Tuesday, July 9, 2019

የእግዚአብሔር መንግስት

የእግዚአብሔር መንግስት
የአዲሱ ኪዳን የእግዚአብሔር መንግስት በይፋ ለአለም የተዋወቀው በክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት በስጋው ወራት በምድር ላይ በነበረው የአገልግሎት ቆይታ ነው። ይህ የእግዚአብሔር መንግስት አንዳንዴም መንግስተ ሰማያት ደግሞም የክርስቶስ መንግስት እና የፍቅሩ ልጅ መንግስት እየተባለ በተለዋጭ ሲጠራ ይስተዋላል። ይህ መንግስት የመሲሁን፣ የእግዚአብሔርን ልጅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ አለም በስጋ መምጣት ጨምሮ የተነገረለት መንግሥት ነው። ይህ መንግስት በመጀመርያ የተነገረው መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ ባቀረበው ስብከቱ ነው፤ እርሱም "መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ።" (ማቴዎስ 3፥ 1- 2) ይላል። ዮሐንስ "ቀርባለች" ሲል ያስተዋወቃት የሰማይ መንግስት በንስሃ የሚቀበሏትና የሚገቡባት መንግስት ናት። የዮሐንስን ታልፎ መሰጠት ተከትሎ "ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር" (ማቴዎስ 4፥ 17)፣ ሲሉ ወንጌላውያኑም ይነግሩናል።

ይህ የአዲሱ ኪዳን የእግዚአብሔር መንግስት ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከመሞቱ አስቀድሞ ለአይሁድ ያስተምራቸው በነበረበት ጊዜ ያኔ ገና ለማደግ በጅማሬው ላይ ነበር። የዚህ መንግስት ፍጹማዊ ሙላትና አገዛዙ የሚሰፍነው በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ላይ እንደሆነ ቃሉ በግልጽ ያስተምራል፣ ይህም የአብዛኛው ክርስቲያኖች እምነት ነው፤ በአመዛኙ ልዩነቱ ያለው ለዳግመኛ ምጽአቱ ተፈጻሚ መሆን የተቀጠረውንና የተወሰነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የጊዜ ማእቀፍ በመረዳትና በመተርጎሙ ላይ ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት መጻህፍት ገለጻ፣ ጌታ ኢየሱስ "እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ" (ማቴዎስ 16፥ 28) ብሎ ሲያስታውቅና፣ ደግሞም "እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" (ማቴዎስ 24፥ 34) ሲል እንዳስተማረውና፣ ሐዋርያቱም በተደጋጋሚ እንዳስተማሩት ከሆነ፣ የዳግመኛ ምጽአቱ ኹነት ፍጻሜ ከኢየሩሳሌም ከተማ መፈራረስና ከቤተ መቅደሱ መደምሰስ ጋር የተያያዘ ነው፤ እነርሱም ጌታ በነገራቸው የተስፋ ቃል ላይ ቆመው፣ በትውልዳቸውና በዘመናቸው እንደሚሆን ሲናፍቁትና ሲጠባበቁት የነበረው ዋና ጉዳይ ይኸው የጌታ የዳግሙኛ ምጽአቱ ፓሮዥያውን ነበር። ይህንንም ከእስራኤል ቤዛነትና ከአሮጌው የሙሴ ስርአት መወገድ ጋር አያይዘው ይረዱት ነበር።  ይህ ደግሞ የሆነው የዚያ አሮጌ ስርዓት ማእከልና መገለጫ የሆነው ቤተመቅደስ ፈጽሞ ሲደመሰስና ሲጠፋ፣ ከተማይቱም በእሳት ስትቃጠልና ሕዝቡም በሰይፍ ሲወድቁና ለባርነት ሲማረኩ በ70 ዓም ላይ በሆነባቸው ፍርድ ነው። የክርስቶስ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው በ70 አም ላይ እስኪሆን ድረስ ታዲያ መንግስቱ ገና በሙላት አልተመሰረተም ነበር።

ይህ የእግዚአብሔር መንግስት መንፈሳዊ መንግስት እንጂ፣ ተዳሳሽ መንግስት አለመሆኑን "መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም" (ዮሐንስ 18፥ 36) ሲል ኢየሱስ በግልጽ ተናግሯል። "ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው።" (ሉቃስ 17፥ 20- 21) ተብሎ እንደተጻፈ፤ በእምነት በኩል በክርስቶስ በሆኑቱ ሁሉና ዳግመኛ ተወልደው የእርሱ ምርጦች በሆኑት ምዕመናንን ውስጥ የሚኖር መንፈሳዊ መንግስት፣ የእግዚአብሔር አገዛዝ ነው እንጂ፣ እዚህ አለም ላይ በሚታወቅ በየትኛውም ፖለቲካዊ አገዛዝ የሚለካና የሚተረጎም መንግስት አይደለም። በመንግሥቱ በሚኖር በእያንዳንዱ ዳግም በተወለደ አማኝ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አድሮበታል።
ስለዚህም "ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን" (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 13) እንደተባለ፤ በመንግሥቱ ውስጥ የሚገኘው ጽድቅ ብቻ ነው፣ እንጂ አመጽ የለበትም። ምክንያቱም፣ "የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥" (ማቴዎስ 13 ፥40) ሲል፣ እንደ ተስፋ ቃሉ ይጠበቅ የነበረው ጽድቅ የሚኖርበት  አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይኸውም መንግሥቱ በዳግመኛ ምጽአቱና በፍርዱ ከክፉዎችና ከአመጻ የሚጸዳ መሆኑን ያሳያል። ክፋት የሚለቀመው "ከመንግስቱ" ነው እንጂ ከግዑዙ አለም ላይ አለመሆኑን እናስተውላለን። መንግስቱ ደግሞ ከዚህ አለም አይደለችም። ክርስቶስ በዳግመኛ ምጽዓቱ በዙፋኑ ሆኖ የነገሰባትና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ለዘላለም የሚገዛባት፣ ጽድቅና ቅድስና የሰፈነባት፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ኃሴትና ደስታ የሞላባት መንግስቱ፣ እደግመዋለሁ፣ እዚህ ተዳሳሹ አለም ላይ ካለ ከየትኛውም ሥጋዊና ነባራዊ የሰው ስርአት ጋር እናስተያያት ዘንድ የሚመጥናትና የሚገልጣት ምንም አምሳያ የላትም። እርስዋ የሰማይ መንግስት ናት። የምድር ላይ ኃያላን በምድራዊው መንግስታቸው የለበሱትን ካባ እና በራሳቸው ላይ የደፉትን ዘውድ፣ የተቀመጡበትን ዙፋንና የሚሰጡትን ፍርድና ዳኝነት ስንራቀቅ ውለን ብናድርበት፣ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ጋር ሆኖ በሚገዛበት በሰማያዊው መንግስቱ ካለው ግርማና ክብር ጋር ሊጠጋጋ ቀርቶ ምሳሌ ለመሆን እንኳ አይበቃም።

መንግስቱን ልንረዳውና ልናስተውለው የምንችለው የክርስቶስ አካል ተብላ በምትጠራዋና በማትታየዋ ሉል አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ባህርይና ተፈጥሮ ውስጥ ነው እንጂ፣ በሚታይና በሚዳሰስ የትኛውም ምድራዊና አለማዊ አደረጃጀት ውስጥ አይደለም። እርስዋም የብሉይ ኪዳንዋን እስራኤል ዘስጋን የተካቻት እውነተኛዋ የእግዚአብሔር እስራኤል፣ የእግዚአብሔር መንግስት ናት። እግዚአብሔርም በአብርሃም በኩል ለእስራኤል የሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ "አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚማላ የእርሱ ሙላቱ" በሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያኑ ውስጥ በክርስቶስ ፍጻሜውን አግኝቷል። መቼም ቢሆን ከነገድና ከቋንቋ ከህዝብም ተዋጅተው፣ በጽድቅና በጸጋ ተጠርተው የገቡባትን፣ መንግስቱና ግዛቱ ሊሆኑ የተመረጡቱ ቅዱሳን የሚኖሩባትን፣ እውነተኛዋን እስራኤልን ሊገልጣት የሚችለው ኪዳን ነው እንጂ ዘር አይደለም።

ይህ መንግስት ተፈጥሮው መንፈሳዊ ሲሆን፣ የወንጌል እና የክርስቲያን መንግስትም ነው፣ እንጂ ተዳሳሽ የሆነ፣ የሙሴ ሕግና የአይሁድ መንግስት አይደለም። ይህ በአሮጌው ሰማይ የተወከለው የአሮጌው ኪዳን ህጎች ሁሉ፣ መስዋአቶቹ፣ ኃይማኖታዊ ስርዓቶቹ፣ ልዩ ልዩ በአላቱ እና የበአላቱ ቀኖች ሁሉ፣ ከዚህ በአሮጌው ምድር ከተወከለውና በ70 አም ላይ ፍጻሜውን ካገኘው የእስራኤል ሕዝብ ውድመት፣ የኢየሩሳሌም ከተማ ጥፋት እና የመቅደሱ መደምሰስ ጋር ዳግም ላይታሰቡ በክርስቶስ ፍርድ እንዲያልፉ ተደርገዋል። በትንቢታዊ ገለጻቸው "ሰማይ እና ምድር" የሚወክሉት ኪዳንን ነው እንጂ በቁሙ አይተረጎሙም።

ያኔም በ70 አም ላይ አሮጌውን ሰማይና አሮጌውን ምድር በማስወገድ፣ በፍጥረቱ መንፈሳዊ የሆነው የአዲሱ ኪዳን ወንጌል ዘላለማዊው መንግስት፣ በሙላት ተመስርቷል፣ ይህም የእግዚአብሔር ፍጹማዊ አገዛዝ፣ በምድር ላይ በሚኖረው የሰው ልጆች ታሪክ ሁሉ ውስጥ፣ በተፈጠረው አዲሱ ሰማይ እና አዲሱ ምድር ሳይቋረጥ መግዛቱን ይቀጥላል። ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ መንግስት ንጉስና ገዢ፣ የምድርም ነገስታት ሁሉ ገዢ መሆኑ ለአለምና ለዘላለም እየታወጀ፣ በውጭ ያሉ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ በእምነትና በንስሃ ወደማይዘጋው ወደ ፍቅሩ ልጅ የጸጋ መንግስ እንዲገቡ ለትውልድ ሁሉ ጥሪና ግብዣ እየተደረገ አለም ይቀጥላል። መንግስቱ በምድርም በሰማይም የሚቀጥል መንግስት ነው። የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለከልካይ በሰማይ እንደሆነች በምድርም ደግሞ ናት፣ (ማቴዎስ 6፥ 10፤ ሉቃስ 11፥ 2)።

ማስታወሻ፦ ይህ ጽሁፍ ዘርዘር ብሎና በበርካታ የቅድሳት መጻህፍት ማገናዘቢያ ጥቅሶች ላይ ተመስርቶ ካዘጋጀሁት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ተጨልፎ የተወሰደ እጥጥር ሲሆን፣ ጌታ ፈቅዶ ጊዜ ከሰጠኝ ትምህርቱን አደራጅቼ በአንድ ወይም በሁለት ክፍል በስፋት እመለስበታለሁ። እስከዚያው ግን እንደ ፕሪቴሪስት ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምን እንደምናምን እና እንደምናስተምር በዚህች አጭር ክትባት በመጠኑ መረዳት ይቻላል። ተጨማሪ የነገረ ፍጻሜ ትምህርት የሚቀርብበትን philologus66 የተሰኘውን የፌስ ቡክ ገጽ እና http://gizachewkr.blogspot.com/ የተሰኘውን ብሎገር እንድትጎበኙ ግብዣዬ ነው።
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/

No comments:

Post a Comment