የጥፋት ርኩሰት
“ከእርሱም ጋር ሠራዊቶች ይቆማሉ፥ መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ፥ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፥ የጥፋትንም ርኵሰት ያቆማሉ።” (ዳንኤል 11፥ 31)
“ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥” (ማርቆስ 13፥ 14)
ኢየሱስ ይህንን “የጥፋት ርኩሰት” የተሰኘ ርእሰ ጉዳይ በንግግሩ ያነሳው ደቀመዛሙርቱ (ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ) በግል ቀርበው እየሩሳሌም እና መቅደስዋ መቼ እንደሚደመሰሱ፤ የዳግመኛ ምጻቱና፣ የአይሁድ ዘመን ማብቂያ ምልክቱም ምን እንደሆነ፣ በጠየቁት ጊዜ ነው። የጥያቄዎቻቸውን ይዘት አለመረዳት ግን የተለያዩ ተርጓሚዎችን በየዘመናቱ የትርጉም ቀዋሚነት ለጎደላቸው መላምቶች ሲያጋልጣቸው ይስተዋላል። ጥያቄዎቹን ከምስስለ ወንጌላት አቀራረብ ለመረዳት እነሆ ጥቅሶቹ፦
(ማርቆስ13፥ 2-4፤ ማቴዎስ 24፥ 1-3፤ ሉቃስ 21፥ 5-7)።
ጌታ ኢየሱስ በመልሱ በዚያን ጊዜ ሊሆኑ ስላሉ ምልክቶች እና ሁነቶች በርካታ ነገር ለጠያቂዎቹ ነግሮአቸዋል። እነዚህም ሁነቶች “ይህ” የተባለው የዚያ አንድ ትውልድ ሁነቶች ናቸው፡፡ ለእነርሱም ከነገራቸው ነገሮች መካከል በትውልዳቸው ውስጥ ሲሆን የሚያዩት አንዱ በነብዩ በዳንኤል የተነገረው “የጥፋት ርኩሰት” ጉዳይ ፍጻሜ ነው። እርሱም በሰጣቸው መመርያ መሰረት በዚያን ጊዜ በይሁዳ የሚኖሩ እነዚህ የተመረጡ ምእመናን ይህንን “የጥፋት ርኩሰት” የተሰኘ ምልክት ሲያዩ የኢየሩሳሌም ጥፋት የቀረበ መሆኑን ስለሚያስረዳቸው ያኔውኑ ፈጥነው በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ተራሮች ወደ አንዱ ሸሽተው ማምለጥ ይኖርባቸዋል። ይህም ማለት በተሰጣቸው መመርያ መሰረት የጥፋትን እርኩሰት ባዩ ጊዜ፣ ከይሁዳ ሁሉ ወደ ተራሮች ሸሽተው ማምለጥ አለባቸው ማለት ነው፤ (ማቴ 24፥ 15-16፤ ሉቃ 21፥ 20-22)።
የጥፋት ርኩሰት እርሱም ጥፋትን የሚያመጣ ርኩሰት፣ ምናልባትም ራሳቸውን ቀነናውያን ወይም ነጻ አውጪዎች ሲሉ የሰየሙና፣ እርስ በርሳቸው እየተዋጉ ሕዝቡን ለአሙጽ ያነሳሱ የነቡሩ የአይሁድ ሽፍቶች በቤተመቅደሱ ያለውን ቅድስተ ቅዱሳን ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠሩበትና የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፍ እጅግ የከፋ የአመጽና የኃጢአት ተግባር በሚፈጽሙበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ያሳይ ይሆናል። ይህም አመጽ ለሮም መንግስት የሚቀርበውን የሰላም መስዋዕት ጨምሮ የዘወትሩን መስዋእት በማስቀረትም የታጀበ ነበር።
እነዚህ የአይሁድ ቀነናውያን ቅዱሱን መሰውያ አረከሱት፣ በውስጡም ገብተው መላውን ቤተመቅደሱን አቆሸሹት፣ ሌሎች የተከለከሉ ርኩሰቶችንም ሁሉ ፈጸሙ። በቅርቡም እየሩሳሌምንና መቅደስዋን ፈጽሞ በሚደመስስበት ሁኔታ የእግዚአብሔር ቁጣ ይፈስባቸው ዘንድ እጅግ እየከፉ ሄዱ። ድንጋይ በድንጋይ ላይ እስኪፈርስም ድረስ ከመቅደሱ አንድ ድንጋይ እስከማይቀር ድረስ ይወድቁ ዘንድ የተመደቡ ናቸው (ማቴ 24፥ 2)።
ሉቃስ ግን፣ የጥፋት ርኩሰት የሚታይበትን እና ደቀ መዛሙርትም ሸሽተው የሚያመልጡበትን አይነተኛ ጊዜ ለይቶ ሲያመለክት፣ ከተማይቱ በጦር ኃይል መከበብዋን ሲያዩ እንደሆነ ግልጽ አድርጎአል። ይህ ማለት ግን ከላይ እንደተገለጸው የአይሁድ ቀነናውያን የአመጽ ጦር በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ እና ውጭ ሲሰበሰብ ማለት ብቻ አይደለም፣ ይልቁን ግን በጌሲዩስ ፍሎሩስ የሚመራውና ይሁዳን የሚሰባብረው የሮማውያን ጦር ሰራዊት የከተማይቱን በሮች ዘግቶ ከበባ ሲያደርግ ማለትም ነው (ከ64-66 ad)።
ይህንን በጌታ የተነገረ የሽሽት መመርያ በሰአቱ ለመተግበር በንቃት ሲጠባበቁ የቆዩ በይሁዳ ይኖሩ የነቡሩ ክርስቲያን አማኞች የፍሎሩስ ወታደሮች የላይኛውን የቤተ መቅደሱን የገበያ ስፍራ ማጥቃት ከመጀመራቸው ጥቂት ጊዜ ቀድመው ኢየሩሳሌምን የሚያጠቃ ጦር ከተማይቱን እንደከበባት ሲያዩ የያኔውኑ ሳይዘገዩ ከተማይቱን ሙሉ በሙሉ ለቀው ወጡ። ጊዜውም ያራ በተባለው ወር (በግሪኩ አርጤምስዮስ) (በሚያዝያና በግንቦት ወር)16ኛ ቀን ላይ ነው። በዚያን ጊዜው ጥቃት ብቻ ከ3600 አይሁድ በላይ ተገድለዋል። ያኔ የአይሁድ አማጽያን የመከላከልና የመልሶ ማጥቃት ተጋድሎ በማድረጋቸው ፍሎሩስ አፈግፍጎ ወረራውን በማቋረጥ ቂሳርያ ወደሚገኘው የማዘዣ ጣቢያው ተመልሶ ነበር። ይህ የሆነው እንግዲህ በቨስፓስያንና በልጁ በጀነራል ቲቶ የሚመራው ዋነኛው የሮም መንግስት የጦር ኃይል ከጥቂት ወራት በኋላ በሙሉ ኃይላቸው ወደ ጦርነቱ ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ነበር።
ጆሳፈስ እንደ ጻፈው "ቤተመቅደሱ በተደመሰሰ ጊዜ የቲቶ ሰራዊት የሮማዊያን ግርማ ምልክት የሆነውን SPQR የተጻፈበትንና የሮምን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እና የሕዝብ ኃይልና ብዛት የሚወክል የንስር ምልክት ይዘው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ዘልቀው በመግባት በዚያ አስቀመጡት፤ በዚያም በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በግንባራቸው ወድቀው ቄሳርን አመለኩ" ሲል ይዘግባል /Wars, መጽሐፍ 6፣ ምዕራፍ 6 አንቀጽ 1/፡፡ ይህ እንግዲህ ቤተ መቅደሱን ያረከሰና በቅድስት ከተማ ላይ ጥፋትን ያደረገው ርኩሰት የመጨረሻ ተግባር ነው፤ የቁጥር 15 የጥፋት ርኩሰት በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ግልጽ በሆነ ቃል ቀርቦልናል፡፡ ይህ የጥፋት ርኩሰት የጀመረው በሉቃስ 21÷ 20 እንደተዘገበው ገና ኢየሩሳሌም በሮማውያን ጦር ተከባ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡
ወንጌላዊው ሉቃስ ይህንን የጥፋት ርኩሰት እንዴት እንደሚታወቅ ተርጉሞ እንዲህ ሲል አቅርቦልናል፦
“ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፥ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ፤ የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል ጊዜ ነውና።” (ሉቃስ 21፥ 20-22)
ኢየሱስ ሐዋርያቱን ነቅተው እንዲመለከቱ ከነገራቸው ብዙ ነገር መካከል፣ ኢየሩሳሌምን የሚከባት ሠራዊት ዋነኛው ምልክት ነው፡፡ ያ መሆን ሲጀምር ያ እርሱ በትንቢት የተናገረለት ጥፋት እና ፍርድ እንደቀረበና ጊዜው እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ሊመጣም ባለው እልቂት ከቅዱሳኑ መካከል ማንም እንዳይካፈል ፈጥነው በችኮላ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ አምልጠው በሽሽት መውጣት አለባቸው፡፡ የጥፋት ርኩሰቱ ገና ሲጀምር በይሁዳ ያሉ ፈጥነው ከዚያ እንዲወጡ የሚያሰጠነቅቅ ቃል በማቴዎስ 24÷ 16 ላይ እናገኛለን፡፡
"በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥" (ማቴ 24÷ 16)
ይሄ በተለይ ለደቀ መዛሙርቱና በይሁዳ ለሚገኙ ለዚያን ዘመን ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያና መመርያ ነበር።
በ68 ዓ.ም በጦርነቱ መሃል ኔሮ በቤተ መንግስቱ ውስጥ ራሱን ካጠፋ በኋላ፣ ኢየሩሳሌምን ለመሰባበር ዘምቶ የነበረው የሮማውያን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል ቨስፓሲያን ወደ ሮም በመመለስ አዲሱ ተተኪ ንጉሰ ነገስት ለመሆን ውጊያ አደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አካባቢ የነበሩ ክርስቲያኖች በማቴዎስ 24÷ 16 ያለውን ማስጠንቀቂያ ስላስተዋሉ በተከፈተላቸው በር ኢየሩሳሌምን ለቀው ወጡ፤ አይሁድ ግን በተቃራኒው ፍሎሩስ አፈግፍጎ ወረራውን በማቋረጡና ወደ ማዘዝ ጣቢያው በመመለሱ፣ ቨስፓሲያንም ጦሩን ይዞወደ ሮም በመመለሱ ይህ ሁኔታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነላቸው የድል መንሳት ምልክት አድርገው ስለ ወሰዱት በኢየሩሳሌም ከቀድሞው ይልቅ በብዙ ቁጥር በመሰባሰብ የተጀመረውን አመጽ በማጋጋል ቀጠሉበት፡፡ በፍጻሜው ግን ሮማውያን ተመልሰው በመምጣት ከተማይቱን ፈጽመው አወደሟት፡፡
የሚቀጥለው ታሪካዊ ትንታቴ ዊኪፒዲያ ድህረ ገፅ ላይ ስናነብ፦ በ70 አመተ ምህረት ከተለያየ የአለም ክፋሎች ተጉዘው የፍሲካን በአል ለማክበር ወደ እየሩሳሌም የመጡ ዳያስፖራ አይሁዶች ከጥቃቱ ማምለጥ ስላልቻሉ በሮማዊያን ወራሪ ጦር እንዳለቁ ይጠቁመናል ፦
"According to Josephus, 1.1 million non-combatants died in Jerusalem, mainly as a result of the violence and famine. Many of the casualties were observant Jews from across the world such as Babylon and Egypt who had travelled to Jerusalem wanting to celebrate the yearly Passover but instead got trapped in the chaotic siege." [ትርጉም፦ ጆሴፈስ እንደዘገበው ከሆነ፣ 1,1 ሚልዮን የሚገመቱ በጦርነቱ መሃል የተጨፈጨፉ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች በኢየሩሳሌም ተገድለዋል። አብዛኞቹ የጦርነቱ ሰለባዎች እንደ ባቢሎን እና ግብጽ ካሉ ሩቅ ሃገር ተጉዘው ታዋቂ የሆነውን አይሁዳውያንን ዓመታዊውን የፋሲካ በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ዲያስፖራዎች ናቸው። ከከተማይቱ ሊወጡ እንዳይችሉ ሆነው የተታለሉና የተጠመዱ ነበሩ።]
በ60ዎቹ ዓ.ም አጋማሽ ላይ ሮማውያን ይሁዳን እና ኢየሩሳሌምን በጦርነት አጥቅተው በ70 ዓ.ም መላውን አገሪቱንና ቤተ መቅደሱን ጭምር እንዳወደሙ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ከ 1,000,000 በላይ የሚሆኑ አይሁድ በጦርነቱ ተገድለዋል፣ የተረፉትንም ሮማውያኑ ማርከው በመውሰድ የሚበዙትን በየክብረ በዓላቱ ለጣኦቶቻቸውና ለነገስታቶቻቸው ክብር መስዋዕት አድርገዋቸዋል፤ የቀሩትንም ባሪያዎችና ግዞተኞች አድርገው ሸጠዋቸዋል፡፡ ቅድስት ከተማቸው፣ ቤታቸውና ምድራቸው፣ የተቀደሰው መቅደሳቸው፣ እንዲሁም እንደ አይሁድ የነበራቸው የአኗኗር ዘይቤአቸው ሁሉ የተፈታ ሆኖ ሊቀር እንደገናም ላይሰራ ሙሉ በሙሉ ፈጽሞ ተደምስሶ ጠፍቶአል፡፡ የኢየሱስ ትንቢትም ሳይፈጸም የቀረ የለም፣ ሁሉ ተፈጽሞአል።
በዘመናት ውስጥ ቤተክርስቲያን በወጉ ልብ ካላለቻቸው ታሪካዊ ሁነቶች መካከል በ70 ዓ•ም በኢየሩሳሌም ከተማና በመቅደስዋ ላይ የደረሰው ይህ ውድመት፣ በህዝቡም ላይ የተከናዉነው ፍርድና እልቂት ዋናው ነው። ይህ ግን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች አስቀድሞ የተነገረባቸው ብሔራዊ ውድመት ነበር እንጂ ዝም ብሎ አጋጣሚ አይደለም። በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ለፈጸሙት ወንጀል እና በሕጻንዋ ቤተክርስቲያኑ ላይ ለፈጸሙት ግፍ የሚመጥናቸውን ቅጣት እንዲቀበሉ በእግዚአብሔር በቀል ስር ወድቀው ነበር። ይህ ታሪካዊ ክስተት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት ንግሮችን ለመተርጎም በምናደርገው ጥረት ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ያለው እንደሆነም ማስተዋል ያስፈልጋል። ይህ ታሪካዊ ማስረጃ ከእምነታችን ቀጥሎ የቃሉን ታማኝነት፣ ኢየሱስም እግዚአብሔር በወንድሞቹ መካከል ቀብቶ ያስነሳው እውነተኛ መሲህና ነብይ መሆኑን ይመሰክራል። የኢየሱስን ቃሎች እንዳንጠራጠር ተጨማሪ ማስረጃችን እንደቃሉ የተፈጸሙ እነዚህ ታሪካዊ ሁነቶች ናቸው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ” ታዩታላችሁ ሲል የነገራቸው የጥፋት ርኩሰት ያኔ ድሮ ተፈጽሞ አልፎአል። እርሱ ለእኛ ታላቅ መጽናናትን የሚሰጠን፣ የእግዚአብሔርንም የፍርዱን ጽናትና ጭከና እያስተማረን የምንመከርበት ያለፈ ታሪክ ነው።
No comments:
Post a Comment