ልጅነታችን
ልጆች የተደረግንበት መንገድ፣ ይኸውም በእግዚአብሔር የተመረጡትን አማኞች ሁሉ እውነተኛና ትክክለኛ የእግዚአብሔር ልጆች ያደረጋቸው መለኮታዊ አሰራር መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ነው። እግዚአብሔር ባዳነን ጊዜ ያዳነን፣ በኃጢአታችን ምክንያት ከሚገባን እና ልንቀበለው ካለን ዘላለማዊ ቅጣት ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን በገዛ ራሱ ሰማያዊና መለኮታዊ ቤተሰብ ውስጥ ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር ልጆቹ አድርጎ ደግሞ ተቀብሎናል። በውድ ልጁም ምክንያት ብቻ ወራሾቹ ልንሆን ልጆቹ አድርጎናል።
በፈጸመው ገደብ ያጣ ወንጀል ጽኑ ፍርድ ለሚገባው ወንጀለኛ፣ በፍርድ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ያለው ዳኛ ህጉን ጠቅሶና ለዚያ ጥፋት ተገቢ የሆነው ዋጋ መከፈሉን አውጆ፣ ያንን ወንጀለኛ ምህረት ቢያደርግለት ያ አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን ዳኛው ከዚህ በላይ አልፎ በፍርድ ችሎት ላይ እንዳለ ያንን ምህረት የተደረገለትን ወንጀለኛ ሰው በርህራሄ አይን አይኑን እያየ፣ “ከዛሬ ጀምሮ ከልጆቼ እንደ አንዱ ትቆጠርና የቤተሰቤ አባል እንድትሆን እንደ ልጅ ተቀብዬሃለሁ፣ እነሆ ልጄ ሆነሃል!” ቢለውና አቅፎ ቢስመው፣ ወደ ቤተሰቡም ወስዶ ቢቀላቅለው፣ ከተወላጅ ልጆቹም እንደ አንዱ ሆኖ በገበታው ከእርሱ ጋር እንዲቀመጥ ርስቱንም እንዲካፈል እኩል መብት ቢሰጠው ይህ ደግሞ ከምህረትና ከይቅርታ ያለፈ ሌላ ነገር ነው። ምናልባት ልጆቹ የተደረግንበትን የጸጋ አሰራር የሚያሳይ ከዚህ የተለየና የተሻለ ምሳሌ ይኖር እንደሆነ አላውቅም። ለእግዚአብሔር ልጆቹ ይሆንነው ግን እርሱ ከውድ ልጁ የተነሳ እንደ ልጆች ተቀብሎን ነው። ልጆች የሆንነው ልክ እንደ ጉዲፈቻ (adopted) ተደርገን ነው። ይህ የትኛውንም ኃይማኖታዊ የሆነ ባዶ የስጋ ኩራትና ትምክህትን ያስወግዳል ብዬም አምናለሁ። ልጅነታችን የተሰራበት ይህ የጉዲፈቻ (adoption) መንገድ ከጠፋብን ከጸጋው ተለይተን የኃይማኖትና የማንነት ኩራትና ትምክህት ፈተና ውስጥ እንወድቃለን
ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታችንና መድሃኒታችን፣ ንጉሳችንና ሊቀ ካህናታችን ነው፣ እኛም በእርሱ (ውስጥ) ነን። ሁሉም ነገራችን ያለው ኢየሱስ ጋር ነው፣ ከእኛ በእኛ የሆነ ምንም የለም። እርሱ ከአባቱ ጋር ሊያስታርቀን፣ ፍጹም የሆን የመታዘዝን ሕይወት ኖሮ ፍጹም የሆነ መስዋዕታዊ ሞትን ሞተ፤ ሕጉ የሚጠይቀውንና መከፈል የነበረበትንም የኅጢአት እዳ በመስቀሉ ደም ከፍሎ ሥርየትን ሰጠን፤ የዘላለምንም ሕይወት በትንሳአኤው አምጥቶ በጸጋው አደለን፤ ባለመታዘዝ የጠፋነውንና በበደላችን ምክንያት የሞትነውንም ለአዲስ ሕይወት አስነስቶ ወንድሞቹና እህቶቹ በምንሆንበት ማዕረግ የእግዚአብሔር ልጆች አደረገን። ይህም የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ፣ እኛም ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ያደረገው ነው።
ሁሉም ነገር የእርሱ የኢየሱስ ነው፣ አብ ልጁን ይወዳል፣ ማጽደቅንም መኮነንንም ሰጥቶታል፤ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃላትና በረከቱ ሁሉ የእርሱ ነው። የእርሱ ያልሆነ ምንም የለም። በጸጋው የእግዚአብሔር ልጆች የተደረጉ ሁሉ፣ የእርሱ ለእርሱ እና በእርሱ ናቸው። እግዚአብሔር ህጋዊና አግባብ በሆነ መንገድ፣ ይኸውም በራሱ ሉዓላዊ የጸጋ አሰራር በእርሱ ፊት እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ መብትና ስልጣንን አጎናጽፎ የእርሱ የክርስቶስ ስላደረገን፣ የእርሱ የሆንን ሁላችን ከእርሱ ጋር አብረን የምንወርስ ሆነናል። እኛ ክርስቲያኖች ከክርስቶስ የተነሳ ያለፍርሃትና ያለጭንቀት፣ ሙሉ በሆነ መተማመን፣ ግርማን ወደ ተሞላው ወደ እግዚአብሔር የጸጋ ዙፋን መቅረብ እና መምጣት እንችላለን፤ “አባ አባት” ብለን ልንጠራውም እንችላለን። ፍጻሜ በሌለው መንግስቱም ከዘላለም የተዘጋጀውን የመዳንን ተስፋም ወርሰናል።
“ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።” (ገላትያ 4፥ 4-7)
ይህ አባ የተሰኘውን አጠራር ጌታ ኢየሱስ በጌትሰማኒ በስቅላቱ ዋዜማ ትጨንቆ ሲጸልይ በምን ሁኔታ እንደተጠቀመው በማርቆስ ወንጌል ላይ ተመልከቱ፦
“አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ” (ማርቆስ 14፥ 36)
ጌታችን አባቱን የሚጣራበትን ቅርበትና ዝምድና አስተውሉ “አባ አባት ሆይ፥” በዚያ በጭንቀቱ ሰዓት እንዲህ ብሎ መጣራቱ የሚይሳየው በልጁና በአባቱ መካከል ያለውን ታላቅ ግንኙነት፣ ኢየሱስስም ለአባቱ በእቅፉ ያለ የባህርይ ልጅ እንደመሆኑ በአብ ላይ ያለውን አስገራሚ መደገፍ ነው። የመከራውን ጽዋ ለመጨለጥ አቅምና ጉልበት የሆነው የአባቱ ልጅ መሆኑን ከማወቁ ነው። ለእኛም በእርሱ ላይ ያለን መደገፍ የሚቀዳው “በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት” ነው። እንደ እግዚአብሔር ልጆች ለመኖር በጸጋው በታደልነው በዚህ ሕይወት የምናልፍበትን የትኛውንም ተግዳሮት ፊት ለፊት ተጋጥመን አቸንፈን የምንወጣውም በአባትነቱ ፍቅርና በመንፈስ ቅዱስ መሰጠት በተረጋገጠው የልጅነታችን ማዕረግ ነው፦
“በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና።” (ሮሜ 8፥ 14-15)
(gKR)
No comments:
Post a Comment