የአብርሃም እቅፍ
“ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። እርሱም እየጮኸ፦ አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ። አብርሃም ግን፦ ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ። ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ” (ሉቃስ 16፥ 19-26)።
“የአብርሃም እቅፍ” የተሰኘው ሃረግ ገነትን ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ገነት በግሪኩ paradeisos በስትሮንግስ የግሪክ ቃላት መፈለጊያ #3857 አትክልት ለሞላበት አረንጓዴ ፓርክ ወይም የመናፈሻና የመዝናኛ ስፍራ የሚል ትርጉምን የሚሰጥ ምስራቃዊ ቃል ነው፣ እርሱም ኤደን ይባላል፣ ይኸውም እጅግ ደስ የሚልና ደስታ የሞላበት ስፍራ ነው፤ ሲል ያብራራዋል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከጎኑ ተሰቅለው ከነበሩ ወንበዴዎች ንስሃ ለገባው ለአንዱ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” (ሉቃስ 23፥ 43) ሲል እንደ ነገረው እናውቃለን።
ገነት የሆነው “የአብርሃም እቅፍ” ማለት ሃደስ (ሲኦል) በተሰኘው ስፍራ የሚገኝና የሞቱ ጻድቃን መንፈሶች ትንሳኤን የሚቀበሉበትን የቤዛነታቸውን ቀን እየተጠባቡቁ የሚቆዩበት ቦታ ነው። በመላው መጽሐፍ ቅዱስም ይህ “የአብርሃም እቅፍ” የተሰኘ ሃረግ የተጠቀሰው በሉቃስ 16፥ 22-23 ባለው ክፍል አድ ጊዜ ብቻ ነው። ክርስቶስ ይህንን የተናገረውም ፈሪሳውያን ከደቀመዛሙርቱ ጋር ሊሰሙት በተገኙበት ነው። ሲኦል በእብራይስጥ ሼኦል በመጀመርያውም ኪዳን ከአጠቃላይ ትንሣኤ አስቀድሞ ሙታን የሚከማቹበት ቦታ ነው። በአይሁድ እምነት በኪዳኑ የታመኑ እስራኤላውያን በሞታቸው ጊዜ "ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ" እስከ ተባለላችው ድረስ፣ ያ የሚከማቹበት ስፍራ ወይም ሲኦል “የአብርሃም እቅፍ” ተብሎም ይታወቃል። ስለዚህ ሲኦል ሁልጊዜ እና የግድ የስቃይና የቅጣት ቦታ ብቻ ላይሆንም ይችላል ማለት ነው። ለምሳሌ፣ ከአባቶች መካከልእንደ ያእቆብ ያሉ ታማኝ የያሕዌ ባሪያዎችም ከሞትን በኋላ እንሄድበታለን ብለው የሚጠብቁት ስፍራ እንደሆነ እናያለን፦
"ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፤ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ፦ ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ።" (ዘፍጥረት 37፥ 35)
"እርሱም አለ፦ ልጄ ከእናንተ ጋር አይወርድም፤ ወንድሙ ሞቶ እርሱ ብቻ ቀርቶአልና፤ በምትሄዱበት መንገድ ምናልባት ክፉ ነገር ቢያገኘው ሽምግልናዬን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።" (ዘፍጥረት 42፥ 38)
" ይህንም ከእኔ ለይታችሁ ደግሞ ብትወስዱት ክፋም ቢያገኘው፥ ሽበቴን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። .... ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በኅዘን ወደ መቃብር ያወርዳሉ።" (ዘፍጥረት 44፥ 29፣ 31)
በእነዚህና መሰል በርካታ የብሉይ ኪዳን ምንባባት፣ አባቶች በሞታቸው ጊዜ እንወርድበታለን የሚሉት የ”ሙታን ስፍራ” እርሱም “መቃብር” ሲኦልን የሚያመለክት እንደሆነ፣ በዚያም አንቀላፍተው ከአባቶቻቸው ጋር የሚከማቹበት “የአብርሃም እቅፍ” መሆኑን እናስተውላለን።
በዚህ የክርስቶስ ምሳሌ ገለጻ ውስጥ “ሲኦል” የተባለውን ሃደስን፣ እርሱም ሙታን ከአጸደ ሥጋ ተለይተው በአጸደ ነፍስ የሚሄዱበትን ሥፍራ፣ ከአንዱ ወደ ሌላው ማንም አቋርጦ ማለፍ እንዳይችል በመካከሉ በጥልቅ ጉድጓድ፣ በገደል፣ ወይም በታላቅ መለያየት በተከፈለ ሁለት ምድብ ገጽታው ያቀርበዋል። ስፍራውም የሲኦል የእረፍት ቦታን እና የሲኦል የስቃይ ቦታን በሁለት ከፍሎ የያዘ ነው። ምሳሌው የሚያመልክተን አንዱ እውነታ ኃጢአተኞችም ሆኑ ጻድቅን ሁለቱም ወገኖች ስጋና ደም ከሆነ ተዳሳሽ አካል ተለይተው በአጸደ ነፍስ ሆነው ያሉበት ሃደስ ውስጥ ንቁ እና የሚያውቁ መሆናቸውን ነው። በተጨማሪም ለነዚያ በስቃይ ሃደስ ውስጥ ላሉ ሙታን ሁለተኛ የይግባኝ እድልም ሆነ ወይም አጠቃላይ (universal) እርቅ የሌለ መሆኑን ይህ ምሳሌ ያረጋግጥልናል።
ክርስቶስ ሲናገር “አልዓዛር” የሚባል አንድ ደሃ ለማኝ ሰው በሞተ ጊዜ “መላእክት ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት” ይለናል። አንድ ባለጠጋ ሰው ደግሞ ሲሞት ተቀበረና በስቃይ ስፍራ ሆነ ይለናል። ይህንን የስቃይ ስፍራ በግሪኩ “bsanos” ይለዋል፣ ስትሮንግስ የተሰኘው የግሪክ ቃላት መፈለጊያ #931 ሲተረጉመው፣ እጅግ የከፋ ስቃይን የቀላቀለ በቀል ባለበት ሁኔታ፣ በምስያው ጥቋቁር ድንጋዮች እየተሰቃዩ እንደሚፈተኑባቸው፣ ብረቶችም እንደሚቀልጡባቸው ያለ ጥልቀት ውስጥ መውረድ ይለዋል። ይህ እንግዲህ አማኝ ያልነበሩ የአሮጌው ኪዳን ኃጢአተኞች፣ ከሞቱ በኋላ በ70 ዓ.ም የሚሆነውን ይግባኝ የሌለውን የመጨረሻ ፍርድ እየተጠባበቁ የሚቆዩበት በሃደስ ውስጥ የተዘጋጀላቸው የስቃይ ስፍራ ያለበት ምድብ ነው። ያ ሟች ባለጠጋ ሰው ከሲዖል የስቃይ ስፍራ ሆኖ አሻቅቦ ሲያይ አብርሃምንና አልዓዛርን ተመለከተ።
ባለጠጋው ሰው በእሳት ነበልባል እየተሰቃየ ስለነበር፣ ለአብርሃም ያቀረበው ጥያቄ አልዓዛር በጣቱ ጥቂት ውሃ ይዞ ምላሱን እንዲያረጥብለት ነበር። አብርሃም ግን ለባለጠጋው ሲመልስለት ይህ አይቻልም! ምክንያቱም አንተ በምድር ሳለህ እጅግ ተመችቶህ መልካሙን እየተቀበልህ በመጽናናት ስትኖር አልዓዛር ደግሞ በከፋ ስቃይ ውስጥ መከራን እየተቀበለ ነበር። አሁን ግን ሁለቱም ከሞቱ በኋላ በአጸደ ነፍስ ሆነው አልዓዛር መጽናናትን ባለጠጋው ደግሞ ስቃይን እየተቀበሉ መሆናቸውን ያመለክታል። ጨምሮም አብርሃም ሲናገር መጽናናት ባለበት የሃደስ ምድብ (ይኸውም የአብርሃም እቅፍ ነው) እና ስቃይ ባለበት የሃደስ ምድብ መካከል ማንም ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው ማለፍ እንዳይችል በመካከል የሚከፍል፣ ጥልቅ የሆነ ታላቅ ገደል ተደርጎአል የሚል ነው። ይህ “የአብርሃም እቅፍ” የተባለ ስፍራ ገነትም ይሁን ወይም ሲኦል፣ በምንም ስም ቢጠራ ከክርስቶስ ትንሳአኤና ከእርገቱ በፊት በነበረው አሮጌ ኪዳን ውስጥ ለኖሩ ቅዱሳን ግን ሰማይ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ይህ “የአብርሃም እቅፍ” የተባለው ስፍራ ማለትም ገነት ክርስቶስ ሞትንና ሲኦልን ድል ነስቶ በትንሳኤው ግርማ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ሃደስ ከሚባለው ስፍራ ተለይቶ ወደ ሶስተኛው ሰማይ እንደ ተወሰደ ማመን እንችላለን። ይህም የሆነው ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ ከ40 ቀን በኋላ ነው ( ሐዋ 1፥ 3፣ 9)። የሆነውም “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።” (ኤፌ 4፥ 8-10) ሲል ጳውሎስ እንደሚጽፈው ክርስቶስ ምርኮኞችን በማረከ ጊዜ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ጨምሮም ስለ ገዛ ራሱ መንፈሳዊ ልምምድ ሲናገር፣ እርሱ ራሱ ደግሞ ገነት ወዳለበት ወደ “ሦስተኛው ሰማይ” ተወስዶ ቃላት ሊገልጡት የማይችሉትን ድምጽ እንደሰማ በ57 ዓ.ም ላይ “ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።” (ቆሮ 12፥ 2-4) ሲል ይጽፋል። ጳውሎስ ይህንን በሚጽፍበት ጊዜ ይህ ገነት የተባለው ስፍራ የመገኛው ቦታ በ”ሦስተኛው ሰማይ” እንደሆነ እናስተውላለን።
እነዚያ ሟች የነበሩ ያንቀላፉት የአሮጌው ኪዳን ምርጦች እና ከዳግመኛ ምጽአቱ በፊት የሞቱ ቅዱሳን፣ ከሙታን እስኪነሱ እና ክርስቶስ በ70 ዓ.ም በዳግመኛ ምጽአቱ ከዚያ እስኪፈታቸው ድረስ በዚያ ምርኮኛ ሆነው የቤዛነታቸውን ቀን እየተጠባበቁ ነበር። አሁን ግን “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤” (ዮሐንስ 11፥ 25-26) ተብሎ እንደተጻፈ፣ በአሮጌው ኪዳን ስር አስቀድመው ሞተው በዳግመኛ ምጽአቱ ትንሳኤን የተቀበሉ አባቶች፣ “ትንሳኤ” ከሆነው ከክርስቶስ የተነሳ በዚያ በሃደስ እንደሌሉ ሁሉ፤ በክርስቶስ ሆነን በብጽእና የምንሞት ሁላችን “ህይወት” ከሆነው ከክርስቶስ የተነሳ “ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን” እንጂ ስንሞት ወደዚያ አንሄድም። ጌታ ኢየሱስ ለማርታ ይህንን ከተናገረ በኋላ የጠየቃት ቀላል ጥያቄ “ይህንን ታምኛለሽን?” የሚል ነበር፣ የሚያስፈልገው የክርስቶስን ቃል ማመን ብቻ ነው።
ይህንን ደግሞ ስሙ፦
“ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።” (1ተሰሎንቄ 4፥ 13-17)። “ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም!” የተባለለት ጌታ፣ “እነሆ በቶሎ ብዬ እመጣለሁ ባለው ቃሉ መሰረት፣ ቃሉን ጠብቆ “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ” ወርዷል፤ ትንሳኤም ንጥቀትም ሆኖአል። እግረ መንገዴን ልንገራችሁ ብዬ ነው፣ ይህ መፈጸሙን አለማመን ብዙ የፎረሸ ትምህርት ውስጥ ያስገባል። አሁን ስለ ገነት የጀመርነውን እንቋጭ...
ገነት የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አካል ለመሆን ወይም ራስዋን ከተማይቱን ለመሆን በክርስቶስ ትንሣኤ እና በእርገቱ ከፍ ከፍ ካለችበት ከ”ሦስተኛው ሰማይ” በላይ፣ “ከሰማያትም ሁሉ በላይ” በዳግመኛ ምጽአቱ ከፍ እንዳለችም ጭምር ማየት እንችላለን። ይህም ሰማይ የእግዚአብሔርና የልጁ ሰማይ፣ ድል ነሺው ንጉሰ ነገስት ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ለዘላለም የሚገዛበት፣ ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ሆና የተመሰረተችበት መንፈስዊው ሰማይ ነው። ይህም የሆነው ክርስቶስ በ70 ዓ.ም ዳግመኛ ሲመጣ በ”ፓሮዥያው” ነው። ዮሐንስ በራእዩ ሲጽፍ “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ” (ራእይ 2፥ 7)፣ ሲል ክርስቶስ ማወጁን ይነግረናል።
በንባብ ክፍላችን እንደምንመለከተው አብርሃም ጨምሮ የሚናገረው፣ እነዚያ በሲኦል የስቃይ ስፍራ ያሉ ነፍሳት ገና በህይወት እያሉ ሙሴና ነብያት ስለ መሲሁ የሚሉትን ሊሰሙ ያልፈለጉ ናቸው፤ ስለዚህም ከሙታን አንድ ቢነሳላቸው እንኳ የሚሰሙም የሚያምኑም አይሆኑም። ይህ ባለጠጋ ሰው ሙሴና ነብያት ስለመሲሁ የተናገሩትን ከማመን ልባቸውንና አንገታቸውን ያደነደኑትን የእስራኤልን ቤት ይወክላል። አልዓዛር ደግሞ በህጉና በነብያት የተነገረውን አምኖ የሚጠባበቅን ጻድቅ እስራኤላዊ ይወክላል። ክርስቶስ ከመስቀሉ ሞት በኋላ ከመቃብር ተነስቷል፣ ብዙዎች ሟች የሆኑ ቅዱሳንንም በኢየሩሳሌም እንዲመሰክሩ ከሃደስ አስነስቶአል (ማቴዎስ 27፥ 52-53፤ ሉቃስ 23፥ 27-31)። ምንም እንኳ ከትንሳኤው በኋላ ሕያው ሆኖ ክርስቶስ ቢታይም፣ ከሙታን የተነሱትን ቅዱሳን ምስክርነት ለመስማትም ቢታደሉ፣ ከዚህም በላይ የትንሳኤው የአይን ምስክር በሆኑ ሐዋርያት ለ40 ዓመታት ቢሰበኩም፣ የሚበዙት አይሁድ ግን እንደ ሟቹ ባለጠጋና በአባቱ ቤት እንዳሉ የማያምኑ አምስት ወንድሞቹ ለእምነት ሳይታዘዙ ቀርተው በ70 ዓም በሚያጠፋው ጠፉ። ይህንን የአልዓዛርንና የባለጠጋውን ሰው ምሳሌ ኢየሱስ ለአይሁድ የተናገረው ገና በስጋው ወራት እያለ መሆኑንም ልብ አድርጉ።
(gkr)
No comments:
Post a Comment