በክርስቶስ ማመን ብቻ!
እግዚአብሔር በውድ ልጁ ምትካዊ ሕይወትና ሞት በኩል አለሙን ሁሉ ከራሱ ጋር ያስታረቀ መሆኑ በወንጌሉ የሚሰበከው የምሥራች ነው። ኃጢአተኞችም ሁሉ አምነው ይድኑበት ዘንድ ይህ በክርስቶስ የተገለጠው የማስታረቅ ስራ ለሰዎች ሁሉ ያለ ገደብ እንዲታወጅ በወንጌሉ ያዘዘ መሆኑም የታመነ ነው። እነሆ እግዚአብሔር በክርስቶስ በገለጠው የእርቅ ወንጌል ለሚያምኑ በደል አይቆጠርም። መታዘዝም ጽድቅ ሆኖ የሚቆጠር የእምነት መታዘዝ ብቻ ነው።
"ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።" (2 ቆሮ 5÷ 18፣ 19)
"በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤" (ሮሜ 1፥ 5)
"ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።......ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው" (ሮሜ 4፥ 5፣ 24-25)
ስለዚህም ከእግዚአብሔር ጋር በግል እርቅን ለማድረግ፣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታን ለማግኘት በክርስቶስ ማመን ለኃጢአተኛ ሰው ብቸኛው መንገድ መሆኑን የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ሁሉም ቅዱሳት መጻህፍት በግልጽ ይመሰክራሉ፣
" በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።"(ሐዋ 10፥ 43)
"በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።...በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።"(ዮሐ 3፥ 16-18፣ 36)
ለመዳን ሌላ ተለዋጭና አማራጭ መንገድ የለም፣ ይህም በወንጌሉ የተገለጠው የድነት መንገድ የመለኮት ድንጋጌ ነው፤ ሳናፍርበት ለታላቁም ለታናሹም የምንሰብከው የክብር ወንጌል ነው እንጂ እኛ ይምናካብደው ወይም የምናከረው ኃይማኖታዊ ጉዳይ አይደለም። ሰዎች የኃጢአት ይቅርታን በሚያገኙበት በክርስቶስ በሆነው በዚህ እምነት ብቻ ይድናሉ ማለት የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትሎ የአምላክን ሕግ ለመፈጸም በሚደረግ ማናቸውም የሰው ጥረትና ኃይማኖታዊ ሙከራ ይድናሉ ማለት አይደለም። ሰዎችን ከኃጢአታቸው እንዲድኑ የምንመክረውን ያህል ለመጽደቅ ከሚያደርጉትም ኃይማኖታዊ ሙከራ እንዲድኑ በወንጌሉ ቃል አጥብቀን እንመክራለን። በወንጌሉ ማመን ይለያል፣ ይኸውም ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ በተሰጠንና በወንጌሉ በቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ወይም ጽድቅ ማመን ብቻ ነው፣ አለቀ! በክርስቶስ ማመን እግዚአብሔር በታሪካችን ውስጥ ሊገኝ እርሱ ወደ እኛ የመጣበት ራሱ ያዘጋጀውና የጀመረ ቀልብ ለድነታችን የሚሆን የእምነት መንገድ ነው እንጂ እኛ ወደ እርሱ ለመድረስ የምንኳትንበት አስቸጋሪ መንገድ አይደለም። ይህም እምነት የሚያጸድቀው ጸጋው ባቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ላይ ብቻ ሙሉ በሙሉ ባረፈ መጠን ነው እንጂ እምነት በራሱ የሰው ሥራና ሙከራ በሆነ መጠን አይደለም። ሐዋርያው ሲጽፍ "ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤" (ሮሜ 4፥ 16) ይላል። ጥረት ሆይ ምንኛ መላላጥ ሆንሽብኝ? በይ ኃይማኖተኝነት ደህና ሰንብች።
(ቄስ ግዛቸው ከበደ)
No comments:
Post a Comment