማለትም "መንፈሳዊ እስራኤል" ለሆኑት ብቻ ነው። የአዲሱ ኪዳን የክርስቶስ መንግስት እግዚአብሔር በተከለውና ባጸደቀው መልካሙ የወይራ ዛፍ ውስጥ እንደገና እንዲገቡ በተደረጉ አማኝ አይሁድና እግዚአብሔር ከበረሃ አምጥቶ ባስገባቸው ከአህዛብ ወገን በሆኑ አማኞች የተዋቀረ ነበር። እነዚህም ደግሞ በክርስቶስ አንድ የሆኑ "ክርስቲያኖች" ተብለው የሚጠሩ ሁሉ ናቸው። ይህም የአዲሱ ኪዳን መንፈሳዊው የወንጌል መንግስት በሙላት ተመስርቶ የተገለጠው በ70 አ.ም በዳግመኛ ምጽአቱ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ በመላው የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ቀጥሎ ሳይቋረጥ እየተሰበከ፣ ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ ላይዘጋ በተከፈተው በር በክርስቶስ በኩል ወደ ተገለጠው መንግስቱ በእምነትና በንስሃ ይገቡ ዘንድ በዘላለማዊ ድምቀት ወደፊት በክብር ሲያበራ ይኖራል።
"በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።" (ሮሜ 10፥ 12-13)
ቸር ያሰንብታችሁ።
(gkr)
No comments:
Post a Comment