የሥርየቱ መንገድ
ከአሮጌው ኪዳን በታች ተገዝቶ ይሰራ በነበረው የአይሁድ የኃይማኖት ሥርዓት፣ እግዚአብሔር ካህናቱን ያለማቋረጥ ስለ ህዝቡ ኃጢአት በቤተመቅደሱ የመጀመርያ ክፍል የማስተሰርያውን መስዋእት እንዲያቀርቡ ይጠይቃቸው ነበር። ይህም የእንስሶችን መስዋዕት እና የእንስሶችን ደም በእግዚአብሔር መሰዊያ ላይ በመርጨት የሚከናወን አምልኮተ ሥርዓትን የሚጨምር ነበር። (ለምሳሌ፦ ዘሌ 9፥ 7፣ 12፣ 18፣ 23-24)። እንደገናም በአመት አንድ ጊዜ በሥርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ ብቻ ለራሱና ለህዝቡ ኃጢያት የሚያቀርበውን የመስዋዕቱን ደም ይዞ ቅድስተ ቅድሳን ወደ ሚባለው ሁለተኛው ክፍል ወይም ወደ መቅደሱ ውስጥኛ ክፍል ይገባል።
"ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤" (ዕብራውያን 9፥ 6-7)
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የመጨረሻውን መስዋዕት ያቀረበ እውነተኛው ሊቀ ካህናት ነው። በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፣ ተቀበረም፣ ከመቃብርም ተነሳ። ከአርባ ቀናትም በኋላ ወደ ሰማይ አርጎ በሰማያት በምትገኘው ቅድስተ ቅዱሳን የማስተሰርያውን ሥራ አጠናቀቀ።
"ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው።" (ዕብራውያን 9፥ 14-15)
የክርስቶስ ደም እግዚአብሔር ለመረጣቸውና ለጠራቸው አማኞች የዘላለምን ሕይወት ተስፋ መቀበል ይችሉ ዘንድ ከኃጢአታቸው ሊነጹበት ለእግዚአብሔር የቀረበ ዘላለማዊው መስዋዕት ነው። የእርሱ ደም የመጨረሻ ማስተሰረያ ሆኖ ይቀርብ ዘንድ መፍሰሱ የግድ አስፈላጊ ነበር። አለበለዚያ ምንም አይነት ዘላልማዊ የኃጢአት ይቅርታና ሥርየት የሚባል ነገር አይኖርም።
"እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም።" (ዕብራውያን 9፥ 22)
ክርስቶስ የፈጸመው የማስተስረያ ስራ ተጠናቆ የተፈጸመው፣ ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ በሚጠራው በሰማያዊው መቅደስ በመጋረጃው ውስጥ ነው። (ዕብራውያን 9፥ 3) የአይሁድ ሊቀ ካህናት በምድራዊው ቤተመቅደስ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በየአመቱ የእንስሶችን ደም ይዞ በመግባት እንደሚያደርገው አይነት ራሱን ብዙ ጊዜ ምስዋእት ማድረግ አላስፈለገውም።
" እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነጻ እንጂ በሰማያት ያሉቱ ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።" (ዕብራውያን 9፥ 23-26)
ጌታ ኢየሱስ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ይኸውም በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ለኃጢአት ማስተሰረያ የሚሆነውን ስራ አከናውኖአል። ሆኖም ግን የህዝቡ ሁሉ ድነት እና በእግዚአብሔር ሀልዎት ፊት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ ለመቅረብ ያላቸው ዘላለማዊ ድፍረት ሁለት ነገሮች በይፋ እስኪከናወኑ ድረስ ገና ወደፊት ይጠብቅ ነበር።
የመጀመርያው፣ እርሱ የፈጸመው የማስተሰርያ ስራ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን እንዳገኘ ያሳይ ዘንድ ለነዚያ ያድናቸው ዘንድ ይጠባበቁት ለነበሩ ምዕመናን ሁለተኛ ጊዜ ተመልሶ መምጣት ነበረበት። የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት በአመት አንድ ጊዜ የመስዋእቱን ደም ይዞ ሊያስተሰርይላቸው፣ እግዚአብሔር እገኝበታለሁ ወዳለው ሥፍራ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ግብቶ ያቀረበው መስዋዕት ተቀባይነት እንዳገኘ ለመግለጥ በአውደ ምህረቱ ላይ ሊታይ ተመልሶ እንደሚወጣ ሁሉ፣ እንዲሁ ኢየሱስ ይህንን ያከናወነው በ70 ዓም በዳግመኛ ምጽአቱ ነው። "እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (ዕብራውያን 9፥ 28)፤ እነዚህ ይጠባበቁት የነበሩ በትውልዳቸው ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣ የተነገራቸው የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ምዕመና ናቸው። ኢየሱስ እንደተስፋ ቃሉ ያኔውኑ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ተመልሶ ካልመጣ ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመቅረብና ለመግባት ገና የማይቻል ነው፣ ገናም በአሮጌው የሙሴ ሥርዓት ስር ተገዝተን አለን፣ እግዚአብሔር የክርስቶስን መስዋዕት እንደተቀበለውም ሆነ በአጠቃላይ ስለ መዳናችን እርግጠኞች መሆን አንችልም ማለት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ፣ ያ የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ፈራርሶ መጥፋት ነበረበት። ይህንንም እንደ ትንቢቱ ቃል ያከናወነው ያንን በኢየሩሳሌም የነበረውን ምድራዊ ቤተ መቅደስ በ70 አም ያጠፉት ዘንድ በአህዛብ እጅ አሳልፎ በመስጠት ነው። "ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።" (ዕብራውያን 9፥ 8)። ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ይገለጥ ዘንድ ያቺ ድንኳን መውደቋ ቅድመ ሁኔታ ነበር ማለት ነው።
"ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፥ እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ፤ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም።" (ዕብራውያን 9፥ 9-10)
(gkr)
No comments:
Post a Comment