በክርስቶ ማመን ብቻ!
እግዚአብሔር በውድ ልጁ ምትካዊ ሕይወትና ሞት በኩል አለሙን ሁሉ ከራሱ ጋር ያስታረቀ መሆኑ በወንጌሉ የሚሰበከው የምሥራች ነው። ኃጢአተኞችም ሁሉ አምነው ይድኑበት ዘንድ ይህ በክርስቶስ የተገለጠው የማስታረቅ ስራ ለሰዎች ሁሉ ያለ ገደብ እንዲታወጅ በወንጌሉ ያዘዘ መሆኑም የታመነ ነው። እነሆ እግዚአብሔር በክርስቶስ በገለጠው የእርቅ ወንጌል በደል አይቆጠርም። መታዘዝም ጽድቅ ሆኖ የሚቆጠር የእምነት መታዘዝ ብቻ ነው።
"ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።" (2 ቆሮ 5÷ 18፣ 19)
"በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤" (ሮሜ 1፥ 5)
"ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።......ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው" (ሮሜ 4፥ 5፣ 24-25)
ስለዚህም ከእግዚአብሔር ጋር በግል እርቅን ለማድረግ፣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታን ለማግኘት በክርስቶስ ማመን ለኃጢአተኛ ሰው ብቸኛው መንገድ መሆኑን የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ሁሉም ቅዱሳት መጻህፍት በግልጽ ይመሰክራሉ፣
" በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።"(ሐዋ 10፥ 43)
"በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።...በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።"(ዮሐ 3፥ 16-18፣ 36)
ለመዳን ሌላ ተለዋጭና አማራጭ መንገድ የለም፣ ይህም በወንጌሉ የተገለጠው የድነት መንገድ የመለኮት ድንጋጌ ነው፤ ሳናፍርበት ለታላቁም ለታናሹም የምንሰብከው የክብር ወንጌል ነው እንጂ እኛ ይምናካብደው ወይም የምናከረው ኃይማኖታዊ ጉዳይ አይደለም። ሰዎች የኃጢአት ይቅርታን በሚያገኙበት በክርስቶስ በሆነው በዚህ እምነት ብቻ ይድናሉ ማለት የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትሎ የአምላክን ሕግ ለመፈጸም በሚደረግ ማናቸውም የሰው ጥረትና ኃይማኖታዊ ሙከራ ይድናሉ ማለት አይደለም። ሰዎችን ከኃጢአታቸው እንዲድኑ የምንመክረውን ያህል ለመጽደቅ ከሚያደርጉትም ኃይማኖታዊ ሙከራ እንዲድኑ በወንጌሉ ቃል አጥብቀን እንመክራለን። በወንጌሉ ማመን ይለያል፣ ይኸውም ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ በተሰጠንና በወንጌሉ በቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ወይም ጽድቅ ማመን ብቻ ነው፣ አለቀ! በክርስቶስ ማመን እግዚአብሔር በታሪካችን ውስጥ ሊገኝ እርሱ ወደ እኛ የመጣበት ራሱ ያዘጋጀውና የመረቀልን ለድነታችን የሚሆን የእምነት መንገድ ነው እንጂ እኛ ወደ እርሱ ለመድረስ የምንኳትንበት አስቸጋሪ መንገድ አይደለም። ይህም እምነት የሚያጸድቀው ጸጋው ባቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ላይ ብቻ ሙሉ በሙሉ ባረፈ መጠን ነው እንጂ እምነት በራሱ የሰው ሥራና ሙከራ በሆነ መጠን አይደለም። ሐዋርያው ሲጽፍ "ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤" (ሮሜ 4፥ 16) ይላል። ጥረት ሆይ ምንኛ መላላጥ ሆንሽብኝ? በይ ኃይማኖተኝነት ደህና ሰንብች። (ቄስ ግዛቸው ከበደ)
Wednesday, July 31, 2019
በክርስቶስ ማመን ብቻ
Saturday, July 20, 2019
የሥርየቱ መንገድ
የሥርየቱ መንገድ
ከአሮጌው ኪዳን በታች ተገዝቶ ይሰራ በነበረው የአይሁድ የኃይማኖት ሥርዓት፣ እግዚአብሔር ካህናቱን ያለማቋረጥ ስለ ህዝቡ ኃጢአት በቤተመቅደሱ የመጀመርያ ክፍል የማስተሰርያውን መስዋእት እንዲያቀርቡ ይጠይቃቸው ነበር። ይህም የእንስሶችን መስዋዕት እና የእንስሶችን ደም በእግዚአብሔር መሰዊያ ላይ በመርጨት የሚከናወን አምልኮተ ሥርዓትን የሚጨምር ነበር። (ለምሳሌ፦ ዘሌ 9፥ 7፣ 12፣ 18፣ 23-24)። እንደገናም በአመት አንድ ጊዜ በሥርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ ብቻ ለራሱና ለህዝቡ ኃጢያት የሚያቀርበውን የመስዋዕቱን ደም ይዞ ቅድስተ ቅድሳን ወደ ሚባለው ሁለተኛው ክፍል ወይም ወደ መቅደሱ ውስጥኛ ክፍል ይገባል።
"ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤" (ዕብራውያን 9፥ 6-7)
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የመጨረሻውን መስዋዕት ያቀረበ እውነተኛው ሊቀ ካህናት ነው። በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፣ ተቀበረም፣ ከመቃብርም ተነሳ። ከአርባ ቀናትም በኋላ ወደ ሰማይ አርጎ በሰማያት በምትገኘው ቅድስተ ቅዱሳን የማስተሰርያውን ሥራ አጠናቀቀ።
"ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው።" (ዕብራውያን 9፥ 14-15)
የክርስቶስ ደም እግዚአብሔር ለመረጣቸውና ለጠራቸው አማኞች የዘላለምን ሕይወት ተስፋ መቀበል ይችሉ ዘንድ ከኃጢአታቸው ሊነጹበት ለእግዚአብሔር የቀረበ ዘላለማዊው መስዋዕት ነው። የእርሱ ደም የመጨረሻ ማስተሰረያ ሆኖ ይቀርብ ዘንድ መፍሰሱ የግድ አስፈላጊ ነበር። አለበለዚያ ምንም አይነት ዘላልማዊ የኃጢአት ይቅርታና ሥርየት የሚባል ነገር አይኖርም።
"እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም።" (ዕብራውያን 9፥ 22)
ክርስቶስ የፈጸመው የማስተስረያ ስራ ተጠናቆ የተፈጸመው፣ ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ በሚጠራው በሰማያዊው መቅደስ በመጋረጃው ውስጥ ነው። (ዕብራውያን 9፥ 3) የአይሁድ ሊቀ ካህናት በምድራዊው ቤተመቅደስ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በየአመቱ የእንስሶችን ደም ይዞ በመግባት እንደሚያደርገው አይነት ራሱን ብዙ ጊዜ ምስዋእት ማድረግ አላስፈለገውም።
" እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነጻ እንጂ በሰማያት ያሉቱ ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።" (ዕብራውያን 9፥ 23-26)
ጌታ ኢየሱስ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ይኸውም በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ለኃጢአት ማስተሰረያ የሚሆነውን ስራ አከናውኖአል። ሆኖም ግን የህዝቡ ሁሉ ድነት እና በእግዚአብሔር ሀልዎት ፊት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ ለመቅረብ ያላቸው ዘላለማዊ ድፍረት ሁለት ነገሮች በይፋ እስኪከናወኑ ድረስ ገና ወደፊት ይጠብቅ ነበር።
የመጀመርያው፣ እርሱ የፈጸመው የማስተሰርያ ስራ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን እንዳገኘ ያሳይ ዘንድ ለነዚያ ያድናቸው ዘንድ ይጠባበቁት ለነበሩ ምዕመናን ሁለተኛ ጊዜ ተመልሶ መምጣት ነበረበት። የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት በአመት አንድ ጊዜ የመስዋእቱን ደም ይዞ ሊያስተሰርይላቸው፣ እግዚአብሔር እገኝበታለሁ ወዳለው ሥፍራ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ግብቶ ያቀረበው መስዋዕት ተቀባይነት እንዳገኘ ለመግለጥ በአውደ ምህረቱ ላይ ሊታይ ተመልሶ እንደሚወጣ ሁሉ፣ እንዲሁ ኢየሱስ ይህንን ያከናወነው በ70 ዓም በዳግመኛ ምጽአቱ ነው። "እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (ዕብራውያን 9፥ 28)፤ እነዚህ ይጠባበቁት የነበሩ በትውልዳቸው ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣ የተነገራቸው የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ምዕመና ናቸው። ኢየሱስ እንደተስፋ ቃሉ ያኔውኑ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ተመልሶ ካልመጣ ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመቅረብና ለመግባት ገና የማይቻል ነው፣ ገናም በአሮጌው የሙሴ ሥርዓት ስር ተገዝተን አለን፣ እግዚአብሔር የክርስቶስን መስዋዕት እንደተቀበለውም ሆነ በአጠቃላይ ስለ መዳናችን እርግጠኞች መሆን አንችልም ማለት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ፣ ያ የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ፈራርሶ መጥፋት ነበረበት። ይህንንም እንደ ትንቢቱ ቃል ያከናወነው ያንን በኢየሩሳሌም የነበረውን ምድራዊ ቤተ መቅደስ በ70 አም ያጠፉት ዘንድ በአህዛብ እጅ አሳልፎ በመስጠት ነው። "ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።" (ዕብራውያን 9፥ 8)። ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ይገለጥ ዘንድ ያቺ ድንኳን መውደቋ ቅድመ ሁኔታ ነበር ማለት ነው።
"ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፥ እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ፤ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም።" (ዕብራውያን 9፥ 9-10)
(gkr)
በክርስቶስ ማመን ብቻ
በክርስቶስ ማመን ብቻ!
እግዚአብሔር በውድ ልጁ ምትካዊ ሕይወትና ሞት በኩል አለሙን ሁሉ ከራሱ ጋር ያስታረቀ መሆኑ በወንጌሉ የሚሰበከው የምሥራች ነው። ኃጢአተኞችም ሁሉ አምነው ይድኑበት ዘንድ ይህ በክርስቶስ የተገለጠው የማስታረቅ ስራ ለሰዎች ሁሉ ያለ ገደብ እንዲታወጅ በወንጌሉ ያዘዘ መሆኑም የታመነ ነው። እነሆ እግዚአብሔር በክርስቶስ በገለጠው የእርቅ ወንጌል ለሚያምኑ በደል አይቆጠርም። መታዘዝም ጽድቅ ሆኖ የሚቆጠር የእምነት መታዘዝ ብቻ ነው።
"ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።" (2 ቆሮ 5÷ 18፣ 19)
"በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤" (ሮሜ 1፥ 5)
"ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።......ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው" (ሮሜ 4፥ 5፣ 24-25)
ስለዚህም ከእግዚአብሔር ጋር በግል እርቅን ለማድረግ፣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታን ለማግኘት በክርስቶስ ማመን ለኃጢአተኛ ሰው ብቸኛው መንገድ መሆኑን የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ሁሉም ቅዱሳት መጻህፍት በግልጽ ይመሰክራሉ፣
" በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።"(ሐዋ 10፥ 43)
"በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።...በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።"(ዮሐ 3፥ 16-18፣ 36)
ለመዳን ሌላ ተለዋጭና አማራጭ መንገድ የለም፣ ይህም በወንጌሉ የተገለጠው የድነት መንገድ የመለኮት ድንጋጌ ነው፤ ሳናፍርበት ለታላቁም ለታናሹም የምንሰብከው የክብር ወንጌል ነው እንጂ እኛ ይምናካብደው ወይም የምናከረው ኃይማኖታዊ ጉዳይ አይደለም። ሰዎች የኃጢአት ይቅርታን በሚያገኙበት በክርስቶስ በሆነው በዚህ እምነት ብቻ ይድናሉ ማለት የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትሎ የአምላክን ሕግ ለመፈጸም በሚደረግ ማናቸውም የሰው ጥረትና ኃይማኖታዊ ሙከራ ይድናሉ ማለት አይደለም። ሰዎችን ከኃጢአታቸው እንዲድኑ የምንመክረውን ያህል ለመጽደቅ ከሚያደርጉትም ኃይማኖታዊ ሙከራ እንዲድኑ በወንጌሉ ቃል አጥብቀን እንመክራለን። በወንጌሉ ማመን ይለያል፣ ይኸውም ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ በተሰጠንና በወንጌሉ በቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ወይም ጽድቅ ማመን ብቻ ነው፣ አለቀ! በክርስቶስ ማመን እግዚአብሔር በታሪካችን ውስጥ ሊገኝ እርሱ ወደ እኛ የመጣበት ራሱ ያዘጋጀውና የጀመረ ቀልብ ለድነታችን የሚሆን የእምነት መንገድ ነው እንጂ እኛ ወደ እርሱ ለመድረስ የምንኳትንበት አስቸጋሪ መንገድ አይደለም። ይህም እምነት የሚያጸድቀው ጸጋው ባቀረበልን የኃጢአት ይቅርታ ላይ ብቻ ሙሉ በሙሉ ባረፈ መጠን ነው እንጂ እምነት በራሱ የሰው ሥራና ሙከራ በሆነ መጠን አይደለም። ሐዋርያው ሲጽፍ "ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤" (ሮሜ 4፥ 16) ይላል። ጥረት ሆይ ምንኛ መላላጥ ሆንሽብኝ? በይ ኃይማኖተኝነት ደህና ሰንብች።
(ቄስ ግዛቸው ከበደ)
Tuesday, July 9, 2019
የእግዚአብሔር መንግስት
የእግዚአብሔር መንግስት
የአዲሱ ኪዳን የእግዚአብሔር መንግስት በይፋ ለአለም የተዋወቀው በክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት በስጋው ወራት በምድር ላይ በነበረው የአገልግሎት ቆይታ ነው። ይህ የእግዚአብሔር መንግስት አንዳንዴም መንግስተ ሰማያት ደግሞም የክርስቶስ መንግስት እና የፍቅሩ ልጅ መንግስት እየተባለ በተለዋጭ ሲጠራ ይስተዋላል። ይህ መንግስት የመሲሁን፣ የእግዚአብሔርን ልጅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ አለም በስጋ መምጣት ጨምሮ የተነገረለት መንግሥት ነው። ይህ መንግስት በመጀመርያ የተነገረው መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ ባቀረበው ስብከቱ ነው፤ እርሱም "መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ።" (ማቴዎስ 3፥ 1- 2) ይላል። ዮሐንስ "ቀርባለች" ሲል ያስተዋወቃት የሰማይ መንግስት በንስሃ የሚቀበሏትና የሚገቡባት መንግስት ናት። የዮሐንስን ታልፎ መሰጠት ተከትሎ "ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር" (ማቴዎስ 4፥ 17)፣ ሲሉ ወንጌላውያኑም ይነግሩናል።
ይህ የአዲሱ ኪዳን የእግዚአብሔር መንግስት ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከመሞቱ አስቀድሞ ለአይሁድ ያስተምራቸው በነበረበት ጊዜ ያኔ ገና ለማደግ በጅማሬው ላይ ነበር። የዚህ መንግስት ፍጹማዊ ሙላትና አገዛዙ የሚሰፍነው በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ላይ እንደሆነ ቃሉ በግልጽ ያስተምራል፣ ይህም የአብዛኛው ክርስቲያኖች እምነት ነው፤ በአመዛኙ ልዩነቱ ያለው ለዳግመኛ ምጽአቱ ተፈጻሚ መሆን የተቀጠረውንና የተወሰነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የጊዜ ማእቀፍ በመረዳትና በመተርጎሙ ላይ ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት መጻህፍት ገለጻ፣ ጌታ ኢየሱስ "እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ" (ማቴዎስ 16፥ 28) ብሎ ሲያስታውቅና፣ ደግሞም "እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" (ማቴዎስ 24፥ 34) ሲል እንዳስተማረውና፣ ሐዋርያቱም በተደጋጋሚ እንዳስተማሩት ከሆነ፣ የዳግመኛ ምጽአቱ ኹነት ፍጻሜ ከኢየሩሳሌም ከተማ መፈራረስና ከቤተ መቅደሱ መደምሰስ ጋር የተያያዘ ነው፤ እነርሱም ጌታ በነገራቸው የተስፋ ቃል ላይ ቆመው፣ በትውልዳቸውና በዘመናቸው እንደሚሆን ሲናፍቁትና ሲጠባበቁት የነበረው ዋና ጉዳይ ይኸው የጌታ የዳግሙኛ ምጽአቱ ፓሮዥያውን ነበር። ይህንንም ከእስራኤል ቤዛነትና ከአሮጌው የሙሴ ስርአት መወገድ ጋር አያይዘው ይረዱት ነበር። ይህ ደግሞ የሆነው የዚያ አሮጌ ስርዓት ማእከልና መገለጫ የሆነው ቤተመቅደስ ፈጽሞ ሲደመሰስና ሲጠፋ፣ ከተማይቱም በእሳት ስትቃጠልና ሕዝቡም በሰይፍ ሲወድቁና ለባርነት ሲማረኩ በ70 ዓም ላይ በሆነባቸው ፍርድ ነው። የክርስቶስ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው በ70 አም ላይ እስኪሆን ድረስ ታዲያ መንግስቱ ገና በሙላት አልተመሰረተም ነበር።
ይህ የእግዚአብሔር መንግስት መንፈሳዊ መንግስት እንጂ፣ ተዳሳሽ መንግስት አለመሆኑን "መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም" (ዮሐንስ 18፥ 36) ሲል ኢየሱስ በግልጽ ተናግሯል። "ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው።" (ሉቃስ 17፥ 20- 21) ተብሎ እንደተጻፈ፤ በእምነት በኩል በክርስቶስ በሆኑቱ ሁሉና ዳግመኛ ተወልደው የእርሱ ምርጦች በሆኑት ምዕመናንን ውስጥ የሚኖር መንፈሳዊ መንግስት፣ የእግዚአብሔር አገዛዝ ነው እንጂ፣ እዚህ አለም ላይ በሚታወቅ በየትኛውም ፖለቲካዊ አገዛዝ የሚለካና የሚተረጎም መንግስት አይደለም። በመንግሥቱ በሚኖር በእያንዳንዱ ዳግም በተወለደ አማኝ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አድሮበታል።
ስለዚህም "ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን" (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 13) እንደተባለ፤ በመንግሥቱ ውስጥ የሚገኘው ጽድቅ ብቻ ነው፣ እንጂ አመጽ የለበትም። ምክንያቱም፣ "የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥" (ማቴዎስ 13 ፥40) ሲል፣ እንደ ተስፋ ቃሉ ይጠበቅ የነበረው ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይኸውም መንግሥቱ በዳግመኛ ምጽአቱና በፍርዱ ከክፉዎችና ከአመጻ የሚጸዳ መሆኑን ያሳያል። ክፋት የሚለቀመው "ከመንግስቱ" ነው እንጂ ከግዑዙ አለም ላይ አለመሆኑን እናስተውላለን። መንግስቱ ደግሞ ከዚህ አለም አይደለችም። ክርስቶስ በዳግመኛ ምጽዓቱ በዙፋኑ ሆኖ የነገሰባትና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ለዘላለም የሚገዛባት፣ ጽድቅና ቅድስና የሰፈነባት፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ኃሴትና ደስታ የሞላባት መንግስቱ፣ እደግመዋለሁ፣ እዚህ ተዳሳሹ አለም ላይ ካለ ከየትኛውም ሥጋዊና ነባራዊ የሰው ስርአት ጋር እናስተያያት ዘንድ የሚመጥናትና የሚገልጣት ምንም አምሳያ የላትም። እርስዋ የሰማይ መንግስት ናት። የምድር ላይ ኃያላን በምድራዊው መንግስታቸው የለበሱትን ካባ እና በራሳቸው ላይ የደፉትን ዘውድ፣ የተቀመጡበትን ዙፋንና የሚሰጡትን ፍርድና ዳኝነት ስንራቀቅ ውለን ብናድርበት፣ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ጋር ሆኖ በሚገዛበት በሰማያዊው መንግስቱ ካለው ግርማና ክብር ጋር ሊጠጋጋ ቀርቶ ምሳሌ ለመሆን እንኳ አይበቃም።
መንግስቱን ልንረዳውና ልናስተውለው የምንችለው የክርስቶስ አካል ተብላ በምትጠራዋና በማትታየዋ ሉል አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ባህርይና ተፈጥሮ ውስጥ ነው እንጂ፣ በሚታይና በሚዳሰስ የትኛውም ምድራዊና አለማዊ አደረጃጀት ውስጥ አይደለም። እርስዋም የብሉይ ኪዳንዋን እስራኤል ዘስጋን የተካቻት እውነተኛዋ የእግዚአብሔር እስራኤል፣ የእግዚአብሔር መንግስት ናት። እግዚአብሔርም በአብርሃም በኩል ለእስራኤል የሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ "አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚማላ የእርሱ ሙላቱ" በሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያኑ ውስጥ በክርስቶስ ፍጻሜውን አግኝቷል። መቼም ቢሆን ከነገድና ከቋንቋ ከህዝብም ተዋጅተው፣ በጽድቅና በጸጋ ተጠርተው የገቡባትን፣ መንግስቱና ግዛቱ ሊሆኑ የተመረጡቱ ቅዱሳን የሚኖሩባትን፣ እውነተኛዋን እስራኤልን ሊገልጣት የሚችለው ኪዳን ነው እንጂ ዘር አይደለም።
ይህ መንግስት ተፈጥሮው መንፈሳዊ ሲሆን፣ የወንጌል እና የክርስቲያን መንግስትም ነው፣ እንጂ ተዳሳሽ የሆነ፣ የሙሴ ሕግና የአይሁድ መንግስት አይደለም። ይህ በአሮጌው ሰማይ የተወከለው የአሮጌው ኪዳን ህጎች ሁሉ፣ መስዋአቶቹ፣ ኃይማኖታዊ ስርዓቶቹ፣ ልዩ ልዩ በአላቱ እና የበአላቱ ቀኖች ሁሉ፣ ከዚህ በአሮጌው ምድር ከተወከለውና በ70 አም ላይ ፍጻሜውን ካገኘው የእስራኤል ሕዝብ ውድመት፣ የኢየሩሳሌም ከተማ ጥፋት እና የመቅደሱ መደምሰስ ጋር ዳግም ላይታሰቡ በክርስቶስ ፍርድ እንዲያልፉ ተደርገዋል። በትንቢታዊ ገለጻቸው "ሰማይ እና ምድር" የሚወክሉት ኪዳንን ነው እንጂ በቁሙ አይተረጎሙም።
ያኔም በ70 አም ላይ አሮጌውን ሰማይና አሮጌውን ምድር በማስወገድ፣ በፍጥረቱ መንፈሳዊ የሆነው የአዲሱ ኪዳን ወንጌል ዘላለማዊው መንግስት፣ በሙላት ተመስርቷል፣ ይህም የእግዚአብሔር ፍጹማዊ አገዛዝ፣ በምድር ላይ በሚኖረው የሰው ልጆች ታሪክ ሁሉ ውስጥ፣ በተፈጠረው አዲሱ ሰማይ እና አዲሱ ምድር ሳይቋረጥ መግዛቱን ይቀጥላል። ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ መንግስት ንጉስና ገዢ፣ የምድርም ነገስታት ሁሉ ገዢ መሆኑ ለአለምና ለዘላለም እየታወጀ፣ በውጭ ያሉ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ በእምነትና በንስሃ ወደማይዘጋው ወደ ፍቅሩ ልጅ የጸጋ መንግስ እንዲገቡ ለትውልድ ሁሉ ጥሪና ግብዣ እየተደረገ አለም ይቀጥላል። መንግስቱ በምድርም በሰማይም የሚቀጥል መንግስት ነው። የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለከልካይ በሰማይ እንደሆነች በምድርም ደግሞ ናት፣ (ማቴዎስ 6፥ 10፤ ሉቃስ 11፥ 2)።
ማስታወሻ፦ ይህ ጽሁፍ ዘርዘር ብሎና በበርካታ የቅድሳት መጻህፍት ማገናዘቢያ ጥቅሶች ላይ ተመስርቶ ካዘጋጀሁት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ተጨልፎ የተወሰደ እጥጥር ሲሆን፣ ጌታ ፈቅዶ ጊዜ ከሰጠኝ ትምህርቱን አደራጅቼ በአንድ ወይም በሁለት ክፍል በስፋት እመለስበታለሁ። እስከዚያው ግን እንደ ፕሪቴሪስት ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምን እንደምናምን እና እንደምናስተምር በዚህች አጭር ክትባት በመጠኑ መረዳት ይቻላል። ተጨማሪ የነገረ ፍጻሜ ትምህርት የሚቀርብበትን philologus66 የተሰኘውን የፌስ ቡክ ገጽ እና http://gizachewkr.blogspot.com/ የተሰኘውን ብሎገር እንድትጎበኙ ግብዣዬ ነው።
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/